ወንድሜ ፀረ-ትግራይ ዘመቻህን ትተው ዘንድ ልለምንህ! (ለአለምነህ ዋሴ የተሰጠ ምላሸ)

(ክብሮም)

ወንድሜ አለምነህ፤ ያንተን ጣፋጭና አስገምጋሚ ድምፅ ከልጅነቴ ጀምሮ እያዳመጥኩ ያደኩኝ፤ ላንተም ሙያዊ አክብሮትና አድናቆት ብልቤ ውስጥ ሰጥቼ የኖርኩኝ ወጣት ነኝ፡፡

ባጠቃላይ አንተን በሚድያው ዘርፍ 1989 ዓ.ም ጀምሮ ተከታትየሃለው፡፡ በተለያዪ ወቅቶች የዓለም የፖለቲካ ትኩሳት በዛ ማራኪ ድምፅህ ስታስደምጠን በአድናቆትና በጉጉት ያደምጡህ ከነበሩ ውስጥ ነኝ፡፡ በተለይ በኮርያ-ጃፓኑ የዓለም ዋንጫ ግዜ በብራዚልና በጀመርን መሃከል የነበረውን ፉክክር ስዕላዊ በሚመስል ሁኔታ ታቀርበው የነበረውን ሃተታ መቼም ቢሆን አልዘነጋውም፡፡ እንደውም ከቻልክ እነዛን የመሳሰሉትን ቆንጆ ቆንጆ ሃተታዎችህን ወደ ዪቱዪብ ብትጭናቸው የሚል ምክረ-ሃሳብ አለኝ፡፡

ወደ ዋናው ጉዳዪ ልመለስ፤ በቅርቡ ኢቢሲ ይቅርታ ስለጠየቀበት ካርታ ጉዳይ እንዲሁም ዜናውን የሰራው የኢቢሲ ጋዜጠኛ ጭምር በግሉም ስህተቱን እንዴት እንደሰራውና ለዚህ ስህተት ሌላ ተጠያቂ አካል የሌለ ስለመሆኑም ጨምሮ በይፋ ይቅርታ ስለጠየቀበት ነው፡፡

እዚህ ላይ ሁለት መሰረታዊ ስህተቶችን ሰርተሃል ብየ አምናለው፡፡

አንደኛው፡ ካርታው ላይ ያለህ የተንሽዋረረ እንደውም የተደበቀና ፖለቲካዊ ቅኝት ያለው አመለካከትህ ነው፡፡ መቼስ ታሪክ እንደምታውቅ እሙን ነው፡፡ስለትግራይ የግዛት ሁኔታ ስፋትና ጥበት ከሀ/ስላሴ ጀምሮ እስከ ደርግ ምን ይመስል እንደነበረ የማታውቅ ከሆነ መለስ ብለህ እውነተኛና ገለልተኛ የታሪክ መፃሕፍትን ማጣቀስ ሊኖርብህ ነው፡፡

የሆነው ሆኖ አሁን አገራችን በምትከተለው ፌደራላዊ ቋንቋን መሰረት ያደረገ የክልሎች አወቃቀር መሰረት ድሮ ትግራይ ውስጥ የነበረ ለምና ሰፊ መሬቶች ወደ ዓፋር ሄደዋል፡፡ የተወሰኑትም ወደ አማራ ክልል ሄደዋል፡፡ ከሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ሁኔታ አለ፡፡ በዚህ ሂደትም ያልነበሩ አዳዲስ ክልሎችም ተፈጥሮዋል(እንደ ኦሮሚያና ዓፋር የመሳሰሉት)፡፡ በዚህ አወቃቀር መርህ መሰረት ትግራይ በምዕራብ በኩል በሑመራ ከሱዳን ጋር ተገናኝታለች፡፡ ይህ ይፋዊ የሆነው የአገሪቱ ህጋዊ ካርታም በግልፅ የሚያሳየው ነው፡፡

አሁን ያንተ ችግር እዚህ ላይ ነው ያለው ፡፡ ኢቢሲ ይቅርታ በጠየቀበት ካርታ ላይ ትግራይ ከዚህ በፊት ከሱዳን ጋር ትገናኝ ያልነበረች አስመስለህ ያቀረብከው ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ከእውነት የራቀ ዘገባህ ነው፡፡ትግራይን በጎንደር ጀርባ አድርጋ ከሱዳን ጋር ተገናኘች አልክ፡፡ በጣም ያሳፍራል፤ያሳዝናልም፡፡ ካርታው ላየ ግን የሚታየው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከታች ተስቦ የአማራ አካባቢዎችንም ወደ ራሱ አጠቃሎ ከሱዳን ጋር እንዴት እንደተገናኘ ነው የሚያሳየው፡፡ አንተ ግን የቤኒሻንጉሉ ነገር አላሳሰበህምና ችግሩን በግልፅ ከመተችት ትግራይን ባልተገኘችበት ፀረ-ትግራይ ፖለቲካዊና ፕሮፓጋዳዊ ሃተታ መስራትህን መረጥክ፡፡

ይህ ዓላማው ፈልገሀውም ይሁን ሳትፈልገው በትግራይ ህዝብ ላይ አላስፈላጊ ፖለቲካዊ ጥላቻ መፍጠርና ለጥቃት ተጋላጭ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህም ባለፈው ዓመት በጎንደር የሆነውን ማሳታወስ በቂ ነው፡፡መሰረተ-ቢስና ዘረኛ ቅስቀሳዎች መጨረሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል በተግባር ያየነው ነው፡፡

ሁለተኛው፤ ከዚህ ካርታ ጋር በተያያዘ ትግራይን ለመገንጠል ሴራዎች አሉ፤ ይህ ካርታ በተለያየ ግዜ ብቅ እንዲል እየተደረገ ያለው እንድንለማመደው ነው፤ታላቅዋን ትግራይ እውን ሊያደርጉ ነው ከሚለው መሰረተ-ቢስ፤ከእውነት የራቀ፤ሆን ተብሎ በአንድ ኦሪጅናል ኢትዪጵያዊ በሆነ ህዝብ ላይ ጥላቻን በመንዛት በማሸማቀቅ አንገቱን እንዲደፋ ለማድረግ ብሎም የፌደራል ስርዓቱን በማፍረስ የቀደመውን አሃዳዊ ስርዓት ለመመለስ ህልም ካላቸው ሃይሎች ጋር የተያያዘ አመለካከት ነው፡፡አንተም የዚህ አመለካከት ሰለባ ከሆንክ በጣም ቆይተሃል፡፡ 

እዚህ ላይ አንድ ነገር ልንገርህ፤ መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኘ የምነገርህ ትግራይ አትገነጠልም፡፡ ማንም ሃይል ሊገነጥላት ቢፈልግም ፈፅሞ የሚሆን አይደለም፡፡ ለምን ብትል፤ ትግራይ ለኢትዪጵያ ማለት ምን ማለት እንደሆነች ጋዜጠኛ ቴድሮስ ፀጋዪ ባለፈው የተናገረውን አንተም በአድናቆት ዘገባ የሰራህበትን ትንታኔ መልሰህ አድምጠው፡፡

ኢትዪጵያ ለትግራይ ህዝብ የእጅ ስራው ነች፤የደሙና የላቡ ቅርሱ ነች፡፡ ኢትዪጵያ ስትጀመር በትግራይ ነው የጀመረችው፡፡ በአጭር አገላለፅ ኢትዪጵያ መጀመርያ ትግራይ ነበረች፡፡ ትግራይ ስትሰፋ ያሁናን ኢትዪጵያ ታገኛለህ፡፡ የመጀመርያ ኢትዪጵያውያንም ተጋሩ ናቸው፡፡ በሰዎች እኩልነት አምናለው፡፡ኢትዪጵያዊነት ላይ ደረጃ ማውጣት ግድ የሚሆን ከሆነ ግን የትግራይ ህዝብ የመጀመርያ ደረጃ ኢትዪጵያዊ ነው፡፡ ስለዚህ ትግራይ ልትገነጠል ነው የሚለው አባባል ከንቱ፤መሰረተ-ቢስና ውሃ የማይቋጥር የፈጠራ ወሬ ነው፡

ትግራይ ኢትዪጵያ ነች፤ኢትዪጵያም ትግራይ ነች፡፡ ሁለቱም ያንድ ሳንቲም ሁለት ገፆች ናቸው፡፡ እነዚህን አንድ ሳንቲም ላይ ያሉ ሁለት ገጾች ሰንጥቆ ያ አንድ የነበረው ሳንቲም ሁለት ሆኖ ዋጋ ኖሮት መቀጠል ይችላል;  መልሱ አይችልም ነው፡፡ ኢትዪጵያም ያለ ትግራይ፤ ትግራይም ያለ ኢትዪጵያ እንዲያ ናቸው፡፡ አንዳቸው ያለ ሌላኛቸው ሂወት የላቸውም፡፡ አንተ ግን ይህንን እውነት መገንዘብ አቅቶህ የኢሳት ወሬ አመዝኖብህ ከነፈሰው ጋራ አብረህ መንፈስህን ተያያዝከው፡፡

አንድ ጭንቅላትህን ብሎም ህሊናህን የሚፈትን ጥያቄ ልጠይቅህ፡-

ትግራዋይ ኢትዪጵያዊ አልሆንም(አስበው ትግራዋይ ራሱ የፈጠረውን ኢትዪጵያዊ ማንነት አውልቆ ሲጥል ማለት ነው!) ካለ በኢትዪጵያ ውስጥ ኢትዪጵያዊ ሆኖ የሚቀጥለው ማን ነው!? አማራው ነው? ኦሮሞው ነው?ሶማሌው ነው?ዓፋሩ ነው?ጋምቤላው ነው?ቤኒሻንጉሉ ነው? አረ ከቶ ማን ነው? እንግዲህ ህሊናህን ተጠቅመህ ከመረመርከው፤ ትግራይ የለችም ማለት በኢትዪጵያ ውስጥ አንዲት ሌሊት የሚያድር ሶማሌ፤ዓፋር፤ጋንቤላ፤ቤኒም ሆነ ኦሮሞ እንደማይኖር ነው፡፡

ሁለተኛ ጥያቄ ልጨምርልህ፡-

ኤርትራ ስትገነጠል ኢትዪጵያ እንደ ሃገር ሳትፈርስ የቀጠለችበት ሚስጥር እውነት ምን እንደሆነ ታውቀዋለህን? መልሱ ልንገርህ፤ቢዋጥልህም ባይዋጥልህም የኢትዪጵያዊነት ማህፅንና መሰረት የሆነቸው አክሱምን አቅፋ የያዘቸው ትግራይ ከኤርትራ በተቃራኒ እኔ እራሴ እኮ ኢትዪጵያ ነኝ፤አፈጣጠሬ የትም እንድሄድ አይፈቅድልኝም በማለትዋና በማለትዋ ብቻ ነው፡፡

ለማንኛውም ውድ ወንድሜ የኢትዪጵያን ፖለቲካ ስታስብ የኢትዪጵያ ምንጭ የሆነችውን ትግራይን ፈፅመህ አትዘንጋ፤ትግራይ የኢትዪጵያ ሲም ካርድ ነች የሚባለውም ግነት ሳይሆን እውነት መሆኑን በሙሉ ልብህ አምነህ ተቀበል፡፡አልያ ግን ትልቅ ስህተት ላይ ትወድቃለህ፡፡

መልካሙን ሁሉ እመኝልሃለው፡፡
ታናሽ ውንድምህ ክብሮም!

********

Guest Author

more recommended stories