ለተከሰተው አመፅና አለመረጋጋት ዋናው ተጠያቂ አንድ ሰው ነው

ካለፈው ዓመት ጀምሮ በሀገራችን የታየውን አመፅና አለመረጋጋት በማነሳሳት ረገድ ተጠያቂ ናቸው የሚባሉት አካላት ብዙ ናቸው። ግብፅና ኤርትራ፣ ኦነግና ግንቦት7፣ የኒዮሊብራል አራማጆች እና የቀለም-አብዮት አቀንቃኞች፣…ወዘተ። ከእነዚህ ውስጥ እኔ በየትኛው እንደምመደብ ባላውቅም “ሕዝብን ለአመፅ በማነሳሳት” በሚል ወንጀል ተከስሼ ለ82 ቀናት ያህል በእስር ቤት እና በተሃድሶ ስልጠና ላይ ቆይቼያለሁ። በጦላይ በተሰጠኝ የተሃድሶ ስልጠና መሰረት አንድ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር ከላይ ከተጠቀሱት ኃይሎች ለተከሰተው አመፅና አለመረጋጋት የነበራቸው ሚና አንድ ላይ ቢደመር እንኳን ከአንድ ግለሰብ ሚና እንደማይበልጥ ነው። ለመሆኑ በዋናነት ተጠያቂ የሆኑት እኚህ ግለሰብ ማን ናቸው፣ ለምንና እንዴት?

በጦላይ የሚሰጠው የተሃድሶ ስልጠና በዶክመንተሪ ፊልሞች እና በዜና ዘገባ ጥንቅሮች የተደገፈ ነበር። ማታ ከ2፡00 በኃላ ሰልጣኞች/እስረኞች ከመኝታ ክፍሎቻችን አቅራቢያ በሚገኝ ሜዳ ላይ እንቀመጥና የተዘጋጁትን ቪዲዮዎች በፕሮጀክተር እንመለከታለን። ከእነዚህ ውስጥ እንቅልፍ ሳይወስደኝ በንቃት የተከታተልኩት ዶክመንተሪ የቀድሞ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በ1995 ዓ.ም በሀገራዊ ፖሊሲ ዙሪያ ለከፍተኛ አመራሮች የሰጡትን ስልጠና ነው። ከዚያ በፊት በተደጋጋሚ ተመልክቼዋለሁ። ነገር ግን፣ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አያይዤ በጥልቀት ለመመልከት እድልና ግዜ አልነበረኝም።

በተጠቀሰው ወቅት ጠ/ሚኒስትሩ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደነበሩ በግልፅ ያስታውቃል። በተደጋጋሚ በሚከሰተው ድርቅና ረሃብ፣ እንዲሁም ዝቅተኛ በሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲጨመርበት ድህነት በሀገሪቱ ላይ የሕልውና አደጋ እንደጋረጠ ተገንዝበዋል። ጠ/ሚኒስትሩም በወቅቱ ለገጠማቸው ችግር መፍትሄ ለመሻት ብዙ ዘመናት ወደኋላ ተጉዘው የህዝቡን ኑሮና አኗኗር እንደገና ለማጤን ተገደዋል። አቶ መለስ የተናገሩትን ቃል-በቃል ለማስታወስ ቢከብደኝም ዋና ፍሬ ሃሳቡን ግን እንደሚከተለው ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፡-

“ለብዙ ዘመናት በተራራዎች ተከበን፣ ከሌላው ዓለም ተነጥለን በድህነት ውስጥ ስንኖር ነበር። በድሮ ግዜ በድህነት ውስጥ በዘላቂነት (sustainably) መኖር ይቻል ነበር። አሁን እየጨመረ ካለው የሕዝብ ቁጥር አንፃር፣ በድህነት ውስጥ እንኳን እንደ ድሮ መኖር የማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ስለዚህ ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ የሕልውና ጉዳይ ነው። …ልክ እንደ ድህነት የመልካም አስተዳደር ችግርም ለኢትዮጲያ ሕዝብ አዲስ ነገር አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ለሕዝቡ አዲስ ሊሆን የሚችለው መልካም አስተዳደር ራሱ ነው…”

በዚህ መልኩ ለሀገሪቱ ክፍተኛ አመራሮች በሰጡት ስልጠናና አመራር ከ1995 ዓ.ም በኋላ ባሉት አስር አመታት ሀገሪቱ ፈጣንና ተከታታይ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ በቃች። ከመሰረተ ልማት ግንባታ ጋር በተያያዘ በመንገድ፣ ትምህርት፣ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) እምርታ ሊባል የሚችል ለውጥ ተመዘገበ።

የቀድሞ ጠ/ሚ አቋም በጥቅሉ ሲታይ፣ ፈጣንና ተከታታይ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ድህነትን መዋጋትና መቀነስ ካልተቻለ በስተቀር ሀገሪቱ የመበታተን አደጋ ያጋጥማታል።…ለኢኮኖሚ እድገት ቀጥተኛ የሆነ አስተዋፅዖ ባይኖረውም፣ ዴሞክራሲ በራሱ ጠቃሚና አስፈላጊ ነው ብለው ያምናሉ። እዚህ ጋር አቶ መለስና ተከታዮቻቸው ፈጣንና ተከታታይ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ጥያቄን ከቀን ወደ ቀን እንዲጨምር እንደሚያደርገው በደንብ የተገነዘቡት አይመስለኝም። የእሳቸውን ሌጋሲ እናስቀጥላለን ከሚሉት ውስጥም አብዛኞቹ ይህን እውነታ በግልፅ የተገነዘቡት አይመስለኝም።

በእርግጥ አንዳንድ የኢህአዴግ ባለስልጣናት በሀገሪቱ እየታየ ላለው የሕዝብ አመፅና ተቃውሞ መንስዔው ሀገሪቱ ላለፉት 25 ዓመታት እያስመዘገበችው ልማትና እድገት እንደሆነ ሲናገሩ ይሰማል። ነገር ግን፣ ልማትና እድገት እንዴት ለአመፅና አለመረጋጋት መንስዔ እንደሚሆን የጠራ ግንዛቤ ያላቸው አይመስለኝም። ፅንሰ-ሃሳቡን በግልፅ ለመረዳት በቅድሚያ በልማትና እድገት እና በዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግር መካከል ያለውን ቁርኝት በዝርዝር መረዳት ያስፈልጋል።

ልማትን “ሰላም፥ ጤና፥ ትምህርት እና የመሰረተ ልማት መስፋፋት” በማለት በአጭሩ መግለፅ ይቻላል። እነዚህ አራት መሰረታዊ ነገሮች የዳበረ ማህበራዊ ግንኙነት እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር በማስቻል የዜጎችን ኑሮና አኗኗር እንዲሻሻል ያስችላሉ፣ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋሉ። ስለዚህ፣ ልማት ከቦታና ግዜ አንፃር የዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ፈጣንና ቀልጣፋ ያደርጋል። “ፖለቲካ” ደግሞ የሕዝቡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት የሚመራበት ሥርዓት ነው። ስለዚህ፣ ፈጣን የሆነ እድገትና ልማት ማስመዝገብ ፖለቲካዊ ስርዓት ወደ ላቀ ደረጃ ከማሻሻል ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። በዚህ መሰረት፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ልማትና እድገት እስካለ ድረስ ሀገሪቱ የምትመራበት የፖለቲካ ስርዓት ከቀን ወደ ቀን እየተሻሻለ መሄድ አለበት።

በመሰረቱ፣ ማንኛውም የልማት ስራ ዓላማው ብዙኑን የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግ ነው። ምክንያቱም፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ልማት ሊኖር የሚችለው በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ሰላምና ደህንነት ሲኖር፤ የጤና፥ ትምህርትና ሌሎች ተቋማት አገልግሎት ተደራሽ ሲሆኑ፤ የመንገድ፣ ውሃ፥ መብራት፥ ቴሌኮምዩኒኬሽን መሰረተ-ልማት አውታሮች ሽፋን ሲጨምር ነው። ስለዚህ፣ ልማት ብዙሃኑን የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ በማድረግ እኩልነት (equality) እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ያስችላል።

የልማት መሰረታዊ ዓላማ አብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግ ነው። እኩልነትን ለማረጋገጥ በቅድሚያ በዜጎች መካከል ያለው ልዩነት (Inequality) መጋለጥና መታወቅ አለበት። በዚህ መሰረት፣ የልማት የመጀመሪያው ግብ ደግሞ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ያለው ልዩነት ማጋለጥ ነው። ይህ የልማቱ አካል በሆኑት የመገናኛና ኮሚዩኒኬሽን አውታሮች አማካኝነት የሚከናወን ይሆናል። በዚህ መልኩ፣ ልማት የእኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄን ያስከትላል። ልማት የዴሞክራሲ ጥያቄን ይወልዳል።

በሀገራችን ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ የተመዘገበው ፈጣን እድገት በዜጎች መካከል ያለውን የገቢ ልዩነት አስፍቶታል። በተለይ በመንገድ፣ ትምህርትና በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ረገድ የተመዘገበው ፈጣን የሆነ የመሰረተ ልማት መስፋፋት በዜጎች መካከል ያለውን የመረጃ ፍሰት በብዙ እጥፍ አሳድጎታል። ይህ በገጠርና በትናንሽ ከተሞች የሚኖሩት ወጣቶችን በውጪና በሀገር ውስጥ በሚገኙ ትላልቅ ከተሞች ያለውን የተቀናጣ ኑሮና አኗኗር በቀላሉ እንዲያውቁ ያስችላቸዋል። በገጠርና በትናንሽ ከተሞች የሚገኙ ወጣቶች በኑሮና አኗኗር ደረጃ ቀድሞ የነበረውና አሁን እየተፈጠረ ስላለው ልዩነት ግንዛቤ ተፈጥሯል። ይህን ተከትሎ በተለይ በልማቱ እኩል ተጠቃሚ ባልሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ተነስቷል። ከእነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚነሱ ጥያቄዎች በሂደት ወደ አመፅና ተቃውሞ እየተቀየሩ ለግጭትና አለመረጋጋት ምክንያት ይሆናሉ።

በአጠቃላይ ሀገራት ፈጣን የሆነ ልማትና እድገት ማስመዝገብ ሲጀምሩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በብዙ እጥፍ ይጨምራሉ። ለምሳሌ ቻይና ፈጣን የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ባስመዘገበችባቸው አስር ዓመታት ውስጥ የአመፅና አለመረጋጋት አደጋዎች ከአስር ሺህ ወደ ስልሳ ሺህ ጨምሯል። ይህ በሀገራችን በተጨባጭ እየታየ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ እንደ ቻይናና ህንድ ባሉ ሀገራት ጭምር በተግባር የተረጋገጠ ክስተት ስለመሆኑ የዘርፉ ተመራማሪዎች ከነምክንያቱ እንዲህ ሲሉ ይገልፃሉ፡-

“Inequality results in unsustainable life styles among both those who consume excessively as well as among those who are compelled to ravage their environment for their very survival. Widening income disparities have also been linked to social unrest and violence in developing countries, threatening the sustainability of society itself. In an age of mass communication, rising prosperity in one section of the population raises expectations of a better life everywhere. Television carries images of luxurious life in the metropolis and overseas to impoverished urban slums and outlying rural villages. When this growing awareness is not accompanied by growing opportunities, it gives rise to increasing frustration, social tensions and violence, as expressed by the increasing incidents of violence in China between 1993 and 2003, a period of rapid economic growth.” Human Capital and Sustainability

በኢትዮጲያ የተመዘገበውን ፈጣን እድገት ተከትሎ አዲስ አበባን ጨመሮ በሀገሪቱ ትላልቅ ከተሞች የተፈጥሮ ሀብትና አገልግሎት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረ ግልፅ ነው። የዜጎችን ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንፃር ቁልፍ ሚና ያለው መሬት ነው። ኢኮኖሚው በፍጥነት እያደገ በሄደ ቁጥር በመሬት ፍላጎትና አቅርቦት ረገድ ያለው ልዩነት በጣም እየሰፋ መምጣቱ እርግጥ ነው።

በተለይ የከተማ ነዋሪዎች፣ ባለሃብቶችና የመንግስት የመሬት ፍላጎት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ በሄደ ቁጥር በከተማ ዙሪያ ያሉ የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎችን የመሬት ይዞታ ያለ በቂ ካሳና የመልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ መቀራመት ተጀመረ። ለዘመናዊ የሪል ስቴት መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የደሃ አርሶ አደር ጎጆ ቤት ሲፈርስ፣ ባለሃብት ለሚገነባው ፋብሪካ የጤፍ እርሻ መሬቱን የተቀማ አርሶ አደር፣ ለወደፊት የሚመኘው ቀርቶበት በእጁ ላይ ያለውን የተቀማ ወጣት፣ … በአጠቃላይ፣ በተለይ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ያሉት ዓመታት የአንደኛው የሕብረተሰብ ክፍልን የተሻለ ሕይወት ፍላጎት በሌላኛው ኪሳራ ለማርካት የተሞከረበት ወቅት ነበር። ይህ የአከባቢውን ወጣቶች በፌስቡክና በስልክ እየተወያዩ፣ ስለ ራሳቸውና ስለ ቤተሰቦቻቸው እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል። ጥያቄያቸው በአግባቡ ምለሽ ሳያገኝ ሲቀር ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ መውጣት፣ ይህም ወደ ግጭትና አለመረጋጋት ቢወስድ ሊገርመን አይገባም። የነገ ተስፋውን የተቀማ ወጣት ዛሬ ላይ አመፅና ሁከት የሚፈራበት ምክንያት የለውም።

በአጠቃላይ፣ የብዙሃኑን የሕብረተሰብ ክፍል እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ያልታገዘ ልማትና እድገት መጨረሻው አመፅና አለመረጋጋት ነው። የብዙሃኑን እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጡ ለመሄድ ልክ እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም ቁርጠኛ መሆን ይጠይቃል። “ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ የሕልውና ጉዳይ ነው፣ ያለ ዴሞክራሲ መኖር ግን ልማዳችን ነው” እያሉ ወደፊት መሮጥ መጨረሻው ከሌላ የሕልውና አደጋ ጋር በድንገት መላተም ነው።

በእርግጥ ድህነት የጋረጠውን የሕልውና አደጋ ለማስወገድ በሚል የተመዘገበው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የዴሞክራሲ ጥያቄን በማስከተል ሌላ የሕልውና አደጋ ፈጥሯል። አሁን ላይ የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ከድህነት ባልተናነሰ ሁኔታ በሀገሪቱ ላይ የተጋረጠ ተጨማሪ የሕልውና አደጋ ሆኗል። ስለዚህ፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በሀገራችን ለታየው አመፅና አለመረጋጋት በዋና መንስዔነት ሊጠቀስ የሚገባው ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ የተመዘገበው ፈጣን ግን ደግሞ በዴሞክራሲ ያልታገዘ ግንጥል የሆነ ልማትና እድገት ነው። ለዚህ ደግሞ ፖሊሲና ስትራቴጂ ከመንደፍ ጀምሮ ስልጠናና አመራር እስከመስጠት ድረስ ትልቁን ሚና የተጫወቱት የቀድሞ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ናቸው።

በተመሣሣይ፣ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የተነሳው የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ወደ አመፅና አለመረጋጋት እንዲቀየር ያደረገው ደግሞ የኢህአዴግ መንግስት በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ረገድ ልክ አንደ ኢኮኖሚው ቁርጠኛ የሆነ አቋም ስላልነበረውና ተከታታይ የሆነ ለውጥና መሻሻል ማድረግ አለመቻሉ ነው። ለዚህ ደግሞ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር በዴሞክራሲ ላይ የነበራቸው ለዘብተኛ አቋም ያሳደረው ተፅዕኖ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ መገመት ይቻላል።

ሀገሪቱ ላስመዘገበችው ፈጣን ልማትና እድገት ሆነ ዘገምተኛ ለሆነው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትልቁ አስተዋፅዖ የአቶ መለስ ዜናዊ እንደመሆኑ በዚህ ምክንያት ለተከሰተው አመፅና አለመረጋጋትም ግንባር ቀደሙን ድርሻ ሊወስዱ ይገባል። ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ እንደ ግብፅና ኤርትራ፣ ኦነግና ግንቦት7፣ ወይም ደግሞ የኒዮሊብራል አቀንቃኞችና የቀለም አብዮተኞች በሀገሪቱ በአመፅና አለመረጋጋቱ እንዲከሰት የተጫወቱት ሚና አንድ ላይ ቢደመር እንኳን ከአቶ መለስ ሚና ጋር አይቀራረብም። ታዲያ አንግዲህ፤ “ለተከሰተው አመፅና ግጭት ዋናው ተጠያቂ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር ናቸው” ብል “ተሳስተሃል!” የሚለኝ አለ? ካለም ሃሳቡን በዝርዝር ያስቀምጥና በግልፅ እንከራከር።

***********

Seyoum Teshome

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago