የርእዮት አለም ግልፅነት መጓደል እና አህአዴግ

(Amanuel Alemayehu)

የአንድ አገር የተረጋጋ እና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ከተፈለገ ስርዓት ያለው አገር መሆን አለበት፡፡ ስርዓት (state) ደግሞ ሊመሰረት (ሊገነባ) የሚችለው፤ የሚገነባው የስርዓት ዓይነት አስቀድሞ አንጥሮ ያስቀመጠ ርእዮት ዓለም (ideology) መኖር አለበት፡፤

በታሪካዊ መሰረት ወደ ኋላ ስመለከት በቅርቡ በእድገት እንደ ተምሳሌት ተደርገው የሚገለፁት አገራት ስርዓታቸው የተገነባው ወይንም እየተገነባ ያለው በሚከተሉት ርእዮት ዓለም (ideology) መሰረት ነው፡፡

ለምሳሌ የቻይናውያ ስርዓት እየተገነባ ያለው በማኦይዝም አስተሳሰብ ቅኝት አዲሱ ዲሞክራሲ (the new democracy) እየተባለ በሚጠራ እሳቤ ልማት ከሁሉም ይቀድማል በሚል ርእዮት በሚታወቀው የኮሚኒስታዊ መር ርእዮት ዓለም ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የምእራቡ ዓለም እየተባለ የሚታወቀው የሀገሩ ስርዓት መነሻ ርእዮት ዓለሙ የካፒታሊዝም (capitalism) እሳቤ የተገነቡ ስርዓታት ናቸው፡፡

ስለዚህ አንድን ስርዓት ለመገንባት ስርዓቱ የሚገነባበትን አገር ህዝብ ባህል፣ ፖለቲካዊ መሰረት፣ የገቢ መጠን (economic status) ፣ ህያው ፀጋዎቹን (existing resources) መሰረት ያደረገ እና ሊገነባ የታሰበው ስርዓት (state) የሚያመለክት አንዲሁም የሚገነባው መንግስት ባህሪ ያነጠረ ርእዮት ዓለም መቀመር ወይም መዋስ የማይታለፍ አስፈላጊ ተግባር ነው፡፡

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው የተረጋጋ ስርዓት ያለው አገር፡-

1/ ስርዓቱ የሚገነባበት ሃሳብ የሚያነመጭ ርእዮት ዓለም (ideology) አለው

2/ የተመላከት ስርዓት (envisioned system) አለው

3/ ርእዮት አለሙን መሰረት አድርጎ ስርዓቱን የሚገነባ ወቅታዊ ፖሊሲዎች ያሉት መንግስት አለው፡፡

ከላይ በገለፅኩት አጭር መግቢያ መሰረት ወደ አገራችን መለስ ብለን ኢትዮጲያ ሊገነባ የሚፈለገው ስርዓት የከበርቴው ስርዓት (capitalist state) እንደሆነ ከገዥው ፓርቲ በተደጋጋሚ የሰማነው በተጨማሪም ሁሉም ተቀናቃኝ (ተቃዋሚ) የፖለቲካ ፓርቲዎች እምነት የዳበረ የከበርቴው ስርዓት (capitalist state) መፍጠር እንደሆነ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደዚህ ሊገነባ የሚፈለገው የከብረቴው ስርዓት መዳረሻ መሆኑን ተማምነን ነገር ግን መንገዱን በተመለከተ ግን በኢትዮጲያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ እጅግ አከራካሪ እና አወያይ ርእስ ነው፡፡

በርግጥ የሚገነባው ስርዓት የከበርቴው (capitalist system/state) ነው ብለው ሁሉም ፓርቲዎች ሊባል በሚቻል ደረጃ ስለሚሰማሙ የሚፈጠረው ስርዓት እሳቤ ላይ ወይንም ርእዮት ዓለም ላይ ልዮነት ሊፈጠር አይችልም ከተፈጠረም በመሰረቱ የከበርቴው ስርዓት ርእዮት ዓለም ሆኖ የፉክክሩ መለያዎች በመሃከሉ ባለው ንኡሳን ርእዮት ዓለም ልዮነቶች ይሆናል፡፡

ለምሳሌ በዳበረው የከበርቴው ስርዓት ርእዮት ዓለም ውስጥ፡-

1/ ወግአጥባቂ ከበርቴዊነት (conservative capitalism)

2/ የነፃ ገበያ አክራሪ ከበርቴዊነት (neo-liberal capitalism)

3/ ማህበረሰባዊ ከበርቴያዊነት (social capitalism) ወዘተ እነዚህ ከላይ የገለፅኳቸው ብዙ ክፍልፋይ ሊኖራቸው ይችላሉ፡፡

ወግ አጥባቂ ካፒታሊስቶች ፡- የቀኝ ጫፍ አክራሪዎች፣ የመሃከለኛ ቀኝ አራማጆች ወይንም የቀኝ ካፒታሊዝም አራማጅ እየተባሉ በንኡስ ንኡስ እሳቤዎች ሊከፋፈሉ ይችላሉ፡፡

ስለዚህ የሚገነባው ስርዓት የከበርቴው ስርዓት ከሆነ ስርዓቱ ተገንበቶ ሲያልቅ ብዙ ዓይነት የከበርቴው እሳቤዎችን ቢያካትቱም በስርአት ደረጃ ግን በአንድ ስርዓት የሚካተት ነው፡፡

በዚህ በከበርቴው ስርዓት የስርዓት ምርቱ ባለቤቶች በአመዛኙ በሶስት ትላልቅ መደቦች የተከፈሉ ሲሆን እነዚህ፡-

1/ ከበርቴው (the capitalist)

2/ ወዛደሩ (the proletariat)

3/ ባለ መካከለኛ ገቢው (the middle class) ይህ ባለ መካከለኛ ገቢው በውስጡ ብዙ ክፍልፋዮች የያዘ መደብ (class) ነው፡፡

የስርዓቱ ባለቤት የሆኑት እነዚህ ሶስት ትላልቅ መደቦች በመካከላቸው መሰረታዊ ያልሆነ የእሳቤ ልዮነቶች አሉዋቸው፡፡ የእነዚህ ልዮነቶቻቸው ምንጭም በስርዓቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖራቸው ተጠቃሚነት መሰረት ያደረጉ የጥቅም ግጭቶች እንጂ ከዚሁ በዘለለ የጠነከረ ቅራኔ ስለሌላቸው ስዓቱን የሚጠብቁት በጋራ ነው፡፡ ይህ ስርዓት ደግሞ ጥቅሞቻቸው የሚጠብቁላቸው እና የሚያስከብሩላቸው ተቋማት (institutions) መሰረት ያደረገ በመሆኑና እዚህ የጥቅም ልዮነቶች በዴሞክሲያዊ እና አሳታፊ በሆነ መንገድ ስለሚያስተናግዱ ዴሞክሲያዊ ተቋማት ናቸው፡፡ ዴሞክሲዊ መሆናቸው ደግሞ ተጠያቂነትን (accountability)፣ የህግ የበላይትን (rule of low) እዲሁም ተደራሽነትን (accessibility) መሰረት ባደረገ መንገድ የሚዋቀሩ በርካታ ተቋማት የያዙ ናቸው፡፡

1/ መንግስታዊ ተቋማት

1.1/ ህግ አውጪው (legislative body)

1.2/ ህግ አስፈፃሚው (executive body)

 1.3/ ህግ ተርጓሚ (judiciary)

2/ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆነ (public and private)

 2.1/ የመገናኛ ብዙሃን ( media)

3/ መንግስታዊ ያልሆኑ (non-governmental bodies)

3.1/ የፖለቲካ ማህበራት (political organizations)

3.2/ የሲቪል ማህበራት (civic organizations)

በመሳሰሉት ተቋማት የተደራጀ እንዲሁም ከመንግስት ጋር ግልፅ የሆነ መስተጋብር (interaction) ያለው ስርዓት ስለሆነ ስርዓት መንግስት ቅንብሩ እየተጠባበቀ እና እየተስማማ የሚሄድ ስርዓት ስለሆነ የአብዛኛው ስርዓት ይሆናል፡፡

ነገር ግን ጥያቄው እዚህ የተባለውና በአመዛኙ መላው ማህበረሰብ ሊሰማማበት የሚችል ስርዓት ለመድረስ በየት በኩል እንሂድ የሚለው ጥያቄ የወቅቱ ፈተና (order of the time) ነው፡፡

ወደ ከበርቴው ስርዓት መሄጃ መንገድ/ዶች፡-

ወደ ከበርቴው ስርዓት ለመሄድ አንዱ ቀመር ወይንም ርእዮተ አለም (በእኔ እይታ የተሸለው) የአብዮታዊ ዴሞክሲያዊ ርእዮት አለም ነው፡፡

አንድ ርእዮት አለም ሲቀመር መነሻዎቹን ግልፅ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

በኢትዮጲያ ወቅታዊ ህብረተሰብአዊ ሁኔታ የሚከተሉት ነገሮች ግምት ውስጥ ገብተው ወደሚፈለገው ስርዓት የሚወስደው ርእዮት አለም መቀመር አስፈላጊ ነው ባይ ነኝ፡፡

1/ ያልዳበረና በግብርና መሰረት ያደረገ የህብረተሰብ አብዛሃ ክፍል (peasant society) ከ 85% በላይ

2/ እጅግ ኋላ የቀረና በአለም ደረጃ ተወዳዳሪ ያልሆነ የአምራች ኢንዱስትሪ መሰረት

3/ እጅግ ዝቅተኛ የትምህርትና የጤና ስርዓት

4/ ዝቅተኛ መሰረተ ልማት

5/ ከበርቴነትን የሚያወግዝ ማህበራዊ እሳቤ

እና በመሳሰሉት ሁኔታዎች የተከበበ አገርን ወደ በለፀገ የከበርቴው ስርዓት የሚሄድበትን መንገድ በማያሻማ ሁኔታ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል፡፡

ከዚህ በመነሳት አሁን በኢትዮጲያ ውስጥ ያሉት የማህበረሰብ ክፍሎች (መደቦች)

1/ ገበሬው (peasant) ከ85% በላይ ብዛት

2/ የከተማ ነዋሪው አመዛኙ የመደብ መሰረቱ ገበሬ ሆኖ ነገር ግን ከግብርናውና ከመሬቱ ተፈናቅሎ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኝ ነው

3/ የተማሪው የህረተሰብ ክፍል

4/ ወዛደሩ፤ይህ የማህረሰብ ክፍል በተወሰኑ የግል አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተቀጥሮ የሚሰራ የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡

5/ ባለሃብት፤የአገራችንባለሃብት ከፍተኛ ባለሃብት ተብሎ ሊመደብ የሚችል ካለመሆኑም ሌላ ከላይ በጠቀስኳቸው የማህረሰብ ክፍሎች ጋር ተደብሎ የተፈጠረና ብዙ ሃይማኖታዊ፣ ማህበረሰባዊ እንዲሁም መንግስዊ ጫና ውስጥ ያለ እና የዳበረ የከበርቴ አስተሳሰብ የማይመራው የምርት ሂደት የሚመራ መደብ ነው፡፡

እነዚህ በመሰረቱ በአራት ሊጠቃለሉ የሚችሉ መደቦች ናችው

1/ የገበሬው መደብ

2/ የምሁርና የከተማ ነዋሪው

3/ የወዝአዱሩ

4/ የባለሃብቱ መደቦችሲሆኑ

እነዚህን መደቦች ታሳቢ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን ግምት ውስጥ ያስገባ ርእዮ አለም መቀመም ወይንም ከሆኔታችን ጋር አጣጥሞ መዋስ አስፈላጊ ነው፡፡

አብዮታዊ ዴሞክራሲ ምንድን ነው?

አብዮታዊ ዲሞክራሲ ርእዮት አለም እንደ ኢትዮጲያ ባሉ በእድገት ወደኃላ በቀሩ፣ መሰረተልማት ባልተስፋፋባቸው፣ የህዝባቸው ወሳኝ ክፍል አርሶ አደር (peasant) በሆነባቸው እንዲሁም ሃብት (wealth) ባልተፈጠረባቸው አገራት ዴሞክራሲን እና ልማትን ጎንለጎን መገንባት ይቻላል የሚል እሳቤ የሚያራምድ ርእዮት አለም ነው፡፡

እደሚታወቀው እስከ አሁን የበለፀገው አለም ወደ ብልፅግና የሄደበት መንግድ ፍፁም ኢ-ዴሞክራሲያዊ በተለይ ደግሞ እጅግ በልፅጓል የሚባለው የምእራቡ አለም ስልጣኔ ብናይ በሰው ልጆች ሊፈፀም ይችላል ተብሎ በማይታሰብ ጭካኔና አረመናዊነት ተጠቅሞ የተገኘ ስልጣኔ ነው፡፡ ለአብነት ያክል የተወሰኑት ብናይ በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ አውስትራልያ፣ ኒውዝላንድ እና በመሳሰሉት ነባር ህዝቦችን በጅምላ በመጨፍጨፍና መሬት ንብረታቸውን በመቀማት፣ በተጨማሪም የሰው ልጅን እንደ እንስሳ በባርነት በመግዛትና በነፃ ጉልበት በማሰራት የተገኘ የከበርቴው ስርዓት ነው፡፡ በአውሮፓም መልኩን የቀረ ቢሆንም ከባርያ ንግድና ነፃ ጉልበት ብዝበዛ ጀምሮ እስከ የቀኝ ግዛት የአፍሪካ እና የሌሎች አህጉር ህዝቦችን ጉልበትና ተፈጥሮ ሃብት በመበዝበዝ ባጠቃላይ በከፋ ኢሰብአዊ መንገድ የተገነባ የከበርቴው ስርዓት ነው፡፡

ከነዚህ ሻል ባለ መንገድ በአገር በቀል እሳቤ የተገነባው የከበርቴው ስርዓት የሚታየው በሩቅ ምስራቅ አገሮች እንደ ታይዋን፣ ኮርያ፣ ማሌዥያ፣ ጃፓን፣ኢንዶኔዥያ፣ ሲነጋፖር በመሳሰሉትም ቢሆን እጅግ ጨቋኝ የህዝቦቻቸውን ዴሞክራሲዊና ሰብአዊ መብት በመርገጥ በጉልበት የተገነባ የከበርቴው ስርዓት ሲሆን የእድገት ደረጃቸው ከፍ ካለ በኋላ ግን ዴሞክራሲን በስርዓታቸው ውስጥ በማስተዋወቅ አሁን እኩል ከበለፀጉ አገራት ጋር ሊሰለፍ የሚችል የዳበረ የከበርቴው ስዓት ባለቤት ሆነዋል፡፡

አገራችን ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ስንመነዝረው ኢትዮጲያ ዴሞክራሲ የግድ ያስፈልጋለታል ምክንያቱ የኢትዮጲያ ህዝብ በባህል በቋንቋ እንዲሁም በታሪካዊ እሳቤ እጅግ ተራራቀ ነገር ግን ወደ የጋራ መግባባት መምጣት የሚችልና የወል እሴት መፍጠር የሚችል ህዝብ ነው፡፡ በመሆኑም የወል እሴት ለመፍጠር እንዳንዴ ህዝብ በህዝብ ደረጃ እንዲሁም እያንዳንዱ ዜጋ በተናጠል የሚኖረው የእሳቤ ልዮነትና የባህል የቋንቋ መለያየት ሊያስተናግድ የሚችል ዴሞክራሲዊ ተቋማትን መገንባት የግድ ይላል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አገራችን ካለችበት የከፋ ድህነት መውጣትና እንዳንዱ ዜጋ ተጠቃሚ የሚሆነበት ልማት ማረጋገጥ እንደ አገር የማድረግ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የዲሞክራሲ መብትም ጭምር ነው፡፡ በአገራችሁ ሁኔታ አንዱን አስቀድሞ ሌላው ትቶ መሄድ አይቻልም፡፡ ልማት ያለ ዴሞክራሲ ዴሞክራሲ ያለ ልማት በኢትዮጲያ ሊታሰብ ይችላል ይሆን እንጂ ሊተገበርና አገሪቱን እንደ አገር ጠብቆ (ይዞ) ለመቆየት እንኳን የሚያስችል አይደለም፡፡

ዜጎች የግልም የጋራም ዴሞክሲያዊ መብታቸው የሚያስከብር ስርዓት መገንባት አለበት ምክንቱም የጋራ መብታቸው እንደ ህዝብ (ብሄር/ብሄረሰብ) ወይንም እንደ ቡድን በፖለቲካ እሳቤያቸው፣ በሞያቸው፣ በፆታቸው ወዘተ ማንነት የገነቡ በመሆኑ እና ይህ ማንነት መከበር በኢትዮጲያ የትግል ታሪክ የነበሩትን የብሄር ብሄረሰብ የመብት ጥያቄ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መመለስ ስላለበት የማይታለፍ ነው፡፡ በዋናነት ግን አንድ ዜጋ በሂወት የመኖር፣ በጤንነት የማደግና የማህበራዊ አገልግሎቶች የማግኘት መብቱን ያረጋገጠ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት አለበት፡፡ አንድ ዜጋ በጤናና በሂወት የመኖር መብቱ አንዲከበር የበለፀገ/ያደገ ኢኮኖሚ መኖር አለበት ስለዚህ ልማት ከዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው፡፡

በአሁኒቱ ኢትዮጲያ የዜጎች የጤናና በሂወት የመኖር፣ ብዛሃነታቸውን የመግለፅ መብቶችን መነጣጠል አይችልም፡፡ እነዚህ መብቶችም በቀጥታ ከዴሞክራሲዊነትና ከልማታዊነት ጋር የተቆራኙ እና የማይነጣጠሉ አንደም ሁለትም የኢትዮጲያ የህልውና መሰረቶ ናቸው፡፡

ሰለዚህ አብዮፓዊ ዴሞክራሲያዊ ርእዮት አለም አሁን አገራችን ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ዴሞክራሲንያዊነትና ልማታዊነት የማይነጣጠሉ ብቸኛ ወደ በለፀገ የከበርቴው ስርዓት መሄጃ መንገድ ነው ብሎ የሚያምን ርእዩት አለም ነው፡፡

የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ርእዮት አለም መለያ ባህርያት

1/ አብዮታዊ ነው: – ምክያቱም እመርታዊ ለውጥ (fundamental transformation) ከማምጣቱም በተጨማሪ አርሶ አደርነትን (peasantry) ወደ ወዝአደርነት፣ ወደ ባለሃብትነት እና ወደ ሙሁራዊ ማንነት በገቢ፣ በባህል በሎም በመደብ ስለሚቀይር ነው፡፡

2/ ዲሞክራሲያዊ ነው፡- ምክንያቱም የአስተሳሰብ፣ የማንነት፣ የሞያ፣ የገቢ፣ የፆታ እንዲሁም የፖለቲካ ልዮነቶች እውቅና ሰጥቶና አማራጮቹ እንዲኖሩ በጋራ ሰርቶ ማደግን የሚያውቅና የሚያከብር ስርዓት ስለሚገነባ ነው፡፡

3/ ልማታዊ ነው፡- ምክንያቱም ሰብአዊና ዴሞክሲያዊ መብቶች ሊሟሉ የሚችሉት ሰዎች (ዜጎች) መልማት ሲችሉ በመሆኑ እና በከፋ ድህነት ውስጥ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማክበር እጅግ አዳጋች ስለሆነ እንዲሁም በዋናነት የሚገነባው ስርዓት መለያው ሃብት ፈጠራ በመሆኑ ልማታዊነት ሌላኛው መሰረታዊ መለያው ነው፡፡

የመደቦች ሚና በአብዮታዊ ዲሞክሲያዊ ርእዮት አለም 

1/ ገበሬ (peasant)

ገበሬው የከበርቴው ስርዓት በመገንባት ሂደት ወቅት የሚኖረው ሚና በግልፅ ካልተቀመጠ የሚፈጠረው መደናገር የገበሬውን እና የሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን አቅም አሟጦ ተጠቅሞ በፍጥነት ወደሚፈለገው ስርዓት የሚኖረው ሽግግር ከማጓተት አንስቶ እስከ ሙሉ በሙሉ ማደናቀፍ ሊደርስ ይችላል፡፡

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ በፃፉት “የኢትዮጲያ የህዳሴ ጉዞ የልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ ድርሰቶች” በሚል መፅሃፍ ገፅ 178 “አንድ ድርጅት የአርሶ አደሩም መብትና ጥቅም ማስጠበቅን በዋነኛ አላማነተት ይዞ ከተነሳና በአርሶ አደሩም ተቀባይት ካገኘ በፖለቲካ ሂደቱ ላይ ወሳኝ ተፅእኖ ማሳረፍ የሚችል ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው የፓርቲዎች ቦታ እጅግ ጠባብና የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ በቂ ዕድል የማይከፍት ነው፡፡” ይላሉ፡፡

ከዚህ አባባል ልወስድ የምችለው ነገር ቢኖር በኢትዮጲያ ተጨባጭ ሁኔታ ስልጣን ለመያዝ ወሳኙ ገበሬው ነው፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወደ ስልጣን ለመውጣት ወሳኙ ገበሬው ከሆነ በስልጣን እንዲቆይ ከፈለገም የገበሬው መደብ መኖር እጅግ ወሳኝ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የገበሬው ዘልአለማዊ ህልውና ስልጣን ምንጭ መሆኑን ስለሚገነዘብ የገበሬውን መደብ የሚያደርገውን የመደብ ሽግግር በማደናቀፍ ሚና ላይ ይሰማራል በሌላ አባባል የገበሬው መደብ ዘልአለማዊ እንዲሆን ይሰራል ማለት ነው፡፡

ከላይ በጠቀስኩት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ እሳቤ የሚፈለገው የመደብ ሽግግር ማምጣት አይቻልም፡፡ ገበሬውን እንደ ስልጣን ምንጭ አድርገው እያሰቡ የገበሬው ድምፅ እየቀነሰ ሄዶ ከወሳኝነት ወደ ወሳኝ ወዳልሆነ ቁጥር እዲወርድ ስለማይፈልግ የገበሬው የፖለቲካ ጨዋታ ወሳኝነት ሚና ተጠብቆ እዲቆይ የሚያደርግ ከመሆኑም ባሻገር የአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ርእዮት አለም ሊገነባው ካሰበው የዳበረ የነፃ ገበያና የከበርቴው ስርዓት አንፃር መሰለፍንና ፀረ መዋቅራዊ ለውጥ (anti transformational change) መሰለፍን ያስከትላል፡፡ በመሆኑም የገበሬው ሚና በቅጡ አለማስቀመጥ ከማደናገርም አልፎ አፍራሽ ሚና ይኖረዋል፡፡ የገጠር ልማት ፖሊሲዎች በከፍተኛ ደረጃ መሳካት እንዳይችሉ አንደኛው ምክንያት ከላይ የጠቀስኩት የጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ እሳቤ እንቅፋት ነበር ብየ አምናለሁ፡፡

የገበሬው ሚና በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ርእዮት አለም የከበርቴ ስርዓት ግንባታ ወቅት፡-

የጋራ መግባባት ሊደረስበት የሚገባው የገበሬው ሚና በኔ እይታ የገበሬው መደብ ራስን የማጥፋት ሚና ማለትም በሚገነባው የከበርቴ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ የፖለቲካ ጨዋታውን የመወሰን ዓቅሙን የመቀነስ እና የፖለቲካ ስልጣን ወሳኝነቱ ከገበሬው መደብ ወደ ወዝአደሩ (proletariat)፣ መካከለኛ ገቢው (middle class) እና ወደ ከበርቴው (the capitalist) የሚሸጋገርበትን እሳቤ እያሰቡ የገበሬውን መደብ ማሸጋገር የግድ ይላል፡፡

በበለፀገው የከበርቴው ስርዓት ወቅት የገበሬ መደብ (peasant class) የሚባል ሊኖር አይችልም ስለሆነም የከበርቴው ስርዓት ግንባታ በሌላ አገላለፅ የገበሬው መደብን የማጥፋት ሂደት ማለት ነው፡፡ ይህ የገበሬውን መደብ እንደ መደብ እንዳይኖር እና የስልጣን ምንጭ እንዳይሆን የማድረግ ሂደት ከዛሬይቱ ኢትዮጲያ የገበሬው መደብ ጋር በዋናነት በተጨማሪም ከቀሪዎቹ መደቦች ጋር በግልፅ መግባባት ላይ ተደርሶ ወሳኙ የአገራችን የገበሬው መደብ የፖለቲካ ወሳኝነት ሚና የማጥፋት ብሎም የሌሎቹ የሶስቱ መደቦች ሚናን የማሳደግ እሳቤ ሊያዝ ይገባዋል፡፡

በአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ርእዮተ አለም እሳቤ የበለፀገ የከበርቴው ስርዓት መገንባት ማለት የገበሬው መደብ የፖለቲካ ወሳኝነት ሚናን ማጥፋት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የገበሬው መደብ የሚኖረው ሚና የራስን ማጥፋት ሚና (self-transformation role) መሆን አለበት፡፡

የከበርቴው መደብ  (የባለሃብት) ሚና

በማቴወስ ወንጌል ምዕራፍ 19 ቁጥር 23 እየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “እውነት እላቸኋለሁ ባለጠጋ ወደ መንግስተ ሰማያት መግባት ጭንቅ ነው፡፡”

ቁጥር 24፡- “ዳግመኛ እላችኋለሁ ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል” ይላል

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች አቶ መለስ ዜናዊ እና አቶ ሃይለማርያም ዳሳለኝ በተለያዮ ወቅቶች ባለሃብቱን እየሰበሰቡ እጅ እንቆርጣለን፣ ጣት እንቆርጣለን ወዘተ በማለት ሲያስፈራሩት ኖረዋል፡፡ በቅርቡ እንኳን ጠቅላይ ሚኒሰቴር ዶ/ር አብይ አሕመድ በቢሮአቸው አዳራሽ ሰብስበው “ወደ ውጭ ያሸሻችሁትን የውጭ ምንዛሪ አምጡት” ብለው ተቆጡ፡፡ ባለሃብቱ አገር ፈርቶ እንዲሸሽ እያደረገው ያለ ነገር ምንድን ነው ለምን አገሩ ሳይመቸው የሰው አገር ተመችቶት ሸሸ ብለው ቢጠይቁ መልሱንም መፍትሄውም ያገኙት ነበር፡፡

በኢትዮጲያ የከበርቴው መደብ ገና በመፈጠር ላይ ያለ መደብ ነው በአንድ የታሪክ አጋጣሚ ከበርቴው እንደ አድሃሪ፣ በዝባዥ ተቆጥሮ የንብረትና የሃብት መወረስ አጋጥሞት መቀመቅ ገብቶ የነበረና አሁንም ድረስ ከነበረው ድንጋጤ ሊያስወጣ የሚችል መተማመኛ ከመንግስት ሊሰጠው ያልቻለ መደብ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በማህበረሰቡ ዘንድ አንደ ለፅደቅ ያልታደለ እና ከሃብቱ ጀርባ ሃጢያት አንዳለ የሚሰብክ ሀይማኖታዊ አስተምህሮ ባለበት አገር ውስጥ ለመፈጠር እየተፍጨረጨረ ያለ በመሆኑ ትልቅ ፈተና ላይ ያለ መደብ ነው፡፡

የሚገርመው ነገር የአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ርእዮት አለም ተከትየ የዳበረ የከበርቴው ስርዓት መመስረት እፈልጋለሁ የሚለው የኢህአዲግ ባለስልጣናት እንኳን ከበርቴው እንደ ሰርቆ የበለፀገ ጠላት እንጂ እንደ ወዳጅ እና ከታገዘ እና ሙሉ መብት ከተሰጠው በህግና በስርዓት የብልፅግናው እና የአገር ግንባታው ቁልፍ ተዋናይ መሆኑን ሲያሳዮ አይታዮም፡፡

ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ የምንሰማው “ድህነት ጠላታችን ነው” ከድህነት ሮጠን እናምልጥ የሚሉ መፈክሮችን ነው፡፡ ጥሩ ነው፤ ድህነት ጠላታችን ነው! ወዳጃችንስ ማን ነው? ጥሩ ነው ከድህነት ሮጠን እናምልጥ፤ ግን ወዴት?

ጠላታችን ድህነት ከሆነ ወዳጃችን ሃብት እና ሃብታም መፍጠር እንደሆነ በስብከቱም በተግባሩም ሃብታሞች የሚከብሩበት መብታቸው የማይደፈርበት የማይሸማቀቁበት ስርዓት መሆን አለበት፡፡ ሮጠን የምናመልጠው ከድህነት ከሆነ ሄደን የምንጠለልበት ሃብት እንዲሁም ሃብትንና ሃብታምን የሚያከብር ስርዓት እንደምንገነባ በተግባር ማሳየትም ማስተማርም አለብን፡፡

“የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ የልትና ዴሞክራሲ ግንባታ ድርሰቶች” በሚለው የቀድሞ ጠ/ሚር አቶ መለስ ዜናዊ መፅሃፍ ገፅ 449 ቁጥር 1 ላይ “የኢነዱስትሪ ልማት ስተራተጂው ሞተር የግል ባለሃብቱ መሆኑን መቀበል” በሚል ርእስ ስር “በአገራችን የተሳካ የኢነዱሰትሪ ልማት ስራ ሊሰራ የሚችለው የዚሁ ስራ ሞተር የግል ባለሃብቱ መሆኑን የተቀበለ ስትራተጂ መንደፍ፣ የግል ባለሃብቱ ይህንኑ ሚናዉን እንዳይጫወት የሚገቱትን ነገሮች በዝርዝር በማየትና ከዚህ ተነስቶ የግል ባለሃብቱ ሚናውን እንዲጫወት ለማድረግ የሚያሰችሉ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ በመረባረብ ነው፡፡” ይላሉ፡፡ ከዚህ አባባላቸው መረዳት የሚቻለው የግል ባለሃብቱን ሚና ሊተካ የሚችል ሃይል አንደሌለና የቀጣዩ የኢነዱሰትሪያላዊ ስርአት ባለቤት መሆኑን ነው፡፡

እዚህ ላይ ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር የምስማማው የብዮታዊ ዲሞክሲዊ ርእዮት አለም መገንባትና መድረስ የሚፈልገው የዳበረ የከበርቴው ስርዓት ነው፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ የኢህአዲግ አመራሮች በተዛባ መልኩ እንደሚገለፀው ሳይሆን የትግሉ/የከበረቴው ስርዓት ግንባታው ባለቤት በዋናነት ባለሃብቱ ነው፡፡ ባለሃብቱ የሚገነባው ስርዓት አጥብቆ የሚመኘውና ከስርቆት እና ከዘረፋ ፣ ከሙስና እንዲሁም ከመፍረስ የሚጠብቀው የመዳረሻው ስርዓት ባለቤት መሆኑን ሲያውቅ ነው፡፡ ነገር ግን በኮሚኒስታዊ ታሪካዊ እሳቤ ውስጥ ሆነን የዳበረ የከበርቴው ስርዓት እንገነባለን ብለን ብንለፍፍ የይምሰል ካልሆነ በስተቀር የዳበረ ስርዓት ሊኖረን ልንገነባውም አንችልም፡፡

በአንድ ወቅት በትግራይ ክልል የህውሓት አመራሮች ከሙህራን ጋር ባደረጉት ውይይት ስለ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ርእዮት አለም ለማብራራት ሲባል አቶ ስብሃት ነጋ “የትግሉ መሪዎች ወዛደሩ፣ ገበሬው፣ አብዮታዊ ምሁሩ እና የታችኛው ባለሃብት ነው” ሲሉ የድርጅቱ የስራ አስፈፃሚ አባል አቶ አለም ገብረዋህድም የትግሉ መሪ “ንኡስ ከበርቴው ነው” ይላሉ፡፡

እዚህ ላይ የሚገነባው ስርዓት የባለሃብቱ የከበርቴው ስርዓት ሆኖ ሲያበቃ ከበርቴው የሚጠቅመውና የራሱ የሆነውን መዳረሻው ሃብቱን አና ጥቅሙን የሚያስከብርለትን ስርዓት መገንባት ላይ ብቁ አይደለም ብሎ ማሰብ ሊበሉዋት ያሰቡን አሞራ ምን ይሉዋታል እንደሚባው ነው ፡፡ ከዚህ እሳቤ ወይም ከኮሚኒስታዊ አስተሳሰብ ሳይፋቱ ለመተንተን እና ለመምራት እየተሞከረ ነው ወይም ደግሞ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርእዮት አለም እሳቤ እና አላማ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው፡፡

በግልፅ መቀመጥ ያለበት፡-

1/ አብዮታዊ ዲሞክሲዊ ስርዓት የሚገነባው መደረሻ ዓላማው የዳበረ የከበርቴው ስርዓት ነው፡፡

2/ የዳበረ የከበርቴው ስርዓት በመገንባት ወቅት ልክ እንደ ሙሁሩ/መካከለኛ ገቢው፣ ወዛደሩ ሁሉ ያለምንም መከፋፈል ባለሃቱም የግንባታ ሂደቱ መሪ ነው፡፡ በግንባታው ወቅት ሚና ከሌለው ጥቅሙን በሚያስከብር መንገድ ለመገንባቱ ዋስትና ሊኖረው አይችልም፡፡

3/ ወዛደሩ ያለ ባለሃብቱ (ያለ ከበርቴው) ህልውና ሊኖረው አይችልም፡፡ ስለሆነም ያለ ከበርቴው ህልውና የሚፈጠር ወዛደር ሊኖር አይችልም፡፡ በተጨማሪም ያለ ከበርቴው ህልውና የምሁሩ ህልውና ፋይዳ አይኖረውም ያለ ከበርቴው ጠንካራ ተሳትፎ የሚፈጠረው ምሁር ያለው አማራጭ የመሪነትና የከበርቴው ቦታ ተኪነት ሚና እጅግ አደገኛ እና በስርዓትም በፍጥነት ወደ በዝባዥነት ያውም ፀረ ዴሞክራሲያዊ እና በሙስና የተዘፈቀ መደብ ይሆናል ስለሆነም ሚናቸውን በግልፅ ሊቀመጥ ይገባል፡፡ የተጠናከረ የከበርቴው መደብ መኖር ሞያዊ (professional) ምሁር እንዲኖር ያደርጋል ስለዚህ የከበርቴው መደብ ጠንክሮ የትግሉ መሪ አባል መሆን በፍጥነት ከድህነት የመውጣቱን እና የማህረሰባዊ ሽግግር (class transformation) ሂደቱን ያፋጥነዋል ቁልፍ ሚናም ይጫወታል፡፡

4/ በሰፋፊ የኢንቨስትንት መስኮች ከአርሶ አደርነት ወደ ወዛደርነት ለሚቀየሩ ዜጎች የስራ እድል ፈጣሪ ይሆናል፡፡ ምርታማነትን ለማሳደገደ ወደ ጥናትና ምርምር ስለሚገባ ከአርሶ አደርነት ወደ ሞሁሩ ክፍል ለሚቀየረው የህብረተሰብ ክፍል የስራ እድል ይፈጥራል፡፡ የከበርቴው መደብ የሚያገኘውን መንግስታዊ ጥበቃ በማየት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የህብረተሰብ ክፍል የስራ ፈጣሪነት (entrepreneurship) መነቃቃት በመፍጠር ኢኮኖሚውን ያሳድጋል፡፡

ለማጠቃለል አብዮታዊ ዲሞክራሲ ርእዮት አለም በሚከተለው የዳበረ የከበርቴው ስርዓት ፈጠራ ትግልና ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው የከበርቴው መደብ ስለሆነ መንግስት በፖሊሲዎቹና በተቀን ተቀን ተግባሩ ከበርቴውን ከዘራፊነትና ከበዝባዥነት እይታ በሚያስወጣ መንገድ መያዝና ማገዝ አለበት፡፡ መንግስት ባለሃቶች ገንዘባቸውን አሸሽተው ወደ ባእድ አገር የሚያጎርፉበት ዋና ምክንያት ከነሃብታቸው ጥበቃ ተደርጎላቸው ለመኖር የሚያስችል ሁኔታ (environment) አለመኖሩ ነው እንጅ የባእድ ሃገርን ጥገኝነት ፍለጋ ሊሆን አይችልም በማለት ቢቻል የባእድ ሃገር መንግስት ከሚሰጡት ጥበቃ (security) በላይ ካልሆነም ግን የነሱን ያክል ባለሃብቱን ሊያግዘውና ዋስትና ሊሰጠው ይገባል፡፡ በሁሉም መዋቅሩ “ሃብታም ሌባ ነው” ከሚል እሳቤ እዲወገድ ሊሰራበት ይገባል፡፡ ህዝብም በመግቢያየ እንደገለፅኩት ከሃብት ጀርባ ሃጢያት አለ ከሚል እሳቤ እንዲወጣ የተጠናከረ አስተምህሮ መኖር አለበት፡፡

የምሁሩና የመካከለኛው ገቢ (middle income) ሚና

የዳበረ ዲሞክረሲና የዳበረ የከበርቴው ስርዓት ያለ ምሁሩ አይታሰብም ምክንቱም ምሁሩ የእውቀት፣ የምርት ጥራት፣ የመፍትሄ እና የፍልስፍና ምንጭ በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡ ምርምር የሌለው ሃገር እና መንግስት   ልክ እንደ ረጋ እና እንደማይንቀሳቀስ ዋሃ ነው የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር መሸተቱና መመረዙ አይቀርም፡፡

ሙሁር ሙሁር ሊባል የሚችለው በተማረው ትምህርት ወይንም አንብቦ፣ አጥንቶ እና ተመራምሮ ባመቀው እውቀት ሲለካ እና ተጨባጭ ላውጥ በህዝብ ኑሮ ላይ ሲያመጣ እንጅ እውቀቱ እና ትምህርቱ ሌላ ሆኖ ሲያበቃ የትምህርት ማስረጃ ስላለው እና በማያውቀው/ አንብቦ በማይረዳው ዘርፍ ታማኝ በመሆኑ ምክንያት ብቻ የተመደበ ሙሁር ሊባል አይችልም፡፡ ይባስ ብሎም ታማኝነትን ታሳቢ ያደረገ እውቀትና ክህሎት መሰረት ያላደረገ ምሁር በአንድ አገር ፖለቲካ እና የመንግስት መዋቅር ቦታ እያገኘ የሚሄድ ከሆነ አሁን በአገራች እደምታዘበው የመንግስተ /የፖለቲካ ፓርቲው ታማኞች እንዲሞላ እና ምሁርነት እና ሞያዊነት (intellectualism and professionalism) እንዲጠፋ ያደርጋል፡፡

እንዲሁ አይነት ከሙሁርነት ይልቅ የታማኝነት ምልመላ እና አቀራረብ ፓርቲውን ገድሎ አገር እስከ ማፍረስ ሊደርስ ይችላል፡፡ በኔ እይታ የሙሁሩ ሚና በአብዮታዊ ዴሞክራሲዊ ርእዮት አለም ውስጥ በሞያው እና በእውቀቱ ያገለገለ ምሁር ሁሉ የስርዓቱ ገንቢ ነው፡፡ ሙሁር በእውቀቱ ሲሰራ ምርታማነትና አገልግሎት ሰጭነት ይጨምራል፣ አገራዊ እውቀት በጥልቅ ምርምር ይዳብራል ስለዚህ እውቀት እና ክህሎት የአገሪቱ የለውጥ ሞተር ይሆኑና የሚፈለገውን እድገት (transformation) ማሳካት ይችላል፡፡

ስለዚህ የኢትዮጲያ ሙሁር የዳበረ የከበርቴውን ስርዓት በመገንባት ወቅት የሚኖረው ሚና የመሪነት ሚና ነው አገራዊ እውቀትን ተጠቅሞ ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል የጥናትና ምርምር ሰነዶች በማዘጋጀት፣ ተቋማትን በእውቀት በመምራት፣ ህዝቡን በማስተማር፣ ምርታማነትን በማዘመን እንዲሁም የመንግስት እና የፓርቲ አመራር ከዕድገት ምህዋሩ እንዳይወጡ ሂሳዊ አቀራረቡን በማጠንከር የመሪነት ሚናው ሊጫወት ይገባል፡፡

አንዳንድ የኢህአዲግ አመራሮች እደሚሉት የኢትዮጲያ ሙሁር የመሪነት ሚናውን ለመጫወት የግድ የፓርቲ ጥግ (party affiliated) መሆን የለበትም፡፡ ነገር ግን ሞያዊ ነፃነቱን ጠብቆ ትምህርቱን እና እውቀቱን መተግበር የሚችልበት ምህዳር እንዲሰፋ መታገል እና በትግል ሂደቱ የማፍራት አቅምን ማሳደግ ታሳቢ ያደርገ መዓልታዊ (የቀን ተቀን) ሃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡

ለማጠቃለል ሙሁሩ እና የከተማ ነዋሪው የዳበረ የከበርቴው ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ የመሪነት ሚና አላቸው ሊታይ የሚችው የእድገት ምህዋር ኡደቱን በማፍጠን እና ከገበሬነት እየተቀየረ ለሚይቀላቀለው ዚጋ በፍጥነት ወደ አምራች ምሁር የሚሆነበት መሰረታዊ መደላድል መፍጠር ያለበት አሁን ያለው ሞያዊው (professional) ምሁር ነው፡፡

ወዝአደሩ፡-

በኢትዮጲያ ተጨባጭ ሁኔታ የወዝአደሩ መደብ ገና እየተፈጠረ ያለና ገና ያልጠነከረ ነው፡፡ ምንም እንኳን የኢኮኖሚ መሰረቱ በፋብርካዎች ተቀጥሮ የሚሰራ ቢሆንም በቁጥርና በአገሪቱ ፖለቲካ መዘውር ላይ ያለው ተፅእኖ እጅግ አናሳ ነው፡፡ በመሆኑም የከበርቴው መጠናከርና የማያቋርጥ የስራ እድል መፍጠር የሚችሉ የአምራች ኢንዱስትሪዎች መስፋፋትን አጥብቆ የሚመኝ መደብ ነው፡፡

የወዝአደሩ ህልውና በቀንታ ከከበርቴው ህልውና ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ከበርቴው ያለ ወዛደር፤ ወዛደር ያለከበርቴው አሁን አለማችን ባለችበት ሁኔታ መኖር አይችሉም፡፡

ስለዚህ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሊገነባው በሚፈልገው የከበርቴው ስርዓት ውስጥ የወዛደሩ ሚና እያደገ ሄዶ በስተመጨረሻ የስርዓቱ ባለቤት ከሚሆኑት ሶስት መደቦች አንዱ ነው፡፡

************

* The writer, Amanuel Alemayehu, can be reached at ami4410@yahoo.com

Guest Author

Guest Author

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago