ከኢትዮጵያዬ ወደ ኢትዮጵያችን

(ቴዎድሮስ ደረጄ (ዘበደሌ)

ጠቅለል አድርጎ “የኢትዮጵያውያን እይታ” እያሉ ማተቱ ትንሽ ከባድ ቢሆንም ጎልተው በሚወጡ ነገራት ላይ ተነስቼ እይታዬን አቀርባለሁ ።

በታሪክ ድርሳናት ኢትዮጵያ በውል መቼና እንዴት ተመሰረተች? ስሟስ እንዴት ኢትዮጵያ ተባለ? በሚለው ስምምነት ላይ ያልተደረሰ ቢሆንም እያንዳንዱ ኢትዮጵያ ከተመቸው የታሪክ ክምር እያፈሰ ኢትዮጵያዬ የሚለውን እየሳለ እዚህ ደርሷል። ይህ ኢትዮጵያችን ወደሚለው ከፍ ይል ዘንድ ግዜ እሚጠይቅ ይመስላል።

አንድ የስነ ፅሑፍ መምህር:- ይህን አንብበሃል?

ተማሪ:- አላነበበኩም

መምህር፡ ያንንሳ ?

ተማሪ:- እረ በጭራሽ

መምህር:- ምኑን የስነ ፅሑፍ ተማሪ ሆንክ?

እውነት ነው በአንድ የትምህርት ክፍል ጥናት ወቅት ፈርጥ እሚባሉትን ማጥናት ስለነሱ ማወቅ የትምህርት ዘርፉ ሀሁ ነው። ነገር ግን መምህር በተከተሉት መንገድ የግድ መጓዝ ካልሆነ በቃ ስህተት ነው ማለትም እንዲሁ ይከብዳል። እድሉን ሰጥቶ ማየት እንጂ። መምህር መሪ ነው እንዲሉ መንገዱን ማሳየት መታዘብ መቀበል ያሻል። የተሻለን መፍጠር እንጂ መጣል ማሳለፍ ብቻ አይደለም የመምህር ስራ ። እርሱ ፈርጥ ካላቸው ሌላ ሌሎች ፈርጦችም ይኖራሉ።

Photo - Ethiopian children
Photo – Ethiopian children

የኢትዮጵያዊነት መምህራንም ከዚህ እጅግ በራቀ መንገድ ባረጀ የኢትዮጵያዊነት መፅሐፍ እየተመሩ ይገኛል። ይህ መብት ቢሆንም መፅሐፍ “ግዜውን ዋጁ” እንዲል ወቅቱን የዋጀ ስብከት ያሻል። መሰረቷ የፀና ይሆን ዘንድ ኢትዮጵያዊነት ሁሉም በፍቅር የሚኖርባት ሀገር እንጂ ስላንተ እኔ ልወስን በሚል መሆን የለበትም። በዚህ ርዕስ የቀድሞዋ ኢትዮጵያን እና የአሁኗን ልቃኝ:

የቀድሞዋ ኢትዮጵያ

በተለያየ ወቅት ውይይት ሲነሳ የቀድሞዋ ኢትዮጵያ ልዩ እንደሆነችና ማንም ዘሩ እማይጠየቅበት እንደነበር ተደርጎ ይወራል። ቅድመ-ኢህአዴግ የዘረኝነት ጣጣ እንደሌለ ይወራል። እንግዲህ ይህን “ንፁህ ” ዘመን ስንቃኝ ስለምን እንደሚወራ ግራ ይገባናል።

በመሰረቱ በዘር ሀረጌ ተበደልኩ የሚሉ እንቅስቃሴዎች በቅርብ እንኳን ብናይ ከሐይለስላሴ ዘመን ይጀምራሉ። ከዛም ገፋ ብለን ካየን ዘር ተኮር ብዙ ሹኩቻዎች ይገጥሙናል። ንግስተ ነገስት ጣይቱ ወደ ጎን የተባሉት የስልጣን በትሯን ወደ ጎንደር ለመመለስ እየዶለቱ ነው በሚል ነው።

ሰለሞናዊ ዘር እምንለው በራሱ ከዘር የተለየ ዘር አለ የሚል የዘረኝነት አመለካከት ነው። በብሔርተኝነት ስር ባይገባም እራሱን የቻለ በተፃፉ ድርሳናት እና በሃይማኖት ህብረት በትግበራ ላይ የዋለ አገዛዝ ነበር። ይህ የቤተ መንግስት እና የቤተ አምልኮ ቁርኝት ለዘመናት ዘልቀዋል። እከክልኝ ልከክልህ ነበር። ህዝቡን በሃይማኖት አባቶች ይይዛሉ ከዛ ነገስታት ደግሞ ለአብያተ ክርስትያን የተለዩ ጥቅማጥቅም ያበረክታሉ። ነገስታቱም ለታላላቅ ደብር ስጦታን ያበረክታሉ በዚህም በምህመናን ዘንድ ፍቅርን ይቸራሉ። ይህ እንግዲህ ለብዙ ዘመናት ዘልቋል።

በየስብከቱ እምናዳምጠው ንጉስ እከሌ እንዲህ አለ እንዲህ ሆነ ዝና ወይ ያ ዘመን ብለን እድንናወድስ ይህንን እንድናቆሽሽ የራሱን ድርሻ ተወጥቷል። የድሮዋ ኢትዮጵያ የተቻላትን ምሽጎች እየያዘች እያዘመተች ትገኛለች። ቤተ እምነት እና ስነ ጥበብ ለዚህ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው። ሁለቱም ብዙ መልካም ጎንን ለሀገራችን እንዳበረከቱት ሁሉ ክፍተትም አላቸው። ማን እንደ ንጉስ እከሌ እስክንል አስደማሚ ትርክቶችን ያቀርቡልናል።

የአሁኗ ኢትዮጵያ

ይህች የአሁኗ ኢትዮጵያ ብዙ እርምጃ ወደ ፊት ያለች ናት። ብዙ ለውጦች ታይተዋል። በስነ ጥበብ “በወርቃማው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘመን” እንኳን ያልወጡ ስራዎች ሙዚቃዎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው። ፈረንሳዊው ፍራንሲስ ፋልሴቶ በብዙ ቁጥር ያወጣቸው የሙዚቃ ስራዎቹ ለዚህ ማሳያ ናቸው። ይህ ይበል እምያሰኝ ነው።

ግና የአሁኗም ኢትዮጵያ ሁሉንም ልታስደስት አልቻለችም። ስነጥበቡ ላይም የድሮው ቢት እየጮኸ መሆኑ ግልፅ ነው። ግን በሂደት መቀየሩ አይቀርም። በየግዜው እሚነሱ ትችቶች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ያለን መለያየት ከፍተኛ ውይይት እሚሻ ነው።

የአሁኗም ኢትዮጵያ ብዙ ችግሮች አሉባት። ብዙ ተግዳሮቶችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ የፌዴራል ስርሃቱ በአግባቡ አለመተግበር ሁሌ እሚነቀፍ ነው። ይህንን በተመለከተ የፌዴራል መንግስት ምሁራንን ማሳመን ወይም እራሱ መማርና ትግበራውን መሞረድ እንዳለበት ይሰማኛል።

በፌዴራል ደረጃ በአገልግሎት ላይ ያለው ቋንቋ አማርኛ ብቻ መሆን ሌላው ድከመት ነወ። የፌዴራል ቋንቋ ጥያቄም እንደቀልድ እሚገፋ አይደለም። ስንቱን የፌዴራል ቋንቋ ተደርጎ ይቻላል የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል። ይህንንም በምን መልኩ ማስኬድ እንደሚቻል መምከር ያሻል።

የፖለቲካዊ ውይይት አለመዳበር የመሳሰሉት በተደጋጋሚ እየተጠየቁ ያሉ ችግሮች ናቸው። እነዚህ ላይ በሰፊው በመወያየት መፍትሔ ማፈላለግ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ። የፖለቲካ ውይይቶች ምርጫ እና ችግር ሲኖር ብቻ መሆን ያለባቸው አይመስለኝም። ኢትዮጵያውያኖች ወደ መድረክ “ኢትዮጵያዬን” ይዘው ወጥተው ሀሳብ አብላልተውና አፋጭተው “ኢትዮጵያችንን” መፍጠር መቻል አለባቸው እላለሁ፡፡

********

Guest Author

more recommended stories