የቆሼው አደጋ በዴሞክራሲ እጦት ምክንያት የተከሰተ ነው

ሰው ሟች ነውና ሁላችንም እንሞታለን። ሞት ለሁሉም እኩል ነው፣ አሟሟታችን ግን ለየቅል ነው። በአንድ ተፈጥሯዊ አጋጣሚ ያገኘነውን ሕይወት በሌላ ተፈጥሯዊ አጋጣሚ ማጣታችን እርግጥ ነው። ለምሳሌ፣ የሰው ልጅ እድሜ ዘመኑን ጨርሶ፥ በበሽታ ታሞ፣ በድንገተኛ የጎርፍ አደጋ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፥ መሸራተት፥ መናድ፣ እና በመሳሰሉት ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ሕይወቱን ሊያጣ ይችላል። ነገር ግን፣ ሰው እንዴት የቆሻሻ ክምር ተንዶበት ይሞታል?

ይህ ነጋሪ ሆነ ለቀባሪ የማይመች አሟሟት ምን ይሉታል፡ ተፈጥሯዊ ወይስ ሰው-ሰራሽ አደጋ? “ተፈጥሯዊ” እንዳይሉት ቆሻሻው ሰው-ሰራሽ ክምር ነው፤ “ሰው-ሰራሽ” እንዳይሉት ቆሻሻው የተናደው በሰው አይደለም። ሰዎቹ ከቆሻሻው ስር የተገኙት በአጋጣሚ ነው እንዳይባል ዘወትር የሚኖሩበት ወይም የሚሰሩበት ቦታ ነው። የሟቾች የመኖሪያና መስሪያ ቦታ ከቆሻሻው ስር ነው እንዳይባል ደግሞ አንደ ሁላችንም ከቆሻሻ የፀዳ አከባቢ መኖርና መስራት የሚሹ ሰዎች ናቸው።

ነገሩ ለብዙዎች ግራና ግር የሚል ነው። የአዲስ አበባንና የኦሮሚያን ፖለቲካ በቅርበት ለሚከታተሉ ሰዎች ግን ነገሩ ቀጥተኛና ግልፅ ነው። ምክንያቱም፣ ባለፉት ጥቂት አመታት በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ባሉ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ከቆሻሻ ጋር በተያያዘ ያጋጠማቸውን ችግር እና በሁለቱ መስተዳደሮች መካከል የነበረውን ፍጥጫ በቅርበት ሲከታተል ለነበረ ሰው ከትላንት በስቲያ ስለ ደረሰው አደጋ ምንነትና ምክንያት በእርግጠኝነት መናገር ይችላል። አዎ…በረጲ (ቆሼ) የቆሻሻ ማስወገጃ አከባቢ የደረሰው አደጋ “የዴሞክራሲ አደጋ” ሲሆን የአደጋው መንስዔው የዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት እጦት ነው።

Photo - Landslide at Addis Ababa Qoshe Landfill, March 12, 2017
Photo – Landslide at Addis Ababa Qoshe Landfill, March 12, 2017

አንዳንዶቻችሁ “ለራስህ የሀዘን ስሜት፣ ለወዳጅ-ዘመድ ደግሞ መፅናናትን መመኘት ሲገባህ፣ ይህን አሰቃቂ ክስተት እንዴት “የዴሞክራሲ አደጋ” እያልክ ታሾፋለህ?” እንደምትሉ መገመት ቀላል ነው። ነገር ግን፣ የሀዘን ስሜት ስለ አደጋው ምንነትና ምክንያት እንዳናውቅ ሊያደርገን አይገባም። ከዚህ በመቀጠል በረጲ (ቆሼ) የቆሻሻ ማስወገጃ አከባቢ የደረሰው “የዴሞክራሲ አደጋ” ምንነትና ምክንያትን በማስረጃ አስደግፌ በዝርዝር ለማስረዳት እሞክራለሁ።

በእርግጥ አዲስ አባባ ገና ከአመሰራረቷ ጀምሮ በዙሪያዋ ካለው የኦሮሞ ማህብረሰብ ጋራ የነበራት ግንኙነት ኢፍትሃዊ ነበር። በዚህ ላይ “ማስተር ፕላን፡- የችግሩ መነሻና መጨረሻ” በሚለው ፅሁፌ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ ስጥቼበታለሁ። ከቆሻሻ ማስወገድ ጋር በተያያዘ የተከሰተው ችግር የዚሁ ነፀብራቅ ነው፡፡ 

የአዲስ አበባ መስተዳደር በሰንዳፋ የተገነባው የቆሻሻ ማስወገጃ ቦታን ለግንባታ ከመረከቡ በፊት፤ የቦታ መረጣ (Site Selection)፣ የአከባቢ እና አዋጭነት ጥናቱን (Physical and Feasibility study) ያደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና “Horn of Africa Regional Environmental Center and Network” (HOARE&N) በጋራ ሆነው ነው። በመሰረቱ፣ እንዲህ ዓይነት የግንባታ ፕሮጀክት ቦታ መረጣና የአዋጭነት ጥናት ለማድረግ ከሚያገለግሉት አመስት ዋና ዋና መስፈርቶች ውስጥ “የሕግ አዋጭነት” (Legal feasibility) አንዱ ነው። በመሠረቱ፣ የተጠቀሱት ሁለት ተቋማት ለአዲስ አበባ የቆሻሻ ማስወገጃ የሚሆን ቦታን ከከተማዋ 37 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ሄደው በአንድ ሉዓላዊ ክልላዊ መስተዳደር የመሬት ይዞታ ውስጥ ገብተው መምረጣቸው በራሱ ሕገ-ወጥ ተግባር ነው።

በእርግጥ በዘመናዊ የአወጋገድና አስተዳደር ስርዓት መሰረት “ቆሻሻ” እንደ ስሙ አስቀያሚ ሳይሆን አዋጭ የሆነ ቢዝነስ ነው። ለምሳሌ፣ የአዲስ አበባ የደረቅ ቆሻሻ መልሶ-መጠቀምና ማስወገድ ፕሮጀክት ፅ/ቤት በ2006 የበጀት አመት ብቻ ከ1.2 ሚሊዮን ብር ገቢ ከአገልግሎት ክፍያ ሰብስቧል። በቀጣይ 50ና 60 አመታት ከእያንዳንዱ የአዲስ አበባ ነዋሪ በአማካይ በቀን የሚጥለውን 2.1 ሜትር ኪዩብ ቆሻሻ እየሰበሰበ ወደ ሰንዳገፋ ወስዶ በመጣል ዳጎስ ያለ ገቢ እንደሚሰበስብ ይጠበቃል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ሊጠናቀቅ ጥቂት የቀረው የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት በየቀኑ የ50 ሜ.ዋ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በአማካይ በአመት 22,265,000 ብር ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ገቢያስገኛል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ላለፉት 50 ዓመታት ከተጠራቀመው ቆሻሻ ስር የሚፈጠረው “Methane” የሚባለው ጋዝ ከካርቦን ዳይኦክሳይድ 20 እጥፍ ከባቢ አየርን የሚበክል ነው። የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ይህን በካይ ጋዝ በመቀነሱ ረገድ በሚያበረክተው አተዋፅዖ ሀገሪቱ ከካርቦን ክሬዲት (Carbon Credit ) በየአመቱ 100000 ዶላር (2185000 ብር) ታገኛለች። በአጠቃላይ፣ ከረጲ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ጋር በተያያዘ ብቻ የከተማ መስተዳደሩና የፌደራል መንግስት በአመት 25.6 ሚሊዮን ብር ገቢ ይገኛል።

በኢፌድሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 92 ከተዘረዘሩት የአከባቢ ደህንነት ጥበቃ አላማዎች እንዳሉ ሆነው፣ በሰንዳፋ የሚገነባው የቆሻሻ ማስወገጃ እንደ ተቋም ለአከባቢው ነዋሪዎች “ማህበራዊ ኃላፊነት” “Corporate Social Responsibility – CSR) አለበት። ነገር ግን፣ በሰንዳፋ የቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክት የአዋጭነት ጥናት እና በወደፊት እቅዱ ውስጥ የአከባቢው ነዋሪዎችን ማህበራዊ ደህንነት (Social wellbeing) በጭራሽ ከግምት የገባ አይመስልም። አዲስ አበባ ከተማ የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ እና የ“HoARE&EN” ዋና ዳይሬክተር በሰንዳፋ የቆሻሻ ማስወገጃ ተመሣሣይ ከኤሌክትሪክ ኃይል እና ከካርቦን ክሬዲት ገቢ ሊገኝ እንደሚችል ይጠቁማሉ።

ሆኖም ግን፣ በቀድሞው ሆነ በአዲሱ ፕሮጀክት የሰንዳፋ አከባቢ ማህብረሰብ ከቆሻሻ ከሚገኘው ገቢ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታሳቢ አልተደረገም። ለሰንዳፋ የቆሻሻ ማስወገጃ ግንባታ 137 ሄክታር መሬት ከአከባቢ አርሶ-አደሮች ተወስዷል። ለአርሶ-አደሮቹ ተከፈለ የተባለው ጠቅላላ የካሣ መጠን 25 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ቢሆን በአግባቡ ለአርሶ-አደሮቹ አልተከፈላቸውም።

Photo - Addis Ababa Sendafa Landfill, August 2016
Photo – Addis Ababa Sendafa Landfill, August 2016

ነገር ግን፣ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት፤ 1ኛ፡- መሬት በሀገራችን ዋንኛ የሃብት ምንጭ ስለሆነ የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የፍትሃዊነት ተጠቃሚነት አንዱ ማረጋገጫ መሳሪያ መሆኑን፣ 2ኛ፡- በሀገራችን ሁኔታ መሬት ከማንነት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ብሔር ብሄረሰቦች የማንነት መገለጫዎቻቸውን ማሳደግ የሚችሉት ከመሬት ያለመነቀል ዋስትና ሲያገኙ ነው የሚል መርህ አለው፡፡ አንቀፅ 49(5) ተግባራዊ ባለመደረጉ ምክንያት የሰንዳፋ አከባቢ ነዋሪ የመሬት ባለቤትነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሕጎችና መመሪያዎች አልወጡም። በዚህ ምክንያት፣ የሰንዳፋ አከባቢ ነዋሪዎች ሕገ-መንግስታዊ መብታቸው አልተከበረም።

እዚህ ጋር ሊሰመርበት የሚገባው ነጥብ፣ የአከባቢው አርሶ-አደሮች ለመሬታቸው ይከፈላቸዋል የተባለው የ25 ሚሊዮን ብር ካሣ የፌዴራሉ መንግስትና የአ.አ መስተዳደር ከቆሻሻ ብቻ በየአመቱ ከሚያገኙት የ25.6 ሚሊዮን ብር ገቢ ያነሰ መሆኑ ነው። እስኪ አስቡት፣ አዲስ አበባ ቆሻሻዋን ሰንዳፋ ወስዳ ደፍታ በሚሊዮኖች ገቢ ስታገኝ፣ የአከባቢ ንፅህና እና የነዋሪዎቿ ጤንነት ሲጠበቅ፣ የሰንዳፋ አርሶ-አደር ግን 18 ብር በካ.ሜ ካሣ እየተከፈለው ከመሬቱ ሲፈናቀል፣ የአከባቢው ንፅህና እና የቤተሰቡ ጤንነት አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ …ከዚህ በላይ ግፍና በደል ሌላ ምን አለ?

የአዲስ አበባ እድገት ተፈጥሯዊና ሊቋረጥ የማይችል ነው። ነገር ግን፣ ከተማዋ ላለፉት 129 ዓመታት ስታደርግ እንደነበረው፣ በዙሪያዋ ያለውን የኦሮሞ ገበሬ እያፈናቀለች መቀጠል አትችልም። ከዚያ ይልቅ፣ አዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ያሉት የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች በጋራ እጅ-ለእጅ ተያይዘው አብረው ማደግ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) መሰረት ግልፅ የሆነ የሕግ ማዕቀፍና የአፈፃፀም መመሪያ ሊዘጋጅ ይገባል። የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን አዘገጃጀት ከዚህ መርህ ውጪ ስለነበረ በህዝብ አመፅና ተቃውሞ እንዲቋረጥ ተደርጏል። በዚህም የከተማዋ እድገት ባላት ውስን የከተማ መሬት ላይ ወደ ሰማይ እንዲሆን ተወሰነ። ነገር ግን፣ ወደ ሰማይ ለማደግም ከመሬት ላይ መቆም ያስፈልጋል። ስለዚህ፣ የአዲስ አበባ መስተዳደር ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን ለመስራት የሚያስፈልገውን ቦታ ለማግኘት በምድር ላይ ያሉ መኖሪያ ቤቶችን በዘመቻ ማፍረስ ጀመረ። ላለፉት አስር አመታት ያልታየው ሕገ-ወጥ ወረራ ዛሬ ላይ በድንገት ተገለጠለት።

በተመሣሣይ፣ በሰንዳፋ የተነሳውን የገበሬዎች ተቃውሞን አስመልክቶ፣ የአዲስ አበባ ፅዳት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ፣ ከ7 ዓመት በፊት በጉዳዩ ዙሪያ ከአከባቢ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውንና በወቅቱ ከመግባባት ላይ ደርሰው እንደነበር ያስታውሳሉ። ነገር ግን፣ በሕገ መንግስቱ መሰረት ልዩ ጥቅም ለማስከበር የሚቻልበት ዝርዝር ሕግና መመሪያ በሌለበት ከአከባቢው ማህብረሰብ ጋር መወያየት በራሱ ሕጋዊ መሰረት የለውም። ከዚህ በተጨማሪ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባን ጨምሮ የከተማ መስተዳደሩ ኃላፊዎች ከኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ጋር በሰንዳፋ ጉዳይ ላይ ለሰባት ቀናት ያህል በደረጉት ስብሰባ ከስምምነት ላይ አለመድረሳቸው ተገልጿል። ነገር ግን፣ እንኳን ስምምነት ላይ መድረስ፣ ውይይቱ በራሱ የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) የሚጥስ ነው። ይህ አንቀፅ ተግባራዊ እስካልሆነ ድረስ በአዲስ አበባ በጣም ብዙ መኖሪያ ቤቶች ይፈርስሉ፣ ከፍተኛ የቆሻሻ ክምር ይኖራል። በዚህም፣ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የራሳቸውን መኖሪያ ቤት የመገንባት እና ንፅህናው በተጠበቀ አከባቢያ የመኖር መብታቸው ሊረጋገጥ አይችልም፡፡

ከላይ በዝርዝር ለመጥቀስ እንደተሞከረው፣ የፌዴራል መንግስት፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳደር ሁሉም ሕገ-መንግስቱን አክብረው አላስከበሩም፡፡ በዚህ ምክንያት፣ የሰንዳፋ አከባቢ እና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሕገ-መንግስታዊ መብታቸው አልተከበረም፡፡ በመሆኑም፣ የሰንዳፋ አከባቢ ነዋሪዎች ከአዲስ አበባ ከተማ የሚወጣው ቆሻሻ በአከባቢያቸው እንዳይደፋ በመቃወም መንገድ ዘጉ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ እና የኦሮሚያ መስተዳደር ከፍተኛ ሃላፊዎች ከአንድ ሣማንት በላይ ስብሰባ ተቀምጠው ለችግሩ መፍትሄ መስጠት ተሳናቸው፡፡

Photo - Addis Ababa Qoshe Landfill
Photo – Addis Ababa Qoshe Landfill

የረጲ (ቆሼ) ቆሻሻ ማስወገጃ የአገልግሎት ዘመኑ በመጠናቀቁ መዘጋት ነበረበት፡፡ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ የሰንዳፋ ቆሻሻ ማስወገጃ ግንባታ ሕጋዊ መሠረት በሌለው ቦታ መረጣ፣ ግልፅነት በጎደለው ጨረታ፣ ያለ በቂ ካሣ ክፍያና ለአከባቢያዊና ማህብረሰባዊ ጤና ትኩረት ባልሰጠ መልኩ የተካሄደ ነው፡፡ ስለዚህ፣ ለአመታት የተሰራ ስህተት በቀናት ስብሰባ መፍትሄ ሊያገኝ አይችልም፡፡ በአንድ ቢሊዮን ብር ተገነባ የተባለው የሰንዳፋ ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ ተዘጋ፡፡ የአገልግሎት ዘመኑን ጨርሶ ተዘግቶ የነበረው የረጲ (ቆሻ) ቆሻሻ ማስወገጃ ዳግም ተከፍቶና ላለፉት 6ወራት ከአቅም በላይ አገልግሎት ሰጠ፡፡

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ መስተዳደር ለከተማዋ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብታቸውን ከማረጋገጥ ይልቅ “ሕገ-ወጥ ግንባታ” እያለ የማፍረስ ዘመቻውን አጣጡፎ ከረመ፡፡ የነዋሪዎቹን አቤቱታ የሚሰማ ሲጠፋ በየስርቻው ስር ፕላስቲክ ወጥረው መኖር ጀመሩ፡፡ በቆሼ ቁጥራቸዉ እስከ 500 የሚደርሱ ሰዎች ቆሻሻዉን በመለየት፣ በመመነጣጠልና በመልቀም የሚተዳደሩ ሲሆን በአደጋ በብዛት ሰለባ የሆኑት በአካባቢው በደሳሳ ጎጆ ዉስጥ የሚኖሩ ደሃና ለፍቶ አዳሪ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ፣ እነዚህ ሰዎች በመስተዳደሩ ዘመቻ የተፈናቀሉ፣ መኖሪያና መጠለያ የማግኘት መብታቸውን የተነፈጉ፣ ወይም ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ ካሉ የኦሮሚያ አከባቢዎች በመሠረተ-ልማት ግንባታና በኢንቨስትመት ምክንያት ከመሬታቸው የተፈናቀሉ ናቸው፡፡

“እነዚህ ቁጥራቸዉ እስከ 500 የሚደርሱ ሰዎች የሚተዲደሩት ቆሻሻን በመለየት፣ በመመነጣጠልና በመልቀም ሥራ ስለሆነ የከተማው መስተዳደር ተጠያቂ ሊደረግ አይገባም” የሚሊ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን፣ የአንድ ከተማ መስተዳደር ለነዎሪዎቹ ከቆሻሻ የተሻለ የሥራ ዕድል መፍጠር ከተሳነው ከህዝቡ ግብርና ታክስ የሚሰበስበው ምን ሊሰራበት ነው ታዲያ? እሺ መስተዳደሩ በከፋ ድህነት ውስጥ ላሉ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንኳን ባይችል በከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም እንዲታቀፉ ማድረግ ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን፣ ላለፉት ሶስት አመታት የሴፍቲኔት ፕሮግራሙ “ሊጀመር ነው” እያሉ ከመጮህ የዘለለ ሥራ አልተሰራም፡፡ በአጠቃላይ፣ እነዚህ ሰዎች መሠረታዊ መብትና አገልግሎት ተነፍጏቸው፣ የተሻለ ምርጫና አማራጭ አጥተው ካልሆነ በስተቀር ኑሮና ውሏቸውን ከቆሻሻ ክምር ስር የሚያደረጉበት ሌላ ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡

አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የሰንዳፋ ቆሻሻ ማስወገጃ የግንባታ ሂደት አሳታፊ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ቢሆን ኖሮ የአከባቢውን ነዋሪዎች መብትና ተጠቃሚነትን በደንብ ማረጋገጥ ይቻል ነበር፡፡ ይህ ባለመሆኑ የሰዳፋ አከባቢ ነዋሪዎች በተቃውሞ መንገድ ዘጉ፡፡ በዚህ ምክንያት፣ የከተማዋ ፅዳትና ውበት ዳይሬከተር “ዳግም ላይከፈት ተዘግቷል” ያሉት የረጲ ቆሻሻ ማስወገጃ ዳግም ተከፍቶ ላለፉት 6ወራት ከአቅም በላይ ቆሻሻ ሲከመርበት ቆየ፡፡ ባሳለፍነው ግማሽ ዓመት ብቻ በአማካይ 150,000 ቶን ቆሻሻ በቆሼ ተጥሏል፡፡ “በግማሽ ዓመት ውስጥ ከቦታው አቅም በላይ የተጣለው ቆሻሻ ለተፈጠረው አደጋ እንደ ምክንያት ሊወሰድ አይገባም ” የሚሉ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን፣ ከባለፈው ዓመት መገባደጃ ጀመሮ ቆሻሻው በታቀደው መሠረት አዲስ በተገነባው የሰንዳፋው ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ የሚጣል ቢሆን ኖሮ አደጋው ሲከሰት ነበሩ ከተባሉት 150 ሰዎች ውስጥ አብዛኞቹ በቦታው ስለማይኖሩ እንደ የብዙ ሰዎች ሕይወት አይጠፋም ነበር፡፡

በአጠቃላይ፣ በፌደራል፣ ክልልና በከተማ መስተዳደር ደረጃ ያሉ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ድርሻና ኃላፊነታቸውን በተገቢው ሁኔታ ቢወጡ ኖሮ፤ የሰንዳፋ ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ በተባለለት ግዜ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ይጀምር ነበር፣ ከአገልግሎት ውጪ የሆነው የረጲ የቆሻሻ ማስወገጃ (ቆሼ) ዳግም ተከፍቶ ከአቅም አገልግሎት እንዲሰጥ አይደረግም ነበር፣ አደጋው በደረሰበት ዕለት የነበሩት 150 ሰዎች በቦታው አይገኙም፣ በሌላ አጋጣሚ አደጋው ቢከሰት አንኳን አንደ አሁኑ የብዙ ሰዎች ሕይወት አይቀጥፍም።

በአዲስ አበባ ከተማ እና በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳደር ያሉ የመንግስት ኃላፊዎች እና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትና ሥራና ተግባራቸውን አሳታፊና ቀልጣፋ፣ እንዲሁም ግልፅነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት መልኩ ቢከናውኑ ኖሮ በከተማዋ የሕገ-ወጥ ግንባታ አይስፋፋም፣ መኖሪያ ቤቶች አይፈርሱም፣ አርሶ አደሮች ከመሬታቸው አይፈናቀሉም። አስፈላጊው የማህበራዊ ዋስትና ሥርዓት ቢዘረጋ ኖሮ ዜጎች መኖሪያቸው ከቆሻሻ ክምር አያደርጉም፣ 500 ሰዎች የዕለት ጉርሳቸውን ከቆሻሻ ውስጥ ሲፈልጉ አይውሉም። ይሄ ሁሉ ለመንግስት ኃላፊነት፣ ለነዋሪዎቹ ደግሞ መብት ነው። መንግስት ኃላፊነቱን በአግባቡ ቢወጣና የነዋሪዎቹ መብት ቢከበር ኖሮ የሰዎች ሕይወት ያለ አግባብ ባልጠፋ ነበር፡፡ ስለዚህ፣ የቆሼው አደጋ በዴሞክራሲ እጦት ምክንያት የተከሰተ ነው ማለት ይቻላል፡፡

*********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories