Dec 28 2016

በመከላከያ ሰራዊታችን የፖርቲ ፖለቲካ ገለልተኝነትና ተያያዥ ጉዳዮች [ክፍል 2]

(/ አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሽፈራው)

(የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ)

9/ በሰራዊቱ ዉስጥ ገለልተኝነትን የሚሸረሽርና ለኢህአዴግ የወገነ አሰራር አልነበረም፡፡

የመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ሰነዱ የሰራዊቱን ገለልተኝነት የሚሸረሽር ስለመሆኑ በሰራዊት ግንባታ ሰነዱ ላይ ዉይይት በተደረገባቸዉ ጊዜያትም ሆነ  ከዚያ  በኋላ በሰራዊቱ ዉስጥ አንድም ጊዜ ቅሬታ ሲቀርብ  አልሰማሁም፡፡ በሰራዊቱ ዉስጥ በነበርኩበት ወቅት በመመሪያዉ ላይም ሆነ በአፈጻጸም ረገድ በሰራዊቱ ገለልተኝነት ላይ የቀረበ ትችት ስለመኖሩ አላስታዉስም፡፡ በርግጥ አንዳንድ የቀድሞዉ ነባር ታጋዮች አካባቢ ለዚያዉም በጣም ጥቂቶቹ ዘንድ ለቀድሞ ድርጅታቸዉ በተለየ ሁኔታ የመቆርቆር ነገር አልፎ አልፎ በግለሰብ ደረጃ ቢታይም ከሰራዊቱ በጡረታ አስከተገለልኩበት ድረስ “ገዥዉን ፓርቲ መወገን ይገባችኋል” የሚል መመሪያ ሲሰጥ በጭራሽ አልሰማሁም፡፡ እንዲያዉም ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መንገድ  ለየትኛዉም የፖለቲካ ፓርቲ መወገን ህገወጥ መሆኑንና በገለልተኝነት ስራችንን መስራት እንደሚገባን ህገመንግስቱንና የሰራዊቱን መተዳደሪያ ደንብ መነሻ በማድረግ በተደጋጋሚ ዉይይት ከመደረጉና መመሪያ ከመሰጠቱ ዉጭ ከህገመንግስቱ ጋር ተጻራሪ በሆነ ደረጃ ሰራዊቱን ለገዥዉ  ፓርቲ የስልጣን ጠባቂ ለማድረግ የተደረገ አንዳችም ሙከራ አልነበረም፡፡  

በርግጥ በምርጫ 97 ወቅት የመከላከያ ሰራዊቱን ገለልተኝነት በሚሸረሽር መልኩ የሰራዊቱን አባላት በማወናበድና አጉል ተስፋ በመስጠት  ወደራሳቸዉ ለመጥለፍ የሞከሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንጂ ኢህአዴግ አልነበረም፡፡ በወቅቱ የ97ቱን ምርጫ ተከትሎ ከተፈጠረዉ ግርግር ጋር ተያይዞ በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥም በተደረጉ ግምገማዎችና ሂስና ግለሂስ መድረኮች ላይ ከህገመንግስቱ ደንጋጌ ዉጭ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የተለየ ወገናዊነት በማሳየት ከህግ ዉጭ ለመንቀሳቀስ የሞከሩ አባለት እየተለዩ ግማሹ በግለሂስ በይቅርታ ሲታለፉ አክራሪ አቋም ይዘዉ ራሳቸዉን ለማስተካከል ያልፈቀዱ በጣም ጥቂቶቹ ደግሞ ከሰራዊቱ እንዲሰናበቱ መደረጉን አስታዉሳለሁ፡፡ የተባረሩትም ሆኑ ግለሂስ አድርገዉ እንዲቀጥሉ የተደረጉት ተቃወሚ ፓርቲን የደገፉ ብቻ ሳይሆን ገዢዉ ፓርቲንም የወገኑትም ጭምር ነዉ፡፡ ገዢ ፓርቲን ለመደገፍ መሞከር ተቀዋሚ ፓርቲን ለመደገፍ ከመሞከር ተለይቶ ስለማይታይ ለየትኛዉም ፓርቲ አንዳችም የዉገና ሁኔታ እንዳይኖር ጥረት ሲደረግ እንደነበር አስታዉሳለሁ፡፡

1997ቱ ምርጫ በአዲስ አበባ ላይ ቅንጅት ማሸነፉን በሚመለከት የተሰማቸዉን ስሜት ማንም ሳያስገድዳቸዉ በመግለጽ ራሳቸዉን ግለሂስ ያደረጉ የቀድሞ ነባር ታገዮች መካከል እንዲህ ያሉ ይገኙበታል፡፡ ‹‹“የአዲስ አበባ ህዝብ ኢህአዴግን ከዳዉ፤ ኢህአዴግን በቅንጀት ለወጠዉ፣ ትልቅ ክህደት ነዉ የተፈጸመብንበማለት በህዝቡ ላይ ቅሬታ መያዜ ትክክል አይደለም፡፡ ከአንድ ህገመንግስታዊ ገለልተኛ ሰራዊት የማይጠበቅ አመለካከት ተንጸባርቆብኛል›› የሚል ግለ -ሂስ ማንም ሳይጠይቃቸዉና ሳያስገድዳቸዉ በራሳቸዉ ላይ ያቀረቡ ነበሩ፡፡ ከዚህ ግለሂስ ለመረዳት እንደሚቻለዉ በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ የገለልተኝነት ጉዳይ ምን ያህል ትኩረት ተሰጥቶት እንደነበር ነዉ፡፡ በወቅቱ የነበረዉ ሂስና ግለሂስ ዋናዉ ዓላማ  ለምን “ኢህአዴግን ወይም ተቃዋሚን መረጣችሁ?” በሚል አልነበረም፡፡ ማንም የፈለገዉን  የመምረጥ መብት አስካለዉ ድረስ በዚህ ጉዳይ የተነሳ ጥያቄም አልነበረም፡፡ ለዚያዉም ማን የትኛዉን ፓርቲ እንደመረጠ ለማወቅ በማይቻልበት ሁኔታ ይሄ ጉዳይ ለጥያቄ የሚነሳም አልነበረም፡፡

ዋናዉ ጉዳይ የነበረዉ ከምርጫዉ በኋላ በመደበኛ የሥራ ሰዓት ስራቸዉን እርግፍ አደርገዉ ትተዉ ከአንዱ የስራ ቦታ ወደሌላዉ እየተዘዋወሩና ቢሮ እየቆለፉ  ነጋ ጠባ ስለ ፓለቲካ ወሬ ሲሰልቁ የሚዉሉና ከዚያም አልፈዉ ቅስቀሳና የፓርቲ አባልነት ምልመላ አስከማድረግ የተደረሰበት፤ እንዲሁም በሽብርተኛዉ ቡድን በኦነግ ተልእኮ ተቀብለዉ የጥፋት ዓላማ ያለዉ የቅስቄሳ ወረቀት በግቢዉ ዉስጥ በድብቅ መበተንና የግቢዉን ደህንነት ስጋት ላይ በመጣላቸዉ በዚህ ተግባር የተሳተፉ በግምገማና በጥቆማ ተለይተዉ ከሰራዊቱ እንዲሰናበቱ ተድርጓል፡፡  በወቅቱ የነበረዉ ግምገማም  ይሄንና የመሳሰለዉ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነበር እንጂ “ማን ቅንጅትን መረጠ? ማን ኢህአዴግን መረጠ?” በሚል አልነበረም፡፡ እንግዲህ በዚህ ደረጃ እጅግ አደገኛ አመለካከት ያላቸዉና በተግባርም አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ሲያደርጉ የተደረሰባቸዉ ጥቂት ሰዎች ለተቋሙ ደህንነት ሲባል ከስራዊቱ መወገዳችዉን አስታዉሳለሁ፡፡ እንደዚያ ዓይነት እርምጃ መወሰዱ ትክክልና መደረግ የነበረበት ነበር፡፡ ይህ እርምጃ የተወሰደዉም በድብቅ  ሳይሆን መላዉ የሰራዊቱ አባላት በተገኙበት ጥፋታቸዉ በይፋ ተገልጾና እምነዉ እንዲካላከሉ ተደርጎና ተጨማሪ አስተያየትም ከሰራዊቱ ቀርቦባቸዉ የተወሰደ ዉሳኔ ነዉ፡፡

ከዚያ ዉጭ ግን በግንባታ መመሪያዉ ምክንያት የመከላከያ ሰራዊቱን ገለልተኝነት የሚሸረሸር ተግባር በሰራዊቱ ዉስጥ ሆን ተብሎ ስለመሰራቱ አላዉቅም፡፡ በሰራዊቱ ዉስጥ ሲሰሩ የነበሩና አሁንም እየተሰሩ ያሉ የኢንዶክተሪኔሽን ስራዎች መከላከያ ሰራዊቱን ከህገመንግስቱ ፍላጎት አኳያ በመቅረጽ ላይ ያተኮረ እንጂ የፓርቲ ፖለቲካ ቅስቀሳ አልነበረም፡፡ ሰራዊቱ ዉይይት ሲያደርግባቸዉ የነበረዉ በመንግስት ፖሊሲዎች ላይ እንጂ በኢህአዴግ ፕሮግራም ላይ አልነበረም፡፡ ስለ ኢህአዴግ እንደ አጀንዳ ተይዞ የተነገረበትን ወቅት አላስታዉስም፡፡ ከኢህአዴግ ጋር የተያያዘ ጽሁፍም በሰራዊቱ ዉስጥ አልነበሩም፡፡

Photo – Ethiopian troops in AMISOM

Photo – Ethiopian troops in AMISOM

10/ የመከላከያ ሰራዊታችን አባላት የፓርቲ ዝንባሌ በእኔ እይታ ሲቃኝ፤

የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ለየትኛዉም ፓርቲ መወገን የሚከለክል ህግ ቢኖርም ማንኛዉም አባል በግሉ ለሚፈልገዉ ፓርቲ ጥሩ አመለካከት ለመያዝ መቻሉ ከገለልተኝነት መሪህ ጋር የሚጋጭ አይደለም፡፡ የመከላከያ ሰራዊቱ በምርጫ ወቅት የፈለገዉን ዕጩ እንዲመርጥ የሚደረገዉም ይሄንን ከግምት በማስገባት ነዉ፡፡ ስለሆነም በጥናት ላይ የተደገፈ መረጃ ባይኖረኝም የሰራዊቱ አባላት የትኛዉ ፓርቲ ይበልጥ እንደሚማርካቸዉ ዝንባሌቸዉን ለመገመት አላዳገተኝም፡፡ ይህ ዝንባሌ ከ97 ምርጫ ወቅትና ከዚያ ዉጭ በነበሩት ጊዜያት የተለያዩ እንደነበር ማስታወስ እወዳለሁ፡፡

ላለማወሳሰብ ስል የፓርቲ ዝንባሌን በሶስት ምድብ መክፈሉን መርጫለሁ፡፡ (1) የገዢዉ ፓርቲ (ኢህአዴግ) ደጋፊ፣ (2) ተቃዋሚ (ቅንጅት፤ ኢዴፓ፤ የኦሮሞ ድርጅቶችና ህብረት በዋነናነት በዚህ ስር ይካተታሉ)፤ (3) ገለልተኛና አቋማቸዉ ተለይቶ የማይታወቅ ናቸዉ፡፡ በዚሁ መሰረት ከ97 ምርጫ በፊት- ኢህአዴግ 75%፤ ተቀዋሚ 15%፤ገለልተኛና የማይታወቅ 10% ነበር፡፡ በ97 ምርጫ ሰሞን -የኢህአዴግ ደጋፊ 60%፤ ተቃዋሚ35% ፤ገለልተኛና የማይታወቅ 5% ነበር፡፡ ከ97 ምርጫ በኋላ እስካሁን ባለዉ ጊዜ- የኢህአዴግ ደጋፊ 90% ተቃዋሚ  5% ገለልተኛ 5% ነዉ፡፡

በዘጠና ሰባቱ  ምርጫ ሰሞን ተቀዋሚዎች ሰራዊቱን ወደራሳቸዉ ለመሳብ ብዙ እንደጣሩና በተወሰነ ደረጃ እንደተሳካላቸዉ መረዳት አያዳግትም፡፡ ለዚህም የረዳቸዉ ከነሱ ቅስቀሳ ብቃት ይልቅ በሰራዊቱ ዉስጥ በነበረዉ ሰፊ አስተዳደራዊ ችግር መማረርና ብሶት መብዛት፤ ከጦርነቱ በኋላም  በተሃድሶዉ ወቅት በተፈጠረዉ ቀዉስ ምክንያት ነዉ፡፡ ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት መከላከያና መንግስት በሰራዊቱ ዉስጥ የነበሩ አስተዳዳራዊ ችግሮችን ከሞላ ጎደል በመቅረፋቸዉ፤ ሰፊ የሪፎርም ስራዎች መሰራታቸዉ፤ በሃገሪቱ ዉስጥ በተጨባጭ እየታየ ባለዉ ልማት በመማረካቸዉና በተጨማሪም ተቃዋሚ የሚባሉት እምነት የማይጣልባቸዉ መሆኑን ሲገነዘብ ለዚህች አገር ከሁሉም የተሻለዉ አማራጭ ኢህዴግ ነዉ የሚል አመለካከት መፍጠሩ አልቀረም፡፡

ሰራዊቱ የዚህ አይነት አመለካከት ለመያዝ ማንም አስገድዶት ሳይሆን በራሱ ፈቅዶ ያደረገዉ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ገዥዉ ፓርቲ ሰራዊቱ እንዲደግፈዉ ወይም ወደሱ ዝንባሌ እንዲኖረዉ ሆን ብሎ የሰራዉ ነገር የለም፡፡ ያ ማለት ግን ኢህአዴግ የሰራዊቱን ድጋፍ አይፈልገዉም ማለት እንዳልሆነ ግን መዘንጋት የለበትም፡፡ በዚህ መሰረትም 90% በላይ የሚሆነዉ የሠራዊቱ አባላት በግላቸዉ ቀልባቸዉ ከኢህአዴግ ጋር እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ዝንባሌ የነበራቸዉ  የቀድሞ የኢህአዴግ ነባር ታጋዮች ብቻ ሳይሆኑ ከ83 ዓ/ም በኋላ ወደ ሰራዊቱ የተቀላቀሉና በተጨማሪም እንደእኔ ከቀድሞዉ ሰራዊት የመጡትም ጭምር እንደሚያካትት መታወቅ አለበት፡፡

ከድሮዉ ሰራዊት የመጣነውን ከኢህአዴግ ነባር ታጋዮች እና ከአዲሶቹ የሰራዊት አባላት ለየት የሚያደርገን ነገር ቢኖር ሁለቱንም ስርአቶች ማለትም የቀድሞዉንም የአሁኑንም በተግባር የማዬትና የመመዘን እድሉ ስለነበረን ስለኢህአዴግም ሆነ ስለስርአቱ የነበረን አመለካከትና አቋም  ከጭፍን ወገኝተኝነት ወይንም ጥላቻ በጸዳ ሁኔታ በእምነት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ነዉ፡፡ እኛን በሚመለከት  አብዛዎቻችን የነበረብን ችግር ባለፈዉ ስርአት ዉስጥ ፖለቲካን በሚመለከት ከነበረን መጥፎ ትዉስታ የተነሳ በየትኛዉም መድረክ ላይ በየትኛዉም ጉዳዮች ላይ በግልጽ አመለካከትን ወደ መድረክ ለማዉጣት ያለመፈለግ/የመቸገርና መደበኛ ስራ ከተሰራ ሌላዉ ዕዳዉ ገብስ ነዉ የማለት ዝንባሌ መኖሩ ነዉ፡፡

እንደዚያም ሆኖ አብዛኛዉ ከቀድሞወ ሰራዊት የመጣዉ አመለካከቱና ዝንባሌዉ ለስርአቱና እንደፓርቲም ለገዢዉ ፓርቲ ቀና አመለካከት እንደነበረዉ  አስታዉሳለሁ፡፡ በርግጥ የማይካድ ነገር በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በኛ ላይ ጫና እንደነበረ መካድ አይቻልም፡፡ በግል ለገዢዉ ፓርቲ ለኢህአዴግ ቀና አመለካከት የነበራቸዉም በነባሩ የቀድሞ ታጋዮች ዘንድ “እንዴት ከኛ እኩል ኢህአዴግን ሊደግፉ ይችላሉ” በማለት የመጠራጠር ሁኔታ በተወሰኑ ሰዎች ዘንድ እንደነበር አስታዉሳለሁ፡፡ አንዳንዴ የድሮዉ ስርእት ናፋቂ ተደርጎ መቆጠርም አለ፡፡ እንደዚያም ቢሆን ይሄን ያህልም የሚያማርር አልነበረም፡፡

ለአንድ ፓርቲ የግል ዝንባሌ መኖር ከገለልተኝነት መርህ ጋር የሚጋጭ ነገር እንዳልሆነ በዚህ አጋጣሚ መግለጽ የሚገባኝ ይመስለኛል፡፡ የዳበረ ዲሞክራሲ በገነባችዉ በአሜሪካም የመከላከያ ሰራዊታቸዉ አባላት ዉስጥም አብዛኛዎቹ ከዲሞክራትስ ፓርቲ ይልቅ ለሪፖብሊካን ፓርቲ የተለየ አድናቆትና ዝንባሌ እንዳላቸዉ በጥናት የተደገፈና በሚገባ የሚታወቅ ነዉ፡፡ አንዳንዴ በዘንድሮዉ የምርጫ ዘመን የዲሞክራትክ ፓርቲ እጩ ፕሬዝዳንትን የመረጠ በሚቀጥለዉ ምርጫ ዘመን ደግሞ ካልመሰለዉ አቋሙን ቀይሮ  የሪፖብሊካን ፓርቲ ዕጩ ፕሬዝደንትን ሊመርጥ ይችላል፡፡  ስለዚህ ለአንድ ፓርቲ በግል የሚኖረዉ ዝንባሌ ከህገ መንግስቱ ድንጋጌ ጋር በሚጋጭ መልኩ በደጋፊነትና በተቃዋሚነት ደረጃ የሚገለጽ ካልሆነ በስተቀር እንዲሁ በደፈናዉ አንድን የሰራዊት አባል ለገዥዉ ፓርቲ ሆነ ለሌላ ተቃዋሚ ፓርቲ በግሉ ዝንባሌ ሲላለዉ ብቻ  ገለልተኝነትን የሚሸረሽር ተግባር ተደርጎ ሊቆጠር የሚገባዉ አይደለም፡፡

11/ ሀገሪቱ የምትመራበት ፖሊሲዎች ላይ የሰራዊቱን ግንዛቤ ለመፍጠር የሚደረግ ስራ የፓርቲ የፓለቲካ ሥራ እንደተሰራ የሚያስቆጥር አይደለም፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት መንግስት በየጊዜዉ በሚያወጣቸዉ የተለያዩ  የልማት ተኮር ፖሊሲዎችና ድንጋጌዎች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ዉይይት ሲያደርጉ የሚያዩ አንዳንድ የዋህ ሰዎች መከላከያ ሆን ብሎ ህገመንግስቱን በመጣስ ሰራዊቱን የፓርቲ ፕሮግራምን እያስተዋወቀ እንደሆነ አድርገዉ የሚቆጥሩ እንዳሉ አዉቃለሁ፡፡ ይህ ግን እጅግ የተሳሳተ አመለካከት ነዉ፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ በሀገሩ ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ ፖሊሲዎችን ስትራቴጂዎችንና ልዩ ልዩ መመሪያዎች ላይ የጠራ ግንዛቤ ሳይኖረዉ ለሀገሩ ፍቅርና ለስርአቱ አክብሮትና አድናቆት ከቶ ሊኖረዉ አይችልም፡፡ በስርአቱ ትክክለኛነት ላይ ለማመን በቅድሚያ ከህገመንግስቱ ጀምሮ ስርአቱን እንደ ስርአት ባቆሙ መመሪያዎች ላይ የጠራ ግንዛቤ ሊኖረዉ የግድ ነዉ፡፡ በማያምንበት ጉዳይ ላይ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን መጠበቅ አይችልም፡፡ ስለዚህ በመንግስት መመሪያዎች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረዉ ሰራዊቱን ማስተማርም ሆነ ማወያየት የፓርቲ መመሪያን ለማስተዋወቅ እንደተደረገ ተደርጎ መቆጠር የሚገባዉ አይደለም፡፡ በፓርቲ መመሪያና በመንግስት መመሪያ መካከል ያለዉን ልዩነት ሳያጤኑ በዘፈቀደ በሚሰጥ ትችት በመደናገጥ ብዙዎቹ የዋህ የሆኑ የሰራዊቱ አባላት በመመሪያዎቹ ላይ የመወያየት ተገቢነት ላይ ይጠራጠሩ እንደነበር በሚገባ አስታዉሳለሁ፡፡

ፖለቲካዊ ንቃት ያለዉ (politically conscious) ወታደር መሆንና ፖለቲከኛ መሆን የተለያዩ ጉዳዮች ናቸዉ፡፡ ወታደሮች የፖለቲካ ተዋናይም ሆነ የፖለቲካ እንቅስቀሴ ዉስጥ በማናቸዉም ደረጃ  ተሳታፊና አራማጅ (political activist) መሆን አይገባቸዉም፡፡ ይህ ማለት ግን ወታደር የፖለቲካ መሃይም መሆን አለበት ወይም ደግሞ  የሀገሪቱ መንግስት የሚከተለዉ ፖለቲካና ፖሊሲዎች ምንነት የማይገባዉና አለም አቀፍ ሁኔታዎችንም መተንተንና መረዳት የማይችል ደንቆሮ መሆን አለበት ማለት አይደለም፡፡ በተለይ ወታደራዊ መኮንኖች የሀገሪቱን ፖለቲካ በሚገባ የሚገነዘቡና ሃገራዊና አለምአቀፋዊ ሁኔታዎችን በቅጡ ማንበብና መተንተን  የሚችሉ መሆን አለባቸዉ፡፡ የሀገሪቱን የሲቪል  አመራር ፍላጎት ለመረዳት የሚቻለዉ የሀገሪቱን ወይንም የመንግስትን ፖለቲካ  ጠንቅቀዉ ሲያዉቁ ነዉ፡፡ የፖለቲካ ግንዛቤዉ ከፍተኛ የሆነ ሰራዊት የፓለቲካ መሃይም ከሆነ ሰራዊት በበለጠ ገለልተኛ ይሆናል፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ ለአንድ ፖለቲካ ፓርቲ አቀንቃኝ መሆን የለበትም፡፡ በፓርቲ ፖለቲካ ዉስጥ( partisan politics) ገብቶ መሳተፍ አይገባዉም፡፡ ከህገመንግስቱ ጀምሮ ሀገሪቱ የምትመራበትን ፖሊሲዎች፤ ሌሎች ህጎችንና መመሪያዎችን ጠንቅቆ የማያዉቅ የመከላከያ ሰራዊት አባል የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ለማሰጠበቅ ብሎም ህገመንግስታዊ ስርአቱን ለመጠበቅ አይችልም፡፡

12/ ፓርቲና ዉትድርና በተደበላለቀበት በደርግ ስርአት የሰራዊት ገለልተኝነት የሚታሰብ አልነበረም፤

የአንድ አገር መከላከያ ተቋም የሚገኝበት ስርአት ነጸብራቅ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ  የሀገሪቱን መከላከያን በማዬት ሰራዊቱ ስለአለበት ስርአት መናገር ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ስርአቱን በማየትም ስርአቱን እያገለገለ ሲላለዉ ሰራዊት ባህሪይ መናገር አይከብድም፡፡ ከዚህ መንፈስ ስንነሳ የደርግ ስርአት አምባገነናዊ ስርአት ስለነበር ስርአቱ የመሰረተዉ ሰራዊትም የስርአቱ ባህረይ ወራሽ መሆኑ ላይ የሚያከራክር አይደለም፡፡

በደርግ ስርአት የገለልተኝነት ሁኔታ ፈጽሞ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ እንዲያዉም ቃሉና ጽንሰ ሃሳቡ ራሱ አይታወቅም፡፡  ወታደር በቀጥታ ከፓርቲ አመራር በሚቀበልበት ስርአት ገለልተኝነት ብሎ ነገር አይታሰብም፡፡ ይሄ በኛ አገር ብቻ ሳይሆን ለብዙ ዓመታት በቅርብ በማወቀዉ የሶቭዬት ህብረት ዉስጥ አብዛኛዉ መኮንን የሶቭየት ኮሚኒስት ፓርቲ አባል ነበረ፡፡ በቻይናና በኩባ በአጠቃላይ በሁሉም  ሶሻሊሰት ሀገሮች ሀኔታዉ ተመሳሳይ ነበር፡፡ በደርግ ስርአት ከፓርቲዉ አመራሮችም ሆነ   ተራ አባላት በአብዛኛዉ የሰራዊቱ አባላት ነበሩ፡፡ የሰራዊት አባላት የፓርቲ አባላትም በሆኑበት  ሁኔታ ስለ መከላከያ ገለልተኝነትና ህዝባዊ ወገንተኝነት ማንሳት እንደሞኝነት የሚቆጠር ነዉ፡፡

በፓርቲዉ (ኢሠፓአኮ/ኢሠፓ)ና በመከላከያ ተቋሙ መካከል አንዳችም ልዩነት ባልነበረበት ሁኔታ ስለገለልተኝነት እንደ ጥያቄ የሚነሳ ጉዳይም አልነበረም፡፡ ወታደሩ ባንድ ጊዜ ወታደርም ፖለቲከኛም በሆነበት በዚያን ጊዜዉ ሁኔታ የፓርቲ አባል ለመሆን ከመሽቀዳደም ዉጭ ራስን ከፓርቲዉ ለመነጠል መሞከር ፈጽሞ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ፓርቲዉ በሰራዊቱ ዉስጥ ነበር፡፡  ሰራዊቱም በፓርቲዉ ዉስጥ ነበረ፡፡ የፓርቲዉ መዋቅር ከላይ አስከ ታችኛዉ ጓድ ድረስ በወታደራዊ ተቋሙ ዉስጥ ተዘርግቶ በግላጭ  የፓርቲም የወታደራዊ ጉዳይም በአንድነት በሚሰራበት በዚያ ሁኔታ ዉስጥ ስለ ገለልተኝነት  ማሰብ ጨርሶ የሚታሰብ አይደለም፡፡

እኔ ራሴ የፓርቲዉ አባል እንድሆን ከተደረኩ በኋላ ነዉ ለትምህርት ወደ ዉጭ ለመላክ የበቃሁት፡፡ በሰራዊቱ  ዉስጥ የፓርቲ ፖለቲካ ስራ እንኳን እዚህ አገር ቤት ይቅርና ለትምህርት በተላክንበት ዉጭ አገርም ቢሆን አልቀረልንም ነበር፡፡ በደርግ ስርአት መላዉ ሰራዊት ፓርቲዉ የሚከተለዉን አይዲኦሎጂ ማጥናት ግዴታ ነበረበት፡፡ እንዲያዉም የፓርቲ ፖለቲካዊ ስራ በጦር ኃይል ዉስጥ (Party Politiclal Works in Armed Forces) የሚባል የትምህርት ዘርፍ በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ በዚህ በቋሚነት ይሰጥ ነበር፡፡  በዚህ አጋጣሚ አንባቢ እንዲረዳልኝ  የምፈልገዉ በደርግ ወቅት ስለነበረዉ አብዮታዊ ሰራዊት (የኢህድሪ ሰራዊት)ና የአሁኑን የአፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት እያነጻጸርኩ ወይም እያወዳደርኩ ሳይሆን በተነሳዉ ጉዳይ ላይ እግረመንገዴን የተወሰነ መረጃ ጣል ለማድረግ በማሰቤ መሆኑን ነዉ፡፡

በሁለቱ ስርአት የነበሩት መከላከያ ሰራዊት መሰረታዊ ልዩነቶች አሉዋቸዉ፡፡

አንደኛ፡የደርግ ስርአት መድበለ ፓርቲ ስርአት ያልነበረበትና መንግስታዊ ፓርቲ ከሆነዉ ኢሰፓአኮ/ኢሰፓ ዉጭ ሌላ ፓርቲ በህግ የተከለከለበት ሁኔታ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም መከላከያ ሰራዊቱ በሃገሪቱ ብቸኛ የነበረዉን ፓርቲ አባል እንዲሆን በመደረጉ ሰራዊቱ የአንድ ፓርቲ አገልጋይና ጠባቂ መሆን መቻሉ የሚያስገርም አይደለም፡፡ በደርግ ስርአት በፓርቲዉና በሰራዊቱ መካከል አንዳችም ልዩነት አልነበረም፡፡ አብዛኛዎቹ  የሰራዊቱ አባላትም የፓርቲ አባላት አባላት መሆን ችለዉ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ጭረሽ የፓርቲዉ የፖሊት ቢሮና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባለት ነበሩ፡፡ የዚህ ዓይነት ሁኔታ በነበረበት ስርአት ዉስጥ ስለ ሰራዊቱ ገለልተኝነት እንደ ጥያቄ ማንሳት ትርጉም አይኖረዉም፡፡ በደርግ ህገመንግስት ሳይቀር “ከኢሠፓ ዉጭ ሌላ ፓርቲ አይኖርም” የሚል ድንጋጌ በግልጽ በተቀመጠበት ሁኔታ መከላከያም እንደተቋም ለገዢዉ ፓርቲ ታማኝና አገልጋይ መሆኑ የሚያስገርም ሊሆን አይገባዉም፡፡

ሁለተኛ፡ በደርግ ስርአት ወቅት የሰራዊት ግንባታ መመሪያ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ በርግጥ በደርግ ስርአት ዉስጥ በጭፍን “አድርግ አታድርግ ከሚል” ደረቅ የሆነ ወታራዊ ድስፕሊን ዉጭ ሰራዊቱን በስርአት ለመምራትና ለማሰተዳደር የሚያገለግል አንዳችም መመሪያ አልነበረም፡፡

ሶስተኛ፡በደርግ ስርአት ዉስጥ የሰራዊት መተዳደሪያ ደንብ የሚባል ነገር በወቅቱ አይታወቅም፡፡  ያ ማለት ሰራዊቱ መብቱንም ግዴታዉንም የማያዉቅና እንዲያዉቅም የማይፈለግና በግለሰቦች ፍላጎት ብቻ የሚመራ ግኡዝ አካል ነበር ማለት ይቻላል፡፡

አራተኛ፡ሰራዊቱ በየትኛዉ አዋጅ እንደተቋቋመ ግዳጁ ከየትኛዉ ህግ ወይንም ህገመንግስት እንደሚመነጭ አይታወቅም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አንድም ጊዜ ዉይይት ተደርጎበት አለመታወቁ ብቻ ሳይሆን ራሱ የሰራዊቱ ህገመንግስታዊ ግዳጅም ምን እንደሆነ ሰራዊቱ እንዲያዉቀዉ ተደርጎም  አያዉቅም፡፡

አምስተኛ፡ የሠራዊቱን አባላት ሰብአዊ መብትና ፍትህን የሚመለከት አንዳችም ድንጋጌም ሆነ መመሪያ ሰነድ አልነበረም፡፡  እነዚህን መብቶች እንዲያዉቃቸዉ ባለመደረጉም መብቴ ተጥሷል ቢሎ መጠየቅ የሚያስችለዉ አንዳችም ሁኔታ አልነበረም፡፡

ስድስተኛ፡ ወታደራዊ ፕሮፌሽናሊዝም በተዛባ ሁኔታ የተተረጎመበትና የተተገበረበት ነበር፡፡ ይሄን ጉዳይ የበለጠ ግልጽ ለማድረግ እንድቻለኝ ከሁለት አብነቶች አንጻር ለማስቀመጥ ልሞክር፡፡ አንደኛዉ ዉትድርና የግዴታ አገልግሎት እንጂ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ያልነበረ መሆኑ ነዉ፡፡ በአንድ በኩል ቋሚ ወይም መደበኛ ሰራዊት የሚመስል በሌላ በኩል በግዴታ ምልመላ ላይ የተመሰረተ ብሄራዊ ወታደራዊ  አገልግሎት ስርአት የነበረዉ በመሆኑ ሰራዊቱ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ (voluntary standing army)ነበር ለማለት አያስችልም፡፡ ስለዚህ ሰራዊቱ የግዴታ አገልግሎት (obligatory service) የሚሰጥበትና ያለፈቃዱ ታፍሶ የመጣ የሚበዛበት እንደነበረ እናስታዉሳለን፡፡ ሁለተኛዉ ድግሞ  የሙያ ነጻነት (professional autonomy) ያልነበረበትና በፖለቲካ ተጽኢኖ ስር የወደቀ አዛዦች በራስ መተማመን መመንፈስ ለማስራት የሚቸገሩበት ነበር፡፡

ሰባተኛ፡ሰራዊቱን ከህዝቡ ጋር ለማቀራረብና ህዝባዊ አመለካከት እንዲኖረዉ ለማድረግ ታስቦ የተሰራ ስራ ልነበረም፡፡ በዲሞክራሲያዊ አገሮች ሰራዊቱን ከወጣበት ህዝብ ጋር ለማስተሳሰርና ህዝባዊ አመለካከቱን ጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ  ሆን ተብሎ በጥንቃቄ የሚሰሩ ስራዎች አሉ፡፡ እነዚህ ስራዎች  በደርግ ዘመን ቦታ አልነበራቸዉ፡፡

አጠር አጠር አድርጌ ለመጥቀስ ልሞክር፡፡  

ሀ) ወደ ሰራዊቱ ለመግባት በተለይም ኦፊሴር ለመሆን የሚያበቃ የተለየ የምልመላና ቀጠራ መስፈርት አልነበረም፡፡ ህዝባዊ አመለካከቱ ሳይጠና በዘፈቀደ ተመልምሎ በመሰልጠን መኮንን ይሆናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ዉስጥ ያለፈ አመራርና አባል ህዝባዊ ተቆርቋርነት ሊኖረዉ አይችልም፡፡ (There was no established requirements for entry, particularly for the officer corps).

ለ) ለወታደሮችም ሆነ ለመኮንንነት የሚዘጋጀዉ የትምህርትና ስልጠና ስርአቱ (military education system) ደረቅ ከሆነ ወታደራዊና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ዉጭ የህዝብ የበላይነት እንዲያምን፤ሰብአዊ መብትን፤ ለዲሞክራሲ ጠበቃ እንዲሆንና በሕግ የበላነት እንዲያምን ተብሎ የተቀረጸ የትምህርትና ስልጠና መሪሃ ግብሮች አልነበሩም፡፡  በመደበኛ ትምህርት ቤቶችም ቢሆን የሥነ ዜጋና የስነምግባር ትምህርቶች ስለማይሰጡ እነዚህን መሰረታዊ ባህሪያት ሳይኖሩት ለህዝብ መወገን የሚባል ነገር ሊመጣ አይችልም፡፡  

ሐ) በደርግ ስርአት ሲሰራበት የነበረዉ ዕድገት መስፈርት (Promotion standards) በሙያ ብቃትና በትምህርትና በስራ አፈጻጸም ሳይሆን በዘፈቀደ በመሆኑ ፍትሃዊና ሚዛናዊነት (fair and unbiased) የጎደለዉ ስለነበረ በሰራዊቱ አባላት ዘንድ ለሙያዉ ፍቅር ማጣትና አጠቃላይ ብቃት መዉደቅ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የሰራዊቱ ድስፕሊንም ዝቅተኛ መሆን ከዚህ በመነጨ እንደሆነ ለመረዳት አያዳትም፡፡  

ስምንተኛ፡- በደርግ ስርአት ወቅት መከላከያ ሰራዊቱ ዛሬ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ዉስጥ እየተደረገ እንዳለዉ በዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ላይ፡፡  በአለም አቀፍ የጦርነት ህግጋት ላይ፤ በህግ የተከለከሉና በጦር ወንጀለኝነት ስለሚስጠይቁ ድርጊቶች፤ ስለቀይ መስቀል ድንጋጌዎች ፤የህጻናትና የሴቶች መብት ኮንቬንሽን ወዘተ አንድም ጊዜ እንደ አጀንዳ ተነስቶ ዉይይት ተደርጎበት አይታወቅም፡፡  ለነገሩ የዚህ ዓይነት መመሪያዎች ስለመኖራቸዉም የሚታወቅ ነገር አልነበረም፡፡  

ዘጠነኛ፡-  በየትኛዉም  አገር  መከላከያ  ሰራዊት ዉስጥ የተኩስ(ግዳጅ) አፈጻጸም ደንብ (rules of engagement) በማዘጋጀት ሰራዊቱን ማስተማር ግዴታ ሆኖ እያለ ይሄ ነገር በደርግ ሰራዊት ዉስጥ ጨርሶ አይታወቅም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለሁሉም አገሮች ገዢ የሆነዉ  አለም አቀፍ የጦርነት ህግም(international law of armed conflict) በደርግ ዘመኑ መከላከያ ተቋም ዉስጥ አይታወቅም ነበር፡፡ እንደ ትምህርትም አይሰጥም፡፡ በምዕራቡ አለም የመማር እድሉ የነበራቸዉ አንዳንድ አዛዦች ስለዚህ ጉዳይ በግላቸዉ ጠንቅቄዉ ያዉቁ እንደነበር ባይካድም ነገር ግን ለብቻቸዉ ይዘዉት የቆዩት እንጂ በመንግስት ደረጃ ታምኖበት እንደመመሪያ በመላዉ ሰራዊት ዉስጥ የተሰራበት አልነበረም፡፡ በዚህም ምክንያት ይመስለኛል በአንዳንድ የሠራዊት አባላት ዘንድ ሲቪሉን ከተፋላሚዉ  ጠላት ለመለየት ሳይጨነቁ እንዲሁ እንዳለ በጅምላ ያገኙትን ሁሉ ለመደምሰስ ሲሞክሩ የነበረዉ፡፡

ዛሬ በኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ዉስጥ አለም አቀፍ ህግጋት ላይ ትኩረት ተደርጎባቸዉ ሰራዊቱ እንዲያዉቃቸዉ ከመደረጉም ሌላ በግዳጅ ወቅት ለግዳጅ አስፈላጊነት ተብሎ ሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይደረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ በተለይ የሀገራችን መከላከያ ሰራዊት አባለት ከፍተኛ ዲስፕሊን በሚጠይቀዉ የሰላም ማስከበር ተልኢኮ ላይ አዘዉትረዉ የመሳተፍ ዕድል በማግኘታቸዉ  አለም አቀፍ የጦርነት ህግጋትን በተግባር ለመለማመድ አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል፡፡  ዛሬ ሰራዊታችን በጦር  ሜዳ ወንጀል ፈጽሞ የማይታማበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

በሶማሊያ የተሰማራዉ መከላከያ ሰራዊታችን መስጊድ ጣራ ላይ ወይም ህዝብ መሃል ሆነዉ ጥይት የሚተኩስባቸዉን የሽብር ኃይሎችን የእምነት ቦታዉን በማክበርና በህዝብ ላይም ጉዳት ላለማድረስ ብለዉ የአጸፋ ተኩስ በማድግ ራሳቸዉን እንኳን ለመከላከል ሳይሞክሩ በራሳቸዉ ላይ ጉዳት እንዲደርስ ሲፈቅዱ እንደነበረ በተደጋጋሚ የታየ ጉዳይ ነዉ፡፡ ይህን ሁኔታ በ80 ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ላይ አንዳችም ትጥቅ ባልነበራቸዉ ሰላማዊ የሃዉዜን ህዝብ ላይ በአይሮፕላን ከደረሰዉ ጭፍጨፋ ጋር በማነጻጸር ልዩነቱን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡

13/ አዲስ መከላከያ ሰራዊት ግንባታ በደርግና በኢህአዴግ

በብዙ አገሮች እንደታየዉ አዲስ መንግስትና አዲስ ስርአት ሲመሰረት ሁልጊዜም ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራዉ ስራ ለአዲሱ ስርአት ታማኝ የሆነ የመከላከያ ተቋም እንዴት ይገንባ የሚለዉ ጥያቄ ነዉ፡፡ ለስርአቱ ታማኝ የሆነ ሰራዊት ባልተመሰረተበት ሁኔታ የትኛዉም መንግስት ረዥም እድሜ እንደማይኖረዉ ስለሚታወቅ ለራሱ ተስማሚ የሆነ ሰራዊት መመስረቱ የግድ ነዉ፡፡ ከዚህ ጋር አብሮ መጠቀስ የሚገባዉ የቀድሞዉን ስርአት ሲያገለግል የነበረ ሰራዊት በሚመለከት እንዳለ መቀጠል አለበት ወይስ መፍረስ ይገባዋል የሚል ጥያቄ መነሳቱ የማይቀር ነዉ፡፡  በተለይ አዲሱ መንግስት የቀድሞዉን ስርአትና መንግስት የጣለዉ በኃይልና በጦርነት ከሆነ በፊት ሲፋለመዉ የነበረዉን ሰራዊት መፍረሱ የማይቀርና የተለመደ ነዉ፡፡ ለማንኛዉም ይሄ ሁኔታ በአብዛኛዉ የሚወሰነዉ በአዲሱ የስርአቱ ባለቤት ይሆናል ማለት ነዉ፡፡

አዲስ ስርአትና አዲስ መንግስት በሚመሰረትበት ወቅት መከላከያን በሚመለከት የተለያዩ ተሞክሮዎች አሉ፡፡ እነዚህ አማራጮች አዲስ መንግስት ወደ ስልጣን በወጣበት መንገድ ማለትም በትጥቅ ትግል ወይም በሰላማዊ መንገድ በመሆን ላይ የሚወሰን ይሆናል፡፡ በትጥቅ ትግል ከሆነ የራሱ ሰራዊት እንዳለዉ ስለሚያመላከት የቀድሞዉን ሰራዊት የማስቀጠል ጉዳይ አጠራጣሪ  ያደርገዋል፡፡ ለማንኛዉም ቀጥለን ያሉትን አመራጭችና ተሞክሮዎች እንመልከት፡፡  

አንደኛ፤ የቀድሞዉ ሰራዊት እንዳለ እንዲቀጥል የሚደረግበት አማራጭ

አዲሱ መንግስት መሰረታዊ የስርአት ለዉጥ ቢያደረግም ባያደረግም የሀገሪቱን መከላከያ ሰራዊት ሳያፈርስ እንዲቀጥል የሚደረግበት ነዉ፡፡ የዚህ ዓይነተኛ መገለጫ የሚሆነዉ አዲሱ መንግስት  ስልጣን ለመያዝ የትጥቅ ትግል ማድረግ ሳያስፈልግና ጦር በማደራጀት ጦርነት መግጠም ሳያስፈልገዉ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ፤በኩዴታ ወይም በአብዬት ስልጣን ለመቆጣጠር  የቻለ እንደሆን ነዉ፡፡  በዚህ መንገድ ስልጣን የያዘ መንግስት ነባሩን የሀገሪቱን ሰራዊት ማፍረስ ሳያስፈልገዉ ምናልባት አጠራጣሪ የሆኑ የተወሰኑ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችን በጡረታ በማሰናበት ብቻ የቀረዉን እንዳለ ማስቀጠል ይችላል፡፡ ስልጣን የያዘዉ አዲሱ መንግስት የሀገሪቱን መከላከያ ሰራዊት ለስርአቱና ለአገዛዙ በሚስማማ መንገድ በመቅረጽ ታማኝ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችን ሊሰራ እንደሚችል የሚያጠራጥር አይደለም፡፡  ከዚያ ዉጭ ሰራዊቱን የሚበትንበትና ተቋሙን የሚያፈርስበት ምክንያት አይኖረዉም፡፡ በዚህ ረገድ እንደ አብነት ሊጠቀስ የሚችለዉ  ዘዉዳዊዉን ስርአት የተካዉን ደርግ የቀድሞዉን ስርአት ሲያገለግል የነበረዉን መከላከያ ሰራዊት መበተንና ተቋሙንም ማፍረስ ሳያስፈልገዉ  እንዳለ ያስቀጠለበት አግባብ ነዉ፡፡ ደርግ የዘዉዳዊዉን ስርአት ሙሉ በሙሉ አፍርሶ በምትኩ አዲስና ከዚህ ቀደም በሃገሪቱ ያለነበረ ስርአት መስርቶ እያለ ከቀድሞዉ ስርአት ዉስጥ ሲያገለግል የነበረዉን ሰራዊት ግን ለማፍረስ አላስፈለገዉም ነበር፡፡

ሁለተኛ፡የቀድሞዉ  ሰራዊት አንደ ተቋም የሚፈርስበት አማራጭ

ከቅኝ አገዛዝም ሆነ አገር በቀል ከሆነዉ ጨቋኝ አገዛዝ ለመላቀቅ በትጥቅ ትግል ሲፋለሙ ቆይተዉ ቀንቶአቸዉ ስልጣን የመያዝ እድል ባገኙ አንዳንድ አገሮች ዉስጥ የነበረዉ ሁኔታ እንደሚያሳየን  የነበረዉን  አገዛዝና ስርአት በትጥቅ ትግል በጋራ ታግለዉ ለመጣል የቻሉ የተለያዩ ታጣቂ ኃይሎች ሁሉን ያካተተ ለጊዜዉም ቢሆን የጥምር ወይም ሽግግር መንግስት ከመመስረታቸዉም ሌላ መከላከያዉን በሚመለከት ለዚህ ስልጣን ያበቁአቸዉን  ታጣቂ ኃይሎች ሁሉ በሚያካትት ሁኔታ የጋራ መከላከያ ሰራዊት የሚመሰረቱበት አግባብ ነዉ፡፡ አንዳንዴ አንድ ታጣቂ ቡድን ብቻ በመከላከያ ሰራዊትነት እንዲሰራ የሚደረግበት ሁኔታም አለ፡፡ በሃገራችን እንደታየዉ ማለት ነዉ፡፡ ኦነግ የተባለዉ ታጣቂ ቡደን የት እንደነበረና መቼ እንደታገለ ሳይታወቅ እኔም ታግያለሁ በሚል ታጣቂዎቹን በመካለከያ ዉስጥ ለማካተት ጥረት ማድረጉ ባይቀርም ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም፡፡

ስለዚህ የኢህአዴግ ሰራዊት ብቻ በመከላከያ ሰራዊትነት እንዲቀጥል ነዉ የተደረገዉ፡፡ በብዙ አገሮች በትጥቅ ትግሉ የጎላ ሚና እንደነበራቸዉ የሚታወቁ ታጣቂ ቡድኖች  በትግሉ ወቅት እንደ ነበራቸዉ የትግል አስተዋጽኦና የሰራዊት አቅም  እየተመዘኑ በአዲሱ ሰራዊት ዉስጥ በኮታ ቦታ እንዲያገኙ የማድረግ አሰራርም አለ፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ከኢህአዴግ ሰራዊት ጋር እኩል ለመታየት ፈልጎ የነበረዉ ኦነግ ግን አሶሳ አካባቢ አንድ ወቅት ላይ ከሻዕቢያ ጋር ተመካክሮ አማርኛ ተናጋሪዎችን ብቻ እየመረጠ ህጻን ሽማግሌ ሴት ወንድ ሳይል ከመጨፍጨፉ ዉጭ የረባ የትግል አስተዋጽኦ ሲላላደረገ የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት የመሆን ብቃቱ እንደለለዉና ከሁሉም በላይ ደግሞ በኢትዮጵያ ህዝብም ተቀባይነት እንደማይኖረዉ በመረጋገጡ ትጥቁን እንዲፈታ ተደርጓል፡፡ ኢህአዴግ ጨፍጫፊዉን ኦነግን እንደ ድርጅት ስልጣን ከማጋራት ባይከለክለዉም ለሀገሩ ሉአላዊነት ሲፋለም ከነበረዉ ከቀድሞዉ የሀገሪቱ ሰራዊት ይልቅ የጨፍጫፊዉን ኦነግን ሰራዊት በመካለከያ ዉስጥ አካቶ ቢሆን ኖሮ  ሊፈጠር ይችል የነበረዉ አደጋ  ማሰብ ራሱ ይከብዳል፡፡  

በሁሉም አገሮች የተለመደዉ አዲሶች ታጣቂዎች ወደ ስልጣን ሲመጡ የቀድሞ መንግስት ሰራዊት የነበረዉን በሚመለከት አንድ ወጥ አሰራር የላቸዉም፡፡  አንዳንዶቹ ሙሉ በሙሉ አፍርሰዉ የራሳቸዉን ታጣቂ ብቻ በሰራዊትነት የሚያስቀጥሉ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ የተለየ ወንጀል አልሰሩም የተባለላቸዉን  በጣም በጥቂቱ በመምረጥ ለአዲሱ ሰራዊት እንደ እርሾ እንዲያገለግሉ ያደርጋሉ፡፡

ወደ ስልጣን በትጥቅ ትግል የመጡ ኃይሎች ለስልጣን የበቁት  ህዝብ ፈቅዶና በዲሞክራሲያዊ መንገድ መርጦአቸዉ ሳይሆን አሸናፊ ስለነበሩ ብቻ በመሆኑ የህዝብን መሰረታዊ ጥያቄ ከመፍታት ይልቅ በቀጥታ ወደ ዝርፊያ ስለሚገቡ  ከድሮዉ የባሰ ጨቋኝ ስርአት መመስረታቸዉ የተለመደ ነገር ነዉ፡፡ የተቀደሰዉን የቀድሞዉኑ ዓላማቸዉን ዘንግተዉ የቀድሞዉን ስርአት መጣላቸዉን እንደ ትልቅ አስተወጽኦ በመቁጠር ህዝቡ ለዚህ ዉሌታቸዉ እንዲከፍል በመፈለግ ለዘመናት በስልጣን ላይ ለመቆየት ይሻሉ፡፡ አስራ ሰባት ዓመት በስልጣን ላይ የቆየን መንግስት በመጣል በምትኩ እነሱ ሪኮርዱን በማሻሻል አርባ ሰባት ዓመት ለመቆየት ይጥራሉ፡፡ አንዳንዴ የጭቆናዉ መብዛት ምነዉ የቀድሞዉ ስርአት ባይፈርስ ኖሮ የሚያሰኝ ሊሀን ይችላ፡፡ እንግዲህ አዲሶቹ ታጣቂዎች እንደዚህ እንደሚያደርጉ አስቀድሞዉኑ ስለሚያዉቁ  ለስልጣን ያበቃቸዉን ታጣቂ ኃይል ብቻ በመያዝ በስልጣን ለመቆየት ይጥራሉ፡፡ በዚህ ምክንያትም ከነሱ ዉጭ ያለዉን የሀገሪቱን የቀድሞ ሰራዊት ሲለሚጠራጠሩት ቦታ አይሰጡትም፡፡ በሚፈጠረዉ የአቅም ክፍተት ምክንያትም የሀገሪቱ መከላከያ  ኃይል እየተዳከመ ስለሚሄድ ሀገሪቱ ለዉጭ ወረራ ተጋላጭ ትሆናለች፡፡ ማንም እንደሚገነዘበዉ  የአንድ ሀገር መካለከያ አቅም በአንድ ጊዜ የሚገነባ ሳይሆን ለዘመናት በቅብብሎሽ በሚደረግ ጥረት በመሆኑ ስልጣን ያየዘ አዲስ መንግስት ሁኔታዉ አመቼኝ ቢሎ ሃላፊነት በጎደለዉ ሁኔታ ነባሩን ሰራዊት የሚበትን ከሆነ አገሪቱን በሂዴት ሊጎዳት እንደሚችል የሚያጠራጥር አይደለም፡፡  

) ደርግ የንጉሱን ዘመን ሰራዊት ለማፍረስ የሚያበቃዉ ምክንያት ስላልነበረዉ አላፈረሰም፡፡

ደርግ ስልጣን እንደያዘ  የንጉሱን ዘመን ሰራዊትን ለማፍረስ ወይንም ለመበተን ሳያስፈልገዉ እንዳለ ያስቀጠለበትን ምክንያቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡

1ኛ) ደርግ ስልጣን ላይ የወጣዉ በሰላማዊ መንገድ እንጂ በረሃ ገብቶ ሰራዊት አሰልፎ በጦርነት አይደለም፡፡ ደርግን ወደ ስልጣን ለመዉጣት ያገዘዉ የራሱ የሆነ የተለየ ሰራዊት አልነበረዉም፡፡ በሌላ በኩልም ደርግ ስልጣን እንዳይይዝ የተቀናቀነዉ ታጣቂ ኃይልም አልነበረም፡፡

2ኛ) ደርግ የሚባለዉ አካል ራሱ የቀድሞዉ የንጉሱ ዘመን ሰራዊት አባላት ጥርቅም እንጂ ሌላ አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያትም ነባሩን ሰራዊት እንደተቋም ለማፍረስ ወይንም ለመበተን የሚያበቃዉ አንዳችም ምክንት አልነበረም፡፡  

3ኛ) ደርግ ወደ ስልጣን ከወጣም በኋላ ስልጣኑን በመቀናቀን ሰራዊቱ አንዳችም ተቃዉሞ አላሰማም፡፡ ሰራዊቱ ራሱ ደርግ የወጣበት በመሆኑ እንዲያዉም ከየጦር ክፍሉ ተመርጠዉ ለመጡት ያለ አቅማቸዉ በመሾም ለስልጣን ያበቃቸዉ ደርግ ስለነበር እሱን የሚቀናቀኑበት ምክንያት አልነበረም፡፡ 

4ኛ) ደርግ ስልጣን በያዘበት ወቅት የነበረዉ የሀገሪቱ ሁኔታም አስቀድሜ ለጠቀስኳቸዉ ምክንያቶች እንደ ተጨማሪ ሊወሰድ የሚችል ነዉ፡፡ ደርግ ስልጣን በያዘበት ወቅት ሀገሪቱ ዉስጥ እጅግ ምስቅልቅል ሁኔታ የነበረበት ወቅት ነበር፡፡ በተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች መካካል የነበረዉ ሽኩቻም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነዉ፡፡ በተጨማሪ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የሶማሊያ መንግስት ለወረራ ዳርዳር እያለ የነበረበትና በተመሳሳይ ወቅትም በኤርትራ የነበረዉ ተገንጣይ ቡድን ኤርትራን ለመገንጠል እጅግ የተመቻቸ ሁኔታ የተፈጠረለት ወቅት ስለነበር ደርግ ጥቂት የንጉሱን ዘመን ጄነራሎች በጡረታ ከማሰናበት ዉጭ ሰራዊቱን ወደ መበተን አልገባም፡፡ ደርግ እንደተቋም እንዲቀጥል ያደረገዉ ጦር ኃይሉን ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን የደህንነት መስሪያ ቤትና ፖሊስ ሰራዊትንም ጭምር ነዉ፡፡ ደርግ እንዲህ  በማድረጉ የሚያስወቅሰዉም የሚያስመሰግነዉም አይደለም፡፡  እንደዚያ እንዲያደርግ ሁኔታዉ ያስገድድ ስለነበር በዚያ መንገድ መሄዱ ተገቢ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

) ኢህአዴግ የደርግ ዘመኑን ሰራዊት የበተነበት አግባብ ሲቃኝ

የኢህአዴግን የወሰደዉን እርምጃ በሚመለከት ደርግ ተከትለት ከነበረዉ መንገድ  ለየት ባለ ሁኔታ የቀድሞዉን ሰራዊትን እንዳለ በመበተን ተቋሙንም አፍርሷል፡፡ ኢህአዴግ በወቅቱ የወሰደዉን እርምጃ ደርግ ካደረገዉ ጋር ለማነጻጸር ከሞከርን ስህተት ላይ ጥለናል፡፡ ምክንያቱም የኢህአዴግ ሁኔታ ከደርግ ሁኔታ በእጅጉ የተለየ በመሆኑ፡መታየት ያለበት ለብቻዉ በወቅቱ ከነበረዉ ሁኔታ አንጻር ነዉ፡፡ በሀገራችን ኢህአዴግ ደርግን ከስልጣን ለማስወገድ የቻለዉ በወታደራዉ ኩዴታ ወይም በምርጫ  ሳይሆን ለአስራ ሰባት ዓመታት ተዋግቶ በማሸነፉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡  ይህ ማለት ኢህአዴግ የራሱ ሰራዊት ነበረዉ ማለት ነዉ፡፡ ኢህአዴግ የራሱ ሰራዊት ሲለነበረዉም ስልጣን እንደያዘ የቀድሞዉን ሰራዊት እንዳለ እንደተቋም አፍርሶ በምትኩ አሸናፊ የሆነዉን የራሱን የኢህአዴግን ሰራዊት የሀገሪቱ ሰራዊት አድርጎታል፡፡ ኢህአዴግ የቀድሞዉን ሰራዊት ማፍረሱ ትክክል ነዉ፡፡ ወይንም ማፍረስ አልነበረበትም የሚል ክርክር መክፈት ጥቅም የለዉም – ያለፈ ነገር ስለሆነ፡፡ ከዚያ ይልቅ ጠቃሚ የሚሆነዉ ለምን እንዲህ አደረገ የሚለዉን ለመረዳት መሞከሩ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ የቀድሞዉን ሰራዊት ለመቀበል ያልፈለገበትና ተቋሙንም አስከማፍረስ የደረሰበት የራሱ ምክንያቶች ሊኖሩት እንደሚችል ሳልዘነጋ የራሴን ግምቶች ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፡፡ የግል አስተያየት እንጂ ማንንም የሚወክል እንዳልሆነ በቅድሚያ መግለጽ እወዳለሁ፡፡

ለነገሩ ኢህአዴግ የቀድሞዉን መካለከያ ሰራዊት እንደተቋም ማፍረሱ  ካልሆነ በስተቀር   ከሽግግሩ ዘመን ጀምሮ ከዚህ ዉሰጥ ወደ አየር ኃይሉ የተቀላቀሉትን  2000 ጨምሮ በቁጥር ከ9000 የማያንሱ የተለያዩ ሙያ ባለቤት የሆኑትንና ከማንኛዉም ወንጀል ነጻ መሆናቸዉ የተረጋገጠላቸዉን ባለሌላ መእረግተኞችና መኮንኖችን መርጦ ወደ ስራ በመመለሱ መከላከያ ተቋሙን  እንደገና በማቋቋም  ስራ ላይ ከፍተና አስተዋጽኦ ሲያርጉ እንደነበር መዘንጋት አይኖርበትም ፡፡እኔም  በወቅቱ ወደ አየር ኃይል የተመለስኩት በዚሁ መንገድ መሆኑን ማታወስ እወዳለሁ፡፤በወቅቱ ከነበረዉ ወደ  50 ሺህ ከሚገመተዉ  የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ዉስጥ 18-20 % የቀድሞ ሰራዊት የነበሩ ናቸዉ፡፡

አንደኛ፡የቀድሞዉን ሰራዊት ለመበቀል ያደረገዉ ነዉ መባሉ

ለዚህ ግምት ያበቃኝን ሁኔታ ለመመልከት እንሞክር፡፡  የደርግ ሰራዊት ኤርትራ እንዳትገነጠል ለዓመታት የሞት ሽረት ከማድረጉም ሌላ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ለመምጣት ያደረገዉን ጉዞ በማዘግየትና እንቅፋት በመሆን በዚህ ሂዴትም በርካታ የድርጅቱን ተዋጊዎች በጦርነቱ ሂዴት እንዲያጣ ምክንያት የሆነ ሰራዊት ነዉ፡፡ በህወኃት ሰራዊት ላይ የደረሰዉ ጉዳት እጅግ ከፍተኛ መሆን ህወኃት/ኢህአዴግ  ስልጣን ከያዘ ከመበቀል እንደማይመለስ ቀድሞዉኑ ስልጣን ከመያዙ በፊት ሲጠበቅና ብዙ ሲነገር የነበረ ነዉ፡፡

ኢህአዴግ በተለይም ህወኃት ከቀድሞዉ ሰራዊት ጋር በተደረገዉ ፍልሚያ ላይ በጦርነቱ ሂደት ከደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት ይልቅ እጅጉን ያስቆጣዉና ለበቀልም ያነሳሳዉ በትግራይ ተናጋሪ ህዝብ ላይ በደርግ ባለስልጣነትና ደህንነቶች አመካኝነት ሲደርስ የነበረዉ ግፍ ነዉ፡፡ በወቅቱ በጅምላና ያለምንም ማስረጃ ከየመንገዱና ከየመንደሩ እየተለቀሙ በማይታወቁ አስርቤቶች በማጎር ሲያሰቀዩአቸዉ እንደቆዩና በርካታዎቹንም በግፍ መግደላቸዉ ስለሚታወቅ ነዉ፡፡ ስለዚህ ሁኔታ የሰሙ የህወኃትን ታጋዮችና አመራሮች ቢያስቆጣ የሚበዛባቸዉ አይመስለኝም፡፡ እንደዚህም ሆኖ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ የቀድሞዉን ባለስልጣናትን በቁጥጥር ስር በማድረግ በሂዴትም ለፍርድ አቅርቦ በእስር ከመቅጣት ዉጭ የሞት ቅጣት የተፈጸመበት ባለስልጣን አልነበረም፡፡

የቀድሞ ሰራዊትንም በተመለከተ በተሃዲሶ ማእከል አንድ ቦታ ሰብስቦ እየቀለበ የቀድሞ ጥፋታቸዉን አምነዉ ለወደፊቱ እንዲታረሙ ሂስና ግለሂስ በማድረግ ፤ለወደፊቱ ከህዝቡ ጋር በሰላም መኖር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ የስነሊቡና ዝግጅት በማድረግና  ኢህአዴግ የታገለለት ዓላማ ምንነት በማስረዳት፤ ለጥፋት የታገለ ድርጅት ሳይሆን ህዝቡን ከተጫነበት አምባገነን አገዛዝ ነጻ በማዉጣት  በምትኩ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት የታገለ መሆኑን ሲያስተምር ቆይቶ በመጨረሻም ወደ የቤታቸዉ እንዲሄዱ ነዉ ያደረገዉ እንጂ ለበቀል ቢሎ ያሰቃየበትና የእጅ እልፍት ያደረገበት አንዳችም ሁኔታ አልነበረም፡፡ በዚያ የተሃዲሱ ሂዴት ያለፉ የቀድሞ ወታደሮች መካከል ከፍተኛ ደረጃ የደረሱና አንዳንዴ በቴሌቪዝን መስኮት የምናያቸዉ አሉ፡፡  ሌላዉ ቀርቶ በራሳቸዉ በሰራዊቱ አባላት ጥቆማ የከፋ ወንጀል ሰርተዋል የተባሉትን ሳይቀር በጊዜ ሂደት እንደለቀቃቸዉ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ የቀድሞዉን ሰራዊት ተበቀለ የሚባለዉ ምናልባት በወታደርነት እንዲቀጥሉ ባለማድረጉ ካልሆነ በስተቀር ከዚያ ዉጭ ሊጠቀስ የሚችል የበቀል ማሳያ የሚሆን ድርጊት አልነበረም፡፡

ሁለተኛ፡አሸናፊና ተሸናፊ በአንድነት መቀጠል አይችልም ከሚል ሃልዮት በመነጨ

ሁለቱ ሰራዊቶች በተለያዩ ጎራዎች ተሰልፈዉ  አንዱ የመንግስት ወታደር ሆኖ በሉአላዊነት ስም ሌላዉ በነጻ አዉጭነት እርስበርስ ሲፋለሙ የቆዩና  ደም የተቃቡ በመሆናቸዉ ምክንያት እርስ በርስ መተማመን ስለማይኖር  አንድ ላይ ቀይጦ እንደ አንድ የሀገር መካለከያ ሰራዊት ለማስቀጠል አዳጋች ነዉ ከሚል ነዉ፡፡ የወደቀን ስርአት ሲያገለግል የነበረና ስርአቱን ታግሎ የጣለ  በአንድ ላይ እንደ ሰራዊት መዝለቅ አይችሉም የሚል አመለካከት ነዉ የነበረዉ፡፡

ሶስተኛ፡በአገር ሉአላዊነት ጥያቄ ላይ መሰረታዊ የሆነ የአመለካከት ልዩነት መኖር

በደርግ ወቅት የነበረዉ ሰራዊት ለሀገር ሉአላዊነት የታገለ ፤ኤርትራ እንዳትገነጠል የሚችለዉን ያደረገና ለዚህ ዓላማም ቢሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት በበረሃ ወድቀዉ የአዉሬ ሲሳይ የሆኑበት፤ ይሄ ሁሉ መስዋእትነትም ተከፍሎ ሁሉ ኤርትራን ከመገንጠል ማዳን ባለመቻሉ ከፍተኛ ቁጭት ያለዉ ሰራዊት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይባስ ቢሎም እንደልዩ ፍጡር ሲተማመንባቸዉ የነበሩት መሪዉ ኮ/ል መንግስቱ የሰራዊቱን የወደፊቱን ዕጣፈንታ ሳደላድሉና ደህና ሁኑ እንኳን ሳይሉ አገር ጥለዉ በመሄዳቸዉ በሰራዊቱ ላይ የፈጠረበት ብስጭት ቀላል አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብም ቢሆን ጦርነትን በደፈናዉ ይጥላ እንጂ ለደርግም  መልካም አመለካከት አይኑረዉ እንጂ ኤርትራን ከመገንጠል ለማዳን ሲደረግ የነበረዉን ጦርነት አንድም ጊዜ ያወገዘበት ወቅት አልነበረም፡፡ የልጆቹ የትም ወድቀዉ መቅረት ቢያሳዝነዉም ከዛሬ ነገ ድል ይገኛል እያለ በተስፋ የተጠየቀዉን ሁሉ ከመስጠት ተቆጥቦ አያዉቅም፡፡ በመጨረሻም ከብዙ ኪሳራ በኋላ ከዚህ በፊት እየሸለሉና እያቅራሩ በመሪያቸዉ  ፊት በኩራት ሲያልፉ እያየ በደስታ የሸኛቸዉ ልጆቹ  ዛሬ ተሸናፊ ሆነዉ አንገታቸዉን ደፍተዉ ከጦር ግንባር ሲመለሱና በየመንገዱ ዳር ቆመዉ  ምጽዋት ሲለምኑ እያየ ማዘኑ አልቀርም፡፡

እንግዲህ ኤርትራ እንዳትገነጠል ከፍተኛ ተጋድሎ ሲያደርግ የነበረ የቀድሞዉ አብዮታዊ ሰራዊት ለኤርትራ መገንጠል ታላቅ አስተዋጸኦ አድርጌአለሁ እያለ በኩራት  ከሚናገረዉ የኢህአዴግ ሰራዊት ጋር በአንድነት ለመቀጠል የሚያስችለዉ ሁኔታ ስላልነበረ ኢህአዴግም ሁኔታዉን ተገንዝቦና አስግቶት በሰላም ወደየቤታቸዉ ለማሰናበት የተገደደዉ ከዚህ መነሻ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡

አራተኛ፡ኢህአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲ ሊሰራቸዉ ላቀዳቸዉ ግዙፍ ዕቅዶቹና በሂዴትም ሊያጋጥሙ ይችላሉ ተብለዉ ግምት ለተወሰደባቸዉ ሁኔታዎች እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት መያዙ

ኢህአዴግ ለቀድሞዉ ሰራዊት አባላት ብቻ ሳይሆን ለቀረዉ የሀገሪቱ ህዝብም ቢሆን  ለመረዳት አስቸጋሪ ሆነዉ የነበሩና ዛሬም አልፎ አልፎ የትችት አጀንዳ የሆኑ አዳዲስ ጉዳዮችን ለማስተዋወቅና ለመተግበር ባደረገዉ ሂዴት የቀድሞዉ ሰራዊት በእምነት ተቀብሎ ለማስፈጸም ይንቀሳቀሳል የሚል እምነት ስላልተጣለበት ማፍረሱን እንደመፍትሄ ወስዶታል፡፡ እነዚህ በመላዉ ህዝብ አከራካሪ ከነበሩት መካከል በከፊል ለመጥቀስ ያህል፤

 1) ኤርትራ በሪፌሬንደም ነጻነቷን እንድታዉጅ የተደረገበት፤

2) የአሰብን ወደብ ባለቤትነትና ወደብ አልባ የመሆናችን ጉዳይ

3) አስከመገንጠል የሚፈቅደዉ ህገመንግስታዊ ድንጋጌ፤

4) ኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ ባለቤት መሆኗ ቀርቶ በምትኩ ከመቶ አመት የማይበልጥ ታሪክ ያላት መሆኑን የሚተርክ አዲስ ታሪክ ለማሰተዋወቅ የተደረገዉ ጥረት፤

5) አዲስ የድንበር ማካለል ጉዳይ አንዳንዱን አትራፊ ሲያደረግ ሌላዉን አክሳሪ ያደረገ

6) የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ናቸዉ፡፡

በተለይ የመሬት ይዞታ ባለቤትነት በሚመለከት ቀድሞዉኑ በደርግ ህገመንግስትም የነበረና ምናልባት በአፈጻጸም ልዩነት አለዉ ካልተባለ በስተቀር ተመሳሳይ የነበረ ነዉ፡፡ ሆኖም መመሪያዉ በደርግም ሆነ በአሁኑ ወቅት ከየራሱ ባህሪይ ከመነጩ  ችግሮች  የጸዳ አይደለም፡፡ በተለይም መመሪያዉ ባንድ በኩል መሬት በመንግስት ስር ሆኖ ህዝብ እንዲጠቀምበት የሚፈቅድ መሆኑ፤ በሌላ በኩል ሁሉም ዜጋ ያለገደብ እየተንቀሳቀሰ በፈለገበት ቦታ የመስራትና የመኖር መብት መኖርና ይህን መብት  በሚጋፋ መልኩ በየአካባቢዉ “ባለቤቶች እኛ ስለሆን ሌላዉ ለቆ መዉጣት አለበት” የሚለዉ ጠባብ አመለካከት በአንድ ላይ ተደማምሮ  የዉዝግብና የግጭት መንስኤ መሆን መቻሉ ነዉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ዉስጥ  ችግር ሲከሰትና ከአቅም በላይ ሲሆን መንግስት መከላከያን ለመጠቀም ሲገደድ  ለዚህ ተልእኮ  ከሰራዊቱ የሚያገኘዉ ምላሽ ወይም ፈቃደኝነት ከግምት መግባት የሚገባዉ ነዉ፡፡ አንድ የመከላከያ ሰራዊት አባል ሻእቢያን ሄደህ ዉጋ ሲባልና  በራሱ ህዘብ ዉስጥ በሚነሳ አለመግባባት በኃይል ችግሩን ፍታ  ተብሎ መላክ እኩል ምላሽ ያገኛል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡

ወደ ጀመርኩት ወደ ብተናው ልመለስና ኢህአዴግ በስልጣን ዘመኑ እጅግ ከባድና አደገኛ ዉሳኔ የወሰነባቸዉ ሁለት አጋጣሚዎች ቢኖሩ አንደኛዉ የባህር በር ጉዳይ ላይ የወሰደዉ ዉሳኔ ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ የቀድሞዉን መከላከያ ሰራዊት እንዲበተን ያደረገበት ዉሳኔ ነዉ ማለት እችላለሁ፡፡ የባህር በር ጉዳይ የዚህ ጽሁፍ ትኩረት ባለመሆኑ አልፈአዋለሁ፡፡ ኢህአዴግን እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ ሊያስከፍለዉ ይችል የነበረ የቀድሞዉን ሰራዊት እንዳለ መበተኑና ተቋሙንም ማፍረሱ ነዉ፡፡ የቀድሞዉ መከላከያ ሰራዊት አባላት በደርግ ስርአት እጅግ የተሰላቹና ለነበረዉ አገዛዝ የመረረ ጥላቻ እየያዙ የመጡ በመሆናቸዉ የስርአቱን መዉደቅ በእጅጉ ይፈልጉት እንደነበር በዉስጡ የነበርነዉን በሚገባ የምናስታዉሰዉ ጉዳይ ነዉ፡፡

የኢህአዴግ ሰራዊት ከዉጭ የመጣ የሌላ አገር ወራሪ ሰራዊት እንዳልነበረና ጨቋኙን ስርአት ለመጣል የሚታገል እንደነበረ ከበቂ በላይ ግንዛቤ የነበረዉ ሰራዊት ነበር፡፡ ኢህአዴግ ግን ስለዚህ ጉዳይ የሚያዉቅ አልመሰለኝም፡፡ ምናልባትም እያወቀም ለመቀበል አልፈለገ ሊሆን ይችላል፡፡ የቀድሞዉ ሰራዊት ከነትጥቁ በሰላም እጁን ለኢህአዴግ መስጠቱና ወደ ዝርፊያና ወደ ግድያ አለመግባቱን ኢህአዴግ ራሱን አድለኛ አድርጎ የቆጠረ አልመሰለኝም፡፡ በብዙ አገሮች እንደታየዉ መንግስት ሲወድቅ ሰራዊቱ ወደ መገዳደል ስለሚገባ ሀገሪቱን ወደ መበታተን ሊያስገባት ይችል ከነበረ አደጋ ነዉ ያመለጥነዉ፡፡ ኢህአዴግ ሰራዊቱን እንዳለ ሲበትን ይሄን መሰሉ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል ገምቶ ነበር ለማለት አልችልም፡፡ ለማንኛዉም የቀድሞዉ መካላከያ ሰራዊት በዚህ ረገድ ሊመሰገን ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡

14/ በመከለካያ ሰራዊታችን ገለልተኝነትና ህዝባዊ ቅቡልነት ላይ ወደፊት ጫና ሊያሳድሩ የሚችሉ ሁኔታዎች፤

) መከላከያን አንደ ተቋምና በተለይም አንዳንድ እዉቅ ጄነራሎችንም በግል አለቅጥ የመካብና የማጋነን አባዜና መዘዙ፤

የአንድ አገር መከላከያ ሰራዊት የኋላ ታሪኩ ሲፈተሽ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ህዝባዊ ሞገስና ሰፊ ተቀባይነት ያስገኙለት አኩሪ የሚባል ገድል ያለዉ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ የሀገሪቱን ዜጎች ከቅኝ አገዛዛም ሆነ አገር በቀል ከሆነ ጨቋኝ አገዛዛ ነጻ የማዉጣት ተልዕኮዉን በተሳካ ሁኔታ የተገበረ እንደ ነጻ አዉጭ (liberator) መቆጠሩ፣ሀገሪቱን በተደጋጋሚ ከዉጭ የሚሰነዘር ጥቃት መከላከል የቻለ የሀገር መከታና ጠባቂ (defendor and savior) መሰኘቱ ፤አዲስ አገር በመመስረት ትልቅ ሚና የነበረዉ አገር ፈጣሪ (nation founder) ወዘተ የመሳሰሉ ጉልህ ሚናዎች ከነበሩት በህብረተሰቡ ከፍ ያለ ከበረታ ሊያተርፍ መቻሉ እሙን ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የህዝብ አመለካከት ገደብ ከለለዉ ወታደሩ ቀስ በቀስ ራሱን ከህዝብና ከመንግስት በላይ አድርጎ መቁጠር ይጀምራል፡፡ በተለይ የድሮ ዉሌታዉ እንዳይረሳ ደጋጋሞ ደጋግሞ መነገሩ ባያስከፋም ነገር ግን አለቅጥ ሲበዛ “ህዝቡን ነጻ ያወጣሁ ነኝ ፡፡  ህዝቡ ሊንከባከበኝ ይገባል፡፡ ሕዝብን መምራት ያለኝብኝ እኔ ነኝ” ወደማለት ይገባል፡፡ ወታደር ዛሬ የሚገመገመዉ ዛሬ ላይ ሆኖ በሚያሳየዉ ባህሪይዉ እንጂ ከኣመታት በፊት ሰራሁ በሚለዉ የድሮ ታሪኩ አይደለም፡፡ ትላንት የህዝብ ከበሬታና ፍቅር የነበረዉ ሰራዊት ዛሬ እንደ አደገኛና አስፈሪ ተቋም ሊቆጠር ይችላል፡፡ የዛሬ ምግባሩ ነዉ ወሳኙ፡፡

በብዙ አገሮች ጦር ኃይሉ በመንግስትም ሆነ በህዝቡ ከሚገባዉ በላይ የመወደስና  ያለቅጥ በመካብ  በትእብት እንዲወጠርና ከየትኛዉም የህዝብ ተቋማት በበለጠ ሃላፊነት ያለበት አድርጎ ራሱን እነዲቆጥር በመደረጉ በዚህ ምክንያትም ህዝብንና መንግስትን በመናቅ ህዝባዊ ባህሪይዉ እየተሸረሸረ በመሄድ ለህዝቡም ለስርአቱም አደጋ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ መንግስትም ሆነ ህብረተሰቡ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አንዳንድ ከፍተኛ የመከላከያ ሰራዊቱ አዛዦችን  ከሚገባዉ በላይ ያለቅጥ በመካብና ሆን ተብሎ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን እንዲሰጣቸዉ በማድረግ  የተጋነነ የገጽታ ግንባታ በመስራት በመጨረሻም ራሳቸዉን የአገር አዳኝና ለሀገሪቱ ችግሮች ሁሉ ብቸኛ መፍትሄ ማምጣት የሚችሉ አድርገዉ በመቁጠር  በሂደት በህዝበ የተመረጡ የመንግሰት አመራሮቸንም በመናቅ አገር ካልመራሁ ወደ ማለት ይገባሉ፡፡ አልፎ አልፎም ቢሆን የዚህ ዓይነት ዝንባሌና አዝማሚያ ያላቸዉ ሰዎች መኖራቸዉን ሰንሰማ መስጋታችን አልቀረም፡፡

ከብዙ አገሮች ሁኔታ መረዳት እንደሚቻለዉ ጦርነት በባህሪዉ በርካታ ጀግኖችን ሲለሚፈጥር አንዳንድ ጄነራሎች ከሌሎች በተለየ አጅግ ዝነኛ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ክፋቱ ግን ጦርነቱ ካለፈም በኋላ ጦርነቱ በፈጠረላቸዉ መልካም አጋጣሚ  የገነቡትን እዉቅናና ህዝባዊ ከበረታ ለግል ዓላማቸዉ ለመጠቀም የሚፈልጉ መኖራቸዉ ነዉ፡፡  በአጉል ኩራት ተወጥረዉ  “ከእኔ በላይ ማን አለ?” በሚል  የሀገሪቱን የፖለቲካ አመራር በመናቅ በአደባባይ የማጥላላትና በህዝብ እንዲጠላ የማድረግና  ጭራሽ ድጋፍ የሚሰጣቸዉ ካገኙም የመንግስት ስልጣንን ከመንጠቅ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ አንድ ጄነራል የሲቪል ባለስልጣናትን በአደባበይ መተችና ማጥላላት ከጀመረ ነገ ምን ሊያደርግ እንደሚችል የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በማዬት መረዳት አያቅተንም፡፡ ከዚህ አኳያ ሜ/ጄነራል አበበ(ጆቤ) በጻፉት አንድ ጽሁፍ ላይ መቀሌ ላይ በተደረገ አንድ የፓናል ዉይይት ላይ ክቡር ጄ/ል ሳሞራ የኑስ ተናግረዋል የተባለዉ ነገር ብዙ ሲከነክነኝ ቆይቷል፡፡

ጄነራል ሳሞራ አንድ አዳራሽ ሙሉ ህዝብ በተሰበሰበበትና በሚዲያም ለሚሊዮኖች በተለቀቀ ሁኔታ ሲቪል ባለስልጣናትን በመተቸትና መከላከያ ከሲቪሉ የተሻለ መሆኑን ከመናገራቸዉም ሌላ ህወኃት ማለት የትግራይ ህዘብ ማለት ነዉ፤ ኢህአዴግ ማለት ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ማለት ነዉ፤ ኢህአዴግ ከለለ ኢትዮጵያ አትኖርም ብለዉ ገልጸዋል የተባለዉን ራሴ በጆሮዬ አድምጨ ለማረጋገጥ ባልታደልም ይህን ጉዳይ የገለጹትን ጄነራል አበበን ተጠራጥሬ እንዳላምናቸዉ  የሚያደርገኝ ምክንያት አልነበረም፡፡ ጄነራሉ ተናገሩ የተባለዉን ሌላ ሲቪል ተናግሮት ቢሆን ብዙም ባላስከፋ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ለዚያዉም በአደባባይ የተናገሩት እጅግ የማከብራቸዉና የማደንቃቸዉ መከላከያ ኤታማዦር ክቡር ጄነራል ሳሞራ የኑስ መሆናቸዉን ሳዉቅ በሳቸዉ ቅር መሰኘቴን መደበቅ አልችልም፡፡

እንኳን ለሲቪል ባለስልጣናት ቀርቶ ለቤታቾቻቸዉ ትሁት እንደሆኑ የማዉቃቸዉ ጄነራል ሳሞራ ምናልባት በዚህ አስቸጋሪ በሆነ ከፍተኛ የስራ ሃላፊነት ረዥም ጊዜ መቆየታቸዉ በፈጠረባቸዉ መሰላቸት ለስህተት ተዳርገዉ ካልሆነ በስተቀር ይህን እንዲናገሩ የገፋፋቸዉን ምክንያት (motive) ከማንአለብኝነት የመነጨ ነዉ ለማለት አልችልም፡፡ አኔ ጄነራል ሳሞራን የማከብራቸዉ ጀግና ወታደርና ምርጥ የጦር መሪ ስለሆኑ እንጂ ፖለቲከኛ ስለሆኑ አይደለም፡፡ የመከላከያ ሰራዊታችንን ገለልተኝነት ለሚጠራጠሩና በሰበብ በአስባቡ ሰራዊታችንን ለመዝለፍ ለሚፈልጉ ኃይሎች ጥሩ አጋጣሚ የሆነላቸዉ ይመስለኛል፡፡ ለማንኛዉም ማንኛዉም የሠራዊት አባል ጄነራል ሳሞራም ቢሆኑ በግላቸዉ ለኢህአዴግ/ህወኃት መልካም አመለካከት ቢኖራቸዉ ማንንም አስካልወከሉና በግል ደረጃ አስከሆነ ድርስ የሚያስከፋ ባይሆንም ነገር ግን እንዲህ በግላጭ ሲሆን ግን ችግር ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ለወደፊቱ እሳቸዉም ሆኑ ሌሎች የዚህ ዓይነት ስህተት እንዳይፈጠር መጠንቀቅ ይገባቸዋል እላለሁ፡፡  

) በሀገሪቱ ኢኮኖሚና በቢዝነስ ዉስጥ ያለቅጥ መሳተፍና ቁጥጥር ያለመኖሩ ሊያስከትል የሚችለዉ  መዘዝ

መከላከያ በልማት ተግባር በመሳተፍ ሀገሪቱን በማገዙ ሊበረታታ የሚገባዉ ቢሆንም ነገር ግን አሁን በሚታየዉ ደረጃ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ዉስጥ በሰፊዉ እጁን እያስገባ መሄዱና ለወደፊቱም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በሰፊዉ ለመቆጣጠር  ወደሚያስችለዉ ሁኔታ እየተንደረደረ መሆኑን አንዳንድ ፍንጮችን በማዬት መስጋታችን አልቀረም፡፡ ሁኔታዉን ይበልጥ አስጊ የሚያደርገዉም መከላከያ በህግ አዉጭዉ እዉቅና በይፋ ከሚመድብለት ባጄት ዉጭም ሌሎች የገቢ ምነጮች እንዳሉት መነገሩና በሚመለከተዉ አካል የሚደረገዉ ክትትል(ቁጥጥር) ጠንካራ አይደለም መባሉ  ወደፊት እንዴ ግብጽ መከላከያ ንጉስ ሻሪና አንጋሽ ወደ ሚሆንበት ደረጃ እንዳይደርስ በመስጋታችን ነዉ፡፡ በኢኮኖሚና በቢዝነስ ዉስጥ እንዳሻዉ የሚዳክር መከላከያ ጡንቻዉ እየፈረጠመ ሰለሚሄድ ሲቪል አመራሩ ባዶ እጁን ሀኖ ሊቆጣጠረዉ አይችልም፡፡ አንድ ጊዜ ጥቅም የለመዱ ጄነራሎች ተቋማዊ ጥማቸዉን (corporate interest) የሚቀናቀን  ሁኔታ እንዲፈጠር በጭራሽ አይፈቀዱም፡፡ ለዚህ ጥሩ አብነት የሚሆነን በግብጽ የተከሰተዉ ሁኔታ ነዉ፡፡ የግብጽ መከላከያ ከጋማል አብዴል ናስር ዘመን ጀመሮ እስከ ሙባሬክ መዉደቅ ድረስ በተለያዩ ደረጃዎች  በኢኮኖሚ ዉስጥ ጣልቃ እየገባ ሲዳክር የነበረ ነዉ፡፡ ሙባረክ ከእንግዲህ ለማንም እንደማይበጁ የተረዱት የግብጽ ጄነራሎች ህዝባዊ ተቃዉሞዉነ እንደቀድመዉ ለማፈን ሳይመክሩ ጭራሽ በመደገፍ ሙባሬክን ከስልጣን አዉርደዉ ለእስር ዳርገዋቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ በግብጽ ታሪክ የመጀመሪያዉ ነዉ በተባለለት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በህዝቡ ሙሉ ፈቃድ ስልጣን የያዙትን  መሃመድ ሙርሲን የግብጽ ጄነራሎች ከስልጣን በማዉረድ ወደከርቸሌ ለመወርወር ብዙ ጊዜ አልጠየቃቸዉም፡፡ ሙርሲ ገና ሰልጣናቸዉን እንኳን በቅጡ ሳያላድሉ የግብጽ መኮንኖች  ለዘመናት የለመዱትን ጥቅም የሚያስቀር እርምጃ ለመዉሰድ እየተዘጋጁ መሆናቸዉ ሲታወቅ ወዲያዉኑ ከስልጣን እንዲወርዱ በማድረግ ለእስር ተዳርገዋል፡፡  ስልጣኑንም በምርጫ ስም ጄነራል አል ሲሲ ያዙ፡፡ የግብጽ መከላከያ ከሚያገኘዉ መጠነ ሰፊ ትርፍ ለመንግስት ታክስ ከፍሎ አያዉቅም፡፡ ኦዲት የሚባል ነገር ማንም ደፍሮ አይጠይቃቸዉም፡፡ ሙሉ ትኩረታቸዉ ቢዝነስ ላይ በመሆኑ ለመደበኛ ወታደራዊ ግዴታቸዉ ቁብ አይሰጣቸዉም፡፡ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ባላቸዉ ፍላጎት መከላከያዉ ያልገባበት የቢዝነስ ፤የኢንዲስትሪና አገልግሎት ዘርፍ የለም፡፡

የግብጽ መከለላከያ 40%የሚሆነዉን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ተቀጣጥረዉታል፡፡ የሀገሪቱ ፕራይቬታይዜሽን አጄንስ በመከላከያ ስር ያሉ ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ ለማስተላለፍ መድፈር አልቻለም፡፡ ማንኛዉም ፕሮጄክት ኮንትራት ጨረታ ቅድሚያ የሚሰጠዉ ለመከላከያ ነዉ፡፡ በቅርቡ 8 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የወጣበትና በየአመቱ በትንሹ 6ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ያስገባል የተባለለት  ሁለተኛዉ የስዊዝ ካናል ማስፋፊያ ፕሮጄክት የተረከበዉ የግብጽ መከላከያ ነበር፡፡  ስራዉን ለማጠናቀቅ ሶስት ዓመት ይጠይቃል የተባለዉን መከላከያ በአንድ ዓመት ዉስጥ ለማጠናቀቅ ችሏል፡፡ ይህን መረን የለቀቀ ሁኔታ የሚገታ ማኛዉንም ዓይነት የመንግስት ፖሊሲን በጽኑ ይቃወማሉ፡፡ ከመንግስት ቁጥጥር ዉጭ ግዙፍ ከሆኑ ዓለም አቀፍ ኩባኒያዎች ጋር የፈጠሩት ግንኙነት ጡንቻቸዉ አለቅጥ እንዲፈረጥም በመደረጉ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንትንም ቢሆን እንዳይፈሩ የልብ ልብ ሰጥቶአቸዋል፡፡ በመሰረቱ ኢኮኖሚዉን ያለተቀናቃኝ መቆጣጠር የቻለ አካል ፖለቲካዉን መቆጣጠር አያዳግተዉ፡፡ ይሄዉ ኃይል አስከ አፍንጫዉ የታጠቀ ጦር ኃይል ሲሆን ደግሞ የህዝቡን ተስፋ ጭራሽ የሚያጨልምና ስጋት ዉስጥ የሚከት ይሆናል፡፡

ሐ) መከላከያ ሰራዊቱ  ከዉጭ ስጋት ይልቅ በዉስጥ ጸጥታ ማስከበር ተግባር  ላይ አዘዉትሮ እንዲሳተፍ ሲደረግ  ሊያስከትል የሚችለዉ  ችግር፤

መከላከያ መደበኛ ፖሊስን ተክቶ በዉስጥ ጸጥታ ማስከበር ላይ በስፋትና አዘዉትሮ  ሲሰማራ እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚነሱ የህዝብ አመጽንና የተቃዉሞ እንቅስቃሴዎችን በኃይል በማፈን ተግባር ላይ በተደጋጋሚ እንዲሳተፍ ሲደረግ በዚህ መነሾ ወታደሩ ከህዝብ ጋር ቅራኔ ዉስጥ እየገባና ቅራኔዉም በየጊዜዉ እየሰፋ ስለሚሄድ በዉጤቱም እስካሁን ከህዝቡ የተቸረዉን ከበሬታ ተነፍጎት ህዝባዊ እዉቅና(legitimacy) በማጣት ህዝቡ “የእኔ ሰራዊት አይደለም” ወደሚል አመለካከት እንዲመጣ  ሊያደርገዉ ይችላል፡፡

) ዉትድርና እንደሙያ ተፈላጊነቱ  እየቀነሰ መሄድ፤

ይህ ሁኔታ ከሁለት ምክንያቶች የመነጨ እንደሆነ አገምታለሁ፡፡

አንደኛዉ ምክንያት፡- በተለያዩ ምክንያቶች ወታደራዊ ሙያ ከበረታ እያጣ መሄድና  በህብረተሰቡ ዘንድም ዉትድርና ዝቅ ያለ ደረጃ (low status) እየያዘ ሲሄድና ይህ የዝቅተኝነት ስሜት ወታደሩ ከህብረተሰቡ መገለልን ማስከተሉ፤፤በሃገሪቱ በተፈጠረዉ የተሻለ የስራ አማራጭ ዕድሎች የተነሳ ከሌሎች ሙያዎች ጋር ተወዳዳሪ መሆን ባለመቻሉ  ሌላ አማራጭ ካልጠፋ በስተቀር  ወጣቱ በፍላጎት የማይገባበት መሆኑና በዚህ ምክንትም ወደ ሰራዊቱ ለመግባት የሚፈልገዉ ወጣት  ቁጥር በየጊዜዉ እየተመናመነ መሄድ ፡፡ በሌላ በኩል መንግስት በሰራ ላይ ላለዉ  የሰራዊቱን ፍላጎት ለማርካት የአቅም ዉስንነት መኖር ወዘተ የመሳሰሉት ሁኔታዎች ተዳማምረዉ በመከላከያ ሰራዊቱ ባህሪይ ላይ አፍራሽ ተጽኢኖ ለፈጥሩ ይችላል፡፡

ሁለተኛዉ ምክንያት፡- ዉትድርና ሙያን ለሀገሪቱ ዜጎች ደህንነት ካለዉ ፋይዳ ይልቅ ለአንድ ስርአት አገዛዝ ተብሎ የቆመ ተደርጎ በመቆጠሩ መንግስት በተቀያየረ ቁጥር በየጊዜዉ እየፈረሰ እንዳዲስ ለመገንባት በሚደረገዉ አድካሚ ስራ ከትዉልድ ወደ ትዉልድ እየተወራረሰ መሄድ ባለመቻሉ በመጪዉ ተተኪ ትዉልድ ላይ የሚፈጥረዉ ስነሊቡናዉ ጫና ከፍተኛ መሆኑ ነዉ፡፡ በአገራችን እንደ ልማድ የያዝነዉ ነገር ቢኖር የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት በሃገር ሉአላዊነትና በብሄራዊ ጥቅም ማስከበር ተግባር ታዞ በተሳተፈባቸዉ ጦርነቶች ድል ሲቀናዉ የማሞገስና ክብር መስጠት በሌላ ጊዜ ደግሞ  ሽንፈት ሲመጣ ንቀትና ጥላቻ በማሳዬት ሰራዊቱ ሃፍረት እንዲሰማዉ ማድረግና (Shame and honor clash) ፤ እንደዚሁም በሰራዊቱ ላይ መስዋእትነቱና ኪሳራዉ በዝቶ ሲገኝ ለህዝብ አላማ የተከፈለ መስዋእትነት መሆኑ ቀርቶ እንደ ተራ አደጋ ተቆጥሮ የሚገባዉን ክብር እንኳን ተነፍጎት አቀርቅሮ እንዲኖር መደረጉ፤ ከሁሉም በላይ የከፋዉ በአገር ሉአላዊነትና አንድነት ለማስከበር ያደረጋቸዉ ተጋድሎዎች እንደጥፋት ተቆጥሮ እንደ ወንጀለኛ እንዲታይ ተደርጎ የሚደረግበት ሁኔታ  ጭራሽ የሃገሪቱ ሰራዊት መሆኑ ቀርቶ እንዲበተንና ራሱና ቤተሰቡ ለችግር እንዲጋለጡ ሲደረግ ለምን የሚል ጠያቂ አለመኖሩ ነዉ፡፡ ይህ ሁኔታ አንድ ቦታ ላይ የሚያቆም ባለመሆኑ አሁን ላለዉ ብቻ ሳይሆን  ወደፊት የሚመጣዉ  ትዉልድ ም ቢሆን ያለፈዉን መንግስት  ወታደር መጥፎ እድል በማስታወስ ነገም እኔም እንደዚያ ልሆን እችላለሁ በሚል ለሙያዉ ፍቅር ማጣት ሊጠቀሰ የሚችል ነዉ፡፡  በ97 ምርጫ ቅስቄሳ ወቅት “ቅንጅት ስልጣን ከያዘ እንደደርግ ሰራዊት ይበትናችኋል” ሲባሉ የቀድሞዉን ሰራዊት ሁኔታ አስታዉሰዉ መስጋታቸዉ አልቀረም፡፡ ከተወሰነ ኣመታት በፊት በጂቡቲና በኬኒያ መንግስታት ሰራዊታቸዉ አካባቢ ትንሽ ችግር በተፈጠረ ቁጥር “እንደ ኢትዮጵያ  ሰራዊት መበተን አማራችሁ?” እየተባሉ እኛን ማስፈራሪያ ማድረጋቸዉን ለሰማ ኢትዮጵያዊ ማናደዱ አይቀርም፡፡

ሚሊታሪዉን በፖለቲካ ዉስጥ ጣልቃ እንዲገባ ሁኔታዉን የሚያመቻቹት ራሳቸዉ ሲቪል ፖለቲከኞች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ሚሊታሪዉ ያለስራዉ በፖለቲካ ዉስጥ ገብቶ እንዲበጠብጥ ሁኔታዉን የሚያመቻቹትና ግፊት የሚያደርጉት ተቀዋሚ ፖለቲከኞች ወይም ራሱ ገዢዉ ፓርቲ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በሀገራችንም ከምርጫ 97 ወቅት ጀምሮ ወታሩን ወደራሳቸዉ ለመጥለፍ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ይታወቃል፡፡  ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆኑ ገዥዉ ፓርቲ  የመከላከያ ሰራዊቱን አባላት እንዲደግፏቸዉ ወደራሳቸዉ ለመሳብ ለማድረግ በሚፈጥሩት አጉል ፉክክር ሰራዊቱን ያለፍላጎቱ ወደ ፖለቲካ ተዋናይነት ሊቀይሩት ይችላሉ፡፡ ሰራዊቱ አንዱን የፖለቲካ ፓርቲ መወገን ሲጀምር እርስ በርሱ የመከፋፈል አደጋ ይገጥመዋል፡፡ ገለልተኝነት ባህሪይዉን እየተወ ሰለሚሄድም ለህዝቦች አደጋ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የመከላከያ ሰራዊቱን ገለልተኝነት ለማረጋገጥ መትጋት ያለበት መንግስት ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፤ ሲቪል ፣ማህበረሰቡ፤ ሚዲያዎች፤ ህዝቡና ራሱ መከላከያ  ጭምር በጋራ የሚሰሩት መሆን አለበት፡፡

) የእርስ በርስ ግጭቶችና መከላከያ ሊኖረዉ የሚችለዉ ሚና

በሀገሪቱ ዉስጥ በህዝቡ መካከል በማንነት ጥያቄና ያን ተከትሎ ብልሃት የጎደለዉ የችግር አፈታት መንገዳችን፤ በመሬት አጠቃቀምና ሽሚያ፤. በሃብት (ሪሶርስ) ቅርምት ወዘተ መነሾነት ብሄር ተኮር ግጭቶች ሲቀሰቀሱ ችግሩን በገለልተኝነት ለመፍታት መከላከያ ሰራዊቱ ጣልቃ እንዲገባ ሲደረግ የተለየ ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ ባላቸዉ ሲቪል አመራሮች ግፊት አንዱን ህዝብ ወግኖ ሌላዉን የማጥቃት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ በተለይ የፌዴራላዊ ስርአታችን አተገባበር ላይ መሰናክል መብዛቱ ከጋራ አገራዊ አጀንዳ ይልቅ ጠባብ የአካባቢ አጀንዳን በዋነኛነት የሚያራምዱ ፓርቲዎች መብዛትና  ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሰራዊቱ ብሄራዊ ተዋጽኦ አተገባበር ቅሬታዎች መኖራቸዉ፤ በሌላ በኩል በአንዳንድ ህዝቦች አካባቢ የጥቃት ሰለባ ወይም የተጠቂነት የጋራ አመለካከት መንፈስ (Collective sense of victimhood) መኖርና ያን ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ለወጡበት አካባቢ ህዝብ በተለየ የመቆርቆር ሁኔታ ሲኖር ችግር ሊከሰት ይችላል፡፡

የአንዳንድ ብሄር ልሂቃን ሆን ብለዉ የቆየ ታሪክ ቆፍረዉ እያወጡና የፈጠራ አፈ-ታሪክ አሳምረዉ በማቅረብ  የቋንቋዉ ተናጋሪዎች ዛሬም ልዩነት እየተደረገባቸዉና በደል እየተፈጸመመባቸዉ እንደሆነ አድርገዉ እንዲሰማቸዉ በማድረግ   በህዝቡ ዉስጥ “የጥቃትና የጭቆና ሰለባ ነኝ” የሚል መንፈስ (self-perceived collective victimhood ) እንዲሰማቸዉ ስለሚያደርጉ አንዳንድ ከብሄሩ የወጡ  የሰራዊት አባላትም የህዝቡን ስሜት ተከትለዉ ያለማመዛዘን ወደ ጥፋት ሊገቡ ይችላሉ፡፡ በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ብሄራዊ ተዋጽኦን በተግባር እዉን ለማድረግ ጥረት መደረጉ ባይቀርም ነገር ግን በይፋ የሚታይ ጉልህ ያለመመጣጠን መኖር የተነሳ መከላከያዉ “የእኛ አይደለም፡፡ እኛን አይወክለንም“ የሚል አመለካከት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ በስርአቱ ዉስጥ የአንድ አካባቢ ሰዎች ብቻ ተጠቃሚ ሆነዋል የሚለዉን የአንዳንድ ሰዎች ትችት እዉነት በሚያመስል ሁኔታ በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥም ብሄራዊ ተዋጽኦን የጠበቀ እንዲሆን በህገመንግስቱ የተቀመጠዉ ድንጋጌ በአግባቡ ሊተገበር ባለመቻሉ እስካሁንም በመከላከያ ዉስጥ ቁልፍ በሆኑ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በበቂ ሁኔታ አልተወከልንም፡ በሰራዊቱ ዉስጥ እኩል ዕድል ተጠቃሚነት(equal opportunity) የለም የሚለዉ ስሜት አልተቀረፈም፡፡ አንዳንድ ሃላፊዎች አዉቀዉም ይሁን ባለማወቅ ተዋጽኦን በታችኛዉ የሰራዊት አባላት አካባቢ በቁጥጥር የማመጣጠን ነገር ብቻ አድርገዉ በመገመትና ይልቁንም በከፍተኛ ሃላፊነት ቦታ ማመጣኑ በሚገባ ተግባራዊ አለመደረጉን እያወቁ ችግር እንደለለ ለማድረግ መሞከራቸዉ ተገቢ አይደለም፡፡ ተዋጽኦን በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ በአንድ ጊዜ ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነ ግልጽ ነዉ፡፡ በተለይም በላይኛዉ አመራር ሃላፊነት ደረጃ በማመጣጠን ተግባራዊ ለማድረግ የብቃት ችግር ሊኖር መቻሉ እርግጥ ነዉ፡፡ ነገርግን ተዋጽኦዉን ያለችግር ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልባቸዉ በዝቅተኛና መካከለኛ አመራር ደረጃና በልዩ ልዩ እድሎች እኩል ተጠቃሚነት መፍጠር አለመቻል ምንም አይነት ምክንያት ሊቀርብበት የሚችል አይደፈለም፡፡ የዚህ ዓይነት የተበዳይነት  ስሜት ከእርሰበርስ ግጭቶች ጋር ሲዳበል አደጋ ማስከተሉ አይቀርም፡፡

15/ ምን መደረግ አለበት?

* የመከላከያ ሰራዊቱ ህዝባዊ አሜነታ ከሚያሳጡ ማንኛዉም ድርጊቶች እንዲቆጠብ ማድረግ ይገባል፡፡

* ህዝቡ በጥቅሉ ሚዲያዎችና ሲቪክ ማህበራት ስለመከላከያ ሰራዊታችን ያለመሸማቀቅ የመሰላቸዉን አስተያየት የሚሰጡበት ሁኔታ መመቻት አለበት፡፡ በየጊዜዉ የፓናል የዉይይትና የምክክር መድረኮች እየተዘጋጁ የጋራ ግንዛቤ መፍጠርና ሰራዊቱን ከህዝቡ ጋር ማቀራረብ ያስፈልጋል፡፡

* ሰራዊቱ እየገነባበት ያለዉ የግንባታ መመሪያ ሆኑ የኢንዶክትሪን ስራዎች በየጊዜዉ  ሪቫይዝ እየተደረጉ ወቅታዊ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ገለልተኝነትን ሊሸረሽሩ የሚችሉ አሰራሮች ካሉ እየተፈተሸ እንዲታረሙ ማድረግ ያሻል፡፡

* ሰራዊቱን በተሟላ ደረጃ ፕሮፌሽናል ለማድረግ ከቴክኒካል ጉዳየች ዉጭ ባሉ ዲሞክራሲያዊና ህዝባዊ አመለካከቶች ላይ መሰረታዊ የባሪይ ለዉጥ እንዲያመጣ የሚያደርጉ የሪፎርም ስራዎችን በጥልቀት መስራት ይገባል፡፡

* በአገራችን በአስደንጋጭ ሁኔታ ተንሰራፍቶ ያለዉ ሙስና (endemic corruption) በመከላከያ ዉስጥ እንደተቋም ሲታይ የተሻለ ሁኔታ ላይ እንዳለ ባይካድም  አጋጣሚዉ ስለፈቀደላቸዉ ራሳቸዉን በህገወጥ መንገድ ለማበልጸግ ሰፊ እድል ያላቸዉ ግለሰቦች እንዳሉ ሳይዘነጋ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል፡፡ የሀገሪቱ ህግ አዉጭ በዚህ ረገድ ጠንክሮ መስራት ይገባዋል፡፡

* መከላከያ በሀገሪቱ ልማቱ ላይ በመሳተፍ እገዛ ማድረጉ ላይ  ቅሬታ ባይኖርም ከግብጽ ሁኔታ ትምህርት ተወስዶ አንዳንድ ቁጥጥሮች ሊደረጉ ይገባል፡፡  በተለይ METEC  እየሰራ ባለዉ ስራ አድናቆቴን መደበቅ ባልችልም ነገር ግን ሌሎች አገር በቀል ድርጅቶች ሊሰሩት የሚገባ የሲቪል ምርቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ ወታደራዊና ቴክኒካዊ አቅምን በሚያጠናክሩ ዘርፎች ላይ በይበልጥ ትኩረት ቢያደርግ የተሻለ እንደሆነ መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ ከወዲሁም ለኦዲተሮች  በሩን ክፍት አድርጎ ራሱን ለማስመርመር ዝግጁ መሆን ይገባዋል፡፡  የድርጅቱን ዋና ዋና አመራር ኃላፊነትም  ሲቪሎች የሚረከቡበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡

* የሀገሪቱ ህግ አዉጭ መከላከያን የመከታተሉን(የመቆጣጠር)ስራ ለአስፈጻሚዉ ትቶ ከሚቀመጥ ራሱ ዲሞክራሲያዊ ቁጥጥር ማድረግ መጀመር አለበት፡፡ ከሌለች አገሮች ልምድ በመነሳትም ህግ አዉጭዉ በመከላከያና በደህንነት ጉዳዮች ላይ የግንዛቤ እጥረት እንዳይኖርበት በዚህ መስክ ሰፊ ልምድ ያካበቱ ሲቪልና ጡረታ የወጡ የመከላከያ አባላትን በፓርላማዉ ጽ/ቤት ቀጥሮ እንዲያማክሩት  ማድረግ የሚችል ይመስለኛል፡፡  ከሁሉም ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥቶ በመከላከያ ጉዳይ ላይ አስፈጻሚዉን ተጠያቂ ለማድረግ ተነሳሽነቱን አቅሙ የለለዉ ፓርላማ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ያደርጋል ብሎ ለመገመት ይከብዳል፡፡ 

* የመከላከያ ሰራዊቱን ብሄራዊ ተዋጽኦ ለማመጣጠን አስካሁን የተደረገዉ አስመስጋኝ ጥረት እንዳለ ሆኖ ይበልጥ ትኩረት መደረግ ያለበት በታችኛዉ ሰራዊት አባላት ሳይሆን ከዚያ ይልቅ በዋነኛነት በአመራር ደረጃ ባሉት የሃላፊነት ቦታዎች ስለሆነ በዚያ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል፡፡ በተጨማሪ ለጥቂት የተመረጡ ሰዎች የተለየ ተጠቃሚነት (privilaged) የሚባል አሰራር እንዳይኖርና የሁሉም እኩል ተጠቃሚነት(equal opportunity) የሚረጋገጥበት ሁኔታ መፍጠር ይገባል፡፡

* መከላከያ ሰራዊቱ በዉስጥ ጸጥታ ማስከበር ተግባር (law enforcement task) ላይ ያለዉ ተሳትፎ በሚመለከት ዘርዘር ያለ የአፈጻጸም መመሪያ ተዘጋጅቶ የሰራዊቱ አባላትም ሆኑ ህዝቡም ጭምር እንዲያዉቅ የሚደረግበት ሁኔታ መፈጠር ይገባዋል፡፡ በተጨማሪ መከላከያ አዘዉትሮ በጸጥታ ማስከበር ሲሳተፍ ብዙ ችግር ሊያስከትል ስለሚችል በተቻለ መጠን የፖሊስ ኃይልንና የጸጥታ አስከባሪ ኃይልን ማጠናከሩ ይመረጣል፡፡ ችግሩ ከፖሊስ አቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር መከላከያ የፖሊስ ስራን ባይሰራ ይመረጣል፡፡ መከላከያ  ዋነኛ ትኩረቱንና ተልዕኮዉን በዉጭ ስጋት ላይ (external threat) ቢያደርግ  ይመረጣል፡፡

* የሀገሪቱ ገዥ ፓርቲ ለረዥም ጊዜ ስልጣን ላይ መቆየት ጋር ተያይዞ የመከላከያ ሰራዊቱ አመራሮችም ሆኑ አባላቱ  ገዥዉን  ፓርቲ  ቀስ በቀስ በመላመድ ራሳቸዉን ከፓርቲዉ ጋር የማቆራኘት ዝንባሌ በመፍጠር  በሂዴትም ከገለልተኝነት ባፈነገጠ መልኩ በስልጣን ላይ ያለዉን ፓርቲ ለመወገን  ስለሚችሉ ይህ ነገር ትኩረት ተሰጥጦት ከአሁኑ  ሰራዊቱን ማስተማር ይገባል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የመከላከያ ኤታ ማዦር ሹም ቢበዛ በየአምስት ዓመቱ መቀያየር ሲገባ ለአንድ ሰዉ የዕድሜ ልክ ስልጣን መደረጉ ተገቢ አይሆንም፡፡ የኤታማዦር ሹመት ከፓርቲ ጋር የሚያገኛነዉ ነገር እንደለለ ግልጽ ነዉ፡፡ ነገር ግን ፓርቲዉ ሳይለወጥ ለረዥም ጊዜ በሚቆይበት ሁኔታ ከፓርቲዉ ጋር መላመድ መጀመሩ የማይቀር ነዉ፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ በኛ ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም የሚባለዉና በነሱ (chairman of joint chief of staffs)የሚባለዉ በአብዛኛዉ ለአራት ዓመታት ነዉ የሚያገለግሉት፡፡ በሚቀጥለዉ ምርጫ ፕሬዝዳንቱም ሆኑ ፓርቲዉ ባይለወጥም ኤታማዦር ሹሙ በሌላ ተቀይረዉ በጡረታ ይሰናበታሉ፡፡ በዚህ መሰረት ከ2ኛ ዓለም ጦርነት በኋላ በአሜሪካ ኦባማን ጨምሮ አስራ ሁለት ፕሬዝዳንተች ተፈራርቀዉ ስልጣን የያዙ ሲሆን በዚህ ጊዜ ዉስጥ ሃያ አንድ ኤታማዦር ሹሞች እየተፈራረቁ ተሹመዋል፡እንደ አሰራርም ከምርጫ በፊት ሁለት ዓመት ከአዲሱ የፕሬዝዳንት ምርጫ በኋላ ደግሞ ተጨማሪ ሁለት ዓመት  በድምሩ ለአራት ዓመት ካገላገለ በኋላ ይሰናበታል፡፡ ይህ የኤታ ማዦር ሹሞች መቀያየር(chairman turnover)ለጥንቃቄ ተብሎ የሚደረግ ነዉ፡፡

ማጠቃለያ

ዛሬ በሃገራችን ዉስጥ በተከሰተዉ የፖለቲካዊና የጸጥታ ችግር ምክንያት መከላከያ ሰራዊታችን ከምንጊዜም  የበለጠ ትልቅ ተጋዳሮትና ጫና እንደገጠመዉ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ በዚህ መሰሉ ቀዉስ ዉስጥም መከላከያ ሰራዊታችን  የዜጎችንና ደህንነትና  የስርአቱን ህልዉና  ለማስጠበቅ ህገ መንግስታዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ መከላከያ ሰራዊታችን ከሌሎች ጸጥታ ኃይሎችና ከህዝቡ  ጋር በጋራ ተቀናጅቶ እየተወጣ ያለዉ የአሁኑ ሃላፊነት ከተለመደዉ ወታደራዊ ግዳጅ በባህሪይዉና በዉስብስብነቱ ለዬት ያለና አስቸጋሪ መሆኑ ግልጽ ነዉ፡፡  በራስ ህዝብ መሃል ከሚከናወን የጸጥታ ማስከበር ተግባር ይልቅ ከለየለት ጠላት ጋር በጦር ግንባር የሚደረግ ወታደራዊ ግዳጅ(ጦርነት) ሺህ ጊዜ ይመረጣል፡፡ የዜገችን ደህንነት ለማስከበር በሚደረግ ጥረት ሊፈጠር የሚችሉ ተግዳሮቶች ብዙ ናቸዉ፡፡ እያንዳንዱ ያልተጠበቁና ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታ የሚከሰቱ ክስተቶች በመከላከያ ሰራዊታችን መልካም ገጽታ ሊያበላሽ የሚችል መሆኑ ግልጽ ነዉ፡፡ ሀገር ሲታመስና ህዝቡ ሰላሙና ደህንነቱ አደጋ ላይ ሲወድቅ ዳር ቆሞ ማዬት አይገባዉምና መከላከያ ሰራታዊታችን በተቻለ መጠን ጥንቃቄ በታከለበት ሁኔታ ሰላምና ጸጥታን ለማስከበር ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይገባዋል፡፡ የመከላከያ ሰራዊታችኝንኝ የወቅቱን ተግባር የገዥዉን ፓርቲ ዕድሜ ማስቀጠል ጋር ለማያያዝ የሚሞክሩ ወገኖች ዓላማቸዉ ቀዉሱ ተባብሶ እንዲቀጥል ማድረግ በመሆኑ  መከላከያ ሰራዊቱም ሆነ ሌሎች ጸጥታ ኃይሎች ለዚህ መሰሉ አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ሳይዘናጉ ሃላፊነታቸዉን በብቃት መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የመከላከያ ሰራታዊችን ህዝባዊ ወገንተኝነት መፈተኛዉ ወቅት አሁን በተፈጠረዉ አገር አቀፍ ቀዉስ ዉስጥ ሆኖ የዜጎችንን ደህንነት በብቃት በማረጋገጥ ነዉ፡፡ ስለዚህ መላዉ የአገራችን ህዝቦች መከላከያ ሰራዊታችን የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ በሚያደርገዉ አልህ አስጨራሽ ተግባር ድጋፋቸዉ እንዳይለይና የበኩላቸዉንም አስተዋጺኦ እንዲያደርጉና በሁሉም ረገድ ከሰራዊታችን ጎን እንዲቆሙ በዚህ አጋጣሚ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

የሰራታችንን ገለልተኝነትና የህዝብ ወገናዊነት በተመለከተም  ከሁላችንም በተሻለ ሁኔታ መፍረድ  መፍረድ የሚችለዉ  ህዝቡ ነዉ ብዬ ነዉ የማስበዉ፡፡ መንግስት ስለ መከላከያ ሰራዊቱ ህዝባዊ ባህሪይ ከሚነግረን ይልቅ የመከላከያ ሰራዊቱ ባለቤት የሆነዉ ህዝብ ራሱ ቢናገር የበለጠ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡ በእኔ የግል አመለካከት አሁን ያለዉ የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት በመሰረቱ ከህዝብ ፍላጎትና ጥቅም የቆመና  ለህዝቡ ያለዉ ተቆርቋሪነትን  እጅግ ከፍተኛ መሆኑን እገነዘባለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሚፈጠሩ አስቻጋሪ ሁኔታዎች ተገፋፍቶና ከአቅሙ በላይ ሆኖበት  ሃላፊነቱን በሚወጣበት ወቅት ከህዝባዊ  ባህሪይዉ እየወጣ ነዉ የሚያሰኙ ክስተቶች በአንዳንድ አባላት ዘንድ  አልፎ አልፎ መታየታቸዉ ባይቀርም መከላከያ ሰራዊቱ እንደተቋም አሁንም ወደፊትም ህዝባዊ ወገንተኝነቱ እንደተጠበቀ ይቆያል፡፡ ህዝባችን እንዲያዉም የዚህ ዓይነት ለህዝብ ተቀርቋሪና ጀግና ሰራዊት ባለቤት በመሆኑ  ራሱን እንደ እድለኛ መቁጠር ነዉ ያለበት፡፡ ህዝቡ በመከላከያ ሰራዊቱ ሊኮራና የዚህ ሰራዊት ባለቤት እንዲሆን ያበቃዉ እግዜርን ማመስገን ይገባዋል፡ብዬ አስባለሁ፡፡

መከላከያ ሰራዊታችንን የሃገራችንን ሰላም በማረጋገጥ ህዝባዊ ወገንተኝነቱን በድጋሚ ያስመሰክራል!

ፈጣሪ ሃገራችንን ይጠብቃት!

*********** 

የኮ/አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሌሎች ጽሑፎች ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፡፡

Source: HornAffairs.com
ይህን ጽሑፍ ወስደው ሊያትሙ ቢሹ፤ የሆርን አፌይርስን እና የፀሐፊውን ስም በግልጽ መጥቀስ እና የዚህን ፖስት Link ማስቀመጥ ይገባል፡፡

0 Comments