እኛ እኮ ውድድር አንወድም፣ ፉክክር እንጠላለን! እኛ መወዳደር አያስደስተንም፣ መፎካከር ያስጠላናል። በሁሉም ዘርፍ፤ በፖለቲካ፥ በማህበራዊ ሆነ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያችን ውድድር አንፈልግም፣ ፉክክር ያስጠላናል። በእርግጥ እኛ ኢትዮጲያዊያን ውድድር የማንወደው መወዳደር ስለማንፈልግ ነው። ተወዳዳሪ የማንወደው ለመወዳደር አቅም ስለሌለን ነው። ፉክክር የምንጠላው ለመፎካከር ብቃት ስለሌለን ነው። በውድድር ብንሳተፍ ከሌሎች ጋር ተፎካካሪ ለመሆን ስለማንችል ነው። በፉክክር ከሌሎች የተሻለ ነገር ለማቅረብ አቅመ ስለሌለን ነው። ውድድር የማንወደው፣ ፉክክር የምንጠላው፣ ከእኛ የተሻለ ምርጫና አማራጭ እንዲኖር ስለማንሻ ነው።

አሁን ያለውን የኢትዮጲያ ፖለቲካ ብንወስድ፣ ነፃ የሆነ ውድድርና ፉክክር የለም። መንግስት ተቃዋሚ ድርጅቶችን የሚፈልጋቸው ለቁጥር ማሟያ እንጂ ከእሱ ጋር ጠንካራ ፉክክር እንዲያደርጉ አይደለም። በዚህ ምክንያት፣ በሀገራችን የፖለቲካ ፉክክርና ተፎካካሪ አለ ለማለት አይቻልም። በነፃ የምርጫ ውድድር በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ፉክክር ከተደረገ 10 አመታት አልፈዋል። የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ከኢህአዴግ ጋር ተፎካካሪ በነበሩበት ወቅት የኢትዮጲያ ህዝብ ምርጫና አማራጭ ነበረው። አሁን ባለው የይስሙላ ውድድር ጠንካራ ተፎካካሪ የለም። በአስመሳዮች ፉክክር ነፃ ምርጫና አማራጭ ሊኖር አይችልም። ነፃ ምርጫና አማራጭ በሌለበት በራስ ፍላጎትና ምርጫ መመራት አይቻልም። በዚህም የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት አይከበርም።

እኛ ኢትዮጲያኖች ስንዝናና እንኳን ተወዳዳሪ አንወድም፣ ተፎካካሪ እንጠላለን። እስኪ የሀገራችን እግር ኳስ አፍቃሪዎች ተመልከቱ። በቅዱስ ጎዮርጊስ እና በግብፁ አል_ሃሊ መካከል የሚደረግን ጨዋታ የሚከታተል የቡና ክለብ ደጋፊ ከሀገሩ ቡድን ይልቅ ለግብፁ ክለብ መደገፍ ይመርጣል። አል_ሃሊ በሌላ ውድድር ከቡና ጋር ተወዳዳሪ ስለሚሆን አይወደውም፣ ቅ.ጊዮርጊስ ግን የቡና ተፎካካሪ ነው። የቅ.ጎዮርጊስ ተጫዋቾችን በድጋፍ ከማድነቅ ይልቅ በስድብ ማሸማቀቅ ይቀናዋል።

ከስፖርት ወደ ፊልም ብንሄድም ያው ነው። የቢሆን አለም ተረት-ተረት የሚመስል ታሪክ ያላቸው የሀገር ውስጥ ፊልሞች በእንግሊዘኛ ቋንቋ የፅሁፍ ወይም የድምፅ ትርጉም ይኖራቸዋል። ፊልሞቻችን ለውጪ ሀገር ታዳሚዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ስለሚያስችል ይህ ጥሩ ተግባር ነው። ነገር ግን፣ ለአንዳንድ የሀገራችን የፊልም ባለሞያዎች የውጪ ሀገር ፊልሞችን ወደ አማርኛ ቋንቋ ተርጉሞ ማቅረብ ኢንዱስትሪውን የሚያቀጭጭ ተግባር ነው። ምክንያቱም፣ እነዚህ ፊልሞች፣ “ትርጉም በእከሌ….” እየተባሉ፣ በዝቅተኛ የድምፅ ጥራት በትናንሽ ቪዲዮ ቤቶች እና በሲዲ ሲቀርቡና በገበያው ተወዳዳሪ ሲሆኑ አልወደዷቸውም ነበር። ቃና ቴሌቪዥን በከፍተኛ የድምፅ ጥራት ወደ አማርኛ ቋንቋ ተርጉሞ ሲያቀርባቸው ግን ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን በቁ። ጥራት የሌለውን ፊልም በውድ ዋጋ ሲመለከት የነበረው የሀገር ውስጥ የፊልም ተመልካች ጥራት ያለው ፊልምን በነፃ የመመልከት ምርጫና አማራጭ አገኘ። ምርጫና አማራጭ በሌለበት ተመራጭ መሆን የሚሹ “አንዳንድ”የፊልም ባለሞያዎች ደግሞ ተወዳዳሪ አይወዱም፣ ፉክክር ያስጠላቸዋል።

በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያችንም ቢሆን ውድድር አንወድም፣ ፍክክር ያስጠላናል። የሀገራችን ነጋዴ ተመካክሮ የምርትና አገልግሎት መሸጫ ዋጋን ይጨምራል እንጂ አይቀንስም። ለዚህ ነው፣ የአንድ ሸቀጥ መሸጪያ ዋጋ በሁሉም ቦታ ተመሣሣይ የሚሆነው። በእንዲህ ያለ ሁኔታ፣ የመሸጪያ ዋጋን በሳንቲም ደረጃ መቀነስ የሽያጭ መጠንን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ ትርፋማ ያደርጋል። ነገር ግን፣ ከሌሎች ጋር ተመካክሮ ዋጋ የጨመረ ነጋዴ በግሉ እንኳን መቀነስ አይችልም። በየግዜው በሚጨምረው ዋጋ የተማረረው ሸማች መጠንኛ የዋጋ ቅናሽ ካገኘ ፊቱን ወደዚያ ስለሚያዞር፣ ሌሎቹም ተመሣሣይ ቅናሽ እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል። ስለዚህ፣ ሥራና አሰራራቸውን በማሻሻልና ወጪያቸውን መቀነስ፣ በዚህም ምርትና አገልግሎታቸውን በዝቅተኛ ዋጋ ማቅረብና ትርፋማ ለመሆን ከመጣር ይልቅ ሌሎች ተወዳዳሪ ድርጅቶች ዋጋ እንዳይጨምሩ ለማድረግ በትጋት ይሰራሉ።

በእርግጥ አንዳንድ የመርካቶ ነጋዴዎች በጋራ ተመካክረው የመሸጪያ ዋጋን ይቀንሳሉ። ነገር ግን፣ ይህን የሚያደርጉት የተጠቃሚዎች ቁጥር ለማሳደግ ሳይሆን አዲስ ተፎካካሪ ድርጅት ወደ ገበያው ሲገባ ነው። የድርጅታቸውን አቅምና አገልግሎት ለማሳደግ ያላደረጉትን፣ አዲስ ተፎካካሪ ድርጅትን ከገባያው ከስሮ እንዲወጣ ለማድረግ ግን በጋራ በጀት መድበው ይንቀሳቀሳሉ። ምክንያቱም፣ የዚህ ሀገር ነጋዴዎች ውድድር አይወዱም፣ ተፎካካሪ ይጠላሉ። 

በመጨረሻም የተወሰኑ የመዝገበ-ቃላት ፍቺዎችን በመመልከት ሃሳቤን ልቋጭ። በእንግሊዘኛ “compete” የሚለው ቃል “competere” ከሚለው የላቲን ቃል የመጣ ሲሆን፣ ስርዖ-ቃሉ Com- “together” እና petere “to strive” ነው። በዚህ መሰረት፣ “compete” ማለት “to strive together” እንደማለት ነው። በዚህ መሰረት፣ በሁሉም ዘርፍ ውድድር ያለመውደድ፥ ፍክክር መጥላት፣ በጋራ ሆኖ ለመትጋት እና ተፎካክሮ ለመስራት አለመቻል ነው። ይህ ደግሞ፣ በሌሎች ዘንድ ተፈላጊና ተመራጭ የሆነ ነገር በማቅረብ ከመወዳደር ይልቅ ተጠቃሚዎች ሌላ አማራጭ እንዳይኖራቸው በማድረግ ላይ አተኩሮ የሚሰራ አይለውጥም፥ አይሻሻልም። በመሰረቱ፣ በራስ የተሻለ አማራጭ ሆኖ ከመቅረብ ይልቅ ሌሎች ከእኛ የተሻሉ አማራጮች እንዳይሆኑ እንቅፋት የሚሆን ውድቀት እንጂ እድገት አያመጣም።

የተሻለ ተፎካካሪ ለመሆን ያለማቋረጥ ጥረት ከማድረግ ይልቅ ተፎካካሪን የሚያደናቅፍ በበዛበት ማህብረሰብ ዘንድ እድገትና ብልፅግና አይኖርም። ውድድር የማይወድ፣ ፉክክር የሚጠላ፣ ምርጫና አማራጭ በሌለበት ብቻውን ተመራጭ መሆን የሚሻ ነው። እንዲህ ለራሱና ለሌሎች እድገት ማነቆ የሚሆን በበዛበት ዘንድ እድገትና ብልፅግና የሩቅ ሀገር ሀሜት ናቸው። እኛ ኢትዮጲያዊያን ውድድር አንወድም፣ ፉክክር እንጠላለን። እኛ  እኮ፤ አብሮ ማደግ የተሳነን፣  ለራሳችን እድገት እንቅፋት የሆንን፣…እኛ እኮ እንደዚህ ነን።

*********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories