Apr 19 2017

መንግስትን ከማረም ለመንግስት ጥብቅና የሚቆም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት

የኢትዮጲያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት “ከሰኔ 2008 ዓ.ም እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በነበሩት ወራት በኦሮሚያ፣ አማራና በደቡብ ብሔር ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ክልሎች ተፈጥረዋል ባላቸው ሁከትና ብጥብጥ 669 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ 1018 ሰዎች ላይ የተለያዩ የአካል ጉዳቶች ደርሶባቸዋል፣ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል” ብሏል።

እስኪ ከላይ የቀረበውን ሪፖርት ከኢትዮጲያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር ፪፻፲/፲፱፻፺፪ ዓ.ም. አንፃር እንመልከተው። የኮሚሽኑ ሥልጣንና ተግባር በሚወስነው አንቀፅ ፮. ስር፤ “በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ውስጥ የተደነገጉት ሰብአዊ መብቶች በማንኛውም ዜጋ፣ በመንግሥት አካላት፣ በፖለቲካ ድርጅቶች፣ በሌሎች ማኅበራት እንዲሁም በባለሥልጣኖቻቸው መከበራቸውን ማረጋገጥ፣ በመንግሥት የሚወጡ ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች፣ እንዲሁም ትዕዛዞች በሕገ መንግሥቱ ከተረጋገጡ የዜጎች ሰብአዊ መብቶች ጋር የማይቃረኑ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ የሰብአዊ መብት መጣስ ቅሬታዎች ሲቀርቡለት ወይም በራሱ አነሳሽነት ምርመራ ማካሔድ” የሚሉት ተጠቅሰዋል።

በኢፊዲሪ ሕገ መንግስት ምዕራፍ ሦስት፥ ክፍል አንድ ስር ከተዘረዘሩት “ሰብአዊ መብቶች” ውስጥ የተወሰኑትን ስንመልከት፤ አንቀፅ 14፡- “ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፥ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት አለው”፣ አንቀፅ 15፡- “ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት አለው። ማንኛውም ሰው በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን አያጣም”፣ አንቀፅ 16፡- “ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት አለው”፣ እንዲሁም አንቀፅ 17፡- “በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጪ ማንኛውም ሰው ነፃነቱን አያጣም” የሚሉትን እናገኛለን።

ከላይ በኮሚሽኑ ሪፖርት እንደተገለፀው፣ በአራት ወራት ውስጥ ብቻ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች በሕግ ከተደነገገው አግባብ ውጪ 669 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ 1018 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ብዙ ሺህ ሰዎች ደግሞ በነፃነት የመኖር መብታቸውን ተገፍፈዋል። በዚህ መሰረት፣ በኢፊዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 14፥ 15፥ 16 እና 17 ላይ የተደነገጉት ሰብአዊ መብቶች ተጥሰዋል። በአዋጅ ቁጥር ፪፻፲/፲፱፻፺፪ ዓ.ም. መሰረት የኢትዮጲያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሥልጣንና ተግባር እነዚህ “ሰብአዊ መብቶች መከበራቸውን ማረጋገጥ” ነው። ኮሚሽነሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት በብዙ ሺህ የሀገሪቱ ዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈፀሙን በይፋ አረጋግጠዋል።

በኢፊዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 14፥ 15፥ 16 እና 17 ስር የተደነገጉት ሰብዓዊ መብቶች የሚጀምሩት “ማንኛውም ሰው…” በሚለው ሐረግ ነው። ምክንያቱም፣ የሀገሪቱ ዜጎች በጅምላ አንዱ ወይም ሌላ ተብለው ከመፈረጃቸው በፊት ሰብዓዊ ፍጡራን ናቸው። በመሆኑም፣ ሁሉም የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፥ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት አላቸው። ስለዚህ፣ የመብት ጥሰቱን የተፈፀመው በግለሰብ ሆነ በመንግሥት አካላት፣ በፖለቲካ ድርጅት ሆነ በመንግስት ባለሥልጣናት ልዩነት የለውም። በተመሣሣይ፣ ሕይወታቸውን ያጡት፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው፣ ወይም ከቀያቸው የተፈናቀሉት ሰዎች፤ አመፅ ጠሪዎች ሆኑ ፀጥታ አስከባሪዎች፣ አርሶ አደሮች ሆኑ ወታደሮች፣ ፖሊሶች ሆኑ ፖለቲከኞች፣…ወዘተ ልዩነት የለውም። ነገር ግን፣ የኢትዮጲያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበውን ሪፖርት በዝርዝር ከተመለከትነው ከዚህ የሕገ መንግስት መርህ እና በአዋጅ ከተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም።

ለዚህ ደግሞ በሪፖርቱ ውስጥ የተካተቱትን አንዳንድ ዓ.ነገሮች በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ፣ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ “የሁከቱ መንስዔ በአብዛኛው የመልካም አስተዳደር እጦት እና ምጣኔ ሃብታዊ (ኢኮኖሚያዊ) ችግር መሆናቸውን ገልጿል። እነዚህን መንስዔዎች ሕጋዊና ሕገ ወጥ የፖለቲካ ኃይሎች አባብሰዋቸዋል” ብሏል። በተለይ በኦሮሚያ የተከሰተውን አስመልክቶ ደግሞ “በክልሉ የተፈጠረውን አለመረጋጋትና ተቃውሞን የመሩ በመንግስትም በአሸባሪነት የተፈረጁ የፖለቲካ ድርጅቶች በሕግ መጠየቅ እንዳለባቸው” አሳስቧል። በሌላ በኩል ደግሞ “የተፈጠረውን ሁከት ለመግታት የፀጥታ ኃይሎች በአንዳንድ ስፍራዎች ሕጋዊና ተመጣጣኝ ኃይል ተጠቅመዋል፣ በሌሎች ደግሞ ተቃራኒው እንደተፈፀመ” በሪፖርቱ አስረድቷል።

ከላይ እንደተገለፀው፣ የኢትዮጲያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት በፀጥታ ኃይሎች የተወሰደውን እርምጃ በከፊል “ሕጋዊና ተመጣጣኝ” እንደነበረ ገልጿል። በሕግ ከተደነገገው አግባብ ውጪ 669 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተው፣ 1018 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸው፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በነፃነት የመኖር መብታቸው ተገፍፎ፣ በዚህ ምክንያት በኢፊዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 14፥ 15፥ 16 እና 17 ላይ የተደነገጉት ሰብአዊ መብቶች ላይ ጥሰት ተፈፅሞ ሳለ፣ በማንኛውም አግባብ ቢሆን የመንግስት እርምጃ “ሕጋዊና ተመጣጣኝ ነበር” ሊባል አይችልም።

ምክንያቱም፣ አንደኛ፡- እነዚህ ሁሉ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተው፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው እና ከቀያቸው ተፈናቅለው መንግስት በሕገ መንግስቱ የተጣለበትን ድርሻና ኃላፊነት በአግባቡ ተወጥቷል ማለት አይቻልም። በሕገ መንግስቱ የተደነገጉ ሰብዓዊ መብቶችን ከማክበርና ማስከበር አንፃር እንደ መንግስት የሚጠበቅበትን ሚና በአግባቡ አልተወጣም። ሁለተኛ፡- በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ በግልፅ እንደተጠቀሰው፣ የኮሚሽኑ መሰረታዊ ዓላማ “የሕዝቡ ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ መጠበቅ፣ መብቶች ሳይሸራረፉ ሥራ ላይ እንዲውሉ እና ተጥሰው ሲገኙ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ነው።” ነገር ግን፣ በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው ስለ መንግስት እርምጃ ሕጋዊነትና ተመጣጣኝነት የመከራከሪያ ሃሳብ ማቅረብ ከሕገ መንግስቱ መርሆች እና በአዋጅ ከተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት ውጪ ነው።

በመቀጠል “የሁከቱ መንስዔ በአብዛኛው የመልካም አስተዳደር እጦት እና ምጣኔ ሃብታዊ ችግር ነው” የሚለውን እንመልከት። በመሰረቱ፣ የችግሩ ዋና መንስዔ የመልካም አስተዳደር እጦት ከሆነ፣ ከሁሉም በፊት ተጠያቂ መሆን ያለበት አካል የመንግስት አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ነው። በሁለተኝነት የተጠቀሰው “ምጣኔ ሃብታዊ ችግር” ደግሞ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 40፥ 41፥ 43 እና 44 ላይ የተደነገጉት ዴሞክራሲያዊ መብቶች አለመከበራቸውን ይጠቁማል። ስለዚህ፣ በተጠቀሱት አከባቢዎች ሁከትና አለመረጋጋት የተከሰተው የመንግስት አካላት ከሕብረተሰቡ ለሚነሳው የእኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ተገቢ የሆነ ምላሽ ባለመስጠታቸው እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።

በዚህ መሰረት፣ ለችግሩ በመንስዔነት ለተጠቀሱት ችግሮች በቅድሚያ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው በየደረጃው ያሉ የፌደራልና የክልል መንግስት አካላት ናቸው። ነገር ግን፣ የኢትዮጲያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በዋናነት ተጠያቂ ያደረገው የችግሩ መንስዔ የሆነውን የመንግስት አስተዳደራዊ ሥርዓት ሳይሆን “ችግሩን አባብሰዋል” ያላቸውን የፖለቲካ ኃይሎች ነው። ኮሚሽኑ የኢህአዳግ መንግስትን ግንባር ቀደም ተጠያቂ አለማድረጉ በአዋጅ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለመቻሉን ያሳያል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ “ችግሩን አባብሰዋል” በማለት በሪፖርቱ የጠቀሳቸው የፖለቲካ ኃይሎች ኮሚሽኑ በአዋጅ ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በግለፅ ያሳያል። ምክንያቱም፣ በኢትዮጲያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ኮሚሽኑ የሚከተለው “የሥልጣን ገደብ” አለበት፡-

“ኮሚሽኑ በም/ቤቱ ወይም በፌዴሬሽን ም/ቤት ወይም በክልል ም/ቤቶች ወይም በማንኛውም ፍ/ቤት በየትኛውም ደረጃ በመታየት ላይ ካሉ ጉዳዮች በስተቀር የሰብአዊ መብት መጣስን አስመልክቶ በማንኛውም ሰው ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ሁሉ ተቀብሎ የመመርመር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል፡፡” የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር ፪፻፲/፲፱፻፪

በአዋጁ መሰረት ኮሚሽኑ በማንኛውም ፍ/ቤት በየትኛውም ደረጃ በመታየት ላይ ያሉ ጉዳዮችን የመመርመር ሥልጣን የለውም። ኮሚሽኑ ግን ገና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮችንና የሚዲያ ተቋማትን “በአባባሽነት እና በአመፅ ጠሪነት” ፈርጇቸዋል

በአጠቃላይ፣ የኢትዮጲያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የመልካም አስተዳደር እጦት እና ምጣኔ ሃብታዊ ችግርን ለሁከቱ በዋና መንስዔነት ጠቅሶ መልካም አስተዳደርንና የዜጎች እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የተሳነውን መንግስታዊ ሥርዓት ተጠያቂ ማድረግ ተስኖታል። በሕግ ከተደነገገው አግባብ ውጪ 669 ሰዎች ሕይወታቸውን ተገድለው፣ 1018 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸው፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በነፃነት የመኖር መብታቸው ተገፍፎ፣ በዚህም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሞ እያለ፣ በሕግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት መንግስት አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ ለሰብዓዊ መብት ከመከራከር ይልቅ ለመንግስትን ሥራና ተግባር ጥብቅና መቆሙ በጣም ያሳዝናል። በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር መሰረት መንግስትን ተጠያቂ ማድረግ የተሳነው ኮሚሽን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችንና የሚዲያ ተቋማትን ተጠያቂ ለማድረግ ሲሆን ግን የሥልጣን ገደቡን ይጥሳል።

***************

Source: HornAffairs.com
ይህን ጽሑፍ ወስደው ሊያትሙ ቢሹ፤ የሆርን አፌይርስን እና የፀሐፊውን ስም በግልጽ መጥቀስ እና የዚህን ፖስት Link ማስቀመጥ ይገባል፡፡

5 Comments
 1. Chalew Alehegn

  እናመሰግናለን ለመረጃው! ጥያቄዬ ከላይ ለችግሩ መንስኤ የተባሉት 26 ኣመት ሙሉ ሲመሩ ያልቀረፉበት ምክንያት ምንድን ነው? ምክንያቱ ለሌላ ሆኖ ሳለ እንደ መንስኤ በመጥቀስ , ጥላሸት መቀባባት ምን ኣመጣው? ሀቅ ተደብቆ ኣይቀርም ! ህዝብን ሳትይዝ ጉዞ ተጠልፎ መውደቅ ነው ! ለምን ህዝብ በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጣ ይደረጋል? ይሄ እኮ ኣሜኔታን ይቀንሳል ግልፅ ነው::
  የሚሻለው ጥፋትን ኣምኖ, ላይደገም ሀላፊነት መውሰድ ነው!አዲስ የተሻለ ስርኣት / አሰራር መዘርጋት ነው!
  እውነት የተዘረጋው ስርኣት ኢትዮጵያዊነት ካለው ደሞ ስልጣንን ለህዝብ መስጠት ነው ! ካብ ለ ካብ እየተያዩ መኖር ቢበቃ ኣይሻልም!!!?

 2. gugsakumera

  i dont know why ato addisu always trys to hide the fact.he was doing the same thing when working as deputy for national election board.After transferred to this new post he has been repeating the same thing..how dare an Ethiopian intellectual leans to be loyal to party than his people?

 3. Mamush Daniel

  በምርጫ 2007 ገዥውን ቡድን 100 በ100 አሸናፊ አድርጎ ወደ ሰብዐዊ መብት ኮሚሽን ተወርውሮ ከመጣ ጭፍን አድር ባይ ግለሰብ ከዚህ የተለየ ነገር መጠበቅ አይገባም። በምርጫው ላይ የታየው ሕሊና ቢስነት አሁንም ተደገመ። ካልጠፋ ሰው ይህን ዶክተር ተብዬ ግለሰብ በየቦታው መሰንቀር የጤና አይደለም። የድንጋያማ ሕሊና ባለቤት ሰው ፍለጋ እንጅ!

 4. baggabulle

  –እውነት የተዘረጋው ስርኣት ኢትዮጵያዊነት ካለው ደሞ ስልጣንን ለህዝብ መስጠት ነው —–ከስልጣን ማስረከብ በመለስ ማንኛዉንም ማስተካከያ ለማድረግ ችግር አይኖርብንም ፡፡ስልጣን ማስረከብ የሚባል ቀልድ ግን አይሰራም፡፤ለመሆኑ ለማንስ ነዉ የምናስረክበዉ? ለሸእቢያ፤ ለኦነግ፤ ለግንቦት ሰባት፤ ለአልቃይዳና ለአልሻባብ ወኪል ነዉ ስልጣን የምናስረክበዉ?በመጀመሪያ ስልጣን ለመረከብና ሀገር ለማስተዳደር አቅሙና ታማኝነቱ ያለዉ ማን አንደሆነ ንገሩን ፤፤ከዚያ በኋላ እንነጋገራለን