ጋምቤላ ክልል እና ብሄራዊ የፀጥታ ስጋት – ኣጭር ቅኝት

በደርግ ዘመነ መንግስት በጆን ጋራንግ የሚመራው የደቡብ ሱዳን ነፃ ኣውጪ (SPLM) በጋምቤላ ክልል ወታደራዊ ካምፖች ነበሩት። ኢህኣደግ ደርግን ላይመለስ ሲገረስስ የSPLM እጣ ፈንታ ኣገር ለቆ መውጣት ወይ ድግሞ ትጥቁን ኣራግፎ ስደተኛ ካምፕ ገብቶ መኖር ነበር። በወቅቱ ሁለቱም ኣማራጮች የሚዋጡለት ስላልነበሩ ከባሮ ወንዝ ወዲያ ያለው የጋምቤላ (የኢትዮጵያ) ግዛት የራሴ ነው በማለት በቁጥጥሩ ስራ ማዋልን መረጠ። ደርግ እያለም ሲወድቅም ያስታጠቀው የጦር መሣሪያ በመጠቀም ኢህኣደግ ድልድዩን ተሻግሮ ግዛቱን እንዳይቆጣጠር የተቻለውን ያክል ጥረት ኣደረገ። SPLM ከሰራዊቱ በተጨማሪ በጋምቤላ የነበሩ የደርግ ሰራዊት ኣባላት፣ የክልሉ ታጣቂ ምልሻዎች (ኢትዮጵያዊያን) ከጎኑ በማሰለፍ ለመዋጋት ሙከራ ኣድርጎ ነበር። ነገር ግን የኢህኣድግ ተዋጊዎችን ሊቋቋም ስላልቻለ በሽሽት ላይ ሆኖ በወቅቱ በኢትዮጵያ ረጅሙ የነበረውን የባሮ ድልድይ በከባድ መሳሪያ ሊያፈርስ ሞከረ፣ ግን የተሰነዘረበት ጥቃት ከባድ በምሆኑ እግሬ ኣውጪኝ ብሎ ወደ ደቡብ ሱዳን ኣቅጣጫ ፈረጠጠ።

በዚህ ወቅት የተወሰኑ የSPLM ኣባላት የስደተኞች ካምፕ ትጥቅ ፈተው የገቡ ሲሆን ከኣንዳንድ የጋምቤላ የደርግ ታጣቂዎች ጋር በመሆን በኣስገዳጅ ሰፈራ ተወስደው የሰፈሩትን ’’ኣበሻ’’ ብለው በሚጠሯቸው ወገኖች (ትግራይ፣ ኣማራ፣ ኦሮሞ፣ ከምባታ ወዘተ) ላይ ኣሰቃቂ ጭፍጭፋ ፈጸመው ከኣንድ ሺህ (1000) በላይ ዜጎችም ተገደሉ፣ ብዙዎችም ሞትን ሲሸሹ ኣውሬ በላቸው፣ በጣም ጥቂት የሚባሉም ድንብር ኣቋርጠው ሰሜን ሱዳን ገቡ። ይህ ጥቃት በተፈፀመበት ኣካባቢ የኢህኣደግ ሰራዊት ገብቶ ቀሪውን ህዝብ ለመታደግ ችሏል።

ኢህኣደግ ኣልበሽር ከሚመራው የሱዳን መንግስት ጋር ወታደራዊ ግጭት እስካጋጠመው ድረስ የጆን ጋራንግ ሰራዊት ዋናው ማዘዣ ጣቢያው ከነበረው ጋምቤላ ሽሽቶ በገባበት ኡጋንዳ እና የደቡብ ሱዳን ጫካዎች ሆኖ ቆይቷል። በ1980ቹ ዓ.ም. ኣጋማሽ ላይ ኢትዮጵያና ሰሜን ሱዳን በድንበር ምክንያት በተጋጩበት ጊዜ ግን ጆን ጋራንግ በድንበር ኣካባቢ መንቀሳቀስ ሳይፈቀድለት ኣልቀረም። ቢያንስ ከየኢትዮጵያ መንግስት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ለማድረግ በቅቷል። በደቡብ ሱዳኖች እና በኢትዮጵያ መንግስት የነበረው ሁኔታ በእንዲህ መልኩ ሲጠናቀቅ የጋምቤላ የውስጥ ጉዳይ ግን ኣሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል።

Map – Gambella, Ethiopia

መንግስት ቀደም ሲል ወንጀል የፈፀሙትን (ብዙ ንፁሃን የገደሉ) የክልሉ ተወላጆች ችላ ብሎ የተወ ሲሆን ኣገር ውስጥ እና ወደ ውጭ ኣገር የሸሹ ኣኩራፊ ኣሊያም ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች ግን መኖራቸው ይታወቃል። በመሆኑም በሂደት ትልልቅ ችግሮች ሆነው የቀጠሉ ሶስት ነገሮች ተፈጠሩ። ፩ኛ፣ በኣኙዋክ እና በኑዌር ብሄረሰቦች ያለመስማማት እስከ ግጭት የሚሄዱ ችግሮች ፪ኛ፣ ከሁለቱም ብሄረሰቦች ያሉት ኣኩራፊ ግለሰቦች ’’ኣበሻ ከክልላችን ይውጣ’’ እያሉ በተደጋጋሚም የግድያ ወንጀል የመፈጸም ሁኔታ ስለቀጠለ መንግስት ብዙ ጊዜ ጣልቃ ለምግባት የተገደደበት ሁኔታ ፫ኛ፣ መሬት ለኢንቨስትመንት ከማዋል ጋር የተያያዙ ችግሮች ናቸው። እነዚህ እና ሌሎች ከመልካም ኣስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖራቸው ሲታወቅ (ከም ሃገሮም) ክልሉ ኣሳሳቢ የፀጥታ ችግር እንዳለበት ይታወቃል።

እንደተባለው ከውስጥ ችግሩ በተጨማሪ በመቶ ሺዎች (284,000) የሚቆጠሩ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችም የሚኖሩበት፣ የድንበር ተሻጋሪ የጎሳ ግጭት እና ከብቶች መሰራረቅ የሚፈጸምበት፣ በእርዳታ ሰጭነት ስም ብዙ የውጭ ሃይሎች የሚንቀሳቀሱበት፣ የክልሉ የተፈጥሮ ሃብት ላይ ፍላጎት ያላቸው የምዕራቡ ኣለም ተዋናዮች የሚንቀሳቀሱበት፣ ሻዕቢያን ጨምሮ ሌሎች ፀረ ሰላም ሃይሎች የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ የሚሞክሩበት ክልል ነው።

ይህ እንዳለ ሆኖ በደቡብ ሱዳን ያለው የውስጥ ሰላም የማጣት ሁኔታም ጦሱ ለኢትዮጵያ ሳይተርፍ ኣልቀረም። ሰሞኑን በኢትዮጵያዊያን ላይ የተፈፀመው ዘግናኝ ጭፍጨፋም በደቡብ ሱዳን ያለው ስርኣት ኣለበኝነት ኣንደኛው ምክንያት ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታና የመከላከያ ሃይሎች ደካማነትም ኣስተዋጽእ ኣድርገዋል ማለት ይቻላል። የመከላከያ ሰራዊታችን የምዕራብ እዝ ኣብዛኛውን የምዕራቡ የኣገሪቱ ድንበር ለመጠበቅ ሃላፊነት የተሸከመ ኣካል ነው። ይህ በጀነራሎች የሚመራው ግንባር ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ያለበት ክልል/ድንበር የሌላ ኣገር ታጣቂ ቡዱኖች መጥተው እንዲህ ኣይነት ወንጀል እስኪፈፅሙ ምን እየጠበቀ እንደነበር መንግስት የማጣራት ስራ ሰርቶ በሃላፊነት የሚጠየቁ የስራ ሃላፊዎች ሊኖሩ ይገባል።

በጋምቤላ ክልል ከፍ ሲል የተጠቀሱት ሊፈቱ ያልቻሉ ውስብስብ የፀጥታ ችግሮች መኖራቸውን እየታወቀ፣ ድንበር ተሻጋሪ የጎሳ ግጭቶች/ችግሮች እንዳሉ ግልፅ ሆነ ሳለ፣ የደቡብ ሱዳን የውስጥ ግጭት ለኢትዮጵያም የተረፈ መሆኑ እየታወቀ፣ በክልሉ ከመቶ ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች እንደሚኖሩ እየታወቀ፣ በጋምቤላ ክልል እና በደቡብ ሱዳን ለብሄራዊ ፀጥታችን ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ የተለያየ ጭምብል የለበሱ የውጭ ሃይሎች መኖራቸውን እየታወቀ፣ በሁለቱም ሱዳኖች ሰላም ያለመኖር በኢትዮጵያ ላይ ተፅእኖ እንዳለው እየታወቀ፣ ሻዕቢያ ብንግድ ስም ያሰማራቸው ዜጎቹ በደቡብ ሱዳን እና ኡጋንዳ በስፋት የሚንቀሳቀሱበት ቀጠና መሆኑ እየታወቀ፣ ሻዕቢያ የሚያንቀሳቅሳቸው የጋምቤላ እና የቤንሻንጉል ኣማፂ ነን የሚሉ ቡዱኖች እንዳሉት እየታወቀ፣ ግብፅ ከደቡብ ሱዳን ጋር ወታደራዊ ትብብር የማድረግ እንቅስቃሴ እንዳላት ግልፅ ሆኖ ሳለ፣ ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት የብሄራዊ ፀጥታ ኣደጋ መሆኑን ተገንዝቦ ለሁኔታው የሚመጥን ዝግጅት ኣለማድረጉ እጅግ ኣሳሳቢ ነው።

ባለፉት ኣመታትና በዓፋር ክልል በቅርቡም በትግራይ በሻዕቢያ የተፈፀሙት ድንበር ዘለል ጥቃቶች የዚህ ድክመት መገለጫዎች ናቸው። ማነኛውም ሃይል ከጎረቤት ኣገር ድንበር ጥሶ በመግባት ጥቃት መፈፀም እንደሚቻል ማረጋገጫ ናቸው። ይህ በድንበር ለሚኖሩ ህዝቦች እጅግ ኣስፈሪ እና ሊያስተኛ የማይችል የፀጥታ ኣደጋ ነው። በድንበር ኣካባቢ የሚኖሩ በሚሊዮን የሞቆጠሩ ህዝቦች ያላት ኣገር፣ በየኣካባቢው ሜጋ ፕሮጀክቶች ያሏት ኣገር፣ ከበቂ በላይ የሆኑ የውስጥና የውጭ የፀጥታ ስጋቶች ያሏት ኣገር፣ በሰላም ኣስከባሪነት ሰራዊቷ በየኣገሩ የምትልክ ኣገር የራሷ ፀጥታ በተገቢ ሁኔታ ማስከበር ይጠበቅባታል እንላለን።

መልካም ሳምንት!
ገብረ ሥላሴ ኣርኣያ
************

ሰሞኑን በተፈፀመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ሂወታቸው ላለፉት ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ነብስ ይማር፣ ለቤተሰቦቻቸውም ፅናቱን ይስጥ!

Gebre Selassie Araya

ገብረ ሥላሴ ኣርኣያ ኣብ ሃገራዊን ዞባዊን ከምኡውን ዓለም ለኻዊ ፖለቲካ ጉዳያት ዝከታተል፣ ኣብዝኾነ ፖለቲካዊ ውዳበ ዘይነጥፍ ውልቀ ሰብ እዩ። ንሃናፃይ ሪኢቶ ኣብ gebreselassiea@yahoo.com

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago