ኢህአዴግ – ከለውጥ እና ከሞት አንዱን ምረጥ

ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህብረሰብ ሊሰጥ የታቀደው ስልጠና ዛሬ ላይ ተጀምሯል። ለስልጠናዉ ከተዘጋጁ ሰነዶች ውስጥ የመጀመሪያው “የሩብ ምዕተ ዓመታት የልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጉዞ…” የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል። በመረሃ-ግብሩ መሰረት ጠዋት ላይ በአሰልጣኞቹ ገለፃ ሲሰጥ እንደተለመደው በአሰልጣኝነት የተመደቡት የመንግስት ኃላፊዎች ለታዳሚው የሚመጥን ስልጣና ለመስጠት የአቅምና ክህሎት ችግር እንዳለባቸው በግልፅ ያስታውቃል። ይህ ግን ላለፉት አስር አመታት የታዘብኩት ነገር ስለሆነ ብዙም አላሳሰበኝም። ከዚያ ይልቅ ትኩረቴን ሰነዱ ላይ አድርጌ ነበር። 

ለውይይቱ የቀረበው ፅሁፍ ላለፉት 25 ዓመታት የተመዘገቡ አንኳር አገራዊ ለውጦችን በመዘርዘር ይጀምራል። የሚቀጥለው ንዑስ-ክፍል ደግሞ በሀገሪቱ እየታዩ ያሉ ፈተናዎችንና መፍትሄዎቻቸውን ይዘረዝራል። እዚህ ጋር ስደርስ ግራ ገባኝ። ማንበቤን አቁሜ በዙሪያዬ የተቀመጡትን መምህራን ስመለከት ሁሉም ገለፃውን በቸልተኝነት እየተከታተሉ ነው። ከምሳ በኋላ ግን በእኔ ውስጥ የነበረው ግራ-መጋባት በሁሉም ፊት ላይ በግልፅ መታየት ጀመረ።

ከሰዓት በኋላ በነበረን ውይይት ሲነሱ የነበሩት ጥያቄዎች በሙሉ በስልጠናው ስለተነሱ ሃሳቦች ላይ ሳይሆን በስልጠናው አግባብነት ላይ ብቻ ያተኮሩ ነበሩ። ሊደረግ የታሰበው የውይይት ፕሮግራም ስለ ውይይቱ በመወያየት ላይ ብቻ ታጥሮ ቀረ፡፡ ለዚህ ደግሞ “እየታዩ ያሉ ፈተናዎችንና መፍትሄዎቻቸው” በሚለው ስር ከተዘረዘሩት ሃሳቦች የሚከተለው በዋናነት የሚጠቀስ ነው፡-

“ባለፉት ሃያ አምስት አመታት የነበሩ የመልካም አስተዳደር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር፣ የትምክህትና ጠባብነት አደጋዎች እንዲሁም ሃይማኖትን ሽፋን የሚያደርገው አክራሪነት ፈተናዎች አሁንም ቅርፃቸውን ቀይረው ወይም በሌላ ተተክተው ስላሉ ፈተናዎቹን ለማለፍ የተከተልናቸውን ስልቶች ይበልጥ አጠናክረን ያገራችንን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማደናቀፍ ወደ የማይቻልበት ደረጃ ማድረስ አስፈላጊ በመሆኑ…”
የከፍተኛ ትምህርት ማህብረሰብ ሥልጠና ለ2009 ትምህርት ዘመን ዝግጅት ምዕራፍ ማጠናቀቂያ፣ ትምህርት ሚኒስቴር፥ መስከረም 2009፥ ገፅ-7 

በመጀመሪያ ደረጃ የተጠቀሱት ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው በጣም ከመደጋገማቸው የተነሳ ትርጉም-አልባ ወደ መሆን ተቃራበዋል። ከዚህ በተጨማሪ፣ የተጠቀሱት ችግሮች በዋናነት ከመንግስት ኃላፊዎች ጋር የተያያዙ እንደመሆናቸው ከመምህራን ሥራና ኃላፊነት ጋር ብዙም የተያያዙ አይደሉም። በአብዛኛው ከመምህራኑ ሲነሳ የነበረው ጥያቄ ግን፤ “‘መልካም አስተዳደር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የትምክህት፣ ጠባብነትና አክራሪነት’ የሚባሉት ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ከአመት-እስከ-አመት አይቀየሩም እንዴ?” የሚለው ነበር። 

የዛሬው ስልጠና እንደተጠናቀቀ በቀጥታ ወደ ቤት በመሄድ በ2006 ዓ.ም ላይ ተሰጥቶ ለነበረው ተመሳሳይ ስልጠና የተዘጋጀውን ሰነድ ማገላበጥ ጀመርኩ። በሐምሌ ወር 2006 ዓ.ም “የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ስርዓት ግንባታ ትግላችንና ፈተናዎቹ” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ሰነድ ውስጥ የሚከተለው ሃሳብ አገኘሁ፡-

“በቅድሚያ በማንም ሊላከክ የማይችል የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ቀጥሎም ትምክህትና ጠባብነት እንዲሁም የሃይማኖት አክራሪነት እና የእነዚህ ሁሉ መንስዔ የሆነው ያለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌ (ኪራይ ሰብሳቢነት) በመፍታት የተያያዝነውን የልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጉዞ አጠናክረን ልንቀጥልበት እንደሚገባ…”
የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ስርዓት ግንባታ ትግላችንና ፈተናዎቹ፥ ሐምሌ 2006 ዓ.ም፥ ገፅ-34 

በ2006 ዓ.ም የተዘጋጀው የሥልጠና ሰነድ በሐምሌ ወር ይሁን እንጂ ስልጠናው ግን የተሰጠው እንደ ዘንድሮው በመስከረም ወር 2006  ዓ.ም ላይ ነበር። ከዘንድሮው አንፃር ሲታይ በወቅቱ ሰፋ ያለ ግዜ ተሰጥቶት እንደተዘጋጀና ብዙ ጉዳዮችን የሚዳስስ እንደነበረ መገንዘብ ይቻላል። ሆኖም ግን፣ በ2006ቱ እና በ2009ኙ ሰነዶች ውስጥ በሀገሪቱ እየታዩ ስላሉት ችግሮች በመንስዔነት ሆነ በመፍትሄነት የተጠቀሱት ነገሮች አንድና ተመሳሳይ ናቸው፡-መልካም አስተዳደር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የትምክህት፣ ጠባብነትና አክራሪነት፡፡ 

ከላይ እንደተጠቀሰው የኢህአዴግ መንግስት አመት በወጣና በገባ ቁጥር ተመሣሣይ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ የሙጥኝ ማለቱ ባለበት እየረገጠ ከመሆኑ በላይ ሌላ ነገር አያሳይም። አዎ… አሁን በሀገሪቱ እየታዩ ያሉ ፈተናዎች የኢህአዴግ መንግስት ከሕዝብ ጥያቄና የለውጥ ፍላጎት ጋር አብሮ መሄድ ባለመቻሉ የተከሰቱ ሲሆን መፍትሄዎቻቸውም ከሕዝቡ ጥያቄና ፍላጎት ጋር አብሮ መሄድ ብቻ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። 

ለምሳሌ በ2006 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ የነበረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ እንደ አምቦ ባሉ አከባቢዎች ላይ ብቻ የተወሰነ ነበር። በ2008 ዓ.ም የታየው የሕዝብ አመፅና ተቃውሞ ግን በመላው ኦሮሚያ የተስፋፋ ከመሆኑም በላይ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በመቋረጥ እንኳን ሊገታ አልቻለም። ከዚህ ይልቅ፣ የተቃውሞ እንቅስቃሴው ወደ አማራ ክልል በመስፋፋቱ ለሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ስጋት እየሆነ መጥቷል። ከኦሮሚያና አማራ ክልሎች በተጨማሪ በደቡብ ብሔር፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጭምር እየተስፋፋ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።  

በእርግጥ እንደ ኢህአዴግ አገላለፅ፣ ከሁለት አመት በፊት ሆነ ከሁለት አስርት አመታት በፊት ለሀገሪቱ ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ፈተና የሆኑት ችግሮች አንድና ተመሳሳይ ናቸው፡፡  ነገር ግን፣ ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ ብቻ እንኳን በሀገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ የታየው ለውጥ የሩብ ምዕተ አመታት ያህል ልዩነት አለው። ሕዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችና እያሳየ ያለው የለውጥ ፍላጎት ከእለት-ወደ-እለት እየተቀያየሩና እየጨመሩ መጥተዋል። በዚህ ፈጣን የለውጥ ሂደት ውስጥ ባለበት የቆመ ብቸኛ አካል ቢኖር ኢህአዴግ ነው። 

ከወራት በፊት ባወጣሁት ፅሁፍ የኢህአዴግ መንግስት ባለበት የቆመና ከሕዝቡ የለወጥ ፍላጎት ጋር አብሮ መሄድ የተሳነው እንደሆነ ለመግለፅ ሞክሬ ነበር። ነገር ግን፣ በወቅቱ ይህን ያልኩት ‘ኢህአዴግ ከሕዝቡ ጋር በሚፈለገው ፍጥነት የመጓዝ ችግር አለበት’ ከሚል እሳቤ እንጂ ‘እንዲህ እንደ አሁኑ ባለበት ተቸንክሮ፥ ተቀርቅሮ ይቀራል’ የሚል ግምት ግን አልነበረኝም። አሁን ላይ ግን ይበልጥ እያሳሰበኝ ያለው ነገር፣ ኢህአዴግ ከሕዝቡ ጥያቄና ፍላጎት ጋር አብሮ መሄድ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን በዚህ ምክንያት የሀገሪቱ ዜጎች ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ እየወደቀ መምጣቱ ነው። 

3ኛው ማዕበል በሚለው ፅሁፍ የአሁኗ ኢትዮጲያ ሁኔታ ከ30 አመት በፊት በደቡብ ኮሪያ ከነበረው ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ሁኔታ አንፃር ዝርዝር ትንታኔ ለመስጠት ሞክሬያለሁ። በአጭሩ ለማጠቃለል ያህል፣ ከ1984 – 1994 ዓ.ም ባሉት የመጀመሪያ አስር አመታት የመንግስት ዋና ትኩረት የሚሆነው አዲስ የተገነባውን ስርዓት ህልውና ማረጋገጥ (Survival) ላይ ነበር። በመቀጠል ከ1995 – 2005 ዓ.ም ባሉት አስር አመታት ደግሞ በሀገሪቱ ኢኮኖሚና የመሰረተ-ልማት ግንባታ ረገድ እምርታ የሚታይበት የእድገት (Growth) ዘመን ነው። ከ2005 – 2015 ዓ.ም ባሉት አስር አመታት ደግሞ የልማት (Development) ዘመን ሲሆን አራተኛውና የመጨረሻው ዘመን ደግሞ በሁሉም አቀፍ የዳበረ የፖሊቲካዊ-ኢኮኖሚ ሥርዓት በመገንባት ብልፅግናን (Evolution) መቀዳጀት ነው። 

ባለፉት ሃያ አምስት አመታት የኢህአዴግ መንግስት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተጠቀሱትን ከሞላ-ጎደል አሳክቷል ማለት ይቻላል። ነገር ግን፣ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ከተጠቀሰው ልማት (Development) አንፃር ግን አስፈላጊውን ለውጥና መሻሻል ከማምጣት አንጻር የመጀመሪያውን እርምጃ እንኳን ለመራመድ ተስኖታል።

በ3ኛው ማዕበል የሚነሳው ዋና የሕዝብ ጥያቄና ፍላጎት ከዜጎች ነፃነት እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጋር የተያያዘ ነው። በ2ኛ ደረጃ ላይ የተመዘገበው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትና የመሰረተ-ልማት መስፋፋት የአብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ንቃተ-ህሊና ያጎለብቷል። በዚህም፣ ስለ ዜጎች መብትና ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ እንዲሁም የሕግ-የበላይነትና ሌሎች ዴሞክራሲያዊ እሴቶች የጋራ ግንዛቤ ተፈጥሯል። ከዚህ አንፃር፣ የመንግስት ሥራና አሰራር ከሕዝቡ ጥያቄና የለውጥ ፍላጎት ጋር አብሮ መጓዝ መቻል አለበት። እ.አ.አ በ1987 ዓ.ም የደቡብ ኮሪያ መንግስት በዚህ ወሳኝ የለውጥ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረ ሲሆን በትክክለኛው ግዜ ተገቢውን ምላሽ መስጠት በመቻሉ ሀገሪቱን ዛሬ ላይ ከደረሰችበት የብልፅግና ደረጃ እንድትደርስ አስችሏታል።

በተመሣሣይ፣ ዛሬ ላይ ኢትዮጲያ በተመሳሳይ ወሳኝ የለውጥ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በአሁን ላይ የኢትዮጲያ የሕዝብ ጥያቄ ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትህ ናቸው። በሕዝቡ ዘንድ ያለው የለውጥና መሻሻል ፍላጎት የዜጎች መብት፣ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚረጋገጥበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመግንባት ላይ ያነጣጠረ ነው። እዚህ ጋር የኢህአዴግ መንግስት ሁለት አማራጮች አሉት።

የመጀመሪያው አማራጭ ከሕዝቡ ጥያቄና የለውጥ ፍላጎት ጋር አብሮ በመጓዝ የሀገሪቱን የልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ማሸጋገር። ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ በሕዝቡ ዘንድ እየተነሳ ያለውን ጥያቄና የለውጥ ፍላጎት በማፈን የተሻለ ሕይወት የመኖር ተስፋን ማጨለም ነው። በሁለተኛው መንገድ የብዙ ንፁሃን ዜጎችን ሕይወትን በመስዕዋትነት የሚጠይቅ ከመሆኑ በስተቀር እንደ ማንኛውም አምባገነናዊ ሥርዓት መጨረሻው ውድቀት ነው።

አሁን በሀገራችን እያታዩ ያሉት ችግሮች መሰረታዊ መንስዔያቸው የኢህአዴግ መንግስት በሕዝቡ ዘንድ ካለው የለውጥና መሻሻል ፍላጎት ጋር አብሮ መሄድ ባለመቻሉ ምክንያት የተከሰቱ ናቸው። ችግሩ አንድ እንደመሆኑ መጠን መፍትሄውም አንድና አንድ ነው። የኢህአዴግ መንግስት ከሕዝቡ ጥያቄና የለውጥ ፍላጎት ጋር አብሮ መለወጥ ወይም እንደ ማንኛውም አምባገነናዊ ሥርዓት ውድቀትን መጎንጨት ይሆናል። በአጠቃላይ፣ የኢህአዴግ መንግስት በተለይ በዚህ አመት የሚወስደው እርምጃ ወይ ለለውጥ ወይም ደግሞ ለሞት ይዳርገዋል፡፡

*********

8.550175737.9839584
Seyoum Teshome

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago