የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት 2 | በየዘመኑ የነበሩ መሪዎቻችን የኤርትራን ጉዳይ ያስተናገዱበት አግባብና ሲከተሉት የነበረዉ ፖሊሲ

(ኮ/ል አስጨናቂ ገ/ፃድቅ)

(የዚህን ፅሁፍ የመጀመሪያ ክፍል በዚህ ሊንክ ማግኘት ይችላሉ)

Highlights 

+ የኤርትራ ችግር የአንድ ዘመንና የአንድ ወቅት መንግስት የብቻ ስህተት ሳይሆን  የቀደመዉ  መንግስት የሰራዉን ስህተት ተተኪዉ መንግስት በከፋ ሁኔታ  እያወሳሰበ ለመፍትሄም አስቸጋሪ እያደረገዉ በመጨረሻም ለይቶለት ለግንጠላ የዳረገ በቅብብሎሽ የተሰራ ጥፋት ነዉ፡፡ ክፋቱ ደግሞ ኤርትራ ራሷን ችላ ወይንም ከኛ ተነጥላም ከኛ ራስ አልወርድ እያለች ስታስቸግረን መቆየቷ ነዉ፡፡

+ የኤርትራ መገንጠልና እንደ ዋዛ እዉቅና ማግኘት የአንድ ክልል ወይም ህዘብ የመነጠል ጉዳይ ብቻ ተደርጎ የሚቆጠር አይደለም፡፡ የኤርትራ መገንጠል በቀጥታ ካስከተለዉ ዉጤት በላይ ለኢትዮጵያ የወደፊቱ ሉአላዊነት ላይ ከፍተኛ የስጋት የፈጠረዉ መጥፎ አርአያነት (dangerous precedent) ለሌሎች ብሄሮችና ህዝቦች መገንጠል እንደሚቻል ያስተማረና ሁልጊዜም ስለመገንጠል እንዲያስቡ ያደረገ መጥፎ ክስተት መሆኑ ነዉ፡፡

+ በተለይ ካለፈዉ ሁለት ዓመት ግዜ ወዲህ በሀገራችን አንዳንድ ክልሎች የታየዉ “ራስን በተለየ ተበዳይና ተጎጂ” የማድረግ፤ የክልሉን የተፈጥሮ ሃብት ለብቻ መጠቀም አለብን ከሚል አመለካካት በመነሳት ማንም አይደረስብን የሚለዉ ሌላዉን ህዝብ የመጥላትና ከዚሁ ጋር አብሮ በአንዳንድ ክልሎች መካካል የታየዉ የመስፋፋት አባዜና የወሰን ግጭቶች ወዘተ ሁሉ በድምር ሲታይ በሀገሪቱ አንድነት መጻኢ እድል ላይ አደጋ  ሊያስከትል የሚችል አዝማሚያ በመሆኑ አስቀድሜ ለጠቀስኩት ስጋት ጥሩ ማሳያ ነዉ፡፡

+ እንደሚታወቀዉ በየዘመኑ የነበሩት የኢትዮጵያ መንግስታት ከሚነቀፉበት አንዱና ትልቁ ጉዳይ ኤርትራን በሚመለከት ሲከተሉት የነበረዉ ፖሊሲ ነዉ፡፡ ኤርትራን በሚመለከት ከሚሰነዘረዉ ወቀሳ ጣሊያንን ድባቅ በመምታት እንጸባራቂዉን የአድዋ ድል የተገኘበትን ጦርነት በመምራት ስመ ገናና የሆኑት ዳግማዊ ምንሊክም ከወቀሳዉ ሊያመልጡ አልቻሉም፡፡ ምንሊክ በሽሽት ላይ የነበረዉን የጣሊያንን ሰራዊት መረብን አሻግረዉ ከሚተዉት አስከመጨረሻዉ አሳዳዉ መደምሰስ ነበረባቸዉ በሚል ነዉ የሚተቹት፡፡

በምንሊክ ላይ ወቀሳ አቅራቢዎቹ ሁኔታዉን አቅለዉ እንደሚናገሩት ሳይሆን ምንሊክ በወቅቱ እንደዚያ ለማድረግ ቢፈልጉ እንኳን ማድረግ የሚችሉበት አቅም (ሁኔታ) አልነበራቸዉምና ወቀሳዉ ያለቦታዉ የተሰነዘረና አግባቢነት የሌለዉ መሆን ብቻ ሳይሆን እንዲያዉም ለምንሊክ ካላቸዉ ጥላቻ ስማቸዉን ለማጉደፍና ዉለታቸዉን ለማሳነስ የሚደረግ አጉል ሙከራ ነዉ፡፡ በምንሊክ ላይ የሚሰነዘረዉ ትችት የአንድነት ስሜት ከነበራቸዉ ኤርትራዉያንም ጭምር ነዉ፡፤“እኛ ኤርትራዉያን  ንጉስ ምኒሊክ ለጣሊያን ሸጠዉን ነዉ እንጂ ኢትዮጵያዉን ነን ”የሚሉ የቁጭት ንግግሮች ከራሳቸዉ ከኤርትራዉን ይደመጥ እንደነበር አምባሳደር ዘዉዴ ረታን ጨምሮ በተለያዩ ታሪክ ጸሃፊዎች ተዘግቧል፡፡

የደርግ ባለስልጣን የነበሩት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርግስም “የደም እምባ” በሚለዉ መጽሀፋቸዉ ላይ እንደጠቀሱት  በኤርትራ ከሁሉም ከብረ በዓላት ሁሉ በቀዝቃዛ መንፈስ የሚከበረዉ የአድዋ ድል በዓል መሆኑንና የዚህ ዋነኛ ምክንያትም “ምንሊክ ጣሊያንን ከመረብ ምላሽ አባረዉ የቀረዉን የኤርትራን ህዝብ ለጣሊያን ባሪነት አሳልፈዉ ሰጥተዉናል” ከሚል ቁጭት  ነዉ፡፡ ይህንን ቁጭት መንፈስ ገልብጠዉ ለራሳቸዉ ኣላማ ለመጠቀም የሞከሩ ገንጣዮች ምንሊክ ይሄን ያደረጉት ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል እንዳልነበረች በመረዳታቸዉ ስለሆነ“ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ሆና አታዉቅም” ለሚለዉ ክርክራቸዉ እንደ አንድ ትልቅ መከራከሪያ የሚያቀርቡት ይሁንን ከስተት ነዉ፡፡

+ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴን በሚመለከት ደግሞ ፌዴሬሽኑን በማፍረስ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት በመፈጸማቸዉ ከዚያ በኋላ ለተከሰቱት ችግሮች ሁሉ መነሻ ሆኗል በሚል ይወቀሳሉ፡፡ ይህን ወቀሳ ብዙዎቹ የሚስማሙበት ነዉ፡፡ ንጉሱ ይህን እርምጃ ለመዉሰድ የበቁት ሁኔታዉ ለአስተዳደራቸዉ ስለአላመቻቸዉ በተለይም ይሄ ሪፌሬንደም የሚባለዉ ጣጣ ወደ ሌሎች ክልል ህዝቦችም ተጋብቶ መጥፎ አርአያነት እንዳይሆን በመስጋትና በተጨማሪ የምጽዋና የአሰብ ወደብ ዕጣ ፈንታ ስለአሰጋቸዉ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

ንጉሱ ወደዚህ ዉሳኔ የደረሱት በራሳቸዉ ተነሳሽነት ሳይሆን አንድነትን እንጂ ፌዴረሽኑን እንፈልግም በሚሉ የራሳቸዉ የኤርትራ ፓርላማ አባላትና በአብዛኛዉ የኤርትራ ህዝብ ጥያቄ ተደፋፍረዉ ያደረጉት ነዉ፡፡ የንጉሱ ዉሳኔ ምንም ይሁን ምን የኤርትራን ጉዳይ ማወሳሰቡ ግን እርግጥ ቢሆንም እሳቸዉ (ንጉሱና) አክሊሉ ሃብተወልድ ኤርትራን መጀመሪያ ከጣሊያን ቅኝ አገዛዝ ከዚያ ደግሞ ሞግዚት አስተዳደር አላቀዉ መጀመሪያ በፌደረሽን ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ አካል እንድትሆን ለበርካታ አመታት ያደረጉት እልህ አስጨራሽ ጥረት እጅግ የሚደነቅና የሰሩት ስህተት ቢኖር እንኳን ለኢትዮጵያ ጥቅም ተብሎ መሆኑ ሊዘነጋ የሚገባዉ አይደለም፡፡

+ ደርግ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነትን ያደረገዉን ተጋድሎ መካድም  ሆነ ማጣጣል ትልቅ ታሪካዊ ግድፈት ነዉ፡፡ የደርግ ትልቁ ችግር ለአንድነት መታገሉ ወይም ኤርትራን እንዳትገነጠል ለማድረግ መዋጋቱ ሳይሆን አጠቃላይ ችግሩን ያስተናገደበት መንገድ የተሳሳተ መሆኑ ነዉ፡፡

ጦርነትን እንደ ብቸኛ መፍትሄ በመቁጠሩ ከጦርነቱ ጎን ለጎን ወይም አስቀድሞ በሰላማዊ መንገድ ለችግሩ መፍትሄ ለመፈለግ አስከመጨረሻዉ ድረስ ጥረት አለማድረጉ ጥልቁ ችግሩ ነዉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የኤርትራ ህዝብ ከጎኑ እንዲሰለፍ በማድረግ የኤርትራን መገንጠል እንዲያወግዙ ካደረገዉ ጥረት ይልቅ በተቃራኒዉ ህዝቡ እንዲማረር በማድረግ አማጽዉን ቡድን በሞራልና በሰዉ ኃይል እንዲያጠናክሩ ሁኔታዉን ምቹ ማድረጉ  ዋነኛዉ ተጠቃሽ የደርግ ስህተት  ነዉ፡፡

+ የእኔ አመለካከት መነሻ መለስ ግትር በሆኑ አንዳንድ አክራሪ የድርጅቱ ሰዎች ተጽኢኖ ስር በመዉደቃቸዉ እንዳሰቡት ሊሆን ባይችልም ነገር ግን በኢትዮጰያ አንድነት ላይ የማያወላዉል አቋም የነበራቸዉና ኤርትራ ከመገንጠል ይልቅ በአንድነት እንድትኖር  ጽኑ ፍላጎት የነበራቸዉ መሆናቸዉን ስለምረዳ ነዉ፡፡ በእኔ እምነት መለስ በኤርትራ ጉዳይ ከቀሩት የኢህአደግ አመራሮች ጋር ተዳብለዉ እኩል መወቀስ አይኖርባቸዉም፡፡ መወቀስ ካለበትም መወቀስ ያለበት ደርጅቱ ነዉ፡፡

አሰብን ለባለቤቱ ለኢትዮጵያ በማንኛዉም መንገድ ማስመለስ ነበረባቸዉ በሚል መለስን የሚወቅሱ ወገኖች በርካታ መልካም አጋጣሚዎችን ሳንጠቀምባቸዉ የቀረነዉ በመለስ ፍላጎት ማጣት ነዉ በሚል መለስን በተደጋጋሚ ሲወቅሱ ይደመጣሉ፡፡ ከነዚህ መልካም አጋጣሚዎች ከሚባሉት መካከልም የጦርነቱ መነሳት ሲሆን ያን አጋጣሚ በመጠቀም በኃይል ማስመለስ ይቻል ነበር የሚል ነዉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ አሁንም ድረስ በህይወት ያሉ ከፍተኛ የሰራዊቱ አዛዦች ይህን አመለካከት ይጋሩት እንደሆነ አርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ቢያንስ ግን አጋጣሚዉ ፈቅዶልኝ ከጦርነቱ በኋላ መለስ ሲመሩት በነበረዉ አንድ ስብሰባ ላይ መለስ ሲናገሩ ከነበረዉ የተረዳሁት ነገር ቢኖር በጦርነቱ ወቅት መከላከያ ሰራዊታችን አሰብን እንዲቆጣጠር ለማድረግ መለስ መመሪያ ሰጥተዉ እንደነበርና ነገር ግን በተግባር እዉን ማድረግ አለመቻሉን ነዉ፡፡ በወቅቱ መለስ ሲናገሩ እንደሰማሁት የጦርነቱን አጋጣሚ በመጠቀም አሰብን በእጃችን ለማድረግ መሞከራቸዉን ነዉ፡፡

+ የኤርትራ ህዝብ በተለይ በደርግ ስርአት ኢትዮጵያዊ መባሉ ያስገኘለት አንዳች ጥቅም ቢኖር ኖሮ ደርግ ከወደቀ በኋላ አብሮ ለመኖር ፍላጎት ሊያሳይ ይችል ነበር፡፡ ግን አንድም በመልካም ጎኑ የሚያስታዉሰዉ ነገር ስላልነበረ በሪፌሬንደሙ ወቅት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ለብቻዉ መሆኑን መርጧል፡፡ ይህ ሁኔታ ማለትም የኤርትራ ህዝብ በደርግ ምክንያት ከኢትዮጰያ ጋር አብሮ መኖርን እጅግ አደርጎ በመጥላቱ መለስም ሆነ ኢህአዴግ ይሄን ነገር መለወጥ የሚችሉበት አንዳችም አድል አልነበራቸዉም፡፡

+ ስለዚህ ገና ለገና የመለስን ሆነ የድርጅቱን የሚያሳጣ ነገር ሊኖርበት ይችል ይሆናል ተብሎ ሚሊዮኖች የሚያዉቁትን ታሪክ ለመደበቅ መሞከር የዋህነት እንጂ ሌላ ሊሆን  አይችልም፡፡ አቶ መለስን ፍጹምና ጨርሶ የማይሳሳቱ አድርገዉ የሚቆጥሩ ሰዎች የመኖራዉን ያህል የሳቸዉን ቅንጣት ስህተት በማጉላት ያበረከቱትን ዉሌታ ለመካድ የሚፈልጉ ሁለቱም ዓይነት ሰዎች ለእኔ አይስማሙኝም፡፡

+ ሰራዊታችን በኤርትራ ዉስጥ ገብቶ በጥልቀት ሲያደርግ የነበረዉን ማሳዳድ ,እንዲያቆም መለስ ከማዘዛቸዉ በፊት የጄኔራሎቻቸዉን ሃሳብ ለማወቅ በቅድሚያ እንዳማከሯቸዉና እነሱም ከዚ በላይ ወደፊት መግፋት እንደማይችሉ መልስ እንደሰጧቸዉ ይታወቃል፡፡ መጀመሪያም ወደዚህ ዉሳኔ ለመምጣትም ጉትጎታ የነበረዉ ከሌሎቹ የፓርቲዉ አመራሮችና ከአንዳንድ ወታደራዊ ሹሞች እንደነበርም ግልጽ ነዉ፡፡

መለስ ጄኔራሎቹን አማክረዉ ወደፊት ለመግፋት አንደማይችሉ መልስ ከሰጡዋቸዉ በኋላ ነዉ ዉሳኔዉን የወሰኑት፡፡ መለስ ሰራዊቱ ማጥቃቱን እንዲያቆም ትዕዛዛ ከመስጠታቸዉ በፊት ወታደራዊ ሽማምንቱን አማክረዋል፡፡ ስለዚህ ሁኔታ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ እሳቸዉ በሚመሩት አንድ ስብሰባ ላይ ሁኔታዉን አስታዉሰዉ በድጋሚ ስናገሩ ከጀኔራሎቹም ሆነ በቦታዉ ከነበሩት አንዳንድ የፓርቲያቸዉ አመራሮች መካከል ይሄን ጉዳይ ያስተባበለ አንድም ሰዉ አልነበረም፡፡

+ መለስ በሉአላዊነት ጉዳይ ላይ ያለአግባብ ሲወቀሱ እንደነበር ጥሩ ማሳያ የሚሆነን ለኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላዉ ዓለም መሳቂያ መሳለቂያ ያደረገን “ባድመ ለኛ ተወስኗል! ”ተብሎ ህዝብን ያለአግባብ አስጨፍረን ስናበቃ በማግስቱ እንደተባለዉ አለመሆኑ የታወቀበት አሳፋሪ ክስተት ነዉ፡፡ ይሄን ግዙፍ ስህተት የሰራዉ (ነገሩ ስህተት ሳይሆን ሆን ተብሎ የተደረገ ነዉ የሚመስለዉ) ባለስልጣን መለስ እንደዚያ በህዝብ ላይ እንዲቀልድ ሰላዘዙት እንዳልነበር ሁላችንም ጠንቅቀን እናዉቃለን፡፡

+ ኢህአዴግ በተደጋጋሚ በተግባር ያረጋገጠልን አንድ መሰረታዊ ችግሩ በኢትዮጵያ ህዝብና በፓርቲዉ መካከል በሆነ ጉዳይን በሚመለከት የግድ አንዱን የመምረጥ ጉዳይ ሲኖር ብዙዉን ግዜ ለፓርቲዉ ማድላቱ ነዉ፡፡ ፓርቲዉንና የፓርቲዉን ቁልፍ አመራር ከማሳጣት ይልቅ የ90 ሚሊዮን ህዝብ ጉዳይን ችላ ማለት እንደሚቀለዉ አስቀድሜ የጠቀስኩት ”የባድመ ለኛ ተወስኗል“ ታሪክ ጥሩ ማሳያ ነዉ፡፡

+ ዶክተር ቴድሮስ ከአብዛኛዎቹ የህወሃት/ኢህአደግ ባለስልጣናት በብዙዎቹ ኢትዮጵያዉን ዘንድ ጥሩ ስም ያላቸዉና ተወዳጅ እንደሆኑ ጠንቅቄ አዉቃለሁ፡፡ እኔም ብሆን ለሳቸዉ የተለየ አክብሮት አለኝ፡፡ በመመረጣቸዉ የከፋቸዉ ጥቂት ሰዎች ባይጠፉም አብዛኛዎቻችን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል፡፡

ይሁን እንጂ መንግስትና ኢህአዴግ ዶክተር ቴድሮስ እንዲመረጡ ያደረገዉን ከፍተኛ ጥረት ሲነገር የሰማን ሰዎች መንግስት አንድን ግለሰብ ለማሾም ይሄን ያህል ከደከመ ምንአለበት ታዲያ የኢትዮጵያ ሉአላዊነት ጉዳይ ላይ በተለይ ከኤርትራ ጋር በነበረዉ ሙግትና በአሰብ ጉዳይ የዚህን ግማሽ ያህል እንኳን ጥረት አለማድረጉ የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡

+ መለስ ስህተት የሚባል ነገር አልሰሩም በሚል እየተሟገትኩላቸዉ አይደለም፡፡ ስህተትማ ይኖራል፡፡ መለስ እንደመሪም እንደዜጋም የሰሩት ስህተት ይኖራል፡፡ ነገር ግን የስህተቶች ሁሉ ተሸካሚ ለማድረግ መሞከሩ ግን ተገቢ ስላልሆነ ነዉ፡፡ መለስ በመጨረሻም የመሳሪያ ግዥዉ እንዲከናወን ቢፈቅዱም መቼም እሳቸዉ (መለስ) በየሀገሩ እየዞሩ በመሳሪያ ግዥዉ ላይ እንደማይሳተፉ ግልጽ ነዉ፡፡ በርካታ የዉጭ ምንዛሪ ወጥቶ መሳሪያ ካልተገዛ እያሉ ሲጎተጉቱ የነበሩ ሰዎች ለዚህ ተብሎ የተረከቡትን የዉጭ ምንዛሪ ገንዘብ በሙሉ ለታለመለት ዓላማ ለመሳሪያ ግዥ አዉለናል ብለዉ ቢነግሩን ማን ያምናቸዋል?

+ ለማናዉቃቸዉ ለእነ ሌኒንና ማርክስ ሃዉልት ሲቆምላቸዉ በነበረ ሀገር እንዲሁም በየክልል ከተሞች ከዚያዉ አካባቢ ዉጭ ለመላዉ ሀገሪቱና ለኢትዮጰውያ ህዝብ ምን እንደሰሩ በዉል ታሪካቸዉ ለማይታወቁ ግለሰቦች በፉክክር በየስርቻዉ መታሰቢያ ሃዉልት በሚቆምባት ጉደኛ የሆነች ሀገር ዉስጥ የመላዉ ኢትዮጵያን ክብር ከፍ እንዲል ላደረጉና ሀገራችንን ከወደቀችበት አንስተዉ ተገቢዉን የክብር ቦታዋን እንዲታገኝ እድሜ ልካቸዉን ለደከሙት ለመለስ እንድ እንኳን መታሰቢያ ሃዉልት በሀገሪቱ እምብርት በዋና ከተማዋ አለመኖሩ እጅግ የሚያስተዛዝብ ነዉ፡፡ ይህ ግን የሳቸዉን በተለየ መታወስ የማይሹ ጥቂት ግለሰቦች ሴራ ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያ ህዘብ ፍላጎት እንዳልሆነ እረዳለሁ፡፡

+ የኤርትራ ነጻ መዉጣት ጉዳይ መጀመሪያዉኑ በትጥቅ ትግል መልስ ያገኘና  የኤርትራ ህዝብ የነጻነት ትግል ዉጤት እንጂ የመለስ ሴራ ዉጤት አይደለም፡፡ ወይንም ኢሳይያስ ያለፍላጎቱ በመለስ ሴራ ተገፋፍቶ እንዲገነጠል የተደረገበት ሁኔታም አይደለም፡፡

ኢህአዴግ ስልጣን እንደያዘ ሰሞን ራሱ የኤርትራዉ ኢሳይያስ በታዛቢነት በተገኘበት የአዲስ አበባዉ የሰላም ጉባኤ ላይ አሁን በህይወት የለሉት ፕሮፌሰር አስራት ስለ ኤርትራ መገንጠል ጉዳይ አንስተዉ ተቃዉሞ ሲያቀርቡ ኢሳይያስ “ኢትዮጵያ አንድነት ምናምን የምትሉትን ተረት ተረት ወዲያ አድርጉት፤ የኤርትራ ነጻ መዉጣት ጉዳይ በጦርነት መልስ ያገኛና ያበቃለት ጉዳይ  ነዉ” በሚል ነበር በቁጣ የገለጹት፡፡

ኢህአዴግን በሚመለከት ለየት የሚያደርገዉ የቀድሞዎቹ መንግስታት ከሰሩት ጥፋት ተቃራኒ በሆነ መልኩ ለኤርትራ መነጠል ከሞላ ጎደል“ ቀላል የማይባል  ሚና” መጫወቱ ነዉ፡፡ ይህ የኢህአዴግ ሚና ከአንድነት ይልቅ የኤርትራ መገንጠል ይበጃል በሚል የተደረገ ሳይሆን ህዝቡ ከጨቋኝ ስርአት ጋር ሲያደርግ የነበረዉን ትግል በመርህ ደረጃ ትክክል ነዉ ብሎ ስላመነበት ነዉ፡፡ ዞሮ ዞሮ ዉጤቱ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚጎዳ መሆኑ ባይቀርም ነገር ግን ሆን ተብሎ መገንጠል አለባቸዉ በሚል የኢትዮጵያን አንድነት በመቀናቀን  እንደተከናወነ አድርገን እንድንቆጥር አያደርግም፡፡ የኢህአዴግ ሚና ለኤርትራ መገንጠል ምንም ይሁን ምን እንደ ኢትዮጵያዊ ድርጅት ሲታይ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት መሆኑ ላይ አያከራክርም፡፡ 

+ ብዙዎቹ እንደሚስማሙበትና እኔም እንደማምንበት ለኤርትራ ነጻ መዉጣት ወሳኙ የኤርትራ ህዝብ ተጋድሎ እንጂ የህወሃት ድጋፍ ማድረጉ አልነበረም፡፡ ይህ ማለት ግን ሻእቢያ የህወኃትን ሚና በመካድ አኮስሶ እንደሚገልጸዉ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ህወኃት ሆን ብሎ ለኤርትራ መገንጠል ለዓመታት ሲሰራ የቆየ ድርጅትና ለኤርትራ መገንጠል ወሳኝ ድርሻ እንደነበረዉ አድርገዉ እንደሚናገሩትም አይደለም፡፡ ለኤርትራ መገንጠል የህወኃትን ሚና ወሳኝ ማድረግም ሆነ ለኤርትራ ህዝብ ነጻነት ኢህአዴግ ያደረገዉን በጎ አስተዋጽኦ መካድ ሁለቱም አስተያየቶች የተዛቡ ናቸዉ፡፡

+ የቀድሞዎቹ መሪዎች ያጠፉት ነገር ካለ እንደ ራሱ ጥፋት ቆጥሮ ማስተካከልና መስመር ማስያዝ ይጠበቅበታል እንጂ የቀድሞዎቹ ባበላሹት እኔ ምን አገባኝ ማለት አይችልም፡፡ ምንኒሊክ ከአቅም በላይ ሆኖባቸዉ ወይም በዚያን ዘመን የነበረዉ ልዩ ሁኔታ ሳይፈቅድላቸዉ ቀርቶ በዘመናቸዉ የሰሩት ስህተት ካለ የአሁኑ መንግስት ስህተቱን ለማረም መጣር አለበት እንጂ የቀድሞዎን ስህተት ለራሱ ስህተት እንደሰበብ መጠቀም አይኖርበትም፡፡ ይሄን ታሪካዊ ሃላፊነትን ኢህአዴግ በትክክል ለመረዳቱ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

+ ደርግ ብዙ ነገሮችን በማበላሸቱ ኤርትራዉያን ከእንግዲህ ወዲያ ከኢትዮጵያ ጋር በአንድነት ለመኖር በጭራሽ ፍላጎት እንዳልነበራቸዉ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ዛሬ የኤርትራም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ስሜት ቢፈተሽ ድሮ በነበረዉ አቋም እንደማይገኝ መገመት አያዳግትም፡፡ በኤርትራ በኩል መገንጠሉ የፈለጉትን ዲሞክራሲ፣ ፍትህ፣ ነጻነትና ብልጽግና ባያመጣላቸዉም በዚህ ምክንያት ብቻ በሪፌረንደሙ ወቅት ነጻነትን መምረጣቸዉን እንደ ስህተት ይቆጥሩታል ብሎ ለመገመት አይቻልም፡፡ ኤርትራዉያን  ለነጻነት የሚሰጡትን ትርጉም በነሱ ቦታ ሆነን ከላየን በስተቀር ከኛ ፍላጎት አንጻር ብቻ መፍረድ አንችልም፡፡

+ ሻዕቢያ የእስመራን ቤተመንግስት የተቆጣጠረዉ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ነዉ፡፡ በወቅቱ ሻዕቢያ ከኢህአዴግ የበለጠ ወታደራዊ ኃይል አለኝ በሚል የሚኩራራ ስለነበር ኢህአዴግ የሚለዉን ለመቀበል የሚገደደድበት ሁኔታም አልነበረም፡፡ እንደሚታወቀዉ የኤርትራ ሪፈረንዴም ከመከናወኑ በፊት ቢያንስ ለሁለት ዓመት ያህል ሻዕቢያ ኤርትራን ለማስተዳደር ችሎም ነበር፡፡ ለሁለት ዓመታት ነጻነቱን ሳያዉጅ የቆየዉም የኢህአዴግን ፈቃድ ለማግኘት ብሎ ሳይሆን ለሪፌሬንደሙ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ግዜ ስላስፈለገዉ በራሱ ምክንያት ነዉ፡፡

+ በኢህአዴግ በኩል ያደረገዉ ነገር ቢኖር ማድረግ የሚገባዉን ነዉ፡፡ ኢህአዴግ የሪፌሬንደሙ ሂደት ላይ አንዳችም እንቀፋት አለመፍጠሩና ከዚያ በኋላ እንደ ማንኛዉም አገር እዉቅና መስጠቱ ነዉ፡፡ እንደዚያ ባያደርግም ዞሮ ዞሮ የኤርትራ ለብቻዋ መሆን ሊያስቀር የሚችል ሁኔታም አይሆንም ነበር፡፡

+ ከትችቶች መካካል ተገቢነት የሚኖረዉ ሪፌረንደም ከመደረጉ በፊት የሁለቱን አገራት በጋራ በሚነካኩ ጉዳዮች ላይ በተለይ በድንበርና በወደብ ጉዳይ አንድ እልባት ላይ መደረስ ነበረበት የሚለዉ ነዉ፡፡ ኤርትራና ኢትዮጵያ ወደፊት እንደሁለት አገር የሚኖራቸዉ ወሰን የት ላይ መሆን አለበት የሚልና የባህር በር አጠቃቀምም ሆነ ባለቤትነትን በሚመለከት በመግባባት ላይ የጠመሰረተ ዉል መደርግ ነበረበት የሚለዉ ነዉ፡፡ ይህ ግን በምንም መንገድ ሪፈረንደሙን ለማዘግየት ወይንም እስከነአካቴዉ እንዳይደረግ ለማገድ  ያለመ መሆን እንደለለለበት ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፤ይሄን ማድረግ በጭራሽ አንችልም፡፡

+ የኤርትራ ጉዳይ ገና በደርግ ግዜ ያባለቀለት ጉዳይ በመሆኑ ኢህአዴግን በአለቀለት ጉዳይ ላይ መተቸትም ሆነ ማመስገን ትርጉም አይኖረዉም፡፡ የኤርትራ ከኢትዮጵያ መነጠል ጉዳይ ከዚህ በኋላ መጸጸቱና መቆጨቱ ግዜዉ ያለፈበት ጉዳይ ነዉ፡፡ ኤርትራን በሚመለከት ከዚህ በኋላ ዋናዉ ተፈላጊ ጉዳይ ቢቻል መልካም ጎረቤታሞች ሆነን እንዴት በሰላም እንኑር ካልሆነም ደግሞ ኤርትራ በየግዜዉ ከምታደርስብን ትንኮሳ እንዴት እንድትተቃብ እናድርጋት የሚለዉ ነዉ፡፡ ከዚያ ዉጭ ባለፉ ጉዳዮች እንዲህ ቢሆን ኖሮ እያልን መቆጨቱ ስለማይጠቅመን ከዚያ ይልቅ ከዚህ በኋላ ማስተካከል በምንችለዉ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርገን ብንሰራ ነዉ የተሻለ ይመስለኛል፡፡

——

መግቢያ

የኤርትራ ችግር የአንድ ዘመንና የአንድ ወቅት መንግስት የብቻ ስህተት ሳይሆን  የቀደመዉ  መንግስት የሰራዉን ስህተት ተተኪዉ መንግስት በከፋ ሁኔታ  እያወሳሰበ ለመፍትሄም አስቸጋሪ እያደረገዉ በመጨረሻም ለይቶለት ለግንጠላ የዳረገ በቅብብሎሽ የተሰራ ጥፋት ነዉ፡፡ ክፋቱ ደግሞ ኤርትራ ራሷን ችላ ወይንም ከኛ ተነጥላም ከኛ ራስ አልወርድ እያለች ስታስቸግረን መቆየቷ ነዉ፡፡

በየዘመኑ የነበሩ የቀደሙት የሀገራችን መንግስታት የሰሩትን ጥፋት በማመን አዲሱ የኢትዮጵያ መንግስት ኤርትራ እንደ ሀገር ራሷን ችላ በነጻነት እንድትኖር እድል ተሰጥቷተ እያለ ጭራሽ ተመልሳ ለሰላማችን ጠንቅ እየሆነች ነዉ፡፡ ለሰላሳ ዓመታት ኤርትራ እንዳትገነጠል ለማድረግ የከፈልነዉ መስዋእትነትና አጠቃላይ ጉዳት ሳያንሰን ነጻነታቸዉን እንዲያገኙ ሙሉ ተባባሪ ሆነን እያለም ከበፊቱ ባልተናናሰ ሁኔታ እያደማችን ነች፡፡ ኤርትራ በተለያዩ መንገዶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እያደረገችብን ካለዉ ደባ የማይተናነሰዉ ከአንድነት ይልቅ መበታተንን ለሚያልሙ ጸረ አንድነት ኃይሎች መጥፎ አርአያ  መሆኗ ነዉ፡፡

የኤርትራ መገንጠልና እንደ ዋዛ እዉቅና ማግኘት የአንድ ክልል ወይም ህዘብ የመነጠል ጉዳይ ብቻ ተደርጎ የሚቆጠር አይደለም፡፡ የኤርትራ መገንጠል በቀጥታ ካስከተለዉ ዉጤት በላይ ለኢትዮጵያ የወደፊቱ ሉአላዊነት ላይ ከፍተኛ የስጋት የፈጠረዉ መጥፎ አርአያነት (dangerous precedent) ለሌሎች ብሄሮችና ህዝቦች መገንጠል እንደሚቻል ያስተማረና ሁልጊዜም ስለመገንጠል እንዲያስቡ ያደረገ መጥፎ ክስተት መሆኑ ነዉ፡፡

በተለያዩ ጥቃቅን ምክንያች ያኮረፈ የአንድ አካባቢ ህዝብ በጥቂት ስልጣን በጠማቸዉ ግለሰቦች ግፊትና ደባ ሁልጊዜም ስለመገንጠል እንድያስብ ያደርገዋል፡፡ በተለይም ሀገሪቱ የበርካታ ህዝቦች አገር መሆን መልካም ጎኑ እንዳለ ሆኖ ነገር ግን ኋላ ቀር በሆነ የፖለቲካ ባህል ምክንያት በቀላሉ ሊቀረፉ የሚችሉ ችግሮችን ከሚገባዉ በላይ በማጦዝና ሰማይ ጥግ በማድረስ ጥቂት ሰዎችን አስተባብሮ ህዝቡን በማነሳሳት የመገንጠል ጥያቄ እንዲያነሳ በማድረግ በሂዴት ለሀገሪቱ መበታተን መንገዱን እጅግ ምቹ አድርጎታል፡፡

ለብቻ የመሆን (የመገንጠል) ጥያቄ ሁልጊዜ በቁጥር ንኡሳን የሆኑ ህዝቦች ላይ ብቻ የሚታይ ሳይሆን እንደ ኦሮሞና አማራ ያሉ የትልቅ ህዝብ ባለቤት የሆኑ ክልሎችም ሳይቀሩ በህገመንግስታዊ ስርአቱ አንዳችም የተለየ በደል ወይም ጭቆና ሳይደርስባቸዉና በስርአቱ እኩል ተጠቃሚ ሆነዉ እያለ በጥቂት ግለሰቦች  አነሳሽነት አብሮ ከመኖር ይልቅ ለብቻ በመሆን የበለጠ እንጠቀማለን በሚል ብቻ የመገንጠል ጥያቄ ከማንሳት የሚከለክላቸዉ ነገር አይኖርም፡፡ አስከዛሬም በብሄር ስም ትጥቅ ያነሱ ድርጅቶች መኖር ለወደፊቱ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ገና ከአሁኑ አደጋዉን አመላካች ነዉ፡፡

በተለይ ካለፈዉ ሁለት ዓመት ግዜ ወዲህ በሀገራችን አንዳንድ ክልሎች የታየዉ “ራስን በተለየ ተበዳይና ተጎጂ” የማድረግ፤ የክልሉን የተፈጥሮ ሃብት ለብቻ መጠቀም አለብን ከሚል አመለካካት በመነሳት ማንም አይደረስብን የሚለዉ ሌላዉን ህዝብ የመጥላትና ከዚሁ ጋር አብሮ በአንዳንድ ክልሎች መካካል የታየዉ የመስፋፋት አባዜና የወሰን ግጭቶች ወዘተ ሁሉ በድምር ሲታይ በሀገሪቱ አንድነት መጻኢ እድል ላይ አደጋ  ሊያስከትል የሚችል አዝማሚያ በመሆኑ አስቀድሜ ለጠቀስኩት ስጋት ጥሩ ማሳያ ነዉ፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በአንዳንድ አካባቢዎች የተነሱ ዉስን የሆኑ የመብት ጥያቄዎችም በአግባቡ መመለስ አቅቶን እንዴት ወደ አጠቃላይ ቀዉስ እንደተቀየረና አገሪቱንም አደጋ ዉስጥ ከቷት እንደነበር እናስታዉሳለን፡፡ ቀድሞዉኑ ትንሽ በተነኩ ቁጥር “ካልፈለጋችሁን እኮ ለብቻ መሆን  የሚከለክለን ነገር የለም“ በሚል ከአንዳንድ ወገኖች ሲሰነዘር የቆየዉን ማስፈራሪያ እንደዋዛ ሰምተን  ያለፍነዉ ጉዳይ  አሁን በደንብ እንድናስብበት የሚያደርገን ነዉ፡፡ በዚህ ምክንያትም ነዉ የኤርትራ ሁኔታ ለብቻዉ ተነጥሎ መታየት የማይገባዉና ይልቁንም ለቀሩት ክልሎችና ህዝቦችም “መገንጠልን “ያስተማረ መጥፎ ምሳሌ ነዉ እያልኩ ያለሁት፡፡

የኤርትራ ህዝብ ከመገንጠሉ ምን ተጠቀመ የሚለዉን ጥያቄ ወደ ጎን ትተን መገንጠልን እንደ መፍትሄ ለሚያልሙ ጠባቦችና ራስ ወደድ ግለሰቦች ግን የአንድነት ኃይሎችን ለማስፈራራት እንደመሳሪያ መጠቀም መቻላቸዉን መዘንጋት አይኖርብንም፡፡ ከዋናዋ ሀገር በተለያዩ ሰበቦች ተገንጥለዉ የራሳቸዉን ሀገር የመሰረቱ ህዝቦች መገንጠሉ እንደታሰበዉ ሰላምና ብልጽግናን እንዳላመጣላቸዉ ይልቁንም ለራሳቸዉ ለተገነጠሉትም ሆነ ለቀድሞዉ እናት ሀገራቸዉ የግጭትና የብጥብጥ  መነሻ በመሆን ሰላም እንደራቃቸዉ የኩርዲሰታን፤የካሸሚር፤ ሱማሌ ላንድ፤ዩክራይና፤አብካዚያ፤ማሲዶኒያ ደቡብ ሱዳንና የኤርትራ ወዘተ ሁኔታ ጥሩ ማሳያ ነዉ፡፡

ለመሆኑ በኢትዮጵያን እየተፈራረቁ ስልጣን የያዙ መሪዎቻቸን ኤርትራን በሚመለከት አንዱ ከሌላዉ በተለየ የሚወቀስበትም ሆነ የሚመሰገኑበት ምክንያት ይኖር ይሆን? በኤርትራ ህዝብ ላይ በደል ፈጽመዋል ተብለዉ ከሚወቀሱት የቀደሙ መንግስታትም ሆኑ ለኤርትራ ህዝብ ባለዉለታ ነዉ የሚባለዉ የአሁኑ መንግስት አስተዳደር ዘመንም በኤርትራ ዳፋ ሀገራችን ከደህንነት ስጋት አለመላቀቋና ለችግር መዳረጓ ከቶ ለምን ይሆን? ለመሆኑ የኤርትራ ጉዳይ አሁን ላለበት ደረጃ እንዲደርስ በማድረግ ረገድ ተጠያቂዉ ማነዉ? በዚህ ጉዳይ ላይ ጥቂት ነገሮችን ቀጥዬ ላነሳ እሞክራለሁ፡፡

1/ ዳግማዊ ምንሊክ፡ ቀ..ሥና / መግስቱ ኃይለማሪያም

እንደሚታወቀዉ በየዘመኑ የነበሩት የኢትዮጵያ መንግስታት ከሚነቀፉበት አንዱና ትልቁ ጉዳይ ኤርትራን በሚመለከት ሲከተሉት የነበረዉ ፖሊሲ ነዉ፡፡ ኤርትራን በሚመለከት ከሚሰነዘረዉ ወቀሳ ጣሊያንን ድባቅ በመምታት እንጸባራቂዉን የአድዋ ድል የተገኘበትን ጦርነት በመምራት ስመ ገናና የሆኑት ዳግማዊ ምንሊክም ከወቀሳዉ ሊያመልጡ አልቻሉም፡፡ ምንሊክ በሽሽት ላይ የነበረዉን የጣሊያንን ሰራዊት መረብን አሻግረዉ ከሚተዉት አስከመጨረሻዉ አሳዳዉ መደምሰስ ነበረባቸዉ በሚል ነዉ የሚተቹት፡፡

በምንሊክ ላይ ወቀሳ አቅራቢዎቹ ሁኔታዉን አቅለዉ እንደሚናገሩት ሳይሆን ምንሊክ በወቅቱ እንደዚያ ለማድረግ ቢፈልጉ እንኳን ማድረግ የሚችሉበት አቅም (ሁኔታ) አልነበራቸዉምና ወቀሳዉ ያለቦታዉ የተሰነዘረና አግባቢነት የሌለዉ መሆን ብቻ ሳይሆን እንዲያዉም ለምንሊክ ካላቸዉ ጥላቻ ስማቸዉን ለማጉደፍና ዉለታቸዉን ለማሳነስ የሚደረግ አጉል ሙከራ ነዉ፡፡

በምንሊክ ላይ የሚሰነዘረዉ ትችት የአንድነት ስሜት ከነበራቸዉ ኤርትራዉያንም ጭምር ነዉ፡፡ “እኛ ኤርትራዉያን ንጉስ ምኒሊክ ለጣሊያን ሸጠዉን ነዉ እንጂ ኢትዮጵያዉን ነን ”የሚሉ የቁጭት ንግግሮች ከራሳቸዉ ከኤርትራዉን ይደመጥ እንደነበር አምባሳደር ዘዉዴ ረታን ጨምሮ በተለያዩ ታሪክ ጸሃፊዎች ተዘግቧል፡፡ የደርግ ባለስልጣን የነበሩት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርግስም “የደም እምባ” በሚለዉ መጽሀፋቸዉ ላይ እንደጠቀሱት በኤርትራ ከሁሉም ከብረ በዓላት ሁሉ በቀዝቃዛ መንፈስ የሚከበረዉ የአድዋ ድል በዓል መሆኑንና የዚህ ዋነኛ ምክንያትም “ምንሊክ ጣሊያንን ከመረብ ምላሽ አባረዉ የቀረዉን የኤርትራን ህዝብ ለጣሊያን ባሪነት አሳልፈዉ ሰጥተዉናል” ከሚል ቁጭት ነዉ፡፡

ይህንን የቁጭት መንፈስ ገልብጠዉ ለራሳቸዉ ኣላማ ለመጠቀም የሞከሩ ገንጣዮች ምንሊክ ይሄን ያደረጉት ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል እንዳልነበረች በመረዳታቸዉ ስለሆነ “ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ሆና አታዉቅም” ለሚለዉ ክርክራቸዉ እንደ አንድ ትልቅ መከራከሪያ የሚያቀርቡት ይህንኑ ከስተት ነዉ፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴን በሚመለከት ደግሞ ፌዴሬሽኑን በማፍረስ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት በመፈጸማቸዉ ከዚያ በኋላ ለተከሰቱት ችግሮች ሁሉ መነሻ ሆኗል በሚል ይወቀሳሉ፡፡ ይህን ወቀሳ ብዙዎቹ የሚስማሙበት ነዉ፡፡ ንጉሱ ይህን እርምጃ ለመዉሰድ የበቁት ሁኔታዉ ለአስተዳደራቸዉ ስለአላመቻቸዉ በተለይም ይሄ ሪፌሬንደም የሚባለዉ ጣጣ ወደ ሌሎች ክልል ህዝቦችም ተጋብቶ መጥፎ አርአያነት እንዳይሆን በመስጋትና በተጨማሪ የምጽዋና የአሰብ ወደብ ዕጣ ፈንታ ስለአሰጋቸዉ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

ንጉሱ ወደዚህ ዉሳኔ የደረሱት በራሳቸዉ ተነሳሽነት ሳይሆን አንድነትን እንጂ ፌዴረሽኑን እንፈልግም በሚሉ የራሳቸዉ የኤርትራ ፓርላማ አባላትና በአብዛኛዉ የኤርትራ ህዝብ ጥያቄ ተደፋፍረዉ ያደረጉት ነዉ፡፡ የንጉሱ ዉሳኔ ምንም ይሁን ምን የኤርትራን ጉዳይ ማወሳሰቡ ግን እርግጥ ቢሆንም እሳቸዉ (ንጉሱና) አክሊሉ ሃብተወልድ ኤርትራን መጀመሪያ ከጣሊያን ቅኝ አገዛዝ ከዚያ ደግሞ ሞግዚት አስተዳደር አላቀዉ መጀመሪያ በፌደረሽን ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ አካል እንድትሆን ለበርካታ አመታት ያደረጉት እልህ አስጨራሽ ጥረት እጅግ የሚደነቅና የሰሩት ስህተት ቢኖር እንኳን ለኢትዮጵያ ጥቅም ተብሎ መሆኑ ሊዘነጋ የሚገባዉ አይደለም፡፡

ትግሉ የተደረገዉ ከፍተኛ ተደማችጭነት ከነበራት ቅኝ ገዥዋ ጣሊያንና እሷን ከሚደግፉ ኃያላን መንግስታት ጋር ጭምር መሆኑ ሲታሰብ ያደረጉት ተጋድሎ ከፍተኛ እንደነበረ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ኤርትራን ወደ ኢትዮጵያ በማስመለስ ለአላዊነታችንን ለመስከበር ንጉሰነገስቱና አክሊሉ ሃብተወልድ ያደረጉትን ታላቅ ተጋድሎ ለማወቅ ለሚፈልግ የአምባሳደር  ዘዉዴ ረታን “የኤርትራ ጉዳይ ”የተሰኘዉን እጅግ ድንቅ መጽሃፍ ማንበቡ በቂ  ነዉ፡፡

ከንጉሱ በኋላ የመጣዉ የደርግ መንግስት ደግሞ በወታደራዊ  የኃይል የበላይነት ችግሩን መፍታት ይቻላል በሚል የተሳሳተ እምነት የሠላም መንገዶችን ሁሉ በመዝጋትና ጦርነት ላይ ብቻ ትኩረት በማድረጉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሰራዊት ህይወት ገብሮም ግንጠላዉን ማስቀረት አልቻለም፡፡ ደርግ የኤርትራን የመገንጠል ጥያቄ ዝም ብሎ መቀበል ነበረበት ወይም ጦርነት ማካሄድ አልነበረበትም የሚል አስተያየት አስካሁን ስለ መኖሩ አላዉቅም፡፡ እንኳን ደርግ ይቅርና ለአርትራ ነጻ መዉጣት ቀላል የማይባል ሚና የነበረዉ የኢህአዴግ አንዳንድ አመራሮች አሁን ቢጠየቁ የኤርትራን መገንጠል ለማስቀረት ደርግ ጥረት ማደረጉን የሚያወግዙ አይመስለኝም፡፡

ደርግ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነትን ያደረገዉን ተጋድሎ መካድም  ሆነ ማጣጣል ትልቅ ታሪካዊ ግድፈት ነዉ፡፡ የደርግ ትልቁ ችግር ለአንድነት መታገሉ ወይም ኤርትራን እንዳትገነጠል ለማድረግ መዋጋቱ ሳይሆን አጠቃላይ ችግሩን ያስተናገደበት መንገድ የተሳሳተ መሆኑ ነዉ፡፡

ጦርነትን እንደ ብቸኛ መፍትሄ በመቁጠሩ ከጦርነቱ ጎን ለጎን ወይም አስቀድሞ በሰላማዊ መንገድ ለችግሩ መፍትሄ ለመፈለግ አስከመጨረሻዉ ድረስ ጥረት አለማድረጉ ጥልቁ ችግሩ ነዉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የኤርትራ ህዝብ ከጎኑ እንዲሰለፍ በማድረግ የኤርትራን መገንጠል እንዲያወግዙ ካደረገዉ ጥረት ይልቅ በተቃራኒዉ ህዝቡ እንዲማረር በማድረግ አማጽዉን ቡድን በሞራልና በሰዉ ኃይል እንዲያጠናክሩ ሁኔታዉን ምቹ ማድረጉ  ዋነኛዉ ተጠቃሽ የደርግ ስህተት  ነዉ፡፡

ደርግ ሌላዉ ቀርቶ የአንድነት አቋም የነበራቸዉን የክልሉን ተወላጆች እንኳን በአግባቡ ማባበልና ማግባባት ተስኖት ነበር፡፡ እንደ ጄኔራል አማን የመሳሰሉ የክልሉ ተወላጆች የሆኑ ባለስልጣናቱ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሲያደርጉ የነበረዉን ጥረት በትዕግስት ከመጠበቅና ከማበረታታት ይልቅ እንደ ወንጀልና እንደ ክህደት ቆጥሮባቸዉ እንዲገደሉ ማድረጉ ሲታሰብ ደርግ መቼም ቢሆን ለኤርትራ ችግር መፍትሄ ማምጣት እንደማይችል ገና ከመጀመሪያዉኑ ያመላከተ ነበር፡፡

ደርግ ኤርትራን በሚመለከት የሠራዉና ታሪክ ይቅር የማይለዉ ከባድ ጥፋት  ኤርትራን ከእናት ሀገሯ ጋር ለመደባለቅ በሀገራችን የዲፕሎማሲ ታሪክ ተወዳዳሪ የሌለዉን  ግዙፍ ስራ የሰሩትን አክሊሉ ሃብተወልድን በጭካኔ መግደሉ ነዉ፡፡ ደርግ በዚህና በኋላም ሲወስዳቸዉ በነበሩ ጀብደኛ እርምጃዎች የኤርትራ ጉዳይ ይበልጥ እየተወሳሰበ እንዲሄድ አድርጓል፡፡

በትግራይ ክልል በነበረዉ ህዝብ ላይም በኤርትራ ዉስጥ ሲከተል ከነበረዉ ባልተለየ ሁኔታ ህዝቡን በአስገንጣይነትና ተገንጣይነት በጅምላ በመፈረጅ ከአማጽዎቹ ጋር ባልተለየ ሁኔታ ከፍተኛ በደል ማድረሱ አይዘነጋም፡፡ ደርግ በትግራይ ዉስጥ ሲካሄድ የነበረዉ የህወሃት ትግል በቀጥታ ትግራይን ለመገንጠል ያለመ እንዳልነበርና ይልቁንም ስርአቱን በሌላ የተሻለ ስርአት ለመተካት ዓላማ ያነገበ እንደነበር መቶ በመቶ ያዉቅ ነበር፡፡ ነገር ግን የኤርትራን አማጽያን ያግዛሉ በሚል የትግራይ ተወላጆችን በሰበብ አስባቡ ሲገድል ሲያስር እንደነበር የቀድሞ የደርግ ባለስልጣኖች ራሳቸዉ ዛሬ እየመሰከሩት ያለ ሃቅ ነዉ፡፡

ስለዚህ ደርግ በኤርትራ ሲያካሂድ የነበረዉ ጦርነት ዉጤት አልባ እንዲሆን የራሱ የደርግ ድክመት ዋነኛዉ ምክንያት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ እንኳን የኤርትራ ህዝብ ይቅርና የቀረዉ የኢትዮጵያ ህዝብም ቢሆን የኤርትራን መገንጠል ባይደግፍም ነገር ግን ሰላማዊ ጥረት በሚፈለገዉ ደረጃ ባለመደረጉና በጦርነቱም ዉጤት ተስፋ ቆርጦ መሰላቸት ሲመጣ ደርግን ወደ መተቸትና መቃወም መግባቱ የሚታወስ ነዉ፡፡

ደርግ ከዉጭም ከዉስጥም ዉግዘት ሲበዛበትና በጦር ሜዳ ሽንፈት ባጋጠመዉ ቁጥር ለይስሙላና ለማስመሰል አንዳንዴ ወደ ድርድር ጠረጰዛ መምጣቱ ባይቀርም ነገር ግን “እኔ የምላችሁን ካልተቀበላችሁ በኃይል አጠፋችኋላሁ”በሚል በማስፈራራት ስለነበር አንዳቸዉም ድርድሮች ዉጤት ሊሰጡ አልቻሉም፡፡

የመንግስቱ ኃይለማሪያም ድርጊት ልክ አንድ ሩሲያዊ ፖለቲከኛ ስለ ሩሲያዉ ፕሬዝዳንት ፑቲን ከጠቀሰዉ ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡ ኪሪል ሮጎቭ የተባለ ይህ የሩሲያ ፖለቲካ ተንታኝ ስለ ሀገሩ መሪ ፕሬዝዳንት ፑቲን “እያስፈራሩ የመደራደር” ባህሪይ ሲገልጽ “ፑቲን ሁልጊዜም ድርድር ከመጀመራቸዉ በፊት በቅድሚያ  በጠረጰዛቸዉ ላይ ስለት የማስቀመጥ ልማድ አላቸዉ፡፡ (“Putin likes to open talks by putting a knife on the table first.”) ነበር ያለዉ፡፡ ኮ/ል መንግስቱም ከዚህ የሚለዩበት ነገር ቢኖር ማስፈራሪያና መስጠንቀቂያዉን የሚጠቀሙት ለአማጽያኑ ብቻ ሳይሆን በዋነኛነት እንዲደራደሩ ራሳቸዉ መርጠዉ ለላኳቸዉ  ባለስልጣኖቻቸዉም ጭምር መሆኑ ነዉ፡፡

ሌላዉ ተጠቃሽ ጉዳይ ደግሞ በተቻለ መጠን ድርድሩ እንዳይሳካ ማድረጋቸዉም ጭምር ነዉ፡፡ በዚህ ምክንያትም የመንግስቱ ተደራዳሪዎች ወደ ድርድር የሚሄዱት ድርድሩ እንደማይሳካ እያወቁ ነዉ ማለት ነዉ፡፡ ለኮ/ል መንግስቱ በጣም ጠቃሚዉ ጉዳይም ሰላማዊ መፍትሄ እያፈላለጉ ነዉ መባሉ ብቻ እንጂ ስምምነት ላይ መደረሱና ጦርነቱ መቆሙ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ጦርነቱ እንዲቆም በጭራሽ አይፈልጉም ነበርና፡፡

የጦር መሳሪያ ዋነኛ አቅራቢ አገር የነበረችዉ ሶቭየት ህብረት መሪ ጎርባቾቭ ሳይቀሩ ችግሩን በድርድር እንዲፈቱ ጫና ቢያደርጉም ኮ/ል መንግስቱ ግን ለድርድር በራቸዉን እሰከመጨረሻዉ በመዝጋታቸዉ ለጦርነቱ በሽንፈት መጠናቀቅም ሆነ ለኤርትራ መገንጠል ዋነኛዉ ተጠያቂ ቢሆኑ አይበዛባቸዉም፡፡

ኮ/ል መንግስቱ ምናልባት ለድርድር ከልባቸዉ ቁርጠኛ ሆነዉ የቀረቡበት አንድ ብቸኛ አጋጣሚ ቢኖር በሽረ እንዳስላሰ 604ኛ ኮር ከተደመሰሰና ጦርነቱ በኢህአዴግ የበላይነት መካሄድ ሲጀምርና ባለቀ ሰዓትና ተስፋ በቆረጡበት ወቅት ነዉ፡፡ ከዚያ በፊት ለድርድር ግድ አልነበራቸዉም፡፡ በዚህ ምክንያትም ነዉ ለኤርትራ መገንጠል የመወቀስም ሆነ የመጠየቅ ጉዳይ ሲነሳ ዋነኛዉ ተጠያቂ መሆን ያለበት ኢህአዴግ ሳይሆን ደርግ መሆን አለበት የምለዉ፡፡

2/ መለስና ህወሓት/ኢህአዴግ

 2.1/ መለስ ከኢትዮጵያ ይልቅ ለኤርትራ ያደላ ነበር የሚለዉ ዉንጀላ መሰረተ ቢስ ነዉ

አንዳንንድ ሰዎች የኤርትራን መገንጠል በሚመለከት በተለይም የባህር በር የማጣታችን ጉዳይ ሲነሳ የመለስ አቋም ራሳቸዉ ሲመሩት ከነበረዉ ህወኃት/ኢህአዴግ ተነጥሎ መታየት አይገባዉም በሚል ወቀሳዉም ሆነ ምስጋናዉም በጅምላ መሆኑን ይመርጣሉ፡፡ በእኔ በኩል ግን ይሄን አመለካከት አልጋራዉም፡፡ ይህ አመለካከቴ ከባዶ የሚነሳም አይደለም፡፡

የእኔ አመለካከት መነሻ መለስ ግትር በሆኑ አንዳንድ አክራሪ የድርጅቱ ሰዎች ተጽኢኖ ስር በመዉደቃቸዉ እንዳሰቡት ሊሆን ባይችልም ነገር ግን በኢትዮጰያ አንድነት ላይ የማያወላዉል አቋም የነበራቸዉና ኤርትራ ከመገንጠል ይልቅ በአንድነት እንድትኖር  ጽኑ ፍላጎት የነበራቸዉ መሆናቸዉን ስለምረዳ ነዉ፡፡ በእኔ እምነት መለስ በኤርትራ ጉዳይ ከቀሩት የኢህአደግ አመራሮች ጋር ተዳብለዉ እኩል መወቀስ አይኖርባቸዉም፡፡ መወቀስ ካለበትም መወቀስ ያለበት ደርጅቱ ነዉ፡፡

መለስ በህይወት በነበሩበት ወቅት የኤርትራዉ መሪ ኢሳይያስ ከሌሎቹ የህወሃት አመራሮች በተለየ ለመለስ የከረረ ጥላቻ እንደነበራቸዉና በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ መለስ ከሲ.አይ.ኤ. ጋር ተባብሮ ሊያስገድላቸዉ እንደሚችል ስጋታቸዉን በተደጋጋሚ  ሲገልጹ እንደነበር በሰፊዉ ሲነገር ነበር፡፡ መለስ ለኤርትራ ጋጠወጥ አመራሮች የማይመቹ እንቅፋት ተደርገዉ ይቆጠሩ እንደነበርም የሚታወቅ ነዉ፡፡

የኤርትራን ቅጥ ያጣ ብዝበዛም በማስቆም ረገድም መለስ ግንባር ቀደም እንደነበሩ ሻእቢያ ስለሚያዉቅ ቅም በቀል ቋጥሮባቸዉ ነበር፡፡ በተለይ የኤርትራን ገንዘብ “ናቅፋ” በኢትዮጵያ ብር ጋር እኩል ለመጠቀም የተደረገዉን የኢሳይያስን ሴራ ለመቅጨት መለስ የወሰዱት ፈጣን እርምጃ ሻዕቢያን ክፉኛ ማበሳጩትን ራሳቸዉ የኤርትራዉ መሪ በተደጋጋሚ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡

ዛሬ መለስ በሌሉበት ግዜም በድርጅቱ (በመንግስት) ከፍተኛ ስልጣን ላይ ያሉ አንጋፋ አመራሮች የባህር በርን በሚመለከት የምንቸገረኝ ባህሪያቸዉ አስካሁንም አለመቀየሩና ወደብ አልባ በመሆናችን ጉዳይ ላይ አንድም ግዜ ሲቆጩ አለመደመጣቸዉን ለታዘበ ሰዉ ቀድሞዉኑ ይሄ ጉዳይ የድርጅቱ እንጂ በግላቸዉ የመለስ ችግር እንዳልነበር በቀላሉ ለመረዳት ይችላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የመለስን አቋም የሚጋሩ ጥቂት የድርጅቱ አመራሮችና አባላት ሊኖሩ እንደሚችሉ ብንገምትም ነገር ግን  እንደ ድርጅት ወጥ የሆነ የጋራ አቋም ስለመኖሩ ግን እርግጠኛ ሆነን መናገር አንችልም፡፡

መለስ ከሌሎች ተለይተዉ ስማቸዉ ከፍ ከፍ መደረጉና ሰብእናቸዉ መጉላቱ የሚያስከፋቸዉ አንዳንድ ሰዎች መለስ ኤርትራን በሚመለከትም ሆነ በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከፓርቲዉ የተለየ አቋም ሊኖራቸዉ ስለማይችል መለስን ነጥሎ ማሞካሻት (ማመስገን)ና የቀሩትን የድርጅቱን አመራሮች መዉቀስ ተገቢ አይደለም በሚል በብስጭት የሚናገሩ አሉ፡፡ በርግጥ የቀሩት የድርጅቱ አመራሮች ከመለስ ጋር መፎካከሩን ትተዉ የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎት በማዳመጥ በሉአላዊነታችን ላይ የተከሰቱ ክፍተቶችን ለመድፈን ተጨባጭ እርምጃ በመዉሰድ በተግባር ሊያሳዩን ይገባል፡፡

የባህር በር እንዳይኖረን የተዳረግነዉ በመለስ ስህተት ወይም ፍላጎት ማጣት እንዳልሆነ ለምናዉቅ ሰዎች የአሁኖቹ መሪዎች በዚህ ረገድ መለስ ሰርቷል የሚሉትን ስህተት በማረም የኢትዮጵያን ሉአላዊ ጥቅም በማስከበር ረገድ ከመለስ የተሻሉ መሆናቸዉን በተግባር ሊያሳዩን ይገባል፡፡ እስከዚያዉ ግን እኔንም ጨምሮ ብዙዎቻችን መለስ የዉስጥ እንቅፋትና እሾክ አመኬላዉ ባይበዛባቸዉና አክራሪ በሆኑ አንዳንድ የድርጅታቸዉ ሰዎች ተጽኢኖ ባይበዛባቸዉ ኖሮ የባህር በር ጥያቄን በሆነ መንገድ  እልባት መስጠት  በቻሉ ነበር እያልን በመለስ አለመኖር መቆጨታችን እንቀጥላለን፡፡

አሰብን ለባለቤቱ ለኢትዮጵያ በማንኛዉም መንገድ ማስመለስ ነበረባቸዉ በሚል መለስን የሚወቅሱ ወገኖች በርካታ መልካም አጋጣሚዎችን ሳንጠቀምባቸዉ የቀረነዉ በመለስ ፍላጎት ማጣት ነዉ በሚል መለስን በተደጋጋሚ ሲወቅሱ ይደመጣሉ፡፡ ከነዚህ መልካም አጋጣሚዎች ከሚባሉት መካከልም የጦርነቱ መነሳት ሲሆን ያን አጋጣሚ በመጠቀም በኃይል ማስመለስ ይቻል ነበር የሚል ነዉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ አሁንም ድረስ በህይወት ያሉ ከፍተኛ የሰራዊቱ አዛዦች ይህን አመለካከት ይጋሩት እንደሆነ አርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ቢያንስ ግን አጋጣሚዉ ፈቅዶልኝ ከጦርነቱ በኋላ መለስ ሲመሩት በነበረዉ አንድ ስብሰባ ላይ መለስ ሲናገሩ ከነበረዉ የተረዳሁት ነገር ቢኖር በጦርነቱ ወቅት መከላከያ ሰራዊታችን አሰብን እንዲቆጣጠር ለማድረግ መለስ መመሪያ ሰጥተዉ እንደነበርና ነገር ግን በተግባር እዉን ማድረግ አለመቻሉን ነዉ፡፡ በወቅቱ መለስ ሲናገሩ እንደሰማሁት የጦርነቱን አጋጣሚ በመጠቀም አሰብን በእጃችን ለማድረግ መሞከራቸዉን ነዉ፡፡

እሳቸዉ እንደተመኙት ግን ሊሳካለቸዉ አልቻለም፡፡ እኔ በበኩሌ ይሄን የሳቸዉን አቋም ከሰማሁ በኋላ ለግዜዉ ባይሳካ እንኳን ቢያንስ ጥረት መደረጉን እንደትልቅ ድል ነበር የቆጠርኩት፡፡ መለስ ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት ደንታ አልነበራቸዉም የሚለዉን ዉንጀላ ተገቢ አለመሆኑን የተገነዘብኩት በወደብ (አሰብ) ጉዳይ ላይ የነበራቸዉን አቋም ከተረዳሁበት ከዚያች ቀን ጀምሮ ነዉ፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ባይሳካ ነገና ተነገ ወዲያ በተግባር እዉን የምናደርግበት አመቺ ወቅት ሊመጣ ይችላል የሚል ተስፋ ያሳደረብኝ ስለነበር ነዉ፡፡ በወቅቱ እሳቸዉ አሰብን በወታደራዊ ሃይል ለማስመለስ ሞክረን አልቻልንም ብለዉ ሲናገሩ አንድም ጀኔራል ወይም የጦር አዛዥ ወይም በዚያ ቦታ የነበሩ የፓርቲዉ ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዳቸዉም ለማስተባበል አለመሞከራቸዉ የመለስን አቋም ትክክለኛነት የሚያሳይ ነዉ፡፡

መለስ የራሳችን ባህር በር ወይንም ወደብ አለመኖር ምን ያህል እንደጎዳን ከብዙዎቻችን በተሻለ ይረዱ እንደነበር መገመት አያዳግትም፡፡ ለባህር በር ጭራሽ ደንታ እንዳልነበራቸዉ ወይንም ደግሞ የወደብን ባለቤትነት ፋይዳዉን ጭራሽ  እንደማይረዱ ተደርጎ ሲነገር የቆየዉ ትችት ሚዛናዊነት የጎደለዉ ትችት ይመስለኛል፡፡ ለወደብ ማጣታችን ምክንያት የነበሩት መለስ ከሆኑ ዛሬ መለስ በለሉበት ወቅት በቦታቸዉ የተተኩት አዲሶቹ አመራሮች ይህን መለስ ሰርተዉታል የተባለዉን ስህተት በተግባር እንዲያርሙት እንሻለን፡፡

2.2/ መለስ በግላቸዉም ሆኑ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ኤርትራን ስገንጠል አልታገሉም

/ መንግስቱ የኤርትራን መገንጠል  በኃይል ለማስቀረት ካደረጉት ከንቱ  ሙከራ ይልቅ መለስ ኤርትራዉያንን በፍቅር ለመያዝ  ያደረጉት ጥረት የበለጠ ጠቀሜታ ነበረዉ፡፡  

እኔ እንደሚገባኝ መለስ በግላቸዉም ሆነ ሲመሩት የነበረዉ ድርጅት ህወሓት/ኢህአዴግ ኤርትራንም ለማስገንጠልም ሆነ ትግራይን ለመገንጠል ብሎ የታገለ ድርጅት አልነበረም፡፡ ምናልባት ህወሓት በምስረታዉ አካባቢ እንደ ማንኛዉም ጀማሪ ድርጅት ጥሪት ያለ የትግል ዓላማ  በማስቀመጥ ላይ የተወሰነ እንከን ሊኖርበት ይችላል፡፡ የድርጅቱ ገላጭ ባህሪይ መሆን ያለበት አቋሙን አርሞ ሙሉዉን የትግል ዘመን በታገለለት ዓላማና በተጨባጭም ባስመዘገበዉ ዉጤት ነዉጂ ‹‹የዛሬ አርባ አመት በፊት እገለ እንዲህ ተናግሮ ነበር›› ‹‹የሆነች ወረቀት ተገኝታለች›› እየተባለ የአንድ ድርጅት የትግል ታሪክ መገምገም የለበትም፡፡

በመሪዎቹ ደረጃ ካየንም በተለይ መለስ ገና ከትግሉ ግዜ ጀምሮ ኤርትራን በሚመለከት የነበራቸዉ አቋም ህዝቡ የራሱን ዕጣ ፈንታ መወሰን አለብት የሚል ነዉ የነበረዉ፡፡ ደርግ ከወደቀና ኢህአዴግ ሀገር የመምራት ሃላፊነት ከተረከበም ወዲህ ይህ አቋማቸዉ አልተለወጠም፡፡ መለስ የኤርትራ ህዝብ ፍላጎት መከበር እንዳለበትና እንደሳቸዉ ፍላጎት ቢሆን ኖሮ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ሳትገነጠል በአንድነት ቢኖሩ እንደሚበጅ ጽኑ እምነት ነበራቸዉ፡፡

መለስ በአንድነት መቆየት ባይቻል እንኳን ቢያንስ መነጣጠሉ ቀርቶ ኤርትራና ኢትዮጵያ እንደቀድሞዉ በፌዴሬሽን ቢተሳሳሩ እጅግ የተሻለ አመራጭ እንደሆነ በጽኑ ያምኑ ነበር፡፡ በኤርትራ ያለዉ ህዝብ ግን በአብዛኛዉ የቀድሞዉ ፌዴሬሽን ሲመሰረትም ሲፈርስም ያለነሱ ፈቃድ ስለነበር በዚህ ምክንያትም  የቆየ ቅሬታ ሰለነበራቸዉ ዳግመኛ አንድነትን ባይፈልጉ ብዙም የሚያስገርም ሊሆን አይገባዉም፡፡

ደርግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ንጉሱ በጀመሩት የኃይል መንገድ በመቀጠሉ በባሰ ሁኔታ ህዝቡን እንዲማረር በማድረጉ ህዝቡን አንድነት ይሻልሃል ብሎ ለማሳመን በጣም አዳጋች አድርጎት ቆይቷል፡፡ ደርግን የተካዉ ኢህአዴግ ደርግ ያበላሸዉን ለማረም እጅግ አዳጋች እንደሆነበት ለማንም ግልጽ ነዉ፡፡

መለስ ኤርትራና ኢትዮጵያ በአንድነት እንዲቀዩ ብርቱ ፍላጎት ቢናራቸዉም አንድነቱ ባይሳካ ቢያንስ የሁለቱ አገሮች ህዝቦች በመካከላቸዉ የነበረዉን ልዩነት ግምብ በማፍረስ ጠንካራ ወዳጅነት በመመስረት በጉርብትና በሰላም መኖር ይችላሉ የሚል የጸና እምነትም ስለነበራቸዉ ከሪፌሬንደሙ በፊትም ሆነ በኋላ የኤርትራን ችግር ለመጋራት ብሎም የኢትዮጵያ አቅም በፈቀደ መጠን ለማገዝ ብዙ ጥረት  አድርገዋል፡፡

እንዲያዉም መንግስቱ ኃይለማሪያም የአትዮጵያን አንድነት ለማስከበር ከህዝቡ ፍላጎት ዉጭ በኃይል ካደረጉት ዉጤት አልባ ሙከራ ይልቅ መለስ ዜናዊ በሰላምና በወዳጅነት የኢትዮጵያና ኤርትራ አንድነት ለማስጠበቅ ያደረጉት ጥረት የበለጠ ትርጉም የበለጠ ጠቀሜታ ነበረዉ፡፡ የኤርትራን ህዝብ ወዳጅነት ለማትረፍና ልባቸዉን ለማማለል መለስ ከመንግስቱ  የተሻለ ስራ ሰርተዋል፡፡

ሌላዉ ቀርቶ ኤርትራ የቀሰቀሰችዉ ጦርነት ካበቃም በኃላ የኤርትራ ዜጎች የኢሳይያስን ስርአት ሸሽተዉ በገፍ እያደረጉት ላለዉ ስደት ተቀዳሚ ተመራጭ መዳረሻ ያደረጉት ኢትዮጵያን መሆኑና መንግስትም ለኤርትራዉያኑ ስደተኞች ፍጹም የተለየ እንክብካቤ በማሳየት እያደረገ ያለዉ መልካም ተግባር በአለም ማሀርበረሰብ ሳይቀር እጅግ ያስመሰገነና ኤርትራዉያንም ለኢትዮጰያ የተለየ ፍቅር እንዲኖራቸዉ ያደረገ ተግባር ነዉ፡፡

መንግስታችን እንደሚያረገዉ ጥረት ቢሆን ወደፊት ሁኔታዉ ፈቅዶ ኤርትራዉያን በድጋሚ የሪፌረንደም አድል ቢሰጣቸዉ ያለጥርጥር ከኢትዮጵያ ጋር መሆንን እንደሚመርጡ በርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ባለፈዉ የደርግ ዘመን የዚህ ዓይነት ፍቅርና ከበሬታ ኤርትራዉያን አሳይተናቸዉ ቢሆኑ ኖሮ ለመገንጠል ባልወሰኑ ነበር፡፡ በኢህአዴግ የሚመራዉ መንግስት በተለይም አቶ መለስ ኤርትራዉያን ጥለዉን እንዳይሄዱ የበኩላቸዉን ጥረት ማድረጋቸዉ ባይቀርም ነገር ግን ደርግ አስቀድሞ ሁሉን ነገር አበላሽቶ ስለቆዬ ያንን ሁሉ ለማስተካከል ለመለስ እጅግ አዳጋች መሆኑ እርግጥ ነዉ፡፡

የኤርትራ ህዝብ በተለይ በደርግ ስርአት ኢትዮጵያዊ መባሉ ያስገኘለት አንዳች ጥቅም ቢኖር ኖሮ ደርግ ከወደቀ በኋላ አብሮ ለመኖር ፍላጎት ሊያሳይ ይችል ነበር፡፡ ግን አንድም በመልካም ጎኑ የሚያስታዉሰዉ ነገር ስላልነበረ በሪፌሬንደሙ ወቅት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ለብቻዉ መሆኑን መርጧል፡፡ ይህ ሁኔታ ማለትም የኤርትራ ህዝብ በደርግ ምክንያት ከኢትዮጰያ ጋር አብሮ መኖርን እጅግ አደርጎ በመጥላቱ መለስም ሆነ ኢህአዴግ ይሄን ነገር መለወጥ የሚችሉበት አንዳችም አድል አልነበራቸዉም፡፡

ኢህአዴግ በተለይም መለስ ገና ሀገር የመምራት ሃላፊነት ላይ ከመዉጣታቸዉ በፊት ጀምሮ የአንድነቱ አቋምና ፍላጎት ስለነበራቸዉ በሪፌሬንደሙ ጊዜ የኤርትራ ህዝብ ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ መኖርን ሊመርጥ ይችላል የሚል ትልቅ ተስፋና ምኞት ነበራቸዉ፡፡ ነገር ግን እንደተመኙት ሊሆን አልቻለም፡፡

ብዙዎቻችን እኔንም ጨምሮ ያለ አንዳች ማስረጃ ስንተች እንደነበረዉ የኤርትራ ህዝብ በወቅቱ በሪፌሬንደሙ ለመገንጠል (ነጻነቱን) የመረጠዉ በሻዕቢያ ስለተጭበረበረ ወይም ጫና ስለተደረገበት ሳይሆን ለብቻዉ መሆንን ስለፈለገ ነዉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ሪፌሬንደሙ ላይ ጫና ለማድረግ አለመሞከሩ ብቻ ሳይሆን የህዝቡን ምርጫ ተቀብሎ ለኤርትራ ነጻነት እዉቅና ሰጥቷል፡፡  በወቅቱ ከዚያ ዉጭ ማድረግ የሚችለዉ ሌላ አማራጭም አልነበረም፡፡

ስለእዉነት እንነጋገር ከተባለ ሁላችንም የአቅማችንን ያህል ስህተት ሰርተናል፡፡ በወቅቱ የሀገራችን መሪ የነበሩትም አቶ መለስ ዜናዊ የሰሩት ስህተት ሊኖር ይችላል፡፡ ምናልባትም አቶ መለስ በግላቸዉ ከሰሩት የበለጠ ስህተት የተሰራዉ እሳቸዉ በሚመሩት ድርጅት ሊሆን ይችላል፡፡

ስለዚህ ገና ለገና የመለስን ሆነ የድርጅቱን የሚያሳጣ ነገር ሊኖርበት ይችል ይሆናል ተብሎ ሚሊዮኖች የሚያዉቁትን ታሪክ ለመደበቅ መሞከር የዋህነት እንጂ ሌላ ሊሆን  አይችልም፡፡ አቶ መለስን ፍጹምና ጨርሶ የማይሳሳቱ አድርገዉ የሚቆጥሩ ሰዎች የመኖራዉን ያህል የሳቸዉን ቅንጣት ስህተት በማጉላት ያበረከቱትን ዉሌታ ለመካድ የሚፈልጉ ሁለቱም ዓይነት ሰዎች ለእኔ አይስማሙኝም፡፡

ከኢትዮጵያ ሉአላዊነትና አንድነት ጋር የሚነሱ ስሞታዎችን ሁሉ ሆን ብለዉ ከመለስ ጋር ለማቆራኘት የሚፈልጉ አሉ፡፡ መለስ ከሁሉም ተደማጭነትና ወሳኝነት የነበራቸዉ መሪ ቢሆኑም እጅግ ግትር፤ የማያላዉስና ደረቅ የሆነዉ የድርጅታቸዉ ዉስጣዊ አሰራርና ድስፕሊን የፈጠረባቸዉ ጫና እንደሚኖር ከበፊት ጀምሮ መጠርጠራችን አልቀረም፡፡ ለምሳሌ መለስ ስልጣን ለመልቅቅ ለመቼ እንዳሰቡ በተደጋጋሚ የቀረባለቸዉን አሰልቺ ጥያቄ ሲመልሱ የነበረዉ “ድርጅቴ እስከፈለገኝና ስራ እስካለኝ ድረስ አሰራለሁ” የሚል እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ከፈለገኝ እንዲሰራለት ከፈለገ አላሉም፡፡

መለስ ይሄን ነገር ደጋግመዉ እንዲናገሩ ሆን ተብሎ በቅንብር ተመሳሰይ ጥያቄ እንዲቀርብላቸዉ የተደረገዉ ከኢትዮጵያ ህዝብ ይልቅ የድርጅታቸዉ ፈቃድ ወሳኝነት እንዳለዉ ህዝቡ እንዲያዉቅ በሳቸዉ በኩል ለማስነገርና እሳቸዉን ለማሳጣት የተደረገ ሴራ ነዉ የሚመስለኝ፡፡ ይህን መልስ እንዲሰጡ ከጀርባ ሆነዉ የሚገፏፉ ሰዎች እንደነበሩ ዘግይተንም ቢሆን አሁን  ተረድተናል፡፡ መለስ ከማናችንም በበለጠ በህዝብ ዋሳኝነት የሚያምኑ ሆነዉ እያለ እንደዚያ እንዲናገሩ የተደረጉት በሌሎች ሰዎች ጫና እንደሆነ እረዳለሁ፡፡

2.3/ የኤርትራ ማጥቃት እንዲቆም የተደረገዉ በጄነራሎቹ ሙሉ ድጋፍ እንጂ መለስ ማንንም ሳያማክሩ በግላቸዉ የወሰኑት አልነበረም

በኤርትራ ጉዳይ፤ በወደብ ጉዳይ ሁሉ መለስን ተጠያቂ በማድረግ እሱ እንጂ እኛ የለንበትም የሚሉት የራሱ ጓዶች ናቸዉ፡፡ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞም ከአነሳሱ አስከፍጻሜዉ ድረስ የነበሩ ስህተቶች የመለስና የመለስ ብቻ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡ ጥረታቸዉም ተሳክቶላቸዉ በኤርትራ መገንጠልም ሆነ በወደብ ጉዳይ ሁለግዜም መለስ ሲወቀሱ እንዲኖሩ ተደርገዋል፡፡

ሰራዊታችን በኤርትራ ዉስጥ ገብቶ በጥልቀት ሲያደርግ የነበረዉን ማሳዳ ,እንዲያቆም መለስ ከማዘዛቸዉ በፊት የጄኔራሎቻቸዉን ሃሳብ ለማወቅ በቅድሚያ እንዳማከሯቸዉና እነሱም ከዚ በላይ ወደፊት መግፋት እንደማይችሉ መልስ እንደሰጧቸዉ ይታወቃል፡፡ መጀመሪያም ወደዚህ ዉሳኔ ለመምጣትም ጉትጎታ የነበረዉ ከሌሎቹ የፓርቲዉ አመራሮችና ከአንዳንድ ወታደራዊ ሹሞች እንደነበርም ግልጽ ነዉ፡፡

መለስ ጄኔራሎቹን አማክረዉ ወደፊት ለመግፋት አንደማይችሉ መልስ ከሰጡዋቸዉ በኋላ ነዉ ዉሳኔዉን የወሰኑት፡፡ መለስ ሰራዊቱ ማጥቃቱን እንዲያቆም ትዕዛዛ ከመስጠታቸዉ በፊት ወታደራዊ ሽማምንቱን አማክረዋል፡፡ ስለዚህ ሁኔታ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ እሳቸዉ በሚመሩት አንድ ስብሰባ ላይ ሁኔታዉን አስታዉሰዉ በድጋሚ ሲናገሩ ከጀኔራሎቹም ሆነ በቦታዉ ከነበሩት አንዳንድ የፓርቲያቸዉ አመራሮች መካከል ይሄን ጉዳይ ያስተባበለ አንድም ሰዉ አልነበረም፡፡

2.4/ በጦርነቱ ወቅት መለስ ሰራዊታችን አሰብን እንዲቆጣጠር ትእዛዝ ሰጥተዉ የነበረ ቢሆንም በአቅም ማነስ ተግባራዊ ሊሆን (ሊሳካ) አልቻለም፡፡  

አስቀድሜ እንደጠቀስኩት መለስ አሰብን ለማስመለስ በነበራቸዉ ፍላጎት መሰረት ለሰራዊቱ አዛዦች እንዲተገብሩት ትእዛዝ መስጠታቸዉንና ሰራዊቱ ግን ሞክሮ ለግዜዉ እንዳልተሳካለት በገለጹበት ወቅትም ይህንንም ያስተባበለ አንድም ጄኔራልና ኮሎኔል አልነበረም፡፡

እንዲዉም በጣም የገረመኝ መለስ በአሰብ ጉዳይ ብዙ እየተተቹ እንደነበር በሚገባ እያወቁ ነገር ግን ስማቸዉን ለመጠበቅ በሚል እንኳን አሰቀድሜ የገለጸኩትን የአስብን በሃይል የማስመለስ እቅዳቸዉን ለፖለቲካ ፍጆታ ሊጠቀሙበት አለመሞከራቸዉ ነዉ፡፡ እንዲያዉም እጅግ የገረመኝ በወቅቱ የተናገሩት ነዉ፡፡ “ይሄ ጉዳይ (ስለአስብ የነገሩንን ማለታቸዉ ነዉ) መቼም ከዚህ አዳራሽ ዉጭ ይወጣል ብዬ አላስብምበሚል በተዘዋዋሪ መንገድ እንዳናወራ ምክር ወይ ማስጠንቀቂያ ነዉ የሰጡን፡፡

እኔ ግን እጅግ የገረመኝ ይሄ ነገር ቢወራ የሳቸዉን ስም ለማደስ ጠቀሜታዉ የጎላ ሆኖ እያለ እንዲነገር ያልፈለጉበት ምክንያት ከሳቸዉ ስም ይልቅ ለመከላከያ ሰራዊታችን ስምና ክብር በማሰብ እንደሆነ ነዉ የተገነዘብኩት፡፡ መከላከያ ሰራዊታችን የሀገሩን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር አልቻለም ተብሎ ክብሩ ዝቅ ከሚል የእሳቸዉ ስም ቢጎድፍ እንደሚመርጡ የተረዳሁበት አጋጣሚ ነዉ፡፡

በደርግ ስርአት የነበርን እንደምናስታዉሰዉና በቀድሞ ከፍተኛ መኮንንች በጦርነቱ ዙሪያ በተጻፉ በርካታ መጽሀፍት ላይ በተደጋጋሚ የተገለጸዉ የዚያን ግዜ የሀገሪቱ መሪ ኮ/ል መንግስቱ በሳቸዉ አመራር ድክመትና ያለአግባብ በሚያደርጉት ጣልቃገብነት የተነሳ በጦርነቱ የደረሱ ዉድቀቶችን ሁሉ በሰራዊቱ አዛዦች ላይ ማላከክና ተጠያቂ ማድረግ ልማድ ማድረጋቸዉን ነዉ፡፡ መለስ ግን በሰራዊቱ አቅም ማነስ ሆነ በአዛዞች ድከመት የተፈጠረን የዘመቻ ዉድቀት ሃላፊነቱን ራሳቸዉ መዉሰዳቸዉ እጅግ አስገራሚ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በሁለቱ መሪዎች መካካል የነበረዉን ልዩነት በሚገባ የሚያሳይ ነዉ፡፡

ይሄ ግምት የእኔ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ አብሮኝ ስብሰባዉን የታደመ ጓደኛዬም ጭምር ነበር፡፡ ጓደኛዬ በወቅቱ ሁኔታዉ በጣም ገርሞት መለስ አሰብን ለማስመለስ መሞከራቸዉ በይፋ ቢነገር ጠቃሚ መሆኑን እያወቁኑ እሳቸዉ ግን እንደዚያ እንዲባል አለመፈለጋቸዉን አስታዉሶ በቁጭት ሲናገር እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ መለስ ለመከላከያ ሰራዊታችን ክብር ሲሉ ራሳቸዉን መጉዳታቸዉ አንድ ነገር ሆኖ ለባህር በር የነበራቸዉ ትክክለኛ አቋምም በተዛባ መንገድ በመተረጎሙ ምክንያት አለአግባብ ለትችት ሰለባ መሆናቸዉ ነዉ፡፡ ፡

2.5/ ባድመ ለኛ ተወስኗል ተብሎ በሃሰት ህዝብ ላይ የተቀለደዉ መለስ እንደዚያ እንዲሆን ስለፈለጉ አይደለም

መለስ በሉአላዊነት ጉዳይ ላይ ያለአግባብ ሲወቀሱ እንደነበር ጥሩ ማሳያ የሚሆነን ለኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላዉ ዓለም መሳቂያ መሳለቂያ ያደረገን “ባድመ ለኛ ተወስኗል! ”ተብሎ ህዝብን ያለአግባብ አስጨፍረን ስናበቃ በማግስቱ እንደተባለዉ አለመሆኑ የታወቀበት አሳፋሪ ክስተት ነዉ፡፡ ይሄን ግዙፍ ስህተት የሰራዉ (ነገሩ ስህተት ሳይሆን ሆን ተብሎ የተደረገ ነዉ የሚመስለዉ) ባለስልጣን መለስ እንደዚያ በህዝብ ላይ እንዲቀልድ ሰላዘዙት እንዳልነበር ሁላችንም ጠንቅቀን እናዉቃለን፡፡

ያንን ያደረገዉ ባለስልጣንም ሌላዉ ቀርቶ ተሳስቻለሁ፡፡ ስህተቱ የድርጅቴ ሳይሆን እኔ በግሌ የሠራሁት ስህተት ነዉ ብሎ ህዝቡን ይቅርታ ያለ መጠየቁ ድፍረት በመለስ ምክንያት አልነበረም፡፡ ድርጅቱም ቢሆን ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ የተሰራዉ ስህተት የአንድ ግለሰብ እንጂ የፓርቲዉ (የመንግስት አመራሩ) ስህተት አይደለም በማለት ለማስተባባልም ሆነ ህዝብን ለማረጋጋትም አልሞከረም፡፡ ሌሎች የፓርተዉና የመንግስት ባለስልጣናት ያን ባለስልጣን በአደባባይ ሲተቹትና ሲወቅሱት ያልተሰማዉ ለአቶ መለስ ክብር ተብሎ እንዳልሆነ ጠንቅቀን እናዉቃለን፡፡

በአደባባይ ለዋሸዉ ባለስልጣን ክብር ታስቦ ከሆነ ደግሞ የአንድ ባለስልጣን ክብር ከኢትዮጵያ ህዝብ ክብር እንደሚበልጥ በአዋጅ ሊነገረን በተገባ ነበር፡፡ ባለስልጣኑ ከነበረበት ሃላፊነት ቦታ የተነሳዉም የኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ላይ በደል ፈጽመሃል ተብሎ በቅጣት ሳይሆን በመተካካት ስም ነዉ፡፡ በዘጠና ሚሊዮን ህዘብ ላይ ላሳየዉ ንቀት በሰራዉ አሳፋሪ ድርጊቱም ጭራሽ አለመወገዙ ከመለስ ጋር የሚያገናኘዉ ነገር አይደለም፡፡

ይህ ባለስልጣን በሚመራዉ የመንግስት መስሪያ ቤትና በፓርቲዉ ዉስጥ በነበረዉ ቁልፍ ሃላፊነት መሰረት የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም እንዲያስከብር አደራ ተሰጥቶት እያለ ነዉ ከኤርትራ ጋር በነበረዉ ድርድር ላይ ሃላፊነቱን ዘንግቶ ለሽንፈት እንድንዳረግ ያደረገዉ፡፡ የድርጅቱ ሌሎች አመራሮች ግለሰቡን አንድም ግዜ ሳይወቅሱት ጥፋቱን ሁሉ በተዘዋዋሪ መንገድ ለማላከክ የተሞከረዉ መለስ ላይ ነዉ፡፡ ስለዚህ የግል ሚዲያዎች፤ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ፤የሰራዊታችን አባላት፤ ህዝቡ እኔንም ጨምሮ  በከሸፈዉ ሙግት ምክንያት መለስን ብቻ ነጥለን ስንወቀስ ቆየን፡፡

መለስ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም ላይ በደል ለመስራት ዓላማ ያልነበራቸዉ መሆኑ እንጂ እንደማንኛዉም ሰብአዊ ፍጡር ተሳስተዉ የማይገባ ነገር ሲሰሩ ከተገኙ የፓርቲዉ አመራሮች ለምንድነዉ በግልጽ ማረምና መገሰጽ የሚሳናቸዉ? መልሱ ግልጽ ነዉ፡፡ በመለስ ላይ ሲሰነዘር የነበረዉ ዉንጀላ ሁሉ አለአግባብ የተሰነዘረና ዒላማዉን የሳተና ዉሸት ስለነበር ነዉ፡፡  ዋናዉ ተጠያቂ ማን እንደሆነ ወደፊት ታሪክ ገሃድ ያወጣ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡

የራሳችንን መሬት ለዚያዉም የደማንበትን በፍርደገምድል ለኤርትራ አሳልፈን መስጠታችን ሳያንስ ጥፋቱን የሰራዉ ማን እንደሆነና ተጠያቂዉ ምን ህጋዊ ቅጣት  እንደተወሰነበት  አልተነገረንም፡፡ የድንበር ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ይልቅ ለኤርትራ የሚያደላ ስለነበር ነዉ እንዳይባል ይሄ ግምት አንዳችም መሰረት የለዉም፡፡ ዋናዉ ምከንያት የኛ ተደራዳሪዎች ድክመት መሆኑን በግልጽ መቀበል ይኖርብናል፡፡ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተሰራዉ በደል በዚህ ብቻ የሚበቃ አልሆነም፡፡ መሬቱን ማጣታችን ሳያንስ ጭራሽ ለኛ ተወስኗል ቢሎ እንደ ህጻን በህዝብ ላይ መቀለድ እጅግ አሳፋሪ ነዉ፡፡

ዜናዉን የተከታተለዉ የአለም ህዝብ እስኪታዘበንና አስከሚሳለቅብን ድረስ የአዲስ አበባን ህዝብ ወደ አደባባይ አስወጥተን በቀጥታ የቴሌቭዝን ስርጭት አስጨፍረን ስናበቃ በማግስቱ ደግሞ ዉሼት ሆኖ ተገኘ፡፡ ይሄን ሁሉ ጫወታ በህዝብ ላይ የተጫወተዉ ባለስልጣን እንዳችም ግሳጸ አልተሰጠዉም፡፡ ኢህአዴግ በተደጋጋሚ በተግባር ያረጋገጠልን አንድ መሰረታዊ ችግሩ በኢትዮጵያ ህዝብና በፓርቲዉ መካከል በሆነ ጉዳይን በሚመለከት የግድ አንዱን የመምረጥ ጉዳይ ሲኖር ብዙዉን ግዜ ለፓርቲዉ ማድላቱ ነዉ፡፡ ፓርቲዉንና የፓርቲዉን ቁልፍ አመራር ከማሳጣት ይልቅ የ90 ሚሊዮን ህዝብ ጉዳይን ችላ ማለት እንደሚቀለዉ አስቀድሜ የጠቀስኩት ”የባድመ ለኛ ተወስኗል“ ታሪክ ጥሩ ማሳያ ነዉ፡፡

ኢህአዴግ መራሹ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ችግር እንዳለበት ሌላዉ ማሳያ በሰሞኑ የዶ/ር ቴድሮስ ለአለም ጤና ድርጅት ለመመረጥ የቻሉበት ሁኔታ ነዉ፡፡ ዶክተር ቴድሮስ ከአብዛኛዎቹ የህወሃት/ኢህአደግ ባለስልጣናት በብዙዎቹ ኢትዮጵያዉን ዘንድ ጥሩ ስም ያላቸዉና ተወዳጅ እንደሆኑ ጠንቅቄ አዉቃለሁ፡፡ እኔም ብሆን ለሳቸዉ የተለየ አክብሮት አለኝ፡፡ በመመረጣቸዉ የከፋቸዉ ጥቂት ሰዎች ባይጠፉም አብዛኛዎቻችን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል፡፡

ይሁን እንጂ መንግስትና ኢህአዴግ ዶክተር ቴድሮስ እንዲመረጡ ያደረገዉን ከፍተኛ ጥረት ሲነገር የሰማን ሰዎች መንግስት አንድን ግለሰብ ለማሾም ይሄን ያህል ከደከመ ምንአለበት ታዲያ የኢትዮጵያ ሉአላዊነት ጉዳይ ላይ በተለይ ከኤርትራ ጋር በነበረዉ ሙግትና በአሰብ ጉዳይ የዚህን ግማሽ ያህል እንኳን ጥረት አለማድረጉ የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡

የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫን ከአዲስ አበባ ለማስነሳት በነጋዳፊና በመሰሎቹ የተዶለተዉን ዱለታ  እንዴት አድርገዉ ድባቅ በመምታት እነ ጋዳፊን አፋቸዉን እንዳስያዙና ምንዉ በቀረብን አስከሚሉ ድረስ በሃፍረት አንዳለሸማቀቋቸዉ ካየሁ በኋላ ምን ነበረበት ታዲያ መለስ የዚህ አይነት ተቀባይነትና ተደማጭነት የማሳመን ችሎታና ለኢትዮጵያ ታላቅ ራእይ የነበራቸዉ መሪ ሆነዉ እያለ ከኤርትራ ጋር በተያያዘ የዚያን ዓይነት አስቀያሚ ዉሳኔ እንዴት ለወሰንብን ቻለ እያልኩ ሁልግዜ በቁጭት ራሴን እጠይቃለሁ፡፡

2.6/ መለስ ያለ አግባብ ለብዙ ትችቶች ሰለባነት ርገዋል  

የተሰሩ ስህተቶችን ሁሉ ከመለስ ጋር ብቻ ለማቆራኘት መሞከርና ራስን ንጹህ ለማድረግ መሞከር ብዙም የሚያወጣ አይደለም፡፡ የጦርነቱን ግምገመማ የማናደርገዉ መለስን ያሳጣል ተብሎ ከሆነ መለስ ከሌላዉ በተለየ የሚሳጡበት ወይንም የሚተቹበት አንዳችም የተለየ ሃጥያት ሰለሌለባቸዉ ነው? ይልቁስ አጉል ሰበብ ከመደርደር ግምገማዉ ላይ ብንበረታ ለሀገሪቱም ለመከላከያችንም ይበጃል፡፡

መለስ ስህተት የሚባል ነገር አልሰሩም በሚል እየተሟገትኩላቸዉ አይደለም፡፡ ስህተትማ ይኖራል፡፡ መለስ እንደመሪም እንደዜጋም የሰሩት ስህተት ይኖራል፡፡ ነገር ግን የስህተቶች ሁሉ ተሸካሚ ለማድረግ መሞከሩ ግን ተገቢ ስላልሆነ ነዉ፡፡ መለስ በመጨረሻም የመሳሪያ ግዥዉ እንዲከናወን ቢፈቅዱም መቼም እሳቸዉ (መለስ) በየሀገሩ እየዞሩ በመሳሪያ ግዥዉ ላይ እንደማይሳተፉ ግልጽ ነዉ፡፡ በርካታ የዉጭ ምንዛሪ ወጥቶ መሳሪያ ካልተገዛ እያሉ ሲጎተጉቱ የነበሩ ሰዎች ለዚህ ተብሎ የተረከቡትን የዉጭ ምንዛሪ ገንዘብ በሙሉ ለታለመለት ዓላማ ለመሳሪያ ግዥ አዉለናል ብለዉ ቢነግሩን ማን ያምናቸዋል?

መለስ በወቅቱ ከቻልን በእጃችን ባለዉ መሳሪያ እንዋጋ፤ካልተቻለና የግድ ከሆነ ደግሞ የግድ የሚያስፈልገንን ብቻ እንግዛ አሉ እንጂ መሳሪያ በጭራሽ መገዛት የለበትም አላሉም፡፡ መለስ በወቅቱ ወጪያችን የሀገሪቱን አቅም ለዘለቄታዉ የሚጎዳ እንዳይሆን ጥረት ማድረጋቸዉ ከየትኛዉም ለሀገር አሳቢ መሪ የሚጠበቅ ባህሪይ በመሆኑ መለስ በዚህ አቋማቸዉ ሊመሰገኑበት ሲገባ ጭራሽ ጦርነቱን ለማደናቀፍና የኢትዮጰያን ሰራዊት ተሸናፊ ለማድረግ አስበዉ ያደረጉት ተደርጎ በሃሰት የተሰነዘረባቸዉ ዉንጀላና ትችት ብዙ ነዉ፡፡

መለስ ላይ የተሰራዉ ደባ ቀላል አለመሆኑ ጥሩ ማሳያ የሚሆነዉ እሳቸዉ ለሰሩትም ሆነ ላልሰሩትም ሁሉ ተወቃሽ በመደረጋቸዉ ይሄዉ ዛሬ በህይወት በሌሉበት ወቅትም ለሀገሪቱ የሰሩት ስንት ዉለታ እያለ ህዝቡ ተገቢዉን ከብር እንዳይሰጣቸዉና በአግባቡ እንዳይታወሱ መደረጋቸዉ ነዉ፡፡ ይህ መቼም ለሁላችንም በጣም አሳዛኝ ነዉ፡፡

ለማናዉቃቸዉ ለእነ ሌኒንና ማርክስ ሃዉልት ሲቆምላቸዉ በነበረ ሀገር እንዲሁም በየክልል ከተሞች ከዚያዉ አካባቢ ዉጭ ለመላዉ ሀገሪቱና ለኢትዮጰውያ ህዝብ ምን እንደሰሩ በዉል ታሪካቸዉ ለማይታወቁ ግለሰቦች በፉክክር በየስርቻዉ መታሰቢያ ሃዉልት በሚቆምባት ጉደኛ የሆነች ሀገር ዉስጥ የመላዉ ኢትዮጵያን ክብር ከፍ እንዲል ላደረጉና ሀገራችንን ከወደቀችበት አንስተዉ ተገቢዉን የክብር ቦታዋን እንዲታገኝ እድሜ ልካቸዉን ለደከሙት ለመለስ እንድ እንኳን መታሰቢያ ሃዉልት በሀገሪቱ እምብርት በዋና ከተማዋ አለመኖሩ እጅግ የሚያስተዛዝብ ነዉ፡፡ ይህ ግን የሳቸዉን በተለየ መታወስ የማይሹ ጥቂት ግለሰቦች ሴራ ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያ ህዘብ ፍላጎት እንዳልሆነ እረዳለሁ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ አግረመንገዴን አንድ ጠቀስ አድረጌ ማለፍ የፈለኩት ከሰሞኑ በአይጋ ፎሬም ድረ-ገጽ ላይ ኤርትራ የግላችን ኢትዮጵያ የጋራችን…” የሚል ርእስ በተሰጠዉ ጽሁፍ ላይ አቶ ብሩክ የተባሉ ጸሃፊ መለስን ለማመስገን ይሁን ወይንም በታሪክ ተጠያቂ ለማድረግ ታስቦ ይሁን በዉል ባልተረዳሁት መንገድ መለስን ኢሳይያስንና የኤርትራን መገንጠል በሚመለከት የሰጡት የተዛባ ትንታኔ ነዉ፡፡

ጸሀፊዉ በርካታ ሌሎች ጠቃሚ ጉዳዮችን ያነሱ ቢሆንም የእኔ ዋነኛ ትኩረት መለስና ኢሳይያስን እያነጻጸሩ ለኤርትራ መገንጠል ከኢሳይያስ ይልቅ የመለስ ድርሻ ወሳኝ እንደነበር ያመለከቱበትን የጽሁፉን ክፍል ነዉ፡፡ ጸሃፊዉ በዋህነትና በቅንነት የሰራዉ ስህተት እንደሆነ እረዳለሁ፡፡

ጸሃፊዉ የኤርትራ መገንጠል ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ሲባል ተገቢ እንደነበር ሊያሳምነን ሞክሯል፡፡ በኤርትራ ነጻነቷን ማግኘት ከኛም በላይ እጅግ የተከፉት ራሳቸዉ ኢሳያስ አፈወርቂ መሆናቸዉን አስገራሚ ትንተና ይሰጥና በመቀጠልም ለዚህ ሁሉ ለኤርትራ መነጠል የመለስ ብልህነት የተሞላበት አመራር ዉጤት ነዉ በሚል ለኤርትራ መገንጠል መለስን ያደንቃል፡፡ ያመሰግናልም፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ይመስለኛል ተመሳሳይ ነገር ሰምቻለሁ፡፡ በአንድ ከዉጭ የሚለቀቅ ቴሌቭዥን ጣቢያ ጋዜጤኞችና አንዳንድ የኢሳይስ አድናቂዎች ኢሳይያስ ለኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ የሚጨነቁለትና ለኛ መልካም ነገር በማሰብ እንቅልፍ አጥተዉ እንደሚያድሩና ኢህአዴግ በስልጣን ላይ ባይኖርና እንቅፋት ባይሆን ኖሮ እንደ ኢሳይያስ ምኞት ቢሆን ከኢትዮጵያ ጋር በአንድነት ለመኖር ፍላጎት እንደነበራቸዉ ተደርጎ የተቀነባበረ ድራማ መሰል ዝግጅት ተከታትለን ስቀንባቸዋል፡፡

ዛሬም ይሄዉ ጸሃፊም ይህንኑ ለመድገም የሞከሩ ይመስል ኢሳይያስ በአንድነት ለመኖር እየፈለገ “በመለስ ብልህ አመራር ነዉ እንዲገነጠሉ የተደረገዉ የሚል ነገር በድፍረት ነግሮናል፡፡ ኢሳይያስ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ ነጻ ሀገር ለመመስረት ባይፈልግ ኖሮ ያን ሁሉ ዘመን ሳህል በረሃ ላይ መሽጎ መፋለምሰ ለምን አስፈለገዉ?

ኢሳይያስ ደርግ እንደወደቀ በአንድነት ለመኖር ፈልጎ ነገር ግን መለስ እምቢተኛ ስለሆነበት ነው የተገነጠለዉ የሚለዉ ገለጻ መለስን ሆን ቢሎ ለኤርትራ መገንጠል በታሪክ ተጠያቂ ለማድረግ ታስቦ ካልሆነ በስተቀር ”የመለስን ብልህነትና አርቆ አሳብነት “ለማድነቅ ተብሎ የቀረበ ማብራሪያ አይመስለኝም፡፡ እዉነቱን ብቻ እንነጋገር ከተባለ ኢሳይያስ ከኢትዮጵያ ጋር ለመቀጠል አንድም ቀን ፍላጎት ኖሮአቸዉ አያዉቅም፡፡

ኢሳይያስ ከኢትዮጵያ መነጠል የለብንም አብረን እንኑር የሚል በግላቸዉ ፍላጎት ቢኖራቸዉ እንኳን የኤርትራ ህዝብ እሽ እንደማይላቸዉ ግልጽ ነዉ፡፡ ምክንያቱም አስቀድሜ በዚህ ጽሁፍ ዉስጥ እንደጠቀስኩት የኤርትራ ህዝቡ በደርግ ብልሹ አመራር ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ የመኖር ፍላጎቱ ተሟጦ ስለነበር ነዉ፡፡ ሌላዉ ደግሞ ኢሳይያስ በአንድነት እንቀጥል የሚል ሃሳብ አንስተዉ ቢሆን ኖሮ መለስ “መገንጠል ነዉ የሚበጃችሁ” ብለዉ እምቢተኛ እንደማይሆኑ በጣም እርግጠኛ ነኝ፡፡

የኤርትራ ነጻ መዉጣት ጉዳይ መጀመሪያዉኑ በትጥቅ ትግል መልስ ያገኘና  የኤርትራ ህዝብ የነጻነት ትግል ዉጤት እንጂ የመለስ ሴራ ዉጤት አይደለም፡፡ ወይንም ኢሳይያስ ያለፍላጎቱ በመለስ ሴራ ተገፋፍቶ እንዲገነጠል የተደረገበት ሁኔታም አይደለም፡፡

ኢህአዴግ ስልጣን እንደያዘ ሰሞን ራሱ የኤርትራዉ ኢሳይያስ በታዛቢነት በተገኘበት የአዲስ አበባዉ የሰላም ጉባኤ ላይ አሁን በህይወት የለሉት ፕሮፌሰር አስራት ስለ ኤርትራ መገንጠል ጉዳይ አንስተዉ ተቃዉሞ ሲያቀርቡ ኢሳይያስ “ኢትዮጵያ አንድነት ምናምን የምትሉትን ተረት ተረት ወዲያ አድርጉት፤ የኤርትራ ነጻ መዉጣት ጉዳይ በጦርነት መልስ ያገኛና ያበቃለት ጉዳይ  ነዉ” በሚል ነበር በቁጣ የገለጹት፡፡

ኢሳይያስ ኤርትራን የገነጠለዉ መለስ ‹‹አንድነቱን አልፈልግም›› በማለታቸዉና እንቅፋት በመፍጠራቸዉ አይደለም፡፡ ስለ መለስ የትግሉ ዘመን አመለካከታቸዉ በዉጭ ሰዎች የተሰጡ በርካታ ጽሁፎችን ለማንበብ እድል አግኝቻለሁ፡፡ ነገር ግን አንድም ጽሁፍ ላይ መለስ የአንድነቱ ተቀናቃኝ እንደነበሩ የተገለጸበት አላጋጠመኝም፡፡ በተቃራኒዉ አንድነቱ እንደሚበጅ ነገር ግን ወሳኙ የኤርትራ ህዝብ እንደሆነ ነዉ ሲጠቀስ የነበረዉ፡፡ እንግዲህ እንደዚህ ጸሃፊ ዓይነት ሰዎች አዉቀዉም ይሁን ባለማወቅ በየዋህነት በሚሰጡት የተዛቡ አስተያየቶችና መግለጫዎች ምክንያት ነዉ መለስ ሁልግዜም ለሁሉም ጥፋቶች የትችት ዋነኛ ሰለባ ሆነዉ የኖሩት፡፡

ይህን ጉዳይ እዚህ ላይ ገታ አድርጌ አስቀድሜ ወደ ጀመርኩት ኤርትራን በሚመለከት የተጠያቂነት ወቀሳ ላምራ ፡፡

ኤርትራን በሚመለከት ኢህአዴግም ቢሆን ከትችት ሊያመልጥ ስለማይችል የራሱን የተጠያቂነት ድርሻ መዉሰድ ይገባዋል፡፡ በኢህአዴግ በኩል ወቀሳዉ የሚበረታበት ኤርትራን በሚመለከት ስህተት መስራቱ ወይም ጥፋት ማጥፋቱ አይደለም፡፡ ከሞላ ጎደል ሁሉም ያለፉት መንግስታት ጥፋት አጥፍተዋልና፡፡ ንጉሰ ነገስቱም ሆኑ ኮ/ል መንግስቱ ለኤርትራ እዚህ ደረጃ መድረስ የየበኩላቸዉን አስተዋጽኦ አድርገዋልና፡፡ ነገር ግን የሁለቱም ጥፋት ከኢህአዴግ የሚለየዉ ከኢትዮጵያ ሉአላዊነት አኳያ ኤርትራን ላለማጣት ተብሎ የተሰራ ጥፋት መሆኑ ነዉ፡፡

ኢህአዴግን በሚመለከት ለየት የሚያደርገዉ የቀድሞዎቹ መንግስታት ከሰሩት ጥፋት ተቃራኒ በሆነ መልኩ ለኤርትራ መነጠል ከሞላ ጎደል“ ቀላል የማይባል  ሚና” መጫወቱ ነዉ፡፡ ይህ የኢህአዴግ ሚና ከአንድነት ይልቅ የኤርትራ መገንጠል ይበጃል በሚል የተደረገ ሳይሆን ህዝቡ ከጨቋኝ ስርአት ጋር ሲያደርግ የነበረዉን ትግል በመርህ ደረጃ ትክክል ነዉ ብሎ ስላመነበት ነዉ፡፡ ዞሮ ዞሮ ዉጤቱ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚጎዳ መሆኑ ባይቀርም ነገር ግን ሆን ተብሎ መገንጠል አለባቸዉ በሚል የኢትዮጵያን አንድነት በመቀናቀን  እንደተከናወነ አድርገን እንድንቆጥር አያደርግም፡፡ የኢህአዴግ ሚና ለኤርትራ መገንጠል ምንም ይሁን ምን እንደ ኢትዮጵያዊ ድርጅት ሲታይ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት መሆኑ ላይ አያከራክርም፡፡

ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ኢህአዴግን ያስተቸዉ ያለፉ ጥፋቶቹን ተቀብሎ አጥፍቻለሁ ብሎ ራሱን ለመዉቀስም ሆነ ለመጸጸት ከተቻለም ህዝብን ይቅርታ ለመጠየቅ እስከዛሬም አለመፈለጉ ነዉ፡፡ በርግጥ ኢህአዴግ ለኤርትራ መገንጠል (ነጻነት) ከፍተኛ አስተዋጺኦ እንዳደረገ ዛሬም ድረስ የሚያምንበትና የሚኮራበት አቋሙ ስለሆነ በዚህ ጉዳይ ይቅርታ መጠየቅ ነበረበት የሚባል ነገር ትርጉም ላይኖረዉ ይችላል፡፡ ዛሬም ድረስ በዚህ ድርጊታቸዉ በአደባባይና በሬዲዮ ሳይቀር በኩራት የሚናገሩ የአህአዴግ አመራሮች እንዳሉ ስለምናዉቅ መቼም ቢሆን እንደ ስህተት ቆጥረዉ ህዝብን ይቅርታ ይጠይቃሉ ብለን አንጠብቅም፡፡

ኢህአዴግ ከዚህ በፊት በነበሩ ሁኔታዎች አስገዳጅነት ኤርትራን (ወደብን) በሚመለከት የሠራቸዉ ስህተቶች ካሉ ወደኋላ ተመልሶ “እዚህ ላይ ትክክል ነበርኩ፡፡ እዚህ ላይ ግን ተሳስቻለሁ” አለማለቱ ወደፊትም ኤርትራንና በአጠቃላይም የኢትዮጵያን አንድነት በሚመለከቱ ሌሎችም ጉዳዮች ላይም የህዝብ አመኔታ እንዳይኖረዉ ጋሬጣ እንደሚሆንበት ግልጽ ነዉ፡፡ ከኤርትራ ጋር በተደረገዉ ጦርነት በጦርነቱ ዝግጀት፤ አካሄድና አጨራረስ በኃላም በድርድሩ ስኬታማ አለመሆን ላይ ህዝቡ ኢህአዴግን ክፉኛ መጠራጠሩ ያጋጣሚ ነገር ሳይሆን በየግዜዉ ኤርትራን በሚመለከት የደርጅቱ አመራሮች ሲሰጡት ከነበረዉ እርስበርሱ የተምታታ መግለጫና በተግባርም ለኤርትራ ሲያሳዩ ከነበረዉ የተለየ ፍቅር የተነሳ በህዝቡ አይምሮ የተፈጠረዉ ኢህአዴግን የመጠራጠር አመለካከት የመነጨ ነዉ፡፡

በኤርትራ መገንጠል ገና ከመነሻዉ የህወሃት/ኢህአዴግ ሚናን በሚመለከት የተዛቡና እርስበርስ የሚጋጩ መግለጫዎችን ነዉ ሲነገረን የቆየዉ፡፡ ህዝቡ ለኤርትራ መገንጠል የመጀመሪያዉ ተጠያቂ ናችሁ ሲላቸዉ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነዉ በሚለዉ መሪህ መሰረት በጸረ -ደርግ ትግል ላይ ዉስን የሆነ ትብብር አደረግን እንጂ ለኤርትራ መገንጠል ወሳኝ ሚና አልነበረንም” ይላሉ፡፡ በሌላ ግዜ ደግሞ “ሻእቢያ የኛ ወሳኝ ድጋፍ ባይኖረዉ ኖሮ  ከናቅፋ ምሽጉ ሳይወጣ አድሜ ልኩን ይኖር ነበር፡፡ ስለዚህ እድሜ ለወያኔ ይበል” ይሉና ይፎክራሉ፡፡ እንደዚህ የሚሉት ሻእቢያን ለማናደድ ይሁን ወይንም ደግሞ እኛን ለማበሳጨት በቅጡ ለመረዳት አልቻልንም፡፡

2.7/ ለኤርትራ ህዝብ ነጻነቱን ግኘት ኢህአዴግ ተወቃሽም ተመስጋኝም አይደለም

ብዙዎቹ እንደሚስማሙበትና እኔም እንደማምንበት ለኤርትራ ነጻ መዉጣት ወሳኙ የኤርትራ ህዝብ ተጋድሎ እንጂ የህወሃት ድጋፍ ማድረጉ አልነበረም፡፡ ይህ ማለት ግን ሻእቢያ የህወኃትን ሚና በመካድ አኮስሶ እንደሚገልጸዉ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ህወኃት ሆን ብሎ ለኤርትራ መገንጠል ለዓመታት ሲሰራ የቆየ ድርጅትና ለኤርትራ መገንጠል ወሳኝ ድርሻ እንደነበረዉ አድርገዉ እንደሚናገሩትም አይደለም፡፡ ለኤርትራ መገንጠል የህወኃትን ሚና ወሳኝ ማድረግም ሆነ ለኤርትራ ህዝብ ነጻነት ኢህአዴግ ያደረገዉን በጎ አስተዋጽኦ መካድ ሁለቱም አስተያየቶች የተዛቡ ናቸዉ፡፡

ለደርግ እንደ ስርአት መንኮታኮት የህወኃት ጸረ-ደርግ ትግል የነበረዉን ድርሻ ለመቀበል ያልፈለጉ ወገኖች ገና ከመጀመሪያዉ ትልቅ ዋጋ አስከፍሎአቸዋል፡፡ ከ/ል መንግስቱ የህወኃትን /ኢህአዴግን ጥንካሬ ምንጭ ለመረዳት ስለተሳናቸዉም በትግራይ ሲካሄድ የቆየዉን ጸረ ደርግ ትግል እዉቅና ለመስጠት በጭራሽ አልፈለጉም ነበር፡፡ ይህ የኮ/ል መንግስቱ ስህተት ለሚመሩት ስርአት መንኮታኮት  ቁልፍ ድርሻ እንደሚኖረዉ መረዳት የቻሉት እጅግ ዘግይተዉ ሁሉም ነገር እያበቃለት መሆኑን ከተረዱ በኋላ ነዉ፡፡

የህወኃት ትግል የደርግን ስርአት መዉደቅ እዉን ያደረገ ወሳኝ ትግል እንደነበር ደርግ ለመረዳት ብዙ ግዜ ፈጅቶበታል፡፡ የኢህአዴግ አመራሮች በግልጽ ይናገሩ አይናገሩ ዞሮ ዞሮ ኢህአዴግ ለደርግ ስርአት መዉደቅና ለኤርትራ ህዝብ ነጻነት ትልቅ አስተዋጽ እንደነበረዉ መካድ አይቻልም፡፡

በተለይ በትግራይ ዉስጥ በሽረ እንደስላሰ ጦርነት በ604ኛ ኮር ላይ የደረሰዉ ድምሰሳ ጉዳዩ የአንድ ኮር መደምሰስ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የደርግ ዉድቀት እሩቅ እንዳልሆነ ያመላከተ ነበር፡፡ ከዚህ ሽንፈት በኋላ ባሉት አጭር ግዜያት በኤርትራም ሆነ በሌላዉ አካባቢ የነበረዉ የመንግስት ሰራዊት ከፍተኛ የሞራል መንኮታኮት የገጠመዉና የመዋጋት ፍላጎቱ የላሸቀበት፤ያን የሽንፈት ክስተት ተከትሎም የደርግ መኮንኖች በደርግ አመራር ላይ ክፉኛ ጥላቻ በመቋጠራቸዉ የኩዴታ ሙከራ የቃጡበት፤ ሰራዊቱ ብቻ ሳይሆን መላዉ የኢትዮጵያ ህዘብም በደርግ ላይ ተቃዉሞዉን በግልጽ መናገር የጀመረበት በአጠቃላይ ደርግ በራሱ በአመራሩ ዉስጥም በተፈጠረበት ቀዉስም በአጭር ግዜ እንደሚወድቅ ግልጽ የሆነበት ሁኔታ የተፈጠረዉ ኢህአዴግ በሽሬ እንዳስላሴ ባገኘዉ ታላቅ ወታደራዊ ድል ነዉ፡፡

የደርግ መዉደቅ በአጭር ግዜ እዉን እንደሚሆን ግልጽ በሆነበት ሰዓት ነዉ ሻእቢያ ሰራዊቱን ፈራ ተባም እያለ  ከምሽግ አዉጥቶ መዳፈር የጀመረዉ፡፡ ኢህአዴግ ለኤርትራ ህዝብ ነጻነት ያደረገዉን አስተዋጽኦ ሻእቢያ ስለሚያሳፍረዉ ደፍሮ በአደባባይ መናገር አይፈልግም፡፡ ሀቁ ግን ማንም ሊለዉጠዉ የማይችለዉ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ ለኤርትራ ህዝብ ትግል ድጋፍ ባይሰጥ ኖሮ በሻእቢያ አቅም ብቻ እዉን ሊሆን ባልቻለ ነበር፡፡

የኤርትራዉ ትግል ከአጠቃላይ የደርግ አንደ ስርአት መዉደቅ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ስለነበር ደርግ በትግራይና በቀጣይም ወደ መሃል አገር እየተደረጉ በነበሩ ዉጊያዎች ባይዳከም ኖሮ በኤርትራ የነበረዉ ጦርነት ለሚቀጥሉትም ሰላሳ ዓመታት መቆየት በቻለ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ለደርግ እንደስርአት መዉደቅም ሆነ ለኤርትራ ህዝብ ነጻነቱን ማግኘት የኢህአዴግን ደርሻ መካድ ትልቅ ስህተት ነዉ፡፡

እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጥያቄ ኢህአዴግ ለኤርትራ ነጻ መዉጣት (መገንጠል) በወቅቱ ያደረገዉ አስተዋጽኦ ዛሬ ላይ ቆመን ስናስብ እንደጥፋት ነዉ መቆጠር ያለበት ወይንስ እንደበጎ ተግባር  የሚለዉ ነዉ፡፡ በርግጥ ሁኔታዉን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅምና ሉአላዊነት አንጻር ስናየዉ የኢህአዴግ ድርጊት የሚያስወቅሰዉ እንጂ የሚያስመሰግነዉ አይሆንም፡፡ የኢትዮጵያን አንድ አካል እንዲገነጠል ረድቶ በዚህ ስራዉ ከቶ ልናመሰግነዉና ልናደንቀዉ አንችልም፡፡ ነገር ግን ለኤርትራ ነጻ መዉጣት ዋናዉ ወሳኝ ኃይል የነበረዉ ሻእቢያና የኤርትራ ህዝብ ነዉ ብዬ ስለማስብ  የኢህአዴግ  ለኤርትራ መነጠል የሚወቀስበትም ሆነ የሚመሰገንበት ሁኔታ አይታየኝም ፡፡

እንደሚታወቀዉ ገዥዉ ፓርቲ (ኢህአዴግ) ከሁሉም ትችቶች ሁሉ በጣም የሚያስቆጣዉ ስለ ኤርትራ በተለይም ስለ ባህር በር ጉዳይ ሲነሳበት ነዉ፡፡ ኢህአዴግ በሌሎች ጉዳዮች የፈለገዉን ያህል ወቀሳና ትችት ቢደርሰበት ተረጋግቶ መልስ ይሠጣል እንጂ ብዙም አይቆጣም፡፡ አያኮርፍም፡፡ ለምሳሌ “ልማት ያለ ጥርጥር አለ፡፡ ነገር ግን ፍትሃዊ የሆነ የሃብት ክፍፍል አላመጣህም፣ ድህነትንም እንደሚነገረዉ አላጠፋህም” ብንለዉ በልማቱ ረገድ የሰራቸዉን ስራዎች በመዘርዘር ለማሳመን ይሞክራል እንጂ ለምን ተተቸሁ ብሎ አይቆጣም፡፡

ስለዲሞክራሲ፡ ስለ ሰብአዊ  መብት ስለ ሙስና መንሰራፋት ወዘተ ቢወቀስ ለማሳመን ከመሞከር ዉጭ  እንዴት ተደፈርኩ ብሎ አይቆጣም፡፡ የወደብ ጉዳይ ሲሆን ግን በተለየ ሁኔታ የሚቆጣበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፡፡ ባለማወቅ በስህተት በሠራዉ ጥፋት ተጸጽቶ ነዉ ብለን ይቅርታ እንዳናደርግለት አንድም ጊዜ በዚህ ጉዳይ ላይ “ተሳስቼ ነበር” ሲልም አልሰማነዉም፡፡

በኢህአዴግ የሚመራዉ መንግሰት አሁን በስልጣን ላይ የሚገኝ መንግስት በመሆኑ ወደ ፊት ለሚሆነዉ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም ራሱ ላጠፋዉም ሆነ ከሱ በፊትም በነበሩ መንግሰታት የተሰሩ ጥፋቶችንም ጭምር የማስተካከል ሃላፊነት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ የትኛዉም ሃላፊነት የሚሰማዉ መንግስት ከሱ በፊት ከነበሩት መንግስታት የወረሳቸዉን በጎም ሆነ መጥፎ ድርጊቶች ላይ ሃላፊነት መዉሰድ መቻል እንዳለበት ይሰማኛል፡፡

የቀድሞዎቹ መሪዎች ያጠፉት ነገር ካለ እንደ ራሱ ጥፋት ቆጥሮ ማስተካከልና መስመር ማስያዝ ይጠበቅበታል እንጂ የቀድሞዎቹ ባበላሹት እኔ ምን አገባኝ ማለት አይችልም፡፡ ምንኒሊክ ከአቅም በላይ ሆኖባቸዉ ወይም በዚያን ዘመን የነበረዉ ልዩ ሁኔታ ሳይፈቅድላቸዉ ቀርቶ በዘመናቸዉ የሰሩት ስህተት ካለ የአሁኑ መንግስት ስህተቱን ለማረም መጣር አለበት እንጂ የቀድሞዎን ስህተት ለራሱ ስህተት እንደሰበብ መጠቀም አይኖርበትም፡፡ ይሄን ታሪካዊ ሃላፊነትን ኢህአዴግ በትክክል ለመረዳቱ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

ኢህአዴግ በምንሊክ ዘመን የነበረና ግዜ የሻረዉን ሰነድ በምንቸገረኝነት ለዛሬ ጉዳይ ለመጠቀም መሞከሩ የተጠቀሰዉን ሃላፊነት በትክክል ለመረዳቱ እንድንጠራጠር አድርጎናል፡፡ ጣሊያን በድጋሚ ወረራ በማድረግ ራሱ ያፈረሰዉን የምንሊክ ዘመን ዉል ኢህአዴግ ለአሁኑ የኤርትራ ጉዳይ ለመሟገቻነት ይዞ መቅረቡ በሃገራችን ብሄራዊ ጥቅም ላይ ምን ያህል ጉዳት እንዳስከተለብን ኢህአዴግ አሁን አሁን ሳይረዳ የሚቀር አይመስለኝም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ዛሬ ኢህአዴግ የሰራቸዉን ጥፋቶች ነገ በቦታዉ የሚተካዉ መጪዉ መንግስትም እንደራሱ ቆጥሮ ማስተካከል ይጠበቅበታል እንጂ ኢህአዴግን ለመንቀፍ መልካም አጋጣሚ አድርጎ በመቁጠር  በዝምታ ማለፍ አይገባዉም፡፡ ፡

3/ ህወሃት/ኢህአዴግን ኤርትራን በሚመለከት ለትችት ከዳረጉት ሁኔታዎች መካከል ጥቂቶቹ

አንደኛ ህወኃት የኤርትራን መገንጠል(ነጻነት) ገና ከመጀሪያዉ በመደገፍ ከሻዕቢያ ጎን ተሰልፎ ለሉአላዊነቱና ለአንድነቱ ሲዋደቅ የነበረዉን የኢትዮጵያን ሰራዊት መዉጋቱ ብቻ ሳይሆን የህወኃት ድጋፍ ባይታከል ኖሮ ሻዕቢያ መቼም ቢሆን ደርግን ማሸነፍ ስለማይችል እዚያዉ ናቅፋ ምሽግ ዉስጥ ተቀብሮ ይቀር ነበር መባሉ ነዉ፡፡

ይህን በሚመለከት ዛሬም ድረስ የህወኃት አንዳንድ አመራሮች ይህንን ታሪክ የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ኤርትራዉያን ጭምር ሰምተዉ እንዲያደንቋቸዉ ደጋግመዉ ደጋግመዉ በአደባባይና በሬዲዮ በኩራት ሲገልጹ መስማት የተለመደ ነዉ፡፡ ህወሃት /ኢህአዴግ ለኤርትራ መገንጠል ወሳኝ ሚና ነበረኝ ካለ አንደ ኢትዮጵያዊ ሆነን ስናየዉ ድርጊቱን በሀገር ላይ እንደተሰራ ትልቅ ታሪካዊ ጥፋት እንዳንቆጥር የሚያደርገን አንዳችም ምክንያት አይኖርምና  ከዚህ አኳያ ትችቱ ተገቢ ነዉ እላለሁ፡፡

ሁለተኛ፡ ከደርግ ዉድቀት በኋላ ሻዕቢያ የመገንጠል ሃሳቡን እንዲተዉና ኤርትራና ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ስርአት መስርተዉ በአንድነት መኖር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ በኢህዴግ በኩል ተገቢዉን ማግባባት አልተደረገም፡፡ እንድያዉም ኢሳይያስ “ለብቻ የመሆኑን አጀንዳ ሰርዘናልና አብረን እንሁን” የሚል ጥያቄ አቅርበዉ ቢሆን ኖሮም ከኢህአዴግ በጎ ምላሽ ላያገኙ ይችሉ ነበር የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ እንደ እኔ እምነት ቁምነገሩ ኢህአዴግ የአትዮጵያንና የኤርትራን አንድነት አለመፈለጉ ሳይሆን የጉዳዩ ባለቤት የሆነዉ የኤርትራ ህዝብ ፍላጎት ነጻ ሆኖ መኖር በመሆኑ ነበር፡፡

ፓወል ሄንዝ (paul henze) የተባሉት አሜሪካዊ ዲፕሎማት ደርግ ከመዉደቁ አንድ አመት በፊት ከአቶ መለስ ጋር ያደረጉትን ሰፊ ዉይይት አስታዉሰዉ እንደገለጹት አቶ መለስ ኤርትራ ባትገነጠል እንደሚፈልጉ ነገር ግን በኢሳይያስ በኩል ህዝቡን የመገንጠል ሃሳቡን እንዲተዉ ለማሳመን አንደሚከብደዉ ገልጸዉላቸዉ እንደነበር ጽፈዋል፡፡ አቶ መለስ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በአንድነት እንድትቀጥል ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸዉ ቢሆንም ነገር ግን የኤርትራ ህዝብ በደርግ ድርጊት ምክንያት ከፍተኛ ጥላቻ ስላደረበት እንኳን አንድ ሆኖ መኖር ይቅርና ስለ ኢትዮጵያም መስማት እንደማይፈልግ ስለሚታወቅ መለስ ሁኔታዉን መቀየር የሚችሉበት አንዳችም ዕድል አልነበራቸዉም፡፡

ደርግ ብዙ ነገሮችን በማበላሸቱ ኤርትራዉያን ከእንግዴህ ወዲያ ከኢትዮጵያ ጋር በአንድነት ለመኖር በጭራሽ ፍላጎት እንዳልነበራቸዉ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ዛሬ የኤርትራም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ስሜት ቢፈተሽ ድሮ በነበረዉ አቋም እንደማይገኝ መገመት አያዳግትም፡፡ በኤርትራ በኩል መገንጠሉ የፈለጉትን ዲሞክራሲ፣ ፍትህ፣ ነጻነትና ብልጽግና ባያመጣላቸዉም በዚህ ምክንያት ብቻ በሪፌረንደሙ ወቅት ነጻነትን መምረጣቸዉን እንደ ስህተት ይቆጥሩታል ብሎ ለመገመት አይቻልም፡፡ ኤርትራዉያን  ለነጻነት የሚሰጡትን ትርጉም በነሱ ቦታ ሆነን ከላየን በስተቀር ከኛ ፍላጎት አንጻር ብቻ መፍረድ አንችልም፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ህዝብ በኩል የኤርትራን (የሻእቢያን) አመራሮችና ፖለቲከኞች ጋጤወጥነት ከተመለከተ በኋላ ከኤርትራ ጋር አንድ ላይ የመሆን ፍላጎቱ መደብዘዙን ለመረዳት አያዳግትም፡፡ በዚህ መሰረትም የኢትዮጵያ ህዘብ ዛሬ ከኤርትራ ጋር አንድ ለመሆን ይፈልግ እንደሆን ቢጠየቅ “አልፈልግም” እንደሚል ምንም ጥርጥር የለዉም፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንዲያዉም አሁን አሁን “አረ እንኳን አንድ ላይ አልሆንን፣ ግልግል ነዉ” የሚሉ እንዳሉ አዉቃለሁ፡፡

በተለይ ሁለቱ ድርጅቶች (ሻዕቢያና ኢህአዴግ) በሚመከተሉት እጅግ የተራራቀ የአይዶኦሎጂና የአድገት አቅጣጫና ፍልስፍና የተነሳ ኢህአዴግና ሻእቢያ በአንድነት ህልዉናቸዉ እንደተጠበቀ በሰላም መኖር የሚችሉበት ዕድል እጅግ ጠባብ በሆነ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያትም በሀገሪቱ ዉስጥ ቀዉስ  ሊከሰት እንደሚችል ቅንጣት መጠራጠር አይቻልም፡፡ ለዚህም ነዉ እኔን ጨምሮ ብዙዎቹ “አሬ እንኳን ቀረብን!፤እንዲያዉም ግልግል ነዉ!“ እያልን ያለነዉ፡፡

ኢሳይያስ እንድነትን እየፈለገ መለስ ነዉ ፊት የነሳቸዉ ወይም የኢሳይያስን የአንድነት ፍላጎት ተስፋ ያስቆረጣዉ መለስ ነዉ የሚለዉ አስተያየት ትክክል አይምስለኝም፡፡ ኢሳይስን ለኢትዮዮጵያ አንድነት አሳቢ መለስን ደግሞ የአንድነት እንቅፋት አድርጎ መግለጽ ፍጹም የተሳሳተ አመለካከት ነዉ፡፡

ሶስተኛ፡ ሪፈረንደም ማድረግ የግድ መሆኑ ከታወቀ በኋላም የኤርትራና ኢትዮጵያ ወደፊት ስለሚኖራቸዉ ግኑኝነት በተለይም የድንበር ጉዳይና የአሰብ ወደብ ጉዳይ አስቀድሞ ስምምነት መደረግ ሲገባዉ አልተደረገም፡፡  የሪፈረንደሙ ፋይዳ ላይም እንኳን ኢትዮጵዉያን ቀርቶ የኤርትራ ህዝብም  በአግባቡ ዉይይት አላደረገበትም፡፡ የሪፈረንደሙን ጥቅምና ጉዳትም ጠንቅቆ ሳይረዳ ነዉ ወደ ምርጫ የገባዉ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎት ባልጠበቀ ሁኔታ የሪፌረንደሙን ዉጤት አጽድቆ ለኤርትራ እዉቅና እንዲሰጥ ለመንግስታቱ ድርጅት የድጋፍ  ደብዳቤ ጽፋል፡፡

አራተኛ፡- ኤርትራ ራሷን ከቻለች በኋላም ቢሆን በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረዉ ግኑኝነት ለኤርትራ የወገነ ግኑኝነት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በእጅጉ የጎዳና ለዝርፊያ ያመቻቸ ግኑኝት ነበር፡፡ ጦርነቱ ተነስቶ እስለሚገላግለን እሰከ 1990 ዓ/ም ድረስ በተከታታይ ለሰባት ዓመታት አገሪቱ በሻዕቢያ ነጣቂዎች ስትበዘበዝ ኢህአዴግ አንዳችም እርምጃ አልወሰደም ነበር፡፡

አምስተኛ፤  ኢትዮጵያን ለመዉረር ሰፊ ዝግጅት እያደረገች መሆኗ እየታወቀ መንግሰት አንዳችም ዝግጅት ሳያደርግ በመቆየቱ  በጦርነቱ በአስር ሺህዎች የሚቆጠር ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል፡፡

ስድስተኛ፡ በኤርትራ ቆስቋሽነት በተጀመረዉ ጦርነት  እኛ የጦርነቱ ተጠቂዎችና ሰለባ ሆነን እያለ መንግስት በድርድሩ ወቅት በሃላፊነት ስሜት ባለመከራከሩ የእኛ መሆናቸዉ ላይ ጥያቄ የማይቀርብባቸዉ ቦታዎች ሁሉ ሳይቀሩ (ለምሳሌ ባድመ) ወደ ኤርትራ እንዲካለሉ ተደርገዋል፡፡ በዚህም ለሉአላዊነት የተከፈለዉን መስዋእትነት መና አስቀርቶታል፡፡

ሰባተኛ፤ ጦርነቱን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ማንኛዉንም መስዋእትነት ተከፍሎም ቢሆን  አሰብን ማስመለስ ሲገባዉ ኢህአዴግ አንዳችም ጥረት አላደረገም፡፡ የአሰብን ጉዳይ ገና በሪፌሬንደሙ ወቅት እንደቅድሜ ሁኔታም ሊያስቀምጥ ይችል ነበር፡፡ ከጦርነት በኋላም በድርድሩ ወቅትም የባህር በር ጉዳይን ለማስወን ሌላ ዕድል ተፈጥሮ እያለ ኢህአዴግ በአሰብ ጉዳይ ላይ አንዳችም የይገባኛል ጥያቄ አላነሳም የሚሉ ናቸዉ፡፡ በአጠቃለይ የባህር በር የማግኘት ዕድላችን በኢህአዴግ ፍላጎት ማጣት የተነሳ ለሶስት ጊዜ ያህል እድል አምልጦናል የሚል ወቃሳ ነዉ፡፡

4/ ኢህአዴግ የኤርትራን ህዘብ ነጻነት (ሪፈንደም) ማስቀረትም ማዘግየትም የሚችልበት ምክንያትም አቅምም አልነበረዉም

ቀደም ሲል ከተዘረዘሩት መካካል በኢህአዴግ ክስ ላይ ጥፋቱንና ፍርዱን ለማክበድ ያገለግሉ ይሆናል በሚል ግምት ካልሆነ በስተቀር ከተጠቀሱት መካካል አንዳንዶቹ ኢህአዴግን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያበቁ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም አንዳንዶቹ ኢህአዴግ ፍላጎት ቢኖረዉ እንኳን በወቅቱ ሊያስተካክላቸዉ የማይችላቸዉና ከአቅሙ በላይ የነበሩና በዚያን ወቅት ኢህአዴግ ራሱ የነበረበት ሁኔታም ቢሆን ያን ለማድረግ የማያስችለዉ ስለነበረ ነዉ፡፡

ሻዕቢያ የእስመራን ቤተመንግስት የተቆጣጠረዉ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ነዉ፡፡ በወቅቱ ሻዕቢያ ከኢህአዴግ የበለጠ ወታደራዊ ኃይል አለኝ በሚል የሚኩራራ ስለነበር ኢህአዴግ የሚለዉን ለመቀበል የሚገደደድበት ሁኔታም አልነበረም፡፡ እንደሚታወቀዉ የኤርትራ ሪፈረንዴም ከመከናወኑ በፊት ቢያንስ ለሁለት ዓመት ያህል ሻዕቢያ ኤርትራን ለማስተዳደር ችሎም ነበር፡፡ ለሁለት ዓመታት ነጻነቱን ሳያዉጅ የቆየዉም የኢህአዴግን ፈቃድ ለማግኘት ብሎ ሳይሆን ለሪፌሬንደሙ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ግዜ ስላስፈለገዉ በራሱ ምክንያት ነዉ፡፡

ሪፌረንደሙም የተደረገዉ በኢህአዴግ ፈቃድ ሳይሆን በራሱ በሻዕቢያና በኤርትራ ህዝብ ፍላጎት ነዉ፡፡ የኤርትራ ህዝብ ነጻነት በኢህአዴግ ፈቃድ የተገኘ አይደለም፡፡ በሻዕቢያና  በኤርትራ ህዝብ ትግል እንጂ፡፡ ስለዚህ ለኤርትራ ህዝብ ነጻነት ወይም ለኤርትራ መገንጠል ኢህአዴግ የሚመሰገንበትም የሚወቀስበትም ምክንያት አይኖርም፡፡

በኢህአዴግ በኩል ያደረገዉ ነገር ቢኖር ማድረግ የሚገባዉን ነዉ፡፡ ኢህአዴግ የሪፌሬንደሙ ሂደት ላይ አንዳችም እንቀፋት አለመፍጠሩና ከዚያ በኋላ እንደ ማንኛዉም አገር እዉቅና መስጠቱ ነዉ፡፡ እንደዚያ ባያደርግም ዞሮ ዞሮ የኤርትራ ለብቻዋ መሆን ሊያስቀር የሚችል ሁኔታም አይሆንም ነበር፡፡

ኢህአዴግ በወቅቱ በሪፌሬንደሙ ዉጤት ላይ ጫና በማድረግ ዉጤቱን ለኢትዮጵያ እንደሚጠቅም አድርጎ ለመቀየር የሚችልበት አንዳችም ምክንያት፤ አድልም ሆነ አቅም አልነበረዉም፡፡ በወቅቱ ኢህአዴግ ራሱን እንደ መንግስት ባላጠናከረበትና የዉስጥ የማራጋጋት ስራ  ሰርቶ ገና ባላጠናቀቀበትና በዉጭዉ ማህበረሰብም እንደ አገር ገና ጠንካራ የሚባል ዲፕሎማሲያዉ እዉቅናና ተቀባይነት ባላገኘበት ወቅት ላይ የኤርትራን ጉዳይ ለመቀየር የሚችልበት አንዳችም እድል ያልነበረዉ በመሆኑ ለምን እንዲህ አላደረገም ብሎ መዉቀስ ተገቢ አይሆንም፡፡

ኢህአአዴግ ስልጣን በያዘበት ወቅት በሀገሪቱ ዉስጥ የነበሩ በርካታ ታጣቂ ኃይሎች በአራቱም አቅጣጫ አገሪቱን ለመቦጫጨቅ በሚፋለሙበት ወቅት ኢህአደግ ሀገሪቱ እንዳትበታተን ጸጥታ የማስከበርና የማረጋጋት ስራ ከመስራት ዉጭ ሌላ ጦርነት ከሻዕቢያ ጋር መክፈት የሚችልበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ እንደዚያ ማድረግም አይገባዉም ነበር፡፡ የኤርትራ ነጻነት ጉዳይ በራሱ በኤርትራዉያን የዓመታት ትግል አስቀድሞ ያለቀለት ጉዳይ በመሆኑ ኢህአዴግን ባለቀ ጉዳይ ላይ መዉቀስ ትርጉም አይኖረዉም፡፡

ምናልባት ከቀረቡት ትችቶች መካካል ተገቢነት የሚኖረዉ ሪፌሬንደም ከመደረጉ በፊት የሁለቱን አገራት በጋራ በሚነካኩ ጉዳዮች ላይ በተለይ በድንበርና በወደብ ጉዳይ አንድ እልባት ላይ መደረስ ነበረበት የሚለዉ ነዉ፡፡ ኤርትራና ኢትዮጵያ ወደፊት እንደሁለት አገር የሚኖራቸዉ ወሰን የት ላይ መሆን አለበት የሚልና የባህር በር አጠቃቀምም ሆነ ባለቤትነትን በሚመለከት በመግባባት ላይ የጠመሰረተ ዉል መደርግ ነበረበት የሚለዉ ነዉ፡፡ ይህ ግን በምንም መንገድ ሪፈረንደሙን ለማዘግየት ወይንም እስከነአካቴዉ እንዳይደረግ ለማገድ  ያለመ መሆን እንደለለለበት ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፤ይሄን ማድረግ በጭራሽ አንችልም፡፡

ኢህአዴግ ኤርትራን በሚመለከት ከበፊት ጀምሮ ይዞ የቆየዉ አቋሙና በኋላም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የታየበት መለሳለስ አንዳንዶች እንደሚሉት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ይልቅ የሻዕቢያ ወዳጅነት ስለበለጠበት አይደለም፡፡ ይህን መሰሉን ትችት በበኩሌ አልቀበለዉም፡፡ ሻዕቢያ ለአጠቃላዩ ኢትዮጵያ  ህዝብ ብቻ ሳይሆን በተለይ ለኢህአዴግና እንደ ህዝብም በትግራይ ህዝብ ላይ ያለዉን ስር የሰደደ ጥላቻና ንቀት በሚገባ የሚታወቅ ነዉ፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ  የሚሆነዉ ያለ አንዳች ርህራሄ የአይደር ህጻናትን በክላስተር ቦንብ መጨፍጨፉ ነዉ፡፡

የሻዕቢያን ዝርፊያ ለማስቆም መንግስት ከመንቀሳቀሱ በፊት ቀድሞ እርምጃ መዉሰድ የጀመረዉ  በአድግራት አካባቢ ያለዉ የትግራይ ህዝብ እንደነበር ሻዕቢያ በሚገባ የሚያዉቀዉ ነዉ፡፡ በዚህ ምክንያትም ነዉ ሻዕቢያ የትግራይን ህዝብ ለመበቀል አስቦ አድግራት የሚገኘዉን መድሃኒት ፋብሪካ ለማጋዬት የሞከረዉ፡፡ የትግራይን ህዝብ ለመበቀል ስለፈለገም ነዉ ጨቅላ ህጻናትን በአይሮፕላን ቦንብ የጨፈጨፈዉ፡፡ በድንበር አካባቢ ያሉትን ነዋሪዎች በታንክ መጨፍለቁና ዛላምበሳን እንዳለ በዶዘር ማፈራረሱ  የሻዕቢያ የበቀል እርምጃ ዉጤት ነወ፡፡

ሻዕቢያ ባስነሳዉ ጦርነት ጦስም በአስርሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞቻችን አጥተናል፡፡ ከሁሉም በላይ በኤርትራ አመራሮች ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ ያዘነዉ አንድም ርህራሄ ሳያሳይ የአይደር ህጻናትን መጨፍጨፉና ለዚህ ወንጀሉም ለይስሙላ  አንኳን ይቅርታ አለመጠየቁ ነዉ፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ “ጦርነት ህግ የለዉም“ ብሎ ነዉ የተሳለቀብን፡፡

በትግሉ ዘመን ወቅትም ከ77ዓ/ም ረሃብና ከደርግ አይሮፕላን ድብደባ ለማምለጥ በነፍስ አድን ሽሽት ላይ የነበሩትን የትግራይን አርሶአደሮች ሻእቢያ በሚቆጣጠረዉ መሬት አልፈዉ ወደ ሱዳን እንዳይሸሹ በመከልከል ሻዕቢያ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወገኖቻችን እልቂት ምክንያት የሆነ ድርጅት ነዉ፡፡ በተጨማሪ ሻዕቢያ በደርግ ዉድቀት መጨረሻ አካባቢ  በአጋጣሚ በእጁ የገቡትን የቀድሞ ሰራዊት አባላት መካከል በሺዎች የሚቆጠሩትን በግፍ መጨፍጨፉን ኢህአዴግ መረጃዉ አይኖረዉም ብዬ አላስብም፡፡

ታዲያ በኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ እንደዚህ ዓይነት ግፍ ፈጽሞብን እያለ ኢህአዴግ ከኢትዮጵያ ጥቅም ይልቅ ለዚህ አረመኔ መንግስት- ለኤርትራ ይወግናል የሚለዉ ክስ ፍጹም መሰረተ ቢስ ነዉ፡፡ በርግጥ በግለሰብ ደረጃ ለኤርትራ በተለይም ለሻዕቢያ የተለየ ተቆርቋሪነት የሚያሳዩ አንዳንድ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በግልም ለኢሳይያስ ባላቸዉ ፍቅርና አድናቆትም በየመሸታ ቤቱ አዝማሪ አስቁመዉ ግጥም የሚያስገጥሙ ኢሳይያስ ሰምቶ እንዲያመሰግናቸዉ በራዲዮ ጭምር በድፍረት ሲናገሩ የነበሩ ሰዎች እንዳሉ እናዉቃለን፡፡

የዚህ ዓይነት ለሻእቢያ ልዩ ተቆርቋሪነት የሚያሳዩ ግለሰቦች ተራ ዜጎች  ቢሆኑ ኖሮ ብዙም ባላስከፋን ነበር፡፡ ነገር ግን  በኛም በእነሱም በኩል እኩል የሚታወቁና ለሀገሪቱ አመራር ቅርብ ከሆኑ ሰዎች መሆኑ እጅግ አሳዝኖናል፡፡ እነዚህ ጥቂት ግለሰቦች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለኤርትራ (ኢሳይያስ) ተቆርቋሪነታቸዉን በአደባባይ በመግለጽ የኢትዮጵያን ህዝብ ሆን ብለዉ ተስፋ ለማስቆረጥና ለማበሳጨት ሲሞክሩ እንደነበርም እናዉቃለን፡፡

ከጦርነቱ በፊት ብቻ ሳይሆን ሻእቢያ በእብሪት በቆሰቆሰዉ ጦርነት ወቅት ባደረሰዉ ኢሰብአዊ  ጭፍጨፋ ሰለባ የሆኑ የአይደር ህጻናት ደም ገና ሳይደርቅ ከጦርነቱ በኋላም እንደለመዱት በአደባባይ ለኤርትራ ጥብቅና ሲቆሙ የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦችን ድርጊት መቼም ቢሆን አንዘነጋዉም፡፡ ደግነቱ ግን የዚህ ዓይነት ባህሪይ ያላቸዉ ግለሰቦች እጅግ ጥቂት በመሆናቸዉ የነሱ ድርጊት በምንም ሁኔታ ቢሆን የገዢዉን ፓርቲ ወይም የመንግስትን አቋም የሚወክል ተደርጎ ሊቆጠር አይገባዉም፡፡

ለማንኛዉም ይህን ሃሳብ ለማጠቃለል ኢህአዴግም ሆነ እሱ የሚመራዉ መንግስት ለሻእቢያና ለኤርትራ ወግኖ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም አሳልፎ የሰጠበት አጋጣሚ አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የሚሰጥበት ምክንያት ስለማይኖር  በዚህ ጉዳይ  በጥርጣሬ ብቻ ተነሳስተን የምንሰነዝረዉ መሰረተቢስ ዉንጀላ አንዳችም ጠቀሜታ አይኖረዉም፡፡

5/ ማጠቃለያ

ኤርትራን በሚመለከት ለዚህ ሁሉ መጥፎ ዉጤት መፈጠር ባእዳን ካደረሱብን ሴራም ሆነ  ሻእቢያና ጀብሃ ካደረሱት በደል ባልተናነሰ እኛዉ ራሳችን በተለይም ከአጼ ምንሊክ ዘመን ጀምሮ  የነበሩ መሪዎቻችን ይብዛም ይነስም የየራሳቸዉን ስህተት በመፈጸም ለችግሩ መፈጠርና ለመፍትሄዉም አስቸጋሪ መሆን የየበኩላቸዉን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በተለይም የደርግ ስርአት ሲከተለዉ በነበረዉ የጦረኝኝነት አካሄድ ምክንያት የኤርትራን ጉዳይ የበለጠ በማወሳሰቡ የኤርትራ ህዝብ ከኢትዮጵያ ጋር በአንድነት የመቆየት ተስፋዉ እንዲጨልም በማድረግ ለኤርትራ መገንጠል ግንባር ቀደም ተጠያቂ ነዉ፡፡ ,

የኤርትራ ከኢትዮጵይ መነጠል ኢህአዴግ በተለየ የሚወቀስበትም ሆነ የሚወደስበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ለኤርትራ ህዝብ በሪፌረንደም ነጻነቱን ማግኘት የራሱ የኤርትራ ህዝብ ፊላጎት አንጂ የኢህአዴግ ልዩ ድጋፍ ወይም ግፊት ዉጤትም አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ለሀገሪቱ ይበጃል በሚል ገና ከመነሻዉ ፈዴራላዊ ስርአትን መምረጡም ሆነ አስፈላጊ ከሆነ አስከመገንጠል መብት የሚፈቅደዉ አንቀጽ 39 በህገመንግስታችን መካተቱ ሆን ተብሎ የኤርትራን መገንጠል ለማመቻቸት የተደረገ ሴራ ተደርጎ በአንዳንድ ተቺዎች የሚሰጠዉ አስተያየት የተዛባ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ፌዴራላዊ ስርአቱም ሆነ ህገመንግስቱ ከኤርትራ ህዝብ ነጻነትት ጋር አንዳችም ቁርኝት የለላቸዉና ስርአቱንም ሆነ ህገመንግስቱን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያበቃ አንዳችም መሰረት አለመኖሩ ነዉ፡፡

የኤርትራ ጉዳይ ገና በደርግ ግዜ ያባለቀለት ጉዳይ በመሆኑ ኢህአዴግን በአለቀለት ጉዳይ ላይ መተቸትም ሆነ ማመስገን ትርጉም አይኖረዉም፡፡ የኤርትራ ከኢትዮጵያ መነጠል ጉዳይ ከዚህ በኋላ መጸጸቱና መቆጨቱ ግዜዉ ያለፈበት ጉዳይ ነዉ፡፡ ኤርትራን በሚመለከት ከዚህ በኋላ ዋናዉ ተፈላጊ ጉዳይ ቢቻል መልካም ጎረቤታሞች ሆነን እንዴት በሰላም እንኑር ካልሆነም ደግሞ ኤርትራ በየግዜዉ ከምታደርስብን ትንኮሳ እንዴት እንድትተቃብ እናድርጋት የሚለዉ ነዉ፡፡ ከዚያ ዉጭ ባለፉ ጉዳዮች እንዲህ ቢሆን ኖሮ እያልን መቆጨቱ ስለማይጠቅመን ከዚያ ይልቅ ከዚህ በኋላ ማስተካከል በምንችለዉ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርገን ብንሰራ ነዉ የተሻለ ይመስለኛል፡፡

*********************

(የዚህን ፅሁፍ ቀጣይ ክፍሎች በዚህ ሊንክ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኮ/ል አስጨናቂ ገ/ፃድቅ ማግኘት ይችላሉ)

*የኮ/ል አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሌሎች ጽሑፎች ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፡፡ 

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories