ኢሕአዴጎችና ጽንፈኞች – ባሉበት የቆሙና ባለፈው የቆዘሙ

በሁሉም የሳይንስ ዘርፎች፤ “Nothing is static” ወይም “Change is constant” የሚል ተፈጥሯዊ ህግ አለ። በዚህ ተፈጥሯዊ ሕግ መሰረት፤ የማይቀየር፥ የማይለወጥ ነገር የለም። በሌላ አነጋገር፣ የማይቀየር፥ የማይለወጥ ወይም በቋሚነት የሚቀጥል ብቸኛ ነገር ቢኖር ራሱ “ለውጥ”ነው። ነገር ግን፣ የኢትዮጲያ ፖለቲካን በአንክሮ የሚከታተል ሰው ከዚህ ተፈጥሯዊ ህግ ውጪ የሆኑ ሁለት አካላት እንዳሉ መገንዘብ ይችላል፣ ኢህአዴጎች እና ፅንፈኞች።

በቅድሚያ፣ ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ፣ “ግልፅ ደብዳቤ ለጠ/ሚ ኃይለማሪያም” በሚል በአቶ አሰፋ ጫቦ የቀረበው ፅሁፍ ነው። በእርግጥ የግለሰቡን ቀናነትና አባታዊ ምክር አከብራለሁ። ነገር ግን፣ ሃሳቡ በደንብ ተጨምቆ ያልተጠናቀረ በመሆኑ፣ ደብዳቤው የሃሳብ ድግግሞሽ የበዛበትና ልክ እንደ ማራቶን ረጅ…ም ነው። ከዚህ በተረፈ፣ በምክር መልክ የቀረበው ሃሳብ ፍፁም ስህተት ነው። በመሰረቱ፣ የአባት ምክር’ም ቢሆን፣ በነባራዊ እውነታ ላይ የተመሰረተና ተግባራዊ ለውጥ ለማምጣት በሚያስችል መልኩ እንጂ፣ ሀገራዊውን የለውጥ ሂደት በራስ ትርክት ውስጥ አጨማዶ ለማስገባት መሆን የለበትም።

አቶ አሰፋ ጫቦን ያሳሰባቸው ጉዳይ በእርግጥ ብዙ ሰዎችን እንዳሳሰበ እሙን ነው። በተለይ ገዳዩ ለጠ/ሚ ኃይለማሪያም እና ለመንግስታቸው ከመቼውም ግዜ በላይ አሳሳቢ ሆኗል። ነገር ግን፣ በተቃውሞ እንቅስቃሴው ተሳታፊ የሆነ ሰው፣ ወይም ደግሞ ጉዳዩን በጥልቀት እየተከታተለ ያለ ሰው፣ ባለፉት አራት ወራት የታየው አለመረጋጋትና ውጥረት እንደሚከሰትና ወደፊት’ም እንደሚቀጥል መገንዘብ ይችላል።

የህዝቡ ጥያቄና እንቅስቃሴ ተፈጥሯዊ የለውጥ ሂደትን ተከትሎ የመጣ እንደመሆኑ አይቀሬና አስገዳጅ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የህዝቡ ኑሮና አኗኗር እየተለወጠ፣ በተለይ ደግሞ የመረጃ አቅርቦትና አጠቃቀም እየተሻሻለ በሄደ ቁጥር፣ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል መብትና ግዴታውን ይበልጥ ያውቃል፥ ይጠይቃል። በልማትና ዴሞክራሲ ረገድ ህዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ይበልጥ እየሰፉና እየተወሳሰቡ መሄዳቸው እርግጥ ነው። በመሰረቱ፣ የልማትና ዴሞክራሲ ግቦች እውን የሚሆኑት አብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል በመረጃ በማብቃት ነው (empowering people through information)።

በህዝቡ ዘንድ እየተነሳ ያለው የለውጥና መሻሻል ጥያቄ ከፍተኛ ሥጋት የጣለባቸው ይህን ተፈጥሯዊ የለውጥ ሂደት ለማፈንና ለማቆም እየጣሩ ያሉ አካላት ናቸው። በዚህ ረገድ፣ ከማንም በላይ ስጋት ውስጥ ያሉት ደግሞ ኢህአዴጎች (መንግስት) እና ፅንፈኞች ናቸው። “ለምን?” የሚለውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት፣ ባለፉት አስር አመታት በኢትዮጲያ ውስጥ ስለታዩት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦች የተወሰኑ ምሳሌዎችን በመጥቀስ እንመልከት።

መንግስት በሚለው ደረጃ የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እየተመነደገ ባይሆንም፣ ባለፉት 11 አመታት ፈጣን የሆነ እድገት ማስመዝገቡ እርግጥ ነው። በተለይ ከመንገድ መሰረተ-ልማት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሀገሪቱ ገበሬ ምርቶቹን በተሻለ ሁኔታ ለገበያ ማቅረብ ችሏል። ይህ ገበሬውን ለምርቱ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ፣ በዚህም የተሻለ የመክፈል አቅም እንዲኖረው አስችሎታል። ሌላው ከኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን መሰረተ-ልማት መስፋፋት እና ከቴክኖሎጂ አቅርቦት ጋር ተያይዞ ያለው ለውጥ ነው። ይህ ለውጥና መሻሻል፣ በከተማና ገጠር መካከል የነበረውን ድንበር (ልዩነት) ሰብሮታል። በገጠርና በከተማው ማህብረሰብ መካከል የነበረው መሰረታዊ ልዩነት በዋናነት ከግንኙነት እና ከመረጃ አቅርቦትና አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ነው።

በመንገድና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ረገድ የታየውን ለውጥ፣ ከገጠር የት/ት ሽፋን መጨመር ጋር ተያይዞ ሲታይ፣ የገጠሩን ማህብረሰብ ይበልጥ ለመረጃ ቅርብ እንዲሆን አስችሎታል። ዛሬ የገበሬ ግንኙነት፣ እንደ አያት፥ ቅድመ-አያቶቹ በአንድ ገጠርማ አከባቢ ተወስኖ ብቻ የሚቀር አይደለም። ለምሳሌ፣ ከአስር አመት በፊት በትንሽ ከተሞች ውስጥ ብቻ ተወስኖ የነበረውን የሞባይል ስልክ አገልግሎት ዛሬ ለአብዛኛው የገጠሩ ማህብረሰብ ዘንድ ተደራሽ ሆኗል። ከአስር አመት በፊት ለአብዛኛው የከተማ ማህብረሰብ የመረጃ ምንጭ የነበሩት የሀገር ውስጥ የህትመት ውጤቶች እና ሚዲያዎች፣ ዛሬ በአለም-አቀፍ የዜና አውታሮች ተቀይረዋል። እስኪ ለትዝብት ያህል በሰፈራችሁ ያሉትን የመኖሪያ ቤት ጣሪያዎች ወይም የኮንዶሚኒየም ህንፃዎችን ግርግዳ ተመልከቱ። የከተማ የመኖሪያ ቤቶች ጣሪያና ግርግዳ ከሳተላይት ዲሽ የተሰራ ነው’ኮ የሚመስለው።

ከላይ የተጠቀሱት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦች በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥረዋል። የኢኮኖሚ እድገቱን ተከትሎ በማህብረሰቡ ውስጥ የተሻለ ሕይወት የመኖር ፍላጎት ጨምሯል። ይህ ህዝቡን የተሻለ ምርጫና አማራጭ እንዲጠይቅ አድርጎታል። ከዚህ በተጨማሪ፣ የተሻለ የመረጃ አቅርቦትና አጠቃቀም እያደገ በሄደ ቁጥር የህዝቡ ኑሮና አኗኗር እየተለወጠ መጥቷል። ይህ፣ በሕዝብና መንግስት መካከል ዋና መገናኛ በሆኑት በአስተዳደርና እና ፍትህ ሥርዓት ውስጥ የማያቋርጥ ለውጥና መሻሻል እንዲኖር ያስገድዳል። ምክንያቱም፣ ህዝብ የተሻለ ምርጫና አማራጭ ስለሚሻ፣ መንግስት የተሻለ ሥራና አሰራር፣ የበለጠ ግልፅነትና ተጠያቂነት ሊኖረው ይገባል። ነገር ግን፣ አሁን መንግስት አለብኝ እያለ ያለው “የመልካም አስተዳደር ችግር” ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ከህዝቡ ጋር አብሮ መሄድና መለወጥ እንደተሳነው ያሳያል።

በ2008 ዓ.ም እየታየ ያለው ተቃውሞ ህዝቡ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መብቱን ለማስከበር የሚችልበት አማራጭ መንገድ በማጣቱና ብሶትና ምሬቱን የሚተነፍስበት ትንሽ ቀዳዳ ባለመኖሩ የተከሰተ ነው። በአንድ በኩል ህዝቡ በፍትህና የመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት እየተሰቃየ ነው። በሌላ በኩል፣ ለአስር አመታት የተጠራቀመ ብሶቱንና ምሬቱን የሚያስተነፍስበት ቀዳዳ ሲያጣ፣ አመፅና ተቃውሞ ብቸኛ አማራጭ ይሆናሉ። በተለይ ደግሞ፣ ቀልጣፋ አገልግሎትና ፍትህ ያልሰፈነበት ምክንያት ሌላ ሳይሆን መንግስት የአስተዳደርና ፍትህ ሥርዓቱን ማሻሻል ስለተሳነው እንደሆነ በበቂ መረጃ ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ ሲኖረው ህዝብ ይቆጣል፣ ህዝባዊ አመፅ ይቀሰቀሳል። ዘንድሮ እየሆነ ያለው ይህ ነው።

ከፍትህና የሕግ-የበላይነትን ከማረጋገጥ አንፃር ያለውን ለውጥና መሻሻል ለመገንዘብ በ1997/98 ዓ.ም እና በ2008 ዓ.ም የተከሰቱትን አለመረጋጋቶች በንፅፅር ማየቱ ብቻ በቂ ነው። ከአስር አመት በፊት፣ አብዛኞቹ ተቃዋሚዎች “ሕገ-መንግስቱ የተፃፈበትን ወረቀት ያህል ዋጋ አያወጣም!” የሚል አቋም ሲያንፀባርቁ ነበር፣ ኢህአዴግ ደግሞ “ሕገ-መንግስቱን አክብሩ” የሚል አቋም ነበረው። ከአስር አመት በኋላ፣ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ከቀድሞው አቋሙ በተቃራኒ ሆኖ መንግስትን “ሕገ-መንግስቱን አክብር?” እያለ ነው። ነገር ግን፣ ኢህአዴግ ሆዬ አሁንም ቀድሞ በነበረበት ቦታ ተተክሎ ቆሞ “ሕገ-መንግስቱን አክብሩ” የሚለውን ሐረግ ለራሱ እየደገመ ይገኛል።

ማንኛውም ዜጋ ተቃውሞውን በአደባባይ ለመግለፅ ለሚመለከተው አካል በቅድሚያ “ማሳወቅ አለበት” የሚለውን “ማስፈቀድ አለበት” ወደ የሚል አውርዶ፣ መንግስት የዜጎችን የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትን ገድቧል። በፀረ-ሽብር አዋጁ፣ “የሞራል ድጋፍ፣ ምክር መስጠት” እና የመሳሰሉት ዓ.ነገሮችን በውስጡ አጭቆ፣ ዜጎች ስለ ሽብርና አሸባሪዎች መናገርና መፃፍ ቀርቶ ማሰብና ማንበብን እንኳን የማይቻሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። መንግስት ግን የፈለገውን ግለሰብ ሆነ ቡድን በፈለገው ግዜና ቦታ “አሸባሪ” ብሎ ይወነጅላል፥ ይከሳል፥ ያስራል፥ ይፈታል። እንደ አንድ ጉልበተኛ ዜጎቹን ባልተመቸው ግዜ አስሮ፣ በተመቸው ግዜ ይፈታል። በአጠቃላይ፣ ከ1997/98 ጀምሮ ኢህአዴግ የህዝቡን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች በተግባር ለማክበርና ለማስከበር ከመጣር ይልቅ፣ ጭራሽ አስር ዓመት ወደኋላ (ወደ 1987 ዓ.ም) ተመልሶ፣ በሕገ-መንግስቱ ላይ የተቀመጡት የዜጎች መብቶች በዚያው በወረቀት ላይ ብቻ ተወስነው እንዲቀሩ ለማድረግ እየጣረ ይመስለኛል።

በሌላ በኩል፣ እንደ አቶ አሰፋ ጫቦ ያሉት የብሔራዊ አንድነት አቀንቃኞች “ክቡር ጠ/ሚ፣ ባለፉት አራት ወራት እንዳየነው፣ ህዝቡ ይህ ‘ልማት፣ እድገት’ የምትሉትን አልወደደውም፣…ወዘተ” እያሉ፣ 1987 ዓ.ም ላይ ባለበት የቆመውን የኢህአዴግ መንግስት፤ መንግስታዊ መዋቅሩንና ፖለቲካዊ አስተዳደሩን 20 ዓመት ወደኋላ (ወደ 1967 ዓ.ም) እንዲመለስ በደብዳቤ ይወተውታሉ። እንደ እሳቸው ላሉ የብሔራዊ አንድነት ፅንፈኞች፣ ዘንድሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየታየ ላለው አለመረጋጋትና ውጥረት መፍትሄ የሚፈልጉት ከ40 ዓመት በፊት በነበረ ትርክት ላይ በመቆዘም ነው። ከእነሱ በተቃራኒ ጠርዝ ላይ ያሉት የብሔር ፅንፈኞች ደግሞ ለዛሬው ችግር መንስዔውን ከ100 ዓመት በፊት በሆነ ታሪክ ላይ ይነታረካሉ። ኢህአዴግ’ም በየአመቱ እየሰፋና እየተወሳሰበ ለሚመጣው የልማትና ዴሞክራሲ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ሲሳነው 21 ዓመት ወደኋላ ተመልሶ፣ በሕገ-መንግስቱ የተመለሰውን “የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት” ጥያቄ እንደ አዲስ ይቀሰቅስና ከፅንፈኛ ብሔርተኞች ጋር ይጨፍራል። እንዲህ ኢህአዴግ ባለበት እንደ ቆመ፣ ፅንፈኞች ባለፈው ግዜ ላይ እንደቆዘሙ፣ ህዝቡ ግን ወደፊት እየሄደ፥ ለውጥና መሻሻልን እየናፈቀ፣ የተሻለ ምርጫና አማራጭን እየጠየቀ ነው።

***********

Seyoum Teshome

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago