Apr 12 2017

የብሔር ፖለቲካ፣ የኢትዮጲያ ታሪክና የመሪዎቿ ተጠያቂነት

“በአንድ ሀገራዊ ጀግና ላይ እንኳን መግባባት ያቅተን?!” ይህ ባለፈው ሳምንት በአንዱ የፌስቡክ ገፅ ላይ ያነበብኩት ነው። በእርግጥ ፅሁፏ አንድ ዓ.ነገር ናት። በጥያቄው ውስጥ የታጨቀው ሃሳብ ግን የአንድ ክፍለ ዘመን ታሪክ ያህል ረጅምና ውስብስብ ነው። ጉዳዩ ከጄ/ል ጃጋማ ኬሎ ሞት ጋር ተያይዞ እንደተነሳ መገመት ይቻላል። በተለይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በአንዱ ወገን በጄ/ል ጃጋማ ሞት የተሰማን ሀዘን መግለፅ የጄ/ል ታደሰ ብሩን መቃብር እንደመቆፈር ተቆጠረ። በሌላ ወገን ያሉት ደግሞ የጃጋማን ጀግንነት ለማድነቅ የጄ/ል ታደሰ ብሩን እና የዋቆ ጉቶን ታሪክ ማጣጣል ጀመሩ። ይህን ተከትሎ እንደተለመደው ሰሞኑን “የባንዳ እና ሽፍታ” ፖለቲካ ተጧጧፈ።

እንኳን በቀድሞ የጦር መሪ በሀገራችን መሪዎች ላይ እንኳን በጋራ መግባባት አልቻልንም እኮ! ለምሳሌ፣ አፄ ዩሃንስ፣ አፄ ሚኒሊክ እና ጄ/ል ጃጋማ ኬሎ፣ በቅደምተከተላቸው መሰረት የሀገር ሉዓላዊነትን፣ አንድነትን እና ሥርዓትን ከማስከበር አንፃር የነበራቸው የመሪነት ሚና በአረዓያነት የሚጠቀስ ነው። ነገር ግን፣ በሀገር ሉዓላዊነትና፣ አንድነት እና ሥርዓት ሰበብ በንፁሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ በደል፣ ጭቆና እና ክህደት ተፈፅሟል። በዚህ ፅሁፍ እነዚህን መሪዎች በምሳሌነት በመውሰድ ከሀገሪቱ ታሪክ፣ ከነበራቸው ሚና እና አሁን ካለው ፖለቲካዊ አለመግባባት ጋር አያይዘን በዝርዝር እንመለከታለን።

በመጀመሪያ ደረጃ ከሦስቱ መሪዎች ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚነሱ ሁለት ተፃራሪ ሃሳቦችን ለማሳያ ያህል ወስደን እንመልከት፡- 1ኛ) አፄ ዩሃንስ “የግብፅ ተደጋጋሚ ወረራ በመመከት የኢትዮጲያን ሉዓላዊነት አስከብረዋል” – “የወሎ ሙስሊሞችን እጅ ቆርጠዋል”፣2ኛ) አፄ ሚኒሊክ “የኢትዮጲያን አንድነት በማረጋገጥ ሀገሪቱን ከቅኝ-ገዢ ኃይሎች ተከላክለዋል” – “በአኖሌ የእናቶችን ጡት ቆርጠዋል”፣3ኛ) ጄ/ል ጃጋማ ኬሎ “ፋሽት ኢጣሊያን የተጋሉ ብሔራዊ ጀግና ናቸው” – “ጄ/ል ታደሰ ብሩን አሳልፈው የሰጡ ከሃዲ ናቸው”

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የሦስቱ መሪዎች ስም በተነሳ ቁጥር አንዱ ወገን “ጥሩ” ሥራቸውን በማጉላት “መጥፎ” ሥራቸውን ያጣጥላል። ሌላኛው ወገን ደግሞ “መጥፎ” ሥራቸውን በማጉላት “ጥሩ” ሥራቸውን ያጣጥላል። በአጠቃላይ፣ የቀድሞ መሪዎች ስም ሲነሳ ያለቅጥ የተጋነነ ሙገሳና አድናቆት ወይም ቂምና ጥላቻ የታጨቁ ቃላት እርስ-በእርስ እየተወራወሩ መለጣጠፍ የተለመደ ተግባር ሆኗል።

በእርግጥ በቀድሞ መሪዎች ሚና እና በታሪካዊ ክስተቶች ዙሪያ የተለያየ አቋምና አመለካከት መኖሩ በራሱ እንደ ችግር ሊወሰድ አይገባም። ሁሉም ታሪካዊ ክስተቶች “ጥሩ እና መጥፎ”፣ የሀገሪቱ መሪዎችም “ባንዳ እና ሽፍታ” ተብለው በጅምላ የሚፈረጁ ከሆነ ግን በጣም አሳሳቢ ነው። በመሰረቱ፣ የሰው ልጅ ሕይወትንና የሀገር ታሪክን እንዲህ በጅምላ መፈረጅ የመንጋ አስተሳሰብ ነው።

Photo - Emperor Yohannes, Emperor Menilik, Gen. Tadesse Biru, Gen. Jagama Kelo (Left to right, clockwise)

የብሔር ፖለቲካና የኢትዮጲያ ታሪክ

“Jose Ortega y Gassett” የተባለው ታዋቂ ምሁር “The Revolt of the Masses” በተሰኘው መፅሃፉ ይህ አስተሳሰብ በዋናነት ፖለቲካዊ አብዮትን ተከትሎ የሚከሰት ማህበራዊ ቀውስ እንደሆነ ይገልፃል። አብዮቱን ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጣው የፖለቲካ ኃይል የራሱን ቅቡልነት ለማረጋገጥ የቀድሞው ሥርዓት በሀገሪቱ ታሪክና በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ ያለውን ሚናና አስተዋፅዖ ያለ ማቋረጥ በመጣጣሉ፣ እንዲሁም በዕውቀት ላይ ከተመሰረተ ግንዛቤና አመለካከት ይልቅ ጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ በማበረታታቱ ምክንያት የሚፈጠር ማህበራዊ ቀውስ ነው። ለምሳሌ፣ ምዕራባዊያን በ18ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ በምዕራብ አውሮፓ ሀገራትና በአሜሪካ የተካሄደውን የፖለቲካ አብዮት ተከትሎ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ለተመሣሣይ ችግር ተጋልጠው ነበር።

ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን በኢትዮጲያ የተዘረጋው የብሄር ፖለቲካ ሀገሪቱን ለተመሣሣይ ቀውስ ዳርጓታል። በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በሕዝብ ዘንድ ያለውን ቅቡልነት ለማረጋገጥ በሚያደረገው ያላሳለሰ ጥረት የቀድሞ ሥርዓትና መሪዎች በሀገሪቱ ታሪክና በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ የነበራቸውን ሚና እና አስተዋፅዖ አሳጥቷቸዋል። በዚህ ምክንያት፣ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ በሀገሪቱ ታሪክና የቀድሞ መሪዎች ዙሪያ የጋራ መግባባት እንዳይኖር አድርጓል። የብሔር ፖለቲካን ያለ ቅጥ በማጦዝ የብሔር ፅንፈኝነትን እያስፋፋ እና ለሉዓላዊነትና ነፃነት የታገሉ ብሔራዊ ጀግኖችን እየገፋ በመሄዱ ሀገራዊ መግባባትና የአንድነት ስሜት ከሕብረተሰቡ ውስጥ ተሟጥጦ በማለቅ ላይ ይገኛል።

ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን በኢትዮጲያ የተዘረጋው የብሄር ፖለቲካ ሀገሪቱን ለተመሣሣይ ቀውስ ዳርጓታል። በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በሕዝብ ዘንድ ያለውን ቅቡልነት ለማረጋገጥ በሚያደረገው ያላሳለሰ ጥረት የቀድሞ ሥርዓትና መሪዎች በሀገሪቱ ታሪክና በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ የነበራቸውን ሚና እና አስተዋፅዖ አሳጥቷቸዋል። በዚህ ምክንያት፣ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ በሀገሪቱ ታሪክና የቀድሞ መሪዎች ዙሪያ የጋራ መግባባት እንዳይኖር አድርጓል።

የብሔር ፖለቲካን ያለ ቅጥ ሲጦዝ የብሔር ፅንፈኝነትን እያስፋፋና ብሔራዊ ጀግኖችን እያጠፋ መሄዱ እርግጥ ነው። ነገር ግን፣ አሁን ያለው የብሄር ፖለቲካ የችግሩ መሰረታዊ መንስዔ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ምክንያቱም፣ ሀገራዊ አለመግባባቱ በስፋት የሚስተዋለው ከወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ይልቅ በሀገሪቱ ታሪክና የቀድሞ መሪዎች ዙሪያ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ የብሄር ፖለቲካ በራሱ ከሀገሪቱ ታሪክና መሪዎች ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። ስለዚህ፣ የችግሩ መሰረታዊ መንስዔ ለመረዳት ከወቅታዊ ፖለቲካ ይልቅ በቀድሞ የሀገራችን ታሪክና መሪዎች ሕይወት ዙሪያ ማተኮር ይኖርብናል። በተመሣሣይ፣ “Jose Ortega y Gassett” የችግሩ መሰረታዊ መንስዔ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ስለ ሀገር ታሪክና የመሪዎች ሕይወት ያለው የተዛባ ግንዛቤና አመለካከት እንደሆነ እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፡-

“All the features of the present day, and in particular the rebellion of the masses, offer a double aspect. Any one of them not only admits of, but requires, a double interpretation, favourable and unfavourable. …On the contrary, I believe that all life, and consequently the life of history, is made up of simple moments, each of them relatively undetermined in respect of the previous one, so that in it reality hesitates, walks up and down, and is uncertain whether to decide for one or other of various possibilities. It is this metaphysical hesitancy which gives to everything living its unmistakable character of tremulous vibration.” The Revolt of the Masses, CH_IX, Page 51

ሁሉም ሰው ለራሱ ትክክል ነው

በመሰረቱ፣ አንድ ተግባር “ጥሩ” ወይም “መጥፎ” የሚሆነው በራሱ ትክክል ወይም ስህተት ስለሆነ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ጥሩነት ወይም መጥፎነት የሚወሰነው ከተግባሩ አግባብነት አንፃር ነው። አግባብነት ያለው ተግባር (expedient) መደረግ ባለበት ሁኔታ ውስጥ የተደረገና ተቀባይነት እና ጠቀሜታ ያለው ነው። በዚህ መሰረት፣ መደረግ ባለበት ሁኔታ ውስጥ የተደረገ ተግባር ትክክል (right) ስለሆነ ጥሩ (good) ነው። አግባብነት የሌለው (inexpedient) ደግሞ ስህተት (wrong) እንደመሆኑ መጥፎ (bad) ነው።

ስለዚህ፣ ስለ ቀድሞ መሪዎች ጥሩነት ወይም መጥፎነት መናገር ከመጀመራችን በፊት በቅድሚያ በዘመናቸው የፈፀሟቸውን ተግባራት ትክክለኝነት ወይም ስህተትነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ነገር ግን፣ አንድን ተግባር “ትክክል” ወይም “ስህተት” ለማለት ደግሞ ከተፈፀመበት ግዜ፣ ቦታና ምክንያት አንፃር አግባብነቱን ማጤን ያስፈልጋል።

አንድን ተግባር ከቦታ፥ ግዜና ምክንያት አንፃር አግባብነቱን ለማጤንና “ትክክል” ወይም “ስህተት” መሆኑን በመወሰኑ ሂደት ውስጥ ብዙ አማራጮች ይኖራሉ። ትክክለኛ እና ስህተት የሆኑ ተግባራት በግልፅ ተለይተው አልተቀመጡም። በመሆኑም፣ ሰው አንድን ተግባር የሚፈፅመው ካለበት ቦታና ግዜ አንፃር፣ እንዲሁም በራሱ ምክንያታዊ ግንዛቤ መሰረት አግባብ ስለሆነ ነው።

በዚህ መሰረት፣ እያንዳንዱ ግለሰብ በተወሰነ ግዜና ቦታ በራሱ ግንዛቤ መሰረት የሚፈፅመው ተግባር ቢያንስ ለራሱ “ትክክል” ነው። ነገር ግን፣ ከቅፅበት በኋላ ለራሱም ሆነ ከሌሎች ሰዎች እይታ አንፃር ስህተት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ፣ ተግባሩን በሚፈፅምበት ቅፅበት ግን ከሁኔታውና ከግንዛቤው አንፃር ቢያንስ ለራሱ ትክክል ነበር። ማንኛውም ሰው አንድን ተግባር የሚፈፅመው በራሱ አመለካከት ተገቢና ትክክል ስለሆነ ነው። ሰው በቦታውና በሰዓቱ ትክክል አለመሆኑን እያወቀ ስህተት አይሰራም። ምክንያቱም፣ አውቆና ፈቅዶ ስህተት መስራት ከምክንያታዊ አስተሳሰብ ጋር አብሮ አይሄድም። በራሱ አውቆና ፈቅዶ ስህተት የሚሰራ ሰው ተግባርና እንቅስቃሴውን መቆጣጠር የማይችል ከሆነ ብቻ ነው።

በአጠቃላይ፣ የአንድን ተግባር ትክክለኝነት ወይም ስህተትነት መወሰን ከውጪ ሆኖ “ጥሩ” ወይም “መጥፎ” ብሎ እንደመፈረጅ ቀላል አይደለም። ስለ ሌላ ሰው ተግባር ያለን አመለካከት ከቦታ፥ ግዜና ምክንያት አንፃር ባለን ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም፣ ተግባሩ ስለተፈፀመበት ቦታ፥ ሰዓትና ምክንያት ያለን ግንዛቤ እየጨመረ በሄደ ቁጥር የግለሰቡ ተግባር ይበልጥ “ትክክል” ይመስለናል። በተቃራኒው፣ ተግባሩ ስለተፈፀመበት ቦታ፥ ሰዓትና ምክንያት ያለን ግንዛቤ እየቀነሰ በሄደ ቁጥር የግለሰቡ ተግባር ይበልጥ “ስህተት” ይመስለናል። የአንድን ሰው ተግባር ከቦታ፥ ግዜና ምክንያት አንፃር ምሉዕ የሆነ ግንዛቤ ሊኖረን የሚቻለው የዚያን ሰው አከባቢያዊ፣ አካላዊና መንፈሳዊ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ መገንዘብ ስንችል ነው። በዚህም፣ ግለሰቡ ራሱን በአካልና በመንፈስ መሆን የሚጠይቅ ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ ቀድሞ ግለሰቡ የፈፀመውን መልሶ ከመድገም ሌላ ምርጫ የለንም።

የቀድሞ መሪዎች ተጠያቂነት

ቀደም ሲል የሰዎችን ተግባር “ጥሩ” ወይም መጥፎ” ብሎ ለመፈረጅ በቅድሚያ ከተፈፀመበትን ቦታ፥ ግዜና ምክንያት አንፃር መታየት እንዳለበት ተገልጿል። ለምሳሌ፣ ባለፈው ሳምንት ከአህያ ቄራ መከፈት ጋር ተያይዞ በሀገራችን የአህያ ስጋን መብላት ተቀባይነት የለውም በሚል “አህያ የጅብ ናት” ሲባል ነበር። ነገር ግን፣ በአስገዳጅ ሁኔታ (necessity) ውስጥ እንኳን አህያን ጅብን መብላት በራሱ ተቀባይነት ሊኖረው እንደሚችል “ጅብ ከሚበላኝ ጅብ በልቼ ልጠመቅ” ከሚለው አባባል መገንዘብ ይቻላል። በተመሳሳይ፣ በየትኛውም ሕግ ሰውን መግደል ተቀባይነት የሌለው ተግባር ቢሆንም ሊገድል የመጣን ሰው በአልሞት-ባይ ተጋዳይነት መግደል ግን ተቀባይነት አለው።

በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ የሚፈፀም ተግባር አግባብነቱ የሚመዘነው በአይቀሬ ሕግ (laws of inevitability) ነው። ምክንያቱም፣ “ማንኛውም ሰው በተመሳሳይ ቦታ፥ ሰዓትና ምክንያት ውስጥ ቢሆን ያንኑ መድገሙ አይቀሬ (inevitable) ነው” ተብሎ ይታሰባል። በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ያለ ሰው ያደረገውን ከማድረግ ውጪ ሌላ ምርጫና አማራጭ የለውም። ስለዚህ፣ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የፈፀመው ተግባር አግባብና “ትክክል” ነው። ሆኖም ግን፣ አስገዳጅ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ በራሱ ፍቃድ (free will) የሌሎችን ሰዎች ነፃነት የሚፃረር ተግባር መፈፀም ግን “ስህተት” ነው።

በዚህ መሰረት፣ በታሪክ የተፈፀሙ ተግባራትን “ትክክል” ወይም “ስህተት” ከማለታችን በፊት ተግባራቱ የተፈፀሙት በአስገዳጅ ሁኔታ ወይስ በመሪዎቹ ፍቃድ የሚለውን ከግዜ፣ ቦታና ምክንያት አንፃር ጠንቅቀን ማወቅ ይኖርብናል። በዚህ ፅሁፍ መግቢያ ላይ በማሳያነት የተጠቀሱት የቀድሞ መሪዎች ተግባራት ከ50 ዓመት በፊት የፈፀሙ ናቸው። ከወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ተያይዘው እየተነሱ ለአለመግባባት ምክንያት ይሁኑ እንጂ አግባብነታቸው መታየት ያለበት ከታሪክ አንፃር ነው። ስለዚህ፣ የቀድሞ መሪዎች እነዚህን ተግባራትን የፈፀሙት በአስገዳጅ ሁኔታ (necessity) ወይም በራሳቸው ፍቃድ (free will) ስለመሆኑ መወሰንና የተግባራቱን ትክክለኝነት እና ስህተትነት መለየት የሚቻለው በታሪክ ፍልስፍና መርህ መሰረት ነው። በዚህ ረገድ ፈር-ቀዳጅ የሆነው ልሂቅ ¨Leo Tolstoy” ሲሆን ፅንሰ-ሃሳቡን እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-

“In the experimental sciences what we know we call the laws of inevitability, what is unknown to us we call vital force. Vital force is only an expression for the unknown remainder over and above what we know of the essence of life. …So also in history what is known to us we call laws of inevitability, what is unknown we call free will. Free will is for history only an expression for the unknown remainder of what we know about the laws of human life.” War And Peace, EP2|CH10, Page 1193

ከላይ እንደተገለፀው፣ የቀድሞ መሪዎች በታሪክ የፈፀሟቸው ተግባራት በሙሉ በአስገዳጅ ሁኔታ (necessity) ውስጥ የተፈፀሙ እንደመሆናቸው አግባብና ትክክል ናቸው። ከዚህ በተቃራኒ፣ እነዚህ ተግባራት በቀድሞ መሪዎች ነፃ ፍቃድ (free will) የተፈፀሙ ማሰብ፣ እንደ “Leo Tolstoy” አገላለፅ፣ ከቦታ፥ ግዜና ምክንያት አንፃር ያለን ግንዛቤ ውስን ስለመሆኑ በራሳችን ለይ ከመመስከር ሌላ ትርጉም የለውም።

በዚህ ፅሁፍ በማሳያነት የተጠቀሱት፣ አፄ ዩሃንስ፣ አፄ ሚኒሊክ እና ጄ/ል ጃጋማ ኬሎ በመሪነት ዘመናቸው የፈፀሟቸውን ተግባራት ከግዜ፥ ቦታና ምክንያት አንፃር ሲታዩ ሁሉም በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ የተፈፀሙ ናቸው። ለምሳሌ፣ አፄ ዩሃንስ፡- “የግብፅን ተደጋጋሚ ወረራ በመመከት የኢትዮጲያን ሉዓላዊነት ማስከበራቸው”፣ አፄ ሚኒሊክ “የኢትዮጲያን አንድነት በማረጋገጥ ሀገሪቱን ከቅኝ-ገዢ ኃይሎች መከላከላቸው”፣ እንዲሁም ጄ/ል ጃጋማ ኬሎ “የፋሽት ኢጣሊያን ጦር ለአምስት አመት በፅናት መፋለማቸው” አግባብነት ያላቸው ተግባራት ናቸው። ምክንያቱም፣ በወቅቱ የግብፅ ወረራ በኢትዮጲያ ሉዓላዊነት ላይ፣ የቅኝ-ገዢ ኃይሎች በሀገሪቷ አንድነት ላይ፣ እንዲሁም የጄ/ል ታደሰ ብሩ ሴራ በመንግስታዊ ሥርዓቱ ላይ የሕልውና አደጋ ተጋርጦ ነበር። በሕልውና ላይ የተቃጣ ጥቃት ደግሞ ፍፁም አስገዳጅ (necessity) ነው። በአይቀሬ ሕግ (laws of inevitability) መሰረት፣ የራስን ሕልውና ለመታደግ የሚፈፀም በማንኛውም ተግባር ትክክል ነው። በእንዲህ ያለ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ሌሎችን ሕልውና በማሳጣት የራስን ሕልውና መታደግ ተቀባይነት አለው።

ነገር ግን፣ በሀገር ሉዓላዊነት፣ አንድነትና ሥርዓት ላይ የተጋረጠውን የሕልውና አደጋ በማስወገድ ሂደት ውስጥ በንፁሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ በደል፣ ጭቆና እና ክህደት ተፈፅሟል። ለምሳሌ፣ አፄ ዩሃንስ ከግብፅ ጋር አሲራችኋል በሚል ሰበብ “የወሎ ሙስሊሞችን እጅ ቆርጧል”፣ አፄ ሚኒሊክ የሀገር አንድነትን ለማረጋገጥ በሚል “በአኖሌ የእናቶችን ጡት ቆርጧል”፤ እንዲሁም ጄ/ል ጃጋማ ኬሎ “የፊውዳሉ ሥርዓትን ለመታደግ ጄ/ል ታደሰ ብሩን አሳልፎ በመስጠት በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ክህደት ፈፅሟል።”

በመሰረቱ፣ በአፄ ዩሃንስ ዘመን በሀገሪቱ ሉዓላዊነት ላይ የሕልውና አደጋ የተጋረጠው በግብፅ ጦር እንጂ በወሎ ሙስሊሞች ወረራ አልነበረም። በአፄ ሚኒሊክ ዘመን በሀገሪቱ አንድነት ላይ የሕልውና አደጋ የተጋረጠው በአውሮፓ ቅኝ-ገዢዎች አንጂ በአርሲ ኦሮሞዋች አልነበረም። እንዲሁም፣ ጄ/ል ታደሰ ብሩ በዘውዳዊው ሥርዓት ላይ ያሴረው ለኦሮሞ ሕዝብ እኩልነትና ነፃነት እንጂ ለግል ጥቅሙ አልነበረም።

ስለዚህ፣ ምንም እንኳን በሀገር ሉዓላዊነት፥ አንድነትና መንግስታዊ ሥርዓት ላይ የሕልውና አደጋ ተጋርጦ የነበረ ቢሆንም በዚያ ሰበብ አሰቃቂ በደል፥ ጭቆና እና ክህደት የተፈፀመው ግን ለአደጋው መንስዔ ባልሆነ የሕብረተሰብ ክፍል ላይ ነው። ይህ ደግሞ በማንኛውም አግባብ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። ይህን እንቆቅልሽ የሚፈታው ብቸኛ የሞራል ሕግ “Immanual Kant” እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-

“‘Necessity has no law’. And yet there cannot be a necessity that could make what is wrong lawful.” The Science of Right, tran. W. Hastie CH1, Page 6

በሕልውና ላይ የተቃጣን ጥቃት በሞራል ሆነ በሕግ መዳኘት አይቻልም። ምክንያቱም፣ ሕልውናን ማጣት በየትኛውም ደንብ ሊጣል ከሚችለው ቅጣት ይበልጣል። በዚህ መሰረት፣ ከላይ የተጠቀሱት የቀድሞ መሪዎች ተግባራት በሀገር ሉዓላዊነት፣ አንድነትና ሥርዓት ላይ የተቃጣውን የሕልውና አደጋ ለመከላከል የፈፅሟቸውን ተግባራት “ስህተት” ማለት አይቻልም። በተመሣሣይ፣ በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈጸሙት አሰቃቂ በደሎች፥ ጭቆናዎች እና ክህደቶች “ትክክል” ሊሆኑ አይችሉም።

በአጠቃላይ፣ በቀድሞ መሪዎች የተፈፀሙ ተግባራትን “ትክክል” ወይም “ስህተት” ብሎ ለመፈረጅ የሚያስችል ምንም ዓይነት የሞራል ሕግ የለም። በዚህ ላይ የጋራ ግንዛቤ እስካልተፈጠረ ድረስ በሀገራችን ታሪክ እና በቀድሞ መሪዎቻችን ዙሪያ ሀገራዊ መግባባት ሊኖር አይችልም።

***********

Source: HornAffairs.com
ይህን ጽሑፍ ወስደው ሊያትሙ ቢሹ፤ የሆርን አፌይርስን እና የፀሐፊውን ስም በግልጽ መጥቀስ እና የዚህን ፖስት Link ማስቀመጥ ይገባል፡፡

7 Comments
 1. aschenaki

  ሁላችንም በጋራ በእኩል የምናከብራዉ ጅግኖችን ማፍራት አለመቻላችን በጣም አሳዛኝ ነገር ነዉ፡፡እኔ የአጼ ቴዎድሮስን፤አጼ ዮሃንስንና አጼ ምንሊልክን የሀገር ዉሌታ በዘር መነጽር ማዬት ስንጀምር ታላቅነታቸዉ ጎልቶ የሚታየን የብሄራችን ተወላጅ ለሆኑ ብቻ ከሆነ መቼም ቢሆን የጋራ ጀግና ልናፈራ አንችልም፡፤ታላላቅ መሪዎችን ስናወሰድስ አንዳችም እንከን አልነበራቸዉም በሚል እሳቤ ሊሆነ አይገባዉም፡፤ ነግርግን ዮሀንስ ስህተት ሲነገር የትግራይ ተወላጆች ብቻ የሚቆጡ ከሆነ ሚኒልክ በበጎ ሲነሱ ኦሮሚኛ ተናጋሪዉ የሚከፋዉ ከሆነ አስቸጋሪ መሆኑ የግድ ነዉ፡፤ ጀግኖቻችንን ለመምረጥም በዘርና በብሄር መነጽር ማየት የትም አያደርሰንም፡፡ጄ/ል ጃካማ ኬሎን የሚያወገዙት ጄ/ል ታደሰ ብሩን አሳልፈዉ ስለሰጡ ዋቆ ጉቱን በማሳደዳቸዉ የኦሮሞን እንደከዱ ተደርጎ በመቁጠር ከሆነ ትልቅ ስህተት ነዉ፡፡ ፤ምኒሊክ በደቡብና በሀረር ህዝብ ላይ የሰሩትን ጥፋት በይቅርታ ያለፍን ሰዎች አርሲ ላይ ሰሩት የተባለዉ ጥፋት ለብቻ ተለይቶና ተጋኖ ይነገራል፡፤ ስለዚህ ምኒሊክ ለአንዱ ጀግና ለሌላዉ ወንጀለኛ ሆነዉ መቅረብ የግድ ሆኗል፡፡አብዲሳ አጋን ኃይለስላሴም መንግስቱ ኃይለማሪምም ሁለቱም ተገቢዉን ክብር ሳይሰጡት ያለፈ የመላዉ ጥቁር አፍራካ ህዝቦች አርበኛ ነዉ፡፤ በላይ ገብረአብ የተባለዉ የጥቁር አንበሳ ጀግና ለሱ የመታሰቢያ የቆመለት ሀዉልት ቢኖርም ስሙ በሚገባ አይነሳም፡፤ ያለፉ መሪዎችን ከሰሩት ግዙፍ ስራ ይልቅ ጥፋታቸዉን የማጉላት አባዜ አለብን፡፤ መለስ ዜናዊ እንደ ግለሰብና አንደ መሪ የሰሩት ስህተት ቢኖር የሚያስደንቅ አይደለም፡፤ነገር ግን በጥቂት ስህተቶቻቸዉ ምክንያት ለሀገሪቱ የሰሩት ወደር የለሌዉ ዉሌታ ወደ ጎን ተደርጎ ሃጥያታቸዉ ብቻ ጎልቶ እንዲወጣ በማድረግ በታሪክ ሊኖራቸዉ የሚገባዉ ክብር ለመንፈግ እንሞክራለን፡፡መለስ መከበርና መወደስ ያለባቸዉ በትገርኛ ተናጋሪዉ ብቻ እንደሆነ አድርገን እናባለን፡፡ስለዚህ መሪዎቻችንንና ጅኖቻችንን በብሄር መነጽር ማየት አቁመን እኩል ክብር እንስጣቸዉ፡፡ ጃኬማ የመላዉ ኢትዮጵዉያን ጀግና እንጂ የአንድ ህዝብ ብቻ አይደሉም፡፡ድንቅ ከተባለላቸዉ የአለም መሪዎች መካከል እንከን አልባ የሆነ አንድም መሪ የለም፡፡የሰዎች ስራ መመዘን ያለበት በአንጻራዊነት ነዉ፡፡ዛሬ ስለመሪዎቻችን ብቻ ሳይሆን ስለ ሀገራችን ታሪክ ለመናገር ከብሄር መነጽር ዉጭ አስቸጋሪ እየሆነ ነዉ፡፡ስለዚህ ልጆቻችንን ለማስተማር ቀርቶ ራሳችንም በእርግጠኝነት መናገር የምንችለዉ ታሪክ እያጣን ነዉ፡፡ስለ የትኛዉም ያለፈ ታክ ኩኔት ለመናገር በራስ መተማመን የለንም፡፡ ግራ ገባዉ ነገር ነዉ፡፡፡

 2. Mamush Daniel

  “………. እንዲሁም ጄ/ል ጃጋማ ኬሎ “የፊውዳሉ ሥርዓትን ለመታደግ ጄ/ል ታደሰ ብሩን አሳልፎ በመስጠት በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ክህደት ፈፅሟል…..”

  ከጽሁፉ የተወሰደው ይህ አባባል ጠንጋራ አባባል ነው። የታደሰ ብሩ አልፎ መሰጠት የሚባለው ጉዳይ ሃቅነት ካለው ታደሰ ብሩ በኢትዮጵያ ላይ ምሴራ ሸረበ ብሎ ጉዳዩን ማየት ተገቢ ነው…. በሶማሊው የዚያድ ባሬ ጦርነት ወቅት በኢትዮጵያ ጦር ውስጥ ሆነው የኢጥዮጵን ጦር የሚወጉ፣ አዋጊዎችን የሚገድሉ የኢሕአፓ አባላት ነበሩ። ይህ ጉዳይ ለኢሕአፓ የራሱ የሆነ ጥቅም አለው ቢባልም ጠቅላላ ውጤቱ ከኢሕአፓ ይልቅ የሶማን ወረራ የመኒጠቅም ነበረ….. የዃላ ዃላ ወታሮች እነዝን የኢሕአፓ ሰርጎ ገቦች አጋልተዋቸዋል…. አጋላጮቹ ከሀዲ ሊባሉ ነውን?

 3. aschenaki

  ወንድሜ ማሙሸት ሆይ!ጃኬማ ኦሮሞ ሆነዉ ሳለ ኦሮሞዉን ታደሰን መያዛቸዉ የሚያመለክተዉ ኦሮሞነታቸዉን መካዳቸዉን ሳይሆን ምርጥ ወታደር መሆናቸዉን ነዉ::ጥፋት ያጠፋ በራሱ ብሄር ተወላጅ ሊያዝ አይገባዉም እየተባለ ከሆነ አያስከድም::ዋቆ ጉቱም ቢሆን ኦሮሚያን ለዚያድ ባሬ ለመሸጥ ሲያስማማ የነበረ ነዉ::ለማንኛዉም እንደ ጃኬማ ያለ የጀግና ጀግና በታደሰ ብሩና በዋቆ ጉቱ ምክንያት መወቀስ አዬገባቸዉም::የጥሩ ወታደር ተግባር ስርአቱን(ሀገሪቱን) መጠበቅ እንጂ ስርአቱን መቀየር አይደለም::ትላንትም ዛሬም ነገም የማይለወጥ መሪህ!

 4. subiwalal

  wako gutu fiwudalawiwun bemekawem sishefitu enji etiyopian lebaiddi zeyid bare lemeshet yedoletu alneberum. gobez general taddesem hagerin lishet yetezegaje adirgeh yakerebkew haset newu yihi yetsere oromo hayiloch fetera tera wushet dirama newu . Behagerachin yepoletika tarik wust sile oromo hulu sinnesa yetiyopiya afrirah tedergo mayetu yasazinal.

 5. aschenaki

  Wako was kown not for his struggle against the feudal system but by his support for ziadbare.tadese,s cause is different. he was struggling for oromo people right but unforunatelly his dream was hijaked by narow minded indivisuals and ended by founding the terrorist group OLF.so jakama was true oromo than wako and the most respected and praised ethiopian..finally who ever he is oromo, tigre wolayta ,amhara if voiced and fought for dismantlling ethiopia he is enemy of people.

 6. aschenaki

  Wako was known not for his struggle against the feudal system but by his support for ziadbare. tadese,s cause is different. he was struggling for oromo people right but unforunatelly his dream was hijaked by narow minded indivisuals and ended by founding the terrorist group OLF.so jakama was true oromo than wako and the most respected and praised ethiopian..who ever he is oromo, tigre wolayta ,amhara if voiced and fought for dismantlling ethiopia he is enemy of people.

 7. guest

  poorly written and fictional/political narratives with no evidence used as premise to draw your conclusions. I feel for the students you teach. There is evidence for how Atse Yohannes treated muslims. How ever this is not evidence about the Anole and General jagema. As a student/practitioner of ethnic politics, you take your unfounded fiction as facts.