አስገደ እና የትግራይ ህዝብ ትግል ምን አገናኛቸው?

(ብሓቂ ተኸስተ (ሳዕሲዕ)

አቶ አስገደ ከህወሓት ነባር ታጋዮች አንዱ ነበር። በሂደቱ መሳተፉ የሚቆጨው ቢሆንም በአኩሪ የትግል ሂደትም የራሱን ድርሻ የተወጣ ታጋይ ነበር። ትግሉ ለድል ከበቃ በኃላም ዓረናን ተቀላቅሎ በትግራይ የተፎካካሪ ፓርቲ በመሆን የራሱን ድርሻ ሲወጣ ነበር። ወደ መሃል ሀገርም በመሄድ ለመሳተፍ ሞክሮ ነበር። በቅርብ ግዜም የልብ ችግር ገጥሞት የእርዳታ ጥሪ ቀርቦ አሁን አሜሪካ ህክምና እያገኝ ይገኛል፤ እሰየው ነው። እኔና ጏደኞቼም የበኩላችን አስተዋፅኦ አድርገናል (መጥቀስ አስፈላጊ ከሆነ)። እግዚአብሄር ቶሎ ያድነው እያልኩ ወደ ዋና ጉዳየ ልግባ።

አቶ አስገደን ለማሳከም ሲደረግ በነበረው ገቢን የማሰባሰብ ዘመቻ አቶ አስገደን ከትግራይ ህዝብ ትግል ጋር በማቆራኘት የድረሱለት ጥሪዎች በተደራጀ አዃሃን ሲደረጉ ሳይ: አቶ አስገደና የትግራይ ህዝብ ትግል ምን እና ምን ናቸው? አቶ አስገደ የኮነኑትን ትግል እንዴት የገቢ ምንጭ ያደርጉታል? ይህንን ለመመለስ የአቶ አስገደን መፅሃፍ በማጣቀስ በ 3 መሰረታዊ ነገሮች ላይ በማተኮር ሃሳቤን ላቅርብ።ይህ ፁሁፍ ዓረና ይሁን አንድነትን ሳይሆን አቶ አስገደን ብቻ የሚመለከት መሆኑ ልብ ይባልልኝ።

1/ ጋህዲ ቁጥር አንድ ገፅ 34 “ህወሓት በራዛ ዘመቻ ወቅት ከሻዕብያ ያደረገችው ዉል የጊላነት ( የባርያነት ዉል) ነው። ህወሓት የሻዕብያ ባርያ ነበር።” ይላል አስገደ።

ልብ በሉ ይህ ህወሓት የደርግ ዘመቻን በስኬት ያሸነፈበት የ 1968 ዓ.ም ዉል ነው። ህወሓት ያኔ አንድ ዓመት ከጥቂት ወሮች ጨቅላ ድርጅት ሆኖ ታክቲካሊ የደርግን ዘመቻ ለማክሸፍ ከሻዕብያ ማበሩ አስገደ ህወሓት የሻዕብያ አሽከር ነበር ይለናል። ደርግ መደምሰሱ ይቆጨው ይሆን እንዴ።

በዚህ ጦርነት 35 ሺ ጦር ማርከው ህወሓት ደግሞ በርካታ መሳርያና የሰው ሃይል አገኘ፣ በተጨማሪም ህወሓት እንደ ልቡ ወደ ማህል እና ምስራቅ ትግራይ እንዲሄድ ያደረገ ጦርነት ነው። አስገደ ግን ይህን ስኬት ሻዕብያን እንጂ ህወሓትን አልጠቀመም ይላል። 35 ሺ ሚሊሻ ተበትኖ የህወሓት ደጋፊ ነበር የሆነው። ህወሓትን ፕሮሞት ያደረገ ጦርነት ነበር። አስገደ በካደው ትግል ስር ተጠልሎ ህክምና መጠየቁ የሞራል ጥያቄ ያስነሳል።

በዉሉ መሰረት የሚማረክ ከባድ መሳርያ ለሻዕብያ እንዲሆን የተደረገው ህወሓት ትንሽ ሂት ኤንድ ራን የሚከተል ለጋ ድርጅት ከባድ መሳርያ ስራ ላይ ሊያዉልበት የሚችል አቅም ስላልነበረው ለቁመናው የሚጠቅመዉን መሳርያ ነበር የወሰደው። ለአስገደና (ለገብሩ) ይህ የባርያነት መለክያ ነው። ታክቲካል ስምምነት እና ስትራቴጅያዊ ጉዞ አስገደ ቀላቅሎታል። ከባድ መሳርያ ያኔ ህወሓት ብታገኘው ምንም አታረገዉም።

ጥልቅ ፖለቲካዊና ወታደራዊ የስትራቴጂና ስልት ልዩነት የነበራቸው ድርጅቶች አንዱ የአንዱ አስከር ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱ ባርያ ይሄ የኔ ነው፣ ያንተ ስትራቴጂ ለድል አያበቃም ብሎ ደጋግሞ ወቅሶታል። አሽከር ይህን አያደርግም። አስገደ ድምዳሜው ከጥላቻ ወይም ክድንቁርና ብቻ ነው ሊመነጭ የሚችለው። ሻዕብያ ህወሓትን አንድም ቀን በ ትግሉ ዓላማ እንዲህ ብሎ አስገድዶ አስቀይረዋል እሚል ካለ መረጃ ይምጣ።

2. ጋህዲ ቁጥር አንድ በገፅ 87 ሻዕብያ ተኽለአደን በሚባል ፖሊት ቢሮ አባል የህወሓት ሰዎችን በእስርቤት ያሰቃያቸው ነበር፣ ህወሓትም ምንም ተናግራ አታዉቅም ይላል አቶ አስገደ።

ሌላ ይቅር በምርኮኛ አያያዝ ሳይቀር የነበረው ልዩነት የሰማይና የምድር ያህል ነበር። ሻዕብያ ምርኮኛን እንደ ባርያ ስለሚቆጥር ድርጊቱም ከዛ ይመነጭ ነበር፤ ህወሓት ግን ምርኮኛን የጭቁን ገበሬ መደብ ስለሆነ አስተምረን እናሰልፈዋለን ብሎ በርካታ ምርኮኞችን አስተምረን ምርጫ ሰጥተን ነበር የምንለቀው። አስገደ ግን ይህን ክዶ የህወሓት እስረኞች በሻዕብያ እስር ቤቶች ይሰቃዩ ነበር ይላል።

ይህ ሁለት ዉሸት ነው። አንድ የዲሲፒሊን ችግር ያለበት የህወሓት ታጋይ ሲገኝ ወደ ህወሓት የራስዋ ማረምያ ይገባና ተምሮ ይለቀቃል። ስለዚህ ህወሓት የሻዕብያን እስር ቤት ተጠቅሞ አያቅም። ሁለተኛ፥ በጋራ ትግል የተማረኩ የደርግ ወታደሮች ሲጠብቁ የነበሩ የህወሓት እና የ ሻዕብያ ወታደሮች በምርኮኛ አያያዝ ይጋጩ ነበር፤ ሆኖም ሁሌም የህወሓት መንገድ ይመረጥ እንደነበር ራሱ ሻዕብያ ይመሰክራል።

3. ጋህዲ ቁጥር አንድ ገፅ 97 ላይ ደግሞ ህወሓት ጀብሀን የተዋጋው ሻዕብያን ለማዳን ሲል ብቻ ነው” ይላል። ያው የሻዕብያ ተላላኪ ነበርን ለሚለው ተምበርካኪ ድምዳሜ ማጠናከርያ መሆኑ ነው።

ጀብሀ ከመጀምርያ ጀምሮ ህወሓትን ለማጥፋት ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም፤ ከጠራናፊት፣ ከኢድዩ እንዲሁም ከኢህአፓ ሳይቀር ተባብሮ ህወሓትን ለማጥፋት የተንቀሳቀሰ ቀንደኛ ጠላት ነበር። ጀብሀ ምን ያደርግ ነበር ብለን ትንሽ እንይ።

አንድ፥ ዓዲ ዝብአይ፥ የስልጠና ቦታ ነበር (ከአፅረጋ በፊት)። እዚህ ቦታ አስገደ የነበሩትን ሁለት ከብቶች እንዲጠብቁ ይመድባቸዋል። ጀብሀ መጥቶ ታጋዮችን ረሸናቸው። አስገደ በዚህ ግዜ እጅግ በጣም ተናዶ ነበር። ይህ ታሪክ ጉዕሽ ገብረማርያምና ኮሎኔል ይትባረክ ምስክራችን ናቸው። አስገደ ያኔ “ጀብሀ ከደርግ በላይ ጠላታችን ነው” ብሎ በየስብሰባው ተናገረ።

ከዛ ታጋይ አባይ ፀሀየ ይመጣና ያነጋግራቸዋል። በዚህ ስብሰባ አቶ አስገደ አቶ አባይ ፀሀየን በንዴት <እናንተ የፖለቲካ ክፍል ናቹህ ጀብሀን ፊት ሰጥታቹህ እንዲህ እንዲያርደን ያደረጋቹሁት። ጀብሀ እኛን ለማጥፋት ቀን ለሊት እየሰራ እናንተ ዘግይታቹህ አስጨረሳቹሁን< ብሎ ተናገረ።

ሁለት፥ ከአፅረጋ ትንሽ ራቅ ራለ ቦታ ላይ ፀጋየ (ፀጋይ ቆሚጥ) የሚመራው ክርቢቶች ጀብሀ አጥቅቶ ፀጋይ ቆሚጥ ያኔ ነበር እጁን ያጣው። ይህ ጀግና አሁንም በሂወት አለ። ያኔ አስገደ ጀብሀ ወደ አፅረጋ መጥቶ ጥቃት ሊፈፅም እንደሚችል ምክንያቱም ከደርግ በላይ ጠላት እንደሆነ፣ እያሰቸገረን እንደሆነ በመዘርዘር ማድረግ ስለሚገባ ጥንቃቄ መመርያ ሰጥቶ በመፈክር ስብሰባዉን ዘጋው። ያኔ አስገደ ኮሚሳር ነበር።

ሌላ፥ ጀብሀ ከኢህአፓ ጋር በመተባበር ወደ አፅረጋ በመጠጋት ገምሀሎ አካባቢ ህወሓትን ለመደምሰስ የተዋጋ ድርጅት ነው። በፋሲካ ቀን ነበር። እገላ፣ዓይጋ፣ በለሳ፣ ባድመ ላይ የነበረው የህወሓት ቤዝ ለማጥቃትም ከኢህአፓ ጋር በማበር ጥቃት ሰንዝሯል። አስቡት ጀብሀ በራሱ ቀስቃሽነት ነው ወደ ህወሓት ማሰልጠኛና ቤዝ ማእከላት እየመጣ የሚተናኮለን።

ስለዚህ ህወሓት እስኪደመሰስ ዝም ማለት ነበረበት? አስገደ ራሱ በመፅሃፉ የጀብሀ ጥቃት ገልፀዋል። ሆኖም ድምዳሜው ከዘረዘረው እዉነታ ለይቶ ህወሓትን የሻዕብያ ተላላኪ ለማስመሰል ይሞክራል። አስገደ በዛ አሳፋሪ መፅሓፉ የራሱን ቃል ክዶ የትግራይን ህዝብ ትግል ለነፍጠኛ ተረክ ለገበያ ያቀረበ ሰው ነው። ታሪክ አጉድፎ በነፍጠኝነት ስር ተሽጉጦ የዉስጥ አዋቂ በመምሰል ትምክህትን ሲቀልብ ቆይቷል።

ማጠቃለያ

ከላይ በማስረጃ አስደግፈን እንዳየነው አቶ አስገደ ትግሉን በግላጭ ክደዋል። የሻዕብያ ተላላኪ ነበርን፣ አሽከር ነበርን ብሎ የትግራይ ህዝብን ፍትሓዊ ትግል ለገበያ ያቀረበ ሰው ነው፤ ለዛዉም በዉሸት፣ ራስንና አእላፍ ሰማእታትን በመክዳት። እኔም ለዚህ ነው አቶ አስገደ የእርዳታ ጥሪ በካዱት ህዝባዊ ትግል ዛፍ ስር ሆነው መጠየቃቸው ነውረኝነትን አለማወቅ ነው። ጤንነትዎ እንዲመለስ ስንፀልይና ስንተባበር እንደ አባት እንጂ ክደው ለገበያ ባቀረቡት ትግል ምክንያት አይደለም። አቶ አስገደ ትግሉን ክደው ነገዱ፣ ትግሉን ተጠቅመው ደግሞ እየታከሙ ነው። በሁለት ቢላዋ መብላት ማለት ይሄ ነው።

አቶ አስገደ በቁርጥ ሰዓት የደረሰላቸው የሰገዱለት ሀይል ሳይሆን ሲቀር ምን እንደተሰማቸው ለማወቅ እጓጓለሁ። ፈጣሪ ሙሉ ጤንነት ይስጠው።

*********

Guest Author

more recommended stories