Jan 30 2017

ጊዜው ያለፈበትና የከሸፈ የትግል ስልት (ታጋይ ካሕሳይ ቃሉ)

(ታጋይ ካሕሳይ ቃሉ)

ከያዝነው ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ በተከታታይ በአቶ እውነቱ ዘለቀ የተባሉ ፀሃፊ (የብአዴን ከፍተኛ አመራር እንደሆኑ እራሳቸው ያስተዋወቁ) በትግራይ ተወላጆችና መሪ ድርጅታቸው ህወሓት ላይ ያነጣጠሩ ፅሁፎች በተለያዩ ድረገፆች አውጥተዋል ብዙ ሰውም እንደሚያነባቸውና የተለያዩ ሃሳብ እንደሚያነሳ የታወቀ ነው፡፡ አንዳንዱ የተለመደ የትምክህት ሃይሎች የፈጠራ ወሬ ነው በማለት ችላ ብሎ የሚያልፈው፤ ሌላው ደግሞ ብአዴን እንደድርጅት ምን ነካው ብሎ የሚጠላ ሌላው ደግሞ ድሮስ ትግራዋይ ብሎ በጭፍን የሚጠላ ሊኖር እንደሚችል የታወቀ ነው፡፡ እነዚህ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች መልስ በመስጠትም የተገለፁ ናቸው፡፡

የሆነው ሆነና አቶ እውነቱ ማብራሪያ እንዲሰጡበትና ማስረጃ እንዲያቀርቡበት የተጠየቁት ጉዳይ ገሸሽ በማለት አሁንም የተለያየ ርዕስ በመስጠት እየፃፉ ነው፡፡ እኔም እንዲቀጥሉበት እላለሁ መጨረሻ መግባባት የሚቻልበትን ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ካልሆነም አንባቢው በራሱ መንገድ ትክክለኛ የቱ እንደሆነ ለመለየት ያስችላል የሚል እምነት ስላለኝና ህወሓትና የትግራይ ህዝብ የተደበቀና ያልተነገረ ሃጥያት የሌላቸው መሆኑ እንዲሁም ለዚች ሀገር ያበረከቱት አስተዋፅኦ በኩራት የሚነገር እንጂ ራስ የሚያስደፋና የሚያሸማቅቅ ታሪክ በፍፁም ሊገኝ እንደማይችል አፌን ሞልቼ በድፍረት መናገር ስለምችል፡፡

አሁንም ለዚች ሀገር ሰላም፣ ልማትና ነፃነት ሲሉ እንደ ሌላው ብሄር ብሄረሰብና ህዝቦች የጎላ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ጀግኖችና መሪዎች ያበረከተ ህዝብ ነው፡፡ እንደውም በአጋጣሚ ሆኖ በዚች አገር ያጋጠሙት ተግዳሮቶች የመጀመሪያ ገፈት ቀማሽ የሆነው ይህ ህዝብ ነው፡፡ ከጣልያን ወረራ፣ በፀረ-ደርግ ጦርነት እንዲሁም በእብሪተኛው የኤርትራ መንግስት የተቃጣብን ወረራ የመከቱት ሁሉም የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከጫፍ እስከ ጫፍ የተሳተፉባቸው ቢሆኑም ጦርነቱ በዚህ አካባቢ የተደረገ በመሆኑ ህፃናትና እንስሳት ሳይቀር የተቸገሩበት ነው፡፡

ለዚህም የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ለሁሉም የአገራችን ህዝቦች ለነበራቸው ተሳትፎ ታላቅ ክብርና ምስጋና አላቸው፡፡ ክብር የሚገባው አስተዋፅኦ እንዳደረጉ እንጂ ለራሳቸው እኛ ብቻ ነን የሰራነው ብለው መናገር ቀርቶ አስበውት አያውቁም፡፡ እዚህ ላይ ግን ከዚህም ከዚያም በግለሰቦች ( የአቶ እውቱ የአማራን ወይም ብአዴን የማይወክሉ አይነት በሌላ አነጋገር የትምክህትና የጠባብ ሃይሎች ሰለባ የሆኑ) ከትግራዋይ የሉም ባይባልም እነዚህን መለየት ያቃተው ወይም ያልፈለገ ሰው በምንም መለኪያ የዲሞክራሲያዊ ብሄርተኛ ሃይል ሊሆን አይችልም፡፡ አቶ እውነቱም ቢሆኑ በህወሓትና በትግራይ ህዝብ ያለው ቁርኝት በአግባቡ ያልለዩ በግለሰቦችና በህዝብ መካከል ያለው ልዩነትም ለማየት ያልፈቀዱ (የትግራይ ተወላጆችና መሰሎቻቸው እያሉ የሚደፈጥጡ) በምንም መለኪያ የዲሞክራሲያዊ ብሄረተኛ ባህሪ ሊኖራቸው አይችልም አላቸው ብሎ የሚመሰክር ቢኖር “የአይጥ ምስክር ድንቢጥ” ነው የሚሆነው፡፡

በቅርቡ አቶ እውነቱ “ሀሳብ የሚያጥረው ሰው የግለሰቦችን ስም በማጠልሸት ጊዜውን ይገፋል”[PDF] በሚል ርዕስ በዓይጋ ፎረም ለንባብ አቅርበዋል፡፡ በዚህ ፅሁፋቸውም በድረ-ገፆ ሃሳባችን የገለፅን ሶስት ሰዎች ስም በመጥቀስና አንድ ላይ በመፈረጅ (ምናልባትም የትግራይ ተወላጆች ናቸው በሚል ይመስለኛል) ያላቸውን ተቃውሞና  የተለመደው ወቀሳቸውን አቅርበዋል፡፡

ስለ አቆ ታዛቢና አቶ ቀለሙ ያሉት ነገር እኔ ጠበቃ በመሆን መልስ ልሰጣቸው ሃሳቡ የለኝም ምክንያቱም ግለሰቦቹ ለምን እንደዛ እንዳሉ ራሳቸው መመለስ የሚያስችል አንደበት ያላቸው ስለሆኑ አቶ እውነቱ እንዳሉትም (ራሳቸው ተግባራዊ ባያደርጉትም የአቶ ገዱና አቶ ሲሳይን ጠበቃ ሆነው ስለሆነ መልስ እየሰጡ ያሉት) መመለስ አልፈልግም ግለሰቦቹ መልስ መስጠት ይችላሉ ብየም ስለማስብ፡፡

በሌላ በኩል እኔ (ታጋይ ካሕሳይ ቃሉ) የፃፍኩትን የጠባቦች፣ የትምክህትና የዲሞክራሲያዊ ብሄርተኛ ሃይሎች ባህሪ በተመለከተ አቶ እውነቱ ስለተስማሙበት ሳላመሰግንዎ አላልፍም፡፡ ምክንያቱም ለወደፊት ለምናደርጋቸው ክርክር መነሻ ስለሚሆን፡፡

እስከአሁን በተመላለስነው ከአቶ እውነቱ የተማርኩት ነገር ቢኖር ልክ በቀደመው ፅሁፍ እንዳስቀመጥኩት የትምክህትና የጠባብ ሃይሎች ባህሪ አብዛኛው ያነሱትና እኔም በይበልጥ እንዲያብራሩትና በማስረጃ እንዲያስደግፉት በጠየቅኳቸው ጉዳዮች ላይ አድበስብሰው ወይም እኔን መልሰው በመጠየቅ ሊያልፏቸው ነው የሞከሩት፡፡ ይህ ደግሞ ጠንካራ አቋምና ማስረጃ ሳይኖራቸው በተደጋጋሚ ስለተባለ ብቻ በስሜት በትግራይ ህዝብና በመሪ ድርጅቱ ህወሓት ያወረዱት ናዳ መሆኑ ገብቶኛል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እርስዎ ለዓመታት በአቋም የያዙት እና እንደእርስዎ የመሰሉ ሰዎች የሚሉት “የትግራይ የበላይነት” በሚል በመሬት ላይ ሳይሆን ስልጣን በተነጠቁት ፀረ-ህዝብ ሃይሎች ጭንቅላት ላይ ያለው የመንፈስ ቃል (Magic Word) ለመነጋገር መረጥኩ፡፡

አቶ እውነቱ በአሁኑ ፅሁፋቸው እንዲያብራሩ የተጠየቁት ጉዳዮች በተለይ ህዝብን የሚያጥላሉ ውንጀላቸው ምንም ሳይሉ ማለፋቸው አሁንም ወሬና አሉባልታ እንጂ ምንም የእውነት ሽታ የሌላቸው መሆኑ ተረድቻለሁኝ:: በተወሰነ መልኩ የነካኩዋቸውም ቢሆን ትንሽ ቀዳዳ ያገኙ ስለመሰላቸው የኢህአፓ ያለመጋበዝ በተመለከተ እኔን ተመልሰው አንተም እኮ ማስረጃ አላቀረብክም በማለት ብልጥ ለመሆን ሞከሩ ከዛ አልፈውም “በ1983 ዓ/ም እኔ (አቶ እውነቱ) ባለኝ መረጃ መሰረት አጠቃላይ ለተቃዋሚዎች የተሳተፉ ጥሪ ተላልፎ የነበረ መሆኑ ቢታወቅም ኢህአፓ እንደ ድርጅት ግን በኢህአደግ ዘንድ ፍላጎት አልነበረም” ይሉናል ከጅምሩ ስለፍላጎት ቢያወሩ እኔም አልቃወምም ምክንያቱ እንደፍላጎት ቢሆንማ በወቅቱ ከኢህአደግ የተለየ አቋም የነበራቸው እነ ኢድዩ ኦነግ ኢህአደግ ይወዳቸው ነበር እንዳይሉኝ ስለሆነም ኢህአፓ ባይሳተፍና በቁም ቢሞት አይጠላም ግን ይህ ከፍላጎት አልፎ ኢህአደግ በተግባር ሊያውለው ስልጣኑም ፍላጎቱም ስላልነበረው አላደረገውም ሁሉም የታጠቁም ይሁን ያልታጠቁ ፖለቲካ ድርጅቶች ቅድሚያ ተኩስ ማቆምና በአደባባይ ማወጅ እንደሚገባ ሁሉም ሲስማሙ ኢህአፓ አልተስማም ተኩስ አቁሜ አለሁ አላለም:: ተኩስ ያላቆመና የታጠቀ ሃይል ታድያ ለምን ተብሎ ነው ኮንፈረንስ የሚሳተፈው? ለነገሩ ራሱም መሳተፍ አለብኝ ብሎ አላቀረበም:: ስለሆነም የኔ ማስረጃ ራስዎ ያሉት አጠቃላይ ለተቃዋሚዎች የተሳተፉ ጥሪ እንደተላለፈ አውቃለሁ ስላሉ ኢህአፓ በተለየ እንዴት መጋበዝ እንደረበት ባይገባኝም ማስረጃየ እሱ ነው::

ሌላው ወደ ዋናው ጉዳየ ልግባና ለመሆኑ አቶ እውነቱ በ1993 የትግራይ የበላይነት እንዳለ ተቀብላችኋል ብለዋል ይህ ለኔ በ1983 ኢህአፓ አልተጋበዘም ያሉት አይነት ተጨማሪ ውሸት በመሆኑና የነበረው ግምገማና አካሄድ በርካታ ሰው ስለሚያውቀው እንደ መከራከሪያ ማንሳት ግዜ ማጥፋት ነው:: የበላይነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ በተጨባጭ ባለንበት ዘመን በአገራችን የአንድ ብሄር የበላይነት ማስተናገድ እንዴት እንደማይቻል ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡

ይህን ስል ግን ትግራዋይነት የተፈጠርኩበት ማንነቴ ህወሓት/ኢህአዴግ ያደኩበትና ከልጅነቴ ጀምሮ የታገልኩለትና ከልቤ የምደግፈው አላማዎች ያነገበ ድርጅት በመሆኑ የምኮራበትና ትክክል የሆነውን በማመንና በተግባርም የማየው እውነት ለመመስከር እንጂ እንደ አቶ እውነቱ ሁሉን የሚያውቅ በአመራርና በየትኛውም ተቋም ሆኜ እየተናገርኩ አለመሆኑን እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡

አቶ እውነቱ ቀና አስተሳሰብና ነገሮችን ከነባራዊ ሁኔታቸው ጋር አገናዝቦ ለሚያስብ ሰው ከእንደ እርስዎ ያለ የብአዴን ከፍተኛ አመራር የብአዴንና የህወሓት አመጣጥና ታሪክ በሚገባ አውቃለሁ የሚል ሰው እንደዚህ አይነት መሰረት የሌለው አቋም ሲያዝ ገና አሁን ከእርስዎ የሰማሁት ስላልሆነና ብዙ ሰዎች አንዳንዱ እንደ እርስዎ አይነት አመራር ነን ከሚሉ ሰምተው እንደ እርስዎ ደግሞ እያደር የሚመረቅዝ የኢህአፓ ቅሪትና የተበታተነ ሃሳብ ይዞ በአቅሙና በችሎታው ተማምኖ የማይኖር ግን የተሻለ ቦታ ሲፈልግ ብሄርን እንደመሸሸጊያ ተጠቅሞ የሚያነሳው ሃሳብ መሆኑ ስለማውቅ ቢገርመኝ እንጂ አያስደነግጠኝም፡፡

የሆነ ሆኖ የአንድ ብሄር የበላይነት ምን ማለት ነው? መገለጫውስ ምንድነው? እኔ እስከማውቀው ድረስ የአንድ ብሄር የበላይነት ማለት በስልጣንና በሀብት ክፍፍል የሚታይ የአንድን ብሄር (ህዝብ ባይሆንም ገዥ መደቦች) ሰዎች የብሄሩ ተወላጆች በመሆናቸው ብቻ የሚሾሙበትና የሚወደሱበት በአንፃሩ የሌላ ብሄር ተወላጆች ከተቀደሰው ብሄር ባለመሆናቸው የሚሸማቀቁበትና አድልዎ የሚፈፀምባቸው በሀብት ክፍፍል ሰፊው ህዝብ ተጠቃሚ ባይሆንም የብሄሩ ተወላጆች እንደፈለጉ የሚያደርጉበት በአጠቃላይ የበላይነት ያለው ብሄር ካልሆነ የሌላው ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ባህልና አኗኗር የሚንቋሸሹበት ዘርፈ ብዙ የአድልዎ አካሄድ ያለው ማለት እንደሆነ ነው የሚገባኝ ከዚህ ውጭ የመወዳደሪያው ሜዳ ለሁሉም በመክፈት የተሻለ አቅምና ብቃት ያለው ከማንምና ከየትኛውም ብሄር ይምጣ ስልጣን እንዲይዝ ከተደረገ ከዚህ በላይ ፍትህ የት እንደሚገኝ አላውቅም፡፡ ስለሆነም ከሁለቱም መመዘኛ አንፃር በአገራችን ላይ ያለው ሁኔታ

1/ ከስልጣን ክፍፍል አንፃር

በአገራችን እየሆነ ያለው በህገ-መንግስቱ በተቀመጠው መሰረት ማንኛውም ብሄር ብሄረሰብ በዚች አገር እኩል መብት አለው፡፡ ሁሉም ብሄር ብሄረሰብ በሹመኛ ሳይሆን በራሳቸው መርጠው የሚያስቀምጡት እንደሚያስተዳድራቸው ይታወቃል፡፡ ባህላቸው፣ ቋንቋቸውና ታሪካቸው የመጠቀም፣ የማሳደግና የማስፋፋት መብታቸው ተከብሮ ማንም ጣልቃ ሳይገባባቸው እየተጠቀሙ ባሉበት ዘመን የአንድ ብሄር የበላይነት አለ ሲባል አስገራሚ ከመሆኑም በላይ በችሎታቸውና በአቅማቸው ተወዳድረው ማግኘት ያልቻሉ በብሄራቸው ስም ለመደበቅ የሚፈልጉ አቅመ ደካሞች የሚያነሱ ሃሳብ ነው፡፡

በነገራችን ላይ ይህ የብሄር እኩልነት የሚባል ሃሳብ ከሁሉም ቀድሞ (ኢህደን ከመፈጠሩ በፊት) ያነሳውና የአላመዎቹ ምሰሶ በማድረግ ትግል የጀመረው እኮ ህወሓት ነው:: ይህም ከጅምሩ ዋናና መሰረታዊ መለያና መገለጫ ሲሆን ከኢህአፓና የትምክህት ሃይሎች መሰረታዊ ልዩነቱም ይህ ነጥብ ነው፡፡ የኢህዴን መስራቾች መጀመሪያ ለመታገል ሲወስኑና ከህወሓት ጋር በጋራ ለመታገል ሲያስቡ በብሄር እኩልነት ላይ የነበረው አቋምና አላማ ቀዳሚ መለኪያቸው እንደነበረ (እርስዎ ምናልባት ኋላ የመጡ ይሆናል ወይም እያቁ ተኝተው ካልሆነ፤ ኋላ የመጣ አይን አወጣ እንዳይሀን እንጂ) እኮ ይታወቃል፡፡

ስለሆነም ህወሓትም ሆነ ብአዴን (በወቅቱ ኢህዴን) አብረው እንዲታገሉና ስትራተጂካዊ አጋርነታቸውን ለማረጋገጥና ይበልጥ ለማጠናከር አንድ ዲሞክራሲያዊ ግምባር እስከመፍጠር የደረሱት  ሌሎች ተመሳሳይ አላማዎች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ዋናውና መሰረታዊ ነጥብ እኮ በዲሞክራሲያዊ ብሄረተኝነት የነበራቸው አቋምና አላማ አንድና ተመሳሳይ ስለነበረ ነው:: አሁንም ቢሆን ኢህአደግ እንደ ግንባር ለመቀጠል በዚህ ጉዳይ ያለው አቋም ምንም አይነት መሸራረፍ ከሌለ ብቻ ነው::

የአቶ እውነቱ የትግራይ የበላይነት የሚለው መንፈሳዊ እምነታቸው ለማስረዳት በፀጥታ ሃይሎች በተለይ በመከላከያ ከ95% በላይ ጀነራል መኮነን የትግራይ ተወላጅ ነው ይሉናል ይበል መዋሸት ካልቀረ አግዝፎ መዋሸት የዲሞክራሲያዊ ብሄረተኝነት ፀሮች ሁነኛ መገለጫ መሆኑ በግላጭ ያሳያል:: እዚህ ላይ አቶ እውነቱ እርስዎ በአካል የሌሉበትና የማይሰሩበት ክፍሎች በወሬ ሰምተው ለምን ማውራት እንደፈለጉ? ለምን የፀጥታ ሃይሉ ብቻ መርጠው በውጭ ጉዳይና በት/ት ሚኒስትርና ሌሎች አካባቢ ያለው ስብጥር ማንሳት እንዳልፈለጉ? ራሳቸው ግልፅ ያደርጉት ይሆናል:: በኔ እምነት ግን ሁለት ምክንያት አላቸው አንደኛውና ዋናው ጉዳያቸው ሁሉም የትምክህትና የጥበት ሃይሎች ወቅታዊ የተሳሳተ አቅጣጫ በአሁኑ ጊዜ ኢህአደግ እንዳይወድቅ እያደረገ ያለው ጥንካሬ የፀጥታ ሃይሉ ስለሆነ በትጥቅ ባይቻልም በወሬ ማሸመድመድና በውስጡ አለመታማመን መፍጠር ከሚል የሚነሳ ነው::  እንጂ አቶ እውነቱ ቅንነትና እውነት ቢኖሮዎት የበላይነት እንዳሉት በፀጥታ ሃይሉ ቢኖርና በሌላ አከባቢ የተስተካከለና የሌለ ከሆነ የስርአቱ መገለጫና ከስርአቱ በበለጠ ተጠቃሚ ትግራዋይ ነው ሊያስብለው አይችልም ነበር:: ቀና ሰው ሊያነሳው የነበረ ጉዳይ ይህ ጉዳይ ሌላ ችግር ሳይፈጥርና ወደ ሌላ መስሪያቤቶችም እንዳይከሰት ተሎ እናስተካክለው ነበር የሚለው::

ያም ሆኖ በመከላከያም ቢሆን ግን እርስዎ እንዳሉት እንዳልሆነ በየጊዜው በተወካዮች ምክር ቤት ተነስቶ እስከ አሁን ድረስ ሪፖርት እየቀረበበትና እየተገመገመ ከመሄዱም በተጨማሪ ማንኛውም ጀነራል ስሾም በግልፅ ስም እስከነአያቱ በሚድያ እየታወጅ እንጂ በሚስጢር የተሸመ የለም:: ስለሆነም እንዴት ብሎ ነው ትግራዋይ ብቻ እየተሸመ ሌላው ዝም ብሎ የሚተኛ መቼም ይህ በየወቅቱ እነኢሳት የሚያወጡት ስምዝርዝር በእጅዎ ይኖራል እንጂ ሌላ ማስረጃ ሊያቀርቡ እንደማይችሉ ልነግርዎት እፈልጋለሁ::

ባለፈው ፅሁፌ መከላከያ በአንድ ብሄር የበላይነት እናም እንዳሉት ከ95 በመቶ በላይ የትግራይ ተወላጅ ሁኖ እያለ ነው በአገራችን ከጫፍ እስከ ጫፍ ሁሉም ብሄር ብሄረሰብና ህዝቦች የኛ ሰራዊት እያሉ የሚቀበሉት? እውነት በአንድ የብሄር የበላይነት ያለው እንዚህ አይነት ህዝባዊ ሰራዊት መገንባት ይቻላል ብለው ያምናሉ? ሰራዊቱ በራሱስ የጀግንነቱ፤ የጥናካሬውና የህዝባዊነቱ ሚስጢር ምንድነው ይላሉ? አድልዎ ባለበት እሱ ሳይሆን ሌላው ለሚሾመው አማራው ኦሮሞውና ሌላው ብሄር ተወላጅ እንዴት ብሎ ነው እንደዚህ አይነት ህዝባዊ የሚሆነው? ብየ ጠይቄዎት ነበር አልመለሱልኝም::

መጀመሪያ በ1987 ዓ/ም የኢህአደግ ሰራዊት ተቀላቅሎ ሀገራዊ ሰራዊት እንዲፈጥር በሚወሰንበት ወቅት በታሪክ አጋጣሚ በትግሉ ሂደት ብዛትና የተሻለ ልምድ የነበረው የህወሓት (የትግራይ ተወላጅ በነአቶ እውነቱ አባባል) ነበር ይህን ሁኔታ ለማስተካከል ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች እንዲያካትት ከ50 ሺ በላይ የህወሓት ታጋይ እንዲቀነስ ተደረገ በዚህም ሳያበቃ የቀጠለውም በየደረጃው ያሉት ማዕርጎች እንዲመጣጠን የህወሓት አባል የነበረው ከአንድ እስከ ሁለትና ሶስት ደረጃ እየወረደ ማዕርግ ሲሰጠው የሌላው (የብአዴንም ጨምሮ) ከአንድ እስከ ሶስት ደረጃ ወደላይ ከፍ እየተደረገ ነው የተሰጠው:: ይህ አካሄድ ለአገራችን ሰላምና እድገት ይጠቅማል በመሆኑም መከፈል ያለበት መስዋእትነት ስለሆነ በወቅቱም ይሁን ዛሬ የምንቀበለው ውሳኔ ነው:: ከዛ በኋላም ያለው አካሄድ ተመሳሳይ እንደሆነ ሰዎች የሚወዳደሩት ሙያው በሚያዘው ሳይሆን አማራ ከአማራ ኦሮሞ ከኦሮሞ ትግራዋይ ከትግራዋይ እንደሆነ ነው የምንሰማው ይህ አካሄድ ለሙያው የሚያዳክምና ብቁ ወታደር ወደ ፊት እንዳይመጣ ያደርገዋል የሚሉ ወገኖች ያሉ ቢሆንም ለፖለቲካው እስከጠቀመ ድረስ ክፋት የለውም ተብሎ እየቀጠለ ያለ ጉዳይ ይመስለኛል:: ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ውትድርና በባህሪው ብዙ ውጣ ውረድና ልፋት የሚጠይቅ ሙያ በመሆኑ የመጣ እንጂ በሰዎች ፍላጎት የመጣ አይደለም::

እኛ እስከምናውቀው ድረስ አንድ የትግራይ ተወላጅ ጀነራል ለመሆን በኮሎኔልነት ማዕርግ ከአስር አመት በላይ መጠበቅ የግድ ሲለው ሌላው ግን ከሶስት እስከ አምስት አመት በቂ ነው::

እነ አቶ እውነቱ ከ1993 ጀምረው አንስተውት በዚህ መልኩ የተብራራላቸው ቢሆን አሁንም ያኔ ያወጡት ነጠላ ዜማ ላይ ናቸው:: ይህ ነገር በህብረተሰባችን የሚነገረው አንድ አባባል አስታወሰኝ እሱም ሁለት ጓደኛሞች በአንድ ጥላ ስር ተቀምጠው ሲጫወቱ ፊት ለፊታቸው አንድ እንስሳ ያያሉ አንዱ ጅግራ ናት ሲል ሌላኛው ሜዳቋ ናት የሚል ክርክር አንስተው በመጨረሻ ድንጋይ በመወርወር ለማረጋገጥ ወስነው ድንጋይ ሲወረውሩ እንስሳዋ በረረች ታድያ ያ ሜዳቋ ናት ብሎ የተከራከረው አሁን ትብረር እንጂ ሜዳቋ ነበረች ይለዋል:: ስለሆነም የአቶ እውነቱ ክርክርም ከዚህ የተለየና ውሃ የሚቋጥር እንዳልሆነ መገንዘብ አያስቸግርም::

በሌላ በኩል ደግሞ በወቅቱ (በ1993) የትግራይ የበላይነት ህወሓቶች ስለተቀበላችሁ የተወሰኑ አመራሮች ወደ ትግራይ እንዲሄዱ አድርጋችኋል ይሉናል ምን አለበት ዝም ብለው በህልምዎ የሚያዩትና እንዲሆን የሚፈልጉት ብቻ ከሚነግሩን የሆነውንና መሬት ላይ ያለውን ቢነግሩን:: አገር ቀርቶ አንድ ቤተሰብ እንኳ በውሸት ማቃናት አይቻልም እኮ:: ለነገሩ ሌባ ለአመሉ ይባል የለ:: እነ ደ/ር ደብረፅዮንና የተወሰኑ የህወሓት አመራር ከፌደራል መስሪያ ቤቶች ወጥተው ወደ ክልል እንዲሄዱ የተደረገው ዋናውና ብቸኛ ምክንያት በወቅቱ በህወሓት አመራር በተፈጠረው መከፋፈል ምክንያት በክልሉ የተፈጠረው ክፍተት ለመሙላትና የህዝቡን ስሜት ለማረጋጋት እንጂ ሌላ ምንም ምክንያት አልነበረውም የታሰበው መረጋጋት ከተፈጠረና ክፍተቱም በሚገባ ከተስተካከለ በኋላ የሄዱት ሁሉም በሚባል ደረጃ ተመልሰዋል የቀጠሉም ይኖራሉ::

Map - Tigray region and North Gondar of Amhara region

Map – Tigray region and North Gondar of Amhara region

2/ ከሀብት ክፍፍል አንፃር

አገራችን ኢትዮጵያ ከ1983ዓ/ም በፊት ሁሉም ህዝቦች አኗኗር ምን ይመስል እንደነበር ይታወቃል አገሪቷ ማመንጨት የቻለችውን ሀብት ገዢ መደቦች ይገኙበት የነበረ አከባቢ እንዲከማች በመደረጉ ሌላው (የአማራ ህዝብም ጭምር) የበዪ ተመልካች እንደነበር ለማንም በወቅቱ የነበረ ሰው የተሰወረ አይደለም:: ከዛ በኋላ የተደረገው በህገ-መንግስቱ መሰረት ዋናው የልማትና የእድገት ባለቤት ራሱ ህዝቡ ሲሆን በፌደራል ደረጃም ያለፈውን የተዛባው ለማስተካከል የሚያስችልና በህዝቦች መካከል መተማመን እንዲፈጠር አገሪቱን ማመንጨት የቻለችን ሀብት በእኩል መስፈርት ቀጥታ ብሄር ብሄረሰቦች በወኪሎቻቸው አማካይነት እንዲደለደል እየተደረገ ነው::

በፌደራል መንግስት በየአመቱ የተደለደለውና ክልሎች በራሳቸው መንገድ ማመንጨት የቻሉት ሀብት አክለው ማንም ጣልቃ ሳይገባባቸው ክልላቸው እንዲያለሙ እየተደረገ ነው:: ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በፌደራል ደረጃ በሁሉም ክልሎች መሰራት ያለባቸው የመሰረተ-ልማትም በህዝብ ተወካዮች በየአመቱ እየተወሰነ በሁሉም በተመጣጠነ እየተሰራ ነው:: ሃቁ ይህ ሁኖ ሳለ እነአቶ እውነቱ እንደምትሉት ትግራይ በተለየ ሁኔታ ተጠቅመዋል የምትሉት ካለና የተሰሩ ትምህርት ቤቶች፤ ሆስፒታሎች፤ ዩንቨርሲቲዎች፤ መንገዶች እንዲሁም የለሙ ተራራዎች በመንግስት የተለየ ነገር ተደርገዋል ብላችሁ በተጨባጭ ብታሳዩን:: እንግዲያውስ እኛ አናስተማስልም እንጂ በሽግግሩ ዘመን በመንግስት በጦርነት ለተጎዱ አከባቢዎች በልዩ ሁኔታ ይታያሉ የሚለው እኮ አልተተገበረም የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወሓት ያሉት ነገር ቢኖር የተለየ ነገር አንፈልግም አከባቢያችን በራሳችን እናለማለን ብቻ እንቅፋት አትሁንብን ነው ያሉት:: ከዚህ በመነሳት (ልምዓት ዓዲ ብወዲ ዓዲ) የሚል መፈክር ታጥቀው በተለያዩ መንገዶች በርካታ ስራዎች ሰርተዋል የትምህርት ችግር ለመፍታት ቢያንስ በወረዳ ደረጃ ከአንድ በላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ በየቀበሌው ቢያንስ አንድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት ሰላም ባስና የመሳሰሉት በርካታ የልማት ስራዎች በራሱ ወጪ ሰርተዋል:: ከ2000 ዓ/ም ወደዚህ እንኳን ከዳስ ወደ ክለስ በሚል መፈክር ከ700 በላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከፌደራል መንግስት ሰባራ ሳንቲም ሳይጠብቅ ሰርተዋል::

እና ይህ ነው የእነ አቶ እውነቱ አይኑ ደም እያስነባ ያለው ይህ በአማራ ክልል እንዳይሰራ የከለከለ አለ እንዴ? ህወሓት ከጠባብ አስተሳሰቡ በመነሳጥ እንዳይሰራ አደረገው ሊሉን ነው? በሁሉም አካባቢ እንዳለው በትግራይ የመልካም አስተዳደር ችግር ማነቆ ሆነበት እንጂ በህዝቡ ጥረትና ፍላጎት ቢሆንማ ትግራይ ከዚህ በላይ መልማት ትችል ነበር:: ይህ ከሆነ ያስቀናዎት አቶ እውነቱ መፍትሄው እጃችሁ ላይ እያለ የሌለ ነገር የትግራይ የበላይነት ወሬ እየለቀማችሁ ከምትውሉ ክልላችሁ የማልማት ሃላፊነታችሁ ህዝባችሁን በማስተባበር ጠንክራችሁ ስሩ:: አለበለዚያ ተግባር ሲጠፋችሁ ወሬን እያቦካችሁ ጊዜአችሁን አትጨርሱ:: ጊዜ እየሮጠ ነው ቆሞ አይጠብቃችሁም፤ የቆማችሁት የድሮ አይነት እናንተ የበላይ የምትሆኑበት ስርአት ይመጣል ብላችሁ ከሆነ አይሳካም:: የእናቴ ቀሚስ አትበሉ:: ለክልላችሁ ልማትም ሆነ ውድቀት ተወዳሽም ተጠያቂም ራሳችሁ ናችሁ አደናቃፊው ድንጋይ በህዝቦች የተባበረ ትግል ላይመለስ ተወግደዋል::

ስለሆነም የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወሓት የሚገባቸውን እንኳ በይሉኝታ የማይጠይቁ እንጂ ትርፍ የማይፈልጉ መሆናቸው ከትጥቅ ትግሉ ወቅት ጀምረው በተግባር ያሳዩ ናቸው:: ለዚህም ከጅምሩ ኢህዴንም ሆነ ሌሎች ድርጅቶች ከምስረታቸው ጀምረው እንዳይራቡና እንዳይከፉ ካላቸው ያካፈሉና ያበረታቱ በጦርነት እንዳይሞቱ እኛ እንሙት ያሉና ሲሞቱም በአንድ መቃብር የተቀበሩ፤ሁሉም እንደሚያውቀው በ1983 የሎንደን የሰላም ድርድር ወቅት ደርግ ከህወሓት ውጪ ሌላ  አላውቅም አልደራደርም ሲል ህወሓት በበኩሉ እንደኢህአደግ ካልሆነ እንደህወሓት አልደራደርም ያለው እኮ የበላይነትን ለማስወገድ እንጂ ሌላ ትርጉም የለውም:: የትጥቅ ትግሉ ከተጠናቀቀ በኋላም እስከ አሁን አቅምና ብቃት ያለን እኛ ነን እና ለኛ ይገባናል ያሉበት ሁኔታ የለም::

በተረፈ አቶ እውነቱ ሌሎች የሌላ ህዝብ ሲብጠለጠል ምንም አላሉም ብለውኛል ትክክል ሌላ ግለሰብ እንደተሰማው ቢናገር አለማወቁ ነው እናም እሱን ለማረምና የማስተካከል የሁላችን ተግባር ነው:: የእርስዎ ምላሽ ግን በሁለት መንገድ ፍፁም ከሌላ የተለየ ነው:: አንደኛና ዋናው እርስዎ የኢህአደግ ከፍተኛ አመራር ሁነው የህወሓትና የትግራይ ህዝብ ምንነት ስለሚያውቁና በብአዴን ውስጥ ምን እየተደረገ ነው የሚል ስሜት ስለጫረብኝ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ሌሎች እንደመልአክ የሚያመልኩዋቸው ሰዎች ለመከላከል አልመው በመነሳትዎ ነው::

ቸር እንሰንብት

********

4 Comments
 1. dergu temelese

  የጎጃም ሀዘን እና አጼ ዮሀንስ የመተማ ዘመቻ
  አጼ ዮሀንስ ደርቦሾችን ልክ ለማስገባት ወደ መተማ ከመዝመታቸው በፊት ጎጃምን ወረው ጦራቸው የህዘቡን ቤቶች አቃጥሏል፣ ሴቶችን ደፍሯል፣ከብቶችን አርዷል፣ ነድቷል፣ የጎጃም ገበሬ በወዙ እና በላቡ ያፈራውን ሀብትና ንብረት በማጣቱ አምርሮ አዝኗል፡፡
  በዚህም ምክንያት የጎጃም ህዝብ ሀዘኑን እንደሚከተለው በስንኝ ቋጥሯል፡፡
  በሰላም ከመጡ ዮሀንስ ከመተማ፣
  ጎጃም ማተብ የለው እግዜርም የለማ፡፡
  ደርቡሾች የጎጃም ህዝብ ሀዘንም ረድቷቸው የአጼ ዮሀንስን ገድለውና አንገት ቆረጠው መውሰዳቸው በታሪክ ተጽፏል፡፡
  ታሪክ ራስን ይደግማል
  የወቅቱ የአጼ ዮሀንስ ልጆች ( ህወሀቶች) ኢትዮጵያውያንን እየገደሉና እየዘረፉ ነው፡፡
  1/ ብአዴን የሚባል ለሆዳቸው ያደሩና ወገናቸውን የካዱ ባንዳዎችን አደራጅተው በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ እና በረቀቀ መንገድ ጎንደርን እና ጎጃምን እየዘረፉ ነው፡፡ የነገ አገር ገንቢ ወጣቶችንም እየጨፈጨፉ ነው፡፡ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ የአማራ ህዝብ በተለያዩ ስልቶች እንደአጠፉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሳይቀር ተነስቶ ራሳቸውም ተጨቃጭቀወበታል፡፡ ከስልቶቹም መካከል የኤድስ ህሙማንን ከሠራዊቱ ሰብስቦ በብር ሸለቆ በማስፈር፣ ትገሬ የሆኑ የጤና ባለሙያዎችን በአማራ ክልል ገጠሮች በማሰማራት ሴቶች ለህክምና ሲሄዱ መሀን የሚያደርጉ መድሀኒቶችን በመውጋት፣ በበደኖ፣ በወተር፣ በሊማሊሞ፣ በሀረር፣ በባህርዳር በጥይት እና ከእነ ህይወታቸው በመቅበር ገድለዋል፡፡
  2/ የወቅቱ የዮሀንስ ልጆች የጋምቤላን መሬት በኢንቬስትመንት ሰበብ ለመውረር ከ420 በላይ አኝዋኮችን በጠራራ ጸሀይ ገድለዋል ነባር ነዋሪዎችንም አፈናቅለዋል፡፡
  3/ ከ 700 ሺ በላይ ሶማሌዎችን የኦጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅትን ትደግፋላችሁ በማለት በተለያዩ ጊዚያት በጅምላ እንደገደሉ ከ800 ሺ ህዝብ በላይ መኖሪያ ቀየውን ጥሎ እንደተፈናቀለ የፌዴራል ፖሊስ አባል ሆኖ ሥርዓቱን ያገለገለው እና የኢሳ ጎሳ ተወላጅ የሆነ ሻለቃ አሊ የተባለ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በ21/ 04/ 2009 ማጋለጡ እና በ20/05 /2009 ደግሞ የክልሉ ሆድ አደር ባለስልጣን ለማስተባበል መሞከሩ ይታወቃል፡፡ በአጠቃላይ ወያኔ እየተከተለ ያለው የመግደል እና የመዝረፍ ፖሊሲ ሀይ ባይ ያጣ እና ዳፈው ለልጅ ልጅ የሚተርፍ እየሆነ ነው፡፡

  Reply
 2. birhanu

  አቶ እውነቱ የሚባል ፀሀፊ የሚፅፋቸዉን መጣጥፎች ተመልክቻቸዋለሁ፡፡ምንም ቁም ነገር የሌላቸዉ እርባና ቢስ የሆኑ ሀሣቦችን የያዙ ናቸው የሞተውን እና ላይመለስ የተቀበረዉን አሮጌውን አስተሳሰብ ለመትከል በከንቱ ከሚወራጬት ሀይሎች አስተሳሰብ በምንም አይለይም የአቶ እውነቱን መጣጥፍ ማለቴ ነው፡፡

  Reply

ስለጽሑፉ ምን ይላሉ? አስተያየቶን ያካፍሉን፡፡