‹‹የዘመን ክስተት›› አዲስ መጽሐፍ ስለመለስ ዜናዊ

(ገብረሚካኤል ገብረመድህን)

በኢትዮጵያ በየዘመኑ ለሃገራቸውና ለህዝባቸው የደከሙ፣ የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ፣ የህዝባቸውን ክብርና ነፃነት በማስጠበቅ ረገድ የማይዘነጋ ውለታ የዋሉ፣ በዚህም የማይደበዝዝ ታሪክ የፃፉ ታላላቅ ሰዎች ነበሩ፣ አሁንም አሉ፡፡ በህይወት ዘመናቸው ባበረከቱት አስተዋፅኦ ህዝባቸውን በብዙ መልኩ ጠቅመዋል፡፡ሃገራቸው አሁን ያላትን ቅርፅ እንድትይዝ አስችለዋል፡፡ ከዚህ አኳያ መለስ ዜናዊ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡

“የምጡቅ አዕምሮ ባለቤት” የነበረው መለስ በአመራር ጥበቡ በኢትዮጵያ ባስመዘገበው ውጤት “ታላቁ መሪ” የሚል ቅፅል አትርፏል፡፡ በዚች ሃገር ውስጥ ዘመን የማይሽረው አኩሪ ታሪክ ሰርቷል፣ ትውልድ የማይረሳው አሻራ አኑሯል፡፡ በዘርፈ ብዙ አስተዋፅኦውም “ለህዝብ የተፈጠረ፣ ለህዝብ የኖረ፣ ለህዝብ የሞተ መሪ” ለመባል በቅቷል፡፡ መለስን የመሰሉ መሪዎች የሃገራትን እድል የመወሰንና በትውልዶች ህይወት ላይ ተፅዕኖ የማሳደር ሚናቸው የጎላ ነው፡፡ ተግባራቸውና አስተሳሰባቸው በዘመነ ስልጣናቸው ሳይገደብ ዘመናትን ይሻገራል፡፡

የነዚህን ሰዎች ታሪክና አስተዋፅኦ በተደራጀ መልኩ ሰንዶ ለትውልድ ማስተላለፍ ጠቃሚ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ ትውልድ ከህይወታቸውና ከአመራራቸው ብዙ ይማራል፡፡ ህይወቱን በተሻለ መንገድ ለመምራትም ይጠቀምበታል፡፡ የዚህ መፅሐፍ ዓላማም ይኸው ነው፡፡ መጪው ትውልድ ከመለስ የትግል ህይወት፣ ከአመራር ክህሎቱ፣ ከስብዕናው፣ ከአስተሳሰቡና ከአስተዋፅኦው በመማር የተሻለች ሃገር ለመገንባት ይጠቀምበታል ከሚል እሳቤ ነው የተዘጋጀው፡፡

መለስ በሃገር መሪነት በኢትዮጵያ ስፋትና ቁመት ልክ የፈጠረው ተፅዕኖ፣ በህዝቡ ልብ ውስጥ የያዘው ስፍራ፣ በየዘርፉ ያስመዘገበው ለውጥ ትልቅ ነው፡፡ በስልጣን ዘመኑ የኢትዮጵያን ዕጣፈንታ በመወሰኑ ሂደት ሚናው ግዙፍ ነበር፡፡ በመጀመሪያዎቹ አመታት በሽግግር መንግስት ፕረዝደንትነትና በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሃገሪቱን የማረጋጋት፣ የህዝቦቿን ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች የማስታረቅ፣ መሰረታዊ የልማት ስራዎችን የማከናወን፣ የአመለካከት ተቃርኖዎችን የማቻቻል፣ ፖለቲካዊ መስመሩን የማጥራት፣ እንዲሁም ሃገሩ ከዓለምአቀፍ ሃይሎች የተጋረጠባትን ኢፍትሃዊ የጣልቃገብነት ፈተናን የመመከት ተግባራት አከናውኗል፡፡

የዚህ ድምር ውጤት መታየት የጀመረው ደግሞ ከሁለተኛው አስር ዓመት አንስቶ ነው፡፡ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የታላቋ ኢትዮጵያ ግንባታ እውን እየሆነ መጥቷል፡፡ ለዘመናት በድርቅ፣ በረሃብና በጦርነት የጎደፈው ስሟ ከስኬት ጋር መነሳት ጀመረ፡፡ በአይን ከሚታየው ለውጥ በላይ ደግሞ የአስተሳሰብ ለውጡ መሰረታዊ ሆነ፡፡ በመለስ ዘመን ኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ስነልቦና አዳብረዋል፣ የእንችላለን ስሜትም ተጎናፅፈዋል፡፡

በአመራር ጥበቡ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ትርጉም ከመሰረቱ ቀይሮታል፡፡ በዲፕሎማሲው መስክም የሃገሩን ሉአላዊነት አስከብሮ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ የፊት ተሰላፊ አድርጓታል፡፡ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን እድል በራሳቸው እንዲወስኑ አስችሎዋቸዋል፡፡

Photo – Cover page of new book, Yezemen Kestet

መለስ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመርህና በተግባር የገደበ ብቸኛው አፍሪካዊ መሪ ነበር፡፡ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው፣ ሃገሪቱን የሁሉም ወዳጅ ከማድረግ አልፎ፣ በቀጣናው ቁጥር አንድ ተሰሚና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሃገር አድርጓታል፡፡ ለአንድ ሺህ ዓመታት ያህል ከዓለም እይታ ውጪ ሆና በብህትውና የኖረችውን ሃገር፣ በአመራር ዘመኑ የዲፕሎማሲ ተምሳሌትና የዓለም የስበት ማዕከል እንድትሆን አስችሏታል፡፡ በይዘትና በቅርፅ እንደገና በሰራት ሃገሩ ውስጥ ተፅዕኖው የገዘፈ፣ አስተዋፅኦውም የበዛ ነበር፡፡ መለስ በታጋይነትና በመሪነት በኖረባቸው አመታት ሁሉ ለህዝቡ ብልፅግና እና ለሃገሩ ህዳሴ መተኪያ የሌለው ህይወቱን ሰውቶ፣ የማይደበዝዝ ታሪክ ሰርቶ ፋና ወጊነቱን በተግባር አስመስክሯል፡፡

የመለስ ተፅዕኖ በኢትዮጵያ ድንበር የተገደበ አልነበረም፡፡ በዘመነ ስልጣኑ በአዕምሯዊ ሃይል በተገነባው ሁለንተናዊ ብቃቱ፣ ከሃገር መሪነት ወደ አለምአቀፋዊ ተዋናይነት ተሸጋግሮ የአፍሪካን ፖለቲካዊ ስነ-ምህዳር ተቆጣጥሮታል፣ የአህጉሪቱ ልሳን ሆኖም አገልግሏል፡፡ አፍሪካ በማንኛውም መድረክ ላይ እንዲወክላት በመረጠችው ጊዜ መለስ አደራውን ተቀብሎ በርቱዕ አንደበቱ፣ በግዙፍ ስብዕናው፣ በልዩ የአነጋገር ችሎታው፣ በበሳል ሃሳቦቹ የአህጉሩን ድምፅ አስተጋብቷል፡፡

“አፍሪካ የራሷን እድል በራሷ መወሰን አለባት” እያለ ከልብ ተሟግቷል፡፡ አህጉሪቱ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ብድርና እርዳታ እንድታገኝ፣ የራሷ ሃገር በቀል ፖሊሲዎች የመቅረፅ እና የመተግበር ነፃነት እንዲሰጣት፣ በዓለምአቀፍ ገበያ ፍትሃዊ የንግድ ውድድር የምታደርግበት እድል እንዲመቻችላት፣ እንዲሁም የ21ኛው ክፍለዘመን የንግድና የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን ሳይታክት ተከራክሯል፡፡

በየዓመቱ ይካሄዱ በነበሩ የአየር ለውጥ ጉባኤዎች፣ መለስ በሰላ አንደበቱ የአንድ ቢሊዮን አፍሪካውያንን ድምፅ አስተጋብቷል፡፡ የበለፀጉት ሃገራት በሚለቁት በካይ ጭስ ምክንያት የሚከሰተው የዓለም ሙቀት መጨመር በአፍሪካ ላደረሰው ስፍር ቁጥር የሌለው መዘዝ ካሳ እንዲከፍሉ ከመጠየቅ አልፎ፣ ለወደፊት የበካይ ጭስ ልቀታቸውን እንዲቀንሱ ተከራክሯል፡፡

ቡድን ስምንትና ቡድን ሃያ እየተባሉ በሚጠሩት የበለፀጉት ሃገራት ጉባኤዎች፣ እንዲሁም በአለም የኢኮኖሚ ፎረምን በመሳሰሉ ታላላቅ መድረኮች አህጉሪቱን ወክሎ በመሳተፍ ለአፍሪካ ይበጃል ያለውን አቋም አራምዷል፡በነዚህ ጉባኤዎች ላይ ለአፍሪካ ችግር መፍትሄ በማመንጨት፣ ለአለምአቀፍ ተግዳሮቶችም የመውጫ መንገድ በመፈለግ ይታወቃል፡፡ “የዚችን ዓለም እጣ ፈንታ የሚወስኑት ምዕራባውያኑ ብቻ ናቸው” የሚለውን ስነልቦናዊ አመላካከት ሰብሮታል፣ ለዘመናት የተገነባው የበላይነታቸውንም ተፈታትኖታል፡፡

መለስ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ለመምከር በታላላቅ መሪዎችና ዲፕሎማቶች ዘንድ የሚመረጥ፣ በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ላይ በሳልና ጥልቅ ትንታኔ የሚሰጥ፣ በየትኛውም መድረክ ላይ በእጅጉ የሚናፈቅና ከልብ የሚደመጥ ፖለቲከኛ ነበር፡፡ በዚህ ተፅዕኖው የበርካቶችን ልብ አሸንፏል፡፡ ብዙዎች “የኢትዮጵያን የድህነት ታሪክ የቀየረ፣ የብልፅግና ተስፋዋ እንዲያብብ ያስቻለ፣ በሃገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠረ ብልህ፣ አርቆ አሳቢ እና ባለ ራዕይ መሪ፣ በህዝባዊ እና ዲሞክራሲያዊ አንድነት የተገነባች የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አባት፣ የህዳሴዋ መሃንዲስ፣ ለብሄሮች መብት መጎናፀፍ ህይወቱን የሰጠ ጀግና፣ ለአህጉሩ ጥቅም መከበር የተጋ ፓን-አፍሪካኒስት፣ በዓለም መድረክ ብቃቱን ያስመሰከረ ተሟጋች…” እያሉ ያደንቁታል፡፡ ተቺዎቹ ደግሞ መለስ “ለኢኮኖሚ ዕድገት እንጂ ለዲሞክራሲ መስፋት ግድ ያልነበረው፣ ለሚዲያው መጠናከር ከልብ ያልሰራ፣ ለተቃዋሚዎች መነቃቃት እድል ያልሰጠ፣ ብሔርተኝነትን አግንኖ አንድነትን ያላላ፣ ሃገራዊ ስሜትን ያደበዘዘ….” መሪ ነበር እያሉ ይወቅሱታል፡፡

የመለስ ሃገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ሚና የበለጠ ጎልቶ መታየት የጀመረው በሁለተኛው አስር አመት ነበር፡፡ እኔም ያኔ ነበር የህይወት ታሪኩን ለመፃፍ የተነሳሳሁት፡፡ መለስ ምን ዓይነት ሰው ነበር? የትግል እና የፖለቲካ ህይወቱ ምን ይመስላል? በኢትዮጵያ ያኖረው አሻራ ምንድነው? ዓለምአቀፋዊ ሚናው፣ አስተሳሰቡ እና አመራሩ እንዴት ይታያል? በሚሉት ነጥቦች ዙርያ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ጥናት አድርጊያለሁ፡፡ ከእሱ ጋር በተገናኘሁባቸው አጋጣሚዎች የያዝኩዋቸውን ማስታወሻዎች በማገላበጥ፣ ስለ መለስ ዜናዊ የተፃፉትን፣ የተባሉትን እና የተነገሩትን በመዳሰስ፣ ራሱ የተናገራቸውንና የፃፋቸውን ሃሳቦች በመፈተሽ፣ እንዲሁም ከእሱ ጋር ቅርበት የነበራቸውን የሃገር ውስጥ እና የውጭ ሰዎችን በማነጋገር ባደረኩት ጥናት ይህን መፅሐፍ አዘጋጅቻለሁ፡፡

የግለሰቦች ታሪክ ሲፃፍ በዘመናቸው የነበረን ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አስተሳሰብና የስልጣኔ ደረጃ ነፀብራቅ እንደሚሆን ሁሉ፣ ይህ መፅሃፍም በመለስ ዘመን ስለተፈጠረችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ይዳስሳል፡፡ መፅሃፉ መለስ እንደ ሃገር መሪና እንደ ግለሰብ፣ እንደ አለምአቀፋዊ ፖለቲከኛና እንደ አፍሪካዊ ተሟጋች፣ እንደ ፀሃፊና እንደ ተመራማሪ ምን ይመስል እንደነበር ከማብራራት ባሻገር፣ በሃገር ውስጥና በአፍሪካ ደረጃ በየዘርፉ የፈጠራቸውን ተፅዕኖዎች ይቃኛል፡፡ እንደዛም ሆኖ እያንዳንዱ ምዕራፍ በአንባብያን እይታ ሲፈተሽ ክፍተት ላይጠፋው ይችላል፡፡ ከዚህ አኳያ ሲመዘን ምናልባት የጎደሉ ሃሳቦችን ለማሟላት በተጓዝኩበት ርቀት ልክ ሳይሳካልኝ ቀርቶ፣ በማንኛውም መልኩ በመፅሃፉ ውስጥ ለሚስተዋሉ ጉድለቶች ሁሉ ተወቃሹ እኔ ነኝ፡፡

በዚህ ስራዬ በመለስ አስተሳሰብ ዙርያ በርካታ ጥናቶች ሊካሄዱ እንደሚችሉ ተገንዝቤያለሁ፡፡ በአንድ ወቅት አምባሳደር ስዩም መስፍን “የመለስ ማንነት፣ ስብዕና እና ውርስ በአንድ ፓናል ብቻ ተዘርዝሮ ይቋጫል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይህ የአሁኑና የወደፊቱ ትውልዶች ስራ ነው፡፡ ሁለቱም የመለስን ማንነት በመመርመር ሊወያዩበት፣ በማህደር ሊያሰፍሩትና ማስተማሪያም ሊያደርጉት ይገባል” ብለው ነበር፡፡ ተገቢ አባባል ነው፡፡ የመለስ ታሪክ በአንድ ፓናል ተዘርዝሮ እንደ ማያልቅ ሁሉ፣ በአንድ መፅሐፍም ተፅፎ የሚቋጭ አይደለም፡፡ ለወደፊት የዘርፉ ባለሙያዎች ብዙ ሊፅፉበትና ሊመራመሩበት ይችላሉ፡፡ ይህ መፅሃፍም ጥሩ መነሻ ይሆናቸዋል፡፡

********

Guest Author

Guest Author

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago