ቸል የተባለው የሰማዕታት ቀን

በትግራይ ክልል በየአመቱ ሰኔ 15 ቀን ሰማዕታት የሚዘከሩበት/የሚከበረበት እለት ነው። ስለ ሰማዕታት ስናስብ በ17ቱ የትጥቅ ትግል ዓመታት የፋሽሽቱ የደርግን ስርአት ለመገርሰስ መስዋዕት የሆኑ ከ65 ሺ በላይ ታጋዮችና ምልሾች፣ የትግሉ አጋር ከሆነው ህዝብ በክላስተር ቦምብ፣ በታንኮች፣ በመድፎች እና በጥይት በግፍ የተገደሉ ወገኖች እና በጦርነቱ ምክንያት ቤትን ንብረታቸውና መንደራቸው ወድሞ ለመፈናቀል ተገደው በየበረሃው ሲንከራተቱ ሂወታቸው ያለፉ፣ በአስገዳጅ ሰፈራ በየጫካው ተወስደው በወባና አውሬ ሕይወታቸውን ያለፉ፣ በደርግና በ’77ቱ ድርቅ ምክንያት አደጋ ላይ ወድቀው ወደ ሱንዳን ሲጓዙ ሻዕቢያ በፈጸመው ክህደት የተገደሉትን በሺ የሚቆጠሩ ወግኖች፣ በመጨረሻም አሳውን ለማጥፋት ውሃውን ማድረቅ በሚል የደርግ ፋሽሽታዊ ፖሊሲ በተጠቀሰው ቀን ከ2 ሺ አምስት መቶ ንፁሃን በላይ በሃውዜን ገበያ የተጨፈጨፉት ሁሉ ሰማዕታት ናቸው ብለን ብናስብ ተገቢ ነው።

ሰኔ 15 የሰማዕታት ቀን እንዲሆን የተመረጠው የሃውዜኑ ጭፍጨፋ ታሳቢ ተደርጎ ቢሆንም ከላይ የተጠቀሱት ለትግሉ የወደቁ  ስማእታት ሁሉ የሚታሰቡበት እለት ነው። የሚያሳዝነው ነገር እነዚህ ለመላው ሃገርና ህዝብ ሲሉ የወደቁ ሰማዕታት ሰማእትነታቸው በአንድ ክልል ብቻ የታጠረ መሆኑን ነው።

አቶ ጌታቸው በለጠ፣ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ሃላፊ ‹‹ትግራይ ላይ የተሰሩ የትግል ታሪኮች የትግራይ ብቻ አይደሉም፣ የመላው ኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ እንጂ›› ያሉት ነገር ማስታወስ ተገቢ ነው። መቐለ ያለውን የሰማዕታት ሃወልትና ሙዚየም ያዩና በስንፍናችን የተበሳጩ  ጋናዊ ፕሮፌሰርም በበኩላቸው ‹‹ይኼ ታሪክ ‹የትግራይ ሕዝብ ታሪክ ነው› አላችሁት? እንኳን የትግራይ ሕዝብ ታሪክ ማለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ማለትም ያንሰዋል፡፡ ይህ የመላ አፍሪካ ታሪክ ነው፡፡ መቀመጥም ያለበት እዚሁ ተወሽቆ ሳይሆን የአፍሪካ ኅብረት በሚገኝበት ሥፍራ ከኔልሰን ማንዴላ ጎን ነው፡፡ ይኼ ታሪክ ከእሱም በላይ ነው›› በማለት በጣም በማዘን ስሜታቸውን ገልፀዋል (በአቶ ጌታቸው በለጠ የተነገረ)።

Photo - TPLF poster
Photo – TPLF poster

እውነት እጅግ የሚያሳዝን ጉዳይ ነው። በላፉት ዘመናት ብዛት ያላቸው ኢትዮጵዊያን ለሃገራቸውና ህዝባቸው ሲሉ ብዙ መስዋዕት ከፍሏል። በየክልሉ ብንሄድ የብዙ ሰዎችን ስም መጥራት ይቻላል። ሆኖም እነዚህ የሰማዕታት በታሪካችን ተገቢ አገራዊ ክብር በመስጠት እና መልካም ስራቸውን ለቀጣይ ትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ትልቅ ክፍተት ይታያል። የእውቀት ማነስ እንዳንለው ለዚች አገር ያነሰ ትርጉም ያላቸው የውጭ ዜጎች ሳይቀሩ ብስማቸው ጎዳና፣ አደባባይ እና ትምህርትቤቶች ብርእሰ ከተማችን ተሰይመውላቸው እናያለን።

ዊንጌት ትምህርትቤት፣ ንግስት ኤልሳቤት፣ ቸርቺል፣ ሩሲያ፣ ማይክሊላንድ ጎዳናዎች፣ ቦብማርሊ እና ሜክሲኮ አደባባዮች ወዘተ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ሲሆኑ፤ ለዚህች አገር ሲሉ አንገታቸው የሰጡ እንደ  ራስ አሉላ አባ ነጋ፣ አብዲስ አጋ፣ አብራሃም ዶቦጭ፣ ዘርአይ አስገዶም እና በሁለቱም የጣሊያን ጦርነት የተሰዉ ኤርትራን ጨምሮ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ብዙ ስመጥር ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ስማቸው ተቀብሮ ለፈረንጆቹ የተሰጠውን ክብር ተንፍጎአቸዋል። አንዳንድ መኳንንቶች ሁለት ሶስት ጎዳናዎች እና ትምህርትቤቶች የተሰየመላቸው ሲሆን እንደ እነ አፄ ዮሃንስ የመሰሉ ለአገራቸው እና ህዝባቸው አንገታቸው የሰጡ ስመ ጥር መሪዎች ደግሞ በመቶ ሜትሮች የምትለካ ጎዳና ተሰይሞላቸ ስታይ እንዴት የሚያሳዝን ነው። በአጠቃላይ ሌላው ህዝብ የታሪካችን ተካፋይ ያልሆነ እስኪመስል ድረስ በአዲስ አበባ የተሰየሙ ጎዳናዎችን በዘመድ ለአንድ ወገን የተሰጡ ሆነው እናገኛቸዋለን።

ለህዝቦች ነፃነትና እኩልነት ሲሉ መቶ አመት የቆየውን ግፈኛው የነፍጠኞች ስርአት እና የነሱ ቅጥያ የሆነው ሰው በላውን የደርግ መንግስት ለመፋለም ባልተደራጀ እና በተለያዩ አደረጃጀቶች ተሰልፈው ውድ ሂወታቸውን የከፈሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን እያሉ ተገቢ የሆነ ብሄራዊ ክብር አልተሰጣቸውም። ለምሳሌ የቐዳማይ ወያነ፣ የባሌና የጎጃም ገበሬዎች አመፅ፣  የሲዳማ፣ የዓፋር ወዘተ ለፍትህና ነፃነት ሲሉ መስዋዕት የከፈሉ አያሌ ናቸው። በቅርብ በዚህ ትውልድ ስናይም የኢህአደግ አባል ድርጅቶች ታጋዮቹ ከተለያዩ አራት ክልሎች የመጡ ቢሆኑም የከፈሉት መስዋአት በክልል የተወሰነ አልነበረም፡፡

እንደሚታወቀው ከክልላቸው ውጭ የተሰዉ ብሺዎች የሚቆጠሩ የነፃነት ታጋዮች አሉ። ከትግራይ እስከ ደቡብ፣ ከጋምቤላ እስከ ጎዴ፣ ከቤንሻንጉል እስከ ባሌ፣ ከአማራ ክልል እስከ አፋር፣ ከወለጋ እስከ አሩሲ፣ ከከፋ እስከ ሰሜን ሸዋ፣ መስዋዕት ተከፍሏል። ለምሳሌ፡- ሶማሌ ክልል፣ ከፋ፣ ጋምቤላ፣ አምቦ፣ ወለጋ፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ሸዋና ጎጃም የተሰዉ የህወሓት ታጋዮች ለትግራይ ብቻ ሊሆን አይችልም።

እነ አሞራ፣ ቀሺ ገብሩ፣ ገሬ ስፓናቶ፣ ማንጁርና በሺ የሚቆጠሩ ጀግኖች የተሰዉ በትግራይና ለትግራይ ብቻ አይደለም፣ ለመላው ኢትዮጵያ እንጂ። የሌሎች ድርጅቶች ሰማዕታትም እንደዚሁ። በኢትዮጵያ እና በኤርትራ በቅርብ በተደረገው ጦርነትም ትግራይ ክልልን ጨምሮ ከተለየዩ ክልሎች የመጡ ብዙ ኢትዮጵያዊያን በትግራይ እና በአፋር ክልሎች መስዋዕት ሆኗል። በነዚህ ሁለት ክልሎች የሚኖሩ ገበሬዎችም (ወንዱም ሴቱም) ለሰራዊት ምግብ/ወሃ ከማቀብል አልፎ የሞቱ እና የቆሰሉ የሰራዊት አባላት በማንሳት ላይ ተሰማርተው ብዙ መስዋዕት ከፍለዋል።

ሆኖም ጎዳና እና አደባባይ መሰየም ቀርቶ አሁንም እነዚህ ሰማዕታት በአገር ደረጃ የተሰየመላቸው የሰማዕታት ቀን ባለመኖሩ የሰማዕታት ቀን በክልል ብቻ ታጥሮ ታስቦ ሲውል እናያለን። የሚገርመው ግን የተለያዩ በታሪካችን ብዙም ፋይዳ የሌላቸው፣ ለምሳሌ የሲጋራ ቀን፣ የእጅ መታጠብ ቀን ወዘተ እየተባለ ብቴሌቪዥን ሳይቀር ሰፊ አገራዊ ሽፋን ተሰጧቸው ታስበው ሲውሉ እናያለን (ጠቃሚ ቢሆኑም)። አርአያ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች በአገሪቱ የሌሉን ይመስል ባህርን ተሻግሮ ፈረንጅን ፍለጋ ስንዋትት እንታያለን።

አንዳንድ ኢትዮጵያዊያንን የተዛቡ እውቅ አፍሪካዊ ሙሁራን “ያለመገዛቱ የሚቆጭው ህዝብ” ብለው የፃፉብን እውነት እስኪመስል ድረስ በፈረንጅ መንገድና ጎዳና ከመሰየም አልፈን ፈረንጆቹ የሚያከብሩትን ካሁን ቀደም የማናውቀውን ቅዱስ እንትና የተባለ የፈረንጅ ቄስ አመታዊ በዓሉን ማክበር መጀመራችን ሲሰማ ደግሞ እውነትም ሳይገዛ የተገዛ አእምሮ ያለን ይመስላል። በራሳቸው ስልጣን የፈረንጆቹን በአል በመጨመር ‘’ሁለት ልደት እና አዲስ አመት የምታከብር ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ ነች’’ ብለው በEBC የሚናገሩ ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች ስናይም እኛስ መቼስ አንዴ ተዛብቶብናል የአገሪቱ 85 በመቶ የሆነው ገበሬ ቢሰማ ምን ይል ይሆን? ብለን ያለፍነበት ጊዜም ነበር። እረ ስንቱን ቆጥረን እንጨርሰዋለን!

ወገን፣ ይህ ትክክል አይደለም። የጋራ እሴት የምንለውን አጥፍቶ አንድነታችንም ያዳክማል። ስለሆነም የአገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንን ጉዳይ ተመልክቶ ባለፉት ብዙ ዘመናት ለሃገራቸው እና ለህባቸው ነፃነት ሲሉ በተለያዩ አደረጃጀት ተሰልፈው መስዋዕት የከፈሉ ሰማዕታት ተገቢ አገራዊ እውቅና ሰጥቶ በአገር ደረጃ የሚከበር አንድ ቀን ሊወስንላቸው ይገባል። እንዲያውም ከተቻለ የአገሪቱ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ እነዚህ ሰማዕታትን የሚወክል ሙዚየም፣ ሃወልት እና ስም ዝርዝርም ሊኖራት ይገባል።

ሰናይ ቀን!

************

ገብረ ሥላሴ ኣርኣያ ኣብ ሃገራዊን ዞባዊን ከምኡውን ዓለም ለኻዊ ፖለቲካ ጉዳያት ዝከታተል፣ ኣብዝኾነ ፖለቲካዊ ውዳበ ዘይነጥፍ ውልቀ ሰብ እዩ። ንሃናፃይ ሪኢቶ ኣብ [email protected]

more recommended stories