ዶናልድ ትራምፕ – ፍርሃት የወለደው መሪ!

አንድ ጓደኛዬ ከአዲስ አበባ በአግራሞት ተውጦ ደወለልኝና እንዲህ አለኝ፡ “ኧረ ጉድ…ሰውዬው አበደልህ!”። እኔም በሁኔታው ግራ ተጋብቼ “ማነው?…ምንድነው?” በማለት ጠየቅኩት። “ዶናልድ ትራምፕ ነዋ! “ቶርቸር” እንዲደርግ ፈቅጄያለሁ ብሎ አረፈው እኮ!” አለኝና መሳቅ ጀመረ። ባለፈው ዓመት “ከጓንታናሞ እስከ ማዕከላዊ” በሚል መሪ ርዕስ ባወጣኋቸው ተከታታይ ፅሁፎች ውስጥ ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕረዜዳንት የሥቃይ ምርመራን በማስቆሙና የጓንታናሞ አስር ቤትን በመዝጋት ሀገሪቱ ወደ ቀልቧ መልሷታል ስል ነበር። ታዲያ ጓደኛዬም ይህን ስለሚያውቅ ነው በጥድፊያ የደወለልኝ። በእርግጥ አሜሪካን እንደ ተምሳሌት እየጠቀስኩ፣ በኢትዮጲያም እንደ ማዕከላዊ ባሉ እስር ቤቶች የሚካሄደው የስቃይ ምርመራ (torture interrogation) ሊቆም ይገባል እያልኩ ስከራከር፣ ራሷ መልሳ መፍቀዷ በጣም አስደንጋጭ ነው።

አብዛኛው ሰው የስቃይ ምርመራን የሚቃወመው ከተጠርጣሪ እስረኞች መብት አንፃር ነው። ለእኔ ግን የስቃይ ምርመራ የፍርሃት ውጤት ነው። በእርግጥ በዓለም-አቀፉ የፀረ-ሽብር ጦርነት ወቅት የአሜሪካ መንግስት ከተለያዩ የዓለም ሀገራት በቁጥጥር ስር ባዋላቸው ሰዎች ላይ እንደ ጓንታናሞ ባሉ እስር ቤቶች የስቃይ ምርመራ አድርጓል። ይህ የሆነው ግን አብዛኞቹ የአሜሪካ ባለስልጣናት በወቅቱ በፍርሃት ውስጥ ስለነበሩ ነው። አሁንም ቢሆን አብዛኞቹ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች፥ መራጮች የፍርሃት ቆፈን የቀፈደዳቸው ናቸው። አዲሱ ፕረዜዳንትም ይህን በአብዛኛው አሜሪካዊ ዘንድ የተዳፈነውን ፍርሃትና ስጋት እየቆሰቆሱና እያመሱ ነው ወደ መሪነት የመጡት።ይህን የፍርሃት ቆፈን በልበ-ሙሉነት የተጋፈጠ የአንድ ባለስልጣንን አባባል መነሻ በማድረግ ሃሳቤን በዝርዝር ለማስረዳት እሞክራለሁ።

ለፍርሃት ቆፈን እጁን ያልሰጠው አሜሪካዊ ባለስልጣን በወቅቱ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ የኮንዶሊዛ ራይስ አማካሪ የነበረው “Philip D. Zelikow” ነው። በአልቃይዳ ተጠርጣሪ እስረኞች ላይ የስቃይ ምርመራ አንዲፈፀም የሚፈቅደውን የፕ/ት ጆርጅ ቡሹ መመሪያ “ከሞራል፣ ሕግና ከፖሊሲ አንፃር ስህተት ነው” በማለት በግልፅ ለመቃወም የደፈረ ብቸኛ ባለስልጣን ነው። ይህ ባለስልጣን በወቅቱ በአሜሪካ ላይ አጥልቶ የነበረውን የፍርሃት ድባብ አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት እንዲህ ብሎ ነበር፡- “Fear and anxiety were exploited by zealots and fools”።

ከላይ የተጠቀሰችው አባባል መሬት ጠብ የሚል ነገር የላትም። የቀድሞ የአሜሪካ ፕረዜዳንት የጆርጅ ቡሽን እና የዶናልድ ትራፕን ስራና ባህሪ በደንብ ትገልፃለች። ፕ/ት ጆርጅ ቡሽ በጣም “ሞኝ” (fool) የሚባሉ ዓይነት ሲሆኑ ዶናልድ ትራም ደግሞ የለየለት የፖለቲካ ስግብግብ (zealot) ነው። የጆርጅ ቡሽ ሞኝነት በዋናነት ለአልቃይዳ የሽብር ጥቃት አፀፋ ለመስጠት በሚል፤ የራሳቸው የሆነ ሉዓላዊ ሀገር ከሌላቸው፣ የሚከላከሉት ዳር-ድንበር ከሌላቸው የሽብር ቡድኖች ጋር ጦርነት መግጠማቸው ነው። ሌላው ደግሞ ያለ በቂ ምክንያትና ማስረጃ ኢራቅን በመውረር ከአልቃይዳ የባሱ እንደ ”Islamic State in Iraq and Syria- ISIS” ያሉ የሽብር ቡድኖችን መፍጠራቸው ነው። ሞኙ ፕ/ት ቡሽ ያወጁት የፀረ-ሽብር ጦርነት የአሸባሪዎች ዓላማና ግብ ማስፈፀሚያ እንደሆነ ዛሬ ላይ ከናጄሪያ እስከ አፍጋኒስታን፣ ከሶሪያ እስከ ሶማሊያ ድረስ እየተፈለፈሉ ያሉትን የሽብር ቡድኖች ማየት በቂ ነው።

የቀድሞዋ እንግሊዝ የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት (MI5) ዳይሬክተር “Eliza Manningham Buller” እንግሊዝ ከአሜሪካን ጋር በመሆን ኢራቅን በመውረሯ ምክንያት በሀገሪቱ ላይ የሚጠነሰሰው የሽብር ጥቃት እጅግ በብዙ እጥፍ እንደ ጨመረ ትናገራለች። እንደ ዳይሬክተሯ አገላለፅ፣ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል የሚያውቀው በተግባር የተፈፀሙትን የሽብር ጥቃቶችን ነው። ነገር ግን፣ እንግሊዝ ውስጥ በአሸባሪዎች ሊፈፀሙ ታቅደው የነበሩና በድህንነት መስሪያ ቤቱ የከሸፉ የሽብር ሲራዎች በጣም ብዙና ሊያደርሱት ይችሉት የነበረው ጥፋት እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ትጠቅሳለች። እነዚህ የሽብር ሴራዎች የሚጠነሰሱት ግን እንደቀድሞ ከአርብ ሀገር በመጡ አሸባሪዎች ብቻ ሳይሆን በራሷ በእንግሊዝ ዜጎች ጭምር ነው።

በአሜሪካ መሪነት የተጀመረውን ዓለም-አቀፉ የፀረ-ሽብር ጦርነትን (global war on terror) ተከትሎ መላው አውሮፓና አሜሪካን ይበልጥ ለሽብርተኝነትና አክራሪነት አጋልጧቸዋል። ከሰሜን አፍሪካ ጀምሮ በመካከለኛው ምስራቅ ከሚደርሱት የሽብር ጥቃቶች በተጨማሪ፣ እንደ አንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ስፔንና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት እየደረሱ ያሉት የሽብር ጥቃቶች “ዓለም-አቀፉ የፀረ-ሽብር ጦርነት” የሚባለው የሞኞች ሥራ ውጤት ነው። ይህ ደግሞ በአብዛኞቹ የአውሮፓና አሜሪካ ሀገራት ላይ የፍርሃት ድባብ እንዲሰፍን ምክንያት ሆኗል። የፍርሃት ድባብ ደግሞ ለአክራሪና ዘረኛ የሆኑ ኣላዋቂና ስግብግብ ሰዎች ወደ መሪነት እንዲመጡ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል።

የፍርሃት ድባብ (climate of fear) በሰፈነበት ሀገር ውስጥ ፖለቲካው ብቻ ሣይሆን የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ጭምር የፍርሃት ቆፈን ይይዘዋል። የዜጎች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በፍርሃትና ስጋት የሚመራ ሲሆን ግን ደፋር መሳይ ስግብግብ መሪዎች ወደ ፖለቲካው ብቅ ይላሉ። ፍርሃትና ስጋት በዋጣቸው ደጋፊዎቻቸው ፊት ደፋርና ቆራጥ መስለው በመታየት፣ በውስጣቸው የተዳፈነውን ብሔራዊ ስሜት እየቆሰቆሱና በሀገራቸው ለሚታዩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በሙሉ ሌሎችን ተጠያቂና ጥፋተኛ እያደረጉ፣ በምርጫ ቅስቀሳ ስም ዘረኝነትና ጥላቻን እየሰበኩ ወደ መሪነት ይመጣሉ።

ነፃነት በሰፈነበት፣ ግልፅ ተናጋሪና ብልህ የፖለቲካ ልሂቃንና መሪዎች ያሉበት ሀገር ግን ለአምባገነኖች ምቹ አይደልም። እንደ ዶናልድ ትራፕ ያሉ አምባገነኖች የሚበቅሉት የፍርሃት ድባብ በሰፈነበት ሀገር ውስጥ ነው። ምክንያቱም፣ እነሱ ወደ መሪነት የሚመጡት የሞኞችን ደካማነትና ስህተት፣ በሕዝቡ ዘንድ የሰፈነውን ፍርሃትና መከፋት ለራሳቸው የስልጣን ጥማት በመጠቀም ነው። ለዚህ ደግሞ በውሸት የሚያሞኙት፣ በፍርሃት የሚያስፈራሩት ብዛት ያለው ደጋፊ ያስፈላጋቸዋል። በዚህ መልኩ ወደ ስልጣን ከመጡት ውስጥ ከመንግስቱ ኃይለማሪያም እስከ ሞሶሎኒ፣ ከሂትለር እስከ ዶናልድ ትራፕ መጥቀስ ይቻላል።

አንዳንዶቻችሁ “ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን የመጣው የነፃነትና ዴሞክራሲ ተምሳሌት በሆነችው አሜሪካ፣ ፕ/ት ባራክ ኦባማን በመሰለ ግልፅ ተናጋሪና ብልህ መሪ እየተመራች እኮ ነው?” የሚል ጥያቄ እንደምታነሱ እገምታለሁ። በእርግጥ ፕ/ት ባራክ ኦባማ ከፕ/ት ጆርጅ ቡሽ የተረከበው በፋይንስ ቀውስ (financial crisis) እየተናጠ ያለ ኢኮኖሚ እና በዓለም-አቀፉ የፀረ-ሽብር ጦርነት እየታመሰ ያለ ፖለቲካ ነበረ። አሜሪካ በተለይ ደግሞ እንደ ጓናታናሞ እና አቡ-ግሬብ ባሉ እስር ቤቶች በፈጸመችው ተግባር እንደ ሀገር የተመሰረተችባቸውን የነፃነትና ዴሞክራሲ እሴቶች በመጣሷ ምክንያት በአለም-አቀፉ ማህብረሰብ ዘንድ የነበራትን የሞራል የበላይነት ተገፍፋ ነበር። ስለዚህ ባራክ ኦባማ የስልጣን ዘመኑን ፈጀው የጆርጅ ቡሽ አስተዳደር የፈፀማቸውን ስህተቶች በማረም ነው ማለት ይቻላል።

ፕ/ት ባራክ ኦባማ በፋይናንስ ቀውስ ሲናጥ የነበረውን የአሜሪካን ኢኮኖሚ እንዲያገግም አድርጓል። በዚህ ረገድ፣ ወደ ስልጣን ሲመጣ የነበረውን ከፍተኛ የሥራ-አጦች ቁጥር ወደ የምንግዜውም ዝቅተኛ ደረጃ ማድረሱ የሚጠቀስ ነው። የስቃይ ምርመራ እንዲቆምና ይህ ተግባር ሲፈፀምባቸው የነበሩትን እንደ ጓንታናሞ ያሉ እስር ቤቶች እንዲዘጉ በመወሰን፣ እንዲሁም ባለው መልካም የግል ስብዕና አሜሪካ በዓለም-አቀፉ ማህብረሰብ ዘንድ አጥታ የነበረውን የሞራል የበላይነት መልሳ እንድታገኝ ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጓል። ይሁን እንጂ፣ የኦባማ ስኬት ለአብዛኞቹ የዶናልድ ትራፕ ደጋፊዎችና መራጮች ዘንድ የፈጠረው የኩራት ስሜት ሳይሆን ፍርሃትና ስጋት ነበር።

በቃ…አሜሪካ ገና ከአመሰራረቷ ጀምሮ እንዲህ ነች – የነፃነት እና ፍርሃት ጥምር ውጤት ናት። ለአንደኛው አሜሪካዊ ነፃነትና እኩልነት ሲረጋገጥ ለሌላኛው አሜሪካዊ ደግሞ ፍርሃትና ስጋት ይፈጥራል። የጥቁር አሜሪካዊያን መብትና ነፃነት ለማረጋገጥ ሁለት ክፍለ ዘመን ከፈጀባት በኋላ፣ በግማሽ ክፍለ ዘመን ውስጥ ጥቁር ፕረዜዳንት ትመርጣለች። አሁን ደግሞ ጥቁር ፕረዜዳንት በመረጠች ማግስት በዘረኝነት የናወዘ ፕረዜዳንት መርጣ እያስደመመች ነው። አሜሪካ የነፃነትና ፍርሃት ጥምር ውጤት መሆኗን በግልፅ ለመረዳት ከአመሰራረቷ ጀምሮ ማየት ያስፈልጋል።

አሜሪካ ገና እንደ ሀገር ስትመሰረት ያፀደቀችውን ሕገ-መንግስት ብንመለከት፣ ሁሉም ሰዎች እኩል መብትና ነፃነት እንዳላቸው ከሚደነግጉ አንቀፆች ጎን የባሪያ ንግድንና ጉልበት ብዝበዛን የሚፈቅዱ አንቀፆችን (አንቀፅ 1.2፣ 1.9 እና አንቀፅ 4.2) ተካተው ይገኙ ነበር። እነዚህ አንቀፆች በሕገ-መንግስቱ ውስጥ የገቡበት ዋና ምክንያት በደቡባዊ አሜሪካ የሚገኙ የነጭ አክራሪዎችን በህብረቱ ውስጥ ለማቆየት ሲባል ነበር። ከዚህ በተጨማሪ፣ የሕገ-መንግስቱ አርቃቂዎች በ”James Madison” ተፅፎ የተዘጋጀው ረቂቅ በሚስጥር እንዲያዝና ለቀጣይ 50 ዓመታት እንዳይታተም ስምምነት ነበራቸው። በዚህ ምክንያት ሕገ-መንግስቱ ለህትመት የበቃው እ.አ.አ. በ1840 ዓ.ም ነው። አርቃቂዎቹ ይህን ያደረጉት ዋና ምክንያት በሞት አማካኝነት በብዛት በደቡባዊ አሜሪካ በሚኖሩ የነጭ አክራሪዎች ዘንድ ከተጠያቂነት ለመዳን ነበር

በአሜሪካ ታሪክ የጥቁሮች መብትና እኩልነት ሲረጋገጥ በተለይ በደቡባዊ የአሜሪካ ክፍል የፍርሃት ድባብ ይሰፍናል። እነዚህን እንኳን የባራክ ኦባማ መመረጥ የሕገ-መንግስቱ መፅደቅ ራሱ ለፍርሃት ሲዳርጋቸው የነበሩ ናቸው። ጥቁር አሜሪካዊ ፕረዜዳንት ሆኖ ሲመረጥ በተለይ በዚህ አከባቢ ተዳፍኖ የከረመው የነጮች አክራሪነትና ዘረኝነት ፊት ለፊት አግጥጦ እንዲወጣ አድርጎታል።

በአጠቃላይ፣ አሜሪካ በኢኮኖሚው የነበራትን የበላይነት ከግዜ ወደ ግዜ እየቀነሰ መምጣቱ የፈጠረው ስጋት፣ የዓለም-አቀፉ የፀረ-ሽብር ጦርነት አሜሪካን ይበልጥ የአሸባሪዎች ኢላማ ስላደረጋት፣ እንዲሁም በባራክ ኦባማ ፕረዜዳንትነት ከምስረታዋ ግዜ ጀምሮ በውስጧ ታምቆ የነበረው የነጮች አክራሪነትና ዘረኝነት፣ የሀገሪቱን ፖሊቲካ በፍርሃት ድባብ ውስጥ ከተውታል። ዶናልድ ትራፕ ደግሞ የኢኮኖሚ ችግሩን ከሜክሲኮ በሚመጡ ስደተኞች ላይ በማላከክ፣ የሽብር ስጋቱን ደግሞ በሙስሊም አሜሪካኖች ላይ በመለጠፍ፣ እንዲሁም በኦባማ መመረጥ የፈነዳውን የነጮች አክራሪነትና ዘረኝነት በጥቁር አሜሪካዊያን በማነጣጠር፣ በአብዛኛው መራጭ አሜሪካዊ ልብ ውስጥ የተቀጣጠለውን የፍርሃት ስሜት እየቆሰቆሰና እያነደደ የሀገሪቱ ፕረዜዳንት ለመሆን በቅቷል። ስለዚህ፣ የዶናልድ ትራፕ ፍርሃት የወለደው ስግብግብ መሪ ነው!

**********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories