ከዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት ማእከላይ ኮሚቴ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ

ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት ከተመሰረተበት 2000 ዓ/ም ጀመሮ ፖለቲካዊ እርምጃዎችን ለማከናወን ህጋዊ እውቅና ያገኘ ፓርቲ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ድርጅታችን በትግራይ ህዝብ ታሪካዊ ትግል ትልቅ ሚና እየተጫወተና በመጫወት ላይ የሚገኝ ሰላማዊ ድርጅት ብቻ ሳይሆን ለሰላማዊ ትግል የሚያስፈልገውን መስዋእትነት ሁሉ እየከፈለ የመጣና በመክፈል ላይ ያለ ድርጅት ነው፡፡ ስለሆነም ብዙ አባላቶቹና ደጋፊዎቹ በፖለቲካዊ አመለካከታቸው ብቻ በሂወት እንዳይኖሩና ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዳይመሩ የሚያደርግ አሰቃቂ እና ፀረ ህገመንግስታዊ ዓፈና እየደረሳቸው ይገኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በአባላቶቻችን የደረሰ ግድያ፣ ድብደባ፣ እስርና ሌሎች አካላዊና ስነ አእምራዊ ጥቃቶችንና ግፎች ቆመው ህገ መንግስታዊ ስርዓት እንዲከበር እናሳስባለን፡፡
ድርጅታችን ዓረና ክልላዊ ራዕዩና ዓላማው ለማሳካት እንዲሁም ሀገራዊ መልክ ለማስያዝ ከሌሎች የሃገራችን ድርጅቶች በመሆን መድረክ የሚባል ግዙፍና ጠንካራ ሀገራዊ ግንባር አቋቁሞ መስራት ከጀመረ ዓመታት አልፏል፡፡ መድረክ በሀገር ደረጃ የዜጎች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅሞች የሚያስከብርና እንዲከበሩ እየታገለ የሚገኝ ትልቅ የሀገራችን ድርጅት ነው፡፡ ይሄም በሀገራዊ ማንነት፣ በዜጎችና ህዝቦች እኩልነት፣ እንዲሁም ፍትህና ርትዕ ለማረጋገጥ አፅንኦት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ትልቅ ፖለቲካዊ ቀውስ አጋጥሟት በሚገኝ ወቅት የዓረና ትግራይ ማእከላይ ኮሚቴ የዓመቱ እቅድ አፈፃፀም፣ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴው፣ የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታዎችን ትኩረት ሰጥቶ ተወያይቷል፡፡
ድርጅታችን ባለፈው ዓመት የሰራቸው ስራዎች ገምግሟል፣ እንዲሁም ሀገራችን ያለችበት ፖለቲካዊ ቀውስ በመገምገም ፖለቲካዊ ቀውሱ እንደሚያሳስበው ለመግልፅ ይወዳል፡፡
የዚህ ምክንያት ደግሞ ለሰዎስት አስርት አመታት ገደማ የታጀለ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ አፈና የወለደው መሆኑ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

ፖለቲካዊ ምክንያት፡
የቀውሱ ፖለቲካዊ ምክንያት ስናይ የኢህአዴግ ስርዓት ፖለቲካዊ ምህዳር እያጠበበና በእሾህ እያጠረ፤ የዴሞክራሲ ተቋሞች እያጠፋና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቃኝቶ እየተካ፣ ነፃ መገናኛ ብዙሐን እንዳያቆጠቁጡ እየቀጠፈና እያጠፋ፣ ነፃ የሞያ ማህበራት ( ስቪክ ማህበራት) እንዳይኖሩ ለራሱ በሚያገለግሉ ማህበራት እየተካ አሁን ወዳለንበት የቀውስ ደረጃ አድርሶን ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች ወይም የራሳቸው ነፃ አስተሳሰብ ያላቸው ዜጎች በጅምላ ወሀኒ ላይ የታጎሩበትና ለሞትና ለስደት ሰለባ የሆኑበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ውጤቱም ምክንያታዊና ሰላማዊ ፖለቲካ ጠፍቶ የዓመፅና የጉልበት ትግል እየተካው ይገኛል፡፡ ይሄ ደግሞ ለብዙ የሂወት መጥፋት፣ የሰላማዊ ዜጎች ንብረት ውድመት እያስከተለ ከመሄዱም በላይ ሀገራችን ልትወጣው ወደማትችለው የፖለቲካ አረንቋና ስርአት አልበኝነት እያሰፈነ ይገኛል፡፡

በአንድ አገር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር ነፃ፣ ፍትሀዊና በመራጩ ህዝብ ተኣማኒ ምርጫ እንደሚያስፈልግ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ነው፡፡ ሆኖም ግን የኢህአዴግ ስርአት በሚፈፅማቸው ያፈጠጡ ያገጠጡ ወንጀሎች የህዝብ ድምፅ እየተሰረቀ የሀገራችን ስርዓት በአንድ ድርጅት እጅ እንዲወድቅ አስገድዶታል፡፡ የ 2007 ዓ/ም የምርጫ ሂደት ለማየት ስንሞክር ኢህአዴግ “100% በህዝብ ተመረጥኩ” ብሎ ያወጀበት አገባብ ስርአቱ አይን ያፈጠጠ ፀረ ዴሞክራሲ መሆኑ የተጋለጠበት አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡ ይህ ክስተት ደግሞ በዓለም የዴሞክራሲ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ፣ እውነተኛ የሀገራችን ምስል የማይወክል ከመሆኑም በላይ ብዙ ዜጎች በሰላማዊ ትግል የነበራቸው ደካማ እምነት ጨርሶ ያጠፋ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል፡፡
ከዚህ በላይ የከፋ ነገር የክልልና የፌዴራል ወንበሮች በአንድ አምባገነን ድርጅት መዳፍ ስር መውደቃቸው ብቻ አይደለም፡፡ የከፋው ነገር ይሄንን ተከትሎ የተሸረሸረው የዜጎች ህገ መንግስታዊ እምነት፣ የመጣው ፖለቲካዊ ውጥረትና ህዝባዊ እምቢተኝነት ነው፡፡ ህዝባዊ እምቢተኝነቱ ለመቆጣጠር በመንግስት የተወሰዱ አውዳሚና ያልተመጣጠኑ እርምጃዎች ችግሩ እንዲባባስ አድርጓል፡፡ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችና ልዩነቶች በድርድር ምትክ ጥይጥ፤ በዲፕሎማሲና በሰላማዊ ውይይት ምትክ በጉልበት ለመፍታት መሞከሩ ችግሩ እንዲባባስ አድርጎታል፡፡ በሀገራችን በተለያዩ ክልሎች የተፈጠረው ፖለቲካዊ ጥያቄ በግዜውና በአግባቡ ስላልተመለሰ ዘግናኝና አስደንጋጭ ውጤት አምጥቶ ይገኛል፡፡
በየክልሉ እየጠፋ ያለው የዜጎች ሂወት፣ ከሶማልያና ኦሮሚያ የተፈናቀሉ በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ወገኖች፣ ከ ጎንደር፣ ባህርዳርና ሰሜን ወሎ የተፈናቀሉ ተጋሩ ኢትዮጵያውያን፤ ከቤኑሻንጉልና ሌሎች ክልሎች የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ፤ እንዲሁም ከተለያዩ የደቡብ ክልል ዞኖች የተፈናቀሉ ዜጎች ወዘተ የቀውሱ ደረጃ ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ የሚያሳያ ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ የህወሓት ስርዓት በትግራይ ፤ የኢህአዴግ ስርዓት ደግሞ በሀገር ደረጃ የሚታይ ሀገራዊ ቀውስ መፍትሔ እንዲያገኝ ሁሉም የሀገራችን የፖለቲካ ሀይሎች የሚሳተፉበት ቦታ ሊፈጥሩ ይገባል፡፡ ይህ ቀውስ ባለው የይምሰል ፖለቲካ ከቀጠለ አደጋው ከባድ እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ የኢህአዴግ ስርዓት ሀቀኛ መፍትሄዎች ከማፈላለግ ይልቅ በተሃድሶና “በከፍታ ዘመን” የሚሉ ነገር ግን ምንም የአስተሳሰብ ለውጥ የማያመጡ አሰልቺና የተለመዱ ውሳኔዎች መጠመዱ ችግሩን እያባባሰ ይገኛል፡፡

የዓረና ማእከላይ ኮሚቴ “የትግራይ የበላይነት” በሚል የፖለቲካ ውስልትናም ተወያይቷል፡፡ ቁጥራቸው የማይናቅ ፖለቲከኞች በተለይ ደግሞ የመንግስት ስልጣን የጨበጡ የኢህአዴግ ድርጅቶች “የትግራይ የበላይነት” በሚል ውስልትናና ዘመቻ ከፍተው በንፁሃን ተጋሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሱ ቆይቷል፡፡ ይህ ፀረ ሰባኣዊ መብትና ፀረ ዴሞክራሲ ከመሆን አልፎ የሀገር አንድነትና ህልውና የሚያፈርስ እኩይ ተግባር ስለሆነ አጥብቀን እንኮንነዋለን፡፡
ይህንን ደግሞ የሁለት ትልቅ ሀይሎች ውጤት መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ በአንድ በኩል የህወሓት መሪዎች ሊያስቆማቸው የሚያስችል ፖለቲካዊ አስተሳሰብና በራስ መተማመን ስለሌላቸው “ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው” እያሉ በትግራይ ህዝብ ብብት ስር ሲደበቁ ይታያሉ፡፡
ህወሓት “ ትግራዋይ ሲጠቃ ወደ ህወሓት ይጠጋል” የሚል የተሳሳተ አመለካከቱ አርሞ ህዝብ እንደ ማስያዣና እንደ ቁማር መጫወቻ መጠቀም እንደስልት እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ፅንፍ የፖለቲካ ተቃውሞ የሚያራምዱ ፖለቲከኞችና ከህወሓት እልህ የተጋቡ የኢህአዴግ ድርጅቶችን “የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ናቸው” እያሉ በንፁሀን ተጋሩ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ፡፡
በአንፃሩ ግን ህዝባችን ከህወሓት ታማኞችና መሪዎች የሚስተካከል ኑሮና ሀብት ሊኖሮው ይቅርና መሰረታዊ ፍላጎተቹ አማልቶ መኖር በማይችልበት የድህነት አረንቋና ፋታ በማይገኝበት የጦርነት ቀጠና ይገኛል፡፡

ምጣኔ ሀብታዊ ምክንያቶች
የሀገራችን የምጣኔ ሀብት ሁኔታ በከፋ ደረጃ ይገኛል፡፡ በተለይ ደግም የትግራይ ምጣኔ ሀብት እጅግ በጣም በሚያሳስብ ደረጃ ይገኛል፡፡ በትግራይ የግል ኢንቨስትመንት አይበረታታም ብቻ ሳይሆን ዘርፉ ትላልቅ አፈናዎችና ተፅእኖዎች የተጫኑበት ነው፡፡ በትእምት ( EFFORT) ፍፁማዊ የበላይነት የተያዘ ንግድና የፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነት የፈጠረው አሉታዊ ተፅእኖ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ እጅግ በጣም ተቀፍድዶ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ክልላችን በሀገራችን የድህነት ወለል ተርታ ትገኛለች፡፡ ይህንን የወለደው የተማረና ወጣት አምራች ሀይል እግሩ ወደ መራው ስደት እየተንከራተተና የዓሳ እራት፣ ለአሸባሪዎችና ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችን እየተጋለጠ ይገኛል፡፡
በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ የትግራይ ህዝብ በውሸት ዘገባ በሀብት ላይ ሀብት ያከማቸ እንደሆነ ተደርጎ በድርጅቱ ሚድያዎች እና በመንግስት ሲዘገብ የሌላ ክልል ተወላጆች ጥያቄ እስከሚያነሱ እና የተሳሳተ ምስል እንዲጨብጡ ከተደረገና ጉዳት ካደረሰ በኋላ “ ዋሽተን ነው” የሚል ኑዛዜ ማቅረባቸው ነው፡፡

በመጨረሻም የትግራይ ህዝብ ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ጭቆና በዝቶበትና መሮት አልገዛም ማለቱ ገሀድ ሀቅ ነው፡፡ በተመሳሳይም የኢህአዴግ ስርዓት በተለመደው አገባብ ሊገዛ በማይችልበት ደረጃ መድረሱ ግልፅ ሆኗል፡፡ እንደ መፍትሔ የተወሰዱ “ጥልቅ ተሀድሶ፣ የከፍታ ዘመን፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” ወዘተ የሚሉ ጭንቀትና ቀቢፀ ተስፋ የወለዳቸው እርምጃዎች ስለሆኑ ምንም አይነት መፍትሔ ሊያመጡ አልቻሉም፡፡
በዚህ መሰረት የአረና ማእከላይ ኮሚቴ የ 10 ነጥብ አቋሞቹ ይገልፃል፡

1) ወደ ግጭትና ጦርነት የሚያመሩ ሁሉም ፖለቲካዊ ውሳኔዎችና እርምጃዎች የሚቆሙበት፤ ሀገራዊ መግባባት እና ሀገራዊ አንድነት የሚገነባበት መንገድ እንዲፈለግ እናሳስባለን፡፡

2) በፖለቲካዊ አመለካከታቸው የተገደሉ፣ የታሰሩ፣ የተደበደቡና የተንገላቱ ዜጎች ያለምንም ልዩነት ፍትህና የሞራል ካሳ እንዲያገኙ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡

3) በኦሮሚያ ፣ በሶማልያ ፣ በአማራና በሌሎች ክልሎች በፖለቲካዊ አቋማቸው እና በብሄራቸው ምክንያት በንፁሃን ሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰ ግድያ፣ የአካል መጉደል፣ የንብረት መውደም እና መፈናቀል እንዲቆምና ወንጀለኞች ወደ ህግ እንዲቐርቡ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡

4) የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ ጉልበትና አፈሙዝ በህግና ፍትህ ተተክተው ሀገር ከቀውስ የምትወጣበት ፖለቲካዊና ህጋዊ ቦታ እንዲስተካከል እናሳስባለን፡፡

5) መንግስት በሀገር ደረጃ የተጀመረው የፖለቲካ እስረኞች መፍታት በትግራይ ባለመታየቱ ህወሓት ለትግራይ ህዝብ ያለው ልግምተኝነት እና ውሱን ተነሳሽነት እንዲያስወግድ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡

6) የትግራይ ህዝብ በፖለቲካዊም ሆነ በሌሎች ህጋዊ አደረጃጀቶች በነፃ ፍላጎቱ ተደራጅቶ ጥቅሙና ደህንነቱ የሚያረጋግጥበት ቦታ ሊፈጠርለት ይገባል፡፡ ይሄንን ለማረጋገጥ ደግሞ በመሬት ላይ ያሉ ፖለቲካዊ እንቅፋቶች እንዲነሱ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡

7) የገዢው ፓርቲ መሪዎች በቢልዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያደርጉት ዘረፋ እንዲቆም፤ የአርሶ አደሮች መሬት ወረራና ማጭበርበር እንዲቆም፤ እንዲሁም በህዝብ ስም የሚደረግ ማወናበድ እንዲቆም ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡

8) የአንድ ድርጅት ጠቅላይነትና ፍፁም የበላይነት ቀርቶ ህገ መንግስት ወደ ትግባር የሚመነዘርበትና ሁሉም ዜጎች በነፃነት የሚሳተፉበት የፖለቲካ መህዳር እንዲመቻች እና የሀገራችን ሰላም ወደ ተለመደው እንዲመለስ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡

9) ፍትህ፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲያብብ አስፈላጊ የሆኑ የዴሞክራሲ እሴቶች ( ነፃ መገናኛ ብዙሀን፤ ስቪክ ማህበራት) እና ሌሎች ተቋሞች እንዲመሰረቱ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡

10) በህወሓት አፋኝ ተግባር የተነሳ በንፁሃን ሰላማዊያን ተጋሩ እየተፈፀመ ያለው ግድያ፣ ዘረፋ ኣጥብቀን እንኮንናለን፡፡

የዓረና ትግራይ ማእከላይ ኮሚቴ
ጥር 28/2010 ዓ.ም
መቐለ

*******

Curated Content

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago