ከ4000 የሚበልጡ አመራሮችን አራግፈናል ~ ለማ መገርሳ

[ክፍልሶስት] – የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ለማ መገርሳ በዚህ ሳምንት በአዳማ ከተማ በተካሄደው መድረክ ላይ የተናገሩት ንግግር፡፡

(ከአፋን ኦሮሞ ወደ አማርኛ በHornAffairs የተተረጎመ)

ባለፈው ዓመት ከመሰከረም ወር በኋላ በክልላችን የተከሰተው አስከፊ የሞት አደጋን ተከትሎ የብዙ ሰዎችን ህይወት ከሞት አፋፍ ማትረፍ ችለናል፡፡

እኔ personally ይሀን ስራ ሳልጀምር፤ ብዙ ወጣቶቻችን ኢሬቻ ከደረሰው አስከፊ አደጋ ወጥተው፤ በነበረው ሞቅታ መንግስት የወደቀ መስሏቸው፤ እዚም እዛም ያገኙትን ጦር መሣርያ ከ5 እና ከ10 ጥይት ጋራ ታቅፈው ቡሌ ሆራ ጫካ ገብተው ነበር፡፡ አራት አምስት ስድስት ቀናት ጫካ እንደቆዩ የሚበሉት አጥተው ተቸግረው ርቧቸው፤ የኔን ስልክ ከዬት እንዳገኙት አላውቅም ሌሊት 7 እና 8 ሰዓት ደውለውልኝ፣ ጫካ እያለቅን ነው ድረሱልን፣ ነፍሳችንን አድኑን፣ ወደ ቀዬያችን መልሱን እያሉ ደጋግመው ይደውሉ ነበር፡፡

ከከረዩ ብቻ 300 ወጣቶችን በዚህ መልኩ ወደ ቄኤያቸው መመለስ ተችሏል፡፡ እዚህ ምስራቅ ሸዋ አደአ ውስጥም፡ ደቡብ ምዕራብ ሸዋም፡ ምእራብ አርሲም ከሌሎች አከባቢዎችም ስለውትድርና አንዳችም ግንዛቤ ሳይኖራቸው ከህዝብ ወጥተው ለመሞት ጫካ የገቡ ነበሩ፡፡ በዚ በኩል ደግሞ ሰራዊታችን “ሽፍታ ጫካ ገባ” ብሎ ዝግጅት እያደረገ ነበረ:: በዚያ ወቅት ደርሰን intervene በማድረግ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶቻችንን ህይወት በማትረፍ ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ አድርገናል፡፡

እኔም በግሌ ጭምር ከአከባቢው ሀገር ሽማግሌዎች ጋራ በመሆን እዛው ጫካ ውስጥ ዘልቀን፡ ወጣቶቹን አንዳቸውም ሳይቆስሉ እና ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ወደየ ቀዬያቸው እንዲመለሱ አድርገናል፡፡

በወቅቱ ከቡሌ ሆራ አደጋ ማግስት ዝም ብለን ይሀን ባናደርግ እና የታጠቀው ሰራዊታችን እነዚህ ወጣቶች ሽፍታ ናቸው ብሎ ተጨማረ ደም ቢፈስ ኖሮ፤ ጉዳዩ ሀገር እንደ ሀገር መቀጠል ያለመቀጠል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በክልላችን መቼም ሊቀለበስ የማይችል አደገኛ ታሪክ በተከሰተ ነበር፡፡

ይሀን ሁሉ ስናደርግ የግላችን ጉዳይ ሆኖ ሳይሆን ሀገርንም ጭምር ከአደጋ ማዳን ችለናል፡፡ ውድ የሆነውን የሰው ህይወት ከሞት አደጋ ማትረፍ ችለናል፡፡

ሌላ ሊሰመርበት የሚገባ ነገር ቢኖር፤ በትግል ሂደት ውስጥ ትግል አንድ ፎርሙላ የለም፡፡ በተለይ በፖለቲካ ደረጃ በሚካሄደው የትግል ሂደት ውስጥ ትግል አንድ እና አንድ ፎርሙላ ብቻ የለውም፡፡ ብዙ ፎርሙላዎች አሉት፡፡ 1 ሺህ 1 ፎርሙላ አለው፡፡

እንደ አንድ የፖለቲካ አመራር ህዝብና ሀገርን የምንመራ ከሆነ፡ ሂደቱ በራሱ ከሚያመጣው የህዝብ እና የሀገር ለውጥ ጋራ የትግል አካሄዳችንን እያዛመድን ካልተራመድን በስተቀር በቆምነው ቦታ እንቀራለን፡፡ እኛው እራሳችን በድርጅታችን ታግለን ካመጣነው ሀገራዊ ለውጥ ጋራ እንዴት መዛመድ ያቅተናል? ከለውጥ ጋራ መራመድ መቻል ቀጣይነት ላለው ስኬት መሰረት ነው፡፡ በዚህ አኳሀን ተጉዘን በተግባር ተስፋ-ሰጪ የጅምር ውጤት አምጥተናል፡፡

ህዝቡ አሁን የተወሰነ እምነት በኛ ላይ ጥሏል፡፡ ይሀም በጥልቅ ተሀድሶ ወደ ህዝቡ እንመለስ ብለን ባስቀመጥነው መሠረት ከህዝቡ ሳይሆን ወደ ህዝቡ መሸሽ ስለጀመርን ነው፡፡

ወዲህ ወዲያ አላየንም፡፡ ወደ ህዝቡ ነው ያየነው፡፡ ለህዝቡ ነው መስራት የጀመርነው፡፡ ወደ ህዝቡ ሸሽተን እሱን ማዳመጥ ሰለጀመርን ነው፡ ጊዜያዊ አመኔታ ቢሆንም ህዝቡ እኛን ማመንና ጠንክሩ በርቱ ማለት የጀመረው፡፡

ይሀ የሁላችን፣ የመንግስታችን፣ የድርጅታችን እና የአመራሮቻችን ድምር ውጤት መሆኑን በደንብ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ይሀን ማንም በተንደላቀቀ ጥላ ስር ውሎ-ማደር የለመደ ሰው discredit ሊያደረገው የሚችለው አይደለም፡፡ This is a fact.

በዚህ ፈታኝ የትግል ሂደት ውስጥ በተግባር ተፈትነን መለወጥ እንደሚንችል proof አድርገናል፡፡ ማንም ይሀን ለማሳነስ moral ground የለውም፡፡ በተጨባጭ መሬት ላይ የሚታይ ሀቅ ነው፡፡

ይሀን የምላችሁ የተለየ ስራ ሰርተናል ብለን እንድንኩራራበት አይደለም፡፡ ከዚህ ወጥተን እንድንፎክርበትም አይደለም፡፡ ምን ውስጥ እንደነበርን፡ ዛሬ ዬት ነው ያለነው ብለን እውነት ላይ ተመስርተን፡ ለበለጠ ስኬት ሰንቀን በቀጣይ የተሻለ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንድንችል ዘንድ ነው ይሀን የምላችሁ፡፡

በጥልቅ ተሀድሶ ሂደት ውስጥም ባለፉት 10 ወራት ድርጅታዊም ሆነ መንግስታዊ መዋቅሩን ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ transparent በሆነ እና በየደረጃው ህዝብን ባሳተፈ መንገድ መላ መዋቅራችንን ከሞላ ጎደል መልሰን አደራጅተናል፡፡ በዚህም ግልፅ በሆነ መንገድ የተለያዩ ጉድለቶች ይታይባቸው የነበሩ ከ4000 የሚበልጡ አመራሮችን ከአመራር ሰንሰለት አራግፈናል፡፡ ይህን ስራ ብቻችን የሰራነው አይደለም፡፡ በህዝቡ ውሳኔ ሰጪነት ከህዝቡ ጋራ በመሆን የመጣ ለውጥ ነው፡፡

እንደ አመራር እኛ የተለየ የሰራነው ነገር ቢኖር፡ በህልም ያየነውን ምኞት እና ቅዠት ዓላማ አድርገን ሳይሆን ከህዝባችን ጋራ ያቃረንን ነገር ጊዜ ወስደን ስስ-ብልቱን አንድ ሁለት ብለን ለይተን እሱ ላይ ደከመን ሰለቸን ሳንል ተግተን መስራታችን ነው፡፡

ባለፉት 10 ዓመታት በክልላችን ይደረግ የነበረው ኢንቨስትመንት እንደ ዘርፍ ከፍተኛ ችግር የነበረበት ዘርፍ ነበር፡፡ በስመ-ኢንቨስትመንት አርሶ-አደራችን እና ማህበረሰባችን ላይ ይደርስ የነበረውን በደል ሁላችንም እናውቋለን፡፡ ሙሉ በሙሉ ይሀን ማስተካከል ትልቁ ስራችን ነበር፡፡

ከባድ ትግልም የጠየቀ ነበር፡፡ ብዙ ጠላትም ያፈራንበት ዘርፍ ነው፡፡ ማዕድን ዘርፍ ላይ ስንሰራ የነበረው የስራ-አጥ ወጣቶችን ችግር ለመቅረፍ ያደረግነው እንቅስቃሴ ብዙ ሰዎችን እንደጠቀመ እና እንዳስደሰተ ሁሉ ብዙ ጠላቶችንም ያፈራንበት ነው፡፡

ጠዋትና ማታ በሴራ እና በተንኮል እየጦዘ ገንዘቡን በማፍሰስ ጭምር ሰው እያሰማራብን ባገኘው ትንሽዬ ቀዳዳ ሁሉ እኛ ላይ እየዘመተና እያዘመተ፣ ክልላችንን እና ስራችንን ጥላሸት ማድረጉ ላይ የሚሰራ ብዙ ነበር፡፡ ግን አልሰማናቸውም፡፡ እንኳን ለአንድ ቀን ለአንድ ሰከንድም ቢሆን ጆሮ አልሰጠናቸውም፡፡ አልሰማናቸውም፡፡

ስራችን ላይ አትኩረን እየሰራን ነበር፡፡ የሚያዋጣንም ስራችን ብቻ ስለሆነ፡፡ ሳንሰራ ስንቀር ሊያባረን ለሚችለው ህዝቡን ነው የሰማነው፡፡ የሰራነው እና እየሰራን ያለነው ስራ የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል፡፡ ህዝቡ ላይ የሚደርሰውን በደል የሚያስቆም ስራ ነው ብለን እናምናለን፡፡

********* 

[ክፍል አራት ይቀጥላል]

* የፕ/ት ለማ መገርሳ ንግግር ክፍል አንድ – “አምና በዚች ወቅት ምን ውስጥ ነበርን? ዛሬስ የት ነን?”
* የፕ/ት ለማ መገርሳ ንግግር ክፍል ሁለት – ከኛ ጎን ለመሰለፍ ማንም ከማንም የማንነት ሰርተፍኬት እውቅና ሰጪ አያስፈልገውም

Daniel Berhane

more recommended stories