መንግስትን በእጅጉ የፈተነዉ ቀዉስና የተስተናገደበት አግባብ ሲፈተሽ

(አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሺፈራዉ (ኮ/ል))

መግቢያ

በሀገራችን ከጥቂት ወራት በፊት ተከስቶ ለነበረዉ ሁከት ዋነኛ መነሻ ምክንያት ህዝባዊ ቅሬታዎችን በአግባቡ ማስተናገድ አለመቻላችን እንደደሆነ ይታወቃል፡፡ የህዝቡን ብሶት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ህዝባዊ ቅሬታዉን ወደ አጠቃላይ ቀዉስ በመቀየር ረገድ ጸረ -ሰላም ኃይሎች የተጫወቱት አፍራሽ ሚና ክፍተኛ እንደነበርም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ተቃዉሞን በሰላማዊ መንገድ ማሰማት የዜጎች መብት ሆኖ እያለ መንግስት ይህን መብት ያስተናገደበት መንገድ ከመብቱ ጠያቂ ህዝብ ፍላጎት ጋር ሊጣጣም ባለመቻሉ ወደ አልተፈለገ ሁከት ሊቀየር የግድ ሆኗል፡፡ መንግስት ህዝባዊ ተቃዉሞን እንደ ጤነኛ ክስተትና የዲሞክራሲ አንድ ጸጋ አደርጎ በመቁጠር ህዝባዊ ተቃዉሞን በአግባቡ ለማስተናገድ ያልቻለበት ምክንያት ከፍላጎት ማጣት ሳይሆን ከጥርጣሬ የመነጨ ስጋት ስላለበት ይመስለኛል፡፡  

ስጋቱና ጥርጣሬዉም ያለ አንዳች ምክንያት የመጣ ሳይሆን ህጋዊና ሰላማዊ ከሆነዉ የተቃዉሞ ሰልፍ ጀርባ መንግሰት ሊቆጣጠራቸዉ የማይችላቸዉ ስዉር እንቅስቃሴዎች መብዛታቸዉ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ደህንነት ላይ አደጋ ሊከስት ይችላል የሚል መነሾ ያለዉ ነዉ፡፡ በተለይም ወጣቱን እንደ አሻቸዉ ለጥፋት ተግባር የማነሳሳት ዕኩይ ዓላማ አንግበዉ ያለ ማቋረጥ ቀን ከዕለት በመስራት ላይ ያሉትን ማህበራዊ ሚዲያዎች መንግስት ለመቆጣጠር አቅሙ ዉስን በመሆኑ ምክንያት የተሻለ አመራጭ አድርጎ የወሰደዉ የተቃዉሞን አለማበረታታት ይመስለኛል፡፡ እኛም ዜጎች ህገመንግስቱ ያጎናጸፈንን መብት ለሌሎች ኃይሎች እንዲጠቀሙበት በመፍቀዳችን በሀገራችን ህዝባዊ ተቃዉሞ የማሰማት ጉዳይ ጨርሶ የማይቻልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የበኩላችንን አስተዋጽኦ አድርገናል ብየ አስባለሁ፡፡ በዲሞክራሲ ግንባታዉ በሚፈለገዉ ደረጃ ያልተሳካልን መሆኑ ትልቁ ማሳያ ለተቃዉሞ ሰልፍ ያለን ግንዛቤ ማነስና በተግባርም የምናስተናግድበት መንገድ የተዛባ መሆኑ ነዉ፡፡  

ባለፈዉ በገጠመን ቀዉስ ወቅት መንግስት ሁከቱን በመቆጣጠር ወደ ሰላማዊና የተረጋጋ ሁኔታ ለመመለስ ያደረገዉ ጥሬት የሚያስመሰግነዉ ብቻ ሳይሆን በእጅጉ የተሳካለትም ነዉ ቢባልም ነገር ግን ህዝባዊ የተቃዉሞን የሚያስተናግድበትን አግባብ እንደገኛ ሊያጤነዉ የሚገባዉ ይመስለኛል፡፡ በህገመንግስቱ ዋስትና ያገኘን ተቃዉሞ የማሰማት የዜጎች መብት አተገባበር ላይ ያለበትን እንከንና ለዚያ የዳረጉትን ስጋቶቹ ዙሪያ ከራሱ ህዝብ ጋር ቁጭ ብሎ በመመካከር ለወደፊቱ ማሻሻል የሚገባዉ ይመስለኛል፡፡ ያለበለዚያ አሁን እየሄድንበት ባለዉ አካሄድ ብዙ መዝለቅ የምንችል አይመስለኝም፡፡ ከዚህ መሰረተ ሃሳብ በመነሳትና የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ዉስጥ በማስገባት በዚህ ጉዳይ ላይ በእኔ የግንዛቤ ደረጃ የታዘብኳቸዉን እንከኖችና መንግስት የገጠሙትን ተግዳሮቶችና ጫናዎች ፤ ለወደፊቱም ማስተካከል በሚገባን ጉዳይ ላይ የበኩለን አስተያየት ለመሰንዘር እሞክራለሁ፡፡  

1/ ህዝባዊ ተቃዉሞ በማሰማት ረገድ የሚታዪ እንከኖችና ተግዳሮቶች፤

1.1/ ህገመንግስታዊ መብትን ህገ መንግስታዊ ባልሆነ መንገድ የመሻት የተዛባ ዝንባሌ፤

በሃገራችን ሰላማዊ የተቃዉሞ ሰልፍ ማድረግ ህገመንግስቱ ዋስትና የሰጠዉ የማይገሰስ የዜጎች ዲሞክራሲዊ መብት እንጂ ከመንግስት በችሮታ የሚያገኙት ወይም የሚከለከሉት እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ የኢፌድሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ 30 በማያወላዳ መንገድና በግልጽ ቋንቋ ይህን የዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብት ዋስትና የሰጠ በመሆኑ ይህን መብት ፈቃጅም ከልካይም አይኖርም፡፡ ይህ መብት በህገመንግስታችን ዋስትና ካገኘ በኋላ በሀገራችን በተለያዩ ግዜያት ሰላማዊ ተቃዉሞ ሰልፎችና የተቃዉሞ ስብሰባዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ተቃዉሞ ሰልፎችና ስብሰባዎች በሰላም ተጀምረዉ በሰላም የተጠናቀቁ ቢሆንም አልፎ አልፎ ግን እጅግ አሳዛኝ የሆነ ክስተት የታየባቸዉ አጋጣሚዎች እንደነበሩ ግን መካድ አይቻልም፡፡ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በተከሰቱ ችግሮች ምክንያት በጸጥታ ኃይሎችና በሁከት ፈጣሪዎች መካከል ግጭቶች መፈጠራቸዉ ይታወቃል፡፡ የዚህ መሰሉ አጋጣሚ ጥቂት ቢሆንም የችግሮቹ መነሻ ሲፈተሸ ዋነኛዉ መንስኤ ህገመንግስቱ ከሚደነግገዉ ዉጭ ተቃዉሞን ለማራመድ ሲሞከር ሃላፊነት ካለባቸዉ የጸጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት በመፈጠሩ ነዉ፡፡ በተጨማሪ ሆን ተብሎ ችግሩን በማባባስ ረገድ የጥፋት ኃይሎች ከጀርባ ሆነዉ ያቀነባበሩት ሴራ ዉጤት እንደሆነም ለመረዳት አይሳነንም፡፡ ከዚህም ሌላ በሁለቱም ወገን ማለትም በመንግስት የጸጥታ ሃይሎችም ሆነ ለተቃዉሞ በሚወጡ ወገኖች ዘንድ ከዲሞክራሲ ልምድ ማነስ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ አላስፈላጊ ክስተቶች እንዳሉም መደበቅ አይቻልም፡፡  

በህገ መንግስቱ የተቀመጠዉን የዜጎች መብት በአግባቡ ለመተርጎም የሚያስችል የአፈጻጸም መመሪያና ደንብ በመንግስት መዉጣቱ ይታወቃል፡፡ መንግስት ይህን ደንብ ያወጣዉ የዜጎችን ህገመንግስታዊ መብት በተገቢዉ መንገድ ለመተግበርና የተቃዉሞ ሰልፎችና ስብሰባዎች የዜጎችን ደህንነነት ስጋት ላይ በማይጥል ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄዱ ለማድረግ ስለሚያስችለዉ ነዉ፡፡ የደንቡ መኖር በጸጥታ ኃይሎችና ተቃዉሞ በሚወጡ ዜጎች መካከል አላስፈላጊ ቅራኔና ግጭት እንዳይፈጠር የሚያደርግ በመሆኑ ዜጎች መብታቸዉን ተጠቅመዉ ሰለማዊ ተቃዉሞ ለማድረግ እንዲደፋፈሩና እንዲበረታቱ የሚያግዝ ነዉ፡፡ በተጨማሪ ለዜጎች ደህንነት ሲባልም ደንቡ ተጠያቂነትንም እንደያካትት መደረጉ ህገመንግስታዊ መብትንም ቢሆን ለመጠቀምም ሰላማዊና ህጋዊ የሆነ መንገድን ብቻ እንድንከተል አቅጣጫ የሚሰጥና የሚመራ በመሆኑ የደንቡ መኖር እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ይታመናል፡፡ የዚህ ዓይነት መመሪያ ወይም ደንብ አስፈላጊነት የሚያጠያይቅ ባለመሆኑ በሁሉም አገሮች የተለመደ ነዉ፡፡ ሰላማዊ የተቃዉሞ ሰልፍ ማድረግን እዉቅና በተሰጠባቸዉ ዲሞክራሲያዊ አገሮች ሁሉ የተቃዉሞ ሰልፍን የሚመለከተዉ ህጋቸዉ በእጅጉ ተመሳሳይነት አለዉ፡፡ አንዳቸዉም አገሮች ቢሆኑ ህገወጥ በሆነ መንገድ ተቃዉሞ ማሰማትን አይፈቅዱም፡፡  

ማንም ሊገነዘብ እንደሚችለዉ የተቃዉሞ ሰልፎችና ስብሰባዎች እንደታሰበዉ ሁልጊዜ በሰላም ተጀምረዉ በሰላም ላይጠናቀቁ ስለሚችሉ ያን ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ አገራዊ ምስቅልቀል ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል ከኛም ሆነ ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ መረዳት እንችላለን፡፡ በዚህ ስጋት ምክንያትም ዲሞክራሲያዊ በሆኑ አገሮችም ከአለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችና ከህገመንግስታቸዉ ጋር በሚጣጣም መልኩ መንግስታት የመብቱን ተግባራዊነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ መመሪያዎችንና ደንቦችን እንደሚያዘጋጁ ይታወቃል፡፡ እንደዚያም ሆኑ ግን በየትኛዉም አገር ቢሆን አፈጻጸሙ ከችግር የጸዳ ሆኖ አያዉቅም፡፡ ይብዛም ይነስም በሁሉም አገሮች ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ ከታላቋ ዲሞክራሲዊ አገር አሜሪካ ጀምሮ አስከ ደቡብ አፍሪካ ፣ፈረንሳይ ፤ጀርመን ፤ኢንግሊዝ አዉስትራሊያ ወዘተ ሁሉ ችግር ያልተከሰተበትን ወቅት መጥቀስ አይቻልም፡፡ ሌላዉ ቀርቶ የዲሞክራሲ ቁንጮ በሆነችዉ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ባለፈዉ የ2016 የፈረንጆች ዓመት ብቻ በቁጥር 1000(አንድ ሺህ) በላይ ሰላማዊ ዜጎቿ ከመብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ያለአግባብ በፖሊስ ጥይት መገደላቸዉንና በርካቶች ለእስር መዳረጋቸዉን ስንሰማ ችግሩ በሁሉም አገር ያለ መሆኑን ለመረዳት እንችላለን፡፡  

ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለዉ የኢፌዲሪ መንግስትም ለህዝቡ ደህንነት ካለበት ሃላፊነትና ተጠያቂነት አንጻር ይህ የዜጎች መብት በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ የሚሆንበትን የአፈጻጸም መመሪያ ወይም ህግ በማዘጋጀት መብቱ ያለ እንከን ተፈጻሚ እንዲሆን መሞከሩ ተገቢና የሚደገፍ ነዉ፡፡ የሰላማዊ ሰልፍን አፈጻጸም ስርአት የሚደነግግ ደንብ ማዉጣት የዜጎችን መብት ለመጋፋት ተብሎ ሳይሆን መብቱን ያለ አንዳች ችግር ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችልና የዜጎችንም ደህነት ለማረጋገጥም ጠቀሜታ እንዳለዉ ስለታመነበት ነዉ፡፡  

ህገ መመንግስታዊ መብትን ህጋዊ በሆነ መንገድ መጠቀም እየተቻለ ህጋዊና ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ በኃይል ለማሰከበር የሚደረገዉ ሙከራ ብዙ ቀዉስ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡ በተለይም ከጀርባቸዉ የጥፋት ዓላማ ባነገቡ ጥቂት ህገወጥ ግለሰቦች አነሳሽነት ሆን ተብሎ ችግር እንዲፈጠር ይደረጋል፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ለሚመለከተዉ አካል በቅድሚያ ማሳወቅ እየተቻለና ይህን ማድረግም አንዳችም አስቸጋሪነት እንደለለዉ እየታወቀ ነገር ግን የሚመለከተዉን ባለስልጣን ሳያሳዉቁ በግብታዊነትና በድንገት (spontaneously )የሚደረጉ ተቃዉሞ ሰልፎች የጸጥታ ኃይሎች ባልተዘጋጁበት ሁኔታ ስለሚደረግ ተገቢዉን ጥበቃ ማድረግ እየተሳናቸዉ በዚህ ምክንያትም በዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ አላስፈላጊ ጉዳት ሲደርስ በተደጋጋነሚ ታይቷል፡፡ ከዚህ መሰሉ መጥፎ ክስተት ምናልባት ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ ካሉ አጥፊ ዓላማ ያላቸዉ ጥቂት ግለሰቦች እንጂ ህዝቡ በጭራሽ ተጠቃሚ ሊሆን አይችለም፡፡

ብዙዎቻችን እንደምናስታዉሰዉ ባለፉት ስርአቶች ህዝቡ በመንግስት ላይ ተቃዉሞዉን ለማሰማት ወደ አደባባይ ለመዉጣት የነበረዉ እድል ጨርሶ ዝግ ነበር፡፡ ክልከላዉና የመብት አፈናዉ ሳይበግረዉ ህዝቡ በገዛ ፈቃዱ ለተቃዉሞ በወጣባቸዉ ጥቂት አጋጣሚዎችም ፖሊሶችም ሆኑ ጦር ኃይሉ የተቃዉሞ አመጹን በኃይል በመጨፍለቅና የሕዝብ ድምጽን በማፈን የገዢዎችን የሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡ በወቅቱ ተቃዉሞ ማሰማት መሰረታዊ የሆነ የዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብት ነዉ የሚል አመለካከት ጨርሶ አልነበረም፡፡ ተቃዉሞ የማሰማት የዜጎች ዲሞክራሲዊ መብት መሆኑ ታምኖበት በህገመንግስቱ ዋስትና ያገኘዉም ሆነ ከነ እንከኖቹም ቢሆን በተግባር እየተረጋገጠ ያለዉ በዚህ ባለንበት ስርአት ዉስጥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በሀገራችን የተቃዉሞ ሰልፍ አፈጻጸም ረገድ ሊጠቀሱ የሚችሉ አንዳንድ ተግዳሮቶችና እንከኖች ባይጠፉም በደርግ ስርአት እንደነበረዉ በጸጥታ ኃይሎች ተቃዉሞን የማፈን ወይም እስከነአካቴዉ የመከልከል አሰራር የለም፡፡ የሀገራችን ህገመንግስት ተቃዉሞ ሰልፍን መከልከል ይቅርና ፈቃድ መጠየቅን እንኳን እንደ ግዴታ አያስቀምጥም ፡፡ ተቃዉሞ ሰልፍ ለማድረግ አንዳችም ክልከላ ሆነ ፈቃድ መጠየቅም አያስፈልግም፡፡ የግድ መሟላት ያለበት እጅግ በጣም ቀላል ጉዳይ ቢኖር አስቀድሞ ማሳወቅና በሰላማዊ መንገድ ማካሄድ ብቻ ነዉ፡፡ መንግስት አስቀድሞ ማሳወቅን ግዴታ ያደረገዉ እንቅፋት ለመፍጠር ፈልጎ ሳይሆን ህዝባዊ ተቃዉሞዉ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ ተገቢዉን ጥበቃ በማድረግ ለዜጎች ደህንነት ዋስትና ለመስጠት ስለሚያስችል ነዉ፡፡ ምከንያቱም መንግስት የጸጥታ ኃይሎች በመመደብ ጥበቃ ማድረግ የሚችለዉ አስቀድሞ ሲያዉቅ ስለሆነ ነዉ፡፡ በተጨማሪ ለስብሳባ የተመረጠዉ ቦታ በሌሎች አስቀድሞ የተያዘ ወይም ከሀገር ደህንነት አንጻር አመቺነት የለለዉ ሊሆን ስለሚችል አመራጭ ግዜና ቦታ ለማመቻቸትም ስለያስችል ነዉ፡፡

በብዙ ሀገሮች የተለመደዉም የተቃዉሞ ሰልፍ አደራጆች ለደጋፊዎቻችዉ ጥሪ ከማድረጋቸዉ በፊት ለሚመለከተዉ ባለስልጣን በጽሁፍ በማሳወቅ ብቻ ሳይወሰኑ የሰልፉ አስተባባሪዎች ባለስልጣኑ ቢሮ ተገኝተዉ የመመካከርና የመደራደር አሰራርም አላቸዉ፡፡ ዝም ብሎ በድንገት ህዝብን ሰብስቦ የህዝብን ፍላጎት የማይወክል መፈክር አስጨብጦ በግድ እያስጮሁ ወደ አደባባይ መዉጣት በሰለጠነዉ ዓለምም ቢሆን ጨርሶ የሚደገፍ አሰራር አይደለም፡፡

ህገ መንግስታዊ መብታቸዉን ተጠቅመዉ ለተቃዉሞ ሰልፍ ወደ ጎዳና ለመዉጣት የሚፈልጉ ዜጎች ራሳቸዉ በፈቃዳቸዉ ያጸደቁትን ህገመንግስት በሚጋፋ መንገድ መብታቸዉን ከህግ ዉጭ ለመጠቀም መሞከር አይኖርባቸዉም፡፡ የትኛዉንም በህገመንግስቱ ዉስጥ የተደነገጉ ሌሎች መብቶችንም ቢሆን ለመጠየቅ ህገ መንግስቱን መጣስ አያስፈልግም፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ዲሞክራሲያዊ መብት መጠቀም የሚቻለዉ ህጋዊ በሆነ አግባብ ብቻ ሲሆን ነዉ ፡፡ ዜጎች ራሳቸዉ መርጠዉ ወደ ስልጣን ያመጡትን መንግስት የመደገፍም ብቻ ሳይሆን የመቃወምም መብት አላቸዉ፡፡ የመንግስት ፖሊሲም ሆነ አፈጻጸሙ ካልጣማቸዉ ዜጎች የመቃወም መብታቸዉ ህገመንግስታዊ ዋስትና የተሰጠዉ ነዉ፡፡ መንግስትን በአደባባይ ለማዉገዝ የግድ አስር ሺህ ወይም መቶ ሺ ህዝብ ማሰለፍም የግድ አይደለም፡፡ በመንግስት ላይ ተቃዉሞ ካለዉ መቶ ሰዉም ቢሆን ለተቃዉሞ ሊወጣ ይችላል፡፡ ነገር ግን መዘንጋት የለለበት አንድ ሺህ ሰዉም ይሁን አንድ ሚሊዮን በሃገሪቱ ህግ ለዚህ ተብሎ በተቀመጠዉ አግባብ መሰረት መሆን ይኖርበታል፡፡ ከዚያ ዉጭ ግን ለመንግስት ጥያቄ ለማቅረብም ሆነ ተቃዉሞ ለማሰማት ካላሽንኮቭና የእጅ ቦንብ ይዞ መዉጣት ህጋዊ አይደለም፡፡ የዚህ አይነት ደርጊት በየትኛዉም አገር ቢሆን የተከለከለ ነዉ፡፡ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ጠብ የሚፈጠረዉም ከህገ መንግስቱ አግባብ ዉጭ ለመንቀሳቀስ ሲሞከር ነዉ፡፡

የተቃዉሞ ሰልፍ ሰልፍ ሲኖር የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በቦታዉ እንዲገኙ የሚደሩት ተቃዉሞዉ የማይመለከታቸዉ ዜጎችን ብቻ ሳይሆን ራሱ መንግስትን ለመቃወም የወጡትንም ዜጎችንም ጭምር ደህንነታቸዉን የመጠበቅ ግዴታና ሃላፊነት ሲላለባቸዉ ነዉ፡፡ ፖሊሶች ተቃዉሞ ሰልፍ በሚደረግበት ቦታ እንዲገኙ የሚደረግበት ዋነኛዉ ምክንያት ተቃዉሞ ሰልፉን ለማገድ፤ የተቃወሞ የወጣዉን ህዝብ ለመበተን ወይም ለማሰር፤ ለመደብደብ ወዘተ ሳይሆን የተቃዉሞ ሰልፉን አድራጊዎች የመቃወም ህገመንግስታዊ መብታቸዉ ያለአንዳች ችግር እንዲከናወን ዋስትና መስጠት መንግስት ግዴታ ስላለበት ነዉ፡፡ ተቃዉሞዉ የማይመለከታቸዉ ሌሎቸ ዜጎች ብቻ ሳይሆን የተቀዉሞ አድራጊዎችም ደህንነት ማረጋገጥ የመንግስት ኃላፊነት ስለሆነ የጸጥታ ኃይሎች በቦታዉ መገኘታቸዉ ለዚህ ዓላማ ተብሎ ነዉ፡፡ በየትኛዉም አገር ቢሆን በፖሊስ ጥበቃ የማይደረግበት የተቃዉሞ ሰልፍ ተደርጎ አይታወቅም፡፡

የየትኛዉ አገር መንግስት የጸጥታ ኃይሎችን በዚህ ቦታ ሲያሰማራ ለዜጎች መብትና ለሀገሪቱ ደህንነት ካለበት ሃላፊነት በመነሳት ነዉ፡፡ አንደኛ ዜጎች ተቃዉሞ የማሰማት መብታቸዉን ያለአንዳች እንከን ተግባራዊ እንዲደርጉ ዋስትና የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ምክንያቱም ሌሎች ያልታወቁ ኃይሎች በህጋዊ መንገድ ተቃዉሞ በሚያሰሙ ዜጎች ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉና፡፡ ሁለተኛ ሰላማዊ ተቃዉሞ ለማሰማት የወጡ ዜጎች በሌሎች ዜጎች ህይወት፤ ንብረትና የተለመዱ እንቀስቃሴዎች ላይ እንቅፋት እንዳይፈጥሩ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሶስተኛ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የማይፈቀድባቸዉ ተለይተዉ የሚታወቁ ቦታዎች ላይ እንዳይደረጉ ቁጥጥር ለማድረግና በአጠቃላይም የሀገሪቱን ደህንነትም የማስከበር ግዴታ ሲላለበትም ነዉ፡፡ በዚህ ምክንያትም በሰለጠነዉ ዓለም ተቃዉሞ ሰልፍና ስብሰባ አደራጆች የተቃዉሞ ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ በመፈለግ አንዳንዴ ራሳቸዉ ናቸዉ መንግስትን የጥበቃ ኃይል ይመደብልን ብለዉ የሚጠይቁት፡፡ በኛ ሃገር ግን እንኳን የተቃዉሞ ሰልፍ አደራጆች ጠይቀዉ ቀርቶ ራሱ መንግስት ሃላፊነቱን ተገንዝቦ ጥበቃ በማድረጉና አንዳንድ ሰላማዊነት የጎደላቸዉ ተቃዉሞዎች አንዳይደረጉ በመከለክሉ ሰላማዊ የተቃዉሞ ሰልፍን አስከ ነአካቴዉ እንደማይፈቅድ ተደርጎ እንዲታሰብ አድርጎታል፡፡

መንግስት ተቃዉሞ ሰልፍ ከመጠራቱ አስቀድሞ ለሚመለከተዉ ባለስልጣን ማሳወቅን እንደግዴታ መደንገጉና ህጋዊና ሰላማዊ ከሆነ አግባብ ዉጭ ተቃዉሞ ሰልፍ ማድረግን አለመፍቀዱ ከዜጎች ፍላጎት ጋር የሚጋጭ አይደለም፡፡ የዜጎች ህገመንግስታዊ መብት በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግና ደህንነታቸዉንም ለመጠበቅ የሚቻለዉ ህጋዊ መንገዱን ተከትሎ ሲከናወን እንጂ ከዚያ ዉጭ የህዝብን ሰላምና የሀገርን ደህንነት ስጋት ላይ በሚጥል መልኩ ለመተግበር ሲሞከር አይደለም፡፡ መንግስት አንዳችም ጉዳይ ህጉ ከሚፈቅደዉ ዉጪና ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ መፈጸም አይኖርበትም የሚለዉ የጸና አቋሙ ለሁላችንም የሚበጅ እንጂ የሚጎዳን አይደለም፡፡

2/ የጸጥታ ኃይሎችን ጥረት ፈታኝ ያደረጉ ሁኔታዎች፤

2.1/ ህጋዊ የህዝብ ጥያቄን ወደ አመጽ ለመቀየር የተወጠነዉ ሴራና ማህበራዊ ሚዲያዎች የተጫወቱት አፍራሽ ሚና

በአንድ ወቅት በአረቡ ዓለም የተደረገዉን ” የጸደይ አብዮት”የተሰኘዉ ህዝባዊ መነሳሳትና ሁከት ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ለአመጽ ማነሳሻ ዋነኛ መሳሪያ ሆኖ ሲያገለግል የነበረዉ ፌስቡክና የመሳሰሉት ማህበራዊ ድረ-ገጾች ናቸዉ፡፡ እነዚህን ማሀበራዊ ድረ-ገጾች በመጠቀም ቀንና ሌሊት ያለማቋረጥ በመቀስቀስ ዜጎችን ወደ አባደባባይ ገፋፍተዉ እንዲወጡ አድርገዋል፡፡ አስገራሚዉ ጉዳይ ህዝቡን ቀስቀሰዉ ወደ አደባባይ ማዉጣታቸዉ ሳይሆን እነዚህ ህዝቡን ለአመጽ እንዲወጡ ሲያነሳሱ የነበሩ ሰዎች አብዛኛዎቹ በኑሮአቸዉ የደላቸዉና ስልጣን በግርግር ለመያዝ ያቀዱ ግን ደግሞ ማንነታቸዉ እንዲታወቅ በጭራሽ የማይፈልጉና በህብረተሰቡም ብዙም የማይታወቁ ናቸዉ፡፡ ህዝቡን ለአመጽ የሚቀሰቅሱ ግለሰቦች አድራሻቸዉም ሆነ ማንነታቸዉ አይታወቅም ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ አንድ ግለሰብ ይሁን ወይም የተደራጀ ኃይል ይሁን ለማወቅ የሚቻልበት መንገድ የለም፡፡ በዉጭ አገር የሚኖሩ ወይንም በሀገር ዉስጥ ያሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

እነዚህ ሰዎች በወቅቱ በአጋጣሚ በሃገር ዉስጥ የሚገኙ ቢሆኑ እንኳን ራሳቸዉ ወደ ቀሰቀሱት ሰልፍና ረብሻ ድሪሽ አይሉም፡፡ በአመጹ የደረሰዉን ጉዳትና የተፈጠረዉን ምስቅልቅል ሁኔታ በሩቅ ሆነዉ በወኪሎቻቸዉ በኩል ወይም በሚዲያዎች በኩል ነዉ የሚከታተሉት፡፡ ራሳቸዉን ማጋለጥ ስለማይፈልጉ በማንኛዉም የአደባባይ አመጽና ተቃዉሞ ላይ በአካል አይገኙም፡፡ ከመንግስት ጋር ለመደራደር የሚያደርጉት ሙከራም የለም፡፡ ረብሻ ሲቀሰቅሱም በተቻለ መጠን መንግስት በቀላሉ ምላሽ ሊሰጥ የማይችላቸዉን ጉዳዮችን መርጠዉ ህዝቡን የማይወክል መፈክር በማሸከም ነዉ፡፡ የህዝቡ ጥያቄ በቶሎ ምላሽ እንዲያገኝ አይፈገልጉምና፡፡ በዚህም ምክንያትም ከህዝብ ፍላጎት ጋር የማይገኛኙና አግባቢነት የሌላቸዉን በርካታ ጉዳዮችን በአንድ ላይ አጭቀዉ በማጨናነቅና መንግስት ላይ ጫናና ዉጥረት መፍጠር ነዉ የሚፈልጉት፡፡ ቀዉሱ ቶሎ እንዲቋጭ ሳይሆን ዘለግ ላለ ጊዜ እንዲቀጥልና ወደ ሌሎች አካባቢዎችም በፍጥነት እየሰፋና መልኩን እየቀየረ እንዲሄድ ነዉ የሚያደርጉት፡፡ እነዚህ ሰዎች ማንነታቸዉን ስለሚደብቁና አብዛኛዉን ጊዜም በዉጭ አገር መሽገዉ የሚገኙ በመሆናቸዉ ሁኔታዉ እንዳሰቡት ባይሳካለቸዉ እንኳን የሚያጡት ወይንም በህግ እንጠየቅ ይሆናል ብለዉ የሚሰጉበት አንዳችም ነገር የለም፡፡ ዉጥናቸዉ እንዳሰቡት ለጊዜዉ ባይሳካለቸዉ ቢያንስ ብጥብጥ መነሳቱና የዜጎች ህይወት መጥፋትና ንብረት መዉደም በራሱ ትልቅ ድል አድርገዉ ነዉ የሚቆጥሩት፡፡

ባለፈዉ በሀገራችን የደረሰዉ ሁኔታም ሙሉ በሙሉ በዚህ መንገድ የተከናወነ ነዉ፡፡ በወቅቱ በአገራችን ተከሰቶ የነበረዉ ሁከትም ማህበራዊ ድረ-ገጽን በመጠቀም እነማን እንደሆኑና ከየት እንደሆነ ለማወቅ በማይቻልበት ሁኔታ ስማቸዉን እየቀያየሩ አጥፊ የሆኑ ቅስቄሳዎችንና ለወንጀል የማነሳሳት ዘመቻዎች በማድረግ በዜጎች ንብረትና ህይወት ላይ ቀላል የማይባል አደጋ እንዲከሰት አድርገዋል፡፡ እነሱ ብዙ ሺህ ማይል ርቀት ላይ ሆነዉ የጥፋት ዘመቻ ትእዛዝ እየሰጡ እዚህ እኛ የዚህች ደሃ አገራችንን ንብረት ስናወድም ነበር፡፡ አንዳንዶቹን በስም ካልሆነ በስተቀር ከዚህ ቀደም በአካል የማናዉቃቸዉና ደስታችንም ሆነ ሃዘናችንን ሊጋሩን የማይችሉ በመካከላችን የለሉና ከየት እንደሆነ ከማናዉቀዉ አገር ሆነዉ የሚልኩልንን የጥፋት ትእዛዝ ያለ አንዳች ማመዛን ተቀብለን እንደጠላት ንብረት የራሳችንን ንብረት አወደምን፡፡ እርስበርሳችንም ክፉኛ ተጋጨን፡፡ እነዚህ የጥፋት ኃይሎች የሻዕቢያ ቅጥረኞችና የኦነግ ወኪሎች መሆናቸዉ እየተነገረንም አልሰማ ብለን እነሱ እንደሚፈልጉት ታዘዝናቸዉ፡፡

ኦነግና ግንቦተኞች ከአጎታቸዉ ከኢሳይያስ ጋር በማበር ከዚህ ቀደም ሻእቢያ በርካታ የታጠቀ ሰራዊት አሰልፎ በጦርነት ያልተሳካለትን ኢትዮጵያን የመበታተን ሰይጣናዊ ዓላማ ለማሳከት አንድት ጥይት እንኳን መተኮስ ሳያስፈልጋቸዉ በፌስቡክ ብቻ ያደረሱብን ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡

ጸረ- ሰላም ኃይሎች የህዝቡን ህጋዊ ጥያቄን ወደ አመጽ እንዲቀየር በማድረግ መንግስትን በኃይልና በጫና ከስልጣን ከማዉረድ ጀምሮ በሂዴት አገሪቱን ለመበታተን የሚያደረጉትን ሴራ በጽኑ ልንታገለዉ ይገባል፡፡ በነዚህ ኃይሎች ግፊት በከተሞች ዉስጥ ሆን ተብሎ በሚፈጠረዉ ሁከት በአብዛኛዉ ተጎጂ የሚሆኑት ምኑም ዉስጥ የለሉበትናባልተረዱት ሁኔታ ተገደዉና በስሜት ተገፋፍተዉ ወደ ሁከቱ የሚደባለቁ የዋህ ዜጎች ናቸዉ፡፡ አብዛኛዉን ጊዜ ሁከቱን የሚያደራጁትና የሚቀሰቅሱት ወገኖች ሌላ የጥፋት ዓላማ ያነገቡ ለዚህ ብለዉ የተደራጁ ቡድኖችም ወይም ፓርቲዎች ናቸዉ፡፡ የህዝብን ቁጣ ሊያገነፍል የሚችል ሁኔታ በመፍጠር ህዝብ በስሜታዊነት ተገፋፍቶ ወደ ጎዳና አነዲወጣ በማድረግ የአመጹ አደራጆች ሰለማዊዉን ሰዉ ከመንግስት ጸጥታ ሃይሎች ጋር አጋፍጠዉ ከአካባቢዉ ይሰወራሉ፡፡

ማነታቸዉ የማይታወቅና ማንም ያልወከላቸዉ ፤በአካል የማይታዩና የማይዳሰሱ ከዬት እንደሆነ ማወቅም በማይቻልበት ሁኔታ በማህበራዊ ድሬ-ገጽ የሚያሰራጩትን ቅስቄሳ አምኖ መቀበል የዋህነት ነዉ፡፡ ህዝብ የራሱ የሆነ ብሶትም ሆነ ያልተመለሱለት ብዙ ጥያቃዎች ሊኖረዉ ይችላል፡፡ ጥያቄዎቹ እንዲመለሱለት በሰላማዊ መንግድ መንግስትን ላይ ቅሬታዉን ለማቅረብ ወደ ጎዳና ቢወጣ የሚያስገርም አይሆንም፡፡ እንኳን እኛ የዳበረ ዲሞክራሲና በገነቡ አገሮችም እንደ አሜሪካ ጀርመን ፈረንሳይና ኢንግሊዝ ወዘተ በየጊዜዉ የተቃዉሞ ድምጽ ለማሰማት ዜጎቻቸዉ ወደ ጎዳና እየወጡ መሆኑን እናዉቃለን፡፡ የኛን ሁኔታ ለዬት የሚያደርገዉ አሜሪካና አዉሮፓ ሆነዉ የማይታወቁ ሰዎች በሚያደርጉት ቅስቄሳ መመራታችን ነዉ፡፡ ዜጎች ወደ አደባባይ የሚወጡት ተቃዉሞአቸዉን ወይም ድጋፋቸዉን ወይንም ጥያቄ ካላቸዉም በስልጣን ላይ ያለዉን መንግስት ለመጠየቅ ሲሆን ለጥያቁዉ መልስም ሆነ ማብራሪያ መስጠት የሚገባዉም መንግስት ራሱ እንጂ ሌላ አካል አይደለም፡፡ መወቀስ ካለበትም ወቀሳዉ የሚመለተዉ መንግስትን ነዉ፡፡ የፈለገዉ ዓይነት ጥያቄ ቢኖር ህዝብና መንግስት በቀጥታ ተነጋግረዉ የሚፈቱት እንጂ ሌሎች ኃይሎች ጣልቃገብንት የሚጋብዝ ፡፡አይደለም፡፡

እነጃዋርና ሌሎቹ በዉጭ ሀገር ሆነዉ በፌስቡክና ለዚሁ ተብሎ በቋቋሙት የቴለቭዝን ጣቢያዎቻቸዉ አማካኝነት ሃያ አራት ሰዓት የጥፋት ቅስቀሳ ሲያደርጉ እያየን ዝም አልን፡፡ እነዚህን የጥፋት ኃይሎች በግንባር ገጥሞ ለመፋለምም ሆነ ከድርጊታቸዉ እንዲቆጠቡ ለማድረግ የማይቻለን ስለነበር ለግዜዉም ቢሆን እንደፈለጉ ሲፈነጩብን ከረሙ፡፡ በርግጥ መንግስትና የጸጥታ ኃይሎቻችን ከማይታይና ከማይዳሰስ ከዚህ ዓይነቱ ጠላት ጋር ለመፋለም ለጥቂት ግዜም ቢሆን መቸገራቸዉ እዉነት ነዉ፡፡ መንግስት ቢያንስ የአጥፊዎች ዋነኛ የጥፋት መሳሪያ የሆነዉን የሞባይል ኢንተርነት ለግዜዉ እንኳን በመዝጋት ፋታ እንድናገኝ ለማድረግ ባለመድፈሩ ሊወቀስበት ይገባል፡፡ መንግስት ልዝጋ አልዝጋ እያለ ሲያመነታ ቆይቶ እርምጃ የወሰደዉ ብዙ ጥፋት ከደረሰ በኋላ እጅግ ዘግይቶ ነዉ፡፡ ከሀገሪቱ ደህንት የሚበልጥብን ምንም ነገር እንደማይኖር ተገንዝቦ መንግስት ያን ያህል መዘግየት ሳያስፈልገዉ ፈጥኖ እርምጃ መዉሰድ ይገባዉ ነበርና፡፡

2.2/ መንግስትን ከህዝቡ ጋር ለማጋጨት የተደረገዉ ከንቱ ጥረት

መንግስት የጸጥታ ችግር ሲከሰት ሁኔታዉን በሰላም መቆጣጠር ሲያዳግተዉ ተመጣጣኝ የሆነ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ያን ካላደረገ ሃላፊነቱን ሊወጣ የማይችል ደካማ መሆኑን ማረጋገጫ ስለሚሆን በስልጣን ላይ መቆየት ላይኖርበት ነዉ፡፡ ስለዚህ ሆን ብለዉ ቀዉስ እንዲፈጠር የሚፈልጉ ወገኖች መንግስት ሁኔታዉ ከቁጥጥሩ ዉጭ ሲሆንበት ተደናግጦ የኃይል እርምጃ ሊወስድ ይችላል የሚል ተስፋ አድርገዉ ነዉ ቀዉሱን ሲያቀጣጥሉት የከረሙት፡፡ እነሱ የሚፈልጉትም ይህ እንዲሆን ነበር፡፡ በነሱ ስሌት መሰረት መንግስትና ህዝብ አንድ ግዜ ግጭት ዉስጥ ከገቡ በኋላና ደም ከፈሰሰ ህዝብ በመንግስት ላይ ጥላቻ ሊያሳድር እንደሚችል ጠንቅቀዉ ስለሚያዉቁ ለፖለቲካ ዓላማቸዉ መልካም አጋጣሚ እንደሚሆንላቸዉ ተማምነዉ ነበር፡፡ እነሱ፡ ርካሽ ዓላማቸዉ ይሳካ እንጂ የህዝቡ ልጆች እርስበርሳቸዉ ቢገዳደሉና የዚህች ደሃ አገር ንብረት ቢወድም ጉዳያቸዉ አይደለም፡፡

የጸጥታ ኃይሎች ለዚህ ዓይነቱ ተንኮል ምቹ እንዳይሆኑ ጉዳት እየደረሰባቸዉም ቢሆን ተቻኩለዉ የኃይል እርምጃ እንዳይወስዱ መንግስት ባወረደዉ መመሪያ መሰረት ከአንዳንድ የጥፋት መልእክተኞች ወታደሮቻችንን ለማበሳጨት ሆን ብለዉ አስጸያፊ ስድብ በመሳደብ፤ ድንጋይ በመወርወር፤ በመገፍተርና አንዳንዴም በመሳሪያ ጭምር ጉዳት ለማድረስ መሞከራቸዉ ባይቀርም የጸጥታ ኃይሎች ግን ያ ሁሉ ችግር እየደረሰባቸዉም በትእግስትና በዜዴ ሁኔታዉን ለመቆጣጠር ሞክረዋል፡፡ ሁኔታዉ ስብስባቸዉ ራሳቸዉንና ሌሎችን ለመከላከል ተመጣጣን የኃይል እርምጃ መዉሰዳቸዉ በጭራሽ የሚያስወቅሳቸዉ አይሆንም ፡፡

እነዚህ የጥፋት መልእክተኞች የድፍረታቸዉና የብልግናቸዉ ብዛት የጸጥታ ኃይሎችንና በአካባቢዉ የነበረን ህዝብ ከምንም ሳይቆጥሩ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ሰንደቅ ዓላማ ከክብር ቦታዉ አዉርደዉ እያጎሳቆሉ የሽብርተኛዉና የሰይጣን መልእክተኛ የሆነዉን የኦነግ አርማ ያለበትን ጨርቅ ለማዉለብለብ ሲሞክሩ እያዩ የጸጥታ ኃይሉ አባላት ምን እንዲያደርጉ ነበር የሚጠበቅባቸዉ? ባለፉት ወራት የደረሰዉ ሁኔታ የመንግስትን ትዕግስት በእጅጉ የሚፈታተን ቢሆንም መንግስት የጸጥታ ኃይሎቹን ያለአግባብ ላለመጠቀም እስከ ምን ድረስ መጠንቀቅ እንዳለበት በተግባር ያሳየበት ይመስለኛል፡፡ የመንግስት ትዕግስተኝነትና የጸጥታ ኃይሎቻችን በህዝብ ላይ አፈሙዝ ላለማዞር ያደረጉት ከፍተና ጥንቃቄ ጸረ -ሰላም ኃይሎችን በእጅጉ እንዳስከፋ አናዉቃለን፡፡ ብዙ ጉዳት ደርሶ ማየት ለሚፈልጉት ጃዋርና መሰሎቹ ወታደሮች ለምን ህዝቡ ላይ እንደማይተኩሱ ለመረዳት ተቸግረዋል፡፡ በመንግስታችን ተእግስተኝነትና በሰራዊታችን ህዝባዊነትና ጥንቃቃነት ምክንት ሁሉም ነገር እንዳሰቡት ልሆን ባለመቻሉ እጅግ ተበሳጭተዋል፡፡ እንግዲህ እነ ጃዋር በሌላ ዙር ሌላ ሙከራ እስከሚያደርጉ ድረስ ለግዜዉ የአሁኑ ምኞታቸዉ ሊሳካላቸዉ አልቻለም፡፡

2.3/ የህዝቡን የመብት ይሟላላኝ ጥያቄ የመንግስት ለዉጥ ጥያቄ እንዲመስል የተደረገዉ ከንቱ ሙከራ

ማንም እንደሚያዉቀዉ የህዝቡ ጥያቄ የነበረዉ መንግስትን(ገዥዉ ፓርቲን) ስልጣን እንዲለቅ አልነበረም፡ ምላሽ ማግኘት ሲገባቸዉ ያልተመለሱ የተወሰኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንደነበሩ ግን እርግጥ ነዉ፡፡ ከዚህ በፊትም እነዚህን መሰል ጥያቄዎች ሲኖሩ ባሉት ህዝባዊ አደረጃጀቶችና ዲሞክራሲያዊ መድረኮች በኩል የመሰለዉን ጥያቄ ሁሉ ሲጠይቅና አቅም በፈቀደ ሁሉ ምላሽ ሲያገኝበት የነበረ ነዉ፡፡ ህዝቡ የልማትና ሌሎች የመብት ጥያቁዎች ሲኖሩት ለመንግስት የማቅረብ ጉዳይ በፊትም የተለመደና ጤነኛ አሰራር ነዉ፡፡ አሁን የታየዉ ግን ከዚህ ቀደም ከነበረዉ በተለየ ሁኔታ የጉዳዩ ባለቤት የሆነዉን ህዝብ በተለይም ወጣቱን በመቀስቀስ ከፊት በማስቀደም ራሳቸዉ የጥፋት ኃይሎች ግን ከጀርባ ሆነዉ ህዝቡን ለጥፋት ድርጊት ስለዳረጉት ነዉ፡፡ በተለይ የዋህ ወጣቶች ለነዚህ መሰሪዎች ዓላማ ባለማወቅ በመሳሪያነት ማገልገላቸዉ ካልሆነ በስተቀር የቀዉሱ ዋነኛ ተዋናዮችና አቃጆች ጸረ- ኢትዮጵያ ኃይሎች ናቸዉ፡፡

የህዝቡ ጥያቄ የመንግስትን ስልጣን የመሳጣት ጥያቄ ቢሆን ኖሮ ህዝቡ ህጋዊ መንገዱ የቱ እንደሆነ ጠንቅቆ ያዉቃል፡፡ ህዝቡ የዚህ ዓይነት ጥያቄ ሲኖረዉ ምን ማድረግ እንዳለበት እነ ጃዋር እንዲነግሩት አየሻዉም፡፡ ራሱ ያዉቃልና፡፡ በስልጣን ላይ ያለዉ መንግስት ከእንግዲህ ሀገሪቱን የመምራት አቅም ስለለለዉ ወርዶ በሌላ መተካት አለበት የሚል ጥያቄ ቢኖረዉ ኖሮ ይህንና ሌሎች ጥያቄዎችንም ማስተናገድ የሚቻልበት ህገ መንግስታዊ አግባብ ሲላለ በዚያ መሰረት ብቻ ነዉ ሊሆን የሚችለዉ፡፡ ህዝቡ በስልጣን ላይ ያለዉን ፓርቲ የማይፈልገዉ ከሆነ ምን ማድረግ እንዳለበት ብቻ ሳይሆን ምን ማድረግ እንደሚችልም ጠንቅቆ ያዉቃል፡፡ ህዝብ በመንግስት ላይ ቅሬታ ሲኖረዉ ለመቅጣት ከፈለገ ምህረት እንደለለዉ በየ1997 ምርጫ ወቅት የአዲስ አበባን የምርጫ ዉጤት ማስታወስ ብቻ በቂ ነዉ፡፡

የአሁኑ የህዝቡ ጥያቄ ግን መንግስትን ያለ መፈለግ ጥያቄ አልነበረም፡፡ ምንም እንኳን ባይሳካለቸዉም አንዳንድ ወገኖች የህዝቡ ጥያቄ እንደዚያ እንዲሆን መሻታቸዉ ቢያንስ በዚያ መልክ እንዲተረጎም መፈለጋቸዉ ባይቀርም የህዝቡ ትክክለኛዉ ጥያቄ የነበረዉ ተጨማሪ የልማት ጥያቀዎቹ እንዲመለሱለትና እጅግ ያስመረሩትን መልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ነቀርሳዎች እንድነቀልለት ነዉ፡፡ እኔ ይህን የምልበት ምክንያት አሁን ያለዉ መንግስት(ገዥ ፓርቲ) በጭራሽ ስልጣን መልቀቅና በሌላ መተካት የማይገባዉ ነዉ በምል አይደለም፡፡ ህዝቡ ኢህአደግን ወደስልጣን ያወጣዉ ፈቅዶ ሲሆን ባሰኘዉ ግዜ ደግሞ ማዉረድ እንደሚችል ስለተገነዘበ ነዉ፡፡ ፍላጎቱን ማሟላት በተሳነዉ ግዜ ያለ አንዳች ግርግር እንደሚያወርደዉ ህዝቡም ኢህአዴግም ሁለቱም ያዉቃሉ፡፡ ስለዚህ ሰላመዊና ህገመንግስታዊ መንገድ ተጠቅሞ ህዝቡ ኢህአዴግን ከስልጣን መዉረድ እየቻለ የቀዉስ መንገድን የሚከተልበት አንዳችም ምክንት አይኖርም፡፡ ህዝቡ ዛሬዉኑ ስልጣን ይልቀቅ የሚልበት ምክንያትም የለዉም ፡፡ እንደዚህ ኣይነት ጥያቄም አላቀረበም፡፡

ጸረ-አንድነትና ጸረ ህዝብ ኃይሎች በእጅጉ ጠብቀዉ የነበረዉ እንደዚያ ይሆናል ብለዉ ነዉ፡፡ ባይሳካላቸዉም ይህን ፍለጎታቸዉን እዉን ለማድረግም ብዙ ጥሬት አድርገዋል ፡፡ በተጨማሪ የህዝቡ ጥያቄ ኢህአዴግ ሊፈታዉ የማይችል የስልጣን ይልቀቅ ጥያቄ እንደሆነ አድርገዉ በዉጭ ሀገር ሳይቀር ብዙ ፕሮፖጋንዳ ነዝተዋል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ያልተረዱት ነገር ቢኖር እንደዚህ ዓይነት የስልጣን ይልቀቅ ጥያቄ አልቀረበም እንጂ አስር ሺህ ይሁን መቶ ሺህ ሰዉ ወደ አደባባይ ወጥቶ መንግስት ዛሬዉኑ ስልጣን ይልቀቅ ብሎ ቢጠይቅ እንኳን መንግስት በዚህ ተደናግጦ ስልጣን ይለቃል ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም አስር ሺህም ይሁን መቶ ሺህ ሰዉ የቀረዉን ዘጠና ሚሊዮን ህዝብ ፍላጎትን መተካት አይችልምና፡፡

የመንግስትን በሰልጣን መቆየት የሚፈልጉ ወይም የሚያምኑበት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ዜጎች አስካሉ ድረስ የተወሰነ ቡድን በአደባባይ ወጥቶ መንግስትን ይልቀቅ ብሎ ሲለጮሄ መንግስት ተደናግጦ ስልጣን መልቀቅ አለበት ማለት አይደለም፡፡ በሌላ በኩል መንግስት እንኳን በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ይቀርና አስር ሰዉም ቢሆን ተገቢ የሆነ ተቀዉሞና ቅሬታ ካቀረበበት እኩል ክብደት ሰጥቶ ለህዝብ ጥያቄ ተገቢዉን መልስ መስጠት እንዳለበት ያዉቃል፡፡ መንግስት ከህዝብ እየቀረቡ ላሉ ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ የማይችል ከሆነ በቀጣዩ ምርጫ ህዝቡ ድምጹን እንደሚነፍገዉ ጠንቅቆ ስለሚረዳ ከአቅም በላይ ካልሆነበት በስተቀር ለህዝብ ጥያቄ ደንታቢስ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ምድር ከዚህ በኋላ በግርግር ወደ ስልጣን መዉጣት የሚቻልበት አንዳችም እድል እንደለለ ሊታወቅ ይገባል፡፡

3/ መንግስት የህዝቡን ደህንነት የማስከበር ኃላፊነቱን ሲወጣ የነበረዉ በከፍተኛ ጫናና ዉጥረት ዉስጥ ሆኖ ነበር

መንግስት በተፈጠረዉ አደገኛ ቀዉስ ወቅት የዜጎችን ደህንነት ለማስከበር ሲሰራ የቆየዉ በከፍተኛ ጫና ዉስጥ ሆኖ ነዉ :: በአንድ በኩል የመብቱ ባለቤት የሆን ዜጎች መንግስት የኛኑ ድህነት ለማስጠበቅ ሲያደርግ የነበረዉን ጥሬት በሚያበላሽ ተግባር ላይ መሳተፋችን ነዉ፡፡ ዜጎች በተለይ ጠቃዉሞ ማማት የሚፈልጉ ወገኖች የመንግስትን ሃላፊነት ካልተገነዘቡለትና ካላገዙት በመንግስት ጥሬት ብቻ ሰላም ማስፈን ስለማይቻል የመጀመሪ ተጎጂ የሚሆኑት ረሳቸዉ ዜጎች ናቸዉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በሰብአዊ መብት አስከባሪነት ስም የሚንቀሳቀሱ እንደአሸን የፈሉ በርካታ አለም አቀፍ ድርጅቶች ሆን ብለዉ የሚፈጥሩት ጫናም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ህዝብ መርጦ ስልጣን ላይ ካወጣዉ መንግስት ይልቅ እነሱ ለህዝቡ ተቆርቋሪ የሚሆኑበት አግባብ ተቀባነት የለለዉ ነዉ፡፡

3.1/ የአለም አቀፍ ተቋማትና ድንጋጌዎቻቸዉ በመንግስት ላይ የሚፈጥሩት ጫና

በሰብአዊ መብት ማስከበር ስም የሚንቀሳቀሱ በርካታ ድርጅቶች በድምር ሲታዩ በመንግስት ላይ እጅግ ከፍተኛ ጫና ሲፈጥሩ ነበር፡፡ እነዚህ ተቋማት ሁከት ፈጣዎች መረን የለቀቀ መብት እንዲኖራቸዉ ለመጎትጎት ካልሆነ በስተቀር መንግስት የዜጎችንን ደህንነት በማስከበር ረገድ ያለበትን ኃላፊነትና የሚገጥመዉን ተግዳሮት ከግምት አያስገቡም፡፡ የዜጎችንን ደህንነት በማስጠበቅ ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለበት መንግስት መሆኑ እየታወቀ ነገር ግን እጁ የፍጥኝ ታስሮ አንድም የቁጥጥር እርምጃ እንዳይወስድ ጫና ማድረጋቸዉ የዜጎችን ድህንነት ለአደጋ የሚያጋልጥና በአንጻሩ ህገ ወጦች ሁከት እንዲፈጥሩ ከማበረታታት ባለፈ ለሃገሪቱ የሚበጅ አንዳችም መፍትሄ አያመጣም፡፡

በነዚህ ድርጅቶች ጉትጎታ በየግዜዉ በመንግስት ላይ በርካታ ክሶችና ዉንጀላዎች ቢቀርቡም የኢፌድሪ መንግስት ግን በዚህ መሰረተ- ቢስ ክስ ተደናግጦ የሃገሪቱን ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነቱን ለአፍታም ቢሆን ችላ ማለት አይኖርበትም፡፡ መንግስት የዜጎችን ተቃዉሞ የማድረግ መብት መከበር እንዳለበት በጽኑ የሚያምን ቢሆንም በህገወጥ መንገድ የሚከናወኑና የደህንነት ስጋት የሚሆኑ ሁከቶችን በዝምታ እንዲያይ አይጠበቅበትም፡፡ ለነገሩ እኛ ላይ ሲሆን ይበረታሉ እንጂ የዲሞክራሲ አስተማሪና የሰብአዊ መብት ዳኛ ነን በሚሉ እንደ አሜሪካ ባሉ አገሮችም ቢሆን በዘረኝነትና በዜጎች መብት ጥሰት የሚስተካከላቸዉ የለም፡፡ እነዚህ የስብአዊ መብት ተሟጋች ነን የሚሉ ድርጅቶች ግን አፍንጫቸዉ ስር እየተደረገ ሲላለዉ ጉድ በጭራሽ መናገር አይፈልጉም፡፡

3.2/ ከሀገሪቱ ደህንነት ይልቅ የግለሰቦች መብት ይቅደም የሚሉ ወገኖች የሚፈጥሩት ጫና

የዜጎችን መብት በማስከበርና የዜጎችንን ደህንነት በመጠበቅ ረገድ አንዳንዴ ግጭት መፈጠሩና መንግስት አንዱን መምረጥ የሚገደድበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ህገመንግስታዊ መብትም ቢሆን ከህጋዊና ሰላማዊ አግባብ ዉጭ ለመጠቀም ሲሞከር በሂዴት የሀገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል፡፡ ህገመንግስታዊ ስርአቱ ቀጣይነት እንዲኖረዉና በረባ ባልረባዉ ሁሉ የመፈራረስ አደጋ አንንዳይጋረጥበት መጠበቅ የመንግስት ተቀዳሚ ሃላፊነት ነዉ፡፡ እንግዲህ መንግስት በዚህ መካከል አጣብቂኝ ዉስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ ዜጎች ህገመንግስታዊ ስርአቱም ሆነ አገሪቱ የጋራቸዉ በመሆናቸዉ መንግስት ይህን የማረጋገጥ ሃላፊነት እንዳለበት ተረድተዉ ሊተባበሩት ይገባል፡፡ መንግስት ዲሞክራሲያዊ መብት እንዳይጣስ የመጠበቅ ሃላፊነት ቢኖርበትም የሀገሪቱን ደህንነትም የማረጋገጥ ሃላፊነትም እንዳለበት መዘንጋት አይኖርበትም፡፡ የትኞቹም የዜጎች መብቶች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉት የሀገሪቱ ደህንነት ለአደጋ የሚዳርግ አስካልሆነ ብቻ ነዉ፡፡ በዲሞክረሲያዊ መብትና በሀገር ደህንነት መካከል አንዱን መምረጥ የግድ የሚያደርግ ሁኔታ ከተፈጠረ መንግስት ቅድሚያ መስጠት ያለበት የሀገሪቱን ደህንነት ማስከበር ላይ ነዉ፡፡

3.3/ ከሁከት ፈጣሪዎች የጥፋት ድርጊት ይልቅ የጸጥታ ኃይሎችን ጉድፍ ለማጉላት መሞከሩ

የመንግስትን ጉድፍ ፈልፍሎ በማዉጣትና በመቶ በማበዛት ለማሳጣት ሰንፈዉ የማያዉቁት አንዳንድ የግል ሚዲያዎች ሁኔታዉን በማራገብና ቀዉሱን በማባባስ ረገድ ትልቅ አፍራሽ ሚና እንደነበራቸዉ በሚገባ የሚታወቅ ነዉ፡፡ ,መጀመሪያም ራሳቸዉ ችግሩን በመፍጠር የተጫወቱት ጉልህ የሆነ አፍራሽ ሚና ሳያንሰ እንደገና የፀጥታ ኃይሉን ድርጊት በመኮነን በመቶ እያባዙና ያልሆነዉን ሆኗል አያሉ ህዝቡን በማስቆጣት አመጹ(ረብሻዉ) ወደ ሌላም አካባቢ በፍጥነት እንዲዛመት ጉልህ ድርሻ ነበራቸዉ፡፡ በተለይ በፀጥታ ማስከበር እንቅስስቃሴ ላይ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መሳተፋን ካወቁ በኋላ የመንግስትን ኃጥያት ለማጉላት መልካም አጋጣሚ ሆኖላቸዋል፡፡

መከላከያ ሰራዊቱ የህዝቡን ደህንነት ከማስከበር ያለፈ ሌላ ተልኢኮ እንደለለለዉ ልቦናቸዉ እያወቀ ሰራዊቱን በህዝቡ ላይ እንደዘመተ ወራሪ ሰራዊት አድርገዉ ህዝቡን ለማስደንበርና ለማስፈራት መሞከራቸዉ እጅግ አሳዛኝ ነዉ፡፡ የአሰቸኳይ ግዜ አዋጁ መታወጅንም ቢሆን የህዝቡን ደህንነት ለማስከበር ከነበረዉ ጠቀሜታ ይልቅ ሃገሪቱ በወታደራዊ ጨቋኝ አገዛዝ ሰር እንደወደቀች በማስመሰል ህዝቡን ለማሸበር ብዙ ጥረዋል፡፡ በተለይም እዚሁ ሆነዉ የአደጋዉን ስፋት ለመታዘብ ዕድሉ የነበራቸዉ አንዳንድ ጉምቱ የተቃወሚ ፓርቲ አመራሮች የአስቸኳይ አዋጁን መታወጅ ሲያጣጥሉ ለሰማ ሰዉ እነሱ ወደፊት ሃገር የመምራት ዕድል ቢገጥማቸዉ ምን ያደርጉ ይሆን? እያለ በግርምት መጠየቁ አይቀርም፡፡

4/ ሁከቱን በመቆጣጠር ረገድ በጥንካሬ ሊታዩ የሚገባቸዉ ከመልካም ተሞክሮቻችን በጥቂቱ

በቅርቡ የተከሰተዉን ሁከት በመቆጣጠር ረገድ በመንግስት በኩል ከተመለከትኳቸዉ ጠንካራ ጎኖች አንዱ የሁሉንም የጸጥታ ኃይሎች በማቀናጀት ሁከቱን ለመቆጣጠር የተቻለበት መንገድ ነዉ፡፡

እንደሚታወቀዉ የትኛዉም መንግስት ቢሆን የዜጎች ደህንነትን ፤የመንግስትና የሕዝብ ንብረትን ከአደጋ የማስጠበቅ ሃላፊነት አለበት፡፡ መንግስት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የሚያዉኩ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ለዚህ ተግባር ተብለዉ በሰለጠኑ መደበኛ ፖሊሶችና አድማ በታኝ ኃይል መጠቀም ይገባል፡፡ በርግጥ ሁኔታዉ ከአቅም በላይ ከሆነ መከላከያ ሰራዊቱን መጠቀም የግድ ሊሆን ይችላል፡፡ የመከላከያ ኃይልን ለመጠቀም ሁኔታዉ የግድ ካደረገ ደግሞ መከላከያ ብቻዉን ሳይሆን ከፖሊስ ጋር ተቀናጅቶና ተጣምሮ መሰማራት ይገባዋል፡፡

በአገራችን በቅርቡ በተከሰተዉ የጸጥታ ችግር ወቅት መከላከያ ሰራዊትን፤ፌዴራልና የክልል ፖሊሶችንና ልዩ ኃይል የሚባለዉንም ጨምሮ በአንድ አመራር (ዕዝ)ስር እንዲጠረነፉ በማድረግ ማእከላዊት ባለዉ ሁኔታ ሁከቱን ለመቆጣጠር የተሞከረበት አሰራር እንደ ጠንካራ ተሞክሮ መታየት ያለበት ነዉ፡፡ የጋራ ማዘዣ ጣቢያ በማዋቀር ሁሉንም አመራር በተዋረድ እንዲወርድ መደረጉ ለቅልጥፍናና ለቅንጅታዊ አሰራር ምቹ ከማድረጉም ሌላ ሁሉም በየፊናዉ በግብታዊነት በሚወስደዉ ያልተቀናጀ እርምጃ በዜጎች ላይ ሊደርስ ይችል የነበረዉን አደጋ በእጅጉ እንዲቀንስ ማድረግ ያስቻለ ነዉ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰዉ መንግስት የወቅቱ ሁኔታ ስላስገደደዉ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ እንድታወጅ በማድረግ እጅግ በአጭር ግዜ ሁኔታዉን በቁጥጥር ስር ከማድረጉም ሌላ በጥፋት ድርጊት ላይ ተሳትፈዋል ተብለዉ የተተረጠሩትን ለግዜዉ በቁጥጥር ስር አዉሎ በተሃዲሶ ፕሮግራም አሰተምሮና መክሮ ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ያደረገዉ ጥረትና የተገኘዉ ዉጤት የሚደነቅ ነዉ፡፡ አዋጁ የታወጀበት መንገድ በራሱ ህገ መንግስታዊ አግባብን ተከትሎ ሲሆን በአፈጻጸምም የመብት ጥሰት እንዳይኖርም የሚከታተል አካል በማቋቋም በየግዜዉ ለህዝቡ በይፋ እንዲገለጽ የተደረገበት አካሄድ መንግስት በሰብአዊ መብት አከባበር ላይም ትኩረት ማድረጉን የሚያሳይ አስመስጋኝ ተግባር ነዉ፡፡

5/ ለወደፊቱ ሊታረሙ የሚገባቸዉ ድክመቶቻችን

5.1/ በህብረተሰቡ በኩል የታዩ ድክመቶች

አንደኛ፤ መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄ ዬቱ እንደሆነ መለዬት ያለመቻልና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በመደበላለቅ መንግስትን ለማስጨነቅ መሞከር፡፡

ህዝብ ወደ አደባባይ በረባ ባልረባዉ ይወጣል ተብሎ አይገመትም፡፡ በተለያዩ ህዝባዊና ዲሞክራሲያዊ አደረጃጀቶችና መድረኮችና በተወካዮቹ በኩል መሰረታዊ የሚባሉ ጥያቄዎችን በየጊዜዉ ሲያቀርብ ቆይቶ አጥጋቢ ምላሽ ሲያጣ ብቻ ነዉ ወደ አደባባይ ለተቃዉሞ መዉጣት ያለበት፡፡ በዚህ መሰረት ወደ አደባባየይ ይዞ መዉጣት የፈለገዉ እጅግ መሰረታዊና ተቃዉሞ ሰልፍ ማድረግን የግድ የሚያደርግ ከበድ ያለ ጥያቄ ሲሆን ብቻ ይመስለኛል፡፡ ተቃዉሞ ለማሰማት በተፈለገበት ጉዳይ ትኩረት በማድረግ መልእክቱ ለህዝብም ይሁን ለመንግስት በሚገባ እንዲደርስ መደረግ አለበት እንጂ ከሌላ ነገር ጋር መደበላለቅ አይገባዉም፡፡ ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ተደበላልቆ የሚቀርብ ከሆነ ዋናዉን ጥያቄ ስለሚያደበዝዘዉ በሁለተኛ ደረጃ ሊታዩ በሚችሉና ብዙም አንገብጋቢ ባልሆኑ ጉዳዮች ተድበስብሶ አላስፈላጊ ጊዜና ኃይል ማባከን ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በእግር ኳስ ዉጤት ተስፋ ቆርጠናልና የፌዴሬሽኑ አመራሮች በሙሉ ከስልጣን ይዉረዱ የሚል ጥያቄና የማዳበሪያ ዋጋ ይቀንስልኝ የሚል ጥያቄ አብሮ ከቀረበ አንዱም ሁኔኛ መልስ ሳያገኝ እንዲሁ ይቀራል፡፡ የጥያቄዎቹ ባለቤቶችም የተለያዩ ናቸዉና ፡፡ ለአንድ አርሶአደር አንገብጋቢዉ ማዳበሪያ እንጂ እግር ኳስ አይደለም፡፡

ስለዚህ መንግስትን ለማስጨነቅ ተብሎ አግባብነት የለላቸዉን ጥያቄዎች ሁሉ በአንድ ግዜ በማቅረብ ዛሬዉኑ መልስ ካለገኘን አገር ምድሩን እንገለባብጣለን ብሎ ማስፈራራት አግባብነት የለዉም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ህዝቡ የመንግስትንም ሆነ የሃገሪቱን አቅም የት ድረስ እንደሆነ ለይቶ ማወቅ መቻል አለበት፡፡ መንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን አስጠንቶ የሚተገብረዉ ለራሱ ለህዝቡ ይበጃሉ በሚል ነዉ፡፡ መንግስት ራሱ አስቦ ከሚሰራዉ ዉጭ ህዝቡ ራሱ እንዲሰራለት የሚጠይቃቸዉና የሚፈጸሙለት ብዙ ናቸዉ፡፡ ህዝቡ በዚህ ሁሉ ባለመርካትም ከክልል ዋና ከተማም አልፎ በየዞኑና በየወረዳዉ ሁሉ ሳይቀር ከተለመዱት ከአስፋልት፤ መብራት፤ ዉሃ ጥያቄዎች ዉጪ ለኛም ሆስፒታል ይከፈትልን፤ ዩኒቨርሲቲ ይቋቋምልን፤ስታድየም ይገንባልን ፤የእንዱስትሪ ፓርክ ይቋቋምልን- ወዘተ የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በግልጽ ሲጠይቅ አንዳንድ ግዜ በሁኔታዉ እገረምና መንግስት ይሁን ሁሉ እየሰራ ያለዉ ገንዘብ ከዬት እያመጣ ነዉ እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ ታዲያ ህዝቡ መንግስት ሊመልሰዉ አቅሙ የማይፈቅድለትን ጥያቄ ሁሉ ሳይቀር ሳይሸማቀቅ መጠየቅ እየቻለ የእነ ጃዋርን ፍላጎት ለሟሟላት ተብሎ ወደአደባባይ ለአመጽ የሚወጣበት ምክንያት ፈጽሞ ሊገባኝ አልቻለም፡፡

ሁለተኛ፤ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ህገመንግስታዊ መብቱን ነጥቀዉ ለእኩይ ዓላማቸዉ መጠቀሚያ ሲያደርጉት ሲሞክሩ እሻፈረኝ በሚል ለመገዳደር አለመሞከሩና ለመሰሪ ተንኮላቸዉ መመቻቸቱ፡

ህዝቡ ምንግዜም ቢሆን ህዝቡ ጥያቄ ለመጠየቅም ሆነ ተቃዉሞዉን ማሰማት ያለበት ራሱና ራሱ በመረጣቸዉ ወኪሎቹ በኩል ብቻ ሊሆን ይገባ ነበር፡፡ የህዝብን ጥያቄ ለመንግስት መቅረብ ያለበት ተጠያቂነት ባለባቸዉና ድርድር ማድረግም ካስፈለገ ከመንግስት ጋር ቀርበዉ ለመደራደር ከሚችሉ አስተባባሪዎቹ ጋር እንጂ በሌሎች በማይታወቁና በአካልም በለሉ ኃይሎች በፌስቡክ በመመራት መሆን አልነበረበትም፡፡ ህገመንግስታዊ መብታቸዉን ተጠቅመዉ በሰላማዊ መንግድ ተቃዉሞአቸዉን ለማሰማት ወደ አደባባይ የሚወጡ ዜጎች የራሳቸዉን አጀንዳ ይዘዉ በራሳቸዉ የሰልፍ አደራጆች መመራት ይገባቸዉ ነበር እንጂ አጋጣሚዉን ተጠቅመዉ የተለየ ዓላማ ለማሳካት በሚሞክሩ ኃይሎች ፍላጎት መመራት አልነበረባቸዉም፡፡

ህዝብ መጠየቅ ከፈለገዉ ዉጭ ሆን ብለዉ ሌላ ነገር እያስከተሉ በቀላሉ መፍትሄ ማግኘት ይችል የነበረ ነገርን እወሳሰቡና ህዝቡን በመንግስት ላይ እያነሳሱና እርስበርሱም እያናከሱት ለግጭት መንስኤ ሲሆኑ በተግባር እያየ ቢያንስ የራሱን ልጆች በመገሰጽ በጥፋት ተግባር እንዳይሳተፉ ለማድረግ የተንቀሳቀሰበት ፍጥነት ጥሩ የሚባል አይደለም፡፡ እጅግ ዘግይቶ ነዉ፡፡ ከህዝባችን ነባሩ የመቻቻል ባህል ባፈነገጠ መልኩ አንዳችን ሌላዉን ለመጉዳት መንቀሳቀሳችን በምንም ሁኔታ ተቀባይነት የለዉም፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ህዝብ ተጎጂ እንጂ ተጠቀሚ ሊሆን እንደማይችል ለመረዳት የቻልነዉም እጅግ ዘግይተን ነዉ፡፡  

በአካል የማያዉቃቸዉ ችግሩን ጠንቅቀዉ በማይረዱ ሰዎች ከባህር ማዶ ሆነዉ በሚያራግቡት ወሬና ቅስቀሳ ተታሎ ለጥፋት ተግባር በመነሳሳቱ መንግስት ሰላም ለማስፈን ሲያደርግ የነበረዉን ጥሬት ለማገዝ የተንቀሳቀሰዉ ከብዙ ጉትጎታ በኋላ ነዉ፡፡ በመጀመሪያ አካባቢ ላይ ለመንግስት እጅግ አዳጋች የሆነበትም በዚህ ምክንያት ነዉ፡፡  መጀመሪያ ላይ እኮ መንግስትን በራስህ ተወጣ ብሎ የተወዉ ነዉ ኢኮ የሚመስለዉ፡፡ ቢያንስ የራሱን ልጆች በመምከር በጥፋት ተግባር እንዳይሳተፉ ማድረግ ይችል ነበርና፡፡ በኋላ ግን ህዝቡ የጸረ ሰላም ኃይሎችን ደባ በመረዳት ሁከቱን ለማስቆም በመንቀሳቀስ ከሰራዊቱ ጎን መሰለፍ ሲጀምር የመንግስት የጸጥታ ኃይሎችም ስራቸዉ ቀና ሆነላቸዉ፡፡ ያለህዝብ ድጋፍ ምንም ማድረግ እንደማይቻል በተግባር ተረጋገጠ፡፡ ከዚያ በኋላ ከሰራዊቱ ወድሞ አጥፊዎችን በወረንጦ እየለቀመ ያመጣዉ ራሱ ህዝቡ ነበር፡፡ ህዘቡ መጀመሪያ በመንግስት ላይ ያደመ መምሰሉና በኋላ ላይ ደግሞ ግንባር ቀደም የሆነበት ሁኔታ ከምን የመነጨ እንደሆነ የመተንተን ጉዳይ ለምሁራን የሚተዉ የቤት ስራ ነዉ፡፡

5.2 በመንግስት በኩል የታዩ ድክመቶች

አንደኛ፤ በአደባባይ ተቃዉሞ የማሰማት እድል መጥበቡ ለቀዉስ በር ከፋች መሆኑ፤

ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን የሚፈቀድ መብት በሀገመንግስቱ የተረጋገጠ ቢሆንም በተግባር ግን መንግስት የተለያዩ ሰበቦችን በመደርደር እንቅፋት እየፈጠረ ነዉ የሚለዉን ትችትና ክስ መስማት ከጀመርን ቆይተናል፡፡ ‹‹ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በተደጋጋሚ ጠይቀን ሊፈቀድልን አልቻለም፡፡ መንግስት ሆን ብሎ ለተቃዉሞ እንዳንወጣ እንቅፋት ይፈጥርብናል፡፡›› የሚለዉ ስሞታ እንዳለ ሆኖ ተቃዉሞ ለማድረግ አድሉን ያገኙትም ቢሆኑ ይህን እድል በሌላ ግዜ በድጋሚ አናገኝም በሚል መንግስትን መጠየቅ ወይም መቃወም የሚገባቸዉን ጉዳይ በደንብ ሳይለዩ በአንድ ግዜ እርስበርሱ የሚጣረስና አላስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን ሁሉ በአንድ ላይ አጭቀዉ ወደ ጎዳና ስለሚወጡ በቁምነገር ቆጥሮ የሚያዳምጣቸዉ ስለማይኖር ሰልፉ አንዳችም ዉጤት ሳይሰጥ ሲያበቃ ታዝበናል፡፡

በሌላ በኩል የተቃዉሞ ሰልፍን በሚመለከት ኃላፊነት ካለበት የመስተዳደሩ አካል ጋር በቅርበት በመመካከር በሰላም ተጀምረዉ በሰላም የተጠናቀቁ የተቃዉሞ ሰልፎች ብዙ ናቸዉ፡፡ አንዱ ድርጅት ጠይቆ ባደራጀዉ የተቃዉሞ ሰልፍ ላይ ሌላዉ የማይመለከተዉ ድርጅት ደጋፊዎች ያለ ሰልፍ አደራጆቹ ፈቃድ በቦታዉ በመገኘት ለግጭት ምክንያት የሆኑበት አጋጣሚ ብዙ ነዉ፡፡ አብዛኛዉን ግዜ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲቀርብ የነበረዉ ወቀሳ ሰልፍ ለማድረግ አስቀድሜን አሳዉቀን ምላሽ ተነፍገናል ወይም ደግሞ የቦታና የቀን ለዉጥ አድርጉ ተብለናል የሚል እንጂ አስከነአካቴዉ ሰልፍ ማድረግ አትችሉም በሚል ስለመከልከላቸዉ የገለጹበት ወቅት አላስታዉስም፡፡

በእኔ እምነት መንግስት ሰላማዊ ሰልፍ ጭራሽ እንዳይደረግ የመከልከል ስልጣን እንደለለዉ ይገነዘባል ብዬ ስለማስብ ምናልባት በሚፈለገዉ ፍጥነት መልስ የማይሰጥበት ምክንያት የሰልፉ አስተባባሪዎቹ ወይም ጠያቂዎቹ ለተቃዉሞ የጠሩትን ህዝብ በአግባቡ መቆጣጠር አይችሉም በሚል ጥርጣሬ የጸጥታ ችግር ሊፈጠር ይችላል ከሚል ስጋት የመነጨ ይመስለኛል፡፡ አንዳንዴ በዚህ ቀንና በዚህ ቦታ ማድረግ ስለማትችሉ ሌላ ቦታና ግዜ መርጣችሁ ንገሩን ሲባሉ እምቢተኛ በመሆን የመጣዉ ይምጣ በሚል በእልህ ደጋፊዎቻቸዉን ለተቃዉሞ ወደ አደባባይ የሚጠሩ አሉ፡፡

በዚህ ረገድ ትልቁ ችግር ተቀራርበዉ ያለ መነጋገር ይመስለኛል፡፡ መንግስት ተቃዉሞ ሰልፍ እንዲደረግ በጭራሽ ፊላጎት የለዉም የሚለዉ የተቃዋሚዎች አመለካከትና መንግስት የሀገሪቱን ደህንነት የመጠበቅ ተቀዳሚ ኃላፊነት አለበት ከሚለዉ እዉነታ ጋር ለማጣጣም የሚቻለዉ ሁለቱም ወገኖች ተቀራርበዉ በመነጋገር ልዩነቶቹን ሲቀርፉ ይመስለኛል፡፡ በተረፈ ግን መንግስት ካልፈቀደ በግድ እናደርጋለን የሚለዉ አቋም ከህጋዊዉ መንገድ ይለቅ ህገ ወጡን መንገድ የመምረጥ አዝማሚያ በመሆኑ እየተለመደ ሲሄድ ችግር ሊያስክትል ይችላልና በመንግስት በኩል ማስተካከል የሚገባዉ ነገር ካለ ቢያስተካክል ለሁላችንም ይበጃል፡፡

መንግስት ህዝብ ተቃዉሞዉን በሰላማዊ መንገድ እንዲገልጽ የማያበረታታና ተስፋ የሚያስቆርጥ ከሆነ የበለጠ ተጎጂ የሚሆነዉ ራሱ መንግስት ነዉ፡፡ ህዝብ የሚፈልገዉን ነገር በሰላማዊ መንገድ ማግኘት ካልቻለ የቅርብ ግዜዉ ዓይነት ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ድሮም ቢሆን በሚገባ የሚታወቅ ሆኖ እያለ መንግስት ግን ምንም ነገር ሊፈጠር እንደማይችል ሆኖ በክልከላዉ ከጸና የባሰ ቀዉስ ዉስጥ ሊገባ ይችላል፡፡

በቀላሉ መልስ ልታገኝ ትችል ለነበረች ቀላል ጥያቄ መፍትሄ አስቀምጦ መገላገል እየቻለ መንግስት ጉዳዩን ሲያስታምምና በሌላ ሲያላክክ ያች ትንሽና ምናልባትም የጥቂት ሰዎች ጥያቄ የነበረች እየተለጠጠችና ብዙ ህዝብም ወደ ተቃዉሞዉ ጎራ እየሳበች በመጨረሻም በቀላሉ መፍትሄ ማስቀመጥ ወደማይቻል ደረጃ ታደርሳለች፡፡ መንግስት ባንድ ጊዜ ዲሞክራትም አምባገነንም መሆን አይችልም፡፡ ከሁለት አንዱ ነዉ ሊሆን የሚችለዉ፡፡ ቆንጆ ህግ አዉጥቶና እንከን የለለዉ ህገመንግስት አዘጋጅቶ ሲያበቃ ህዝቡ የመብት ይከበርልኝ ጥያቄ ሲያነሳ እምቢተኛ ከሆነ ወይም ፈጥኖ ምላሽ መስጠት ካልቻለ የዚያን ሰሞን ዓይነት ችግር ዉስጥ ሊገባ ይችላል፡፡

በእኔ እምነት መንግስት የተቃዉሞ ሰልፍን የሚሸሽበት ወይም የሚፈራበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም፡፡ በአደባባይ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በህዝባዊ ሰብሰባዎችም ወይንም በሚዲያዎች ለመንግስት ቀርበዉ ምላሽ ሳያገኙ ችላ የተባሉ እንጂ አዲስ ጥያቄም አልነበረም፡፡ መንግስት አስቀድሞ የማያዉቀዉ አንዳችም የተለየ አዲስ ጥያቄ አልቀረበለትም፡፡ መንግስት ያላሟላዉንና እንደ ጉድለት የሚታዩበትን ድክመቶቹን ራሱ ጠንቅቆ ስለሚያዉቅ ወደ አደባባይ መዉጣቱ ሊፈጥርበት የሚችል ስጋት አይታየኝም፡፡ ከህዝብ ጥያቄ ጀርባ ሌላ ዓላማ ያነገቡ ኃይሎች አጋጣሚዉን ተጠቅመዉ የደህንነት ስጋት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ መስጋት ተገቢ ቢሆንም ይህን ፈርቶ መብትን እንዳለ መዝጋት ግን ለአጥፊዎች የበለጠ እድል አንደመስጠት ነዉ የሚቆጠረዉ፡፡

ሁለተኛ፤ መንግስት ቀዉሱ (አደጋ) እንዳይከሰት ቀድሞ የማምከን እርምጃ ለመዉሰድ ፈጣን አለመሆኑ፤

በአንዳንድ አካባቢዎች ከህዝብ ጀርባ ተከልለዉ አደጋ ለማድረስ የሚፈልጉ የጥፋት ኃይሎች እንዳሉና ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ በቂ መረጃ እያለ ለዚያ የሚመጥን እርምጃ መዉሰድ ተስኖት ንጹሃን ዜጎች በጸረ ህዝቦች ሴራ ለአደጋ መጋለጣቸዉና ንብረት መዉደሙ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ የቢሾፍቱ ኢሬቻ በአል መጥፎ ክስተተት ከዚህ አኳያ የመጀመሪያዉ ተጠቃሽ ነዉ፡፡ በቢሸፍቱ የደረሰዉ ይህ አደጋ ያልተጠበቀ ነዉ የሚያሰኝ አይደለም፡፡ ከቀናት በፊት ጀምሮ መርዘኛ ቅስቄሳ ሲደረግ እንደነበር ይታወቃልና ፡፡ በርግጥ መንግስት እያንዳንዱን ቀዳዳ መድፈን ባይችልም ነገር ግን ችግር ሲፈጠር ምን ማድረግ እንዳለበት ቀደም አድርጎ መዘጋጀት ይገባዉ ነበር፡፡

በቢሾፍቱ ኢሬቻ በዓል አደጋ ሊከሰት እንደሚችል እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ከቀናት በፊት ጀምሮ ሲያደርጉ ከነበረዉ ቅስቄሳ መረዳት አያዳገትም ነበር፡፡ በርግጥ በዓሉ ከወትሮዉ ለየት ባለ ድምቀት እንዲከበር የመንግስትም የህዝብም ፍላጎት ስለነበር እጅግ በርካታ ህዝብ ወደዚያ መትመሙ እንደማይቀር ቅድመ -ግምትም ነበር፡፡ ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የጸጥታ ኃይሎችም እጅግ ጠንካራ ጥበቃ ሲያደርጉ እንደነበርም አይተናል፡፡ ሆኖም መጀመሪያዉኑ እንደተሰጋዉ ጸረ- ሰላም ኃይሎች አጀማመሩ እጅግ ደማቅና ሰላማዊ የነበረዉን የበዓሉን አከባበር በድንገት ቀይረዉ አሳዛኝ በሆነ ክስተት እንዲቋረጥ አደረጉት፡፡ በደቡብ ክልልም በጌዴኦና ኮምሶ ልዩ ወረዳ እንዲሁም በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች በሰዉና በንብረት ላይ የደረሰዉ ጉዳት አስቀድም በግልጽ ቅስቄሳ እየተደረገ የተፈጸመ እንጂ ድንገተኛና የአጋጣሚ ክስተት አልነበረም፡፡

ከዚሁ ብዙ ሳንርቅ ሌላዉ ተጠቃሽ ድክመት ደግሞ በወቅቱ መርዘኛ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ ማህበራዊ ድረ- ገጾችና(በተለይ የሞባይል ኢንተርነት) ሌሎች ሚዲያዎችን ለመዝጋት መንግስት ፈጣን አለመሆኑ ነዉ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ ከዉስጥም ከሃገር ዉጭም ሆነዉ በማህበራዊ ድረ-ገጾች እጅግ አደገኛ ቅስቀሳና ለአመጽ የማነሳሳት ተግባር እያካሄዱ እንዳሉና በተግባርም በርካታ ጥፋት እየተሰራ መሆኑን እየታየ መንግስት አጥፊ ኃይሎች ለዚህ እኩይ ተግባራቸዉ እየተጠቀሙበት ያለዉን ማህበራዊ ገጽ ፈጥኖ ለመዝጋት አለመሞከሩ ትልቅ ስህተት ይመስለኛል፡፡ አንተርነት ለአጭር ግዜ ይቋረጥና ወዲያዉኑ ደግሞ ይጀምር ነበር፡፡ መንግስት በዚህ ረገድ ለማመንታቱ ምክንት ነዉ ተብሎ የተገመተዉ ኢንተርኔት ይዘጋል የሚል ትችት እንዳይሰነዘርበት ስለፈራ ነዉ የሚል ነበር፡፡ በኋላ ግን መንግስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ እንዳደረገዉ መጀመሪያዉኑ እንደዚህ ዓይነት እርምጃ ፈጥኖ ወስዶ ቢሆን ኖሮ በወቅቱ የደረሰዉን አደጋ ሊቀንሰዉ በእጅጉ ይችል ነበር ብዬ አስባሁ፡፡

ሶስተኛ፤ ተቃዉሞ የማሰማትም ሆነ ሁከትን የመቆጣጠር ተሞክሮአችን አናሳ መሆን ፤

እስካሁን በአገራችን እየታየ ካለዉ ሁኔታ ተነስቼ ስታዘብ የተቃዉሞ ሰልፍን ተከትለዉ የሚነሱ የከተማ ዉስጥ ሁከትን ለመቆጣጠር መንግስት ምን ማድረግ እንዳለበት የልምድ ችግር ያለበት ይመስለኛል፡፡ አሜሪካ፤ ፈረንሳይ፤ ኢንግሊዝ ስፔይይን፤ ጀርመን ወዘተ ጠንካራ ዲሞክራሲ ስርአት ገንብተዉ የህዝብን የልማት ፍላጎት በተጨባጭ መልሰዉ ከፍተኛ አድገት ደረጃ ላይ የደረሱ አገሮች ዉስጥም በየግዜዉ ህዝቡ ተቀዉሞና ስራ ማቆም አድማ ሲያደረግ በዜና ማሰራጫዎቻቸዉ እያየን ነዉ፡፡ በተደጋጋሚ የተቃዉሞ አመጽ የተጋለጡ በመሆናቸዉ የዚህ ዓይነቱን የህዝብ ቁጣና የከተማ ሁከት መቆጣጠር የሚያስችላቸዉን ልምድ አዳብረዋል፡፡ ጠንካራ የረብሻ መቆጣጠሪያ ስልትም (riot control mechanism) በሂዴት ገንብተዋል፡፡ ረብሸኞችን ባሀሪይ (crowd behavior) ጠንቅቀዉ ስለሚያዉቁ ሁከቱ ተባብሶ ወደ ከፋ ሁኔታ እንዳይቀየር ማድረግ የሚችሉበት የዳበረ ልምድ አላቸዉ፡፡

የጸጥታ ኃይሎች (ፖሊሶች) የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲዊ መብት ሳይደፈርና ኃይል መጠቀም (use of force) ሳያስፈልጋቸዉ እንዴት አድረገዉ ችግሩን እንደሚሻገሩት በስልጠናም በተግባርም የዳበረ ልምድ አላቸዉ፡፡ ህዝቡም ቢሆን የመንግስትን ኃላፊነትን ጠንቅቄዉ ያዉቃል፡፡ መብታቸዉን እንዴት መጠየቅ እንዳለባቸዉም ይገነዘባሉ፡፡ ህዝቡ ራሱ ፈልጎ ካልሆነ በስተቀር በጥፋት ኃይሎች ሴራ ተገፋፍቶ ወደ አደባባይ የሚወጣበት ሁኔታ የለም፡፡ በሰለጠነዉ ዓለም የመብት ይሟላልኝ ጥያቄና የመንግስት ስልጣን ይልቀቅ ጥያቄ መካከል ያለዉን ልዩነት ህዝቡ ጠንቅቆ ይረዳል፡፡ ራሳቸዉ መርጠዉ ሃላፊነት የሠጡትን መንግስት በረባ ባልረባዉ ሁሉ ስልጣን ይልቀቅ አይሉም፡፡ በማንም አጭበርባሪ ስብከት አያጎበድዱም፡፡

የአሜሪካ ወይንም የእንግሊዝ ዜጋ መንግስታቸዉን ለመተቸት ወይንም የመብት ጥያቄ ለመጠየቅ አንደ መስቀል በዓል በዓመት አንድ ግዜ የሚመጣ ሰላማዊ ሰልፍን መጠበቅ አያስፈልጋቸዉም፡፡ ምክንያቱም በየቀኑ ባሰኛቸዉ ነጻ ሚዲያ ላይ ቀርበዉ በነጻነት መተቸት ስለሚችሉ ነዉ፡፡ ካሰኛቸዉ ደግሞ በየቀኑ ለተቃዉሞ ወደ አደባባይ መዉጣት ይችላሉ፡፡ የሀገሪቱ ጋዜጠኞች ራሳቸዉ መንግስትንም ሆነ የሌላ አካል ስህተት አይተዉ በይሉኝታ የሚያልፉ አይደሉም፡፡ በዚህ ላይ ህግ አዉጭዉ አስፈጻሚዉ እንዳሻዉ እንዲፈነጭ ዕድል የሚሰጥ አይደለም፡፡ ስለዚህ መንግስታቸዉ(አስፈጻሚዉ) ሁልግዜም ተጠንቅቆ ለመስራት ይገደዳል፡፡ በአሜሪካ አንድ የጋዜጣ ወይም ቴለቭዥን ጋዜጠኛ በመደበኛ ፕሮግራሙ በቀላሉ በዜና መልክ ሊሰራ የሚችለዉን ጉዳይ እኛ እዚህ ተመሳሳይ ይዘት ያለዉ ትችት በመንግስት ላይ ለማቅረብ የአንድ ከተማ ህዝብ ሙሉ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ይገባዋል፡፡ ለዚያዉም ከተፈቀደለት ማለት ነዉ፡፡

በዚህ ላይ እኛ መንግስትን ለመንቀፍም ሆነ ጥያቄ ለመጠየቅ የምንንቀሳቀሰዉ በራሳችን ፍላጎት ተነሳስተን ሳይሆን በአጭበርባሪዎች ስብከት ተገፋፍተን ነዉ፡፡ መብታችን ዳር ድንበሩ አስከ ምን ድረስ እንደሆነ ብዙ አያሳስበንም፡፡ ለአመታት የገነባነዉን በአንድ ጀምበር ስናወድም ትንሽ እንኳን አይሰቀጥጠንም፡፡ የኦሮሞ ህዝቦችን ታለቅ ኩራት የሆነዉን የጌዳ ስርአት በዩኔስኮ በቅርስነት ለማስመዝገብ ብዙ ሲደከምበት ቆይቶ ዉጤቱ በጉጉት እየተጠበቀ እያለ ስንት የዉጭ ታዛቢዎች በተገኙበት የኢሬቻ በዓልን ለማጨናገፍ መሞከራችን ስለ ሁኔታዉ በሰሙ የዉጭ ዜጎች ዘንድ እንድናፈር ያደረገ የተረገመ ድርጊት ነዉ፡፡ ከዚያ የጥፋት ድርጊት ምንድነዉ የተጠቀምነዉ? እነጃዋርን ለማስደሰት ብለን የኦሮሞን (የኢትዮጵያን) ህዝብ ያሳዘነ ድርጊት መፈጸምስ ተገቢነቱ ምኑ ላይ ነዉ? እኛ የጎደለንን ነገር እንዲሟላልን ለመጠየቅ በስንት ድካም ያፈራነዉን የግድ ማዉደም ያለብን ይመስል በገዛ ንብረታችን ላይ ጥፋት ፈጸምን፡፡ ለዚህም ነዉ እኛ ተቃዉሞ እንዴት ማሰማት እንዳለብን አናዉቅም ፤መንግስትም ተቃዉሞን ለማስተናገድም ሆነ ሁከቱን ለመቆጣጠር የልምድ ችግር አለበት ለማለት የደፈርኩት፡፡

6/ ችግሩን የተገነዘብንበት አግባብ

በአገራችን የደረሰዉ ቀዉስ ካስከተለዉ ጥፋት በመነሳት ዳግመኛ የዚህ ዓይነቱ ችግር ዉስጥ እንዳንገባ ማድረግ ተገቢነቱ እንተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን ተከስቶ የነበረዉ አደጋ ራሳችንን በሁሉም ረገድ ፈትሸን ለወደፊቱ የሚጠቅመንን ትምህርት ለመቅሰም የሚያስችለን መልካም አጋጣሚም ጭምር ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባዉ ነዉ፡፡ የሁኔታዉ አስተማሪነት እንደ እያንዳንዳችን ግንዛቤ ደረጃ የተለያየ ሊሆን መቻሉ እርግጥ ነዉ፡፡ ነገር ግን አደጋዉን (ቀዉሱን) የተመለከትንበት አግባብ ለየቅል የመሆኑ ጉዳይ ከቀዉስ አዙሪት ለወደፊቱም ማምለጥ ስለመቻላችን እንድንጠራጠር ያደርገናል፡፡ በዚህ ረገድ በእኔ አረዳድ በሶስት ምድብ የሚፈረጁ አመለካከቶች(ወገኖች) እንዳሉ እገምታለሁ፡፡

በመጀመሪያ ወገን የሚመደቡት ከሀገሪቱ ይልቅ ለድርጅት የሚጨነቁ በመሆናቸዉ ቀዉሱን በአጠቃላይ በሀገሪቱ ላይ የተጋረጠ አደጋ አድርገዉ ሳይሆን በድርጅቱ ስልጣን ላይ ያነጣጠረ አደጋ አድርገዉ የቆጠሩ ናቸዉ፡፡ ቀዉሱን በገዢዉ ፓርቲ ስልጣን ላይ የተነጣጠረ አደጋ አድርገዉ በጠባቡ የሚያዩ እነዚህ ወገኖች ከችግሩ መዉጫ ብለዉ የሚያቀርቡልንን የመፍትሄ ሃሳብ አምነን ለመቀበል እንቸገራለን፡፡ ምክንያቱም ቀዉሱን የተረዱበት መንገድ በራሱ ችግር ያለበትና በድርጅት ወገንተኝነት ላይ ያነጣጠረ ስለሆነ ለችግሩም የሚታያቸዉ መፍትም ከዚሁ አቋማቸዉ የማይርቅ በመሆኑ ነዉ፡፡ እነዚህ ወገኖች በሀገሪቱ ላይ የደረሰዉን ያን ሁሉ መመሰቃቀል በገዥዉ ፓርቲ ስልጣን ላይ ያነጣጠረ አደጋ ብቻ አድርገዉ የሚቆጥሩና እንደዚያም እንዲመስል የሚፈልጉ በመሆናቸዉ መፍትሄ አምጡ ሲባሉም ቀድሞ የሚታያቸዉ መፍትሄ የኢህአዴግን ስልጣን ዳግመኛ ለአደጋ ተጋላጭ እንዳይሆን ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ከመሆን አያልፍም፡፡ በጥልቅ ተሃድሶዉ ላይም “ወገቤን “እያሉ እያስቸገሩ ያሉትም እንደዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች እንደሆኑ ከተረዳን ቆይተናል፡፡ የድርጅቱና የመንግስት የላይኞቹ አመራሮች ድክመታቸዉን ሳይደባብቁ ማማናቸዉን አንደሽንፈት የቆጠሩና ድርጅቱ ላይ ክህዴት እንደተፈጸመ የሚቆጥሩ ናቸዉ፡፡ ድርጅትን ከሀገር የሚያስቀድሙ በመሆናቸዉ መንግስት በሰሩት ጥፋት ከቦታቸዉ ያነሳቸዉን አንዳንድ ባለስልጣኖችን በስም እየጠቀሱ ከስልጣን መነሳታቸዉ የፈጠረባቸዉን ንዴት ሳይደብቁ በአደባባይ በቁጭት የሚናገሩም እንዳሉ ተረድተናል፡፡ እንግዲህ ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ህልዉና ይልቅ ለጥቂት ግለሰቦች ከስልጣን መነሳት መጨነቃቸዉ ያለነገር የሆነ ሳይሆን በደረሰዉ ቀዉስ በጭራሽ አለመቆርቆራቸዉን የሚያመለክት ነዉ፡፡

በሁለተኛዉ ወገን ያሉትም ከመጀመሪያዎቹ ብዙም የማይለዩ ሆነዉ በሀገሪቱ ላይ የደረሰዉን ቀዉስ የመንግስትን (የኢህአዴግን)ስልጣን ለመነቅነቅ ብሎም ለወደፊቱ አሽቀንጥሮ ከስልጣን ለማዉረድ እንደሚቻል ያመላከተ መልካም አጋጣሚ አደርገዉ የቆጠሩ ናቸዉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ቀዉሱን የተረዱት ለስልጣን ነጠቃ ከነበረዉ ጠቀሜታ አንጻር ብቻ በመሆኑ በሀገሪቱ ህዝብ ላይ የደረሰዉ ያ ሁሉ ችግር በጭራሽ የማይሰማቸዉ ናቸዉ፡፡ ችግሩ በቶሎ በቁጥጥር ስር ባይዉል ኖሮ በሀገሪቱ ላይ ሊያስከትል የሚችለዉን የመበታተን አደጋ ሊታያቸዉ አልቻለም፡፡ እነዚህ ወገኖች ኢህአዴግን ከስልጣን ለማባራር ሲባል አገሪቱ ሺህ ቦታ ብትበታተን ደንታ የለላቸዉ ራስ ወዳዶች ናቸዉ፡፡ እንደዚህ ከአፍንጫቸዉ አርቀዉ የማያስቡ የስልጣን ጥማት ያሰከራቸዉ ግለሰቦች ቀዉሱ እንዳሰቡት ሳይሆን በቶሎ በመገታቱ እጅግ የሚቆጩና ለወደፊቱም በከፋ ሁኔታ ተመልሶ እንዲመጣ የሚመኙ ናቸዉ፡፡

በሶስተኛ ደረጃ ያሉት ደግሞ ብዙም የተለየ ፖለቲካዊና ቡድናዊ ዓላማ የለላቸዉና ከቡድናዊ ስሜት ይልቅ የሀገራቸዉን አጀንዳ የሚያስቀድሙ ናቸዉ፡፡ እነዚህ ወገኖች አብዛኛዉን ህዝብ የሚወክሉ በመሆናቸዉ የተለያዩ መገለጫዎች ሊኖራቸዉ የግድ ነዉ፡፡ ለምሳሌ የደረሰዉን አደጋ አስከፊነቱን እየተገነዘቡ ነገር ግን አቃለዉ ለማየት የመፈለግ አዝማሚያ ይታይባቸዋል፡፡ አደጋዉን አቅለዉ የማየታቸዉ መነሾ “ከዚህም የባሰ አለና በዚህ ይብቃ? ” ወይም “ለበጎ ነዉ!” ከሚል መጪዉን አደጋ እያሻገሩ እያዩ ከአሁኑ የሚሰጉ በመሆናቸዉ እንጂ ቀዉሱ ያስከተለዉ ጉዳት ስለአልተሰማቸዉ አይደለም፡፡ እነዚህ ወገኖች አደጋዉን ትክክለኛ ገጽታ ለመደበቅ የሚፈልጉበት አንዱ ምክንያት ለጠላት ደካማ ሆኖ መታየት ካለመፈለግ የመነጨና “ለማን ደስ ይበለዉ ብዬ ነዉ” የሚል የሀበሻ ልማድ የታጠሩ በመሆናቸዉ ነዉ፡፡

እነዚህ ወገኖች እንኳን ሌላ ቀዉስ ለወደፊቱ ተከስቶ ቀርቶ አሁንም በደረሰዉ እጅግ የሚንገበገቡና የሚቆጩ ናቸዉ፡፡ ሌላዉ ዓይነተኛ መለያቸዉ መንግስትን ከስልጣን ለማዉረድ ተብሎ አገር መበታተን አለባት ከሚሉት እብዶች ዉጭ መሆናቸዉ ነዉ፡፡ የመንግስትን ጥፋትና ልማት ለማመዛዘን ስለሚችሉ መንግስትን ሲያጠፋ ማረም፤ ጥሩ ሲሰራ ደግሞ ማመስገንና ማበረታተት እንጂ በጭፍን መጥላት አይገባም የሚል አቋም የሚያራምዱ ናቸዉ፡፡ ስለዚህ ገዥዉ ፓርቲ በማንኛዉም ግዜ ህዝብ ካልፈለገዉ ስልጣንን ሊለቅ እንደሚችል መሰረታዊ እምነት ቢኖራቸዉም ነገር ግን ዓይነ-ግቡ የሆነና በተለይ ሀገሪቱን አንድ አድርጎ በማቆየት ረገድ እምነት የሚጣልበት ሌላ ፓርቲ ለጊዜዉ የለም በሚል ጥርጣሬ የገዥዉን ፓርቲ በሌላ መተካት ላይ ምቾት የማይሰማቸዉ ናቸዉ፡፡ “ከነ እንከኑምም ቢሆን ይሄዉ መንግስት ይሻለናል” የሚሉ ናቸዉ፡፡

7/ ከቀዉሱ ምን ተረዳን? ምንስ መማር እንችላለን?

1/ የህዝብ ጥያቄ በአግባቡ ካልተፈታ በቀላሉ ወደማያበራ ከፍተኛ አመጽ(ቀዉስ) ሊገባ እንደሚችልና ያን ተከትሎ ብዙ ጉዳት እንደሚከተል በተግባር የተማርንበት ነዉ፡፡ በተለይም ህዝብ አንዴ ካመረረና ቁጣዉ ከገነፈለ የት ድረስ እንደሚሄድና ምን ማድረግ እንደሚችል ተረድተናል

2/ ህዝብ በልማት ወይም በዳቦ ብቻ እንደማይረካና ከዚያ በላይም ብዙ እንደሚጠብቅ በተለይም የዲሞክራሲ መብትና የመልካም አስተዳዳር ጉድለት በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ያሳየ ነዉ፡፡ በዚህ ምክንያትም ኢህአዴግና መንግስት ከምንግዜም በላይ ራሳቸዉን ለህዝብ ግልጽ አድርገዉ ከዚህ ቀደም ያልተመለሱ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲተጉ ያስገደደ አጋጣሚ ነዉ፡፡

3/ ሙስና፤ የሀገር ሃብትን በግላጭ መዝረፍ እጅግ ስር እየሰደደና መቆጣጠርም የማይቻልበት ደረጃ በመደረሱ ለወደፊቱ የአገሪቱን ለመበታተን ዋነኛ ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል ጠንካራ ስጋት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ከዚሁ ጋር አብሮ በስልጣን ላይ ያለዉ ገዥ ፓርቲ ሙስናን ሊያጠፋ አይችልም የሚለዉ የቆየ ግምት ትክክል ወይም የተሳሳተ መሆኑን ማረጋጋጫ ትክክለኛዉ ወቅት አሁን ነዉ የሚል አምነት አሳድሮአል፡፡

4/ በሀገሪቱ ተአማምነት ያለዉ ነጻነት ተሰምቶት የሚሰራ የግል ሚዲያ አለመኖር ሀገሪቱንም መንግስትንም በእኩል ደረጃ የጎዳና በተለይም ሙሰናና ብልሹ አሰራርን በማጋለጥ ረገድ ሊያግዘን እየቻለ በአግባቡ ያልተጠቀምንበት ስለሆነ መንግስት በዚህ ረገድ መሰረታዊ ለዉጥ ማምጣት እንዳለበት ያመላከተ ነዉ፡፡ በተጨማሪ አፍራሽ ዓላማ ያላቸዉ የዉጭ ሚዲያዎች የሚያደርሱትን ጥፋት መቀነስ የሚቻለዉም ህዝቡ አመራጭ አገር በቀል የመረጃ ምንጭ ሲኖረዉ ብቻ እንደሆነ በተግባር የተረዳንበት አጋጣሚ ነዉ፡፡

5/ አንዳንድ ኢትዮጵያዉያን ዲያስፖራዎችና የኢትዮጵያዊነት ካባ ደርበዉ በእኛ ስም የተደራጁ ኃይሎች ስልጣን ለመያዝ አስፈላጊ መስሎ ከታያቸዉ ከለየላቸዉ የህዝብና የሀገር ጠላቶች ጋር ሳይቀር አብረዉ አስከ መቆም ድረስ ሊሄዱ እንደሚችሉ በተግባር ያረጋገጥንበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ለምሳሌ ትላንት አገር ለመምራት ለስልጣን ሲወዳደር የነበረዉ ግንቦት- 7 የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላት ከሆነዉ ሻእቢያ ጋር አብሮ መስራቱ ግራ አጋብቶን እያለ ጭራሽ ከነጃዋር ጋር መዶለት መጀመራቸዉ ለዚህ አባባል አንድ ማረጋጋጫ ነዉ፡፡

6/ በህዝብ ትከሻ ላይ ተቀምጠዉ ሲመዘምዙትና መልካም አስተዳደር በመንፈግ ሲያስቸግሩ የነበሩ ጥቂት ባለስልጣናትን ለመንቀልና ለፍርድ እንዲቀርቡ ለማድረግ ያስቻለ መልካም አጋጣሚ መሆኑ፤

7/ ሰፊ አካባቢን የሚያካልል አገር አቀፍ ቁዉስና ሁከት ሲፈጠር ጸጥታ የማስከበር አቅማችን ምን ያህል እንደሆነ ራሳችንን እንድንፈትሽ ያስቻለንና ለወደፊቱም በዚህ ረገድ ማስተካከል ያለብንን ያመላከተ አጋጣሚ መሆኑ ፡ በተለይም መከላኬ ሰራዊታችንን በህግ ማስከበር ተግባር ላይ ሊኖረዉ ስለሚገባ ሚና አግባብነት ጉዳይ በሚገባ ሊፈተሸ እንደሚገባ ያሳየ ነዉ፡፡

8/ ገዢዉ ፓርቲ የድሮዉ ደረቅ አቋሙ ከዚህ በኋላ ብዙም እንደማያዋጣዉ ተረድቶ ህገ መንግስቱን አስከ መፈተሸ ድረስ የሚደርስ እርምጃ ለመዉሰድ ፈቃደኝነቱን እንዲገልጽ ያስገደደዉ መሆኑ ፤

9/ ለወትሮዉ ኢህአዴግን በመጥላትና በመፍራት በሩቁ ሲሸሹት የነበሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ኢህአዴግ ከሰሞኑ እያሳያቸዉ ያለዉ አዲስ አቀራረብ ብርታት ስለሆናቸዉ በመጨዉ የሀገሪቱ ምርጫ ተስፋ እንዲያደርጉ አደርጎአቸዋል፡፡

10/ ቀድሞዉኑ ቁርጠኝነት እንዳልነበራቸዉ የሚታወቁ አንዳንድ የገዢዉ ፓርቲ አባላት ከድርጅቱና ከቆሙለት ህዝብን የማገልገል ዓላማ ይልቅ ለግል ጥቅማቸዉ የሚጨነቁ መሆናቸዉን በድጋሚ በሚያረጋግጥ ሁኔታ ፓርቲዉ በጀመረዉ ጥልቅ መታደስ ላይ ህዝቡ አመኔታ እንዲኖረዉ በማድረግ ድርጅታቸዉንና መንግስትን ከማገዝ ይልቅ የወደፊቱን የግል እጣ ፋንታቸዉን ማመቻቸት ላይ መጠመዳቸዉ እጅግ አስተዛዛቢ ነዉ፡፡

11/ ኢህአዴግ በቅርብ በታየዉ ቀዉስ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ከገጠሙት ቀዉሶች ሁሉ በከፋ ሁኔታ ለአደጋ ተጋልጦ የነበረ ቢሆንም እንደገዥ ፓርቲ አሁንም ከነጥንካሬዉ የሚገኝና መቼም ቢሆን በቀላሉ እንደማይፈረካከስ ለጠላቱም ለወዳጁም ያረጋገጠበት አጋጣሚ ነዉ ማለት ይቻላል፡፡ ሆኖም ህዝባዊ አመኔታዉ ሁንም ሳይሸረሸር ልክ አንደ ድሮዉ ነዉ ለማለት የሚያስችለኝ መነሻ የለኝም ፡፡ ሰለዚህ ድርጅቱም ሆነ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ቢያስጠኛ ለራሱ ይበጀዋል በረየ አስባለሁ፡፡

ማጠቃለያ

በሀገራችን የደረሰዉ ቀዉስ ዋነኛ መነሾ ምክንያት እኛ ደረስንበትም አልደረስንበትም ወይም እዉነቱን ደበቅንም አልደበቅንም ቀዉሱ ያለ አንዳች ምክንያት በራሱ ግዜ የተፈጠረ አይደለም፡፡ ለዚህ ችግርም የተዳረግንበትን ትክክለኛ ምክንያት መገመት ካልቻልን ለወደፊቱም በድጋሚ እንዳይከሰት ሁነኛ መፍትሄ ማስቀመጥ አንችልም፡፡ የችግሩ መንስኤ ምክንያት ላይ የጋራ መግባባት ከለለን ከችግሩ ጋር ተመጣጣንኝ የሆነ ተግባራዊ ምላሽ ወይም መፍትሄ ማስቀመጥ ይቸግረናል፡፡

በሀገራችን ተከስቶ የነበረዉ ችግር የአንድ ድርጅት ወይም በስልጣን ላይ ያለ መንግስት ወይንም የአንድ ክልል ችግር ሳይሆን የሁላችንም የጋራ ችግር ነዉ፡፡ ለችግሩ የተዳረግነዉ በሁላችንም ድክመት እንጂ በፓርቲ፤ ወይም በመንግስት ድክመት ብቻ አይደለም፡፡ በሻእቢያ፤ ኦነግ፣ ግንቦት 7፣ ጃዋር፣ ብርሃኑ ነጋ፣ ወዘተ ቀዉሱን በማቀጣጠልና በአንድነት እንዳንቆም እኛን በመከፋፋል የተጫወቱት አፍራሽ ሚና ከፍተኛ እንደነበር ባይካድም ነገር ግን ለነሱ ሴራ ተጋላጭ የሆነዉ በራሳችን ድክመት መሆኑን አምነን መቀበል ይገባናል፡፡ መንግስትም በቀጥታ ራሱ የችግሩ ፈጣሪ ባይሆንም ነገር ግን ለቀዉስ ምቹና የተደላደለ ሁኔታ እንዳይኖር ማድረግ ባለመቻሉ ለደረሰዉ ችግር የሱም የጎላ ድርሻ እንዳለበት ስህተቱን አምኖ ሊቀበል ይገባል፡፡ በተለይም በተደጋገሚ እንደተገለጸዉ በህዝቡ ላይ ሲቀልዱ የነበሩ ጥቂት የማይባሉ ባለስልጣናቱን ማስታገስ ባለመቻሉና ራሱም ገዥዉ ፓርቲም ድሮ በእጅጉ የሚኩራራበት ህዝባዊ ባህሪይዉ እየተሸረሸረ በመሄዱ ህዝብን ማዕከል ካደረገ ልማት ይልቅ ግለሰቦችን ማበልጸግ ላይ ያተኮረ ፖሊሲ የሚከተል እስኪመስል ድረስ ህዝቡን በልማት ዉጥኖቹ ላይ ማማከር ትቶ በኃይል ለማስፈጸም በመፈለጉ የተፈጠረ ችግር ነዉ፡፡

ስለዚህ መንግስት እንደ መንግስት ለችግሩ ተጠያቂነት በአንደኛ ደረጃ ብናስቀመጥም ነገር ግን አንዳችንም ብንሆን ከተጠያቂነት አናመልጥም ፡፡ ምክንያቱም የመታገል ወኔያችን በመሞቱ ምክንያት መንግስት ሲያጠፋ እየገሰጽን ልናስተካከለዉ ባለመሞከራችንና ከዚያም በላይ ደግሞ መንግስትን የጎዳን እየመሰለን ለጠላቶቻቸን መሰሪ ቅስቄሳ ተታለን ለጥፋት ዓላማቸዉ ተባባሪ በመሆናችን ነዉ፡፡ ጠላቶቻችን ሀገራችንን ሊያፈራርሱብን ሲዶልቱ እየሰማን ከጥፋት ለመታደግ ኢህአዴግ አስኪነግረን መጠበቃችን አስተዛዛቢ ነዉ፡፡ በሁላችንም ላይ የተቃጣ ጥቃት መኖሩን እንዳወቅን ከአደጋዉ ለማምለጥ ማንም ነጋሪ ሳያስፈልገን እኛዉ ራሳችን መንቀሳቀስ የነበረብን ቢሆንም ነገር ግን በሚያልፍ ጊዜያዊ ችግር ተበሳጭተን ሳናመዛዝን በጀብደኝነት ራሳችን በራሳችን ላይ ዘመትን፡፡ ያ የምንታወቅበት በችግር ግዜ በአንድነት የመቆም አኩሪ ታሪካችንም በነጃዋርና ሻዕቢያ መናኛ ቅስቄሳ ጎደፈ፡፡

ቀዉሱን ለማባበስ የዉጭ ኃይሎች ጉልበት ያገኙትና በጥፋት ተግባራቸዉ የተበረታቱት እኛ እርስበርስ መደማመጥ ስላቆምንና ደካማ ሆነን ስለተገኘንላቸዉ ነዉ፡፡ የእነ ኦነግንና ሻእቢያ ሴራ ዓላማዉ በሀገራችን ሉአላዊነት ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ በሚገባ እያወቅን ተላላኪዎቻቸዉን አሳፍረን መመለስ እየቻልን ታዘዝናቸዉ፡፡ በዚህ ምክንያትም በሀገራችን ዉስጥ ለተከሰተዉ ቀዉስ ሃላፊነኑን ተቀብለን በጋራ መቆም ይገባናል፡፡ ስለዚህ አገራችን እንደ ሶሪያና ሊቢያ ሆና ማየት ለሚመኙ የጥፋት ኃይሎች ሴራ ሳንንበረከክ በአንድነታችን በጽናት ልንቆም ይገባል፡፡

በዚህ አጋጣሚ መግለጽ ያለብኝ በአገራችን በተከስቶ በነበረዉ የጸጥታ ችግር ሁከቱን በመቆጣጠር ወደ ነባሩ ሰላማችን በመመለስ ረገድ የጸጥታ ኃይሎች መንግስትና የህዝብ ትብብር መኖር እጅግ ወሳኝ እንደ ነበር አይተናል፡፡ እንደ ተከሰተዉ ቀዉስ ክብደት ቢሆን ኖሮ ሊደርስ ይችል የነበረን ጉዳት በእጅጉ ለመቀነስ በመቻሉ መንግስት ሊመሰገን ይገባል፡፡ በተለይም የጸጥታ ኃይሎች በዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ያደረጉት ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ በእጅጉ ያስመሰግናቸዋል፡፡ መላዉ የኢትዮጵያ ህዝቦች ከጸጥታ ኃይሎችና ከመንግስት ጎን ሳይለዩ ላደረጉት ትብብርና ላሳዩት ትዕግስት አክብሮቴም ከፍተኛ ነዉ ፡፡ የህዝቡ ትብብር ባይኖር ኖሮ እንዲህ በአጭር ግዜ ከቀዉሱ መዉጣት አንችልም ነበር፡፡ ይህ የህዝብና የመንግስት የአንድነት መንፈስ ለወደፊቱም ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባዉ ነዉ፡፡ በተረፈ ፡አሁን በጀመርነዉ ጥልቅ መታደስም የሚፈለገዉ ዉጤት ሊመጣ የሚችለዉ የሁላችንም ተሳትፎ ሲኖር ብቻ መሆኑን አዉቀን ከመንግስት ጎን ቆመን ልናግዘዉ ይገባል፡፡

*********

የኮ/አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሌሎች ጽሑፎች ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፡፡

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories