Apr 30 2017

ሕገ-መንግስቱን በሚጥስ አዋጅ የኦሮሚያን "ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም" ማስከበር አይቻልም

ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ዙሪያ የተለያዩ ፅሁፎችን አውጥቼያለሁ። ማስተር ፕላን፡ የችግሩ መነሻ እና መድረሻ” በሚለው ፅሁፍ የአዲስ አበባ ከተማ ገና ከአመሰራረቷ ጀምሮ የኦሮሞን ሕዝብ መብትና ተጠቃሚነት ያላረጋገጠች መሆኗንና ማስተር ፕላኑ ደግሞ ይሄን የሚያስቀጥል ስለመሆኑ፣ “የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ማቋረጥ ስህተትን እንደ መሳሳት ነው” በሚለው ፅሁፍ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ ለተከሰተው ችግር ዘላቂ መፍትሄ መስጠት የሚቻለው የችግሩን ዋና መንስዔ መለየት ሲቻል እንደሆነ፣ በመቀጠል “ኦሮሚያን ለአመፅ፣ አዲስ አበባን ለቆሻሻ የዳረገች አንቀፅ” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅሁፍ ደግሞ የኦሮሚያ ሕዝብ እና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መብትና ተጠቃሚነት በዘላቂነት ሊረጋገጥ የሚችለው የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) ተግባራዊ ሲደረግ እንደሆነ በዝርዝር ገልጬያለሁ።

ከላይ በተጠቀሱት ሦስት ፅሁፎች በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል መካከል ያለው ግንኙነት ከጭፍን ደጋፍና ተቃውሞ በፀዳ መልኩ እንዲመራ እና የክልሉ ሕዝብና የከተማዋ ነዋሪዎች መብትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ፣ ለዚህ ደግሞ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) አስፈላጊው የሕግ አዋጅ እና የአፈፃፀም መመሪያ መዘጋጀት አለበት በሚል መርህ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ስለዚህ፣ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም የሚያስከበር አዋጅ መውጣት አለበት እያልኩ በፅሁፎቼ ተከራክሬያለሁ። በጉጉት ስጠብቀው የነበረው ረቂቅ አዋጅ ግን እንዲህ ቅስሜን ይሰብረዋል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር።

በመሰረቱ፣ በሀገር ወይም ክልል ደረጃ ሰላም፥ ልማትና ዴሞክራሲ ለማረጋገጥ በሚል የሚወጡ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች በምንም መልኩ ቢሆን ሕገ-መንግስታዊ መርሆችንና ድንጋጌዎችን መፃረር የለባቸውም። ሕገ-መንግስቱ በማንኛውም አካል ቢሆን ለሚወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች እንደ መነሻ ሆኖ ያገለግላል የሚል እምነት አለኝ። “ሕገ-መንግስቱ በራሱ ክፍተቶች ስላሉበት አንቀበለውም” የሚሉ ወገኖች መኖራቸው እርግጥ ነው። ነገር ግን፣ “በሕገ-መንግስቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ራሱ ሕገ-መንግስቱ ላይ በተደነገገው አግባብ መሰረት መቀየርና ማሻሻል ይቻላል” የሚል ፅኑ አቋም አለኝ።

ይህ አቋም “ሕገ-መንግስቱ ፍፁም ነው” ከሚል ጭፍን አመለካከት የመነጨ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ሕገ-መንግስት ለዜጎች መብት እና ለመንግስት ስልጣን ዋስትና ነው። ስለዚህ፣ የሕገ-መንግስቱ መርሆችና ድንጋጌዎች የሚፃረሩ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን ማውጣት በዜጎች ላይ ከሚፈፀመው የመብት ጥሰት በተጨማሪ የሕግ አውጪዎችን፣ አስፈፃሚዎች እና ተርጓሚዎችን (ሦስቱንም የመንግስት አካላት) ሥራና ተግባር ተቀባይነት ያሳጣዋል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ሕገ-መንግስቱን የሚፃረር ማንኛውም ተግባር ከመሰረታዊ የመብት መርህ አንፃር ተቀባይነት አይኖረውም።

በመሰረታዊ የመብት መርህ (universal principle of right) መሰረት፣ ማንኛውም ዓይነት ተግባር በራሱ ወይም በዓላማው በሁሉም የእንቅስቃሴው ተሳታፊዎች ነፃነት ላይ ተፅዕኖ እስካልፈጠረ ድረስ ትክክለኛ ተግባር ወይም “መብት” ተደርጎ ይወሰዳል። ስለዚህ፣ የእኔ “መብት” የሌሎችን ሰዎች ነፃነት በማይገድብ መልኩ መንቀሳቀስ መቻል ነው። በመሆኑም፣ የእኔን ነፃነት ማክበር ለሌሎች ሰዎች ግዴታ፣ የሌሎችን ሰዎች መብት ማክበር የእኔ ግዴታ ነው። በተመሣሣይ፣ የኦሮሚያን መንግስትና ሕዝብ ሕገ-መንግስታዊ መብት ለአዲስ አበባ መስተዳደርና ነዋሪዎች ግዴታ ነው፣ የከተማ መስተዳሩንና የነዋሪዎቹ ሕገ-መንግስታዊ መብት ማክበር ደግሞ ለኦሮሚያ መንግስትና ሕዝብ ግዴታ ነው።

በአጠቃላይ፣ በመሰረታዊ የመብት መርህ እኛ ለሌሎች ያለብን ግዴታ ሳንወጣ ወይም የሌሎችን መብት ሳናከብር ሌሎች የእኛን መብት እንዲያከብሩ ወይም ለእኛ ያለባቸውን ግዴታ እንዲወጡ መጠየቅ አንችልም። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የአዲስ አበባ መስተዳደር እና የነዋሪዎቿን ሕገ-መንግስታዊ መብት በሚጥስ መልኩ የክልሉን ልዩ ጥቅም ማስከበር አይችልም። ይህን መርህ የሚፃረር ማንኛውም ሥራና ተግባር በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም። እንዲህ ያለ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ ወይም እቅድ ውሎ-አድሮ ለሕዝባዊ አመፅና አለመረጋጋት መንስዔ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

የኦሮሚያ መንግስትና ሕዝብን መብትና ተጠቃሚነት ለማስከበር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ በሌለበት ተግባራዊ ሊያደርገው የነበረው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። በአዲስ አበባ እና በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች መካከል የተቀናጀ የመሰረተ ልማትና የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ለመዘርጋት በሚል የፀደቀው የአዲስ አባባ ማስተር ፕላን ከክልሉና ከተማዋ አልፎ በሀገሪቱ ሰላም፥ ልማትና ዴሞክራሲ ላይ ትልቅ ጠባሳ ፈጥሯል። ለዚህ መነሻ ምክንያቱ ማስተር ፕላኑ በተለይ ከመሬት ሀብት አጠቃቀምና ከመሰረተ ልማት ግንባታ ጋር ተያይዞ የኦሮሚያን መንግስትና ሕዝብ መብትና ተጠቃሚነት የማያረጋግጥ ስለሆነ ነው። በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) መሰረት የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም ለማስከበር የወጣው አዋጅ የአዲስ አበባን መስተዳደርና ነዋሪ መብትና ተጠቃሚነት የሚፃረር ከሆነ ተመሣሣይ እጣ-ፋንታ ይገጥመዋል።

በእርግጥ ይህ ፅሁፍ የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። ሆኖም ግን፣ እስካሁን ድረስ ትኩረት ያደረግነው በሕገ-መንግስቱ መርሆችና ድንጋጌዎች ላይ ነው። ለዚህ ዋና ምክንያት ረቂቅ አዋጁ የክልሉን ሕገ-መንግስታዊ መብት ለማስከበር በሚል ሰበብ የአዲስ አበባ ከተማ መሰተዳደርን ራስን በራስ የማስተዳደር ስልጣን እና የነዋሪዎች ሕገ-መንግስታዊ መብት የሚጥስ፣ የኦሮሚያን ክልል ሕዝብና መንግስት መብትና ተጠቃሚነት አያረጋግጥም። በአጠቃላይ፣ የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣው ረቂቅ አዋጅ ከሕገ-መንግስቱ አንፃር ሦስት መሰረታዊ ስህተቶች አንዳሉበት አንደሚከተለው በዝርዝር ለማሳየት እሞክራለሁ፡-

1ኛ፡- በኦሮሚያ ክልል “መሀል” ወይስ “አካል”?

በረቂቅ አዋጁ ውስጥ የሚስተዋሉት ክፍተቶች ከሞላ-ጎደል ሁሉም ማለት ይቻላል በዚህ የተሳሳተ እሳቤ ወይም ግንዛቤ ምክንያት የተፈጠሩ ናቸው። ጉዳዩን በዝርዝር ለማየት እንዲያስችለን በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 5 ላይ ያለውን ድንጋጌ እንመልከት፡-

የኦሮሚያ ክልል፤ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም ተፈጥሯዊ ሀብር አጠቃቀምና የመሳሰሉት ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል “መሀል የሚገኝ በመሆኑ” የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል።”  የኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት፥ ምዕራፍ አራት፥ አንቀፅ 49

የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣው ረቂቅ አዋጅ ሕገ-መንግስቱን መነሻ አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ለማሳየት አንቀፅ 49(5) በመግቢያው ላይ እንደሚከተለው አጣሞ አቅርቦታል፡-

“የኢትዮጲያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ሕገ-መንግስት በአንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ (5) የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም ተፈጥሯዊ ሀብር አጠቃቀምና የመሳሰሉት ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል “አካል በመሆኑ” የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለውን ልዩ ጥቅም እንዲጠበቅለት በመደንገጉ፤…”  ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል።”  የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁጥር…..2009 (ረቂቅ አዋጅ) ገፅ 1

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) “አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ” የሚለው ሐረግ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ “አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል አካል በመሆኑ” በሚለው ተቀይሯል። በረቂቅ አዋጁ ውስጥ የሚስተዋሉት ክፍተቶች ሕገ-መንግስቱ “መሀል” ያለውን “አካል” ብሎ ከመውሰድ የመጡ ናቸው። ምክንያቱም፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 2ና 5 መሰረት፣ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል “መሀል የሚገኝና ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን” ያለው የከተማ መስተዳደር ነው። ረቂቅ አዋጁ ግን “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል አካል ስለሆነ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን የለውም” በሚል እሳቤ የተዘጋጀ ነው።

አዲስ አበባ “በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ” የሚለው ሐረግ በአዋጁ ውስጥ “በኦሮሚያ ክልል አካል በመሆኑ” ተብሎ የተጠቀሰው በቃላት አጠቃቀም ምክንያት የተፈጠረ ስህተት ሊባል ይችላል። ነገር ግን፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 106 መሰረት የሕገ-መንግስቱ የአማርኛ ቅጂ የመጨረሻ ሕጋዊ እውቅና ያለው ሰነድ ስለሆነ የረቂቅ አዋጁን አገላለፅ ከስህተት አያድነውም። በአጠቃላይ፣ የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣው ረቂቅ አዋጅ በተሳሳተ የሕገ-መንግስት ትርጓሜ ወይም እሳቤ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም።

2ኛ የኦሮሚያ “ልዩ ጥቅም” ወይስ “ልዩ መብት”?

በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 5 ላይ ለኦሮሚያ ክልል የተደነገገውን “ልዩ ጥቅም” እንመልከት፡-

“የኦሮሚያ ክልል፤ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም ተፈጥሯዊ ሀብር አጠቃቀምና የመሳሰሉት ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል “መሀል የሚገኝ በመሆኑ” የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል” የኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት፥ ምዕራፍ አራት፥ አንቀፅ 49 (5) 

የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 5 በረቂቅ አዋጁ ውስጥ የተሰጠውን ትርጉም እንመልከት፡-

“ልዩ ጥቅም” ማለት በሕገ-መንግስቱ ውስጥ እውቅና ያገኙ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ አስተዳደራዊ፣ የልማት፣ የፖለቲካ፣ የአከባቢ ደህንነት፣ የንብረት መብቶች የመሳሰሉትን በልዩ ሁኔታ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአዲስ አበባ ላይ የሚያገኘው ጥቅም ማለት ነው” የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁጥር…..2009 (ረቂቅ አዋጅ)፣ ገፅ 2

በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 5፣ አዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ክልል መሀል የምትገኝ እንደመሆኑ ከአገልግሎት አቅርቦት፣ ተፈጥሯዊ ሀብር አጠቃቀም እና ክልሉንና መስተዳደሩን በሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት “ልዩ ጥቅም” ሊኖረው እንደሚችልና ይህም ሊከበርለት እንደሚገባ ይደነግጋል። በዚህ መሰረት፣ የኦሮሚያ ክልል “ልዩ ጥቅም” በዋናነት ከአገልግሎት አቅርቦት፣ ተፈጥሯዊ ሀብር አጠቃቀም እና ከመስተዳደሩ ጋር በሚያገናኘው አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ የተወሰነ ነው። ነገር ግን፣ የኦሮሚያ ክልል በከተማዋ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን በወጣው አዋጅ መሰረት ግን ክልሉ ከኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ አስተዳደር፣ ልማት፣ ፖለቲካ፣ አከባቢ ደህንነት እና ንብረት አንፃር በአደስ አበባ ላይ ልዩ መብት እንዳለው ይደነግጋል።

ነገር ግን፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) ላይ ከተደነገጉት ከአገልግሎት አቅርቦት፣ ተፈጥሯዊ ሀብት አጠቃቀም እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ባለፈ በሁሉም ዘርፍ በከተማዋ ላይ ልዩ ጥቅም ይገባኛል ማለቱ ፍፁም ተቀባይነት የለውም። በዚህ የተሳሳተ እሳቤና የሕግ-መንግስት ግንዛቤ የመነጩና በረቂቅ አዋጁ ውስጥ የተዘረዘሩት፤ በክፍል ሁለት ተራ ቀጥር 11፥ 12፥ 13፥ 14 እና 16፣ በክፍል ሦስት ተራ ቀጥር 17፥ 18 እና 21፣ እንዲሁም በክፍል አምስት ተራ ቀጥር 30 እና 32፣ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የላቸውም።

3ኛ የኦሮሚያ ክልል “ሕዝብ” ወይስ “ተወላጅ”?

በኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም ለመወሰን በወጣው ረቂቅ አዋጅ መገቢያ ላይ “በኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት መግቢያ ላይ የኢትዮጲያ ብሔር፥ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መጪው የጋራ እድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነው የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበላችን፣” የሚለው የሕገ-መንግስታዊ መርህ ተጠቅሷል። ለዚህ መርህ የአዲስ አባባ ከተማ ገና ከአመሰራረቷ ጀምሮ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር የነበራት ኢፍትሃዊ ግንኙነት በማሳያነት የሚጠቀስ ነው።

በእርግጥ አዲስ አበባ የሀገሪቱ ዋና ከተማ እንደመሆኗ መጠን በሁሉም ዘርፍ እየሰፋችና እያደገች መሄዷ የማይቀር ነው። በዚህ ምክንያት፣ የከተማዋ እድገት የራሷ ግዛት በሆነው የ54ሺህ ሄክታር ላይ ብቻ ተወስኖ ሊቀር አይችልም። ከተማዋ በኦሮሚያ ክልል መሃል እንደመገኘቷና የመሬት ይዞታዋ ውስን እንደመሆኑ መጠን፣ ከተማዋ እያደገች በሄደች ቁጥር በዙሪያዋ ካለው የኦሮሚያ ልዩ ዞን ጋር መሬት እና አገልግሎት እንድትጋራ ትገደዳለች። ነገር ግን፣ ከተማዋ ላለፉት 130 ዓመታት ስታደርግ እንደነበረው፣ በዙሪያዋ ያለውን የኦሮሞ ገበሬ እያፈናቀለች መቀጠል የለባትም። ከዚያ ይልቅ፣ አዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ያሉት የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች በጋራ እጅ-ለእጅ ተያይዘው አብረው ማደግ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ በአንቀፅ 49(5) ላይ በተደነገገው መሰረት የክልሉና የከተማ መስተዳደሩ መካከል፤ በአገልግሎት አቅርቦት፣ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ረገድ ግጭት እንዳይፈጠር በሚያስችል መልኩ ዝርዝር ጉዳዩ በሕግ እንዲወሰን በሕገ-መንግስቱ ተደነገገ።

በዚህ መሰረት፣ የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) የአዲስ አበባ እና ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር የነበራትን የተዛባ ግንኙነት ለማረምና የኦሮሞን ሕዝብና የከተማዋን ነዋሪዎች የጋራ ጥቅም ለማረጋገጥ ያለመ ነው። በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለው የኦሮሞ ሕዝብ ከከተማዋ እድገት ጋር ተያይዞ ከመሬት ያለመፈናቀል መብቱን ለማረጋገጥ ያለመ ነው። ይህ ደግሞ፣ አንደኛ፡- መሬት በሀገራችን ዋንኛ የሃብት ምንጭ ስለሆነ የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የፍትሃዊነት ተጠቃሚነት አንዱ ማረጋገጫ መሳሪያ መሆኑን፣ ሁለተኛ፡- በሀገራችን ሁኔታ መሬት ከማንነት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ብሔር ብሄረሰቦች የማንነት መገለጫዎቻቸውን ማሳደግ የሚችሉት ከመሬት ያለመነቀል ዋስትና ሲያገኙ ነው” ከሚለው የሕገ-መንግስት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) መሰረታዊ ዓላማ በጥቅሉ የኦሮሚያ ክልል ሕዝብን፣ በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ ማዕከል ያደረገ ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የማስተዳደር ተጠሪነቱ ለክልሉ ሕዝብ ነው። ስለዚህ፣ ክልላዊ መንግስቱ የሚያወጣቸው አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ዋና ትኩረታቸው የክልሉን ሕዝብ መብትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ ማዕከል ሊያደርጉ ይገባል። ነገር ግን፣ የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም ለመወሰን በወጣው አዋጅ ዋና ትኩረቱ ለክልሉ ሕዝብ ሳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን ጥቅምና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ ነው። በመሆኑም፣ ረቂቅ አዋጁ በተሳሳተ ግንዛቤና የሕገ-መንግስት ትርጓሜ ላይ የተመሰረተና የክልሉ ሕዝብ መብትና ተጠቃሚነት ስለማያረጋግጥ ተቀባይነት የለውም።

በመጨረሻም፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት የማሻሻል ዓላማና ግብ ካለው በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 106 መሰረት ተግባራዊ አንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅበታል። ነገር ግን፣ የሕገ-መንግስቱን ድንጋጌዎችና መርሆች የሚጣረስ ረቂቅ አዋጅ በማዘጋጀት “ሕግ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም” ይከበርልኝ ብሎ መጠየቅ አይችልም፥ አይቻልም። በአጠቃላይ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) ላይ የተደነገገውን የክልሉን “ልዩ ጥቅም” ለመወሰን የቀረበው ረቂቅ አዋጅ፤ በተሳሳተ እሳቤና በአጉል የቃላት ጨዋታ የታጨቀ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ሕገ-መንግስታዊ መብትና የከተማ መስተዳደሩን ራስን-በራስ ስልጣን የሚፃረር፣ እንዲሁም የኦሮሚያን ክልል ሕዝብና መንግስት መብትና ተጠቃሚነት የማያረጋግጥ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም።

**************

Source: HornAffairs.com
ይህን ጽሑፍ ወስደው ሊያትሙ ቢሹ፤ የሆርን አፌይርስን እና የፀሐፊውን ስም በግልጽ መጥቀስ እና የዚህን ፖስት Link ማስቀመጥ ይገባል፡፡

11 Comments
 1. Zerihun

  ጥሩ አስተያየት ነው፡፡ ግን ተጨማሪ ትችቶች መቅረብ ነበረባቸው፡፡ ለምሳሌ በረቂቅ አዋጁ ከንቲባውን ለሹመት የሚያቀርበው የኦሮሞው ካውንስል መሆኑ፣ የከተማው አስተዳደር ለነዋሪዎቹ የከተማው ቀደምት ተወላጅ/ባለቤት የኦሮሞ ህዝብ መሆኑን ማስተማር አለባቸው የሚሉት አንቀጾችን ያስገርማሉ፡፡ 1ኛ፡ 5 ሚሊዮኑ የአዲስአበባ ነዋሪ የት ሄዶ ነው ሌላው ከንቲባ የሚመርጥለት? 2ኛ፡ የታሪክ ምሁራን በግልፅ እንዳስቀመጡት የኦሮሞ ህዝብ በ16ኛው ከባሌ አካባቢ ተነስቶ ወደ አዲስ አበባና ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የተስፋፋው ሌሎች ነባር ህዝቦች አጥፎቶ አሊያም assimilate አድርጎ ነው፡፡ ከዛሬ 120 በፊት ደግሞ አሁን የያዘችውን አሰፋፈር ይዛለች፡፡ እውነታው ይህ ከሆነ አ/አ ላይ አንዱን ነባር ሌላውን መጤ የምንልበት መስፈርት ምንድነው? ሀሳቤን ሳጠቃልል ህዝብ ከህዝብ ደም ሊያፋስስ የሚችል የፖለቲካ ቁማር መጫወቱ አያዋጣም፡፡

 2. Dulla Furi

  utter stupid. You have no right to propagate anti Oromo propaganda in the name of free press and expression of ideas. Let the so-called Ethiopia fall apart if it fails to respect the true owners of the land. We are not and shall not be dump site for settlers. Down with your dirty stand.

 3. Samuel

  Dear writer your article is completely biased, to mention a few,

  ” የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም ለመወሰን በወጣው አዋጅ ዋና ትኩረቱ ለክልሉ ሕዝብ ሳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን ጥቅምና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ ነው። ” false.
  “…ልዩ ጥቅም” ለመወሰን የቀረበው ረቂቅ አዋጅ፤ በተሳሳተ እሳቤና በአጉል የቃላት ጨዋታ የታጨቀ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ሕገ-መንግስታዊ መብትና የከተማ መስተዳደሩን ራስን-በራስ ስልጣን የሚፃረር፣ እንዲሁም የኦሮሚያን ክልል ሕዝብና መንግስት መብትና ተጠቃሚነት የማያረጋግጥ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም።” completely biased! Am not saying it’s not hard,it is, but given the past history of Addis, current situation, this is the exact and solution.

  Anyways i respect your opinion as you too should respect mine. I look forward to your opinion. Thank you Brother.

 4. aschenaki

  እኔ አስካሁን የምንመራበት ፌዴራላዊ ስርአታችን ችግር አለበት ብዬ በጭራሽ አስቤ አላዉቅም፡፡ነገር ግን መሴሪ በሆኑ ግለሰቦች ሴራ በቀላሉ ለቀዉስ ልንጋለጥ እንደምንችል ሁልግዜም መስጋቴ አልቀረም፡፡ይሄዉ ዛሬ ደግሞ ግዜዉ ደርሶ በዜጎቸ መካካል በማንነትና በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የመብት ልዩነት ከሚያደርግ ከፋፋይ የሆነ ህግ እሰከማዉጣት ደርሰናል፡፤ይሄ ረቂቅ አዋጅ ምን የሚሉትና ለማንስ ጥቅም ተብሎ የታሰበ አዋጅ አንደሆነ ልረዳ አልቻልኩም፡፡ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን ለወደፊቱ እርስበርስ ግጭትና ጥላቻ በር የሚከፍት እጅግ ጠንቀኛ የሆነ አዋጅ ነዉ፡፤ይህን ረቂቅ ያዘጋጀዉ አካል የዘረኝነተ ልክፍት የተጠናወተዉ ህመምተኛ መሆን አለበት፡፡ህዝብን እርስበርስ የሚከፋፈፍል ህግ ማዉጣት ጤነኛ ከሆነ ሰዉ መቼም አይጠበቅምና፡፡፡የኦሮሞን ህዝብ ከሌላዉ ህዝብ ለመነጠልና ለማጋጨት ያለመ አደገኛ ሴራ ነዉ፡፤ለአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ከሌላዉ ህዝብ የተለየ መብት የሚሰጥና ሌላዉን የሚነፍግ በደቡብ አፍሪካ ከነበረዉ አፓርታይድ ጋር የሚመሳሰል ስርአት ለመመስረት የታለመ አስመስሎአል፡፤በመሰረቱ የኦሮሞ ህዝበ ጥያቄ ይሄ አልነበረም፡፤የኦሮሞ ህዝብ ከሌላዉ በተለየ ተጠቃሚ ልሁን አላላም፡፤የሌላዉን መብት ልንጠቅ አላለም፡፤ማንኛዉንም በህገመንገስቱ የተደነገጉ መብቶች ሁሉ ቅድሚያ ለእኔ መሆን አለበት አላለም፡፡ ኦሮሚኛ ተናጋሪ ያልሆኑ ህዝቦች በአዲስ አባባ ዉስጥ ያለእኔ ፈቃድ መኖር አይችሉም አላለም፡፡ለመሆኑ በአዲስ አበባን ተሞክሮ በመዉሰድ በሌሎች ክልሎቸም ተመሳሳይ እርምጃ እንዳይወስዱ የሚከለክለቸዉ ነገር አለ አንዴ?ከእንግዲህ ወዲያ በአማራ ክልል የሚኖሩ ትግሬዎቸ ቅድሚያ ለአማራ ነዉ ተብለዉ ህገመንገስታዊና የዜግት መብታቸዉ እንደማይጣስ ፤በሀዋሳ የሚኖሩ አማራና ኦሮሞ ሲዳማና ወላይታ አይደላችሁም ተብለዉ መብታቸዉ በሰፊዉ እንደማይደፈጠጥ ማንም እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይችልም፡፡ይህ አዋጅ ተበዬ ተግባራዊ መሆን በጀመረ በሁለት ዓመት ባልበለጠ ግዜ ዉስጥ በመጀመሪያ አዲስ አባባ ዉስጥ ቀጥሎ ደግሞ በቀረወዉ የሀገሪቱ አካባቢዎች ፈጽሞ መቆጣጠር የማይቻል ቀዉስ ሊፈጠር እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ይሄን አዋጀ ያረቀቁ ሰዎች በሌሎች አገሮች የደረሰዉን እርሰበርስ መተላለቅ መነሾ ለማወቅ ትንሽ እንኳን ጥረት አለማድረጋቸዉ ያስታዉቃል፡፤ከዚህ አዋጅ ጀርባ በተዘዋዋሪ መንገድ የኦነግና ሻእቢያ እጅ እንዳለ መጠርጠር ይቻላል፡፤የኢትዮጵያ ጠላ የሆነዉ ጃዋር እኛ ለማጣላት ከዚህ አዋጅ የከፋ ከፋፋይ ህግ ለማርቀቅ መቻሉን እጠራጠራለሁ፡፡ ኦህደዴድ/ ኢህአዴግ በኦሮሞ ስም የዚህ ዓይነት ጭፍን እርምጃ በመዉሰድ የኦነግን ተጽኢኖ መቀነስ ይቻላል ብለዉ አስበዉ ከሆነ ትልቅ ስህተት ነዉ፡፤ይህን አዋጅ ለማዉጣት እየተዘጋጀ ያለዉ አካል የፈለገዉ ሁኔታና ማንኛዉም ዓይነት ቀዉስ ቢፈጠር ግድ የለለዉ እንደሆነ ለመረዳ አያዳግትም፡፡አንደአዋጁ መንፈስ ከሆነ ከዚህ በኋላ የኦሮሞ መነድር የአማራ ሰፈር የትግሬ ቀበሌ ወዘተ እየተባለ በጎጥ መከፋፈል ይመጣል፡፡የኦሮሞን ህዝብ መብት ከዚህ በላይ ማስከበር የሚቻልበት ሁኔታን አጥንቶ መተግበር እየተቻለ ከሌሎች ዜጎች ጋር እርስ በርስ ለማናከስ ነዉ የተፈለገዉ፡፡መዘንጋት የለለብን ጥቂት ነገሮችን ልጥቀስ፡፤1ኛ)ለማንም ተብሎ ህገመንግስቱን መጣስና መሸርሸር አይቻልም፡፡ 2ኛ)የትኛዉም ህዝብ ከሌላዉ የበለጠና ያነሰ መብት አይኖረዉም፡፤3ኛ)የትኛዉም ኢትዮጵያዊ በየትኛዉም የሀገሪቱ አካባቢ ያለአንዳች ክልከላ የመኖር፤ሃብት የማፍራትና እኩል የመስተናገድ መብቱን ማንም ሊነጥቀዉ አይገባም፡፡ 4ኛ)ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያዉያን ስለሆነች ማንም ከሌላዉ በተለየ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችልባት አገር ልትሆን አይገባም፡፡በየትኛዉም የሀገሪቱ አካባቢ በተፈጥሮ የሚገኝ ሃብት የመላዉ የሀገሪቱ ዜጎች የጋራ ሃብት ነዉ ሊሆን የሚገባዉ ፡፡በተረፈ ኦሮሚኛ ቋንቋ በአዲስአባባ ቀርቶ በፌዴራል ደረጃ ከአማራኛ ጎን ለጎን የስራ ቋንቋ ቢሆን የሚቃወም ሰዉ ያለ አይመስለኝም፡፡ስለዚህ ለኦሮሞ ህዝብ በትክክል የታሰበ ከሆነ ይሄን ከፋፋይና ዘረኛ አዋጅ ወዲያ ጥላችሁ ሌላ የተሻለ እንድታዘጋጁ ትመከራላችሁ፡፡

 5. hasab

  ሌሎች ክልሎች ቀድመው አድርገውታል፡፡ ጥያቄው አዲስ አበባ ላይ እስካሁን አልተደረገም አሁን ይደረግ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ክልል ላይ ብትሄድ መኪና አጣቢ ወይም ኩሊ ትሆናታለህ እንጂ የከተማው አስተዳደር ውስጥ ፒቼችዲ(ዶክተር) ብትሆን እንኳ ለጥበቃና ተላላኪነት አትቀጠርም፡፡ እውነታው ዘጠኙም ክልል ውስጥ የአካባቢውን ቋንቋ ካልቻልክ መስራት አትችልም፡፡ ፊንፊኔ ለመብቷ ትጮሃለች . . . መደማመጥ የአባት ነው . . .
  በነገሩ ላይ እንኳን አይደለም አዲስ አበባ ጥንታዊቷ ጎንደር እንድትቋቋም የኦሮሞዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበር ፕሮፌሰሮቻቹህ (ጌታቸው ሃይሌ፣ መስፍን ወልደማርያም፣ ሃይሌ ላሬቦ እና ጋሻ-ታሪክ-አጃግሬዎቻቸው . . . ) ለምን እንደማይነግሯቹህ አይገባኝም? መሰል-ምሁራን የአማራን ህዝብ የታሪክን-ልጅ-ታሪክ-በላው ባታደርጉት ደስ ይለኛል፡፡
  እዚህች ሃገር የኦሮሞን ሚና አሳንሰው ለሚመለከቱ ምሁራን እንዲህ እላለሁ፤
  ግፍ ከሰራ ከአንዱ ንጉስ ብቻ ሳይሆን በዚህች – ምድር – ታሪክ ውስጥ የነገስታትም ሆኑ የመሪዎች ዘመን ሁሉም ተደምሮ ከተሰሩት ግፎች በበለጠ ሁኔታ ግፍን በእጃቹህ አድርጋችኋልና – ንፁ- ታሪክን መርምሩ- በቅን ልቦና ተርጉሙም- ጭቆናንም ተፀየፉ – ያለፈውንም ብቻ ሳይሆን መጪውን ተመልከቱ . . .
  ከዚህም በላይ ኢትዮጵዊነት ኦሮሞነት የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ እንደአቻዎቹ ሁሉ መካከል (መሃል) እና ግንባር (front-and-center) መጥቶ ካልተቀመጠ በስተቀር መጪው ዘመን የከፋ ስለመሆኑ ከታሪክ አልተረዳችሁምን እላችኋለሁ፡፡
  አንዳንዶች ኦሮሞዎች ይህንን ሁሉ ከሃገራችን ላይ የሚትጠይቁት ቁጥራቸው እንደቆሎ ስለበዛ ነው እንዴ ብለው ይዘባበታሉ . . . እኔ እንዲህ እላለሁ . . . እንግዲው አላስቆም አላስቀምጥ የምትሉት አሁን ስልጣኑን የሚዘውሩት በቁጥር አናሳ ናቸው እያላቹህ አይደለምን? . . . እንኪያስ መንገዳቹህ ምንድን ነው? ጎረቤቶቻቹህ ሲበዙባቹህ ችግር! ጎረቤቶቻቹህ ሲያንሱባቹህ ችግር! ከማንስ ልትኖሩ ወደዳቹ? ከራሳችሁና ከራሳችሁ ብቻ እንዳይሆን፡፡
  መፅሃፍ ቅዱስ በግዕዝ ብቻ ካላስተማርን ተብሎ ድርቅ ሲባል ይኸው ጊዜ ተቀይሮ ነገሮች እንዳይሆኑ እየሆኑ ነው . . . ታሪክንም ከነገስታትና ከመኳንንት አንጻርና አንጻር ብቻ እያያችሁ ሃገር እንዳትሆን ሆና አረፈችው፡፡ የነገስታትና የመኳንንት ጦስ ለደርግ ስርዓት አበቃን ቀጥሎም ለኢህአደርግ ዳረገን፡፡ አሁንም ከኦሮሞ ጋር ያላችሁን ችግር መፍታት አልቻላችሁም . . . ናፍቂ ሆናችኋል – ነገስታትንና መኳንንትን ብቻ፡፡
  በማስተር ፕላኑ ጉዳይ ዳር ተቆሞ – ታዲያ ከተማዋ ላትሰፋ ነው! ሲባል ነበር . . . ለዚያም ነው 2006 ዓ.ም. ለተጀመረው የማስተር ፕላኑንና ሌሎች የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች በቀጥታ የአጋርነት ድምፅ ሳይሰማ እስከ 2008 ዓ.ም ክረምት የዘለቀው . . . አንዳንዶች አጋርነት ጨርሶ መች አሰሙስ . . .
  አዋጁ በእውነት የኦሮሞዎችን ጥቅም ያስጠብቃል ብላችሁ አጋርነታችሁን ማሳየት ሲገባቹህ መብት ይረገጥን ምን አመጣው? . . . ደምህ ደሜ ነው መባባሉ ወንበር ለማስለቀቅ ብቻ ከሆነ . . . ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሆን
  በመጨረሻ እንዲህ እላለሁ . . . ብቸኝነት እንኳን ለሃገር ለሰው ይከብዳል፡፡ ስለዚህ በሙሉ ልብ ሁላቹህ እውነተኛ ወዳጅነትን ፍጠሩ፡፡ እውነተኛ ማለት ምን ማለት ነው?
  እውነት በታሪካችን ውስጥ እንዴት ይገለፃል?
  – እውነት ለአንዱ ፅዋዋ ግማሽ-ሙሉ፤ እንዳይፈስ ጎድሎ የተሞላ የድሎት እና የፀጋ ብርጭቆ
  – እውነት ለሌላው ፅዋዋ ግማሽ-ባዶ፤ እንዳይዳረስ ጎዶሎ የተሞላ የበደል እና የፀብ ብርጭቆ
  ትክክል
  1. ሁለቱም አንድላይ እውነት ነው
  2. ሁለቱም በተናጠል እውነት ነው
  ስህተት
  1. ከግማሽ-ሙሉ ፅዋው ምንም ሳያካፍለው፣ ለራሱ ግጥም አድርጎ ጠጥቶ ከጨረሰ በኋላ ግማሽ-ባዶን ጠጥቻለሁ የድሎቱና የፀጋው ተካፋይ ነኝ ብለህ በግድ መስክርልኝ ሲል
  2. ከግማሽ-ባዶ ፅዋው ምንም ሳይደርሰው ማለቁና መቸገሩ ቀርቶ ፣ በግማሽ-ሙሉ ተጠጥቶ ያለቀው የወይን-መጠጥ ሳይሆን የእኔ-ደም ነው ብሎ ሲቆጭ
  እኔ ለግማሽ-ሙሉ እንዲህ እለዋለሁ
  መስጠት እየቻልክ አለመስጠትህ ጥፋት፣ ክፋት፣ ስግብግብነት፣ አርቆ-አለማየት ነው. . . ስትጠጣ ትን ቢልህ በማን ፅዋ ይቀርብልሃል? . . . ከግማሽ-ባዶ አይደለምን? ለወደፊቱ ቢቻል ፅዋውን በጋራ ቅዳ (ለብቻህ የቀዳህ ጊዜ ዕድልህን አበላሽተሃልና) ባይቻል የምትካፈልበትን መስፈሪያ ቀድመህ አዘጋጅ
  እኔ ለግማሽ-ባዶ እንዲህ እለዋለሁ
  የገዛ ደምህን ባለመጠጣትህ ስለምን ይቆጭሃል . . . ባለፈህ ግማሽ-ሙሉ ፅዋ ሃሴትን አድርግ ፡፡ ለመጪው ግን አለመጠጣት ምን ማለት እደሆነ ስለምታውቅ . . . ቢቻል ፅዋውን እራስህ ቅዳ ባይቻል የምታካፍልበትን መስፈሪያ ቀድመህ አዘጋጅ
  አርበኝነት እውነተኛ ወዳጅነትን መፍጠር ነው!
  አዲሱን አዋጅ ከድብቅ የማስተር ፕላን ማስፈፀሚያነት እንጠብቅ!