(ኤቢሳ ከጨፌ ዶንሳ)

ውሃ ሽቅብ አይፈስም ነው ተረቱ፡፡ ሀቅ ነው ውሃ ሽቅብ አይፈስም፡፡ ታዲያ ተፈጥሮ ብትዛባና ቢገደድ አይደለም ሽቅብ መፍሰስ ተራራም አይወጣ ብላችሁ? አሳምሮ ነዋ፡፡ ይኸው እየጠመዘዝነው ስንቱን ዳገት እናስገፋው፤ ስንቱን ፎቅ ሽቅብ እናንደረድረው የለ? እንግዴህ ዛሬ ቀዳሚዎቹን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቁንጩ ኦህዴድ አባቶቼን ለመምከር መነሳቴ እንደ ውሃው ሊሆንብኝ ሆነ፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ይህን ምሳሌ ማምጣቴ ያለ ነገርም አይደል፡፡

በሀገራችን ህዝቦች ፈቃዳቸው የሚሞላበትን ስርዓት ሲናፍቁ፤ ያጎደለባቸውን በአንድም በሌላም መልኩ ሲታገሉት፤ ነፍጥም ነፍስም ሲያነሱበት ዘመናት እንዳስቆጠሩ ታሪክ ምሰክራችን ነው፡፡ ነገስታቱ በዘመናቸው ያደረና የገበረላቸውን ሲያስደስቱ ሌላውን ሲያግዙና ሲያፈናቅሉ፤ ወገን “ያደገደገልን” ነው ብለው ሲሉ፤ ተራውን የኔ ቢጤ ዜጋ ቁም ስቅሉን ያበሉት ነበርና ቢታገላቸው አይገርምም፡፡ ትግሉ እያበበና እየነበበ፤ ከመደራጀት ወደህዝባዊነት ከመሸጋገሩም በላይ ድሉም የራሱ ህዝቡ አኩሪ መስዋእትነት የተከፈለበት ድል ሆኖ መመዝገብ ችሏል፡፡

እነሆ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ህዝቦች የየራሳቸውን ማንነት ባከበረና እውቅና በሰጠ ስርዓት ውስጥ የጋራ ቤታቸውን ለመገንባት ምህላ የገቡትም ለዚህ ነው፡፡ የዚህ መስመር ጠንሳሾች ታዲያ ያኔ ሲያግባቡን መስመራችን አልፋና ኦሜጋው የህዝብ ተጠቃሚነት ነው ብለውን በደስታ ተቀብለናቸው ነበር፡፡ የህገ መንግስቱ ዓላማ ህዝቦች ባላቸው እኩል የመልማት እድል ተጠቅመው ባፈሰሱት ጉልበት፤ እውቀትና ሀብት መጠን ተጠቃሚ የሚሆኑበትና አንድ የጋራ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ የሚፈጥሩበት ነው ባሉን ጊዜም በእልልታ ፈረምንበት፡፡

ፌዴራል ስርዓቱ የሁሉም ህዝቦች መብት ሳይሸራረፍ የሚከበርበት ከብሔራዊ ማንነት ወደ ሀገራዊ ማንነት የሚያድግ እውነተኛ ተፈጥሮን የተከተለ ሰርዓት ነው፤ እንዱን አግሎ ሌላውን በእቅፉ ሊያኖር የሚያስብ ስርዓት በሀገራችን ቦታ የለውም ብለው ባስተማሩን ጊዜ ህብረ ብሔራዊ ዜማዎቻችንን አዚመን ቤት ለእንቦሳ አልናቸው፡፡ እንዲያውም እነዚህ ልጆች ለመብታችሁ መከበር ልንሞት ወደ ጫካ ወጣን ባሉን ጊዜ የምናውቃቸውና መርቀን የሸኘናቸው የኛው ልጆች ናቸው እንዴ? ብለንም ሳንጠይቅ አልቀረንም፡፡

እንግዲህ ሁሉም አልፎ የነፃነታችን ጀንበር ከባተች ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ቆመን ራሳችንን እንድናይ ህዝባዊ ማእበል እስኪውጠን ድረስ ምንም ያልሆነ ይመስለን የነበርን ብዙዎች ነን፡፡ በማእበሉ ማግስት ግን መርከቢቱ መርገፍገፏ አይሎ ድብቅ እውነቶች እርቃናቸውን አደባባይ ተሰጥተው ሁሉም ጉድ ይል ጀመር፡፡ አመራሩ ራሱን ረገም፤ ምሁሩ ድርሻዬን አልተወጣሁም ሲል ራሱን ኮነነ፤ ህዝብ በዝምታ ባያችሁ ብታገሳችሁ በገዛ እጄ ነውና አይለመደኝም ሲል ዛተ፤ ብቻ ሁሉም ድርሻውን ወሰደና የችግሩ ምንጭ አመራሩ፤ የችግሩ መልክ ኪራይ ሰብሳቢነትና ከህዝብ ወገንተኛነት ፈቀቅ ማለት፤ መፍትሔውም ጥልቅ ተሃድሶ እንደሆነ ያሰመረበት ሁኔታ ተፈጠረና ሁላችንም አብረን ገባንበት፡፡

ከዚህ በኋላ ምልከታዬን ወደ ኦሮሚያ ላድርግና ጥልቅ ተሃድሶው በርግጥም በአካሄድና በተወሰደው እርምጃ ለሌሎች ክልሎችም ሆነ እህት ፓርቲዎች ምሳሌ መሆን የቻለ ነበር፡፡ አመራሩ ከምንም ነገር በፊት የህዝብ ወገንተኛነቱን መልቀቄ ትልቁ ኃጢያት ነው ሲል አመነ፡፡ ህዝቡም አስጠቃኸኝ ሲል በቀጥታ ኮነነውና ተግባቡ፡፡ ይኸው ሂደቱ ዛሬ የፈጠረውን አዲስ ንቅናቄ በክልላችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወልዶና አሳድጎ እያሳየን ነው፡፡

ንቅናቄውም በሁሉም ዘንድ መነቃቃትም መነቃነቅም ፈጥሮ ከፊሉ በጥርጥር፤ የተቀረው በፍርሃት፤ አንዳንዱም በእልህ አታሞ ሲደልቅ እያየን ቢሆንም ከሁሉም በላይ አግራሞት የጫረብኝ እንደ ቤተመዘክር ከምንመለከታቸው ቀደምት የትግሉ አውራዎች አንዳንዶቹ ኦህዴድና የክልሉ መንግስት በስመ ጥልቅ ተሀድሶ እኛ ከተዋደቅንለት ዓላማና መስመር እየወጡ ነው
ብለው መኮነን መጀመራቸውን በገዛ ጆሮዬ ስሰማ የመደንዘዝ ያህል ይህን ፅሁፍ እስካዘጋጅ ትከሻዬን ጨምዶኝ እንደነበር አልደብቃችሁም፡፡

አብዛኞቹን በቅርበት ሳውቃቸው ለተከታታይ ትውልድ ተመሳሳይ አቋም መያዝ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ህዝብ የሚጠቀምበትን ነገር በመፍጠር ታሪክ ሲሰሩ የኖሩና /ስማቸው ይቆየኝ/ ያሉ እንዳሉ ሁሉ እጃቸው እንዳሻው በጌቶቻቸው የሚጠመዘዙቱ ያሳዝኑኛል፡፡ ከህዝብ ጥቅም መሀል ቆሜ ሳያቸው ደግሞ ደሜን ያፈሉታል፡፡ አንዳንዶቹም ለራሳቸውም ለጌቶቻቸውም ያልሆኑ፤ ልጆቻቸውን ደህና ትምህርት ቤት እንኳን ማስተማር የማይችሉ ከእጃቸው ንፁህ ከልባቸው ግን ሌላ ጌታ ያላቸው መሆናቸውን ስመለከት ፍርሀታቸው ውጥንቅጡ የሚፈታ አልመስልህ ይለኛል፡፡

አንዳንዶቹ ቱባዎች ደግሞ ልክ ድሮ አስተማሪ እያለን እነ ወ/ሮ አያልነሽ ቤት ፈርመን ሽሮና ቀይ ወጥ እንደምን በላው እዛ መሃል ሀገር ደረቱን ከገለጠው ሆቴል ፈርመው ይበሉና እነ….እንቶኔ የሚከፍሉላቸውም እንዳሉ በቅርበት ስለምታዘብ የሆዳቸው ከሃገር መስፋት እርግማን ነው ያሰኘኛል፡፡ የኚህን ሰዎቼን ታሪክ በሌላ ክፍል ልመለስበትና በጀመርነው ክልላዊ አብዮት የቱጋ ቁንጮዎቹ የታገሉለት መስመር እንደተሸረፈ ላጠይቅ፡፡ አንድም አንዳችን እንድንማር፤ አንድም ህዝቡ ልካችንን አውቆ አሰላለፉን እንዲያሳምር ይረዳልና፡፡ ለነገሩ ክብር ይግባውና ህዝባችን ሰልፉን ካሳመረ ውሎ አደረ፡፡ ጥቅሙን ከሚያስጠብቁለት ወዲያ ላሳር ብሏል፡፡

1/ የኦህዴድ ኢህአዴግ አልፋና ኦሜጋ የህዝቦች ተጠቃሚነት ነው

ይህ መርህ በ1980ዎቹ የድርጅቱን መርሀግብር ስማር ቀልቤን ከሳቡት ጉዳዮች አንዱ ነበር፡፡ ያኔ ባልሳሳት አቶ ዓለማየሁ አቶምሳም አቶ ዘላለምም የሁለት ዓለም ሳይሆን የአንድ ዓላማ ጠበቆች ሆነው ደንቢዶሎ ነበሩ /ነገርን ነገር ቢያነሳው ብዬ እንጂ የሰው ስም……/፡፡ እንግዲህ የዛሬው ኦህዴድ ይህንን ዘላላማዊ ተግባር አሁን መተግበር አለብኝ ማለቱ ዘገየህ ቢያሰኘው እንጂ ሌላ አያስብለውም፡፡ የህዝቦች ተጠቃሚነት ሲባልም ሁሉም ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት በተረጋገጠላቸው ልክና ድንበር መርሁን ያስጠብቃሉ ማለት ነው፡፡ የዚህ ድምር የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ህዝቦች
ጥቅም ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ማስጠበቁን ይናገራል የሚል አንድምታ አለው፡፡

ታዲያ ኦህዴድ በኦሮሚያ ህዝብ ጥቅም የማስጠበቅ አጀንዳ እንዴት ሊታማ ይችል ይሆን? አልፋና ኦሜጋው የሚጀምርበት የቀን ቀመር ይነገረንማ! ካልሆነ እንደ ውሃ ሽቅብ ፈሳችሁ አጓጉል ሆናችሁ አትበሉንና የትግል ቁንጮዎቻችን የተዋደቃችሁለትን ዓላማ በተግባር ለመቁጠር ከሁለት አስርት በኋላ ቁርጠኛ አቋም የወሰደው አመራር እውነተኛው ኢህዴድ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልምና ወደ ልባችሁ ተመለሱ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የምትሰጉት ለውጭ ሳይሆን ለውስጥ ጠላት መሆኑን የነገራችሁን እናንተው አይደላችሁ እንዴ?

2/ አንድ የጋራ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ በመፍጠር አዲሲቷን ኢትዮጵያ በማይናወጥ መሰረት ላይ ማቆም

ይህኛው መርህም ከብዙ ሀገራት የፖለቲካል ኢኮኖሚ መርህ በተሻለ መስህብ ያለው ነው፡፡ ብዝሃነትን ያከበረ፤ አንድነትን ሊያጠናክር ያለመ፤ የኢኮኖሚ መነቃቃት በሁሉም ህዝቦች ዘንድ ጣሪያ ነክቶ ዓለማቀፋዊ ውድድርን እንዲቀላቀልና ብልፅግናን ራዕዩ ያደረገ ነው፡፡ ለኔ የገባኝ ነገር እንደዚህ ከሆነና በዚህም ከተማመንን ሁሉም ህዝቦች እኩል የመልማት እድል በየሜዳቸው የተሰጣቸው ይህንን ራዕይ ለማሳካት፤ ፈርጣማ ክንዶች ሁሉም ጋር ተፈጥረው በወንድማማችነትና በአንድነት ሲለሙና ሲጠቃቀሙ ሀገር በዓለም መድረክ ትገኛለች የሚል ህልም ያዘለ ነው፡፡

እንግዲህ በኦሮሚያ አስመጪና ላኪው፤ ታላላቅ የኢንቨስትመንት ተቋም ገንቢው፤ ባለፎቁና ባለ ትራከሩ ለነእንቶኔ ወገን ብቻ ሆነ፤ ደላላና ከጀርባው ቱባ ቱባ የሁላችንም ባለስልጣኖች ማሩን እየላሱ ወንዙን ካርታ አስወጥተው የሚሸጡለት ከሆነ ብቻ ነው አንድ የጋራ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ የሚፈጠረው? እሱም በጀ በኦሮሚያ የሚኖረው ዜጋ ዘበኛ መሆን እያቃተው፤ ከወንዝ አሸዋ ለነእንቶኔ ለመዛቅ የአዲሳባ ካርታ ዋስትና ማስያዣ እየተጠየቀ፤ በተፈናቀለበት ቀዬ የኔ ቢጤና ምግባረ ብልሹ ሆኖ ሲንቀዋለል፤ አባቶቹ ኢረቻን ካከበሩበት አድባር ተገፍቶ ወደዳር እየወጣና ማንነቱ ከእንብርቱ እየተገፈፈ ነው ጠንካራ የጋራ ኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ በሀገራችን የሚፈጠረው? እንዲህም አድርጎ የጋራ ማህበረሰብ፡፡ ትናንት ወደ ትግል ስትቀላቅሉን ያላችሁንን አስታውስና አሁንም ወደልባችሁ ተመለሱልንማ!!

3/ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት የመደመር ራዕይ

በዓለም መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ በቅርቡ ለመደመር ያሰብነው የኦሮሚያን ህዝብ ጥለን ነው እንዴ? ማለቴ ትኩረቴ ኦሮሚያ ላይ ስለሆነ እንጂ ቤኒሻንጉል፤ ጋምቤላ፤ ደቡብ፤ አማራ፤ ትግራይ…. ማላቴ እንደሆነ ይታሰብልኝማ፡፡ ሁሉንም ህዝቦች መቀላቀል ያለብን ወደንም አይደለም፡፡ የፌዴራል ስርዓቱ ህግጋት ከዚህ ማእቀፍ ውጪ ሊያሳስቡን አይቻላቸውምና፡፡ እንደዚህ ከሆነ ታዲያ ሁሉም ክልሎች ለመልማት ባላቸው እድል የአቅማቸውን ያህል የመጠቀም መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በአፈጣጠር አጋጣሚ ሰፊ ህዝብና ትልቅ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያለው ህዝብን የጠንካራ ኢኮኖሚ ባለቤት ማድረግ ካልቻልን እንዴት ከነዚህ ሀገራት ተርታ መሰለፍ ይቻል ይሆን?

በሁሉም አስተሳሰቦች ውስጥ ሁሉም ህዝቦች በየራሳቸው ቀዬ ይህንን መብት በላቀ ደረጃ የተገብሩት ዘንድ ግድ እንደሚልም ታሳቢ ይደረግልኝና ሂሳቡን እንስራው፡፡ እንግዲህ ቱባዎቻችን የቱጋ ነው የታገላችሁለት መስመር የተሸረፈው በሞቴ? ይልቅ ወደ ልባችሁና ወደ ህዝባችሁ ልብ ተመለሱና አዲሱን ታሪክ አብረን እንስራ ስል ሽቅብ ተናገርኳችሁ!!

***********

Guest Author

more recommended stories