ፖለቲካዊ ችግር በፖለቲካ እንጂ በወታደራዊ አገዛዝ አይፈታም

ሀገራችን የገባችበት ፖለቲካዊ ችግር በምን መልኩ ይፈታ? የሚለው ጥያቄ ጥርት ያለና በርካቶችን የሚያስማማ መልስ አላገኝም። ኢህአዴግ “በጥልቅ ታድሼ” ችግሩን እፈታለሁ እያለ ሲሆን፤ ሌላኛው ሀይል ደግሞ መፍትሔው ኢህአዴግን ማደስ ሳይሆን “መገንደስ” ነው እያሉ ነው። ከነዚህ አማራጮች በተጨማሪ በቅርቡ ብቅ-ጥልቅ ማለት የጀመረ ሌላ ሀሳብ ደግሞ “ወታደራዊ ክፍሉ እርምጃ ካልወሰደ መፍትሔ የለም” የሚል ነው።

የዚህ ፁሁፍ ዋና ዓላማም በቅርቡ መንሸራሽር የጀመረዉን ወታደራዊ አማራጭ የመሻት ዝንባሌ ያለዉን አደጋ ለማብራራት ነው። ማባርያ በሌለው ዘመቻ “ደክምያለሁ” ያለዉን የሲቪል አስተዳደር “ሞተሀል” የሚል ፕሮፖጋንዳ እየተነዛ ነው። ይህ ፕሮፖጋንዳ በዋዛ የተለቀቀ አይመስለኝም።

በቅደም ተከተል እንየው።

1/ በተለያዩ ጋዜጦችም ወታደራዊ ክፍሉ “ጣልቃ እንዲገባና” መፍትሔ እንዲሻ የሚጠይቁ ፅሁፎች ተለቀው ነበር፤ አሁንም እየተነገሩ ነው።

2/ በቅርቡም ከገዢው አካል ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የምናዉቃቸው የማሕበራዊ ሚድያ ተዋንያን ጏደኞቻችን ይህንኑ ወታደራዊ ሀይል የመተማመንና የመማፀን ዘመቻ አጠናክረው ቀጥለዉበታል።

3/ ከጭንቀትና “ኢትዮጵያ እንዳትበትን” ከሚል ቀና ስጋትም ነገሮች ከሚባባሱ ወታደሩ ስልጣን ይዞ የሽግግር መንግስት በማደራጀት ነፃና ፍትሓዊ ምርጫ አካሂዶ ስልጣን በህዝብ ለተመረጠ ያስረክብ የሚል ሀሳብ እየተንሸራሸረ ነው።

ይህ ምን ማለት ነው?

Photo - Ethiopian National Palace aka Jubilee Palace
Photo – Ethiopian National Palace aka Jubilee Palace

ይህ ምን ማለት ነው?

የገጠመን ፖለቲካዊ ችግር ሊፈታ የሚችል ፖለቲካ የለንምና ወታደራዊ ክፍሉ ስልጣን ይያዝ ማለት ነው፤ ወይም ባጭሩ ግዝያዊ ( ቛሚ) ወታደራዊ አገዛዝ ይመስረት ነው። የዚህ ሀሳብ መሰረታዊ አደጋዎቹ ካሁኑ ታዉቀው መንገዱ ዝግ ካልተደረገ ከማንወጣበት አዘቅት ዉስጥ እንደምንዘፈቅ ምንም ጥርጥር የለኝም።

ይህን የምለው የመከላከያ ሰዎችን ከመጥላት ወይም ከመዉደድ ሳይሆን ከሀገር ጥቅም አዃያ ነው።

አንድ፥ ሕገ መንግስቱ በማያሻማ ያስቀመጠዉን ስልጣን የሚገኝበት መንገድ “የህዝቦች የሉኣላዊ ስልጣን ባለቤትነት” ይፃረራል። ይህ ለወደፊቱም መጥፎ አሻራ (ባድ ፕረሲደንት) ጥሎ ያልፋል። ይሄ ሕገ መንግስት በደም የመጣ ችግሮቻችን ልንፈታበት የምንችል ሆኖ ሳለ ይህን ገደል መክተት ወደ ኃላ መመለስ መሆኑ መታወቅ አለበት።

ሁለት፥ በዚህ ስርዓት ላይ ከሚነሱ ትችቶች አንዱ እና የሚደጋገመው “መከላከያው የህወሓት (የትግራይ) ተቋም ነው” የሚል ነው። ስለዚህ ወታደራዊ ክፍሉ ስልጣን ልቆናጠጥ ቢል ከህዝቡ የሚመጣው ምላሽ ግልፅና ግልፅ ነው። “ህወሓት በፖለቲካዊ መንገድ መያዝ ያቃታትን ስልጣን በጠብመንጃ ልታሳካ መጣች” መባሉ አይቀርም። ይህ ማለት ወታደራዊ ክፍሉ ከመጀመርያ ከህዝቡ የመነጠል እድሉ ሰፊ ነው ማለት ነው። በግልፅ መነጋገር አለብን።

ሶስት፥ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አካሂደው ወደ ዴሞክራስያዊ ስርዓት መሸጋገር የቻሉ ሀገራት እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው። የተሳካላቸው የሚባሉት ኮርያ፣ ታይዋን፣ ቺሊ እና ስፔንም ቢሆኑ የራሳቸው ልዩ ምክንያት ነበራቸው።

አንድ – ብዝሀነት የሌለባቸው ነበሩ፡፡ የኛ ይለያል፡፡

ሁለት – ረዥም ዘመን ያስቆጠረ የተደራጀ የአስተዳደር ተቛማት የገነቡ ነበሩ፡፡ እኛ ለዚህ አልታደልንም፡፡

ሶስት -በቀጠናቸው ጠቃሚ የንግድና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ነበራቸው፡፡ የኛ በግልባጩ የግጭት እና የሀያላን መፈንጫ ቀጠና ነው፣ ጠላታችንም ብዙ ነው።

እንዲህ ሆነውም ከላይ የጠቅስኳቸው ሀገራት ከወታደራዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር የፈጀባቸው ግዜ ብዙ ነበር፡፡ቺሊ ከ 17 ዓመት በኃላ፣ ኮርያም ብትሆን ከ 14 ዓመት በኃላ ነው ዴሞክራስያዊ ስርዓት የገነቡት። ወደ ባሰ ሁኔታ የገቡት ግን ቁጥራቸው የላቀ ነው።

አራት፥ መከላከያው ከማን ተሽሎ ነው የለዉጥ ሀዋርያ ለመሆን የሚታጨው? ዉስጣዊ አሰራሩን እና ከዛ የተጣቡ እንደ ሜቴክ አይነት ድርጅት ጋር ተጎዳኝቶ በምን ስሌት ነው ከሲቪሉ የሚሻለው?

ስለዚህም ለፖለቲካዊ መፍትሔ ቅድምያ በመስጠት ሀገራችንን ማቅናት ይኖረናል። መከላከያ ሰራዊታችንን ሕገ መንግስታዊ ከሆነ ተልእኮው ለማንሸራተት የሚደረገዉን ውትወታም መቆም አለበት። የሲቪል አስተዳደሩም ይህን በመገንዘብ ችግሩን ባስቸኳይ ይፍታ።

ኢ-ሕገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ ስልጣን መሻት ወንጀል መሆኑ ታውቆ በዚህ ዘመቻ እየተሳተፋቹህ ያላቹህ ሰዎች ከድርጊታቹህ እንትቆጠቡ እመክራለሁ። የሲቪል አስተዳደሩም መፈንቅለ መንግስትን በግላጭ የሚያበራቱትን አድብ ማስገዛት አለበት።

ደርግም ሲመጣ ተራማጅ መስሎ፣ የ ተማሪዎችና የጭቁኖች መፍክር ቀምቶ ጤነኛ መስሎ ነው ስልጣን የያዘው። የመሬት አዋጁን ባወጀ በጥቂት ወራት ዉስጥ ነበር ወደ ትክክለኛ ወታደራዊ አምባገነንነት የተሸጋገረው። ይህ የሆነው ከግለሰቦቹ ባህሪ ሳይሆን ከ ወታደራዊ ባህሪው የመነጨ ነበር። ከዚህ ካልተማርን ደንጋዮቹ እኛው ነን።

ወታደራዊ ክፍሉ ሀገሩንና ህዝቡን የሚወድ መሆኑ የሚያስመሰክረው ሕገ መንግስቱን በማክበርና በማስከበር ብቻ እና ብቻ ነው መሆን ያለበት። ይህ ካልሆነና ለገጠመን ፖለቲካዊ ችግር ወታደራዊ መፍትሔ እሰጣለሁ ካለ ግን የዚህች አገር መጨረሻ እንደሚሆን አልጠራጠርም።

*****************

more recommended stories