ኢትዮጵያዊነት በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ያብባል ይዘምናልም

(አበበ ተክለሃይማኖት (ጆቤ) (ሜጄር ጄኔራል)

Highlights

* አገሮች በውዴታ ብቻ ቢመሰረቱ ኖሮ የማንነት ጉዳይ በተለይ የብሔር ማንነት ጉዳይ በላላ ነበር የመደብ እና ሌሎች ማንነቶች ጎልተው ይታዩ ነበር፡፡ ነገር ግን አብዛኛው አገሮች የግዴታ በኃይል የተመሰረቱ በመሆናቸው የተለያዩ ብሄሮችን አጭቀው ይገኛሉ፡፡ በአገር ግንባታ አንፃር ረጅም ርቀት ተጉዘዋል የሚባሉት የአውሮፓ አገሮች እንኳን የብሄር ጥያቄ በበርካታ አገራት በ21ኛ ክፍለ ዘመን ጎልቶ እየታየ ነው፡፡ በስፔን፣ ጣሊያን፣ ቤልጂየም፣ ታላቋ ብሪታንያ፣ሲዊዘርላንድ ወዘተ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በስርዓታቸው ልዩነት ካለ የብሔር ልዩነት ተቀብሎ አቃፊ ወይም አግላይ በመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ ወይም ደግሞ የአቃፊነቱ ደረጃ ያለው ልዩነት ነው፡፡ የማንነቶች ብዝኃነት (Multiple identities) አንድ ሰው ወይም አንድ የህብረተሰብ አካል የብዙ ማንነቶች (Multiple identities) ባለፀጋ ነው፡፡

* ባለፈው ጥቂት ሳምንታት ዘርን ማእከል ያደረገ የሚመስል ጥቃት በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ሲታይ የነአቶ ለማ አመራር በንግግር ነው እንዴ የሚቀረው የሚል ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም፡፡ ተገቢ ስጋትና ጥያቄ ነው፡፡ የክልሉ መስተዳደር ሁኔታውን በአስቸካይ መቆጣጠርና ወንጀለኞችን ወደ ፍረድ ማቅረብ ተገቢ ይሆናል፡፡ ገና በጅምር ያለ እንቅስቃሴ ስለሆነ ተራማጅ ሃሳቦች ያለው አመራር ቢኖርም ወደ በየደረጃው ያለው አመራር እና ወደ ህዝቡ ዘልቆ ኃይል እስኪሆን ድረስ ጊዜ መጠየቁ አይቀሬ ነው፡፡

* አንዳንድ ምሁራን አሁን ያለው አግላይ ብሄራዊነት የተስፋፋው ብሄር-ተኮር የሆነ ፌዴራላዊ ስርዓት በመመስረቱ ይላሉ፡፡ እኔ ግን የተሳሳቱ ይመስሉኛል፡፡ ቅድመ 83 ኢትዮጲያ በሁሉም አቅጣጫ በነፃነት ድርጅቶች ጦርነት ስትናወጥ የነበረችው ደርግ ብሄር-ተኮር የሆነ ፌዴራላዊ ስርዓት ይከተል ስለነበረ አይደለም፡፡ ዋናው ችግር ጠቅላይ እና ኢ-ዴሞክራቲክ ፌዴራል መንግስት መኖር እና ልፍስፍስ የክልል መንግስታት በመኖራቸው ነው፡፡

* በምፅዋት የሚተዳድሩ ክልሎች ተይዞ ፡ሁሉም ነገር አንጋጦ ወደ አዲስ አበባ የሚያይ ሁሉም ችግሮች ከወደ ፌዴራላዊ እንደሚመጣ አድርገው በመጮህ ኢትዮጵያዊነት ይሸረሽራሉ፡፡ ጠንካራ ክልል የህዝቡን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚጠብቅ በመሆኑ ህዝቡም በራሱ የሚተማመን በመሆኑ ሕገ-መንግስታዊ ያወቀለትን ስልጣን በሚገባ የሚጠቀም እና ፌደራል መንግስቱ የጠቅላይነት ባህሪ ሲያሳይ በጊዜው የሚያስተካክል መሆን ይገባዋል፡፡ እኛ ጥሩ ብንሰራም ፌዴራል መንግስት እየቀጣን ነው የሚል ልፍስፍስ ክልል፣ የገዥው ፓርቲ አባል ሆኖ እዛ ሳይታገል አድልዎ አለ እያለ ህዝብ ለህዝብ የሚያጋጭ አጎብዳጅ ክልል ወ.ዘ.ተ ስላለን ነው፡፡

አቶ ለማ መገርሳ ና በዙርያቸው ያሉት ጎልማሳ ሙሁራን ስለ የኢትዮጵያዊነት መሰረት ስለ አዲሱ ኢትዮጵዊነት እና የህዝቦች አንድነት ሲናገሩ ሕገ-መንግስቱን በሚገባ የሚያውቅ፣ በእምነት ለማራመድ እና ተግባራዊ ለማድረግ ከኢህአዴግ ውስጥ ብቅ የለ አመራር እየተፈጠረ ነው እንዴ የሚያሰኝ ነው፡፡ በተግባር መረጋገጥ የለበት ቢሆንም የ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን የጥርጣሬው ጥቅም (the benefit of the doubt) ሰጥተን ሂሳዊ ድጋፍ (critical support) በመሰጠት ከጎናቸው መሰለፍ የሚገባን ይመስለኛል፡፡

መግቢያ

ብሔር/ብሔረሰብ የሉም ማለት ኢትዮጵያ የምትባል አገር የለችም እንደ ማለት ነው፡፡ የራስ ዕድል በራስ የመወሰን መብትን ዕውቅና አለመስጠት ሀገራችን ዴሞክራሲ አያስፈልጋትም እንደ ማለት ነው፡፡ በኔ አመለካከት የስልጣኔ ማማ የነበረችው ኢትዮጵያችን በመሳፍንት ስርዓት እየደቀቀች ብትሔድም ህዝቦችም ባደረጉት ትግል በዓድዋ ላይ ነፃነታችንን ያረጋገጥን መሆናችን አሁንም በነፃነት አስበን የሚበጀንን ህገ- መንግስት አፅድቀን የአድዋ ድል እያደስን እንገኛለን፡፡

ነፃነታችን በሚመለከት አብዛኛው ስማችን አልዶ፣ሊቺያ፣ጀምስ ወዘተ ወይም አብዛኛው አካባቢያችን ፒያሳ፣ካዛንቺስ ወዘተ አለመሆኑ አይደለም፡፡ በነፃነት አስበን የሌሎች ሃሳብ ቀምረን የሚያስፈልገን ብቻ ወስደን ግን ተመፅዋች ስንሆን የመሰለንን ማድረግ ስንችል ነው፡፡

በዓድዋ የአፍሪካ እና የጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት እንደሆነው ሁሉ በ21ኘው ክፍለ ዘመንም የህሊና ነፃነታችን በመጠበቅ ለመላው ዓለም ተምሳሌት የሚሆን ህገ-መንግስት ሰርተን በጣም አስቸጋሪ በሆነ ሽግግር እንገኛለን፡፡ ከቀኝ አገዛዝ ነፃ በወጡ በአፍሪካ ሀገራት በአስተሳሰባቸው ነፃነታቸው ባለመረጋገጣቸው የአውሮፓ/አሜሪካ ህገ-መንግስት እንዳለ ቀድተው ስማቸው ብቻ ቀይረው እየታገሉ ሲገኙ እኛ ፈር ቀዳጅ የተባለውን ብሔር-ተኮር የፊደላዊ ስርዓት ከነሙሉ መብቶቻቸው ተቀብለን አደጉ ተመነደጉ ለሚባሉትም ተምሳሌት ሆነናል፡፡

ኩቤክ ና ካናዳ ስኮትላንድ ና ታላቁ ብሪታንያ ያስተውላል፡፡ እሰፔን የካታሎናዊያን ጉዳይ በሀይልና በህግ ለመፈታት እየተራወጠች ባለችበት ጊዜ እንደ ቢቢሲ 08/11/2017 ዘገባ The Spanish government will consider holding a nationwide referendum on changing the constitution to allow for legal independence referendums, the foreign minister says፡፡ እኛ 27 ዓመት በፊት አንድነት በኃይል የማይሆን እንደሆነና የኢትዮጵያ አንድነት መሰረት ያለው መሆኑ ብቻ ሳይሆን በዋናነት ለዛሬም ለነገም የሁሉም ህዝቦችዋ ዋስት ና ለሁሉም ህዝቦችዋ የሚጠቅም በመሆኑ በመፈቃቀድ ብቻ የተመሰረተ አንድነት እንዲሆን የነ ዋልልኝ መኮንን ተራማጅ ሃሳብ በህገ-መንግስታችን አስፍረን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡.

ይህም ሆኖ ለዘመናት በሰፈነውና አሁንም እያሰቸገርን የለው መስፍናዊ ኃላ ቀር ፖለቲካዊ ባህል የኢትዮጲያ አንድነት ከሁለት አቅጣጫ የሚነሱ ከፍተኛ ተግዳሮች እያጋጠመው ነው ፡፡ በአንድ በኩል ስለ ህዝቦችም ሳይሆን ሰለመሬት እና አየር አንድነት ማእከል አድርጎ የአንድ ህዝብ ፣የአንድ ሃይማኖት፣የአንድ መንግስት ጠቅላይ ና አግላይ አስተሳሰብና ተግባር በሌላ በኩል በአግላይ ብሔራዊነት በከፍተኛ አደጋ እንገኛለን፡፡

ኢትዮጵያን እንወዳለን ማለት በዋናነት ህዝቦችዋን መውደድ ማለት ስለሆነ ጠቅላይ እና አግላይ ኢትዮጵያውነትን በማውገዝ አግላይ ብሔራዊነት በመታገል ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች አገራትንን በሁለቱም ፅንፍ አስተሳሰብ እንዳትናወጥ ህዝቦችዋን በማስተማር መታገል ይኖርብናል፡፡

ለዚህ ሲባል በመጀመርያ ስለ ማንነት፣የማንነቶች ብዝኃነት፣የማንነት ቅራኔዎች ከቀረበ በኀላ ብሔርነተኝነት እና አገራዊነት፣ ኢትዮጲያዊነት ዴሞክራሲያዊ ብሔርነተኝነት ያሉት ተግዳሮች በዝርዝር ከቀረበ በኀላ መፍትሔው መሰረት ያለው ወሰን በሌለው የህዝቦች መብት የሚቀዳ ኢትዮጵያዊነት በሚል ይደመድማል፡፡

ማንነት (Identity) ሰብዓዊ ፍጡር ከሌሎች እንስሳትና ሌሎች ነገሮች ሲነፃፀር ተመሳሳይ/ አንድ ቢሆንም በውስጡ ደግሞ በተለያዩ ማንነቶች ይገለፃል፡፡ ሕብረተሰብን በዘር ጥቁር፣ነጭ፣ ቢጫ ወ.ዘ.ተ ፡ አፍሪካ/አውሮፓ፣ ኤሽያ፣ አሜሪካ ወ.ዘ.ተ በክፍለ ዓለማት፣ በአፍሪካ ውስጥም ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ ግብፅ ወ.ዘ.ተ ሀገሮች በአንድ ሀገር ደግሞ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ሃይማኖቶች፣ ፆታ፣ ፕሮፌሽን ወዘተ በአንድ ብሄር ራሱም የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ላብ አደር፣ ባለሀብት፣ ባል/ሚስት እና በትውልድ ወጣት፣ ሽማግሌ ወ.ዘ.ተ ያሉ ማንነቶች ይኖራሉ፡፡

ላውለር (2008፣ 04) የተባለ ፀሐፊ፣ ‹‹The concept of identity is centered on the paradoxical merger of sameness and uniqueness›› ይለዋል፡፡ አንድነት የሚኖረው ልዩነት ሲኖር ነው፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ሆኖ ልዩነትን ያለ አንድነት፣ አንድነትን ያለ ልዩነት ሊገልፀው አይችልም፡፡ አንድነት የሚለው ንድፈ ሐሳብ (concept) የተለያዩ ማንነት ያላቸው ግን የጋራ ማንነት እነዳለቸው የሚገልፀም ነው፡፡ Rummens እና ጓደኞቹ (2003:02 “the recognition of socially-silent similarities and differences forms the very corner-story of social interaction” ይላሉ፡፡ ሰብዓዊ ግንኙነት ማዕከሉ ተመሳሳይነት እና ልዩነት መሆኑ ነው፡፡ ሰዎች/ሀገሮች/ብሔሮች ተመሳሳይ በመሆናቸው አብረው ተደጋግፈው በዓለም ላይ ያለውን ፀጋ አብረው ይጠቀማሉ ተግዳሮትን ለመፍታት አብረውም ይታገላሉ፤ ልዩነት ስላላቸው ደግሞ ከዛ የሚመነጨውን በአስተሳሰብ ብዙኃነት ማስተናገድ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ የሰለጠነ ወይም ዴሞክራቲክ አስተሳሰብ ልዩነትን እንደፀጋ የሚወስደው ለዛ ነው፡፡ የወል ማንነት (Collective Identity) የሰው ልጅ እንደግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ ነገድ፣ ብሔር/አገር ወ.ዘ.ተ. ውስጥ ነው የሚኖረው፡፡ የግለሰብ ማንነት ቢኖረውም እንደማህበራዊ እንስሳ የቡድን/ወል ማንነት አለው፡፡ የወል ማንነት የሚመለከት የሀርቫርዱ ኢብዴላል እና ጓደኞቹ (2009፡ 18-19) እንዲህ ይላሉ፡፡

የወል ማንነት በይዞታ (content) ና በሚማጎቱ/የሚወዳደሩ (contestation) ሁለት አቅጣጫ የሚፈስ ማሕብራዊ ምድብ (social category) ብለው የተረጉማሉ፡፡ ቀጥለውም ይዞታ የወል ማንነትን ትርጉም የሚገልፅ ሆኖ አራት የሚደጋግፉ ዓይነቶች ቅርፅ ሊዪዝ ይችላል ይላሉ፡፡

– መደበኛ (formal) ና መደበኛ ያልሆኑና (informal) ቡድኑን የሚገልፁ ህጎች – የብድኑ ማህበራዊ ዓላማ የሚገልፁ የጋራ ግቦች – ራሳቸውን የሚገልፁበትና ከሌሎች የሚለዩበት ወሳኝ መግለጫዎች – ፖለቲካዊ ና ቁሳዊ (material) ሁኔታ ና ጥቅሞች የሚገልፁበት የጋራ ራዕይ ናቸው ሚማጎቱ/የሚወዳደሩ (contestation) በየትኛውም ማንነት የጋራ ይዞታ ትረጉም ላይ ያለ ስምምነት ወይም ልዩነት የሚገልፅ ነው፡፡ ማንነቶች በጊዜ፡ ቦታ ና ሁኔታ ስለሚለዋወጡ፡ ስለሚያድጉ ኣባሎቹ እላይ በተገለፁት አራት የይዞታ ዓይነቶች የሚስማሙበትን ያህል የሚለያዩባቸው ይኖራሉ፡፡ በህጎቹ፤ ግቦች፡ መግለጫዎች እና ራዕይ ቀጣይ የሆነ ስምምነት እና ልዩነት ይኖራቸዋል ይላሉ፡፡

ታላቋ ብሪታንያ የተለያዩ ብሔሮች/ክልል አገር ናት፡፡ እንግሊዝ፣ ስኮትላንድ፣ ዌልስ እና ሰሜን አየርላንድ: የስኮትላንድ ብሄር ታላቋ ብሪታኒያ ከተቀላቀች ከአራት መቶ ዓመታት በላይ ሆነዋል፡፡ ሲቀላቀሉ የነበረው የስኮትላንድ ማንነት በየጊዜው እየተሰራ፣ እየፈረሰ እንደገና እየተሰራ (constructed and deconstructed) ብዙ ለውጦች ታይተዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም የስኮትላንድ ማንነት የሚባል አለ፡፡

በ2014 ኤ.አ.አ. በብሪታኒያ ውስጥ ለመቀጠል ወይም ተነጥለው በራሳቸው ነፃ አገር ለመመስረት ህዝበ ውሳኔ ተካሂደዋል፡፡ ታይቶ በማይታወቀው የመራጭ ብዛት 44.7% ነፃ አገር እንመሰርታለን ሲሉ 55.3% ደግሞ የለም ባለንበት እንቆያለን ብለዋል፡፡ 44.7% የሚሆኑት ታላቋ ብሪታኒያ የምትባል ሀገር አንፈልግም የራሳችን አገር እንፈልጋለን እያሉ ነው፡፡

የእስኮትላንድ ማንነት ዓለማና ግብ እንዲሁም በውስጣቸው እና ከታላቋ ብሪታኒያ ጋር ያለው ግነኙነት ከፍተኛ ልዩነት እየታየ ነው፡፡ የሰሜን አየርላንድ ክልል ህዝቦችም በሃይማኖት ጭምር ተለያይተው ግማሹ ወደ አየርላንድ ለመቀላቀል ሲፈልጉ የሚበዙት በታላቋ ብሪታንያ ስር ለመቆየት ይፈልጋሉ፡፡ ለብዙ ህይወት መጥፋት እና ንብረት መውደም ምክንያት ሆነዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የነጭ ዘረኝነት ማንሰራራት ተከትሎ በአሜሪካ ፉትቦል (NFL) ውስጥ ያሉት ተጫዋቾች የማይነካ የሚመስለው የአሜሪካ ብሔራዊ መዝሙር ቆመን አንዘምርም ማለታቸውን በተለይ አፍሪካ አሜሪካዊያን ተጫዋቾች አሜሪካ ከሚባለው፣ ከሚታወቀው ማንነት ጥያቄ እያነሱ መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በስፔን ካታሎኒያ የተደረገው ህዝበ ውሳኔ ድምፅ ከሰጠው 92.01% ነፃ አገር እንፈልጋለን እያለ ነው፡፡ የመጨረሻው ውጤት ምን ይሁን ምን ያን ያህል ህዝብ እኛ ስፔናውያን አይደለንም የራሳችን አገር እንፈልጋለን እያለ ነው፡፡

በየትኛው አገር የአገር ማንነት ጥያቄ የማይነሳበት አገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ከ20ኛው ክፍለ ዘመን በፊት አገሮች በውስጥ የሚገኙት ህዝቦች ፍቃድ ሳይሆን በኃይል የተመሰረቱ ስለሆኑ ነው፡፡ የአውሮፓ አገሮች አመሰራረት ሚካኤል ሪር (2012፡37) እንዲህ ይላል፡፡ “Between the fourteenth and the twentieth centuries, the number of political entities” in Europe went from approximately one thousand to a mere twenty five and that process of consolidation was accomplished largely by force.” ማናቸውም አሁን ያለው አገር በውድ ብቻ የተመሰረተ የለም፡፡ በኃይልም ጭምር እንጂ፡፡

አገሮች በውዴታ ብቻ ቢመሰረቱ ኖሮ የማንነት ጉዳይ በተለይ የብሔር ማንነት ጉዳይ በላላ ነበር የመደብ እና ሌሎች ማንነቶች ጎልተው ይታዩ ነበር፡፡ ነገር ግን አብዛኛው አገሮች የግዴታ በኃይል የተመሰረቱ በመሆናቸው የተለያዩ ብሄሮችን አጭቀው ይገኛሉ፡፡ በአገር ግንባታ አንፃር ረጅም ርቀት ተጉዘዋል የሚባሉት የአውሮፓ አገሮች እንኳን የብሄር ጥያቄ በበርካታ አገራት በ21ኛ ክፍለ ዘመን ጎልቶ እየታየ ነው፡፡ በስፔን፣ ጣሊያን፣ ቤልጂየም፣ ታላቋ ብሪታንያ፣ሲዊዘርላንድ ወዘተ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በስርዓታቸው ልዩነት ካለ የብሔር ልዩነት ተቀብሎ አቃፊ ወይም አግላይ በመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ ወይም ደግሞ የአቃፊነቱ ደረጃ ያለው ልዩነት ነው፡፡ የማንነቶች ብዝኃነት (Multiple identities) አንድ ሰው ወይም አንድ የህብረተሰብ አካል የብዙ ማንነቶች (Multiple identities) ባለፀጋ ነው፡፡

አንድ ግለሰብ የአንድ ቤተሰብ /አካባቢ/ነገር/ ብሄር /አገር ወይም ወጣት/ ሽማግሌ፣ ሴት/ወንድ፣ ሙስሊም፣ ክርስቲያን ወይም ደግሞ ላብ-አደር፣ ቡርዧ ገበሬ፣ ምሁር ወታደር ወ.ዘ.ተ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ማንነቶች በተለያዩ ደረጃ ግለሰቡ አካሉ ውስጥ ህያው እና ተደማሪ በሆነ መልኩ ተቀናጅተው ሰውዬውን ወይም አካሉን ይገልፁታል ፡፡ ከሁሉም ማንነቶች አንድ ወይም ሁለቱ ግን በጊዜ በቦታ (space) ጎልተው የማንነቱ ዋነኛ መገለጫ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በአንድ አካል ያሉ ማንነቶች እንደሚሰማሙ ሁሉ የተለያዩ ቅራኔዎችም ያዘሉ ናቸው፡፡ ማንነት በጊዜ እና አውድ (context) ሊለያይ ይችላል፡፡

የማንነት ቅራኔዎች (identity conflicts) ቅራኔ (conflict) የፖለቲካ ማዕከል (cornerstone) ነው፡፡ ለዚህ ጽኁፍ ሲባል ፖለቲካ ስንል የአንድ ማንነት (አገር፣ ብሄር፣ ፆታ፣ መደብ፣ ሃይማኖት፣ ሙያ ወዘተ) ቁሳዊ ጥቅሞችን እና እሴቶችን ለመጠበቅ፣ ለማዳበር የሚደረግ ሁሉ ዓቀፍ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ፖለቲካ በነዚህ ጥቅመቶች እና እሴቶች ዙሪያ ያለውን ቅራኔዎች በሰላማዊ ይሁን በሓይል ለመፍታት የሚደረግ ትግል ነው፡፡ ለዛ ነው ጦርነት የፖለቲካ የሰላ ጫፍ ነው የሚባለው፡፡ ሰዎች እንደ እንስሳ በንዋታዊ ቅራኔ ተዘፍቀው ይኖራሉ፡ እንደ ማህበራዊ እንስሳ (social animal) ደግሞ የእሴት ልዩነት ወደ ቅራኔ ያመራል፡፡

አንዳንድ ምሁራን ሁሉም ቅራኔዎች የማንነት ቅራኔዎች (all conflicts are identity conflicts) ናቸው ይላሉ፡፡ በኔ እይታ ይህ እይታ ትክክል ይመስለኛል፤፤ ቁሳዊ ጥቅም እና እሴት ተዋድደው የሚገለፁት በማንነት በመሆኑ፡፡ መደብ ትግል በላብ አደር እና በቡርዣ ንዋታዊና እሴታዊ ግጭት ማዕከል አድርጎ ይካሄዳል፡፡ በሃይማኖት ስም ሲካሄዱ የነበሩት እና ያሉት ጦርነቶች የእምነት ብቻ አልነበረም አይደለምም ቁሳዊ ጥቅም ማን የበለጠ ያረጋግጥ ጭምር ነው፡፡ የፆታ እኩልነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ትግልም የወንድ የበላይነት የሚባለው መጥፎ እሴት አስወግዶ ፖለቲካዊ እኩልነት የሚባል እሴት ለመተካት ብቻ አይደለም፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምችን የማግኘት እና የማጣት ጭምር እንጂ፡፡

በሀገሮች መካከል ጥቅሞችንና እሴቶችን ለማስጠበቅ ወደ ጦርነት መሄድ እየቀነሰ ቢሄድም አሁንም አልቀረም፡፡ ታዛቢዎች አሜሪካ ኢራቅን የወረረችው ዋና ምክንያት የተፈጥሮ ሀብቷን (ነዳጅና ጋዝ) ለመዛቅ እና የሊበራል ዴሞክራሲ እሴትዋን ለመጫን ነው ይላሉ፡፡ እንደነዚህ ምሁራን አባባል ለአካዳሚክ ጠቀሜታ ሲባል ቁሳዊ ቅራኔ (resource conflict) ወይም የእሴት ቅራኔ ብለን ለየብቻው መግለፅ ቢቻልም እውነታው ግን አንዱ ከአንዱ ለመለየት በማያስችል ሁኔታ ተቆላልፈው ነው የሚኖሩት፡፡

በዓለም/አገር/ብሄር ደረጃ ሲታይ የተለያዩ ማንነቶች በተለያዩ ወቅቶች ህብረተሰብን በፖለቲካ ለማሳለፍ የተለያዩ አቅም ይኖራቸዋል፡፡ የመደብ ትግል፣ በአገሮች መካከል የሚደረግ ትግል፡ የብሄር ትግል ወ.ዘ.ተ አንዴ አንዱ ጎልቶ ሌላ ጊዜ ሌላው ተደብቆ (hibernate) የሚያደርጉበት ነው፡፡ ከስፔን መገንጠል አለብን ብለው የመረጡት ካታላውያን (catalian) የመደብ፣ ፆታ፣ ምናልባትም የሃይማኖት ወ.ዘ.ተ ልዩነት በውስጣቸው መኖሩ የግድ ነው፡፡ ከስፔን ጋር ያለው ቅራኔ ለመፍታት ቅድሚያ በመስጠት ግን ሌላው ግጭቶች በሁለተኛ ደረጃ አይተው ያቆዩታል፡፡

ብሔርነተኝነት እና አገራዊነት አማኑኤል ካስቴል (2004፡01) our world, and our lives, are being shaped by the conflicting trends of globalization and identity. The information technology revolution, and the restructuring of capitalism, have a new form of society.”

ዓለም አንድ መንደር እየሆነች ናት በተባለበት ሁኔታ የማንነት ፖለቲካ በዓለም ደረጃ እያገረሸ የመጣበት ሁኔታ እናያለን፡፡ ልክ የግሎባላይዜሽን ለውጥ መቀበል የግድ እንደሚሆን ሁሉ የማንነት ፖለቲካ የግድ ተቀብለን ለህብረተሰብ አዎንታዊ ለውጥ እንዴት እንጠቀምበት ማለቱ ብቻ ነው ተገቢ የሚሆነው፡፡ የማንነት ፖለቲካ የለም ወይም እንዲኖር አንፈቅድም ማለት ‹‹የሰጎን ፖለቲካ›› ነው የሚሆነው፡፡ ላለማየት ዓይንን አሸዋ ውስጥ እንደ መደበቅ ይታሰባል፡፡ በአውሮፓ እንደ እነ ታላቋ ብሪታኒያ ጣሊያን፣ ስፔን ወዘተ የማንነት ፖለቲካ እያናወጣቸው ይገኛል፡፡ ካሊፎርኒያ እና ቴክሳስ ግዛቶች በተለያዩ ምክንያቶች የመገንጠል ጥያቄ የሚያነሱ ቡድኖች በተባበሩት አሜሪካ መከሰታቸው ራሱ አቅጣጫ አመላካች ነው፡፡

ማርክሲስቶች እና ሊብራል ዘመናውያን (liberal modernists) ብሄር ተኮር ማንነት መሸጋገሪያ እንደሆነ እና በግሎባላይዜሽን እየከሰመ እንደሚሄድ ይተነብዩ ነበር፡፡ ነገር ግን የተገላቢጦሽ ነው የሆነው፡፡ ሩዶልፍ (2003) ብሄርተኝነት የዓለማችን ካሉ ወሳኝ የፖለቲካ ጉዳዮች መካከል ቁልፍ ከመሆኑ ባሻገር ቀጣይነቱ እየሰመረ ይገኛል ይላል፡፡ ይህ የሩዶልፍ ሀሳብ በሀችንሰንና ስሚዝ (1996) ድጋፍ ተችሮታል፡፡ እንዲህ ሲሉ ያብራራሉ፡፡ ብሄርተኝነት በማናቸውም አህጉር የፖለቲካና ማህበራዊ ህይወት ቁልፍ ቦታ እየያዘ ሲሆን የመደብዘዝ ሁኔታ በጭራሽ እየታየ አይደለም ይላሉ፡፡

ምንም እንኳን አብዛኞቹ የአፍሪካ መንግስታት ይህንን ሃቅ ቢክዱም በብሄር ጉዳይ የሁሉም ፖለቲካዊ ማህበራዊ ማዕከል እየሆነ መሆኑም አላጌ (2004) የተባለው ምሁር ይገልፃል ሳላህ (2001፡21)”ምንም እንኳን የአፍሪካ ፖለቲካዊ ፓርቲዎች በራሳቸው ብሄር መሰረት አድርገው የተፈጠሩ ቢሆንም የአፍሪካ መሪዎችና ልሂቃን ህዝቦቻቸውን ብሄር መሰረት አድርገው ፓርቲዎች እንዲያቋቁሙ ይከለክላሉ፡፡”

የአፍሪካ ህዝቦች በቀኝ ገዥዎች በተፈጠሩት ሃገራት በጋራ እጣ ፈንታ ያላቸው እምነት በአገር/መንግስት ያላቸው ታማኝነት ዝቅተኛ ነው፡፡ ሲጀመር አፍሪካውያን አዲሱ አገራቸው/መንግስታቸው ኢ-ሰብዓዊ በሆነ መንገድ ሲያስተዳድራቸው ከነበረው የቅኝ ገዥዎች ተከትለው ስልጣን ላይ የወጡት አፍሪካውያን ልሂቃን የተሻሉ አልነበረም፡፡ አፍሪካውያን ከመንግስታቸው ይልቅ አባል በሆኑበት ብሄር አልያም ሃይማኖት ቡድን የጠነከረ ግንኙነትና ታማኝነት አላቸው፡፡ ደህንነታቸው፣ እድገታቸው ሁሉም ነገራቸው ከብሄር/ሃይማኖት ጋር ያስተሳስሩታል፡፡

በዚህም ምክንያት በሁሉም የአፍሪካ አገሮች ያለው ግጭት፣ በዋናነት በብሔር/ጎሳ የተመሰረተ ነው፡፡ በቅርቡ በኬንያ የተደረገው ምርጫ እንደሚያመላክተው ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአብዛኛው በብሄር/ጎሳ ስም ባይጠሩም መራጩ በአብዛኛው በሚያምነው ግን የብሄር/ጎሳ አባል ነው፡፡ ቢቢሲ እንደገለፀው የፕሬዚዳንቱ እና ምክትል ፕሬዚዳንቱ ብሄር/ብሄረሰብ ባለበት ከፍተኛ ህዝብ ወደ ምርጫ ሲጎርፍ ተቃዋሚዎች በጠሩት በምርጫው አለመሳተፍ ጥሪ በተወዳዳሪዎች ኦዲንጋ እና ሽርካቸው ብሄር/ብሄረሰብ ተቀባይነት በማግኘቱ እዛ አካባቢ ምርጫው ከሽፈዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቅኝ አገር ያልተገዛች ነጻነትዋን አሳልፋ ያልሰጠች ብትሆንም የራስዋ የረዥም ጊዜ መንግስት ቢኖራትም ኢትዮጵያዊነት ሃገራዊነት የተሻለ መሰረት ቢኖረውም አንድ ጊዜ እየሰፋች ሌላ ጊዜ እየጠበበች እንዲሁም ማህበረ ኢኮኖሚ የደቀቀ በመሆኑ ህዝቦች እርስ በርስ መገናኘት እድላቸው አነስተኛ በመሆኑ ከላይ ስለአፍሪካውያን የተገለፀውን ይመለከታል፡፡ የማንነት ፖለቲካ በዓለም ደረጃ እየተከሰተ ያለ በመሆኑ ኢትዮጵያዊነት እንዳለ ሆኖ ብሄርተኝነትም ልንክደው የማንችል ቁልፍ ክስተት ሆኖዋል፡፡

ፀረ-ደርግ የተሰለፉት ህብረ-ብሄራዊ ድርጅቶች (ኢህአፓ/ሜኤሶን ወ.ዘ.ተ)በአንድ በኩል በሌላ በኩል ደግሞ ብሔራዊ ድርጅቶች (ሕወሓት/ ኦነግ ወ.ዘ.ተ) ነበሩ፡፡ ኢህአፓ ከነበረው የምሁራን ስብስብ፣ የአባላቱ ቆራጥነት እና የተሻለ ዓለማዊ እውቅና ለምን አላሸንፈም የሚል ጥያቄ ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩት ቢችልም ከኢህአፓ ተገንጥሎ የወጣው ኢህዴን ግን ከብሄራዊ ድርጅቶች ጋር ተሰልፎ ድል መጎናፃፉ አመለካች ነው፡፡ በኔ እምነት ኢህአፓ በመጀመሪያ የራስ እድል በራስ በመወሰን እስከ መገንጠል የሚል አቋም ቢኖረውም በሂደት ግን ብሄራዊ ድርጅቶች ለሃገራዊ የመደብ ትግል አደናቃፊዎች ናቸው የሚል አቋም በመያዙ እና ብሄራዊ ትግል ቢኖርም በኢህአፓ ስር መሆን አለባቸው የሚል ግትር አቋም በመያዙ እና ህዝቦችን ማሳለፍ ባለመቻሉ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት እና ብሄርተኝነት ጎን ለጎን ያሉ ማንነቶች ናቸው፡፡ በአብዛኛው ከሃገራዊ ማንነት ይልቅ ብሄርተኝነት ጎላ ብሎ የሚታይበት ሁኔታ እንገኛለን፡፡ ኢትዮጵያዊነት እና ብሄራዊነት ያላቸውን ተነፃፃሪ ነፃነት መሰረት አድርገን አዋህደን ፖለቲካው ካልተመራ አንደኛውን መካድ ጥፋት እንጂ ሰላም ዴሞክራሲ እና ልማት አያመጣም፡፡

የኢትዮጵያዊነት እንቆቅልሽ በ1899 (ከመቶ አስራ አንድ ዓመት በፊት) በደብተራ ፍስሀ ጊዮርጊስ ዓብይዝጊ ‹‹ታሪክ ኢትዮጵያ›› በሚለው የትግርኛ መጽሐፍ ኢትዮጵያ ስም አጠራር በግርድፉ ወደ አማርኛ ሲተረጎም እንዲህ ይላል፡፡ ከሰባቱ ከንዓናውያን አንዱ የሆነው ‹ኩሳ› የደረሰውን አገር በልጁ በኢትዮጵያ ሰየመው፡፡ ሃገርዋም ኢትዮጵያ ተባለች፡፡ በሳቸው አፃፃፍ አገራችን በሶስት ስሞች ትጠራለች፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሳባ፣ እና ሀገረ አግዓዚ/አግዓዚት፡፡

ባሕሩ ዘውዴ (2007፡01) ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለው ስያሜ መሰረቱ ግሪክ ሲሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት በውል ከታወቀችው ከግብፅ በስተደቡብ የሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል የሚጠራበት አጠቃላይ ስም ነበር” ይላል፡፡ ‹አዲስ ጊዜ› ተብሎ በሚጠራው መጽሔት የመስከረም 2010 እትሙ እንደዘገበው ፓስተር በንቲ ኡጁሉ የተባሉ ፕሮቴስታንት መሪ ‹‹ኢትዮጵያ በሚለው መጠሪያ ግሪኮች ያወጡልን ሲሆን ትርጉሙም ‹የተቃጠለ ፊት› በመሆኑ እና እኛን ዝቅ የሚያደርግ የዘረኝነት ስያሜ በመሆኑ በ‹ኩሽ› እንጠራ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ 45 ቦታ ኢትዮጵያ ተብሎ የተጠቀሰውን በኩሽ እንዲቀየር አድርገዋል፡፡

አዲስ ጊዜ ‹‹ዛሬ ያለችው የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ብቻ ሳትሆን መላው አፍሪቃም የኢትዮጵያ ግዛት ስለነበረ ኢትዮጵያ ይባል ነበር›› እና የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ምንጫቸው/ቅድመ አባት ኢትዮጵያ የሚባል ሰው እንደሆነ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ በሰጡት ቃለ መጠይቅ እንዳሉ አስነብቦናል፡፡ 100 ሚሊዮን በተለያየ መልክአ ምድር፣ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ የተለያዩ ውብ ተክለ ሰውነት እና ዘር ያለው ያውም በአራት ሺህ ዓመታት ከአንድ ሰው ነው የተገኙት የሚለው ለማመን በጣም ቢያስቸግርም መላው አፍሪካ የኢትዮጵያ ግዛት ነበር የሚለውን ግን ከዓለማዊ ሕግ (international law) አኳያ የይገባኛል መብት ማንሳት አይገባንም ወይ የሚል ጥያቄ ይጭራል፡፡ (ተረት ተረት ከፕሮፌሰር ዘንድ አንጠብቅም ከሚል እሳቤ)

ዶክተር ላጲሶ ጌ ዴሌቦ ‹‹በኢትዮጵያዊነት ታሪካዊ መስረቶችና መሳሪያዎች (1999፡ 04) በሚለው መጽሐፋቸው ‹‹የኢትዮጵያ›ና የኢትዮጵያውያን ታሪካዊ መነሻ ስያሜ በሚመለከት ከተጠቀሱት ጥንታዊ የአካባቢው ህዝቦች በተለይም ሁለቱ ግብፃውያንና አይሁዳውያን ‹ፑንት› ግሪኮች ‹ኢትዮጵያ› አረቦች ደግሞ ‹ሀበሻ› በተሰኙ የአገር እና የህዝብ ስሞች እንዲጠሩ ከታሪክ መረጃና ትምህርት ታውቋል›› ይላሉ፡፡

የሀገራችን አጠራር ታሪክ በዝርዝር ማየት ለዘርፉ ባለሙያዎች ትተን አሁን ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ያለን ህዝቦች ሰላም ዴሞክራሲ እና ልማት ለማስፈን በምናደርገው ያላሰለሰ ጥረት በጋራ እና የግል በማንነታችን እጅጉን የተሳሰረ ስለሆነና የድሮ ማንነታችን የአሁኑ እኛነታችን የወደፊቱ ኢትዮጵያዊነት ምን መምሰል እንዳለበት የጋራ መግባባት መኖር አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡

ሁላችንም አንድ ዓይነት የሓላ ታሪክ (background) ስሌለን ማለት መሐመድ ድሌቦ፣ ገመቹ፣ ሐጎስ፡ደስታ፤ ዓይሻ፣ወ.ዘ፣ተ ስለሆን በአንድ በኩል ከደቡብ፣ ምዕራብ፣ ምስራቅ ሰሜን፣ ከደጋ፣ ወይናደጋ፣ ቆላ ወ.ዘ.ተ በሌላ በኩል የተገኘን በመሆናችን የኢትዮጵያዊነት ያለን አረዳድ የተለያየ ሊሆን እንደሚችል እያወቅን ለሁላችን በሚያጋራ የኢትዮጵያዊነት እስቴች ላይ አትኩረን ለመስራት መረባረብ ለሁላችንም ይጠቅመናል፡፡ አንድ ባለታሪክ ሌላው ባዶ እንደሆነ የሚያመለክት ኋላቀር አስተሳሰብ ትተን፡፡ ነፃነታችን ጠብቀን የኖርንን ሃገር በአንድ አካባቢ በመኖራችን ደግሞ የህዝቦች ማህበረ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ መስተጋብር የተፈጠረች አገር ዋና እሴቶችዋ እንደሆኑ በማመን ወደፊት መመረሽ ይጠበቅብናል፡፡ የአሰፋ እንደሻው (1993፡ 13) የኢትዮጵያ ብርቅነት ከገለፀ በኋላ አሁን ያለን ኢትዮጵያውያን የመልካም እሴቶችዋ ብቻ ሳይሆን የከፍተኛ እዳ ተሸካሚዎች መሆናችንን በማመልከት የገለፀው አባባል ጠቃሚ ሆኖ አግኝቸዋሎህ፡፡ ‹‹ከነዚህ መሃል የመንግስቷ አወቃቀር፤ የብሄረሰቦችና የቋንቋዎች ስብጥር የሚያልቅ ትርምስና ግብግብ አስከትለዋል ከውጭ ወራሪዎች መዳፍ ማምለጥ ቢቻላትም የተፈጥሮና ሰብአዊ ሀብቶችዋን በቅጡ አቀናጅቶ የሚመራት መንግስት በማጣቷ ትርምሱና ግብግብ እንደቀጠለ ነው›› ይላል፡፡

የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ

የኢትዮጵያ ፖለቲካ በማንነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነት፣ የብሔር ማንነት፣ ሃይማኖታዊ ማንነት፣ መደባዊ ማንነት፣ ፆታዊ ማንነት ወ.ዘ.ተ ለየብቻም ተሳስረውም ይገኛሉ፡፡ በሃገራችን ጎልተው የሚታዩት የኢትዮጵያዊነት እና ብሔራዊ ማንነት ቅራኔዎች ናቸው፡፡ አንዳንድ ምሁራን የኢትዮጵያዊነት እና ብሄር ማንነት ቅራኔ የለም፡፡ የአማራው ልሂቃን የነበራቸውን የበላይነት ለማስጠበቅ የኢትዮጵያዊነት ሽፋን ስለሚላበሱ ነው የሚሉ አሉ፡፡

በኔ እምነት ደረጃው ሊለያይ እንጂ ሁሉም/አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝቦች ኢትዮጵያውያን ነን ስለሚሉ በብሔራቸው እና በኢትዮጵያዊነት ቅራኔ መኖሩ የማይቀር ነው፡፡ አንድ ግለሰብ በቤተሰቡ ውስጥ የተለያዩ ቅራኔዎች ይኖራሉ፡፡ ያ ቤተሰብ ደግሞ ከሌሎች ቤተሰቦች ቅራኔ ይኖረዋል፡፡ ጎሳ፣ ነገድ፣ ብሔር፣ አገር እያለም በተመሳሳይ መንገድ ስለሚሄድ ኢትዮጵያዊ ማንነት እና የብሄር ማንነት ቅራኔ መኖሩ አይቀርም፡፡ ዋናው ጉዳይ እነዚህን ቅራኔዎች እንዴት አድርገን በሰላማዊ እና ዘላቂነት ባለው መንገድ እንፍታው ነው መሆን ያለበት፡፡

ቅራኔዎችን ለመፍታት የኋላ ታሪካችን፣ መንፈሳችን እና ስሜታችን ብቻ ሳይሆን የዛሬ ና የነገ ማንነታችን (ጥቅሞቻች እና እሴቶቻችን) ለማስጠበቅ አንድነት በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡ አሁን ባለን ዓለማዊ ሁኔታ እንኳን አንድ ብሔር አንድ አገር፣ በማደግ ላይ ያለን አገር ሆነን አደጉ ተመነደጉ የሚባሉት አገሮች እንኳን በእውነት ነፃነታቸው ደህንነታቸው እና ልማታቸው ለየብቻ ለማረጋገጥ አስቸጋሪ መሆኑን ተገንዝቦው የተለያዩ የህብረት/አንድነት መንገድ ለመፍጠር የሚታገሉበት ሁኔታ እናያለን፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ሳንበታተን የጋራ እሴቶቻችን መሰረት አድርገን የሁሉም ብሔር/ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ንዋታዊ ጥቅሞችና እሴቶች በእኩልነት በመጠበቅ አንድነታችንን በማጠናከር ልማታችን፣ ድህነታችንን እና ነጻነታችን ማረጋገጥ ይገባናል፡፡ በማያቋርጠው የኢትዮጵያዊነት እና ብሔራዊነት ቅራኔዎች የተለያዩ አመለካከቶች ይንፀባረቃሉ፡፡ በነዚህ ላይ በሰከነ መንፈስ ተወያይተን የሚበጀን የጋራ አስተሳሰብ መያዝ ይጠቅመናል ባይ ነኝ፡፡ በሦስት መሰረታዊ አመለካከቶች ከፍያቸው አሎህ፡፡ 

1/ አንድ ሀገር፣ አንድ ህዝብ አንድ መንግስታዊ ሃይማኖት አንድ ቋንቋ መንግስት፡-

ይህ ከአንድ ንጉሠ ነገስት (ሞኣ አንበሳ ዘእምገደ ይሁዳ) አንድ መንግስታዊ ሃይማኖት (ኦርቶዶክስ) አንድ ህዝብ (ኢትዮጵያዊ) አንድ ሀገር (ኢትዮጵያዊ) ከሚል የሚመነጭ አስተሳሰብ በኔ አመለካከት አግላይም ጠቅላይም ብቻ ሳይሆን የሞተውን ስርዓት ከመቃብር አውጥቶ ህያው ለማድረግ የሚሞክርም ይመስለኛል፡፡

አግላይ ነው ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውሰጥ ከ44% የማይበልጡት የኦርቶዶክስ ተከታዮች ማዕከል በማድረግ ከ56% በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ያገላል፡፡ ዘእምነገደ ይሁዳ የሚባለው አስተሳሰብም የከፋው አግላይ ነው ምናልባት ከ99% በላይ የኢትዮጵያ ህዝቦችን የሚያገል ነው፡፡ ባህሩ ዘውዴ (2008፡05) ‹‹… የሷ (ንግስት ሳባ ማለቱ ነው) ጉዞና ጉዞው ያስከተለው የቀዳማዊ ምኒልክ መፀነስ ሥርወ መንግስትን እንጂ የአገርን ታሪክ ልደት ስለሚያበስር ነው፡፡ “

አግላይ ነው ስንለው የሰሜኑን ታሪክ ብቻ የኢትዮጵያ ታሪክ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን የሰሎሞናዊ ሀረግ መጥቀሱ፡፡ የዛግዌ አገዛዝ ሕገ ወጥ እንደነበር ለማመልከት ጭምር ነው፡፡ ላሊበላን ማዕከል ያደረገውን የኢትዮጵያ ስልጣኔን ለማግለል የሚቃጣ አባባል ነው፡፡ ይህ አባባል የአገራችን ህዝቦች ልዩ ልዩ ታሪኮች እንዳልነበሩ ያደርጋል፡፡ በደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ምስራቅ ስልጣኔዎች ባህልና ቋንቋዎች በኢትዮጵያዊነት ያለውን ቦታ የሚያገል ነው፡፡

ላጲሶ (1999፡81) ዩኔስኮን (UNESCO) ጠቅሶ ሀገራችን በሁሉም አቅጣጫዎች የደረሰችበትን የስልጣኔ ማማ ያበስረናል፡፡

የኢትዮጵያ የፖሌኦንቶሎጂና የአርኪዮሎጂ መረጃዎች ግኝት – መረጃ የተገኘበት ስፍራ የመረጃ ዕድሜ በዓመት የግኝቱ ዘመን

* የሀዳር ሰው አጽም ከ4000000 ዓመት በላይ 1973

* የኦሞ ሰው አጽምና የድንጋይ መሳርያ ከ2000000 ዓመት በላይ 1967-1968

* የመልካ ቁንጥሬ ሰውና የድንጋይ መሳርያ ከ1.5፣000000 ዓመት በላይ 1965-1976

* የሊጋኡዳ ዋሻ እንስሳት ስዕል 4000 ዓመት 1970-1978

* የሻቤ ዋሻ እንስሳት ስዕል 3000 ዓመት በ1920ዎቹ

* የሸዋ፣የአሩሲ፣ የሐረር፣ የሲዳሞ ትክል ድንጋይ ሐወልቶች የብዙ ሺህ ዓመታት በ1920ዎቹ 

* የደአማት-አክሱም የድነጋይ ላይ ጽሑፎች 2500 ዓመታት 1959-1973

እነዚህ እና በተደጋጋሚ የሚገለጹት ደምሮ ከየትኛው የስልጣኔ ማማ ወርድን ወርደን ተመፅወች የሆንበት ታሪካችን የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ አሁንም ከዛ አሳፋሪ ውርደት ገና አልተላቀቅንም፡፡ መስፍናዊ ስርዓት ይህ ነው የሚባል ፖለቲካዊ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ መሻሻል ማምጣት የተሳነው በመሆኑ ይቺን ታላቅ አገር መቀመቅ አስገባት፡፡ አሰፋ እንደሻው (1999፡ 20) ያንን የበሰበሰ ስርዓት በዚህ መልኩ ይገልፀዋል፡፡

‹‹ስድስተኛ የሻገተው አስተሳሰብና የማህበራዊ ስርዓት እያዘገሙ ከሚያድጉት የከተማና የገጠር እንቅስቃሴዎች ይበልጥ የገጠጠና ጊዜ የማይሰጥ አደጋ ላይ ወደቀ፡፡ ረሀብ አገሪቱን በተደጋጋሚ ዓመታት የኖረ ቢሆንም የ1966/65 ድርቅ በሚልዮኖች የሚገመት የትግራይ፣ የወሎ እና የሰሜን ሸዋ ህዝብን በጠኔ መታው፤ በብዙ መቶ ሺ የሚሆነውንም ጨረሰ፡፡ ከብቱን አጋሰሱንና ሌላውን የቤት እንስሳት ጨምሮ ህዝቡን አራቆተው፡፡ የኩሩው ህዝብ ቅስም በአውሮፓ ምፅዋት ተሰበረ፡፡ ለጥቁር ዘር የነፃነት ምልክት የነበረችው ኢትዮጵያዊ ስሟ አብሮ ጠፋ፡፡›› … ዞሮ ዞሮ ያን በመሰለ መከራ የኢትዮጵያ ህዝቡ ሲመታ ባንዲራዋ የጥቁሮች የነፃነት ምልክት ሆና ከመቅረቷ በስተቀር የታሪኳ ገናናነት እና አርአያነቷ ሟሸሸ … ጥንታዊት ኢትዮጵያ የረሃብና የጠኔ ምልክት ተደርጋ በአለም ሙሉ ተናቀች›› ይላል፡፡

አንድ ህዝብ፣ አንድ ንጉሰ ነገስት ወ.ዘ.ተ የሚባል አስተሳሰብን ኢትዮጵያዊነት እንዴት እንዳዋረደ እና እንዴት እንደቆሸሸ ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ ከሁሉም በላይ የሚገርመው የንጉሠ ነገሥቱ 80 ዓመት ልደት በዓል እንዳይበላሽ ነው ድርቁ ያመጣው ረሀብ በመደበቁ ጥፋቱ ከፍተኛ የሆነው፡፡

በአገራችን ውስጥ ባሉት ብሔር ብሔረሰቦች ያሉትን ሁሉ ዓይነት ፀጋዎችን ከመጠበቅ ይልቅ የመሳፍንቱን ጥቅም ማስጠበቅ ሆነ፡፡ ለምሳሌ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ባሕርይ ያለውን ስርዓት መከተልን የኮንሶ ህዝቦች የውሃ እና አፈር ጥበቃ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዴሞክራቲክ ስርዓትን የማንገስና ድርቁን መከላከል ወደ ጆሮአቸው የሚቀርብ አይደለም፡፡

ከግዛት መስፋፋት እና አንድነት በሚመለከትም መሳፍንቶቹ የአገር ጥቅም ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም ያስቀድማሉ፡፡ እነ አክሊሉ ሀብተወልድ የኤርትራ ፌዴሬሽን እንዳይፈርስ የነበረው አሰተያየት በካሳ ሃይሉ የሚመራው የመሳፍንት ቡድን የነበረው ሙጉት እሰቲ በዘውዴ ረታ (የኤርትራ ጉዳይ፣ 427) አነብቡልኝ፡፡

መስፍናዊ ስርዓት ከዛ የስልጣኔ ማማ እየሽቆለቆለ ለረዢም ምእተ ዓመታት አውርዶ አውርዶ ወደ ውርደት ቢያሸቀነጥረንም አውሮጳዊያን አፍሪቃን ለመቀራመት ያደረጉትን ጉዞ በማደነቀፍ ነፃነታችንን ማንነታችን ጠብቀን እንድነቆይ የስቻሉንን መሪዎች ማመስገን ተገቢ ይመስለኛል፡፡ አገራችንን ለማዘምን ባደረጉት ጥረት ባስቸጋሪ ሁኔታ ሆነው ሳይሸሹ ወይም እጃቸው ሳይስጡ ሽጉጣቸውን የጠጡ የአይበገርነት ምልክት የሆኑትን አፄ ቴዎድሮስን፡ ተደጋጋሚ የውጭ ጠላቶቻችን በማሸነፍ በመጨረሻም እንገታቸው በመስጠት የመሰዋእትነት አርማ የሆኑትን አፄ ዮሓንስን፡ የኢትዮጵያን ህዝቦችን መርተው ወሳኝ የሆነውን ድል ኣድዋ ላይ በማረጋገጥ ኢትዮጲያዊነታችንን ማቀብ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪቃም ሆነ ለጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት እንድትሆንና እኛ ኢትዮጵያዊን የአካል ብቻ ሳይሆን የመንፈስ ነፃነትን እንድንጎናፀፍ ያበቁትን አፄ ሚኒልክ ናቸው፡፡

አንድ ሀገር፣ አንድ ህዝብ አንድ መንግስታዊ ሃይማኖት አንድ ቋንቋ መንግስት የሚለው አስተሳሰብ የሚከተሉት ፅንፈኞት ስለ ኢትዮጲያዊነት በዙ የሚለፈልፉ ቢሆንም ፋቅ ቢደረግ ሁሉን ትተው ለተወለዱበት የቀድሞ ጠቅላይ ግዛት ይሰለፋሉ፡፡ ተጨማሪ ፋቅ ሲደረጉ ደግሞ ለተወለዱበት አውራጃ እና ወረዳ ሌላውን በማንካሰስ አንገታችን እንሰጣለን ብለው የዉሸታቸውን ዘራፍ ይላሉ፡ 

2/ አግላይ ብሔርተኝነት

ብሔርተኝነት የአንድ ማንነት የጋራ ንዋታዊ ጥቅም እና እስቴች በውስጥ የሚንፀባረቅበት ከውጭ ደግሞ መለያ በሚሆንበት ታሪክ፣ መንፈስ፣ ስሜት ብቻ ሳይሆን እውነታ (objective) ምክንያቶች ያሉት የሚያድግ፣ የሚሻሻል የሚዘምን ፖለቲካዊ አይዲዮሎጂ ነው፡፡ ይህ በዓለም ደረጃ በማህበራዊና ፖለቲካዊ መግለጫዎች ያሉት ክስተት አግላይ ሊሆን እንደሚችል ሁሉ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ሊሆን ይችላል፤ እንደማንኛውም ህብረተሰባዊ ማንነት፡፡ ለንፅፅር እንዲበጀን በመጀመርያ ዴሞክራሲያዊ ብሄርነተኝነት እንይ፡፡

ዴሞክራሲያዊ ብሄርነተኝነት ስንል የጋራ ንዋታዊ ጥቅም እና እሴቶች እንዳሉ ሁሉ በውስጡ የተለያዩ ንዋታዊ ጥቅሞች እና እሴቶች እንዳሉ ተቀብሎ አቃፊ አሳታፊ ሲሆን ነው፡፡ በአንድ ብሄር ውስጥ ገበሬ፣ ላብአደር፣ ባለሃብት፣ ምሁር፣ ወዘተ ያሉ ማንነት በመኖራቸው እነሱም የየራሳቸው ንዋታዊ ጥቅምና የአስተሳሰብ ብዙኃነት ያላቸው መሆኑን የሚቀበል ነው፡፡ በብሄር ውስጥም አንድነት እና ልዩነት የሚያስተናግድ ነው፡፡

ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ሌሎች ብሔር/ብሄረሰቦች ጋርም በጋራ መስተጋብር ያዳበሩት ታሪክ፣ ባህል፣ አስተሳሰብ ያለመሆኑ ተቀብሎ በተለይ አሁን ባለው ዓላማዊ ሁኔታ ተባብሮ በአንድነት ካልሆነ በስተቀር ንዋታዊ ጥቅሞቻችንን እሴቶችን የማሳደግ የመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ደህንነቱም አደጋ ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል ተረድቶ አንድነትን የሚመኝ፣ ለአንድነት የሚታገል ግን በእኩልነት የተመሰረተ አስተሳሰብ ነው፡፡

አግላይ ብሄርተኝነት ስንል በውስጡ ያለውን አንድነት እና ልዩነት የማይቀበል ስለዚህም አንድ የብሔር አባባል (narrative) ይዞ ልክ እንደጠቅላይ እና አግላይ ኢትዮጵያዊነት አንድ ህዝብ፣ አንድ ብሄር፣ አንድ ሃይማኖት/ቋንቋ ወ.ዘ.ተ የሚል ነው፡፡ የ‹አንድ ልብ› አባባል የሚከተል ነው፡፡ ከሌሎች ህዝቦች ያለውን የጋራ ታሪክ/ባህል መስተጋብር የሚክድ የሚያስታውሰው ከሆነም በጎውን ደብቆ የተፈፀሙትን በደሎች ብቻ እያንሸራሸረ የሚኖር አስተሳሰብ ነው፡፡ አግላይ በመሆኑ በውስጡም ልዩነት የማይቀበል በመሆኑ ብሄራዊነትን የሚሸረሸር እንጂ የሚያጠናክርም አይደለም፡፡

አግላይ ብሄርተኝነት በኢትዮጵያ በተለያየ መንገዶች ይገለፃል፡፡ ኢትዮጵያችን የጋራ እሴቶች እንደሌሏት እና የህዝብ ለህዝብ መስተጋብር እና ማህበራዊ ገጽታ እንዳልነበረ እና በምኒልክ ዘመን የተገጣጠመች በጎ ገፅታዋን በመደበቅ አገር በመመስረት ሂደት ያጋጠሙትን ግፎች ብቻ በማስጮህ አገሪቷ የአንድ መሪ እና ተከታዮቹ አድርገው እንዲታይ ያደርጋሉ፡፡ ነፃነት በዋጋ የማይገመት (priceless) መሆኑን ዘንግተው ለሰው ልጅ ማንነት ያለው ትርጉም በማሳነስ በጋራ ቅኝ ገዢዎችን ያሳፈርንበትን የጥቁር ህዝቦች አለኝታ የሆነውን የአንድነት ማንነት ያንኳስሳል፡፡ ከላይ የተገለጹት የፈጠራ ስራዎች እና የተደነቀ ታሪካዊ ቅርሶቻችን ህብረተሰብ እንዳያውቅ የጋራ እሴቶችን እንዳይንከባከብ ያደርጋል፡፡

ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በሁላችን ፈቃድና መተማመን የምትገነባ አገር መሆንዋን በመቃወም ልሂቃኑ የራሳቸውን ጠባብ ጥቅም ለማስጠበቅ በህዝቡ መካከል መሰረታዊ ቅራኔ እንዳለ በማስመሰል ህዝብ ለህዝብ ማጋጨት ሥራዬ ብለው ተያይዘውታል፡፡ ‹‹የብሔሬ ልጅ ይብላኝ›› አስተሳሰብ በመያዝ ሁላችን ኢትዮጵያውያን ለምንገነባት አገር ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት እና ኪራይ ሰብሳቢነት ለመታገል የምናደርገው ትግል ለማደናቀፍ የብሄር ከለላ ይጠቀማሉ፡፡ አግላይ ብሄርተኞች የራሳቸው ጠባብ ጥቅም ለማስጠበቅ ኢትዮጵያ ብትፈርስም በእርስበርስ ጦርነት ውስጥ ብትኖርም አይገዳቸውም፡፡

የተፈጥሮ ሀብት እና የድሮ ታሪክ ለሰላም፣ ልማት ዴሞክራሴ ወሳኝ ባልሆነበት ዓለማዊ ሁኔታ የተትረፈረፈ ሃብት አለን ወይ ታሪክ አለን በማለት ራሳቸውን አጉልተው ሌላውን አሳንሰው ያያሉ፡፡ ዋናው ኃይል የሰው ሀብት መሆኑን እና የ100 ሚሊዮን ሀብት ለሁሉም ህዝቦች በጣም ጠቃሚ መሆኑን ይዘነጋሉ፡፡

አግላይና ጠቅላይ ሃይሎች ብሔር እና ብሄረሰቦች ሲያንኳስሱ እና ማንነታቸውን ሲያበሳብሱ አግላይ ብሄርተኞች ደግሞ ግብረ-መልሱ እነሱ የመጡበትን ማህበረሰብ ማውረድ ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ አግላይ እና ጠቅላይ ኢትዮጵያዊነት እና አግላይ ብሄርተኝነት እየተመጋገቡ አገሪቱ የጀመረችውን የልማት፣ ሰላም ዴሞክራሲ ጉዞ ለማደናቀፍ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ሕብረተሰባዊ አቅማችን ሰብስበን ወደፊት እንዳንራመድ ይከፋፍሉናል፡፡ ወደኋላ ይጎትቱናል በማያባራ ጦርነት እንድንኖርም የተቻላቸውን ያህል ይሞክራሉ፡፡

ኢህአዴግ ጠቅላይና አግላይ በመሆኑ ኢትዮጵያዊነትን እያቆሸሸ ለአደጋ እያጋለጠ ነው

ባለፉት 25 ዓመታት በኢህአዴግ መሪነት የኢትዮጵያ ህዝቦች ባፀደቁት ቻርተር እና ሕገ- መንግስት እየተመሩ በአገሪቱ በአጠቃላይ ሰላም የሰፈነበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ የግለሰብ እና የቡድን መብቶች በተወሰነ ደረጃ በመረጋገጡ እና በተገኘው ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ልማት ኢትዮጵያዊነት መለምለም ጀምሮ ነበር፡፡

የአገራችን ሰላም ለሌሎች አርአያ እና የሚደርስላቸው ሆኖ ነበር፡፡ ድርቅ፣ ረሃብ መሆኑ ያቋረጠበት በዓለም ውስጥ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ካረጋገጠ አንድም መሆኑን ጀምራ ነበረ፡፡ እየተከማቸ በመጣ ብሶት ባለፊት 3 ዓመታት ሰላምዋ እየተረበሸ የመጣች አገር ሆናለች፡፡ በዚህ ከቀጠለ ልማትዋ ይጎተታል አገሪቱም ወደ አላስፈላጊ ግጭቶችም መሄድ ሊያስከትል ይችላል፡፡

በኢህአዴግ አምባገነንነት ምክንያት ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱ አደጋ ላይ ነው ያለው፤ ጠቅላይ እና አግላይ በመሆኑ ካለ ኢህአዴግ መስመር ሁሉም የጥፋት መንገድ ነው ነው›› የሚለው አስተሳሰብ ሕገ-መንግስቱን ይፃረራል ብቻ ሳይሆን አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል የሚያገል ሆነዋል፡፡ ጸረ- ዴሞክራሲ በመሆኑ ምናልባት ስባት ሚሊዮን አባላቱ (በዓላማ የተሰለፉ ከሆነ) ሌላውን ከ90 ሚሊዮን በላይ ህዝቦችን ያገለለ ነው፡፡ በስሩ የሚልከሰከሱት አጎብዳጅ ‹‹ምሁራን›› ካልሆነ የምሁር ወሳኝ አቅም የተገለሉ ሆነዋል፡፡ ተቃዋሚዎችን እንደ ፀጋ ስለማይቀበል የተደራጁትን (የእውነት ተቃዋሚዎች) አግልሎ የፖለቲካዊ ተቃውሞ ማእከሉ ወደ ዲያስፖራ ልኮታል፡፡ ግጭትም እያስከተለ ነው፤ ከድርጅቱ በአስተሳሰብ የሚለዩትን ታዋቂ ሰዎች አርቲስቶች ጠላት፣ ትምክህተኛ ጠባብ ወዘተ በማለት ያገላል፡፡ ከህብረተሰብ የሚያገኘውን አቅም አጥቶ በአንድ እጁ የሚያጨበጭብ ሆነዋል፡፡ በአይዲዮሎጂካል እና ፖለቲካዊ ቀውስ ስለተዘፈቀ ኢህአዴግ በቅርፅ (form) እንጂ በይዘቱ (content) አለወይ የሚያሰኝ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ጥርናፌ ብሎ የሚጠራው ግን አውቶክራቲክ ጥርነፌ መሰረት የድርጅቱ ዴሞክራሲያዊ ህይወት በመግደል፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን እና መጠላለፍን በማጎልበት አባሎችንም እያገለለ ነው፡፡ ይህ ውስጣዊ አሰራር ድርጅቱን ማኮላሸት ብቻ ሳያንስ ሕገ-መንግስቱን በመጣስ ፌዴራል ስርዓቱን አደጋ ውስጥ ዘፍቆታል፡፡ ሁሉም ከአንድ ማእከል እንዲፈስ በማድረግ ለፌዴራል ማእከሉ እና ለክልሎች የተሰጠውን ፖለቲካዊ ስልጣን በመዘባረቅ ‹‹organized system of irresponsibility›› የሚሉት ዓይነት ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

የፌዴራል/ክልሎች ሕገ-መንግስታዊ ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራት ወ.ዘ.ተ የራሳቸውን ተነፃፃሪ ነፃነት አግኝተው እንዳይንቀሳቀሱ አውቶክራቲክ አሰራር ጠፍሮ ይዞታል፡፡ ሲቪል ሰርቪሱም ብቃት በሌላቸው አባላቱ በመሞላቱ እና የጥርናፌ አሰራር ሽባ አድርጎታል፡፡ በመንግስት መገናኛ ብዙኃን በተመሳሳይ በተለይ ኢቢሲ የብዝኃነት እና የሕዳሴ ብሎ ቢፎግርም የጠቅላይ እና አግላይነት ቀንደኛ ማሰሪያ ሆነዋል፡፡ ጠቅላላ ስርዓቱ አግላይ እና ጠቅላይ ሆነዋል፡፡

ልክ ህዳሴ፣ ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር ያሉ ጉዳዮች ኢህአዴግ እንደሚያጨማልቃቸው ቃላቶች ስለሆኑ ትምክህተኝነት እና ጠባብነት የሚሉት አባባሎች ለመጠቀም አልፈለኩም፡፡ እንደማንኛውም ፀረ-ዴሞክራቲክ አባባሎች መሸፈኛ ስለሆነ ይቀፋል፡፡ ዛሬ ዛሬ ደግሞ ትምክህትና ጠባብነት ጠላት ከውጭ ወራሪ የማይተናነስ ጠላት ነው ተባለ፡፡ ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ›› ነው የሆነው፡፡

በኔ አመለካከትም በእርግጥ ትምክህትና ጠባብነት ኋላቀር አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ እነዚህ አመለካከቶች የሚገኙት በገበሬው፣ በላብአደሩ፣ በባለሀብቱ፣ በምሁሩ በሴቱ፣ በወጣቱ፣ በሽማግሌ፣ በፓርቲዎች እና ሌሎች አደረጃጀቶች ናቸው ሰፍረው የሚገኙት፡፡ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱት ፅንፈኞችም (ጠላት ሊሆኑ የሚችሉት) በህዝቡ ያለውን ኃላቀርነት ተጠቅመው እያጮሁ አገር ለማበጣበጥ መሞከራቸው አልቀረም፡፡

እነዚህ ፅንፈኞች አይቀየሩም፡፡ ስለዚህ ዋናው ፍልሚያ በህዝቦች ውስጥ ያለው ኋላቀር አስተሳሰብ ለማሳመን መታገል ነው፡፡ አግላይና ጠቅላይ (ትምክህትና ጠባብነት) የህዝቦች ንዋታዊ ጥቅሞች እና እሴቶች የሚፃረሩ ናቸው፡፡ በህዝቦቸ ውስጥ የሚገኝ የህዝቦች ጥቅም ክፉኛ የሚጎዳ አሜኬላ!! ህዝቦች እስከተገነዘቡት ድረስ የማይጠቀማቸው በመሆኑ ያስወጉዱታል፡፡ ህዝቦች በእነዚህ ኋላቀር አስተሳሰቦች ተጠቂ የሚሆኑት እጅግ የከፋ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ድባብ ሲኖር ነው፡፡ ፅንፈኞችም በህዝቦች ውስጥ ያለውን ስጋት፣ ጥርጣሬ፣ ውዥንብር እና ንዴት አቅጣጫ በመቀየር ህዝቡ እርስ በርሱ እንዲፋጅ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡

ዋናው ችግር ዋናው ጠላት ድህነት ና ፀረ-ዴሞክራሲ ድባብ ነው፡፡ በዋናነት ገዢዎች ስልጣናቸውን በኃይል ለመጠበቅ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ኢህአዴግ ዋናው ችግራችን ፀረ- ዴሞክራሲ ነው በሁሉም መልክ በዋናነት በአመራር ያለውን እንታገለው ከማለት ልክ እንደ ጽንፈኞች አቅጣጫ በመቀየር የሌለ ጠላት ፈጥሮ ወደ ጦርነት ገብቷል፡፡ ትምክህትና ጠባብነት የሚሉት ጠላት፡፡ የጠላት ፍለጋ ዠዋዥዌ በሞሞት ላይ ያለ ስርዓት ምልክት መሆኑን ግንዛቤ ይያዝልኝ፡፡

የዚህ ጠንካራ ፀረ- ዴሞክራሲ አመለካከት ሰለባ ከሆኑት በወቅቱ አነጋጋሪ የሆነው የሙዚቃው ንጉስ ቴዲ አፍሮን እንየው፡፡ ቴዲ ስለ ሰላም፣ ፍቅር፣ ኢትዮጵያዊነት በተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ቢሆም ተቀባይነት ያገኘ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ በአንድ በኩል የሁሉም ኢትዮጵያውያን ወኔ የሚቀሰቅስ ኢትዮጵያዊነት ሲያቀርብ በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊነትን የሚያቆሽሽ፣ አግላይ እና ጠቅላይ (እላይ እነደገለፅኩት) አመለካከት ያለውን ኢትዮጵያዊነትን ያራምዳል፡፡ ለኔ ቴዲ በተቃርኖ የተሞላ ኢትዮጵያዊነት ነው የሚያራምደው፡፡ እሱ ትክክል በመሰለው በድፍረት እና ማንነቱ በጠበቀ (መንግስትን የፅንፈኛው ዲያስፖራን) ሳይፈራ የመሰለውን እያራመደ ስላለ ትልቅ ክብር አለኝ፡፡ በርከት ያሉ አርቲስቶች ለጥቅም ሲሉ የመንግስትንና የፅንፈኛው ዲያስፖራ ጫማ ለመላስ በሚንቀሳቀሱበት ሀገር እንደ ልዩ ሃብት መታየት ይገባው ነበር፡፡

ታዋቂ ሰውን ከማስፈራራት፣ ከማገድ፣ ከመከልከል ይልቅ በነጻነት ሃሳቡ ቢያቀርብ እና ተቃርኖ አለው የሚሉ ቢቀላቀሉትና አብዛኛው ህዝቦች የሚቀበሉት ኢትዮጵያዊነት በውይይት ቢጎለብት እንዴት ጥሩ ነበር፡፡ ክልከላ እና ማፈን የአዲሱ ኢትዮጵያዊነት ባህሪ አይደለም፡፡ የተለየ ሀሳብ ከሚፈራ መንግሰት ይገላግለን!!

ኢህአዴግ ተሃድሶ ይበለው ጥልቅ ይሁን ከምሩ ከሆነ አግላይነት እና ጠቅላይነትን ነበር መታገል የነበረበት፡፡ በአመለካከት፣ በአደረጃጀት፣ አሰራር ወ.ዘ.ተ ከዴሞክራሲ ጋር የሚፃረሩትን የማስተካከል ህዝቡን በመስማት ሕገ-መንግስቱን በማክበር፡፡ ይህ ከፍተኛ የህዝብ ጊዜ ጉልበት ገንዘብ የባከነው “ ጥልቅ ተሀድሶ ” ከፖለቲካው ሙስና ወደ ጥልቅ ፖለቲካዊ ሙስና ተሸጋገረ፡፡

ከተሃድሶ አኳያ የሚታይ ፍንጭ ያለው ከኦህዴድ ይመስላል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ተጽእኖ ያመጣ ይመስላል፡፡ ‹‹ጨው ሆይ ለራስህ ስትል ጣፍጥ›› በሚል መጣጥፌ የመሰለኝን ያብራራሁ ይመስለኛል፡፡ የኦሮሞያ ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ለማ መገርሳ የተናገሩት ሆርን አፌርስ ከሚለው ዌብ ሳይት (Horn affairs) የተቀነጫጨበ ላካፍላችሁ፡፡

‹‹27 ዓመታት በኋላ በምንም መመዘኛ ደርግ ይህን አድርገዋል፤ ኃ/ስላሴ ይህን አድርገዋል እኛ ይሄን አድርገንልሃል ብለን የምንነግድበት ሸቀጥ በእጃችን የለም›› (ስርዝ የኔ)

‹‹እርግጥ ነው ንግግራችን ትልቅ ነው፡፡ ከይቅርታ ጋር ምላሳችንን አርዝመን ብዙ ተናግረናል፤ የምላሻችን ያህል እጃችን ሊደርስ አልቻለም፡፡ የችግሩ ስፍራ አላየንም አልነካንም አልወጋንም…›› (ስርዝ የኔ)

‹‹እኛ በዕውቀታችን ሁሉ ነገር አሟልተን አይደለም ሀገር እየመራን ያለነው በእውቀት መታገዝ እና መረዳት አለብን፡፡ በአዲስ ሃሳብና ጥናት መደገፍ አለብን››(ስርዝ የኔ)

‹‹አጭር እድል ነው የሰጠን እንጂ ህዝቡ ሰላም አይደለም፤ ዕድል ሰጥቶናል በመጨረሻ ዕድል፡፡ (ስርዝ የኔ)

‹‹… መስራት ያለብንን ሥራ ሰርተን ብንገኝ ኖሮ ህዝቡ ለምን ያኮርፋል? ለምን ይነሳብናል? ለምን ይቆጣል ማመስገን ሲገባው ስላልሰራን ነው ይህ አያጠያይቅም፡፡ የቤት ሥራችንን ስላልሰራን ነው›› (ስርዝ የኔ)

አዲሱ አመራር ባሕር ዳር ደረስ ዘልቆ ከአማራ ክልል መሰተዳድር በመሆን የሁለቱ ህዝቦች አንድነት ለማጉላት የተደረገው እንቅስቃሴ የሚያስመሰግን ነው፡፡ ለኢትዮጲያ አንድነት ትልቅ ትርጉም ስላለው፡፡ ከሌሎች አዋሳኝ ክልሎችም ተጠነክሮ መቀጠል ይገባዋል፡፡ በተለይ ከሶማሊያ ክልል ጊዜ መሰጠት ያለብን አይመስለኝም፡፡ ወንጀል በተፈፀመበት ተጠርጣሪዎች ወደ ፍርድ ማቅረብ ጎን ለጎን የህዝቦች አንድነት ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ የገባል፡፡

ሦስተኛ ወገን ህዝቦችን የሚያጣላ ለመፈለግ በእንዳንድ ወገኖች የተደረገው ችግሩን ውጫዊ (externilization) እንደሆነ ማስመስል ግን አደገኛ ሙከራ ነው፡፡ በብሔር/ ብሔረሰቦች መሓከል አንድነት እንዳይኖር ወሳኝ ዕንቅፋት የሚሆኑት በውስጥ ባሉት ሊሂቃን ያለው ጠቅላይ እና አግልይ አመለካከት ና ተግባር ነው፡፡ የታሪካችን አሻራ ብቻ ሳይሆን በፊታችን የተደቀኑት መሰረታዊ የስላም፣ ልማት እና ዴሞከራሲ ጥያቄዎች በጠቅላይ ና በአግላይ መንገድ ለመፍታት የሚደረግ ሙከራ ነው ህዝቦችን የሚያፋጀው፡፡

ተስፋ እየጣልንበት ያለው አዲሱ የኦህዴድ አመራር ዋናው የመጀመርያ ተግዳሮት ግን የኦሮሞ ህዝብ ሰብኣዊ እና ዴሞከራሲያዊ መብተች መስረት አድርጎ የኦሮሞ ህዝብ ቁሳዊ ጥቅሞች ና እሴቶች ማስጠበቅ ሲችል ነው፡፡ እዚህ ከተሳከለት ብቻ ነው በኢትዮጵያ ደረጃ አመራር ለመስጠት የሚችለው፡፡ የኦሮሞ ይሁን የኢትዮጵያ አንድነት የሚጠበቀው በዴሞከራሲያዊ ብሔረተኝነት አና ኢትዮጵያውነት በመሆኑ ና በጠቅላይ ና በአግላይ የሚመሰረት አንድነት ፈራሽ በመሆኑ፡፡

አቶ ለማ መገርሳ ና በዙርያቸው ያሉት ጎልማሳ ሙሁራን ስለ የኢትዮጵያዊነት መሰረት ስለ አዲሱ ኢትዮጵዊነት እና የህዝቦች አንድነት ሲናገሩ ሕገ-መንግስቱን በሚገባ የሚያውቅ፣ በእምነት ለማራመድ እና ተግባራዊ ለማድረግ ከኢህአዴግ ውስጥ ብቅ የለ አመራር እየተፈጠረ ነው እንዴ የሚያሰኝ ነው፡፡ በተግባር መረጋገጥ የለበት ቢሆንም የ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን የጥርጣሬው ጥቅም (the benefit of the doubt) ሰጥተን ሂሳዊ ድጋፍ (critical support) በመሰጠት ከጎናቸው መሰለፍ የሚገባን ይመስለኛል፡፡ ከኦሮሞ ጭፍን ድጋፍ ከሌለው ደግሞ ከብሔሬ ካልሆነ ብሎ ማኩረፍ ለሁላችን አይጠቅመንም፡፡ ከመሀል ኢትዮጵያ ከኦሮሚያ፣ ኢትዮጵያን ለወደፊት የሚያራምድ አመራር ብቅ በሚልበት ጊዜ ዘረኝነት የማያጠቃን ኢትዮጵያውያን ቢያንስ ቢያንስ እስከ እንየው የእውነት መሆኑንን እያረጋገጥን ስንሄድም ሙሉ ድጋፋችን መስጠት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ክልሎች የሚማርበት ሁኔታ መፍጠር ተያይዘን ልማትን ሰላምን እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችንን መገንባት ይገባናል፡፡

በ1984 ዓ.ም ያጋጠመኝን ላካፍላችሁ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ተመድቤ ስላልነበረ ከብዙ ምሁራን ጋር ስለ አገራችን ሁኔታ ብዙ ጊዜ እናወራ ነበር፡፡ ደርግ በመወገዱ ሁሉም ደስታቸውን ይገልፁ ነበር፡፡ ስለቻርተሩ ስናወራ የመገንጠሉ ስጋት እንዳላቸው ቢገልፁም ይዘቱ ይስማሙበት ነበር፡፡ አንዳነዶቹ ግን በማይገባኝ ነገር ያልተዋጠላቸው ነገር እንዳለ ግን ይሰማኝ ነበር፡፡ አንዱ ወዳጄ ሲነግረኝ የተወሰኑት የማይቀበሉት በቻርተሩ ቁምነገር ሳይሆን አቀንቃኙ እና የኢህአዴግ ኮሩ ወያነ (ከትግራይ) መሆኑ ነው አለኝ፡፡ ለማመን አቃተኝ ስለኢትዮጵያዊነት ብዙ ይናገራሉ ያለቅሳሉ፡፡ እዬዬ ይላሉ እነዚህ ጥቂት ሰዎች ቢሆንም መሪዎች ከአማራ ካልሆኑ የማይቀበሉ ሆኑ፡፡ የዲያስፖራው ፅንፈኛም የነዚህ ተቀጥያ ነው የሆነው፡፡ አይ ዘረኝነት!!

ኢትዮጵያን ከገባችበት ማጥ የሚያወጣ ኮር ሃሳብ ከየትኛው ይምጣ እውነት ኢትዮጵያዊን ነን የምንለው መሰለፍ የሚያርብን ይመስለኛል፡፡ ህወሓት እና ብአዴን አብዛኛው ተቃዋሚዎችም ምንም ተራማጅ አመራር ለመስጠት በማይችሉበት ወቅት በአክሱም፣ ላሊበላ፣ ጎንደር፣ ስልጣኔዎች በትጥቅ ትግል በነበረው ሚና እየተኮፈስን መኖር ለጥፋት ካልሆነ ለልማት አይሆንም፡፡

ባለፈው ጥቂት ሳምንታት ዘርን ማእከል ያደረገ የሚመስል ጥቃት በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ሲታይ የነአቶ ለማ አመራር በንግግር ነው እንዴ የሚቀረው የሚል ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም፡፡ ተገቢ ስጋትና ጥያቄ ነው፡፡ የክልሉ መስተዳደር ሁኔታውን በአስቸካይ መቆጣጠርና ወንጀለኞችን ወደ ፍረድ ማቅረብ ተገቢ ይሆናል፡፡ ገና በጅምር ያለ እንቅስቃሴ ስለሆነ ተራማጅ ሃሳቦች ያለው አመራር ቢኖርም ወደ በየደረጃው ያለው አመራር እና ወደ ህዝቡ ዘልቆ ኃይል እስኪሆን ድረስ ጊዜ መጠየቁ አይቀሬ ነው፡፡

በዛላይ በአዲስ አመራር ተራማጅነት ስጋት የገባቸው ኃይሎችም እንቅፋት ቢፈጥሩ የምንጠብቀው ነው፡፡ የኦሮሞ ሀዝብ እድል ሰጥቶናል እንዳሉት ሁሉ እኛም በ1966 የልጅ እንዳልካቸው መኮንን ካቢኔ ‹‹ፋታ ሰጠኝ›› አይነት ጊዜ መግዣ ሳይሆን የሚወሰዱትን እርምጃዎች እያየን በተለይ በኦሮሚያ ውስጥ በሚያካሄዱት ዴሞክራሲን የማስፈን ሂደት እየመዘንን ጥንቁቅ ድጋፋችን መስጠት የሚገባን ይመስለኛል፡ 

3/ መሰረት ያለው ወሰን በሌለው የህዝቦች መብት የሚቀዳ ኢትዮጵያዊነት

ማንነታችንን እንደብዙሃነታችን ሰፊ አርጎ የመተርጎም ነጻነት የሚሰጥ ሕገ መንግስት አለ (ኖላዊ መልዐከ ድንግል (horn affairs)) ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሟላ የህዝቦች መብት መሰረት አድርጎ እነዚህን መብቶች ለማረጋገጥ ብቻ ሌላ ተግባር የሌለው መንግስት የሚያቋቁም ሕገ-መንግስት አለን፡፡ ዋናው መመዘኛ የህዝቦች መብቶች ያደረገ ኢትዮጵያዊነት በቀጣይነት ለመገንባት ያለው ሕገ- መንግስት፡፡

የ1987 ሕገ-መንግስት መግቢያውን በሚገባ በማንበብ እየተገነባ ያለው ስርዓት ምን እንደሆነ ማወቅ ይቻላል፡፡ አንዳንዶቹን ልጥቀስ

‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦች ሀዝቦች በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን፣ የራሳችንን እድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣ በነፃ ፍላጎታችን፣ የሕግ የበላይነት፣ እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን ተነስተናል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ሀገራችን የራሳችን አኩሪ ባህል ያለን፤ የየራሳችን መልክዓ ምድር አሰፋፈር የነበረን ያለን፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስረን አብረን የኖርንበትና የምንኖርበት ሀገር በመሆንዋ፣ ያፈራውን የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለን ስለምናምን››

‹‹መጪውን የጋራ እድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን የማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል›› ይላል፡፡

በዴሞክራሲ ትውልድ በአግላይና ጠቅላይ ጽንፍ አመለካከት ወጊድ ብሎ ይህን ሕገ-መንግስት ተግባራዊ እንዲሆን ኢትዮጵያ ትጣራለች፡፡

በጠንካራ ክልሎች ኢትዮጵያችን ትለምልም

ከ95% በላይ የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚኖሩት በክልሎች ነው፡፡ ልማት፣ ዴሞክራሲ የሚገነባውም ሰላም በዋናነት የሚረጋገጠው በነዚህ ክልሎች የሚደረግ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ፌደራል መንግስት ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፈቃዳቸው የሰጡት ስልጣን ተጠቅሞ እነሱ መስራት የማይችሉትን በሕገ-መንግስቱ መሰረት እያሰራ ክልሎችን ማጠናከር ማለት የጋራ እሴቶቻቸውን የማጎልበት እና የአንድነት ተምሳሌት የመሆን ጭምር ነው፡፡

ሀገራችን የምትለማው ሁሉም ማንነቶች እንደየአቅማቸው በተሟላ መንገድ በግንባታው ያለ ምንም ገደብ ሲሰለፍ ነው፡፡ ቀጣይነት ያለው ሕገ-መንግስት መሰረት ያደረገ ማንነቶች እንቅስቃሴ ኢትዮጵያዊነት፣ ብሄርተኝነት፣ ሃይማኖት፣ መደቦች፣ ፆታ፣ ምሁራን ወጣቶች ሽማግሌዎች ሁሉም በሕግ መሰረት መብታቸውን ለማስከበር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ግዴታቸውን እየተወጡ የሚያደርጉት ሁለንተናዊ ትግል ነው ኢትዮጵያ የምትለመልመው፡፡ በተወሰኑ አካሎች ብቻ አብዛኛውን ጎናችንን በልተው ሰላም ልማት፣ መረጋገጥ የሚቻል አይመስለኝም፡፡

ህዝቦች በሁሉም ዓይነት አደረጃጀት (የሌላውን መብት ሳይነኩ በሕግ መሰረት) መሰለፍ ሲችሉ ነው አገራችን በከፍተኛ ፍጥነት የምታድገው ልማት፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲ ያላቸው ዲያሌክቲካዊ ቁርኝት ማለት ያለ ልማት ዴሞክራሲ ያለ ልማት እና ዴሞክራሲ ሰላም እንደማይኖር ሁሉ ያለ ሰላም ልማት እና ዴሞክራሲ በጭራሽ የማይታሰቡ ናቸው፡፡

በኔ አመለካከት ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት ለመገንባት ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ያስፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት መሰረት ያደረገ ደልዳላ ክልላዊ መንግስት መኖር ኢትዮጵያዊነት ህያው እንዲሆን መሰረት ይጥላል፡፡ ህዝቦች ከፌደራል መንግስት በቀጥታ የሚገናኙት በቀጭን ገመድ ነው፡፡ ወይም ግንኙነቱ የላላ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ብሎም የሕግ የበላይነት፡ግልፅነት ና ተጠያቂነት ሲሰፍን ልማት ሲፋጠን ሰላም ሲደለድል የእውነት ኢትዮጵያዊነት ለመገንባት ወሳኝ እርምጃ ተወስደዋል ማለት ነው፡፡ ፖለቲካዊ መብቶቹን፣ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶችን የምታሟላ ደህንነቱ የተጠበቀ ወጣት ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ አያልምም፡፡

አንዳንድ ምሁራን አሁን ያለው አግላይ ብሄራዊነት የተስፋፋው ብሄር-ተኮር የሆነ ፌዴራላዊ ስርዓት በመመስረቱ ይላሉ፡፡ እኔ ግን የተሳሳቱ ይመስሉኛል፡፡ ቅድመ 83 ኢትዮጲያ በሁሉም አቅጣጫ በነፃነት ድርጅቶች ጦርነት ስትናወጥ የነበረችው ደርግ ብሄር-ተኮር የሆነ ፌዴራላዊ ስርዓት ይከተል ስለነበረ አይደለም፡፡ ዋናው ችግር ጠቅላይ እና ኢ-ዴሞክራቲክ ፌዴራል መንግስት መኖር እና ልፍስፍስ የክልል መንግስታት በመኖራቸው ነው፡፡

በምፅዋት የሚተዳድሩ ክልሎች ተይዞ ፡ሁሉም ነገር አንጋጦ ወደ አዲስ አበባ የሚያይ ሁሉም ችግሮች ከወደ ፌዴራላዊ እንደሚመጣ አድርገው በመጮህ ኢትዮጵያዊነት ይሸረሽራሉ፡፡ ጠንካራ ክልል የህዝቡን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚጠብቅ በመሆኑ ህዝቡም በራሱ የሚተማመን በመሆኑ ሕገ-መንግስታዊ ያወቀለትን ስልጣን በሚገባ የሚጠቀም እና ፌደራል መንግስቱ የጠቅላይነት ባህሪ ሲያሳይ በጊዜው የሚያስተካክል መሆን ይገባዋል፡፡ እኛ ጥሩ ብንሰራም ፌዴራል መንግስት እየቀጣን ነው የሚል ልፍስፍስ ክልል፣ የገዥው ፓርቲ አባል ሆኖ እዛ ሳይታገል አድልዎ አለ እያለ ህዝብ ለህዝብ የሚያጋጭ አጎብዳጅ ክልል ወ.ዘ.ተ ስላለን ነው፡፡

ብሄር ተኮር ፌደራል ስርዓት እንደማንኛውም የአስተዳደር ዘይቤ ችግሮች ሊኖሩት ቢችሉም (ፍፁም የሚባል ስርዓት የለም እና) በ25 ዓመት ላገኘነው ሰላም እና ልማት መሰረታዊ ንጣፍ አስቀምጧል፡፡ በዴሞክራሲ ችግር ሲኖር ፌዴራል ስርዓቱ (I.C.U) ስለሚገባ ነው አሁን ያለው ችግር፡፡

እንደ እኔ ብሄር ተኮር ፌዴራላዊ ስርዓት አያስፈልግም ማለት ብሄር ብሄሮች የሉም ወይም ብሄር/ብሄረሰቦች ራሳቸውን ማስተዳደር አይፈልጉም እንደማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ህዝቦች መደበላለቅ ሁሉ አቀፍ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መርሀ ግብሮች የተመሰረተች ማለት የብሄሮች ማንነት ጠፍቷል ማለት አይደለም፡፡ እንኳን በኛ መስፍናዊ ስርዓት ከልማት ጠፍሮ ያስቀራት በጣም ዝቅተኛ ታህታይ መዋቅር (infrastructure) ያላት አገር በኢንዱስትራላይዜሽን አብዮት ያለፈ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተካኑ በጣም የረቀቀ የኮሙኒኬሽን እና ትራንስፖርት ያላቸው እንደ ታላቋ ብሪታኒያ፣ ቤልጅየም፣ ስፔን ወዘተ ያሉት ብሔሮች ማንነታቸውን እየተጠናከረ እንጂ እየተዳከመ አልሄደም፡፡

ኢትዮጵያ ዛሬ እና ነገ ቁጥር 3 (2008፡90-91) አሰፋ እንደሻው ስለብሄርተኝነት ህልውና እንዲህ ይላል፡፡

‹‹ዛሬ ማንም፣ የትም ያለ ዜጋ ሁሉ ብሄርና ብሄረሰብን እንደ ቋሚ መገልገያዎች አድርጓቸዋል፡ (አናውቅም አልሰማንም፣ አንቀበልም፣ አሻፈረን ከሚሉት በጣም አነስተኛ ክፍሎች በስተቀር)›› ቀጥሎም ‹‹የኢትዮጵያ ማህበረሰባዊ ውጥንክር በተለይ የብሄረሰባዊ ክፍፍል በዓለም ላይ የተለየና አስቸጋሪ ተደርጎ ይናፈሳል፡፡ የትም አገር የሌለና ለውድቀቷ የሚያመቻች ነው ብለው የሚያምኑ በርካታ ናቸው፡፡ ነገር ግን የብሄረሰቦች ህልውና ሰዎች በአሻቸው መልክ የሚፈጥሩት፤ ቀጥቅጠው የሚሰሩት ክስተት አይደለም››

በቁጥር አነስተኛ ከሆኑ ብሄረሰቦች በሚመለከትም እንዲህ ይላል፡፡

‹‹የአጼ ቴዎድሮስ ዝርያዎች የሆኑት ቅማንቶች ጠፉ፣ አማራው ውስጥ ገብተው ቀለጡ ከተባለ ከስንት ዓመታት በኋላ እንደገና ለማንሰራራት መሞከራቸው ሙሉ በሙሉ ከመንግስት ባለስልጣኖች እኩይ ቁስቆሳ የተነሳ አድርገው በጥያቄያዎችን ተገቢነት ለመቀበል አሻፈረን ያሉት በርካታ ናቸው፡፡ ባለስልጣኖች ቆሰቆሱ አልቆሰቆሱ ቅማንትነታቸው መነሻ አድርገው የራሳቸው ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋና አስተዳደር በጃችን እናስገባለን ቢሉ ምንድነው ጥፋቱ?

አንድ ሰው ኩናማ ነው ሌላ አፋር ነው ወ.ዘ.ተ ብሎ ማመልከት በሬ ቀንድ አለው፤ ላም ጡት አላት፣ ሰዎች በአብዛኛው ሁለት እጅ አላቸው ከሚያሰኘው ትረካ የሚለይ አይደለም፤ በሚል ህልውናቸው (objective existence) የብሄረሰቦች ይገልፃል፡፡ ብሄሮች በየጊዜው እየፈረሱ እና እየተገነቡ (de-constructed and constructed) የሚቀጥሉ ሲሆን ተነፃፃሪ ነፃነታቸውና ህልውናቸው አላቸው፡፡ ከ50 ዓመት በፊት የተጻፈላቸው ብሄር እና ብሄሮች 1983 በፊት ‹‹ነፃ አውጪ›› ድርጅት የነበራቸው እና በ1987 በሚገባ የተደራጀች ብሄር ብሄረሰቦች የሉም፤ አልሰማሁም የሚል ድንቁርና ድርቅና ምን ይባላል፡፡ በድሮ መኖር፣ ወይም ቆሞ ቀር አመለካከት ይሉሃል ይሄ ነው፡፡

ሕገ-መንግስቱ ያወቀላቸው መብቶች ተጠቅመው በተወሰነ መልኩ ማጣጣም ቢጀምሩም በጠቅላይ ፌደራል መንግስት በመነጠቁ፣ ልፍስፍሶች የክልል መንግስታት መከላከል ስላልቻሉ አሁንም ፌደራሊዝሙ ከዚህ በላይ ይለጠጥልን የሚል ይመስለኛል፡፡ ሕገ-መንግስቱ በህዝቦች ፈቃድ የታወጁ አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እስኪ ይሁን ተብሎ ህዝበ ውሳኔ ቢደረግ የለም ብሄር ተኮር ፌደራል ስርዓቱ አንፈልገውም እንደብሔር በራስ ማስተዳደር በዝቶብናል እና ይቀነስሉን፣ ኢትዮጵያዊ ባህል እና ቋንቋ እንጂ የራሳችን የሚዳብር ቋንቋ እና ባህል የለንም የሚሉ ይመስላችኋል?

ኢትዮጵያዊነት የሚፈካው የብሄር ብሄረሰቦች መብት በተሟላ ሲረጋገጥ ነው፡፡ ጠንካራ ክልሎች መኖራቸው ለኢትዮጵያ ስጋት የሚሆኑ ከሆነ ይቺ ኢትዮጵያ አንድ አጉራ ዘለል የጦር አበጋዝ ጠፍጥፎ እንደሰራት እና በቀላሉ እንደምትፈርስ እንደምትበተን ማሰብ ኢትዮጵያን ማሳነስ ነው ወይም ኤቢሳ ከጨፌ ዶንሳ ‹‹የኦሮሞ ብሄርተኝነት ከኢትዮጵያዊነት አይጣላም›› በሚል horn affairs እንደፃፈው፡፡

‹‹ይህቺ ሀገር ደግሞ በሁላችን ፈቃድና መተማመን የምትገነባ እየተገነባችም የምታብብ ሀገር ናት፡፡ ነሸጥ ያደረገው በአንድ ጀንበር ተነስቶ የሳላት ወይም የሚሳላት ንግርትም አይደለችም፡፡››

የነበሩን ኢትዮጵያዊ እሴቶች መሰረት አድርገን የኢትዮጵያችንን እንደ አዲስ እንገንባ የዛሬ ና የወደፊት ቁልፍ እሴታችን ማንነታችን ነፃንነታችን በዴሞከራሲ ባህላችን ይወስናልና፡፡ ዓለማየሁ ተረዳ (2008) እንዳለው ‹‹… ጠቀመም ጎዳም ነባር እሴቶቻችን ማፍረስ ቀላል ነው ምትክ የሚሆኑ አዲስ እሴቶች መፍጠር ግን ከባድ ነውና ልታስቡበት የሚገባ ይመስለኛል›› እንዳለው፡፡ 

****************

Guest Author

more recommended stories