የርዕዮተ ዐለም መፋለስ እና የምደባ ችግር በኢህአዴግ

(ሀብቶም ገብረእግዚያብሄር)

ኢህአዴግ እንደ ድርጅት መጠንከር እንዳለበት የፀና እምነቴ ነው፡፡ ይህንንም በሀሳብ ብቻ ሳይሆን አነሰም በዛ የበኩሌን አስተዋፅኦ በማድረግ መገለፅ እንዳለበት አስባለሁ፡፡ ይህም ለግንባሩ ካለ ቀና አስተሳሰብ የሚመነጭ ብቻ ሳይሆን በህገ መንግስቱ የተረጋገጠ ዲሞክሪሲያዊ መብቴም ስለሆነም ጭምር ነው፡፡

በኔ እምነት ኢህአዴግ አቻ የሌለው ርዕዮተ አለም ያለውና በዚህም ርዕዮተ አለማዊ ቅኝቱም ሀገራችንን ከነበረችበት አዘቅት አውጥቶ ወደአለም አቀፉ መድረክ እየመለሳት ነው፡፡ ከዚህም በበለጠ ወደከፍታ ማማ እንደሚያወጣን እረግጠኛ ነኝ፡፡

ኢህአዴግ እንደግንባር አንድ ፓርቲ ነው፡፡ አባላቱም የኢህአዴግ ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ በየብሔራዊ ድርጅቶቻቸው አማካኝነት ኢህአዴግን መስርተዋልና! በኔ እምነት የህወሓት መድከም ለብአዴን ሊያሳስብው ይገባል፤ የብአዴን መድከም ለኦህዴድ ሊያሳስበው ይገባል፡፡ የኦህዴድ መቀዛቀዝ ለደኢሕዴን ለያሳስበው ይገባል፡፡ ለምን ቢባል በአንድ ርዕዮተ አለም ጥላ ስር ድህነትን ለማጥፋት ታግለው ለማታገል የተሰለፉ ኢህአዴጎች ስለሆኑ ነው፡፡ የአንዱ ድካም ለአንዱ ጥንካሬ ሊሆን አይችልም፡፡ ያው የሱም ድካም እንጂ! በመሀከላቸውም ፉክክር የለም፤ ሊኖርም አይገባም፡፡

አንዳንድ ግልብ ካድሬዎችና ደጋፊ ነን ባዮች የሚስቱትን ትልቅ እውነታ እዚህ ጋር ላንሳ፡፡ ህወሓትን ደግፈህ ሌሎች አጋሮቹን የምታንቋሽሽ ከሆነ ለህወሓት ጠላቱ ነህ፤ ብአዴንን እያሞካሸህ እህት ድርጅቶቹን የምታጥላላ ከሆነ ለብአዴን ጠላቱ ነህ፡፡ ኦህዴድን እያሞገስክ ሌሎቹ አጋሮቹን የምታንኳስስ ከሆነ ደመኛ ጠላቱ ነህ፡፡ የደኢሕዴን ስራ እና ተግባራት እያደነቅክ አጋሮቹን ብታጥላላ ለደኢሕዴንን ለራሱ ጠላቱ ነህ፡፡ ለምን ቢባል አንድ አድርጎ ያስተሳሰራቸው አብዮታዊ ዴሞክራሲ እሳቤ በመሆኑ ነው፡፡ ኦህዴድም፣ ደኢህዴንም፣ ብዐዴንም ሆነ ህውሓት የየብቻቸው ርዕዮተ አለም የላቸውም፡፡ አራቱም አንድ አለማዊ አተያይ ነው ያላቸው፡፡

ስለዚህ ይህንን እውነታ ግልብ ካድሬዎች እና የየራሳችሁን ምናባዊ ምሽግ ሰርታችሁ እና በአንድ ርዕዮተ አለም ስር ባሉ እህትማማች ድርጅቶች ላይ በመከፋፈል እሴት የማይጨምርና ውሃ የማይቋጥር ንትርካችሁ ትርጉም አልባ መሆኑን ልትረዱት ይገባል፡፡

ይህንን ካልን ዘንዳ አንድ ጉዳይ እዚህ ጋር እናክል፡፡ አንድ ደኢህዴን ኢህአዴግ ውስጥ ያለ ግለሠብ ኦህዴድ ኢህአዴግ ውስጥ ያለን ግለሠብ ቢተች መተቸት ያለበት በመሠረታዊው ርዕዮተ አለማዊ መነፅር መሆን አለበት፡፡ በመሆኑም ርዕዮተ አለማዊ መፋለስ በከፍተኛ አመራር እንኳ በሚታይበት በዚህ ጊዜ በግለሠቦች ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶችን መላውን ፓርቲ ለማጥቃት እንደተሰነዘረ መውስድ አይግባም፡፡ ለምሳሌ አንድ ኦህዴድ ውስጥ ያለ ከፍተኛ አመራር አንድ ስህተት ቢፈጥር በሱ ላይ ከርዕዮተ አለም አንፃር የሚደረግ ትችት በመላው ኦህዴድ ላይ እንድተደረገ ጥቃት መቁጠር ተገቢ አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህን የሚያደርጉ የሉም ማለት አይቻልም፡፡ በዚህ ግሎባላይዜሽን ዘመን ሁሉም ለማስፈፀም የሚተጋለት የየራሱ አጀንዳ አለውና!

የሆነ ሆኖ ማንም ሰው በተለይ የሚሰራ ሰው መተቸት የለበትም ብሎ ማሰብ በራሱ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ነው፡፡ ትችቶች ለግንባሩ የወደፊት ጉዞ እና ጥንካሬ አስተዋፅኦ ማድረጋቸው ሊፈተሽ ይገባል እንጂ በፍፁም አትተቹ አይባልም፡፡ እዚህ ጋር ሳላነሳው የማላልፈው ነገር ቢኖር ኢህአዴግን ከኛ በላይ ደጋፊ የለም ብላችሁ የምትመፃደቁ ግለሠቦች የመፈረጅ አባዜያችሁን ማቆም አለባችሁ፡፡ አንድ ለማጠንከርና ለማረም በቅንነት የሚሰነዘርን ትችት የተቺውና የተተቺውን ብሄራዊ መሰረት በማጥናት ግንባሩን በመሰረቱት ድርጅቶች መሀከል ቅራኔ ለመፍጠር የተደረገ ነው ብሎ መፈረጁ እጅግ ዝቅጠት እና ኢ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ በርግጥ የተለየ አጀንዳ ኖሮት ይህንን አይነት ተግባር የሚፈፅም አይኖርም የሚል እምነት የለኝም፡፡ እንደዚህ አይነቶቹን ግን በፅሁፎቻቸው እና በሐሳቦቻቸው መለየት ያስፈልጋል እንጂ በጅምላ መፈረጅ የሰነፍ ተግባር ነው፡፡

ስንተችም ሆነ ሀሳቦችን ስንገመግም በርዕዮተ አለማዊ ቅኝት የምናያቸው ከሆነ ጠቃሚ ምልከታ እና ጠቃሚ ውጤት እናገኝበታለን፡፡ እንጂ ፈፅሞ ሰው እይተች አይባልም፡፡ ይህንን ይሉኝ ይሆን ብሎም ሰው የተሰማውን ከመናገር ሊቆጠብ አይገባም፡፡ በኢትዮጲያዊነት ጥላ ስር ለወገናችን ብልፅግና የምንተጋ ነንና መሸማቀቅ አማራጭ አይደለም፡፡

ባንድ ወቅት ታጋይ መለስ ዜናዊ ስለመተቸት ነፃነት ያነሳውን እዚህ ጋር ማስቀመጡ ነገሩን ያሳጥረዋል፡፡

‹‹ ማንም ሠው መለስ መላጣ ነው ማለት ይችላል፡፡ መላጣዬን ግን መንካት አይችልም፡፡ ››

ስለዚህ እኛም የማይጠየቅ እና የማይተች አመራር አይደለም የምንፈልገው እና የሚጠቅመን፣ ሲሳሳቱ የሚተቹ እና የሚታረሙ እንጂ!!

ወደዋናው ሐሳብ ስንመጣ የሚከተለውን ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡

ታዲያ ኢህአዴግ ይህን የመሰለ ምርጥ ርዕዮተ አለም አለው ካለን መሠረታዊ ድክመቱ ምኑ ላይ ነው?

ግንባሩ ብዙ ድክመቶች አሉበት፡፡ እኔ ግን በዋነኝነት የወሰድኩት ትልልቆቹን ባለስልጣናት ጨምሮ በመላው አባላቱ ላይ ግልፅ በሆነ መልኩ ርዕዮተ አለሙን ያለማስረፁ ነው ባይ ነኝ፡፡ በጥናት ላይ የተመሰረተ ባይሆንም፤ አባላቱ የኢህአዴግ ርዕዮተ አለም ምንድነው ትብለው ቢጠየቁ አብዛኛዎቹ ምላሽ የላቸውም፡፡ የሚመልሱ ቢኖሩ እንኳ እዚም እዛም የረገጠ እና እርስ በርሱ የሚጋጥጭ ሀሳብ ይነግሩናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄ ደግሞ ለፓርቲው ትልቅ ፈተናና ከፍተኛ አደጋ የሚጋርጥ እውነታ ነው፡፡

መሠረታዊ የሆኑ የግንባሩን ምሰሶ እሳቤዎችን የማያውቅ ባለስልጣን ህዝብ ቢያስለቅስ፣ በአደባባይ ዝርፊያ ሲያከናውን ቢውል አስገራሚነቱ ምኑ ላይ ነው፡፡ አንድ ፓርቲ ግዑዝ አካል አይደለም፡፡ በርዕዮተ አለም የተስማሙ ሰዎች ስብስብ ነው፡፡ታዲያ ይህ የሰዎች ስብስብ አንድ ያደረጋቸውን እሳቤ የማክበርና የማስከበር የውዴታ ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህም የሚደረገው የፓርቲውን ህልውና ለማስጠበቅ ነውና ማንኛውም ዋጋ ተከፍሎ ሊደረግ ይገባል፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀርና ፓርቲውን ከመሰረተው ርዕዮተ አለም የራቁ እሳቤዎች ሰርገው በመግባት ሲያቆጠቁጡ እና አድገው አጀንዳቸውን ማስፈፀም ሲጀምሩ ለፓርቲው ህልውና አደገኛ ይሆናል፡፡

ኢህአዴግ እየታመሰ ያለው ከተመሰረተበት ርዕዮተ አለም በተፃራሪ ሰርገው በገቡ እሳቤዎች ነው፡፡ እነዚህ እሳቤዎችም አላማቸው የማይታወቅ እና መድረሻ የሌላቸው እንዲሁም እሳቤውን በተሸከሙ የግንባሩ አባላት ልክ የበዙ ናቸው፡፡ በዋናነት ግንባሩ የርዕዮተ አለም መፋለስ ሲያጋጥም በፍጥነትና በጥብቅ ዲሲፒሊን አለማረሙ፤ የመልካም አስተዳደር እንበለው ሌላም የከፋ ነገር መፈልፈያ ኩዪሳ አድርጎታል፡፡ ርዕዮተ አለሙን የማስረፁ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ አባላትን ባልተጠና መልኩ የማግበስበሱም ጉዳይ ችግሩበከፋ መልኩ እንዲስፋፋ አድርጓል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ግለሰቦች ለፓርቲው መሰረታዊ መሰሶዎች ያላቸው ታማኝነትና የማስፈፀም ብቃት ሳይሆን የሚመዘኑት ባብዛኛው ለአለቆቻቸው ባላቸው ታማኝነት መሆኑ የነገሩን መክፋት ያሳየናል፡፡ ይህም ያልተገባ አካሄድ በየመድረኩ ርዕዮተ አለም የሚያፋልሱ ቱባ ባለስልጣናት እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርቦ አንድ መግለጫ እየሰጠ ያለ አንድ ከፍተኛ አመራር የገዛ ፓርቲውን ርዕዮተ አለም ያፋለሰ እና በዛ ያልተቃኘ ንግግር ሲያደርግ በጣም ያስደነግጣል፡፡ የበለጠ የሚያስደነግጠው ደግሞ ኢህአዴግ ይህንን ለማረም ዝግጁ አለመሆኑ ነው፡፡ ርዕዮተ አለሙን ማስረፅ እና ማስከበር ያቃተው የፖለቲካ ፓርቲስ ህልውናውን አስጠብቆ ለመሄዱ ምን ያህል እርግጠኛ ነው?

ይህንን እዚህ ጋር አቁመን ሌላ ሌላኛውን መሠረታዊ ጉዳይ እናንሳ፡፡

ኢህአዴግ ሚያ በሚፈልግ ቦታ ላይ እውቀቱ የሌለውን ሰው ይሾማል፡፡ ኢህአዴግ በሚመራው መንግስት የኬሚስትሪ ሙሁሩን የግብርና ቢሮ ሀላፊ እንዲሁም የባዮሎጂ ሙሁሩን የንግድ ቢሮ ሀላፊ አድርጎ ለመሾም ችግር የለበትም፡፡ የአደባባይ ሚስጥር ነውና፡፡ ከርዕዮተ አለም ባሻገር የምትመራውን ሴክተር መስሪያ ቤት መሠረታዊ እውቀቶች አስፈላጊ ናቸው፡፡ በተለይ ሞያና ፕሮፌሽናሊዝም በሚጠይቁ ተቋማትና ሴክተር መስሪያ ቤቶች ላይ! ኢህአዴግ ጋር በዚህ ችግር የለም፡፡ አንዳንዴም በዚህ መልኩ ማሰብ የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ ይህ ነገር በ1983 ቢሆን ኖሮ ምንም የሚያስገርም ጉዳይ አልነበረም፡፡ ከ40 በላይ ዩኒቨርስቲዎችን ገንብቶ የተማረ የሰው ሀይል እንድአሸን እያፈላ ያለ መንግስት እንዴት ለተገቢው ቦታ ተገቢውን ሰው መመደብ ያቅተዋል? ይህ ራሱ ትልቅ መፋለስ ነው ብዬ ነው የምወስደው፡፡

በአፍሪካ እንደኢህአዴግ ለልማት እና ድህነትን ለማጥፋት የቆረጠ ፓርቲ አይገኝም፡፡ ካለው ደካማ የህዝብ ግንኙነት ማዋቅር የተነሳ ግን የሚሰራውን ከማስረዳት ይልቅ ከሱ በተፃራሪ ቆመው አሉታዊ ፕሮፓጋንዳ የሚነዛበትን የመመከት ስራ ላይ ተጠምዶ ይገኛል፡፡ ይህ መሰረታዊ ችግር ባፋጣኝ ካልተቀረፈ መዘዙ የከፋ ነው ባይ ነኝ፡፡

ለኢህአዴግ የህዝብ ግንኙነት ደካማ መሆን ከመዋቅራዊው ችግሩ ባለፈ ከላይ የጠቀስኳቸው የአመዳደብ ጉዳይ መሰረታዊ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የህዝብ ግንኙነት ስራ እጅግ የተከበረ ሞያ እና ክህሎት የሚሻ ሞያ ነው፡፡ ይህም በትምህርት እና በስልጠና ሊታገዝ ግድ ይላል፡፡ ለምን ቢባል ግንኙነትህ ክቡር ከሆነው ህዝብ ጋር በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ የህዝብን ስነልቦና እውነተኛ በሆነ መልኩ ማንበብ የሚችል መሆን አለበት፡፡

ኢህአዴግ ግን በዚህም ችግር ያለበት አይመስልም፡፡ በፓርቲው መድረኮች ላይ አንደበተ ርቱዕ ሁን እንጂ አንተን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ከማድረግ ወደ ኋላ የሚል አይመስለኝም፡፡ አብዛኛውን የሀገራችንን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊዎች የሞያ ክህሎት ብንፈትሽ በዘርፉ የሠለጠኑ ሀላፊዎችን ማግኘት የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ አፈ ቀላጤ መሆን በራሱ የህዝብ ግንኙነት እንደማያደርግ ኢህአዴግ የገባው አልመሰለኝም ወይም አውቆ ተኝቷል፡፡ ከ40 በላይ ዩንቨርስቲ ባለበት ሀገር የባለሙያ እጥረት አለ ማለት ተዓማኒ ስለማያደርግ ማለት ነው፡፡

ሰሞኑን እንኳ በማህበራዊ ሚዲያው አቧራ አስነስቶ የነበረውን የአቶ ንጉሱ ጥላሁንን የአማራ ክልል የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ሀላፊ በፌስ ቡክ የተሰጠውን አስተያየት ማንሳት ይቻላል፡፡ በማንኛውም ምክንያት ሊሆን ይችላል የተከበሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ላይ ትችት ሲሰነዝር ለነበረው ጋዜጠኛ ዳንኤል ብርሃነ በቀጥታ ምላሽ ለመስጠት ሲሞክሩ ተስተውለዋል፡፡ አንደኛ፡- አንድ ሠው ትልቅ የመንግስት ሀላፊነት ከተሸከመ በኋላ የህዝብ እንጂ የራሱ ስሜት ነፀብራቅ አይደለም (የቅርብ ጓድህ ሲጠቃ በሚሰማህ ስሜት ብቻ አትንቀሳቀስም፡፡ ከብዙ አቅጣጫ እርምጃህ ያለውን አንደምታ ታጠናለህ)፡፡ ሁለተኛ፡- አስተያየትህ የፓርቲህን ርዕዮተ አለም ያላፋለሰ መሆኑን ታረጋግጣለህ፡፡ ሶስተኛ፡- አንተ የህዝብ ግንኙነት እንጂ የግለሠብ ግንኙነት እንዳልሆንክ ታስታውሳለህ፡፡

ዋናው መሠረታዊ ነገር ግን ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት የኢህአዴግ ልክፍት ነው፡፡ ይህም ልክፍት የታጋይ ገዱን ህዝባዊነት እና አገልጋይነት አቶ ንጉሱ በሚመሩት ቢሮ በኩል ለህዝቡ በተከታታይ መልካም ግንዛቤ መፍጠር ሲቻል፤ ያው የተለመደው የመከላከል ተግባር ውስጥ መገባቱ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የአቶ ንጉሱ መገለጫ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ችግር ነው፡፡ መልካም የሚሰራ መልካሙ ሊነገርለት ይገባልና ይህ አስቀድሞ ቢደረግ ወደ መከላከል የሚያስገባ ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ የዚህም ምንጩ በዋነኝነት የክህሎት እና በሞያው ላይ ያለ የእውቀት ውስንነት ነው፡፡

እኔ አሁን አቶ ንጉሱን የምመድብ ቢሆን ከህዝብ ግንኙነት ይልቅ ለትምህርት ቢሮ ሀላፊነት ነበር የማጫቸው፡፡ ለምን ቢባል በሰሜን ሸዋ ዞን ሞላሌም ሆነ መሀል ሜዳ የሂሳብ መምህር ሆነው በሚያገለግሉበት ወቅት በተማሪዎቻቸው የተመሰገኑ፣ የመምህራኑን ሆነ የትምህርት ቤቱን ችግር ሊፈቱ የሚተጉ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከህዝብ ግንኙነት ይልቅ የትምህርት ቢሮ ሀላፊ ሆነው ቢመደቡ ኖሮ በቅርበት የሚያቁትን የመማር ማስተማር ችግሮችን በቀላሉ መፍታት ይችሉ ነበር ባይ ነኝ፡፡ በዚህም ጥረት ታላቅ ሀገራዊ ውጤት ማስመዝገብ ይችሉ ነበር፡፡

ነገር ግን ኢህአዴግ ችግር የለበትም፡፡ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው በሚል ጭፍን አኬያሄድ መበስበስ የፈለገ ይመስላል፡፡ የአቶ ንጉሱ ጉዳይ ሰሞንኛ አጀንዳ ሆነ እንጂ ሙሉ ኢትዮጲያ ውስጥ ያሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ቢፈተሹ ያለሙያቸው በደመነፍስ የሚመሩ ሀላፊዎች ቢበዙ እንጂ የሚያንሱ አይሆኑም፡፡

እንደው በትንሹ እንኳ ለባለሙያዎች እድል ለመስጠት በኢህአዴግ በኩል ቁርጠኝነቱ አይታይም፡፡ ኢህአዴግ መቁረጥ ካለበት ሁሉም ላይ ሊሆን ይገባል፡፡ ድህነትን ለማጥፋት የቆረጠ ፓርቲ ሙያ ለሚፈልጉ ተገቢ ቦታዎች ተገቢ ሰዎችን መመደብ ይኖርበታል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ አቶ ንጉሱም ሆኑ በመላው ሀገራችን ያለቦታቸው ተመድበው የሚሰሩ ሰዎችን ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም፡፡ ተጠያቂ የሚሆነው ራሱ ፓርቲው ነው፡፡

ቸር እንሰንብት

*********

(ይህ አስተያየት የግሌ እና የማንንም የማይወክል መሆኑን ሊታወቅ ይገባል፡፡ ለአስተያየት [email protected])

Guest Author

more recommended stories