የወልቃይት ጥያቄና የፕሮፌሰር መስፍን ክሽፈት

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ሰሞኑን ወልቃይትን በተመለከተ ኣንድ ጽሁፍ ለጥፈዋል፡፡ ጽሁፉ ኣጭር ቢሆንም እንደተለመደው ክህደትና ትእቢት የተቀላቀለበት ብቻ ሳይሆን እርስ በርስ የሚጋጩ ሃሳቦችንም ያካተተ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ወትሮው የሳቸውን ሃሳብ እንደወረደ ሲያራግቡ የነበሩ ተከታዮቻቸው ሲያራግቡት ኣልታየም፡፡

ጽሁፉ “ወልቃይት የማን ነው? የሚለው ጥያቄ ትክከል ኣይደለም፣የማይረባና መጥፎ ጥያቄ ነው” ብሎ ይጀምርና ጥያቄው መጥፎ መሆኑን ለማስረዳት የቀረበው መከራከሪያ ደግሞ ወልቃይት የኣማራ ነው ወይም የትግሬ ነው ማለት ጎሰኝነት ነው፣ “ወልቃይት የኢትዮጵያ ነው” ይላሉ፡፡ በዚህ መከራከሪያ መሰረት ትግራይም ኣማራም ኢትዮጵያ ውስጥ እስከሆኑ ድረስ ወልቃይት በኣማራ ወይም በትግራይ ስር መሆኑ ለውጥ የለዉም የሚል መደምደምያ ላይ ሊያደርሰን ይችላል፡፡ ነገር ግን ፕሮፌሰሩ ብዙ ሳይርቁ በኣዲስ መስመር “ትልቁና መሰረታዊው ጥያቄ በኣማራ ክልል ስር የነበረው ወልቃይት በወያኔ ኣገዛዝ ወደ ትግራይ ክልል መግባቱ ነው” ይላሉ፡፡

እስቲ እርስ በርሳቸው ከሚቃረኑት የፕሮፌሰሩ መከራከሪያዎች ቀንጨብ ኣድርገን እንይ፡፡

Photo – Professor Mesfin Woldemariam

ፕሮፌሰሩ “ትልቁና መሰረታዊው ጥያቄ በኣማራ ክልል ስር የነበረው ወልቃይት በወያኔ ኣገዛዝ ወደ ትግራይ ክልል መግባቱ ነው” ኣሉ፡፡

ሲጀመር ከወያኔ “ኣገዛዝ” በፊት ኣማራ የሚባል ክልል ኣልነበረም፡፡ ኣሁን ያሉት ትግራይና ኣማራ ክልሎች የተፈጠሩት በወያኔ ጊዜ ነው (ኣሁን ያለው ትግራይ ከወያኔ በፊት ከነበረው የተለየ ነው – ለምሳሌ በድሮው ምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ትግራይ የነበሩ ቦታዎች ኣፋርኛ ተናጋሪ ህዝብ ስለሆኑ ወደ ኣፋር ተካለዋል)፡፡ ከመጀመርያው ኣማራና ትግራይ ክልሎች ሲፈጠሩ ወልቃይት ትግራይ ክልል ስር ሆኖ ነው፡፡ ስለዚህ ኣንድ ላይ የተፈጠሩ ክልሎች ሆነው ሳለ ኣንዱ ኣንዱን ወሰደብኝ ማለት ኣይችልም፡፡ ኣማራ የሚባል ክልል ባልነበረበት ሁኔታ ከኣማራ ክልል ተወሰደ ማለት የሚቻል ኣይመስለኝም- ሌላ መከራከርያ ነጥብ ያስፈልጋል፡፡ እንደዉም ሰውዬው በዚሁ ጽሁፋቸው በፊት ኣማራ የሚባል ጎሳ ኣልነበረም ኣማራን የፈጠረው መለስ ዜናዊ ነው ይሉናል፡፡ “ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት መለስ ዜናዊን “አማራ የሚባል ጎሣ አሁን የለም፤ ግን አንተ ትፈጥረዋለህ ብዬው ነበር፤ ገና በሕጻንነት ነው እንጂ አሁን ተፈጥሮአል” በማለት ያሉት ነገር እንዳልቀረ ይነግሩናል፡፡ በርግጥ እሳቸው እንደሚሉት ሳይሆን ኣማራ የሚባል ሕዝብ ነበረ ኣሁንም ኣለ፡፡ ትግራይና ኦሮሞ የሚባሉ ብሄሮች (በሳቸው ኣባባል ጎሳዎች) ከነበሩ ኣማራም የማይኖርበት ምክንያት ኣይኖርም፡፡

ፕሮፌሰሩ ወረድ ብለው ደግሞ “ክርክሩ መሆን ያለበት የወልቃይት ኣውራጃ ከጎንደር ክልል ወጥቶ ወደ ትግራይ የገባበት መንገድ ትክክል ኣይደለም ፡፡ የኣስተዳደር ለውጡ የተፈፀመው የፌዴራል መዋቅሩን ሰርኣት በጣሰ መንገድ ኣንዱ ክልል (ትግራይ) በሌላው ክልል ላይ የጉልበተኛነት ኣካሂዷል” ይላሉ፡፡

እዚህ ላይ ፕሮፌሰሩ የፌዴራል ኣወቃቀሩን የሚያምኑበት ከሆነ የትኛው የፌዴራል ስርኣት እንደተጣሰ ኣይገልጹም፡፡ ኣንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ወልቃይቶች ኣማርኛ ተናጋሪ ሆነው ሳለ በግድ ወደ ትግራይ ተካለሉ የሚል መከራከርያ ነው እንዳንል ደግሞ ፕሮፌሰሩ መልሰው “እዚህ ላይ ጥያቄው የወልቃይት ወረዳ ወይም ኣውራጃ ነው፣ በውስጡ የሚኖሩ ሰዎች የጎሳ ኣይነት የጎሳ ስብጥር ኣይደለም” ይላሉ፡፡ በርግጥ በፌዴራል ስርኣቱ ኣከላለል መሰረት ኣድርገን እንከራከር ካልን በመጀመርያ የሚመጣው የወልቃይቶች ማንነትና በተለይ ደግሞ ቋንቋ ምንድን ነው የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ሰውዬው ራሳቸውና የነበሩበት የትምህርት ክፍል እንዲሁም የደርግ ስርኣት ያወጡት የኣካባቢው የቋንቋ ስብጥር ካርታ ላይ ወልቃይት በዋናነት ትግርኛ ተናጋሪ ህዝብ መሆኑን ስለሚያሳይ (ኣማርኛ ተናጋሪዎች የሉም ማለት ግን ኣይደለም) በዚህ ክርክር መቀጠል ኣልፈለጉም- እናም ውስጡ የፈለገ ኣይነት ጎሳ ይኑር ጉዳዩ የግዛት (በደርግ ጊዜ የነበረ ኣስተዳደር) የማስመለስ ጥያቄ ነው በማለት ጉዳዩን ይሸሹታል፡፡

የፕሮፌሰሩ ግራ መጋባት (ወይ ማምታታት ልበለው) በዚሁ ኣያበቃም፡፡

ሰውዬው ይሄ ጎንደር ላይ በትግራይ ክልል የተካሄደው ወረራ (ወልቃይትን ከጎንደር ወደ ትግራይ የተካለለው) ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ መሆኑን በዚሁ መልኩ ለመግለጽ ይሞክራሉ … “ወያኔ የበቀለበትን ትግራይን ሲያይ አነሰችው፤ በዚያ ላይ በሰሜን በቂልነት ደም ከተቃባቸው ከኤርትራውያን ጋር በደቡብ ደግሞ የሥልጣን ችጋሩ ጠላት በአደረጋቸው ኢጣልያ ‹‹አማራ›› ብሎ በከለላቸው ሰዎች በጎንደርና በወሎ በኩል ታፍኗል፤ በዚያ ላይ በትግራይ ውስጥ ካለው የእርሻ መሬት የተሻለ በጎንደርና በወሎ አለ፤ ጉልበተኛ ሆኖ መቸገር አይበጅምና በጊዜ፣ በጠዋቱ ከጎንደርም ቀንጨብ፣ ከወሎም ቀንጨብ አደረገና አበጠ” ይሉናል፡፡ እዚህ ላይ ሰውዬው ኣርጅተዋል ብለን ከማለፍ ውጪ ባልሆነ ነገር ላይ መከራከር ከንቱ ልፋ ነው፡፡

የወልቃይት ጉዳይን በተመለከተ ኣንድ ግልፅ ያልሆነ ነገር ኣለ፡፡ ጥያቄው የማንነት ጥያቄ ነው ወይስ የድሮ (በደርግ ጊዜ የነበረውን) ግዛት የማስመለስ ጥያቄ – “ኣረሱት የሁመራን መሬት” ???

ኣንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት የወልቃይት ጥያቄ የማንነት ጥያቄ ከሆነና ወልቃይቶች ኣማራ ስለሆኑ ወደ ኣማራ መካለል ኣለባቸው የሚል ከሆነ ግልፅ ጥያቄ ነው መልሱም ቀላል ነው፡፡ መልሱ ያለው ደግሞ በወልቃይቶች እንጂ በኣማሮች ወይም በትግራዮች ኣይደለም (ሪፈረንደም ኣንድ መፍትሄ ነው)፡፡ እኛ ኣማራ ነን የሚሉ ከሆነና መልስ ኣጥተው ከሆነ እዛው ወልቃይት ውስጥ ራሳቸው ተነስተው መሰለፍና መታገል ኣለባቸው፡፡ ለምንድንው የጎንደር ወጣት ስለነሱ የሚሰለፈውና የሚሞተው? እነሱ መሰለፍ ኣይችሉም? ወይስ ኣልፈለጉም? ወልቃይት ውስጥ ኣልተፈቀደላቸዉም ከሆነ ጎንደር ላይ ያሉትም በራሳቸው እንጂ የተፈቀደላቸው ኣይመስለኝም፡፡

በሌላ በኩል ጉዳዩ እነ ፕ/ር መስፍን እንደሚሉት የወልቃይት ጥያቄ ውስጣቸው የፈለገ ኣይነት ጎሳ ወይም የጎሳ ስብጥር ይኑር በደርግ ጊዜ የነበረ ግዛት የማስመለስ ጥያቄ ከሆነ (በርግጥ ጎንደርም፣ባህርዳርም፣ ዲሲም የሚነሱ ጥያቄዎች ይሄንን ያሳያሉ) ኣሁን ካለው ህገ-መንግስትና የክልሎች ኣወቃቀር ስርኣት (ማንነት ቋንቋ ላይ ያተኮረ) መያያዝና መቀላቀል የለበትም፡፡ በዚሁ መከራከርያ ከሄድን ደግሞ የድሮ ግዛቶችን ከትግራይ ብቻ ሳይሆን ከኣፋር (የድሮ ወሎና ሸዋ) ከቤኒሻንጉል (የድሮ የጎጃም ግዛት መተከል)፣ ከኦሮሚያና ደቡብ (የድሮ ሸዋ ክፍለሃገር) የተወሰዱ መሬቶች ውስጣቸው የፈለገ ኣይነት የጎሳ ስብጥር ይኑረው መመለስ ኣለባቸው ማለት ነው፡፡ ይሄንን ለማድረግ ደግሞ ብቸኛው መፍትሄ ኣሁን ያለውን ስርኣት (የፌዴራል ስርኣቱና ወያኔ) ኣስወግዶ የክልሎችን ኣወቃቀር ወደ ድሮ መመለስ ነው፡፡

ግራ የገባው የፕሮፌሰሩ ፅሁፍ እዚህ ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡

***********

Jossy Romanat

Jossy Romanat

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago