Categories: EthiopiaNews

ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ወደ ሌላ ሥፍራ እንዲዛወር ተወሰነ

(በውድነህ ዘነበ)

የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንቶች መቀመጫ ሆኖ ሲያገለግል የቆየው የኢዮቤልዩ (ብሔራዊ) ቤተ መንግሥት ሙዚየም እንዲሆን፣ ከስድስት ኪሎ በላይ የሚገኘው የልዑል መኮንን ኃይለ ሥላሴ ግቢ ደግሞ ቤተ መንግሥት እንዲሆን ተወሰነ፡፡

ቀጣዩ ቤተ መንግሥት ሆኖ እንዲያገለግል የተወሰነው የልዑል መኮንን ግቢ ሕንፃና ተያያዥ ግንባታዎች ዲዛይናቸው የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ግንባታቸውም ለኮንስትራክሽን ኩባንያ ተሰጥቷል፡፡

ነባሩ የልዑል መኮንን ሕንፃ ጥንታዊነቱን ሳይለቅ ከመታደሱም በተጨማሪ፣ ሌሎች ግንባታዎች እንደሚካተቱ ታውቋል፡፡ ከነባሩ ሕንፃ ጋር በተጣጣመ ሁኔታ የሚገነቡት እንግዳ መቀበያ፣ ልዩ ልዩ ቢሮዎችና መኖሪያ ቤቶች ናቸው፡፡ 

የሕንፃዎቹን ዲዛይን አልቲሜት ፕላን አማካሪ ድርጅት ያካሄደው ሲሆን፣ ግንባታውን ለማካሄድ ዛምራ ኮንስትራክሽን ሥራውን ተረክቧል፡፡

የቤተ መንግሥት አስተዳደር ግንባታዎቹን ለማካሄድ ያወጣውን ጨረታ ዛምራ ኮንስትራክሽን አሸንፏል፡፡ ሥራው ነባሩን የልዑል መኮንን ሕንፃ ዕድሳት ያካትታል፡፡ ምንጮች እንደገለጹት ኩባንያው በቅርብ የግንባታውን ሳይት የተረከበ ሲሆን፣ ከ170 ሚሊዮን ብር በላይ ለሥራው ወጪ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

በንጉሣውያኑ ቤተሰቦች የተገነባው ይህ ሕንፃ በኪነ ሕንፃ ውበቱ ዘመን ተሻጋሪ የሚባል መሆኑን የገለጹት ባለሙያዎች ለቤተ መንግሥት አገልግሎት ሊውል የሚችል ነው ብለውታል፡፡  ሕንፃው ቀደም ሲል ለረዥም ጊዜያት የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር ሲገለገልበት ቆይቷል፡፡ ሚኒስቴሩን የተካው የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ቦሌ ወሎ ሠፈር አካባቢ ባለ የግለሰብ ሕንፃ በመዛወሩ ባዶውን ጥበቃ እየተደረገበት ተቀምጧል፡፡ ይህ ሕንፃ በደርግ መንግሥት የሥልጣን ዘመን የአብዮታዊ ኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር (አኢሴማ) ይገለገልበት ነበር፡፡ 

መንግሥት ፕሬዚዳንቱና ጽሕፈት ቤታቸው ወደ ልዑል መኮንን ግቢ እንዲዛወር የወሰነበትን ምክንያት፣ የቤተ መንግሥት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረፃዲቅ ገብረሚካኤል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት፣ ታላቁ የምኒሊክ ቤተ መንግሥት፣ መቐለ የሚገኘው የዮሐንስ ቤተ መንግሥትና ድሬዳዋ የሚገኘው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግሥት፣ የመንግሥት ሥራ እየተሠራባቸው ለጉብኝት ክፍት እንዲሆኑ በመወሰኑ ነው፡፡

በዚህ መሠረት ከፕሬዚዳንቱና ከጽሕፈት ቤታቸው ውጪ ያሉ የመንግሥት ሥራዎች እየተካሄዱ ቤተ መንግሥታቱ ሙዚየም ሆነው ለጉብኝት ክፍት እንዲሆኑ ተወስኗል በማለት፣ አቶ ገብረፃዲቅ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ቤተ መንግሥታት የሙዚየም አገልግሎት እንዲሰጡ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን አቶ ገብረፃዲቅ ገልጸው፣ በተለይ የአስጎብኚዎች ሥልጠና እንደሚኖር ጨምረው አብራርተዋል፡፡

ምንጮች እንደሚገልጹት ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት አጠገቡ ከሚገኘው ከግዮን ሆቴልና ከፍል ውኃ አስተዳደር ጋር በጋራ ሆነው የሙዚየምና የፓርክ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርገው ይዋቀራሉ፡፡

ቤተ መንግሥቱ የአገሪቱ ቀደምት ሥልጣኔ የሚያሳይ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በውስጡ በርካታ ቅርሶችን የያዘ ነው፡፡ ቤተ መንግሥቱ ከግዮን ሆቴል ጋር የሚያገናኘው ራሱን የቻለ መግቢያ በር አለው፡፡ 1,236 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ካረፈው ባለአራት ኮከቡ ግዮን ሆቴል ጋር እንዲቀናጅ ይደረጋል የሚል ሐሳብ እንዳለ የሚናገሩት ምንጮች፣ ከዚህም በጥልቀት በመሄድ በፍል ውኃ አስተዳደርና በሥሩ ካለው ፊንፊኔ አዳራሽ (ሆቴል)፣ እንዲሁም ከግቢው ጀርባ ያለው ሰፊ ሜዳ ከቤተ መንግሥትና ከግዮን ሆቴል ጋር ተቀናጅቶ ውብ ፓርክና ሙዚየም የመፍጠር ሐሳብ እንዳለ አመልክተዋል፡፡

*******
Source: ሪፖርተር፣ ነሐሴ 25/2006

Curated Content

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago