‹አንድነት› ፓርቲ ‹መድረክ›ን አስመልክቶ ያደረገው ግምገማ (ሙሉ ቃል)

የአንድነት/መድረክ የፖለቲካ ግንኙነት እና የጋራ እንቅስቃሴ ከመቀናጀት እስከ ግንባር ያለው አጠቃላይ ሁኔታ ግምገማ

የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት አቋምን የሚያሳይ ሰነድ
ሚያዝያ 19 ቀን 2005 ዓ.ም.

ማውጫ

መግብያ
1. ፕሮግራምና ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች
ሀ. የፕሮግራም ጉዳይ
ለ. ስትራቴጂካዊ ግቦች
ሐ. ጠቃሚ ድምዳሜዎች
2. የመድረክ መተዳደሪያ ደንብን ግምገማ
ሀ. ከይዘት፣ አወቃቀርና ከአሠራር አንጻር
ለ. ከዴሞክራሲያዊነት አንጻር
ሐ. ከአሳታፊነት አንፃር
መ. ከምርጫ ሕግ አንጻር
ሠ. ጠቃሚ ድምዳሜዊች
3. የመድረክ አባል ድርጅቶችና አመራሮች በአንድነት ላይ ያላቸው እይታ
4. መድረክ በሕብረተሰብ ውስጥ ያለው ተቀባይነትና የአፈጻጸም አቅም ግምገማ
ሀ. መድረክ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለው ተቀባይነት
ለ. የመድረክ የማስፈጸም አቅም ግምገማ
5. የአንድነት አመራር ሚና
6. የመፍቴ አሳቦች

መግቢያ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ መድረክን ከተቀላቀለ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከጥንስሱ ጀምሮ መድረክ በይዘቱ ለየት ያለና በኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ላይ እና በብሔር ላይ የተመሰረቱ ፓርቲዎች መሃል የተደረገ ጥምረት ነበር፡፡ መድረክ ከመነሻው ጀምሮ በአባላትና በደጋፊዎች ውስጥ ተስፋንና ስጋት ያጫረ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ፓርቲያችን ይህን ሀገራዊ ፕሮጀክት የተሳካ እንዲሆን ከፍተኛ ዋጋ ከፍሎበታል፡፡በተጨማሪም መድረክ ከመነሻው ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍና ተቃውሞ አልተለየውም፡፡

መድረክ ለተወሰኑ ጊዜያት በቅንጅነት ደረጃ ሲንቀሳቀስ ቆይቶ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ራሱን ከቅንጅትነት ወደ ግንባርነት ማሸጋገሩ ይታወቃል፡፡ በዚህ ሂደት በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዬች ላይ አብሮ ለመስራት ተሞክራል፡፡ ከዚህ አንጻር መድረክ አሳሳቢ በሆኑና በበርካታ ችግሮች የተተበተበ ቢሆንም ሀገራችንን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርሃት ለማሸጋገር በሚደረገው ትግል ውስጥ እየተጫወተ ያለውን ሚና እውቅና ሊቸረው ይገባዋል፡፡ ይሁን እንጂ ትግሉ የሚፈልገውን ድርጅታዊ ቁመና፣ የጋራ ራዕይና መተማመን ከመፍጠር አንጻር ጉልህ የሆነ ክፍተቶች መስተዋላቸው አልቀረም፡፡ የአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት መጋቢት 14 ቀን 2005 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የመድረክ ድክመቶች የሚስተካከልበት እና ጥንካሬዎቹን የሚያጎሎብትበትን ሁኔታ እንዲፈጠር፣ ብሎም ትግሉ የሚፈልገውን ሁለንተናዊ አቅም ለመፍጠር እንዲችልና ፤ እንዲሁም የአንድነት ፓርቲ ሚና ምን መሆን እንደሚገባው ለመፈተሸ አምስት አባላት ያካተተ ኮሚቴ ቋቁሟል፡፡

ኮሚቴው በብሔራዊ ምክር ቤቱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የተሰጠውን ኃላፊነትአጠናቆ እንዲያቀርብ የተሠየመ ነው፡፡ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተከታታይ ውይይቶችን አካሂዷል፡፡ በነዚህ ስብሰባዎች የአንድነት ፕሮግራምና ደንብ፣ የመድረክ ፕሮግራምና ደንብ፣ የመድረክ ማኒፌስቶ፣ የሌሎች የመድረክ አባል ፓርቲዎች ፕሮግራም፣ በመድረክ ዙሪያ የተዘጋጁ የተለያዩ አርቲክልና ሰነዶች፣ 42 በላይ ቃለ-ጉባኤዎችን ፈትሿል፡፡ በተጨማሪምይህ ሪፖርት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አገዛዙ በመድረክና በአባል ፓርቲዎች ላይ የሚያደረገውን አፈና ከመድረክ ስኬታማነት አንጻር የራሱን ተጽኖ ያሳረፈ መሆኑን ከግንዛቤ ያስገባ ቢሆንም፣ ለመድረክ አጠቃላይ ችግር ዋንኛ ምክንያት ነው ብሎ አልተቀበለውም፡፡ በመሆኑም ይህ ሪፖርት ትኩረቱን በመድረክና በአባል ፓርቲዎች አጠቃላይ ሁኔታ የውስጥ ፍተሻ አድርጓል፡፡

የመድረክ አንድነት አጠቃላይ የሁኔታ ግምገማ ሪፖርት በስድስት ዋና ዋነ ክፍሎች ተቀምጧል፡፡ የመጀመሪያው ክፍል በፕሮግራም እና ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በክፍል ሁለት ውስጥ የመድረክ ህገ-ደንብ ከአሳታፊነት፣ ከዴሞክራሲያዊነት እና ከአሳሪነት አንጻር ተፈትሻል፡፡ በክፍል ሶስት በመድረክ አባል ፓርቲዎች መሃከል የነበር የሥራ ግንኙነትና የመድረክ አባል ድርጅቶች አመራሮች በአንድነት ላይ ያላቸው ዕይታ ገምግሟል፡፡ ክፍል አራት የመድረክ የማስፈጸም አቅምና በሕብረተሰብ ውስጥ ያለውንየተቀባይነት ደረጃ ተመልክቷል፡፡ ክፍል አምስት በመድረክ ውስጥ አንድነት ፓርቲ የተጫወተውን ሚና ተመዝኗል፡፡ በመጨረሽያም አንድነት ፓርቲ ከመድረክ አንጻር ጠቃሚ ድምዳሜዎችን አስከምጧል፡፡በተጨማሪም በመድረክ ዙሪያ ፓርቲያችን ሊወስዳቸው የሚገባቸውን የመፍቴ ሃሰቦች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ 1

1. ፕሮግራምና ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተቃውሞ ጎራ ውስጥ የተለያዩ ጥምረቶችና ቅንጅቶች ተመስርተው እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ እነዚህ ህብረቶች ረጅም ርቀት መሄድ አልቻሉም፤ አብዛኛዎቹ የተመሠረቱለትን ግብ ማሳካት ሳይቻላቸው ቀርቷል፡፡ ከውጤታማነት አንጻር በ1997 ምርጫ የተቋቋመው ቅንጅት የተሻለ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ አብሮ የመስራት ሙከራዎች በስተመጨረሽያ ላይ መክሸፋቸው በሕብረተሰብ ውስጥ ፓርቲዎች ያላቸውን አሜኔታና ተቀባይነት በከፍተኛ ሁኔታ የጎዳ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

የተቃዋሚው ጎራ በትርምስና በቀውስ ውስጥ በነበረበት ወቅት፣ የተደራጀና የተቀናጀ ትግል ለማድረግ ከትብብር ውጭ ምንም ዓይነት መፍቴ እንደማይኖር ከግንዛቤ በማስገባት መድረክን ለመመስረት ረጅም ጊዜ ተወስዶ፣ ከዚህ ቀደም የነበሩ ልምዶች ተቀመሮ አዲስ ዓይነት ጥምረት ለመመስረት ተችላል፡፡ መድረክ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኃይሎች ከመጠላለፍና ከመጠፋፈት ፖለቲካ ወጥተው የጋራ ዓላማቸውን ከዳር ለማድረስ የጋራ ስትራቴጂና የጋራ ትግል ለመፍጠር ወጥኖ የተነሳ ነበር፡፡

መድረክ ረጅም ጊዜ ከወሰደ ውይይት በኃላ መሠረታዊ የአመለካከት ልዩነቶች ቢኖሩም፣ የጋራ መግባባት የተደረሰበት መለስተኛ ፕሮግራም እንዲኖረው ለማድረግ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ከስትራቴጂክ ግቦች እንጻር በጋራ ስምምነት የተደረሰባቸው አቋሞች ነበሩ፡፡ከዚህ አንጻር የዚህ ጹህፍ ክፍል ውስጥ የመድረክ አባል ፓርቲዎች የፕሮግራምና የስትራቴጂክ አንድትና ልዩነት ዳግም ለመፈተሸ ሞክራል፤ ከዚህም ተነስቶ ጠቃሚ ድምዳሜዊችን አስቀምጧል፡፡

ሀ. የፕሮግራም ጉዳይ

መድረክን በመመስረት ሂደት ውስጥ የጋራ ሀገራዊ ዓላማ (ፕሮግረም) ከመቅረፅ አንጻር ሁለት ከመሠረቱ የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳቦችን ማቻቻልና ማቀራረብ ያስፈልግ ነበር፡፡ በአንድ በኩል አንድነት ፓርቲ የሚያራምደው የፖለቲካ ፍልስፍና የሆነውን ነጻና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት የእያንዳንዱ ዜጎችን መብት/ነጻነት የትግሉ ማዕከል በማድረግ የሚያምን የሊብራል ዴሞክረሲ አራማጅ ፓርቲ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከኢሶዴፓ በስተቀር ሌሎች የመድረክ አባል ድርጅቶች የብሔርን መብትን የትግላቸው ማዕከል ያደረጉ ኃይሎችን ያቀፈ ስብስብ ነው፡፡ እነዚህ ልዮነቶችን ለማቀራረብ የጋራ ፕሮግራም በመቅረጽ ላይ ከፍተኛ ክርክር እንደተደረገበት በድርድሩ ወቅት የተያዙ ቃለ-ጉባዓዎች በግልጽ ያሳያሉ፡፡

መድረክን በመፍጠር ሂደት ውስጥ በተደረጉት ድርድሮች ፓርቲያችን ከአይዶሎጂ ትብታብ ራሱን አላቆ፣ ሀገርና ትግሉን መሃከል ባደረገ ሁኔታ መድረክ እውን እንዲሆን ላደረገው ጥረት ተገቢ እውቅና ሊቸረው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ይሁን እንጂ አንድነት በድርድሩ ምህራፍ ውስጥ ያሳየውን ያህል ሆደ ሰፊነት ሌሎች የመድረክ አባል ፓርቲዎች አሳይተዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ለዚህም ይመስላል የመድረክ ፕሮግራም መሠረታዊ በሆነ ሁኔታ ከአንድነት ፕርግራም የራቀ ሆኖ የሚታየው፡፡ ስለሆነም አንድነት ይህን ጥምረት የፈጠረው በፖለቲካ ፍልስፍናቸው መሠረታዊ ልዩነት ካላቸው ኃይሎች ጋር መሆኑ የተዋጣለትና ዘላቂነት ያለው ቅንጅት/ግንባር ለመፍጠር ከፈተናዎቹ ዋንኛው ነበር፡፡

በአንድነት ፕሮግራምና በመድረክ ፕሮግራሞች መሃከል ልዩነቶች ቢኖሩም፣ ሶስት ልዩነቶች ግን መሠረታዊ የፕሮግራም ልዩነቶች አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ የመጀመሪያውና መሠረታዊ ልዩነት የግለሰብና የቡድን መብት አስመልክቶ ያለው ልዩነት ነው፡፡ የአንድነት ፕሮግራም በአንቀጽ 1.3.8 የሚከተለው አስቀምጣል “አንድነት በግለሰብ ነፃነት ላይ በተመሠረተ የዴሞክራሲ መሠረታዊ መርሆዎችና ፍልስፍና ይመራል፡፡ የቡድን መብትም የዚህ መርህ አካል እንደሆነ ይቀበላል፡፡ ሆኖም ከሶሻል ዴሞክራሲና ከስምምነት (ኮንሰንሰስ) ዴሞክራሲ አመለካከቶች ለአገራችን እድገትና ብሔራዊ ግንባታ ጠቃሚ የሆኑ እሴቶችንም ይጠቀማል፡፡”በሌላ በኩል የመድርክ ፕሮግራም የሚከተለውን ይላል፤ “የግለሰብ፣ የብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ህዝቦችና የቡድን መብቶች እኩል እንዲከበሩ ሳንታክት እንሠራለን፡፡”በመሠረቱ አንድ የፖለቲካ ኃይል የመጣበትን ብሔር መብት ለማስከበር ሲደራጃ፣ የግለሰብን ነጻነት ላይ ከተመሠረተው የሊብራል ዴሞክረሲ አስተሳሰብ የራቀ እንደሚያደርገው ግልጽ ነው፡፡

ይህ መሠረታዊ የሆነ የፖለቲካ ፍልስፍና ልዩነቶች የአንድ ሀገር ማህበረሰብ እንዴት መደራጀትና መዋቀር አለብት ከሚለው ፖለቲካዊ ጽንሰ-ሃሳብ ጀምሮ በሌሎች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፖሊሲዎች አዘገጃት ላይ ልዩነቶች ማምጣቱ የግድ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአንድነትና በመድረክ አባል ፓርቲዎች ፕሮግራም መሃከል ያለው ሁለተኛ ልዩነት ፌዴራላዊ ሥርዓት አወቃቀር መስፈርቶችን በተመለከተ ነው፡፡ የመድረክ አባል ፓርቲዎች ፕሮግራም ፌደራላዊ አወቃቀሩን በሚመለከት ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት በጽናት እንቆማለን መገንጠልን አንደግፍም ከሚለው በስተቀር ከኢህአዴግ ህገ መንግሥት ውስጥ ከተገለፀው የፌዴራል ሥርዓት አደረጃጀት መስፈርቶች ብዙም ያልተለየ ነው ፡፡ ከኢህአዴግ አንጻር ልዩነቱ የትግበራ ብቻ ይመስላል፡፡

በሶስተኛ ደረጃ የፕሮግራም ልዩነት የመሬት ጥያቄ ነው፡፡የአንድት ፕሮግራም በአንቀጽ ቁጥር 4.2.1.2. የሚከተለውን አስቀምጣል፤ “እያንዳንዱ የመሬት ባለቤት መሬቱን የማልማት የመንከባከብ የማከራየት የመሸጥ የመለወጥ በውርስ ወይም በስጦታ ለሌሎች የማስተላለፍ መብቱ በሕግ የተጠበቀ ይሆናል”ይላል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የመድረክ ፕሮግራም የሚከተለውን ያስቀምጣል፤ “…. በራሱ በአርሶ አደሩ በግል ባለቤትነት የሚያዝና አርሶ አደሩ ከመሬት የማይፈናቀልበትን ሁኔታ የሚያረጋግጥ ይሆናል” ይላል፡፡ ከዚህ በግልጽ ለመረዳት የሚችለው አርሶ አደሩ መሬቱን የመሸጥ የመለወጥ መብት የሌለው መሆኑን ነው፡፡ኢህአዴግ መሬትን ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ይልቅ ይበልጥ ለፖለቲካ ግብ እንደተጠቀመበት ሁሉ፣ የመድርክ ፕሮግራም በተወሰነ ደረጃ ይህን የሚያስተጋባ ነው፡፡ እነዚህ የፕሮግራም ልዩነቶች በምርጫ 2002 ጊዜ መደረክ ከሚተችበት ዋንኛጉዳዮች መሃል አንዱ ነበር፡፡ ሆኖም መድረክ በምርጫ አሸንፎ የመንግሥት ስልጣን ቢይዝ የመሬትን የመሸጥና የመለወጥን ጉዳይ ለሕዝብ ውሳኔ ለማቅረብ በአባል ፓርቲዎች መካከል ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

እነዚህ መሠራታዊ የሆኑ ሀገራዊ እይታ ላይ ልዮነቶች ቢኖሩም፣ ያለንበት የትግል ምህራፍ ከአይዶሎጂም በላይ የተሻገረ መሆኑን ያገናዘበና የትግሉ ዋንኛ ግብ የህግ የበላይነትና ሰባዓዊ መብቶች የተከበረባት ነጻና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የመፍጠርን ጉዳይ ቅድሚ መስጠት ግድ የሚልበት ወቅት መሆኑን ከግንዛቤ ያስገባ ነበር፡፡ ስለሆነም መድረክን እንደ ስትራቴጂክ መሳሪያነት በመውሰድ በጥምረትነት ወደ ምርጫ 2002 መግባቱ በሕብረተሰቡ ዘንድ የተሻለ ተቀባይነት ለማግኘት ተችሎ ነበር፡፡ መድርክ በምርጫ 2002 ቀላል ያለሆነ ድጋፍ የተቸረው እንደነበር መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም የመድርክ ፕሮግራም እነዚህና ሌሎች መሠረታዊ የፖለቲካ ፍልስፍና ልዩነት ይኑረው እንጂ፣ መለስተኛ ፕሮግራም በሀገራችን ዴሞክረሲያዊ ስርዓትን ከመፍጠር አንጻር በቂ ነው የሚል ግምገማ መወሰዱ ትክክለኛ አቋም እንደነበረ መግልጽ ይቻላል፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ መድረክ ሶስት ድሎች ማስመዝገብ መቻሉን እንረዳለን፡፡ የመጀመሪያው ውጤት ላሉፉት 40 ዓመታት (በተለይም ላለፉት 22 ዓመታት) በተቃዋሚ ጎራ አብሮ ላለመስራት ፈታኝ ሆኖ የቆየውን ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትና ብሔር ላይ ከተመሰረቱ ፓርቲዎች መሃከል የነበረው ክፍተት በተወሰነ መልኩ ማጥበብ የተቻለበትን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ፓርቲያችን በኢትዮጵያ ብሔርተኝነትና ብሔር ደረጃ ከተደራጁ ፓርቲዎች መሐል ለመፍጠር የሞከረው ድልድይ ለቀጣዩ የትግል ምዕራፍም ጠቃሚ ስንቅ ተደርጐ መወሰድ ይገባል፡፡ በሁለተኛው ደረጃ ምንም እንኳን በህዝብ ውስጥ ያለው ተቀባይነት በሂደት እየቀጨጨ የሄደበት ሁኔታ ቢኖርም፣ በምረጫ 2002 የተሻለ ድጋፍ ከሕብረተሰብ የማግኘቱ ጉዳይ እንደ መልካም ጎኑ ሊታይ ይችላል በዚህ የምርጫ ወቅትም 38% የሕዝብ ድምጽ ማግኘቱ የሚታወቅ ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ መድረክ በተነጻጻሪነት የተሻለ የመደራደር አቅም ይዞ ለመውጣት መቻሉን መረዳት ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ መድረክ ከምርጫ 2002 በኃላ የጀመረውን ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ከይዘት አንጻር ወደ ላቀ ትብበርና ሀገራዊ ራዕይ ከማስያዝ ይልቅ ቁልቁል መሄድ መጀመሩን የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶችን መለየት ይቻላል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ መድረክ በሠጥቶ መቀበል መልኩ መሠረታዊ የሆኑትን የፕሮግራም ልዩነቶች የማጥብብ ሥራ ማድርግ ሳይችል በድፍረት ወደ ግንባር ተሸጋግሯል፡፡ ይህ የቅርጽ እንጂ የይዘት ለውጥ ያልታየበት ሽግግር ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ በመለስተኛ ፕሮግራሙ ላይ ምንም ዓይነት ለውጣ ሳይደረግ በ2002 የነበረው መለስተኛ ፕሮግራም ወደ ሙሉ ፕሮግራምነት ተቀይሯል፡፡ የመድረክ መለስተኛ ፕርግራም በገጽ 9 ላይ በግልጽ እንደሚያስረዳው “መለስተኛ ፕሮግራሙ ያልተሟሉ በርካታ ነገሮች እነደሚኖሩት እንገነዘባለን፣ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ግንባታ ስራ የመላ ኢትዮጵያዊያን ስራ እንደመሆኑ መጠን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ለዚህ ፕሮግራም መጎልበት እና ተፈጻሚነት የራሳቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ በአክብሮት እንጠይቃለን” ይላል፡፡ ይህን ተሰርቶ ያላለቀን ፕሮግራም እንደግንባሩ ፕሮግራም አድርጎ መወሰዱ ስህተት እንደነበረ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ግንባር በባህሪው ከጥምረት በተለየ መልኩ በመሠረታዊ የፖለቲካ አጀንዳዎች ላይ ወጥ አቋም የሚያዝበት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ስለሆነም መድረክ እንደ ፖለቲካ ድርጅት በወሳኝ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ግልጽ አቋም መያዝ ሲገባው እንደተንጠለጠለ እንዲቀር መደረጉ አደገኛነቱ በግልጽ ይታያል፡፡ ይህ ያልተሟሉ በርካታ ችግሮች ያሉት ፕሮግራምን የግንባሩ ፕሮግራም ማድረግ በአባላትና በደጋፊዎችን (አመራሮችን ጨምሮ) ግራ መጋባት ውስጥ የከተተ ነው፡፡ እንደ አጭር የስትራቴጂ አቅጣጫ መድርክ በጥምረት ወቅት መለስተኛ ፕሮግራም ይዞ መጓዙ አግባብ እንደሆነ የተወሰደ አቋም ቢሆንም፣ ወደ ግንባርነት ሲሸጋገር የይዘት ለውጥ ማምጣት የግድ ይል ነበር፡፡ ከዚህም አንፃር አንድነት መሠረታዊ መለያው የሆነው የፖለቲካ ፍልስፍናዎቹ ይበልጥ እንዲዳብሩና የአይዲዬሎጂ ጥራት በሂደት ማምጣት እንዳልቻለ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህ የጥራት ችግር አንድነት ግልጽ የሆነ የኃይል አሰላለፍ ከመፍጠር አንፃር የሚጠበቅበትንና የሚፈለገውን ኃላፊነት ለመወጣት ያለመቻሉን ያሳያል፡፡

በተጨማሪም እነዚህን መሠረታዊ የፖለቲካ ፍልስፍና ልዩነቶችን ይዞ መድረክ የጋራ ዝርዝር ፖሊሲ (ሪፎርም) መቅረጽ አዳጋች እንደሚሆንበት መገንዘብ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የመድረክ አባል ፓርቲዎች በመሬት ጉዳይ ላይ ባላቸው የተለያየ አቋም የተነሳ አንድነትና መድረክ ተመሳሳይ የሆነ የግብርና የኢንዲስትሪ ፖሊሲ ሊኖራቸው አይችልም፡፡ በአንድነት እምነት ያለፉት ስርዓቶችና ኢህአዴግ በመሬት ጉዳይ ላይ የተከተሉት ፖሊሲ ሀገራችን ግብርና መሠረት ካደረገ ኢኮኖሚ ወደ ኢንዲስቱሪ የማሸጋገር እድል ጠባብ እንዲሆን እንዳደረጉት ያምናል፡፡ መሬት በኢትጵያ ታሪክ ውስጥ ያለውን ውርስ (የሌጋስ ችግር) ከግምት ማስገበት አግባብ ሆኖ፣ መሬት ግን ሙሉ በሙሉ የፖለቲካ መሳሪያነት መጠቀም ከኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገታችንን ወደ ኃላ እንዳስቀረን የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አንድነት ፓርቲ እንደ ሊብራል ፓርቲ ተከታይነቱ ለግለሰብ መብት ቅድምያ የሚሰጥ ነው፡፡ በመድረክ ፕሮግራም ውስጥ ያለው ዕይታ ከዚህ እጅግ የተለዬ ነው፡፡

እነዚህ መሠረታዊ የፕሮግራም ልዩነቶች መድረክ ወደ ግንባር ሲሸጋገር ማቀራረብ ይገባ ነበር፡፡ መሠረታዊ የሆነ የፕሮግራም መቀራረብ ሳይፈጠር፣ አብሮ የመስራት ሂደቱ ጠንካራ መተማመንን ሳይፈጠር በችኮላ ግንባር መመስረቱ ከፍተኛ ስህተት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ መሠረት ላይ ሆኖ በግንባርነት የተደረጀና የተቀናጀ ትግል ለማድረግ አዳጋች ነው፡፡ አሁን በግንባርነት ያለው መድረክ ካሉበትና ከላይ ከተጠቀሱት ለዩነቶች ምክንያት አገዛዙን ሊገዳደር የሚችል ኃይልን ማሰለፍ የሚችል ስብሰብ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም፡፡ ይህ ባልተፈታበት ሁኔታ አንድነት በመድረክ በኩል ስትራቴጂካዊ ግቡን እውን ሊያደርግ ይሳነዋል፡፡ ስለሆነም መድረክ ሰጥቶ በመቀበል መንፈስ የአባል ፓርቲዎችን ፕሮግራም ማቀራረብ ቢቻል አንድ ወጥ የሆኑ ፓርቲ ሆነው የሚወጡበት ዕድልን መፍጠር፣ መቻል አለባቸው፡፡ ይህ ካልተቻል መድረክ ትርጉም ያለው ስብስብ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ስለሆነም በምንለያይባቸው ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ማድረግ አስፈላጊነቱና አጣዳፊነቱ በግልጽ መገንዘብ ያስፈልጋል ብለን እናምናለን፡፡

ለ. ስትራቴጂካዊ ግቦች

መሠረታዊ ሊባሉ የሚችሉትን ከፍ ብለው የተዘረዘሩትን የፕሮግራም ልዩነቶችከግንዛቤ ስናስገባ መድረክን ከዓላማ አንድነት ይልቅ የስትራቴጂካዊ ጥምረት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባዋል፡፡ የመድረክ ዋና ግብ ተብሎ ሊወሰድ የሚገባው አሁን ካለንበት አምባገነናዊ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚወስድ የመሸጋገሪ ድልድይ ነው፡፡ በሌላ አነጋገገር ያለንበት የትግል ምዕራፍ ከአይዶሎጂም በላይ ያለፍ፣ ሀገርን ከጥፋት የመታደግ የትግል አቅጣጫ የያዘ ነው፡፡ ከዚሀ አንጻር አንድነት ራሱን ከአይዶሎጂ ትብታብ በማውጣት ትግሉ ወደ ፊት እንዲራመድ ከማድረግ አንጻር መድረክ እንዲመሰረት ማድረጉን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሂደቱም ኢህአዴግ በሁለቱ ኃይሎች (በኢትዮጵያ ብሄርተኞች እና ብሔር ላይ የተመሠረቱ ኃይሎች) መሃል የተፈጠረውን ሸለቆ መሻገር አይችሉም ተብሎ የተወሰደውን እምነት በተወሰነ ሁኔታ ለመናድ መቻሉን አንረዳለን፡፡

መድረክን እንደ አጭር ጊዜ ስትራቴጂክ ጥምረት አድርገን ስንገመግመው፣ አንድነት መድረክን እንዲመሠረትና የተሻለ ሆኖ እንዲወጣ ፓርቲ ለማድረግ የወሰደቸው ውሳኔዎች ተገቢና አግባብ ነበሩ ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ችግሮች እንዳሉ ሆኖም፣ በ2002 ምርጫ የታዩ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች የመድረክ ፕሮጀክት በአባል ፓርቲዎች መሐል ሰጥቶ መቀበል ከተለመደ የተሻለ ሀገራዊ ፕሮጀክት ማድረግ እንደሚቻል አሳይቶናል የሚል እምነት አለን፡፡

አንድነት መድረክን እንደ ስትራቴጂ ጥምረት የወሰደው ስልጣን በዚህው ስብስብ በዘላቂነት መያዝ ይቻላል ከሚል አስተሳሰብ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ መድረክ እንደ ስትራቴጂክ ጥምረትነት ማሳካት ያለበት ግብ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መፍጠር ነው ብለን ብናምንም፣ አንዳንድ የመድረክ ድርጅቶች ከዚህ ተጻራሪ በሆነ መንገድ መድረክን የስልጣን ኮርቻ ላይ የመቆናጠጥ ግብ አድርገው ይዘው የሚንቀሳቀሱ እደሆን መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ የመድረክ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትግል በ“ደቡብ” (የኦሮሞና የደቡብ ብሔረሰቦች ጥምረት) እና በሰሜን (አማራና ትግራይ) መሃከል ያለ ትግል አድርገው መውሰዳቸው በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ ይህ አደገኘ አስተሳሰብ ዋንኛው ግብ ስልጣን ቢቻል በምረጫ ካለሆንም የጋራ መንግስት የመመስረት አቅጣጫ ይዞ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ በምርጫ 2002 አንድት በአንዳንድ ቦታዎች እጩ እንዳያቀርብ የተከለከለው ከዚህ አንጻር ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ አንድነት ፓርቲ በአዲስ አበባና በአማራ ክልል ብቻ ታጥሮ እንዲኖር ግልጽ ፍላጎት መኖሩን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ የተንሸዋረረ ስትራቴጂክ ዕይታ የሚሰጠን መልክት ቢኖር መድረክ አባል ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ ልዩነቶች ፕሮግራምን ከማዋሃድ ያልተናነሰ ለድል የሚያበቃ የጋራ ስትራቴጂ ሊኖረን እንደሚገባ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

ሌላው አሳሳቢ የሆነው ችግር የመድረክ አባል ድርጅቶች ውስጥ አንዳንዶቹ በግልጽ አንድነትን የመጠቅለል ዝንባሌ ያለውና ይባስ ሲልም የአማራ ፓርቲ አድርጎ የማቅረብ/የማመን ሁኔታ አለ፡፡ ይህ ችግር የሚመነጨው አንዳንድ የመድረክ አባል ፓርቲዎች መድረክ የብሔር ጥምረት ውጤት አድረገው በመውሰዳቸው እንደሆነ እንረዳለን[1]፡፡ በመሆኑም መድረክ ይህን መሠረታዊ የትግል አቅጣጫ ካላስተካከለ፣ ውህድ ፓርቲ ለመሆን መንገዱ ዝግ ነው፡፡

ትግሉን በዚህ ዓይነት የትግል አቅጣጫ በመተንተን፣ አብዛኞዎች የመድረክ አባል ድርጅቶች ፕሮግራም አቀራርቦ ውህደት የመፈጸም ፍላጎት እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ውህደት ብንፈጥር ሕዝባዊ መሠረታችንን (ኮንስቲቱዮንሲያችንን) እናጣለን የሚል እምነት አላቸው፡፡ ፕሮግራም የማቀራረብ ስራ የምር ሳይሞከር ይህ ፍራቻ በፓርቲዎቹ ውስጥ የሚፈጠርበት ዋንኛ ምክንያት የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል “የነፍጠኛች ጉያ ውስጥ ተሾጎጣችሁ” ይለናል ከሚል ሰንካለ ምክንያት ነው፡፡ ስለሆነም ሙከራዎች ቢኖሩም፣ የመቀራረቡና የመተማመን መንፈሱ ገና ሩቅ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ልዩነቶች ምክንያት መድረክ መናበብ የሚችል፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ተፎካካሪ የሆነ የኃይል አስላለፍ ይዞ የሚወጣ ኃይል ሆኖ የማግኘቱን እድል ጠባብ ያደርገዋል፡፡

ሐ. ጠቃሚ ድምዳሜዎች

ከዚህ አንጻር አንድነት አባል የሆነበት መድረክ እንደ ግንባር ትርጉም ያለው ፖለቲካ ኃይል ሆኖ ለመውጣት ከተፈለገ፤

* በመድረክና በአንድነት ፕሮግራም መሃል መሠረታዊ የሆነ የአይዶሎጂ ከፍተቶች መኖራቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

* ይሁን እንጂ በጥምረት ደረጃነት ይህን አቻችሎ መሄድ መሞከሩ ትክክለኛ የትግል አቅጣጫ መሆኑን ከግንዛቤ አስገብተናል፤

* መድረክ እስከ 2002 ምረጫ ድረስ የፈጠረው ምስል፣ የመደራደር እቅም እና በኢትዮጵያ ብሔርተኞችና ብሔር ፓርቲዎች የተሞከረው ጥምረት ትክክለኛ መስመር ነበር ማለት ይቻላል፡፡

* ይሁን እንጂ መሠረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ ግልጽ አቋም የሌለውፕሮግራምተይዞ ግንባር ሆነናል መባሉም ክፍተት እንደሆነ ተገንዝበናል፡፡

* አንድነት በመድረክ ውስጥ በግንባርነት መቀጠል ካለበት አንድ ወጥ ፕሮግራም ሊኖረው ያስፈልጋል የሚል እምነት አለን፡፡ ይህን ሰጥቶ በመቀበል፣ በሆደ ሰፊነት እና በተከታታይ ውይይቶች ሊመነጭ ይችላል የሚል እምነት አለን፡፡

* በአንድትና በመድረክ ፕሮግራም መሃከል ያለው ልዩነት በአባላትና በደጋፊዎች መሃል ግራ መጋባት ውስጥ ከቷል፡፡ ይህ በሂደትም የእይታና የፓርቲውን ብራንድ ከመበረዝ አንጻር የራሱ የሆነ ችግር አስከትሏል፡፡ አልፎ አልፎም አንድነት መድረክ ውስጥ የሚገኝ የአማራ ተወካይ ተደርጎ እስከመወሰድም ደርሷል፡፡ ይህ ባፋጣኝ ሊቀረፍ የሚገባውና መፍቴውም የፕሮግራም ወጥነት ብቻ ነው ብለን እናምናለን፡፡

* መድረክ ከስትረቴጂክ ግብ አንጻር ግልጽነት ይጎድለዋል፡፡ በአንድነት በኩል የመድረክ ስትራቴጂካዊ ግብ ነጻና ዴሞክራሲያዊትን ኢትዮጵያ መመስረት መሆን አለበት ብለን እናምለን፡፡

በመድረክ ውስጥ የሚታዩትን ውስጣዊ ድክመቶች፣ የአይዶሎጂ ግልጽነት እጦት፣ መተማመንንና መቻቻል ከመፍጠር አንጻር ያሉ ችግሮች የነዚህ ችግሮች ነጸብራቅ ነው የሚል እምነት አለን፡፡

2. የመድረክ መተዳደሪያ ደንብን ግምገማ

መተዳደሪያ ደንብ ከማዕከል እስከ መሠረታዊ ደርጅት በሚዘረጋው መዋቅሩ በመመሪያነት የሚጠቅም ዓላማን፣ፕሮግራምን፣ፖሊሲና ስትራቴጂን ለማስፈጸም የሚረዳ ህግ ማለት ነው፡፡መተዳደሪያ ደንብ አባሎች መብትና ግዴታቸውን አውቀው የሚሳተፉበትን ሁኔታ በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ከዚህም በላይ በአመራር አካሎች እና በበታች አባሎች መሐከል ዲሞክራሲያዊ የሆነ አሰራር እንዲኖር አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡መተዳደሪያ ደንብ ዓላማን ተግባራዊ ለማድረግ የግልና የጋራ ኃላፊነትን በተጣጣመ መልኩ በሥራ ላይ የሚውልበትን መርሆዎች ማካተት አለበት፡፡

የግንባር መተዳደሪያ ደንብ የአባል ፓርቲዎች ሃሳብና የተግባር አንድነት እንዲኖረው፤የስራ ተነሳሽነትና የአላማ ፅናት እንዲያድግ ብሎም የግንባሩ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ቀልጣፋ፣አስተማማኝና አመርቂ እንዲሆን በአባል ፓርቲዎች ተሳትፎ መጠናከርን ከመርሆዎቹ ውስጥ በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡መተዳደሪያ ደንብ የአባሎችን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ የውክልና አሰራርን እንደ ዋነኛ አሰራር ስልት ይጠቀማል፡፡

ከእዚህ መሠረታዊ ነጥቦች አንጻር የኢትዮጵያ ፌዴራላላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ(መድረክ)የግንባሩ መተዳደሪያ ደንብ ለአባል ፓርቲዎችና አባላት ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አንጻር፣ መቀራረብ፣መተማመንና ለአንድ አገራዊ ግብ ከመጓዝ አንጻር ሲታይ ምን ይመስላል የሚለውን ማየት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ስለሆነም የመድረክ ደንብ ከሚከተሉት አራት ጉዳዮች አንጻር ታይቷል፤(ሀ) ከአወቃቀር፣ከይዘትና ከአሰራር አንጻር፣ (ለ) ከዲሞክራሲዊነት አንጻር፣ (ሐ) ከአሳታፊነት አንጻር፣ እና (መ)ከምርጫ ህግ አንጻር ናቸው፡፡

ሀ. ከይዘት፣አወቃቀርና ከአሠራር አንጻር

የመድረክ መተዳደሪያ ደንብ መድረክ ቅንጅት በነበረበት ወቅት የነበረው በመሆኑ ከይዘት አንጻር ብዙ ለውጥ እንደሌለው ተረድተናል፡፡ ሆኖም ቅንጅትና ግንባር በመሰረቱ በምርጫ ህግም ሆነ ከተግባር አንጻር መሰረታዊ ልዩነት ያለው በመሆኑ (ቅንጅት ለተወሰነ ተግባር የሚቋቋም ሲሆን ግንባር ግን ላልተወሰነ ጊዜ የሚቋቋም በመሆኑ)በዚያው መጠን ልዩነት ስላለው ታስቦበት፣ተጠንቶና ታቅዶ የተሰራ አይደለም፡፡

በመድረክ ህገ-ደንብ ውስጥ ከአወቃቀር አንጻር መሠረታዊ ሊባሉ የሚችሉ ክፍተቶች ተስተውሏል፡፡ አንቀጽ 5 “የግንባሩ መዋቅር” በሚለው አርስት ስር እንደተቀመጠው በዚህ መዋቅር ውስጥ በግልጽ የተቀመጠው የግንባሩ ጠቅላላ ጉባኤና የግንባሩ ስራ አስፈጻሚ ብቻ ናቸው፡፡ በመሆኑም መድረክ የራሱ ብሔራዊ ም/ቤት አለመኖሩ የስራ አስፈጻሚውን ሥልጣን በማብዛት ኃላፊነት አንድ ቦታ አከማችቷል የሚል እምነት አለን፡፡ ስለዚህም የተጠያቂነትና አሳታፊነትን መንፈስን ለማጎልበት ብሔራዊ ም/ቤት ያስፈልገዋል ብለን እናምናለን፡፡

በመድረክ ህገ-ደንብ ውስጥ የተቀመጡ አንዳንድ አንቀጾች ከአሰራር አንጻር ችግር ይዞ ሊመጡ እንደሚችሉ ታይቷል፡፡ አንደኛ የመድረክ ህገ-ደንብ አንቀጽ 3 “አንድ አባል ድርጅት ብቻ በሚንቀሳቀስባቸው ዞኖች ወረዳዎች (የጋራ አመራር ያለው ኮሚቴ ለመመስረትካልተቻለ) በቦታው ያለው አባል ድርጅት ጽ/ቤትና አመራር ግንባሩን ወክሎ እንዲሠራ ይደረጋል“ ይላል፡፡እዚህ ላይ የጽህፈት ቤቶቹ ወጪዎች ኪራይ በማን ይሸፈናል የሚለው አልተብራራም፤ ለአሠራር አስቸጋሪ ነው ብለን እናምናለን፡፡

ሁለተኛ አንቀጽ 17/ለ “የእጩዎች አቀራረብ ስነስርዓት“ በሚለው አንቀጽ ስር “በምርጫ ህጉ መሠረት በየጊዜው ለሚካሄዱት የጠቅላላ፣የአካባቢ እና የማሟያ ምርጫዎች አባል ድርጅቶች በመድረክ ስም 45% ዕጩዎችን በእኩልነት ሊያቀርቡ ይችላሉ” ይላል፡፡እዚህ ላይ 45% በዕኩልነት ማቅረብ ባይቻል ምን ይሆናል የሚለውን አይመልስም፡፡ በተጨማሪም ህገ-ደንቡ “ዕጩዎች ማቅረቢያ መስፈርቶች በጋራ ስምም”ነት ተዘጋጅተው ስራ ላይ እንዲውሉ ይደረጋል“ይላል፡፡ ይህ በ2002 ዓ.ም ካየነው አገር አቀፍ ምርጫ ልምድ ስንነሳ ብዙ ችግር ያስከተለ መሆኑ በተጨባጭ የሚታወቅ ስለሆነ የእጩ ማቅረቢያ መስፈርት በግልጽ መቀመጠ አለመቻሉ ተገቢ አይደለም፡፡ ምርጫ ሲደርስ ሊሰሩ የሚገባቸው ብዙ ጉዳዮች ስለ አሉ መስፈርቱ አስቀድሞ መሠራት አለበት፡፡ ያለበለዚያ ችግርን አስቀድሞ አለመፍታት መሠረታዊ ስህተት ይሆናል፡፡

ሶስተኛ ከአሰራር አንጻር ግልጽ ያልሆነው የህገ-ደንብ ክፍል አንቀጽ 21 “የአባል ድርጅቶች ግዴታ“ የሚለው ነው፡፡ አንቀጽ 21 ስር “መድረክ በምርጫ ካሸነፈ የጋራ መንግስት የማቋቋምና የመድረክን የፖለቲካ ፕሮግራም በስራ ላይ ማዋል” ይላል፡፡ሆኖም የጋራ መንግስት ከማን ጋር ሊመሠረት እንደሚገባው በግልጽ አልተቀመጠም፡፡ መድረክ በምርጫ ካሸነፈ ለምን የጋራ መንግስት ማቋቋም አስፈለገው? ከአባል ድርጅቶች ጋር ለማለት ተፈልጎም ከሆነ እንዴት የጋራ መንግስት ከአባል ድርጅቶች ጋር እናቋቁም ለሚሉ ጥያቄዎች ህገ-ደንቡ መልስ የለውም፡፡ እነዚህ ነጥቦች መሬት ላይ ወርደው በአሰራር ሂደት በተግባር ሲታዩ ችግር የሚያስከትሉ በመሆናቸው መስተካከል ወይም መዳበር ወይም ግልጽ መሆን አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡

ለ. ከዴሞክራሲያዊነት አንጻር

የመድረክ መተዳደሪያ ደንብ የግምባር መተዳደሪያ ደንብ ነው ካልን ሰፊ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎን የሚያበረታታ መሆን ይገባዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የመድረኩን አንዳንድ አንቀጾች ለማየት ምክረናል፡፡ አንቀጽ 4“አባልነት” በሚለው አንቀጽ “ማንኛውም የግንባሩን ፕሮግራም፣መተዳደሪያ ደንብና የስምምነት ሰነድ የተቀበለ፣በሕግ የተመዘገበ እና ከግንባሩ አባል ድርጅቶች ሙሉ የድምጽ ድጋፍ ያገኘ የተቃዋሚ ፓርቲ የግንባሩ አባል መሆን ይችላል” ይላል፡፡ ይህ አንቀጽ መድረክ ዝግ ስብሰብ ለመሆኑ ዋንኛ መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይቻላል፡፡በተጨማሪም አንቀጽ 8 “የመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ ስልጣንና ተግባር” በሚለው ስር “የግንባሩን መስፈርት የሚያሟሉ ፓርቲዎች የአባልነት ጥያቄ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በኩል ተመርምሮ ሲቀርብለት በአባል ድርጅቶች ሙሉ ድጋፍ መሆኑን አረጋግጦ አባልነቱን ያጸድቃል ይላል፡፡ ሰረዝ የኛ ሲሆን ይህ ሙሉ የድምፅድጋፍ የሚሉ አገላለፆች ኢ-ዲሞክራሲያዊ የሆነና አንድ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማስፈን እታገላለሁ ከሚል ግንባር የሐሳብ፣ የፍላጎትና የአመለካከት ነፃነትን የሚገፍ ነው፡፡ ደንቡ በአብዛኛው ቦታ ተቀባይነት ያለውን በአብላጫ ድምጽ 5ዐ+1 የመወሰን አሰራር እናዳይኖር የተደረገበት ምክንያት ከአራት ዓመት በኋላም ቢሆን በመድረክ አባል ፓርቲዎች መሃል ያለውን ዝቅተኛ የመተማመን ደረጃ ማሳያ ነው፡፡ መድረክ ከተመሠረተ በኋላ ለአለፉት አራት ዓመታት ብዙ ፓርቲዎች አባል ለመሆን ቢያመለክቱም አባል ለመሆን አለመቻላቸው ይህው ኢ-ዴሞክራሲያዊ የሆነው የውሳኔ አሰጣጥ ደንብ ነው፡፡

በመጨረሽያም አንቀጽ 20 “የአባል ድርጅቶች መብት”በሚለው አንቀጽ ስር አንድ አባል ድርጅት ከግንባሩ መልቀቅ እንደ መብት ሊታይለት ይገባል ሆኖም ይህ መብት በአንቀጹ ስር አልሰፈረም፡፡በነዚህና በመሳሰሉ ጉዳዮች የተነሳ የመድረኩን መተዳደሪያ ደምብ ዴሞክራሲያዊነት ይጎድለዋል ብለን እናምናለን፡፡

ሐ. ከአሳታፊነት አንፃር

የመድረክ መተዳደሪ ደንብ የመድረክን አባል ፓርቲዎችና አባላት አሳታፊ ሊያደርግ ይገባል፡፡መድረኩ ግንባር እንደመሆኑ መጠን በቀጣይ ወደ ውህደት ማምራት ይጠበቅበታል፡፡በዚህ ረገድ ሠፊ የአሳታፊነት ሜዳ ሊኖረው ግድ ቢልም የሚከተሉት ጉድለቶች በደምቡ ውስጥ ተንፀባርቀዋል፡፡ አንቀጽ 7 “የመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ” ውስጥ“የመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ ከአባል ድርጅቶች ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በድርጅቶቹ የሚወከሉ፣አስር አስር አባላት የሚሳተፉበት አካል ይሆናል፡፡ቁጥሩም የግንባሩ አባል ድርጅቶች ሲመጨመሩ ቁጡሩ ይጨምራል” ይላል፡፡

ከመርህ ደረጃ አንድ በፓርቲነት የተቋቋመ ግንባር አባላት በግንባሩ በተለያዩ እቅስቃሴ ውስጥ እዲንቀሳቀሱ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ይሁን እንጂ መድረክ ከላይ የተንጠለጠለና የአባላት መሠረት የሌለው ስብስብ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ስለሆነም መድረክ የአመራሮች እንጂ የሠፊው አባለትና የደጋፊዎች አይደለም፤ በአባላትና በደጋፊዎች ውስጥ የኔነትና የባለቤትነት ስሜት መፍጠር እንዳይችል፣ ተጠያቂነት ያለው አሰራር እንዳይኖር አድርጎቷል፡፡ መድረክ ምን አቀደ? ምን ያህሉን አሳካ? የሚለው እንኳን ለማወቅ ፈጽሞ አይቻለም፡፡ ለምሳሌ አብዛኞዎቹ የአንድነት አባላት (የአንድነት ከፍተኛ የአመራር ሰጪ ነው የሚባለውን የብሔራዊ ምክር ቤቱን ጨምሮ) መድረክ በቅርቡ ስለአወጣው ማኒፌስቶ ምንም ዓይነት ግንዛቤ የላቸውም ማለት ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የመድረክ ፕሮግራምና ደንብ በአባለት ውስጥ ግልጽ ግንዛቤ አለ ማለት አይቻለም፡፡ ይህ አደረጃጀቱ አሳታፊ ባለመሆኑ የሚመጣ ችግር እንደሆነ ተገንዝበናል፡፡ በዚህ ዓይነት አደረጃጀት ወደ ህዝብ መውረድ አዳጋች እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ እነዚህ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስብሰባዎች በየአባል ፓርቲዎች አማካኝነት ሊሰጡ ይገባቸዋል የሚለው መከራከሪያ በቂ አይደለም፡፡ የመድረክ አባል ፓርቲዎች የጋራ ግንዛቤ ይኖራቸው ዘንድ መድረክ ይህን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባው ነበር፡፡

ስለሆነም የመድረክ ጠቅላላ ጉባኤን አባላት በአስር አስር አባላት ባሉት የሥራ አሰፈጻሚ ስብስብ መገደቡ አግባብ ነው ብለን አናምንም፡፡ ግንባር ነን ካልን አባል ፓርቲዎች መዋቅር ያላቸ በመሆኑ፣ እንደማንኛውም ጠቅላላ ጉባኤ አጠራር መስፈርት የግንባሩ አባል ድርጅቶች ከታች ከመሰረታዊ ድርጅት ጀምሮ በመወከል ትርጉም ሊሰጥ የሚችል ጠቅላላ ጉባኤ ተደርጎ ዳግም ሊዋቀር ይገባል ብለን እናምናለን፡፡ በዚህው ሂደት መደረክ ከመሠረታዊ ድርጅት ጀምሮ የአሳታፊነቱን ደረጃውን ማጎልበት ይጠበቅበታል ብለን እናምናለን፡፡ይህን ማድረግ ባለተቻለበት ደረጃ መድረክን የምር ልንወስደ የሚገባ ስብስብ አድረግን መመልከት አይኖርብንም የሚል እምነት አለን፡፡

በሌላ በኩል አንቀጽ 11 “የግንባሩ ለቀመንበር ተግባርና ኃላፊነት” ስር ሊቀመንበሩና ም/ሊቀመናብርትና ፀሐፊው በዙር ይመረጣሉ ይላል፡፡ ደንቡ ግንባሩን ወደ ፊት ሊያራምድ የሚችል ችሎታውና አቅሙ ያላቸውን ሰዎች ወደ ፊት ሊወጡበት የሚችልበት ስርዓት ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን፡፡ በተለየም የግንባሩ ሊቀመንበር ም/ሊቀመናብርት ፀሐፊው አስር አሰር ሆነው በተወከሉ የስራ አሰፈጻሚ አባላት በተዋቀረው “ጠቅላላ ጉባኤ” ሳይሆን፣ የግንባሩ አባል ፓርቲዎች መሠረታዊ ድርጅቶች በተወከሉበት ሰፊ ስብስብ በችሎታቸው ሊቀመንበሩ ም/ሊቀመናብርና ፀሐፊው በነፃ ሊመረጡ ይገባል ብለን እናምናለን፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው ከ2ዐዐ እስከ 3ዐዐ አባላትን ያጠቃለለ መሆን አለት ብለን እናምናለን፡፡

ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ጠቅላላ ጉባኤ አለ አሳታፊ ነው ማለት አይቻልም፡፡ጠቅላላ ጉባኤ የግንባሩን አጠቃላይ አሰራርና ስትራቴጂ የሚቀይስ በመሆኑ አሁን ባለው የመድረከረክ ጠቅላላ ጉባኤ ምንም ተግባር የማይፈጸምበት በመሆኑ ሊስተካከል የሚገባው ነው፡፡

መ. ከምርጫ ሕግ አንጻር

የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 ክፍል አራት “ስለ ፖለቲካ ፓርቲዎች መዋሃድ፣ግንባር መፍጠር መቀናጀትና መሰረዝ” ስር ምዕራፍ አንድ አንቀጽ 34 “ግንባር ስለመፍጠር“ በሚለው ስር አንድ ግንባር ሲፈጠር መሟላት ያለበትን በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ በዚህ ረገድ የመድረክ መተዳደሪያ ደምብ አንቀጽ 21 “የአባል ድርጅቶች ግዴታ” በሚለው ስር 21-9 “ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የሚደረገው ትብብር በውህደት ደረጃ ብቻ የማድረግ“ ይላል፡፡ይህ ከላይ ከተጠቀሰው የምርጫ ህግ ውስጥ መቀናጀትን የሚከለክል ግልጽ ድንጋጌ ባለመኖሩ በግንባር ላይ ግንባርን ሊከለክል ይችል ይሆናል እንጂ መዋሃድን ብቻ ፈቅጃለሁ ማለቱ ከህጉ አንፃር ተገቢ አይደለም፡፡

ሠ. ጠቃሚ ድምዳሜዊች

የመድረክን ህገ-ደንብ በሚመለከት የሚከተሉትን ድምዳሜዊች መውስድ ይቻላል ብለን እምናለን፡፡

* ህገ-ደንቡ መድረክ ከተፈጠረም አራት ዓመታት በኃላም በአባል ፓርቲች መካከል ያለውን እጅግ ዝቅተኛ የመተማመን ደረጃ ያሳያል፡፡ እንደምሳሌነት ደንቡ ሊቀመንበር፣ ም/ሊቀመናብርትና ፀሐፊው የሚመረጥበትን መስፈርት በችሎታ ላይ የተመሠረተ ሊያደርገው አልቻለም፡፡

* ህገ-ደንብ አንዱ አንዱን ሚጠብቅበትና አባል ፓርቲች በተናጥል ሊያድጉበት የሚችሉበትን ዕድል ያቀጨጨ ነው፡፡ እንደ ምሳሌነት የእጩ አቀራረብ ስርዓቱን መውሰድ ይቻላል፡፡

* የመድረክ ህገ-ደንብ ከአደረጃጀት አንጻር ኢ-ዴሞክረሲያዊና አባላትን የማያሳትፍ ነው፡፡ በተለይ ጠቅላላ ጉባኤ በስራ አሰፈጻሚዎች ብቻ የተገደበበት ፓርቲ መድረክ ብቻ ሳይሆን አይቀርም፡፡

* የመድረክ ህገ-ደንብ ቀላላ,ል በሆነ ድምጽ ብልጫ በቂ ሊሆኑ በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይ በሙሉ ድምጽ ወይም በ2/3 ድምጽ እንዲያልፉ ያስገድዳል፡፡ ይህ ከአሰራር አንጻርና ከዴሞክራሲያዊነት አንፃር ጠቃሚ እዳልሆነ ከግንዛቤ አስገብተናል፡፡ ከዚህ አንጻር የስብሰባዎች ውሳኔ አሰጣጥና አዲስ አባል ፓርቲያች ስለማስገባት የሚያትተውን የህገ-ደንብ ክፍልን መመልከት በቂ ነው፡፡

ስለሆነም የመድረክ መተዳደሪያ ደንብ አሳሪና ዴሞክራሲያዊነት የሚጎድለው መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

3. የመድረክ አባል ድርጅቶችና አመራሮች በአንድነት ላይ ያላቸው እይታ

አንድነት ወደ መድረክ ሲገባ ይዞ የተነሳው መረህ የብሔርና ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች በርቀት በጥላቻና በጥርጣሬ ከመተያየት ወጥተው በዋና ዋና አገራዊ ገዳዩች ላይ አብረው ቆመው ኢህአዴግን መታገል ይችላሉ በማለት ነው፡፡ አብሮ መሠራት ሲጀምር ተራርቀው በነበሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል፡- (ሀ) በሂደት የነበረው አለመተማመን የፈጠረው የበጎ መንፈስ እጦት ቀስ በቀስ እየቀነሰ ይሄዳል፤ (ለ) የልዩነቶች መኖርን እንደ ተገቢ ነገር አርጎ የመቀበል የፖለቲካ ባህል ይዳብራል፤ (ሐ) እያንዳንዱ ፓርቲ የሌላውን ስጋት በተገቢው መንገድ የመመልከት ሁኔታ ይፈጠራል፤ እና (መ) በጥላቻ ፖለቲካ የመጠመድ ባህልና አንዱ ፓርቲ ሌላውን ፓርቲ ሊጠፋ እንደሚገባው ጠላት ማየቱ ተወግዶ እርስ በእርስ ተከባብሮ በወንድማማችትነት መንፈስ ወደ ታላቁ ግብ ወደ ውህደት መድረስ ይቻላል በሚል ስሌት ነበር፡፡ በሂደትም ኢህአዴግን በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን ይይዛል በሚል እምነት ነው፡፡በመጨረሻም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመገንባት ሕዝቡን የሥልጣኑና የአገሩ ባለቤት ለማድረግ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ አንድነት ከላይ የተጠቀሱትን መርሆዎች ውጤታማ ለማድረግ ብዙ ጎዳና ተጉዟል፡፡ ጥቂቶቹን እንደሚከተለው መጠቀሱ ተገቢ ይሆናል፡፡

ሀ) ሕዝባዊ ስብሰባዎች በአንድነት ወጭም ቢሆን በመድረክ ስም እንዲካሄድ ማድረግ ተችሏል፡፡

ለ) በ2ዐዐ2 ዓም አገራዊ ምርጫ ወቅት መልቀቅ የሌለብን ወረዳዎች በመልቀቅ (ለምሳሌ በሀድያና በከንባታ ውስጥ) አንድ ሰው እንኳን እንዳናወዳድር ሲደረግ በትግስት አልፈናል፡፡ በዚህም በሁለቱም ቦታዎች የነበሩን ጠንካራ መዋቅሮች ፈርሰዋል፡፡

ሐ) 2ዐዐ2 ምርጫ ሕብረ ብሔር ፓርቲ መሆናችን እየታወቀና በአገሪቱ በአብዛኛው ዞኖች የበርካታ ቢሮዎችና፣ አባላት፣ ደጋፊዎች እያሉና ከአካባቢው ፓርቲዎች በብዙ ቦታዎች የበለጥንና የተሻልን ሆነን እያለን አንድነት የአማራ ፓርቲ ነው፡፡ ኦፌዴን ጎንደር ሄዶ እንደማይወዳደር ሁሉ በኦሮሚያም አንድነት እንዳይወዳደር ጫና በመፈጠሩ በብዙ ቦታዎች እጩዎች እንዳናቀርብ ሲደረግ በትእግስት አልፈናል፡፡ ዛሬም ድረስ አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ እየተካሄደብን ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ያህል አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በአዲስ ታይምስ ታህሳስ 2ዐዐ5 ዓም እና ላይፍ መጽሔት ጥር 2ዐዐ5 ላይ ፡-

1. ‹‹አንድነት ዶ/ር ነጋሶን ሊቀመንበር አድርጎ ቢመርጥም የአማራ ፓርቲ ወይም የአዲስ አበባ ልሂቃን ፓርቲ መሆኑን መካድ አያስፈልግም›› ስርዝ የተጨመረ፡፡
2. ‹‹ አንድነት ከመድረክ ገዝፎ ለመታየት የሚፈልግ ይመስላል››
3. ‹‹ አንድነት የሚጠራቸው ስብሰባዎች በመድረክ ስም ይሁን የሚል ሃሳብ አቅርቤ ነበር አልተሳካም››
4. ‹‹ የአንድነት አዝማሚያ በደቡቦች፣ በአረና እንዲሁም በኦሮሞ ላይ የበላይነትን ለማሳየት ነው››
5. ‹‹ አንድነት ፌዴራሊዝምን አይወዱም ፍዴራሊዝምን የሚጠሉት አማሮች ናቸው››
6. ‹‹ አንድነቶች በግድ ነው ከእኛ ጋር የሚታገሉት››
7. ‹‹ ከዶ/ር ነጋሶ ውጭ መሪዎቹ አማሮች ናቸው፡፡ ይህን የምለው ስለ ማውቀው ነው››
8.‹‹ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲ ሲዳማ ወለጋ ወዘተ ሄዶ ድምጽ ማግኘት አይችልም››
9.‹‹ ኦሮሞ አማራ ክልል ሄዶ ምረጡኝ ቢል ድምጽ አያኝገም ኦሮሞ ከሆነ ለምን ኦሮሞ ፓርቲ አይገባም አማራው ኦሮሞ አገር ሄዶ አይመረጥም››
10.‹‹ፍኖተ-ነፃነት ጋዜጣ የመድረክ ይሁን የሚል ሃሳብ አቅርቤ ነበር አልተቀበሉኝም እንጂ›› የሚሉ አስተያየቶች ይገኙበታል፡፡

መ) አንድነት/መድረክን ወክለው ለፓርላማ የተመረጡት የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉን በሚመለከት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ
በመጀመሪያ በመጋቢት ወር 2ዐዐ በወጣው የእኛ ፕሬስ ጋዜጣ ሁለተኛ በጥር ወር 2ዐዐ5 ዓም በወጣው አዲስ ጉዳይ መጽሔት በቅርቡ ደግሞ መጋቢት 2 ቀን 2ዐዐ5 ዓም በወጣው ኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ

1. ስንትና ስንት የዴሞክራሲ አርበኞች ባሉበትና ደጋግመው በምርጫ ያሸነፉ ሰዎች እያሉ አንድ ተወዳዳሪ ብቻ አሸንፏል መባሉ ያሳፍራል ፡፡
2. የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉን መመረጥ የሚያውቀው ኢህአዴግ ነው፡፡ የእሳቸው መመረጥ የኢህአዴግ አሻጥር ነው፡፡
3. ጥርጣሬዎቼን በሙሉ ልናገር ከተባለ መኖር አይቻልም፡፡
4. የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይ ፉ በመድረክ ስም መናገር አይችሉም ተብሎ ተወስኗል እና ሌሎችንም አፍራሽ አስተያየት ሲሰጡ ቆየተዋል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ በመድረክ የወቅቱ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ መሠረት የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ መድረክን መወከል አይችሉም ብሎ ለመወሰን የ6ቱም የመድረክ አባል ድረጅቶች ስምምነት ያስፈልገው ነበር፡፡ አንድነት ፓርቲ ብቻ የ5ቱን ፓርቲዎች ውሳኔ ያስቆመው ነበር፡፡ በወቅቱ ግን አረናና ኦፌዴን የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉን በፓርላማ መድረክ መወከል ደግፈውት ነበር፡፡ በተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ የፓርቲው ም/ሊቀመንበር ላይ የተሰነዘሩት አፍራሽ አስተያየቶች በግለሰብ ላይ ብቻ የተሰነዙሩ ብቻ ሳይሆን በቀጥታ በፓርቲው እና በመላ አባላቱ ላይ የተሰነዘሩ ጎጂና አፍራሽ አስተያየቶች አርገን ነው የምንወስደው፡፡

ሠ) የመድረከ አንዳንድ አባል ፓርቲዎች በተለይም ደቡብ ህብረት ለአንድነት የሚያሳዩት ጥላቻ፣ ለኢህአዴግም ካለው ጥላቻ የሚበልጥ ነው፡፡ ከደቡብ ህብረት ጋር ያለው ግንኙነት በትንኮሳ ላይ የተመሠረተ ነው፤ ጤናማ ግንኙነት የሚያንሰው ነው፡፡ ይህ ደግሞ የተፈጠረው በዓብይ አገራዊ ጉዳዮች በሚደረግ ውይይቶች ቢሆን አይገርምም ነበር፤ ችግሮቹ ግን በጣም ትናንሽ በሚያሰኙ ነገሮች ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድነት ፓርቲ ሚያዚያ 28 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም. በጋሞ ጎፋ ዞን አርባ ምንጭ ከተማ ሕዝባዊ ስብሰባ አካሄዶ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ “የደቡብ ህብረትና የኢሶዴፓ ፓርቲዎች አባላት በስብሰባው እንዳይካፈሉ ተደርገዋል” ሲል የደቡብ ህብረት በደብዳቤ አንድነትን ከሷል፡፡ ክሱ ግን ሀሰት መሆኑን አንድነት አጣርቷል፡፡

ከመድረክ አባል ፓርቲዎች መካከል በተለይ ደቡብ ህብረት ለአንድነት ፓርቲ የሚያሳዩዋቸው ጥላቻና በጎ ያልሆነ አስተያየት በጣም ከፍተኛ በመሆኑ እንታገለዋልን ከሚለው ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ እንኳን ይህ ይብሳል፡፡ እስቲ ጥቂት ምሳሌዎች እናንሳ፡፡

የደቡብ ህብረት በ27/ዐ9/2ዐዐ4 ለመድረክ በፃፈው የክስ ማመልከቻ፡፡

1. የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራርና የማዕከላዊ ም/ቤት አባላት የሆኑና ስማቸው እንዲገለጽ የማይፈልጉ ሰዎች ሚያዚያ 12 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም. በፍትሕ ጋዜጣ ደቡብ ህብረትንና ኢሶዴፓን የሚያጥላሉ መግለጫዎች ሰጥተዋል፡፡
2. በአርባ ምንጭ ከተማ ሚያዚያ 28 ቀን 2ዐዐ4 ዓም በተካሄደው ሕዝበዊ ስብሰባወቅት ‹‹ የደቡብ ህብረትና የኢሶዴፓ አባላት በስብሰባው ለመካፈለ እንዳይችሉ ተደርጓል፡፡ በተለይም አቶ ጴጥሮስ ተፈራ የሁለቱ ፓርቲዎች የጋራ ኮሚቴ ሰብሳቢ (ተጣርቶ ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል) ስብሰባ እንዳይገቡ ተከልክለዋል››
3. ‹‹የደቡብ ህብረት መሪ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስን አገር ለቆ ወጥቷል የፓርቲው ማህተም ወርቋል›› ተብሏል
4. ‹‹ዶ/ር መረራ ጉዲና አቶ ገብሩ አሥራት በስብሰባው ላይ ይገኛሉ በማለት ዋሽተዋል፡፡››
5. ‹‹ከኢህአዴግ ባልተሻለ መንገድ በስብሰባው የማይገኙ ሰዎችን ይገኛሉ በማለት ዋሽተዋል፡፡ ተቃዋሚዎችን ታማኒነት እንዲያጡ ተደርጓል፡፡››
6. አንድነቶች ‹‹ በአቋራጭ ሥልጣን የሚፈልጉ የነፍጠኛ አቋም ያላቸው ናቸው›› ብለው ጽፈዋል፡፡

እነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች በግልጽ የሚያሳዩት የመድረኩ ሦስት አባል ፓርቲዎች ጋር ያለው ግንኙነት በጣም ጥሩ ያለመሆኑን ነው፡፡ ፓርቲዎችንና ግለሰቦችን ነጣጥለን ማየት ይገባናል የሚል ክርክር ሊነሳ የሚችል ነው፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታና እኛም በግል ካለን ግንዛቤ ስንነሳ ፓርቲዎቻቸውና ሰዎቹ የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ከአረናና ከኦህኮ ጋር የነበረውና እየተፈጠረ ያለው መቀራረብ ተስፋ ሰጭና ጥሩ ደረጃ ላይ ያለነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የመድረኩ አባል ፓርቲዎች አምስት በመሆናቸው ኦህኮ የሚባለው በኦፌኮ ተተክቷል፡፡

ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ መጋቢት 2ዐ ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም. ለአንድነት ፓርቲ በፃፉት ደብዳቤ ላይ አንድነት የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉን ወደ ፓርላማ መግባት በአጀንዳ አቅርቦ ጉዳዩ በተባበረ ድምጽ መወሰን ባለመቻሉ አጀንዳው ውሳኔ ሳያገኝ መቅረቱን ገልፀዋል፡፡ የመድረክ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ቃለ ጉባኤ የ21/ዐ1/2ዐዐ3 የሚለው ግን በወቅቱ የመድረክ ሊቀመንበር የነበሩት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ጉዳዩን በአጀንዳነት አላቀረቡትም፤ ለተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ መድረክ የሚሰጠው መመሪያ አለ ወይ የሚል ጥያቄ ነው ያቀረቡት፣ ጥያቄው ደግሞ አጀንዳ አይደለም፡፡ ከስድስቱ የመድረክ ፓርቲዎች አምስቱ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ ፖርላማ አይግቡ ወይም ቢገባቡም መድረክን አይወክሉም ብለው ድምጽ ቢሰጡ ውሳኔዎች ተግባራዊ የሚሆኑት በተባበረ ድምጽ ወይም በሙሉ ድምጽ ስለሆነ፣ አንድነት ፓርቲ ብቻ ከተቃወመው ውሳኔው ውድቅ ሆኖ ፖርላማ የመግባት መድረክንም የመወከል መብቱ ስለሚጠበቅ በማንኛውም መመዘኛ አንድነት የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ ፖርላማ ይግቡ፣ አይግቡን መድረክን ይወክሉ፣ አይወክሉን የሚል አጀንዳ አላቀረበም፡፡ በወቅቱ አንድነት በመድረክ የተወከለው የፖለቲካም ይሁን የእውቀት ጥንካሬ ባለቸው በኢ/ር ግዛቸው ሽፈራውና በአቶ ስዬ አብርሃ እንደነበር ማስታወሱ የሚጠቅም ነው፡፡

በ21/ዐ1/2ዐዐ3 ቃለ ጉባኤ ላይ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉን በሚመለከት የተነሱት መድረክን አይወክልና ፓርላማ አይግባ ክርክሮች በ28/ዐ1/2ዐ03 ውድቅ ሆኗል፡፡ በ3/2/2ዐዐ3 ዓም ቃለ ጉባኤም እንደሚያሳየው ጉዳዩን አስመልክቶ ሠፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ‹‹ … በጉዳይ ላይ ሁለት የተለያዩ አቋሞች በመንፀባረቃቸው ባለው ሕገ-ደንብ መሠረት ጉዳዮን በተባበረ ድምጽ መወሰን ስላልተቻለ የቀረበው አጀንዳ ቀሪ ሆኗል›› ይለል፡፡ ይህ ማለት የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ ፖርላማ አይግባ፣ መድረክንም አይወክል የሚለው አቋም ውድቅ ሆኗል ማለት ነው፡፡

ከመድረክ ጋር በመሆን አንድነት በርካታ ሥራዎችንና እንቅስቃሴዎች ማድረጉ የሚታወቅ ነው፡፡ ሆኖም ግምገማው የሚያተኩረው በአሉ ችግሮች ላይ መሆኑን እዚህ ላይ ማስገንዘብ ይጠቅማል፡፡

4. መድረክ በሕብረተሰብ ውስጥ ያለው ተቀባይነትና የአፈጻጸም አቅም ግምገማ

ማንኛውም ፓርቲ የያዘውን እቅድና ስትራቴጂ ከግብ ለማድረስ ጠንካራ የማስፈጸም አቅም መገንባት እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡ የማስፈጸም አቅም በቀጥታ ከአደረጃጀት እዲሁም በሕብረተሰብ ውስጥ ባለ ተቀባይነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ኮሚቴው በዚህ የጹሁፍ ክፍል ውስጥ መድረክ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ተቀባይነት ደረጃና የአፈጻጸም አቅሙን ለመፈተሽ ተሞክሯል፡፡

ሀ. መድረክ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለው ተቀባይነት

መድረክ ሰፊ ውይይትና ምክክር አድርጎና ጊዜ ወስዶ ከተመሠረተ በኃላ፣ በምርጫ 2002 የፈጠርው መነቃቃትና ተስፋ ከፍተኛ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በተለይም በምርጫ 2002 ኢህአዴግ ካዘጋጀው ወጥመድ ራሱን በመጠበቅ፣ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ላለመግበት የወሰደው በሳል የፖለቲካ አመራር ከሕብረተሰቡ ከፍተኛ ድጋፍ እንዲያገኝ ረድቶቷል፡፡ ይህ በሕብረተሰቡ ውስጥ መድረክ ከኢህአዴግ አንጻር የፈጠረው ምስል በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በተጨማሪም መድረክ በምሁሩ አካባቢ አዲስ ተስፋ ያጫረ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡

እነዚህ እውነታዊ ሁኔታዎች ተደማምረው መድረክ በፍጥነት በኢትጵያ ፖለቲካ ተጽኖ ፈጣሪ ለመሆን ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም ነበር ማለት ይቻላል፡፡መድረኩ ከተቋቋመም በኋላ ለህልውናው አስጊ የነበሩትን መሰናክሎች አልፎ (ለምሳሌ የእጩ አቀራረብ ጉዳይ ላይ) ዓይነ-ግቡ ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡ በምርጫ 2002 መድረክ ምንም እንኳን የኢህአዴግን አጠቃላይ አፈናና ዝርፊያ የሚቋቋምበትን ኃይል በወቅቱ ያልፈጠረ ቢሆነም፣ በተወዳደረባቸው የምርጫ ክልሎች ያገኘው ድጋፍ ሕብረተሰብ ውስጥ የፈጠረው ተጽኖ ነጸብራቅ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ ከአጠቃላይ መራጭ ሕዝብ መድረክ 38 በመቶ ድምጽ ለማግኘት ችሎ ነበር፡፡

ከምርጫ 2002 በፊት መድረክ የጀመረውን ሰጥቶ የመቀበል ጥረት በመግፋት የላቀ ትብብር ብሎም ውህደት ለመፈጸም በቁርጠኝነት ሊቀጥል ሲገባው፣ ባለበት መርገጥ መለያው ሆነ፡፡ ይባስ ብሎም ከመጋረጃ በስተጀርባ የነበረው የመድረክ አባል ፓርቲዎች እርስ በእርስ የመወነጃጀል አባዜ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ አደባባይ መውጣት ጀምሯል፡፡ የመድረክ አባል ፓርቲዎች ከሚያቀራርባቸው ጉዳዮች ይልቅ፣ የሚያራርቃቸው ጉዳዮች የበዛ አስመስሎታል፡፡ ይህንና መሠል ጉዳዮች ተጨማምረውበት መድረክ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለው ተሰሚነት በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ይገኛል፡፡ በዚህም ከቀጠለ መድረክ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትርጉም ያለው ኃይል ሆኖ መውጣት ይቅርና ህልውናውን አስጠብቆ መቀጠል ፈታኝ ይሆንበታል ብለን እናምናለን፡፡

እነዚህ ሁሉ ችግሮች የተፈጠሩት ፡-
ሀ) አንድነት ፓርቲ ለመድረክ ይህ በመገናኛ ብዙሃን የሚካሄደው አሉታዊ ፕሮፓጋንዳ እንዲቆም ደብዳቤ ጽፎና አጀንዳም አስይዞ ጭምር ነው ፡፡
ለ) የግንባሩ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 22 ተ.ቁ 11 አባል ፓርቲዎች ግዴታ ሥር ‹‹በመድረክ ፕሮግራም መሠረት የመድረኩን የጋራ አቋም ማራመድና ከአፍራሽና ተቃራኒ ከሆኑ እንቅስቃሴዎች መቆጠብ›› የሚለው ተጥሶ ነው፡፡ 14

ለ. የመድረክ የማስፈጸም አቅም ግምገማ

መድረክ በቅንጅት ደረጃም ሆነ በግባርነት ደረጃ ወጥ የሆነና ግልጽ ግብን አስቀምጦ ተጠያቂነት ባለው መንገድ ሲሰራ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ መድረክ ካወቃቀሩ ጀምሮ በየወቅቱ ክትትልና ግምገማ የሚያደርግና ያሉትን ክፍተቶች በሰዓቱ እዲሞሉ የሚያደርግአደረጃጀትና አሰራር መፍጠር አልቻለም፡፡በመድረክ ውስጥ አለፊነት በዙር ለአባል ድርጅቶች እንደድርሻ የሚሰጥ እንጂ፣ በአቅምና በአፈጻጸም ብቃት ብቻ እንዲሆን ማድረግ አልተቻለም፡፡

መድረክ ባሳለፈው አራት ዓመታት ውስጥ የጋር የእንቅስቃሴ እቅድ አለው ብሎ ለመናገር አዳጋች ነው፡፡ በተግባር ኮሚቴዎች ባልተቀናጀ ሁኔታ ዕቅድ የሚመስል የስራ እቅስቀቃሴ እዚህም እዛም ቢዘጋጀም፣ መሬት ወርዶ ሲተገበሩ አልታየም፡፡ የመድረክን አቅም በተለያዩ መንገዶች ለማየት ተሞክራል፡፡ ከዚህ አንጻር ኮሚቴው የአፈጻጸም አቅምን ከሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች አንጻር ለመፈተሸ ሞክራል፡፡ እነዚህም ከሰው ኃይል፣ ከፋይናንስ፣ ከቁሳቁስና ከቢሮ አቅም አንጻር በማተኮር ለመገምገም ጥረት የተደረገ ሲሆን በሦስቱም ዋና ዋና የመገምገሚያ ነጥቦች ግንባሩ አንድ እርምጃ ወደ ፊት መግፋት እንዳልቻለ መገንዘብ ተችሏል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት መድረክ ከሕዝብ ግንኙነት ተግባር ኮሚቴ አንጻር ተጽኖ ለመፍጠር የሚያስችል ስራ መከወን ሳይችል ቀርቷል፡፡ ከአደረጃጀት አንጻርም ለአለፉት አራት ዓመታት እዚህ ግባ ሊባል የሚችል ስራ መስራት አልቻለም፡፡ የመድረክ የድርጅት የተግባር ኮሚቴ ባለፉት አራት ዓመታት በአባል ፓርቲዎች መካከለ የተቀናጀና የተባበር ስራ እንዲሰራ ከማደረግ አንጻር ምንም ሚና አልነበረውም፡፡ በመድረክ ህገ-ደንብ ውስጥ ለኮሚቴ የተሠጠውን አላፊነት የትኛውንም ወደ መሬት አውርዶ አስፈጽሞዋል ማለት አይቻልም፤ ስለሆነም መድረክ ከአደረጃጀት አንጻር ተቋማዊ አሰራር መፍጠር ባለመቻሉ ግንባሩ ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው ማድረግ ሳይቻል ቀርቷል፡፡

ከፋይናንስ አሰባሰብ አንጻር በቅርቡ ወደ ሰሜን አሜሪካ በተጓዘው የልዑካን ብድን አማካኝነት ከተሰበሰበ የተወሰነ የፋይናንስ ገቢ በስተቀር፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ እዚህ ግባ የሚባል ፋይናንስ አሰባስቦ አያውቅም፡፡ ከዚህ ባሻገር የራሱ ቢሮ የሌለውና በአባል ፓርቲዎች ወርሃዊ መዋጮ በጥገኝነት በሌሎች ፓርቲዎች ውስጥ እየተጠቀመ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ መድረክ በሕዝብ ግንኙነት ስራ ሻል ያሉ ስራዎች ቢሞከርም (ለምሳሌ የመድረክን ድረ-ገጽ ከመክፈት አንጻር)፣ ከውጤት አንጻር ክፍተቶች እዳሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡

5. የአንድነት አመራር ሚና

የአንድነት ፓርቲ አመራር በአለፉት አራት ዓመታት በመድረክ ውስጥ በአመራርነት ሲንቀሰቀሱ አንደነበር ይታወቃል፡፡ የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት፣ ስራ አስፈጻሚ እና በመድረክ ስራ አሰፈጻሚ ውስጥ የአንድነት ወኪሎች በቅጡ መፈተሸ አስፈለጊ ነው፡፡ ከዚህ በታች የእያንዳንዱ አካል እንቅስቃሴ ለማስቀመጥ ተሞክሯል፡፡

ብሔራዊ ምክር ቤት ጠንካራ ጎን፤
* መድረክን በመፍጠር ሂደት ውስጥ ያሳየው አመራርና መድረክ እውን እንዲሆን የወሰደው አመራር እንደ በጎ ጎን ሊታይለት ይገባል፡፡

ብሔራዊ ምክር ቤት ደካማ ጎን፤
* ምክር ቤቱ በአጠቃለይ በመድረክ ጉዳይ ላይ የአመራርነት ሚናው መወጣት አልቻለም ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ከነዚህ ድክመቶች ውስጥ ጥቂቶቹ እንሚከተለው ተቀምጧል፡፡የመድረክን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚከታተለው የአንድነትን ስራ አሰፈጻሚ፣ ምክር ቤቱ ተገቢውን ክትትልና እርምት ሊወስድ እዲችል አላደረገም፡፡ በእርግጥ መድረክን በጥልቀት የመፈተሽ ፍላጎት በተወሰነ ደረጃ የነበረው ቢሆንም ገፍቶ ሊሄድበት አልቻለም፡፡ በመሆኑም መድረክ ውስጥ ለተስተዋሉ ችግሮች ምክር ቤቱ ከአላፊነት ሊያመልጥ አይችልም፡፡

የአንድነት ስራ አስፈጻሚ ከመድረክ አንጻር ያሳዩት ጠንካራ ጎኖች፤
* የአንድት ስራ አስፈጻሚ በሁለት ጫፍ (ጠርዝ) ላይ ቆመው ሊገናኙ የማይችሉ የሚመስሉ የብሔር ተኮርና የሕብረ ብሔረ የፖለቲካ ድርጅቶችን ቀደም ሲል ባልተለመደ ሁኔታ በማገናኘት ፌዴራላዊ መድረክ ለዴሞራሲና ለፍትሕ (መድረክ) የሚባለውን የፖለቲካ መድረክ በማቋቋም አማራጭ የፖለቲካ አቋም በመያዝ ሕዝቡ በ2ዐዐ2 አገራዊ ምርጫ አማራጭ እንዲያገኝ የአንድነት ተወካይ አመራሮች ያደረጉት አወንታዊ አስተዋጽኦ ጉልህ ቦታ ሊሰጠው ይገባል፡፡

* የአንድነት ተወካይ አመራሮች በመድረክ አባል ጅርጅቶች እንዲሁም በአንድነት ውሰጥ ከመድረክ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የጋጠማቸውን ተግዳሮቶች በትዕግሥት ተቋቁመው የመድረክ ሕልውና እንዲቀጥል ማድረጋቸው ሌላው በአወንታዊነት ሊታይ የሚችል ጉዳይ ነው፡፡

የአንድነት ስራ አስፈጻሚ ከመድረክ አንጻር ያሳዩት ደካማ ጎኖች
* መድረክ ሊያሳካቸው የወጠናቸው ስትራቴጂካዊ ግቦች ትኩረት በተገቢው ሁኔታ ባለማግኘታቸው እስካሁን ሊሳኩ አልቻሉም፡፡ የመድረኩ ከቅንጅት ወደ ግንባር ሽግግር የዓይነትና የይዘት ለውጥ ያላሳየ ከመሆኑም ለቀጣዩ ምእራፍ (ውህደት) ሁኔታዎች ያመቻቸ ሆኖ የሚታይበት ሁኔታ የለም፡፡ የመድረክ አባል ድርጅቶች በአብዛኛው ወደ ስትራቴጂካዊ ግብ መዳረሻ ከመሄድ ይልቅ የኋልዮሽ ጉዞ ወይም ባለህበት ሂድ ላይ ቆመዋል፡፡

* የአንድነት አመራር መድረኩ ወደ ታሰበው የላቀ ምእራፍ እንዲሸጋገር ተነሳሽነት በመውሰድ የሽግግር ስትራቴጂ አጀንዳ በማስያዝ መድረኩ ትኩረት ስጥቶ እንዲወያይበት ጠንካራ አቋም በመያዝ የተንቀሳቀስበት ሁኔታ አልታየም፡፡

* የመድረክ አፈፃፀም (ሁኔታ) ተገምግሞ እንዲቀርብ ከአንድነት ምክር ቤት አባላት ጥያቄ ሲቀርብ የአነድነት ተወካዮች የመከላከል Protective አቋም በመያዝ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ሲቸገሩ ታይተዋል፡፡ በቅርቡ እንኳን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው መድረክ ያለበት ተጨባጭ እውነታ ተገምግሞ ሪፖርት እንዲያቀረብ መመሪያ ተላልፎ በምንም መልኩ ተቀባይነት በሌለው ምክንያት ሪፖርቱ ሊቀርብ አልቻለም፡፡

* በመድረክና አባል ድረጅቶች ላይ ተጽኖ የመፍጠር አቅምን አልገነባም፤ በመሆኑም በመድረክ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ የነበረው ሚና ዝቅተኛ ነው፡፡

* በመድረክ ጉዳይ የአንድነት አባለት በተለያዩ ሁኔታዎች የሚሳተፉበትን መድረክ ማዘጋጀት አልቻለም ወይም አልፈለገም፡፡

* በአሁኑ ወቅት የአገሪቷ ሁኔታ እጅግ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ በወደቀችበት ሁኔታ መድረኩ ጉዳዮን በጥልቀት ገምግሞ ራሱን በማጠናከር አማራጭ የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ ተገቢውን እንቅስቃሴ በማድረግ ሕዝቡን በዙሪያው የማሰባሰብ ተግባር እንዲያከናውን የላቀ ጥረት አለመደረጉ እንደ ክፍተት የሚታይ ነው፡፡

* ለወደፊቱም ቢሆን የአንድነት ተወካዮች ከዚህ ሁኔታ ተላቀው የProactive በመሆኑ መድረኩ ስትራቴጂክ ግቦቹን እንዲያሳካ የአድቮኬሲ ሥራና ሌሎች የማሳመኛ ስልቶችን በመጠቀም፡፡ መድረክ ከቆመበት እንዲነሳ (Take-off) እንዲያደርግ አፋጣኝና የበሰለ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡

6. የመፍቴ አሳቦች

በዚህ የመድረክ አጠቃላይ ግምገማ ውስጥ የፕሮግራም፣ ስትራቴጂክ ግቦች፣ የደንብ፣ የእርስ በእርስ ግንኙነት፣ የአፈጻጸም አቅም፣ በሕብረተሰብ ውስጥ ያለው ተቀባይነት እና የአንድነት አመራር ሚና ተዳሷል፡፡ ከነዚህ መሠረታ ከሆኑ ነጥቦች ተነስቶም ኮሚቴው ድምዳሜዎችን በእያንዳንዱ ክፍል ውስጥ ለማስቀመጥ ሞክሯል፡፡ ከነዚህ መሠረታዊ ድምዳሜዎች በመነሳት ኮሚቴው የአጭር ጊዜና የረጅም ግዜ የመፍቴ ሃሰቦችን እንደሚከተለው አስቀምጧል፡፡

የአጭር ጊዜ የመፍቴ ሃሳቦች (ከመድረክ አንጻር)

ሀ. መድረክ ከምርጫ 2002 በኋላ እያደረገ ያለውን የቁልቁለት ጉዞ አቁሞ፣ ሰጥቶ በመቀበል መንፈስ የፕሮግራምና የስትራቴጂ አንድነት ለመፍጠር ተግቶ መስራት ይጠበቅበታል ብለን እናምናለን፡፡ ስራ አሰፈጻሚው ይህን ጉዳይ ከግብ ለማድረስ መስራት ይጠበቅበታል ብለን እምናለን፤ የደረሰበትንም መደምደሚያ ለብሔራዊ ምክር ቤት በመጪው ሶስት ወራት ማቅረብ ይገባዋል፡፡ የፕሮግራምና ስትራቴጂ አንድነት መፍጠር ካልቻለ፣ ኮሚቴው መድረክ (እንደ ግንባር) የተደራጀና የተቀናጀ ትግል በማድረግ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ስብስብ ይሆናል የሚል እምነት የለውም፡፡

ለ. የመድረክ ህገ-ደንብ በአንድ ግንባር ውስጥ ለተካተቱ ፓርቲዎች ሳይሆን በጥምረት ደረጃ ላይ ላለ ስብስብ ሊያገለግል የሚችል ነው የሚል እምነት አለን፡፡ ስለሆነም የመድረክ ደንብ የእርስ በእርስ ጥርጣሬንና መጠባበቅን በመቅረፍ ጠንካረ አባል ድርጅቶችን እና ጠንካራ ግንባርን ሊፈጠር የሚችልበት የመተዳደሪያ ደንብ ሊኖረው ይገባል የሚል እምነት አለን፡፡ በተጨማሪም መሠረታዊ የሚባሉ የአደረጃጀት ችግሮች በመፍታት የመድረክ ህገ-ደንብ አባለት ከታች ጅምሮ ሊያሳትፍ በሚችል ሁኔታ ሊዋቀር ይገባል፡፡ በተለይም የመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ እያንዳንዱ አባል ፓርቲዎች መሠረታዊ ድርጅት የተወከሉ ከ200 እስከ 300 የሚደርሱ አባልት የሚሳተፉበት ሊሆን ይገባዋል፡፡ የመድረኩ ሊቀመንበር ም/ሊቀመናብርትና ፀሐፊ በዚህው ሰፊው ስብስብ ሊመረጥ ይገባዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የመድረክ ስራ አስፈጻሚን ስራ ሊገመግም የሚይችል የራሱ የሆነ ብሔራዊ ምክር ቤት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህ ዴሞክረሲያዊ አሰራርን፣ የአባላትን ተሳትፎና የተጠያቂነትን አሰራርን ያሰፍናል፤ ይህም ለተሻለ አፈጻጸም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን ስራ የአንድነት ስራ አሰፈጻሚ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ አንዲያከናውንና ለብሔራዊ ምክር ቤቱ የደረሰበትን ውጤት ሪፖርት ቢያደርግ የሚል አስተያየት አለን፡፡

ሐ. ኮሚቴው በአንዳንድ የመድረክ አባል ፓርቲዎች አመራሮች አከባቢ በአንድት ፓርቲ ላይ ግልጽ የሆነ ጥርጣሬዎች፣ ከዚህም ሲያልፍ ጥልቻና ሲያንጸባርቁ ይሰተዋላል፡፡ ለምሳሌ አንድነትን የአማራው ፓርቲና የሌሎችን መብት የማያከብር (ወይም የጠቅላይነት አስተሳሰብ) ያለው አስመስሎ ያለምንም አፍረት በአደባባይ ይህን አቋም የሚያራምዱ እንዳሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ እነዚህ ሰዎች የአንድነት ፓርቲ የአባልነት መስፈርት ኢትዮጵያዊ ዜግነት ብቻ እንደሆነ ጠፍቷቸው ሳይሆን፣ ሆን ተብሎ በሕብረተሰብ ውስጥ ብዥታንና ጥርጣሬን ለመፍጠር ታቅዶ የሚደረግ ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ አንድነት እነዚህን ችግሮች በሰከነ ሁኔታ ለማስተናገድ መሞከሩ የሚያስመሰግነው ቢሆንም፣ ይህን አስተሳሰብ በመድረክ መአቀፍ ውስጥ አጀንዳ አስይዞ አፍረጥርጦ መወያየት ያስፈልጋል፡፡ አንድነት አንዱ የመድረክ አባል ድርጅት ቢሆንም፣ በግልጽ በፕሮግራሙ እንዳስቀመጠው በኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ላይ ብቻ የተደራጀ ኃይል እንደሆነ ግልጽ አድርጓል፡፡ አንድነት ሌሎች የመድረክ አባል ድርጅቶች ብሔር ተኮር አደረጃጀት ታቅፈው መደራጀታቸውን የተሻለ ነው ብሎም ባያምንም ዴሞክራሲያዊ መብት ነው ብሎ ተቀብላል፡፡ ዘረኝነት እስከሌለና ዴሞክራቶች እስከ ሆኑ ድረስ በተመሳሳይ ሁኔታ የመድረክ አባል ድርጅቶች የአንድነት አባላትና ደጋፊች የተሰባሰቡበትን በኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ዙሪያ መደራጀት ዴሞክራሲያዊ መብት እንደሆነ ግልጽ አቋም ሊይዙ ይገባል፡፡ ይህን ጉዳይ ጨምሮ በመድረክ አባል ድርጅቶች መሃከል ያለውን አለመተማመንና መጠራጠር ለመቅረፍ በመድረክ በኩል ሰፋ ያለ (ቢያንስ የሁሉንም ፓርቲዎች የብሔራዊ ምክር ቤት ባሳተፈ ሁኔታ) ነጻ የውይይት መድረክ መፍጠርና መግባባት ላይ መድረስ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ለዚህ ተፈጻሚነት ስራ አስፈጻሚው አላፊነት ወስዶ መስራት ይገባዋል፤ አፈጻጸሙን ብሔራዊ ምክር ቤቱ ቢከታተል የተሻለ ውጤት ሊኖረው ይችላል ብሎ ይታመናል፡፡

መ. መድረክ ከአፈጻጸም አንጻር (ከፋይናንስ፣ ከሰው ኃይል፣ ከቢሮና ቁሳ ቁስ አንጻር) ሊወራለት የሚችል ውጤት አለው ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ የዚህ ችግር በከፊል የሚመነጨው ተጠያቂነት ያለው አሰራር ማስፈን ባለመቻሉ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የመድረክ አወቃቀር ብሔራዊ ምክር ቤት ሊኖረው ይገባል፤ ከታች ጀምሮ የተዋቀር ጠቅላላ ጉባኤ ሊኖረው ይገባል፡፡

ሠ. የአንድነት አመራር (ስራ አስፈጻሚና ብሔራዊ ምክር ቤት)ሚና ከመድረክ አንጻር የሚታዩትን ድክመቶች በአፋጣኝ ማረም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስራ አስፈጻሚው በየሶስት ወሩ የሚያቀርበው ሪፖርት የመድረክን ጉዳይ በስፋት መዳደስ ይጠበቅበታል፡፡ በመድረክ ጉዳይ የስራ አሰፈጻሚ ጉዳይ ብቻ ተደርጎ የሚታየውን አስተሳሰብ አሶግዶ፣ መላው አባለት የሚሚሳተፉበት ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡

ስለሆነም መድረክ ሕይወት እንዲዘራ አንድነት አቅሙ የፈቀደውን እርብርብ በማድረግ፣ ከላይ የተዘረዘሩ ችግሮች ለመፍታት ያስፈልጋል የሚል እምነት አለን፡፡

የረጅም ጊዜ የመፍቴ ሃሳቦች (አብሮ ከመስራት አንጻር)

በአሁኑ ወቅትበአንድ በኩል የተቃዋሚው ጎራ ውስጡ ባሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተተብትቦና ከዚህ ችግር ለመውጣት ግልጽ እይታና መስመር ነጥሮ መውጣት ያልቻለበት ሲሆን፣ በሌላ በኩል አገዛዙ የሚያደርሰው ሁለገብ ተጽኖ ተጨምሮ ፓርቲዎች በሕብረተሰብ ውስጥ ያላቸው የተቀባይነት እና የእምነት ማጣት ጉዳይ በስፋት ይስተዋላል፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ፓርቲዎች እየተንቀሳቀሱበት የሚገኙበት ኢኮኖሚካዊ፣ ማህበራዊና ፖሊተካዊ ከባቢ ሁኔታ እጅግ ፈታኝ የሆነበት ወቅት ነው፡፡ እነዚህ ሁለንተናዊ ችግሮች የአበላትንና የደጋፊዎችን ቁጥር በከፍተኛ ሀኔታ መቀነስ እንዳስከተለ በግልጽ የምገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡በዚህ ትርምስና ቀውስ ውስጥ ያለውን የተቃውሞ ጎራ መልሶ እንዲያንሰራራ ብሎም የመድበለ-ዴሞክረሲ ሥርዓት በሀገራቸን ጠንካራ መሠረት እንዲይዝ ከሌሎች የተቋዋሚ ኃይሎች ጋር መጠላለፍና መጠፋፋት ፖለቲካ የትም እንደማያደርስ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ወቅቱ የሚፈልገው ቢቻል ደጋፊ የሚበዛበት፣ ካልተቻለ የጠላትነት መንፈስ እንዳይፈጠር መስራት አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይም በብሔር ላይ ከተደራጁ ወገኖች ጋር የባላንጣነት ስሜት እንዲወገድና አንድነት የሁሉም ኢትዮጵያውን ቤት ይበልጥ እንዲሆን በአስተሳሰብና በአሰራር አንድነት ብዙ ሊጓዝ ይገባዋል፡፡ ስለሆነ አብሮ ከመስራት ውጭ በሀገራችን ውስጥ ለውጥ ሊመጣበት የሚችል እድል ዝግ ከሆነ፣ እንዴት አብሮ መስራት ይቻላል የሚባው ጉዳይ በስፋት ሊታይ ይገባዋል፡፡ ከዚህ አንጻር አንዳንድ የመፍቴ ሃሳቦች ቀርቧል፡፡

ሀ. ኮሚቴው አሁን በምንገኝበት የትግል ምህራፍ ከሌሎች የዴሞክራሲ ኃይሎች ጋር በጋር ከመታገል ውጭ የተናጥል ትግል ለድል ሊያበቃ እንደማይችል ግልጽ ግንዛቤ መውስድ እንደሚገባ ያምናል፡፡ ይሁን እንጂ አብሮ በመታገል ስም፣ መሠረታዊ በሆነ ተቃርኖዎች የታጨቀን ስብስብ ለድል ይበቃል ብሎ ማሰብ ከፍተኛ ስህተት እንደሆነ ተገንዝበናል፡፡ ለወደ ፊቱም ፓርቲያችን ማንኛውን ዓይነት ትብብር ከመመስረቱ በፊት ሰፊ ትንተናና ክርክር፣ ትብብሩ ሊያሳካቸው የሚችሉትን ግልጽ ግቦች እና የማስፈጸሚያ ስትራቴጂዎች ሲነደፉ ብቻ የትብብሩ አካል ሊሆን ይገባዋል ብለን እናምናለን፡፡ ስትረቴጂካዊ ጥምረትንና አይዶሌጂካል አንድነትን ለያይቶ መረዳት ይገባል የሚል እምነትአለን፤ ለሁለቱም የመተባበሩ ጥልቀት በግልጽ መለየት አለበት፡፡ የእነዚህ ግቦች ውጤታማነት በስራ አሰፈጻሚና በምክር ቤት ደረጃ ቁጥጥርና ግምገማ ሊደረግባቸወ ይገባል የሚል እምነት አለን፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ ትብሮችና ሕብረቶች መርህ ላይ የተመሠረቱ ማድረግ እና ከአጭር ጊዜ ጥቅሞች ይልቅ ረጅም ጊዜ ሊወስዱ የሚችሉትን የፕሮግራምና ፖሊሲ መቀራረብ ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ለ. አንድነት የሚፈጥራቸው ትብብሮችና ጥምረቶች ዋና ግባቸው ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መመስረት ላይ ያተኮረ ሊሆን ይገባል፡፡በዚህ ሂደትም ጠንካራ መደብለ ፓርቲ ስርዓት የሚፈጠርበት ሁኔታ ሊያመቻች ይገባል፡፡

ሐ. ይህን ለማሳካት የአንድነትን ተጽኖ ፈጣሪነት ማሳደግ እጅግ ወሳኝ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለመፍጠር የድርጅታችንን ሁለንተናዊ አቅም (የሰው ኃይል፣ የፋይናንስና የቁሳቁስ) ማሳደግ ወሳኝ ነው የሚል እምነት አለን፡፡

መ. በኢትዮጵያ ውስጥ ትብብሮች ረጅም ርቀት እንዳይሄዱ መሰናክል ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የፓርቲዎች ህገ ደንብ ነው የሚል እምነት አለን፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የምርጫ ህግ አንድም ፕሮፖርሽና ውክልናን አይቀበልም፤ በሌላ በኩል ጥምረቶችንና ቅንጅቶችን ከምርጫ ውድድር በኃላ ሳይሆን በፊት መፍቀዱ ድምጽን ላለመከፋፈል ቅንጅቶችና ሕብረቶች ከምርጫ በፊት እንዲመሠረቱ የግድ አድርጎታል፡፡ አንድነት ፕሮፖርሽና ውክልናን ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም የሚለውን ፈትሾ በፕሮግራም ደረጃ ሊታገልለት ይገባል፡፡

የግርጌ ማስታወሻ፡-
[1] ለዚህም ነው በአንዳንድ ፓርቲዎች አንድነት በአዲስ አበባና በአማራ ክልል ብቻ ታጥሮ እንዲኖር ፍላጎቱ ያለው፡፡

************************

ውድ አንባቢዎቻችን፡-
ከዚህ በላይ ያነበባችሁት ጽሑፍ ሙሉ በሙሉ – የአርትዖት ሥራዎችን (bold, underline, etc) ጨምሮ – ከፓርቲው መግለጫ የተገለበጠ መሆኑን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

በዚሁ አጋጣሚም በኢትዮጲያ የሚገኙ በሕግ የተመዘገቡ ፓርቲዎች መግለጫቸውን ቢልኩልን ያለአንዳች ቅድመ-ሁኔታ ለማስተናገድ ነባር ፈቃደኝነታችንን እያስታወስን፤ ይህም ለፓርቲዎቹ የምንውለው ‹‹ውለታ›› ሳይሆን የአንባቢዎቻችንን ፍላጎት ለማርካት እና የፓርቲዎቹን በቂ የሚዲያ ሽፋን የማግኘት ሕገ-መንግስታዊ መብት ከማስከበር አንጻር መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

9.14540.489673
Daniel Berhane

Daniel Berhane

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago