መሪዎቻችን እልህ እየገቡ ወይስ ግራ እየተጋቡ?

(ሰለሞን ወልደገሪማ)

የአንድ ህዝብ ህልውና የሚረጋገጠው ራሱ ህዝቡ በሚያደርገው ያልተቋረጠ ትግል፣ በሚያነሳቸው አንኳር የመብት ጥያቄዎች እና ይህን ተከትሎ በሚፈጠር የእርካታ ደረጃ ነው፡፡ መሪዎች ከራሱ በታች እንደሆኑ አውቆ የህዝቡ ህልውና በፖለቲካ ሹማምንት ይሁንታ ሳይሆን በራሱ ውሳኔ የሚረጋገጥ የህልውና ቀጣይነት እንደሚረጋገጥ ማስመር መቻል አለበት፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ አሁን በኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በትግራይ እያየነው ያለ ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነው፡፡

ማመን ያቃተኝ ግን እየሆነ ያለው ተስፋ አስቆራጭ ነገር በትግራይ ህዝብ ላይ የሚሰነዘረው የህወሓት ንቀት ነው፡፡እኔ የምለው ወገኔ እውነተም እነዚህ መሪዎቻችን ግን እልህ እየገቡ ወይስ ግራ እየተጋቡ ነው? አካሄዱ ጤነኛ አይመስለኝም፡፡

በበኩሌ መፍትሄ ለማግኘት አገር መጋየት፤ መረበሽ አለበት ብየ አላስብም፡፡ እየሆነ ያለው ግን ይህን የሚጋብዝ ነው፤ ፈንጅ አምካኝ የሆኑት ገዢዎቻችን ካለፈው የኦሮሞ አመፅ እንኳን መማር የቻሉ አይመስለኝም፡፡ በተለይ የህወሓት መሪዎች ጥልቅ ተሃድሶ እንዳሉት ሁሉ ሶስተኛ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሊያዉጅለት የተዘጋጁ ነው የሚመስሉት፤ ለዚህም ነው ህዝቡን በግድ እንዲያምፅ እየገፋፉት ያሉት፡፡

“አንተ እኔኮ ታላቅ ወንድምህ ነኝ” በሚል ተልካሻ ምክንያት በአስተሳሰብ ከኔ የተሻለ ታናሽ ወንድሜ ለመጨቆን ምንም ጥያቄ እንዳያነሳ የምጠቀምባት የማታለያ ወሬ ህወሓት የትግራ ህዝብ ለመደለል አልያም አፍን ለመዝጋት ከሚጠቀምበት መንገድ ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡ አሁን ግን ግዜ አልፎበታል።

ባለፈው በኦሮምያ ክልል የተፈጠረው ብጥብጥና ሁከት መነሻው የአ/አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ማስፋፍያ ቢባልም ቅሉ ዉስጠ ወይራው ግን አጠቃላይ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄ ነበር፡፡ አሁንም እየሆነ ያለው በትግራይ ክልል ውስጥ የባቡር መሰረዝ ጥያቄ መነሻ እንጂ ችግሩ ከዚህም በላይ ነው፡፡ ያዘነነና ያኮረፈ ህዝብ አለ፤ ሰሚ አጣ፤ “እኔ ነኝ የማውቅልህ” የሚል በዛበት እንጂ ይህ አስተዋይና ጀግና ህዝብ በተለያየ መድረክ በሰለጠነ መንገድ ቁጣውን ገልፆታል፡፡

የስራ አጥ ወጣት ብዛት ጀበና ቡና ለመጠጣት በሚል የማምለጫ ወይ መደበቂያ ምክንያት በየሰፈሩ ለስዓታት ተቀምጦ የሚውል የለውጥ ሃይል ብዛት፥ የግብር አሰባሰብ ስርዓት፤ የተለየ ሃጥያት ወይም ስርቆት የፈፀመ ይመስል ምንም ሳተቀርቡለት የምትቀሙት ምስኪን ነጋዴ፤ ይህ አልበቃ ብሏችሁ “አንደኛ ግብር ሰብሳቢ ክልል በኢትዮጵያ እኛ ነን” እያላችሁ የበለጠ ደም የመምጠጥ ዕቅድ እያወጣችሁ ነጋዴውን አስደንግጣችሁ ንግዱ ቤቱ ዘግቶ ወደ ሌሎች ክልል እንዲሰደድ ታስገድዳላችሁ፡፡

እንደ አሁን ሳትበላሹ ድሮማ የምናቃት ትግራይ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና (ቃላሚኖን ጨምሮ) የምትልከው የተማሪ ብዛት ከኢትዮጵያ አንደኛ ነበረች፡፡ አሁን ግን እድሜ አይስጣቹህና መጨረሻ ሆነናል፡፡ ይህ ማለት በትምህርት ዘርፍም ከፍተኛ ችግር እንዳለ ለመጠቆም ያህል ነው፡፡

አበሳጭታችሁ የመለሳችሁት የትግራይ ተወላጅ ባለሃብት፤ የሁለት አገር ዜጎች እስኪመስሉ ድረስ በተለይ በድንበር አከባቢ ያሉ ገበሬዎቻችን በማዳበሪያ እጦትና ዋጋ የሚቃሰቃዩት፤ ዋስትና ያጣውና እናንተን ያገኙ እየመሰላቸው የትግራይ ተወላጅ በየክልሉ የሚጨፈጨፈው ዜጋ፤ በመልካም አስተዳደር እጦት የታፈነ ህዝብ፤ የንፁህ ወሃ እጦት… የክልሉን መስተዳድር ፕሬዝደንት ህዝቡ አንፈልገዉም እያለ በንቀት አናታችን ላይ ጫናቹሁብን… አረ ስንቱ ጃል፡፡ ለማስታወስና ለማስጠንቀቅ ካልሆነ በስቀር ሳታውቁት ቀርታችሁ ኣይደለም : :

ህወሓት እኮ ፓርቲ እንጂ ደማችን አይደለቸም! በማንኛውም ግዜ መጥፎ ሁና ካገኘናት እንደ ቀዳዳ ካልሲ ኣውልቀን እንደምንጥላት መረዳት የተሳናቸው ገዚዎቻችን “ህወሓት ማለት የትግራይ ህዝብ፤ የትግራይ ህዝብ ማለት ህወሓት ማለት ነው” ብለው ሲደልሉን ቆይቶዋል: :

ህዝቡ ዝም ስላለ አቅም የሌለው የመሰለው አካል ካለ ተሳስተዋል፤ ጋዜጠኛ ነጋ “የትግራይ ህዝብ ከተነሳ አያስተርፋቸውም” እንዳለው በዚህ ሰዓት እየጋለ ያለው ወጣት የት እንደሚሄድ ግልፅ መሆን አለበት።

በቅርብ ግዝያቶች የታዘብነው አንድ ነገር ደግሞ የትግራይ መንግስት ባለስልጣናት እና አጫፋሪዎቻቸው ድክመታቸዉን ለመሸፈንና ራሳቸዉን ከሃጥያት ነፃ ለማድረግ ጣታቸዉን ወደ ፌዴራል መንግስት እየጠቆሙ ነው። ትግራይን እሚያስተዳድረው ህወሓት እንጂ የፌዴራል መንግስት አይደለም፤ ስለዚህም ለዉሃ ጥማታችን፣ ለፍትሕ እጦታችን፣ ለዴሞክራስያችን መቐጨጭ፣ ለስራ አጥነታችን፣ ለገበሬዎቻችን ግፍና በደል፣ ለትምህርታችን መዝቀጥ፣ ለተስፋችን መጨለም ተጠያቂው የክልሉ መንግስት መሆኑ መዘንጋት የለብንም። ባቡር እነዚህ ድምር ችግሮቻችን ፈንድቶ እንዲወጣ ምክንያት ሆነ እንጂ ጥያቅያችን ከባቡር በላይ ነው። የትግራይ ባቡር እንደ ኦሮምያው ማስተር ፕላን፣ የትግራይ ወጣት እንደ ኦሮምያ ወጣት የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም። ይህ ለሁሉም ግልፅ መሆን አለበት።

*******

Guest Author

more recommended stories