Jan 05 2017

ፖለቲካዊ ችግር በፖለቲካ እንጂ በወታደራዊ አገዛዝ አይፈታም

ሀገራችን የገባችበት ፖለቲካዊ ችግር በምን መልኩ ይፈታ? የሚለው ጥያቄ ጥርት ያለና በርካቶችን የሚያስማማ መልስ አላገኝም። ኢህአዴግ “በጥልቅ ታድሼ” ችግሩን እፈታለሁ እያለ ሲሆን፤ ሌላኛው ሀይል ደግሞ መፍትሔው ኢህአዴግን ማደስ ሳይሆን “መገንደስ” ነው እያሉ ነው። ከነዚህ አማራጮች በተጨማሪ በቅርቡ ብቅ-ጥልቅ ማለት የጀመረ ሌላ ሀሳብ ደግሞ “ወታደራዊ ክፍሉ እርምጃ ካልወሰደ መፍትሔ የለም” የሚል ነው።

የዚህ ፁሁፍ ዋና ዓላማም በቅርቡ መንሸራሽር የጀመረዉን ወታደራዊ አማራጭ የመሻት ዝንባሌ ያለዉን አደጋ ለማብራራት ነው። ማባርያ በሌለው ዘመቻ “ደክምያለሁ” ያለዉን የሲቪል አስተዳደር “ሞተሀል” የሚል ፕሮፖጋንዳ እየተነዛ ነው። ይህ ፕሮፖጋንዳ በዋዛ የተለቀቀ አይመስለኝም።

በቅደም ተከተል እንየው።

1/ በተለያዩ ጋዜጦችም ወታደራዊ ክፍሉ “ጣልቃ እንዲገባና” መፍትሔ እንዲሻ የሚጠይቁ ፅሁፎች ተለቀው ነበር፤ አሁንም እየተነገሩ ነው።

2/ በቅርቡም ከገዢው አካል ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የምናዉቃቸው የማሕበራዊ ሚድያ ተዋንያን ጏደኞቻችን ይህንኑ ወታደራዊ ሀይል የመተማመንና የመማፀን ዘመቻ አጠናክረው ቀጥለዉበታል።

3/ ከጭንቀትና “ኢትዮጵያ እንዳትበትን” ከሚል ቀና ስጋትም ነገሮች ከሚባባሱ ወታደሩ ስልጣን ይዞ የሽግግር መንግስት በማደራጀት ነፃና ፍትሓዊ ምርጫ አካሂዶ ስልጣን በህዝብ ለተመረጠ ያስረክብ የሚል ሀሳብ እየተንሸራሸረ ነው።

ይህ ምን ማለት ነው?

Photo - Ethiopian National Palace aka Jubilee Palace

Photo – Ethiopian National Palace aka Jubilee Palace

ይህ ምን ማለት ነው?

የገጠመን ፖለቲካዊ ችግር ሊፈታ የሚችል ፖለቲካ የለንምና ወታደራዊ ክፍሉ ስልጣን ይያዝ ማለት ነው፤ ወይም ባጭሩ ግዝያዊ ( ቛሚ) ወታደራዊ አገዛዝ ይመስረት ነው። የዚህ ሀሳብ መሰረታዊ አደጋዎቹ ካሁኑ ታዉቀው መንገዱ ዝግ ካልተደረገ ከማንወጣበት አዘቅት ዉስጥ እንደምንዘፈቅ ምንም ጥርጥር የለኝም።

ይህን የምለው የመከላከያ ሰዎችን ከመጥላት ወይም ከመዉደድ ሳይሆን ከሀገር ጥቅም አዃያ ነው።

አንድ፥ ሕገ መንግስቱ በማያሻማ ያስቀመጠዉን ስልጣን የሚገኝበት መንገድ “የህዝቦች የሉኣላዊ ስልጣን ባለቤትነት” ይፃረራል። ይህ ለወደፊቱም መጥፎ አሻራ (ባድ ፕረሲደንት) ጥሎ ያልፋል። ይሄ ሕገ መንግስት በደም የመጣ ችግሮቻችን ልንፈታበት የምንችል ሆኖ ሳለ ይህን ገደል መክተት ወደ ኃላ መመለስ መሆኑ መታወቅ አለበት።

ሁለት፥ በዚህ ስርዓት ላይ ከሚነሱ ትችቶች አንዱ እና የሚደጋገመው “መከላከያው የህወሓት (የትግራይ) ተቋም ነው” የሚል ነው። ስለዚህ ወታደራዊ ክፍሉ ስልጣን ልቆናጠጥ ቢል ከህዝቡ የሚመጣው ምላሽ ግልፅና ግልፅ ነው። “ህወሓት በፖለቲካዊ መንገድ መያዝ ያቃታትን ስልጣን በጠብመንጃ ልታሳካ መጣች” መባሉ አይቀርም። ይህ ማለት ወታደራዊ ክፍሉ ከመጀመርያ ከህዝቡ የመነጠል እድሉ ሰፊ ነው ማለት ነው። በግልፅ መነጋገር አለብን።

ሶስት፥ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አካሂደው ወደ ዴሞክራስያዊ ስርዓት መሸጋገር የቻሉ ሀገራት እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው። የተሳካላቸው የሚባሉት ኮርያ፣ ታይዋን፣ ቺሊ እና ስፔንም ቢሆኑ የራሳቸው ልዩ ምክንያት ነበራቸው።

አንድ – ብዝሀነት የሌለባቸው ነበሩ፡፡ የኛ ይለያል፡፡

ሁለት – ረዥም ዘመን ያስቆጠረ የተደራጀ የአስተዳደር ተቛማት የገነቡ ነበሩ፡፡ እኛ ለዚህ አልታደልንም፡፡

ሶስት -በቀጠናቸው ጠቃሚ የንግድና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ነበራቸው፡፡ የኛ በግልባጩ የግጭት እና የሀያላን መፈንጫ ቀጠና ነው፣ ጠላታችንም ብዙ ነው።

እንዲህ ሆነውም ከላይ የጠቅስኳቸው ሀገራት ከወታደራዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር የፈጀባቸው ግዜ ብዙ ነበር፡፡ቺሊ ከ 17 ዓመት በኃላ፣ ኮርያም ብትሆን ከ 14 ዓመት በኃላ ነው ዴሞክራስያዊ ስርዓት የገነቡት። ወደ ባሰ ሁኔታ የገቡት ግን ቁጥራቸው የላቀ ነው።

አራት፥ መከላከያው ከማን ተሽሎ ነው የለዉጥ ሀዋርያ ለመሆን የሚታጨው? ዉስጣዊ አሰራሩን እና ከዛ የተጣቡ እንደ ሜቴክ አይነት ድርጅት ጋር ተጎዳኝቶ በምን ስሌት ነው ከሲቪሉ የሚሻለው?

ስለዚህም ለፖለቲካዊ መፍትሔ ቅድምያ በመስጠት ሀገራችንን ማቅናት ይኖረናል። መከላከያ ሰራዊታችንን ሕገ መንግስታዊ ከሆነ ተልእኮው ለማንሸራተት የሚደረገዉን ውትወታም መቆም አለበት። የሲቪል አስተዳደሩም ይህን በመገንዘብ ችግሩን ባስቸኳይ ይፍታ።

ኢ-ሕገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ ስልጣን መሻት ወንጀል መሆኑ ታውቆ በዚህ ዘመቻ እየተሳተፋቹህ ያላቹህ ሰዎች ከድርጊታቹህ እንትቆጠቡ እመክራለሁ። የሲቪል አስተዳደሩም መፈንቅለ መንግስትን በግላጭ የሚያበራቱትን አድብ ማስገዛት አለበት።

ደርግም ሲመጣ ተራማጅ መስሎ፣ የ ተማሪዎችና የጭቁኖች መፍክር ቀምቶ ጤነኛ መስሎ ነው ስልጣን የያዘው። የመሬት አዋጁን ባወጀ በጥቂት ወራት ዉስጥ ነበር ወደ ትክክለኛ ወታደራዊ አምባገነንነት የተሸጋገረው። ይህ የሆነው ከግለሰቦቹ ባህሪ ሳይሆን ከ ወታደራዊ ባህሪው የመነጨ ነበር። ከዚህ ካልተማርን ደንጋዮቹ እኛው ነን።

ወታደራዊ ክፍሉ ሀገሩንና ህዝቡን የሚወድ መሆኑ የሚያስመሰክረው ሕገ መንግስቱን በማክበርና በማስከበር ብቻ እና ብቻ ነው መሆን ያለበት። ይህ ካልሆነና ለገጠመን ፖለቲካዊ ችግር ወታደራዊ መፍትሔ እሰጣለሁ ካለ ግን የዚህች አገር መጨረሻ እንደሚሆን አልጠራጠርም።

*****************

Source: HornAffairs.com
ይህን ጽሑፍ ወስደው ሊያትሙ ቢሹ፤ የሆርን አፌይርስን እና የፀሐፊውን ስም በግልጽ መጥቀስ እና የዚህን ፖስት Link ማስቀመጥ ይገባል፡፡

5 Comments
 1. አሰጨናቂ ገብረ ጻድቅ(ኮ/ል)

  አቶ ናሁ ሰናይ ልትመሰገን ይገባል፡፡ አደጋዉ በትክክል የገባህ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ወታደራዊ አማራጭ የመሻት ዝንባሌ እጅግ አደገኛ መሆኑንና በዚህ መታለል እንደለለብን እኔ ራሴ በአገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ሳስጠነቅቅ ቆይቻለሁ፡፡በሀገራችን በቅርቡ የተፈጠረዉ ቀዉስም ቢሆን ወታደራዊ ጣልቃገብነትን የሚጋብዝም አይደለም፡፡ሁኔታዉ አሁን ረግቧል፡፡አቶ ናሁ ሰናይ ለስጋት መነሻ የሆነህን ጽሁፎች ምንጭ ጠቅሰህ ቢሆን ኖሮ መልካም ነበር፡፡ ወታደራዊ ደርግ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያደረሰዉን በደል ለመዘንጋት ግዜዉ ገና ነዉ፡፡ አገር በወታደር ጭንቅላት አይመራምና ከዚህ የዕብደት ሃሳብ እንቆጠብ እላለሁ፡፡
  አሰጨናቂ ገብረ ጻድቅ(ኮ/ል)

 2. Ewuntu Zeleke

  ናሁሰናይ ባነሳኸው ሀሳብና በሰጠኸው በምሳሌ የተደገፈ ማብራሪያ እኔም ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ፣ በተለይም የመከላከያውን ከፍተኛ አመራር የህወሀት ነባር ታጋዮች በተቆጣጠሩበት ሁኔታና የወታደሩ ክፍልም ቢሆንም ከሲቪሉ መንግስት የተሻለ አመራር ባልያዘበት ሁኔታ ይልቁንም የመከላከያ አመራሩ ራሱ በሙስና ተዘፍቆ ባለበት ወቅታዊ ችግር የወታደሩ አማራጭ በፍጹም የሚታሰብ ሊሆን አይችልም፡፡ ያውም በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዴሞክራሲያዊ የሆነውን መንገድ ትቶ ወደ ወታደራዊ አማራጭ ለመመለስ መሞከር በራሱ ከእጅ አይሻል ዶማ ብቻ ሳይሆን የድንቁርና አካሄድ መሆኑ አይቀርም፡፡ የሆነ ሆኖ እንደ አንተ አይነት ወጣት ምሁራን በዚህ መልኩ ደፍሮ ግልጹን መናገር ሲችል የሚሰሙ ከሆነ እሰየው እንጂ አዝማሚያውስ ተስፋ አስቆራጭ ይመስላል፡፡

 3. Kurabachew Alula

  The culprit for bad governance in Ethiopia relates primarily to a poor organization of the Executive branch of the government. The organization does not support the doctrine of the “Developmental State”. There must be a scheme for building a soft and hard infrastructure which ought to be managed by independent professional groups organized along the lines of different sectors so that the executive could be getting professional information for sound and sustainable decisions.
  The executives should not be immersed on daily routines – they are expected to engage themselves on strategic (developmental) issues of the country.
  My crude proposal, with this regard, is thus, the previous cluster based organization, discarded after the reshuffle, need to be reorganized and be staffed by professionals each group to be led competent directors with rich experiences in their respective occupations (sectors).
  These groups shall not be involved on operations of the industries,rather, they would be engaged in research and development based on problems they feel impede the development of the industries.
  These Bodies shall be working independently and be evaluated by the parliament.

 4. Kurabachew Alula

  This is rather a quest for clarity with what Ato Abay Woldu, President of Tigrai Regional State, has said when addressing the business community at Mekelle. In an attempt to give answers to the complaints coming in from the participants of the conference, he said that,”the government is working make you rich; …our objective is to establish a capitalist led government”. Unfortunately, I, and hope, all concerned citizens alike, would like to be clear with this statement, with all its implications?