በሁሉም የጋራ ጉዳዮቻችን ላይ መግባባት ተስኖን አስከ መቼ መዝለቅ እንችላለን?

መቅድም

በዚህ ጽሁፍ ዉስጥ ሶስት ወቅታዊና መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አስተያየት መስጠት ተገቢ መስሎ ታይቶኛል፡፡አንደኛዉ ጉዳይ ለምን መግባባት ተሳነን የሚል መነሻ ያለዉ ሲሆን አሁን በሚታየዉ ደረጃ ከቀዉስ መዉጣት ያለ መቻላችን መነሾም ተቀራራበን መነጋገርና መግባባት አለመቻላችን የሚል አምነት ሲላለኝ ነዉ፡፤በሁለተኛዉና ሶስተኛዉ ነጥቦች መቋጫ የጠፋለት ስለመሰለዉ የተቃዉሞ እንቅስቃሴና በአሳፋሪነቱ የሚጠቀሰዉና አሳሳቢ የሆነዉ የርስበርስ ግጭትን የሚመለከቱ ናቸዉ፡፡በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ መነጋጋሩም ሆነ መጻፉ ለመፍትሄ የሚረዳ ካልሆነ በስተቀር የሚያስከፋ ስለማይመስለኝ እኔም በነዚህ ጉዳዮች ላይ የተወሰኑ ነጥቦችን ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡

መግቢያ

ስለ መግባባትና አለመግባባት ለመጻፍ ስነሳ ፖለቲከኞች በተደጋጋሚ ሲገልጹት ስለነበረዉ ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ስለሚባለዉ ለመዉሳት ፈልጌ አይደለም፡፡አስካሁን ብሄራዊ መግባባትና እርቅ የሚባለዉን መተግበርም ሆነ በሱ ላይ መነጋገሩ የተሳነን መግባባት የሚያሻን አለመግባባት ስላልነበረንና እርቅ የሚያሻዉ የእርሰበርስ ግጭትና ጠብ ስላልነበረን ሳይሆን መግባባት የተሳነን መሆኑ ላይ መግባባት ስለሌለን ነዉ፡፡በምንም ነገር ላይ መግባባት እንደተሳነን ልባችን እያወቀ መግባባት እንደሌለን ለመግባባት ባለመፍቀዳችን ብቻ ሊተገበር ያልቻለ በመሆኑ በዚህ ላይ አስተያየት መስጠት አልሻም፡፡እኔ መግባባት እያልኩ ያለሁት ፖለቲከኞች ስለሚያወሩት መግባበት ሳይሆን እንደ ተራ ዜጋ የእርስበርስ መደማመጥና ማስማማት አለመቻላችንን ለመግለጽ ፈልጌ ነዉ፡፡መግባባትና መስማማት ማለቴ ሌላ ቃል ስላጣሁለት እንጂ ስለ ተወገዘዉ ብሄራዊ መግባባት ለማዉሳት ፈልጌ እንዳልሆነ በቅድሚያ ተረዱልኝ፡፡ ስለዚህ አነሳሴም ቢያንስ አሁን የምንገኝበት አደገኛ ሁኔታ ምክንያት ትንሽ ደንገጥ ብለን ለሀገራችን ስንል ተቀራርበን በመነጋገር መስማማት እንኳ ባንችል ቢያንስ ከነልዩነቶቻችንም ቢሆን በሰላም የምንኖርበትን መንገድ እንድንፈልግ ለማሳሰብ ነዉ፡፡ይህንንም ለማድረግ ፖለቲከኞችን ሆነ መንግስትንም መጠበቅ የግድ ሳያስፈልገን የምናከብራቸዉ የሀገር ሽማግሌዎች ምሁራንና ሀገር ወዳዶች ሰብሰብ ቢለዉ ተመካክረዉ መፍትሄ እንዲያፈላልጉን ለማሳሰብ ነዉ፡፡ለመንደርደሪያ ያህል ይህን ያህል ካልኩ ወደተነሳሁበት ጉዳይ በቀጥታ ላምራ፡፡

መግባባት ተስኖናል፡፡ ከምንግባባበት ይልቅ የማንግባበት ይበዛል እያልኩ ያለሁት እንዲሁ በስሜት አይደለም፡፡ አንዳንድ ጉዳዮችን እያነሳን ብንፈትሽ አለመግባባታችን የቱን ያህል የከፋ እንደሆነ መረዳት አይሳነንም፡፡ሌላዉ ቀርቶ በታሪካችን ላይ እንኳን ስምምነት እንደሌለን እናዉቃለን፡፡ በቀደሙ መሪዎቻችንም ላይ መስማማት ስለ አልተቻለን በአርአያነታቸዉ ሁላችንም በአንድ ድምጽ መጥቀስ የምንችለዉ መሪ ስም መጥቀስ ተስኖናል፡፡በዕሌታዊና ጥቃቅን በሚመስሉ ጉዳዮች ላይ መግባባት ቢሳነን ብዙም ባላስከፋ ነበር ፡፡ እኛ ግን መግባባት የቃተን አብይ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ወይም ብሄራዊ አጀንዳዎቻችን ላይ ጭምር መሆኑ ነዉ አሳሳቢ ያደረገዉ፡፡ አስኪ አንዳንዶቹን ላንሳላችሁ፤-

1. መግባባትና መስማማት የተሳነን ለመሆናችን ጥቂት ማሳያዎች፤

1.1. የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ የዲሞክራሲ እጦት መሆኑን አምነን መቀበል አልቻልንም፡፡

በዚህ ሁለት አስርተ አማታት ዉስት በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገብን ብንሆንም ፈጽሞ ሊሳካልን ያልቻለ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ልንተገብረዉ በድፍረት ያልገባንበት ጉዳይ ቢኖር ዲሞክራሲ ግንባታ ነዉ፡፡ስለ ዲሞክራሲ ደጋግመን የመናገራችን ያህል ልንተገብራት ድፍረት እንዳነሰን ከኛ ዉጭ ሌላ ምስኪር አያሸንም፡፡የዲሞክራሲ እጦት ለአብዛኛዎቹ ችግሮቻችን መንስኤ መሆኑንም ለመቀበል አንፈልግም፡፡ላንተገብራት ለምን ዲሞክራሲን ደጋግመን እንደምንጠራትም አይገባኝም፡፡

በዚህ ረገድ ያለብን ጉድለት ለማየት አስኪ ከትልቁ የዲሞክራሲያዊ ተቋም -ከፓርላማ ጀምረን እንፈትሽ ፡፡ሌሎች ሲደርጉ ሰምተን እኛም በ“ከማን አንሼ” መንፈስ ፓርላማ ማቋቋም አልተሳነንም ፡፡ነገር ግን የኛ ፓርላማ እንደ ሌሎች ሀገሮች ሳይሆን ክርክርና ሙግት የማይደረግበት ሌላዉ ቀርቶ አንድም ጊዜ አስፈጻሚዉን ተጠያቂ ሲያደርግ ያልታየበትና እጅግ በሚገርም ሁኔታ አንድም ተቃዋሚ የሌለበት ፓርላማ መሆኑ ነዉ፡፡በፌዴራል ምክር ቤት ቀርቶ በክልሎችም አንድም ተቃዋሚ በሌለበት ሁኔታ ስለ ዲሞክራሲያችን ማበብ ስናወራ አናፍርም፡፡የኛ ዲሞክራሲና የኛ ፓርላማ ከሌላዉ ሀገር የተለየ በመሆኑ ማፈር ሲገባን ስለዲሞክራሲያዊ ተሞክሮአችን ስንናገር የገዛ ህዝባችን ይታዘበናል ብለን እንኳን አንጨነቅም፡፡ የደርጉ መሪ ኮሎነል መንግስቱ ዲሞክራሲን ያልፈለጓት እኮ ዲሞክራሲ ስልጣን የምታሳጣ ፤እንደፈለጉ ለመግዛት አድል የማትሰጥ ፤ተቃዉሞዉን በአደባባይ ከመግለጽ የማትከልክል፤ የፕሬስ ነጻነት ላይ ገደብ የማታደርግ፤ ከገዥዉ ፓርቲ ኢሠፓ ዉጭ ሌሎችም ፓርቲዎች ፓርላማ መግባትና ለስልጣን መወዳዳርን የማትከለክልና ከዚያም በላይ ህዝብ ባልፈለገ ጊዜ ስልጣን ለመልቀቅ የምታስገደድ በመሆኗ እንጂ ያለበለዚያማ ኮሎነል መንግስቱ ዲሞክራሲን ለምን ይጠሏት ነበር፡፡ ዲሞክራሲ ስልጣናቸዉን የማታስደፈር መሆኗን ቢያዉቁ ኖሮ ምን በወጣኝ ቢለዉ ነዉ አምባገነን የሚሆኑት ?እንዲህ እንደ ኢህአዴግ ነጋ ጠባ ስለ ዲሞክራሲ እየተናገሩ በተግባር ግን ዲሞክራሲን እየጠሉ ሰላሳ ዓመት መግዛት የሚቻል መሆኑን ደርግ ተረድቶ ቢሆን ኖሮ ምን ቸገረኝ ቢሎ ነዉ አምባገነን የሚሆነዉ ነበር?

ከእንግዲህ በዚህ ላይም መግባባት መጀመር አለብን፡፡ዲሞክራሲ የሁሉም ችግሮቻቻን ቁልፍ መፍትሄ መሆኑን ልባችን እያወቀ ላለመተግበራችን ሌላ ሰበብ የምንደረድርበት ሳይሆን ብዙም ስለአልፈለግናት መሆኑን እንመን፡፡ችግራችን እንደ አንዳንዶች ትንተና “አብዮታዊ ዲሞክራሲ ”ተብሎ አብዮትና ዲሞክራሲ በመጣመራቸዉ የተፈጠረ ችግር አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ዲሞክራሲ የምትባለዋን ጣጠኛ ነገር ብዙም ስላልወደድናት ነዉ፡፡መዘዟ ብዙ ነዉና ፡፡ወደዋት ሲያቀርቧት ስልጣን እያስደፈረች ስለምታቸግር ነዉ፡፡ዛሬ በችግር ተተብትበን የምናደርገዉም ጨንቆን እንቅልፍ አጥተን የምናድረዉም የዲሞክራሲ እጦት ባመጣብን ጣጣ ነዉ፡፡ ዲሞክራሲያዊ ስርአትን በአግባቡ ብንገነባ ምናልባት ስልጣን ሊያሳጣንና የሀገር ሃብትን እንዳሻን ለመዝረፍ ዕድሉን ሊነፍገን ከመቻሉ ዉጭ የምንወዳትን ሀገርና የሚያከብረንን ህዝብ አያሳጣንም ነበር፡፡ህዝባችንም እንዳሁኑ ሰላምና ደህንነት ባልራቀዉ ነበር፡፡ስለዚህ ብዙ ብንዘገይም ከዚህ በኋላም ቢሆን ዲሞክራሲን በአግባቡ መተግበር እንደጀመርን ችግሮቻችን ሁሉ መፍትሄ ሊያገኙ እንደሚችሉ እርግጠኛ እንሁን፡፡

1.2. በመከላከያ ሰራዊታችን ላይም የተዛባ አመለካካት አለን፤

የልዩነቶቻቻን መክፋት አንዱ ማሳያ የጋራችን በሆነዉና እኛዉ ራሳችን ባቋቋምነዉ መከላከያ ሰራዊታችን ላይ እንኳን አንድ ዓይነት አረዳድ አለመያዛችን ነዉ፡፡ትላንት የሀገሪቱን ሉአላዊነት የማስከበር ግዳጅ ተሰጥቶት ለአመታት ሲፋለም ቆይቶ በመጨረሻም በየበረሃዉ የትም ወድቆ የአዉሬ ሲሳይ የሆነዉንና እኛዉ ራሳችን መርቀን የላክነዉን የቀድሞዉ ሰራዊት የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት መሆኑን መቀበል እንኳን ከብዶን አንዴ “የደርግ ሰራዊት” በሌላ ጊዜ ደግሞ “የወራሪ ጠላት ሰራዊት” አድርገን በመቁጠር ለብተና ዳረግነዉ፡፡ዛሬም ከዚያ መጥፎ ታሪካችን ሳንማር በመቅረታችን አሁን ላለዉ መከላከያ ሰራዊትም ያለን አመለካካትና የምንሰጠዉ ክብርም ከኛ ከሚጠብቀዉ በታች ለሰራዊታችን የማይመጥን መሆኑ ሊያስቆጨን ይገባል፡፡

ይህ ሰራዊት ትላንት የሻዕቢያን የዕብርት ወረራ እንዲመክትልን መርቀን ልከን በአስርሺዎች የሚቀጠሩት ጀግኖቻችን መስዋእት ሆነዉ ሉአላዊነታችን አስከብረዉልን ገና ለጥቅት ጊዜ እንኳን ሰላማችንን በሚገባ ሳናጣጥም መንግስት አልባ በሆነችዉ ሶማሊያ መሽጎ በየዕለቱ የሽብር ድርጊት እየፈጸመብን ለደህንነታችን ጠንቅ ሆኖ የነበረዉን የሽብር ኃይል እዚያዉ ሶማሊያ ድረስ ዘልቆ በመግባት በከፍተኛ መስዋእትነት ድህንነታችን ማስከበሩና ከጭንቅ መገላገሉን ሁላችንም እናስታዉሳለን፡፡ዛሬም እዚሁ እኛዉ ራሳችን ሆን ብለን በምንቆሰቁሰዉ ግጭት የኛኑ ሰላምና ደህንነት ለመስከበር ቀን ከለት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እዚህም እዚያም እየተሯሯጠ ሃላፊነቱን በመወጣት ላይ ያለዉን መከላከያ ሰራዊት የሚገባዉን ክብር እንኳ ለመስጠት አለመፈለጋችን ሳያንስ ጭራሽ የኛ ሰራዊት መሆኑን ክደን ለገዥዉ ፓርቲ ስልጣን ማቆያነት እንደቆመ መቁጠር መጀመራችን ሲታሰብ በዚህ በጣም ግልጽ በሆነ ጉዳይ ላይ እንኳን መግባባት ማጣታችን እጅግ አሳዛኝ ነዉ፡፡

በዚሁ ከቀጠልን ነገ ደግሞ ኢህአዴግ ወርዶ ሌላ ፓርቲ ስልጣን ሲይዝ መከላከያ ሰራዊቱን እንደ ደርግ ዘመኑ ሰራዊት“የኛ ሰራዊት ስለአልሆነ ይፍረስ!” እንደማንል እንዴት እርግጠኛ መሆን ይቻላል? መከላከያን በሚመለከት ከፍተኛ ሃላፊነት ያለበት የሀገራችን ፓርላማም ቢሆን ለመከላከያ ሰራዊቱ ተቆርቋሪነት በማሳየት ሰራዊቱ የተሻለ እንክብካቤ እንዲደረግለት፤ደሞዝና ቀለቡ እንዲሻሻል፤የፍትህና አስታዳደራዊ መጓደልም እንዳይኖር እንዲሁም የታጠቀዉ ትጥቅ እንዲዘምንና የተሻለ ስልጠናና አደረጃጃት እንዲኖረዉ ወዘተ በመሳሳሉት ጉዳዮች ላይ ራሱ መንግስት አስቦ ካላደረገ በስተቀር የፓርላማ ተወካዮቻችን ለሰራዊቱ ይሄን ይሄን ለምን አላሟላችሁም ቢለዉ ሲጠይቁ ሰምተን እናዉቃለን?ይሄ ሰራዊት ደሞዝ አነሰኝ ፤ኑሮ አልተመቸኝም፤በየጊዜዉ የሚሰጠኝ ግዳጅ ከብዶኛል ወዘተ እያለ አንድም ጊዜ መንግስትን ሲያማርር ያልተሰማና እንዲያዉም ወደፊት ህዝቡ ሲያልፍለት እኔም ከህዝቡ ጋር አብሮ ያልፍልኛል በሚል በአነስተኛ ባጄት የሚተዳዳር ሰራዊትን ፍቅር መንፈግና የገዥዉ ፓርቲ ስልጣን ጠባቂ አድርጎ የማይገባዉን ስም መስጠት እጅግ የሚያሳዝን ነዉ፡፡

1.3. በልማት ጥሬቶቻችና ስኬቶቻችን ላይም መግባባት ተስኖናል፡፡

በዚህ ባለንበት ስርአት ሀገራችን እጅግ ፈጣን በሆነ ልማት ማስመዝገብ መቻሏን አንዳንዶቻችን አምነን መቀበል ቢሳነንም መላዉ የሀገራችን ህዝብ የሚመሰክረዉና ተጨባጭ ሁኔታዉም የሚያረጋግጥ ነዉ፡፡በጥረታችን ላገኘነዉና በእጃችን ላለዉ እዉቅናና ከበረታ ሰጥተን ተጨማሪ ለማምጣት መትጋቱ ተገቢ ሆኖ እያለ ለማንኳሰስ ካልሆነ በስተቀር ለማድነቅ አልታደልንምና ስኬቶቻቻን ባይታየን ብዙም አያስደንቅም፡፡

ፈጽሞ ሊተገበር ይችላል ብለን በዉናችን ቀርቶ በህልማችን አስበን የማናዉቀዉን የታላቁ ህዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጄክት የገዥዉ ፓርቲ አመራር ዉጤት በመሆኑ ምክንያት ብቻ ኢህአዴግ የነካዉና እጁን ያስገባባት ሁሉ የሰይጣን ስራ ይመስል መወገዝ አለበት በሚል እሳቤ የፕሮጄክቱን ፋይዳ ለብዙ ጊዜ መቀበልና መግባባት አቅቶን እንደቆየን እናስታዉሳለን፡፡ዛሬ የተሻለ መግባባት መፍጠር ቢቻልም ፕሮጄክቱ ቶሎ እንዲጠናቅ እያደረግን ያለነዉ አስተዋጽኦ ብዙም የሚነገርለት አይደለም፡፡በተለይም የተሻለ ገንዘብ አላቸዉ የሚባሉ አካባቢ የሚያደርጉት መዋጮም በቁጥቁጥ መሆኑ አስቀድሜ ከገለጽኩት ፕሮጄክቱን በግማሽ ልብ ከመቀበል የመነጨ ነዉ፡፡አንዳንድ ተቃዋሚዎች ፕሮጄክቱን ሲቃወሙ የነበረዉ ኢህአዴግን ለመቃወም በመፈለጋቸዉ ብቻ መሆኑን የሚያሳብቀዉ ኢህአዴግ ስልጣን ሲለቅ እኛ እናስጨርሰዋለን ከማለት ይልቅ ፕሮጄክቱ ከመጠናቀቁ በፊት ኢህአዴግ ስልጣን የግድ መልቀቅ አለበት ማለቱን መምረጣችን ነዉ፡፡ግድቡ ኢህአዴግን ክብርና ሞገስ የሚያሰጠዉ ስለሆነ የግድ መወገዝ አለበት በሚል ነዉ የዉግዘት ዘመቻ ሲደረግበት የቆየዉ፡፡ለዚህም ነዉ አንዳንድ ኢትዮጵያዉያን ዉጤቱን በጉጉትና በተስፋ የሚጠብቁትን ይህን ፕሮጄክት ኢህአዴግ ከሌለ ስራዉ ሊቆም ይችላል በሚል ስጋት የገባቸዉ፡፡ሌላዉ ቀርቶ በጋራ ጥቅማችን ላይ እንኳ መግባባት የተሳነን መሆኑን ከዚህ በላይ ሌላ ማስረጃ ማምጣት አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡

1.4 አብሮነታችንና አንድነታችን እየተሸረሸረ መንደርተኝነትና ዘረኝነት እየጎለበተ መምጣቱን አምነን መቀበል ተስኖናል፡፡

የጥንት አባቶቻችን በየዘመኑ ከተነሱ ወራሪ ጠላቶች ጋር ተፋልመዉና ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍለዉ ባቆዩልን የጋራ ሀገራችን ዉስጥ እትብታቸን በተቀበረበትና ለዘመናት በሰላም በኖርንበት መንደር አሁን ላይ አብረን መኖር እንኳን እየተሳነን አንዳችን ባለሀገር ሌሎቻችን ሀገር አልባ አንዳችን ተፈናቃይ ሌሎቻችን አፈናቃይ አንዳችን ተባራሪ ሌሎቻችን አባራሪ እየሆን በእርስበርስ ጥላቻ እየተናቆርን በዚህ ሁኔታ አስከመቼ መዝለቅ እንችላለን? ይህ ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞዉኑ ሲነገረን የነበረና አካሄዳችንን ካላስተካከልን በስተቀር አያያዛችን ሩቅ እንደማያዘልቀን ወደፊትም ካሁኑ በእጅጉ የከፋ ችግር ዉስጥ ሊያስገባን እንደሚችል ገና ቀደም ተብሎ ምክር ቢለገሰንም በዚህ ጉዳይ ላይም ለመስማማትም ለመግባባትም ባለመፍቀዳችን ይሄዉ ዛሬ ደግሞ ለከፋ ችግር ተዳረግን፡፡አሁንም ከዚህ ሁሉ ቀዉስ በኋላም በመፍትሄዉ ላይ ለመስማማት ዝግጁነቱ ገና እንደሌለንና ከዚህም በላይ እጅግ የከፋ አደጋ ቢመጣብንም ለመስማማት እንደማንችል የሚያሳብቁ ፍንጮችን እያየን ነዉ፡፡በጋራ ችግሮቻችን ላይ ሳይቀር ሊያስማማን የሚችል መፍትሄ ማስቀመጥ ቢያቅተን ቢያንስ ችግር መኖሩን እንኳን አምነን ለመቀበል ለምን ተሳነን?

እጅግ ጥብቅ የነበረዉ የእርስበርስ ግንኝነታችንና ለዘመናት የቆየዉ አብሮነታችን አደጋ ላይ መዉደቁን አሳስቦአቸዉ መፍትሄ እንዲፈለግ ገና ከጠዋቱ ሲያስጠነቅቁ የነበሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዉያን አልነበሩምና ነዉ ከዚህ በፊት ችግር ደርሶ እንደማያዉቅ ሆነን ዛሬ እንደ አዲስ ማዉራት የጀመርነዉ?የአማራዎች ከደቡብ መፈናቀል የትግሬዎች ከጎንደር መፈናቀል የሶማሌና የኦሮሞ መካከል በተነሳዉ ቀዉስ በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች መፈናቀል በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን መጤዎች በሚል በሺዎች የሚቆጠሩ ከአካባቢዉ መፈናቀል እንደ ችግር ሲታይ አንዱ ከሌላዉ በምን ይለያል?ምናልባት በተፈናቃይ ብዛትና በደረሰዉ ጉዳት መጠን ካልሆነ በስተቀር የችግሩ ባህሪይ እንደሆን አንድና አንድ ነዉ፡፡እናም የዚህ ዓይነቱ ቀዉስ በትንሽም ቢሆን መከሰት እንደጀመረ ወደፊትም እየከፋ ሊሄድ እንደሚችል በአንዳንድ ወገኖች ማሳሳቢያ ሲቀርብ ሲላላነበር ነዉ አምነን መቀበል የተሳነን?

እንደ አሁኑ ባይሆንም ያለመግባባታችን ጉዳይ በፊትም የነበረ ነዉ፡፡ከመቶ ዓመታት በፊትም የማንስማማባቸዉ ብዙ ጉዳዮች ነበሩን፡፡ሌላዉ ቀርቶ ከአስርና ከሃያ ዓመታት በፊት በዚሁ አሁን ባለንበትም ስርአትም ቢሆን ያልተስማማንባቸዉ ጉዳዮች ሳይኖሩ ቀርተዉ አይደለም፡፡ነገር ግን የቀድሞዉ አለመግባባታችን ኢትዮጵያን እንዴትና በምን ዘዴ እናበልጽጋት?የተሻለዉ የልማት መንገድ የቱ ነዉ?ዲሞክራሲያዊ ስርአትን እንዴት እንገንባ ?ፍትህና መልካም አስተዳዳርን እንዴት እዉን እናድርግ? ወዘተ በሚል የአካሄድና የስልት ልዩነት ከመሆን ያለፈ አልነበረም፡፡ አሁን ግን የኢትዮጵያን ህልዉናና የህዝቦችን ብሄራዊ ጥቅምና አንድነት የመፈለግና ያለመፈለግ ባጭሩ ለኢትዮጵያ ጥብቅና የመቆምና የኢትዮጵያን ህልዉና የማሳጣትና መቃብር የመማስ ጉዳይ እየሆነ ነዉ፡፡እንደዚህ ባይሆን ኖሮማ ፤ለጋራ ሀገራችን ሁላችንም እኩል ፍቅር ቢኖረን ኖሮማ ከሀገር ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅም በልጦብን በዚህ ደሃ ህዝብ ላይ ዓይን ያወጣ ዝርፊያ ባላከሄድን ነበር፡፡ነባሩና ሌሎች ሀገሮችን ሲያስቀና የነበረዉ የአብሮነታችን እሴት ከስሞ በመንደር፤ በቋንቋና በጎጥ እየተቧደንን አርስበርስ ባልተጣላን ነበር፡፡ለዚህች ሀገር ሁላችንም እኩል ፍቅር ቢኖረን ኖሮ አትዮጵያዊ መሆንና መባል አስጠልቶን ለኢትዮጵያ ሌላ ስም ለመሰየም ባልቃጣን ነበር፡፡ዜግነታችንም ባልካድን ነበር፡፡የኢትዮጵያ ጉዳይ የጋራ አጀንዳችን መሆኑ ያበቃ ይመስል በየዕለቱና በተገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ ስለ ክልል ስለመንደር ስለጎጥ ፤ ስለ ልዩነታችን ስለ ጥንቱ የጨቋኛ የተጨቋኝ የወራሪና የተወራሪ የፈጠራ ታሪክ ካልሆነ በስተቀር በጋራ የሚያስማማን የኢትዮጵያዊነት ጉዳይ የአደባባይ አጀንዳ መሆኑ አክትሟል፡፡

የአሁኑ አለመግባባታችን የሪኡይተዓለም ልዩነት ያመጣዉ ፤የልማትና የዲሞክራሲ ማሳለጫ ንድፈሃሳብ ልዩነት የፈጠረዉ፤ ፈጣን እድገት ማምጫ የተሻለ አቋራጭ መንገድ በመምረጥ ላይ የተፈጠረ ልዩነት ሳይሆን መሰረታዊ የሆነ የኢትዮያዊነትና የጸረ ኢትዮጵያዊነት የአቋም ልዩነት የፈጠረዉና በርስበርስ ጥላቻ የታጀበ ባላንጣነት ነዉ፡፡የአሁኑ ልዩነታችን ከራሳችን በላይ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም በማስቀደምና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ይልቅ የራስን ጥቅም በማስቀደም መካካል ያለ ግጭት ነዉ፡፡ ልዩነቶቻችንና አለመግባባቶቻችን የኢትዮጵያዊነትን ፋይዳ ከግዜያዊ ጥቅም አንጻር ብቻ በማየትና ኢትዮጵያዊነትን የህልዉናችን መሰረትና የኩራታችን ምንጭ አድርጎ በማየት መካካል ያለ መሰረታዊ ልዩነት ነዉ፡፡ኢትዮጵያዊነት ሲደላን የምንኮራበት ሲከፋን ደግሞ የምናፍርበት ሊሆን ባልተገባ ነበር፡፡ኢትዮጵያዊነት ሲያሰኘን የምናገጥበትና ካላሳኘን ደግሞ አዉልቀን የምንጥለዉ ካባ ባልሆነም ነበር፡፡አሁን እየሆነ ያለዉ እንደዚያ ይመስላል፡፡ልዩቶቻችን እየበዙ በሁሉም ነገር መግባባት የተቸገርንበት ዋነኛዉ መነሻም ይሄዉ ለሁሉም ጉዳይ የራስን ጥቅም ከሀገር በላይ ማድረጋችን ያመጣብን ጣጣ ነዉ፡፡

1.5 ሌላዉ ቀርቶ በፌዴራላዊ ስርአታችን ላይም መግባባት ተስኖናል፤

አስቀድሜ መነሻዬ ላይ እንደጠቆምኩት በብዙ ጉዳዮች መግባባት የለንም፡፡እንዲያዉም በምን ጉዳይ ላይ እንደምንግባባም መጥቀስ እየቸገረን ነዉ፡፡ የማንግባባባቸዉ ጉዳዮች መብዛታቸዉ ማስከፋቱ ባይቀርም ከሁሉም በላይ የሚያሳስበን በምንመራበት ስርአት ላይ ልዩነት መፍጠራችን ነዉ፡፡ ማንኛችንም ደጋግመን የምንጠይቀዉና መልስ ያጣንለት አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ቢኖር ፌዴራላዊ ስርአቱ የልዩነት አጀንዳ መሆኑ አብቅቶ የጋራ መግባባት የሚፈጠርበት ወቅት መቼ ነዉ ?የሚል ነዉ፡፡ ስርአቱ የኢህአዴግ የብቻ ጉዳይ ተደርጎ ሌሎቻችን ልናፈርሰዉ ስንጣጣር ቢያንስ ስናጥላላዉ ኢህአዴግ ብቻ የሰርአቱ ቋሚ ጠበቃና ተከላካይ መሆኑ የሚያበቃበት ወቅት የሚመጣዉስ መቼ ነዉ? ከስርአቱ ወይም ከህገመንግስቱ ዉስጥ ያላስደሰተንና ያልተመቸን ነገር አለ እንዴ?ለምንድነዉ ከሁለት አሰርተዓማታት በኋላም ስርአቱን ማጥላላት ያልተዉነዉ?ለምንስ ነዉ ስርአቱን ለችግሮቻቻን ሁሉ እንደ መፍትሄ ሳይሆን እንዴ ችግርና ለአንድነታችንም እንደ እንቅፋት ቆጥረን የምናብጠለጥለዉ? በሌላ በኩል ስርአቱና ህገመንግስቱ ፈጽሞ ሊስተካካል የማይገባቸዉ አንዳችም የሚጠቀስ እንከን የሌላቸዉ ማድረግስ ለምን አስፈለገ?ስርአቱንና ህገመንግስቱን በመሰረቱ ተቀብለን ነገር ግን አሁን ከደረስንበት ደረጃና ካለንበት ልዩ ሁኔታ አንጻር ሊጣጣም በሚችል መንገድ የተወሰነ ማስተካከያ ወይም ማሻሻያ ማድረጉ ያን ያህል የተፈራበትስ ምክንያት ምንድነዉ?የህዝብ ፍላጎት መነሻ ባደረገ መልኩ በቀላሉ የተወሰነ ማሻሻያ ማድረግ እየተቻለ ህገመንግስቱም ሆነ ፌዴራላዊ ስርአቱ ሁልጊዜ የጥቃት ዒላማ እንዲሆኑ መደረጋቸዉ ተገቢነቱስ ምን ላይ ነዉ?እስከመቼስ ነዉ እንደዚህ ዓይነኬ ሆነዉ ሊቆዩ የሚችሉት?

ሁላችንም ስለ ኢትዮጵያ ስናወራ ሀገራችን የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባህል፣ ወግ፣ ታሪክ . . . ያላቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት መኖር ስለሚችሉባት የጋራ መኖሪያ መሆኗን ባለመዘንጋት ነዉ። ስለ ሀገር አንድነት ስንናገርም መላዉ የሀገራችን ህዝቦች በህገመንገስቱ የተረጋጋጠላቸዉ ሁሉም መብቶቻቸዉ ያለአንዳች መሸራረፍ ተከብረዉላቸዉ ከሁሉም ጋር ተቻችለዉ ለጋራ ሀገራቸዉ ጥቅምና ሉአላዊነት እንደ አንድ ሰዉ ሆነዉ እንደሚቆሙ እርግጠኛ በመሆን ነዉ፡፡ ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች ራሳቸዉን በራሳቸዉ የማስተዳዳርና የራሳቸዉን ጉዳይ በራሳቸዉ የመወሰን መብታቸዉ እንደተጠበቀ ሆኖ ሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦችም ባሻቸዉ ቦታ የመኖርና ሃብት የማፍራትና ያለአንዳች የርስበርስ ግጭት ሰላም የሰፈነበት ጠንካራ የህዝቦች አንድነት እንደሚኖር ተስፋ ተደርጎ ነዉ፡፡

ሀገራችን ለሁሉም የምትመች በህዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ያላትና ከግጭት፤ የርስበርስ መገዳደልና አንዱ ሌላዉን የማፈናቀል ድርጊት የማይፈጸምባትና ከበፊቱ የተሻለ የህዝቦች አብሮነት የዳበረበት ሀገር እንደምትሆንም ተስፋ በማድረግ ነበር፡፡እንደታሰበዉም ለጥቂት ዓመታት እጅግ በሚያስቀና ሁኔታ ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነት መፈጠሩ ባቀርም ነገር ግን እንደተመኘነዉ ሆነ ተስፋ እንዳደረግነዉ ዘላቂ ሊሆንልን አልቻለም፡፡ለዚህ ጉድለት ተጠያቂዉ ማን እንደሆነና የችግራችን ትክክለኛዉ ምንጭም ምን እንደሆነም ልንደርስበትም አልቻልንም፡፡

ባለፉት አምስት ሀገራዊ ምርጫዎች ሁሉ ፌዴራላዊ ስርአታችንን በሚመለከት በርከታ ነቀፌታዎች ሲቀርቡ አድምጠናል፡፡ይህን ስርአት በመምረጣችንም እንደተሞኘን አድርገዉ የነገሩንም አልጠፉም፡፡በሀገራችን በየግዜዉ ለሚከሰቱ የትኞቹም ዓይነት ችግሮች መንስኤዉና ተጠያቂዉም የምንከተለዉ ፌዴራላዊ ሰርአት ተደርጎም ብዙ ተዘግቧል፡፡ሌላዉ ቀርቶ በፈጣሪ ትዕዛዝ ለሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ሳይቀር ተጠያቂዉ ስርአቱ እስከ መሆንም ተደርሷል፡፡ በተለይም በተደጋጋሚ እየተከሰቱ ላሉ የርስበርስ ግጭቶች የተዳረግንበትም ዋነኛዉ ምክንያትም በስርአቱ ችግር ምክንያት መሆኑንም እርግጠኛ ሆነዉ የሚሟገቱ ቁጥራቸዉ ቀላል አይደለም፡፡ዛሬም በሀገራችን ለተፈጠረዉ ቀዉስ ሰበብ ሆኖ እየቀረበ ያለዉ ይሄዉ መከረኛ ፌዴራላዊ ስርአቱ ነዉ፡፡ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ዛሬም ድረስ መግባባት ያቃተንስ ለምንድነዉ?

ለሀገራችን ደህንነትና ሰላም ልማትና ለዲሞክራሲዉ መቀላጠፍና ለህዝቡ የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት በተሻለ መከበር ሊያግዘን የሚችል የተወሰነ ለዉጥ በህገመንግስቱ ላይ ማድረግ ከተቻለ ለህዝብና ለሀገር ጥቅም ሲባል ማድረግ የማይቻልበትስ ምክንያት ምንድነዉ ?ለመሆኑ አንዳችም ማሻሻያ ማድረግ አይገባም በሚሉትና የተወሰነ ማሻሻያ እናድርግ በሚሉት መካካል ያለዉ እሰጣገባ በዋነኛነት በተቃዋሚዎችና በኢህአዴግ መካካል ብቻ መሆኑ በራሱ ተገቢነቱ ምን ያህል ነዉ?

ፌዴራላዊ ስርአቱን በሚመለከትም ከሚታዩ ችግሮች መካካል አንዱ በስርአቱ ደስተኛ ባልሆኑ በተቃዉሞ ጎራ ባሉትና ሌሎች ወገኖች የተሻለ የሚባል አማራጭ እንኳን ማቅረብ ባልቻሉበት ሁኔታ ስርአቱን በጭፍን በማጥላላት ህዝቡን ተስፋ የማስቆረጥ አካሄድ መከተላቸዉ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በገዥዉ ፓርቲና በደጋፊዎቹ አካባቢ በፌዴራላዊ ስርአቱ በተለይም በአተገባባር ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶች ከምን እንደመነጩ ለይቶ ለማወቅ በመጣር እርምት ለመዉሰድ ከመሞከር ይልቅ አንዴ ገብተንበታል በማለት በጭፍን በእዉር ድንብር ለመቀጠል የመፈለግ አመለካከት መኖር ሲሆን ሶስተኛዉ ደግሞ ስለ ስርአቱ ከኛ ዉጭ ማንም አስተያየት መስጠት የለበትም በሚል በስርአቱ ላይ ብቸኛ ባለቤት ለመሆን የመፈለግ አዝማሚያ መኖሩ ነዉ፡፡እነዚህ የስርአቱ ብቸኛ ባለቤት መሆን የሚዳዳቸዉ ወገኖች ያለህዝብ ተሳትፎ ብቻቸዉን ስርአቱን ጠፍጥፈዉ የሰሩ ይመስል እነሱ ከሚያስቡት ዉጭ የሚያስቡትንና በቅንነት የተለየ አስተያየት የሚሰጡ ዜጎችን የተለያዩ ቅጥያ ስሞች በመስጠት በማሸማቀቅ የሚታወቁ ናቸዉ፡፡ “ችግር ካለም እኛዉ የስርአቱ ባለቤቶች እንናገር እንጂ ሌላዉ ምን ቆርጦትና ምንስ አግብቶት ነዉ በስርአቱ ላይ ተችት የሚሰነዝረዉ?” የሚሉ ናቸዉ፡፡ ዛሬ በስርአቱ ላይ ከፍተኛ አደጋ ተጋርጧል በሚባልበት ወቅት እንኳን እነሱ ከሚያስቡት ዉጭ ገንቢ አስተያየቶችን ለመቀበልም አይፈልጉም፡፡

በመሰረቱ የፌዴራላዊ ስርአታችን የህዝብን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እየፈታና በሂዴት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶቹንም እያረመ ከግዜ ወደግዜ እየተጠናከረ የሚሄድ እንጂ ለእርምትና ለመስተካካል ዕድል ሳይሰጥ በጭፍን የሚከድበት አይደለም፡፡ወቅቱ በሚጠይቀዉ ደረጃና አዳዲስ የህዝብ ፍላጎቶችን መነሻ ባደረገ ሁኔታ በሂዴት እየተኮረኮመና ትክክለኛ ቅርጹን እየያዘ የሚሄድ እንጂ በአንድ ወቅት ግንባታዉ ተጠናቆ ለምርቃት እንደሚዘጋጅ ህንጻ ሊቆጠር የሚገባዉ አይደለም፡፡

ከሁለት አስርተ ዓመታት በፊት ፌዴራላዊ ስርአትን ለሀገራችን ይበጃል ተብሎ ሲመረጥ በጭፍንና የጥቂት ግለሰቦችን ፍላጎት መነሻ ያደረገ ስለሆነ ሳይሆን ከሁሉም ስርአቶች በተሻለ ለኢትዮጵያ ልዩ ሁኔታ ይበጃታል የሚል እምነት ስለተያዘ ነዉ፡፡ አብዛኛዎቻችን የሀገሪቱ ዜጎች ወደዚህ ስርአት ስንገባ ሁላችንም በእኩል ደረጃ የስርአቱን ምንነትና ባህሪይ ከሌሎች ስርአቶች የሚሻልበትን ዓይነተኛ መገለጫ በሚገባ ተረድተን አስበንና አመዛዝነን ነዉ ማለት አይቻልም፡፡ሃሳቡ የመነጨዉ የሌሎችን ሀገሮችን ተሞክሮ ጠንቅቄዉ የሚያዉቁና የሀገራችንንም ልዩ ሁኔታ የተረዱ ጥቂት ምጡቅ አይምሮ ባለቤትና ሩቅ አሳቢ በሆኑ ባለራዕይ በሆኑ ሰዎች እንደሆነ እገምታለሁ፡፡

በህገ መንግስቱ ረቂቅ ዉይይት ወቅት በፌዴራላዊ ስርአቱ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ለመነሻ የቀረበዉ ማብራሪያ ጽሁፍ በራሱ ለብዙዎቻቸን ለመረዳት ዉስብስብ ከመሆኑ የተነሳ ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛዎቻችን በግምት ብቻ የደገፍንና የተቃወምን በቁጥር እናመዝናለን፡፡ በወቅቱ የስርአቱን ፋይዳ ፈጥነዉ የተረዱ ጥቂት ሰዎች የተረዱትን ያህል ሊያስረዱን ሲሞክሩም አብዛኛዎቻችን ፈጥነን ልንቀበላቸዉ አልቻልንም፡፡ የፌዴራላዊ ስርአቱን ይነቅፉ ከነበሩት በቁጥር የሚበዙት የሶማሊያን፤ ዩጎዝላቪያንና ሶቭየት ህብረትን መበታታን ሁኔታ በወሬ ደረጃ የሰሙትን በመጥቀስ በኛም ሀገር መበታተን ሊያስከትል ይችላል ከሚል ስጋት በመነጨ ነዉ፡፡የጉዳዩ ዉስብስብነት በፈጠረዉ ብዥታ ተገፋፋተዉ በዚያን ወቅት ብዙዎቹ ሰዎች የሀገራቸዉ ዕጣ ፈንታ አሳስቦአቸዉ መስጋታቸዉም ተገቢ የነበረ ይመስለኛል፡፡

ዛሬም ቢሆን የፌዴራላዊ ስርአቱን ተገቢነት እንዳለ በመቀበሉ ረገድ ብዙም አስቸጋሪነት ባይኖረዉም ለመረዳትና ለመግባባት አዳጋች ያደረገዉ ጉዳይ ግን በፌዴራላዊ ስርአቱ ዉስጥ የሚነሱ የተለያዩ የቅርጽ፤ የአደረጃጃት ፤የመሪህ ፤የአቅጣጫ፤ የሪኡይተዓለም ወዘተ አማራጮች መኖራቸዉ ሲሆን ለመግባባት ችግር የፈጠረዉም ከጉዳዩ ዉስብስብነት የተነሳ በጥልቀት ለመረዳት ባለመቻሉ እንጂ ስርአቱን በመፈለግና ባለመፈለግ ምክንያት አይደለም፡፡ በተጨመሪ በፌዴራላዊ ስርአቱና በህገመንገስቱ እንዳንድ ጉዳዮች ላይ ክለሳ አንዲደረግ የሚሹ ወገኖች ህገመንገስቱንና ስርአቱን የማይፈልጉ ናቸዉ በሚል በጭፍን የሚወገዙ ሳይሆኑ ስርአቱንማ ህገመንገስቱንም ሀገሪቱንም ከኛ ባለነሰ የሚፈልጉና የሚወዱ የኛዉ ዜጎች ናቸዉ፡፡

ዛሬ ከዓመታት በፊት እንደነበረዉ የምንከተለዉ ስርአት ትክክለኛነት ላይ ጥርጣሬ ያለዉ ሰዉ ብዙ ነዉ ብዬ አላስብም፡፡ዛሬ የስርአቱን ጥቅም ሁሉም ወይም አብዛኛዉ ህዝብ ያምንበታል ብዬ አስባለሁ፡፡ በስርአቱ ላይ ይህን መሰል የአመለካካት ለዉጥ ሊመጣ የቻለዉም በምሁራን ጉትጎታና ባካድሬ ቅስቄሳ ብዛት ሳይሆን ህዝቡ ራሱ በተግባር ጠቀሜታዉን በሂዴት እየተገነዘበ በመምጣቱ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡መላዉ የሀገራችን ህዝብ ስርአቱን የህልዉናዉ አስትንፋስ አድርጎት ተቀብሎታል ብዬም አስባለሁ፡፡ከዚህ በኋላ ከዚህ ስርአት ዉጭ ማሰብ የሚቻልበት ዕድል አይኖርም፡፡ይህ ማለት ግን በአተገባባር ረገድ የሚታዩ እንከኖችና በሂዴት መስተካካል የሚገባቸዉ ጉድለቶች የሉም ማለት አይደለም፡፡ የዚህ ዓይነት እንከኖች ባይጠፉም “ስርአቱ ይበጀናል ወይንስ አይበጀንም?” ተብሎ የስርአት ለዉጥ ለማድረግ የምንደራደርበት ወቅት አልፏል፡፡

ዛሬ ሁሉም ህዝቦች ከሞላ ጎደል ከስርአቱ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡በዚህ ምክንያትም ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ ተመልሰን ሌላ ስርአት ለማማረጥና እንደአዲስ ለመመስረት የምንደክምበት ምክንያት አይኖርም፡፡ከዚህ ሁሉ ግዜ በኋላ ወደ ኋላ ተመልሰን የአሁኑን ስርአት በሌላ ለመተካት መሞከር ጥፋት እንጂ ጥቅም አይኖረዉም፡፡ በምሁራኑ መካካል፡በገዥዉ ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካካል ወዘተ ሁሉ በየትኛዉም መድረክ ቢሆን የስርአቱን ህልዉና ጥያቄ ዉስጥ የሚያስገባ አይነት ክርክርም ሆነ ድርድር ወቅቱ ያለፈበት ስለሆነ ግዜ ከማባከን ባለፈ አንዳችም እርባና አይኖረዉም፡፡በስርአቱ ማዕቀፍ ዉስጥ ሆነን ስርአቱን እንዴት እናጠናክረዉ ፤ህዝቡ ከስርአቱ የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ምን ምን ሁኔታዎችን እናሟላ ፤ በአፈጻጸም ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን እንዴት እናስወግድ ወዘተ የሚል ካልሆነ በስተቀር ወደ ኋላ ተመለስሰን እንደ አዲስ በስርአቱ ተገቢነት ላይ የምንነጋገርበት ሁኔታ ሊኖር አይገባም፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል ስርአቱንና ህገመንግስቱን በጭፍን የሚያጥላሉ የሉም ባይባሉም በአንጻሩ ምክንያታዊ ከሆነ መነሻ ተነስተዉ በስርአቱ ዙሪያና በአጠቃላይ የመንግስት ፖሊሲዎችና አካሄድ ላይ በሚገባ የተቀመረ የየራሳቸዉ አማራጭ ፖሊሲ ያላቸዉና ፖሊሲያቸዉን ከአስር ዓመት በፊት ጀምሮ ለህዝብ ሲያስተዋዉቁ የቆዩ እንዳሉ መዘንጋት አይኖርብንም፡፡ሰርአቱን አምኖዉበት ነገር ግን የተለየ የትግበራ አማራጭ ያላቸዉ አንዳንድ ፓርቲዎች በስርአቱ ማዕቀፍ ዉስጥ ሆነዉ የሚሰጡትን አስተያየትና ትችት ገዥዉ ፓርቲ ለማዳመጥ የማይፈልግበት ምክንያት ጨርሶ ሊኖር አይገባም፡፡መንግስት ስርአቱንም ህገመንግስቱንም በጅምላ ለማፍረስ ከሚያልሙ አንዳንድ ነዉጠኛ ቡድኖች ጋር አብሮ በማዳበል ሌሎች ሰላማዊ ፓርቲዎችን በጅምላ በጸረ- ስርአትነት መፈረጅ እንደማያዋጣዉ ሊረዳ ይገባዋል፡፡ስለዚህ ገዥዉ ፓርቲ በስርአቱና በህገመንግስቱ ዙሪያ አንዳንድ ማሻሻያ እንዲደረግ ሃሳብ ለሚያቀርቡ ፓርቲዎች በደፈናዉ ሃሳቡን ከማጣጣል ይልቅ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ቢመረምረዉና ከሌሎች ጋር ቁጭ ቢሎ ቢመካካርበት የተሻለ እንደሚሆን አገምታለሁ፡፡

ፌዴራላዊ ስርአታችን ከጅምሩ አንስቶ አስካሁን ከፍተኛ መሰናክል ያልተለየዉ ቢሆንም ስርአቱን እንደ ስርአት የሚያምኑበት ዜጎች ቁጥር ግን ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ስርአቱ በደካማ አመራሮች ስንኩል የችግር አፈታትና በአፈጻጸም ድክመት ምክንያት በሚፈጠሩ መሰናክሎች አንዳንዴ የመንገራገጭ ሁኔታ ቢየጋጥመዉም ነገር ግን እንደተሰጋዉና ጠላቶቻቻን እንደሚመቹት ከመዳከም ይልቅ ጭራሽ እየተጠናከረ መምጣቱን በተግባር ማረጋገጥ ችለናል፡፡ዛሬ የፌዴራላዊ ስርአታችንን ምንነትና ጠቀሜታ በሚመለከት ለማስረዳትና ለማሳመን ከጥቂት ዓመታት በፊት እንደነበረዉ የካድሬ ቅስቀሳና ስብከት እንዲሁም የዩኒቨርስቲ ምሁራን ረቀቅ ያለ ትንተና የሚያስፈልገበት ወቅት ላይ አይደለንም፡፡

ዛሬ አርሶአደሩ፤ አርብቶአደሩም ሆነ የከተማዉ ነዋሪ ወጣቱም ሆነ አዛዉንቱ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የተማረዉም ያልማረዉም ፤ወታደሩም ሆነ ሲቪሉ በአጠቃላይ ሁሉም ዜጎች ስርአቱን ቢያንስ ለየግላቸዉ ካመጣላቸዉ ጠቀሜታ አንጻር በመመዘን እንደተቀበሉት አያጠራጥርም፡፡ዛሬ ሁሉም ዜጎች ለስርአቱ ቋሚ ጠበቃና መስካሪ መሆን ችለዋል፡፡ስርአቱን መንከባከብም ሆነ ከአደጋ የመጠበቅ ሃላፊነት የተመረጡ አካላት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ የሀገሪቱ ዜጋ የጋራ ሃላፊነት መሆኑንም ተገንዝበዋል፡፡ስለዚህ ስርአቱ ጉድለቶች ካሉበት ወቅቱ በሚጠይቀዉ ደረጃ እየተሞረደና እየተሻሻለም ቢሆን ይቀጥላል እንጂ ከእንግዲህ ወዲያ ወደ ኃላ ተመለስን ሌላ ስርአት ማማረጥ የምንችልበት ዕድል የለንም ፡፡

ስርአቱን በሚመለከት እያጋጠመን ያለዉ ትልቁ ቸግር በሂዴት የሚከሰቱ እንቅፋቶችን በዜዴ ማለፍ የሚችል ብቃት ያለዉና ለህዝብ የተጠያቂነት ሃላፊነት የሚሰማዉ አመራር አለመኖር ነዉ፡፡በፓርቲዉም ሆነ በመንግስት ከፍተኛ አመራርነት ቦታ ተቀምጠዉ ህዝቡን እንዲመሩ ሃላፊነቱን ከተቀበሉት መካካል ቁጥራቸዉ ቀላል ያልሆኑት ስለሚመሩት ስርአት ዝርዝር ጉዳዮችን በቅጡ ለመረዳት የተሳናቸዉ ናቸዉ፡፡ስለ ስርአቱ በመድረክ ትንቴና ከመስጠትና ባዶ መፈክር ከማሰማት ባለፈ በሂዴት ሊገጥሙ የሚችሉ ችግሮችን እንዴት ማለፍ እንዳለባቸዉ ግንዛቤዉ የሌላቸዉ ናቸዉ፡፡በዚህ ምክንትያም በቀላሉ መፍትሄ ሊያገኙ ይችሉ የነበሩ ችግሮች እየተባባሱ በተደጋጋሚ ለቀዉስ መደረጋችን ሁሉም የሚያዉቀዉ ነዉ፡፡ብዙዎቹ የፓርቲዉም ሆነ የመንግስት አመራርነት ቦታዎች ብቃቱ በጎደላቸዉና በማይመጥኑ ሰዎች እጅ በመዉደቃቻዉ የተዋጣለት አመራር የሚሰጠን ጠፍቶ በተደጋጋሚ ለችግር እንድንዳረግ የግድ ሆኖብናል፡፡ለዚህ አብነት የሚሆነዉ ለዘመናት ተፈቃቅረዉና ተቻችለዉ በኖሩ ህዝቦች መካካል በረባ ባልረባዉ ሁሉ ግጭትና አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ብቃት በጎደለዉ የችግር አፈታት ምክንያት ግጭቶቹንና አለመግባባቶችን በዜዴ መፍታት እየተሳነን ጭራሽ እንዲካረሩ እያደረግን ለዉስጣዊ አንድነታችን ጠንቅ እንዲሆን ማድረጋችን ነዉ፡፡

የትኞቹም ችግሮች ቢሆኑ ከህገመንግስቱ ዉጭ ያልሆኑና ህገመንግስታዊ መፍትሄ ለመስጠት የማያዳግቱ ሆነዉ እያለ በህገመንግስቱ መሰረት ገለልተኝነት ባልተለየዉ መንገድ ሁሉንም ወገን ሊያረካ የሚችል ዘላቂና ሁነኛ መፍትሄ መስጠት ሲገባን አንዱን ወግነን ሌላዉን በማጥላላትና በመወንጀል ላይ ስለምንበረታ ችግሩን መፍታት ስለተሳነን ቀድሞዉኑ ፌዴራላዊ ስርአቱን የግጭት ምንጭ አድርገዉ ይቆጥሩ ለነበሩት ወገኖች ስርአቱን ለማጠልሸት መልካም አጋጣሚ ነዉ የሆነላቸዉ፡፡ህገመንግስታችን የምንተዳዳርበት ብቻ ሳይሆን የምንዳኝበትና የጋራ ችግሮቻቻንም የምንፈታበትም መፍትሄ እንጂ በአዳራሽ ስብሰባ ለድስኩር ማድመቂያ ብቻ ተብሎ ሊጠቀስ የሚገባዉና ከዚያ ዉጭ ፈጽሞ የማናስታዉሰዉ ሊሆን ባልተገባ ነበር፡፡

ህገመንግስቱንና ሌሎችንም ህጎች ከለላ በማድረግ ንጹሃን ዜጎችን መብት ለመጨፍለቅ ፤የማይገባንን ሃብት ለመዝረፍ እንዲያስችለን ካልሆነ በስተቀር ህገመንግስታችን ለጋራ ሰላማችን ለጋራ ደህንነታችን ለአብሮነታችን ሁላችንንም የሚያግባባንና የሚያስተሳሳረን መሆኑን ተረድተን ለበጎ ዓላማ ልንጠቀምበት አልሞከርንም፡፡ እንዲያዉም ካላሰኘንና ካለስፈለገን በስተቀር ሀገሪቱ ህገመንግስት ወይም ህግ እንዳላትም የምናስታዉስ አይመስለኝም፡፡እናም አመራሩ ራሱ ህገ መንግስቱን አክብሮ በህገመንግስቱ መሰረት ሊዳኘንና ሊያስተዳዳርን አቅም አንሶታል፡፡የህግ የበላይነት የሚያስከብር ጠፍቶ ህገወጥነት እየተስፋፋ እያየን ትንሽ እንኳን አይከነክነንም፡፡ የሌሎች አጎራባች ሀገሮችን የርስበርስ ግጭት ለመፍታት የማይሰንፈዉ የሀገራችን አመራር እኛን ከቁዉስ ለማዉጣት ያዳገተዉ ይመስላል፡፡የመሪዎቻችን ድክመት እኛ ዜጎቹ ለዘመናት እርሰበርስ ተስማምተን ተዋደንና ተዋልደን ባደግንበት ቀዬ በሰላም መኖር ተስኖን እየየ መፍትሄ ባለማሰቀመጥ ባለመቻሉም ጭምር ይገለጻል፡፡ኑሮዉ ባይደላንና ዲሞክራሲዉ ባያጠግበን እንኳ ቢያንስ በድህነትም ቢሆን በሰላም መኖር ሊሳነን ባልተገባ ነበር፡፡

በሀገሪቱ ዉስጥ ለሚከሰቱ ችገሮች ሁሉ መንስኤዉ ስርአቱ እንደሆነ ተደርጎ የሚቀርበዉ የተዛባ ትንተና የስርእቱን ተአማኒነት ለማሳጣትና እኛ ዜጎች ይህን ስርአት በመምረጣችን እንደተታለልን ቆጥረን ተስፋ እንድንቆርጥ ለማድረግ የታለመ ካልሆነ በስተቀር ለኛ አንዳችም የሚያመጣልን ጥቅም የለም፡፡ጥቂት የመንግስት ባለስልጣናት ድክመት ላይ ግፋ ሲልም የራሱ የመንግስት ድክመትና ስህተት ላይ በቀጥታ በማነጣጠር እነሱን ከመዉቀስ ይልቅ ለሁሉም ችግሮች መንስኤዉ የስርአቱ ችግር እንደሆነ አድርገን ስርአቱ ላይ መረባረባችን ተገቢ አይመስለኝም፡፡

የኢህአዴግን ድክመት ለኢህአዴግ ማድረግ ሲገባን የስርአቱ ድክመት ማድረጉን መምረጣችን መልሶ እየጎዳ ያለዉ እኛኑ ነዉ፡፡ኢህአዴግን ከስርአቱ ህልዉና ጋር በቀጥታ በማቆራኘታችን ስርአቱን መደገፍ ማለት ኢህአዴግን መደገፍ ተደርጎ እንዲቆጠር ሆኗል፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግን መቃወምም ሆነ ከስልጣን ማዉረድ ማለት ሆን ተብሎ ስርአቱን ከማፍረስ ጋር እንዲቆራኝ በመደረጉ የፌዴራላዊ ስርአቱ ተገቢነት እንደ ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል ፡፡

ኢህአዴግና ስርአቱ የግድ እንዲቆራኙ በመደረጉ የተነሳ በተቃዋሚዎች አካባቢ ኢህአዴግንና ስርአቱን ለመለየት በመቸገራቸዉ ልዩነታቸዉ በህገመንግስታዊ ስርአቱ ላይ ሳይሆን ስርአቱን እየመራ ባለዉ ገዥ ፓርቲ ላይ መሆኑን ለማስረዳት ተቸግረዋል፡፡ኢህአደግን መተቸት ስርአቱን ለማፍረስ እንደመሞከር በመቆጠሩ፤በተመሳሳይ ሁኔታ በስርአቱ ላይ የሚታዩ የተወሰኑ እንከኖቹን ለመረም መጣርም ኢህአዴግ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ተደርጎ በመታሰቡ ምክንያት ስርአቱንና ኢህአዴግን አንድ አድርጎ የማዬት አመለካካት በተቃዉሞ ጎራ ባሉት ላይም የሚታይ ችግር ነዉ፡፡የኢህአዴግና ስርአቱ በመደበላለቁ ምክንያት መለየት ማዳገቱን ለተቃዋሚዊች ምቾት ባይሰጥም ኢህአዴግ ግን የሚፈልገዉ እንደዚያ እንዲመስል መሆኑን ከአንዳንድ ሁኔታዎቹ መረዳት አያዳግትም፡፡ ኢህአዴግ ማለት ስርአቱ ስርአቱ ማለት ደግሞ ኢህአዴግ ተደርጎ በመቆጠሩ አንዱን መንካት ሌላዉን እንደ መዳፈር ስለሚያስቆጠር አንዱን ከሌላዉ መለየት ካልተቻለ መፍትሄዉ ኢህአዴግን ማስወገድ ነዉ የሚል አቋም በአንዳንድ ፓርቲዎች መያዙም በዚህ መነሾ አንደሆነ ይሰማኛል፡፡

ሀገር በቀል ከሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካካል በጣም ጥቂቶቹ ምናልባትም አንድ ወይም ሁለቱ ፌዴራላዊ ስርአቱን በድፍኑ የሚቃወሙ ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡አብዛኛዎቹ ግን ፌዴራላዊ ስርአቱን እንዳለ ተቀብለዉ ነገር ግን በአንዳንድ ጉዳዮችና በተለይም በአተገባባበር ላይ ልዩነት ያላቸዉ ናቸዉ፡፡እናም እነዚህ ፓርቲዎችና ሌሎች ግለሰቦች በፌዴራል ስርአት ላይ የጸና አቋም ኖሮአቸዉ ነገር ግን በአተገባበር ላይ ያላቸዉን ልዩነት በህጋዊ መንገድ አስካንሸራሸሩ ድረስ እንደ ችግር ሊቆጠር የሚገባዉ አይደለም፡፡የመንግስት ቅርጽን በሚመለከትም ለኢትዮጵያ ልዩ ሁኔታ የሚበጀዉ ፓርላሜንታዊ ነዉ ወይንስ ፕሬዝዳንታዊ ? የሚል ሙግት መነሳቱ እንደ አደጋ የሚቆጠር አይደለም፡፡ የፓርላማ ዉክልና ጉዳይ ላይም አነስተኛ ዉክልና ያላቸዉን ዜጎችንም መብት ታሳቢ በሚያደርግ መልኩ ከአብላጫ ቁጥር ይልቅ ተመጣጣኝ ዉክልና ወይም ቅይጥ የሆነ ይሻለናል የሚል ሃሳብ ከበፊት ጀምሮ ሲያቀርቡ የነበሩ እንደ ኢዴፓ የመሳሰሉ ፓርቲዎች ይህን ገንቢ አስተያየት መስጠታቸዉ ስርአቱን እንደተቃወሙ የሚያስቆጥር አይደለም፡፡

ዛሬ ከስንት ዘመን በኋላ ቅይጥ ዉክልና አሰራር ለመተግበር እየተመከረበት ያለዉ ከበፊት ጀምሮ ከተቃዋሚዎች ሲቀርብ የነበረ ሃሳብ አልነበረም እንዴ?ኢዴፓ ገና ከዓመታት በፊት ጀምሮ በፕሮግራሙ ላይ አካቶ ባቀረበበት ወቅት ሃሳቡን በጭፍን ከማጣጣል ይልቅ እንደአሁኑ ተግባራዊ ማድረግስ አይቻልም ነበር እንዴ? ገዥዉ ፓርቲም ቢሆን ይህን ጉዳይ ለብዙ ግዜ ሲያጥጥል ቀይቶ የአቋም ለዉጥ በማድረግ ፈቀደኝነቱን በመሳየት ሰሞኑ በጉዳዩ ላይ ከፓርቲዎች ጋር በመደራደር መግባባት ላይ መድረሱ የሚያስመሰግነዉ ነዉ፡፡ይህ የኢህአዴግ የአቋም ለዉጥ ጤነኛ ለሆነ የፓርቲ ፖለቲካ ስርአት መስፈን ትልቅ እርምጃ ነዉ፡፡የአሁኑ የኢህአዴግ የአቋም ለዉጥ ለወደፊቱም በሌሎች ጉዳዮች ላይም በመነጋገር መግባባት እንደሚቻል ፍንጭ የሰጠ ነዉ፡፡አስከዚህ ወቅት ድረስ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ መነጋገር የሚቻል አልነበረም፡፡እንግዲህ በስርአቱ ዙሪያ በተለይም በአተገባባር ሂዴት ላይ ይህን መሰል ሌሎች ገንቢ አስተያየቶችን ማቅረብ ምን ላይ ነዉ ስርአቱን ማጥላላት የሚሆነዉ ? በእኔ እምነት በጭራሽ ሊሆን አይገባም፡፡

ፌዴራላዊ ስርአቱን በሚመለከት ብዙ አጨቃጫቂ የሆኑ ሌሎች ጉዳዮችም እንዳሉ ይታወቃል፡፡በተለይም የክልሎች አከላለልም ሆነ ስርአቱ የተመሰረተበት መሪህ መነሻዉ በቋንቋ ብቻ ከሚሆን በተጨማሪ የሕዝብን ፈቃደኝነት፣ ታሪካዊና ባህላዊ ትስስርን፣ የሕዝብን አሰፋፈርና የመልክዓ ምድር አቀማመጥን፣ የልማት አመቺነትንና የአስተዳደር ቅልጥፍናን የመሣሠሉትን መመዘኛዎች ባገናዘበ መንገድ ቢደራጅ ይበጃል የሚለዉ ሃሳብ ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲነሱ የነበሩ ሙግቶች ህገመንግስቱን በተቀበሉና ጸረ ህገመንግስት በሆኑ፤ ፌዴራላዊ ስርአቱ ደጋፊ በሆኑና የስርአቱ ጠላት በሆኑ መካከል የተደረገ የሚመስል እንጂ በሀገራችን ጉዳይ ሁላችንም እኩል ይመለከተናል በሚል መንፈስ የተደረገ ሆኖ ባለመቆጠሩ ከመጯጫህ ባለፈ አንዳችም ያመጣዉ ለዉጥ የለም፡፡በዚህ ምክንያትም የተወሰነ ማሰተካከያ በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ያስችል የነበረዉን እድል ሳንጠቀምበት ቀርተናል፡፡በዚህ መነሾም ከሁለት አስርተ ዓመታት በኋላም የጋራችን በሆነዉ ስርአት ላይ መግባባት አለመቻላችን እጅግ አሳዛኝ ነዉ፡፡ ስለዚህ እጅግ ቀላል የነበሩ ጥቂት ልዩነቶቻችን ላይ ተነጋግረን መግባባት ባለመቻላችን የስርአቱ ደጋፊና የስርአቱ ጠላት እየተባባልን ማዝገም የግድ ሆኖብናል፡፡

አስቀድሜ እንደጠቀስኩት በሀገራችን ፌዴራላዊ ስርአት አይበጀንም የሚል አቋም የሚያራምድ የፖለቲካ ፓርቲ የለም ባልልም አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆኑ ምሁራንና ፖለቲከኞች ቢያንስ ፌዴራላዊ ስርአት መሆኑ ላይ ተቃዉሞ ያላቸዉ አይመስለኝም፡፡ፌዴራላዊ ስርአቱን እንዳለ ተቀብለዉ በአተገባባር ረገድ ጥቂት ግን ደግሞ ወሳኝ የሆኑ ልዩነቶች እንዳላቸዉ ግን አያጠያይቅም፡፡ቢቻል ልዩነቱን በዉይይት ማቀራረብ ፤ካልተቻለም ደግሞ ከነልዩነቱ በሰላም መዝለቅ አለመቻላችን መልካም አይደለም፡፡ ስርአቱን በሙሉ ልብ እደግፋለሁ፡፡ነገር ግን በዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ማስተካከያ ይደረግ ቢሎ አቋም መያዝ በምን ሂሳብ ነዉ ጸረ-ህገመንግስትና ጸረ-ህዝብ በሚል የሚያስፈርጀዉ? ፌዴራላዊ ስርአቱን እንዳለ አለመፈለግና በስርአቱ ማእቀፍ ዉስጥ ሆኖ አንዳንድ ማስተካካያ ማድረግ ለየቅል ናቸዉ፡፡ከህገመንግስቱ አንዲቷን አንቀጽ ከነካህ ከእኔ ጋር ትጣላለህ ማለት በጭራሽ የሚያስከድ አይሆንም፡፡ስርአቱ ሆን ተብሎ ለተወሰኑ ወገኖች ብቻ እንደሚበጅ ተደርጎ የተዘጋጀ ይመስል አንዳችም ማሻሻያ እንዳይደረግ መከልከል የጤና አይመስለኝም፡፡ ስርአቱን እንዳለ ተቀብሎ የተወሰነ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ እንዲደረግ የሚጠይቅ ስርአቱን ጭራሽ እንደማይፈልግ ተደርጎ ሊተረጎምበት አይገባም፡፡ስርአቱን እንዳለ የሚቃወምንና ስርአቱን ለማጠናር የሚያስችል የተወሰነ ማስተካከያ እንዲደረግ የሚፈልግ በአንድ ላይ ሊወቀሱ አይገባም፡፡

በስርአቱ ጉዳይ ላይ አንዳችም አስተያየት ወይም ነቀፌታ እንዳይነሳ መከልከስ በምን አግባብ ነዉ የስርአቱ ቋሚ ጠበቃና ተከራካሪ የሚያሰኘዉ?የስርአቱ ባለቤት ማንም ሳይሆን መላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑ ላይ ልዩነት ከሌለን ከቡድን ፍላጎት ወጥተን የህዝብን ፍላጎት መነሻ ባደረገ መልኩ መነጋጋር የማንችለዉስ ለምንድነዉ?ስርአቱ የማይመለከተዉና በስርአቱ ላይ የተለየ ኃላፊነት ያለዉ፤ስርአቱ የመጣለትና ስርአቱ የመጣበት ወዘተ መባባሉስ ምን ያህል ተገቢነት አለዉ? አንዱን የስርአቱ ወዳጅ ሌላዉ ደግሞ ጠላት እያለ ለመፈረጅ የተለየ ስልጣን የተሰጠዉ አካልስ የትኛዉ ነዉ? ስርአቱ ማንም ያምጣዉ ማን ለሁላችንም የሚጠቅመን መሆኑን ተቀብለን በሚቸግሩን ጉዳዮች ላይ ምን ቢናደርግ ይሻላል እያልን መመካካሩ ነዉ የሚበጀን፡፡

በመሰረቱ ፌዴራላዊ ስርአታችንን በሚመለከት ይህን መንገድ የመረጥነዉ በዉጭ ለጋሽ ሀገሮች ጉትጎታ ወይም እነሱን ለማስደስት ተብሎ ሳይሆን ለኛ ይበጀናል በሚል እምነት ነዉ፡፡. አስካሁን በነበረዉ ሁኔታ የዉጭ ሀገር ምሁራን ስለምንከተለዉ ፌዴራላዊ ስርአት ልዩ መሆን ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የነበሩ ግጭቶችና በማስወገድና ሰላምና መረጋጋትን በማስፈንና የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር ብቻ ሳይወሰን ሁሉንም ህዝቦች ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችልና በአጭር ግዜም ከፍተኛ የሆነ ሁለንተናዊ እድገት ለማስመስዝግ ያስቻለና ለሀገሪቱ ለኡላዊነት መረጋገጥ ፊቱን መድሃኒት እንደሆነ ከኛዎቹ ምሁራን በበለጠ ምስክርነታቸዉን ሲሰጡ ቆጥተዋል፡፡

እነዚህ የዉጭ ምሁራን መጀመሪያ አካባቢ ላይ በምንከተለዉ ስርአት ትክክለኛነት ላይ ጥርጣሬ የነበራቸዉ ቢሆንም ከግዜ በኋላ ግን ስርአቱን የኢትዮጵያ ብቸኛና ልዩ ተሞክሮ አድርገዉ በመዉሰድ ከማበረታታትና በሌሎች ሀገሮችም የኛን መልካም ተሞክሮ እንዲቀስሙ ከመምከር ዉጭ ስርአታችሁ አይበጃችሁም አላሉንም፡፡ እነዚህ ትላንት አድናቆታቸዉን ስገልጹልን የነበሩ የዉጭ ሰዎች ዛሬ በየአካባቢዉ የሚታየዉን የርስበርስ መቆራቆዝ ሲያዩ ምን ሊሉን እንደሚችሉ አላዉቅም፡፡እንዳንድ የዉጭ ፀሀፍት ቀደም ሲል የስርአቱን ልዩ መሆን በበጎ ጎኑ ሲያሞካሹ እንዳልነበር አሁን ግን ቀድሞዉኑ ብሄር(ቋንቋ)ን መሰረት ያደረገ ፌዴራላዊ ስርአትን የተሳሳተ መሆኑን አስጠንቅቀናችሁ ነበር ማለት መጀመራቸዉ አስገራሚ ነዉ፡፡

በርግጥ እኛ ልንክደዉ የማይገባ ነገር ከአሃዳዊ ስርአት ይልቅ ፌዴራላዊ ስርአትን መምረጣችን አንዳችም ጥያቄ የማይነሳበትና ተገቢም ሆኖ አያለ ነገር ግን በዚሁ በፌዴራላዊ ስርአቱ ማዕቀፍ ዉስጥ ሆነን በአተገባባር ረገድ በሚገባ አስበንበት ልንገባባት ይገቡ የነበሩና የተወሰነ ግድፈት የተደረገባቸዉ ጉዳዮች ያሉ ይመስለኛል፡፡ከሁሉም በላይ የወቅቱን ሁኔታና የህዝብ ፍላጎትን መነሻ ባደረገ መልኩ በሂዴት እየታየ እርምትና ማስተካከያ ለማድረግ ፈጽሞ የማይሞከር ማድረጋችን ነዉ ትልቁ ችግር የምመስለኝ፡፡አንዴ ገብተንበታልና አይናችንን ጨፍነን መቀጠል አለብን የሚለዉ አመለካከት እጅግ እየጎዳን መሆኑን ለመገንዘብ ብዙ ግዜ ጠይቆናል፡፡አሁንም ቢሆን በዚህ ጉዳይ ላይ ለመነጋጋር ገና ዝግጁ የሆን አይመስለኝም፡፡

ፌዴራላዊ ስርአት ስለተከተልንና የብሄር ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን መብትና እኩልነት የሚያረጋጋጥ ህገ መንግስት ስላጸደቅን ብቻ ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ምድር የማንነት ጥያቄና የእርስበርስ ግጭት የሚባል ነገር ጨርሶ እንደማይነሳ አድርገን ቆጠርን፡፡ለምናልባቱ ብለን እንኳ ቀዉሶችን መቆጣጠሪያ ዜዴም ሆነ መግቻ ልጓም አላበጀንለትም፡፡እናም አሁን በየቦታዉ ችግሮች ሲከሰቱ እንዴት መፍታት እንዳለብን መላዉ የቸገረን ነዉ ያስመሰለዉ፡፡ይሄን የመሰለ ምርጥ ህገመንግስታዊ ስርአት እያለን ለምንድነዉ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት አካባቢ በገፍ ሲፈናቀሉ መቆጣጠር ያቀተን?ወልቃይት፤ ቅማንት፤ ቦረና ፤ሲዳማ፤ጌዲኦ ፤ኮንሶ ፤ሶማሌና ኦሮሚያ ወዘተ የሚባሉ በየዕለቱ የምንሰማዉ መርዶ መሰል ዜና በዚህ ዘመንና በዚህ ስርአት ዉስጥ ሊከሰት ይገባዉ ነበር እንዴ?ለዘመናት ተዋዶና ተቻችሎ በጋብቻም ተሳስሮ የኖረ ህዝብ እንዳልተባልን ዛሬ መዋደዱና በጋብቻ መተሳሳሩ ቀርቶብን ቢያንስ እርሰበርስ ሳንጋጭና ለዘመናት ከኖርንበት አካባቢ ሳንፈናቀል በሰላም መኖር እንኳን የተሳነን ለምነድነዉ? ሀገራችን የኤርትራን፤የሶማሊያንና የሱዳንን በርከታ ስዴተኞች መጠጊያ ሆና በሀገራቸዉ ማግኘት ያልቻሉትን ሰላምና ደህንነት እንዲያገኙ ማድረግ በመቻላችን በሰራነዉ በጎ ተግባር በዓለም ማህበረሰብ ከፍተኛ አድናቆት ተቸሮን እያለ የራሳችን ህዝቦች በገዛ ሀገራቸዉ ያለስጋት መኖር ያልቻሉበትና እንደ ጠላት ተቀጥቅጠዉ የሚባረሩበት ምክንያትና ምስጥር ምንድነዉ? ይሄን ጉዳይ ማንነዉ ሊያስረዳን የሚችለዉ?

2 መቋጫ ባጣዉ ህዝባዊ ተቃዉሞ ዙሪያ አንዳንድ ጉዳዮች ፤

2.1 ተቃዉሞዉና ህዝባዊ ቁጣዉ ተገቢነቱን አምነን ለመቀበል ብዙ ጊዜ ጠይቆናል፤

የወቅቱን አመጽ ለተከታታለ ሰዉ ህዝቡ በሆነ ጉዳይ ላይ እርካታ እንደሌለወ ቢያንስ ያልተስማማዉ ነገር እንዳለ መረዳት አይሳነዉም፡፡የአሁኑ የህዝብ ተቃዉሞ እንደበፊቱ ተጨማሪ የልማት ጥያቄ የመጠየቅ ጉዳይ አልመሰለኝም፡፡ያ ወቅት አልፏል፡፡አሁን ጥያቄዉ ተቀይሮ ሌላ መልክ ይዟል፡፡ዛሬ የህዝቡ ጥያቄ በአንድ በተወሰነ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሳይሆን አጠቃላይ ለዉጥ የፈለገ ይመስላል፡፡ሰንደቅ ዓላማ የሚቀዳድድ ፤የሚማርበትን ት/ቤት የሚያፈራራስ ፤ራሱ የሚገለገልበትን የህዝብ ማመላለሻ የሚያቃጥልና ተቀጥሮ የሚሰራበትን ፋብሪካ የሚያጋይ ትዉልድ ተጨማሪ የመብት ጥያቄ ይሟላልኝ በሚል ሊሆን አይችልም፡፡በእጁ ያለዉንና የሚጠቀምበትን እያወደመ መሆኑን እያየን ጥያቄዉን በስራ ማጣትና በኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ብቻ መተርጎም የሚያስከድ አይደለም፡፡የተቃዉሞዉ ዓላማ ምንም ይሁን ምን በሀገርና በህዝብ ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስና ንጹሃን ላይ ጥቃት ማድረስ ተገቢ ነዉ ልንል አንችልም፡፡የተቃዉሞ አድራጊዎች ቁጣ እጅግ ያየለ ለመሆኑ ማሳያዉ የሀገሪቷ ጉዳይ ብዙም ያሳሰባቸዉ አለመሆኑ ነዉ፡፡

እየቀረበ ያለዉ ጥያቄ የስርአት ለዉጥ ነዉ እንዳንል ህዝቡ በተለይ ወጣቱ እንዲመለሱለት ከሚፈልጋቸዉ በርካታ ጥያቄዎች መካከል በህገመንግስታዊ ስርአቱ ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ ሲያነሳ አልሰማንም፡፡ነገር ግን ስርአቱን እየመራ ባለዉ መንግስት ላይ ጥያቄ እንዳለዉ ግልጽ ነዉ፡፡ በመንግስት አመራር ብቃት ላይ አመኔታ ማጣቱም ምንም አያጠራጥርም፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት በየግዜዉ በአደባባይ ቃል በሚገቡት ላይ አመኔታ ማጣቱና በዚህም ተስፋ መቁረጡ እርግጥ ነዉ፡፡ነገር ግን ህገመንግስታዊ ስርአቱንም ሆነ ህገመንግስቱን አልፈልግም አላለም፡፡ ከዚያ ይልቅ እያለ ያለዉ ህገመንግስቱን በትክክል እያሰከበራችሁ አይደለም ነዉ ፡፡

የመልካም አሰተዳዳር ችግር ለምን መቅረፍ እንዳልተቻለና ሙሲና ወይም ዝርፊያ ሊገታ ያልቻለበትን ምክንያት የሚያስረዳዉ አካል ይፈልጋል፡፡መሬት አይሸጥም አይለወጥም እየተባለ በጎን አንድ የበሬ ግንባር የሚታክል ቁራሽ መሬት በሚሊዮኖች የሚቸረቸርበት ምክንያትን እንዲያስረዱት ይፈልጋል፡፡የበርካታ አርሶአደሮች መሬት እዚህ ግባ በማይባል ካሳ መንግስት ተረክቦ ግለሰቦች አንዳችም ነገር ሳይሰሩበት ለዓመታት አጥረዉ የሚያስቀምጡበትና አንዳንዶቹ ደግሞ በብዙ ሚሊዮን ብር የሚቸበችቡበትን ህገመንግስታዊ አግባብ የሚያስረዳዉ አካል ይፈልጋል፡፡

ህዝቡ ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላም ሀገሩ ዲሞክራሲ ቅንጦት የሆነባትና በአንዳንድ ጥጋበኛ ባለስልጣናት ሰብአዊ መብት የሚጣስባት ሀገር ለመሆን የተገደደችበትን ምከንያት እንዲያስረዱት ይፈልጋል፡፡

በገዛ ሀገሩ በየትኛዉም ባሰኘዉ አካባቢ ተዘዋውሮ በሰላም የመኖርና የመስራት መብቱ ተነፍጎ ከየአካባቢዉ እንደ ጠላት ሰራዊት እየተቀጠቀጠ እንደ ዉሻ የሚባረርበትን ምክንያትና መንግስትም ይህንን ድርጊት እስካሁን ሊያስቆም ያልቻለበትነ ምክንያት ማወቅ ይፈልጋል፡፡እናም ወጣቱም ሆነ ህዝቡ በህገመንግስቱ የተረጋገጠላቸዉንና በዜግነት መብታቸዉ ማግኘት የሚገባቸዉን እንጂ መጠየቅ የማይገባቸዉን ትርፍ ነገር አልጠየቁም ፡፡

እየተነሳ ያለዉ ቅሬታ የአንድ አካባቢ ህዝብ ብቻ ጥያቄም አይደለም፡፡ኦሮሞዉም ትግሬዉም ደቡቡም አፋሩም አማራዉም ወዘተ ሁሉም ቅሬታ አላቸዉ፡፡እናም የወጣቱ ችግር ነዉ ፤የትምክህተኞች ሴራ ነዉ ፤የጠባቦች አመለካካት ነዉ ወዘተ እያልን ራሳችንን ከማታለል መስተካከል የሚገባዉን ግዜዉ ሳይረፍድብን ካሁኑ ማስተካከሉ ይመረጣል፡፡ግትር መሆንና “ድርቅ ”ማለትም የትም እንደማያደርስ ልንገነዘብ ይገባል፡፡ስርአቱን እንደሆነ አማራዉ ከትግረዉ ባላነሰ ይፈልገዋል፡፤ኦሮሞዉ ከደቡቡ ባልተናናሰ የስርአቱን ጥቅም ይረዳል፡፡አፋሩ ከወላይታዉ ባልተናናሰ ስርአቱን ይፈልገዋል፡፡ከስርአቱ የሚገኘዉ ጥቅም ሆነ ችግርም ቢኖር ሁሉም የሚጋራዉ እንጂ የአንድ አካባቢ ህዝብ የብቻ ችግር አይሆንም፡፡

ኦሮሞ ቅሬታ አለኝ እያለ ለአማራ ተብሎ ዝም ብለህ ተቀበል አይባልም፡፡ትግሬዉ አማራዉ ወይም ኦሮሞዉ ከኖሩበት ቀዬ እየተፈናቀሉና እየተገደሉ ደቡቡንና አፋሩን አናንተን ስለማይመለከት አርፋችሁ ተቀመጡ ሊባሉ አይገባም፡፡ስለዚህ ስርአቱ የሁሉም ህዝቦች ነዉ፡፡ ሕገመንግስቱም የሁሉም ህዝቦች ነዉ፡፤ሀገሪቱ ዉስጥ የተከሰተዉ ችግርም ሁሉን ህዝቦች የሚመለከት ነዉ፡፡የወጣቱ ጥያቄም የሁሉም ህዝቦች ጥያቄ ነዉ፡፡ የአርብቶ አደሩ ችግር የአርሶ አደሩም የከተሜዉም ችግር ነዉ፡፡ስለዚህ በስርአቱ ዉስጥ መከፋትም ሆነ መድላት ካለ ስሜቱ የሁላችንም እንጂ የአንድ አካባቢ ብቻ ሊሆን አይችልም፡፡ከስርአቱ በተሻለ የተጠቀመና የተጎዳ በሚል መፈረጅ አይቻልም፡፡እናም መፍትሄዉም በተናጠል የሚታሰብ ሳይሆን አጠቃላይ ፍተሻ ማድረግን የሚሻ ነዉ፡፡

2.2 ጥያቄዎቻችንም ሆኑ የተቃዉሞአችን ዓላማ በሚገባ የተቃኘ አይደደለም፡፡

ጥያቄአችን ምንድነዉ? ምን እንዲሟላልን ነዉ የምንፈልገዉ? ፍላጎታችን የስርአት ለዉጥ እንዲደረግ ነዉ ?ወይንስ ስርአቱ እንዳለ ሆኖ አገዛዙ በሌላ እንዲተካ ነዉ?ጠባችንስ ከማን ጋር ነዉ?ከባንድራችንና ከሀገራችን ወይንስ ከገዥዉ ፓርቲና ከመንግስት?እንደዚያም ሆኖ እርስበርስ መገዳዳልና መፈናቀል ሳይኖር ት/ቤት፤ ፋብሪካ፤ ተሸከርካሪ ወዘተ የሀገር ንብረት ሳናወድም ጥያቄአችንን ግፋ ስልም ተቃዉሞአችንን በሰላም ማቅረብ እንችልም ማለት ነዉ? የምናነሳዉ ጥያቄ ንጹሃን ወገኖቻቸን ከመግደልና ከማፈናቀል ጋር ምን ያገናኘዋል? ለመሆኑ ጥያቄያችንን እንዲመልስን የምንፈልገዉ ማን ነዉ? የትኛዉም ዓይነት ጥያቄ ቢኖረን ከመንግስት ዉጭ ምላሽ እንዲሰጠን የምንጠብቀዉ ሌላ የዉጭ አካል ሊኖር ይችላል ? መንግሰትስ ቢሆን አስርሺዎች በሰላማዊ ሰልፍ አደባባይ ካልወጡና በቁጣ ንብረት ወድሞ ካላየና በህዝብ ላይ ጉዳት ካልደረሰ በስተቀር የቀረበለትን ጥያቄዎች በጊዜ ማስተናገድ አይችልም ነበር ማለት ነዉ?

መጠየቅ ያለብን ልንጠይቅ የምገባንና የግድ መለስ ልናገኝለት የምንችለዉን እንጂ መልስ የሌለዉንና ተገቢ ያልሆነዉን ሁሉ መሆን አይኖርበትም፡፡ጥያቄያችንን ሊመልስልን የሚገባዉም የኛዉ መንግስት እንጂ ሌላ የዉጭ አካል አለመሆኑን ተገንዝበን ወደ ዉጭ ወደ ሌላ ባእድ አካላት ማማተሩንና ከነሱ መመሪያ መቀበሉን ማቆም ይገባናል፡፡ በሌላ በኩል ገዥዉ ፓርቲንና መንግስትን ለመዉቀስ የሚያስችለን ከበቂ በላይ ምክንያቶች ሲላሉን መንግስትን በምን ጉዳይ ልክሰሰዉ በምንስ ጉዳይ ላሳጣዉ እያልን ከዉጭ ምክር መጠየቅ የሚያስፈልገን አይመስለኝም፡፡

ዛሬ አንዳችን ከሌላዉ ሳንለይ ሁላችንም “የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል” እንደሚባለዉ ከጠዋት እስከማታ ገዥዉ ፓርቲን ሳንራገምና ቢያንስ ሳንወቅስ በሰላም ዉለን ያደርንበት ቀን ስሌለለ በመንግስት ላይ ወቀሳ የማቅረብ እጥረት ያለብን አይመስለኝም፡፡እንደ ችግሮቻችን መብዛት ይሄን ማድረጋችንም በጭራሽ አያስወቅሰንም፡፡ነገር ግን መንግስትን መዉቀስና መተቸት ያለብን መተቸት በሚገባን ጥፋቱ ላይ ቢሆን ይመረጣል፡፡የምናቀርበዉ ትችትም መንግስት ሰምቶን እንዲያርምና እንዲያስተካክል የምንፈልገዉን እንጂ በዘፈቀደና ሌሎች አካላትን ለማስደሰት ሊሆን አይገባም፡፡

2.3 የኛ ቸልተኝነት እንጂ ተቃዉሞና ህዝባዊ ቁጣዉ ያልተጠበቀም አይደለም፤

ህዝባዊ ተቃዉሞዉ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በሚሳተፈዉ ህዝብ ብዛት፤ በሚያካልለዉ አካባቢ ስፋትና በሚነሳዉ ጥያቄ ባህሪይ ዉስብስብነት አንጻር ስንመዝነዉ ለመንግስትም ሆነ ለኛ ለዜጎች ቀላል ተግዳሮት እንዳልሆነ ለመረዳት አይከብድም፡፡ የተቃዉሞዉና ህዝባዊ ቁጣዉ ድንገት እንደዱብድ የተከሰተ ሳይሆን ቀስ በቀስ ሲብላላ ቆይቶ በሂዴት አሁን የደረሰበት አደገኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ነዉ፡፡አሁን ላይ እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች ጎልተዉ እንዲወጡ ከመደረጉ ዉጭ በፊትም የሚታወቁና በተደጋጋሚ ሲጠየቁም የነበሩ ናቸዉ፡፡ በወቅቱ ሲቀርቡ ለነበሩ ጥያቄዎች ትኩረት ተደርጎበት አቅም በፈቀደ መጠን ተገቢዉ ምላሽ ባለመሰጠቱ ምክንያት እያንዳንዱ ጥያቄ ከሌላዉ ጥያቄ፤ አንዱ ብሶት ከሌላ ብሶት ጋር እየተዳበለ በመወሳሰቡ አሁን ላይ ለመፍትሄም የማይቻል አደረገዉ እንጂ በፊት የማይታወቅ አዲስና እንግዳ የሆነ ጥያቄ አልቀረበም፡፡

ጉዳዩን ከዲሞክራሲ መብት መጓደል አንጻር እንዃን ብንመዝነዉ የሀገራችን ዲሞክራሲ ህዝቡ በሚጠብቀዉ ደረጃ አለመሆኑ ከዚህ ቀደምም በሚገባ የሚታወቅ ነዉ፡፡ሰብአዊ መብትንም በሚመለከት በአንድ ወይም በሌላ መንገድ በባለስልጣናትና ራሳቸዉን ከህግ በላይ ባደረጉ ግለሰቦች የዜጎች ሰብአዊ መብት እንደሚጣስ በሚገባ ይታወቃል፡፡ስራ አጥነትና ድህነት የሀገሪቱ ዋኛ ችግር የነበረና አሁንም መሻሻል ያልታየበት መሆኑን እኛም መንግስትም እኩል ጠንቅቄን እናዉቃለን፡፡ የትኛዉ ችግርና የትኛዉ ጥያቄ ነዉ አዲስና በፊት የማይታወቅ?ወጣቶች ኮሌጅ ጨርሰዉ ስራ አጥተዉ አማራጭ ሲያጡ የአደንዛዥ እጽ ሰለባ መሆናቸዉና ገሚሱ ደግሞ ስዴትን እንደ አማራጭ ወስዶ በየበረሃዉ ተደፍቶ ሲቀርና የባህር ሲሳይ ሲሆን ዛሬ ገና ነዉ የሰማነዉ?እናም ወጣቱ አማራጭ ሲያጣና በመንግስት ተስፈ ሲቆርጥና ትእግስቱ ሲሟጠጥ በቁጣ ለአመጽ ሊነሳ እንደሚችልና የራሱንም ንብረት ሳይቀር ከማወደም እንደማይመለስ ቀድሞዉኑ አናዉቅም ነበር እንዴ? ወጣቱ የተጫነበት ችግር ከአቅሙ በላይ ሲሆንና ተስፋ ሲቆርጥ የፌዴራል ፖሊሲና የመከላከያን ጥይት መፍራት እንደሚያቆምና ለመሞትም እንደማያመነታ በፊቱኑ የማይታወቅ ሆኖ ነዉ?ሌላዉ ቀርቶ ወጣቱ የሚያነሳዉ ጥያቄ የራሱ የወጣቱ ብቻ ጥያቄ ሳይሆን የህዝብም ጥያቄ መሆኑን ለመቀበል ለምን ከበደን ? እየቀረበ ያለዉ ጥያቄና ተቃዉሞዉ ተገቢ ነዉ ብለን አምነን ከተቀበልን የጎዳና ላይ አመጽና ቁጣ ከመቀስቀሱና ንብረት ከመዉደሙ በፊት ገና በሰላም ግዜ መፍትሄ ማስቀመጥስ ለምን ተሳነን?

3. አሳሳቢዉ የእርስ በርስ ግጭትና ሰንካላዉ የግጭት አፈታት ዘዴያችን፤

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ለዘመናት ተፋቅረዉና ተከባብረዉ ምናልባትም ተዋልደዉ በኖሩ ህዝቦች መካከል በተለያዩ ምክንያቶች እየተቀሰቀሱ ያሉ ግጭቶች ህዝቡ ራሱ ፈቅዶና ወድዶ ያደረገዉ ሳይሆን በሌሎች መሴሪ ኃይሎች ተንኮል እንደሆነ በሚገባ የሚታወቅ ነዉ፡፡መነሻዉ ምንም ይሁን ምን የዚህ መሰል በህዝቦች መካካል የሚቀሰቀሱ ግጭቶች በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ያልነካዉ የሀገሪቱ አካባቢ ወይም ክልል ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ከጥቂት ዓመታት በፊት የዚህ ዓይነት ግጭት ጋምበላ ወይም ደቡብ ክልል አካባቢ ተከሰተ ሲባል በመንግስት በኩል አምኖ ለመቀበል አለመፈለግ እንዳለ ሆኖ አብዛኛዉ የኢትዮጵያ ህዝብም ቢሆን በሁኔታዉ ግራ በመጋባት እንዴት በኢትዮጵያ ምድር እንደዚህ ዓይነት ነገር ይፈጠራል በሚል እዉነታዉን ለመቀበል እንኳን ያለመፈለግ ነገር በሰፊዉ ይስተዋል ነበር ፡፡

ዛሬ ዛሬ ላይ ግን ግጭት የተከሰተባቸዉን አካባቢዎችን በስም መጥቀሱ ብዙም አስቸጋሪነት በሌለዉ ሁኔታ በተለያዩ አካባቢዎች ወቅቱን እየጠበቀ ተከስቷል፡፡አሁን አሁንማ መንግስትም ቢሆን እንደ ድሮዉ ግጭት መከሰቱን ለመደባበቅ የሚሞክርበት ዕድል የለዉም፡፡ ፡፡በዚህ ምክንያትም ስለ እርስበርስ ግጭት፤ስለመፈናቀልና ግድያ ዜና ሲሰማ ህዝቡ ከሁኔታዉ ጋር እየተለማመደ ስለመጣ በሚመስል ምክንያት በሚሰማዉ መጥፎ ዜና ብዙም ግር አይሰኝም፡፡ተመሳሳይ ከስተቶች ወቅታቸዉን እየጠበቁ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሲከሰቱ ስለቆየ ስለሁኔታዉ የማያዉቅ ህዝብ አይኖርም፡፡ህዝቡ በከስተቱ መደጋገም የተነሳ በዜናዉ ግራ መጋባት ቢያቆምም ነገር ግን ሁኔታዉ በወደፊቱ የሀገሪቱ ዕጣ ፈንታ ላይ ምን ሊያስከትል እንደሚችል በማሰብ ከፍተኛ ስጋት እንደገባዉ መደበቅ አይቻልም፡፡

አሁን በሚታየዉ ደረጃ የከፋ ባይሆንም ይህን መሰል ግጭቶች ሲከሰቱ የመጀመሪያችን አይደለም፡፡ከዚህ በፊት በተለያዩ አካባቢዎችና በተለያዩ አጋጣሚዎች ግጭቶች ሲፈጠሩ እንደነበር የሚታወቅ ነዉ፡፡በአርባ ጉጉ፣ በአርሲ ነገሌ፣ በመተከልና በቤንች ማጂ የተካሄዱ ግጭቶች ፤በጉጂ ኦሮሞና በጌዲኦ ሕዝብ መካከል፣ በምሥራቅ ወለጋ ጊዳ ኪራሞና አቢደንገሮ ወረዳዎች በሠፈሩ ዜጐች ላይ የተከሠተው ችግር፣ በወላይታና ጋሞ ሕዝብ መካከል፣ በአሬሮ ወረዳ በጌሪና የቦረና ኦሮሞ መካከል፣ በአኙዋክና ኑዌር ሕዝብ መካከል፣ በአማራና በአፋር፣ በአፋርና ሶማሌ፣ በአፋርና አሮሞ፣ በአሮሞና በሶማሌ ወዘተ ሕዝብ መካከል፣ በተደጋጋሚ ጊዜያት የተከሠቱ ግጭቶች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸዉ፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በአንድ ወይ በሌላ መንገድ መፍትሄ ለማስቀመጥ መሞከሩ ባይቀርም ነገር ግን የችግሩ ዋነኛ ምንጭ በሚገባ ሳይለይና ሁሉንም ወገን እኩል ስምምነት ባላገኘበት ሁኔታ ለጊዜዉ ለመገላገል ያህል ብቻ ዘላቂነት የሌለዉ ፖለቲካዊ ዉሳኔ እየተሰጠበትና ዳግመኛ እንዳይቀሰቀስ የሚያደርግ ዘላቂ መፍትሄ አየተበጀለት ባለመመጣቱ በአንድ ወቅት መፍትሄ አግኝቷል የተባለለት ጉዳይ በሌላ ግዜ በቀላሉ በጥቂት ግለሰቦች ቆስቋሽነት ተመልሶ ወደ ግጭት ሲያስገባን እያየን ነዉ፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ የሚታዩት የርስበርስ ግጭቶች አዝማሚያቸዉ እጅግ አሳሳቢ እንደሆኑ ለማንም ግልጽ ነዉ፡፡ አንዳንዴ መንግስት ህዝቡን ለማረጋገትና ተስፋ ላለማስቆረጥ እያለ ሁኔታዉን ሊያቃልለዉ እንደሚሞክረዉ ሳይሆን የችግሩ አሳሳቢነት በገዜ መፍትሄ ካልተቀመጠለት በስተቀር ሀገራችንን ወደ አደገኛ ሁኔታ ሊያስገባት የሚችል መሆኑን ማንም ይገነዘባል፡፡

በየግዜዉ ሲከሰቱ የነበሩ የርስበርስ ግጭቶች ፈጣን ምላሽ እንዳያገኙና በመፍትሄዉ ላይም ህዝቡና ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች በንቃት እንዲሳተፉ ማድረግ ያልተቻለበት ዋነኛዉ ምክንያት የምመስለኝ የዚህ ዓይነት በህዝብ መሃል ለሚነሱ ግጭቶች በይፋ እዉቅና መስጠት ማለት የምንከተለዉን ፌዴራላዊ ስርአቱን ገጽታ የሚያበላሽ ብሎም ስርአቱን ለሚነቅፉ ኃይሎች መልካም አጋጣሚ ይሆናል በሚል ስጋት በመነጨ ችግር መኖሩ እየታወቀም ለመሸፋፋን በመሞከሩ ነዉ፡፡ይህ ድብቅነታችን ግን እየጎዳ ያለዉ እኛኑ መሆኑን ተገቢዉ ግንዛዜ የተያዘበት አልመሰለኝም፡፡የዚህ አይነት ችግሮች በየትኛዉም ሀገር ሊከሰቱ የሚችሉ መሆኑን ዘንግተን እኛ ከሌሎች በተለየ ሁኔታ አንድም ችግር የማይታይባት ሀገርና ስርአት የመሰረትን ለመምስል መሞከራችን እጅግ አስተዛዛቢ ነዉ፡፡በሀገራችንና በህዝባችን ላይ በተጨባጭ እየደረሰ ካለዉ ችገር ይልቅ ለስርአቱ ገጽታ መጠበቅ መጨነቅ ላይ ነዉ ትኩረት እያደረግን ያለነዉ፡፡ፌዴራላዊ ስርአቱ እንደሆን በምንም መንገድ ቢሆን የግጭት መንስኤ እንደማይሆን ማናችንም ብንሆን ጠንቅቄን እንረዳለን፡፡

እጅግ የዳበረ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዜዴ አለን፡፡ለዚያዉም አማርጠን ልንጠቀምበት የሚያስችለን፡፡የሲዳማዉ፤ የኦሮሞዉ፤ የትግሩዉ የአማራዉ የጉራጌዉ ወዘተ የየራሳቸዉ ልዩ የሆነ አስጋራሚና እጅግ የተዋጣለት የችግር አፋታት ባህል ባለቤቶች ሆነን እያለ ነገር ግን ጊዜ አመጣሽ የሆኑ ጥቃቅን ልዩነቶቻችንን ፖለቲከኞቻችን መፍታት ተስኖአቸዋል፡፡አዳዲስ ግጭቶችን ከመቀስቀስ በስተቀር ግጭት ማስወገድና ማስታረቅ ያልለመደባቸዉ የኛ ፖለቲከኞች ቢያንስ የሀገር ሽማግሌዎችን ምክር መጠየቅ ሲገባቸዉ ችግሮችን እንዳሌለ አደርገዉ መደባባቁን ነዉ የሚመርጡት፡፡በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ነፍሳቸዉን ለማዳን ከኖሩበት አካባቢ ሲሸሹና በግድ ሲፈናቀሉና በመቶ የሚቆጠሩትም በግፍ ሲገደሉ እያዩ ኃላፊነት ያለባቸዉ አመራሮቻችንም ቅድሚያ ሰጥተዉ መፍትሄ ማስቀመጥ ሲገባቸዉ “የራሷ እያረረባት የሰዉ ታማስላለች” እንደሚባለዉ ሆኖ ነዉ መሰለኝ ከኛ ችግር ይልቅ የሌላዉ ሀገር በልጦባቸዉ በሌሎች የዉስጥ ግጭት አፈታት ላይ ብዙ ሲደክሙ ስናይ ማዘናችን አይቀርም፡፡

የርስበርስ ግጭት ስጋት እንደተጋረጠብንና አስካሁን የታየዉ የግጭት አፈታት ዜዴያችን አስተማማኝ አለመሆኑን አምነን ለመቀበልና አምነን ተቀብለንም ሁኔኛ መፍትሄ ለማስቀመጥ ይሄን ያህል ዘመንስ ለምን ጠየቀን? በተለያዩ ክልል ህዝቦች መካካል በተከሰተዉ ግጭት የተፈጸመዉ የእርስበርስ መገዳደልና በገፍ መፈናቀል ወዘተ የመሳሳሉ ቀዉሶችን የግድ በተግባር ደርሰዉ ካላየን በስተቀር አስቀድመን ችግሩን ለመረዳትና ተረድተንም መፍትሄ ለማስቀመጥ አንችልም ማለት ነዉ?የግድ አደጋ ደርሶ በዓናችን ካላየንና የዉጭ ሚዲያዎች እየተቀባባሉ ካላራገቡት በስተቀር እኛዉ ራሳችን ችግራችንን መረዳትና መፍታት አንችልም ማለት ነዉ?እኔ እንደምመስለኝ ለሀገራችን በዚህ ደረጃ ቀዉስ ዉስጥ መግባት ማንም ከማንም ሳይለይ ሁላችንም ሃላፊነት አለብን፡፡የሁላችንም ደክመት መሆኑን አምነን መቀበል ይኖርብናል፡፡ዋናዉ የችግራችን ምንጭ የዲሞክራሲ ባህላችን አለመዳበሩና የረባ ጥረትም አለማድረጋችን ሲሆን ከሁሉም በላይ ደግሞ ከሀገርና ከህዝብ ጥቅም ይልቅ ራስ ወዳድነታችንና ስግብግብነታችን ያስከተለዉ ጣጣ መሆኑን መቀበል ይኖርብናል፡፡

ማጠቃለያ

በሀገራችን አየታየ ያለዉ አለመረጋጋት ያለአንዳች ምክንያትና ሳናስበዉ የተፈጠረ ዱብድባ ሳይሆን መፍትሄ መስጠት ባለመቻላችን ለዓመታት ስናስታምመዉ የቆየ ችግር ነዉ፡፡እንኳን መፍትሄዉ ላይ ልንስማማ ቀርቶ ችግር መኖሩ ላይ እንኳን መግባባት ተስኖን በመቆየታችን እንጂ የሀገራችን ችግር መፍትሄ የሚጠፋለት ሆኖ አይደለም፡፡አሁንም ቢሆን “የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል” እንደሚባለዉ ለሁሉም ችግር ነጋ ጠባ መንግስትን ከመንቀፍና ጣት ከመቀሰር ተላቀን ለመፍትሄዉ ቁጭ ብለን መወያየት መጀመር አለብን፡፡በመንግስት በኩልም ሃላፊነት የሚሰማዉ ነጻ ሚዲያ ሊኖረዉ የሚችለዉን ጠቃሚ ድርሻ ተረድቶ የግል ሚዲያዉን ከማበረታታት ጀምሮ በመንግስት ሚዲያ አካባቢም ለዉጥ ማምጣት መጀመር አለበት፡፡ከሰሞኑ ኢቢሲ ላይ የተስተዋለዉ ዓይነት የህብረተሰቡን አስተያዬት ሳይቆርጥ ሳይቀጥል በግልጽ ማቅረብ የጀመረበት አሰራር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡

መንግስት በየመንደሩና በየወረዳዉ የሚነሱ ተቃዉሞዎችን በተናጠልና አንድ በአንድ ለመቆጣጠር መሞከሩ ኃይል ከማባከንና ግዜ ከመግደሉ ዉጭ የረባ ዉጤት እንዳማያመጣ ተረድቶ ለሁሉም ምላሽ የሚሆን አጠቃላይ የሆነ መፍትሄ ቢያፈላልግ ይበጃል፡፡

ገዥዉ ፓርቲ በር ዘግቶ ብቻዉን የሚያመጣዉ መፍትሄ የትም እንደማያደረሰን ተረድቶ ከታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎች ምሁራንና ፖለቲከኞች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶችና ሲቪክ ማህበራት ተወካዮች የመንግስት ጣልቃገብነት በሌለበት በነጻነት ተመካክረዉ መፍትሄ እንዲያመጡ ሁኔታዉን ሊያመቻችላቸዉ ይገባል፡፡የተቃወሚ ፓርቲ አመራሮች በኩልም የወቅቱን አለመረጋጋት እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀሙን ለጊዜዉ ተወት አድርገዉ ከቀዉስ መዉጫ መፍትሄ በጋራ በማፈላለጉ ጥረት ላይ ከመንግስት ጎን ቆመዉ የበኩላቸዉን ድርሻ እንዲወጡ በዚህ አጋጣሚ ማሳሳብ እንወዳለን፡፡በተረፈ አስካሁን መግባባት በተሳነን ጉዳዮች ላይ ጭምር ለመግባባት ከወሰንና ከራስ ጥቅም ይልቅ ቅድሚያዉን ለሀገር ማድረግ ከጀመርን መፍትሄ የሚጠፋለት አንድም ችግር አይኖርም፡፡

*******

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories