ሕገ-መንግስቱን በሚጥስ አዋጅ የኦሮሚያን “ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም” ማስከበር አይቻልም

ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ዙሪያ የተለያዩ ፅሁፎችን አውጥቼያለሁ። ማስተር ፕላን፡ የችግሩ መነሻ እና መድረሻ” በሚለው ፅሁፍ የአዲስ አበባ ከተማ ገና ከአመሰራረቷ ጀምሮ የኦሮሞን ሕዝብ መብትና ተጠቃሚነት ያላረጋገጠች መሆኗንና ማስተር ፕላኑ ደግሞ ይሄን የሚያስቀጥል ስለመሆኑ፣ “የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ማቋረጥ ስህተትን እንደ መሳሳት ነው” በሚለው ፅሁፍ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ ለተከሰተው ችግር ዘላቂ መፍትሄ መስጠት የሚቻለው የችግሩን ዋና መንስዔ መለየት ሲቻል እንደሆነ፣ በመቀጠል “ኦሮሚያን ለአመፅ፣ አዲስ አበባን ለቆሻሻ የዳረገች አንቀፅ” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅሁፍ ደግሞ የኦሮሚያ ሕዝብ እና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መብትና ተጠቃሚነት በዘላቂነት ሊረጋገጥ የሚችለው የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) ተግባራዊ ሲደረግ እንደሆነ በዝርዝር ገልጬያለሁ።

ከላይ በተጠቀሱት ሦስት ፅሁፎች በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል መካከል ያለው ግንኙነት ከጭፍን ደጋፍና ተቃውሞ በፀዳ መልኩ እንዲመራ እና የክልሉ ሕዝብና የከተማዋ ነዋሪዎች መብትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ፣ ለዚህ ደግሞ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) አስፈላጊው የሕግ አዋጅ እና የአፈፃፀም መመሪያ መዘጋጀት አለበት በሚል መርህ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ስለዚህ፣ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም የሚያስከበር አዋጅ መውጣት አለበት እያልኩ በፅሁፎቼ ተከራክሬያለሁ። በጉጉት ስጠብቀው የነበረው ረቂቅ አዋጅ ግን እንዲህ ቅስሜን ይሰብረዋል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር።

በመሰረቱ፣ በሀገር ወይም ክልል ደረጃ ሰላም፥ ልማትና ዴሞክራሲ ለማረጋገጥ በሚል የሚወጡ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች በምንም መልኩ ቢሆን ሕገ-መንግስታዊ መርሆችንና ድንጋጌዎችን መፃረር የለባቸውም። ሕገ-መንግስቱ በማንኛውም አካል ቢሆን ለሚወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች እንደ መነሻ ሆኖ ያገለግላል የሚል እምነት አለኝ። “ሕገ-መንግስቱ በራሱ ክፍተቶች ስላሉበት አንቀበለውም” የሚሉ ወገኖች መኖራቸው እርግጥ ነው። ነገር ግን፣ “በሕገ-መንግስቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ራሱ ሕገ-መንግስቱ ላይ በተደነገገው አግባብ መሰረት መቀየርና ማሻሻል ይቻላል” የሚል ፅኑ አቋም አለኝ።

ይህ አቋም “ሕገ-መንግስቱ ፍፁም ነው” ከሚል ጭፍን አመለካከት የመነጨ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ሕገ-መንግስት ለዜጎች መብት እና ለመንግስት ስልጣን ዋስትና ነው። ስለዚህ፣ የሕገ-መንግስቱ መርሆችና ድንጋጌዎች የሚፃረሩ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን ማውጣት በዜጎች ላይ ከሚፈፀመው የመብት ጥሰት በተጨማሪ የሕግ አውጪዎችን፣ አስፈፃሚዎች እና ተርጓሚዎችን (ሦስቱንም የመንግስት አካላት) ሥራና ተግባር ተቀባይነት ያሳጣዋል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ሕገ-መንግስቱን የሚፃረር ማንኛውም ተግባር ከመሰረታዊ የመብት መርህ አንፃር ተቀባይነት አይኖረውም።

በመሰረታዊ የመብት መርህ (universal principle of right) መሰረት፣ ማንኛውም ዓይነት ተግባር በራሱ ወይም በዓላማው በሁሉም የእንቅስቃሴው ተሳታፊዎች ነፃነት ላይ ተፅዕኖ እስካልፈጠረ ድረስ ትክክለኛ ተግባር ወይም “መብት” ተደርጎ ይወሰዳል። ስለዚህ፣ የእኔ “መብት” የሌሎችን ሰዎች ነፃነት በማይገድብ መልኩ መንቀሳቀስ መቻል ነው። በመሆኑም፣ የእኔን ነፃነት ማክበር ለሌሎች ሰዎች ግዴታ፣ የሌሎችን ሰዎች መብት ማክበር የእኔ ግዴታ ነው። በተመሣሣይ፣ የኦሮሚያን መንግስትና ሕዝብ ሕገ-መንግስታዊ መብት ለአዲስ አበባ መስተዳደርና ነዋሪዎች ግዴታ ነው፣ የከተማ መስተዳሩንና የነዋሪዎቹ ሕገ-መንግስታዊ መብት ማክበር ደግሞ ለኦሮሚያ መንግስትና ሕዝብ ግዴታ ነው።

በአጠቃላይ፣ በመሰረታዊ የመብት መርህ እኛ ለሌሎች ያለብን ግዴታ ሳንወጣ ወይም የሌሎችን መብት ሳናከብር ሌሎች የእኛን መብት እንዲያከብሩ ወይም ለእኛ ያለባቸውን ግዴታ እንዲወጡ መጠየቅ አንችልም። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የአዲስ አበባ መስተዳደር እና የነዋሪዎቿን ሕገ-መንግስታዊ መብት በሚጥስ መልኩ የክልሉን ልዩ ጥቅም ማስከበር አይችልም። ይህን መርህ የሚፃረር ማንኛውም ሥራና ተግባር በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም። እንዲህ ያለ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ ወይም እቅድ ውሎ-አድሮ ለሕዝባዊ አመፅና አለመረጋጋት መንስዔ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

የኦሮሚያ መንግስትና ሕዝብን መብትና ተጠቃሚነት ለማስከበር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ በሌለበት ተግባራዊ ሊያደርገው የነበረው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። በአዲስ አበባ እና በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች መካከል የተቀናጀ የመሰረተ ልማትና የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ለመዘርጋት በሚል የፀደቀው የአዲስ አባባ ማስተር ፕላን ከክልሉና ከተማዋ አልፎ በሀገሪቱ ሰላም፥ ልማትና ዴሞክራሲ ላይ ትልቅ ጠባሳ ፈጥሯል። ለዚህ መነሻ ምክንያቱ ማስተር ፕላኑ በተለይ ከመሬት ሀብት አጠቃቀምና ከመሰረተ ልማት ግንባታ ጋር ተያይዞ የኦሮሚያን መንግስትና ሕዝብ መብትና ተጠቃሚነት የማያረጋግጥ ስለሆነ ነው። በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) መሰረት የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም ለማስከበር የወጣው አዋጅ የአዲስ አበባን መስተዳደርና ነዋሪ መብትና ተጠቃሚነት የሚፃረር ከሆነ ተመሣሣይ እጣ-ፋንታ ይገጥመዋል።

በእርግጥ ይህ ፅሁፍ የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። ሆኖም ግን፣ እስካሁን ድረስ ትኩረት ያደረግነው በሕገ-መንግስቱ መርሆችና ድንጋጌዎች ላይ ነው። ለዚህ ዋና ምክንያት ረቂቅ አዋጁ የክልሉን ሕገ-መንግስታዊ መብት ለማስከበር በሚል ሰበብ የአዲስ አበባ ከተማ መሰተዳደርን ራስን በራስ የማስተዳደር ስልጣን እና የነዋሪዎች ሕገ-መንግስታዊ መብት የሚጥስ፣ የኦሮሚያን ክልል ሕዝብና መንግስት መብትና ተጠቃሚነት አያረጋግጥም። በአጠቃላይ፣ የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣው ረቂቅ አዋጅ ከሕገ-መንግስቱ አንፃር ሦስት መሰረታዊ ስህተቶች አንዳሉበት አንደሚከተለው በዝርዝር ለማሳየት እሞክራለሁ፡-

1ኛ፡- በኦሮሚያ ክልል “መሀል” ወይስ “አካል”?

በረቂቅ አዋጁ ውስጥ የሚስተዋሉት ክፍተቶች ከሞላ-ጎደል ሁሉም ማለት ይቻላል በዚህ የተሳሳተ እሳቤ ወይም ግንዛቤ ምክንያት የተፈጠሩ ናቸው። ጉዳዩን በዝርዝር ለማየት እንዲያስችለን በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 5 ላይ ያለውን ድንጋጌ እንመልከት፡-

የኦሮሚያ ክልል፤ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም ተፈጥሯዊ ሀብር አጠቃቀምና የመሳሰሉት ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል “መሀል የሚገኝ በመሆኑ” የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል።”  የኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት፥ ምዕራፍ አራት፥ አንቀፅ 49

የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣው ረቂቅ አዋጅ ሕገ-መንግስቱን መነሻ አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ለማሳየት አንቀፅ 49(5) በመግቢያው ላይ እንደሚከተለው አጣሞ አቅርቦታል፡-

“የኢትዮጲያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ሕገ-መንግስት በአንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ (5) የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም ተፈጥሯዊ ሀብር አጠቃቀምና የመሳሰሉት ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል “አካል በመሆኑ” የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለውን ልዩ ጥቅም እንዲጠበቅለት በመደንገጉ፤…”  ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል።”  የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁጥር…..2009 (ረቂቅ አዋጅ) ገፅ 1

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) “አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ” የሚለው ሐረግ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ “አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል አካል በመሆኑ” በሚለው ተቀይሯል። በረቂቅ አዋጁ ውስጥ የሚስተዋሉት ክፍተቶች ሕገ-መንግስቱ “መሀል” ያለውን “አካል” ብሎ ከመውሰድ የመጡ ናቸው። ምክንያቱም፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 2ና 5 መሰረት፣ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል “መሀል የሚገኝና ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን” ያለው የከተማ መስተዳደር ነው። ረቂቅ አዋጁ ግን “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል አካል ስለሆነ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን የለውም” በሚል እሳቤ የተዘጋጀ ነው።

አዲስ አበባ “በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ” የሚለው ሐረግ በአዋጁ ውስጥ “በኦሮሚያ ክልል አካል በመሆኑ” ተብሎ የተጠቀሰው በቃላት አጠቃቀም ምክንያት የተፈጠረ ስህተት ሊባል ይችላል። ነገር ግን፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 106 መሰረት የሕገ-መንግስቱ የአማርኛ ቅጂ የመጨረሻ ሕጋዊ እውቅና ያለው ሰነድ ስለሆነ የረቂቅ አዋጁን አገላለፅ ከስህተት አያድነውም። በአጠቃላይ፣ የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣው ረቂቅ አዋጅ በተሳሳተ የሕገ-መንግስት ትርጓሜ ወይም እሳቤ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም።

2ኛ የኦሮሚያ “ልዩ ጥቅም” ወይስ “ልዩ መብት”?

በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 5 ላይ ለኦሮሚያ ክልል የተደነገገውን “ልዩ ጥቅም” እንመልከት፡-

“የኦሮሚያ ክልል፤ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም ተፈጥሯዊ ሀብር አጠቃቀምና የመሳሰሉት ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል “መሀል የሚገኝ በመሆኑ” የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል” የኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት፥ ምዕራፍ አራት፥ አንቀፅ 49 (5) 

የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 5 በረቂቅ አዋጁ ውስጥ የተሰጠውን ትርጉም እንመልከት፡-

“ልዩ ጥቅም” ማለት በሕገ-መንግስቱ ውስጥ እውቅና ያገኙ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ አስተዳደራዊ፣ የልማት፣ የፖለቲካ፣ የአከባቢ ደህንነት፣ የንብረት መብቶች የመሳሰሉትን በልዩ ሁኔታ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአዲስ አበባ ላይ የሚያገኘው ጥቅም ማለት ነው” የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁጥር…..2009 (ረቂቅ አዋጅ)፣ ገፅ 2

በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 5፣ አዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ክልል መሀል የምትገኝ እንደመሆኑ ከአገልግሎት አቅርቦት፣ ተፈጥሯዊ ሀብር አጠቃቀም እና ክልሉንና መስተዳደሩን በሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት “ልዩ ጥቅም” ሊኖረው እንደሚችልና ይህም ሊከበርለት እንደሚገባ ይደነግጋል። በዚህ መሰረት፣ የኦሮሚያ ክልል “ልዩ ጥቅም” በዋናነት ከአገልግሎት አቅርቦት፣ ተፈጥሯዊ ሀብር አጠቃቀም እና ከመስተዳደሩ ጋር በሚያገናኘው አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ የተወሰነ ነው። ነገር ግን፣ የኦሮሚያ ክልል በከተማዋ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን በወጣው አዋጅ መሰረት ግን ክልሉ ከኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ አስተዳደር፣ ልማት፣ ፖለቲካ፣ አከባቢ ደህንነት እና ንብረት አንፃር በአደስ አበባ ላይ ልዩ መብት እንዳለው ይደነግጋል።

ነገር ግን፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) ላይ ከተደነገጉት ከአገልግሎት አቅርቦት፣ ተፈጥሯዊ ሀብት አጠቃቀም እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ባለፈ በሁሉም ዘርፍ በከተማዋ ላይ ልዩ ጥቅም ይገባኛል ማለቱ ፍፁም ተቀባይነት የለውም። በዚህ የተሳሳተ እሳቤና የሕግ-መንግስት ግንዛቤ የመነጩና በረቂቅ አዋጁ ውስጥ የተዘረዘሩት፤ በክፍል ሁለት ተራ ቀጥር 11፥ 12፥ 13፥ 14 እና 16፣ በክፍል ሦስት ተራ ቀጥር 17፥ 18 እና 21፣ እንዲሁም በክፍል አምስት ተራ ቀጥር 30 እና 32፣ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የላቸውም።

3ኛ የኦሮሚያ ክልል “ሕዝብ” ወይስ “ተወላጅ”?

በኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም ለመወሰን በወጣው ረቂቅ አዋጅ መገቢያ ላይ “በኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት መግቢያ ላይ የኢትዮጲያ ብሔር፥ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መጪው የጋራ እድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነው የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበላችን፣” የሚለው የሕገ-መንግስታዊ መርህ ተጠቅሷል። ለዚህ መርህ የአዲስ አባባ ከተማ ገና ከአመሰራረቷ ጀምሮ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር የነበራት ኢፍትሃዊ ግንኙነት በማሳያነት የሚጠቀስ ነው።

በእርግጥ አዲስ አበባ የሀገሪቱ ዋና ከተማ እንደመሆኗ መጠን በሁሉም ዘርፍ እየሰፋችና እያደገች መሄዷ የማይቀር ነው። በዚህ ምክንያት፣ የከተማዋ እድገት የራሷ ግዛት በሆነው የ54ሺህ ሄክታር ላይ ብቻ ተወስኖ ሊቀር አይችልም። ከተማዋ በኦሮሚያ ክልል መሃል እንደመገኘቷና የመሬት ይዞታዋ ውስን እንደመሆኑ መጠን፣ ከተማዋ እያደገች በሄደች ቁጥር በዙሪያዋ ካለው የኦሮሚያ ልዩ ዞን ጋር መሬት እና አገልግሎት እንድትጋራ ትገደዳለች። ነገር ግን፣ ከተማዋ ላለፉት 130 ዓመታት ስታደርግ እንደነበረው፣ በዙሪያዋ ያለውን የኦሮሞ ገበሬ እያፈናቀለች መቀጠል የለባትም። ከዚያ ይልቅ፣ አዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ያሉት የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች በጋራ እጅ-ለእጅ ተያይዘው አብረው ማደግ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ በአንቀፅ 49(5) ላይ በተደነገገው መሰረት የክልሉና የከተማ መስተዳደሩ መካከል፤ በአገልግሎት አቅርቦት፣ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ረገድ ግጭት እንዳይፈጠር በሚያስችል መልኩ ዝርዝር ጉዳዩ በሕግ እንዲወሰን በሕገ-መንግስቱ ተደነገገ።

በዚህ መሰረት፣ የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) የአዲስ አበባ እና ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር የነበራትን የተዛባ ግንኙነት ለማረምና የኦሮሞን ሕዝብና የከተማዋን ነዋሪዎች የጋራ ጥቅም ለማረጋገጥ ያለመ ነው። በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለው የኦሮሞ ሕዝብ ከከተማዋ እድገት ጋር ተያይዞ ከመሬት ያለመፈናቀል መብቱን ለማረጋገጥ ያለመ ነው። ይህ ደግሞ፣ አንደኛ፡- መሬት በሀገራችን ዋንኛ የሃብት ምንጭ ስለሆነ የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የፍትሃዊነት ተጠቃሚነት አንዱ ማረጋገጫ መሳሪያ መሆኑን፣ ሁለተኛ፡- በሀገራችን ሁኔታ መሬት ከማንነት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ብሔር ብሄረሰቦች የማንነት መገለጫዎቻቸውን ማሳደግ የሚችሉት ከመሬት ያለመነቀል ዋስትና ሲያገኙ ነው” ከሚለው የሕገ-መንግስት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) መሰረታዊ ዓላማ በጥቅሉ የኦሮሚያ ክልል ሕዝብን፣ በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ ማዕከል ያደረገ ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የማስተዳደር ተጠሪነቱ ለክልሉ ሕዝብ ነው። ስለዚህ፣ ክልላዊ መንግስቱ የሚያወጣቸው አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ዋና ትኩረታቸው የክልሉን ሕዝብ መብትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ ማዕከል ሊያደርጉ ይገባል። ነገር ግን፣ የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም ለመወሰን በወጣው አዋጅ ዋና ትኩረቱ ለክልሉ ሕዝብ ሳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን ጥቅምና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ ነው። በመሆኑም፣ ረቂቅ አዋጁ በተሳሳተ ግንዛቤና የሕገ-መንግስት ትርጓሜ ላይ የተመሰረተና የክልሉ ሕዝብ መብትና ተጠቃሚነት ስለማያረጋግጥ ተቀባይነት የለውም።

በመጨረሻም፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት የማሻሻል ዓላማና ግብ ካለው በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 106 መሰረት ተግባራዊ አንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅበታል። ነገር ግን፣ የሕገ-መንግስቱን ድንጋጌዎችና መርሆች የሚጣረስ ረቂቅ አዋጅ በማዘጋጀት “ሕግ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም” ይከበርልኝ ብሎ መጠየቅ አይችልም፥ አይቻልም። በአጠቃላይ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) ላይ የተደነገገውን የክልሉን “ልዩ ጥቅም” ለመወሰን የቀረበው ረቂቅ አዋጅ፤ በተሳሳተ እሳቤና በአጉል የቃላት ጨዋታ የታጨቀ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ሕገ-መንግስታዊ መብትና የከተማ መስተዳደሩን ራስን-በራስ ስልጣን የሚፃረር፣ እንዲሁም የኦሮሚያን ክልል ሕዝብና መንግስት መብትና ተጠቃሚነት የማያረጋግጥ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም።

**************

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories