ግራ በመጋባት ውስጥ የሚፈጠር መናጋትና ማናጋት ከታሪክ ተጠያቂነት አያድንም!

(ኤቢሳ ከጨፌ ዶንሳ)

አብዛኛውን ጊዜ ሀገር ህዝብ ነው ሲባል ይሰማል፡፡ ሀገር ዳር ድንበር፤ ወንዝ፤ ጋራና ሸንተረር፤ ባህርና ሸለቆው ሁሉ ነው፡፡ ነገር ግን ሉዓላዊ የሚሆነው ህዝብ ራሱ ሲኖርበት፤ ህዝብ እንደ ህዝብ ህልውናውን ለማስጠበቅ የመሰረተው መንግስት ሲኖርበት ነው፡፡ ታዲያ ጥንተ ነገር የዓለም ህዝብ መንግስት ወይም የአብሮ መኖራችን ስራ አስፈፃሚ ያስፈልገናል ብሎ የወሰነው በህዝብ ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ግለሰብ ፍላጎት፤ እምነትና አቋም፤ ተስፋና ራዕይ ማሟላት ምኑን ያህል ከባድ እንደሆነ በተግባር ተፈትኖ ስላየው ይመስለኛል፡፡

ከባድ ከመሆኑም ባሻገር ሁሉንም ፍላጎቶችና ጥቅሞችን  ያጣጣመ ህይወት በአብሮነት ለመኖር የሚያስችል መላ እየፈጠረ፤ በመላዎቹ ዙሪያ ምልዓተ ህዝቡን እያሰለፈና እያሳተፈ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚጥር፤ ህዝባዊ አዎንታውን የሚያሳድግ ራዕይ ያለው አካል ከማስግኘት ባሻገር ያለው ነገር የማይገፋ መሆኑን ከመረዳትም የመነጨ ይመስለኛል፡፡ የማይገፋውን በጋራ ለመግፋት፤ በአብሮነት ከችግሮች ጋር ተፋልሞ ድል ለመቀዳጀት፤ የጋራ ተግባቦትንም ወደ ተግባር ለመተርጎም ሁነኛ አካል ስለሆነም ነው፡፡

ታዲያ በዚህ አተያይ ከነ ህፀጹ መንግስት የተሸከመው ኃላፊነት ምንኛ ታላቅና ከባድ እንደሆነ መረዳት ይገባል፡፡ ድሉ የብቻው ያልሆነውን ያህልም ውድቀቱም እንደዚሁ የብቻው አይደለም፡፡ ሁለቱም ፅንፎች የማህበረሰብ እድገቱ የደረሰበት መገለጫዎች ናቸው፡፡ የሮም ሰልጣኔ የአንድ ጀንበር እንዳልሆነ ሁሉ የቄሳሩም የብቻው አልነበረም፡፡ የጃፓን የሔሮሺማ ውድመት የአገዛዙ የብቻው ጉድለት እንዳልነበረ ሁሉ የጥፋት አድራሽ አካላቱም የብቻቸው እብሪት ነበር ማለት ይከብዳል፡፡

የአሜሪካ የ2001 የመንትዮቹ ህንፃዎች ጥቃት የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ብቻ፤ አሊያም የጥቃት አድራሹ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን የድርጊቶቹም ሆነ አስተሳሰቡ ተቋዳሾች ብዙ የጥፋቱ ገፈት ቀማሾችም ብዙዎች ነበሩ፡፡ ናቸውም፡፡ ባጠቃላይ ማለት የፈለኩት የቀለም አብዮቶች ጥፋት የነጆርጅ ሶሮው ባላባታዊና የዓለም አውራነት ሰይጣናዊ ተንኮል ብቻ ሳይሆን የተሰላፊው ወገን ግራ የተጋባ መናጋትና ማናጋት ህፀፅም እንደሆነ ይሰማኛል ለማለት ነው፡፡ ይህን ሀሳብ ሳነሳ የሆነ አካልን ነፃ ለማውጣት የማደርገው ዙሪያ ጥምጥም አድረጎ የሚመለከት ባይጠፋም እውነታው ጋር መጣላት እንደማይችል ግን አፌን ሞልቼ ልናገር፡፡

ባለንበት ክፍለ ዘመን ሀገሬ በሰመመን ውስጥ እንዳለች እመለከታለሁ፡፡ ሰመመን የእንቅልፍ ግማሽ አካል የመሆኑን ያህል የመንቃት ሌላኛው ክፍልም እንደሆነ መካድ ከተፈጥሮ ጋር መጣላት ይሆናል፡፡ ማንም ሊሞግተኝ እንደማይቻለው ባለፉት ሁለት አስርታት ይህቺ ሀገር መጠነ ሰፊ ለውጥ ውስጥ ገብታለች፡፡ የሚዳሰሰውን እንደተመልካቹ እንውሰድና በማይዳሰስ ሀብት ረገድ ሞጋች ህብረተሰብ መፍጠር መቻሏ በራሱ ሀሳቡን ያጠናክረዋል፡፡ ጊዜው የፈጠረው ነው የሚል አስተሳሰብ ለዚህ ሀሳብ ተቃርኖ ሊነሳ ቢችልም ጊዜ ብቻውን ጀግና አይሆንም ከሀገር፤ ከህዝብና ከመንግስት ጋር እንጂ ባይ ነኝ፡፡ ስለዚህ አሻራውን ለዘመን ብቻ ሰጥቶ ማለፍ የሚቻል አይሆንም፡፡ ይልቅስ የሁላችን ብለን ስንግባባ ትክል ይሆናል፡፡

በዚህ ሀሳብ መደድ ሀገሬ ሰመመን ውስጥ ናት ያልኩበትን ምክንያት ላስረዳ፡፡

ዜጎች ማንነታቸው የማይታወቅበት፤ እንደ ሀገር ባለቤትነት ቀርቶ እንደ አኗኗሪ የማይቆጠሩበት፤ ዜጎች ሲባል መሳፍንቱና ባላባቶቹ ብቻ የከበሩበትና የተቆጠሩበትን አስተሳሰብ ያሳለፈ ህዝብ፡፡ መብቶቹን በተፈጥሮ የተቸርኩ ነኝ ብሎ መጠየቅ የማይችልበት፡፡ ፈጣሪ በቸረው ቋንቋ መናገር አፍሮ ገዢዎቹ በመረጡለት የሚናገርበት፡፡ ስለሀብትና ኑሮው ራሱ መወሰን የማይችልበት ሀገርና ህዝብ ነበር፡፡ ሌላም ሌላም ማለት ይቻላል፡፡ ይህንን በራሱ ትግልና መስዋእትነት የተጎናፀፈ ህዝብ በአካልና አስተሳሰብ ያልደረሰበትን እጆቹ ሲዳስሳቸውና በመንፈሱ መቃመስ ሲጀምር ሰመመን ቢሆንበት ምን ይገርማል፡፡

ደግሞስ በሰመመን ውስጥም ሆኖ ያገኛቸውን ድሎች አጣጥሞ ሳይጨርስ ዳግም ብልጣ ብልጦች ቀድመውት ሲገኙ፤ እሱ በተመኘበት ሳይሆን አሳይቶ የመንሳት ያህል ራሳቸው እድሎቹን ለመቀራመትና በትግሉ ያገኛቸውን ድሎች ሊቀለብሱበት ሲተሙ በተመለከተበት አተያይ ተወራጭቶ ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት ዳግመኛ ሰመመን ብለው ስህተት አይሆንም ስል አሰብኩ፡፡ ግራ በመጋባት ውስጥ ባለ መናጋትና ማናጋት ሁሌም ተጠቃሚዎቹ ብልጣ ብልጦቹ እንጂ የዋሁ ህዝብ አይደለም፡፡

ከግራ መጋባት ተወጥቶ ድሎችን በማጣጣም ወደበለጠ ድል ለማበልፀግ ስክነት ይሻል፡፡ ለማጣጣም በሚወሰድ ጎዜ ውስጥ ያሉ ተኩላዎችንም በትኩረት አደብ እያስገዙ ነገር ግን ራስንና የራስን ሀብት እየጠበቁ፤ የደጅን የላቦት እንጥፍጣፊ ለአፍታም ባለማቋረጥ ጠርቀምቀም በማድረግ፤ ብልህነትን የተቸሩ ብላቴናዎችን በመደገፍና በመጠበቅ፤ መጓዝ ካልተቻለ ጥፋቱ እንደ ሮማ ውድቀት፤ እንደ ጃፓን ጥፋት፤ እንደ ሶሪያ መጋየት ይሆናል፡፡ ደግሞም ከነዚህ መሰል ውድመቶች ውስጥ ሁሉም እጅ እንደሚኖረው ልብ ይሏል፡፡ የእከሌ ተብሎ የሚላከክ ቁልቁለት ጊዜን ያሳልፍልን እንደሁ እንጂ አለባብሰው ቢያርሱ ነው እሚሆን፡፡

ታዲያ ዓለም ባሳለፈቻቸው የትግል ዘዴዎችና የበትረ ስልጣን መጨበጫ መላዎች ሁሉ እንዳሁኑ ግራ የተጋባችበት ዘመን ያለ አይመስለኝም፡፡ አሊያም የኔ ትንሽ እውቀት ከዚህ ተሻግሬ እንድመለከት ልትፈቅድልኝ አልተቻልትም ይሆናል፡፤ በተለይም የሀገሬ ህዝቦች አሁን አሁን ከደረሱበትና ሊደርሱበት ከሚመኙት አስተሳሰብ፤ የአብሮነት ልዕልናና የተጠቃሚነት ማማ ሲታሰብ ግራ መጋባቱ ያይላል፡፡

እኔ የተገኘሁበት ታላቁ የኦሮሞ ህዝብ ደግሞ በይበልጥ ለዚህኛውም ጉዳይ ተጋላጭ ነው፡፡ ራሱን የሚመለከትበትን መነፅር ተቀምቶ፤ ታላቅነቱን በበታችነት፤ ኩሩ ማንነቱን በሚያፍርበት አኳኋን እንዲኖር የተገደደ ህዝብ ከመሆኑ አንፃር ዘሬ የተገኙና በእጁ ያሉ ድሎችን ሳያንጠባጥብ ለተሻለ ነገ በመተማመንና በተግባቦት እንዳይተም ከራሱም ከወዲያኛውም ወገን ጦር ሲሰበቅበት ዳግመኛ ሰመመን ውስጥ እንዲገባ ከመሆኑም በላይ ከሰመመኑ ለመንቃት በሚያደርገው መወራጨት ራሱን እንዲያቆስል ሆን ተብሎ እየተሰራበት ይገኛል፡፡

ለዚህ ድርጊት የሆነን አካል ተጠያቂ ብሎ ለጊዜው መግባባት ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ገራ በመጋባት ውስጥ በሚፈጠር መናጋትና ማናጋት ከታሪክ ተጠያቂነት መዳን አይቻልምና ሰከን ማለት፤ ቆም ብሎ ማሰብና በተለይም እንደ ህዝብ አንድ ሆኖ በመተማመን መራመድ የሚበጅ ይመስለኛል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ትግል እንደነ እከሌ ተብሎ የሚሰላ አይደለም፡፡ በባህርዩም በታሪኩም ልዩ ነው፡፡ ድሎቹም እንዲሁ፡፡ የብቻው የሆነ ብቸነትም የለውም፡፡

የጋራነቱን በማፍቀርም አሳልፎ የሚሰጠው ማንነት የለውም፡፡ አውቀንለታል የሚሉትን ሁሉ ቆሞ ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ መንግስትንም ቢሆን ህዝቡ በራስ ይሁንታ አብሮት መዝለቁን በማሰብ የሚበጀውን በማስቀጠል፤ የሳተውን በመመለስ፤ የጎደለውን በመጠየቅ፤ እንዲያስተካክል በማስገደድ ሉዓላዊ ስልጣን ጭምር  ነግ ዓለም ከሚደርስበት ላለመነጠል መትጋት እንጂ ግራ በመጋባት መናጋትም ሆነ ማናጋት ሁላችንን አይጠቅምም፡፡ ቸር እንሁን፡፡

*********

Guest Author

more recommended stories