«ህዝቡ አዕምሮውን እየሰለቡ ሌላ ነገር እንዳያስብ የሚያደርጉት የራሱ ልጆች ናቸው» አቦይ ስብሃት ነጋ

Highlights:-

* ‹‹በእኔ ግምት በዝግጅት ደረጃ እንጂ የተሰራ ነገር የለም ነው የምለው፡፡ ድክመቶቻችንን የመለየት ስራ ተሰራ እንጂ ለማስወገድ የተጀመረ ስራ የለም፡፡ ዝግጅት እንዳለ ግን እገነዘባለሁ፡፡ ለማስወገድ የተሰራ ነገር ግን የለም፡፡››

* ‹‹እኔ የምጠይቀው የህዝቡን ትዕግስት ነው። ኢህአዴግም ጊዜ ሳያጠፋ ችግሮቹን እየበጣጠሰ መሄድ አለበት።  በሁለት አመት እና በሶስት አመትም የሚያልቅ አይመስለኝም፡፡››

* ‹‹ለእኔ ብሄራዊ መግባባት ያለ አይመስለኝም። አሁን ላይ ያለው ትምክህት፣ ጠባብነትና እና አክራሪነት ነው።››

* ‹‹በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ኢህአዴግ በተማረ ሀይል የተደራጀ የለም፡፡ የቀበሌ አመራር እንኳን ዲፕሎማ የሌለው የለም፤ የወረዳ ካቢኔም ዲግሪ የሌለው ሰው ያለ አይመስለኝም፤ የክልል ካቢኔም እንደዚያው። የፌዴራል ካቢኔውም በሙሉ የተማሩ ነበሩ።››

* ‹‹እንዴት ይሄዳል? መቼ ይጀምራል? ከማን ይጀምራል? የሚለው ጥያቄ ነው ያለኝ እንጅ ኢህአዴግ ታጥቆ የተነሳበት ቀጣፊውን በቀጠፈውና ባጠፋው መጠን የሚቀጣበት፤ ይሄ ተቻችሎ መሄድ የሚያበቃበት ስርአትን ለመገንባት ቆርጧል።››

* ‹‹ስለዚህ ለሰው ታስቦ ሀገር የሚካድበት ሁኔታ የለም፡፡ ለግለሰቦችም ተብሎ ተቻችሎ መሄድ የኢህአዴግ ቁመና እንዳልሆነ ነው የእኔ ግንዛቤ፡፡››

* ‹‹ኢህአዴግ ለግለሰቦች ሲል ህዝቡን ይከዳል የሚል እምነት የለኝም፡፡ … ኢህአዴግ ሕዝቡ የሚጠብቀውን ጉዳይ ወደኋላ ይላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይሄን ካላደረገ ህዝብን መክዳት ነው፡፡ ሀገር ማፍረስ ነው፡፡››

* ‹‹ኢትዮጵያ እንደ አዲስ ራሷን ሆና ራሷን የምትጠቅምና ከአካባቢዋም አልፎ ለዓለም የምትጠቅም ሀገር ትሆናለች፡፡ ጊዜ የማያመልጣት ሀገር ትሆናለች፡፡ ጠላትን የምታሳፍር፤ ተጠቅማ የምትጠቅም ሀገር ትሆናለች፡፡››

—–

አንጋፋው የኢህአዴግ ታጋይና የህወሓት መስራች አቶ ስብሀት ነጋ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ቁልፍ ድርሻ ካላቸው ግለሰቦች መካከል አንዱና ዋነኛው ናቸው። ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ ሙሉ ቃለ መጠይቁንም እንደ ወረደ አቅርበነዋል።                      

አዲስ ዘመን፡- ከኢህአዴግ ታላላቅ ሰዎች መካከል እንደ እርስዎ በብዙ ሚዲያዎች ላይ አስተያየት በመስጠትና በመጻፍ የሚታወቅ ያለ አይመስለኝም። አሁን ከዚያ እርቀዋል ምክንያቱ ምንድነው?

አቦይ ስብሃት፡- ማንም ሰው በሚዲያ እንዳይነጋገር የተከለከለበት ነገር የለም። እዳልከው ግን አሁን ላይ ረዘም ላለ ጊዜ ከሚዲያ እርቄያለሁ፡፡ ኢህአዴግ ስህተቶቹን አስቀምጦ ገበያ ወጥቶ እኔ የምፈልገውን ነገር እየተናገረ ነው። ስለዚህ የእኔ መናገር አያስፈልግም። ለዚያ ነው ከሚዲያ የራቅኩት፡፡

አዲስ ዘመን፡- አሁን  አገራችን የገባችበት ጉዳይ ሁሉም የሚያዉቀው ነው፡፡ የዚህ ችግር መንስኤ በእርሶ ድምዳሜ ምንድን ነው ይላሉ?

አቦይ ስብሃት፡- መንስኤውም ሆኑ ችግሮቹ ተገልጸዋል። ኢህአዴግ ለዚህ ተጠያቂ እኔ ነኝ ብሏል፡፡ ኢህአዴግ ለቆመለት አላማ ህዝብንና ሀገርን ማዕከል አድርጎ  እራሱን እየፈተሸ  አልሄደም፡፡በአንድ ቃል የህዝባዊነት መንፈስ እና ውግንና ላይ ስንፈት ነበር፡፡ ድርጅቱ ሌት ከቀን አልሰራም፤ ይሄንንም እራሱ ለይቶ አስቀምጦታል፡፡

አዲስ ዘመን፡- አቦይ ይህ ችግር የድርጅቱ ወይስ የግለሰቦች? 

አቦይ ስብሀት፡-  በግለሰብ ወይንም ደግሞ በቡድን ስህተት ከተገኝ ኢህአዴግ ይጠየቃል። ምክንያቱም ድክመት ያሳየው ግለሰብ መወገድ ነበረበት፡፡ ዋናው ተጠያቂ ኢህአዴግ ሆኖ ግለሰቡም ተጠያቂ ይሆናል። ድክመቱ የግለሰብ፣ የሁለት ሰው፣  የአራት ሰው የምትለው አይደለም፤ በአጠቃላይ ችግሩ የኢህአዴግ ድክመት ነው፡፡ አንድ ሰው ድክመት ሲያሳይ ሁለት ሶስት ቀን መቆየት የለበትም፡፡ ስርአቱ፣ አሰራሩና አደረጃጀቱ በየጊዜው የሚለካ መሆን አለበት፡፡

Photo - Sebhat Nega, EPRDF and TPLF veteran
Photo – Sebhat Nega, EPRDF and TPLF veteran

አዲስ ዘመን፡- በተቃራኒው  ሀገሪቷ ለገባችበት ወቅታዊ ችግር ምክንያቱ የፌደራሊዝም ስርአቱ  ነው የሚሉ አሉ፡፡ እዚህ ላይ ምንድን ነው የእርስዎ ሀሳብ?

አቦይ ስብሃት፡- ፌዴራሊዝሙ በባህሪው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን ማዕከል  አድርጎ የተዋቀረ ነው፡፡ ይሄ  ህዝቡ እራሱ ፈልጎ ለዘመናት ታግሎ ያመጣው እና የህብረተሰብ ዲሞክራሲ መሰረት ነው፡፡ ይሄ ስርአቱን ያጠናክራል፣ በእኩልነት የተመሰረተ አንድነት ይፈጥራል፣ ህዝብን ነፃ አድርጎ ለመንቀሳቀስ  እድል ይፈጥራል እንጂ ለግጭትም ይሁን ለሌላ ችግር በር የሚከፍት  አይደለም፡፡ ህዝቡ ሲፈልገውና ሲታገልለት የነበረ ስርዓት ነው የተዋቀረው፡፡ የኦሮሞም በለው የሲዳማ ነጻ አውጪ ግንባር ፕሮግራም ይኑረውም አይኑረው ሲታገልለት የነበረው ይሄንን አይነት ስርዓት ለማዋቀር ነው፡፡ ፌደራሊዚሙም ይህንን ነው ያረጋገጠው፡፡ ስለዚህ ፌዴራሊዝሙ ፀጋ ነው እንጂ ጉድለት የሚፈጥር፣ ለጉድለት በር የሚከፍት አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፡- እንግዲያውስ  ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ እንዳስቀመጠው የችግሩ መንስኤ ራሱ መንግስት የፈጠረው የመልካም አስተዳደርና የውስጥ አሰራር ችግር ነው በሚለው ነው የሚስማሙት ማለት ነው፡፡ እንደዛ ከሆነ ለችግሩ መፍትሄ ሆኖ የቀረበው ተሀድሶ ማድረግ፤  በጥልቅ መታደስ የሚል ነው። ሀገራችን ከገባችበት ችግር አንፃር ተሀድሶ መፍትሄ ይሆናል ብለው ያምናሉ?

አቦይ ስብሃት፡- አዎን። በ1993 እና 1997 ዓ.ም ላይ ችግሮች ነበሩ፡፡ ያን ጊዜ ችግሮቹን አሟጠን ህዝቡን አሰልፈን ቢሆን ኖሮ አሁን ተሀድሶ ውስጥ መግባት አይጠበቀብንም ነበር። ራሱን እያስተካከለ የሚሄድ፣ ሁሉንም ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርዓት ገንብተንም ቢሆን ኖሮ ወደ ተሀድሶ መግባት አይጠበቅብንም ነበር፡፡ ለ15 አመት የተጠራቀሙ ችግሮች ናቸው ወደዚህ ያስገቡን። በጥልቀት መታደስ ማለት እኔ እንደሚገባኝ ከእንግዲህ ወዲህ ተሀድሶ የሚባል ነገር የለም ማለት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እንደ ኢህአዴግ ተመልሳችሁ ወደ ተሀድሶ ላለመግባታችሁ ምን ዋስትና አለ? ምክንያቱም ከ15 አመት በፊትም ተሀድሶ ተካሂዷል?

አቦይ ስብሃት፡-  ወደ ተሀድሶ ተመልሰን ላለመግባታችን መቶ በመቶ ዋስትናችን ህዝቡ ነው፡፡ ህዝቡ በልማት፣ በሰላምና በዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ ይፈልጋል፡፡ ኢህአዴግ ችግር የለብኝም ብሎ አያውቅም። ዋና ዋስትናችን ህዝቡ ነው፤ ኢህአዴግ ደግሞ ህዝብን ማሰለፍ ይችልበታል፡፡ ሌላ ዋስታና የለንም። ህዝቡ ስል ጥራት ያለው ካድሬንና አመራርንም ይጨምራል፡፡ ኢህአዴግ ህዝቡን ይዞ በማያዳግም መልኩ ችግሮች መፍታት አማራጭ የለውም፡፡ እተማመናለሁ ይሄን ያደርገዋል፡፡ ይሄ ካልተደረገ ግን በአንድ ሀገር ተሰባስቦ የመኖር ነገር አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘን፡- እርስዎም እዳሉት ኢህአዴግም ህዝቡን በያዘበት በትግሉ ዘመን ተፈቃሪና ተወዳጅ ፓርቲ ነበር የሚሉ አሉ፡፡ በራሱ ነፃ ግዛቶች ላይም ፍትህን በማስፈን ደረጃ በጣም የተዋጣለት ፓርቲ ነበር፡፡ መንግስት ከሆነ በኋላ ግን ያንን መድገም አልቻለም።  የህዝብ ቅራኔና ተቃውሞ ተነስቶበታል፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው? በፊት የነበረውን ህዝባዊነት ለማምጣት ምን መሰራት አለበት ይላሉ?

አቦይ ስብሃት፡- እንዳልከው በትጥቅ ትግሉ ያሸነፈው ብረት አይደለም።  ያሸነፈው ብረት እንዲመጣም ያደረገው የሕዝቡ መንቃት፣ መደራጀት እና ማስታጠቅ ነበር፡፡ ህዝቡን በአግባቡ ማንቃት፣ ማስታጠቅ፣ ማሰማራት፣ መንግስትንም እንዲቆጣጠር ማስቻል አሁን ላይ ቀንሷል፡፡ ጫካ እያለህና ከተማ ከገባህ በኋላ ነገሮች እኩል አይደሉም፡፡ ከተማ ብዙ የሚያዳክምና የሚያታልል ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ሙስና ላይ  ሁኔታውን የሚመጥን ትግል አልተደረገም፡፡ ህዝባዊነትን የሚፈታተነው ግላዊነት ነው፡፡ ለግለኝነት አመቺ ሁኔታ ያለው ደግሞ ከተማ ነው፡፡ ከተማ ውስጥ ይሄንን ሁኔታ ተገንዝቦ ይሄንን የሚመጥን የፖለቲካ ትግል አልነበረም፡፡ ኢህአዴግ መንግስት ከሆነ በኋላ ያንን የሚመጥን ትግል አላዳረገም፡፡ ግለኝነት ህዝባዊነትን ተፈታተነው፡፡ ለህዝባዊነትና ሀገራዊነት የሚመጥን ትግል ነው መደረግ ያለበት። ትግሉም ተቋማዊ ሆኖ መሄድ አለበት፡፡ አሁንም ሁኔታውን የሚመጥን ትግል መደረግ አለበት፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢህአዴግ  በታሪኩ የገጠመው ትልቁ ፈተና አሁን ያጋጣመው ነው ማለት እንችላለን? በኢህአዴግ ዘመን እንደ አሁኑም ኢትዮጵያ ከዳር ዳር ሰላሟ ተናግቶ አላየንም።

አቦይ ስብሃት፡-  አሁን ያለንበት ሁኔታ ፈታኝ ነው፡፡ አሁን የተፈጠረ ሳይሆን እየተጠራቀመ የመጣ ነው፡፡ አሁን እሱን ይዘን  የማንቀጥልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ እንዳልከው በኢትዮጵያ የሠላም ማጣት ይኖራል የሚል ግምት አልነበረም፡፡ ክልሎቻችንን የምናስተዳድርበት የሠላም ማጣት ይኖራል የሚል ግምት በውስጥም በውጭም አልነበረም። በኢህአዴግ ታሪክ ይሄ አይነት ችግር የመጀመሪያው ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከምርጫ 97 በኋላ ተነስቶ ከነበረው ሁከት ጋር ሲነፃፀር ከባዱ የትኛው ነው? ለስርአቱስ አደገኛ የነበረው የትኛው ነው?

አቦይ ስብሃት፡-  ያንጊዜ የነበረው ይሄን ያህል ስፋት አልነበረውም፡፡ በልማቱና በሌሎች ነገሮች ያለመርካት፤ በከተሞች በተለይም በወጣቶች ላይ ነበር። ያም ሆኖ ሁከቱን የቀሰቀሱት ተቃዋሚ ፓርቲዎች  ነበሩ፡፡ የ1993ቱም የውስጥ ችግር ነው፡፡ ስለዚህ ከዘጠና ሰባቱ የአሁኑ ይከፋል፤ ውስብስብም ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እውነት ነው ፡፡ ያኔ ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅም አልገባንም  ነበር፡፡ ምን አልባት ኢህዴግን ጠንካራ ፓርቲ የሚያስብለው 1997ዓ.ም ላይ ያንን ያህል የህዝብ ተቀባይነትን አጥቶ /በተለይ በከተሞች/ በምርጫ 2002ዓ.ም ላይ መልሶ ያንን የህዝብ ይሁንታ ማግኘቱ ነው የሚሉ አሉ። ከዚህ ተነስተን አሁንም ያስኮረፈውን ህዝብ ልብ መልሶ የማግኘት ተስፋ አለው ማለት እንችላለን?

አቦይ ስብሃት፡-ኢህአዴግ ማህበራዊ መሰረቶች አሉት። ሙሁሩ፣ ገበሬው እና ወዛደሩ የፓርቲው መሰረቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህን መሰረቶቹን አደራጅቶ ወደስራ እንደሚገባና   ወደግራ ወደቀኝ ወደማይልበት ደረጃ እንደሚደርስ አምናለሁ፡፡ አንተ እንዳልከው ሳይሆን ካልከውም በላይ ካሁን በፊት ወዳልነበረበት ጥንካሬ እንደሚመጣ መቶ በመቶ እተማመናለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢህአዴግን  በቅርብ  የሚያውቁ ሰዎች “የኢህዴግ ድርጅታዊው ጉባኤው ብዙም ጠንካራ አይደለም ብሄራዊ ድርጅቶቹ ያሉበትን ሁኔታ የሚፈትሽ አይደለምተቻችሎ የማለፍ ነገር ነግሷል። ማሳያው 10ኛው የኢህዴግ ድርጅታውዊ ጉባኤ በተካሄደ በወራት ውስጥ በአማራ በኦሮሚያ ክልል ህዝቡ ለተቃውሞ አደባባይ መውጣቱ ነው”  ይላሉ። የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ መፈተሽ የለበትም ይላሉ?

አቦይ ስብሃት፡- ይሄ ያልከው ትክክል ነው፡፡ ተቻችሎ መኖር፣ ህዝባዊነት መሸርሸር እና ነገሮችን አስቀድሞ ያለማየት ችግር አለ፡፡ ኢህአዴግም የእያንዳንዱን አባል ድርጅት በአጠቃላይ ደግሞ የኢህአዴግ ጉባኤ መፈተሽ እንዳለበትና የሚፈትሹት መሆኑንም ነው እኔ የምገምተው፡፡ አንድ አጀንዳ ሆኖም እንደሚፈትሹ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ መፈተሸ አለበት? አዎ መፈተሸ አለበት። ያለፈውም መገምገም አለበት፡፡  ይሆናል ወይ? እንደሚሆን ነው የምገምተው፡፡ ይሄ አቋሜ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርሶ ጋር የድሮው የትግል መንፈስ አለ ብዬ ስለማምን በትክክል ጉባኤው ምን አይነት ቢሆን ብለው እንደሚመኙ እንዲነግሩኝ እፈልጋለሁ።

አቦይ ስብሃት፡-  በጉባኤው ዋዜማ ላይ በአጀዳዎቹ ላይ ጉባኤተኛውና አባሉ ሁሉ ቢወያይበት፣ በሁለተኛ ደረጃ ጉባኤተኛው አመራሮቹን ምን እንደሆኑ በደንብ የሚያውቅበት ቢሆን፡፡ ሶስተኛ ደግሞ የአምስት እና የአስር አመት ፖለሲና ስትራቴጂ አሰቀድሞ የሚመለከት ጉባኤ ቢሆን እመርጣለሁ።

አዲሰ ዘመን፡- ጥሩ በጉባኤው አዳራሽ ውስጥ ያለው መንፈስ ምን መምሰል አለበት? በቀደመው ዘመን የኢህአዴግ የመታገል መንፈሱ እና አንተ እንደዚህ ነህ አንተ እንደዚያ ነህ የመባባሉ ነገር በጣም ጠንካራ እንደነበር ይነገራል። በሂደት ግን ይሄ ነገር እየጠፋ ነው የሚባል ትችት ይቀርባል። በዚህ ዙሪያ ምን ይላሉ?

አቦይ ስብሃት፡- ያለምንም ምህረት ማን ምንድነው የሚለው ነገር በደንብ መታወቅ አለበት።

አዲስ ዘመን፡- በጉባኤው ላይ ብሄራዊ ድርጅቶች በሪፖርታቸው ትክክለኛውን ገፅታቸውን ያቀርባሉ? ይሄንን ልጠይቅ የቻልኩት በ10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ድርጅቶቹ ህዝቡ ኢህዴግ ብቻ ነው ያለኝ የሚል አይነት ሪፖርት ባቀረቡ በወራት ውስጥ  ነው በአማራም ይሁን በኦሮሚያ የተፈጠረው ሁሉ ሁከት የተፈጠረው። እንዲያው ይሄንን ሲያዩ የሚቀርበው ሪፖርት የውሸት ነገርም ያለበት አይመስልዎትም? ይሄ የእኔ ድምዳሜ ነው። የእርስዎስ?

አቦይ ስብሃት፡-  የእኔም ድምዳሜ እንደሱ ነው፡፡ ይሄን አምኖ የሚመጣ ጉባኤ መሆን አለበት፡፡ ጉባኤ መደምደሚያ ነው፡፡ በጉባኤው ዋዜማ ይህን እያመነ የሚመጣ ጉባኤተኛ መሆን አለበት፡፡  የተደነቀሩብን  ችግሮች በአንድ ላይ ችግሮቻችን ለመቅረፍ ይቅርና በአንድ ላይ ለመሆንም አያስችሉንም። እንደ ኢትዮጵያ በአንድ ላይ ለመኖር የማያስችለንን በሽታ ተሸክመናል ብለው የሚያምኑ ድርጅቶች መሆን አለባቸው፡፡ ጉባኤው ህዝቡን ማዕከል አድርጎ በዲሞክራሲያዊ እኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት የሚፈጥር መሆን መቻል አለበት፡፡ ይሄ ብቸኛው ኢትዮጵያን አንድ አድርገን የምንሄድበት መንገድ ነው። እያንዳንዱ ጉባኤተኛና አባል ድርጅት በዚህ መንፈስ መንቀሳቀስ አለበት። እንዲያውም የኢህአዴግ አጋሮች ይሻላሉ፡፡ ሁላችንም አጋር ሆነናል። ስለዚህ ያለፈው ጉባኤም መገምገም አለበት፡፡

አዲስ ዘመን፡-  ወደ ሌላ ጉዳይ ልውሰድዎ፤ የስርዓቱ አደጋ ተብለው  የተለዩትን ትምክህት፣ ጠባብነትና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማክሰም  መንግስት እየተጓዘበት ያለው መንገድና ስልት ምን ያህል አስተማማኝ ነው ብለው ያምናሉ? በቀጣይስ ምን መሰራት አለበት ይላሉ?

አቦይ ስብሃት፡-  በእኔ ግምት በዝግጅት ደረጃ እንጂ የተሰራ ነገር የለም ነው የምለው፡፡ ድክመቶቻችንን የመለየት ስራ ተሰራ እንጂ ለማስወገድ የተጀመረ ስራ የለም፡፡ ዝግጅት እንዳለ ግን እገነዘባለሁ፡፡ ለማስወገድ የተሰራ ነገር ግን የለም፡፡ እነዚህ ተለይተው የተቀመጡ ሀጢያቶች ለሁሉም ነገር ዳገት ናቸው፡፡ እነዚህን ለማስወገድ  ሂስ ያደረገና በዝግጅት ላይ ያለ ድርጅት እንዳለ እገነዘባለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ይሄን ያህል አመት በዝግጅት ላይ ማለት ይቻላል?

አቦይ ስብሃት፡-  ምንድን ነው መሰለህ፤ አሁን ያለው ችግር ጠባብነትና ትምክህት በሁለት ወር ወይንም በሶስት ወር ይወገዳል የሚባል አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ተሀድሶ የጀመረው ነሀሴ ይመስለኛል፡፡ ይሄ የችግሩን ምንነት፣ ስፋት እና መጠን አጥንቶ የማን ፖለቲካ እንደሆነ ወ.ዘ.ተ ለመለየት ቀጣይነት ያለው ስራ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ኢህአዴግ በጥለቀት መታደስ ጀምሯል። ይሄ አዋጅ አይደለም፤ ሂደት ነው፡፡ ይሄ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? ጊዜ ላስቀምጥ አልችልም፡፡ ጊዜ ይፈጃል።

ሳይነካ የቆየ አመለካከት ነው። ጉዳዩ እራሱ ገፍቶ ስለመጣ ኢህአዴግ ችግሮቹን አንድ ሁለት ብሎ ለይቶ አስቀምጧል፡፡ በጥልቀት መታደስ ማለት ችግሩን በጥልቀት መረዳት ማለት ነው፡፡ ይሄን ሳንፈታ ዴሞክራሲያዊት አገር መፍጠር አንችልም፡፡ እኔ የምጠይቀው የህዝቡን ትዕግስት ነው። ኢህአዴግም ጊዜ ሳያጠፋ ችግሮቹን እየበጣጠሰ መሄድ አለበት።  በሁለት አመት እና በሶስት አመትም የሚያልቅ አይመስለኝም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ እነዚህ ችግሮች አብረውን ይቀጥላሉ ማነት ነው?

አቦይ ስብሃት፡- እየተቃለሉ እየተቃለሉ አደጋነታቸውም እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ የስርአቱ ዋና አደጋ መሆናቸውም እየተዳከሙ ይሄዳሉ፡፡ መታወቅ ያለበት ህዝብ ህዝብን እንደማይጨቁን ነው። ይህን የሚያመጣው ስርአቱና አንተ ትበልጣለህ የሚሉ ግለሰቦች ናቸው። በቀደመው ጊዜም ይሁን አሁን አንተ ትበልጣለህ የሚል እና ስርአቱ ያመጣብን ጣጣ ነበረ። ይሄን ታሪክ ህዝቡ ማመን አለበት፡፡ አሁን ግን ይሄን የሚያስተናግድ በር የለም፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ የበላይነቱን የሚያረጋግጥ ስርአት የለም፡፡ ኢህአዴግ ይሄንን ሳልፈታ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት የለም ብሎ ያመነ ስለሆነ እንደሚፈታው እርግጠኛ ነኝ፡፡ መፈታቱ ግን ጊዜ እንደሚፈጅ፤ በጥልቀት መታደስም ይሄንን ችግር በጥልቀት መረዳትንም ይጨምራል።

በዚህ አስተሳሳብ ለመኖር የሚፈልጉ ፓርቲዎችም ሌቦችም አሉ። የእኛ የውስጥ ሌቦችም መደበቂያቸው ይሄ ነው። በአጭሩ እነዚህን አስተሳሰሰቦች እያሸነፉ መሄድ ያስፈልጋል። ሰልፍ ማለት ጠላትህን እያስወገድክ ወዳጅህን የምትሰበስበበት ነው፡፡ ህዝብ ህዝብን አይጨቁንም፤ አይበድልም፤ አይጠላም፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርስዎም እንዳሉት ዛሬ አንዱ በአንዱ ላይ የበላይ የሚሆንበት እድል ዝግ ነው። ስለሆነም አማራ ክልል ላለው ህዝብ መጨቆንና መበደል ተጠያቂው ብአዴን፤ ለኦሮሚያው በደልም ኦህዴድ፤ ለትግራዩም ህወሓት፤ ለደቡብ ህዝብ በደል ደግሞ ደኢህዴን፡፡ እውነታው ይሄ ቢሆንም አሁን በጥልቀት መታደሱ ላይ በየብሄራዊ ድርጅቶች ላይ የህወሓት የበላይነት  አለ፤ ለችግሮቹ ተጠይቂው  ህወሓት ነው የሚሉ ሀሳቦች እየተደመጡ ነው፡፡ እዚህ ላይ የእርስዎ ሀሳብ ምንድነው አቦይ?

አቦይ ስብሃት፡-በአመለካከት ደረጃ ከሆነ ዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን የማስፈኑ ስራ የኢሀአዴግ አባል ድርጅቶች ነው፡፡ በአንድ ብሄር ጠባብነት ካለ ኢህአዴግ በመላው መጠየቅ አለበት፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ የሁሉም ድርጅቶች ነው፡፡ በትግራይ ትምክህት ካለ ኢህአዴግ መታገል አለበት፡፡ ሌላውም ጋር ትምክህትም ሆነ ጠባብነት ካለ ኢህአዴግ መታገል አለበት፡፡ ልማት የክልሉ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ፖለቲካው ግን ድንበር ያለው ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ጠባብነትንና  ትምክህትን መሰሉ ችግሮችን  አብረን መመከት አለብን፡፡ ይሄ በየትኛውም ብሄር ሲታይ መመከት መቻል አለብን፡፡  

አንተም እዳልከው ህዝቡ ማወቅ ያለበት አንዱ ብሄር ሌላውን ሊጨቁን ክፍት ቦታና እድሉ አለ ወይ? የሚለውን ነው። የትግራይ ህዝብ ኦሮሚያ ውስጥ የተሰበሰበን ገንዘብ ላኩልኝ ይላል ወይ? መሬቱን ላስተዳድር፣ ቋንቋዬን ባህሌን አስተምሩ ይላል ወይ? በምን አልፎ ነው አንድ ብሄር ይሄንን በሌላው ብሄር ላይ የሚያደርገው? ይሄ ዝም ብሎ ግንዛቤ ነው እንጂ በተጨባጭ የለም። ህዝቡ የለም ብሎ ማመን አለበት። ይሄ የሌቦች መደበቂያ ስልት ነው።

የሚቀጠቅጠው የሚዘርፈው እራሱ ሆኖ ሳለ እንትና ወሰደብህ ይላል። አንተን የመሰለ የለም እያለ እያደነዘዘ የሚዘርፈው እሱ እንደሆነ፤ ፍትህ የሚያጓድልበት የራሱ ልጆች እንደሆኑ፣ ብሄር ከብሄር ጋር የሚያጋጫው አንተን የሚመስል የለም እያለ የሚያቆረቁዘው ራሱ መሆኑን ማወቅ አለበት።

እኔ የትግራይ ህዝብን አንተን የመሰለ የለም ካልኩት ገድየዋለሁ ማለት ነው፤ ከእኔ በላይ ገዳይ የለውም፡፡ በመንግስት ላይ ባለፈው ስርዓት ባጉረመርም ውሸት፤ ዋናው ጠላቱ ካንተ በላይ የለም ያልኩት እኔ ነኝ። ህዝቡ ማወቅ ያለበት ይሄንን ነው። አዕምሮውን እየሰለቡ ሌላ ነገር እንዳያስብ የሚያደርጉት የራሱ ልጆች ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ የህዝቡ ጠላት አጠገቡ ያለው ነው እያሉኝ ነው?

አቦይ ስብሀት፡- ተራ ጠላትም ሳይሆን ከባድ ጠላት። አዕምሮህን ከሰለበህ ምን ታደርጋለህ አገርህ ቀኝ ግዛት ቢያዝብህ ነገ ታግለህ ነፃ ታወጣዋለህ። አዕምሮህን ከተያዝክ እኮ በድን ነህ። ምን አዲስ ነገር ልትቀበል አትችልም።  

አዲስ ዘመን፡- ወደሌላ  ርዕሰ  ጉዳይ  እንሂድ፤ ብሄራዊ መግባባት ተፈጥሯል ብለው የሚያምኑ እንዳሉ ሁሉ፤ እዚህም እዚያም የሚነሱ ጉዳዬችን በመጥቀስ ብሄራዊ መግባባት ቢፈጠር ኖሮ ይሄ ግጭት ባልተፈጠረ የሚሉ አሉ። እርስዎ ብሄራዊ መግባባት ላይ ተደርሶል ብለው ያምናሉ?

አቦይ ስብሃት፡- ብሔራዊ መግባባት የሚባለው ቃሉም ብዙ አይገባኝም። ቀደም ብለን የጠቀስነው የአስተሳሰብ ሰለባ ካለ ብሄራዊ መግባባት አይመጣም። ህገመንግስቱም በየብሄራችን ሆነን አንድ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማህበረሰብ እንፈጥራለን ነው የሚለው፡፡ ይሔ ደግሞ የሚፈጠረው  እያንዳንዱ ብሄር ለሌላው ብሄር በመሬቱ  የሚያስተናግድ ከሆነ ነው፡፡ የሶማሌ ሀብታም፣ የአማራ ሀብታም፣ የኦሮሞ ሃብታም፣ የትግራይ ሀብታም ሌሎቹም ሀብታሞች ወደሌላው ክልል ቢሄዱ ወገኖቼ ናቸው ብሎ መቀበልና እኩል ማየት አለ ወይ? እኔ አይመስለኝም። ካለ ግን ብሄራዊ መግባባቱ ተፈጥሮል ማለት ነው፡፡ በፕሮግራም ደረጃ ግን አለ። መግባባት በአየር ላይ የለም። የአንተ ትርጉም እንደሱ ከሆነ ለእኔ ብሄራዊ መግባባት ያለ አይመስለኝም። አሁን ላይ ያለው ትምክህት፣ ጠባብነትና እና አክራሪነት ነው። ብሔራዊ መግባባት በመሰረታዊነት ሁለት ነገሮች ላይ የተመሰረተ ነው። አደኛው አስተሳሰብ ሲሆን፡፡ ሁለተኛው ኢኮኖሚ ነው፡፡    

አዲሰ ዘመን፡- መንግስት ሀገሪቷ ከገባችበት ቀውስ ለመሻገር ከተሀድሶ ባሻገር ካቢኔውን በአዲስ መልክ ማዋቀር ነው፡፡ መስከረም 24ቀን 2008 ዓ.ም የተቆቆመው ካቢኔ በአመቱ ጥቅምት 22፣ 2009 ነው የፈረሰው፡፡ ያኛውም ተስፋ የተጣለበት ካቢኔ ተብሎ ነበር፡፡ የአሁኑ ካቢኔም በምሁራን  የተዋቀረ  ነው ተብሏል፡፡ እርስዎ በአዲሱ ካቢኔ አወቃቀር ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው? ለችግሩ ይሄ መፍትሄ ይሆናል ብለው ያምናሉ?

አቦይ ስብሃት፡- እኔ ስለ አዲሱ ካቢኔ አወቃቀር የራሴን አመለካከት ነው ልነግርህ የምችለው፡፡ ምክንያቱም በካቢኔው ማቋቋሙ አልነበርኩም።

አዲስ ዘመን፡- ላይኖሩ ይችላሉ፤ ግን የኢትዮጵያን ፖለቲካ ጥንቅቅ አድርገው ከሚያውቁና እንዲያውም የኢትዮጵያ ፖለቲካ አባት አድርጌ ከማያቸው ሰዎች መካከል አንዱ እርስዎ ነዎት፤ ብዙ ዘመንዎንም በፖለቲካው ላይ ነው ያሳለፉት፡፡ ስለዚህ ይሄ ካቢኔ ማየት የሚፈልጉትን አይነት ስርዓትና አገር ለመፍጠር ወደዚያ ይወስዳል?

አቦይ ስብሀት፡- እኔ ይሄንን በአጭሩና በግሌ ነው የምመልስልህ። አንድ ይሄ የካቢኔ ማፍረስ እና መገንባት ነው ወይ የተካሄደው? ሶስት ነገሮች አሉ፤ ለውጥ፣ ቀጣይነት፣ መሻሻልና መለወጥ የሚል። አንድ ስርአት እነዚህ ሳይዝ መቀጠል አይችልም። የአሁኑ ለውጥ ነው ወይ ለሚለው የካቢኔ ማሻሻያ ነው፡፡ አዲስ የተሾመው ነው የሚበዛው ነባሩ ነው ብትለኝ እውነቱን ለመናገር አላውቅም፡፡ ይሄ ለውጥ ያመጣል ወይ? ማስቀመጥ በራሱ ለውጥ አያመጣም። ማስቀመጥና በተቋሙ ተጠያቂ ማድረግ፤ ተቋማዊ ሆኖ ተጠያቂነት ያለበት ስርአት ፈጥረው ይሄዳሉ? ይሄንን መልሼ ነው የምጠይቅህ።

ተሿሚው ወደ ተቋሙ ሲሄድ ጥሩውን ማስቀጠል፤ መጥፎውን ማሸሻል ነው ወይንስ በጅምላ መርገም ነው የሚያስበው? ያላቸው አማርጭ ከሶስቱ አንዱን ማድረግ ነው፡፡ አንዳንዱ የነበረችውን ይዞ የሚቀጥል አለ፡፡ ሌላው ደግሞ የነበረውን ሙሉ ለሙሉ ደምስሶ በአዲስ የሚቀይር አለ፡፡ ሌላኛው ደግሞ የነበረውን እያሻሻለ የሚሄድ አለ፡፡ ጥያቄህን በትክክል መልሼ ከሆነ አላውቅም፡፡ እኔ የሚመስለኝ ግን የተደረገው የካቢኔ ማሻሻያ ነው እንጂ ለውጥ አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ካቢኔው በምሁራን የተዋቀረ ካቢኔ ነው ይባላል፡፡ በእርግጥ በኢህአዴግ ዘመን ኢትዮጵያ እደዚህ  አይነት በምሁራን የተዋቀረ ካቢኔ  አልነበራትም  ማለት ነው?  ይሄንን ሲሰሙ እርስዎ ምን  ይሰማዎታል?

አቦይ ስብሃት፡- እኔም አንተ እንደሰማሀው በምሁራን የተዋቀረ ካቢኔ ሲባል እሰማለሁ፡፡ በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ኢህአዴግ በተማረ ሀይል የተደራጀ የለም፡፡ የቀበሌ አመራር እንኳን ዲፕሎማ የሌለው የለም፤ የወረዳ ካቢኔም ዲግሪ የሌለው ሰው ያለ አይመስለኝም፤ የክልል ካቢኔም እንደዚያው። የፌዴራል ካቢኔውም በሙሉ የተማሩ ነበሩ። ቁጥራቸው ጨምሮ ሊሆን ይችላል። የወጡትም የተማሩ ናቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በዶክተሮች የሚለው ውሸት ነው፡፡ ቁጥራቸው ግን ጨምሮ ይሆናል። ትምህርት ግን በራሱ ፀጋ ነው የሚባለው ባሰላለፉ ነው፡፡ ያንን ትምህርት ተምሮ የሚያመርተው እውቀት ለማን ይጠቅማል? ትምህርት ደግሞ እዳ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ሆነው እኮ ያን የጨለማና የእልቂት ዘመን ይናፍቁታል፡፡ እና ትምህርት በራሱ ጥሩ ነው አይባልም፡፡  ጥሩ ነው የሚባለው ባሰላለፉ ነው፡፡ እና መታወቅ ያለበት ትምህርት እዳም ነው፤ ፀጋም ነው። ዋናው አሰላለፉ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከካቢኔው ጋር በተያያዘ አብዛኛው ወደ አመራር ውስጥ የገቡት በቁጥርም ካየነው መምህራንና ለፖለቲካው እንግዳ ናቸው። የኢህአዴግ ፖለቲካ ደግሞ ሲበዛ ጠንካራና ከባድ ነው፡፡ ፖለቲካ በራሱ መሰጠትን ይፈልጋል።  እነዚህ አዳዲስ የካቢኔ አባላት ፖለቲካው ገብቷቸው ወደ ስርዓቱ ቅኝት እስኪገቡ ድረስ ጊዜ ይወስዳል። ህዝቡ ደግሞ ከሚዲያውም ከፖለቲካውም ቀድሞ ሄዷል።  እና ይሄ ካቢኔ የማህበረሰቡን ጥያቄ በሚፈለገው ፍጥነት ይመልሳል ይላሉ?

አቦይ ስብሃት፡-  ሰው የነበረበት ሙያ መሀንዲስም ይሁን መምህር ማንነቱን አያሳውቅም፡፡ ዋናው ነገር ወገንተኝነቱ ነው። ሰው የሚፈጠረው በተቋም ነው፡፡  የፓርቲም ይሁን የትምህርት አሊያም የመንግስት ተቋም መሪውን ህዝባዊ መሪ አድርገው ይፈጥሩታል ወይ? ተቋሞቻችን መሪ ያፈራሉ ወይ? ይሄ ነው ዋናው ነገር።  

አዲስ ዘመን፡- የኢህዴግ ምክር ቤት ና የየድርጅቶቹ ማእከላዊ ኮሚቴ አካባቢ ያለመነካካት ነገር እንዳለ ይሰማኛል።  ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀር የመንግስትን ስልጣን ለግል የማዋል ዝንባሌ ተግባር ነገር አለ ብለው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ይሄ ነገር ተመንዝሮ እከሌ ይሄን አድርጓል እከሌ ይሄ ነው ጥፋቱ የሚል ነገር እስካሁን አልተሰማም፤ አልታየም። እዚህ ላይ ምን ይላሉ? ህዝቡ የሚጠብቀው በዚህ ጉዳይ የሚወሰደውን እርምጃ ማየትና መስማት ነው።

አቦይ ስብሃት፡- ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ብሄርተኝነት አንዱ ችግር ነው፤ ሌላው ሙስናና ብልሹ አሰራር ነው። ይሄ ደግሞ የጥልቅ ተሀድሶው አንድ አካል ነው፡፡ ስልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል የሚለው አንዱ ስርዓት እየተበጀለት ያለ ጉዳይ ነው። አንዱ የጥልቅ ተሀድሶው አካል ነው፡፡ እንዳልከው ህዝብም በጣም የሚጠብቀው ይሄ ነው፡፡ ይሄ እንዴት ይሄዳል? መቼ ይጀምራል? ከማን ይጀምራል? የሚለው ጥያቄ ነው ያለኝ እንጅ ኢህአዴግ ታጥቆ የተነሳበት ቀጣፊውን በቀጠፈውና ባጠፋው መጠን የሚቀጣበት፤ ይሄ ተቻችሎ መሄድ የሚያበቃበት ስርአትን ለመገንባት ቆርጧል። ጠባብነትንና ትምክህትን የሚያመጣውም ይሄው ተሸፋፍኖ መሄዱ ስለሆነ ገና ያልተጀመረ የሚጀመር አድርጌ ነው የምወስደው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም አስቀምጦታል፡፡ ኢህዲግም እንደ ድርጅት አስቀምጦታል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ግን ተግባር የለማ አቦይ።

አቦይ ስብሀት፡-ተግባር የሚጀምር ይመስለኛል።

አዲስ ዘመን፡- እንጠብቅ? እርስዎ የቅርብ መረጃ አለዎት?

አቦይ ስብሃት፡- እኔ አሁን የቅርብ መረጃ የለኝም፡፡ አሁን ኢህአዴግ የሚታማው ይናገራል እንጂ አያደርግም አይደለም? አሁን ግን ይደረጋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ቀደም ብለው ወደ ማረሚያ ቤት የገቡትን ባለስልጣናት የሚቀላቀል ባለስልጣን ይኖራል?

አቦይ ስብሀት፡-የእነሱም ቢሆን ስርዓቱ ሳይስተካከል ነው የሄዱት። ሰው መልቀምም ብቻውን ዋጋ አይደለም። ኢህአዴግ ያንን ሁኔታ የፈጠረውን እያስወገደ እንደሚያደርገው፤ በምሬትም እንደሚሄድበት ነው ያለኝ ግምት።

አዲስ ዘመን፡- ካልሄደበትስ?

አቦይ ስብሃት፡- ችግሩ ይቀጥላል፤ ሀገር  ይፈርሳል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ጨዋታው በሀገር እና በግለሰብ መሀከል ነው ማለት ይቻላል?

አቦይ ስብሃት፡- ስራ አጥነት፣ ህብረተሰብን በአግባቡ አለማገልገል ችላ ተብሎ እንደማይታለፍ ነው የእኔ ግንዛቤ። ይሄ ካልተቀረፈ ደግሞ ስራ ፈጠራ፣ ዲሞክራሲ፣ ሰላም እና እድገት የሚባል ነገር አይኖርም። ስለዚህ ለሰው ታስቦ ሀገር የሚካድበት ሁኔታ የለም፡፡ ለግለሰቦችም ተብሎ ተቻችሎ መሄድ የኢህአዴግ ቁመና እንዳልሆነ ነው የእኔ ግንዛቤ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ውጤቱ ምን ይሆናል ?

አቦይ ስብሃት፡-  መጠበቅ ነው፡፡ ህዝቡ በጉጉት መጠበቁ ትክክልና ምክንያታዊ ነው። ኢህአዴግ ለግለሰቦች ሲል ህዝቡን ይከዳል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ካልሄደበት ይሄ አገርን ህዝብን መክዳት ነው፡፡ ኢህአዴግ ሕዝቡ የሚጠብቀውን ጉዳይ ወደኋላ ይላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይሄን ካላደረገ ህዝብን መክዳት ነው፡፡ ሀገር ማፍረስ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- አቦይ  የበፊቱን ዘመንና ፖለቲካ በደንብ ያውቁታል፤ በተመሳሳይ የዛሬውንም አሉበት። እስኪ ዛሬ  ላይ ሆነው ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን ይታይዎታል?

አቦይ ስብሃት፡-  ህዝቡ የሚጠብቀው ይታየኛል። ለሰላምም ይሁን ለልማት፣ ለብልፅግና ልቡን አጥፍቶ ሊሰራ የሚፈልግ ህዝብ ስላለ ኢትዮጵያ እንደ አዲስ ራሷን ሆና ራሷን የምትጠቅምና ከአካባቢዋም አልፎ ለዓለም የምትጠቅም ሀገር ትሆናለች፡፡ ጊዜ የማያመልጣት ሀገር ትሆናለች፡፡ ጠላትን የምታሳፍር፤ ተጠቅማ የምትጠቅም ሀገር ትሆናለች፡፡ ጊዜ የማያመልጣት ሀገር እድትሆን እመኛለሁም ብቻ ሳይሆን ትሆናለች፡፡

አዲስ ዘመን ፡- ግን ይሄ የሚሆነው ቅድም ባስቀመጡልኝ ልክ የስርዓቱ አደጋዎች ተብለው የተጠቀሱት ከተወገዱና እርምጃውም ከተጀመረ ብቻ ይመስልኛል አቦይ፡፡

አቦይ ስብሀት፡- አዎን እነሱ ካልተወገዱ ይሄ አይሆንም። እንደሚወገዱ ግን አምናለሁ። ይሄ ከሆነ ጠላትን የምታሳፍር ወዳጅንም የምትጠቅም አገር እንደምትሆን አምናለሁ።

አዲስ ዘመን፡- አቦይ ወደኋላ እንዲሄዱ እድል ቢሰጥዎት እንደ አንድ ፖለቲከኛ ወደ ኋላ ሄጄ ባስተካክለው የሚሉት ነገር ይኖርዎት ይሆን?

አቦይ ስብሃት፡- እንደሰው ያጠፋኋቸው ጊዜዎች አሉ፡፡ ለመጥፎ ያዋልኩት ጊዜ ጊዜ የለም ለጥሩ ያላዋልኩት ጊዜ ግን አለኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለምሳሌ እስቲ ይጥቀሱልኝ?

አቦይ ስብሃት፡- ለምሳሌማ የፖሊስ ጥያቄ ነው። ማህበረሰቡን በሚጎዳ ተግባር ያሳለፍኩት ጊዜ የለኝም፡፡ ነገር ግን በማንበብ እና በመወያየት ማሳለፍ የሚገባኝ ጊዜ ነበር፤ ያንን ሳላደርግ ያሳለፍኩት አለ፡፡

አዲስ ዘመን፡-  ለምሳሌ በ1993ዓ.ም የህወሓት ተሀድሶ ወቅት የነበረዎትን ሚና ያስታውሳሉ፤ ከኤርትራ ጋር የነበረንን ግጭት በተመለከተ የያዙት አቋም አለ፤ ሌላም ሌላም፡፡ በዚህ ዙሪያ መለስ ብለው ያስተካክሉ ቢባሉ የሚያስተካክሉት ነገር ይኖር ይሆን?

አቦይ ስብሃት፡-  በፖለቲካ ረገድ ብዙ የሚቆጨኝም የማስታውሰውም ነገር የለም፡፡ በ1993ዓ.ም የነበረኝ አቋም የተባረሩትም ሁሉም አንድ ላይ እንዲቀጥሉ የሚል ነው፡፡ የፈለኩት ግን አልተሳካም። እሱ የእኔ ድክመት አይደለም፡፡ ነገር ግን በደንብ አልገመገምንም የሚል አቋም ይዤ በቂ ጫና አላሳደርኩም። ምክንያቱም ጠንቁ የውስጥ ነው። ያልሆነ ተቻችለን ነበር። እነሱ ይሄንን ተጠቀሙበት። የሁላችንን ድክመት ወደ አንድ ጫፍ ወሰዱት፤ ወደ ስልጣን ለመምጣት። ሁኔታውን የፈጠርልናቸው ግን እኛ ነን። ችግሩን ግን ወደ እነሱ ብቻ ጣልነው።ሁለታችንም ተጠያቂ ነን። ያኔ እነሱ ላይ በደንብ ጫና አሳድሬ ታይቶ ቢሆን ኖሮ የ1997  ችግርም ባላመጣ። የአሁኑም ባልመጣ ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ወደ ኋላ እንዲሄዱና እንዲያርሙ እድል ቢሰጥዎት የሚያስተካክሉት ይህንን ነው ማለት ነው?

አቦይ ስብሀት፡- አዎን፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ የ1997ዓ.ም ችግርም ባልመጣ የአሁኑም ተሀድሶ አይመጣም፤ ቀጥ ብለን እንጓዝና እንቀጥል ነበር። በእርግጥ የሚሻሻልም የሚለወጥም ይኖራል።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ማብራሪያ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።

አቦይ ስብሀት፡- እኔም አመሰግናለሁ።

***********

* ይህ ቃለ-ምልልስ መጀመሪያ የታተመው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በታህሳስ 26፣ 2009 ዕትም ነው፡፡

Areaya Getachew (MA) is a public relations expert at a foreign embassy. He studied second degree at Addis Ababa University and was deputy editor in-chief of Addis Zemen newspaper.

more recommended stories