ኢህአዴግ አሸነፈም ተሸነፈም ለውጥ አይመጣም

ሀገራችን ኢትዮጲያ ወደፊት ወይም ወደኋላ በሚወስድ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች። የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በኪራይ ሰብሳቢዎች ታግቷል፣ የመንግስት መዋቅር በኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና ተተብትቧል፣ ህዝቡ በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር እጦት ተማሯል። ችግሮቹ በዋናነት በፖለቲካ አመራሩ ብቃት-ማነስ ምክንያት የተፈጠሩና የተባባሱ ናቸው። በሌላ በኩል፣ ችግሮቹ በፖለቲካ አስተዳደር ስርዓቱ ውስጥ ግልፅነትና ተጠያቂነት በማስፈንና የአመራሩን አቅም በማጎልበት የሚፈቱ ናቸው። ስለዚህ፣ የችግሮቹ መንስዔና መፍትሄ ያለው ከአስተዳደሩ እና አመራሩ ጋር የተቆራኘ ነው።

ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች፣ በተለያዩ የውይይት መድረኮች የሚሰነዝሯቸው ሃሳቦች፣ የሚሰጧቸው አስተያየቶች፣ እንዲሁም የሚፈፅሟቸው አንዳንድ ተግባራትን በጥሞና ለሚያጤን ሰው ከፍተኛ ግራ-መጋባት ውስጥ እንደሆኑ ይገነዘባል። ምክንያቱም፣ አመራሩ ራሱ የችግሩ መንስዔ በሆነ የአስተዳደር ስርዓት ውስጥ፣ ቀድሞ ከነበረበት የብቃት-ማነስ ችግር ሳይላቀቅ ለሀገሪቱ መዋቅራዊ ችግሮች መፍትሄ እየፈለገ ስለሆነ ነው። ኢህአዴግ ቀድሞ ችግሩን ከመገንዘብ በጋረደው አመለካከት ውስጥ ሆኖ መፍትሄውን እየፈለገ ነው።

ለችግሩ መንስዔ በነበረው አሰራር፣ አመራርና አመለካከት ውስጥ ሆኖ መፍትሄውን መፈለግ አይቻልም። በመሆኑም፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን ከጭፍን የፖለቲካ ድጋፍ ወይም ተቃውሞ በፀዳ መልኩ በችግሮቹ ዙሪያ በዕውቀት ላይ የተመረኮዘ ትንታኔ መስጠት ይጠበቅባቸዋል። ሆኖም ግን፣ በፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያላቸው ምሁራን በጣት የሚቆጠሩ መሆናቸው እንዳለ ሆኖ፣ እነሱም ችግሮቹን ከመዘርዘር ባለፈ የመፍትሄ ሃሳቦችንና አቅጣጫዎችን ሲጠቁሙ አይታዩም።

ሀገራችን በዚህ ሁኔታ ለተወሰነ ግዜ የምትቀጥል ከሆነ አሁን ባለችበት የመስቀለኛ መንገድ ላይ ወደኋላ በሚወስደው አቅጣጫ መሄዷ አይቀሬ ነው። ከሁሉም በላይ፣ በዚህ መልኩ የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥሉ ለሚችሉ ሁለት መዋቅራዊ ችግሮች አሉ። እነሱም፡- የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ችግር እና የመልካም አስተዳደር እጦት ችግር ናቸው። ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ እነዚህ ችግሮች ደግሞ በአስተዳደር ስርዓቱና በፖለቲካ አመራሩ የአቅም/ብቃት ማነስ የተፈጠሩ እና/ወይም የተባባሱ ናቸው። ስለዚህ፣ የመፍትሄ አቅጣጫው፣ የሀገሪቱን አስተዳደር ስርዓት እና የፖለቲካ አመራሩን ‘መለወጥ’ ወይም/እና ‘ማሻሻል’ ነው።

በዚህ ውስጥ ሁለት አማራጭ መንገዶች አሉ። አንደኛ፡- “የፖለቲካ አስተዳደር ስርዓቱ በአዲስ መቀየርና አመራሩን በሌላ መተካት” ነው። ሁለተኛ፡- “የፖለቲካ አስተዳደር ስርዓቱ ማሻሻልና የአመራሩን አቅም መገንባት” የሚል ነው። በእነዚህ አማራጭ መንገዶች ላይ ግን አንድ ትልቅ እንቅፋት አለ። እሱም፡- የሀገሪቱ የሲቭል ሰርቪስ መዋቅር በፖለቲካ ተሿሚዎች መመራቱ ነው። ከሞላ-ጎደል ሁሉም የሀገሪቱ የሲቪል-ሰርቪስ ተቋማት በዘርፉ ባለሞያዎች ሳይሆን በፖለቲካ ተሿሚዎች መመራታቸው ለሀገሪቱ ለውጥና መሻሻል ዋና እንቅፋት ነው።

የፌዴራል መስሪያ ቤት ሃላፊዎች፥ ሚንስትሮች፥ ሚኒስትር ዲኤታዎች፥ ዳይሬክተሮች፣… የክልል ቢሮ ሃላፊዎች፣ የክልል ተቋማት ሃላፊዎች፣… የዞን መምሪያ ሃላፊዎች፣ የወረዳ ፅ/ቤት ሃላፊዎች፣ የከተማ ከንቲባዎች፥ ስራ አስኪያጆች፥ የከተማ ፅ/ቤት ሃላፊዎች፥ የክፍለ ከተማ ስራ አስኪያጆች፣ የቀበሌ ሊቀመንበርዎች፣ …የሥራ ክፍል ሃላፊዎች፣… በአጠቃላይ ከፌደራል እስከ ቀበሌ ያለው የመንግስት መዋቅር በገዢው ፓርቲ አባላት አመራር ስር ነው። ከዚያ በተጨማሪ፣ በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና የልማት ድርጅቶች ሃላፊዎች፣… ሌላው ቀርቶ በትምህርቱ ዘርፍ እንኳን፤ የዩኒቨርሲቲ ፕረዜዳንቶች፣ የማሰልጠኛ ተቋማት ሃላፊዎች፣ የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተሮች ሳይቀሩ የኢህአዴግ አባላት ናቸው። እስኪ የችግሩን አስከፊነት የበለጠ ለመረዳት የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት ካላቸው ሀገራት አንፃር ጉዳዩን አንመልከት።

በአሜሪካን ሀገር አዲስ ፕረዜዳንት በምርጫ አሸንፎ ወደ ስልጣን ሲመጣ 7000 የፖለቲካ ተሿሚዎች ይኖሩታል። ስለዚህ፣ በአሜሪካ የመንግስት አስተዳደር ለውጥ ማለት የ7000 አመራሮች ለውጥ ነው። እንዲህም ሆኖ ግን፣ በምርጫው ያሸነፈው ፕረዜዳንት ስልጣኑን ተረክቦ ሙሉ-ለሙሉ የማስተዳደር ስራውን እስኪጀምር የ75 ቀናት (የሁለት ወር ከግማሽ) ያህል የሽግግር ግዜ ይኖረዋል። ይህ፣ በአለም የተዋጣለት የሲቭል ሰርቪስ አገልግሎት ካላት እንግሊዝ አንፃር ሲታይ በጣም ረጅም ግዜና የብዙ የአመራሮች ለውጥ ነው።

አንድ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር በምርጫ አሸንፎ ሀገሪቱን የማስተዳደር ስልጣን ሲረከብ ግን ለ100 (አንድ መቶ) ሰዎች ብቻ ነው የፖለቲካ ሹመት የሚሰጠው። ለእነዚህ ተሿሚዎች፣ የሲቭል ሰርቪስ ባለሞያዎችን ስራ ከፓርቲው ፖሊሲዎችና መርሆች ጋር በማሳለጥ ድጋፍ እንዲያደርጉ ከሚቀጠሩ ልዩ አማካሪዎችን (Special Advisors) ጋር፣ በጠቅላላ በእንግሊዝ የፖለቲካ ተሿሚዎች ቁጥር ከ150 (አንድ መቶ ሃምሳ) አይበልጥም። ይህ እንግሊዝን፣ ከየትኛውም ሀገር በተሻለ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ የስልጣን ሽግግር እንዲኖራት አስችሏታል። የምርጫው ውጤቱ በታወቀ በሰዓታት ውስጥ አዲሱ የእንግሊዝ ጠ/ሚኒስትር ስልጣኑን ተረክቦ ሀገሪቱን የማስተዳደር ይጀምራል።

በኢትዮጲያ ውስጥ የመንግስት አስተዳደር ለመቀየር ግን በቡዙ ሺህ የአመራር ቦታዎች ላይ ለውጥ መደረግ አለበት። ለምሳሌ፣ አንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አሸንፎ ስልጣን ቢይዝ የሀገሪቱን የሲቪል ሰርቪስ መዋቅር ሙሉ-በሙሉ አፍርሶ እንደ አዲስ መገንባት ይጠበቅበታል። በመዋቅሩ ውስጥ በአመራርነት ላይ ያሉት ከሞላ-ጎደል ሁሉም የገዢው ፓርቲ አባላት ናቸው። በቀጣይ የኢትዮጲያ ፖለቲካ መዋቅራዊ የሆኑ ችግሮች፡- በኪራይ ሰብሳቢነት እና የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ላይ ቁርጠኛ የሆነ አቋም የሌለው ተቃዋሚ ፓርቲ ወደ ስልጣን ሊመጣ አይችልም። ፓርቲው ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ፣ አሁን ያሉትን የኢህአዴግ አባላት እንደ ማንኛውም የሲቭል-ሰርቪስ ሰራተኛ በአመራርነት ሚናቸው እንዲቀጥሉ ካደረገ የራሱን የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀም ይሳናዋል። ምክንያቱም፣ ሲጀመር ኢህአዴግ ለሽንፈት የዳረገው የእነዚህ አመራሮች የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት እና የአስተዳደር አቅም/ብቃት ማነስ ነው’ና። ነገር ግን፣ የትኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ እነዚህን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አመራሮች በአዲስ የፖለቲካ ሹመኞች ለመተካት አቅምና አደረጃጀት የለውም። ስለዚህ፣ አንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት በምርጫ አሸንፎ ወደ ስልጣን ቢመጣ የራሱን የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀም አይችልም። 

ኢህአዲግ’ም “አስተዳደሩን አሻሽላለሁ፣ የአመራሮቼን አቅም እገነባለሁ” ቢልም፣ የሀገሪቱን የሲቭል ሰርቪስ መዋቅር እንደ አዲስ አፍርሶ ከመገንባት ውጪ ግን አማራጭ የለውም። ምክንያቱም፣ አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጲያ መንግስት እና የኢህአዴግ ፓርቲ መዋቅር ፈፅሞ መለየት በማይቻልበት ደረጃ ተዋህደዋል። የሀገሪቱ ሲቭል ሰርቪስ በራሱ ሥራና የሞያ መርህ፣ መመሪያና ደንብ መስራት አቁሞ በገዢው ፓርቲ ጥላ ስር ወድቋል። በተለይ ከማስፈፀም ብቃት ይልቅ ለታማኝነት ቅድሚያ የሚሰጠው የፓርቲው መርህ፣ የሀገሪቱን ሲቭል ሰርቪስ በቂ የአመራር ብቃትና ክህሎት፣ እንዲሁም የሞያ ስነ-ምግባር በሌላቸው ሰዎች ስር እንዲወድቅ አድርጎታል። እነዚህ አመራሮች በራሳቸው የማይገባቸውን ጥቅምና ሃላፊነት የተሸከሙ ኪራይ ሰብሳቢዎች ስለሆኑ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትን ለመታገል አቅሙ ሆኑ ቁርጠኝነቱ የላቸውም። በተመሳሳይ፣ አሁን ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር የፈጠሩት እነሱ እንደመሆነቸው፣ በቀጣይ መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት’ም እንቅፋት ናቸው።

በአጠቃላይ፣ የኢትዮጲያ ፖለቲካ ወደፊት እንዲራመድ ከተፈለገ፣ የሲቭል ሰርቪሱ አመራር ከፖለቲካ ተሿሚዎች ነፃ ማድረግና የተቋማቱን ስራ ለባለሞያዎች መተው የግድ ነው። ይህ ካልሆነ ግን፣ ኢህአዲግ ተሸንፎ፣ ተቃዋሚ’ም አሸንፎ ለውጥ አይመጣም።

************

8.560328437.9890155
Seyoum Teshome

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago