የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት 4 | በጦርነቱ አጀማመር አጨራረስና ዉጤቱ ዙሪያ ያሉ የተለያዩ አመለካከቶችና የሃሳብ ሙግቶች

(ኮ/ል አስጨናቂ ገ/ፃድቅ)

(የዚህን ፅሁፍ የመጀመሪያ ክፍል ለማንበብ በዚህ ሊንክ፡ ሁለተኛ ክፍል ለማንበብ በዚህ ሊንክ እና ሦስተኛ ክፍል ለማንበብ በዚህ ሊንክማግኘት ይችላሉ)

Highlights

++ ‹‹ ጦርነቱ እንደተጀመረ ሰሞን . . . የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የጦርነቱ የፖለቲካዊ ግቡ ምን እንደሆነ [ስጠይቅ] . . . ጄ/ል አበበ “ጥያቄዉ በጣም ጠቃሚ ነዉ፡፡ ሆኖም  አሁን መልስ ከመስጠት ይልቅ ሁላችሁም ከዚህ ስብሰባ በኋላ በየግላችሁ አስቡበትና እኛም ከሚመለከተዉ ጋር ተነጋግረን መልስ እንሰጣችኋለን” ነበር ያሉት፡፡ . . . በወቅቱ በስብሰባዉ ላይ የነበሩት የአየር ኃይሉ ም/አዛዥ አሁን በህይወት የሌሉት ጄ/ል ኃይሌ ጥላሁን የጆቤ ምላሽ አስቆጥቶአቸዉ ከተቀመጡበት በድንገት በመነሳት ቁጣ በተቀላቀለበት  አነጋገር “ሌላ ቀጠሮ መስጠት አያስፈልግም፤ መልሱ ግልጽ ነዉ፡፡ መንግስት በግልጽ ያስቀመጠዉ የጦርነቱ ግብ አለ፡፡ እኛ የኤርትራን ሉአላዊነት በመድፈር ለመዉረርና ቅኝ ግዛት ለማድረግ አልተነሳንም፡፡ ወደ ጦርነት የምንገባዉ የተነጠቅነዉን  ለማስመለስ ነዉ” በሚል በቁጣ ተናገሩ፡፡ ጆቤ የጄነራሉን መለስ እንዳልሰሙ ሆነዉ ችላ ብለዉ ከማሳለፍ ዉጭ አጸፋ ምላሽ አልሰጡም፡፡ ››

++ ‹‹ በደርግ ዘመን የሶማሊያ ጦር በእብሪት አገራችንን ወርሮ ህዝባችንን ያለምህረት ሲጨፈጭፍ እያየች አሜሪካ ራሳችንን ለመከላከል እንኳን እንዳንችል አድርጋ አሰቀድሞ ገንዘብ የተከፈለበትን መሳሪያ መከልከሏ ሳያንስ ….. ሌላዉ ቀርቶ የጦር መሳሪያ በማቀበልና በምክር ሲረዳን የነበረዉ የሶቭዬት መንግስት ሳይቀር ከአሜሪካ መንግስት በተደረገበት ጫና ሳቢያ የሶማሊያን ጦር እንዳንበቀልና ወደ ሶማሊያም ዘልቀን እንዳንገባ ነጋ ጠባ ይጨቀጭቁ ነበር፡፡  በወቅቱ ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም የሶማሊያን ጦር የመበቀል ጽኑ ፍላጎት የነበራቸዉ ቢሆንም ነገር ግን የሶቭዬት ባለስልጣናት ጎትጎታ በተለይም የአሜሪካንን ማስፈራራት በጭራሽ መቋቋም እንደማይችሉ በመረዳታቸዉ ወራሪዉ ጦርን የመደምሰሱ እቅድ እንዳይተገበር ይልቁንም  ለወራሪዉ ጦር መንገድ ተከፍቶለት በሰላም ለቆ እንዲወጣ ለማድረግ ተገደዉ ነበር፡፡ ››

++ ‹‹ በባለፈዉ ጦርነት አንዳንድ ወላጆች “ልጆቻችን መስዋእት መሆናቸዉ ካልቀረ ባድመ ቀርቶብን አሰብ ላይ ብንረባረብ ይሻል ነበር” ሲሉ ተደምጠዉ ነበር፡፡ እነዚህ ወላጆች የልጆቻቸዉ በጦር ሜዳ ወድቆ መቅረት የሚጸጽታቸዉ  የአሰብ ገዳይ ትዉስ ሲላቸዉ ነዉ፡፡ ዛሬ አንዳንድ ፣የመንግስት ባለስልጣናትም የዚሁ ዓይነት አዲስ አስተሳሰብ  እንዳላቸዉ እናዉቃለን፡፡ ችግሩ ግን ይሄን እምነታቸዉን ወደ መድረክ አዉጥተዉ በግልጽ ለመወያየት የፓርቲያቸዉ ባህል አይፈቅድላቸዉም፡፡ . . . እንኳን ተራዉ አባል ቀርቶ ቁልፍ የሚባሉ የፓርቲዉ አመራሮችም ቢሆኑ ያቺዉ አስቀድሞ አቋም ከተያዘባት ጉደይ ዉጭ አዲስ አመለካከታቸዉን ለዉይይት ወደ መድረክ ለማቅረብ ድፍረት የላቸዉም፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ በአብዛኛዉ የፓርቲዉና የመንግስት አመራርና አባላት ዘንድ እየታመነበትም ነገር ግን የፓርቲዉ የመስመር መቀልበስ ተደርጎ እንዳይቆጠር በስህተቱ መግፋት ተመራጭና እጅግ የቀለለ  ሆኗል፡፡ አንድ ቀን አንድ ደፋር ወደ መድረክ አስከሚያወጣ ድረስ ይቀጥላል፡፡ ››

++ ‹‹ በተለይም የኢሳይያስን “ተአምረኛ ምሽግ” የተመለከተ ሰዉ የኤርትራ ሰራዊት በዚህ ፍጥነት ይሸነፋል ቢሎ ለመገመት መቸገሩ አይቀርም፡፡ የሻእቢያ ምሽግ በ2ኛዉ አለም ጦርነት ወቅት ፈረንሳዮች የጀርመንን ማጥቃት ለመግታት ያስችላል ቢለዉ ለዓመታት ሲገነቡት የኖሩትን ማጂኖት ላይን (maginote line) ከሚባለዉ ምሽግ ጋር በማይተናነስ ደረጃ ሻዕቢያ ከሁለት ዓመት ላላነሰ ጊዜ ሲገነባ የከረመበትና አሌክስ ላስት የተባለዉ የቢቢሲ ዘጋቢ እጅግ አጋኖና አዳንቆ ለዓለም ህዝብ  እንዲደርስ ያደደረገዉን ምሽግ የኢትዮጵያ አንበሶች በአጭር ጊዜ ዉስጥ እንዳልነበር ማድረጋቸዉን የሻእቢያ አመራሮች ሲገነዘቡ ከዚያ በኋላ አጉል መንደፋደፍ እንደማያዋጣ በመረዳታቸዉ ጦርነቱን በሆነ ዜዴ ካላስቆሙ በስተቀር ኪሳራዉ በፍጹም ከሚቋቋሙት በላይ ሆኖ ያለ ወታደር እንዳይቀሩ በመስጋት በፊት ያጣጣሉትን የአፍሪካ ህብረትን ዉሳኔ ለመቀበል ተገደዋል፡፡ ››

++ ‹‹ በወቅቱ በዲፕሎማሲ አቅም ችግር ምክንያት የኛ የሆኑትን ተከራክሮ ህጋዊ ባለቤትነታችንን ማረጋገጥም ሆነ በጦርነቱ ሰለባ በመሆናችን የሚገባን ካሳ ማስወሰን ተስኖን እያለ የበለጠ ትልቅ ስህተት ደግሞ በደንብ ሳናረጋግጥ ባድመ ለኛ ተወስኗል ብሎ መንገስት መግለጫ መስጠቱና ህዝቡን ያለአግባብ ካስጨፈረ በኋላ ግን መንግስት እንዳለዉ ሳይሆን ባድመ ለኤርትራ መወሰኑን ሲታወቅ ህዝቡ ምንድነዉ ሊያስብ የሚችለዉ? በሃገር ሉአላዊነትና በብሄራዊ ጥቅም ላይ ያን ያህል ግደለሽነትና ሃላፊነት የጎደለዉ ድርጊት መደረግስ ነበረበት እንዴ? አንዴ ስህተት ከተፈጠረ  በኋላ ደግሞ የሚመለከተዉ የመንግስት አካል ለተፈጠረዉ ስህተት ተገቢዉን ማረሚያ መስጠትና ህዝብን ይቅርታ መጠየቅም ሲገባዉ አላደረገም፡፡ ››

++ ‹‹ ባድመን እንልቀቅላችሁ እንዳንል ባድመ የተፈረደዉ ለኤርትራ ነዉ፡፡ ብንለቅላቸዉም እንደዉለታ አይቆጥሩትም፡፡ አሰብ ደግሞ ከመጀመሪያዉኑ በይገባኛል ጥያቄም አላነሳንበትም፡፡ በሌላ አባባል አሰብ የኤርትራ መሆኑን አምነን የይገባኛል ጥያቄ እንደማናነሳ አረጋግጠናል ማለት ነዉ፡፡ “ሰጥቶ የመቀበሉ “ጉዳይ በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት ቢያገኝ እንኳን ምን ሰጥተን ምን ልንቀበል እንደምንችል ግልጽ አይደለም፡፡ እኛ ከኤርትራ የምንፈልገዉን እንጂ እነሱ ከእኛ ምን ሊጠይቁ እንደሚችሉ  ብዙም ግልጽ አይደለም፡፡ ››

++ ‹‹ ይህ የሻዕቢያ ብልጠት በታሪክ የሚናዉቀዉን የሃኒባልን አጥቂ ኃይል መቋቋም እንደማይቻል በመረዳት ኪሳራን ለመቀነስ ብሎ ፋቢዮስ (fabius) ሲጠቀም ከነበረዉ “Fabian strategy” ተብሎ በሚታወቀዉ ስልት ሰራዊቱን ወደኋላ እንዲያፈገፍግና ቦታ እንዲቀያይር በማድረግ ከአጠቃለይ ድምሰሳ መትረፍ የቻለበት ዜዴ ይመስለኛል፡፡ ሻዕቢያ ኪሳራዉን በመፍራት ከምሽግ ወጥቶ ለመዋጋት ፈጽሞ አልሞከረም፡፡ ሜዳ ላይ ወጥቶ ራሱን ጭዳ የሚያደርግበት ምክንያትም አልነበረም፡፡ ››

——-

መግቢያ

በኢትየጵያና በኤርትራ መካከል የተደረገዉ ጦርነት ከመነሻዉ አስከ ፍጻሜዉ በአብዛኛዎቹ ጉዳዮች ላይ መግባባት የራቀዉ ለአስካሁንም በአወዛጋቢነቱ ቀጥር አንድ ብሄራዊ አጀንዳ ሆኖ የቀጠለ ነዉ፡፡ ጦርነቱ የሚታወሰዉ በርካታ ወታደሮቻችን  የተሰዉበት ጦርነት በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በጦርነቱ ዙሪያ ባሉ አብይ ጥያቄዎች ላይ መግባባት እንዳይኖረን ያደረገ በመሆኑ ጭምር ነዉ፡፡

የሃሳብ ሙግት ከሚነሳባቸዉ ጉዳዮች መካከል የሻዕቢያ ወረራ ደንገተኝነት ፤ወደ ጦርነቱ ስንገባ ባስቀመጥነዉ ስትራቴጂዊ ዓላማ ፤በተገኘዉ ድልና በተከፈለዉ መስዋትነት ትርፍና ኪሳራ ላይ ፤የሻዕቢያን ሰራዊት መደምሰስ ጉዳይ ላይ፤በኤርትራን ግዛት የመቆየት ጉዳይ ላይ፤ የባህር በር (አሰብ ወደብ) በድጋሚ የማስመለስ ላይና በመጨረሻም በኃይል ያስከበርነዉን በድርድር ስለተነጠቅንበት ሁኔታ ጥቂቶቹ ናቸዉ፡፡ በአንዳንዶቹ ላይ የግል አስተያየቴን ለማካፈል እሞክራለሁ፡፡

1/ ወደ ጦርነቱ የገባንበት ህጋዊ አግባብነት፤ የጦርነቱ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ግቡ

ኤርትራ ወረራ ማድረጓና በድንበር አካባቢ የነበሩትን ዜጎቻችን ላይ ጥቃት መፈጸሟና ከቀዬያቸዉ ማፈናቀሏ እንደታወቀ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ከመጠየቅ ጀምሮ ጦራቸዉን አስወጥተዉ ጥያቄ ካላቸዉ ለመነጋገር ዝግጁ መሆናችንን ለኤርትራ አቻቸዉ ቢገልጹም ተገቢዉን ምላሽ ባለማግኘታቸዉ የሁኔታዉን አሳሳቢነት በመረዳት ለሀገሪቱ ህግ አዉጭ በማቅረብ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንዲሞከርና ሻዕቢያ ለሰላማዊ መፍትሄ ፈቃደኛ ካልሆነና ችግሩን በሰላም መፍታት የማይቻልበት ሁኔታ ከተፈጠረ በኃይልም ቢሆን ሉአላዊነታችን የማስመለስ እርምጃ እንዲወሰድ በፓርላማ አቅርበዉ  አስወስነዋል፡፡

አጠቃላይ አካሄዱ ሲታይ፡

አንደኛ:- ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመጨረስ እድሉ ዝግ ላይደረግ በቅድሚያ ሰላማዊ ጥረት እንዲደረግና ሻዕቢያ ሰላማዊዉን መንገድ አሻፈረኝ ካለ  ወደ ጦርነት መግባትን እንደ መጨረሻ አማራጭ (military solution as last resort)በመዉሰድ ሉአላዊነታችንን ለማስመለስ አስከመጨረዉ እንደምንፋለም ግልጽ የሆነ  አቋም የስቀመጠ፤

ሁለተኛ:- ወደ ጦርነት የተገባዉ በሃገሪቱ ፓርላማ ሰፊ ክርክር ተደረጎ በመጨረሻም ፓርላማዉ በድምጽ ብልጫ በማስወሰን መሆኑና ሁሉም ነገር በህግ አዉጭዉ ፈቃድና እዉቅና (authorization) የተከናወነ መሆኑ፤

ሶስተኛ:- ወደ ጦርነቱ ከመግባታችን በፊት ግልጽ ፖለቲካዊ ግብና ስትራቴጂ (clear political objective and strategy) ማስቀመጣችንና በዘፈቀደ ዘለን የገባንበት ጦርነት አለመሆኑ፤

አራተኛ:- የጦርነቱ ግብ በኃይል የተነጠቅነዉን ሉአላዊነታችንን በማስመለስ ላይ ብቻ የተገደበ እንጂ ከዚያ ያለፈ ትርፍ ፍለጋ ዓላማ ያለዉ  አለመሆኑ፡

አምስተኛ:- ጦርነቱን ለማካሄድ ቢቻል ባለን አቅም የግድ ከሆነ ደግሞ ሀገሪቱን በማይጎዳ ደረጃ የግድ የሚያስፈልገንንና የጎደለንን ብቻ ለማሟላት የጦር መሳሪያ ግዢ እንዲከናወን አቅጣጫ የተቀመጠበት መሆኑ፤

ስድስተኛ:- ጦርነቱ እየተካሄደ በነበረበት ወቅትም ቢሆን መንግስት ከልማት ስራዉ ለአፍታም ትኩረቱን ሳይነፍግ እየተዋጋንም ቢሆን እናመርታለን በሚለዉ ብህል መሰረት በተቻለ መጠን  ልማቱ እንዳይሰተጓጎል ያልተቆጠበ ጥረት ማድረጉና እንደ ደርግ ሁሉን ነገር ወደ ጦር ግንባር ሳይል ሃላፊነት የተሞላበት ትክክለኛ አቅጣጫ መያዙ፤

ሰባተኛ:- ጦርነቱን ያለፍላጎታችን የገባንበትና እንጂ እኛ የጀመርነዉ ባለመሆኑ እኛ ሰለባ የነበርን(victim) መሆናችን እየታወቀም መንግስት ከጦርነቱ ጎን ለጎን ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ ስራ በመስራት የዉጭ ድጋፍ ለማትረፍ የቻለበት መሆኑ ወዘተ በጥቂቱ የሚገለጹ ናቸዉ፡፡

ባጠቃላይ ሀገሪቱ በጦርነት ላይ የነበረች መሆኑ ባይካድም ነገር ግን  መንግስት ሁሉም ነገር ከገደብ እንዳያልፍና በተለይ የህዝቡ ኑሮ ላይ መመሰቃቀል እንዳይፈጠርና በደርግ ጊዜ እንደነበረዉ ሀገሪቱ ወደ ትልቅ የጦር ካምፕነት ሳትቀየር ከጦርነቱ ቀጠና ያለዉ ህዝብ ብዙም ሳያጎሳቆልና ብዙም ሳይማረር ጦርነቱን ፈጥነን  ለመጨረስ የሚያስቸል ህጋዊ አካሄድ ነዉ የተከተለዉ፡፡

Photo - Assab port, Red Sea, Djibouti
Photo – Assab port, Red Sea, Djibouti

2/ በጦርነቱ ዙሪያ ሲሰጡ የነበሩ አስተያዬቶችና ሲንጸባረቁ የነበሩ አመለካከቶች

ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በገዥዉ ፓርቲ ዉስጥ ተፈጥሮ ነበር ከተባለዉ ሽኩቻና የአቋም ልዩነት ያህል ባይሆንም በህብረተሰቡ ዉስጥም የተለያዩ አመለካከቶች ሲንጸባረቁና አስተያቶችም ሲንሸራሸሩ ነበሩ፡፡ አስተያዬቶቹን እንደወረደ ላቅርባቸዉ፡፡

አስተያየት አንድ፡ ጦርነቱ የኢህአዴግ የአመራር ድክመት ዉጤት ነዉ

ይህ የሚሉት ወገኖች መነሻ የሚያደርጉት ኢህአዴግ ቢቻል ስልጣን ከመያዙ በፊት ካልሆነም ራሱን ወደ መንግስትነት ከቀየረ በኋላ (ከሽግግሩ ዘመን ጀምሮ) ከኤርትራ ጋር (ከሪፌሬንደሙ በፊት )በሁለቱ አገሮች የወሰንና ድንበር ጉዳይ ላይ አንድ ዓይነት ህጋዊ ስምምነት ማድረግ ነበረበት፡፡ ኢህአደግ ለኤርትራ እንደ መንግስት እዉቅና መስጠቱ በራሱ እንደ ችግር የሚታይ አይደፈለም፡፡

ነገር ግን ህዝበ ዉሳኔዉ ከመደረጉ በፊት ወደፊት የኢትዮጵያ ጥቅም ላይ አደጋ በማያስከትል ሁኔታ ዋስትና ሊሆን የሚችል ስምምነት ማድረግ ይገባዉ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር አብሮ እየተነሳ ያለዉ ጉዳይ በሽግግሩ ወቅት መንግስት የንግድ ስምምነት ለማድረግ ከመቻኮል (ለዚያዉም እነሱን የበለጠ ተጠቃሚ ያደረገ )ይልቅ ቅድሚያ ሰጥቶ የደንበር ጉዳይ ላይ አንድ መቋጫ አበጅቶ  ቢሆን ኖሮ  ይሔ ሁሉ ጣጣ ባልመጣ ነበር የሚል ነዉ፡፡

አስተያየት ሁለት፡- ጦርነቱ የኢህአዴግ የዲፕሎማሲ ድክመት ማካካሻ ነዉ

ይህ አመለካከት ከቶኒ ቤን አባባል ጋር የሚስማማ ይመስላል ፡፡ ቶኒ እንዳለዉ ሁሉም ጦርነት የዲፕሎማሲ ድክመት ዉጤት ነዉ፡፡ (“All war represents a failure of diplomacy“) ይህን አስተያዬት ሲሰነዝሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች መነሻ የሚያደርጉት በተወሰነ ደረጃ እዉነትነት የነበራቸዉን ሁኔታዎችን እንደ ማስረጃ በመጥቀስ ነዉ፡፡

“በሁለቱ አገሮች መካከል ችግር እየተፈጠረ መሆኑን መንግስት ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያደረጋቸዉ ሙከራዎች ቢኖሩም ነገር ግን ዉጤት አልባ መሆናቸዉ፤ ከጦርነቱ በኋላም በህግ መድረክ በተደረጉ ክርክሮች እኛ ተጎጂዎችና ወረራ የተፈጸመብን የጦርነቱ ሰለባዎች መሆናችን በግልጽ እየታወቀ ነገር ግን ኤርትራን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግ ዉሳኔ እንዲወሰን የተደረገዉ በኛ የማስረጃ አቀራረብና ባጠቃለይ የክርክር ድክመት ነዉ„ ባዮች ናቸዉ፡፡

አስተያት ሶስት፡- የጦርነቱ መነሳት የኤርትራን ቅጥ ያጣ ብዝበዛና የሁለቱን አገሮች የተዛባ ግኑኝነት የሚያስቀር ስለሆነ መልካም አጋጣሚ ነዉ

ይሄ አመለካከት የተሳሳተ አመለካከት አይመስለኝም፡፡ ሁለቱ አገሮች ግኑኝነት የተመሰረተበት  መርህ ለህዝቡ ብዙም ግልጽ ያልነበረና በተግባርም ህዝቡን እጅግ ሲያበሳጭ የቆየ በመሆኑ ጦርነቱን በዚህ መልክ ማዬታቸዉ የሚያስገርም አይመስለኝም፡፡ ህዝባችን በኤርትራዉያን አያያዝ  ሁኔታ ደስተኛ አልነበረም፡፡

በገዛ አገራችን ዉስጥ እንደፈለጉ የሚፈነጩበትና ኤርትራ ዉስጥ በሚኖሩ ኢትዮጵዉያን ወገኖቻችን (አብዛኛዎቹ የትግራይ ተወላጆች ናቸዉ፡ ላይ እያሳዩ የነበረዉ ንቀትና አድሎአዊ አሰራር እየሰማ ህዝቡ መከፋቱ እዉነት ነዉ፡፡ ተራዉ የሀገሪቱ ዜጋ ፖለቲካዊ ትንታኔ ለመስጠት አቅም ቢጥረዉም ቢያንስ ግን በዜግነቱ አንድ የተበላሸና መስመሩን የሳተ ነገር መኖሩን ለመረዳት አይችልም ብሎ ማሰብ በራሱ ሞኝነት ነዉ፡፡

በሀገርና በህዝብ ላይ እየተሳራ ያለን በደል ለመረዳት የግድ የተማረ ፖለቲከኛ መሆን አያስፈልግም፡፡ የተበላሸ ነገር ስለመኖሩ  ህዝባችን በየዕለቱ በየቦታዉ ሲታዘባቸዉ የነበሩት ሁኔታዎች ምስክር ናቸዉ፡፡ በየገጠሩ ባሉ ትናንሽ ገበያዎች ሳይቀር የኤርትራ ሰሌዳ የተለጠፈባቸዉን ባለተሳቢ የጭነት መኪናዎች ማዬት የተለመደ ነበር፡፡

ትንሽ ገንዘብ በለጥ እያደረጉ ገበሬዉን እያታለሉ በየቀኑ ጤፍና ቡና  እየጫኑ ወደ ኤርትራ ሲያጓግዙ ህዝቡ ያይ ነበር፡፡ በአንድ ጊዜ የኑሮ ዉድነትና የዋጋ መናር እንዲፈጠር ያደረጉት ኤርትራዉያን ናቸዉ፡፡ በመሃል አገር በተለይ አዲስ አበባ ዉስጥ በዬትኛዉም አቅጣጫ ዞር ዞር ብሎ የቃኘ ሰዉ የሚያያቸዉ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች አብዛኛዎቹ የኤርትራዉያን መሆኑን ሲረዳ የሚሰማዉ ንዴት ቀላል አይደፈለም፡፡

የነዳጅ ቦቴዉ ወዘተ ሁሉ የነሱ ሰሌዳ የተለጠፈበት እንደ ነበር ህዝቡ እያዬ ለምን ተበሳጨ ብሎ ማሰብ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ የዚህ ሁሉ የገንዘብ ምንጭ ደግሞ ከኛዉ ንግድ ባንክ በተገኘ ብድር መሆኑ ደግሞ የበለጠ ያበግናል፡፡ በወቅቱ እንዲያዉም አንዳንድ ሰዎች በብስጭት ሲገልጹ እንደነበረዉ ኢህአዴግ ሻእቢያ ለዋለለት ዉለታ አስቀድመዉ በተስማሙት መሰረት ለተወሰኑ አመታት ኢትዮጵያን እንዳሻዉ እንዲበዘብዝ በይፋ ፈቃድ የሰጠዉ ነበር ያስመሰለዉ፡፡

ከዋና ከተማዉ አስለገጠር ትናንስ ከተሞች ሁሉ በዘመቻ መልክ ተሰማርተዉ ትላልቅ የመንግስትና ህዝባዊ ተቋማትን ንብረት እየዘረፉ ወደ አስመራ ሲያግዙ እንደነበር ህዝቡ በወቅቱ በስፋት የሚያዉቀዉ ሃቅ ነዉ፡፡ በየመዝናኛ ቦታዉ ሁሉ በየአዝማሪዉ ቤት በሙሉ የተቆጣጠሩት እነሱ በመሆናቸዉ ጎራ ብሎ ለመዝናናትም አዳጋች የነበረበት ሁኔታ ነበር፡፡ አዝማሪ አቁመዉና እኛን ለመስደብ አስቀድሞ የተዘጋጀ ካሴት ዘፈን በመልቀቅ እዚሁ ሃገራችን ዉስጥ ሆነዉ  ኢትዮጵያዉንን ሲያንቋሽሹ እየሰማ ህዝቡ በትዕግስት አልፏቸዋል፡፡ ህዝቡ ይሄ ሁሉ ዉርደት ሆን ተብሎ በኢህአዴግ የተቀነባበረ አድርጎ ነዉ የቆጠረዉ፡፡

አስተያየት አራት:- ጦርነቱ በግርግር ያጣነዉን አሰብ ወደብን ለማስመለስ መልካም አጋጣሚ ነዉ፡፡ ይህን እድል አለመጠቀም ሞኝነት ነዉ

ኤርትራን እንዳለ መመለስ ባይቻል እንኳን አሰብ ወደብን ለማስመለስ ሌላ ጊዜ ብንመኝም የማናገኘዉ መልካም አጋጣሚ ነዉ የተፈጠረልን የሚል አስተያዬት ያላቸዉ ወገኖች ቀድሞዉኑ በኤርትራ መገንጠል በጭረሽ ያልተዋጠላቸዉና በዚህ ምክንትም ሲበግኑ የነበሩ፤ ከኤርትራ መገንጠልም በላይ ደግሞ እጅግ ያስቆጫቸዉ እንዴት ኢትዮጵያን የምታክል ትልቅ አገር ያለ ባህር መዉጫ ትቀራለች በሚል ጥያቄ ሲያነሱ የነበሩ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡

አስተያየት አምስት:- ጦርነቱ የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ ተነጥሎ መኖር እንደማይችል በመረዳቱ ሁለቱን አገሮች እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ሆነ ብሎ የፈጠረዉ ዜዴ ነዉ

ይሄ አስተያዬት ያዉ ከላይ ከጠቀስኩት የኤርትራን ነጻ አገርነት ካለመቀበል የመነጨ ሆኖ ነገር ግን አንድ ቀን በሆነ ተአምር መልሶ የመቀላቀል ነገር (reunification) ሊመጣ ይችላል በሚል ተስፋ አጋጣሚዎችን ሲያልሙ የነበሩ ህልመኞች አስተያዬት ይመስለኛል፡፡ መልካም ነገር ማለም  አንዳችም ክፋት ባይኖረዉም ነግር ግን ባዶ ቅዠት የሚያስመስልባቸዉ ግን ህልማቸቸዉን እዉን ለማድረግ እነሱ ሊሰሩት ከሚገባ ስራ ይልቅ ከኤርትራ መጠበቃቸዉ ነዉ፡፡ ኢትዮጵያ ኤርትራን በጦርነት ስለተቆጣጠረች ብቻ  አንድነት ሊፈጠር ይችላል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነዉ፡፡

3/ የኤርትራን ሰራዊት ሙሉ በሙሉ የመደምሰስ ቅዤት

የሻእቢያን ሰራዊት የመደምሰስ ጉዳይ ላይ ዛሬም ከአስራ ስምንት ዓመታት በኋላም እንደ አዲስ ሲጠቀስ ይታያል፡፡ “ያኔ በዚያ ጦርነት ወቅት የሻዕቢያን ሰራዊት እንዳለ ድምስሰነዉ ቢሆን ኖሮ ይሄ ሁሉ ትንኮሳ አይደርስብንም ነበር” በሚል በወቅቱ በሀገሪቱ (በገዢዉ ፓርቲ) አመራር ዉስጥ የልዩነትና የመከፋፋል ዋነኛዉ መንስኤ ስለነበረዉ ጉዳይ ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላም እንደገና ሲነገር ይሰማል፡፡  በተለይም የኤርትራ ትንኮሳ ዜና በተሰማ ቁጥር በተለያዩ የሕትመት ሚዲያዎች ላይ  የሚሰጡ  ትንታኔዎች“ የመደምሰስ” ጉዳይን ትክክለኛነት ለማሳያነት በመጥቀስ ነዉ፡፡

ከዚህ በኋላ ግን ተመሳሳይ ጥቃት ቢፈጸምብን አስከ አጠቃላይ ድምሰሳና ከዚያም በላይ በመሄድ የሻእቢያን አገዛዝ በኃይል መቀየር ድረስ መሄድ አለብን የሚል አስተያዬትም ለመንግስታችንም ለሻእቢያም ለማስጠንቀቅ የታሰበ የሚመስል መልእክትም አሁንም ድረስ በስፋት እየተነገረ ነዉ፡፡

ይሁን እንጂ በጦርነት ጊዜ አንዱ የሌላዉን አገር ሰራዊት ሙሉ በሙሉ አስከ መደምሰስ የሚደርስ እርምጃ  መዉሰድ አለበት የሚባል ፍላጎትን በተግባር እዉን ለማድረግም አዳጋች ከመሆኑም ሌላ ከአለም አቀፍ ህግም ሆነ ከሞራል አንጻር ተቀባይነት የሌለዉና  አንዳችም ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ የማያስገኝ  ነዉ፡፡ በወቅቱ ወደ ጦርነቱ ስንገባ መንግስት ያስቀመጠዉ ፖለቲካዊ ዓላማና ስትራቴጂ ዉስጥ የሻዕቢያን ሰራዊት ሙሉ በሙለ በመደምሰስ አገሪቱን ያለ ወታደር ማስቀረትም ሆነ አመራሩን አዉርዶ በሌላ መተካት ይገባናል የሚል የጦርነት ዓላማ የነበረን አይመስለኝም፡፡

በርግጥ የማይካድ ነገር በወቅቱ የዚህ ዓይነት ፍላጎት የነበራቸዉ እንዳሉና  የሀገሪቱን አመራርንም ሲጎተጉቱና ጫና ሲያደረጉ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የዚህ ዓይነቱን አጠቃላይ ድምሰሳ ላይ የጸና አቋም የነበራቸዉ ከገዥዉ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችም ሆነ ከመከላከያ ከፍተኛ ጄኔራሎች መካከል እንደነበሩ በሚገባ የሚታወቅ ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ እንደ መንግስት ሲታይ እንደዚያ ዓይነት ገደብ የለሽ የጦርነት ዓላማ አልነበረዉም፡፡ ለጦርነቱ ፈቃድ(authorization) የሰጠዉ የሃገሪቱ ህግ አዉጭም ስለዚህ ጉዳይ(ድምሰሳ) የሚያዉቀዉም በዚህ ጉዳይ የወሰደዉም አቋም አልነበረም፡፡

በዚያን ግዜ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ቢሆን ይህ አመለካከት ተገቢነት የማይኖረዉ የሻዕቢያን ሰራዊት እንዳለ ደምስሰን አመራሩንም አስወግደን  የኤርትራን መሬት ወደ እኛ እናካትታለን የሚባል ግብ በመንግስት እንደ ዕቅድ ያልተያዘ መሆኑ  ብቻ ሳይሆን አግባብነት የለለዉና እዉን ለማድረግም የማይቻል  ስለነበር  ጭምር ነዉ፡፡

ለመሆኑ የኤርትራን ሰራዊት ሙሉ በሙሉ መደምሰስ ለምንስ ያስፈልጋል? የሌላዉን አገር መንግስትንስ በኃይል አዉርዶ በሌላ መቀዬርም ሆነ ስርአቱን ማፍረስስ (enforced regime change) ተገቢነቱ ምን ያህል ነዉ?

ሻዕቢያ በወቅቱ ለጦርነት ካሰለፈዉ ሩብ ሚሊዮን አካባቢ ይገመት ከነበረዉ ሰራዊት ዉስጥ ቢያንስ አንድ አራተኛ አካባቢ በጦርነቱ አጥቷል፡፡ ይህም በቁጥር ሲሰላ ከስድሳ ሺህ (60 ሺህ) የሚሆን ማለት ነዉ፡፡ ሻዕቢያ ለአስራሰባት ዓመታት ከደርግ ጋር ሲያካሂድ በነበረዉ ጦርነት ላይ ከመቶ ሺህ በላይ ታጋዮቹ የሞቱበት ኪሳራ ሲታሰብ ራሱ በቆሰቆሰዉ በአሁኑ ጦርነት እጅግ አጭር በሆነ ጊዜ ዉስጥ ያን ያሀል የሰዉ ኃይል ማጣቱ ጉዳቱ ከባድ እንደሆነበት ለመረዳት አያዳግትም፡፡

በዚህ ጦርነት በሻቢያ ላይ ያን ያህል ጉዳት ስናደረስ በኛ በኩል አንዳችም መስዋእትነት ሳንከፍል በነጻ ያመጣነዉ ድል አድርገን መቁጠር ያለብንም አይመስለኝም፡፡ የከፈልነዉ መስዋእትነት ሻዕቢያ ላይ ከደረሰዉ ጉዳት ጋር ሲጻጸር በእጅጉ አነስኛ ቢሆንም ጭራሽ አልተጎዳንም ማለት ግን አይደለም፡፡ ስለዚህ የሻዕቢያን ሰራዊት ሙሉ በሙሉ የማዉደም ዓላማ ራሱ ትክክል ባይሆንም ነገር ግን እናደርግ ብንል እንኳን አሁን ከከፈልነዉ የበለጠ መስዋእትነት ልንከፍል እንደምንችል እንዴት ይዘነጋል?

ሻዕቢያ ጦርነቱ እንደማያዋጣዉ ሲያዉቅ ያደረገዉ ነገር ቢኖር በሰራዊቱን ላይ ሊደርስ የሚችለዉን ጉዳት ለመቀነስ እንዲያስችለዉ ወደኋላ እያፈገፈገ ከአንዱ ምሽግ ወደ ሌላ ምሽግ፤ ከአንዱ መከላከያ ወረዳ ወደ ሌላ መከላከያ ወረዳ እያፈገፈገ  ኪሳራዉን በመቀነስ (minimize casualties) እድሜዉን የማራዘም ስልት ሲጠቀም እንደነበር  እናስታዉሳለን፡፡

ይህ የሻዕቢያ ብልጠት በታሪክ የሚናዉቀዉን የሃኒባልን አጥቂ ኃይል መቋቋም እንደማይቻል በመረዳት ኪሳራን ለመቀነስ ብሎ ፋቢዮስ (fabius) ሲጠቀም ከነበረዉ “Fabian strategy” ተብሎ በሚታወቀዉ ስልት ሰራዊቱን ወደኋላ እንዲያፈገፍግና ቦታ እንዲቀያይር በማድረግ ከአጠቃለይ ድምሰሳ መትረፍ የቻለበት ዜዴ ይመስለኛል፡፡ ሻዕቢያ ኪሳራዉን በመፍራት ከምሽግ ወጥቶ ለመዋጋት ፈጽሞ አልሞከረም፡፡ ሜዳ ላይ ወጥቶ ራሱን ጭዳ የሚያደርግበት ምክንያትም አልነበረም፡፡

ሻዕቢያ በቆፈረዉ ምሽግ ተማምኖ ኢትዮጵያን መድፈሩ ትልቅ ስህተት እንደሆነ ተረድቷል፡፡ አሁን ደግሞ የተረፈዉን ሰራዊቱን ገላጣ ሜዳ ላይ አድርጎ ሁለተኛ ስህተት ለመስራት አይሞክርም፡፡ እኛም እንደዚያ ያደርጋል ብለንም አንጠበቅም፡፡ ያም ሆነ ይህ  በዚህ ጦርነት ሻዕቢያ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትና ጉዳቱም እጅግ የተሰማዉ ቢሆንም ነገር ግን ሙሉ በሙሉ የዉጊያ አቅሙን አጥቷል፤ ከጠብ ጫሪ ባህሪይዉ ተላቋል፤ የስጋት ምንጭ መሆንም አቁሟል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ እንደ እዉነቱ ከሆነ ሻዕቢያ ከጦርነቱ ላይ ከደረሰበት ጉዳት ይልቅ በጦርነቱ ሽንፈት ተከትሎ የተፈጠሩ አጠቃላይ ቀዉሶች እጅግ የጎዳዉ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡

በርግጥ ይሄ ቀዉስ በድህረ-የጦርነት ሽንፈት ሁልጊዜም የሚከሰት የተለመደ ጉዳይ ነዉ፡፡ ዛሬ ሻዕቢያ በኢትዮጵያ ላይ ያንን የመሰለ ግዙፍ ሰራዊት አሰልፎ ጦርነት ሊገጥም የሚችልበት ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም፤ የህዝብ ድጋፍና አመቺ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች የሉትም፡፡

ነገርግን በዉክልናና በተዘዋዋሪ መንገድ ሰላማችንን ከመበጥበጥ ተቆጥቦ አለማወቁ፡፡ ለማንኛዉም ሻቢያን ሰራዊት ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ የታለመ የጦርነት እቅድ ባይኖረም ባለመደረጉ እንደ ጉድለትና የጦርነት ግባችንን እንዳላሳካን ተደርጎ የምንቆጭበት አይደለም፡፡

4/ መከላከያ ሰራዊታችን የሻዕቢያን ሰራዊት አሳዶ የመደምሰስ ግስጋሴዉን አቁሞ ወደ ኃላ ወደ ራሱ ይዞታ እንዲመለስ መደረጉ

መከላከያ ሰራዊታችን የሻዕቢያን ወራሪ ሰራዊት ከድንበራችን ካስወጣ በኋላ አያሳደደ የመደምሰስ እርምጃ መዉሰድ እንደ ጀመረ ብዙም ሳይገፋበት ማጥቃቱን አቁሞ ወደ ኋላ ወደ ራሱ ይዞታ እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ የዚያ ዓይነት የመንግስት ዉሳኔ ይኖራል ተብሎ በጭራሽ ያልተጠበቀና ድንገተኛ ስለነበር ትእዛዙ ተሰጥቶ ሰራዊታችን ወደ ኋላ እንዲመለስ ሲደረግ ለብዙዎቹ የሰራዊታችን አባላት ሁኔታዉ አስደንጋጭ ሆኖ ነበር፡፡

የሻአቢያን ሰራዊት አሳዶ በመደምሰስ ሻእቢያ በለኮሰዉ ጦርነት የወደቁት ጓዶቹን ደም ለመበቀል ጉጉት ለነበረዉ ሰራዊታችን ማጥቃቱን እንዲያቆም የተሰጠዉን ድንገተኛና ያልተጠበቀ ትእዛዝ አላስከፋዉም ማለት አይቻልም፡፡ የሰራዊታችን አባላት በወቅቱ ግራ መጋባት ብቻ ሳይሆን የቁጭት፤ የብስጭትና የተታለናል ስሜት አንደተሰማቸዉም ግልጽ ነዉ፡፡

መንግስት ይህን ያልተጠበቀ ዉሳኔ ሲወስንም ሰራዊቱን በኤርትራ መሬት መቆዬትም ሆነ ወደ ፊት መግፋትን ከወታደራዊ ፡ ከፖለቲካዊና ህጋዊ ተገቢነትና አዋጭነት አንጻር በሚገባ አጢኖና ጥቅሙና ጉዳቱን ገምግሞ ይመስለኛል፡፡ መንግስት በተለይ የጦር ኃይሉ ጠቅላይ አዛዥ የነበሩት (ነፍሳቸዉን ይማርና) ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በወቅቱ ይህንን ትዕዛዝ ከመስጠታቸዉ አስቀድመዉ የሚመለከታቸዉን ከፍተኛ የጦር አዛዦችን አማክረዉ የወሰኑት ዉሳኔ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡

በወቅቱ አቶ መለስ ሰራዊታችን ወደፊት መግፋት ይችል እንደሆነ ጠይቀዉ አዛዦች ከዚያ በላይ መግፋት እንደማይቻል ገልጸዉላቸዉ እንደነበር ከጦርነቱ በኋላ ከከፍተኛ መኮንኖች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ሲጠቅሱ ሰምቻለሁ፡፡ የጦር አዛዦቹ መልስ “አንችልም!” የሚል ሳይሆን “ይቻላል!” የሚል ቢሆን ኖሮም አቶ መለስ “ዉጊያዉን ቀጥሉና አስመራ ድረስ ዝለቁ” የሚል ትዕዛዝ እንደማይሰጡ እንዲሁ በደመነፍስ መገመት አያዳግተኝም፡፡

ምክንያቱም ጦርነቱ የተጀመረዉም የሚካሄደዉም ለወታደራዊ አስፈላጊነት ብቻ ተብሎ አይደለምና፡፡ አዛዦች ዉጊያዉን የመቀጠል ፍላጎቱ ቢኖራቸዉ እንኳን ለነሱ (ለጄኔራሎቹ) ፍላጎት ተብሎ የሚካሄድ ጦርነት አይኖርም፡፡ ስለዚህ ሰራዊቱ ወደ ፊት መግፋቱን አቁሞ ወደ ኃላ እንዲመለስ የተደረገዉ አዛዞች “አይቻልም” የሚል መልስ ስለሰጡዋቸዉ ብቻ ተብሎና  ምናልባትም የአሜሪካንን ግልምጫ ፈርተዉ አይመስለኝም፡፡

ከዚያ ይልቅ ያን ማድረግ ተገቢ አይደለም ብለዉ ስላሰቡ ይመስለኛል፡፡ ጦርነትን እንደመልካም አትራፊ ንግድ የሚቆጥሩ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ጦርነቱ በማንኛዉም መንገድ ቶሎ እንዲቋጭ አይፈልጉም፡፡ ስለዚህ በተለያዩ መንገዶች ጦርነቱን ለማራዘም ይጥራሉ፡፡ ሲያሻቸዉም ያሻጥራሉ፡፡ ሆን ብለዉም ሲቪል አመራሩን በመገፋፋትም ሆነ በማስፈራራት መንግስት ወደ ጦርነቱ ሲገባ መጀመሪያ ካስቀመጠዉ ግብ ዉጭ ጦርነቱን በመለጠጥ ቶሎ እንዳያልቅ ያደርጋሉ፡፡ ይሄ በደርግ ግዜም ጭምር የታየ ችግር ነዉ፡:

ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ አለመግባባቶች የተነሱት በአንድ አጋጣሚ ብቻ አልነበረም፡፡ በመጀመሪያ የሰላም ሃሳቡን መቀበል አለመቀበል ላይም ሰፊ ልዩነት ነበር፡፡ በጦርነቱ ዝግጅት ስፋትና በትጥቅ ግዢ ላይም ልዩነቶች ነበሩ፡፡ የጦርነቱ አላማና ስትራተጂ ምን መሆን አለበት በሚለዉ ላይም አንድ ዓይነት መግባባት አልነበረም፡፡

ጦርነቱ አንዴ ከተጀመረም በኋላ በመሃል የሚነሱ አለመግባባቶችም ነበሩ፡፡ ሰራዊታችን የሻዕቢየን ሰራዊት እያሳደደ በነበረበት ወቅት ማጥቃቱን አቁሞ ወደ ኋላ እንዲመለስ ሲደረግም በዉሳኔዉ ደስተኛ ያልነበሩ ነበሩ፡፡ የኤርትራ ሰራዊት በሚፈለገዉ ደረጃ አልተደመሰሰም በሚልም ሰፊ ልዩነት ነበር፡፡ በመጨረሻም የድንበር ከሚሽኑ ዉሳኔ ላይም ዉሳኔዉን ተቀብሎ በመሄድና ዉሳኔዉን እምቢተኛ የመሆን የአቋም ልዩነት ነበር፡፡

ከሁሉም በላይ ሰፊ ልዩነት የተፈጠረዉ ከዚህ ቀደም አለአግባብ አሳልፈን የሰጠነዉን የባህር በር ጉዳይ አሁን እልባት መስጠት አለብን የሚል አቋም ባላቸዉና የአስብ ጉዳይ ጨርሶ እንዲነሳባቸዉ በማይፈልጉ መካከል የተፈጠረዉ ሰፊ ልዩነት ነዉ፡፡ ከጦርነቱ ጋር በተያየዘ ለዉዝግብና ለጠብ መነሻ ከሆኑ በርካታ ጉዳዮች መካከል ዛሬም ድረስ መግባባት ያለተፈጠረበት እንዲያዉም በቆየ ቁጥር የበለጠ የልዩነት መነሻ ሆኖ አስካሁንም የዘለቀ ጉዳይ ቢኖር ይሄዉ የባህር በር ጥያቄ ይመስለኛል፡፡

በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከገዥዉ ፓርቲ ጋር ልዩነት የነበራቸዉ ሁሉ በሂደት ወደ አንድ አመለካከት መምጣት የቻሉ ቢሆንም እስካሁንም የጋራ መግባባት ሊያዝ ያልተቻለበት ብሄራዊ ጉዳይ ቢኖር የባህር በር መዉጫ ጥያቄ ነዉ፡፡ የባህር በር ጠቀሜታ ላይ ልዩነት የለም፡፡ የባህር በር የግድ ያስፈልገናል የሚሉት ይሄን ፍላጎት እንዴት እዉን ማድረግ እንደሚቻል የሚሰጡት የመፍትሄ መንገድ የለም፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ የወደብና የባህር በር መዉጫ ጉዳይን ገሸሽ የሚሉ ወገኖች የተሻለ መፍትሄ ሲያቀርቡ አይታዩም፡፡ ልዩነቱ ግን እንደቀጠለ ነዉ፡፡ ከላይ በጥቅል የተጠቀሱት ልዩነቶችና አለመግባባቶች በገዢዉ ፓርቲና በመንግስት አመራሮች ዉስጥ ብቻ ሳይወሰኑ በመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች ዉስጥም ተንጸባርቆ እንደነበር እናስታዉሳለን፡፡

በዚህ ጦርነት ላይ ዙሪያ የተፈጠሩ ልዩነቶች ምን ያህል ከባድ እንደሆኑ ማሳያ የሚሆነዉ በመሪ ድርጅቱ አመራሮች ዉስጥ መከፋፈል በመፈጠሩና በዚያ ጦስ ለዘመናት ካገለገሉበት ድርጅት መወገዳቸዉ ነዉ፡፡ ይሄዉ ክስተት በሰራዊቱ አዛዦችንም የነካ ነዉ፡፡

በዚህ መሰረት በዚሁ የጦርነቱ ጦስ ከሰራዊቱ ለመሰናበት ከበቁት መካከል ኤታማዦር ሹም ሌ/ጄ ጻድቃን ገ/ተንሳይ፤ የመከላከያ አስተዳደር ዋና መም ሃላፊ የነበሩት ሜ/ጀ ታደሰ ጋዉና እና የኢፌድሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩት ሜ/ጄ አበበ ተ/ሃይማኖት (ጆቤ) ይገኙበታል፡፡ የሌሎቹን ትቼ ጄ/ል አበበን ለአብነት ከጠቀስኩ በቂ ይመስለኛልና ወደሳቸዉ ላምራ፡፡

ሜ/ጄኔራል አበበ በሻዕቢያ ሰራዊት የመደምሰስና ከተቻለም የሻእቢያ አመራርን በኃይል የማስወገድ ጉዳይ ላይ ከሁሉም በላይ ደግሞ የባህር በር የማስመለስ ጉዳይ ላይ ከአመራሩ ጋር ሰፊ ልዩነት እንደነበራቸዉ አንዳንድ ፍንጮችን የተመለከትኩት ገና ጦርነቱ እንደተጀመረ ሰሞን ጀምሮ ነዉ፡፡

አየር ኃይል አዛዥ የነበሩትን ጄ/ል አበበን ጦርነቱ እንደተጀመረ ሰሞን የአየር ኃይል መኮንኖችን ሰብስበዉ ስለወረራዉና ቀጣይ የጦርነቱ ዝግጅት ማብራሪያ  በሚሰጡበት ወቅት የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የጦርነቱ የፖለቲካዊ ግቡ ምን እንደሆነ ሰራታችን ምናልባት ድል ከቀናዉ የት ድረስ መዝለቅ እንዳለበት ጦርነቱ አበቃ የሚባለዉም አሰብ ወደብ፤ አስመራ ፤ ወይንም የት ስንደርስ እንደሆነ  ጥያቄ መጠየቄን በስብሰባዉ ላይ የነበሩ ብዙዎቹ ያስታዉሳሉ፡፡

በዚያም ወቅት ለዚህ ጥያቄ የጄ/ል አበበ ምላሽ ወይም ሪአክሽን አቋማቸዉን ግልጽ ያደረገ ነበር፡፡ ያን በዚህ መንገድ ለመረዳት ባልበቃም በኋላ ልዩነት መፈጠሩን ካወኩ በኋላ ነዉ የጆቤ መልስ ለመስጠት የማመንታታቸዉ ምስጢሩ የተገለጸልኝ፡፡ ጄ/ል አበበ በወቅቱ በቀጥታ መልስ መስጠቱን አልፈለጉም፡፡ ጥያቄዬን በዝምታ ማለፍም አልቻሉም፡፡

ያሉት ነገር ቢኖር “ጥያቄዉ በጣም ጠቃሚ ነዉ፡፡ ሆኖም  አሁን መልስ ከመስጠት ይልቅ ሁላችሁም ከዚህ ስብሰባ በኋላ በየግላችሁ አስቡበትና እኛም ከሚመለከተዉ ጋር ተነጋግረን መልስ እንሰጣችኋለን” ነበር ያሉት፡፡ ጆቤ በቀጥታ መልስ ከመስጠት ይልቅ ለሌላ ግዜ የቀጠሩት ለጥያቄዉ የሚመጥን መልሱን ስለማያዉቁ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ለጦርነቱ የተቀመጠዉ ግብ ላይ ያላመነቡበት ነገር ስለነበረ ነዉ፡፡

በወቅቱ በስብሰባዉ ላይ የነበሩት የአየር ኃይሉ ም/አዛዥ አሁን በህይወት የሌሉት ጄ/ል ኃይሌ ጥላሁን የጆቤ ምላሽ አስቆጥቶአቸዉ ከተቀመጡበት በድንገት በመነሳት ቁጣ በተቀላቀለበት  አነጋገር “ሌላ ቀጠሮ መስጠት አያስፈልግም፤ መልሱ ግልጽ ነዉ፡፡ መንግስት በግልጽ ያስቀመጠዉ የጦርነቱ ግብ አለ፡፡ እኛ የኤርትራን ሉአላዊነት በመድፈር ለመዉረርና ቅኝ ግዛት ለማድረግ አልተነሳንም፡፡ ወደ ጦርነት የምንገባዉ የተነጠቅነዉን  ለማስመለስ ነዉ፡፡ …..ወዘተ” በሚል በቁጣ ተናገሩ፡፡ ጆቤ የጄነራሉን መለስ እንዳልሰሙ ሆነዉ ችላ ብለዉ ከማሳለፍ ዉጭ አጸፋ ምላሽ አልሰጡም፡፡

ይሄ ነገር ድጋሚ ሳይነሳ ቆይቶ በሌላ ግዜ መቀለ ላይ በነበረ ጥቂት ስታፎች ብቻ በነበርንበት ስብሰባ ላይ አሁንም መልሼ ጆቤን ተመሳሰይ ጥያቄ ጠይቄ የነበርኩ ብሆንም ጥያቄን እንዳልሰሙ በዝምታ ከማለፍ በስተቀር የተለየ ምላሽ አልሰጡም፡፡ ለስብሰባዉ ካበቃ በኋላ ግን የጆቤ አማካሪ ሆነዉ እየሰሩ የነበሩት ጄ/ል ተጫነ መስፍን ለብቻ ጠርተዉኝ “አንተ ሰዉ ምንነካህ ይሄን ጉዳይ ለምን አትተወዉም?፡፡ ይሄ ጉዳይ እኮ ችግር ሳይኖርበት አይቀርም፡፡” በማለት በአባታዊ ተግሳጽ ተቆጡኝ፡፡

በወቅቱ በጉዳዩ ዙሪያ ምን ችግር እንዳለ ባይገባኝም በኋላ እንደተረዳሁት ግን ጆቤ ቢያንስ የባህር በር (አሰብ ወደብን) ለማስመለስ ጽኑ ፍላጎት እንደነበራቸዉ ነገር ግን መንግስትን ላለማሳጣትም ይሁን ወይንም ምንም ማድረግ እንደማይችሉ በመረዳት መሆኑን ባላዉቅም ሁኔታዉን በዝምታ ማለፋቸዉን ነዉ፡፡ ጦርነቱ አስከሚያበቃ ድረስ በነበሩ ግዜያት ከዚህ አቋማቸዉ ወይም ፍላጎታቸዉ ጋር የሚጣጣም የተለየ ትእዛዝ ወይም መመሪያ ሲሰጡ አላስታዉስም፡፡ በጦርነቱ አካሄድ ላይ ከመንግስት ፍላጎት ዉጭ ያፈነገጠ በተግባር ያደረጉት አንድም የተለየ እንቅስቃሴ አልነበረም፡፡ በአየር ኃይሉ ግዳጅ አፈጻጸም ላይ በቀጥታም ሆነ በተተዘዋዋሪ ከሳቸዉ ጋር ግኑኝነት ለነበረን አመራሮች ከመንግሰት ፍላጎት ጋር የሚጋጭ የተዛባ ትእዛዝ ወይም መመሪያ መስጠታቸዉን አላስታዉስም፡፡

ለማንኛዉም ይሄን ጉዳይ ያነሳሁት በጦርነቱ ዙሪያ በተቀመጠዉ ግብና በአፈጻጸሙ ላይ በሀገሪቱ አመራር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተወሰኑ ወታደራዊ ልሂቃኑ አካባቢም ልዩነት እንደነበረና ወደ ጦርነቱ ሲገባም ከነልዩነቱ እንደነበር  ለመጠቆም ነዉ፡፡ ይህ ልዩነት በጦርነቱ አካሄድ ላይ የራሱን ተጽእኖ መፍጠር አለመፍጠሩን እርግጠኛ ሆኘ መናገር አልችልም፡፡

ጦርነቱ ተራዝሞ ቢሆን ኖሮ ልዩነቱ በግልጽ በመዉጣት ወደ ተዋጊዉ ሰራዊትም በመዝለቅ በሚፈጠረዉ የአቋም ልዩነት ለከፍተኛ አደጋ ሊዳርገን ይችል እንደነበር እገምታለሁ፡፡ ደግነቱ ግን ጦርነቱ በአጭሩ መቀጨቱ ሊፈጠር ከሚችል አደጋ አድኖናል ማለት እችላለሁ፡፡

የኤርትራን ሰራዊት ለመደምሰስ ተብሎ  ወደ ዉስጥ የመግፋት ጉዳይ ሊያመጣ ይችል ከነበረዉ ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ የከፋ ሊሆን በቻለ ነበር፡፡  ምክንያቱም፡-

አንደኛ:- ኤርትራን የመቆጣጠር ወይም ኤርትራ ዉስጥ የመሰንበት ጉዳይ ወደ ጦርነቱ ስንገባ እንደ ዓላማ ያልያዝነዉና ተገቢም ባለመሆኑ፤

ሁለተኛ:- የኤርትራን አመራር ለኛ ፍላጎት በጉልበትና በኃይል የማስገዛት ዓላማ ተገቢነት የሌለዉና የረባ ጠቀሜታም ስለማያመጣልን ነዉ፡፡  ስለዚህ ጉዳይ ክላስዊትዝ (“we may/should not need to render the enemy powerless, in order to impose our will on the enemy…) ብሎ ነበርና፡፡

ሶስተኛ:- አንዳንድ ሰዎች ኤርትራን ተቆጣጥረን አገዛዙን ካስጨነቅነዉ ድርድሩ በኛ ፍላጎት መሰረት እንዲያልቅ ሊያግዘን ይችል ነበር ቢሉም ነገር ግን የሰዉ መሬት ይዘን መደራደር በድርድሩ ላይም ይሄን ያህልም በጎ አስተዋጽኦ የማያመጣና እንዲያዉም ሊጎዳን የሚችል ነበር፡፡ ለነገሩ የአልጄርሱ ስምምነት የተደረገዉም እኛ በኤርትራ ግዛት ዉስጥ እያለንና ወታደራዊ የበላይነት በነበረን ወቅት ነበር፡፡

አራተኛ:- የኤርትራን መሬት ይዞ መቆዬቱ ከኤርትራ ህዝብ ጋር ለዘለቄታዉ የሚያጣላን በመሆኑ፡-

አምስተኛ:- የሌላዉን አገር መንግስት በኃይል ለመቀዬር ማሰብ (enforced regime change) በራሱ ችግር ያለበት አስተሳሰብ በመሆኑ ፤ምክንያቱም የኤርትራ ህዝብ የቱንም ያህል ኢሳይያስን ቢጠላ ከፍላጎቱ ዉጭ በባእድ ጦር ግፊት አገዛዙ እንዲወገድ የሚፈልግ ስለማይመስለኝ ነዉ፡፡

ስድስተኛ:- ሰራዊታችን የበለጠ ወደፊት በገፋና በጠላት ድንበር ዉስጥ የበለጠ በቆዬ መጠን ከፍተኛ ኪሳራ ሊያስከትልበት ስለሚችል  በእጃችን የገባዉን ድልም በሂዴት ልንነጠቅ እንችል ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ ያገኘነዉን አለም አቀፍ ድጋፍ አሳጥቶን በተቃራኒዉ ለከፍተኛ ማዕቀብ ሊዳርገን የሚችል ነበር፡፡

5/ የሻዕቢያን አገዛዝ በማስጨነቅ ለኛ ፍላጎት ተገዢ ለማድረግ ተብሎ በኤርትራ ግዛት የመቆየት ጉዳይ

በዚህ ረገድ ሲሰጡ የነበሩ አስተያየቶች በእንድ በኩል ሰራዊታችን የኤርትራ ግዛት ዉስጥ የተወሰነ ግዜ እንዲቆይ በማድረግ በተለያዩ መልኮች የሚገለጽ ጫና በማሳደር ሻእቢያን ለፍላጎታችን ተገዥ ማድረግ እንችል ነበር የሚል ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የኤርትራ ህዝብም ቢሆን ሻዕቢያ በለኮሰዉ ጦርነት እጅግ በመሰላቸቱና ሻእቢያን ክፉኛ በመጥላቱ በግዛታቸዉ ዉስጥ መቆየታችንንም ሆነ አገዛዙን ለመቀየር በሚደረገዉ ጥረት ብናግዛቸዉ አንዳችም ተቃዉሞ አያሰሙም ነበር የሚል ነዉ፡፡

ይህን መነሻ በማድረግ የሰራዊታችንን ከኤርትራ ግዛት በፍጥነት ለቆ መዉጣቱን እንደ ስህተት እንዳንዶቹ ደግሞ እንደ ክህደት የቆጠሩም ነበሩ፡፡ የዚህ ዓይነት አቋም የነበራቸዉ ሰዎች በጠላት ግዛት ዉስጥ መቆዬትን ህጋዊ ጣጣዉን ወደ ጎን ትተን እንደዚሁ በወታደር ዓይን ብናዬዉ እንኳን ከከፈልነዉ መስዋእትነት የበለጠ መክፌል ብቻ ሳይሆን አስከነጭራሹ በሽንፈት ተዋርደንም ልንባረር እንደምንችል የዘነጉ ይመስለኛል፡፡

በሰዉ አገር ዉስጥ ወይም ጠላት ባልነዉ አገር ህዝብ መሃል ሆኖ መዋጋት አደገኛ መሆኑን መንግስት ከበቂ በላይ ልምድ ያለዉ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ዉስጥ በጥልቀት እንዲገባ ተደርጎ በያዘዉ የጠላት ይዞታ ዘለግ ላለ ጊዜ እንዲቆይ ቢደረግ ኖሮ በሰላም ተመልሶ መዉጣት ስለመቻሉ ማንም በርግጠኝነት መናገር አይችልም፡፡ ሰራዊታችን ወደ ፊት በገፋ ቁጥር መስዋእትነቱና ኪሳራዉ እየጨመረ ስለሚሄድ  በእጃችን ገብቶ የነበረዉን ድል ያለዉዴታችን  ልንነጠቅም እንችል ነበር፡፡

ለነገሩ ወደ ፊት መግፋት ብንችል እንኳን አስከዬት ድረስ ነበር መሄድ የነበረብን? አስመራ ፤ ምጽዋ፤ ሳዋ፤ ወይስ ናቅፋ ድረስ? የጠላትን መሬት ተቆጣጥረን እንቆይ ከተባለም ለምን ያህል ጊዜ ነዉ መቆዬት የሚገባን? ለጊዜዉ ድል ተገኝቷል፤ ጠላት እየሸሸ ነዉ ተብሎ በጭፍን ወደ ዉስጥ መግባት የቀለለዉን ያህል ለቆ መዉጣቱ ቀላል ላይሆን ይችል ነበር፡፡

ጦርነቱ ዉስጥስ ለምን ያህል ጊዜ መቆዬት እንችል ነበር? ጦርነት በተራዘመ ቁጥር በሁሉም ረገድ ኪሳራዉ እየበዛ እንደሚሄድ የዘነጋነዉ ይመስላል፡፡ በታሪክ”የፓይሩስ ድል” (pyrrus victory)ተብሎ እንደሚጠራዉ ድልን በማንኛዉም ኪሳራ ለማምጣት ተብሎ ሰራዊቱ እስከሚያልቅ ድረስ በጭፍን በዉጊያ መቀጠል በአሁኑ ዘመን ፈጽሞ የሚያዋጣ አይደለም፡፡

የጥናታዊቷ ቻይና ወታደራዊ ጠበብት ሳን ዙ(453-221 B.C.) እንደሚለዉ “ጥሩ የጦር መሪ (ጄነራል) ድልን ያለ አንዳች ጦርነት ማግኘት የሚችል ነዉ፡፡ የትኛዉም አገር ቢሆን ከተራዘመ ጦርነት ጥቅም አያገኝም” ነበር ያለዉ፡፡  በተመሳሳይ ሁኔታ ልክ እንደ ሳን ዙ የፕሩሺያዉ እዉቅ ወታደራዊ አሳቢ ክላዉስዊትዝ የጠላትን ሰራዊት የዉጊያ ፍላጎት ማሳጣት እንጂ ሰራዊቱን እንዳለ መደምሰስ ተገቢ እንዳልሆነ ያስረዳል፡፡

በ2ኛዉ የአለም ጦርነት ወቅት (በታላቁ የአርበኝነት ጦርነት )የሶቭዬት ጦር ባልተዘጋጀበት መጥፎ አጋጣሚ  የናዚ ጄርመን ጦር ምንም የረባ መከላከል እንኳን ሳይገጥመዉ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ በርካታ የሶቭዬት ግዛቶችን ለምሳሌም  ቤይለሩሲያን፤ ኡክሬይንን፤ የባልቲክ ሪፖብሊኮችን (ክልሎችን) ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮና በከፊል ደገሞ የሩሲያን ሪፖብሊክ (በዚያን ወቅት አንድ ክልል ነበረች) ግዛት በእጁ አስገብቶ ከዋናዉ ከተማ ከሞስኮ በቅርብ ርቀት የቤተ-መንግስቱን የክሬምሊንን ህንጻ ማዬት በሚያስችለዉ 25 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ደርሶ እያለ በኋላ የሶቭዬት ህብረት ህዝብና ሰራዊቱ በአደረጉት ርብርብ ከጀርመን ወራሪ ሰራዊት በህይወት ተርፎ ወደ ሃገሩ የተመለሰዉ ለወሬ ነጋሪ ያህል ብቻ የሚሆን ጥቂት እድለኞች ብቻ ነበሩ፡፡  አብዛኛዉ ተገደለ፡፡  በጣም በርካታዎቹ ተማረኩ፡፡

ከዚያ በኋላ የሶቭዬት ቀይ ጦር በማጥቃቱ በመበረታታቱ በድል ላይ ድልን እያገኘ የናዚ መቀመጫ ወደ ሆነዉ በርሊን ድረስ በመዝለቅ የናዚን ስርአት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መንኮታኮት ከፍተኛ ሚና ለመጫወት እንዳበቃዉ ይታወሳል፡፡ ታዲያ እኛም የዚህ ዓይነቱ ክፉ እድል እንደማይገጥመን እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን?

ሌላዉ በአንዳንድ ወገኖች እንደ ቀላል እየተቆጠረ የነበረዉ ከኃያላኑ መንግስታት በተለይም ከአሜሪካ መንግስት በየጊዜዉ ሲሰጥ የነበረዉ ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያን ነዉ፡፡ ምንም ጠቀሜታ ለማናገኝበት ነገር ጦርነቱን ወደ ዉስጥ ገፍተንበት እንደ አንዳንዶች ምኞት ሻዕቢያን ከስልጣን ለማዉረድ ብንሞክር ሊጣልብን ይችል የነበረዉን ማዕቀብ መቋቋም የምንችልበት አቅም አይኖረንም ነበር፡፡

ጭራሽ አስመራ ገብተን መንግስትን ለመገልበጥ ብንሞክር ኖሮማ አሜሪካ በማእቀብ ብቻ ሳትገደብ ወታደራዊ ኃይል አስከመጠቀም ልትደርስ እንደምትችል መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም፡፡ በዚያን ወቅት እኮ አሜሪካ ከኛ መንግስት ይልቅ ለኤርትራ የመወገን አዝማሚያ ይታይባት እንደነበር በኛ መንግስት በሚገባ የሚታወቅ ነበር፡፡

አንዳንድ ሰዎች አይናችንን ጨፍነን ጦርነቱን ለምን አልቀጠልንም ከሚል ቁጭት ይመስላል ማዕቀብ ቢደረግብንም እንኳን ይሄን ያህል የተጋነነ ጉዳት አያስከትልብንም ነበር ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይሄ ግን የተሳሳተ አመለካከት ይመስለኛል፡፡

በደርግ ዘመን የሶማሊያ ጦር በእብሪት አገራችንን ወርሮ ህዝባችንን ያለምህረት ሲጨፈጭፍ እያየች አሜሪካ ራሳችንን ለመከላከል እንኳን እንዳንችል አድርጋ አሰቀድሞ ገንዘብ የተከፈለበትን መሳሪያ መከልከሏ ሳያንስ ለዚያድ ባሬ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መሳሪያ በማቀበልና  የሞራል ድጋፍ በመስጠት ስታበረታታ እንዳልነበረችና  የወራሪዉ ጦር አስከ ድሬዳዋ ድረስ እንደደረሰ ሁሉ እያወቀች በዝምታ እያዬች ቆይታ እኛ እንደምንም ብለን ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋግረን የወራሪዉን ጦር ማሳደድ ስንጀምር ማጥቃቱን እንድናቆም ከትእዛዝ የማይተናነስ ማስጠንቀቂያ ነበር የሰጠችን፡፡

ሌላዉ ቀርቶ የጦር መሳሪያ በማቀበልና በምክር ሲረዳን የነበረዉ የሶቭዬት መንግስት ሳይቀር ከአሜሪካ መንግስት በተደረገበት ጫና ሳቢያ የሶማሊያን ጦር እንዳንበቀልና ወደ ሶማሊያም ዘልቀን እንዳንገባ ነጋ ጠባ ይጨቀጭቁ ነበር፡፡  በወቅቱ ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም የሶማሊያን ጦር የመበቀል ጽኑ ፍላጎት የነበራቸዉ ቢሆንም ነገር ግን የሶቭዬት ባለስልጣናት ጎትጎታ በተለይም የአሜሪካንን ማስፈራራት በጭራሽ መቋቋም እንደማይችሉ በመረዳታቸዉ ወራሪዉ ጦርን የመደምሰሱ እቅድ እንዳይተገበር ይልቁንም  ለወራሪዉ ጦር መንገድ ተከፍቶለት በሰላም ለቆ እንዲወጣ ለማድረግ ተገደዉ ነበር፡፡

በወቅቱ የኛ ሰራዊት የሶማሊያን ወራሪ ሰራዊት ለመደምሰስ ብቃቱም ቁጭቱም እያለዉ የአሜሪካንን ቁጣ በመፍራት ብቻ ሳይደረግ ቀርቷል፡፡ የሶማሊያ ወራሪ ሰራዊት የጅግጅጋን ከተማ ቤቶች የጣራ ልባስ ቆርቆሮ፤ በርና መስኮት ሳይቀር እየነቃቀሉና ከየቤቱ የዘረፉትን ንብረት ሁሉ ይዘዉ ሲሄዱ እያዩ ከመብገን ዉጭ የኛ ሰራዊት የመንግስት ትዕዛዝ ስለሆነባቸዉ ብቻ በዝምታ አሳልፈዉታል፡፡

አሜሪካ በዉጭ ግኑኝነት ፖሊሲዋ በኢትዮጵያና ከኤርትራ ጋር ሚዛኑን የጠበቀ እኩል ወዳጅነት ለመፍጠር  መሞከሯ ባይቀርም በተግባር ሲታይ ግን ወደ ኤርትራ ያደላ ነበር፡፡ ይሄ ሁኔታ አስከቅርብ ጊዜ ድረስ ቀጥሎ ነበር፡፡ ለምሳሌ ጦርነቱ እንደተቀሰቀሰ ኢትዮጵያ ለደህንነቷ ሰግታ ኤርትራዊ ዜግነት ያላቸዉን ወደ ሀገራቸዉ መሸኘቷን ተከትሎ የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያን እርምጃ የሚተች ጠንከር ያለ መግለጫ ማዉጣቱ ይታወሳል፡፡

በአንጻሩ የኤርትራ አይሮፕላኖች በመቀሌ አይደር ትምህር ቤት ህጻናት ላይ ያደረሱትን አረመናዊ ጭፍጨፋ አስመልክታ አሜሪካ ድርጊቱን በይፋ አላወገዘችም፡፡ ከዚያ ይልቅ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝምታን መርጣለች፡፡ በተጨማሪ የኤርትራ ወታደሮች ዛላምበሳን ሙሉ በሙሉ በዶዘርና በፈንጂ ሆን ብለዉ አፈራርሰዉ ወደትቢያ መቀየራቸዉንና በትግራይ በጦርነቱ ቀጠና ከ170000 ባለይ ነዋሪዎች ከቀያቸዉ መፈናቀላቸዉን አሜሪካ እያወቀች ድርጊቱን አላወገዘችም፡፡

በጦርነቱ ሂዴትም አሜሪካ ወደ ኤርትራ ያደላ አቋሟን በተለያዩ አጋጣሚዎች ስታንጸባርቅ ነበር፡፡ እንግዲህ አሜሪካ ሁልጊዜም ኢትዮጵያ ለዉጭ ወረራ በተጋለጠችና አደጋ ላይ በወደቀች ቁጥር ለወራሪዉ ጥብቅና የመቆሟና በኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደሯ በተደጋጋሚ የታዬ ጉዳይ ነዉ፡፡ በሶማሊያ ወረራ ወቅት ለወራሪዉ ለዚያድባሬ ድጋፍ ማድረጓ ለዚህ ማሳያ ነዉ፡፡

ዛሬ አሜሪካ ለኢትዮጵያ በሁሉም ነገር ወዳጅ መሆኗ ያጋጣሚ ሳይሆን በኢትዮጰያ መንግስት ዉስጣዊ ጥንካሬ የመነጨና በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ጋር መወዳጀት ለራሷ ለአሜሪካም እንደሚበጃት በመገንዘቧ እንጂ ለኛ  የተለየ ፈቅር ስላላት እንዳልሆነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡

ለማንኛዉም በጦርነቱ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ለአሜሪካ ማስፈራሪያና ዛቻ ተንበርክኮ ነበር የሚለዉ ትችት ኃላፊነት የጎደለዉና ሚዛናዊ ያልሆነ ትችት ይመስለኛል፡፡ መንግስት በወቅቱ ማስጠንቀቂያዉን ችላ በማለት አልህ ቢጋባ ኖሮ ሊፈጠር በሚችለዉ ቀዉስ ተመልሰን መንግስትን መዉቀሳችን አይቀርም ነበር፡፡ ስለዚህ መንግስት በነበረበት ኃላፊነት ጥንቃቄ ማድረጉ የሚያስመሰግነዉ እንጂ  ሊያስወቅሰዉ የሚችል አይደለም፡፡

የሻቢያን ሰራዊት እንዳለ መደምሰስና ህዝቡንና ሀገሪቱን ያለ ወታደር የማስቀረት ሃሳብ በራሱ የተዛባ ከመሆኑም ሌላ የኤርትራን ህዝብ አንገት በሃፍረት የሚያስደፋና የሚያሸማቅቅ በመሆኑ በፍጹም የሚደገፍ አልነበረም፡፡ ድል የተሸናፊን ወገን ሞራልና ክብር የሚነካና አዋራጅ መሆን የለበትምና፡፡

6/ ጦርነቱ ያስከተለብን ዘርፈ ብዙ ጉዳት

ለሁለት ዓመት አካባቢ በዘለቀዉ ጦርነት እኛም ሆን ኤርትራ እንደሀገር የደረሰብን ዘረፈ ብዙ ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ የእነሱን ለነሱ ትተን በኛ በኩል በወታደራዊ፤ በሰብአዊ ፤በኢኮኖሚያዊዉ፤ በልማት ፤ በማህበራዊና በፖለቲካዊ መልኩ የሚገለጹ በርካታ ጉዳቶች አድርሶብናል፡፡

ከሁሉም በላይ ተጠቃሽ የሚሆነዉ በዚሁ ጦርነት ጦስ  በአስርሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቻቸን በጦርነቱ በጀግንነት ሲፋለሙ መዉደቃቸዉና በርካቶች ቁስለኛ መሆናቸዉ፤እንዲሁም በሻዕቢያ አይሮፕላኖች በመቀለ አይደር ት/በት ላይ በተደረገ አረመናዊ ጭፍጨፋ 58 ህጻናት ተማሪዎች የሞቱበትና በቁጥር 185 አካባቢ የሚሆኑ ተማሪዎችና ሌሎች ሰዎች ከፍተኛ የአካል ጉዳት ተጎጂ የሆኑበት ዘግናኝ ክስተት መቼም ቢሆን የሚረሳ አይደለም፡፡

በተጨማሪ  በጦርነቱ ቀጠና የነበሩ አርሶአደሮች በሻዕቢያ በግፍ መጨፍጨፋቸዉና 350 ሺህ የሚጠጋ ህዝብም ከመኖሪያ ቀዬዉ ተፈናቅሎ ለችግር የተጋለጠበትና በተለይ በዛላአምበሳ ደግሞ ከተማዉ እንዳለ በዶዘር፤ በመድፍና በፌንጂ ሆን ተብሎ የፈራረሰበት ከስተት ጦርነቱ ያደረሰብንን ጉዳት በሚገባ የሚያሳይ ነዉ፡፡ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በተመለከተም በጦርነቱ መካካል ከልማት ስራችን ላለመታቀብ መንግስት ጥረት ማድረጉ ባይቀርም መጀመሪያዉኑ ደካማ የነበረዉ ኢኮኖሚያችን ይበልጥ  መንኮታከቱና  የልማት ስራችን መቀዛቀዙ የግድ ነበር፡፡

በጦርነቱ ሳቢያ አስተማማኝ ደህንነት አለመኖር ምክንያትም ቱሪዝም እጅግ በመቀዛቀዙ ማግኘት ይገባን የነበረዉን ቀላል የማይባል የወጭ ምንዛሪም አሳጥቶናል፡፡ ጦርነትና ልማት በጭራሽ አብረዉ የማይሄዱ አጥፊና ጠፊ በመሆናቸዉ በኢኮኖሚያችንና በተለመደዉ የህዝባችን ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶብናል፡፡ ለጦርነቱ ማካሄጃ መሳሪያ ለመግዣ ያወጣነዉ የዉጭ ምንዛሪም ቀላል አልነበረም፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ማዉጣታችንን የዉጭ መረጃ ምንጮች በስፋት ሲዘግቡት ቆይተዋል፡፡ ቢቢሲ በጦርነቱ መጨረሻ አካባቢ ባሰራጨዉ ዜና ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ጥናት ኢንስትቲዩት አገኘሁ ብሎ እንደጠቀሰዉ መረጃ ከሆነ  አገራችን ሁለት ዓመት አካባቢ የዘለቀዉ ጦርነት  ምክንያት ከ2.9 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ  እስወጥቷቷል፡፡

ጦርነቱ እንደተጀመረ መንግስት በፊት ያልነበረ ከፍተኛ የሰዉ ኃይል፤ መሳሪያና የፋይናነስ አቅም ጦርነቱን ለማገዝ ሞብላይዝ ማድረግ ስለነበረበት ብዙ ዉጭ አስወጥቶታል፡፡ የሰራዊቱ ቁጥርም በፊት ከነበረዉ 60 ሺህ አካባቢ ከነበረዉ ወደ 350ሺህ ከፍ እንዲል ተደርጓል፡የመከላከያ በጄቱም ከጦርነቱ በፊት ከነበረዉ ፡95 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ($95m) ወደ 777 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር($777m) አድጓል፡፡

በዚህ መሰረት በወቅቱ የመከላከያዉ  ፍጆታ የአጠቃላይ የሀገሪቱን ባጄት 49.8% ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡ ደግነቱ ጦርነቱን ፈጥነን አጠናቀን ወደ ልማታችን ሳንመለስ ጦርነቱ ዘለግ ላለ ግዜ ቆይቶ ቢሆን ኖሮ ምን ያህል ጉዳት ሊያስከትልብን ይችል እንደነበር ለመገመት አያዳግትም፡፡ ”

ከጦርነቱ በፊት በሀገሪቱ ዉስጥ ሰፍኖ የቆየዉን ሰላማዊና  የተረጋጋ ሁኔታ ተማምነዉ መጥተዉ የነበሩ የዉጭ ኢንቬስተሮች በጦርነቱ ምክንያት ለቀዉ በመዉጣታቸዉ ቁጥራቸዉ እጅግ ሊያሽቆለቁል ችሎአል፡፡ ከጦርነቱ በፊት በቁጥር 217 የሚሆኑ ንብረትነታቸዉ የዉጭ ባለሃብቶች የሆኑና ስራ የጀመሩ ፕሮጄክቶች በጦርነቱ ምክንያት አብዛኛዎቹ ስራ በማቆማቸዉ ቁጥራቸዉ ባንድ ግዜ ወደ 47 አሽቆልቁሎ ነበር፡፡ በተጨማሪ ከጦርነቱ በፊት ስራ ለመጀመር ፈቃድ ወስደዉ ከነበሩ በቁጥር 13700 ከሆኑ የሀገር ዉስጥ ባለሀብቶች መካካል በጦርነቱ ምክንያት ስራ ለመጀመር የቻሉት 1467 ብቻ ነበሩ፡፡

በጦርነቱ ወቅት በዉጭ ባለሃብቶች የተመዘገቡ ኩባኒያዎች ኢንቬስትሜንት መጠን በአማካይ በ800% አካባቢ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ መንግስት በወቅቱ የዉጭ ኢንቬስተሮችን ለማግባባት ብዙ ጥረት ቢያደርግም እነሱ ግን ሁኔታዎች አስከሚረጋጉ በተለይም በሁለቱ አገሮች መካካል የሰላም ስምመነት አስኪደረግ ድረስ  መጠበቅን መርጠዋል፡፡ የቱሪዝም ገቢ መቀነስ በራሱ ጉዳቱ ቀላል አልነበረም፡፡ ከጦርነቱ በፊት የቱሪስቶች ቁጥር በአንድ ዓመት ብቻ 111,371 ጎብኝዎች እንዳልነበሩ በጦርነቱ ወቅት እጅግ አሽቆልቁሎ ወደ 90,847 ወርዶ  ነበር፡፡

ይህ ቁጥር ለሆቴሎች፤ ለትራንስፖርት ዘርፍ ካመለጠን ገቢ ጋር ሲዳበል በዉጭ ምንዛር ገቢያችን ላይ ያስከተለዉ ጉዳት እጅግ ከፍተኛ እንደነበር ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ፤በጦርነቱ ሳቢያ የደረሰብን ጉዳት ተዘርዝሮ አያልቅም፡፤በተለይ የዉጭ ተራድኦ ረገድ የደረሰብን ጉዳት እጅግ አስደንጋጭ  ነበር ማለት ይቻላል፡፡  በፊት በየምክንያቱ ያግዜን የነበሩ የዉች ለጋሽና እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ፊታቸዉን በማዞራቸዉ በፊት እናገኝ ከነበረዉ $700m  ወደ  $500m በመዉረዱ የ200 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ቅናሽ አሳይቷል፡፡

በጦርነቱ ወቅት የግብርና ምርት በእጅጉ በመዳከሙ ለምግብ ፍጆታየሚዉል ምርት 62% በመቀነሱ የህዝባችንን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አዳጋች ሆኖብናል፡፡ በወቅቱ የግብርና መቀዛቀዙና በአጋጣሚዉም የድርቅ መከሰት፤እንዲሁም ድሮ ሲንጠቀምበት የነበረዉ የባህር መዉጫና መግቢያ በር (አሰብ ወደብ) በመዘጋቱ እርዳታ ከዉጭ ለማስመጣትና ወጪና ገቢ ንግድ ለማድረግ የማንችልበት ሁኔታ በመፈጠሩ ሀገራችንና ህዝባችንን  ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጉ እርግጥ ነዉ፡፡

በዚህ ላይ ደግሞ ከጦርነቱ ጥቂት ቀደም ቢሎ በአሰብ ወደብ ላይ ተከማችቶ ማጓጓዣ ይጠብቅ የነበረዉ ከ200000 ቶን በላይ የዕርዳታ እህልና 140 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት ልዩ ልዩ ንብረቶች በሻዕቢያ በመዘረፋቸዉ ለኛ ጉዳቱ ቀላል አልነበረም፡፡ መንግስታችን ቢያንስ እህሉን እንኳን አስቦ በቅድሚያ ለማስነሳት ተስኖት ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ሁኔታዉን አስቸጋሪ ያደረገዉ ጦርነቱ በቆየበት ሁለት ዓመታት ዉስጥ እኛም ሆን ኤርትራ ከዉጭ ለጋሾችና አበዳሪዎች አንዳችም እርዳታና ብድር እንዳናገኝ በመከልከላችን ያስከተለብን ቀላል የማይባል ችግር  ነዉ፡፡

ጦርነቱ ካስከተለዉ ኢከኖሚያዊና ማህበራዊ ጉደት ሌላ ፖለቲካዊ ጉዳቱም አጅግ ከባድ ነበር፡፡ ከኤርትራ ጋር በቀላሉ የማይፈታ የጠላትነት ሁኔታ መፈጠሩ እንዳለ ሆኖ በራሳችንም ዉስጥ በተለይም በገዥዉ ፓርቲ አመራሮች መካከል በዚሁ በጦርነቱ ጦስ የተፈጠረዉ መከፋፈል ለበርካታ ነባር የድርጅቱ አመራሮች መልቀቅ ምክንያት ሆኗል፡፤ችግሩ በፖለቲካ አመራሩ አካባቢ ብቻ ሳይገደብ የመከላከያ ተቋሙንም የነካ በመሆኑ ጥቂትም ቢሆኑ ቁልፍ አመራር ላይ የነበሩ የሰራዊቱ አዛዦች ከሰራዊቱ ለመሰናበት አብቅቶአቸዋል፡፡

በዚሁ መከፋፈልና የአመራሮችም መገለልና ከጦርነቱ ጋር ተያያዞ በተፈጠሩ አንዳንድ ቅሬታዎች ምክንያትም በመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ዘንድም የመከፋት ስሜት መፈጠሩ አልቀረም፡፡ በተለይ በገዥው ፓርቲ አመራር ዉስጥ በተፈጠረዉ መከፋፈል ምክንያት ሁኔታዉ ተቃዋሚዎች በጭራሽ ያልጠበቁት መልካም አድል ስለሆነላቸዉ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በተደረገዉ 1997 ምርጫ ገዥዉ ፓርቲ የነበረዉን በርካታ የፓርላማ ወንበር ለማጣት ተገዶአል፡፡

በአጠቃላይ ጦርነቱ ተገደን የገባንበት ቢሆንም በሁሉም ረገድ ያሰከተለብን ጉዳት እጅግ የሚያሳምም ነበር፡፡ የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ  በማንኛዉም ሰበብ ለሚደረግ ጦርነት እጅግ የመረረ ጥላቻ እንዲኖራቸዉ ያደረጋቸዉና ሁልግዜም የጦርነት ነገር በተነሳባቸዉ ቁጥር ክፉኛ የሚያንገሸግሻቸዉ ዋናዉ ምክንያት ይሄዉ በሀገር ላይ የሚያስከትለዉ ዘርፈ ብዙ ጉዳት ስለሚያዉቁ እንደነበር ለመረዳት አያዳግትም፡፡

7/ በጦርነቱ ከተከፈለዉ መስዋእትነት አንጻር ትርፍና ኪሳራዉ

ጦርነቱ በኢትዮጵያ ድል አድራጊት ከተጠናቀቀ በኋላ ብዙ ሰዉ “ከጦርነቱ ምን አገኘን? ምንስ አጣን?” በማለት ትርፍና ኪሳራን ወደ ማስላት ነዉ  የገባዉ፡፡ “ይህን ያህል መስዋእትነት ከፍለን ዬት አለ አሰብ ወደብን ያስመለስነዉ?”፤ “ሻዕቢያን ከስልጣን መቼ አወረድንና ነዉ ድል ተገኘ የምትሉት?”፤ “የሻቢያን ሰራዊትስ መቼ ደመሰስንና ነዉ ስለ አሸናፊነታችን የምታወሩት” “የደማንላትና የሞትንላትስ ባድመ ዬት አለችና ነዉ ስለ ድል ማድረጋችን የምታወሩት” ወዘተ የሚሉ ነበሩ፡፡

የተከፈለዉ መስዋትነት ቀላል ባይሆንም የተገኘዉን ድል ማሳነስ ግን ትልቅ ስህተት ነዉ፡፡  ይሄ ችግር በህብረተሰቡ ዉስጥ ብቻ ሳይሆን በሰራዊቱ ዉስጥም ተንጸባርቆ እንደነበር አስታዉሳለሁ፡፡ ከጦርነቱ በኋላ በተካሄዱ በርካታ የዉይይት መድረኮች ላይ አስቀድሜ የጠቀስኩት የጦርነቱን ድል ላይ አምኖ ያለመቀበል አመለካከት የነበረና ሲሆን በሂደት ግን ሊስተካከል ችሏል፡፡

7.1/ በሻዕቢያ ወረራ ሳቢያ በኃይል የተነጠቅነዉንና ያጣነዉን በኃይል ማስመለስ መቻላችን ትልቅ ድል ነዉ

እንደኛ ያለፍላጎቱ ተገዶ ወደ ጦርነት ለገባ ወገን ድል የትርፍና ኪሳራ ጉዳይ አይደለም፡፡ የጦርነቱ ሰለባ የሆነዉ ወገን ቢቻል በሰላማዊ መንገድ (በድርድር) ካልተቻለም ደግሞ በኃይል መንገድም ቢሆን የተነጠቀዉን ማስመለስ ይጠበቅበታል፡፡ የተነጠቀዉን ለማስመለስ ያለፊላጎቱ ወደ ጦርነት የሚገባ ወገን ከጦርነቱ በፊት የነበረዉን ሁኔታ ማስመለስ ከቻለ ተጨማሪ ትርፍ ፊለጋ መሄድ አይጠበቀበትም፡፡ የራሱን ማስመለስ ከቻለ ከጦርነት ለመዉጣት እንደ በቂ ሁኔታ ነዉ የሚቆጥረዉ፡፡

በሻዕቢያ በተቃጣብን ወረራ የተደፈረዉን ሉአላዊነታችንን ለማስመለስ ያደረግነዉ ጦርነትም ከዚህ አንጻር መታዬት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ከጦርነቱ በፊት የነበረንን በሻዕቢያ ወረራ ሳቢያ ተነጥቀን የነበረዉን በቦታዉ ማስመለስ ችለናል፡፡ ወደ ጦርነት ስንገባ ካስቀመጥነዉ የጦርነቱ ግብ  አንጻር ካየነዉ ያገኘነዉ ድል  የጠበቅነዉንና ማግኘት የሚገባንን ነዉ፡፡

ለምሳሌ ጥቂቶቹን ቀጥዬ ልጥቀስ፡-

* የተወሰደብንን መሬት አስመልሰናል፡፡ በዚህም ሉአላዊነታችንን አስከብረናል፡፡

* የፈረሰዉን መስተዳደር በቦታዉ እንዲተካ አድርገናል፡፡ ለሉአላዊነታችንና ነጻነታችን መግለጫ የሆነዉን ሰንደቅ አላማችንን ነጻ ባወጣነዉ መሬታችን ላይ የድል ዜማ እየዘመርን  በታላቅ ክብር እንድትዉለበለብ አድርገናል፡፡

* የሻዕቢያን የዕብሪት ወረራ በመቀልበስ  የመስፋፋትና የጥገኝነት ህልሙንም አክሽፈናል፡፡

* በሻዕቢያ ሰራዊት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሰናል፡፡  ለወደፊቱ እንዳይደፍረን ትምህርት ሰጥተነዋል፡፡

* ኤርትራ በአለም አቀፍ መድረክ ከፍተኛ ዉግዘት እንድደርስባትና ማእቀብ እንዲጣልባት ማድረግ ችለናል፡፡ በሽብርተኝነት ጎራ እንድትመደብ አድርገናል፡፡ ለዚህ ሁሉ ኤርትራ ለገባችበት ምስቅልቀል ሁኔታ ተጠያቂዉ ራሱ ሻዕቢያ እንጂ የእኛ መንግስት አይደለም፡፡ መንግስት ያደረገዉ ነገር ቢኖር ራሱን ከሻዕቢያ ትንኮሳ አየተከላከለ የሻዕቢያን ድርጊት ለዓለም ማህበረሰብ ማጋለጥ መቻሉ ነዉ፡፡

* ኢትዮጵያ በምትከተለዉ ፌዴራላዊ ስርአት ሳቢያ ትበታተናለች የሚለዉን ሟርት ፉርሽ ያደረገና እንዲያዉም ከምንጊዜም በላይ የህዝቦች አንድነትና ጥንካሬ የታዬበት እንደሆነ በተግባር ያረጋገጥንበት ነዉ፡፡ በዚህ ረገድም የሻዕቢያ ስለእኛ የነበረዉ ግምገማ እጅግ የተሳሳተ መሆኑን እንዲረዳ ማድረግም ችለናል፡፡

* ጦርነቱ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በቀላሉ የማይበጠስ ጠንካራ ትስስር እንዳላቸዉና ቢያንስ  በሀገር ሉአላዊነት ጉዳይ ላይ ህዝቡ ከመንግስት ጎን እንደሚሰለፍ በድጋሚ ያስመሰከረ ነዉ፡፡ ፡

* መከላከያ ሰራዊታችን የሀገሪቱን ደህንነት፤ የሕዝቦችን ሉአላዊነትና ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር የሚችል አስተማማኝ ብቃት ያለዉ መሆኑን ለጠላትም ለወዳጅም ያረጋገጠበት አጋጣሚም  ነዉ፡፡

7.2/ አብዛኛዉ ህዝብ ዋነኛ የጦርነቱ ማጠንጠኛ ድል አድርጎ በብዙ ተስፋ የጠበቀዉ የባህር በር (የአሰብ ወደብ) ጉዳይ መፍትሄ ያገኝ ይሆናል በሚል ነበር

እንደሚታወቀዉ ወደ ጦርነቱ የገባነዉ ወደን ሳይሆን ያለፍላጎታችን ተገደን ነዉ፡፡ ወደ ጦርነቱ ስንገባ የያዝነዉ ዓላማ በሻቢያ ያጣነዉን የማስመለስ ጉዳይ እንጂ ኤርትራን በቅኝ ግዛትነት የመግዛት፡ አሰብ ወደብን የመቆጣጠር፤የሻዕቢያን ሰራዊት ሙሉ በሙሉ የመደምሰስና ስርአት መቀየር አልነበረም፡፡

መንግስት “የጦርነቱ ዓላማ” ብሎ ያስቀመጠዉ ላይ ህዝቡ ምን ያህል ግልጽ ሆኖለት እንደነበር በርግጠኝነት ለመናገር ባልቻልም “ከባድመ ማስለቀቅ” በለጥ ያለ ነገር ለማግኘት ማሰቡና መመኘቱ አልቀረም፡፡ በተለይም “አሰብ ወደብን የማስመለስ” ጉዳይ ከሁሉም የበለጠ ትኩረት የተሰጠበት ስለነበረ ህዝብ በዚህ ረገድ ከጦርነቱ አንድ ነገር መጠበቁ እርግጥ ነዉ፡፡

ከጦርነቱ በኋላ ያ የተጠበቀዉ አለመፈጸሙን ሲረዳ በጦርነቱ የተገኘዉ ዋናዉ ጉዳይ ሁሉ ዋጋ እንደለለዉ ተደርጎ ተቆጠረ፡፡  አስመራ ድረስ ዘልቀን አገዛዙን ከስልጣን አለማዉረዳችንና የሻዕቢያን ሰራዊት ሙሉ በሙሉ አለመደምሰሳችን በህዝቡ ዘንድ እንደጥያቄ የተነሳና የተጠበቀም አልነበረም፡፡ የዚህ ዓይነቱ ዓላማ ካለም ሊኖር የሚችለዉ በፖለቲከኞችና በመንግስት አመራሮች አካባቢ ብቻ ተወስኖ የነበረ ነዉ የሚመስለኝ፡፡

ህዝቡ ግን “ስለ ሰራዊት ድምሰሳና የኤርትራን አገዛዝ ማዉረድ” ጉዳይ ስላልተነገረዉና የሚያዉቀዉ ነገርም ስላልነበር ከጦርነ አልጠበቀም፡፡ ስለዚህ የኢሳይያስ መንግስት ከስልጣን አለመዉረዱን ሲያዉቅ ህዝቡ የተለየ ስሜት አልተሰማዉም፡፡  ከዚህ ይልቅ ህዝቡ በተስፋ የጠበቀዉና ሳይሆን ሲቀር ደግሞ ተገኘ በተባለዉ ድል ላይ ጥያቄ ያነሳዉ የባህር በር (የአሰብ ወደብ) ማስመለስ አለመቻላችን ነዉ፡፡

እንኳን አሰብ ወደብን ማስመለስ ቀርቶ ከነጭራሹ ብዙ ሺህ ሰራዊት ገብረን ነጻ ያወጣነዉን ባድመን ጭምር በተዛባ የፍርድ ዉሳኔ ማጣታችን ህዝቡን እጅግ አበሳጭቶታል፡፡ “እሽ ከሆነስ ሆነና አሰብ ወደብንስ እንኳን እንዴት ማስመለስ አልተቻለም” የሚለዉ ጥያቄም ተደጋግሞ ይሰማ የነበረና ለመንግስትም በጣም አስጨናቂ ሁኔታ ነበር፡፡

መንግስት የህዝቡን ስሜት ሰከን ለማድረግ በባህር ጉዳይ የተለያዩ አመራጮች እንዳሉ ከመግለጽ ባይቆጠብም ህዝቡ ምን ያህል ተቀብሎታል በሚለዉ ላይ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ “ያለ አሰብ ወደብ መኖር ይቻላል” የሚለዉ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ይዘት ያለዉ ረቀቅ ያለ የካድሬ ትንተና ለተራዉ ህዝብ ቶሎ የሚገባዉ አይደለም፡፡ አሰብ ወደብ “ከሸቀጥ ማራገፊያነት” በበለጠ ለደህንነታችን አስፈላጊ መሆኑን ህዝቡ የካድሬ ትንተና ሳያስፈልገዉ ራሱ ጠንቅቆ የሚረዳዉ ነዉ፡፡

ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት የባህር በር ጉዳይ ዳግመኛ የማይነሳ ያለቀለት ጉዳይ ተደርጎ ቢታሰብም የሆነ አጋጣሚ በተከሰተ ቁጥጥር ስለ አሰብ ወደብ ጉዳይ እንደ ገና ማንሳት የግድ እየሆነ መጥቷል፡፡ ወደ ፊትም ምን ያህል ከህዝብ አይምሮ መፋቅ እንደሚቻል አይገባኝም፡፡ የሚገርመዉ ደግሞ በወላጆቻቸዉ ከተነገራቸዉ ዉጭ ስለ አሰብ ወደብ ለማወቅ አንዳችም እድል ያልነበራቸዉ ከ83ዓ/ም በኃላ የተወለዱ ወጣቶች እንኳን ሳይቀሩ ወደብ አልባ መሆናችንን በቁጭት መንፈስ ሲገልጹ መስማት ነዉ፡፡

ስለባህር በር ማሰብና ስለ አሰብ ወደብ መወያየት የጦረኝነት፤ ያለመሰልጠንና የደደብነት ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ የራስ ያልሆነን ነገር የመፈለግ ጉዳይም አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም የመቆም ጉዳይ ነዉ፡፡ የባህር በር ጥያቄ የአንድ ፓርቲ ወይም የአንድ ብሄር የግል ጉዳይ ሳይሆን የመላዉ የኢትዮጵያ ህዝቦች ጉዳይ ነዉ፡፡ የዚህ ትዉልድ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ለመጪዎቹ ትዉልዶችም የማሰብ ጉዳይ ነዉ፡፡

መንግስታችን በተለይ ገዢዉ ፓርቲ ኢህአዴግ በህዝብ የሚወደስበትና የሚመመሰገንበት በርካታ ጉዳዮችን መዘርዘር ቢቻልም የባህር በር ጉዳይ ሲነሳ ግን ህዝቡ በሆዱ ቅያሜ መያዙ እርግጥ ነዉ፡፡ ለኢህአዴግ ከፍተኛ ፍቅር ያላቸወና ስለኢህአዴግ ዓላማ ራሳቸዉን አሳልፈዉ እሰከመስጠት የማይመለሱ ሰዎች ሳይቀሩ የአሰብ ወደብ ጉዳይ፤ የባህር በር አልባ የመሆናችን ጉዳይ ሲነሳ ሽምቅቅ ይላሉ፡፡

ልክ እጅግ የምንወዳቸዉና የምናከብራቸዉ ወላጆቻችን ላይ የሆነ ጉድፍ ወይም እንከን  ሲገኝ የሚሰማን  ዓይነት ስሜት ማለት ነዉ፡፡ ወላጆቻችን ስማቸዉ በክፉ እንዲነሳ አንፈልግም፡፡ ግን ደግሞ የሰሩትን ተገቢ ያልሆነ ጥፋት መደበቅ ሳንችል የምሰማን ጥሩ ያልሆነ ስሜት ዓይነት ማለት ነዉ፡፡

የኢትዮጵያን ህዝብ ለኢህአዴግ ካለዉ አመለካከት አኳያ ደጋፊና ተቃዋሚና ገለልተኛ በሚል በቀላሉ በሶስት ምድብ ብንከፍለዉ ሁሉንም ማለትም ደጋፊዉንም ተቃዋሚዉንም ሆነ ገለልተኛዉን በአንድ ላይ እንዲቆሙ ያደረገ ጉዳይ ቢኖር የባህር በር (አሰብ ወደብ) ጉዳይ ነዉ፡፡ በእኩል ደረጃም ባይሆን ሁሉም በወደብ ጉዳይ አህአዴግን ተቀይመዉታል፡፡

የህዝቡ ቅያሜ መነሻም የኢህአዴግ መንግስት የኢትዮጵያን ንብረት ማስመለስ እየቻለ ፍላጎቱ ስለሌለዉ ብቻ ወደብ አልባ ለመሆን ተገደናል የሚል ነዉ፡፡ ኢህአዴግ (መንግስት) በግድ በጉልበት በጦር ኃይል አሰብ ወደብን መቆጣጠር አለበት የሚል አስተሳሰብ ያለ አይመስለኝም፡፡ የዚህ ዓይነት አመለካከት ካለ እኔ ራሴ  አጥብቄ እቃወማለሁ፡፡ ነገር ግን አየተባለ ያለዉ  መንግስት በህጋዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ  ጥረት ቢያደርግ ያለጥርጥር ሊሳካ ይችል ነበር የሚል ነዉ፡፡

ኢህአዴግ ፍላጎት እንዳለዉ አሳይቶ በህጋዊ መንገድ ለማስመለስ ሙከራ አድርጎ ባይሳካ  ህዝቡ ቅረታ ባልኖረዉ ነበር፡፡ ነገር ግን ፍላጎቱም የለዉም ነዉ እየተባለ ያለዉ፡፡ ፍላጎት የማጣት ጉዳይም ብቻ ሳይሆን ሌሎች አንዳችም የተለዬ የፖለቲካ ዓላማ የሌላቸዉና በሀገር ተቆርቋሪነት ስሜት ብቻ በጉዳዩ ላይ አስተያዬት የሚሰጡ ዜጎችን በክፉ ዓይን ያያል የሚል ነዉ፡፡ አሰብ ወደብን ለባለቤቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ በህጋዊ መንገድ ለማስመለስ በግላቸዉ ጥረት የሚያደርጉ ዜጎችንም ሆን ብሎ ያሸማቅቃል ነዉ እየተባለ ያለዉ፡፡

መንግስታችን ለዬትኛዉም ዓይነት ዓላማ ተብሎ የሚደረግን ጦርነት እንደሚጠላ ይታወቃል፡፡  ጦርነትን ስለሚጠላም የግድ ካልሆነ በስተቀር ወደ ጦርነት አንደማይገባ በተደጋጋሚ ሲገልጽ አድናቆትን አተረፈ እንጂ “ለምን ጦርነት ወዳድ አልሆነም” ብሎ የወቀሰዉ የለም፡፡ ምናልባት ኢህአዴግ ለጦርነት ያለዉ የመረረ ጥላቻ ተጭኖት “የአሰብ ወደብ ጉዳይ ጦርነት ቀስቃሽ ስለሚሆንብኝ ይቅርብኝ” በሚል ከሆነ ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብም ቢሆን ጦርነትን የሚጠላ በመሆኑ መንግስታችን በዚህ ረገድ ሃሳብ ሊገባዉ አይገባም፡፡

ነገር ግን ኢህአዴግ ስለ አሰብ ወደብ ጉዳይ መነጋገር የማይፈልገዉ እዉነት አሰብ ወደብ የኛ ንብረት ስላልነበረ ነዉ? እዉነት አሰብ ወደብ ከግመል መፈንጫነት ያለፈ ሌላ የረባ ጥቅም የሌለዉ ስለሆነ ነዉ? አሰብ ወደብን አንዲትም ጥይት ማስተኮስ ሳያስፈልግ ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ በማግባባት፤በድርድርም ይሁን በመሟገት ለማስመለስ መሞከር ጦርነት ቀስቃሽ የሚሆንበትና ጦረኛ የሚያሰኝበት አግባብስ ምንድነዉ ነዉ?

ኢህአዴግ በወደብ ጉዳይ የመከራከሩን አስፈላነት ባያምንበት እንኳን ለህዝቡ አክብሮት ብሎ የህዝብን ጥያቄ ተቀብሎ አግዙኝ ቢል የኛ መሆኑን በማስረጃ አስደግፈዉ በማሳመን ሊያስፈጽሙ የሚችሉ በርካታ ኢትዮጵያዉያን ምሁራን ይኖራሉ ብዬ ስለማስብ ኢህአዴግ የዚህ ዓይነት ምሁራንን አሰባስቦ ቢያማክራቸዉ ዉጤት ሊገኝ እንደሚችል ጥርጥር የለኝም፡፡ ኢህአዴግም ዘለዓአለም የወደበወ  ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ከመሸማቀቅ ሳይሻለዉ አይቀርም፡፡

ሩሲያ ክሬሚያን በኃይል ወደ ራሷ የደባለቀችበት፡በምስራቅ ኡክሬይን ባሉ ግዛቶች አፍቃሪ ሩሲያ የሆኑት ዶንስኪና ዶንባስ ግዛቶች ከኡክሬይን ለመገንጠል ትግል የተጀመረዉ በሩሲያ የቅርብ እገዛና ቆስቋሽነት መሆኑ፡፡ ሩሲያ ከጀፓን ጋር ኩርል አይላንድ በሚባለዉ በጃፓን አዋሳኝ የሆነ ይዞታ ለብዙ ዓመታት ስትወዛገብ የቆየችበት (ለዚህ ተብሎ የተደረገዉን የ1904 ጦርነትም አይዘነጋም)፤ ደቡብ ቻይና ባህር (south chaina sea) በሚባለዉ የባለቤትነት ጉዳይ ላይ የይገባኛል ጥያቄ በማንሳት ቻይና ፤ቬትናም፤ፊሊፕንስ፤ታይዋን፤ማሌይዢያና ቡሩኔል ለዓመታት ሲወዛገቡ የቆዩበት፤ቻይና በተጨማሪ ከጃፓን ጋር ሰንካኩ (senkaku island) በሚባለዉ ደሴት ምክንያት ለብዙ ዓመታት እየተወዛገቡ የመቆየታቸዉ ምስጢር ፤ታላቋ ብርታኒያ ከሀገሯ ስምንት ሺህ ማይልስ ርቀት ላይ የሚገኘዉን ፎክላንድን ይገባኛል ምክንያት ከአርጀንትና ጋር የጦፈ ጦርነት ዉስጥ የገቡበት መነሾ ወዘተ እነዚህና ሌሎች ያልተጠቀሱ አብነቶች የሚጠቁሙን ቁምነገር ቢኖር የባህር በር፡ ደሴቶችና የባህር ዉስጥ ሃብት ወዘተ ጉዳይ አቅም ሌለለዉ አገር ካልሆነ በስተቀር የትኛዉም ለሀገሩ ተቆርቋሪ የሆነ መንግስት  በቸልታ የማያልፈዉ የሉአላዊነት ትልቅ የብሄራዊ ጥቅም ጉዳይ መሆኑን ነዉ፡፡ እነዚህ አገሮች ለንግድ እንቅስቃሴ ሊያገለግላቸዉ የሚችል ሌላ አማራጭ የባህር በር መዉጫ ሲላልነበራቸዉ ሳይሆን የሀገር ደህንነት ጉዳይ ስለሆነባቸዉ ነዉ፡

የአሰብ ወደብ ነገር ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳዉም በላይ ለደህንነታችን/ሉአላዊነታችን ወሳኝ መሆኑን ከአስርና ከሃያ አመት በፊት ከነበረዉ በተሻለ አሁን ግልጽ የሆነ ይመስለኛል፡፡ አሁን አሁንማ መንግስትም ቢሆን የባህር በር ጉዳይን ከኛ በበለጠ መገንዘብ ሳይጀምር እንዳልቀረ አንዳንድ ምልክቶችን እያየን ነዉ፡፡

በባለፈዉ ጦርነት አንዳንድ ወላጆች “ልጆቻችን መስዋእት መሆናቸዉ ካልቀረ ባድመ ቀርቶብን አሰብ ወደብ ላይ ብንረባረብ ይሻል ነበር” ሲሉ ተደምጠዉ ነበር፡፡ እነዚህ ወላጆች የልጆቻቸዉ በጦር ሜዳ ወድቆ መቅረት የሚጸጽታቸዉ  የአሰብ ወደብ ገዳይ ትዉስ ሲላቸዉ ነዉ፡፡ ዛሬ አንዳንድ ፣የመንግስት ባለስልጣናትም የዚሁ ዓይነት አዲስ አስተሳሰብ  እንዳላቸዉ እናዉቃለን፡፡ ችግሩ ግን ይሄን እምነታቸዉን ወደ መድረክ አዉጥተዉ በግልጽ ለመወያየት የፓርቲያቸዉ ባህል አይፈቅድላቸዉም፡፡

እንኳን ተራዉ አባል ቀርቶ ቁልፍ የሚባሉ የፓርቲዉ አመራሮችም ቢሆኑ ያቺዉ አስቀድሞ አቋም ከተያዘባት ጉደይ ዉጭ አዲስ አመለካከታቸዉን ለዉይይት ወደ መድረክ ለማቅረብ ድፍረት የላቸዉም፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ በአብዛኛዉ የፓርቲዉና የመንግስት አመራርና አባላት ዘንድ እየታመነበትም ነገር ግን የፓርቲዉ የመስመር መቀልበስ ተደርጎ እንዳይቆጠር በስህተቱ መግፋት ተመራጭና እጅግ የቀለለ  ሆኗል፡፡ አንድ ቀን አንድ ደፋር ወደ መድረክ አስከሚያወጣ ድረስ ይቀጥላል፡፡

በርግጥ መንግስታችንም ቢሆን በጦርነቱ ግዜ ጠንከር ያለም ባይሆን በዉስን ደረጃ ለአሰብ ወደብ ፍላጎቱ ተቀስቅሶ እንደነበር ለማወቅ የቻልነዉ በኋላ ዘግየት ብለን ነዉ፡፡ መንግስት በጦርነቱ ወቅት ለአሰብ ወደብ አንዳችም ፍላጎት ሳያሳይ ሰራዊቱን ሁሉ በምዕራብና በሰሜን አቅጣጫ ብቻ አከማችቶ አሰብ ወደብ ላይ አንዳችም የረባ ጦርነት ሳይደረግ ነዉ ጦርነቱ የተጠናቀቀዉ የሚለዉ የአንዳንድ ሰዎች አስተያዬት የተሳሳተ መሆን ብቻ ሳይሆን ዝም ብሎ በጭፍን የተሰጠ አስተያዬት ይመስለኛል፡፡

ምክንያቱም ልክ እንደ ሌሎች ግንባሮች በአሰብ ወደብ አቅጣጫም ሰራዊታችን ከፍተኛ ተጋድሎ ሲያደረግ እንደነበረና ቀላል የማይባል መስዋእትነትም እንደተከፈለበት ይታወቃልና፡፡ እንዲያዉም ከጦርነቱ በኋላ በጦርነቱ ዙሪያ ላይ በተደረገዉ ስብሰባ ላይ የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ሲናገሩ እንደሰማሁት በጦርነቱ ወቅት መንግስት አጋጣሚዉን በመጠቀም አሰብ ወደብን ለማስመለስ ጥረት ማድረጉንና ነገር ግን በሌሎች ግንባሮች በነበረዉ ጫና ምክንያት ሰራዊታችን ከፍተኛ ጥረት ቢያደረግም አሰብ ወደብን ለመቆጣጠር እንዳልቻለ ገልጸዉ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ የአቶ መለስ ንግግር በዚያዉም ሰብሰባ ላይ ተነግሮ ከዚያ ስብሰባ ዉጭ እንዳይወጣ በመደረጉ ህዝቡ በወደብ ጉዳይ ላይ የኢህአዴግ መንግስት የዚህ ዓይነት ከህዝቡ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም  አቋም እንዳለዉ የሚያዉቀዉ ነገር የለም፡፡

የኢህአዴግ መንግስት የባህር በር ጉዳይ ጨርሶ እንደማያሳስበዉና እንዲያዉም ጥያቄዉ ሲነሳ በተለያዬ መንገዶች ጥያቄዉን እንደሚያዳፍን ተደርጎ የሚሰጠዉ አስተያዬት ትንሽ የተጋነነና ሚዛናዊነት የጎደለዉ ይመስለኛል፡፡ አስቀድሜ እንደገለጽኩት የወደብ ጉዳይን ከብዙዎቻችን በበለጠ መንግስት የሚገነዘብ ይመስለኛል፡፡ በየዓመቱ ለጂቡቲ ወደብ 730 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደምንከፍልና የራሳችን ወደብ ቢኖረን ኖሮ ከዚህ ግማሽ ያህሉን ማዳን እንደምንችል ይህ ለልማታችን ከፍተኛ ጉዳት መሆኑን መንግስታችን በሚገባ ይገነዘባል፡፡

ወደብ አልባ መሆናችን በኢኮኖሚያችን ላይ ካሳደረዉ ጫና በበለጠ ለደህንነታችንም ስጋት እየፈጠረ መሆኑንም መንግስት ዘግይቶም ቢሆን አሁን ለመረዳት የቻለ ይመስለኛል፡፡ ጠቅለይ ሚኒስትራችንም ከሁለት ዓመት በፊት  አሰብ ወደብ አካባቢ እየተፈጠረ ያለዉን መሬት የመቀራመት ሁኔታ አስግቶአቸዉ ማስጠንቀቂያ መስጣቸዉ መንግስትም በጉዳዩ ላይ እያሰበበት መሆኑን የሚያመላከት ነዉ፡፡ የሚያሳዝነዉ ግን እኛ እንደ ቀልድ  ንቀን በጣልነዉ የአሰብ ወደብ ላይ ለኛ ወዳጅ ያልሆኑ አገሮች ጦር ካምፕ  መመስረታቸዉና ወደፊት በአካባቢዉ ለሚነሳ አለመረጋጋት ሰለባ መሆን መቻላችን ነዉ፡፡

አገራችን ወደብ አልባ መሆኗ የኢትዮጵያ መንግስት  በቀላሉ ሊያየዉ የሚገባ ጉዳይ አይደለ፡፡ አነዳንድ ሰዎች ከኢትዮጵያ ዉጭ ሌሎች አሰራ ሁለት አካባቢ የአፍሪካ አገራት፤ በአዉሮፓ አምስት፤ በኤሽያ ስድስት አገራት ወደብ አልባ መሆናቸዉን በማስታወስ  ለኢትዮጵያ መጽናኛ ይሆን ይመስል ጥያቄዉን ለማጣጣል  ይጥራሉ፡፡ ሌሎች አገሮች ወደብ አልባ መሆን እኛን የሚመለከተን ጉዳይ አይደለም፡፡ የራሳቸዉ ጣጣ ነዉ፡፡ “እኛ ብቻ አይደለንም ወደብ የሌለን” የሚል ማግባቢያ ሆን ብሎ ህዝብን ለማሞኘት ካልሆነ በስተቀር የባህር መዉጫ በር ጥያቄአችንን አንድንተዉ የሚያደርገን አይደለም፡፡ የሀገራችን አንድ አካል የነበረችዉ ኤርትራን ማጣታችን ሳያንሰን አንጡራ ሃብታችን የነበረዉን የአሰብ ወደብን ማጣት ፈጽሞ ተቀባይነት የለዉም፡፡

ኢትዮጵያን የምታህል ትልቅ ሀገር ወደብ አልባ ሆና ትንሿ ኤርትራ የሁለት ወደብ ባለቤት የምትሆንበት ምክንያት አይኖርም፡፡ እኛ ወደብ አልባ ለመሆን የተገደድነዉ  የአርትራ ህዝብ  ፊላጎት ስለሆነ ሳይሆን በእኛዉ በራሳችን ድክመትና ቸልተኝነት ምክንያት በመሆኑ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለዉ ነዉን ፡፡ መከላከያ ሰራዊታችን እንደሆን እንኳን የራሳችንን  የባህር በር የማስመለስ ጉዳይ ይቅርና ከሀገሩ ዉጭ ለሌላዉ አገር ህዝብ ደህንነት የሚዋደቅ ሰራዊት ሆኖ እያለ በባህር በር ጉዳይ መንግስታችን አጉል መቅለስለሱ ፈጽሞ ተቀባይነት አይኖረዉም፡፡

መንግስታችን በኃይል መንገድ የወደብ ባለቤት ለመሆን የሚደረግ ሙከራ ላይ አሁንም ከቀድሞዉ የተለየ የአቋም ለዉጥ ባያደርግም ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን በሰላማዊ መንገድ ጉዳዩን መጨረስ ይቻላል የሚል እምነት እየያዘ የመጣ ይመስለኛል፡፡ መንግስት በአሁኑ ወቅት ከምንጊዜም በበለጠ በዓለም አቀፍ መድረክ ያተረፈዉን ትልቅ ተደማጭነትና ከበረታ በመጠቀም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ወደፊት የወደብ ባለቤት ሊያደርግን እንደሚችልና ይህንንም አንድ ቀን ተግባራዊ ሆኖ እንደማዬዉ እምነቴ ነዉ፡፡

“የኢፌድሪ መንግስት (ኢህአዴግ) አገርቱን ወደብ አልባ አደረጋት፤ከኢትዮጵያ ጥቅም ይልቅ ለኤርትራ ይከራከራል” የሚሉ ሁሉ መሳሳታቸዉን በድፍረት የምንናገርበት ዘመን እንዲመጣ እመኛለሁ፡፡ ቢቻል ቢቻል በዚህ ጉዳይ ሰፊ እዉቀትና ትምህርቱ ያላችሁ ኢትዮጵያዉያን ምሁራን ኢህአዴግ ሳይጠይቃችሁም ቢሆን ሰብሰብ ብላችሁ ጠለቅ ያለና ህጋዊ ድጋፍ የሚያስገኝ ጥናት አዘጋጅታችሁ ለመንግስታችን ብታቀርቡና መንግስትን በዚህ ጉዳይ ለማነቃቃት ብትሞክሩ ለሀገርቱ ትልቅ ዉለታ ነዉ፡፡

በተረፈ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ልባዊ ከበረታ ካላቸዉ ማድረግ የሚገባቸዉ አንድ ትልቅ ጉዳይ ቢኖር መለስ ከአቅማቸዉ በላይ ሆኖና በሌላ አስገዳጅ ምክንያት የሰሩት ስህተት ካለ እሳቸዉ ስህተቱን በማረምና በማስተካከል የሳቸዉን ስም በማስጠበቅ እንጂ ስህተታቸዉን በማስቀጠል አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ ለጠ/ሚ ኃይለማርያም ትልቅ ፈተና የሚሆነዉም የባህር በር ጉዳይ ነዉ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከአቶ መለስ ጋር የሚስተካከል ቦታ በታሪክ ለማስመዝገብ እጅግ እንደሚከብዳቸዉ ግልጽ ነዉ፡፡ አዲስ ተአምር የሚሰኝ ነገር ሰርተዉ እንዳያሳዩን የመለስ አሻራ የሌለበት አንድም ግዙፍ አጀንዳ ማግኘት ይቸግራል፡፤በእኔ በኩል አንድ ያልተደፈረችና ያልተመለሰች የህዝብ (ብሄራዊ) አጀንዳ አለች፡ እሷን ማሳካት ቀርቶ ጀምረዉ ሳይጨርሱ ቢያልፉ ከመለስ ያልተናነስ ቦታ በታሪክ ይኖራቸዋል፡፡ ያም ጉዳይ ሀገሪቱን የባህር በርና የራሳችን ወደብ ባለቤት ማድረግ ነዉ፡፡

8/ በጦር ሜዳ በደማችን ያገኘነዉን ድል በድርድር መድረክ እንደዋዛ ተነጠቅን

ሻዕቢያ ጥቃት ሰንዝሮ ወደ ጦርነቱ ሲገባ በቅድሚያ ዉስጣችንን ፈትሾና ግምግሞ በራሱ እይታ ለሱ ጥቃት ተጋላጭ የሚያደርገን ድክመት እንዳለን ተረድቶ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ብትንትናችንን እንደሚያወጣ ተማምኖ ነዉ፡፡ በርግጥ ሻዕቢያ ግምገማዉ የተሳሳተ መሆኑን ለመገንዘብ የቻለዉ ጦርነቱ እንደተጀመረ ሁሉም ነገር እሱ ካሰበበት ዉጭ መሆኑን ሲረዳ ነዉ፡፡

ሻዕቢያ ይፍጠንም ይዘግይም በመጨረሻ የኢትዮጵያ ሰራዊት እንደሚያሸንፍ መገንዘብ ከጀመረ በኋላም ከጦርነቱ አንድ የሆነ ነገር ይዞ ካልሆነ በስተቀር እንዲሁ በባዶ እጅ መዉጣትን አልፈለገም፡፡ ሻዕቢያ ስትራቴጂያዊ ድንገተኝነትን ተጠቅሞ ፈጣን ዉጊያ በማድረግ የተወሰነ ድል ሊያገኝ እንደሚችልና የተወሰነ መሬትም በመቆጣጠርም የኢትዮጵያን መንግስት በኃይል ለፍላጎቱ ተገዢ ማድረግ እንደሚችል እርግጠኛ ሆኖ ነበር፡፡

ሻዕቢያ ለዚህ ታሳቢ ያደረገዉም የኢትዮጵያ ህዝብ የተከፋፈለና በቅራኔ የተሞላ፤ አርስ በርሱ ከመባላት ዉጭ ተባብሮ ሊወጋኝ አይችልም፡፡ ሰራዊቱም ደካማ ስለሆነ ሊቋቋመኝ አይችልም የሚል ግምገማ ይዞ ነዉ፡፡ ሻዕቢያ አነስ ያለችም ብትሆን ግን ደግሞ ትኩረት የምትስብ ድል በፍጥነት በማምጣት ያችን ይዞ ቶሎ ወደ ድርድር ካልገባ ኢትዮጵያ ሰራዊት ግዜ ካገኘ ተጠናክሮ የማታ ማታ ጉድ ሊሰራዉ እንደሚችል ገምቷል፡፡

ለመደራደሪያ የምትሆነዉን የሆነች ነገር ይዞ ወደ ህግ መድረክና ወደ ድርድር ከገባ ይብዛም ይነስም የሆነ ፖለቲካዊ ድል ሊያመጣለት እንደሚችል አስቧል፡፡ ሻእቢያ ለራሱ ህዝብ ሊያሳይ የሚችላት ትንሽ ግን ደግሞ ጠቃሚ የሆነች ፖለቲካዊ ድል ማግኘት እንደበቂ ሁኔታ ቆጥሮና ያን አስልቶ ነዉ ወደ ጦርነቱ በድፍረት ዓይኑን ጨፍኖ የገባዉ፡፡

ሻዕቢያ ጦርነቱ አንዴ ከተነሳ በኋላ አለምአቀፍ ጣልቃገብነት እንደሚኖር ቀድሞዉኑ ስለሚያዉቅ ወደ ራሱ እንዲካተቱ የፈለጋቸዉን ቦታዎች (የኢትዮጵያ መሬት) በህጋዊ መንገድ ባለቤትነቱን ማረጋገጥ እንደሚችል እርግጠኛ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በሚያዋስነዉ ድንበር የግዛት ይገባኛል ጥያቄ በህጋዊ መንገድ ያልተቋጨና ድንበሩም ያልተከለለ በመሆኑ ወደ ፊት ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ሻዕቢያ አስቀድሞ የጠረጠረ ይመስላል፡፡

ሻዕቢያ እንዳሰበዉ ሳይሆን ሰራዊቱ እዚህም እዝያም ድል ማጣቱና  የኤርትራ መሬት በሰራዊታችን ቁጥጥር ስር እየሆነ መሄዱና ጭራሽ ሰራዊታችን ወደ ዉስጥ እየገሰገሰ መሄዱ ብዙ ቢያሳስበዉም ዉሳኔዉን መቀበሉን ከገለጸ ፋታ ሊያገኝ እንደሚችል በደንብ አስልቷል፡፡ ለዚህም ነዉ በድንገት የአፍሪካ ህብረትን ዉሳኔን መቀበሉና ለድንበር ኮሚሽኑ ዉሳኔ ተግባራዊነት ሽንጡን ገትሮ ሲከራከር የነበረዉ፡፡

ሻዕቢያ ወደ ጦርነት የገባዉ ለመሬት ቢሎ ባይሆንም አንዴ ጦርነት መቀስቀሱ ካልቀረ በዚያ አጋጣሚ ግርግር በመፍጠር የዓለምን ትኩረት በመሳብ እሱ የፈለጋቸዉን ቦታዎች በህጋዊ መንገድ ወደ ራሱ ማጠቃለል ያስችለኛል የሚል ስሌት አስልቶ ነዉ፡፡ ሻዕቢያ በወታደር ኃይል በጉልበት የኢትዮጵያን መሬት ይዞ ለመቆዬት እችላለሁ የሚል ሃሳብ ፈጽሞ የነበረዉ አይመስለኝም፡፡

በጉልበት ከሚያደርገዉ ይልቅ በህጋዊ መንገድ ግን ማሳካት እንደሚችል ከፍተኛ እምነት ይዞ ነዉ ወደ ጦርነቱ የገባዉ፡፡ በርግጥ ሻእቢያ በጦርነቱ ተሸናፊ መሆኑና ሰራዊቱ ማለቁ ብዙም አላስጨነቀዉም፡፡ ከዚያ ይልቅ  አስቀድሞ ያሰበዉንና የተመኘዉን ማግኘት ስለቻለ እጅግ ደስተኛ ነዉ፡፡

ሻዕቢያ በጦርነቱ ማሸነፍ ቢችል ባይጠላም አሁን ካገኘዉ የተሻለ ነገር እንደማያገኝ የተረዳ ይመስላል፡፡ ስለዚህ ወታደራዊ ሽንፈቱ ብዙ አላሳሰበዉም፡፡ መጀመሪያዉኑ ሁለት አማራጮች ይዞ ነዉ ወደ ጦርነቱ የገባዉ፡፡ ሁለቱም አመራጮች ሻዕቢያ ወደ ፈለገዉ ግብ እንደሚያደርሱት ተማምኗል፡፡

አንደኛዉ አመራጭ ቢቻል በጦርነቱ አሸንፎ የፈለገዉንም በኃይል ማግኘት ሲሆን ሌላዉ አማራጭ ደግሞ በጦርነቱ ተሸንፎም ቢሆን የፈለገዉን በግርግር በድርድር ስም ማግኘት ናቸዉ፡፡ ሻዕቢያ የመጀመሪያዉ አማራጭ ባይሳካለትም ተሸንፎም እያለ በህጋዊ መንገድ የፈለገዉን ማግኘት በመቻሉ ሁለተኛዉ አማራጭ የሰመረተለት ይመስላል፡፡

የሻዕቢያ ብልጠት ሲታሰብ ሮጀር ፊሼርና ዊሊያም ዩሪ የተባሉ ምሁራን “Getting To Yes:Negotiating Agreement Without Givinging” በሚል ርእስ ለህትመት ባበበቁት መጽሀፍ ላይ ባላጋራን በሙግት መርታት የሚቻልበትን አማራጭ መንገዶች ያስተዋወቁትን በሚገባ አጥንቶ የገባ ይመስላል፡፡

እነዚህ ምሁራን በጠቀሱት ምርጥ የድርድር አማራጮችን ይዞ በመግባት ባላጋራን በመርታት የፈለጉትን የማስወሰን ስልት (Best Alternative To a Negotiated Agreement(BATNA) ጋር በሚመሳሰል መልኩ ሻዕቢያ የጠበቀዉንና ያሰበዉን አግኝቷል፡፡ ለዚያዉም የጦርነቱ ቆስቋሽም ተሸናፊም ሆኖ እያለ ማለት ነዉ፡፡ ኤርትራ አንዱ ባይሳካ ሌላዉ ሊሳካ ይችላል በሚል የተሻለ አመራጮችን ይዛ የቀረበች ይመስላል፡፡ በተገኘዉ ዉጤት ወይም የፍርድ ዉሳኔም እጅግ ደስተኛ ነች፡፡ የብልጠቷ ብዛት የራሷ ያልሆነዉን መሬት (ለምሳሌ ባድመ) ለማግኘትም መቻሏ ነዉ፡፡

በኛ በኩል ግን የሰጡንን ተቀብለን ለመዉጣት የቆረጥን አስመስሎብናል፡፡ በተጠቀሰዉ ጽሀፍ ዉስጥ “አትና” ( ATNA) በሚል ምህጻረ ቃል የሚጠራ ስልት አለ፡፡  (ATNA – Any Alternative To A Negotiated Agreement) እንደማለት ነዉ፡፡ በዚህ አቀራረብ መሰረት ተደራዳሪዉ ጠባብ አማራጭና ደካማ ማስረጃ ይዞ ስለሚቀርብና ቢሸነፍም ቢያሸንፍም ለዉጤቱ ብዙም ሳይጨነቅ የተወሰነለትን ብቻ በጸጋ ተቀብሎ መሄድን የሚመለከት ነዉ፡፡

በርግጥ አንዳንዴ ብዙም እርባና በሌለዉ ነገር ላይ ዘላለም እያለቃቀሱ ጊዜ ከማባከን  ወዲያ ሰጥቶ መገላገሉና ወደ ልማቱ መመለሱ ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጉዳዮች እጀግ ከበድ ያሉ ይሆኑና ዝም ተብሎ የሚጣሉ አይሆኑም፡፡ ሁኔታዉን በአንክሮ የሚከታተሉ ሚሊዮኖች ባሉበት ሁኔታ ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአስር ሺዎች ደም የተገበረበት ጉዳይ ከሆነ እንደዋዛ ልተዉት ቢፈልጉም በጅ አይልም፡፡

በእኛ ሁኔታም ባድመን ለማስለቀቅ የተከፈለዉ መስዋእትነት መብዛት ቦታዉን ትልቅ ፖለቲካዊ ዋጋ እንዲኖረዉ አድርጎታል፡፡ ቦታዉ ከጦርነቱ በፊት ብዙም የማይታወቅ የዉጭ ሰዎች ቀርቶ ብዙዎቻችን ኢትዮጵያዉያን ሳንቀር “ባድመ ” በሚል ስም የሚጠራ ቦታ አስቀድመን የማናዉቅ ብዙ ነበርን፡፡ የት እንድሚገኝ ለማወቅ አንዱ ሌላዉን እስከመጠየቅ የደረሰበትና በካርታ ላይ ፈልጎ ለማግኘትም አዳጋች የነበረ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ባድመ አሁን ከጦርነቱ በኋላ ከአድዋ ባልተናነሰ ስሙ ተደጋግሞ የሚነሳ ቦታ ሆኗል፡፡ ስለዚህ “ባድመ” ሲባል ፖለቲካዊ ትርጉሙ ከፍተኛ በመሆኑ መላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ በሚያምንበት አሳማኝ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር በቀላሉ አሳልፎ መስጠት የሚሞከር አይደለም፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ለዘላቂ ወዳጅነት ሲሉ አንዱ ለሌላዉ የሚሰጠዉና አንዱ ከሌላዉ የሚቀበለዉ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ የአስብ ወደብ ጉዳይ ለኛ ለባለቤቶቹ መልቀቅ ከፈለጉ እኛ ባድመንምም ሆነ ሌላ የግድ ያስፈልጉናል የሚሉትን መሬት ብንለቅላቸዉ ሁለታችንም አንጎዳም፡፡ ይሄ በምኞት ደረጃ ካልሆነ በስተቀር በተግባር ግን አስቸጋሪነቱ አያጠያይቅም፡፡

አንዳንድ ሰዎች ጉዳዩን በቀጥታ ከኢሳይያስ ጋር በማቆራኘት ኢሳይያስ በስልጣን ላይ ባለበት ወቅት ሊተገበር አይችልም ይላሉ፡፡ በርግጥ ኢሳይያስ ስልጣን ላይ እያሉ የሚሞከር አይደለም፡፡ ችግሩ ግን ኢሳይያስ በሌላ ሰዉ ቢተኩም ተግባራዊ ማድረግ ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ አስቸጋሪነቱ ደግሞ በይበልጥ ለእኛ ሲሆን እሱም የኤርትራን ቀልብ ለመሳብና ሊያጓጓት የሚችል በምትኩ ልንሰጣት ያዘጋጀነዉ ነገር ባለመኖሩ ነዉ፡፡

ምክንያቱም ባድመን እንልቀቅላችሁ እንዳንል ባድመ የተፈረደዉ ለኤርትራ ነዉ፡፡ ብንለቅላቸዉም እንደዉለታ አይቆጥሩትም፡፡ አሰብ ወደብ ደግሞ ከመጀመሪያዉኑ በይገባኛል ጥያቄም አላነሳንበትም፡፡ በሌላ አባባል አሰብ ወደብ የኤርትራ መሆኑን አምነን የይገባኛል ጥያቄ እንደማናነሳ አረጋግጠናል ማለት ነዉ፡፡ “ሰጥቶ የመቀበሉ “ጉዳይ በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት ቢያገኝ እንኳን ምን ሰጥተን ምን ልንቀበል እንደምንችል ግልጽ አይደለም፡፡ እኛ ከኤርትራ የምንፈልገዉን እንጂ እነሱ ከእኛ ምን ሊጠይቁ እንደሚችሉ  ብዙም ግልጽ አይደለም፡፡

ሻዕቢያ በዚህ ሁሉ መካከል ፈጽሞ ያልጠበቀዉና ተአምር የሆነበት ነገር የኢትዮጵያ መከላከያ  ሰራዊት እንደዚህ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ድል ማግኘት መቻሉን ነዉ፡፡ ሻዕቢያ የኋላ ኋላ መሸነፉ እንደማይቀር አዉቆና ሽንፈቱንም ለመቀበል ራሱን አሳምኖ እያለ ነገር ግን በዚህ ፍጥነት ይሆናል ብሎ ባልጠበቀዉ አጭር ጊዜ ዉስጥ መሸነፉና ኪሳራዉም ሊቀበለዉ ከሚገባዉ በላይ መሆኑ (beyond tolerable level of casualties) ፈጽሞ ያልጠበቀዉ ነዉ፡፡

በተለይም የኢሳይያስን “ተአምረኛ ምሽግ” የተመለከተ ሰዉ የኤርትራ ሰራዊት በዚህ ፍጥነት ይሸነፋል ቢሎ ለመገመት መቸገሩ አይቀርም፡፡ የሻእቢያ ምሽግ በ2ኛዉ አለም ጦርነት ወቅት ፈረንሳዮች የጀርመንን ማጥቃት ለመግታት ያስችላል ቢለዉ ለዓመታት ሲገነቡት የኖሩትን ማጂኖት ላይን (maginote line) ከሚባለዉ ምሽግ ጋር በማይተናነስ ደረጃ ሻዕቢያ ከሁለት ዓመት ላላነሰ ጊዜ ሲገነባ የከረመበትና አሌክስ ላስት የተባለዉ የቢቢሲ ዘጋቢ እጅግ አጋኖና አዳንቆ ለዓለም ህዝብ  እንዲደርስ ያደደረገዉን ምሽግ የኢትዮጵያ አንበሶች በአጭር ጊዜ ዉስጥ እንዳልነበር ማድረጋቸዉን የሻእቢያ አመራሮች ሲገነዘቡ ከዚያ በኋላ አጉል መንደፋደፍ እንደማያዋጣ በመረዳታቸዉ ጦርነቱን በሆነ ዜዴ ካላስቆሙ በስተቀር ኪሳራዉ በፍጹም ከሚቋቋሙት በላይ ሆኖ ያለ ወታደር እንዳይቀሩ በመስጋት በፊት ያጣጣሉትን የአፍሪካ ህብረትን ዉሳኔ ለመቀበል ተገደዋል፡፡

የአልጄርሱ ስምምነት የተደረገዉ ኢትዮጵያ በጦርነቱ ከፍተኛ የወታደራዊ የበላይነት በያዘችበትና ሰራዊታችን በኤርትራ ይዞታ ዉስጥ በነበረበት ሁኔታ ነዉ፡፡ ስለዚህ የባድመንና የሌሎች አካባቢዎች ያለአግባብ ወደ ኤርትራ የመካለል ጉዳይ  ኤርትራ ለቀን መዉጣታችን ያመጣዉ አይደለም፡፡

ችግሩ የወታደራዊ የበላይነት የማጣት ጉዳይ ሳይሆን አደራዳሪ ሸምጋዮች (mediators) የችግሩን ስረ- መሰረትና የሁለቱን አገር ህዝቦች ታሪካዊ ትሰስር በሚገባ ሳይረዱ በድንበር ማካለል ጉዳይ ላይ ብቻ በማተኮር ችግሩን ለዘቀታዉ ሊቀርፍ የማይችል የተዛባ ዉሳኔ በመስጠታቸዉ ነዉ፡፡ በርግጥ መንግስታችን የወከላቸዉ ተደራዳሪዎች የማስረጃ አቀራረብና የመደራደር (የማስረዳት) አቅም ዋነኛዉ የሽንፈታችን ምክንያት ቢሆንም ነገር ግን አጠቃላይ ሁኔታዉ የተቋጨበት አግባብ ሰራዊታችን ኤርትራ ድንበር ዉስጥ ባለመቆየቱና አስመራ ድረስ ባለመገስገሳችን የተፈጠረ አይደለም፡፡

በወቅቱ በዲፕሎማሲ አቅም ችግር ምክንያት የኛ የሆኑትን ተከራክሮ ህጋዊ ባለቤትነታችንን ማረጋገጥም ሆነ በጦርነቱ ሰለባ በመሆናችን የሚገባን ካሳ ማስወሰን ተስኖን እያለ የበለጠ ትልቅ ስህተት ደግሞ በደንብ ሳናረጋግጥ ባድመ ለኛ ተወስኗል ብሎ መንገስት መግለጫ መስጠቱና ህዝቡን ያለአግባብ ካስጨፈረ በኋላ ግን መንግስት እንዳለዉ ሳይሆን ባድመ ለኤርትራ መወሰኑን ሲታወቅ ህዝቡ ምንድነዉ ሊያስብ የሚችለዉ? በሃገር ሉአላዊነትና በብሄራዊ ጥቅም ላይ ያን ያህል ግደለሽነትና ሃላፊነት የጎደለዉ ድርጊት መደረግስ ነበረበት እንዴ? አንዴ ስህተት ከተፈጠረ  በኋላ ደግሞ የሚመለከተዉ የመንግስት አካል ለተፈጠረዉ ስህተት ተገቢዉን ማረሚያ መስጠትና ህዝብን ይቅርታ መጠየቅም ሲገባዉ አላደረገም፡፡

በጣም ወሳኝ በሆነ የሉአላዊነትና የብሄራዊ ጥቅም ጉዳይ ላይ አንድ ባለስልጣን እንዳሻቸዉ መግለጫ ከመስጠቱ በፊት ከሚመለከተዉ የሀገሪቱ አመራር (በተለይ ከጠ/ሚሩ) ጋር በቅድሚያ መመካከር የነበረባቸዉ ይመስለኛል፡፡ ቢቻልም በሀገሪቱ ህግአዉጭ ወይም በካቢኔ ደረጃ መነጋገር ያለባቸዉ ይመስለኛል፡፡ በወቅቱ ስለ ባድመ ለኛ መወሰን የገለጹት ባለስልጣን በህዝቡ ላይ ለመቀለድና ለማታለል ፈልገዉ ወይም የጉዳዩን ክብደት ሳይረዱት ቀርተዉም አይመስለኝም፡፡ ከዚያ ይልቅ በስህተት እንደሆነ ይገባኛል፡፡

ነገሩ የበለጠ ግራ የሚያጋባዉ ግን ይህን ያደረገዉ አንድ የመንግስት ቃል አቀባይ ወይም የሆነ ጋዘጤኛ ቢሆን ኖሮ ምንጩን ሳያጣራና ሳያረጋግጥ አቀረበ ተብሎ እንደነገሩ በተግሳጽም ሆነ በይቅርታ ሊታልፍ ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ይህን ትልቅ ጉዳይ ለህዝብ ያወጁት ከመንግስት ቁንጮ አመራሮች አንዱ የነበሩትና በድርድሩ ጉዳይም ከሁሉም የበለጠ ኃላፊነት የነበራቸዉ ሰዉ መሆናቸዉ ነዉ፡፡

ማንም ይሁን ማን ስህተት መፈጠሩ ከታወቀ ወዲያዉኑ የእርምት መግለጫ መስጠትም ሆነ በሰለጠነዉ ዓለም እንደሚደረገዉ ደግሞ ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ እየተቻለ ያን ባለማድረጋቸዉ ቀድሞዉኑ በስህተት ሳይሆን ሆነ ተብሎ የተደረገ አስመስሎታል፡፡ በዚህ ምክንያትም ህዝቡ ክፉኛ እንደተቀየመ መካድ አይቻልም፡፡ ስህተቱ በግላቸዉ የፈጠሙት ከሆነ ራሳቸዉ ይቅርታ መጠየቅ ይገባቸዉ ነበር፡፡ ስህተቱ የመንግስት ከሆነ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸዉ ይቅርታ መጠየቅ ነበረባቸዉ፡፡ አስካሁን አንዱንም አላየንም፡፡

9/ በተገኘዉ ድልና ለሉአላዊነታችን ሲባል በከፍልነዉ መስዋእትነት ላይ እኩል አረዳድ የለንም

9.1/ በተገኘዉ ድል ላይ ከግንዘቤ ማነስ የመነጨ የአመለካከት ችግር መኖር

ብዙዎቻቸችን ከጦርነቱ ስንጠብቅ የነበረዉ ድል ተመሳሳይ ያለመሆን  ምክንያት በጦር ሜዳ ድል ምንነት ላይ ካለን የተዛባ አመለካከት የመነጨ ይመስላል፡፡ ጠላትን ማሸነፍ ሲባል በተለምዶ በስፖርቱ ዓለም ከምናዉቀዉ በጣም የተለየ ነዉ፡፡

በእግር ኳስ ጫወታም ይሁን በአትሌትክስ ዉድድር አሸናፊዉን ለመለየት የሚያስችል ከሞላ ጎደል ግልጽ የሆነ መስፈርት ከመኖሩም ሌላ ዳኞች ተሰይመዉ ይፈርዳሉ፡፡ ከነሱም ሌላ ተመልካቾችና የሚዲያ ሰዎች በሚሰጡት አስተያዬት ተሸናፊዉንና አሸናፊዉን ለመለየት አያዳግትም፡፡ ሁለቱም ማለትም አሸናፊዉም ተሸናፊዉም ዉጤቱን በጸጋ ተቀብለዉ ይሄዳሉ፡፡ በስፓርት ማሸነፍ የሞት ሽረት ጉዳይ ስላልሆነ ተሸናፊዉ ሌላ ጊዜ እንደሚያሸንፍም ተማምኖ ራሱን ያዘጋጃል፡፡ ጦርነት ግን ሰላማዊ ከሆነዉ ስፖርት የሚለየዉ ሞትና የንብረት ዉድመት ስላለዉ ብቻ አይደለም፡፡

በጦርነት አሸናፊና ተሸናፊን የሚዳኝ ዳኛ አለመኖሩም ጭምር ነዉ፡፡ አሸናፊዉንና ተሸናፊዉን ለመለዬት የሚያስችል ሁሉንም ሊያስማማ የሚችል አንድ ወጥ ድንጋጌ ወይም ደንብም የለም፡፡ ፈረንጆች “There are no established or even universally accepted rules or conditions for winning in war.” እንደሚሉት ማለት ነዉ፡፡ ለዚህ ተብሎም የሚሰየም ዳኛም የለም፡፡

በጦርነት ሁለቱም ወገኖች በየራሳቸዉ እይታ በቂ ነዉ ብለዉ ያሰቡትን ይዘዉ ይወጣሉ፡፡ አንዱ ወገን አሸነፍኩ ብሎ ሲጨፍር ሌላዉም ወገን በተመሳሳይ አሸንፌአለሁ ብሎ ህዝቡን ወደ አደባበይ አስወጥቶ ሊያስጨፍር ይችላል፡፡ አዲስ አባባም ሆነ አስመራ ባገኙት ድል ደስታቸዉን ለመግለጽ በአንድ ቀንና በተመሳሳይ ሰዓት አደባባይ ሊወጡ ይችላሉ፡፡ እኛ በጦርነቱ ድል አደረግን ብለን መስቀል አደባባይ ላይ ስንጨፍር የኤርትራ መንግስትም በተመሳሳይ ሁኔታ በተለየ መንገድ ድል አድራጊነታቸዉን በሳባ ስታዲየም ህዝቡን ሰብስቦ በደስታ ሲያስጨፍር እንዳልቀረ እገምታለሁ፡፡

የጦርነቱ ዉጤት ለሁለቱም ተጻራሪ ወገኖች አንጻራዊ ነዉ፡፡ የአንዱ ትልቅ ድል (big win) ለሌላዉ ትልቅ ሽንፈት (big lose) መሆን የግድ አይደለም፡፡ ሌላዉ ወገን አገኘሁት የሚለዉ ትልቅ ድል ለሌላዉ ወገን አንዳንዴ ጭራሽ እንደ ሽንፈት ላይቆጥር ይችላል፡፡ የጦርነቱ ድል አድራጊነት ሁለቱም ወገኖች በየራሳቸዉ በሚያደርጉት ግምገማ (assessment)የሚወሰን ነዉ ማለት ነዉ፡፡

በጦር ሜዳ የተገኘዉ ወታደራዊ ድል የፖለቲካ ዓላማዉን እዉን ካላደረገ ጦርነቱ ትርጉም አልባና አጉል መላላጥ ነዉ የሚሆነዉ፡፡ አንዳንዴ በግንባር ያለዉ አዛዥ በጠላት ላይ ባገኘዉ ወታደራዊ ድል ባለመርካት ጠላትን በደንብ አስከ መጨረሻዉ መደምሰስ አለብኝ በሚል ሀሳብ ለተጨማሪ ዉጊያ ሲዘጋጅ በመሃል ያለዉ ኮማንድ ወይም የሀገሪቱ ከፍተኛዉ ፖለቲካ አመራር “የፈለግነዉን አግኝተናል „በምል ዉጊያዉን አስቁሞ ድል ሊያዉጅ ይችላል፡፡

የፖለቲካ አመራሩ ለድል ያለዉ አረዳድ (perception) ከጦር ጄኔራሎች የተለየ ሆኖ ቢገኝ የሚያስገርም አይደፈለም፡፡ ሁለቱም ድልን የሚያዩበት መነጽር እጅግ የተለያዬ ነዉና፡፡ ስለዚህ አንዳንዴ በፖለቲካ አመራሩ ዉሳኔ ግራ የተጋባ ሰዉ ድል የሚባለዉ ይሄ ነዉ ማለት ነዉ?  (“Is that really a win?” ብሎ ቢጠይቅ  አይገርምም፡፡

በመጀመሪያዉ የገልፍ ጦርነት ወቅት ሳዳም ሁሴን በጦርነቱ ብዙ ጉዳት ደርሶበትና ሰራዊቱ እጅግ ተመናምኖበት እያለም “ጦርነቱን አሸንፈናል” እያለ መፎከሩም ከዚህ የመነጨ ነዉ፡፡ በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጦርነቱ በእነሱ አሸናፊነት መጠናቀቁን ለህዝባቸዉና ለመላዉ ዓለም ሲያበስሩ ሳዳምም በበኩላቸዉ “ያሸነፍነዉ እኛ ነን” ማለታቸዉ አይዘነጋም፡፡ ምክንያቱም ለሳዳም ትልቁ ፖለቲካዊ ግባቸዉ አገዛዛቸዉን ሳይነካ ማስቀጠል መቻላቸዉ (regime survival objective) ስለነበር ባሰቡትም መሰረት አገዛዙና ስርአቱ እንዳለ መቀጠል በመቻሉ ሳዳም በተገኘዉ ድል እጅግ ደስተኛ ነበሩ፡፡

ስለዚህ ከሳዳም እይታ አንጻር ሲታይ በጦርነቱ የተፈጠረዉ ሁኔታ እንደሰጉት ባለመሆኑ የተገኘዉን ዉጤት እንደ ስትራቴጂያዊ ድል አድርገዉ  ለመቀበል ለሳቸዉ ከበቂ በላይ ነበር፡፡ ሳዳም በጦር ሜዳ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸዉ ባያጡትም የዉጊያ መንፈሳቸዉና ፍላጎታቸዉ (will) እንዳለ በመሆኑ በሌላ ጊዜ እንደገና በማንሰራራት ለሌላ ጦርነት ዝግጁ መሆን እንደሚችሉ ያዉቁ ነበርና፡፡

በጦርነት ድል ማድረግ (አሸናፊነት) መመዘን ያለበትም ካመጣዉ ፖለቲካዊ ዉጤት አንጻር ነዉ፡፡ ጦርነት የፖለቲካ አላማን ለማሳከት ታስቦ የሚደረግ አስከሆነ ድረስ ድሉም መመዘን ያለበት ከፖለቲካ ስኬት አንጻር ነዉ፡፡ በጦርነት አሸናፊ ሆኛለሁ የሚለዉ ወገን ያገኘዉ ወታደራዊ ድል ፖለቲካዊ ግቡን ማሳካት የቻለ መሆኑን እርግጠኛ ሲሆን ብቻ ነዉ፡፡ ክላስዊትዝ (Carl von Clausewitz) እንደሚለዉ “ፖለቲካዊ ዓላማ የጦርነቱ ግብ ነዉ፡፡ ጦርነትም የዓላማ ማሳኪያ መሳሪያ ነዉ፡፡ ስለዚህ ጦርነት ከዓላማዉ ዉጭ ሊካሄድ  አይገባዉም፡”፡ (“The political object is the goal, war is the means of reaching it, and the means can never be considered in isolation from their purposes.”)

በዚህ ረገድ ያለዉ ችግር ያለ አንዳች ፖለቲካ ዓላማ ወደ ጦርነት የመግባት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ይብዛም ይነስም ፤ትክክልም ይሁን የተሳሳተ ያለ አንዳች ዓላማ ወደ ጦርነት የሚገባ አገር አይኖርም፡፡ ነገር ግን የጦርነት ፖለቲካዊ ዓላማ ወይም ግብ ግልጽ የሆነ፤የተገደበና፤ ሊደረስበት የሚችል መሆን አለበት፡፡ ያለበለዚያ ጦርነቱ ለሁሉም ችግሮች መፍትሄ እንዲያመጣ መጠበቅ አይቻልም፡፡

ኮሊን ኤስ.ግሬይ እንዳለዉ we cannot wage war to end all wars or to establish a permanent universal empire and imperium.” አሸናፊዉ ምጥን ያለ ግብ ከለለዉና ከጦርነቱ  ከሚገባዉ በላይ አብዝቶ ከጠበቀ ካንዱም ሳይሆን ጭራሽ ሽንፈት ሊጎናጸፍ ይችላል፡፡ ለትርፍ ፍለጋ ተብሎ የበለጠ የመሻት ጉዳይ ሁኔታዉን የበለጠ ያባብሰዋል እንጂ ዋናዉን ችግር አይቀርፍም፡፡

ተሸናፊዉ ወገንም ተሸናፊ የሚሆነዉ ወደ ጦርነት የገባበትን ዋነኛ ፖለቲካዊ ግብ ማሳከት ባለመቻሉ እንጂ ሁሉንም ችግሮች ሊፌታ ሲላልቻለ  አይደለም፡፡  አሸናፊዉ ያገኘዉን ምጥን ያለ ፖለቲካዊ ስኬት በቂ ነዉ ብሎ ራሱን ካለሳመነና ሌላ ተጨማሪ ፍለጋ ዉስጥ ከገባ ፤ በተመሳሳይ ሁኔታ  ተሸናፊዉም ወገን ብዙ ኪሳራ ሳይደርስበት ብዙ ሳያጣ ሽንፌቱን አምኖ ለመቀበል ካልፈለገ ጦርነቱ ማለቂያ ስለማይኖረዉ የኋላ መዘዙ ለሁለቱም የከፋ ይሆናል፡፡ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች  ያገኙትን ይዘዉ ከጦርነቱ በመዉጣት  በሚፈጠረዉ ሰላም የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ካልተረዱ በስተቀር ዉጊያዉን መቼም ላያቆሙ ይችላሉ፡፡

አሸናፊዉ የሚያስፈልገዉን ያህልና ተቀባይነት ያለዉን ስኬት ካገኘ ከጦርነት ለመዉጣት እንደ በቂ ሁኔታ ማዬት ይገባዋል፡፡  በጣም የተመጠነ ግብ ካለማስቀመጥ የተነሳ ብዙ ነገር ተፈልጎ የሚደረግ ጦርነት በእጅ ያለዉንም የሚያሳጣ ሊሆን ይችላል፡፡ የተገኘዉን ድል ጠብቆ ከማቆየት ይልቅ ተጨማሪ ድል ለማምጣት በመመኘት አንዳችም የሚያበረታታ ተስፋም ሆነ በቂ አቅም ሳይኖር በጦርነቱ ዓይንን ጨፍኖ መቀጠል ራስን ለሽንፈት መዳረግ ነዉ፡፡

የኛም ሁኔታ ከዚህ አንጻር መታየት ይኖርበታል፡፡ ከመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ በፖለቲከኞችም ሆነ በህዝቡ ዘንድ በጦርነቱ ባገኘነዉ ድል ላይ አንድ ዓይነት አመለካከት ባለመኖሩ አንዱ በተገኘዉ ድል ሲኮራ ሌላዉ ድሉን ሲያጣጥል ማዬት የተለመደ ሆኗል፡፡

ችግሩ የሚመነጨዉ በአንድ በኩል ጦርነትን ለጦርነት ተብሎ እንደሚካሄድ ክስተት እንጂ ለፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያነት ወይም በኃይል የተነጠቅነዉን በኃይል ለማስመለስ ተብሎ መካሄድ ያለበት አድርገን ካለመገንዘብ የመነጨ  መሆኑ ነዉ፡፡  በተጨማሪ በኃይል ያጣነዉን ማስመለስ መቻልን እንደ በቂ ሁኔታ ባለመቁጠር ጠላት ደካማና ተሸናፊ ስለሆነ ብቻ ተጨማሪ ትርፍ ነገር ለማምጣት ብለን ጦርነቱን መቀጠል እንዳለብን ከማሰብ የሚመነጭ ችግር ነዉ፡፡ ለዚህም ነዉ ባገኘነዉ  ድል ያለመርካት ነገር የመጣዉ፡፡

ጦርነትን ከፖለቲካ ዓላማ ዉጭ በማየት ለሁሉም ችግሮች መፍትሄ ማምጣት እንደሚችል ካሰብን በተገኘዉ ድል ስለማንረካ ትርፍ ፍለጋ መሻታችን አይቀርም፡፡  በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ጥናት እንዳደረገ የሚታወቀዉ ቡን ባርቶሎምስ(Boone Bartholomees)በጦርነት ሁሉንም ችግሮች መፍታት እንደማይቻል ይገልጻል፡፡  “..it is certainly possible to succeed in a war without achieving everything one sought or resolving all the extant issues. Winning implies achieving success on the battlefield and in securing political goals, but not, for whatever reason, reaching total political success.”

በጦርነቱ ማሳካት የፈለግነዉ ፖለቲካዊ ግብ ላይም ስምምነት ላይኖረን ይችላል፡፡ አንዳንዱ የጦርነቱን ዓላማ ሰፋና ለጠጥ አድርጎ ሊያስብ ይችላል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ሰዉ  በጦርነቱ ያሰበዉ ሁሉ ባለመገኘቱ በስንት ኪሳራ የተገኘዉን ድል ለመቀበል ሲቸገር ይታያል፡፡ አንዳንዶቻችን የሚቆጠርና የሚጨበጥ ነገር ካላሳዩን በስተቀር አሸናፊነታችንን አምነን ለመቀበል እንቸገራለን፡፡

ለምሳሌ ምን ያህል የጠላትን መሬት ተቆጣጠርን? አሰብ ወደብን አስመልሰናል?ባድመ፤ ጾረና ወዘተ በማን እጅ ናቸዉ? ናቅፋ ድረስ ደርሰናል? ስንት ታንክ አቃጠልን? ወዘተ በሚል በቁጥር የሚገለጽ ነገር ካልሆነ በስተቀር እንደ ድል ለመቀበል እንቸገራለን፡፡ ስንት የጠላት ወታደር ገደልን?ለሚለዉ መልስ ካለገኛን ከዚያ በመለስ ያለዉ ድል  ድል አይመስለንም፡፡ ፈረንጆች “body count syndrom” ይሉታል፡፡ የቁጥር ልክፍት እንደማለት ነዉ፡፡ በዚህ ምከንያትም በጦርነቱ አሸናፊነታችን እየታወቀ በተገኘዉ ድል ላይ ግን እኩል ደስተኛ ላንሆን እንችላለን፡፡

ለምሳሌ ሉአላዊነታችንን አስከብረን የተያዘብንን መሬት አስለቅቀን የፈረሰዉን መስተዳደር መልሰን ማቆማችንን፤ በጦርነቱ ምክንያት ተደነቃቅፎ የነበረዉን ሰላም አግኝተን በአንድ ልብ ወደ ልማት መዞር መቻላችን እንዲሁም  በሻዕቢያ ሰራዊት ላይ የደረሰዉ ቀላል የማይባል ጉዳትና በኤርትራ መንግስትና በህዝቡ መካከል፤ በራሱ በአገዛዙ ዉስጥም ሽንፈታቸዉን ተከትሎ የተፈጠረዉ ቀዉስ  ወዘተ ሁሉ እንደ ድል የማይቆጥሩ ወገኖች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

የጠላት ሰራዊትን ሙሉ በሙሉ ሳንደመስስ ፤የጠላትን ዋና ከተማ ሳንቆጣጠር፤ ተጨማሪ መሬት ወደ ራሳችን ሳናካትት፤ኢሳይያስን ከስልጣን ሳናወርድ ወዘተ  እንዴት ድል ተገኘ ትላላችሁ ብሎ የሚቆጣ ሊኖር ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ ባገኘነዉ ድል ላይ የተለያዬ አመለካከት ለመያዛችን አንዱ መነሾ መንግስት ወደ ጦርነት ለመግባት መንግስት ሲሰናዳ  ያስቀመጠዉ ዓላማ  ወይም ግብ ላይ ህዝቡ በተለያዩ መንገዶች  እንዲያዉቅና እንዲወያይበት ካለመደረጉ የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡

ህዝቡ ይቅርና በአመራሮችና በፖለቲከኞች ዘንድም በጦርነቱ ግብ ላይ አንድ ዓይነት አቋም መያዝ እንዳልተቻለ ይታወቃል፡፡ ጦርነት የማይቀር ከሆነ ሁልጊዜም ህዝቡና መንግስት እንዲሁም ፖለቲከኞች በጦርነቱ ፖለቲካዊ ዓላማ ላይ ግልጽ አረዳድ እንዲኖራቸዉ ማድረግ ተገቢ ነዉ፡፡ ቀደም ብሎ የተቀመጠዉ የፖለቲካ ዓለማ በጦርነቱ ሂዴት እንዳስፈላጊነቱ ሊቀየር የሚችልበት አጋጣሚም ስለሚኖር በየጊዜዉ ህዝቡን ማሳወቅ ይገባል፡፡ ያለበለዚያ ከጦርነቱ ዓላማ ላይ ስምምነት ከለለ ከጦርነቱ በኋላ ዉዝግብ መነሳቱ የማይቀር  ነዉ፡፡ በተለይ የመከላከያ ስራዊቱ ከላይኛዉ አመራር አስከ ታችኛዉ መሰረታዊ አባል በጦርነቱ ዓላማና ግብ ላይ ጥርት ያለ አረዳድ እንዲኖረዉ ማድረግ የግድ ነዉ፡፡

9.2/ የጦር ሜዳ ድልን ያለ መስዋአትነትና ያለ ኪሳራ የመሻት የተዛባ አመለካከት

በየትኛዉም ጦርነት ላይ የህይወት መስዋእትነት መክፈል የግድ ነዉ፡፡  ያለኪሳራ የሚመጣ ድል ብቻ ሳይሆን ጥሩ ተሸናፊ ለመሆንም የተወሰነ ዋጋ መክፈል የግድ ነዉ፡፡ ከኪሳራ ነጻ የሆነ (lose-free war) ጦርነት አይኖርም፡፡ በጦርነት ላይ የተገኘዉን ድልና ለዚያ ተብሎ የተከፈለዉን መስዋእትነት በማነጻጸር ኪሳራዉ ያለቅጥ የበዛ ከሆነ፡ድሉን የማጣጣል አዝማሚያ በሁሉም አገር የተለመደ ነዉ፡፡ ወታደራዊ ድሉ ተፈላጊዉን ፖለቲካዊ ግብ በሚፈለገዉ ደረጃ ካላመጣና በዚያ ላይ ደግሞ የተከፈለዉ ኪሳራ የበዛ ከሆነ ሁልጊዜም ጥያቄ ማስነሳቱ የግድ ነዉ፡፡

ህዝቡ “ለምን ይሄን ያህል መስዋእትነት መክፈል አስፈለገ? ከዚህ ባነሰ ኪሳራ ተመሳሳይ ድል ማምጣት አይቻልም ነበር ወይ?”የሚል ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ “እንደዚህስ ከሚሆን ቢቀርብን ይሻል ነበር” የሚልም ይኖራል፡፡  የሀገሪቱ ፖለቲካ አመራሮች በዚህ ጉዳይ ላይ ለህዝቡ በግልጽ ማስረዳት ይገባቸዋል፡፡ ህዝብ ዓላማዉ ግልጽ ላልሆነ ጦርነት ብቻ ሳይሆን ሙሉ የሕዝብ ድጋፍ ያገኘ ጦርነትም ቢሆን ከመጠኑ ያለፈ መስዋእትነትን (ኪሳራን) በጸጋ ለመቀበል አይፈልግም፡፡

የአሜሪካ ፖለቲከኞች ይህ የህዝብ አመለካካት ስለሚስፈራቸዉ ሚጢጢ ለሆነች ጠላትም ያልተመጣጠነና እጅግ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይልን ለመጠቀም ይመርጣሉ፡፡ የእኛንና የአሜሪካንን ህዝብ በጦርነት ከሚከፈል መስዋእትነት ላይ ባላቸዉ አመለካከት ወይም ዝንባሌ አንጻር ስናነጻጸር የአሜሪካ ህዝብ ኪሳራን በጸጋ የመቀበል ሳይሆን ኪሳራን የመፍራት (casualty phobic) ልማድ አለዉ፡፡ አሜሪካኖች ከጦርነቱ የሚፈልጉትን ድል አግኝተዉም ቢሆን ሂሳብ ወደ ማወራረድ ይገባሉ፡፡ ለምንስ ይህን ያህል ጉዳት ሊደርስብን ቻለ ? የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡

በአንጻሩ የኛ ህዝብ  ድሉ ይምጣ እንጂ መስዋእትነቱ የቱንም ያህል ቢሆን ብዙ የሚያሳስበዉ አይመስልም፡፡ ኪሳራን በጸጋ የመቀበል ወይም የመሸከም (casualty tolerance) ባህል አለዉ ማለት ይቻላል፡፡ ምናልባት ይህ ባህላችን በሀገር ጉዳይ ላይ ለሉአላዊነት ሲባል የፈለገዉን ያህል መስዋእትነት ለመክፈል ቁርጠኛ የመሆን የቆዬ ባህላችን ኢትዮጵያዉያን ለየትኛዉም ጠላት የማይንበረከኩ፤ነጻነታቸዉንም የማያስደፍሩና ሁልጊዜም አሸናፊ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የበኩሉን አስተዋኦ ያደረገ ይመስለኛል፡፡ ሁልጊዜም ተወራሪዎችና ተጠቂዎች የመሆናችን ቁጭት በሀገር ሉአላዊነት ላይ ለመጣ ጉዳይ ማንኛዉንም ኪሳራ ለመቀበል እንዳናመነታ ያደረገን ሳይሆን አይቀርም፡፡

እኛ ሁልጊዜም ወደ ጦርነት የምንገባዉ ትርፍ ፍለጋ አይደለም፡፡ የኛ አላማ ሁልጊዜም አለመደፈርና ካልሆነም የተነጠቅነዉን ማስመለስ ነዉ፡፡ ለኛ ጉዳዩ የትርፍና ኪሳራ ጉዳይ ሳይሆን የመብት፤የክብር ፤የሉአላዊነት ጉዳይ ነዉ፡፡ በሰብአዊ  ፤ኢኮኖሚያዊዉና ማህበራዊ አንጻር ብዙ ጉዳት ደርሶብን ሊሆን ይችላል፡፡ ኪሳራዉ የበዛ በመሆኑ ሊቆጠቁጠን ይችላል፡፡ ኪሳራን ለመቀነስ ጥረት ማድረግ አስፈላጊነት ባያጠያይቅም ነገር ግን ኪሳራን ፈርተን ሉአላዊነታችንን (መብታችንን) ሳናስከብር መቀመጥ አንችልም፡፡

የመስዋአትነታችን መብዛት ካገኘነዉ ድል ጋር የማይጣጣምና የበዛ መስሎ ሊታየን ይችላል፡፡ የመስዋእትነቱ ወይም የኪሳራዉ መብዛት የተገኘዉን ድሉ ሊያደብዘዉ መቻሉ እርግጥ ነዉ፡፡ ነገር ግን በድንገት ጥቃት ተፈጽሞብን ያገኘነዉን ድል በመስዋእትነት መብዛትና ማነስ መለካት አይኖርበትም፡፡ አሜሪካኖች መስዋእትነትን መፍራታቸዉ ከዉጭ ጥቃት ተሰንዝሮባቸዉ ሳይሆን እነሱ ራሳቸዉ ብዙ ሺህ ማይልስ እያቆራረጡ ትርፍ ፍለጋ በሰዉ አገር ላይ ጦርነት እያወጁ ስለሆነ  ለሞት ሽረታችን ብለን ከምንዋጋዉ ከኛ ጋር መነጻጸር  አይገባዉም፡፡

ይህ ማለት ግን እኛም ምክንያታዊ ያልሆኑና በአመራር ድክመት የመነጩ ኪሳራዎችም ሲኖሩ ዝም ብለን በጸጋ መቀበል አለብን ማለት አይደለም፡፡ በጦርነት ኪሳራን ለመቀነስ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በሚገባ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ይህ በወታደሩ ዉስጥ ብቻ ሳይሆን በይበልጥም በፖለቲካ አመራሩ አካባቢ መስራት የሚገባቸዉ ብዙ ነገር ይኖራል፡፡ ከሁሉም  አስተማማኝ ኪሳራ መቀነሻ ዜዴ አለ ከተባለ “ሁሌም ዝግጁ ሆኖ መገኘት” ስለሆነ ሰበብ ሳያበዙ የሀሪቱን መከላከያ ብቃት ለማሳደግና  የወትሮ ዝግጁነቱን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ስራዎችን ያለመታከት መስራቱ ነዉ የሚበጀዉ፡፡

10/ ተገቢ ነዉ የሚባለዉ ኪሳራስ ምን ያህል ነዉ?

ጠላት ጥቃት የሚሰነዝረዉ ወይም ጦርነትን የሚጭረዉ ያለምንም ዓላማ ሳይሆን ማግኘት ይገባኛል ብሎ ያሰበዉንና የራሱ ያልነበረዉንም ጭምር ብዙ ትርፍ ለማግኘት አቅዶ ነዉ፡፡ ያን ዓላማዉን ለማሳካትም ሊገጥመዉ የሚችለዉን ኪሳራም በቅድሚያ አስልቶና  አመቺ ጊዜ ጠብቆ  ነዉ፡፡ ስለዚህ ጠብ የጫረዉ ወገን (aggressor) ዓላማዉ ትርፍ ፍለጋ ስለሆነ ባልጠበቀዉ ሁኔታ ገና አነስተኛ ኪሰራ እየደረሰበት መሆኑን ሲረዳ ከጦርነቱ ፈጥኖ መዉጣትን ይመርጣል፡፡

በሌላ በኩል ጥቃት የተሰነዘረበትና ያለ ዉዴታዉ በግድ ወደ ጦርነት የገባዉ ወገን ራሱን ለመከላከል የሚከፍለዉ መስዋዕትነት የትኛዉንም ያህል የበዛ ቢሆን ለመቀበል ዝግጁ ነዉ፡፡ የሞት የሽረት በሆነ ጉዳይ ላይ፤ የነጻነት የሉአላዊነትና የመብት ጉዳይ ላይ በቂ ነዉ ወይም በዛ የሚባለዉ የኪሳራ መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ ማንም መገመት አይችልም ፡፡  በኢንግሊዘኛዉም የተለመደ “No price is too high to pay for one,s freedom.” አባባል ይህንኑ ሃሳብ የሚያጠናክር ነዉ፡፡

ሁልጊዜም ከጦርነቱ በኋላ የተገኘዉን ድልን ለዚያ ተብሎ ከተከፈለዉ ኪሳራ ጋር የማነጻጸር ነገር  የተለመደ ነዉ፡፡ ኪሳራ ሲባል በጦርነቱ ላይ ያጣነዉን የሰዉ ኃይልና ቁሳቁስ እንዲሁም ጦርነቱን ለማካሄድ የዋለዉ ኢኮኖሚ ሁሉ ተደማምሮ የሚታይ ነዉ፡፡ ሊደል ሃርት (Liddell Hart) “ድል የአሸናፊዉን ኢኮኖሚ ፣ወታደራዊ አቅምና ህብረተሰቡን የሚያደቅ ከሆነ ረብ የለሽ ነዉ” ይላል፡፡ (“a victory is useless if it breaks the winner’s economy or military or society”)፡፡

ይሁን እንጂ አሰቀድሜ እንደገለጽኩት የጦርነቱ ሰለባ የሆነዉ ወገን ማንኛዉንም መስዋእትነት ከፍሎ ሉአለዊነቱን ከማስከበር ዉጭ ሌላ አማራጭ ስለሌለዉ በጦርነቱ ላይ የደረሰበት ኪሳራ  የሚቆጠቁጥ ቢሆንም እንኳን ኪሳራዉን በጸጋ ለመቀበል ይገደዳል፡፡ ጠብ ጫሪዉ ወራሪ ወገን ግን የደረሰበት ኪሳራ እጅግ ይቆጠቁጠዋል፡፡ በራሱ ቆስቃሽነት ለደረሰበት ኪሳራ ወደፊትም እጥፍ ድርብ ዋጋ ይከፍልበታል፡፡ ብዙ ጊዜም እንደታዬዉ ጦርነት ቆስቋሹ መንግስት ስልጣን አስከመልቀቅና ለፍርድ አስከመቅረብ የደረሰ የከፋ ነገር ሊገጥመዉ ይችላል፡፡ ወደ ጦርነት በራሱ ቆስቋሽነት የገባ አገር ሽንፈት ከገጠመዉ ምነዉ በቀረብኝ አስኪል ድረስ ብዙ ችግሮች ይገጥሙታል፡፡

ስለዚህ የጦርነት ኪሳራ ለተሸናፊዉና አሸናፊዉ፤ ለወራሪዉና ለተወራሪዉ ፤ለአጥቂዉና ጥቃት ለተሰነዘረበት ወገን በእኩል  ደረጃ አይመዘኑም፡፡ ተጠቂዉ አገር (የጦርነቱ ሰለባ) ኪሳራዉን ለመቀነስ ያስችሉ የነበሩ የዥግጁነት ስራዎችን አስቀድሞ ሳይሰራ ተዘናግቶና ራሱን ለጥቃት አጋልጦ የተቀመጠ ከሆነ ጦርነቱን እንደምንም ብሎ ማሸነፉ ባይቀርም የሚደርስበት ኪሳራ ግን ከፍተኛ ነዉ የሚሆነዉ፡፡ ተገቢዉን ጥንቃቄ እያደረገ ቢቆይ ኖሮ ጠላት ጭራሽ ለጥቃት እንዳያስብ ማድረግም ይችል ነበር በሚል ሊጠየቅበት ይችላል፡፡ በሰላም ጊዜ መስራት የሚገባዉን ካለመስራት የተነሳ ራሱን ለጥቃት አጋልጦ ከተቀመጠ ብዙ እጅግ ብዙ ኪሳራ ካልከፈለ በስተቀር ወራሪን ኃይል ለመመከት እንደሚያዳግተዉ ግልጽ ነዉ፡፡

ለዚህ አብነት የሚሆነን ከክርስቶስ ልዴት በፊት እንደ ነበረዉ የእፕሩስ (Epirus) ንጉስ የነበረዉ ፓይረስ (Pyrrhus) በሮማ ላይ ድል ለማግኘት የከፈለዉ ኪሳራ ብዛት ከዚያ በኋላ ሌላ ተመሳሳይ ጦርነት ድጋሚ ቢነሳ ፈጽሞ መቋቋም በማያስችለዉ ደረጃ ኃይሉ የተመናመነበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ሮማዉያን ግን ለጊዜዉ ቢሸነፉም እንኳን በቂ ኃይል ለማቀብ በመቻላቸዉ በሌላ ጊዜ ተመልሰዉ እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ ነበሩ፡፡

ተከላካይ ወይም ተጠቂ ስለሆንክ ብቻ የቱንም ያህል ኪሳራ ከፍለህ ሉአላዊነትህን ማስከበር አለብህ ማለትና ኪሳራዉ አንዳችም ጥያቄ አይነሳበትም ማለት ለየቅል ናቸዉ፡፡ ሉአላዊነትን ማስከበር መቻል ለዚያ ተብሎ ለተከፈለዉ ኪሳራ ማካካሻ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ድል መገኘቱ አንድ ጥሩ ነገር ሆኖ ነገር ግን ኪሳራዉ ያለቅጥ የበዛ ከሆነ አነስ ባለ ኪሳራ ድል ማምጣት አይቻልም ነበር ወይ? የሚል ጥያቄ መነሳቱና ማከራከሩ አይቀርም፡፡ ኪሳራዉን ለመቀነስ የሚያስችል(casualty minimizing measures)  ምን እርምጃ ተወሰደ  የሚል ግምገማ ማድረግም  የሚጠበቅ ነዉ፡፡

ጉዳዩ ሂሳብ የማወራረድ ዓይነትም  ባይሆን በስልጣን ላይ ያለዉን መንግስት  ኃላፊነት የመወጣት ብቃት የሚመዘንበት ትልቅ አጋጣሚ ተደርጎ ስለሚቆጠር ነዉ፡፡ መንግስት  የሰዉ ኃይል ብልጫ መኖርን ተማምኖ በሰዉ ማዕበል ጦርነትን ማሸነፍ ይቻላል በሚል የተሳሳተ ግምት አንዳችም ዝግጅት ሳያደርግ የሚቀመጥ ከሆነ  የዚህ ዓይነት መንግስት እምነት የሚጣልበት አይሆንም፡፡ በሀገራችን የኤርትራ የተቃጣብንን ወረራ ለመመከት በተደረገዉ ጦርነት የከለፈልነዉ መስዋትነትና የተገኘዉ ድል በሚመለከት የተደረገ ህዝባዊ ዉይይትም ሆነ የመንግስት ይፋ መግለጫ ስላለለ የራሴን አስተያየት መስጠት ያዳግተኛል፡፡

ለሉአላዊነታችን ማንኛዉንም ኪሳራም ቢሆን ከፍለን ማስመለሳችን ተገቢ ነዉ እላለሁ፡፡ ሁልግዜም ለዉጭ ጥቃት ሰለባ ለሆነዉ ለኛ ከዚህ የተለየ አማራጭ የለንም፡፡ ነገር ግን በሰላም ግዜ ተገቢ ጥንቃቄ ሳናደርግ ተዘናግተን በመቀመጣችን ብቻ ራሳችንን ለጥቃት በማጋለጥ ከሚገባዉ በላይ ኪሳራ ለመክፈል የምንገደድበት መጥፎ ተሞክሮአችን ሊታረም እላለሁ፡፡ ከኤርትራ ጋር ያደረግነዉ ጦርነትም መታየት ያለበት  ከዚህ አንጻር ነዉ፡፡

11/ ድሉ ትልቅ ትርጉም የሚኖረዉ ከጦርነቱ በኋላ ዘላቂ ሰላም ማምጣት ሲቻል ነዉ

ብዙዎቹ የሚስማሙበት ነገር ብዙ መስዋእትነት ተከፍሎበትም ድል ከተገኘም በኋላ ዘላቂ ሰላም ማስፈን በጣም አስቸጋሪ መሆኑ ነወ፡፡ አንዳንዴ በጦርነቱ ወታደራዊ ድል ተገኝቶም ሰላም ላይመጣ ይችላል፡፡ በጦርነት ድል ማድረግና ሰላምን ማስፈን የተለያዩ ነገሮች ናቸዉ፡፡ ወታደራዊ ድልን ተከትሎ ሰላምና መረጋጋት (peace & stability) ካልሰፈነና የነበረዉ ሁኔታ በቦታዉ ከልተመለሰ ተገኘ የተባለዉን ድል ትርጉም አልባ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም ነዉ ከድል በኋላም ሰላምን ማምጣት አለመቻል ከሽንፈት ተለይቶ አይታይም የሚባለዉ፡፡ ፈረንጆች (winning war but losing peace) እንደሚሉት ማለት ነዉ፡፡

ፖለቲከኞች ወደ ጦርነት ለመግባት የሚጣደፉትን ያህል ከጦርነቱ ለመዉጣት ብዙም አይጨነቁም፡፡ ሌላዉ ቀርቶ ወደ ጦርነቱ ከመግባታቸዉ በፊት የጦርነቱን ዓላማ አንጥረዉ ማስቀመጥ ይቸግራቸዋል፡፡ የጦርነት ዓላማና ስትራቴጂ አስቀምጠዋል ቢባል እንኳን በጥቂት ሰዎች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ፡ እጅግ የተለጠጠ ምክክርም ያልተደረገበትነሰ አማራጭ አስተያዬትም ያልተሰጠበትና ምናልባትም ጭራሽ ያልተወያዩበት ሊሆን ይችላል፡፡ ህዝቡንማ ጭራሽ ስለሚዘነጉት የጦርነቱን ትክክለኛ ዓላማም አይገልጹለትም፡፡  ልጆቹ  ለየትኛዉ ዓላማ ተብሎ መሞት እንዳለባቸዉ ህዝቡ የሚያዉቀዉ ነገር ላይኖር ይችላል፡፡

ከሁሉም በላይ የከፋዉ በጦርሜዳ ለሚዋደቀዉ ሰራዊትና አዛዦች ግልጽ የሆነ ግብ ሳያስቀምጡ ፖለቲከኞች ወታደሩን በደመነፍስ ወደ ዉጊያ መስገባታቸዉ ነዉ፡፡ ፖቲከኞች ራሳቸዉ ጦርነቱ መቼ ሊያበቃ እንደሚገባዉ አያዉቁም፡፡ ወታደሩ በጦርሜዳ አንዱን ሲያሳካ በፊት ያልነበረ ሌላ ተልዕኮ እየሠጡት እድሜ ልኩን በጦር ሜዳ እንዲበሰብስ ያይርጉታል፡፡ ፡

ጦርነት የሀገሪቱ ፖለቲካ አመራር ወይም የፖሊሲ አዉጭዎች (policymakers) ዝንባሌና እምነት የሚንጸባረቅበትና በአመራሩ ፍላጎት ተጽኢኖ ስር የወደቀ መሆኑ ባይቀርም ነገር ግን ፖሊሲ አዉጭዎች ወታደራዊ ኃይልን በተግባር ለሚጠቀሙት የጦር መሪዎች (አዛዦች) ከጦርነቱ ምን እንደሚፈልጉና ጦርነቱ እንዴት ባለ ሁኔታ ማብቃት እንዳለበት አስቀድመዉ ማስረዳት ይገባቸዋል፡፡

በኛ ሁኔታም የኤርትራን ሰራዊት ከኛ ይዞታ ካስወጣንና መስተዳድራችንንም በቦታዉ ከተካን በኋላ ወደፊት የመግፋትና ያለመግፋት ጉዳይ እንደ ጥያቄ እንዴት ሊነሳ ቻለ? ጄነራሎቹ አስቀድሞ አልተነገራቸዉም ነበር እንዳይባል አስተያየታቸዉ እንደተጠየቀና ማጥቃቱ እንዲቆም ቅድመ ስምምነት እንደነበረ መረጃዉ አለ፡፡ ታዲያ ይሄ ሁሉ ጫጫታ ለምን ተፈጠረ? ወይንስ ተነግሮአቸዉም እያለ አላመኑበትም ማለት ነዉ? ለምንድነዉ ይህ ሁሉ ዉዝግብ ለመነሳት የቻለዉ? የምንፈልገዉን አግንተናልና ከዚህ በኋላ ጦርነቱን ከዚህ በላይ መግፋት የለብንም የሚል አቋም የነበራቸዉ ሰዎች ለኤርትራ የወገኑ ተደርጎ እንዲቆጠርባቸዉ የተደረገበት ምክንያትስ ተገቢ ነበር እንዴ?

ጦርነት እንዴት ማብቃት እንዳለበት የመረዳት ችግር  በኛ ብቻ ሳይሆን እንደ አሜሪካ ባሉትም አካባቢ ብዙ ግዜ ሲያወዛግብ ይታያል፡፡ በመሰረቱ የጦርነቱ የመጨረሻዉ መዳረሻ ግብ (end-state) ብቻ ሳይሆን ጦርነቱ የሚቆምበት ሁኔታም አብሮ በቅድሚያ መታሰብ አለበት፡፡ ከጦርነቱ ለመዉጣትም እሰቀድሞ የታሰበበት የጦርነት ማብቂያ(ከጦርነት መዉጫ) ግብ ሊኖረን ይገባል፡፡

ስለዚህ የሀገሪቱ መንግስት ጦርነቱን መቼ እንዲጠናቅ እንደሚፈልግ ግልጽ የሆነ ከጦርነት መዉጫ ግብ ማስቀመጥና ለአዛዦች ማስረዳት ይገባዋል፡፡ ከዚያ ዉጭ ግን አስቀድሞ ባልታሰበበት አጋጣሚ ላይ በድንገት ተነስቶ  ዉጊያ (ማጥቃት) እንዲያቆሙ ሲያዝ  በግንባር ያሉ አዛዞች ግራ መጋባታቸዉና ጥያቄ ማንሳታቸዉ አይቀርም፡፡ ይህም አላስፈላጊ ወደ ሆነ ዉዝግብና ቅራኔ ዉስጥ ይከታል፡፡

ይህን ሃሰብ የበለጠ ግልጽ ለማድረግ አንድ አብነትን መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

በሳዳም ሁሴን ስትመራ የነበረችዉ ኢራቅ እ.ኤ.አ. ነሐሴ 2/1990 ዓ/ም ላይ ኩዌትን ወረረች፡፡ ያን ተከትሎም የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ቡሽ በኢራቅ ላይ ስለሚወስዱት እርምጃ ከመከሩ በኋላ ለጥቃቱ ግልጽ የሆነ የብሄራዊ ፖሊሲ ግብ (national policy objectives) አስቀመጡ፡፡ ከግቦቹ ዉስጥ ሁለቱን ብቻ ለመጥቀስ ያህል “ያለምንም ቅደሜ ሁኔታ የኢራቅ ጦር በአስቸኳይ ኩዌትን ለቆ እንዲወጣ ማድረግ“ የሚልና “የፈረሰዉን የኩዌትን ህጋዊ መስተዳድር መልሶ ማቋቋም“ የሚሉ ናቸዉ፡፡ (“… Immediate, complete, and unconditional withdrawal of all Iraqi forces from Kuwait; Restoration of Kuwait’s legitimate government.”):፡

በእቅዱ መሰረትም የሳዳም ጦርም ተቀጥቅጦ ኩዌትን ለቆ እንዲወጣ ከተደረገና የፈረሰዉም መስተዳደድር መልሶ ከተቋቋመም በኋላ አሜሪካኖች የተሟላ ድል ተገኝቷል ለማለት ተስነኗቸዉ ነበር፡፡ ምክንያቱም ጦርነቱ ቢያበቃም ከጦርነቱ በኋላ የተሟላ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር ባለመቻሉ ነዉ፡፡ ከዚህም ሌላ ሳዳም ሁሰን ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ለወደፊቱ ተመሳሳይ ችግር እንደማይፈጥር እርግጠኛ መሆን አይቻልም የሚል አዲስ ነገርም መጣ፡፡

እንዲያዉም አንድ በጦርነቱ የተማረከ የኢራቅ ጄነራል ስለዚሁ ጉዳይ ለአሜሪካኖች እንደገለጸዉ “የእባቡን አካል ከጥቅም ዉጭ አድርጋችኋል፡፡ ነገር ግን ዋናዉን ጭንቅላቱን ገና አልነካችሁትም” በማለት የአመራሩ ራስ የነበሩት ሳዳም ስልጣን ላይ አስካሉ ድረስ ችግሩ ተቀርፏል ለማለት እንደማይቻል በሚገባ ገልጾ ነበር፡፡ “You have destroyed the body of the snake, but you missed the head” ነበር ያለዉ፡፡

የኢራቅ ጦር ኩዌትን ለቆ ከወጣና የፈረሰዉ መስተዳድርም በቦታዉ ከተተካ በኋላ ከዚያ በላይ በጦርነቱ መግፋት ሆን ተብሎ ኢራቅን ያለ ሰራዊት ባዶ ለማስቀረትና የሀገሪቱን መሰረተ ልማት  መዉደም ተደርጎ ስለሚቆጠርና  ህገወጥም ስለሆነ በአስቸኳይ ጦርነቱ መቆም ይገባዋል በሚል ለፕሬዝዳንቱ በቀረበዉ ምክረ- ሀሳብ መሰረት ፕሬዝደንቱም የኢራቅን ጦር በመደምሰስ ሊገኝ ከሚችለዉ ወታደራዊ ጥቅም ይልቅ ሊያስከትል የሚችለዉ ፖለቲካዊ ኪሳራ (political cost)  እንደሚያመዝን በመረዳታቸዉ ማጥቃቱ በአስቸኳይ እንዲቆም አድርገዋል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ የተፈጠረዉ ሁኔታ ግን አሜሪካኖችን ብዙ ነገር ለማስተማር የበቃ ሁኔታ ነበር፡፡ ይሄዉም በታቀደዉ መሰረት ግቡ ከተሳካ በኋላ ማለትም የኢራቅ ጦር ኩዌትና ለቆ ከወጣና መስተዳድሩ በቦታዉ ከተተካ በኋላ የህብረብሄራዊዉ  ጥምር ጦር አዛዥ ቀጥሎ ምን ማድረግ እንዳለባቸዉ ባለማወቃቸዉ ግራ ተጋብተዉ ነበር፡፡

ጦርነቱ ከተገመተዉ ባጠረ ጊዜ ድል ሲያስገኝ ቀጥሎ መወሰድ ስለሚገባዉ አርምጃ የሚያወቅ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም የጦሩ አዛዥ የተቀመጠላቸዉን ግብ ካሳኩ በኋላ በራሳቸዉ ፍላጎት ያለሀገሪቱ ፖለቲካ አመራር ፈቃድ አንዲትም ጋት ወደፊት መግፋት ወይም ሌላ እርምጃ መዉሰድ እንደማይፈቀድላቸዉ ጠንቅቀዉ ስለሚያዉቁ ጠቅላይ አዛዡን (ፕሬዝዳንቱን) መጠየቅ ነበረባቸዉ፡፡ በዚህ መሰረትም ፕሬዝዳንቱ ያደረጉት ነገር ቢኖር ከጦርነቱ በፊት ታስቦበት ያልተቀመጠ አዲስ ግብ ለማስቀመጥ ተገደዱ፡፡  እሱም “ኬዌት ጠንካራ ወደ ሆነ ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንድትገባ ማገዝ” የሚል ነበር፡፡

በፊት ያልነበረ ዲሞክራሲያዊ ስርአት በኩዌት የመመስረት ሃሳብ እንደ አንድ ግብ ተቀመጠ ማለት ነዉ፡፡ በርግጥ በወቅቱ በርካታ ፖለቲከኞች “ስራ ከምፈታ ልጄን ላፋታ” እንደሚባለዉ የሀገራችን አባባል ሰራዊቱ ያለስራ ከሚቀመጥ ለወደፊት በኢራቅም ሆነ በአካባቢዉ አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠር ለማድረግ መሪዉን ሳዳምን ከስልጣን የማስወገድ አዲስ ግዳጅ ለሰራዊቱ እንዲሰጥ ፕሬዝዳንቱን መጎትጎታቸዉ ባይቀርም ፕሬዝዳንቱ ግን ይሄን ሃሳብ አልተቀበሉም፡፡

ለማንኛዉም ከዚህ ሁኔታ መማር የምንችለዉ የጦርነቱ ግብ በማንኛዉም ወቅት ላይ የሀገሪቱ ፖለቲካ አመራር ሊቀይር ወይም ሊያሻሽል እንደሚችል ወታደራዊ አዛዦች ከጠቅላይ ኣዛዣቸዉ ከተቀመጠላቸዉ  ግብ ዉጭ ያለ ፈቃድ  አንድትም ጋት ወደፊት መግፋት እንደማይችሉ እንዲሁም ከጦርነቱ መቼ መዉጣት አንደሚገባ ገና ከመጀመሪያዉ ሊታሰብበት የሚገባ እንጂ በድንገት የሚደረግ አለመሆኑን ነዉ፡፡

12/ ማጠቃለያ

የኤርትራ ወረራ እኛ ፈልገን የገባንበት ሳይሆን ሉአላዊነታችን በመደፈሩ ምክንያት ለዚያዉም ችግሩን በሰላም ለመጨረስ ያደረግነዉ ጥረት በለመሳካቱ ምክንያት ተገደን የገባንበት ነዉ፡፡ ብዙ መስዋእትነት ቢያስከፍለንም በኃል የተነጠቅነዉን ሁሉ በኃይል ማስመለስ ችለናል፡፡ ከሁሉም በላይ በጦርነቱ ምክንያት ተቀዛቅዞ ወደ ነበረዉ የልማት ስራችን በአንድ ልብ ተመልሰን የህዝባችንን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ጥረት እደረግን ነዉ፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ በህዝባችን ዘንድ በድሉ እርካታ እንዳይኖር ያደረገ አንድ ጉዳይ ቢኖር የባህር በር ጉዳይ ነዉ፡፡ ወደ ጦርነት ስንገባ እንደ እቅድ ያልያዝነዉ ቢሆንም መንግስት ወደፊት በተለየ መንገድ መፍትሄ ያገኝለታል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ከኤርትራ ጋር አስካሁን የተቋጨ ነገር አለመኖሩና በመካከላችን ዘላቂ ሰላም አለመፈጠሩ ጦርነቱ ካበቃም በኋላ ከስጋት ነጻ መሆን አልቻልንም፡፡ መንግስት  በቅርብ ግዜ ዉስጥ አንድ መፍትሄ ያመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

********

(የዚህን ፅሁፍ ቀጣይ ክፍሎች በዚህ ሊንክ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኮ/ል አስጨናቂ ገ/ፃድቅ ማግኘት ይችላሉ)

*የኮ/ል አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሌሎች ጽሑፎች ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፡፡

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories