ቁርጠኛ የሆነ አመራርና ነጻ ሚዲያ በሌለበት ሙስናን መታገል ከቶ አይቻልም

(አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሺፈራዉ (ኮ/ል))

በሀገራችን በየጊዘዉ ለሚከሰቱ ችግሮች ሁሉ በቀላሉ ተጋላጭ ለመሆን የተገደድነዉ ተአማኒነት ያለዉ አማራጭ ነጻ መረጃ ምንጭ እጦትና ቁርጠኛ የሆነ አመራር አለመኖር ነዉ፡፡ ዋስትናዉ የተጠበቀ የመረጃ ተደራሽነት መኖር ለአንድ ህዝብ እጅግ ጠቃሚ ነዉ፡፡ ዜጎች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በነጻነት የመወያየት፤ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፤ ነጻ በሆኑ ሚዲያዎችን ተጠቅመዉ ያለመሸማቀቅ መንግስትን የመተቸትና አስፈላጊ ሆኖ ባገኙ ጊዜ ደግሞ ወደ አደባባይ በመዉጣት በሰላማዊ መንገድ ተቃዉሞአቸዉን የማሰማት  መብት ሊኖራቸዉ ይገባል፡፡ ህዝብ በጎዉን ከመጥፎዉ መለየት የሚችልበት አማራጭ ስለሌለዉ አፍራሽ ለሆነ የዉጭ ቅስቀሳዎች በቀላሉ ተጋላጭ ሆኗል፡፡ ሙስና እንዲህ የማይደፈርበት ደረጃ  ለመድረስ የበቃዉም ነጻ ሚዲያ እጦት ምክንያት ነዉ፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ የሀገሪቱ አመራር ሙሰኞች ህዝቡን መቀለጃ እያደረጉት እያየ ጠንካራ እርምጃ ለመዉሰድ አለመድፈሩ ህዝቡ ሙስናን ከሽብርተኝነት በበለጠ እስፈሪ አድርጎ እንዲያይ አድርጎታል፡፡

1/ እጅጉን የጎዳን ተአማንነት ያለዉ የመረጃ ዕጦት ነዉ፡፡

በመንግስት የስልጣን እርካብ የተቆናጠጡ ባለስልጣናት ለዚያ ሃላፊነት ላበቃቸዉ ህዝብ ፍላጎትና ፈቃድ ተገዢ መሆን ይገባቸዋል፡፡ መንግስት ባሰኘዉ ግዜ ያሰኘዉን ህግና ደንብ እያረቀቀ በህዝብ ላይ መጫን አይችልም፡፡ በየትኛዉም  ጉዳይ ላይ ህግ ከመዉጣቱ በፊት ዜጎችን በማወያየት የሚሰጡትን አስተያየት ከግምት ማስገባት ይኖርበታል፡፡ በተለየ ሁኔታ የሃገራዊ ደህንነት ምስጢር ለመጠበቅ ታስቦ ካልሆነ በስተቀር በህግ አዉጭዉ የሚደረጉ ስብሰባዎች ሆኑ የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴዎች ስብሰባ ህዝብ በግልጽ እንዲያዉቃቸዉ መደረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ ጋር አብሮ ነጻ የሆኑ ሚዲያዎች ህዝቡ ማወቅ ባለበት ጉዳይ ላይ ያለ አንዳች ከልከላና መሸማቀቅ ወደ ህዝቡ እንዲያደርሱ እድል ሊያገኙ ይገባል፡፡ መንግስት በሚያወጣቸዉ ፖሊሲዎች ላይ ሚዲያዎች የሚሰነዝሩትን ትችት በጸጋ የመቀበልና ተገቢነት ያላቸዉ አስተያየቶችን ሳይንቅ ፖሊሲዎቹን አስሰከመቀየር ድረስ ሊደርስ ይገባል፡፡

የመረጃ ተደራሽትን የማስፈን ከፍተኛ ጠቀሜታዉ ከሁሉም በላይ ሙስናን ለመወጋት ትልቅ ጉልበት መሆኑ ነዉ፡፡ በነጻ ሚዲያ እይታ ስር ያሉና የህዝብ ክትትል ያልተለያቸዉ የመንግስት ባለስልጣናት በአብዛኛዉ ህጉን ተከትለዉ በታማኝነትና በብቃት ህዝብን የማገልገል ዝንባሌ ይኖራቸዋል፡፡ ነጻ ሚዲያዉ በሙሉ ኃይሉ በነጻነት በሚሰራበት ሁኔታ ባለስልጣናት ከህዝብ እይታ ማምለጥ ስለማይችሉ ስልጣናቸዉን ለግል ጥቅማቸዉ የማዋል ዝንባሌአቸዉ አነስተኛ ነዉ፡፡ ለመረጃ ቅርብ የሆነ ህዝብ መብቱንም ሆነ የዜግነት ግዴታዉን ጠንቅቆ ስለሚገነዘብ ሙስናንና ሌሎች ብልሹ አሰራሮችን በንቃት ለመታገል አያመነታም፡፡አፍራሽ ለሆኑ ፕሮፖጋንዳዎች በቀላሉ አይሸነፍም፡፡ የመንግስትንም የአሰራር ግድፌት ለመተቸት የሚችለዉም ተአማንነት ያላቸዉ አማራጭ ሚዲያዎች ሲኖሩ ነዉ፡፡

ለመረጃ ተደራሽነቱ ከፍተኛ በሆነ ስርአት ዉስጥ መንግስት የትክክለኛና ትክክለኛ ያልሆነ መረጃን ብቸኛ ፈራጅ የሚሆንበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ግልጽነት በሰፈነበት ስርአት ዉስጥ “በእዉነት” ላይ መንግስት በብቸኝነት ባለቤት (monopoly on the truth) ሊሆን አይችልም፡፡ ትክክለኛ መረጃን ከተሳሳተዉ፤ የሚጠቅመዉን ከማይጠቅመዉ አመዛዝኖ መለየት የሚችለዉ ራሱ ህዝቡ ብቻ ነዉ፡፡ ጠንካራ የሚዲያ ተደራሽነት ባለበት አገር መንግስት እንዳሻዉ መሆን አይችልም፡፡ መንግስት በሚሰራዉና በሚናገረዉ ሁሉ ጠንቀቅ ብሎ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ይገደዳል፡፡ ጠንካራ ነጻ ሚዲያ ባለበት ስርአት የመንግስት ባለስልጣናት ዳተኛና ግደለሽ ለመሆን እድል አይሠጣቸዉም፡፡

በርግጥ የማይካድ ነገር የሚዲያ ነጻነት ከአጠቃላይ የስርአቱ ዲሞክራሲያዊነት ዉጭ መጠበቅ አይቻልም፡፡ ዲሞክራሲያዊ ባልሆነ ስርአት ዉስጥ ነጸ ሚዲያ ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ነጻ ሚዲያ በለለበትም ዲሞክራሲ ሊኖር አይችልም፡፡ ያሻዉን መጠየቅና መተቸት  የማይችል ህብረተሰብ ነጻ ነዉ ማለት አይቻልም፡፡ የመጠየቅንና የመቃወምን መብት የማያካትት፤ የመጻፍና የማንበብ መብትን የማይፈቅድ ዲሞክራሲ አስመሳይ ዲሞክራሲ ሊባል ካልሆነ በስተቀር ትክክለኛ ዲሞክራሲ ሊባል አይችልም፡፡ አንድ ስሙን የዘነጋሁት ፈረንጅ “የፕሬስ ነጻነት የለለበት ዲሞክራሲ፤ ኔትዎርክ በሌለበት ስማርትፎን እንደመያዝ ይቆጠራል” ያለዉ ለኛ ሁኔታ ተስማሚ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ከፍተኛ የመረጃ ተደራሽነት ባለባቸዉ የታደሉ አገሮች ምስጋና ለነጻ ሚዲያቸዉ  ይሁንና ህዝቡ መብቱንና ግዴታዉን ጠኝቅቆ የሚያዉቅ በመሆኑ መንግስት ህዝቡን ሳያማክርና  ፍላጎቱን ሳይጠይቅ እንዳሻዉ እንዲሰራ አይፈቅድለትም፡፡ እኛ በዚህ ረገድ ምን ያህል ጉድለት እንዳለብን ሁላችንም ጠንቅቀን እናዉቃለን፡፡ የሀገራችን ህዝቦች ሌለዉ ቀርቶ ለቀዉስ በቀላሉ ተጋላጭ ሊሆኑ የቻሉት ተአማንነት ያለዉ አመራጭ የመረጃ ተደራሽነት ባለመኖሩ እንደሆነ  መናገር ይቻላል፡፡

Image - two hands exchange bribe under a table
Image – two hands exchange bribe under a table

2/ መንግስት ብቸኛ የመረጃ ምንጭ የመሆኑ ጉዳይ ፤

በአገራችን ለተከሰተዉ ሁኔታ እዚህ ደረጃ መድረስ አንዱ ምክንያት ሃላፊነት የሚሰማዉ የግል ሚዲያ አለመኖሩ ይመስለኛል፡፡ ሀሳባቸዉን በነጻነት የሚያቀርቡ የሲቪክ ማህበራትና ደፋር ምሁራንን ጨምሮ መንግስት በአግባቡ ሊጠቀምበት እየቻለ ያልተጠቀመበት ትልቅ ኃይል ቢኖር የግል ሚዲያዉን ነዉ ማለት እችላለሁ፡፡ መንግስትን ሲያጠፋ ሊገስጽና ሊያርም፤ ጥሩ ሲሰራ ደግሞ ሊያበረታታ፤ ህዝቡንም ሊከሰቱ ከሚችሉ አደጋዎች ለማስጠንቀቅና ለማስተማር የሚችል ሃላፊነት የሚሰማዉ የግል ሚዲያ አለመኖሩ ትልቅ ጉድለት ይመስለኛል፡፡

ለአንድ ሰሞን ታይተዉ ወዲያዉኑ ከሚጠፉ ጥቂት የህትመት ዉጤቶች ጀምሮ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዉ ጭምር እርባና ቢስ ከሆኑ ቅራቅንቦ ጉዳዮች ዉጭ ህዝቡን በተለይም ወጣቱን አገራዊ በሆኑና የሕዝብን ብሶት በሚያመለክቱ ጉዳዮች ላይ በሃላፊነት መንፈስ ሊያስተምሩና መንግስትን በድፍረት ሊተቹ አልፈቀዱም፡፡ እንደ ቅርብ ጊዜዉ መሰል በሀገሪቱ ህልዉና ላይ የተጋረጡ አደጋዎች ሲኖሩ ህዝብን ለማረጋጋትና አጥፊዎችንም ደግሞ ለማረምና ለመምከር ፈቃደኛ የሆነ የግል ሚዲያ በመጥፋቱ መንግስት ሁሉንም ችግሮች ብቻዉን እንዲጋተር አድርጎታል፡፡ ሃላፊነት እንዳለበት ከሚታወቀዉ የመንግስት ሚዲያ ይልቅ ማንና ከየት እንደሚያሰራጩ እንኳን መለየት ለማይቻል የመረጃ ምንጮች አመኔታ ለሰጠ ህብረተሰብ የግል ሚዲያዉን በማጠናከር አማራጭ የመረጃ ምንጭ ሆነዉ እንዲሰሩ ከማድረግ ዉጭ ሌላ መፍትሄ አይኖርም፡፡

የመንግስትን ሚዲያ በጭፍን የመጠራጠር ልማድ ላዳበረ እንደኛ ላለ ህብረተሰብ እዚሁ ህዝቡ መሃል ሆነዉ በሃላፊነት ስሜት እዉነቱን የሚዘግቡ የግል ሚዲያዎች ቢኖሩ ኖሮ ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ ወደ ዉጭ ማማተር ባለስፈለገዉ ነበር፡፡ ለእነ ጃዋርና ለእነ ሻዕቢያ አፍራሽ ቅስቀሳም ባልተንበረከከ ነበር፡፡ ለመሆኑ በዚህ ጉዳይ መወቀስ ያለበትስ ማነዉ? በአንድ ስብሰባ ላይ ጋዜጠኛ ሳምሶን ማሞ “እኛ በሃላፊነት መንፈስና በነጻነት እንድንሰራ ባለመደረጋችንና ጫና ስለበዛብን ነዉ ህብረተረሰቡ ከዉጭ ለሚለቀቁ አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ የተጋለጠዉ” ብሎ በምሬት የገለጸዉ ትክክለኛ ይመስለኛል፡፡

ህዝቡን ከጥፋት ለመታደግ የማይችልና ለራሱም የታነቀና ነጻነት የለለዉ የሚዲያ ስርአት ባለበት ሁኔታ ዲሞክራሲያዊ ስርአትን መገንባት ቀርቶ የሀገርን ህልዉናም ማስቀጠል አዳጋች እንደሆነ ከቀድሞ ይልቅ አሁን እየተረዳን የመጣን ይመስለኛል፡፡ መንግስት ራሱ ከሚቆጣጠራቸዉ ሚዲያዎች ዉጭ የመንግስትን አቋም የሚደግፍ አንድም የግል ሚዲያ አለመኖር በእጅጉ ሊያሳስበዉ በተገባ ነበር፡፡ ከፖለቲካ አሰጥ አገባ ዉጭ ባሉ አገራዊ የሆኑ የደህንነት አጀንዳዎች ላይ እንኳን ሳይቀር ድጋፍ መነፈጉ ምቾት የሚሰጥ አይደለም፡፡

ዛሬ ባለንበት ዘመን መረጃን ለማማረጥ ሰፊ እድል ባለበት ወቅት መንግስት ለህዝብ ስነ ልቦና ጎጂ ናቸዉ የሚላቸዉን ፕሮፓጋንዳዎች ብቻዉን ለመቋቋም እንደማይችል ከምንጊዜም በላይ አሁን ግልጽ ሊሆንለት ይገባል፡፡ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መራቀቅና በርካታ አማራጭ የመረጃ ምንጮች መኖር የተነሳ መንግስት ብቸኛዉ የመረጃ አቅራቢ ሆኖ መቀጠል እንደማይችል መረዳት አለበት፡፡ በህጋዊ መንገድ የሚሰሩ ተፎካካሪ አማራጭ የመረጃ ምንጮችን አስፈላጊነት አምኖ መቀበል የግድ ነዉ፡፡ ዛሬ መንግስት እንደድሮዉ ለራሱ የሚመቹትን ጉዳዮች ብቻ እየመረጠ ወደ ህዝቡ እንዲደርሱ ለማድረግ አይችልም፡፡ መረጃን መቆጣጠር ለመንግስት አጅግ ፈታኝ እየሆነበት ነዉ፡፡

ህብረሰተሰቡ የሚፈልጋቸዉና የሚጠቅሙት መረጃዎች የትኞቹ እንደሆኑ የመምረጥ ኀላፊነት የመንግስት መሆኑ አክትሞ የመረጃ ፈላጊዉ የግል ፍላጎት ሆኗል፡፡ በዚህ ምክንያትም ከማይታወቁ ምንጮች የሚለቀቁ የተዛቡ መረጃዎችን ጭምር ለማስተባበልና ጸረ-ፕሮፖጋንዳ ስራ ለመስራት  ለመንግስት እጅግ አዳጋች ሆኖበታል፡፡ በተለይም መንግስት በመረጃ አቅርቦቱ ረገድ ያለ ማንም እገዛና ትብብር ብቻዉን ለመስራት መቁረጡና ሊያግዙት ይችሉ የነበሩትን ሌሎች የግል ሚዲያዎች ለማበረታታት አለመፍቀዱ ሁኔታዉን ይበልጥ ፈታኝ አድርጎበታል፡፡

ከግል ሚዲያዎች አፍራሽ ዓላማ ያላቸዉ ባይጠፉም ሁሉንም በአንድ ላይ ፈርጆ ጥፋታቸዉ እንጀ ሊሰጡ የሚችሉት ጠቀሜታ አልታይህ ብሎት ወደ ጎን ስለገፋቸዉ ሃላፊነት የሚሰማቸዉ ናቸዉ የተባሉትም ሳይቀሩ በግላቸዉ ሊሰጡ ይችሉ የነበረዉን ገንቢ ሚና ተግባራዊ ለማድረግ ድፍረት አንሶአቸዋል፡፡ ሌላዉ ቀርቶ ለአንድነታችን እጅግ አደገኛ ለሆነዉ ለእነ ጃዋር ዘረኛ  ቅስቀሳ ተመጣጣኝ መልስ መስጠትን መንግስት በብቸኝነት የያዘዉ ሃላፊነቱ አስኪመስል ድረስ ሌሎች የግል ሚዲያዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ሲሉ አለመደመጣቸዉ አሰሳቢ ነዉ፡፡ የሻእቢያን ሴራ ለማዉገዝም እኮ የግል ሚዲያዎች ፍላጎታቸዉና ተነሳሽነታቸዉ ቀዝቃዛ ነዉ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሙስና እያደረሰ ያለዉን ጥፋት ለመታገል የበኩላቸዉን አስተዋጽኦ ለማድረግ አለመንቀሳቀሳቸዉ ለምን የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡

ሙስናን ጨምሮ በሀገርና በህዝብ ደህንነት ላይ ያነጣጠረ አደጋ ሲኖር ህዝቡን ለማስጠንቀቅ ወይም ለማስተማር አለመፈለጋቸዉ ምናልባት በዚህ ጉዳይ ላይ አንድም ዘገባ እንዳትሰሩ የሚል የመንግስት ማስጠንቀቂያ ስለደረሳቸዉ ነዉ ወይንስ ራሳቸዉ የግል ሚዲያዎቹ አንባቢና አድማጭ አናገኝም በሚል ነዉ? መንግስትስ ቢሆን ይሄን መሰሉን ትልቅ ኃላፊነት ያለማንም አጋሪነት ብቻዉን መወጣት እችላለሁ የሚል እምነት አለዉ ማለት ነዉ? ኢህአዴግን በመቃወም መጋጨት አልፈልግም የሚል የግል ሚዲያ ቢያንስ  ለሀገርና ለህዝብ የስጋት ምንጭ በሆነ ጉዳይ ላይ መጻፍስ ምን ያስፈራዋል? የግል ሚዲያዉ በፍርሃት ቆፈን ዉስጥ ለመኖሩ ማሳያዉ ይሄ ነዉ፡፡ በአገሩ ጉዳይ ላይ እንኳን መጻፍ አለመፍቀዱ ፡፡

ኢህአዴግ በዚህ በጀመረዉ ጥልቅ መታደስ ዙሪያ ህብረተሰቡ እየሠጠ ካለዉ አስተያየት መረዳት እንደሚቻለዉ ከሁሉም በላይ በሙስና ላይ ተግባራዊ ለዉጥ ማዬት መፈለጉን ነዉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለዓመታት ሰፊ መረጃ ሲያቀርብና ሲያስጠነቅቅ የቆየ ሚዲያ ቢኖር በእኔ ግምት ዛሚ 90.7 ኤፍ.ኤም ሬዲዮ ነዉ፡፡ዛሚ በዚህ ጉዳይ ላይ ለዓመታት አበክሮ ሲያስገነዝብና የህዝቡን ብሶት ሲያሰማ እንደነበር አዉቃለሁ፡፡ በሰሞኑም በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በስልክ በማሳተፍ ጣቢያዉ ማስተናገድ አስከሚሳነዉ ደረስ በተጨናነቀ ሁኔታ እየገለጹ ያለዉ አስተያየት በመንግስት የተጀመረዉ ዘመቻ ቢያስደስታቸዉም  ቁርጠኝነቱና ቀጣይነቱ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸዉ የተገዘብኩ ይመስለኛል፡፡የመንግስትም ሆነ ሌሎች የግል ሚዲያዎች ሙስናን፤ሌሎች ማህበራዊ ችግሮችና የህዝብ ብሶቶች ላይ የተለመደችዋን ዜና እንኳን ለመስራት በፍርሃት በሚርዱበት ወቅት ዛሚ ግን ከሶስትና አራት ዓመት ጀምሮ “ሌባን ሌባ!” እያለ ሳይሸፋፍንና ሳይደብቅ በድፍረት በማቅረብ ላደረገዉ ጥሬት ሊመሰገንና ቢሎም ሊሸለም በተገባዉ ነበር፡፡ በቅርቡ  በሃገራችን ተፈጥሮ በነበረዉ ቀዉስ ወቅትም ብዙዎቹ የግል ሚድዎች ከተለመደዉ አሸሼ ገዳሜ ፕሮግራሞቻቸዉ አንድም ጥቂት ደቂቃዎች መመደብ ተስኗቸዉ በተፈጠረዉ ሁኔታ የህዝቡን ጭንቀት ለመጋራትም ሆነ ያለ አንዳች ገደብ ከዉጪ በሚለቀቁ የጥፋት መልእክቶች ወጣቱን ለመታደግ አልሞከሩም፡፡

ዛሚ ኤፍ.ኤም ሬዲዮ ግን  የጥፋት ድርጊቱን በግልጽ ከማዉገዝ ጀምሮ ህብረተሰቡን ለማስጠንቀቅና ለማረጋጋት የበኩሉን ሃላፊነት ሲወጣ ቆይቷል፡፡ ከሁሉም በላይ ኃላፊነት እንዳለበት ከሚታወቀዉ ከኢቢሲ (EBC)) ይልቅ ዛሚ የዜግነትና የሙያ ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ ያለ ይመስለኛል፡፡ ዛሚ መንግስትንና ገዢዉን ፓርቲ ዉሃ ቀጠነ በሚል የሚነቅፍና ለመንቀፍ ብቻ የቆመ አይደለም፡፡ መንግሰት መልካም ነገር ሲሰራ ከየትኛዉም ሚድያ አዉታር በበለጠ የሚያመሰግነዉና የሚያበረታታዉ ዛሚ ነዉ፡፡ የዛሚ ሰዎች እጅግ በተጨናነቀና ጫና ባለበት ሁኔታ ዉስጥ ሆነዉ የህዝቡን ብሶት ለማሰማት ያደረጉት ጥሬት ሲታይ ምናልባት የተሻለ ነጻነት ተሰምቶአቸዉ ሳይሸማቀቁና ሳይሰጉ ሰርተዉ ቢሆኑ ኖሮ ከዚህ የበለጠ ብዙ ገንቢ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ስንረዳ የሚዲያ ነጻነት ጉድለት ምን ያህል እንደጎዳን ለመረዳት አያዳግተንም፡፡ዛሚ – እንኳን ከዚህ የበለጠ  ነጻነት  ተሰጥቶት ይቅርና አሁንም ብዙ ሙሰኛና ዋልጌ ባለስልጣናት ለዛሚ መልካም አመለካከት እንደለላቸዉ እንሰማለን፡፡ የሕዝብ ብሶትን ከመግለጽ በይሉኝታ የማያልፈዉ ዛሚ በአንዳንድ ወገኖች ለገዥዉ ፓርቲ በታማኝነት የቆመ ነዉ የሚለዉ ሃሜት ምን ያህል ተገቢ ያልሆነ ትችት እንደሆነ ለመረዳት አልተሳነኝም፡፡ ይሄ ሃሜት መንግስት ጥሩ ቢሰራም ባይሰራም የግድ መወገዝ አለበት የሚል አቋም ካላቸዉ ወገኖች የሚሰነዘር ሃሜት መሆኑን ለመረዳት አልከበደኝም፡፡

መንግስት ወይ ራሱ የሚናገረዉ አይታመን – ወይንም ሊታመን የሚችል ሌላ የመረጃ ምንጭ እንዲፈጠር አላደረገ – ህዝብ ማንን ማመን እንዳለበት ግራ ገብቶታል፡፡ የሀገር ንብረት ያለአግባብ አታዉድሙ ለሚለዉ የመንግስት ጉትጎታ ይልቅ አንድም ነገር ሳታስቀሩ የራሳችሁንም ጭምር አዉድሙ፤ እርስበርሳችሁም ተገዳደሉ ብሎ ለሚያዘዉ የጃዋር ትእዛዝ ጆሮ ማዋሳችን ከምን የመነጨ ነዉ? በመንግስት ላይ ይሄንን ያህል አለመታመን እንዲሁ በአጋጣሚ የመጣበት ሳይሆን በራሱ በመንግስት የግልጽነት ችግር የመጣ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ በመንግስት ሚዲያ የሚሰጡ የህዝብ አስተያየት የሚቀርብበት ሁኔታ ራሱ ድብብቆሽ የተሞላበት ነዉ፡፡ የህዝቡን አስተያየት እንዳለ ከማቅረብ ይልቅ ‹አንዳንድ አዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደገለጹት› ተብሎ ዜና መስራት ያለነገር የሆነ ሳይሆን ሆን ተብሎ የተዛባ መልእክት ለማስተላለፍ ስለሚያስችል  ይመስለኛል፡፡ግልጽነት ያለመኖሩ አንድ መሳያ ነዉ፡፡

3/  ኢህአዴግን ማንነት በቀጥታ ከሙስና ጋር የማቆራኘት አመለካከት ፤

ሙስና አለም አቀፍ ችግር በመሆኑ እና በዚህ ረገድ ሰፊ ትብብርና እገዛ ስላለ መንግስት ብቻዉን አይደለም፡፡፡ መንግስት ጸረ-ሙስና ትግሉ ላይ ከመበርታት ይልቅ ስለ ሙስና ንድፈሃሳብ መመራመርና ሪሰርች ማድረግ ባላስፈለገዉ ነበር፡፡ምክንያቱም ሙስና በመላዉ ዓለም ባሉ አገራት የሚታወቅ የጋራ ችግር በመሆኑ በሚመለከታቸዉ አለም አቀፍ ተቋማት በጉዳዩ ላይ ከበቂ በላይ የጥናት ጽሁፎች ቀርበዋልና፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ለሃያ አምስት ዓመታት በሌብነት ላይ ያን ያህል ‹ግንዛቤ መፍጠር› ብሎ ነገር አይገባኝም፡፡ የመንግስትም ሆነ የኮሚሽኑ ሃላፊነት በሙስና ላይ የመማሪያ ማኑዋል ማዘጋጀት ሳይሆን በቁርጠኝነት ሌብነትን መፋለም ነዉ መሆን ያለበት፡፡ መንግስት ሙስናን ለመታገል ብቻዉን ሳይሆን በዚህ ጉዳይ ላይ ትብርር የሚያደረጉ በርካታ አለም አቀፍ ተቋማት እንዳሉ ሁላችንም እናዉቃለን፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በዚህ ረገድ ከህዝቡም ከፍተኛ የሆነ ትብብር አልተለየዉም፡፡

በሙስና የመጀመሪያዉ ተጎጂ ራሱ ህዝቡ ስለሆነ የመንግስት ቁርጠኝነት ባይጎድል ኖሮ እንደ ህዝቡ ትብብር ቢሆን ኖሮ ገና ድሮዉኑ ከሌብነት በተገላገልን ነበር፡፡ ህዝቡ እንደሆነ ከጥቆማ ጀምሮ መንግስት ሳይጠይቀዉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ወደ ኋላ አይልም፡፡ ችግሩ ግን በመንግስት በኩል ለዚህ ቀና ሁኔታ በሚፈለገዉ ደረጃ ተግባራዊ ምላሽ አለማግኘቱና ፍላጎቱና ቁርጠኝነቱም የሚፈለገዉን ያህል አለመሆኑ ነዉ፡፡ አሁን አሁንማ ህዝቡ የገዥዉ ፓርቲ አባል መሆንን በቀጥታ ከሙስና ጋር ማቆራኘት ጀምሮአል፡፡ “ኢህአዴግ ማለት ልማት ነዉ፡፡ ኢህአዴግ ማለት ሰላም ነዉ፡፡“ ከሚለዉ መሪ መፈክሩ ባልተናነሰ “ኢህአዴግ ማለት ሙስና ነዉ” ወደ ማለት ተደርሷል፡፡ የአብዛኛዉ ህዝብ አመለካከት ይሄ መሆኑ መቼም አሳዛኝ ነዉ፡፡

ሙስና  ለህዝቡ ከሽብርተኝነትም በላይ አስጊ እየሆነ ነዉ፡፡ ሽብርተኝነትን በታጠቀ ሰራዊት በተሳካ ሁኔታ እየተፋለምን ብንሆንም ሙስናን እንኳን ድል ልናደርገዉ ይቅርና ጭራሽ በላያችን ላይ ተንሰራፍቶ ሊያጠፋን ደርሷል፡፡ ታንክ መድፍና ዘመናዊ ጦር ጄቶች የታጠቀ ግዙፍ ሰራዊት፤ ከራሱም አልፎ በሌላዉ አገር ድንበር ተሻግሮ ሽብርተኝነትን አይቀጡ ቅጣት የሚቀጣ መከላከያ ኃይል ያለዉ መንግስት ሙስናን ማጥፋት ቀርቶ ለመቀነስ እንኳን አልተቻለዉም፡፡ መንግስት ህዝቡን ከሙስና አደጋ መታደግ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም ቢሆን አይችልም የሚሉ አስተያየቶችን በተደጋጋሚ መሰማታችን ነዉ ይበልጥ የሚረብሸን፡፡ በተለይም የድርጅቱን ዉስጣዊ ባህሪይዉን ጠንቅቀን እናዉቃለን የሚሉ ወገኖች በኢህአዴግ የሚመራ መንግስት መቼም ቢሆን በምንም ሁኔታ ሙስናን ሊያጠፋ አይቻለዉም ማለታቸዉ ነዉ ይበልጥ የሚያሰጋን፡፡ ሙስናን በቁርጠኝነት ለመታገል የድርጅቱ ባህሪይ አይፈቅድለትም የሚሉ እነዚህ ወገኖች አሁን መንግስት እየወሰደ ያለዉን ጠበቅ ያለ እርምጃ ህዝብን ለማደናገሪያ እንጂ ዘለቄታ የለለዉ ነዉ በሚል ተስፋ ሊያስቆርጡን መሞከራቸዉ አልቀረም፡፡ በጥቂት ወራት ዉስጥ ብቻ በመቶ የሚቆጠሩ ባለስልጣናት ከሃላፊነታቸዉ እየተነሱ ጉዳያቸዉ በህግ እንዲታይ እየተደረገ ባለበት ወቅትም መንግስት እየወሰደ ባለዉ እርምጃ በቂ አይደለም መባሉ በመንግስት ተስፋ አድርገን ለነበርን ዜጎች ተስፋ አስቆራጭ ሆኖብናል፡፡

በሙስና የቱንም ያህል ብንማረርም አጥፊ ናቸዉ በሚል በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ መንግስት ህጋዊ መንገዱን ተከትሎ ካልሆነ በስተቀር በዘፈቀደ መዉሰድ የሚችለዉ እርምጃ ያለ አይመስለኝም፡፡ አንድም ሙሰኛ፤ አንድም ህዝብን ያስመረረ ባለስልጣን በህግ ከመጠየቅ ማምለጥ እንደለለበት የሁላችንም እምነት ነዉ፡፡የትኛዉም ሌባ ባስልጣን የሰረቃትን ሳይመልስ ተሸፋፍኖ የሚቀርበት ሁኔታም መኖር እንደማይገባዉ የሁላችንም እምነት ነዉ፡፡ ኢህአዴግ ከዚህ ቀደም ሲነግረን እንደነበረዉ ሙስናን ለመታገል ብቸኛዉ መንገድ በህብረተሰቡ ዉስጥ የአመለካከት ለዉጥ ማምጣት ነዉ የሚለዉ እምነቱ ጊዜዉ ያለፈበት በመሆኑ አሁን ተቀባይነት አይኖረዉም፡፡ ስርቆት፤ ሌብነት፤ ዝርፊያ፤ሙስና ወዘተ የአመለካከት ችግር ፤የግንዛቤ ማነስ ፤የእዉቀት ዕጦት ያመጣዉ አይደለም፡፡እየሰረቁ ያሉት እኮ ከብዙዎቻችን በተሻለ የነቁና የተማሩ ባለስልጣናት ናቸዉ፡፡

ሙስና የድርጅቱ ገላጭ ባህሪይ ነወይ? በሚለዉ ላይ ያለኝ የግል አስተያየት ለሌላዉ ሰዉ ላይስማማዉ ይችላል፡፡በእኔ እምነት ድርጅቱን ተጠግተዉ በድርጅቱ ስም ራሳቸዉን ለማበልጸግ የሞከሩ ብዙ ግለሰቦች ቢኖሩም ይህ የድርጅቱ ፍላጎት  ተደርጎ መታዬት ያለበት አይመስለኝም፡፡ ሙስናን በቁርጠኝነት አለመታገሉ፤ ለሙስና አመቺ ሁኔታ እንዳይኖር ቀዳዳዉን ሁሉ ለመድፈን የሚያስችል ግልጽነትና ተጠያቂነት የሠፈነበት አሰራር ስርአት አለመዘርጋቱ የገዢዉ ፓርቲም ሆነ የመንግስት ተጠያቂነት ላይ ምንም አያከራክርም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ  መንግስትም ቢሆን በግልጽ አምኖ የተቀበለዉ ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ መንግስት ሙስናን አንደ ስርአት ለማስፈን ሆን ብሎ በአዋጅ እንደ ፈቀደ ተደርጎ መቆጠሩና ሙስናን የስርአቱና የዚህ መንግስት መገለጫ ባህሪይ ማድረጉ ግን ተገቢ አይመስለኝም፡፡

ሙስናን ለማስፋፋት ሆን ተብሎና ታስቦ የተደራጀ መንግስታዊ  ተቋም የለም፡፡ ሙስናን ለማስፈን እንዲያግዝ ተብሎ የወጣ መንግስታዊ መመሪያም ሆነ ደንብ የለም፡፡ ነገር ግን ልንክደዉ የማንችለዉ ነገር አንድም መንግስታዊም ሆነ ህዝባዊ ተቋማት ሙስናን በቁርጠኝነት ለመታገል አለመንቀሳቀሳቸዉና ከመካላቸዉም አንድም ተቋም ከሙስና የጸዳ ሊሆን አለመቻሉ ነዉ፡፡ ሚኒስትሩም ይሞስናል፡፡ ዘበኛዉም የአቅሙን ያህል ይሰርቃል፡፡ ከመንግስት መደበኛ የሥራ ሰዓት ዉስጥ በየዕለቱ በአማካይ ከ40 ከመቶ የማያንሰዉ ግዜ የሚባክነዉ ራስን ለማበልጸግ ሲወጠንና ሲዶለት ነዉ፡፡ የትኛዉም መንግስታዊ ተቋም ከሚሰሩ ሰራተኞች መካከል ከ30 ከመቶ የማያንሱት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ቢያንስ በትንሹ በሙስና ጉዳይ እጁን ያላስገባ የለም ማለት እንችላለን፡፡ ይህ ሁኔታ ሲታይ ሙስና የሥርአቱና የፓርቲዉ ልዩ መገለጫ ማስመሰሉ እርግጥ ቢሆንም ለዚህ ማስፈጸሚነት ተብሎ የተደራጀ መንግስታዊ ተቋምም ሆነ መንግስታዊ መመሪያ ባለመኖሩ እንደ ስርአቱ ባህሪይ መቁጠር የሚገባ አይመስለኝም፡፡

4/ ህግ አዉጭዉ አስፈጸሚዉን መቆጣጠር ቢሳነዉ እንኳን ቢያንስ  በጸረ-ሙስና ትግሉ ሊያግዘዉ ይገባ ነበር

አሁን ለታየዉ እጅግ ብልሹ ሁኔታ አንዱ አስተዋጽኦ ያደረገዉ በሃገሪቱ ፓርላማ (ህግ አዉጭዉ) አስፈጻሚዉን በብርቱ መቆጣጠር አለመቻሉ ነዉ፡፡ እንደኛ ፓርላሜንታሪ ስርአት በሚከተሉ ሌሎች ዲሞክራት አገሮች አስፈጻሚዉን አካል ለመቆጣጠር ወይም የክትትል ስራ የሚሰሩ የፓርላማ አባለት የሆኑ የቁጥጥር ኮሚቴ ብዙዉን ጊዜ በተቃዋሚ ፓርቲ ሰብሳቢነት የሚመሩ በመሆናቸዉ አስፈጻሚዉ ግድፌቶች በዝምታ ስለማያልፉ ራሱን እንዲያስተካክልና ተሿሚ ባስልጣናቱ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደረግ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ረገድ የሚጫወቱትም ሚና ቀላል አይደለም፡፡

በኛ አገር በዚህ ደረጃ እየተሰራ አንዳልሆነ ሁሉም የሚያዉቀዉ ነዉ፡፡ የፓርላማ ኮሚቴዎች ቢኖርም ሁሉም የገዥዉ ፓርቲ አባል  በሆኑበት ሁኔታ ምን አዲስ ነገር ሊያመጡ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ለዚህም ነዉ ፓርላማዉ አባላት በየትኛዉም ጉዳይ ላይ በአስፈጻሚዉ የቀረበዉን  በጭብጨባ ከመቀበል ዉጭ አንድም የተለየ የረባ ስራ ሲሰራ አለመታየታቸዉ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ ወክሎ ለላካቸዉ አካባቢ ህዝብ የልማት ጥያቄን አንዳንዴ የሚያቀርቡ ባይጠፉም ነገር ግን አቀራረባቸዉ ሁሉ ፓርቲዉን ላለማሳጣት እጅግ ተጠንቅቁዉና አስቀድመዉም አስፈቅደዉ ነዉ፡፡ አንድም ጊዜ በሆነ ጉዳይ ላይ  የተቃዉሞ ድምጽ ቀርቶ ድምጸ-ተአቅቦ ሰጥተዉ አያዉቁም፡፡

እንግዲህ ለዚህ ዓይነቱ ፓርላማ ለመዳረግ የበቃነዉ በገዥዉ ፓርቲም፤በተቃዋሚ ፓርቲዎችም በኛ በሁላችንም ልፍስፍስነት ይመስለኛል፡፡ በሙስናና መልካም አሰተዳደር ዙሪያ የሀገራችን ፓርላማ ሊሰራ ያልቻለዉን  በተሻለ እየሰራ እንደሆነ የምናዉቀዉ በዛሚ ሬዲዮ ነዉ፡፡ የዛሚ ጥረት አንድ ጠንካራ ሚዲያ ምን ያህል ጠቃሚ ስራ ሊሰራ እንደሚችል ማሳያ ሊሆነን ይችላል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ ቢሶቱን የሚናገርለትና ጭንቀቱን የሚጋራለት፤ህዝቡ የእኔ ነዉ የሚለዉ ሚዲያም ሆነ ፓርላማም ያልተዋጣለት  ሆኖ በመቆየቱ ለብዙ ችግሮች ተጋላጭ ሆኗል፡፡

5/ የአቶ ኃይለማርያም የአመራር ብቃት መለካት ያለበት ከተደቀነብን ችግር ለማላቀቅ በሚሰጡት ቆራጥ አመራር እንጂ በማንነታቸዉ ሊሆን አይገባም

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን አመራርነት ተገቢነት ለመቀበል ገና ከመጀመሪያዉ ጀምሮ  የከበዳቸዉ ወገኖች እንደነበሩ በየጊዜዉ ሲሰጡ ከነበሩ መሰረተ ቢስ አስተየቶች ለማወቅ አላደጋተኝም፡፡ ዛሬም ከስንት ጊዜ በኋላ ቀጥ አድርገዉ ሃላፊነታቸዉን እየተወጡ ባሉበት ወቅትም ነቃፊዎቹ በቀድሞዉ አቋማቸዉ ጸንተዉ አቶ ኃለማርያምን ልክ ሳይፈለግና ሳይጠራ  ያለቦታዉ የተገኘ ሰዉ ጋር ለማመሳል መሞከራቸዉ አልቀረም፡፡ እነዚህ ተቃፊዎች ብቁ አመራርን የሚመዝኑበት መስፈርታቸዉ መነሻዉ ዘረኝነትና ትምክህት ነዉ፡፡ እነሱ ለመሪነት የተፈጠረ የሚሉት አካባቢ ሰዉ ካልሆነ በስተቀር የሌላዉ አካባቢ ሰዉ ሊመራ የማይችል ብቻ ሳይሆን በዚህ ዓይነት ሃላፊነት ላይ መቀመጥ  በራሱ ትልቅ ስህተት እንደሆነ አድርገዉ ለማሳመን ይሞክራሉ፡፡ አንዳንድ ወገኖች ያለ ሃፍረት ሲገለጹ  ከነበሩ አስተያየቶች መረዳት የቻልኩት የሳቸዉን አመራር ለመቀበል እንደከበዳቸዉ ነዉ፡፡

በቅርቡ በሀገራችን ለተከሰተዉ ችግርም በግል የአቶ ሃይለማርም የአመራር ድክመት ዉጤት እንደሆነ አድርገዉ ለማሳመን ብዙ እየጣሩ ነዉ፡፡ ኃይለማርያም ባይሆኑ ኖሮ ይህ ሁሉ ችግር ባልደረሰ ነበር ለማለት እየሞከሩ ነዉ፡፡ በመሰረቱ በሀገሪቱ የታየዉ ቀዉስ ለአመታት ድርጅቱ (ኢህአዴግ) ሆነ መንግስት ሊፈቱት ሲገባ ሁነኛ መፍትሄ ሳያስቀምጡለት ችላ በማለታቸዉ ሲከማቹ በመቆየታቸዉ ህዝቡን በማስቆጣቱ ወደ አደባባይ ወጣ እንጂ በፊት ያልነበረ አዲስ ችግር ስለሆነ አይደለም፡፡ ለዓመታት ተከማችተዉ ለቆዩ ለነዚህ ችግሮቹ ሁሉ አቶ ኃይለማርምን በግል ተጠያቂ ለማድረግ መሞከር እጅግ የተሳሳተ መሆን ብቻ ሳይሆን ከጀርባዉ ሌላ ዓላማ ያነገበም ነዉ የሚመስለኝ፡፡ በተለይም “ለመሪነት የተፈጠርን ስለሆንነ እኛ ብቻ ነን መምራት ያለብን” የሚሉ ቀልደኞች ይህን ሃሳብ ቢያራምዱ አይገርመንም፡፡

አቶ ኃይለማርያም ከዚህ በፊት ሲደረግ ባላየነዉ መልኩ በሀገሪቱ ለተፈጠሩ ችግሮች ሁሉ የሚመሩትን ድርጅትና መንግስት ድክመት መሆኑን በግልጽ ማመናቸዉ ትልቁን የመሪነት ባህሪይ (leadership traits) የተላበሱ መሆናቸዉን ከማሳየቱም ሌላ ጀግንነታቸዉንና ሃቀኝነታቸዉን ነዉ የሚያሳየዉ፡፡ በሀገር መሪነት ቦታ ተቀምጠዉ ስህተትን ለመቀበል የማይፈልጉ መሪዎች አገሪቱን እንዴት ወደ መቀመቅ እንደሚያሰገቧት ከኮ/ል መንግስቱ መንግስት መማር እንችላለን፡፡ ኮ/ል መንግስቱና ሲመሩት የነበረዉ መንግስት በሳቸዉ የአመራር ድክመት ከጦር ሜዳ ዉድቀት ጀምሮ አስከ ቀይ ሽብርና  አስከፊ ለነበሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ሁሉ ተጠያቂ ሲያደርጉ የነበረዉ ሌሎች የማይመለከታቸዉን እንደነበር እናስታዉሳለን፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የሀገሪቱን ችግር ሁሉ የራሳቸዉና የድርጅታቸዉ አድርገዉ መቁጠራቸዉ ኃላፊነት የሚሰማቸዉ መሪ መሆናቸዉን እንጂ በድክመት የሚያስቆጥርባቸዉ ሊሆን ባልተገባ ነበር፡፡ አቶ ኃይለማርያም  ሙሉ ኃላፊነቱን ያለማንገራገር መቀበላቸዉ ለህዝቡ ያላቸዉን ከበሬታ የሚያሳይ ነዉ፡፡ ድክመትን አምኖ መቀበል የመፍትሄዉ የመጀመሪያ እርምጃ ተደርጎ የሚቆጠር መሆኑ ብቻ ሳይሁን  የህዝብ ድጋፍንም ለማግኘት የሚረዳ በመሆኑ ድክመትን በአደባባይ አምኖ ለመቀበል እንደ አቶ ኃይለማርያም ደፋር ላልሆነ ሰዉ አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም፡፡

በሚያሳዝን ሁኔታ ለሳቸዉ የነበረኝን መተማመን የሚሸረሽር ሁኔታ ግን እያየሁ ነዉ፡፡ የሰሞኑን የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ቃለምልልስ ለተከታተለ ሰዉ ግን  መንግስታቸዉ  ባልተጠበቀ ሁኔታ ወደ ኃላ መንሸራተት መጀመሩን ስንገነዘብ በእሳቸዉ ላይ የነበረን መተማመን ባንድ ግዜ ነዉ የሟሸሸዉ፡፡ እኔ በበኩሌ በእሳቸዉ ላይ ለወትሮዉ እመለከት የነበረዉ አይነት ቁርጠኝነት ከሰሞኑ አነጋገራቸዉ  ደግሜ ማዬት ተስኖኛል፡፡ በሀገሪቱ የደረሰዉን ቀዉስም ባልተጠበቀ ሁኔታ ቀለል ለመድረግ የተሞከረበት አዝማሚያ ነዉ የታየዉ፡፡ ሀገሪቱ እያስመዘገበች ያለችዉን አድገት ላይ የመንግስትን ጥንካሬና አይበገሬነት ለማድነቅ ሲባል ብቻ ያ ሁሉ ብዙ የተባለለትን ቀዉስ ማቃለል ተገቢ አልመሰለኝም፡፡መንግስት በሀገሪቱ ህዝብ ላይ ከደረሰዉ ጉዳት ይልቅ የመንግስትን ገጽታ መገንባቱን የመረጠ ይመስላል፡፡ መንግስት ምን እንደሚፈልግ ምን ለማለት እንደፈለገ ለመረዳት ተቸግረናል፡፡

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በቁጥጥር ስር ለማድረግ ያስገደደና ኩሁሉም በላይ ደግሞ አስቸኳይ ግዜ አዋጅ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነን ቀዉስ አቅሎ ለማየት የተሞከረበት አግባብ ልገባኝ አልቻለም፡፡ በዚያ በጭንቅ ወቅት የምንይዘዉና የምንጨብጠዉ ጠፍቶን ግራ ተጋብተን እንዳልቆየን አሁን ነገሮች ሲረጋጉ ችግሩን ለማሳነስ መሞከራችን ተገቢ አይደለም፡፡ መከላከያ ሰራዊታችን ከአንዱ የሀገሪቱ ጫፍ ወደ ሌላዉ እየተወረወረ ከስንት የታጠቀ ነዉጠኛ ጋር የሞት ሽረት ሲያደርግ እንዳልነበር ለዚዉያም አስቸኳይ አዋጁ ገና ባልተነሳበት በሁኔታ ሰኣት  ችግሩን ለማቃለል መሞከራችን ትልቅ ስህተት ነዉ የሚመስለኝ፡፡

በሙሰኛና ዋልጌ ባለስልጣናት ጉዳይ ላይም የችግሩ ዋነኛ ተጠቂና ሰለባ ወደ ሆነዉ ወደ ህዝቡ የገፉ ነው የሚመስለዉ፡፡ ልክ እንደ ጵላጦስ “ከደሙ ንጹህ ነኝ!” የሚለዉን የደገሙት ይመስላል፡፡ ኢህአዴግ በዚያን ሰሞን በጥልቅ ተሃድሶ የነገረንን በጸጋ ተቀብለን አይዞህ በርታ ያልን ሰዎች ሳንቀር “ኢህአዴግ ማስመሰል እንጂ ቁርጠኝነት የለዉም“ እያሉ ሲዘባበቱ የነበሩ ተቃዋሚዎችን ከዚህ በኋላ ደፍረን መንቀፍ የምንችል አይመስለኝም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ ሁኔታቸዉ የተረዳነዉ ሙሰኞችን በተመለከተም ከዚህ ቀደም ጠንከር ያለ ኃይለ ቃል ሲጠቀሙ እንደነበር ለምናስታዉስ አሁን ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ ለዘብ ያለ ዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ መጠቀምን መምረጣቸዉ ያለነገር እንዳልሆነ መጠርጠራችን አይቀርም፡፡ ምናልባት ከዚህ በፊት ጠቆም ለማድረግ እንደሞከርነዉ ከጀርባቸዉ ሌላ መቋቋም የማይችሉት ስዉር እጅ አላላዉስ ብሏቸዉ ሊሆን ይችላል፡፡ መቼም የመክሲኮንና የጣሊያንንና የኮሎምቢያን ማፊያዎች  ታሪክ ላነበብንና በሩሲያ ከመንግስት ታጣቂዎች ያልተናነሰ ጉልበት ያላቸዉ በዝርፊያ የደለቡ አደገኛ ቡድኖች መኖርን ጠንቅቀን ለምናዉቅ ሰዎች “ከፈጣሪ በስተቀር ለማንም አይፈሩም” የተባለላቸዉን ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያለመክንያት እንደዚህ ወደ ኋላ መንሸራተት እንዳልጀመሩ መጠርጠራችን አልቀረም፡፡፡ በሳቸዉ ትልቅ ተስፋ ጥለን ለነበርን ዜጎች ተስፋችን እንዲጨልም እየሆነ ነዉ፡፡

ከሰሞኑም የዛሚ ኤፍ ሬዲዮ  በጋዜጠኞች በክብ ጠረጰዛ ዉይይት ፕሮግራማቸዉ ላይም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰሞኑ ሁኔታ እንዳላማረቸዉና ተስፋቸዉን የሚያጨልም እንደሆነ  በቁጭት ሲገልጹ የሰማሁ ይመስለኛል፡፡ መንግስትም ሆነ በግላቸዉ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አላላዉስ ያላቸዉን እንቀፋት ፍርጥርጥ አድርገዉ ለህዝባቸዉ በይፋ ቢገልጹለት ህዝብ መፍትሄ ያጣለታል ብዬ አላሰብም፡፡ እኔ በበኩሌ በግሌ በሳቸዉ ላይ ያለኝ አመኔታ አሁንም ከፍተኛ ነዉ፡፡ ከዚህ ቀደም በአንድ መጣጥፌ እንደገለጽኩት አቶ ኃይለማርያምን ወደ ኃላ የሚጎትታቸዉ የግል ድክመት ይኖርባቸዋል ብዬ አላስብም፡፡ ይህ ግምቴ ትክክል ከሆነ ከአቶ ኃይለማርያም የሚጠበቀዉ ሙሰኛን ማሽኮርመም ሳይሆን መኮርኮም ነዉ፡፡ ከዚያ ዉጭ ግን ለሌባና ዘራፊዎች ከለላ የሚሰጡ ከሆነና እኝህ ዘራፊዎች የሰረቁትን ሃብት ከሀገር እንዲያሸሹና እንዲደብቁ ግዜ የሚሰጡዋቸዉ ከሆነ የመጀመሪያ ተጠያቂ የሚሆኑት ራሳቸዉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸዉ፡፡ ስለዚህ ተነሳሽነቱም አቅሙም አለኝ ካሉ ነገ ዛሬ ሳይሉ ጠበቅ ያለ እርምጃ መዉሰድ መጀመር አለባቸዉ፡፡ ይሄን ማድረግ የማይችሉበት በቂ ምክንያት ካላቸዉ  በተለይም እንደጠረጠርነዉ ከጀርባ ጫና የሚደርግባቸዉ ሌላ ኃይል ካለ በግልጽ ተናግረዉ የሰለጠነዉ ዓለም እንደሚደርገዉ መንግስታቸዉን እንዳለ ማፍረስ ወይም በግላቸዉ ስልጣን መልቀቅ ካልሆነም ከምሁራኑና ከተቃዋሚዎች ሲቀርብ እንደነበረዉ ብሄራዊ መግባባት የሚባለዉን ማድረግና የሽግግር መንግስት  መመስረት ነዉ፡፤

አቶ ኃይለማርያም ብቻቸዉን እንደሆኑ አድርገዉ መቁጠር አልነበረባቸዉም፡፡ሁሉም የኢህአደግ አመራርም በጅምላ አንዱም ከሌላዉ ሳይለይ ሌባ እንደሆነ አድርገዉ መቁጠርም የለባቸዉም፡፡ ዛሬም ድረስ ህዝባዊ ተቆርቋሪነት ያልተለያቸዉ ብዙ ነባር የድርጅቱ አመራሮች አሉና፡፡ ጸረ ሙስና ኮሚሽን የሚባለዉም ተቋም እንቅፋት ባይበረታበት ኖሮ ብዙ ሊሰራ ይችል የነበረ ነዉ፡፡በቀጥታ በሳቸዉ የሚታዘዝ የታጠቀ ኃይልም አላጡም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ ከጎናቸዉ ለመቆም ወደ ኃላ አላለም፡፡ ታዲያ ይሄ ሁሉ የለዉጥ ኃይል ከጎናቸዉ ማሰለፍ እየቻሉ ለምንድነዉ ማመንታትና ወደ ኋላ መንሸራተት የታየባቸዉ? አቶ ኃይለማርያም ይህን ታሪካዊ አጋጣሚ በሚገባ በመጠቀም የማያልፍ ስም ማትረፍ አለባቸዉ፡፡ ከሳቸዉ በፊት የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ለምድር ለሰማይ የከበደ ክብር ለማትረፍ የበቁት እጅግ በርካታ ፈተናዎች በማለፍና ሀገሪቱንም ከወደቀችበት አዘቅጥ አዉጥተዉ ከፍታ ቦታ ላይ ሲላደረሷት ነዉ፡፤አቶ መለስም እጅግ ሲማረሩበት የነበረዉና  የጀመሩትን ትግል ከዳር ሳያደርሱ ያለፉበት ትልቅ ሸክም ቢኖር ሙስና ነዉ፡፡ ዛሬ አቶ ኃይለማርያም ይህ ትልቅ ሸክም በሳቸዉ ጫንቃ ላይ ወድቋል፡፡ ከአቶ መለስ ያልተናነሰ ክብር የሚያገኙበትም አንድ ብቸኛ እድል ቢኖር ሙስናን ከምድረ ኢትዮጵያ ጠራርገዉ በማጥፋት ህዝቡን ሲገላግሉት ብቻ ነዉ፡፡ ከፈለጉ ማድረግ ይችላሉ፡፡የሚያስፈልገዉ ትንሽ ለመስዋእትነት መቁረጥ ብቻ ነዉ፡፡ ይሄን የምንል አንዳንድ ሰዎች ከድርጅትና ከመንግስትም በላይ የሀገሪቱ ጉዳይ ስለሚያሳሳበን ነዉ፡፡ አፍጦ የሚታየዉን አደጋ በመሸሸግም ሆነ አሳንሶ በማዬት ከአደጋ ማምለጥ አይቻልም፡፡ ማናኛችንም ብንሆን ሟርተኛ መባል አንፈልግም ነገር ግን በህዝብ ላይየተጋረጠ ችግር እያየን ዝም ማለትም አንሻም፡፡

ማጠቃለያ

ዛሬ በሀገራችን የተንሰራፋዉ ሙስና ከሽብርተኝነትም በላይ እያሰጋን ነዉ፡፡ስጋታችን ተገቢ ያደረገዉም ዘራፊ ሙሰኛን ለመታገል መንግስታችን ወገቤን ማለቱን ስናይ ነዉ፡፡ ሙሰኛና ዘራፊን እሽሩሩ እያልን ስለልማት ማዉራት አንችልም፡፡ በሌላ በኩል ሙስናን በመታገል ትልቅ አቅም ሊሆነን ይችል የነበረዉን ነጻ ሚዲያ አለመኖር ስጋታችንን የከፋ አድርጎታል፡፡ የመረጃ ነጻነት በሌለበት ስለዲሞክራሲ ማሰብ አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ትእግስቱ ሲያልቅ ምን ማድረግ እንደሚችል የቅርብ ግዜዉ ክስተት ጥሩ ማሳያ ነዉ፡፡ የህዝብን ጥያቄ በቁርጠኝነት መመለስ የሚችል ቆራጥ የሆነ አመራር ያሻናል፡፡ አሁን ያለዉ አመራር ተስፋ እንዳደረግነዉ አልሆን ብሎናል፡፡ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ ወደ ኋላ መመልከት አይቻልምና አቅሙ አለኝ የሚል ሰርቶ ሊያሳየን ይገባል ካልሆነ ደግሞ ከአቅሜ በላይ ነዉ የሚል ከሆነ  ቦታዉን ለብርቱዎቹ መለቀቅ ነዉ የሚገባዉ፡፡

******* 

የኮ/አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሌሎች ጽሑፎች ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፡፡

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories