መከላከያ ሰራዊትን እንደተዋጊም እንደ ፖሊስም የመጠቀም አደገኛ ዝንባሌ

(አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሺፈራዉ (ኮ/ል))

መቅድም

በሀገራችን ተከስቶ በነበረዉ የጸጥታ ችግር በተያያዘ የህዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ  ተሰማርቶ የነበረዉ መከላከያ ሰራዊታችን ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን አኩሪና አስመስጋኝ ተግባር ማከናወኑ ይታወቃል፡፡ መከላከያ የዜጎችን ይህንነት ለማስከበር ሃላፊነቱን በሚወጣበት ወቅት በዜጎች ላይ አላስፈላጊ የመብት ጥሰት  እንዳይደርስ  ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጉም የሚያስመሰግነዉ ነዉ፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ በዚህ ተግባር ባይሳተፍ ኖሮ በዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ የከፋ ችግር ሊከሰት ይችል እንደነበር ለመገመት አያዳግትም፡፡ መከላከያ ሰራዊታችን ሀገር ለማረጋጋት ጣልቃ መግባቱን  በሚመለከት አስካሁን የቀረበ ተቃዉሞም ሆነ ጥያቄ ያለ አይመስለኝም፡፡ ይሁን እንጂ መከላከያ ሰራዊትን በዚህ ዓይነቱ የዉስጥ ጸጥታ ማስከበር ተግባር ላይ ማሰማራት ጋር ተያይዞ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ በቂ ግንዛቤ ተይዞበት መፍትሄ ካልተቀመጠለት በስተቀር  እየተዘወተረ ሲሄድ አሁን ላይ ሆነን መገመት የማንችላቸዉ ችግሮች ሊገጥሙን ይችላሉ፡፡ በአገራችን ተከስቶ የነበረዉን ሁኔታ ተከትሎ መከላከያ ሰራዊታችን አስመስጋኝ ስራ ሰርቷል ስለተባለ ወደፊትም ትንሽ ሁከት በተፈጠረ ቁጥርና በረባና ባልረባዉ የጸጥታ ችግር ሁሉ መካለከያ ሰራዊቱ ጣልቃ እንዲገባ መደረግ አለበት የሚል ትርጉም ሊሰጠዉ አይገባም፡፡

የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ ትኩረት በሃገራችን ተከስቶ ስለለነበረዉ ቀዉስና ለዚያ ችግር የዳረገን ምክንያት ላይ መተረክ አይደለም፤ ያን የእብደት ወቅት ማስታወስ በራሱ ያስጠላኛልና፡፡ የመከላከያ ሰራዊታችን በወቅቱ የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ስለአከናወናቸዉ አስመስጋኝ ስራዎችም የማዉሳት ዕቅድ የለኝም፡፡ የእኔ ዋነኛ ትኩረት የሚሆነዉ መከላከያ ሰራዊታችን አሁንም ሆነ ለወደፊቱ ህግ የማስከበር ተልእኮ ላይ  የመሳተፉ አግባብነት ዙሪያ ላይ የግል አስተያየት ለመሰንዘር ነዉ፡፡ ዓላማዬ መከላከያ ሰራዊታችን በዉስጥ ጸጥታ ማስከበር በተለይም በህግ ማስከበር ስራ መጠቀም አይገባንም ወይም ይገባናል የሚል አመለካከት ለማራመድ አይደለም፡፡ ህዝብና መንግስት ተገቢ ነዉ በሚል ከተቀበሉትና ካመኑበት  መከላከያ  ሰራዊቱ በህግ ማስከበር ተግባር ቢሰማራ ችግር አይኖረዉም፡፡ ነገር ግን ይህን የምንልበት ምክንያት ከስሜታዊነት በጸዳ ሁኔታ በቅድሚያ ከጉዳዩ ጋር  የተያያዙ አደጋዎችና ተግዳሮቶች ላይ  በቂ ግንዛቤ ከተያዘበት በኋላ ቢሆን ይመረጣል፡፡ እኔም ከዚህ በፊት በሃገራችን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የመከላከያን ተሳትፎ የጠየቁ የጸጥታ ችግሮችና በቅርቡ በሀገራችን ተከስቶ የነበረዉ ቀዉስ ወቅት የሰራዊታችን የተልእኮ አፈጻጸም ችግሮችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በዋነኛነት ደግሞ ሰፊ ልምድ ካላቸዉ ሌሎች አገሮች ተሞክሮ በመነሳት በጉዳዩ ላይ የግል አስተያየት ለመሰንዘር እሞክራለሁ፡፡ በዚህ ጽሁፍ  መከላከያ ሰራዊታችን እንደ ፖሊስ ሆኖ በፖሊስ ተግባር መሳተፍ ይገባዋል ወይንም አይገባዉም የሚል አስተያየት እንድሰጥ አይጠበቅብኝም፡፡ የእኔ ሃላፊነት አደጋዉን በመሳየት ላይ የተገደበ ነዉ፡፡

መግቢያ

ከጥቂት ወራት በፊት ብዙዎቻችን በስሜት ተገፋፍተን በአጉል ጥላቻ መንፈስ ታዉረን ያለ አንዳች ማመዛዘን በጥፋት ተግባር ስንሳተፍ በነበርንበት በዚያን ወቅት ተጨማሪ ጥፋት ከማድረስ እንድንቆጠብ የሚመክር ሃሳብ ለመስንዘርም ሆነ ለመስማት ትእግስቱ ባልነበረን በዚያ የእብደት ዘመን ለሰላም ወዳድ ወገኖችና ለመንግስት መያዣ መጨበጫዉ በጠፋበትና ኢትዮጵያዉያን የገዛ አገራችንን ለማዉደም ተማምለን የተነሳን በሚመስልበት በዚያን አስቀያሚ ወቅት ላይ ነበር  መከላከያ ሰራዊታችን የህዝቡን ሰላምና ደህንነት፤ እንዲሁም የዜጎችንና የመንግስትን ንብረት ከዉድመት ለመታደግ ለመንቀሳቀስ የተገደደዉ፡፡

መከላከያ ሰራዊታችን በፍጥነት ተንቀሳቅሶ ባይደርስላቸዉ ኖሮ ከንብረትም በላይ ህይወታቸዉ ለአደጋ ተጋልጦ የነበሩ በርካታ ዜጎች እንደነበሩ እናስታዉሳለን፡፡ ሰራዊታችን ከፖሊስና ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎችና ከህዝቡ ጋር በመተባበር ሁኔታዎችን ለማረጋገት ያደረገዉን ጥረትና የተገኘዉን ዉጤት ህዝቡ ራሱ መመስከር የሚችለዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢም ከጥቂት ሳምንታት በፊት በምኖርበት ከተማ  በወቅታዊ የሀገራችን ጉዳይ ላይ መስተዳደሩ ከህዝቡ ጋር ባደረገዉ መክክር ላይ የመገኘት እድል አግኝቼ ስለነበር በስብሰባዉ ላይ ህዝቡ ለመከላከያ ሰራዊታችን ሲያሽጎደጉድ የነበረዉን ምስጋናና አድናቆት ብዛት ለመታዘብ በመብቃቴ እጅግ መደሰቴንና በሰራዊታችን መኩራቴን መደበቅ አልችልም፡፡ በተለይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኃላ በነበረዉ አጭር ጊዜ ዉስጥ ሁኔታዎችን በመቆጣጠር ወደ ቀድሞዉ ሰላማዊ ሁኔታ መመለስ በመቻሉ ሊደርስ ይችል ከነበረ የከፋ ጥፋት እንደታደገዉ ህዝቡ በአድናቆት ሲገልጽ አድምጨአለሁ፡፡ በርግጥ መከላከያ ሰራዊታችን በሀገራችን ተፈጥሮ የነበረዉን የጸጥታ ችግር በመቆጣጠርና ህዝብን በማረጋጋት ረገድ ጉልህ ሚና የነበረዉ መሆኑ ባይካድም ስራዉ የተሰራዉ ከፖሊስና  ከህዝቡ ጋር በመተባበር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ዛሬ ለሚታየዉ ሰላምና የተረጋጋ ሁኔታ የበቃነዉም በሁሉም የደህንነት ተቋማትና በመላዉ ህዝብ የተቀናጀ የጋራ ጥረት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

የዚህ ተልእኮ ዉጤታማነት በቀላሉ የተገኘና ያለ አንዳች እንከን የተከናወነ ሳይሆን ከተልእኮዉ ዉሰብስብነት ባህሪይ በመነጨ በአፈጻጸሙ ላይ የተወሰኑ ተግዳሮቶች ሳያጋጥሙ እንዳልቀሩ  መገመት ይቻላል፡፡ በገዛ ህዝብ ዉስጥ ሆኖ ጸጥታን የማስከበር ተልዕኮ በባህሪይዉ እጅግ ዉስብስብ በመሆኑ ከዚያ ሊመነጩ የሚችሉ ተግዳሮቶችና እንከኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተረድተን ለወደፊቱ ተመሳሳይ ሁኔታ ቢፈጠር ለተሞክሮ ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን በጥንቃቄ ለይቶ ለወደፊቱ ማስተካከያ ማድረጉ ነዉ የሚበጀዉ፡፡

1/ የመከላከያ  ሰራዊትን ህግ ማስከበር ተግባር በመጠቀም አግባብነት ላይ የሚታዩ አመለካከቶች

መከላከያ ሰራዊት ለህግ ለማስከበር ተግባር አዘዉትሮ በመጠቀም ረገድ እየታየዉ ያለዉ ያልተለመደ አዝማሚያ በፖሊስ ሊሰራ ይገባ የነበረዉን ተግባርን ወደ ወታደራዊነት (militarization) እንዲቀየር እያደረገ ነዉ የሚለዉ ትችት ዝም ተብሎ የተሰነዘረ ሳይሆን ተገቢ ከሆነ ስጋት የመነጨ ነዉ፡፡ 

ለምሳሌ በአሜሪካ ወታደር በህግ ማስከበር ተግባር መሳተፍ ሊያስከትል የሚችለዉን አደጋ ገና ድሮ አሻግረዉ በማዬት ህግ የማሰከበር ተግባር ላይ እንዳይሳተፉ የሚከለክል ደንብ ካወጡ ብዙ ዘመን አስቆጥሯል፡፡ ይህ “The Posse Comitatus Act” የሚባለዉ ደንብ በየግዜዉ የተወሰኑ ማሻሻያዎች   ቢደረግበትም አስካሁንም ድረስ የፌደሬራል ኃይልን (መከላከያን) በህግ ማስከበር ተግባር መሳተፍን አይፈቅድም፡፡ የአሜሪካ መስራች አባቶች ገና ከመጀመሪያዉ አንስቶ ለመደበኛ ወይም ቋሚ ሰራዊት ካለቸዉ ስጋትና ጥርጣሬ የተነሳ ቋሚ ሰራዊት አስከነጭራሹ እንዳይኖር በማድረግ በምትኩ የህዝብ ሰራዊትን (citizens army) ላይ በመተማመን ለብዙ ዘመን ቆይተዉ ነዉ ቋሚ ሰራዊት ማደርጀት የጀመሩት፡፡ ይህ ለመደበኛና ቋሚ ሰራዊት የነበራቸዉ ስጋት ወይም ጥርጣሬ መነሻ ሆኖ የፌዴራል የጸጥታ ኃይልን (ወታደርን) ህግ በማስከበር ተግባር ለመጠቀም የግድ የሚያደርጉ ልዩ ሁኔታዎች በህገመንግስት የተደነገጉ ካልሆነ በስተቀር በዘፈቀደ አስፈጻሚዉ ወታደሩን በህዝቡ ላይ ማሰማራትን በእጅጉ ሲኮነን የነበረ ነዉ፡፡

ህግ በማስከበር ተግባር ማሰማራትን በሚመለከት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈለገበት ዋናዉ  ቁምነገር የህግ አስከባሪነት ተግባር (law enforcement) እና  የወታደር ሙያ ፈጽሞ የማይገናኙ በመሆኑ ነዉ፡፡ ወታደር (መከላከያ) የሚሰለጥነዉ ፤የሚደራጀዉና የሚታጠቀዉ የባእድ አገር ጠላትን ለመዉጋት  ተብሎ አንጂ በራሱ ዜጎች ላይ ለመዝመት ተብሎ ስላልሆነ ነዉ፡፡ በአብዛኛዉ  ነባር ዲሞክራሲያዊ አገሮች ወታደር በገዛ ህዝቡ ዉስጥ ህግ ለማስከበር መንቀሳቀቀሱን ሲያይ ህዝቡ ራሱን በጠላት ወራሪ ሰራዊት ቁጥጥር ስር እንደወደቀ አድርጎ ነዉ የሚቆጥረዉ፡፡ ህዝቡ በምንም ሁኔታ ቢሆን ወታደሮቹ በእንደዚህ ዓይነት ስራ ላይ ተሰማርተዉ ሲሰሩ ማየት ምቾት አይሰጠዉም፡፡

ይሁን እንጂ ባለፉት ሃያና ሰላሳ ዓመታት ዉስጥ የታየዉ አዲስ አዝማሚያ ግን ወታደር ህግና ስርአት በማስከበር ስራ ላይ በስፋት መሳተፍ እየተለመደ መምጣቱ ነዉ፡፡ አብዛኛዎቹ የአሜሪካ ዜጎች የጦር ኃይል አባላት በዚህ ተግባር መሳተፋቸዉን ከቀድሞዉ በተለየ አሁን ብዙም የሚያስጨንቃቸዉና የሚያሳስባቸዉ ጉዳይ አልሆነም፡፡ ሰራዊታቸዉ በዉስጥ ጸጥታ ማስከበር ተግባር መሳተፍ ከጀመረ በኋላም በአሜረካ ጦር ኃይሉ በህዝብ አስተያየት መሰብሰቢያ ዉጤት መሰረት አሁንም እንደ ቀድሞዉ ከሁሉም አካላት (ከህግ አዉጭዉም ሆነ ከፍትህ አካሉ) በበለጠ ተአማምነት ያለዉ ተቋም ሆኖ ይቆጠራል፡፡ ህዝባዊ አመኔታ አልቀነሰበትም፡፡

በአሜሪካም ሆነ በሌሎች አገሮች መከላከያን ህግ በማስከበር ተግባር መጠቀም የግድ ያደረገዉ የሽብር ስጋት ከምንግዜም በላይ አሁን ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ነዉ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ ከዚህ ቀደም ለመቆጣጠር ለጸጥታ ኃይሎች ብዙም አስቸጋሪነት ያልነበራቸዉ የከተማ ሁከቶች ዛሬ በቀላሉ መልካቸዉን በመቀየር እጅግ አደገኛ ወደ ሆነ ቀዉስ ሊለወጡ እንደሚችሉ በተግባር ማዬት እየተቻለ ነዉ፡፡ በተለይም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዉ ዉጤት የሆኑት ማህበራዊ ድረ-ገጾች እጅግ መስገፋፋት ከሰላማዊ ጥቅማቸዉ ባልተናነሰ ለጥፋት ተግባርም መዋል መጀመራቸዉ የዜጎችን ደህንንት በማወክ እያደረሱት ያለዉ ጉዳት ሲታይ ሁኔታዉን እጅግ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

አሜሪካኖች መከላከያ በዉስጥ ጸጥታ ማስከበር ተግባር በጭራሽ መሳተፍ አይኖርበትም የሚለዉን ነባር አመለካከታቸዉን በእጅጉ የተፈታተነዉና ከአንግዲህ በዚያ መንገድ መቀጠል እነደማይችሉ እንዲረዱ ያደረጋቸዉ ትልቅ አጋጣሚ ቢኖር የ2001 የኒዉዮርኩ የሽብር ጥቃት ነዉ፡፡ ከየኒዮርኩ የሽበር ጥቃት በኋላ ያለ መከላከያ ሰራዊት ተሳትፎ በመደበኛ ፖሊስ ብቻ የዜጎችንን ደህንነት ማስከበር እንደማይቻል በሰፊዉ ግንዛቤ ተይዞበታል፡፡

በዛሬዉ ዘመን አደገኛ የሆኑ የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች (WMD) በአነስተኛ መጠን እየተፈበረኩ (miniaturized) በቀላሉ በሽብርተኞች እጅ መግባት መቻላቸዉና የዋህ ዜጎችም ባለማወቅ ለነዚህ ወንጀለኞች መሳሪያ መሆን እንደሚችሉ ሲታሰብ  የዉስጥ ጸጥታ የማስከበር ስራ እንኳን በፖሊስ አቅም መከላከያም ተጨምሮበት አዳጋች እየሆነ ነዉ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ በሰላም ተጀምሮ በሰላም ይጠናቀቃል ተብሎ ግምት የተሰጠዉ የተለመደዉ የከተማ ዉስጥ የተቃዉሞ አመጽ በአሁኑ ግዜ መልኩን በቅጽበት ቀይሮ አገሪቱን ወደ አደገኛ ሁኔታ ሊያስገባ እንደሚችል በተግባር እየታየ ነዉ፡፡ የችግሩ መወሳሰብ  ለመንግስት ብቻ ሳይሆን ህገመንግስታዊ መብታቸዉን ተጠቅመዉ የአደባባይ የተቃዉሞ ሰልፍ ለማድረግ ለሚፈልጉ ዜጎችም ጭምር መጥፎ አጋጣሚ ሆኗል፡፡ መብታቸዉን በነጻነት እንዳይጠቀሙ እነሱ ራሳቸዉ ከስጋት ነጻ መሆን አልቻሉም፡፡ በዛሬዉ ዘመን ሰላማዊ ተቃዉሞ ሰልፍ ለመዉጣት ለህዝቡ አሳሳቢዉ ጉዳይ በተለምዶ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎችን መፍራት መሆኑ ቀርቶ ከዚያ ይልቅ አድግ አደገኛ ስጋት የፈጠረዉ ሌሎች የጥፋት ኃይሎች አጋጣሚዉን በመጠቀም አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ የሚለዉ ስጋት ሆኗል፡፡

መከላከያ ሰራዊት ህግ የማስከበር ተግባር ላይ መሳተፉን የሚደግፉ የመኖራቸዉን ያህል ወታደር የፖሊስን ስራ የሚሰራበት አግባብ ላይ (police-ization of the armed forces) ከጠቀሜታዉ ይልቁ ጉዳቱ ያመዝናል በሚል በድፍረት የሚቃወሙ ፖለቲከኞች ብዙ ናቸዉ፡፡ በተለይም ወታደራዊ ተቋሙ ጠብቆ ማቆየት አለበት የሚባለዉ ወታደራዊ ብቃት (an authentic combat capability) እየወደቀ ሊሄድ ይችላል ከሚለዉ ስጋት ሌላ ወታደሩ ቀስ በቀስ የዜጎች መብት ጥሴት ላይ እንዲሳተፍ የተመቻቸ ሁኔታ ይፈጥርለታል በሚል  ስጋታቸዉን የሚገልጹ ብዙ ናቸዉ፡፡ ብዙዎቹ የጦር ኃይሉ አዛዦችም ቢሆኑ  ሰራዊቱን በዚህ መሰሉ ህግ የማስከበር ተግባር ላይ መሳተፍን የማይደግፉ ሲሆን በዋነኛነት የሚቃወሙበት ምክንያትም በሂደት የሰራዊቱን የዉጊያ ብቃትና ክህሎት በእጅጉ ይጎዳል ከሚል ስጋት በመነጨ ነዉ፡፡

የቅኝ አገዛዝ አስተዳደር በነበረባቸዉ ብዙዎቹ አገሮች በወቅቱ የነበሩት የቅኝ ገዥዎች የበለጠ ትኩረት ሲያደርጉ የነበረዉ በሀገሪቱ ላይ ከተጋረጠ ዉጭ ስጋት ይልቅ ለአገዛዛቸዉ አደገኛ ተደርጎ ለሚቆጠረዉ ለዉስጥ ደህንነት ስጋት ነበር ፡፡  እነዚህ የቀድሞወቹ ቅኝ ግዛቶች ነጻነታቸዉን ካገኙና ራሳቸዉን ማስተዳደር ከጀመሩ በኋም የቀድሞ ቅኝ ገዥዎች አሻራ አልለቅ ቢሏቸዉ የዉጭ ስጋትንም የዉስጡንም እኩል ለማስከድ ነዉ ሲጥሩ የነበረዉ፡፡

እንደሚታወቀዉ የለየላቸዉ አምባገነን ገዥዎች የዉስጥ ደህንነታቸዉንና  ስልጣናቸዉን ማስጠበቅን በሀገሪቱ ላይ ከዉጭ ከተጋረጠ ስጋት የበለጠ ክብደት ይሰጡታል፡፡ በዚህ ምክንያትም በተለመዱት የደህንነት ተቋማት ላይ ብቻ መተማመን ስለማይችሉ ስልጣናቸዉን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚችሉ ለነሱ በግል ታማኝ የሆኑ ሌሎች የጸጥታ ኃይሎችን የተለያዩ ስሞች እየሠጡ ያደራጃሉ፡፡ ለስልጣናቸዉ እጅግ ቀናኢ በመሆናቸዉ ስልጣናቸዉ ላይ ያነጣጠረ ስጋት በተፈጠረ ቁጥር ያለ ርህራሄ ታማኝ ወታደሮቻቸዉን በህዝቡ ላይ ያዘምታሉ፡፡ አምባገነን ገዥዎች በከተማ ዉስጥ ህግ ማስከበርን ለመሳሰሉት የፖሊስ መደበኛ ተግባር በሆኑት ላይ ሳይቀር ከፖሊስ ይልቅ በጦር ሰራዊቱ ላይ ይበልጥ ይተማመናሉ፡፡ አነስተኛ ለሆነች የከተማ የጸጥታ ችግር ሁሉ ፖሊስን ባለማመን መከላከያ ሰራዊትን ማዝመት ይቀናቸዋል፡፡

አብዛኛዎቹ አገሮች መከላከያ  ሰራዊታቸዉን ለዉስጥ ደህንነታቸዉ ማስጠበቅ ተግባር መጠቀምን በስፋት ስራዬ ብለዉ የተያያዙት ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ማብቃት በኋላ ነዉ፡፡ የቀዝቃዛዉ ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ በሀገሮች መካካል የነበረዉ ፍጥጫና ጦርነት በእጅጉ በመቀነሱ ሀገሮቹ ለመከላከያ ሰራዊታቸዉ(ጦር ኃይላቸዉ) ምን ዓይነት ተለዋጭ ተልዕኮ እንስጠዉ በሚል በእጅጉ መቸገራቸዉ አልቀረም፡፡ በቀዝቃዛዉ ጦርነት ወቅት በነበረዉ አስገዳጅ ሁኔታ ማለትም የማያቋርጥ የጦርነት ስጋትና በሀገሮች መካከል በነበረዉ ፍጥጫ ምክንያት ለዚያ ተብሎ በየሀገሩ ተቋቁሞ የነበረዉን እጅግ የገዘፈ ጦር ኃይል የጦርነት ስጋት በረገበበት ወቅት ላይ በፊት እንደነበረዉ ይዞ መቀጠል ተገቢም የሚቻልም አልሆነም፡፡ በሀገሮች መካከል ሰፍኖ የቆየዉ የደህንነት ስጋት ቢቀንስም ጦር ኃይሉን በአንድ ጊዜ ለማፍረስም ሆነ የመቀነስ እርምጃ ለመዉሰድም ቢሆን ለየሀገራቱ መንግስታት አስቸጋሪና ፈታኝ መሆኑ አልቀረም፡፡ ለብዙዎቹ አገሮች የመከላከያ ተቋማቸዉን በችኮላና በግብታዊነት ከማፍረስ ይልቅ የተሻለ መፍትሄ ሆኖ የተገኘዉ ለጦር ኃይሉ አዲስና ተለዋጭ ተልአኮዎችን ማፈላለግ ነበር፡፡ በዚህ መሰረትም የጦር ኃይሉን ዋነኛና መደበኛ ግዳጅ ሆኖ ከቆየዉ በዉጭ ስጋት ላይ ያተኮረ ተልዕኮ ምትክ የዉስጥ ጸጥታን የማስከበር አዲስ ተልዕኮ እንዲወጣ ማድረግ ነበር፡፡ ይህን ተልዕኮ በይበልጥ የግድ ያደረገዉም በየአገሩ አዳዲስ የርስበርስ የዉስጥ ግጭቶች መባባስ ሲሆን በተጨማሪ ከሀገር ዉጭም በመንግስታቱ ድርጅት የሰላም ማስከበር የመሳሰሉ አዳዲስ የስምሪት መስኮች ላይ መሳተፍ ለየሀገራቱ መንግስታት ፖለቲካዊና ኢኖሚያዊ ጠቀሜታዉ እጅግ የጎላ ነዉ፡፡ እነዚህ አዳዲስ ተልእኮዎች መፈጠራቸዉ ከሚሰጡት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም በላይ የሰራዊታቸዉን ግዝፈት ላለመቀነስ ሰበብ ሲፈልጉ ለነበሩ አንዳንድ መንግስታት እንደመልካም አጋጣሚ ነዉ የተቆጠረዉ፡፡

የዳበረ ዲሞክራሲን በገነቡ አገሮችም ሳይቀር ጦር ኃይሉን ለዉስጥ ደህንነት (internal security) ጸጥታ ማስከበር ተግባር መጠቀምን ለዘመናት ሲወገዝና ከዲሞክራሲ ጋር የማይጣጣም ተደርጎ ሲቆጠር እንዳልነበር ዛሬ ግን እነሱ ራሳቸዉ መከላከያ ሰራዊታቸዉን የዉስጥ ጸጥታን ለማስከበር ተግባር ላይ ማሰማራትን ስራዬ ብለዉ ተያይዘዉታል፡፡ በተለይም በአሜሪካ የኒዉዮርኩ የመስከረም 11/2001 የሽብር ጥቃት ከደረሰ በኋላ መከላከያ ሰራዊቱን ለዉስጥ ደህንነት መጠቀምን ተገቢ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በርግጥ አሁንም ቢሆን በዲሞክራሲያዊ አገሮች ከአቅም በላይ ለሆኑ ሁኔታዎች ካልሆነ በስተቀር ወታደርን (መከላከያን) ለከተማ ረብሻና አድማ ብተና ለመሳሰሉት የጸጥታ ችግሮች በቋሚነት አዘዉትሮ መጠቀምን ማዉገዛቸዉ አልቀረም፡፡

ለዲሞክራሲ ጀማሪ የሆኑ አገሮች መንግስታት መከላከያ ሰራዊታቸዉን ለዉስጥ ጸጥታ ማስከበር ተግባር በጭራሽ እንዳይጠቀሙ አሁንም ለጋሽ አገሮች ከመምከርና ከማስጠንቀቅ ባይቆጠቡም በነዚህ አገሮች ጦር ኃይሉን ለዉስጥ ጸጥታ መጠቀም ቀድሞዉኑ እጅግ የተለመደና እንደ ጤነኛና ተገቢ አሰራር የሚቆጠር ስለነበር እንዲያዉም ከድሮዉ በበለጠ ለዉስጥ ችግር መፍቻነት መጠቀማቸዉ አልቀረም፡፡ የረባ የዉጭ ስጋት በሌለባቸዉ በአንዳንድ አገሮች መከላከያዉ ያለ ስራ ተወዝፎ ከሚቀለብ “ባይሆን ይችን ይችን እንኳን ይስራ !” የሚል ከፍተኛ ግፊት አለ፡፡ በዚህ ምክንያትም ብዙዎቹ አገሮች በህገ መንግስታቸዉ ሳይቀር ጦር ኃይሉን (መከላከያ ሰራዊቱን) በዉስጥ ጸጥታ ማስከበር መጠቀምን የሚፈቅድ ድንጋጌ በማካተት አሰራሩን ህጋዊ እንዲሆን አድርገዉታል፡፡

ከዚህ መረዳት እንደሚቻለዉ ቀደም ሲል በብዙ አገሮች የጦር ኃይሉ ዋነኛ ተልእኮ በዉጭ ስጋት ላይ ብቻ ማተኮር አለበት እንጂ በዉስጥ የሚነሱ የጸጥታ ማስከበር ተግባር ላይ መሳተፍ የለበትም የሚለዉ እምነት አሁን እየቀረ መጥቶ አስፈላጊ በሆነ ግዜ ሁሉ መከላከያን መጠቀም በሁሉም አገሮች እየተለመደ መምጣቱን ነዉ፡፡ 

በመሰረቱ በሀገሪቱ ሉአላዊነትና በብሄራዊ ጥቅሟ፤በዜጎች ደህንነትና በህገ መንግስታዊ ስርአቱ ላይ ከዉጭም ይሁን ከዉስጥ አደጋ ሲጋረጥ ያንን ለመከላከል የሁሉንም የጸጥታ ኃይሎች የጋራ ቅንጅት የሚጠይቅ እንጂ በተወሰነ ኃይል ብቻ የሚሰራ አይደለም፡፡ በዜጎች ሰላምና ደህንነት ላይ የከፋ አደጋ ሲጋረጥና ሁኔታዉን ለመቆጣጠር ከመደበኛ ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች አቅም በላይ ሆኖ ሲገኝ መከላከያ ሰራዊትን በዉስጥ ጸጥታ ማስከበር ተግባር መጠቀም ከዲሞክራሲ መሪህ ጋር የሚጻረር ድርጊት ተደርጎ የሚቆጠርበት ዘመን ላይ አይደለንም፡፡

በተለይ በአሁኑ ወቅት ሽብርተኝነት ፤የሃይማኖት አክራሪነትና ጽንፈኝነት ለሰላም ወዳድ ህዝቦች ሁሉ ከመቼዉም የበለጠ ትልቅ ስጋት  በሆኑበት ሁኔታ መንግስት ለዜጎቹ ደህንነት ስል በእጁ ያለዉን አማራጭ ሁሉ መጠቀም የግድ ይለዋል፡፡  የሃይማኖት አክራሪነትም ሆነ ሽብርተኝነት በባህሪያቸዉ በዉጭ ኃይሎች የሚቀነባበሩ በመሆናቸዉ መንግስት ተከታትሎ ከምንጩ ለማድረቅ እጅግ አዳጋች እንደሚሆንበት ግልጽ ነዉ፡፤ይህ እንዳለ ሆኖ በአሁኑ ግዜ ለዜጎች ደህንነት ይበልጥ አሳሳቢ  እየሆነ የመጣዉ አዲስ አዝማሚያ  ደግሞ አንዳንድ አክራሪ ፖለቲከኞች ለዘመናት ይዘዉት የቆዩት ፖለቲካቸዉ አልሰምር ሲላቸዉ በቀላሉ ራሳቸዉን ወደ ሽብርተኝነት ለመቀየር  መፍቀዳቸዉ ነዉ፡፡  በሀገራችንም በአንድ ወቅት በህጋዊ መንገድ የመንግስት ስልጣን ለመያዝ የፖለቲካ ፉክክር ዉስጥ ገብተዉ ከነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል አንዳንዶቹ እንዳሰቡት ስልጣን ማግኘት እንዳልቻሉ ሲረዱ የተሻለ አማራጭና አቋራጭ መንገድ አድርገዉ የወሰዱት ራሳቸዉን ወደ ሽብርተኝነት በመቀየር በታጠቀ ኃይል የሀገሪቱ ድህንነት ላይ አደጋ ማድረስ ሆኗል፡፡

የዬትኛዉም አገር መከላከያ ሰራዊት ወይም ጦር ኃይል ተቀዳሚ ተግባሩ የሀገሪቱን ሉአላዊነት መጠበቅ ነዉ፡፡ ይህ ኃላፊነት ከዉጭ ሊሰነዘር ከሚችል ጥቃት ወይም ስጋት (external threat) ላይ ብቻ ሳይወሰን በዉስጥ ሊነሱ ከሚችሉ የደህንነት ስጋቶችንም ጭምር የሚያካትት እንደሆነ ይታወቃል፡፡መከላከያ ከሌሎች ተቋማት በተሻለ የተደራጀና ጠንካራ የሎጅስትክስ አቅም ያለዉ በመሆኑ በሀገሪቱ ከፍተኛ ቀዉስ ሲፈጠር የሲቪል ባለስልጣናቱ መከላከያን የመጀመሪያ ተመራጭ ማድረጋቸዉ የሚያስገርም አይደለም፡፡ መከላከያ ተቋሙም ይህን ሃላፊነቱን ጠንቅቆ ስለሚገነዘብ ድጋፍ በተጠየቀ ግዜ ሁሉ ፈጣን መልስ መስጠት በሚያስችለዉ ደረጃ ራሱን ማብቃት ይጠበቅበታል፡፡ መከላከያ በዚህ ብቻ ሳይወሰን በዉስጥ የሚነሱ የተለያዩ የጸጥታ ችግሮች ሲኖሩ  ከፖሊስና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት በጋራ ሰላምና ጸጥታን በማስከበር የሕዝቡን ደህንነት የማረጋገጥና የማረጋጋት ሃላፊነታቸዉን እንዲወጡ ሊታዘዙ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪ ሰዉ ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ ፈጥኖ በመድረስ ህዝቡን ከአደጋ በመታደግ አስመስጋኝ ስራ እየሰራ እንደሆነም ይታወቃል፡፡ 

መከላከያ የሚሰማራባቸዉ ተልኢኮዎች ከመበርከታቸዉና በባህሪያቸዉም የተለያዩ  ከመሆናቸዉ አንጻር አንዱን ከአንዱ የመምረጥም ሆነ ቅደም ተከተል ማስቀመጥ የመከላከያ ተግባር አይደለም፡፡ “ይሄኛዉ ይሸላኛል፡፡ ያኛዉ ቅድሚያ ይሰጠዉ ፡ ይሄኛዉ እኔን አይመለከትም ወዘተ “እያለ ለራሱ ግዳጅ አይመርጥም፡፡  “ወታደሮች የራሳቸዉን ጦርነት አይመርጡም! (Soldiers never choose their war) የሚባለዉ የፈረንጆች አባባል ተገቢነት አለዉ፡፡ ስለዚህ መከላከያ ሰራዊት ከተለመደዉ ወታደራዊ ተልኢኮ ወጣ ያሉና አሜሪካኖች (Military Operations Other Than War-MOOTW) ዉጊያ (ጦርነት) በሌለባቸዉ ወታደራዊ ተልእኮዎች ሁሉ መሳተፍ መቻል አለበት፡፡ አብነት ለመጥቀስ ያህል በህዝቦች መካከል የሚነሱ ከበድ ያሉ የእርስበርስ ግጭቶች በማብረድ ህዝብ የማረጋገት ስራ መስራት፤ የአደንዛዥ ዕጽ፤ ህገወጥ መሳሪያ ዝዉርርና ኮንትሮባድንን መቆጣጠር፤  የተደራጀና በትጥቅ የታገዘ ዝርፊያና ሌሎች ወንጀሎችን መካለከል፤ ሽብርተኝነትን የመፋለም፤ጸረ- ሳይበር ጥቃት ፍልሚያ (counter-cyber attack) የማድረግ ወዘተ በመሳሳሉት ሁሉ መከላከያ መሳተፉ ተገቢ ብቻ ሳይሆን ግዴታዉም ጭምር ነዉ፡፡ በህዝቦች መካካል የሚከሰቱ የርስበርስ ግጭቶች ላይም ለማንም ሳይወግን በገለልተኝነት ግጭቱን ለማብረድና ህዝቡን የማረጋጋት ስራ ሊሰራ ይችላል፡፡ የህዝብን ደህንንት ለማስከበር ተብለዉ የሚከናወኑ ሌሎች የመከላከያ ሰራዊቱ ስምሪቶችን በሚመለከት ከሞላ ጎደል ግልጽነትና የጋራ መግባባት ስላለ የእኔ ዋነኛ ትኩረት የሚሆነዉ በከተማ ዉስጥ ሁከት(ረብሻ) የመቆጣጠር ተግባር ላይ ነዉ፡፤በዚህ ጽሁፍ ማንሳት የፈለኩትም  አስቀድሜ በጠቀስኳቸዉ ተልዕኮዎች ላይ መሳተፉ ሳይሆን ከዚያ ይልቅ ብዙዎቹ አግባብነቱን በጥርጣሬ የሚያዩት ህዝባዊ ተቃዉሞን ተከትሎ በሚፈጠሩ ሁከቶች ወቅት እንደ ፖሊስ ሆኖ  ህግ የማስከበር (law enforcement task) ስራ መስራት አለበት ወይ የሚለዉ ጥያቄ  ዙሪያ ነዉ፡፡ ለክርክር የሚጋብዘዉም ይህ  ተግባር ስለሆነ ነዉ፡፡ 

2/ መከላከያን ለህግ ማስከበር ተግባር መጠቀም ተመራጭ የማይሆንበት ምክንያቶችና ተግዳሮቶች

በከተማ ጸጥታ ማስከበር ወቅት በፖሊሶች አቅም ብቻ ጸጥታ ማስከበር እንደማይቻል ሲታመንበት የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ከፖሊሶች ጋር ሆነዉ ፖሊስን እያገዙ ህግና ስርአት የማስፈን ተግባር እንዲሰሩ ሊሰማሩ ይችላሉ፡፡  ይሁን እንጂ ህገመንግስታዊ አግባብን ተከትሎም ቢሆን መከላከያ ሰራዊት በዉስጥ ጸጥታ ማስከበር ተግባር እንዲሳተፍ ሲደረግ ከሚያበረክተዉ መልካም ተግባር ባልተናናሰ ብዙ አፍራሽ ዉጤት ሊያስከትል ስለሚችል ጉዳዩ ሁልጊዜም አወዛጋቢ መሆኑ አልቀረም፡፡

መከላከያ ሰራዊቱት  አባላት የከተማ ህግ ማስከበር ስራ ከተለመደዉ የዉትድርና ሙያቸዉ ጋር የማይጣጣምና የተለየ በመሆኑ  ለዚህ ተልእኮ ሲሰማሩ በእጅጉ መቸገራቸዉ አይቀርም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የፖሊሶችን ያህል በኃይል አጠቃቀም ረገድ ትዕግስቱና መታቀብ  ስለማይኖራቸዉ ከልምድ ማነስ የተነሳ ከገደብ ያለፈ እርምጃ በመዉሰድ በገዛ ዜጎቻቸዉ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ የሚለዉ ስጋት ከፍተኛ ነዉ፡፡ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት የከተማ ዉስጥ ስምሪት እጅግ ፈታኝና በበርካታ ተግዳሮች የታጀበ ነዉ፡፡ ከነዚህ ተግዳሮቶች ዉስጥ የተወሰኑትን ቀጥዬ በአጭሩ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

2.1/ ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች

መከላከያ ሰራዊቱን ለዉስጥ ደህንነት ማስከበር ተግባር መጠቀም ተገቢነት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖችን ስጋት እንዲሁ በደፈናዉ ማጣጣል አይቻልም፡፡ ለስጋታቸዉ መነሻ የሆኑ ከበቂ በላይ ምክንያቶች አሉና፡፡ በአንድ በኩል ጨቋኝ መንግስታት የሕዝብ ተቃዉሞን ለማፈን መከላከያን ሊጠቀሙ መቻላቸዉና መከላከያዉም ለአገዛዙ የስልጣን ማቆያና የህዝብ መጨቆኛ መሳሪያ ሆኖ ማገልገል መቻሉ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ በስልጣን ላይ ያለዉ መንግስት በባህሪይዉ ዲሞክራሲያዊ የሚባል ሆኖም ነገር ግን ዜጎች ህገመንግስታዊ መብታቸዉን ተጠቅመዉ ተቃዉሞ ለማሰማት ሲሞክሩ መንግስት ሁኔታዉን ለመቆጣጠር ከሌሎች አማራጭ ኃይሎች ይልቅ መከላከያ ሰራዊቱን ለመጠቀም መምረጡ ነዉ፡፡ በተለይም መንግስት በረባ ባልረባዉ የዉስጥ ጸጥታ ችግር ሁሉ መከላከያን እንደ መፍትሄ የመጠቀም ልማድ ካዳበረ ችግር መከሰቱ አይቀርም፡፡  መንግስት እያንዳንዷን ችግር ሁሉ በጦር ሰራዊት ኃይል መፍታት ይቻላል የሚል አመለካከት ከያዘ ቀስ በቀስ ወታደሩን ለራሱ ስልጣን ማቆያነት ከመጠቀም አንደማይመለስ የጉዳዩ አጥኚዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡ መንግስት የህዝብን ሰላማዊ ተቃዉሞን በወታደር ኃይል  በጉልበት ለማፈን ከሞከረ የህዝቦች ዲሞከራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ሊጣሱ መቻላቸዉ እንዳለ ሆኖ መከላከያ ሰራዊቱ የህዝብ ተአማንነት እያጣ ህዝባዊ ወገንተኝነቱ እየተሸረሸረ ይሄዳል፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ ራሱ ከመደበኛ ግዳጁ ዉጭ በከተማ ዉስጥ በፖሊስ ተግባር አዘዉትሮ ሲሰማራና ከሁኔታዉ ጋር እየተላመደ ሲሄድ ዋነኛ ተልእኮዉን ችላ ማለት ስለሚጀምር በሌላ ጊዜ ወደ መደበኛ ተልዕኮዉ ለመመለስ እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ የመከላከያ ግዳጅ አወጣጥ ላይ መዳከም ሲለሚያስከትል በሀገሪቱ ሉአላዊነት ላይ አደጋ መጋበዙ አይቀርም፡፡

መከላከያ በዉስጥ ጉዳይ ዉስጥ እንዲገባ መፍቀድ በተለምዶ በዉጭ ደህንነትና በዉስጥ ደህንነት መካከል የነበረዉን ልዩነት (traditional distinction between internal and external security) በማደብዘዝ አንዱን ከሌላዉ መለዬት በማያስችል ሁኔታ መደበላለቅን ይፈጥራል፡፡ በዚህ ምክንያትም የመከላከያ ተግባርና የፖሊስ ተግባር ልዩነት ለራሳቸዉ ለተቋማቱም ሆነ ለህዝቡ ግልጽ አይሆንም፡፤ ህዝቡም በመከላከያ ሰራዊቱና በፖሊስ መካከል ያለዉን የሃላፊነት ድርሻ መለየት ካልቻለ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የነበረዉ መልካም አመለካከት እየተሸረሸረ ይሄዳል፡፡ በዚህ ምክንያትም  ቀድሞ ለሰራዊቱ የነበረዉን ከበረታና አመኔታ እየቀነሰ  ሲሄድ ተስፋ እንዲቆርጥ ያደርገዋል፡፡ ህዝቡ በምንም ሁኔታ ቢሆን የመከላከያ ሰራዊቱን ወገንተኝነት መንግስት እንዲነጥቀዉ አይሻምና ፡፡

መከላከያን ከተዋጊነት ወደ ፖሊስነት በመቀየር በህግ ማስከበር ስራ ላይ  አዘዉትሮ እንዲሳተፍ ማድረግ የማይደገፍበት ምክንያቶች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ የጉዳዩ አጥኚዎች አበክረዉ የሚያስጠነቅቁት ሌላዉ ችግር ወታደሩ በቀላሉ የፖለቲካ ተዋናይ እንዲሆን  በር የሚከፍትለት ስለሆነም ጭምር ነዉ፡፡ ወታደር መደበኛ ተልእኮዉን ችላ እያለ ዋነኛ ትኩረቱን በዉስጥ ጉዳይ ላይ ማድረግ ሲጀምር ቀስ በቀስ የፖለቲካ ተዋናይ መሆን ይጀምራል የሚለዉ ስጋት በሰፊዉ የሚታመንበት ነዉ፡፡ ወታደር ከመደበኛዉ የግኑኝነት መስመሩ አልፎ በመሄድ ከፖለቲካ አመራሩ ጋር የማይገባ  መቀራረብ በመፍጠር ይጀምርና የተሰመረለትን ቀይ መስመር እያለፈ ቀስ በቀስ ከፖለቲካ ጋር ራሱን እያላመደ በመጨረሻም የለየለት ፖለቲከኛ ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡ የቀድሞ ገለልተኝነቱ ተረስቶ ቀንደኛ የፖለቲከኛ አራማጅ ይሆናል፡፡ ይህ የልብ ልብ ስለሚሰጠዉ ከዚያ በኋላ በህዝብ የተመረጠን ባለስልጣን በአደባባይ አስከ መተቸትና ከዚያም በላይ በመሄድ አገዛዙን በኃይል ለማዉረድ የሚደርስ እርምጃ ሊወስድ ይችላል፡፡ ባሰኘዉ ጊዜም የህዝቡን መብት ከመጋፋትም አልፎ በስልጣን ላይ ያለዉን አገዛዛንም ከመፈታተን ወደ ኋላ አይልም፡፡ ወታደር በፖለቲካ ዉስጥ ጣልቃ መግባትን የሚለማመደዉ ወይም እጁን የሚያፍታታዉ በቅድሚያ ራሱን ከህዝቡ ይልቅ የአገዛዙ ጠባቂ አድርጎ መቁጠር ሲጀምር ነዉ፡፡ አገዛዙን ከአደጋ ማዳን የቻለ ወታደር ለዚህ ተግባሩ ከመንግስት በተለያዩ መንገዶች የሚገለጽ ልዩ ጥቅም መጠበቁና ማግኘቱም የማይቀር ነዉ፡፡ በሌላ አባባል አገዛዙና ወታደሩ እርስበርስ መጠቃቀም ይጀምራሉ ማለት ነዉ፡፡ በከተማ ዉስጥ የአድማ ብተና፤ረብሻ፤ የተቃዉሞ ሰልፍ ሁከት፤አድማ ወዘተ የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ መደበኛ ፖሊስን እየተካ አዘዉትሮ የሚሳተፍ ወታደር አስቀድሜ እንደጠቀስኩት ከገለልተኝነቱና  የህዝብ ወገንተኝነቱ ባህሪይ እየወጣ  አደገኛ ወደሆነ ተቋሚነት በቀላሉ ሊቀየር ይችላል፡፤በዚህ ምክንያትም መከላከያ ሰራዊትን በዉስጥ ጸጥታ ማስከበር ተግባር በተለይም ህግ በማስከበር ስራ ላይ መሳተፍን በተመለከተ በመንግስት በኩል ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖር እንኳን በዜጎችና በፖለቲከኞች አካባቢ ግን ከጥርጣሬና ከስጋት በመነጨ መንፈስ በጽኑ ያወግዙታል፡፡

2.2/ በአፈጻጸም ወቅት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች

የከተማ ዉስጥ ህግ ማስከበር ተግባር ለመከላከያ ሰራዊቱ አባላት በጦር ሜዳ ከለመዱት በእጅጉ የሚለይ በመሆኑ መቸገራቸዉ የማይቀር ነዉ፡፡ የከተማ ረብሻና ሁከት መቆጣጠር ለመከላከያ ሰራዊት አባላት አስቸጋሪ ከመሆኑም ሌላ የሚያስከትለዉ ዉጤትም ቢሆን እንደታሰበዉ ሳይሆን ምነዉ በቀረ የሚያሰኝ ሊሆን ይችላል፡፡ በቀላሉ መፍትሄ ሊያገኝ ይችል የነበረ የጸጥታ ችግር እጅግ እንዲወሳሰብ የሚደረግበት አንዱ ምክንያት የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት የመደበኛ ፖሊስን ተግባር ተክተዉ እንዲሰሩ በመደረጉ ምክንያት ከልምድ ማነስ የተነሳ ሊፈጠር በሚችል ስህተት እንደሆነ የሌሎች አገሮች ልምድ ያሳያል፡፡ ምክንያቱም መከላከያ ሰራዊቱን ለዉስጥ ጸጥታ መጠቀም ለዉጭ ስጋት እንደ መጠቀም ቀላል ስለአልሆነ ነዉ፡፡ ሁለቱ ተልእኮዎች በባህሪያቸዉ እጅግ የተለያዩ ናቸዉ፡፡ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሚሰለሰጥኑት የሚታጠቁትና የሚደራጁበት አግባብ፤ እንደ መሪህ የሚከተሉት የዉጊያ ዶክትሪንና የግዳጅ አፈጻጸም ፍልስፍናዉና አስተሳሰቡ ሁሉ በጦር ሜዳ ከለየለት ጠላት ጋር ለመዋጋት ማለትም ለጦርነት እንጂ በከተማ ዉስጥ በገዛ ህዝቡ ዉስጥ ጸጥታን ለማስከበር ተብሎ አይደለም፡፡ እጅግ ብዙ ከሆነ የራሱ ህዝብ መሃል ገብቶ ምን ማድረግ እንዳለበትም  ስለማያዉቅ ግራ ይጋባል፡፡ በዙሪያዉና ከኃላና ከፊቱ ያሉት ወንድሞቹ፤ እህቶቹ ፤ ደሞዝ የሚከፍሉት የገዛ ወገኖች እንደሆኑ ሲያዉቅ እዚያ ቦታ የተገኘበትን ዕድል ይረግማል፡፡ በራሱ ህዝብ ላይ በሚወስደዉ እርምጃ ተገቢነት ላይም እምነት የለዉም፡፡ ለዚህ ድርጊቱ ከህዝቡም ሊያገኝ የሚችለዉ ምላሽ ላይም እርግጠኛ ስለማይሆን ሁኔታዉ ምቾት አይሰጠዉም፡፡

ይሄ ሁሉ ጭንቀትና ግራ መጋባት የሚፈጠረዉ መከላከያ ለዚህ ስራ የሚመጥን ስልጠና ስላልወሰደና ከዚህ ስራ ጋር አንዳችም ትዉዉቅ ስለለለዉ ነዉ፡፤ ወታደሮች ለዚህ ዓይነቱ ግዳጅ ከመሰማራታቸዉ በፊትም በቂ ገለጻ ተሰጥቶአቸዉ እንጂ ዝም ተብሎ “ሂድና ያን ረብሻ በትን” ተብለዉ ሊላኩ አይገባም፡፡ ያለበለዚያ የጦር ሜዳ ህይወት የመረረዉ ወታደር የከተማ ዉስጥ ረብሻን እንድበትን ትዕዛዝ እንደተሰጠዉ እየተንደረደረ መጥቶ ያለ አንዳች ሃሳብ በገዛ ወገኖቹ ላይ አላስፈላጊ  ጉዳት ሊያደርስ  ይችላልና ፡፡   

በጦር ሜዳ በግልጽ ከሚታወቅ ጠላት ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጦ መፋለምና እዚህ ከተማ ዉስጥ ከራሱ ህዝብ ጋር ጸጥታ ለማስከበር መሞከር በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸዉ፡፡ ለአንድ ወታደር ከራሱ ህዘብ ጋር በከተማ ዉስጥ ከሚፋጠጥ አንደኛዉኑ የለየለት ጦር ሜዳ ከጠላቱ ጋር ፊትለፊት ገጥሞ መዋጋትና በክብር መሞትን ይመርጣል፡፡ 

2.3/ ከሙያዉና ከተልእኮዉ ባህሪይ ልዩነት የሚመነጩ ተግዳሮቶች

የመደበኛ ፖሊስና የጦር ሰራዊት አባል ባህሪይ ( behavior) ተመሳሳይ ናቸዉ ማለት አይቻልም፡፤አንድ የመከላከያ ሰራዊት አባል የፖሊስን ባሀሪይ ተላብሶ በከተማ ዉስጥ ረብሻንና ሁከት ለመቆጣጠር እንዲሰማራ ከተፈለገ የግድ እንደ ፖሊስ ሆኖ መሰልጠን ይገባዋል፡፡ መከላከያን ወደ ፖሊሲነት ለመቀየር (police-ization of the military) የተፈለገዉ በፖሊሶች ቁጥር ማነስ ከሆነ መጀመሪያዉኑ ፖሊሶችን ቁጥራቸዉን በርከት አድርጎ ለምን እንዲሰለጥኑ አይደረግም የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ወታደርን በፖሊስ ሙያ ማሰልጠን ቢቻል እንኳን በሌላ ጊዜ ወደ መደበኛ የዉጊያ ተልእኮዉ መልሶ ለመጠቀም አዳጋች ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ወታደር የራሱ ከሆነዉ የተዋጊነት መንፈስና አስተሳሰብ (war fighting ethos) አንድ ግዜ ከተላቀቀ መልሶ ማምጣት ይከብዳልና፡፡  በፖሊስ ተግባር በከተማ ዉስጥ ለተወሰነ ጊዜ ያገለገለና የከተማ ሁኔታን የተላመደ ወታደር ወደ ጦር ሜዳ ተመልሶ ለመሄድ ፍላጎቱ የቀዘቀዘ ይሆናል፡፡

2.4/ በመከላከያና በፖሊሶች መካከል ከሚኖር መናናቅና ፉክክር የሚመነጩ  ተግዳሮቶች

በጸጥታ ኃይሎች መካካል አጉል ፉክክርና እርስበርስ መናናቅ ባለበት ስርአት ዉስጥ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ለዉስጥ ጸጥታ ተግባር ፖሊስን እንዲያግዙ  መጠራታቸዉን ፖሊሶችም ሆኑ ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ያለነሱ ድጋፍ መቆም እንደማይችሉ ደካማ አድርገዉ መቁጠራቸዉ የተለመደ ነዉ፡፡ ይህ የተዛባ  የግብዝነት (arrogance) አመለካከት ቶሎ ካልተገታና ስር እየሰደደ ሲሄድ ከፍተኛ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል የመስኩ አጥኚዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡ በመሰረቱ የጦር ኃይሉ አባላት ጸጥታ በማስከበር ተልኢኮ ሲሰማሩ ፖሊስን ተክተዉ እንዲሰሩ ሳይሆን ለፖሊስ የአጋዥነት ድርሻ (supporting role to the police) እንዲወጡ ነዉ፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ የጦር ኃይሉ አባላት ይህን የአጋዥነት ድርሻቸዉን አለቅጥ በመለጠጥ ለፖሊሶች አመራር ካልሰጠን ብለዉ ማስቸገራቸዉ አልቀረም፡፡

የመከላከያ ሰራዊት አባላት ካላሰኛቸዉ በስተቀር ፖሊሶችን አያስጠጓቸዉም፡፡ አብዛኛዉን ግዜ ጭራሽ ፖሊሶችን ከአካባቢዉ ገለል እንዲሉላቸዉ በማድረግ ሙሉ በሙሉ ለብቻቸዉ ሁኔታዉን ለመቆጣጠር ይፈልጋሉ፡፡ በፖሊስና በጦር ሰራዊቱ አባላት መካከል የዚህ ዓይነቱ አለመተማመንና መናናቅ  በህዝቡ ደህንነት ላይ ተጨማሪ ስጋት ይፈጥራል፡፡ ሌላዉ ቀርቶ መረጃዎችን አንዱ ለሌላዉ ለማጋራት እንደማይፈልጉ እንዲያዉም እንደሚደባበቁ ይነገራል፡፡ ይህ ሁኔታ የሀገሪቱን ደህንነት ሊጎዳ እንደሚችል ግልጽ ነዉ፡፡ በአብዛኛዉ የንቀት አመለካከት  ጎልቶ የሚታየዉ በጦር ሰራዊት አባላቱ ላይ ነዉ፡፡ ፖሊሶች በተለምዶ የጦር ኃይሉን ያህል ጠቀም ያለ ባጄት ስለማይመደብላቸዉና ጥራት ያለዉ ስልጠናም ስለማይሰጣቸዉ፤ ለስራቸዉ የሚመጥን የተሟላ ትጥቅም ስለማይኖራቸዉ እንዲሁም በሎጂስትክም ደካማ እንዲሆኑ ስለሚደረጉ ሁልጊዜም የመከላከያ (ጦር ሰራዊቱ) ጥገኛና የነሱን ድጋፍና እገዛ ጠባቂ እንዲሆኑ ይገደዳሉ፡፡ 

በመካከላቸዉ ትብብር አለመኖሩና መናናቁ በሁለቱ በመሰረታዊ አባላት ደረጃ ብቻ የተገደበ ሳይሆን እንዲያዉም ጎልቶ የሚታየዉ በተቋማቱ አመራሮችና የበላይ ኃላፊዎች ደረጃ ነዉ፡፡ በመሰረታዊ አባሉ ላይ የሚታዉ የልዩነት መንፈስ  ከላይ በአመራሩ ደረጃ ያለዉ ችግር ነጸብራቅ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ በርግጥ በመከላከያ፤ በፖሊስና በሌሎች ታጣቂ ኃይሎች መካካል ያለመጣጣም መኖር የዳበረ ዲሞክራሲ በገነቡ አገሮችም ቢሆን የሚጠላ አይደለም፡፤በታጣቂዎች መካከል መግባባት አለመኖሩና አንዱ የሌላዉ ጠባቂና ተቀናቃኝ  ኃይል (counterbalance) መሆኑ  ለአገዛዙ ደህንነት በጣም ጠቃሚ ተደርጎ ስለሚቆጠር  ልዩነቱን ለማጥፋት ግዜና ጉልበት ማባከን አያስፈልጋቸዉም፡፡

2.5/ ፖሊሶችንና የመከላከያ አባላትን በአንድነት አቀናጅቶ ለማሰማራት አደጋች መሆኑ

የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ፖሊሶች በአንድ ላይ ለጸጥታ ማስከበር ሲሰማሩ ቶሎ መግባባትና እርስበርስ መናበብ ያለመቻልና ለማቀናጀትም  (Military-police interoperability) አስቸጋሪ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የተለያዩ ባህሪያት ያላቸዉን ሁለቱን ተቋማት በአንድ ላይ አጣምሮ ለተመሳሳይ ተግባር ማሰማራት (synergyy) በጣም አስቸጋሪ ነዉ፡፡ ሁለቱም በግዳጃቸዉ ወቅት የለመዱት ፍጹም የተለያዩ የግዳጅ አፈጻጸም ባህሪይና ፕሮሲጄር ነዉ፡፡ ሁለቱን ሊያግባባ የሚችል የጋራ የሆነ የግዳጅ አፈጻጸም ቋንቋና ፕሮሲጄርም ስለለለ መደነጋገር ማስከተሉ የማይቀር ነዉ፡፤የመከለከያ አባላት የራሳቸዉ የሆነ የግዳጅ ወቅት መግባቢያ ቋንቋ (mission language) አላቸዉ፡፡ በግዳጅ ወቅት ትዕዛዝ የሚተላለፍባቸዉና ሪፖርት የሚደረግባቸዉ ቃላትና ፎርማት ፖሊሶች ከሚጠቀሙት የተለየ ነዉ፡፡ በዚህ ምክንያትም አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ ይህን በሚመለከት አንድ አብነት ልጥቀስ፡፡ በ1992ዓ/ም በአሜሪካ በሎስ አንጀለስ በተከሰተዉ ረብሻና የንብረት ማዉደም ያካተተ አመጽ በፖሊሶች አቅም ብቻ ለመቆጣጠር ባለመቻሉ  አርሚዉንና ማሪን ወታደሮች እንዲያግዙ በተደረገበት ወቅት የታዬዉ መደነጋገር እንደ አብነት የሚጠቀስ ነዉ፡፡ በወቅቱ የታጠቁ ረብሸኞችች ተሸሽገዉበታል ተብሎ የተጠረጠረን አንድ ህንጻ ፖሊሶች ሰብረዉ ለመግባት በማቀድ ማሪን ወታደሮችን ሽፋን እንዲሰጧቸዉ ፈልገዉ “ሽፋን ስጠኝ (cover me)“ ሲሏቸዉ ማሪን ወታደሮች ለዚህ ምላሽ የሰጡት በቅጽበት በህንጻዉ ላይ የተኩስ ዉርጅብኝ በመክፈት ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በዉስጡ የነበሩ ህጻናት ሳይቀሩ ያለ አግባብ ለአደጋ ተዳርገዋል፡፡ በፖሊሶች ቋንቋ ሽፋን ሲጠኝ ማለት “ምናልባት ችግር ካጋጠመኝ የተኩስ ሽፋን ለመስጠት እንድትችል ተዘጋጅተህ ተጠባበቅ” የሚል እንድምታ ያለዉ እንጂ በቅጽበት ተኩስ ክፈት ማለት አልነበረም፡፡ ማሪኖች በወቅቱ መተኮሱን እንዲያቆሙ ማድረግ የተቻለዉም ከስንት መጯጯህ በኋላ  ለዚያዉም ከ200 በላይ ጥይት ከተኮሱ በኋላ እጅግ ዘግይቶ ነዉ፡፡ የአሜሪካ መንግስት ይህ ችግር ከተገነዘበ  በኋላ አርሚዉንና ማሪን  ወታደሮችን ስለከተማ ዉስጥ ረብሻና አድማ ብተና በፕሮግራም ተይዞ አጫጭር ስልጠና እንዲሰጥና በዚህ ስልጠና ስር ያለለፈ ወታደር በከተማ ጸጥታ ማስከበር በጭራሽ እንዳይሳተፍ እስከማድረግ ደርሰዋል፡፡ በተጨማሪ ፖሊስና መከላከያ አባላትን በጋራ ለመጠቀም የሚስችል የጋራ የአፈጻጸም መመሪያም እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡ 

2.6/ ከመርህና ከዶክትሪን ልዪነቶች የሚመነጩ ተግዳሮቶች ፤

ፖሊሶች በዋነናነት የሚሰለጥኑት አነስተኛና ወይም የተመጣጠነ ኃይልን (minimum force)በመጠቀም መሪህ ነዉ፡፡ ለዚያዉም አነስተኛ  ኃይልም ቢሆን መጠም የሚፈቀድላቸዉ ሁኔታዉ ከአቅም በላይ ሲሆን ወይም  ኃይልን መጠቀም የሚያስገድድ ሁኔታ ሲፈጠር ብቻ ነዉ፡፡ እዚያ ደረጃ ከመድረሳቸዉ በፊትም መከተል ያለባቸዉን ቅደም ተከተል ጠንቅቀዉ ያዉቃሉ፡፡ መከላከያ ሰራዊት ግን በጦርሜዳ ከጠላቱ የበለጠ ኃይል መጠቀምን (maximum force) ወይም የተኩስ የበላይነትን (fire superiority)እንደተገቢ መርህ ይከተላል፡፡  ጠላትን ማሸነፍ የሚችለዉ የኃይል የበላይነት ሲኖረዉ እንደሆነ ስለሚያዉቅ በተቻለ መጠን ጠላት መቋቋም የማይችለዉን ኃይል ለመጠቀም ይሞክራል፡፡  በከተማ ዉስጥ ረብሻን ለመቆጣጠር ሲሆን ግን መጀመሪያ ነገር “ጠላት“ የሚባል ነገር የለም፡፡ ሁከት ፈጣሪ የተባለዉ ያ ሰዉ ምንም ያድርግ ምን የሀገሪቱ ዜጋ ነዉ፡፡ በከተማ ዉስጥ እንደ ጦር ሜዳ ማሸነፍና መሸነፍ የሚባል ነገርም አይሰራም፡፡ ህገመንግስታዊ መብቱን ለመጠየቅ የወጣ ዜጋ ላይ በመተኮስ አሸናፊ መሆን አይቻልም፡፡ በጠላት ላይ እንዲጠቀምበት የተሰጠዉን መሳሪያ በወገኑ ላይ ተጠቅሞ የገዛ ወገኑን በመግደል የሚገኝ ክብር አይኖርም፡፡ የታጠቀዉን ጠበንጃ ገዝቶ የሰጠዉና የወር ቀለብ የሚሰፍርለት ፤ደሞዝ የሚከፍለዉ ይሄዉ ህዝብ ነዉ፡፡ አንድ መኮንን በትከሻዉ ላይ የሚደረድረዉ ኮከብ ብዛት በጦር ሜዳ በጠላት ላይ ባሳየዉ ጀግንነት የሚለካ እንጂ በከተማ ዉስጥ በገዛ ወገን ላይ በጣለዉ ግዳይ መጠን አይደለም፡፡ የገዛ ህዝብ ላይ ጥይት በማስተኮሱ ከመንግስት ምስጋና ወይም ሹመት አይጠበቅም፡፡ በራስ ወገን ላይ ጥይት የሚተኩስ ወታደር  በህዝብ መሃል በኩራት መራመድ ያሳፍረዋል፡፡ ለወትሮዉ ከህዝብ ከሚያገኙት ፍቅርና አክብሮት ዉጭ ለሚያበረክቱት የህይወትና የኣካል መስዋእትነት አንዳችም ሌላ ተመጣጣኝ ከፍያ ለማይጠብቁት የመከላከያ  ሰራዊት አባላት የህዝቡ ፊት መንሳትና ፍቅሩን መቀነስ ፈጽሞ መቋቋም የማይችሉት የልብ ህመም ነዉ የሚሆንባቸዉ፡፡ 

የከተማ ዉስጥ ረብሻ፤ዝርፊያ፤ ሁከት፤ የተቃዉሞ ሰልፍ ፤አመጽ፤ነዉጥ፤አድማ ወዘተ ምንም ይባል ምን ህግን የመተላለፍ ሁኔታ ከተፈጸመ አጥፊዎች ተለይተዉ እንደ አስፈላጊነቱ በእስር ወይም በሌላ መልኩ የሚስያቀጣ ሊሆን ይችላል እንጂ የሞት ፍርድ የሚያስፈርድ አይደለም፡፡ በከተማ ዉስጥ ሁከት የፈጠረ ዜጋ በመደበኛዉ ፍርድ ቤት ተከሶ ቢቀርብ የሞት ቅጣት የማያስፈርድበት ሆኖ እያለ ጸጥታን ለማስከበር በተሰማሩ ፖሊሶች ወይም ወታደሮች ፍርድ ቤቶች እንኳን የማይወስኑትን በራሳቸዉ ብይን በመስጠት ተኩሰዉ  መግደል ወይም በሞት መቅጣት የአካል ጉዳት ማድረስ ወዘተ ከሀገሪቱ ህግ ጋር የሚጋጭ ተግባር ነዉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ስህተት ከፖሊሶች ይልቅ በመከላከያ አባላት ላይ ተዳጋግሞ የሚታይ ነዉ፡፡ እንደ ፖሊሶች ለዚህ ስራ የሚስፈልገዉን ስልጠናና ልምድ ስለማይኖራቸዉ ወታደሮች ረብሻን በትዕግስት ለመቆጣጠር ስለሚቸገሩ ስህተት ለመስራት በእጅጉ የተጋለጡ ናቸዉ፡፡ 

2.7/ የህግ ተጠያቂነት አንጻር ያለዉ የአረዳድ ልዩነት ምክንያት የሚመነጭ  ተግዳሮት፤

ወታደር በጦር ሜዳ ጠላቱን በመግደሉ ይሾማል ይሸለማል እንጂ በህግ አይጠየቅበትም፡፡ ገዳይ ያልሆነ ትጥቅ ብሎ ነገርም በመከላከያ አባላት ዘንድ አይታወቅም፡፡ ፖሊሶች ለሚሰሩት የህግ ጥሰት በሃላፊነት እንደሚጠየቁበት በስልጠናና ከተሞኩሮም ካገኙት ግንዛቤ ሌላ መደበኛ ዕለታዊ  ስራቸዉም ቢሆን በአብዛኛዉ ከህግ ጋር የተቆራኘ ስለሆነ  የህግ ጥሰት ላለማድረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡ የመከላከያ አባላት ግን የፖሊሶችን ያህል ትእግስትና መጨነቅ ሳያስፈልጋቸዉ ፈጥነዉ ያሻቸዉን እርምጃ የመዉሰድ ልማድ አዳብረዋል፡፡ ከአጥፊ ጋር መደራደርና ማግባባት የሚባል ነገር በከተማ ዉስጥ ለፖሊሶች ካልሆነ በስተቀር በጦር ሜዳ ጨርሶ የሚታሰብ አይደለም፡፡ በከተማ የጸጥታ ማስከበር ተግባር ወቅት ፖሊሶች በስህተትም ቢሆን ላቆሰሉትም ሆነ ለገደሉት ለእያንዳንዱ ዜጋ ተጠያቂነት ሲላለባቸዉ ጥፋት ካደረሱ ለምን እንዳደረጉ አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ ይገባቸዋል፡፡ የመከላከያ ሰራዊት አባል ግን በተሰለፈበት ጦር ሜዳ ጠላቱን ተኩሶ  ቢገድል ለምን እንደገደለ ማብራሪያ እንዲሰጥ አይጠየቅም፡፡ እንዲያዉም ጠላቱን መግደል እየቻለ ባይገድለዉ ነዉ ሊጠየቅበት የሚችለዉ፡፡ በጦር ሜዳ በዚያኛዉ ወገን የተሰለፈዉን እንደርሱዉ ሰብአዊ ፍጡር የሆነዉን “ጠላት” መግደል የሚያሸልምና የሚያሾም እንጂ የሚስያቀጣ ወንጀል አይደለም፡፡ ጠላትን መግደል ግዴታም ነዉ፡፡ ወታደር የሚሰለጥነዉም ጠላቱን በደንብ አድርጎ እንዲገድል ነዉ፡፡ በጦር ሜዳ በዚያኛዉ በኩል ያለዉ አንዳችም የቆየ የግል ጠብ  ሳይኖረዉ እንዲያዉም ከዚህ ቀደም በጭራሽ አይቶት የማያዉቀዉ ሆኖ እያለ  ዕድሉን ካገኘ ቀድሞ ሊገለዉ የመጣ ጠላት መሆኑን ስለሚገነዘብ ሳይቀደም  ተንደርድሮ ሮጦ ሳንጃ ደረቱ ላይ ይሰካል፡፡ በቦንብ ያጋየዋል፡፡ በጥይት ተኩሶ ይጥለዋል፡፡ ያን ማድረግ እንደጤነኛ ድርጊት ተደርጎ ነዉ የሚቆጠረዉ፡፡ ይህ ድርጊት ያሸልማል እንጂ አያስወቅስም፡፡ ጠላቱን ለመግደል እምቢተኛ ቢሆን ግን ጠላቱ ቀድሞት ይገድለዋል፡፡ ካልሆነም እንደወታደር ማድረግ የሚገባዉን ባለማድረጉ ተከሶ ከባድ ቅጣት ይቀጣል፡፡

በጦር ሜዳ የአንድት ጥይት ድምጽ መስማት ምንም ስሜት የማይሰጥ ተራ ክስተት ነዉ፡፡ በአንጻሩ በከተማ ዉስጥ አንድት የፖሊስ ጥይት ድምጽ መስማት ብዙ የፖለቲካ መዘዝ ታስከትላለች፡፡ ለዚህም ነዉ ፖሊሶች በከተማ ዉስጥ ገዳይ ያልሆኑ የረብሻ መበተኛ መሳሪያ እንዲጠቀሙ የሚገደዱት፡፡ ፖሊሶች ረብሻን ለመበተን ዋነኛ ትጥቃቸዉ ገዳይ ያልሆኑ አድማ መበተኛ መሳሪያዎች እንጂ ገዳይ የሆኑ መሳሪያዎች አይደለም፡፡ በጦር ሜዳ ግን አንድ ወታደር “ገዳይ ያልሆነ መሳሪያ” ስለሚባል ነገር ሰምቶም አይቶም ላያዉቅ ይችላል፡፡ ወታደር ስለማይገድል መሳሪያ  ቢነገረዉ ግራ ይጋባል እንጂ ቶሎ አይገባዉም፡፡ በጦር ሜዳ በጣም ተፈላጊዉ ነገር ጠላቱን በደንብ አድርጎ የሚገድል መሳሪያ መጠቀምን ነዉ፡፡ በጦርሜዳ አስለቃሽ ጋዝ፤የፖሊስ ቆመጥ፤ ዉሃ ፤ማስፈራራት፤ ማስጠንቀቂያ መስጠት የሚባል ነገር ጭራሽ አይታወቅም፡፡ ስለነዚህ ነገሮች ማሰብ በራሱ አስቂኝ  ነዉ፡፡

የመከላከያ አባላት በከተማ ጸጥታ ማስከበር እንዲሳተፉ ሲደረግ “ገዳይ ያልሆነ” ስለሚባለዉ መሳሪያ ትዉወቅ ስለሌላቸዉ ሁኔታዉ አስገድዶ በዕለቱ ቢታደላቸዉ እንኳን እንዴት አድርገዉ መጠቀም እንዳለባቸዉ የሚያዉቁት ነገር የለም፡፡ በከተማ አድማ ብተና ወቅት ፖሊሶች ልምዱ ሲላላቸዉ በተቻለ መጠን ከአድማ መሪዎች ጋር  ለመደራደር፤ለማግባባትና ለማረጋጋት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ የድንጋይ ዉርጅብኝ እየወረደባቸዉምና እየተጎዱም ቢሆን አስከመጨረሻ በመታገስ የአድመኞችን ቁጣ ለማብረድ ጥረት ያደርጋሉ እንጂ እንዴት ተናቅን ብለዉ ፈጥነዉ ተኩስ አይከፍቱም፡፡ ወታደር ግን ረብሻ እንዲበትን ሲላክ ረብሻዉ ያለበት አካባቢ እንደደረሰ ነገሩን እንኳን በቅጡ ሳያጣራ መሳሪያዉን ለመጠቀም ይጣደፋል፡፡ ወታደር የሰለጠነዉና ለበርካታ ዓመታት የተለማመደዉ እንደዚህ ስለሆነ ጥፋት ቢያጠፋ አያስገርምም፡፡ መወቀስ ያለባቸዉ ወታደርን ያለሙያዉና ያለስራዉ  ለዚያዉም ሳያሰለጥኑት በከተማ ዉስጥ በገዛ ህዝቡ መሃል ያሰማሩት  የበላይ አለቆቹ መሆን አለባቸዉ፡፡

2.8/ የመከላከያ አባላት እንደ ፖሊሶች ከማህበረሰቡ ጋር ጠንካራ ትሰስር ስለለላቸዉ የመረጃ እጥረት ይገጥማቸዋል፡፡

ፖሊሶች በከተማ ዉስጥ ከአብዛኛዉ ህዝብ ጋር ትዉዉቅ አላቸዉ፡፡ መረጃ የሚያገኙበት ዜዴም ይኖራል፡፡ የአድማ አስተባባሪዎችና ቀንደኛ ሁከት ፈጣዎችን ማንነት ፖሊሶች አስቀድሜዉ በሚገባ ስለሚያዉቁ ለይቶ በማዉጣት በቁጥጥር ስር ለማድረግ ወይንም ከረብሻዉ በፊት አግኝተዉ ለመደራደርና ለማስጠንቀቅ ወይንም ደግሞ ከረብሻ በኋላ ቀንደኞችንና የአመጽ አስተባባሪዎችን አሳደዉ ለመያዝ አይቸገሩም፡፡ ከጦር ሜዳ የመጣ ወታደር ግን በከተማ ዉስጥ ይሄን ማድረግ የሚያስችለዉ የግኑኝነት መረብ የለዉም፡፡ ከነዋሪዉ ጋርም ትዉዉቅ አይኖረዉም፡፡ ስለዚህ  የፖሊሶች ጥገኛ ለመሆን ይገደዳል፡፡

3/ ለወደፊቱ ምን መደረግ አለበት?

3.1/ ለከተማ ዉስጥ ህግ ማስከበር ተግባር ከፖሊስ ይልቅ መከላከያን ተመራጭ የማድረግ የተዛባ አመለካከት ሊታረም ይገባዋል፡፡

መከላከያ ሰራዊቱን ለህግ ማስከበር ተግባር መጠቀም የሚደገፍ አሰራር አይደለም፡፡ ከፖሊስና ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች አቅም በላይ ካሆነ በስተቀር መከላከያን  ለዚህ ዓይነቱ ተግባር መጠቀም ተገቢም አዋጭም አይደለም፡፡ መከላከያን መጠቀም የግድ የሚደርጉ ልዩ ሁኔታዎች ምን ምን እንደሆኑ በቅድሚያ ታስቦበት የጋራ አረዳድ ሊያዝበት ይገባል፡፡ ለየትኛዉ ዓይነት የጸጥታ ችግር ነዉ መከላከያ መጠራት ያለበት? የሚለዉ ጥያቄ ቀላል ጥያቄ አይደለም፡፡ ፡በአንድ  አካባቢ ትንሽ ረብሻ ወይም ሁከት በተፈጠረ  ቁጥር በቅርብ ያለዉን መከላከያ ሰራዊት መጥራት ተገቢነት አይኖረዉም፡፡  ሰላማዊ ሰልፍና ያን ተከትሎም ሁከት አመቱን ሙሉ ሊከሰትን ይችላል፡፡ ይህ እንደ ጤናማ ሁኔታ መታየት ያለበት እንጂ መንግስትን የሚያስበረግግ ሊሆን አይገባም፡፡ የዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲኖር በተቻለ መጠን ለዚህ ተግባር በሰለጠኑ የጸጥታ ኃይሎች (ፖሊሶች)  መጠቀም ይገባል፡፡ በአንድ አካባቢ  የተፈጠረ ሁከት ምን ደረጃ ላይ ሲደርስ ነዉ  መከላከያ መጠራት የሚገባዉ የሚለዉ ጉዳይ ለፖሊሶች መተዉ ያለበት አይደለም፡፡ ፖሊሶች በተለምዶ ለትንሽ ለትልቁም ችግር ቢሆን መከላከያን የመጥራት ልማድ ስለአለባቸዉ ነዉ፡፡ የሚገባቸዉን ያህል ጥረት ሳያደርጉ ተቻኩለዉ መከላከያን የመጥራት አባዜ አለባቸዉና፡፡

3.2/ ለጸጥታ ማስከበር የተሰማራ ወታደር ሁኔታዉ ከተረጋጋ በኋላ በፍጥነት አካባቢዉን ለቆ መዉጣት ይገባዋል፡፡

መከላከያ ሰራዊት ከነሙሉ ትጥቁ በቡድን ሆነዉ ከተማ ዉስጥ በየመንገዱና በየመንደሩ መንቀሳቀስ ለዜጎች ምቾት አይሰጥም፡፡ ህዝቡ ጭራሽ የበለጠ እንዲሰጋ ያደርግዋል፡፡  ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊቱ ከፍተኛ አክብሮትና ፍቅር ቢኖረዉም በየመንደሩ እየዞረ የፖሊስን ስራ ሲሰራ ማዬት አያስደስተዉም፡፡ የወታደራዊ የብረት ቆብ (ሄልሜት) ያደረገና በብረት ለበስ ተሸካሪ የታገዘ ወታደር በከተማ ዉስጥ በህዝብ መሃል ሲታይ ምቾት ይነሳል፡፡ መከላከያ አባላት በጸጥታ ማስከበርና ተግባር ላይ በቀጥታ ከማሰማራት ይልቅ የተሻለ የሚሆነዉ ፖሊሶችን በመተካት በፖሊሶች ሲጠበቁ የነበሩ ተቋማትንና ቁልፍ ቦታዎችን ተረክቦ ጥበቃ በማድረግ እንዲያግዝና ፖሊሶች በሙሉ ኃይላቸዉ ረብሻ ወደ መቆጣጠር ተግባር ላይ እንዲሳተፉ ቢደረግ የተሻለ ነዉ፡፤ለምሳሌ ባንክ ቤቶች፤ የቴሌ፤ መብራት ኃይል፤ ቴሌቭዥንና ሬዲዮ ጣቢያ ፤ የአይሮፕላን ማረፊያ ፤ጉምሩክ፤  የባቡር ጣቢያ ፤ትላልቅ ድልድዮችን  ወዘተ የመሳሰሉ ቁልፍ ጥበቃ ፤ላይ የተሰማሩትን ፖሊሶች ለግዜዉ በመተካት  ሊያግዝ   ይችላሉ፡፡

3.3/ የጸጥታ ኃይሎችንን የግል ማንነት መለየት የሚያስችል ምልክት ማድረግ አለባቸዉ፡፡ 

አንዳንድ ግዜ የጽጥታ ኃይሎች አግባብነት የለለዉ ድርጊት ሊፈጽሙ ስለሚችሉ ለይቶ ተጠያቂ ለማድረግ ወይንም ጥቆማ ለመስጠት እንዲቻል ማንነታቸዉን የሚገልጽ በጉልህ የሚታይ ምልክት ወይም መለያ ቁጥር በአልባሳታቸዉ ላይ  ሊኖር ይገባል፡፡ በተጨማሪ መከላከያ ሰራዊትን መጠቀም የግድ ሆኖ ሲገኝ  የፖሊሲን ዩኒፎርም አልብሶ ማሰማራት ተገቢ ስለማይሆን በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡

3.4/ የጸጥታ ሃይሎች የህግ ተጠያቂነት ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱ አባላትም ሆኑ ፖሊሶች የዜጎችን ደህንነት በማስከበርና ህግና ስርአትን ለማስፈን በሚያደርጉት ጥረት ሂዴት ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታና በጫና ዉስጥ ሆነዉ በራሳቸዉ ዜጎች ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡ የቱንም ያህል ጥንቃቄ ቢደረግ ይህ ሁኔታ በጭራሽ እንዳይከሰት ማድረግ አይቻልም፡፡ ዋናዉ ጥያቄ መሆን ያለበት መከላከያም ሆኑ ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች በበላይ አካል ታዘዉ የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅና ህገመንገስታዊ ስርአቱን ለማስከበር ተልኢኮ ላይ እያሉ በዜጎች ላይ አላግባብ ያደረሱት ጥፋት ሲኖር የተጠያቂነት ጉዳይ (liability) እንዴት ባለ መንገድ ነዉ የሚታየዉ?  የሚለዉ ጉዳይ በሚገባ መጥራት የሚገባዉ ይመስለናል፡፡ ወታደሮች አዉቀዉም ይሁን ከቁጥጥራቸዉ ዉጪ በሆነ ምክንያት በገዛ ህዝባቸዉ ላይ ጉዳት ሲያደርሱ ከደረሰዉ ጉዳት የበለጠ ህዝቡን የሚያስከፋዉ መንግስት በአጥፊዎች ላይ ተገቢዉን እርምት  ሳይወስድ ጭራሽ ለመሸፋፈን ከሞከረ ነዉ፡፡ ይህ ሁኔታ ህዝቡ በመንግስት ሆነ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ  አመኔታ እንዳይኖረዉ ያደርጋል፡፡

መንግስት በሰላማዊ ሰልፍ ወይም ሁከት ወቅት በየትኛዉም ወገን የደረሰ ጉዳት ካለ ጉዳቱን ማንም ያድርስ ማን ሳይደባብቅ ገለልተኛ በሆነ አካል እንዲጣራ ተደርጎ ለህዝብ ይፋ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ይህ ጉዳይ በይበልጥ የሚመለከተዉ የሀገሪቱን ህግ አዉጭና የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ነዉ፡፡ ህዝቡ በመንግስት ላይ አመኔታ የሚያሳድረዉም መንግስት የህግ ጥሰትን ችላ እንደማይልና ማንም ይሁን ማን የመንግስት ወታደርም ቢሆን ጥፋት ከተገኘበት በህግ ከመጠየቅ የማይድን መሆኑን ሲገነዘቡ ነዉ፡፡

በወቅቱ  ከተገቢዉ በላይ ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅመዉ ከሆነና ይህን ያደረጉት  ከበላይ መመሪያ ዉጭ በግላቸዉ ያደረጉት ከሆነ በግል ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ከዚያ ዉጭ ግን በቅርብ አለቆቻቸዉ ትእዛዝ የደረሰ የህግ ጥሰት ካለና የሀገሪቱ የወንጀል ህግ በሚፈቅደዉ መሰረት ትዕዛዙን የሰጠዉ አካል ወይም ግለሰብ በህግ ተጠያቂ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የዚህ ዓይነት የህግ ተጠያቂነት ካለ በመንግስትና በህዝብ መካከል ከፍተኛ መተማመን ይፈጠራል፡፡ የፀጥታ ኃይሎችም ተጠንቅቀዉ ስራቸዉን እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚያ ዉጭ ግን የመንግስት ባለስልጣናት ከህጉ አግባብ ዉጭ በዜጎች ላይ ጉዳት ያደረሱ የጸጥታ ኃይሎችን ጥፋት በመደባበቅ መንግስትን ተወዳጅ ማድረግ ከቶ እንደማይቻል ሊረዱ ይገባል፡፡  በሰራዊቱም ሆነ በመንግስት ላይ የህዝቡን ዓመኔታ የሚያሳጣዉም ጥፋተኞችን መንግስት መደባበቅና እንዳይቀጡ ከለላ መስጠት ሲጀምር ነዉ፡፡ የሰራዊቱ መሰረታዊ አባላትም ሆኑ ወታደራዊ አዛዦች የህግ ጥሰት ካደረሱ ተጠያቂ እንደሚሆኑና  ከህግ በላይ መሆን እንደማይችሉ ሲረዱ በተሰማሩበት ተልዕኮ ላይ  ተጠንቅቁዉ ሃላፊነታቸዉን እንዲወጡ ያደርጋቸዋል፡፡

ወታደሮች በግዳጃቸዉ ወቅት የሚገጥማቸዉ አንድ ፈታኝ ጉዳይ ቢኖር  በአንድ በኩል ወታደራዊ ትእዛዛን የማክበር ግዴታ (obedeniece to superior order) እንዳለባቸዉ ተገንዘበዉ ያለአንዳች ማመንታት የመተግበር ግዴታ ያለባቸዉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በግዳጅ አፈጻጸም ወቅት ስህተት ሲፈጠር በህግ ተጠያቂነት (liability) ስጋት መኖር ነዉ፡፡ ይህ ጉዳይ ይበልጥ ዉስብስብ የሚሆነዉ በራስ ህዝብ ዉስጥ የጸጥታ ማስበር በሚሰራበት ወቅት ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ ጥርት ያለ መመሪያ ከለለ ወታደሮች በወታደራዊ ትዕዛዝ ማክበርና ወንጀል ባለመፈጸም መካከል አጣብቂኝ ዉስጥ ስለሚገቡ በራስ መተማመናቸዉ ስለሚሸረሸር በግዳጅ አፈጻጸማቸዉ ላይ ጫና ያሳድራል፡፡

3.5/ መከላከያ ፖሊስን የሚያሰለጥንበት አካሄድ እንደገና ሊጤን ይገባዋል

በየትኛዉም ሀገር ያለ ጦር ኃይል (መከላከያ) ከፖሊስ ኃይል አንጻር ሲታይ እጅግ የተደራጀና በሁሉም ረገድ ጠንካራ አቅም እንዳለዉ ይታወቃል፡፤ ከዚህ አንጻር ሲታይ መከላከያ ስራዊት ፖሊሶችን ቴክኒካዊ በሆኑ ሁኔታዎች የማገዝ በሎጂስትክስ ለምሳሌ ተሸርካሪዎችን በስጦታ በመስጠት፤ የግኑኝነት መሳሪያዎች ረገድም የሞችለዉ እገዛ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ መከላከያ በደንብ የተደራጁ ማሰልጠኛ ተቋማት ሲለሚኖሩት ምልምል ፖሊሶችን ሆነ አመራሮችን ተቀብሎ በስልጠና ቢያግዝ የሚያስከፋ ሳይሆን የሚያስመሰግን ተግባር ነዉ የሚሆነዉ፡፡ ነገር ግን ጥያቄ የሚያስነሳዉ ጉዳይ ጦር ሰራዊት (መከላከያ) ፖሊስን በተጨባጭ ምንድነዉ የሚያስተምረዉ የሚለዉ ጥያቄ ነዉ፡፡ 

መከላከያ ፖሊስን የሚያሰለጥነዉ አድማ ብተና ሰላማዊ ሰልፍና ሌሎች የከተማ ዉስጥ ሁከት መቆጣጠር ላይ ነዉ ወይንስ ምንድነዉ የሚያስተምረዉ? የተጠቀሱት ጉዳዮች ደግሞ ለራሱ ለመከላከያ ሰራዊቱም እንግዳ በመሆናቸዉ  ከፖሊሶች መማር የሚገባዉ ሆኖ እያለ ጭራሽ አሰልጣኝ መሆን መቻሉ ግር የሚያሰኝ ነዉ፡፡ መከላከያ ፖሊሶችን ምንድነዉ ሊያስተምር የሚችለዉ? በጦር ሜዳ ዉጊያ ነዉ የሚያስተምረዉ እንዳይባል ፖሊሶች የሚያስፈልጉት በህዝብ መሃል ሆነዉ ጸጥታ እንዲያስከብሩ እንጂ ጦር ሜዳ ተገኝተዉ እንዲዋጉ አይደለም፡፡ ለፖሊሶች የክላስዊዝን ወይም ሳን-ዙ ዉጊያ ጥበብ ለማስተማር ከሆነ ይህ ደግሞ ተገቢ አይሆንም፡፡ መከለከያ  ፖሊሶችን በጦርነት የዉጊያ አስተሳሰብ እየቀረጹ ከሆነ በዚያ መንገድ የሰለጠኑትን ለጦርሜዳ እንጂ ለከተማ ዉስጥ የፖሊስ ተግባር መጠቀም ትክክል አይሆንም፡፡ የተዋጊ ሰራዊት አመለካከት፤ ባህሪይና ፍልስፍና  (Warrior Ethos) ተላብሶ የወጣ ፖሊስ በገዛ ህዝቡ ዉስጥ ሆኖ የፖሊስ ተግባርን ማከናወን እጅግ ያስቸግረዋል፡፡ የመከላከያ ሰራዊት እሴት፤ ሞራል፤ ቀስቃሽ መሪ መፈክሮች (motto)፤ስነልቡና ወዘተ ሁሉ ለፖሊስ ሙያ የሚመቹ አይደለም፡፡ ስለዚህ በጦር ሰራዊቱ  አሰልጣኞች ለፖሊሶች የሚሰጠዉን ስልጠና ስርአተ ትምህርትና መርሃ ግብር በደንብ ሊፈተሸ ይገባዋል፡፡ አንድን ወጣት ጥሩ ተዋጊ ወታደር አድርጎ ማሰልጠንና ጥሩ ፖሊስ አድርጎ ማዘጋጀት ለየቅል ናቸዉ፡፡ በጦርነት አስተሳሰብ አንድ ጊዜ የተቀረጸን ወታደር እንደ ፖሊስ ሆኖ እንዲሰራ ሲደረግ የለበሰዉ ዩኒፎርም ይቀየር እንደሆን እንጂ  ዉስጡ ያለዉ የፖሊስነት ባህሪይ ሳይሆን የጦር ሰራዊት ወታደር ነዉ፡፡

3.6/ ባልተሟላ ተጥቅ የማሰማራት አሰራር መስተካከል አለበት

ወታደሮች ብዙዉን ጊዜ በከተማ ሰላማዊ ሰልፍን ወይም የህዝብ ተቃዉሞ ለመቆጣጠር የሚያስፈልጋቸዉን ትጥቅ አይኖራቸዉ፡፡  ወታደሮች ብዙዉን ጊዜ ለዚህ ተግባር ሲጠሩ የተለመደዉን መደበኛ ትጥቃቸዉን ይዘዉ ስለሚመጡ ችግር ሲፈጠር ይታያል፡፡ በፊት ባልለመዱት መልኩ ህዝቡ ግልብጥ ቢሎ ወደ አደባባይ ወጥቶ ተቃዉሞ ሲያሰማ ይህን የህዝብ ማዕበል (hostile mob) እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸዉ የሚያዉቁት ነገር ስለማይኖር ግራ ይጋባሉ፡፡  አንዳንዴ የአድማ መበተኛ መሳሪያና ሌሎች ራስ መጠበቂያ ትጥቅ ቢሰጣቸዉም እንኳን አጠቃቀሙን በሚመለከት አስቀድሜዉ ያልተለማመዱት በመሆኑ ግራ መጋባታቸዉ የማይቀር ነዉ፡፡ በተለይም ሁኔታዎች ሲጋጋሉና ከቁጥጥር ዉጭ እየሆነ ሲሄድ  ገዳይ ኃይል ላለመጠቀም ማሳየት ያለባቸዉን ትእግስትና የግድ ከሆነ ድግሞ አነስተኛ ኃይልን ብቻ መጠቀም እንዳለባቸዉ (restraint and minimum force) ቢነገራቸዉ እንኳን በዚህ ጉዳይ ላይ የቆየ ልምድ ማነስ  የተነሳ ምን ማድረግ እንዳለባቸዉ ግራ ሲጋቡና ሲጨነቁ ቆይተዉ በመጨረሻም  ከቁጥጥራቸዉ ዉጭ ኃይል ወደ መጠቀም ይገባሉ፡፡ ከዚያ ከስተት በኋላ በገዛ ህዝባቸዉ  ላይ ባደረሱት የማይገባ ድርጊት እጅግ ስለሚጸጸቱ በዚህ ምክንትም ዳግመኛ በዉትድርና ሙያ መቀጠልን አስከመጥላት ይደርሳሉ፡፡ የራሳቸዉን ህይወት የሚቀጥፉም (suicide) ብዙ እንደሆኑ የተለያዩ የዉጭ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

3.7/ ፖሊሶች ያለግዜዉ ተጣድፈዉ መከላከያን የሚጠሩበት አሰራር መስተካከል ይገባዋል፡፡

ፖሊሶች ተጠያቂነትን የሚጋራቸዉ አካል ስለሚፈልጉ ወታደሩን ያለግዜዉ ገፋፍተዉ ወደ ቀዉሱ የማስገባት ባህሪይ እንዳላቸዉ ከሌሎች አገሮች ልምድ መረዳት ይቻላል፡፡ በሀገራችንም ቢሆን ፖሊሶች ከአቅማቸዉ በላይ ሲሆን ብቻ  የወታደሩን ድጋፍ መጠየቅ እንዳለባቸዉ እንደ አሰራር የሚታወቅ ቢሆንም  በተግባር ግን እንደዚያ እንዳልሆነ እያየን ነዉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፖሊሶች  ራሳቸዉ በቂ ጥረት ሳያደርጉ ተቻኩለዉ ወታደሩን ወደዚህ ዉስብስብ ጉዳይ ዉስጥ ያስገቡታል፡፡ ይህን የሚያደርጉት ተጠያቂነትን መከላከያ እንዲጋራቸዉ ስለሚፈልጉ  ከኃላፊነት ለመሸሽ ብለዉ ነወ፡፡ ይህ አዝማሚያ ግን ፖሊሶች ሁልጊዜም ራሳቸዉን እንዳይችሉና በመከላከያ ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ በህንድ አገር ከተደረገ ጥናት ለመረዳት እንደተቻለዉ መከላከያን አንዳንዴ ያለጊዜዉ ፈጥነዉ መጥራት ፤በሌላ ግዜ ደግሞ ሁኔታዎች ከተበላሹና ስር ከሰደዱ በኋላ ዘግይቶ የመጥራት ችግር ታይቷል፡፡ ለዚህ ዋነኛዉ ምክንያት ከፖሊሶች  በራስ አለመተማመን የመነጨ ነዉ፡፡

3.8/ በከተማ የጸጥታ ማስከበር ተግባር ለሚሰማሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ለዚህ ስምርት ብቁ የሚያደርጋቸዉን  ስልጠና  በሰላም ግዜ ሊሰጣቸዉ ይገባል፡፡

የመከላከያ ሰራዊት አባላት ለከተማ ረብሻና ሁከት መቆጣጠር ተግባር ሲታዘዙ አስቀድመዉ ያልተለማመዱትና ያልሰለጠኑበት በመሆኑ ትዕዛዝ ሲሰጣቸዉ ግራ መጋባትና ቶሎ ለመረዳት መቸገራቸዉ የማይቀር ነዉ፡፡ በዚህ ዓይነቱ ተልእኮ ላይ ከልምድ ማነስ የተነሳ ራስን ፈጥኖ ከሁኔታዎች ጋር ለማስማማት ያለመቻል ሁኔታ ይታያል፡፡ ረብሻዎችና ሁከቶች አንዱ ከሌላዉ በጊዜ ቆይታ ርዝመት በቦታ ስፋት በሁኔታዉ አስቸጋሪነት (the potential gravity) የተለያዩ ሊሆኑ ስለሚችሉ  ራስን ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር  ፈጥኖ  ለማላመድ አለመቻል ችግር ስለሚታይ ለዚህ ተግባር እንዲሰማሩ ለሚታዘዙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ያለበቂ ዝግጅት በድንገት እንዲሰማሩ ከማድረግ  በቅድሚያ አዲስ ስለተፈጠረዉ ልዩ የጸጥታ ችግር በቂ ገለጻ ሊደረግላቸዉ ይገባል፡፡ አንዳንድ ግዜ ለዚህ መሰሉ ተልእኮ የሚመጥን ስልጠና የለላቸዉና ከሁሉም በላይ ደግሞ በባህሪያቸዉ የድስፕሊን ችግር ያለባቸዉ መሆናቸዉ አስቀድሞ የሚታወቁ የሰራዊቱ አባላት ካሉ በቅድሚያ ተለይተዉ በዚህ ዓይነቱ ግዳጅ ላይ እንዳይሳተፉ ተገቢዉ ቁጥጥር መደረግ ይኖርበታል፡፡  ድስፕሊን የጎደላቸዉ ወታደሮች እንጠብቅሃለን  በሚሉት ህዝብ ላይ ጉዳት በማድረስ ችግር የመፍጠር ባህሪይ ስላላቸዉ በግድየለሽነት በሚወስዱት እርምጃ  ምክንያት መላዉ ሰራዊትና መንግስት ሊወቀስ ስለሚችል በዚህ ረገድ ተገቢዉ ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል፡፡

3.9/ በፌዴራልና በክልል ደረጃ የጸጥታ ማስከበር ጋር ተያይዞ የሚታዩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች  ተለይተዉ ለወደፊቱ ማስተካከያ ሊደረግባቸዉ ይገባል፡፡ 

በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የሚሆነዉ በክልል ዉስጥ ተከስቷል የሚባል የጸጥታ ችግር ላይ ክልሉና ፌዴራል መንግስቱ እኩል ክብደት ያለመስጠት ሁኔታ መታየቱ ነዉ፡፡ በዚህ ምክንያትም የፌዴራል ፖሊስም ሆነ መከላከያ ሰራዊቱ በክልሉ ዉስጥ ጸጥታ ለማስከበር መግባት አስፈላጊነት ላይም አንድ ዓይነት አረዳድ እንደለለ አንዳንድ ምልክቶች ታይተዋል፡፡ በሌላ በኩል የጸጥታ ችግር የተከሰተባቸዉ ክልሎች የፌዴራሉን መንግስት ጣልቃ መግባት የሚገዳደሩበትና ጥፋተኛች ናቸዉ የተባሉትን የመሸሸግ አዝማሚያም መታየቱ ለወደፊቱ መፍትሄ የሚሻ ጉዳይ ነዉ፡፡

በየትኛዉ ፌዴራላዊ ስርአቶች የተለመደዉና ተገቢ ተደርጎ የሚቆጠረዉ ክልሎች የዉስጥ ጸጥታ ችግር ሲጋጥማቸዉ በቅድሚያ ያለ ፌዴራሉ መንግስት ጣልቃገብነት በራሳቸዉ አቅም ችግሩን መፍታት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ ተግባር ሊገለገሉበት የሚችሉት የራሳቸዉ የሆነ የጸጥታ  ኃይልና ተመጣጣኝ መዋቅርም አላቸዉ፡፡ የክልል መስተዳደርች በክልላቸዉ ዉስጥ የተከሰተን የጸጥታ ችግር በራሳቸዉ አቅምና በራሳቸዉ መንገድ መፍታት መብታቸዉ ነዉ ሲባል የተጋረጠዉን የደህንነት አደጋ የማስወገድ ግዴታም ጭምር እንዳለባቸዉ ሳይዘነጋ ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ በክልሉ ዉስጥ ለሀገሪቱ ሉአላዊነት ከፍተኛ ስጋት የሚፈጥር ሁኔታ ተከስቶ እያለ የክልል አመራሩ በቸልተኝነት ችግሩን እንዳልተፈጠረ እድርጎ ከቆጠረ ወይም ሁኔታዉን ለመቆጣጠር መዉሰድ የሚገባዉን ተመጣጣኝ እርምጃ መዉሰድ ካልቻለ ወይም ካልፈለገ ፌዴራል መንግስቱ ይህን ሁኔታ በዝምታ ማለፍ አይችልም፡፡ ፌዴራል መንግስት ለአጠቃላይ ሀገሪቱ ሉአላዊነት ካለበት  ሃላፊነት ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ችግር የተከሰተበት ክልል ጥያቄ ሳያቀርብለትና ስምምነቱንም (consent) መጠበቅ ሳያስፈልገዉ ፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ ለመግባት የሚገደድበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡

ከዚሁ ጉዳይ ሳንወጣ ሌላዉ በሚገባ መጥራት የሚገባዉ በክልልና በፌዴራል ቁጥጥር ስር ባሉ የጸጥታ ኃይሎች መካከል ያለዉ ትብብር አፈጻጸምን  በሚመለከት ነዉ፡፡ ክልሎች የራሳቸዉ ፖሊስ አላቸዉ፡፡ ፌዴራሉ መንግስትም የፌዴራል ፖሊስና በብቸኝነት የሚያዘዉ መከላከያ ሰራዊት አለዉ፡፡ በዚህ ረገድ መጥራት ያለበት ሁለት ጉዳዮች አሉ፡፡ አንደኛዉ የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች (ፌዴራል ፖሊስና መከላከያ) ወደ  ክልል ዉስጥ  ጣልቃ መግባት የሚችሉት በምን በምን ሁኔታዎች ወቅት እንደሆነና የክልል ፖሊሶች ለፌዴራሉ የጸጥታ ኃይሎች ተባባሪ የማይሆኑበት ሁኔታ ሲፈጠርስ ችግሩ  በምን ህጋዊ አግባብ ሊቋጭ እንደሚችል ማጥራት ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የአንድ ክልል ፖሊስ ወደ ሌላ አጎራባች ክልል ዉስጥ ገብቶ የሚፈልጋቸዉን ሰዎችን  አድኖ በመያዝ ለህግ ለማቅረብ የሚችልበት  አግባብ ላይ ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ያለበለዚያ በክልልና በፌዴራል መንግስታትና በጸጥታ ኃይሎች መካከል አላስፈላጊ ግጭት ሊፈጠር ስለሚችል ችላ ሊባል የሚገባዉ አይደለም፡፡

በፌደራል መንግስትም ሆነ ክልሎች ከፖሊሶች በበለጠ በመከላከያ ሰራዊት ላይ አመኔታ መጣልና አስቀድሜዉ ተገቢዉን ጥረት ሳያደርጉ ፈጥነዉ መከላከያን የመጥራት ዝንባሌ እየተለመደ ሲሄድ እጅግ አደገኛ የሆነ ዉጤት ሊያስከትል ስለሚችል ከዚህ ዓይነቱ ልማድ መላቀቅ ይገባቸዋል፡፡ በክልል ዉስጥ የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን የመከላከል ተቀዳሚ ኃላፊነት የራሳቸዉ  የክልሎች በመሆኑ በስራቸዉ ባለዉ የክልል ፖሊስ በመጠቀም ችግሩን ለመፍታት መሞከር ይገባቸዋል፡፡ ከዚያ በላይ ሲሆን ብቻ ነዉ የፌዴራሉን ትብብር መጠየቅ የሚገባቸዉ፡፡ ከዚህ ጋር አብሮ መጠቀስ ያለበት የአመለካከት ግድፌት መከላከያ ሰራዊት በፌዴራል መንግስቱ በብቸኝነት የተያዘና ለየትኛዉም ተልእኮ ሊታዘዝ የሚችለዉም በፌዴራሉ መንግስት ብቻ መሆኑ እየተዘነጋ ክልል ባለስልጣናት በቅርብ ስላገኙት ብቻ ሰራዊቱን እንደሻቸዉ ለማዘዝ የመቃጣታቸዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ እንደሚታወቀዉ መከላከያ ሰራዊቱ አስፈላጊ መስሎ በታየዉ ግዜ በትኛዉም ክልል ዉስጥ  የጦር ካምፕ መስርቶ በቋሚነት ሊሰፍር ይችላል፡፡ ሰራዊቱ ከሰፈረበት አካባቢ ህዝብ ጋር የቀረበ ግንኙነት በመመስረት አቅሙ በፈቀደ መጠን በማህበራዊና የልማት ተግባራት እንዲሁም የአካባቢዉን ጸጥታ በማስከበር ተግባር ህዝቡንና መስተዳድሩን እንደሚያግዝ ይታወቃል፡፡ ይህ የሚደገፍና ሊጠናከር የሚገባዉ ሆኖ እያለ ከዚህ ዉጭ ግን አንዳንድ ግዜ የክልል መስተዳድሮች የፌዴራሉን መከላከያ  ሰራዊት ለረባዉም ላልረባዉም ሁሉ የመጥራት ልማድ ሊስተካከል የሚገባዉ ነዉ፡፡

ሌላዉ ለወደፊቱ የህግ ማእቀፍ ሊበጅለት የሚገባዉ ጉዳይ በክልሎች ስር የሚደራጀዉና በክልሎች የሚታዘዘዉ የጸጥታ ኃይል (የክልል ፖሊስ ፤ ልዩ ኃይል ሆነ የአካባቢ ሚሊሺያ) ግዝፈት ምን ያህል መሆን አለበት የሚለዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ አንድ ክልል ስለፈለገ ብቻ በራሱ ፈቃድ የፌዴራል ፖሊስንም ሆነ መከላከያ ሰራዊትን ሊገዳደር የሚችል የጸጥታ ኃይል ማዘጋጀት የሚከለክል አሰራር አለ? ክልሎች ምን ያህል የሰዉ ኃይል ያለዉ የጸጥታ ኃይል ነዉ እንዲኖራቸዉ የሚፈቀደዉ? ምን ዓይነት ትጥቅስ ነዉ መታጠቅ የሚፈቀድላቸዉ? የክልል የጸጥታ ኃይሎች ባጀትስ ማን ነዉ የሚያዘዉ? በፌዴራል መንግስት ወይስ በክልሉ?ለመሆኑ የክልል አመራሩ በስሩ ያለዉን የጸጥታ ኃይል ያለ አግባብ እንዳይጠቀም መቆጣጠር የሚቻልበት አሰራር ወይም ስርአት አበጅተናል? ስለዚህ እነዚህን መሰል ጥያቄዎች በሚገባ ታስቦበት መፍትሄ ሊቀመጥላቸዉ ይገባል ባይ ነኝ፡፡

ማጠቃለያ

በሀገራችን የዉስጥ የጸጥታ ችግሮችና ሁከቶችን ለመቆጣጠርና ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር ሁኔታዉ ከፖሊስ አቅም በላይ ሲሆኑ መከላከያ ሰራዊታችንን ተሳትፎ የጠየቁ በርካታ አጋጣሚዎች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡   የመከላከያ ሰራዊታችንን ተሳትፎ የግድ ባደረጉ በነዚህ ስምሪቶች ህግ በማስከበር ሂዴት ወቅት የተወሰኑ የመብት ጥሰቶች ሊደርሱ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ የመከላከያ ሰራዊታችን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጋቸዉ ባይቀርም አንዳንድ ግዜ  የተወሰኑ አባላት  ከአግባብ ዉጭ ጥፋት ወይም ስህተት የሰሩ በጭራሽ አይኖርም ብለ ለመከራከ የሚደፍር አይኖርም፡፡ መከላከያ ሰራዊታችን አባላት ሃላፊነታቸዉን  በሚወጡበት ወቅት ከነሱ ቁጥጥር ዉጭ በሆነ ሁኔታ የሰሯቸዉ ግድፈቶች ቢኖሩ የምንብቅበትና አድበስብሰን የምናልፍበት ምክንያት ሊኖር አይገባም፡፡ የችግሩን ምንጭ ፈትሸን ለወደፊቱ እንዲያስተካከል ማድረግ ሲገባን የዛሬ ጥፋታቸዉን ብንደባብቅ ነገ ይዞልን የሚመጣዉ አደጋ የከፋ ይሆናል፡፡  መከላከያን በከተማ ዉስጥ ህግ ለማስከበር መጠቀም አዳጋች ነዉ የተባለዉም  ለይስሙላ መባል ስላለበት ሳይሆን  ሊያስከትል የሚችለዉን አደጋ በመስጋት ነዉ፡፡

እንደሚታወቀዉ የኢፌድሪ መከላከያ ሰራዊት አባላት ከዚህ ቀደም ከነበሩ የሀገራችን መከላከያ ሰራዊቶች በተለየ ሁኔታ በጦር ሜዳ ከጠላት ጋር በሚደረግ ጦርነት የሚያገለግሉ ዓለም አቀፍ የጦርነት ህግጋትንና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድንጋገጌዎችን በማይጥስ ሁኔታ ግዳጁን ያለ እንከን ሊወጣ የሚያስችለዉን ስልጠና በየጊዜዉ ሲወስድ የነበረና በተግባርም ሲሰራበት የቆየ ነዉ፡፡ አስካሁንም የሰራዊታችንን ስም የሚያጎድፍ ሁኔታ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በዚህ ደረጃ መልካም ስም ያለዉ ሰራዊትም ቢሆን በከተማ ዉስጥ ከገዛ ህዝብ ዉስጥ አድማ ብተና ጸጥታ የማስከበር ተልእኮ ሲሰጠዉ የጦር ሜዳዉ ጉዳይና እዚህ ያለዉ ጨርሶ ስለማይጣጣም ለከፍተኛ ግራ መጋባት መዳረጉ የማይቀር ነዉ፡፡ ይህ ችግር ለኛ ብቻ ሳይሆን በሌሎች በአደጉ አገሮችም ጭምር ትልቅ ራስ ምታት የሆነና ፍቱን መድሃኒት ያልተበጀለት የጋራ ችግር ነዉ፡፡

መከላከያ ሰራዊትን ለህግ ማስከበር ተግባር የመጠቀም ጉዳይ በሚገባ ሊጤን ይገባዋል፡፡ ችግሩ ከፖሊስ አቅም በላይ ሆኖ ሲገኝ መከላከያን እንደመጨረሻ አማራጭ መጠቀም  ተገቢ ነዉ፡፡ ነገር ግን መከላከያን  ለህግ ማስከበር ተግባር የመጠቀም ጉዳይ ሲነሳ “ከአቅም በላይ ሲሆን “የሚለዉ አባባል በተደጋጋሚ የመጠቀሱን ያህል የጋራ መግባባት የተፈጠረበት አይመስለኝም፡፡ “ከአቅም በላይ “የሚባል የጸጥታ ችግር የቱ ነዉ? በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽነት እንደሌለ የሚያሳብቀዉ እዚሁ በችግሩ መሃል ሆነዉ “አስቸኳይ አዋጅ ለማወጅ የሚያበቃ ችግር አልተፈጠረም“ የሚሉ ሰዎች መኖራቸዉ  ነዉ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ መከላከያ ሰራዊቱንና ፌዴራል ፖሊስን ከዚህ በፊትም አስቸኳይ ግዜ አዋጅ ባልታወጀባቸዉ  ወቅቶችም ቢሆን መንግስት የከተማ ዉስጥ ሁከት ለመቆጣጠር እየተጠቀመባቸዉ ስለነበር የአሁኑን ሁኔታ ከሌላዉ ግዜ ለመለየት ማስቸገሩ ነዉ፡፤ ሶስተኛ የአደጋዉን ክብደትን በሚመለከትም በፌዴራሉና በክልል አመራሮች ደረጃም  በእኩል ደረጃ ክብደት መሰጠታቸዉ ላይ ጥርጣሬ የሚያጭሩ ሁኔታዎች መታየታቸዉ ነዉ፡፡ ስለዚህ በሰላም  ወቅት በሚገባ ታስቦበት ሊሰራበት የሚገባ አንዱ ስራ ይሄ ይመስለኛልና ቢታሰብበት መልካም ነዉ፡፡ 

ለዓመታት በጦርሜዳ ህይወት ዉስጥ የኖረ ወታደር ከተማ ዉስጥ ለረብሻ መቆጣጠር ሲሰማራ ምን ያህል ግራ እንደሚጋባ ማንም ሊረዳ የሚችለዉ ነዉ፡፡ ይዞት የቆየዉን ልማድና አስተሳሰብ ቅኝት (orientation) በቂ ግዜ ተወስዶ ከመሰረቱ እንዲቀየር ካልተደረገ በስተቀር መዘዙ እጅግ የከፋ እንደሚሆን ምንም አያጠራጥርም፡፡ በጦር ሜዳ የጦርነት አስተሳሰብ አዳብሮ የቆየ ወታደር ለከተማ  ረብሻ መቆጣጠር ተግባር ሲሰማራ የእለቱ ዕለት የተወሰነ መመሪያ ቢሰጠዉ እንኳን አብሮ በሚገባ የተዋሃደዉ ባለመሆኑ ገና ትንሽ እንቅፋት ሲገጥመዉ  ፈጥኖ  በጦር ሜዳ ወደ ለመደዉ የቀድሞ ባህሪይዉ ይመለሳል፡፡ ምክንያቱም አመለካከቱም፤ አይምሮዉና መላዉ አስተሳሰቡ የተገነባዉ (combat-oriented  architecture) በዉጊያ ላይ ኃይልን እንዳሻዉ ያለ ገደብ በመጠቀም ላይ  በመሆኑ ነዉ፡፡ በከተማ ረብሻና ህዝባዊ ተቃዉሞን ለመቆጣጠር ተግባር ወታደሮችን ማሰማራት የግድ ሆኖ ሲገኝ ለዚህ ስምሪት ብቁ የሚያደረግ ስልጠና በቅድሚያ ሊሰጣቸዉ ይገባል፡፡ 

የከተማ ዉስጥ ጸጥታ ማስከበር ተግባር ለመከላከያ ሰራዊት እጅግ አስቸጋሪና አመቺነት የለለዉ ስራ በመሆኑ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ስለሚችል መንግስት በተቻለ መጠን የከተማ ዉስጥ ሁከት ሲፈጠር ከመከላከያ ዉጪ ባሉ የጸጥታ ኃይሎች ችግሩን ለመፍታት ተገቢዉን ጥረት ሊያደርግ ይገባል፡፡ መከላከያን ባሰኘን ቁጥር የመጠቀምና ከፖሊስ ይልቅ በመካለከያ ላይ የመተማመን  ዝንባሌ እየተለመደ ሲሄድ ለወደፊቱ በቀላሉ ከማንወጣዉችግር ልንጋለጥ ስለምንችል መካለከያን ለዚህ ተግባር ላለመጠቀም መሰረታዊ የአስተሳሰብ ለዉጥ ማምጣት ይገባናል፡፡ ፖሊሶች ለዚህ ስራ በእጅጉ ተመራጭና የተዋጣላቸዉ በመሆናቸዉ ያለባቸዉን የአቅም እጥረት በመቅረፍ ተቋሙ የሚጠናከርበት መንገድ መሻት ይገባል፡፡ ከዚያ በተረፈ ግን የፖሊስ ተግባርን ወደ ወታደር የመቀየር (militarization of police) ሆነ መከላከያ ሰራዊትን እንደ ፖሊስ ሆኖ እንዲሰራ የማድረግ አካሄድ  (police-ization of military ) ሁለቱም አንዱ ከሌላዉ በማይሻል ሁኔታ አደገኛ አዝማሚያዎች በመሆናቸዉ ሁኔታዉ እንደገና ሊጤን ይገባዋል፡፡ 

*********

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories