የህዝብ አመኔታን እያተረፈለት የመጣዉ የኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ

(አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሺፈራዉ (ኮ/ል))

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በሀገራችን እጅግ አስፈሪ በሆነ ሁኔታ ከዳር አስከ ዳር አዳርሶ ከነበረዉ ቀዉስ በመንግስት ትእግስት የተሞላበት አመራር ሰጭነት ወደ ቀልባችን ከተመለስን በኋላ ገዥዉ ፓርቲና መንግስት “ጥልቅ መታደስ ” በሚል የለዉጥና የመታደስ ሂዴት ዉስጥ እንገኛለን፡፡ በከፍተኛ መነሳሳትና የቁጭት ስሜት የተጀመረዉ ይህ የለዉጥና የመታደስ እርምጃ ለዉጤት እንደሚበቃ ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ለዉጡ በመንግስትና በገዢዉ ፓርቲ መሪነት ይካሄድ እንጂ ያለ መላዉ ህዘብ ተሳትፎ ግቡን እንደማይመታ ታዉቆ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔም ይህችን ለመሞጫጨር የተነሳሁት የመንግስትን ጥሬት ላግዝ የምችልበት ሌላ አማራጭ በማጣቴ ቢያንስ በዚህ እንኳን ልሞክር ብዬ ነዉ፡፡

የአነሳሴ  ዋነኛ  ዓላማ  የኢትዮጰያ ህዝብ  ባለፉት ጥቂት ወራት  ከገባበት ዉጥረትና ስጋት የተሞላበት ሁኔታ ከወጣ በኋላ  መንግስት በቀየሰዉ የጥልቅ ተሃድሶ  ተጨባጭ ለዉጥ እንደሚመጣ እርግጠኛ ሆኖ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዲኖረዉ ለማሳሰብ ሲሆን በተመሳሳይ ሁኔታ ገዥዉ ፓርቲና መንግስትም በችግሩ አፈታት ላይ አያያዛቸዉና ጅማሮዉ ጥሩ ስለሆነ በዚሁ ቀጥሉበት፤ በርቱ የምል የድጋፍ ድምጽ ለማሰማት ነዉ፡፡ እንደኔ ያለዉ ሽማግሌ ጡረተኛ ወታደር ፈጣሪን በሀገሬ ሰላም እንዲያወርድ ከመለመን ባሻገር  የሚያሳስቡኝ ሀገራዊ ጉዳዮችን በሚመለከት  የግል አስተያየት ከመስጠት ያለፈ ሌላ ማድረግ የምችለዉ ነገር የለም፡፡

መግቢያ

ኢህአዴግ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከታገለለት ህዝብ ይልቅ የሱ ተሿሚ የሆነ  ባለስልጣን መነካት በጣም የሚያስቆጣዉ መሆኑን በተግባር እንድንረዳለት ያደረገበትን አንድ አጋጣሚ ለታሪክነቱ ስንል በጭራሽ አንረሳዉም፡፡  በወቅቱ ድፍን አዲስ አበባ ህዝብ  “ሌባ! ሌባ!” እያለ የሰደበዉን ሌባ ባለስልጣን ኢህአዴግ ግን ባልገመትነዉ ሁኔታ “ታጋይ እንቶነ በህዝቡ መስደቡ አይገርመኝም፡፡ ህዝቡ ባይሰድበዉ ነበር የሚገርመኝ“ ብሎ ከህዝቡ ይልቅ የአንድ ሌባ ባለስልጣን ጉዳይ የሚያስጨንቀዉ መሆኑን በአደባባይ ሲናገር ሰምተን በኢህአዴግ ቅር እንዳልተሰኘን  በኋላ ላይ ግን ልብ ገዝቶ ያንን ሌባም  ከርቼሌ ወርዉሮ ሲያበቃ  ከህዝብ ጋር  እንደገና ተወዳጅቶ እጅግ የሚያስመሰግኑ  የልማት ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡:

ከዚያም በኋላ ኢህአዴግ  አገር ለማልማት ደፋ ቀና በምልበት ሰዓት  ለህዝብና ለሀገር ቀርቶ ለራሱ ለገዥዉ ፓርቲም ቢሆን ደንታ የለላቸዉ ጥቂት የማይባሉ ሙሴኛ ባለስልጣናቱ ያለ ምህረት ሀገሪቷ በአጥንቷ አስከምትቀር ድረስ ሲግጧትና ሲሰርቆ ቆዩ፡፡ ይህ ስርቆታቸዉ ሳያንስ ጭራሽ መልካም አስተዳደርና ተገቢዉን አገልግሎት በመንፈግ ህዝቡን እጅግ ሲያስመርሩት ኢህአዴግ እያየ እንደላየ ሆነ አለፈ፡፡ በዚህ የኢህአዴግ ግደለሽነት ቁጭት የገባዉ በቁጥር ቀላል የማይባለዉ ህዝብ ኢህአዴግንና የሚመራዉን መንግስት መጥላት ብቻ ሳይሆን ለመቅጣትም መፈለጉን በ97ቱ ምርጫ ተግባራዊ ማድረጉን ማስታወሱ በቂ ነዉ፡፡ በቅርቡ በሀገራችን ለታየዉ መጥፎ ክስተት የተዳረግነዉም ሃላፊነታቸዉን የዘነጉ ጥቂት የድርጅቱና የመንግስት ባለስልጣናት መስራት የሚገባቸዉን ስራ በአግባቡ ባለመስራታቸዉና ይልቁንም ህዝቡን ክፉኛ በመናቃቸዉ ምክንያት ወደ ህዝቡ ቀርበዉ ለማማከርና ፍላጎቱን ለመጠየቅ ሳይሞክሩ ኢ-ዲሞክራሲዊ በሆነ መንገድ በግድ ለማስፈጸም በመሞከራቸዉ የተከሰተ ችግር ነዉ፡፡

ለብሶት የዳረጉትን እነዚህን ጥቂት ባለስልጣናት የሚገስጻቸዉ መጥፋቱን የተረዳዉ ህዝብ ሌላ አማራጭ ሲያጣ ነዉ ለተቃዉሞ ወደ ጎዳና  ለመዉጣት የተገደደዉ፡፡ የሚያሳዝነዉ ግን በህዝቡ ገንዘብ ደሞዝ የሚከፈላቸዉ ባለስልጣናት  የህዝቡን ጥያቄ ፈጥነዉ ምላሽ መስጠት ባለመፈለጋቸዉ “ግርግር ለሌባ ያመቻል !”እንዲሉ ሁኔታዉ ለስርአታችን ጠላቶች መልካም አጋጣሚ ሆኖ ህዝቡን በተለይም ወጣቱን በመሰሪ ቅስቄሳቸዉ ገፋፍተዉ ለጥፋት ተግባር መዳረጋቸዉ ነዉ፡፡ ይህ ሁሉ መተረማመስ ሊፈጠር የቻለዉ አስቀድሜ እንደገለጽኩት ባለስልጣናቱ የህዝብን ጉዳይ ችላ ብለዉ በግል ጉዳያቸዉ ላይ በመጠመዳቸዉ ምክንያት ነዉ፡፡ ኢህአዴግም በየጊዜዉ ከተከሰቱ ቀዉሶች ትምህርት ሆኖት  ራሱ የሾማቸዉን ባለስልጣናት ለመቆጠጠር ባለመንቀሳቀሱ ይሄዉ ዛሬ ከገባንበት  አጠቃለይ ቀዉስ ሀገሪቱንና ራሱን ለማዉጣት ፍዳዉን ለማዬት ተገዷል፡፡ የዚህ አይነት ቀዉሶች የሚስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ ባይሆኑ ኖሮ እንደኛ ዝንጉ ለሆነ መንግስት ጥሩ  ማንቂያና ማስተማሪያ ሊሆን ስለሚችል አንዳንዴ በመጣ የሚያሰኝ ነዉ፡፡ ክፋቱ ግን ቀዉሱ ከሚያስከትለዉ ጉዳትም በላይ የሚያስፈራዉ መንግስትና ገዥዉ ፓርቲ ሁልጊዜም ካለፉት ችግሮች ለመጭዉ ትምህርት ለመዉሰድ ፈጣን ያለመሆናቸዉ ነዉ፡፡

1/ ከጅምሩ አያያዙ ያማረለት የኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ

በአገራችን ከደረሰዉ ከዚህ ሁሉ መመሰቃቀልና መተረማመስ በኋላ ገዥዉ ፓርቲም ሆነ መንግስት ሁኔታዎችን በብልሃት በማርገብ በህዝብ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን አንድ በአንድ ለመፍታትና ለወደፊቱም ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት ለማድረግ ቆርጠዉ ተነስተዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ህዝቡን ሲበድሉና ሲያስለቅሱ የነበሩና ብቃቱም የጎደላቸዉን ዋልጌ ባለስልጣናቱን በህዝብ ጥቆማ እየለየ አግባብነት ያለዉ አስተዳደራዊ፤ፖለቲካዊና ህጋዊ እርምጃ መዉሰድ ጀምሮአል፡፡ በራሱ በድርጅቱ ላይም ስርነቀል ለዉጥ ከማድረግ አልተቆጠበም፡፡ “ጥልቅ ተሃድሶ“ የተሰኘዉ የሰሞኑ የኢህአዴግ እርምጃ ምን ያህል ጥልቀት እንደሚኖረዉ መገመት ባልችልም  መንግስት በእስካሁኑ አካሄዱ ካሳየዉ ፍንጭ ለመረዳት እንደቻልኩት በማንም ላይ በምንም ጉዳይ የሚራራ አንጄት ከእንግዲህ እንደማይኖረዉና ከህዝቡ የሚበልጥብኝ የለም የሚል አቋም እንደያዘ ነዉ፡፡

አሁን አሁንማ “ድርጅቴ ከፈቀደ“ማለት ቀርቶ “የኢትዮጵያ ህዝብ ከፈቀደ” ማለት ተጀምሮአል፡፡ በመንግስትና በፓርቲ መካካል የነበረዉ መደበላለለቅም መጥራት ጅምሮአል፡፡ ህዝቡ የሰሞኑን የኢህአዴግን በራሱ ላይ ጭምር መዝመት መጀመር ሲመለከት መጨረሻዉን ለማየት ጉጉት አድሮበታል፡፡ ኢህአዴግን  “አይዞህ በርታ ከጎንህ አለንልህ !” እያሉትም ነዉ፡፡ የሕዝቡን ሙሉ ድጋፍ እንዳገኘ እርግጠኛ እየሆነ የመጣዉ የኢህአዴግ አመራርም ትልቅ ጉልበት ስለሆነዉ በድፍረት ከበድ ከበድ ያሉ እርምጃዎችን እየወሰደ እንድናምነዉ እያደረገ ነዉ፡፡ በተለይ ከዚህ ቀደም በተወሰኑ ወገኖች አካባቢ በርስትነት የተያዘ ይመስል የነበረዉን የአስፈጻሚዉን ቁልፍ የስልጣን ቦታዎች ከፓርቲ ወገንተኝነት ይልቅ ህዝባዊ ወገንተኝነታቸዉንና የሙያ ብቃታቸዉ ተቀዳሚ መስፈርት ባደረገ መልኩ አዳዲስና ሰርተዉ ቶሎ የማይደክማቸዉን ወጣት ምሁራንን ለመሾም ያደረገዉ ጥረት ከሁሉም በላይ ህዝብን ያስደሰተ ታላቅ ሥራ ነዉ፡፡

የኢፌድሪ  መንግስት በጀመረዉ ዘርፌ ብዙ በሆነዉ ጥልቅ ተሃድሶ  አስካሁን  አይነኬ ሆነዉ የቆዩ ፖለቲካዊና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ሳይቀሩ  አንደ ሁኔታዉ በህዝብ ፍላጎት ማሻሻያ አስከማድረግ ሊደርስ የሚችል ስራ እንደሚሰራ  በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የተሰጠዉ ጥቆማ ወይም ብስራት እኔንም ጨምሮ ብዙዎቹን ያስገረመና የስደሰተ  ጉዳይ ነዉ፡:

Photo - Ethiopian Prime Minister Hailemariam Desalegn
Photo – Ethiopian Prime Minister Hailemariam Desalegn

ጠቅላይ ሚኒስትራችን በተደጋጋሚ በህዝቡ መሐል በአካል እየተገኙም ሆነ በተሌቭዥን መስኮት እየቀረቡ አበክረዉ ሲገልጹ የሰማነዉና በተግባርም ማየት የጀመርነዉ ኢህአዴግ ምን ያህል ራሱን ለህዝብ ፈቃድ ለማስገዛት መፍቀዱን ነዉ፡፡  የድብቅነትና የምስጥራዊነት በሽታ ክፉኛ ተጠናዉቶት የቆየዉ ኢህአዴግ አሁን ግን የዉስጥ ገበናዉን ግልጥልጥ እያደረገ ድክመቱን ራሱ ከመንገሩም ሌላ “እባካችሁን አርሙኝ! አግዙኝ! “እያለ  ህዝቡን መማጸኑ በርግጥም ትልቅ ለዉጥ ነዉ፡፡  ከሁሉም በላይ ደግሞ ህገ- መንግስቱን እንደገና አስከ መከለስ ድረስ የሚደርስ ፈቃደኝነቱንና ፍላጎቱን ማሳየቱ በቀላሉ የማይታይ ነዉ፡፡ በዚህ ምክንያትም ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች ሳይቀር አግራሞትን ፤ከደጋፊዎቹ ደግሞ አድናቆትና ከበረታን አትርፎለታል፡፡ በአንዳንድ የድርጅቱ ሰዎች አጓጉል ተግባር ተስፋ ቆርጦ የነበረዉ ህዝብም ኢህአዴግ ላይ እንደገና ተስፋና አመኔታ ማሳደር ጀምሮአል፡፡ የአስካሁን  አያያዙም ተስፋ የሚጭር ነዉ፡፡

ኢህአዴግ ራሱን ለማደስ ሲነሳ ለዓመታት የታገለለትን የተቀደሰ ህዝባዊ ዓላማ አሽቀንጥሮ በመጣል ሌላ ፓርቲ ሆኖ ይመጣል ማለት አይደለም፡፡ እንደዚያ ሊሆን ይችላል ብለዉ ለሚያስቡ ወይም እንዲሆን ለሚፈልጉ አንዳንድ ወገኖች በጭራሽ እንደዚያ እንደማይሆን ሊረዱት ይገባል፡፡ ኢህአዴግ ኢህአዴግነቱ መቼም ቢሆን አይቀየርም፡፡ ኢህአዴግ የታገለለትና ወደፊትም የሚታገልለት ዓላማ ከቶ አይለወጥም፡፡ የኢህአዴግ ችግር የአላማ ችግርም አልነበረም፡፡ ኢህአዴግ አሁን እያደረገ ያለዉ የዓላማ ለዉጥ ወይም ቅልበሳ ሳይሆን ከተነሳበት ዓላማ ያናጠቡትንና መንገዱን ያሳቱትን እንቅፋቶች በማስወገድ ወደ ተነሳበት ግብ በፍጥነት መገስገስ ነዉ፡፡

የኢህአዴግን መታደስ እንደ ሽንፈት የቆጠሩ ፤ የኢህአዴግን ራሱን ለማረም ቁርጠኝነት ማሳየትን ከፍርሃት የመነጨ አድርገዉ የተረዱ አይጠፉም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ኢህአዴግ ስርነቀል ለዉጥ ለማድረግ ቁርጠኛ ሊሆን የቻለዉ መጪዉን አገራዊና የአካባቢ ምርጫ ለማሸነፍ እንደማይችል በመረዳቱ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ብሎ ነዉ የሚሉም አልታጡም፡፡ እነሱ እንደሚገምቱት ኢህአዴግ ምርጫን ለማሸነፍ ብሎ ቢሆን ኖሮ ራስን አስከማጥፋት በሚያስቆጥር ደረጃ በራሱ ላይ እርምጃ ለመዉሰድ ባልቃጣ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ምርጫን እንዴት ማሸነፍ እንዳለበት የ2002ን ምርጫ ዉጤት ማስታወስ በቂ ነዉ፡፡ ለመሆኑ  ተቀዋሚ ፓርቲዎች  ራሳቸዉ እየተፎካከሩ ያለዉ ለስልጣን አይደለም እንዴ?አንድ ጥሩ ፖሊሲ አለኝ የሚል ፓርቲ ስልጣን ሳይጨብጥ መስራት የሚችልበት አንዳችም ዕድል እንደማይኖረዉ አይታወቅም እንዴ ?፡፡ ኢህአዴግ ምርጫን ለማሸነፍ የሚያግዙትን ተግባራት ቢያከናዉን ምኑ ላይ ነዉ ጥፋቱ ? አሁን የኢህአዴግና የመንግስት ጭንቀት በምርጫ የማሸነፍና አለማሸነፍ ጉዳይ ሳይሆን የሀገርና የህዝብ ፈቃድ የመሟላት ጉዳይ ነዉ፡፡ ምርጫዉ የተለየ ድራማ መስራት ሳያስፈለገዉ በራሱ ጊዜ ይሳካል፡፡ ስለ ኢህአዴግ ቀጣይ የምርጫ ዕጣ ፈንታ ለመጨነቅ አሁን ትክክለኛ ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ ሁላችንም ትኩረታችን በሀገርና በህዝብ አጀንዳ ላይ ሊሆን ይገባልና፡፡

2/ ለለዉጥ በቁርጠኝነት የተነሳና ህዝብን ከጎኑ ያሰለፈ አመራር  ካሰበዉ እንዳይደርስ የሚያግደዉ ኃይል አይኖርም

በሃገራችን ስር ሰደዉ የቆዩ ችግሮችን  ለዘለቀታዉ በመቅረፍ  ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ በአጭር ግዜ ያደርሳታል ተብሎ እምነት የተጣለበት ዘርፌ ብዙ የሆነ ዓላማ ባነገበዉ “ጥልቅ ተሃድሶ”ና ያን ተክትሎም ስርነቀል ለዉጥ በማድረግ ረገድ ኃላፊታቸዉን በብቃት እየተወጡ የሚገኙ በርካታ የፓርቲና የመንግስት ባለ ስልጣናት፤ በየደረጃዉ ያሉ የመስተዳድር አካላት፤ የህብረተሰብ ክፍሎችና ዜጎች ቢኖሩም የዚህ ታሪካዊና ወሳኝ ጉዳይ ዋና መሃንዲስና ግንባር ቀደም መሪ የሆኑትን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም  ደሳለኝን በዚህ አጋጣሚ በተለየ ሁኔታ መጥቀስ የሚገባኝ ይመስለኛል፡፡ የድርጅቱ ሊቀመንበርና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ቁርጠኝነትና ብልሃት ባለተለየዉ ሁኔታ እየሰጡ ባለዉ የሰከነ አመራር በርግጥም ህዝቡ በመንግስት ተስፋ እንዲያደርግ አድርገዉታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝቡን የልብ ትርታ ለማዳመጥ እያደረጉ ያሉት ጥሬት፤ለህዝቡ እያሳዩ ያሉት ከበሬታ ትህትናና ጨዋነት የተላበሰዉ አቀራረባቸዉ ሲታይ በርግጥም በህዝብ ወሳኝነት ማመናቸዉንና የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ቆርጠዉ መነሳታቸዉን አመላካች ነዉ፡፡ ይህ ሁኔታቸዉ በህዝቡም ዘንድ የተወደደላቸዉ ይመስለኛል፡፡

መሪዎች ለበጎም ሆነ ለጥፋት የሚኖራቸዉ ሚና ወሳኝ በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትራችን አቋምና ቁርጠኝነት ላይ እርግጠኛ መሆን ተገቢ ነዉ፡፡ ህዝብ በመሪዉ ላይ አመኔታ ከጣለ የተጀመረዉ ታላቅ ስራ እንደሚሳካ  እርግጠኝነት ባልተለየዉ ተስፋ መጠበቅ ያስችለዋልና፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከኋላ የሚጎትታቸዉና ከተነሱበት ዓላማ የሚያናጥባቸዉ ኃይል እንደለለ ከተረዳን በርግጥ እዉነተኛ ለዉጥን መጠበቅ ይቻለናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ሙስና ከፉኛ የተንሰራፋባት አገር እየመሩ እሳቸዉ በግላቸዉ በዚህ ጉዳይ በጭራሽ  የሚታሙ አለመሆናቸዉና እጃቸዉ ንጹህ ነዉ መባሉ ለዉጡን ያለጥርጥር ከዳር ያደርሱታል የሚለዉ የህዝብ አመኔታ እንዲጎለብት የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት ነዉ ህዝቡ “አቶ ኃይለማርያም ምን አሉ? ምን ቃል ገቡ ወዘተ” እያለ እርስ በርሱ መጠያየቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትራችን ለሀገሪቱ ህዝብ ችግሮች ፍቱን የሆነ መፍትሄ ሊገኝ የሚችለዉ አራት ኪሎ ከመሸጉ ባለስልጣናቱ ሳይሆን ከራሱ ከህዝቡ መሆኑን በሚገባ ተረድተዋል፡፡ ወደ ህዝቡ አዘዉትረዉ መቅረባቸዉና ህዝቡን በስፋት ማሳተፍ መጀመራቸዉም  የዚህ ምልክት ነዉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጀመሪያ አካባቢ ወደዚህ ከፍተኛ ኃላፊነት በመጡ ሰሞን ይታይባቸዉ የነበረዉ እርግጠኛ ያለመሆንና ማመንታት ከብቃትና ከልምድ ማነስ የተፈጠረ ሳይሆን  እጅግ ጥብቅ በሆነዉ ድርጅታዊ ድስፕሊን ተተብትበዉ መፈናፈን ስለተሳናቸዉና በተጨማሪ የስርአቱ ዋና መሃንድስ በነበሩት አሁን በህይወት የለሉት የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በስርአቱ ግንባታ ላይ በነበራቸዉ እጅግ የገዘፈ ሚና የፈጠሩት ሌጋሲ  በድርጅታቸዉ አባላትና ከህዝቡ አይምሮ ቶሎ መደብዘዝ ባለመቻሉ ይህ ሁኔታ የአቶ ኃይለማርያምን ገጽታ ጎልቶ እንዳይወጣ የራሱን ተጸእኖ በመፍጠሩ ነዉ፡፡ የአቶ ኃይለማርያም ብቃትን የተገነዘብነዉ ከጊዜ በኋላ በጅምር የቆዩትንና ሌሎች አዳዲስ የልማት ዉጥኖችን አቅደዉ በአጭር ግዜ ማስፈጸም በመቻላቸዉና በሌሎች ፖለተካዊና ዲፕሎማሲያዊ መስኮች የተሳካ  አመራር ከመስጠታቸዉም ሌላ ወደ ህዝቡ ወርደዉ ከህዝቡ ጋር አጅና ጓንት መሆን ከጀመሩ በኋላ ደግሞ በታየባቸዉ ከፍተኛ ራስ መተማመን፤ እርግጠኝነትና ፈጣን ዉሳኔ አሰጣጣቸዉ ነዉ፡፡

በሳቸዉ እየተመራ ያለዉ መንግስት የህዝብ ፍቅርና ከበሬታ ሊገኝ የሚችለዉ በድርጅታዊ መግለጫና በካድሬ ቅስቀሳ ሳይሆን እንዲህ እንደ ሰሞኑ ከህዝቡ ጋር በቀጥታ በመገናኘትና የህዝብን ፍላጎት እየጠየቁና እየተመካከለሩ ሲሰሩ መሆኑን ጠንቅቀዉ የተረዱ መሆናቸዉን ከተግባራዊ እንቅስቃሴያቸዉ ለመረዳት የቻልን ይመስለኛል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊትአዉራሪነት የተጀመረዉ ይህ ስራ  እጅግ ጠቃሚ መሆኑ ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛም ሊሆን መቻሉም ሊጤን ይገባዋል፡፡ የሀገር ፍቅር ብሎ ነገር ጭራሽ ያልፈጠረባቸዉ ስልጣናቸዉን ለዝርፊያና ለስርቆት ከመጠቀም የማያመነቱና በዚህ መንገድም መጠኑ የበዛ ሃብት ያፈሩ ግለሰቦች አሁን በተጀመረዉ ንቅናቄ ከፍተኛ ስጋት ስለገባቸዉ ሌላ ሴራ እንደማይጠነስሱ እርግጠኛ መሆን ስለማንችል ተገቢዉ ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል፡፡  የተጀመረዉ ህዝባዊ ንቅናቄና ጥልቅ መታደስ ለአፍታም መገታት አይኖርበትምና ዙሪያገባዉን መቃኘት ብልህነት ነዉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትራችን በዙሪያቸዉ ማሰባሰብ ያለባቸዉ አሳቸዉና ድርጅታቸዉ ለተነሱለት ዓላማ ቁርጠኝነት ያላቸዉና ሊያግዟቸዉና ሊደግፏቸዉ የሚችሉትን ብቻ መሆን አለበት፡፡ የተለያዩ ሹሜቶች እየሰጧቸዉ  በቅርብ ያስቀመጧቸዉ ሰዎች በቆራጥነት አብረዋቸዉ እንደሚዘልቁ እርግጠኛ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሳቸዉ አመራርነት የተጀመረዉ ታላቅ ስራ ወደፊት ሊያስከትል በሚችለዉ ስኬትም ሆነ ዉድቀት በግላቸዉ የመጀመሪያዉ ተጠያቂ መሆናቸዉን ለአፍታም መዘንጋት አይኖርባቸዉም፡፡ በየግዜም በሙስናም ይሁን በአቅም ማነስ ምክንያት እንደማይመጥኑ የተረጋገጠላቸዉና ህዝቡ በአይኑ በጭራሽ ሊያያቸዉ የማይፈልጋቸዉ አንዳንድ ባለስልጣናት አሳቸዉን መጠጊያና መሸሸጊያ እንዲያደርጉ መፍቀዳቸዉ ወደፊት ተመልሶ ለሳቸወም ቢሆን ችግር መፍጠሩ አይቀርም፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ቦታ ያበቃኝ ድርጅቴ ነዉ በሚል ድርጅቱ የዋለላቸዉ ዉሌታ ከብዶአቸዉ ከዚህ ታላቅ ህዝብ ይልቅ  በድርጅት ፍቅር እንዳይወድቁና አገርን በፓርቲ እንዳይለዉጡ የመስጋታችን አንዱ መነሾ  የዚህ ዓይነት ሰዎችን  አቅፈዉ ለመዝለቅ  መወሰናቸዉን በማየታችን ነዉ፡፡ ለሀገር ትልቅ ስራ የሰሩ ታላላቅ ሰዎች የትም ይዉደቁ የሚል አቋም የለኝም፡፡ ለሀገራችን ህዝብ ገና ብዙ መስራት የሚችሉ በተለይም በትግል ነጥሮ የወጣ ሰፊ ተሞክሮአቸዉ አሁንም ተፈላጊ ያደረጋቸዉ፤ እርጅና ቢጫጫናቸዉም ተዝቆ የማያልቅ ሰፊ ተሞክሮአቸዉ አሁንም ታላላቅ አገራዊ  ጉዳዮች ላይ ለማማከርና እንዲህ “ቢደረግ ይሻል፤ እንዲህ አታድርጉ” እያሉ ለመምከር የሚችሉ ጉፍቱ ሰዎች ሊሰጡ የሚችሉት አበርክቶት ከፍተኛ ስለሆነ የዚህ ዓይነት ሰዎች ካሉ መንግስት ቢጠቀምባቸዉ ተገቢ ይሆናል፡፡

ነገር ግን ከእዉቀት ቢሉ እዉቀቱ የለላቸዉ ከታማኝነቱ ቢሉ ታማኝነት የጎደላቸዉና ህዝብ እድሉን ቢያገኝ ለጥያቄ የሚፈልጋቸዉ አንዳንድ ሰዎች ጭምር በዉስጣቸዉ መገኘታቸዉ ነዉ ቅሬታን የፈጠረዉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሌሎች ባለስልጣናት ለፓርቲያቸዉ ታማኝ ቢሆኑ እንደችግር የሚቆጠር አይደለም፡፡ እንዲያዉም ብልሹ የሆነ ምግባር ያላቸዉ ሰዎች የኋላ ታሪካቸዉ ቢፈተሸ የወጡበትን ፓርቲ ዓላማ የካዱና ድርጅቱን ለግል መጠቀሚያ ለማድረግ የሚሞክሩ ናቸዉ፡፡ በፓርቲቸዉ ህዝባዊ ዓላማ ጽኑ እምነት ያላቸዉ አባላት ህዝብን ለመበደል አይደፋፈሩም፡፡ ስለዚህ ፓርቲዉ ለቆመለት ዓላማ በጽናት ቢቆሙና ታማኝ ቢሆኑ ችግር የለዉም፡፡ ችግር የሚከሰተዉ በፓርቲና በህዝብ ጥቅም መካከል ግጭት የሚፈጠርበት ሁኔታ ሲኖር ከህዝቡ ይልቅ ለፓርቲ መወገን(ማድላት) ሲመጣ ያኔ ነዉ ችግር የሚፈጠረዉ፡፡ ሚዛናዊ የሆነ ወገንተኝነት ሊኖር ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ በተለምዶዉ ራሱ መርጦ ያልሾመዉን መንግስትንም ቢሆን  የማክበርና የማመን የቆየ ባህሪይ አለዉ፡፡ መንግስት የሚነግረዉን ያምናል፡፡ ቃል የተገባለት ተግባራዊ አስኪሆንም ለዓመታትም ቢሆን ተስፋ ሳይቆርጥ ይጠብቃል፡፡ መንግስት ቃሉን ጠብቆ ለመስራት የሚያደርገዉን መፍጨርጨርና ጥረት ህዝቡ ስለሚገነዘብ ድንገት በጠበቀዉ ፍጥነትና መጠን ባይሳካ ብዙም አይከፋም፡፡ ነገር ግን ህዝብ  ከሁሉም በላይ የሚጠላዉ የሚዋሸዉን መንግስትና መሪ ነዉ፡፡ ችግሩን ለመካፈል የማይፈልግ ይባስ ብሎ ደግሞ ያልሰራዉን ሰራሁ እያለ የሚመጻደቅ መንግስትን ህዝቡ አይሻም፡፡ ለህዝቡ ከበሬታ የለለዉና ህዝብን ቁልቁል የሚያይ የመንግስት ባለስልጣንን ህዝብ አይወድም፡፡ በአንጻሩ ለህዝብ ለመስራት ፍላጎቱና ተነሳሽነቱን በተግባር እያሳየ ነገር ግን በአፈጻጸም ላይ አቅም ያነሰዉ መንግስት በህዝቡ ዘንድ አመኔታን አያጣም፡፡ በምክር እየታገዘ እንዲሰራ ይደረጋልና፡፡ ፡

በሀገራችን በተለይ በዚህ መንግስት አስተዳደር ዘመን ከመንግስት ባለስልጣናት ከላይኛዉ ሚኒስትር ጀምሮ አስከ ታችኛዉ  መዝገብ ያዥ የተሰጠኝኝ ስራ መስራት አልቻልኩም ወይም የመንግስት ፖሊሲ አልተስማማኝም ብሎ የስልጣን መልቀቂያ ያስገባ ባለስልጣን ስለመኖሩ አስካሁን አልሰማንም፡፡ በፈረንጆቹ 2016 ብቻ በተለያዩ ዲሞክራሲያዊ አገሮች በቁጥር በዛ ያሉ የሀገር መሪዎች በግላቸዉ የሰሩት አንዳችም ጥፋት ሳይኖር በሚመሩት መንግስት እንከን ብቻ በገዛ ፈቃዳቸዉ ስልጣን ሲለቁ አይተናል፡፡ በኛ አገር ግን ስንት ጉድ የተሸከመ ባስልጣን እንኳን በፈቀዱ ስልጣን መልቀቅ ይቅርና በስንት የህዝብ ጉትጎታ  የሙጥኝ ካለዉ ቢሮዉ ለማስወጣት መንግስት አንድ ደርዘን የሚሆን የፌዴራል ፖሊስ ኃይል መጠቀም የግድ ይሆናል፡፡ በዚያ መልክ የተነሳዉ ባለስልጣን “ከርቼሌ ነዉ ወይንስ ቅልንጦ ነዉ ያሰሩት?” እያለ ህዘብ ሲያንሾካሽክ እሱ በሌላ ጊዜ በመንግስት ቴሌቭዥን ቀርቦ ስለ ሙስና ወይም ስለ መልካም አስተዳደር መግለጫ ሲሰጥ ልናይ እንችላለን፡፡ ካልሆነም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት አካባቢ ታይቷል የሚል መረጃ ይሰማና እሱ የሰረቀዉ እያለ ሌሎች ስጋት ይገባቸዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ መንግስት ጨከን ለ እርምጃ መዉሰድ በመጀመሩ የዚህ ዓይነት ሁኔታ የማይቀጥልበት ወቅት ላይ እንደደረስን አመላካች ነዉ፡፡

3/ ህዝብ በልማት ብቻ እንደማይረካ ኢህአዴግ ተረድቷል፡፡

በሀገራችን የታየዉ ለዉጥና የደረስንበት እድገት ከታሰበዉ በላይ መሆኑ በተለያዩ ወገኖች ዘንድ በተለየ እንዲመዘን አድርጎታል፡ የዉጭዎቹ ታዛቢዎች መጀመሪያ ላይ አድገታችን ተጠራጠሩና ተጠራጥረዉም ሲያበቁ በተደጋጋሚ እየተመላለሱ ሲያስጠኑና ሲመረምሩ ቆይተዉ በመጨረሻም ስለ እድገታችን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ከኛ ብሰዉ እነሱ ምስክር ሆኑ፡፡ እንደ ግብጽና ኤርትራ ያሉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ደግሞ አድገታችን እዉነት መሆኑን አምነዉ መቀመጥ ብቻ አልፈለጉም፡፡ ይልቁንም ከዚሁ ጥረታችን ሊያሰናክሉን ብዙ ተፍጨረጨሩ፡፡ እንዲያዉም አንድ የግብጽ ባለስልጣን ሲናገር እንደተደመጠዉ ኢትዮጵያ ለአገራቸዉ ለግብጽ ከምንጊዜም በላይ አሁን ለብሄራዊ ጥቅም ከፍተኛ ስጋት የሆነችበት ደረጃ ላይ መድረሷንና የዚህ ሁሉ ስጋት መነሾም ከወታደራዊ ስጋት የሚመነጭ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ፈጣን አድገትና ያን ተከትሎም በዉጭም ዓለም ካተረፈችዉ ከፍ ያለ ተደማጭነትና ከበሬታ የመነጨ ነዉ፡፡

በሌላ በኩል የጉዳዩ ባለቤት ከሆነዉ መካከል አንዳንዶቻችን  እድገቱን ለማደናቀፍ ከሚፈልጉ ኃይሎች ጋር ሰልፋችንን ስናሳምር ሌሎቻችን ደግሞ የእድገት ትርጉሙ በትክክል አልገባ ብሎን አንዳንዴ በእሌታዊ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ መናር ብቻ እየመዘንና የመልካም አስተዳደር እጦት በፈጠረዉ  ሁኔታ ምክንያት በመማረራችን ምክንያት አድገቱን መጠራጠራችን አልቀረም፡፡ ይሁን እንጂ ማንም ያሻዉን ቢናገርም አገራችንን በፈጣን እድገት ላይ የመሆኗን እዉነትነት አይቀይርም፡፡ ልማታችን   ለአፍታም ቢሆን አይገታም፡፡

ኢህአዴግ ለዚህ ህዝብና ለዚህች አገር የሰራዉ ብዙ እጅግ ብዙ ቢሆንም የሰራዉን ያህል በአደባባይ ምስጋና የተቸረዉ አይመስለኝም፡፡ እሱም ቢሆን የሚጠበቅበትን ከመስራት ባለፌ የተለየ ምስጋና እንዳልፈለገ የሚታወቅ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ አስካሁን በሰራዉ ሥራ ሳይኩራራ ገና ብዙ ተጨማሪ መስራት እንዳለበት በጽኑ ያምናል፡፡ ከሁሉም በላይ ኢህአዴግ ህዝብ በልማት ብቻ እንደማይረካ ከዚያም በላይ እንደሚፈልግ ዘግይቶም ቢሆን አሁን መረዳት የጀመረ ይመስላል፡፡ የህዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ማቆሚያና ማለቂያ እንደለለዉ ኢህአዴግ ከሁላችንም በላይ ተረድቷል፡፡ ብዙዎቹ እንደሚያምኑት አገርን ለማልማት ቆርጦ ለተነሳ መንግስትና ፓርቲ የሕዝብ የልማት ጥያቄን በተሟላ ሁኔታ መልሻለሁ ብሎ ተኩራርቶ ሳይቀመጥ ይልቁንም ሌላ ተጨማሪ ስራ ለመስራት መጣር ነዉ የሚገባዉ፡፡ ለዘመናት ከልማትና ከዲሞክራሲ ርቃ ለኖረች እንደ ኢትዮጵያ ላለች አገር መንግስት መሆን በራሱ እጅግ ፈታኝ ነዉ፡፡ በተለይም ደግሞ የህዝብን ህይወት መቀየር አለብኝ ብሎ ለተነሳ እንዴ ኢህአዴግ ላለ ፓርቲ (መንግስት)  አገር የማልማት አጀንዳ እንቅልፍ የሚነሳና ፈታኝ ነዉ፡፡

በአንጻሩ ደግሞ ከጦርነት አጀንዳ  ዉጭ አገር የማልማት አንዳችም የተለየ ዓላማ ላልነበረዉ  እንደ ደርግና የኤርትራዉ ዓይነት መንግስት ደግሞ የሚያስጨንቃቸዉና የሚሳስባቸዉ የህዝብ የልማትና የዲሞክራሲ ጥያቄ ሲላለለ ለነሱ መንግስት መሆን  እጅግ የቀለለ ተራ ነገር ነዉ፡፡ ለምሳሌ በደርግ ዘመን ህዝቡ መንግስት እንዲያሟላለት አንድም የልማት ጥያቄ ጠይቆ አያዉቅም፡፡ የማያገኘዉን ነገር መመኘት ሲላልነበረበትም ህዝቡ መንግስትን ከመጠየቅ ይልቅ ፈጣሪን መማጸኑን ነበር የመረጠዉ፡፡ ለነገሩ በደርግ ዘመን ህዝብ ለመንግስት የልማት ጥያቄ የማቅረብ፤ መንግስትን የመዉቀስና የመገሰጽ ወይም በሰላማዊ ሰልፍ ተቃዉሞዉን የሚገልጽበት አንዳችም ዕድል አልነበረዉም፡፡ ስለዚህ ደርግ መንግስትነትን የተረዳዉ የህዝብን የልማትና የዲሞክራሲ ጥያቄ የመመለስ ከባድ ኃላፊነት የሚጠይቅ ስራ አድርጎ  ሳይሆን የጦርነት አጀንዳን ማራመድ አድርጎ ነዉ፡፡

4/ ለልማት እንጂ ለዲሞክራሲ ያልታደለዉ ኢህአዴግ ከእንግዲህ ለዲሞክራሲም እንደማይሰንፍ ሊያሳየን በቁጭት ተነስቷል፡፡

ኢህአዴግ የጦርሜዳ የግል ማህደሩ እጅግ በሚያኮራ የጀግንነት ታሪክ የተሞላ ቢሆንም  መንግስት ከሆነ በኋላ ግን በዲሞክራሲ  ጉዳይ ያ የድሮ ወኔዉ ከድቶት ፌሪ ሆኖ ቆይቶ አሁን እንደገና ጀግንነቱ አገርሽቶበት መታየት የጀመረበት ወቅት ላይ የደረሰ አስመስሎታል፡፡ ኢህአዴግ ሀገር በማልማት የተሳካለትን ያህል በዲሞክራሲዉ ረገድ ብዙም የተዋጣለት አይመስልም፡፡ ይህቺ “ ዲሞክራሲ… ምናምን…”የሚሏት ነገር ኢህአዴግን ትንሽ ሳታስቸግረዉ አልቀረችም፡፡ ለዲሞክራሲ ብሎ በረሃ ወርዶ በጠበንጃ ለታገለዉ ኢህአዴግ ዲሞክራሲ አስፈሪ መሆኗ አስገራሚ ነዉ፡፡ በርግጥ ዲሞክራሲ ለሷ ብሎ ለታገለዉም ሆነ የቆየ የትግል ታሪክ ለለለዉም ቢሆን -ሁሉንም ያለ አድሎ የመንግስት ስልጣን እንዲመኝ የማድረግ እድል ስለምትሰጥ  ስልጣን በማን እጅ ልትወድቅ እንደምትችል ማንም እርግጠኛ መሆን ስለማይችል ከዚህ ስጋት በመነጨም ኢህአዴግ ብዙም ባይጠላትም ሊደፍራት ግን እንዳልወደደ መጠርጠራችን አልቀረም፡፡

ኢህአዴግ ከበረሃ የመጣ ሰሞን ስልጣኑን ለብቻዉ ጠቅልሎ መያዝ የሚከለክለዉ አንዳችም ተቀናቃኝ ባልነበረበት በዚያን ወቅት ” ኑ ስልጣን እንጋራ !አገር በጋራ እንምራ“ እያለ  ሁሉን መጋበዙን ለምናስታዉስ ኢህአዴግ በተፈጥሮዉ የስልጣን ንፉግ እንዳልነበር መመስከር እንችላለን፡፡ ይሁን እንጂ በስልጣን ላይ ዉሎ ሲያድር “የሥልጣን መያዝ ዋነዉ ፋይዳ ራስን ማበልጸግ ማስቻሉ ነዉ”የሚል ምስጢር የተገለጠላቸዉ አንዳንድ ባለስልጣኖቹ የህዝብን ጉዳይ ችላ ብለዉ ራሳቸዉን በማበልጸግ ተግባር ላይ በመጠመዳቸዉ አለቅጥ ተስፋ አድርጎ የነበረዉ ህዝብ በድርጅቱና በመንግስት ላይ ማኩረፉ እዉነት ነዉ፡፡ እንደዚያም ቢሆን በዲሞክራሲ ዘወትር የሚነቀፈዉ ኢህአዴግ ከልማቱ ጋር በእኩል ፍጥነትና ጥልቀት አላስከደዉም ለማለት ካልሆነ በስተቀር የዲሞክራሲን ጉዳይ ጭራሽ ዝግ አድርጎታል፤ ከአጀንዳዉም አዉጥቶታል ማለት ግን አይደለም፡፡

የዲሞክራሲ ነገር ክፋቷ ደግሞ በህጋዊ መንገድ በህዝቡ መሃል ሆኖ ከሚንቀሳቀሰዉ ኢዴፓን ከመሳሰሉ ህጋዊ የሆኑ ድርጀቶች ጀምሮ በሽብር ድርጊት ለዓመታት ሲያምሱን የነበሩት ኦነግ(OLF)ና ግንቦት ሰባት የመሳሰሉ የሽብር ኃይሎች ሳቀይሩ ዲሞክራሲን ከለላ አድርገዉ የመንግስትን ስልጣን ለመመኘት አለመከልከሉ ነዉ፡፡ ዲሞክራሲ የትኛዉም የሀገሪቱ ዜጋ በግልም ሆነ በቡድን ተደራጅቶ ስልጣን ለመያዝ መመኘትን የማይከለክል በመሆኑ አቅምና ብቃቱ ያለዉም ሆነ የለለዉ ስልጣንን የማይቋምጥ ስለማይኖር ሁሉም አጋጣሚዉን እየተጠቀመ እድሉን ለመሞከር ይፈልጋል፡፡ በመሰረቱ የመንግስት ስልጣን በህጋዊ መንገድ(በምርጫ) መቆናጠጥን የማያካትት ዲሞክራሲ “ዲሞክራሲ” ሊባል አይችልም፡፡ የዲሞክራሲ መኖር ትልቁ ፋይዳዉ በህዝብ ፈቃድ የመንግስት ስልጣንን በመያዝ አገር ማስተዳደር መቻሉ ነዉ፡፡ ዲሞክራሲ ህዝቡ በድምጹ በፊት በስልጣን ላይ የነበረዉን አዉርዶ በምትኩ ሌላዉን ወደ ስልጣን የሚያወጣ ባይሆን ኖሮ አምባገነን ገዥዎች ዲሞክራሲን ለምን ይጠሉት ነበር ?ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም ሆኑ ኮ/ል መንግስቱ ዲሞክራሲን ለምን ጠሉ?መልሱ ባጭሩ ዲሞክራሲ ስልጣናቸዉን የሚያሳጣቸዉ መሆኑን ስለተገነዘቡ ነዉ፡፡

ኢህአዴግን በሚመለከት በዚህ ጉዳይ ላይ ለመፍረድ ትንሽ ሳያስቸግር አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ ለዲሞክራሲ እዉን መሆን ለአስራ ሰባት ዓመታት ፈታኝ ተጋድሎ ያደረገና ብዙ መስዋእትነት ከፍሎ ለስልጣን የበቃ ሆኖ እያለ  ዲሞክራሲን እንዲህ አንደዋዛ ለቀቅ ለማድረግ ግን ሊደፍር አልቻለም፡፡ ኢህአዴግ በመሰረቱ የዲሞክራሲን ምንነትና አስፈላጊነት ከሁላችንም በበለጠ ይገነዘባል፡፡ ኢህአዴግ እንደ መሪ ድርጅት፤እሱ ራሱ የመሰረተዉ ስርአትና ስርአቱን የሚመራዉ መንግስት በመሰረቱ አምባገነን ተብለዉ ሊፈረጁ የሚገባቸዉ አይደሉም፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ከነ ጉድለቶቹም ቢሆን ዲሞክራት ቢሰኝ የሚበዛበት አይደለም፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ከቀደሙት መንግስታት የሚለየዉ ዲሞክራሲን እየፈለጋትና እየወደዳት መፍራቱ ነዉ፡፡ ከኢህአዴግ በፊት የነበሩት ኮ/ል መንግስቱ ዲሞክራት ያልነበሩ፤ ለመሆን ሞክረዉም የማያዉቁና እንዲያዉም የዲሞክራሲን ምንነት ጠንቅቀዉ ያልተረዱ ሆነዉ እያለ ለዲሞክራሲ አንዳችም ፍርሃት አልነበረባቸዉም፡፡ ዲሞክራሲን ይጠሏት ነበር እንጂ አይፈሯትም ነበር፡፡

ኢህአዴግ ግን አስቀድሜ እንደገለጽኩት ዲሞክራሲን እየወደዳትና ጥቅሟንም ጠንቅቆ እየተረዳ ቢሻዉ ዲሞክራት ለመሆን ሳይሳነዉ ግን ደግሞ መፍራቱ ነዉ፡፡ ከደርግ ጋር ልዩነታቸዉ እዚህ ላይ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ በልማት ረገድ ጀግና የሆነዉን ያህል በዲሞክራሲ መስክ  መጀገን እልቻለም፡፡ ኢህአዴግ አስካሁን ከተጓዘበት መንገድ የተረዳንለት ጉዳይ ቢኖር አስር የፓርላማ ወንበር ለተቃዋሚ ከመልቀቅ ይልቅ አስር የህዳሴዉ ግድብ ዓይነት ቢገነባ ሳይቀለዉ አይቀርም፡፡ ለልማት እንጂ ለዲሞክራሲ ያልታደለ ድርጅት ቢኖር ኢህአዴግ ነዉ፡፡

ለመዉቀስም ለመጥላትም ሆነ ለመዉደድ የማይመች በጣም አስቸጋሪ ድርጅት ኢህአዴግ ነዉ፡፡ በዲሞክራሲ ጉዳይ ስትወቀሰዉ ሀገር ለማበልጸግ ያደረገዉን ርብርብና ዉጤቱን ሲታይ ለምን ወቀስኩት ብለህ ትጸጸታለህ፡፡ በሌላ ግዜ ደግሞ ‹‹ፍትሃዊ ልማት ማረጋገጥ አለብኝ፤ የእድገቱ ለዉጥ እያንዳንዱ መንደርና እያንዳንዱ  ጎጆ ድረስ  መድረስ አለበት›› ብሎ ፎክሮ መተግበር ሲጀምር በጎን እየሰረቁ የሚያስቸግሩ ሌቦችን በዝምታ ማለፉና ቆንጣጭ እርምጃ ለመዉሰድ ልቡ አለመጨከኑ ስታይ እንደገና መልሰህ በኢህአዴግ መማረር ትጀምራለህ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በዲሞክራሲዉ ረገድም ሁሉን ነገር መሬን ይለቅና ያለ ልማዳችንና ያለ ባህላችን ሆኖብን መንገታገትና አጉል መዘባረቅ ስንጀመር “እንደዚህ አላልኩም” ይልና ገጨት ያደርግሃል፡፡ “አረ ይሄ የፓርላማችን ነገር ምነዉ ፓርላማ አልመስል አለ ?”ብትለዉም ልታገኝ የምትችለዉን  መልስ  አስቀድመህ ስለምታዉቅ ዝም ትላለህ፡፡

ኢህአዴግ ከዚህ ቀደም በ97 ዓ/ም አካባቢ ያለ ልማዱ ዲሞክራት ለመሆን ሞክሮ የደረሰበትን ችግር መቼም ቢሆን ይዘነጋዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ወንበር የማይነቅንቅ ዲሞክራሲ ሊኖር እንደማይችልና ያነ የሰራዉ ስህተት ሌላ ግዜ መደገም የማይገባዉ ትልቅ ስህተት መሆኑን ተረድቶ ከዚያ በኋላ ዲሞክራሲን ብዙም ሳይደፍርና ራሱንም ሳያስደፍር መቆየቱ ለዚያ ነዉ፡፡

ኢህአዴግ በተለይ የሚዲያ ነጻነት በተመለከተ ልቡ እንዲጨክን ያደረገዉ የዜጎችን መብት መንፈግ ስለፈለገ እንዳልሆነ ሁላችንም ጠንቅቄን እናዉቃለን፡፡ እኛ የመብቱ  ተጠቃሚ መሆን ይገባን የነበርን ዜጎች  በህገመንግስቱ የተጎናጸፍነዉን ይህን መብት በአግባቡ እንዳንጠቀም እንቅፋት የሆነን አንዳንድ ህገወጥ ጋዜጠኞች በፈጠሩት ችግር እንጂ በኢህአዴግ አይደለም፡፡ ያልተሰራዉን እንደተሰራ፤ ያልተነገረዉን እንደተነገረ ያልሆነዉን እንደሆነ እያስመሰሉ ሲጽፉ እያየ “አስኪ ይሁን መቼም “እያለ በዝምታ አለፋቸዉ፡፡ የግል ጋዜጦች መንግስትን እንዳሻቸዉ ሲጨፍሩበት  እያየ ዲሞክራሲ ስለሆነ መቼም ምን ማድረግ እችላለሁ እያለ በትእግስት አለፋቸዉ፡፡ ትንሽ ሰንበትበት ሲሉ ግን ወደ አደገኛ ዘመቻ ተሸጋገሩ፡፡  ህዝብን በህዝብ ላይ የማስነሳትና አንዳንዶቹ ደግሞ የጦርነት ነጋሪት መጎሰም ደረጃ ደረሱ፡፡

ጭራሽ ኦነግ የተባለዉ ሽብርተኛና እጅግ ዘረኛ የሆነ ቡድን ባጄት መድቦላቸዉ እንደሚሰሩ ቀድሞዉኑ ይጠረጠሩ የነበሩ አንዳንድ ጋዜጦች በግላጭ የኦነግ ቃል አቀባይነትና የዉጭ ግኑኝነት ስራ መስራትን ተያያዙ፡፡ የኦነግን ፕሮግራም ማስተዋወቅና ከዚያም በላይ ሄደዉ ኩሩዉ የኦሮሞ ህዝብን አስደንብረዉ  ብን ብሎ ጫካ እንዲገባ ለማድረግ ብዙ ብዙ መርዘኛ ቅስቀሳ አደረጉ፡፡ ባይሳካላቸዉም፡፡  አንዳንድ የህትመት ዉጤቶች ሌላዉን ጉዳይ  ትተዉ ስራቸዉ ሁሉ በኦነግና በሻእቢያ የታዘዙትን ሁሉ አንድም ሳያስቀሩ መቸከችክ ሆኖ አረፈዉ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በህዝቡና በመንግስት ጥርስ ዉስጥ ያስገባቸዉ ለሀገሩ ሉአላዊነት በየቦታዉ እየተዋደቀ የነበረዉን መከላከያ ሰራዊትን ከዓላማዉ ለማዘናጋትና ስርአቱን ፤የወጣበትንና ሊገለግለዉ ቃለመሃላ የፈጸመለትን ህዝብ አንዲክድ መሰሪ ቅስቀሳ ማድረግ መጀመራቸዉ ነበር፡፡

አንዳንድ ጋዜጠኞች ለሻዕቢያ መልእክተኛ በመሆን ባጄት ተመድቦላቸዉና ቀለብ እየተቆረጠላቸዉ በጸረ-ኢትዮጵያ ፕሮፖጋንዳ ሲተባበሩት እንደነበር እናስታዉሳለን፡፡ በጦርነቱ ግዜም ሀገር የማዳን ፈታኝ ስራ ላይ ተጠምዶ የነበረዉን መንግስትና መከላከያ ሰራዊት በማጥላላት ለሻዕቢያ ወራሪ ሰራዊት የሞራል ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ በጋዜጣ በይፋ መለቀቅ ያልነበረባቸዉ አንዳንድ ወታደራዊና የሀገር ደህንነት  ምስጢሮችን አስከመዘክዘክ ድረስ ብዙ ጥፋት ሲያጠፉ ቆይተዋል፡፡ መንግስት ይሄን ሁሉ ጥፋት እያጠፉ  እያየ ዝም ማለቱን አሱንም ለጥፋት ተባባሪ እንደነበረ አስቆጥሮት ነበር፡፡ እንግዲህ ከዚያ በኋላ ነዉ መንግስት ባለበት ኃላፊነትና ተጠያቂነት መሰረት አንዳንድ ቁጥጥሮችን ለማድረግ የተገደደዉ፡፡

ያም ሆኖ እንዲያስተካክሉና ከህገወጥ ምግባራቸዉ እንዲታቀቡ  ከመምከርና ከመገሰጽ ዉጭ ጭራሽ ስራቸዉን እንዲያቆሙ መንግስት አላደረገም፡፡ አብዛኛዎቹ የህትመት ዉጤቶች ስራቸዉን ያቆሙት በመንግስት ተጽኢኖ ምክንያት ሳይሆን አንደ ቀድሞ ብዙ አንባቢ ማግኘት ባለመቻላቸዉ ኪሳራ ላይ ስለወደቁ በራሳቸዉ ዉሳኔ ለመዝጋት በመገደዳቸዉ ነዉ፡፡ ዛሬም ብቅ እያሉ ፈጥነዉ የሚሰወሩ የህትመት ዉጤቶች ባይጠፉም በህዝቡ ዘንድ እንደ ቀድሞዉ ተነባቢ መሆን ባለመቻላቸዉ ብዙም ሳይቆዩ ከህትመት ዉጭ ይሆናሉ፡፡ እንግዲህ በዚህ ጉዳይ ብዙ ሲታማ የነበረዉ ኢህአዴግ ዲሞክራሲን ያለ አግባብ መጫወቻና መቀለጃ ሲያደርጉ እያየ በዚያ መንገድ መቀጠል አደገኛነቱን በመረዳቱ “ ከእንግዲህስ ዲሞክራሲ እንዲህስ ከሆነ ይቅርብኝ! ሲፈልግ ጥንቅር ይበል!” ብሎ ቢያማርር እንዴት ይፈረድበታል?

ኢህአዴግ ለዲሞክራሲ ድፍረት እንዳይኖረዉ ያደረግነዉ እኛዉ ራሳችን ነን፡፡ ዲሞክራሲዉ እንደ ምኞታችን ማበብ ባለመቻሉ የተጎዳነዉ እኛ ብቻ ሳንሆን ኢህአዴግም ጭምር ነዉ፡፡ ኢህአዴግ እንዲበረታታ አላደረግነዉም፡፡ በራሱ ተነሳሽነት ትንሽ ለቀቅ ሲያደርግ ደግሞ በሀገሪቱ ህግ የለለ እስኪመስል ድረስ ትርምስ እንፈጥራለን፡፡ ዲሞክራሲን ዲሞክራሲያዊ ባልሆነ መንገድና ለጥፋት ዓላማ ለመጠቀም ለሚፈልጉ ወገኖች ገና ለገና ዲሞክራት አይደለህም እባላለሁ ብሎ መንግስት ሁሉን ነገር ልቅ ማድረግ አልነበረበትም፡፡ ፡ስለዚህም ነዉ አንዳንዴ ኢህአዴግን የዲሞክራሲ ፈሪ የሚያስመስሉት ባህሪትን የምናይበት፡፡

አሁን ግን ኢህአዴግ  ከዚህ ፍርሃቱ እየተላቀቀ የመጣ ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ  ለዚህ ህዝብና ለዚህች አገር ብዙ ነገር ሰርቶና አበርክቶ እያለ ነገር ግን በዚህች “ዲሞክራሲ“ በሚሏት ጣጠኛ ነገር  የተነሳ  የሰራዉ ሁሉ እንዳልተሰራ መቆጠሩ አጅግ የቆጨዉና የከነከነዉ ይመስላል፡ኢህአዴግ ዲሞክራስን ለቀቅ ካደረግሁ ስልጣን እነጠቃለሁ የሚለዉ ነባር ስጋቱ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አሁንም ባይለቀዉም ነገር ግን እንደ በፊቱ “በመቃብሬ ላይ !“ከሚለዉ  ደረቅ አቋሙ ተለሳልሶ በራሱ ላይ ማስተካከያ ያደረገ ይመስላል፡፡ ኢህአዴግ ዲሞክራሲን በሰፊዉ ካራመደ ከማንም በላይ ቀድሞ ተጠቃሚ የሚሆነዉ እሱ እንደሆነ ተረድቷል፡፡ ዲሞክራሲን ልክ እንደ ልማቱ አጠንክሮ ብይዝ  ኢህአዴግ አሁን ከህዝብ እያገኘ ካለዉ ተቃባይነትና ከበሬታ  እጅግ በበለጠ ሊያገኝ እንደሚችል ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም፡፡ እሱ በርትቶ ዲሞክራሲን እዉን ለማድረግ ይድፈር እንጂ ህዝብ ምን በወጣኝ  ብሎ ነዉ ኢህአዴግን በሌላ የሚቀይረዉ?ለሎቹማ ባለፈዉ ሰሞን ህዝብ ጭንቅ ላይ በነበረበት ወቅት ህዝብን ለማረጋጋትና አጥፊዎችን ለመገሰጽ ስንቀሳቀሱ ባለመታየቸዉ ህዝቡ ስለታዘባቸዉ  ከእንግዲህ ወዲያ በተቃዋሚዎች ላይ አመኔታ ይጥላል ተብሎ በጭራሽ አይታሰብም፡፡

ለዚህም ነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ በኢህአዴግ አመራር ሁልግዜም ተስፋ ከማድረግ ያልተቆጠበዉ፡፡ ኢህአዴግ እየሰራ እንዳልሰራ የሚቆጠር፤ባሰኘን ግዜ ሁሉ በሰራዉ ሆነ ባልሰራዉ ሁሉ ያለ ኃጢያቱ በአደባባይ የምንወቅሰዉ መንግስት መሆኑን ህዝቡ ይገነዘባል፡፡ ብዙዎቻችንም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ህገመንገስታዊ መብት በተግባር የተለማመድነዉ ኢህአዴግን ባጠፋዉም በላጠፋዉም ሁሉ በመንቀፍ ነዉ፡፡  ስለዚህ እንደ ልማቱ ዲሞክራሲዉንም በርትቶ እንዲይዝ ከመጎትጎት ባለፈ ይህችኑን መብት ያጎናጸፈንን ህገ መንግስት ማብጠልጠልና መንግስትንም ለማጉደፍ ተብሎ አምባገነንና ጸረ-ዲሞክራሲ የሚል ቅጽል መስጠት ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በዚያ ደረጃ የሚፈረጅ አይደለምና፡፡ እያንዳንዳችን በግላችን በእለት ከእለት እንቅስቃሴያችንና ምግባራችን  ዲሞክራሲያዊ አመለካከት ለመያዝ ተስኖን እያለ ከመንግስት ብዙ መጠበቃችንም ተገቢ አይመስለኝም፡፡

5/ ኢህአዴግ የህዝብን አመኔታ የሚፈጥሩ ስራዎች ላይ ቅድሚያ ትኩረት ማድረግ ይገባዋል

ኢህአዴግ ስለ ጥልቅ መታደስ ካበሰረን ገና አጭር ጊዜ ቢሆንም ገና ከጅምሩ ተስፋ ፈንጣቂና አበረታች እርምጃዎቹን በተግባር ማዬት ጀምረናል፡፡ አሁን በያዘዉ መንገድ መግፋት ከቻለ ቃል እንደተገባዉም ለህዝቡ ጋሬጣ የሆኑ ችግሮች ሁሉ ይወገዳሉ የሚል እምነት አሳድሯል፡፡ ነገር ግን መዘንጋት የለለብን ነገር  አንዳንድ ችግሮች በባህሪያቸዉ ከሌሎች በተለዬ  ዉስብስብነት ያላቸዉና ለመፍትሄዉም በተነጻጻሪ ዘለግ ያለ ጊዜ የሚጠይቁ ሊሆኑ ስለሚችሉ በአንድ ጀምበር በሁሉም ላይ ለዉጥ መጠበቅ ያለብን አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ ለወጣቶች ስራ የመፍጠር ጉዳይ ከችግሩ ስፋትና ዉስብስብነት በመነጨ ፈጣሪ ራሱ  ከሰማይ ወርዶ ካላገዘን በስተቀር በአንድ ጊዜ መፍትሄ የሚያገኝ ነገር አይደለም፡፡  ይልቅስ ከመንግስት መጠበቅ ያለብን ዋናዉ ጉዳይ ቁልፍና አንገብጋቢ የሆኑ ችግሮችንና የሕዝብ ጥያቄዎችን በሚገባ ለይቶና ቅደም ተከተል አስቀምጦ ተግባራዊ መፍትሄ መስጠት መጀመሩን ነዉ፡፡

መንግስት ተስፋ የሚሰጡና በህዝቡ ዘንድ ተአማንነትን የሚፈጥሩለትን ተግባራት መፈጸም ሲጀምር ህዝብ ከጎኑ ስለሚቆም እንደተራራ ከብደዉ የታዩን  ችግሮቻችን ሁሉ አንድ በአንድ በጋራ እያስወገድናቸዉ መሄድ እንችላለን፡፡ ኢህአዴግና መንግስት ህዝብን በስፋት ሞብላይዝ ማድረግ ከቻሉ ችግሮችን የማናስወግድበት ምክንያት አይኖርም፡፡  ስለዚህ ኢህአዴግ ትኩረት ማድረግ ያለበት ከህዝቡ አሜነታ የሚያስገኙለትንና የህዝብን “የይቻላል!” ተስፋ የሚፈነጥቁ  ተግባራት ማከናወን ላይ ነዉ፡፡ ከዚያ ዉጭ ይሄንንም ያንንም መነካካት ከጀመረ አንዱንም አሟልቶ ሳይሰራ ባለበት ቆሞ ይቀራል፡፡ እንደገና ተመልሶም ወደ ቀዉስ ሊገባ ይችላል፡፡ መንግስት ነጻነት ተሰምቶት ሰላም በሰፈነበት ሁኔታ ሳይረበሽ ሃላፊነቱን መወጠት ይገባዋል እንጂ  ሁኬት በበዛበት ሁኔታ አንዳችም ነገር ሊሰራ አይችልም፡፡ በአንድ ጊዜ ተአምር ሰርቶ እንዲያሳየን መንግስትን ማስጨነቅም አይኖርብንም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ልስራ ካለ የሚያቅተዉ ነገር የለም የሚል እምነት መያዙ ጥሩ ሆኖ ነገር ግን  ከልክ በላይ በማጣደፍ ለአልጠበቅነዉ ችግር ልንዳረግ እንችላለንና ትእግስተኛ መሆንና ትንሽ ፋታ መስጠቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

6/ የጥልቅ ተሃድሶዉ ስኬት አብይ መለኪያ ሙስናንና  አባካኝነትን  መቀነስ መቻሉ ላይ ነዉ፡፡

አንዳንድ ለዉጦች በዓይን የማይታዩ በእጅ የማይዳሰሱ በቁጥር ለመግለጽ የማይመቹ ሊሆኑ ስለሚችሉ ለዉጡን ለመረዳት ለህዝቡ ማስቸገሩ አይቀርም፡፡  መንግስት በቁርጠኝነት በግልጽ እርምጃ ወስዶ በተግባር ማስመስከር ካለበት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰዉ ዝርፊያን ወይም ሙስናን ማስቆም ነዉ፡፡ ሙስና ወይም ራስን በህገወጥ መንገድ  ለማበልጸግ ተብሎ የሚፈጸም  ስርቆትን ማስቆም ላይ መንግስት መበርታት አለበት፡፡ ሙስናን ከኢትዮጵያ ምድር ቢቻል ሊያጠፋ ካልቻለ ደግሞ ለመቀነስ ቃል ገብቶ የነበረዉ የጸረ- ሙስናና የስነምግባር ከሚሽን ምን እየሰራ እንደሆነ ለመረዳት አስከሚስያቸግረን ድረስ ከኮሚሽኑ አንዳችም ጠብ የሚል ነገር ማግኘት ሳንችል ቆይተናል፡፡ ምናልባት ኮሚሽኑ የተሰጠዉን ሙስናን የመታገል ኃላፊነት ትቶ የስራ ለዉጥ አድርጎ እንደሆን ይነገረን ስንል ምሬታችንን ስንገልጽ ቆይተናል፡፡ ፈቃደኝነቱ እያለዉ ነገር ግን የአቅም እጥረት አጋጥሞት ነዉ  ከተባለም ከልማት ተሞክሮ በተጓዳኝ በዚህ መስክም  ከቻይና መማር የሚገባን አንዱ ጉዳይ ሙስናን እንዴት እየታገሉ እንደሆነ ነዉ፡፡

አማራጭ ከጠፋም ጥቂት የቻይና ኤክስፔርቶችን አስመጥተን በተግባር እንዲያሳዩን ማድረግ ይቻላል፡፡ ከዚህ ዉጭ ግን ኮሚሽናችን በሰሞኑ ሁኔታ  እንኳን ትንሽ ደንገጥ ብሎና  በመንግስት ቁርጠኝነት ተበረታትቶ የሆነ ስራ ሰርቶ ያሳየን ይሆናል ብሎ ህዝቡ ተስፋ ማድረጉ ግልጽ ነዉ፡፡ የህዳሴዉን ግድብ የሚያክል  ሁለት ፕሮጄክት ሊያሳራ ይችል ነበር የተባለለት ያህል የዉጭ ምንዛሬ ወደ ዉጭ በህገወጥ መንገድ ተሻግሯል  ተብሎ በተደጋጋሚ የሰማነዉ መረጃ እዉነት አለመሆኑን እንኳን ማረጋገጫ ሊሰጠን አልቻለም፡፡

መንግስትንና ፓርቲዉን ከለላ አድርገዉ ማንም አይነካንም በሚል እብሪት ተወጥረዉ አስካሁን እንዳሻቸዉ ሲዘርፉ የቆዩትን አሁን መንግስት ባሳየዉ ቁርጠኝነት ሰግተዉ ከድሮዉ አሁን ትንሽ ደንገጥ ማለታቸዉ ባይቀርም የኢህአዴግን አመል ቀድሞዉኑ ጠንቅቀዉ  ለሚያዉቁት ለእነዚህ ሙሰኞች ከጥቂት ግዜ በኋላ ከየተደበቁበት ጎሬ ብቅ እያሉ እንደለመዱት ወደ ዝርፊያዉ እንዳይገቡ ኢህአዴግ የድሮዉ ዓይነት ልፍስፍስ አለመሆኑን በተግባር ማሳየት አለበት፡፡ ኮሚሽኑ ደግሞ ተቀዳሚ ኃላፊነቱ ነዉና በተግባር እንዲያሳየን እንጠብቃለን፡፡ ከዚህ ቀደም በአንባገነኑ የደርግ አገዛዝ ዘመን ሁለት ኪሎ በርበሬ ደብቀዋል በተባሉት ላይ  ዘግናኝ አርምጃ ሲወሰድ እንደነበር ለምናስታዉስ  ሰዎች አሁን እንደእኔ ያለ ማህይም አስተካክሎ መቁጠር የማይችለዉን ያህል ሃብት በዝርፊያ ያከማቹ ሌቦች ላይ ለምን መራራት እንዳስፈለገን አልገባ ብሎን ቆይቷል፡፡

ቻይና ለምድር ለሰማይ የከበዱ  ቱባ ቱባ ባለስልጣናቷን በሙስና ምክንያት መቅጣቷን በኛዉ የመንግስት ሚዲያ እየሰማን በቅናት እርር ስንል ቆይተናል፡፡ እኔ በበኩሌ ሙስና ከባድ ቅጣት የሚያስቀጣ አደገኛ ወንጀል መሆኑን በሚገባ ለመረዳት የቻልኩት የቻይናን ጨከን ያለ ቅጣት ሁኔታ ከተከታተልኩ በኋላ ነዉ፡፡ ሳተላይት ማምጠቅና  ዩራኒዬም ማብለያ  መስራት ቢያቅተን ሌባ መቅጣት እንዴት ይሳነናል?ከቅርብ ግዜ ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ እነዚህን ሙሰኞች  በወረንጦ እየለቀመ መሆኑን መስማት ጀምረናል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከመቶ በላይ የሚቆጠሩ ሙሰና የተጠረጠሩ በቁጥጥር ስር አድርጎ ሃብት እገዳ ማድረጉን ስንሰማ ማድነቃችንና መደሰታችን እዉነት ነዉ፡፡ ማን ያዉቃል ያ ወደ ዉጭ ተሰርቆ ወጣ የተባለዉን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አስመልሶ ያስፈነድቀን ይሆናል፡፡ በርቱ እንላለን፡፡

ከዚሁ ጉዳይ ብዙም ሳንርቅ ራሱ ድርጅቱ(ኢህአዴግ) የአንድ አገር ህዝብን የሚያህል በሚሊዮን የሚቆጠር አባላት መያዙ ለብዙ ችግሮች ተጋላጭ እንድንሆን ሁኔታዉን ያመቻቸ ስለሚመስለኝ  ብቃቱና ቁርጠኝነቱ ያላቸዉን ጥቂት አባላቱን በማስቀረት ሌላዉን ከአሁኑ በግዜ ማሰናበት ይገባዋል፡፡ የሀገሪቱ ህዝብ ስድስት ሚሊዮን ካድሬ ለመሸከም የሚያስችለዉ  ጫንቃ የለዉም፡፡ አገር ለማስተዳደርና የድርጅት ዓላማን ወደ ህዝብ ለማዉረድ ስድስት ሚሊዮን የፓርቲ አባል መያዝ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ደርግ አገር ምድሩን ሲገለባብጥ የኖረዉና ሰጥ ለጥ አድርጎ መግዛት የቻለዉ እኮ በቁጥር ስልሳ ሺህ በማይሞሉ አባላቱ ነዉ፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ  ቢበዛ ከግማሽ ሚሊዮን የማይበልጥ አባላት መያዝ  ይበቁታል፡፡ ከዚያ በላይ ሲሆን አስካሁን እንዳየነዉ እኛን ችግር ዉስጥ ከቶ ራሱም መቸገሩ ላይቀር እንዲያዉም ከሱ ቁጥጥር ዉጭ ህዝቡን እያማረሩ ከሚያስኮርፉበት ጥቂቶቹን ብቻ ይዞ ሌላዉን ማሰናበት ይገባዋል፡፡ የኢትዮጰያ ህዝብ እንደሆን ለመመራትም ሆነ ለመገዛት የሚያስቸግር ህዝብ ስላልሆነ በዚህ ረገድ ኢህአዴግ ብዙ ባይጨነቅ ይመከራል፡፡ ኢህአዴግ የሚያስፈልጉት በሚሊዮኖች የሚቆጠር አባላት ሳይሆን በሚሊዮን የሚቆጠር ደጋፊ ህዝብ ነዉ፡፡ መተማመን ያለበትም በህዝቡ እንጂ በአባለቱ ብዛት መሆን አይገባዉም፡፡

ለህዝብ ትዝብት ከዳረጉና ከፍተኛ ብክነት ከሚታይባቸዉ መካከል መስተካከል የሚገባዉ አንዱ  በየቦታዉና በየጊዜዉ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ አጋጣሚዉን  በመጠቀም ኃላፊነትና ተጠያቂነት በጎደለዉ ሁኔታ የሚወጣዉ የህዝብ ገንዘብ ነዉ፡፡ በየስብሰባዉ ላይ ሰርግና ምላሽ የሚመስል ድል ያለ ድግስ፤አላስፈላጊ የአጀንዳና በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀ  አስክርብቶ ፤የአንገት ሰካርፍና ቲ ሸርት ማደል ፤ ልዩ የዉሎ አበልና የአልጋ ኪራይ ወዘተ ይሄ ሁሉ ወጭ ለዚህች ደሃ አገር አለማዘን ስለሚመስለኝ  ለህዝብ ተቆርቋሪ የሆነ  ሁሉ ሌላ ትርፍ ነገር መጠየቅ ሳያሻዉ  ህዝብን  በሃቅ ማገልገል ይገባዋል፡፡ በረባ ባልረባዉ ሁሉ ነጋ ጠባ በተሰበሰቡ ቁጥር የህዝብ ገንዘብ አለአግባብ የሚባክንበት ምክንያት አይኖርም፡፡  ስለዚህ የተጠቀሰዉ ዓይነት አባካኝ አሰራር በአስቸኳይ መቆም ይኖርበታል፡፡ ለሙስናና ስርቆት አንዳችም ቀዳዳ መክፈት አያስፈልግም፡፡ ከሰሞኑ የተከታተልናቸዉ ስብሰባዎች ባልተለመደ ሁኔታ በደረቁ መሆን አይተን ለዉጡ እታች ድረስ እየወረደ መሆኑን በተግባር ለማረጋገጥ አንድ ማስረጃ ሆኖናል፡፡

7/ ከጅምላ (ከቡድን) ተጠያቂነት ወደ ግል ተጠያቂነት መሸጋገር መቻል አለበት፡፡

ኢህአዴግ ከጀመረዉ አካሄዱ ለመታዘብ እንደቻልኩት አንድም ነገር ወደ አደባባበይ ሳይወጣ ተዳፍኖ መቅረት የለበትም በሚል መንፈስ ከሚገባዉ በላይ  ተራ የሚመስሉና ለአደባባይ የማይበቁ ገበናዎቹን ሁሉ ያለ ምህረት እየዘከዘከ  ነዉ፡፡ ከዚህ ቀደም አንድም መልካም ነገር ሳይሰራ የቆየ በሚያመስል መልኩ ስለ ጥንካሬዉ ለመናገር ድፍረት አንሶት ድክመቱን ማጉላት ላይ መበርታቱን  እጅግም አልወደድኩለትም፡፡ የምንናገረዉና ለህዝብ ቃል የምንገባዉ አስካሁን ብዙ የተለፋበትን ስራ ዋጋ በሚያሳጣና ከዘሮ ለመጀመር እንደተፈለገ በሚያስመስል መልኩ መሆን አይኖርበትም፡ኢህአዴግና መንግስት ባለፉትት ሃያ አምስት ዓመታት አንዳችም ስራ አልሰራንም ካሉ ከዚህ በኋላ ለአንድት ቀንም ቢሆን በስልጣን ላይ መቆየት አይገባንም ብለዉ ራሳቸዉ ማረጋገጫ እንደሰጡ ነዉ የሚያስቆጥረዉ፡፡

ኢህአዴግ ምናልባት ለትህትና ያህል ብሎ ካልሆነ በስተቀር በሰራዉ ስራ  እንዳይኮራ የሚያደርገዉ አንዳችም ምክንያት አይኖርም፡፡ ህዝብ የኢህአዴግን በጥልቀት መታደስ በተስፋ የተቀበለዉም ኢህአዴግ ልስራ ካለ ሊሰራ የሚችልና አስካሁንም ብዙ እጅግ ብዙ ነገር መስራቱን ስለሚገነዘብ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ ከሱ ድክመት ያልመነጩና በባህሪያቸዉ ዉጫዊ የሆኑ ይልቁንም ጸረ- አንድነት በሆኑ የዉጭ ኃይሎች ሴራ  የተፈጠሩ ችግሮችን ሁሉ  ሳይቀር ከሱ ድክመት የመነጨ ችግር አድርጎ መቀበሉን አግባብነት የለዉም፡፡ ከዚሁ ጋር አብሮ መጠቀስ ያለበት እንከን ቢኖር ድክመቶችንና እጥረቶችን ሁሉ የጋራ ችግር አድርጎ መቁጠሩ በግል ተጠያቂነት ይልቅ የቡድን እንዲመስልና  ሁሉንም ችግርና  ወቀሳ ለመጋራት የመፈለግ አዝማሚያ  ሲታይ ቀድሞዉን የማይነኩና የማይደፈሩ ናቸዉ የተባለላቸዉን አንዳንድ የድርጅቱን ሰዎች ላለመንካት ሸፋፍኖ ለማለፍ የተፈለገ አስመስሎበታል፡፡ አንዱ የሌላዉን ጥፋት እንዳያወጣና አርስ በርስ ለመሸፋፈን አመቺ አድርጎታል፡፡ አንዱ ሌላዉን በማስፈራራት ብታጋልጠኝ እኔም አጋልጥሃለሁ እየተባባሉ ገሜናቸዉን ለመደባበቅ አመቺ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ከጅምላ  ይልቅ  ወደ ያንዳንዱ  ግለሰብ መዉረድ ካልጀመረ ለዉጡን መቀለጃ ነዉ የሚያደርጉትና ይታሰብበት፡፡

8/ ጥልቅ ተሃድሶዉ  ኢህአዴግን ጉልበት ለመስጠት እንጂ ለማዳከም ያለመ መሆን አይገባዉም

ድርጅቱን ማደስ ማለት ድክመቶችን አስወግዶ  ለወደፊቱ  ተጠናክሮ መቀጠል ማለት እንጂ ብዙ ተአምር ሲሰራ የቀየን ድርጅት ማፍረስ ወይም ማዳከም ማለት ሊሆን አይገባዉም፡፡ ድርጅቱን  ለዚህ ያበቁትን ፤ በሃላፊነት መንፈስ ሰርተዉ ሀገር በማልማት ረገድም ግንባር ቀደም ሆነዉ የቀዩትን አባላቱንና መላዉን ደጋፊዉን  እንዲሁም በኢህአዴግ አመራር አገሪቱ ትልቅ ቦታ ትደርሳለች በሚል አመኔታ ያደረባቸዉ ዜጎችን ተስፋ ማስቆረጥና በጥፋተኝነት ስሜት አንገት ማስደፋት አይገባም፡፡ አንዳንድ የድርጅቱ ሰዎች በልወደድ ባይነት መንፈስ ይመስለኛል ራሳቸዉም የድርጅቱ አመራር አካል መሆናቸዉን እየዘነጉ  በድርጅቱ ላይ ቆመዉ መልሰዉ የድርጅቱ ወቃሽና ገመና ገላጭ መሆናቸዉን ሳይ በጣም ይገርመኛል፡፡

አንዳንዶቹ ደግሞ ድሮ የእግዜር ሰላምታ እንኳን ለመስጠት ከሚጸየፉት ጋር ሆነዉ በየመሸታ ቤቱና በየካፈዉ ሳይጠየቁና ሳይገረፉ ስለ ድርጅቱ ሃጢያት መለፍለፋቸዉ ትዝብት ላይ ከመጣል ዉጭ የሚያስገኝላቸዉ ትርፍ አይኖርም፡፡ ህዝብ በድርጅቱና በመንግስት ላይ አመኔታ እንዳይኖረዉ የሚያደርግ አካሄድ አጅግ አደገኛ ነዉ፡፡

9/ የአማራጭ ጠንካራ ፓርቲ አለመኖር ኢህአዴግንም  ጭምር ሊያሳስበዉ ይገባል

በኢህአዴግ በኩል  አስካሁን በምንቸገረኝነት ችላ ተብለዉ የቆዩ ከዚህ በኋላ ግን በሃላፊነት መንፈስ መስራት ያለበት አንድ አብይ ጉዳይ አለ፡፡ ኢህአዴግ  የዚህችን ታላቅ አገርና ህዝብ ዕድል ብቻዉን ለመወሰን እንደማይችልና እንደማይገባዉም ተረድቶ ሌላ ተገዳደሪና ሃላፊነት መሸከም የሚችሉ አማራጭ ፓርቲዎች ጉልበት የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት፡፡ ልክ ዘንድሮዉ  እንደ ገጠመን ዓይነት መጥፎ ሁኔታ ቢከሰት በስልጣን ላይ ያለዉ ፓርቲ  ከዉጭም ሆነ ከራሱ በሚመነጩ ምክንያቶች የቅቡልት ቀዉስ (legitimacy crisis) ሲያጋጥመዉ አገሪቱ ለአደጋ እንዳትጋለጥ ህዝቡን “እኔ አለሁላችሁ” በሚል ለችግር ግዜ ደራሽ ሊሆን የሚችል አማራጭ ሁነኛ ፓርቲ  አለመኖሩ  ኢህአዴግንም ጭምር ሊያሳስበዉ የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ የኢህአዴግን ያህል ብቃት ባይኖረዉ እንኳን   በችግር ግዜ ቢያንስ ህዝብን አረጋግቶ ለጊዜዉ እንኳን ማቆየት የሚችል ፓርቲ መጥፋቱ ኣሳሳቢ ነዉ፡፡

ይህ ባልተሟላበትና ህዝቡ አማራጭ ፓርቲ ለማማተር አድል ባላገኘበት ሁኔታ“ በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል”እንደሚባለዉ ሆኖብን ኢህአዴግንም ለማዳከም መሞከር ትልቅ  ስህተት ነዉ፡፡ በርግጥ ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ መፍጠር የኢህአዴግ ድርሻ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ፓርቲ ጠፍጥፎ ሰርቶ እንካችሁ ማለትም አይጠበቅበትም፡፡ ከዚያ ይልቅ ምናልባት የሀገራችን ፓርቲዎች አንዱም ከሌላዉ የማይሻሉና አገር መምራት ይቅርና አንድ ቀበሌ ህዝብ የማስተዳደር ብቃት የለለቻዉ የሆኑበትን ምክንያትና  በመንግስት ረገድ ምን እንደጎደለባችዉ በግልጽ አማክሮአቸዉ የሚጠይቁትን ቴክንካዊና ህጋዊ ድጋፍ ሁሉ  ሊያደርግላቸዉ ይገባል፡፡ ኢህአዴግ አዉቆና ፈቅዶ ህዝብ እየፈለገዉም ቢሆን በቃኝ ትንሽ ልረፍ ብሎ መልቀቂያ ካላስገባ በስተቀር የኛ አገር ፓርቲ ተብየዎች በዚህ አያያዛቸዉ በእኔ አድሜ ለቁም ነገር የሚበቁ አልመሰለኝም፡፡

10/ ህገመንግስቱን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ካሁኑ ዝግጅት ሊደረግባቸዉ ይገባል፡፡

ኢህአዴግ ህገ መንግስቱንም ሆነ በተለይ ከምርጫ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ  ማስተካከል የሚቻልበት ሁኔታ ካለ ለመሞከር ፈቃደኛነቱን  አሳዉቋል፡፡ እነዚህ ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ከበድ ያለ ስራ የሚይጠቁና በቂ የዝግጅት ግዜም የሚያስፈልጋቸዉ መሆኑን ስለምረዳ ቀጣዩ ምርጫን ለማካሄድ ከቀረን በጣም አጭር ግዜ አኳያ  ስራዉ መቼ እንደሚጀመር መገመት አልቻልኩም፡፡ የእኔ ስጋት  በዚህ ከባድ ጉዳይ ላይ ለህዝቡ አጉል ቃል ገብተን  በሌሎች ትናንሽ ጉዳዮች ተዉጠንና ተዘናግተን   ቀላል በተገባዉ ዋናዉ ጉዳይ ላይ አንድም  የረባ  ስራ  ሳንሰራ የምርጫዉ ግዜ ይደርስና ዉጤቱ አላምር ስል ወደ ሌላ ቀዉስ እንዳንገባ ነዉ፡፡ ከዉስብስብነቱ በርካታ ባለሙያ መጠየቁ ሰፊ የህዝብ ተሳትፎና ምክክር  የሚጠይቅ በመሆኑ  ከሚቀጥለዉ ምርጫ በኋላ እንኳን ከደረሰልን  ጥሩ ነዉ፡፡ አስፈላጊዉ ዝግጅት ግን ግን ከአሁኑ መጀመር ይገባል፡፡ ኢህአዴግ በዚህ ረገድ ቁርጠኝነትን ሲላሳየ ብቻ በችኮላ የምናደርገዉ ነገር አይደለም፡፡

11/ ኤርትራን በሚመለከት የእስካሁኑ የችግሩ አፈታት መንገድ እንደገና ሊጤን ይገባዋል

መንግስት በጀመረዉ ዘርፌ ብዙ በሆነ መታደስ እንደገና ሊፈተሹ  ከሚገባቸዉ አብይ ጉዳዮች አንዱ በዉጭ ግኑኝነት ፖሊሲያችን ረገድ በተለይ ከኤርትራ ጋር ያለዉ ግኑኝነት ሁኔታ ነዉ፡፡ ኤርትራን በሚመለከት አስካሁን ስንከተለዉ የነበረዉ አካሄድ ተገቢና ህገመንግስቱ ላይ የተቀመጡትን መሪሆዎች ጋር የሚጣጣም እንደሆነ አዉቃለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ኤርትራን በሚመለከት  በተግባር ከሰጠዉ ዉጤት አንጻር ሲቃኝ አጥጋቢ ባለመሆኑ በአዲስ አካሄድ ሊፈተሸ የሚገባዉ ነዉ፡፡ የኤርትራ አመራር በሚያደርስብን ዴባ ምን ያህል እንደተቸገርን ሁላችንም እናዉቃለን፡፡ እንደዚያ ከመሰለዉ ችግር ለዘለቀታዉ መገላገል የምንችለዉ ደግሞ ሰፍኖ የቆየዉን የጠላትነትን ስሜት አስወግደን በምትኩ የወዳጅነትና የወንድማማችንት ስሜት መፍጠር ስንችል ብቻ ነዉ፡፡ ኤርትራ በቀጥታ ራሷ ከምታደርስብን ትንኮሳ በላይ በጣም አሳሳቢ የሆነዉ ለሌሎች ታሪካዊ ጠላቶቻችን መሳሪያና  ለሽብር ኃይሎች መሸጋገሪያ የመሆኗ ጉዳይ ስለሆነ ኤርትራን ከነሱ መነጠል የምንችለዉ በመካከላችን የቆየ ችግራችንን ለዘለቀታዉ መፍታት ስንችል ነዉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ግፊት ማድረግ ያለብንም እኛ ነን፡፡ ከኤርትራ ይመጣል ብለን መጠበቅ አይኖርብንም፡፡ እነሱ ራሳቸዉ በቆሰቆሱት ጦርነት ጦስ ከፍተኛ ቀዉስ ዉስጥ በመግባታቸዉና በጦርነቱም በደረሰባቸዉ ሽንፈት ሳቢያ ከፍተኛ ሃፍረት ዉስጥ በመግባታቸዉ በነሱ በኩል ሊመጣ የሚችል የእርቅ ሃሳብ እንደማይኖር ልንረዳ ይገባል፡፡ በሰሩት እኩይ ስራ እጅግ ለናቃቸዉ ህዝባቸዉ ይዘዉ የሚቀርቡት  የሆነች ነገር ያስፈልጋቸዋል፡፡ በባዶ እጅ ወደ እርቅ መምጣት እንደሚከብዳቸዉ ልንረዳላቸዉ ይገባል፡፡  ስለዚህ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞክረዉት በሻእቢያ በኩል ፈቃደኝነት በመጥፋቱ ተሰናክሎ የቀረዉ በሰጥቶ መቀበል መሪህ ላይ የተመሰረተዉ ባለ አምስት ነጥብ የሰላም ሃሳብ እንደገና ተከልሶና የእነሱ ፍላጎትም ታዉቆ አዲስ ንግግር ቢጀመር መልካም ይመስለኛል፡፡ እነሱ ከኛ የሚፈልጉት በትክክል ምን እንደሆነ ይታወቅና ጉዳዩ ለህዝብ ቀርቦ ህዝብ አጉል ከመቋሰል የሰጠነዉን ሰጥተን መገላገሉ ይሻለኛል ካለ  በዚያ መንገድ መሞከሩ ይመረጣል፡፡

በሻዕቢያ ወረራ ጦስ የወደቁ ጀግኖቻችን  የበለጠ የሚታወሱትና ክብር የሚያገኙት  ዘላቂ ሰላም መፍጠር ስንችል እንጂ ለዘላለም በዉጥረት ዉስጥ በመቆየታችን አይደለም፡፡  ከሰሞኑ ጃፓንና ሩሲያ በጀመሩት አዲስ ንግግር “ ኩሪል ደሴትን “በሚመለከት በሩሲያ በኩል የተያዘዉ የተለሳለሰ አዲስ አቋም ለኛም ትምህርት ሊሆነን ይገባል፡ግትር አቋም ማራመድ ከጉዳት በስተቀር አንዳችም ጥቅም አይኖረዉምና ይታሰብበት፡፡

ማጠቃለያ

ኢህአዴግ እንደ  አያያዙ ከሆነና በዚህ መልኩ ሳይደነቃቀፍ መዝለቅ ከቻለ በዚህች አገር ብዙ ብዙ ተአምር ሊሰኙ የሚችሉ ስራዎች ሰርቶ እንደሚያኮራን አልጠራጠርም፡፡ በኛ  በኩል ትንሽ ትእግስት ማጣታችንና መሰረታዊ ለዉጥን በአንድ ጀምበር እዉን እንዲሆን መጠበቃችን ከፋ እንጂ ኢህአዴግ ለዉጥ እንደሚያመጣ መተማመናችን በጎ ነዉ፡፡ በተለይም እንደ ጉድለለት በተቆጠረዉ በዲሞክራሲዉ ረገድ ተስፋ ሰጪ ጅምሮችን እያየን ነዉ፡፡

ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸዉ ለዉጦች ከህዝቡ የንቃተህሊና ደረጃ በላይና ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ዉጭ ሊሆኑ አይቻላቸዉም፡፡ በአንድ ነገር ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ ሌላዉን ችላ ማለት ሲዉል ሲያድር ችግር ሊያመጣ እንደሚችል ከሃገራችን ሁኔታ ለመረዳት እንችላለን፡፡ ዲሞክራሲን ከልማቱ ጋር በእኩል ፍጥነትና ጎን ለጎን ማስከድ ባመቻላችን አንዱ ቀድሞ ሌላዉ ወደኋላ በመቅረቱ ብዙ ጣጣ እንዳመጣብን በተግባር አይተናል፡፡

ዛሬ ደግሞ የሚያስፈልገን ዲሞክራሲ እንጂ ልማት አይደለም የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ይዘን ብዙ የተደከመበትን  የልማት እንቅስቃሴችን እንቅፋት እንዳይገጥመዉ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ ኢህአዴግ የጀመረዉ የጥልቅ መታደስ ስራ ያለ ህዝብ ተሳትፎ ግቡን ልመታ ስለማይችል ሁላችንም የየበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይገባናል፡፡ ኢህአዴግ ህዝቡን እጅግ ያስመረረዉን ሙስናን ለማጥፋት ወይም ለመቀነስ ድፍረቱ ሊኖረዉ ይገባል፡፡ የህዝብ አመኔታ የሚስገኙለትን ስራዎች ላይ በርትቶ መስራትም ይገባዋል፡፡

ኢህአዴግ ካሰበበት ለመድረስ የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ በመሆኑ  አድርባይና ቅልስልስ ከሆኑና እምነት ከማይጣልባቸዉ አንዳንድ ደካማ ሰዎች ራሱን እያጸዳ መሄድ እንደለበት አንመክራለን፡፡ በሰሩት መጥፎ ስራ ምክንያት ህዝብ ፊት መቅረብ የሚያሳፍራቸዉና የሚሸማቀቁ አመራሮች አያስፈልጉንም፡፡ በራሳቸዉ የሚተማመኑና ንጹህ እጅና ንጹህ አይምሮ ያላቸዉ አመራሮች ወደ መድረኩ እንዲመጡ ይደረግ፡፡ የአቶ ኃይለማሪያምን ቆራጥና ብስለት የተሞላበት አመራር የተመለከቱና ከዚህ ቀደም በአቶ መለስ ሞት ለተደናገጡና በሳቸዉ አለመኖር ቀጣይ የሀገሪቱን ዕጣ ፋንታ ሲጠራጠሩ ለቆዩ ዜጎች ትልቅ እርካታ የሠጠ ነዉ፡፡ በዚሁ ቀጥሉበት እላለሁ!

******* 

የኮ/አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሌሎች ጽሑፎች ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፡፡

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories