Dec 22 2016

ሃገር ሲታመም ትውልድ ምን ያደርጋል?

(ዳግማዊ ተስፋዬ)

የኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂ ኤርትራን ለቀው በገፍ ስለሚወጡት/ስለሚሰደዱት ወጣት ኤርትራውያን ሲጠየቁ እንዲህ ብለው መለሱ : “እነዚህ ወጣቶች በተለያዩ ሃይሎች ና በምእራባዊያን ብልጭልጭ ተታለው የሚሰደዱ ቢሆኑም የትም ሆነው ኤርትራን የሚወዱና የሚረዱ ናቸውና ችግር የለዉም”! ወዲ አፎም ይህን ባሉ ከጥቂት አመታት በህዋላ ከወደ አዲሳባ አንድ ግምገማ ስለ እኔ ትውልድ ተሰነዘረ: ይህ ትውልድ ሃገር ወዳድ አይደለም የሚል!

በሁለቱም የመረብ ወንዝ አቅጣጫዎች ያለው “ያ ትውልድ” ስለዚህ ትውልድ (የኔ ትውልድ) ያለው ግምገማ ከምን መነጨ?  ስለሃገር ፍቅርና አንድ ትውልድ የሃገር ፍቅርን ስለሚገልጽበት መንገድ ካለው አመለካከት! እንዴት? “ከመይ ዝብል ለባም?” ይላል ትግራዋይ!

የኤርትራው መሪ ስልጣን ከያዘ ወዲህ የተወለደው ትውልድ “ኤርትራዊ መሆን ለእኔ ምን ይጠቅመኛል? ኤርትራዊ በመሆኔ ማግኘት የነበረብኝን መብትና ጥቅም እያገኘሁ ነው ወይ? መብትና ጥቅሞቼን የማላገኝ ከሆነስ ለምን ዝም ብዬ ግዴታዬን እወጣለሁ? ከእኔ ግዴታ ብቻ እንጂ ለኔ መብትና ጥቅም የማትቆም ኤርትራስ ምን ትሰራልኛለች?” ወዘተ የሚል ጥያቄ የሚያነሳ ትውልድ አልሆነበትምና ሃገር ወዳድነቱን አልተጠራጠረም። ከመረብ ወንዝ ወደ ደቡብ ያለው አዲሱ ትውልድ ግን ጥንታዊቷን ሃገርና መሪዎቿን ሲሞግት ከርሟልና በሃገር ፍቅር እጦት ተገምግሟል።

አንድ ትውልድ ሃገር ሲታመምበት፣ መንግሰት ሲበላሽበት በሁለት መልኩ ተቃውሞውን ያሰማል። የመጀመርያውና ወሳኙ ድምፅ ማሰማት ነው። ይህም ማለት ትውልዱ ነገሮች እንዲስተካከሉ ይጠይቃል ይታገላል ማለት ነው። ለዚህም አላማ የጊዜ የጉልበትና ብሎም የህይወት መስዋእት ይከፍላል። ይህ ታድያ ሃገሬ የኔ መስዋእትነት ይገባታል ከሚል እምነትና የኔ የድምጽ ተሳትፎ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ከሚል ዳሰሳና ተስፋ የሚመነጭ ነው።

ሃገራችሁ ታማ ለማከም የሚያስፈልጉትን ነገሮች የማድረግ ቁርጠኝነት ከሌላችሁና ሃገሬም የኔ መስዋእትነት አይገባትም እኔ ብሰዋም ምንም ለውጥ አይመጣም ብላችሁ የምታምኑ ፈሪዎች ከሆናችሁስ? “ጭጭ ነዋ! ዝም ነዋ!” ይላቸህዋል ይሄኔ አንዱ ዳያስፖራ አማሪካ ተቀምጦ። ይህ ሰዎች እንድ ነገር ሳይመቻቸው ሲቀር “ወይ በግልጽ ይቃወማሉ ወይም ዝም ይላሉ” ከሚል አመለካከት የሚመነጭ ነው።  የኢሳያስ አፈወርቂና የብዙ ሰዎች የሁኔታዎች ዳሰሳም ከዚህ ይመነጫል።   ኤርትራውያን ሆ ብለው አልተነሱም።  ለምን? ለኢሳያስ ስለተመቻቸው ነው! ለተቺዎች ደግሞ ፈርተው ዝም ስላሉ ነው ።

አይደለም! ዜጎች ያላቸው አማራጭ ዝም ማለት ወይም ድምፅ ማሰማት ብቻ አይደለም ይላል ታዋቂው ጀርመናዊ ስደተኛና አሜሪካዊው ምሁር  አልበርት ሂርሽማን። ሶስተኛ አማራጭ አለ: መውጣት ወይም ኤግዚት! “ኤግዚት” ማለት ሃገር ሲታመምባችሁ ሃገር መቀየር ማለት ነው። ይህም ሁለት መልክ ይይዛል: እንደ ግለሰብ መሰደድ ሲሆን እንደ ቡድን ደግሞ መገንጠል ነው ። (ለጊዜው ስለ መገንጠል ማውራቱን ትተን ስለ ግለሰቦች መሰደድ እናውራ)።

ዜጎች ሃገራቸው ስትታመምባቸውና ታግለው ሃገራቸውን  ለማዳን ፍቃደኝነትና ቁርጠኝነት ሳይኖራቸው ሲቀር አልያም ፍቃደኝነትና ቁርጠኝነት ቢኖራቸው እንኳ በነሱ ትግል ለውጥ መምጣት ይችላል የሚል የተስፋ ጭላንጭል ከሌላቸው ምን ያደርጋሉ? ይሰደዳሉ!  በእግራቸው ተቃውሞአቸውን ይገልፃሉ!  (After all, why raise your voice and get yourself killed as long as you can remove yourself from any environment should it become too unpleasant?)

በ17ኛው ክፍለዘመን ከአውሮፓ ሸሽተው አሜሪካን የመሰረቱት (መሰረትን ያሉት) አውሮፓውያን በአውሮፓ ስለነበረው ጭቆናና እየተካሄደ ስለነበረው አብዮት ጠንቅቀው ያውቁ ነበር ይላል ሂርሽማን! የነሱ አብዮተኝነት ግን የግድየለሽነት አብዮት ነው መሸሻቸውም ራሱን የቻለ አብዮት ነው! (The men in the seventeenth century who fled to America from Europe were keenly aware of the oppressions of European life. But they were revolutionaries with a difference, and the fact of their fleeing is no minor fact: for it is one thing to stay at home and fight the “canon and feudal law,” and it is another to leave it far behind.)

ስለዚህም አንድ ጠንካራ ተቃውሞ በሁለት መንገድ ይገለፃል ማለት ነው: ቁጭ ብሎ በማማረርና በማመጽ (ድምፅ በማሰማት) ወይም ጓዝ ጠቅልሎ በመውጣትና በመሰደድ (ተቃውሞን በእግር ኮቴ ማሳየት)! According to Erik Erikson, “You can actively flee, then, and you can actively stay put.”

ኤግዚትን ታድያ ሁለት አካላት ይወዱታል : አመጽና ትግል የሚፈሩ ዜጎችና መንግስታት! ለዘመናት መንግስታት ስደትን እንደ አመፅ ማብረጃ ሲጠቀሙበት ኖረዋል። ካስትሮ ኩባውያን ሃገራቸው ላይ ተቀምጠው ከሚያማርሩ ቢሰደዱ ይሻለኛል ብሎ ዜጎቹ በገፍ ሲሰደዱ ዝም ብሎ አይቷል እንዲሲሰደዱ አበረታቷል ካስትሮ ለ50 ምናምን አመት የገዛው አንድም በተቃውሞ ሊጥሉት ይችሉ የነበሩት ኩባውያን ማያሚ ስለከተሙ ነው ሁለትም የሶሻሊዝም አምላክ ከ600 የሲአይኤ የግድያ ሙከራ ስላተረፈው ነው!  ኮሎምብያ የቀድሞ ባለስልጣናት ሃገር ውስጥ ተቀምጠው ችግር እንዳይፈጥሩ ወይም አመጽ እንዳያበረታቱ በማሰብ ስደትን የሚያበረታታ ህግ አውጥታለች: አንድ ጡረታ የወጣ ፕረዚደነት ሃገሩ ቢቀመጥ የሚከፈለውን ያከል የኮሎምብያ ብር አሜሪካ ቢቀመጥ በዶላር ይከፈለዋል (አንድ ዶላር አስር የኮሎምብያ ብር ከሆነ አስር እጥፍ ይከፈለዋል ማለት ነው)።

በአጠቃላይ በጣም ቮካል የሆኑ ዜጎቻቸው ቢሰደዱ መንግስታት ለብዙ ዘመን መግዛት ይችላሉ። ስለዚሀም መንግስታት መሰደድን ይወዱታል። ለዚህም ነው 4 ሺ ኤርትራዊ በወር ሲሰደድ ሻእብያ ምንም የማይገደው። ይህ ፍልሰት ጭራሽ የሪሚታንስና የአውሮፓ ህብረት እርዳታ ምንጭ ከሆነማ እልል ነው !

ሌላ ኢግዚትን እንደ መፍትሄ የሚወዱት ሰዎችና ቡድኖች ፈሪዎች ናቸው! ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ወደ ተሻለ መቀየር የማይቻል የሚመስላቸው ተሰዳጆች! ያለው ሃገር መሻሻል የሚችል የማይመስላቸው ተገንጣዮች! According to Hirschman, “in the choice between voice and exit, voice will often lose out, not necessarily because it would be less effective than exit, but because its effectiveness depends on the discovery of new ways of exerting influence and pressure toward recovery. However “easy” such a discovery may look in retrospect the chances for it are likely to be heavily discounted in ex ante estimates, for creativity always comes as a surprise. Loyalty then helps to redress the balance by raising the cost of exit”.

በድምፅ ለውጥ ማምጣት ከባድ የሚመስል ግን ደግሞ ወሳኝ የለውጥ መንገድ ሲሆን ኤግዚትን እንደ ተቃውሞ ስትራተጂ መምረጥ ደግሞ ቀላሉ ግን ብዙ ጊዜ ውጤታማ የማይሆን ስትራተጂ ነው! ሰዎች ከቀላሉ አማራጭ ከባዱን አማራጭ የሚመረጡት ጠንካራ ሃገር ወዳድና ተስፈኛ ሲሆኑ ነው! ስለዚህ አንድ ሰው ከኤግዚት ይልቅ ድምጽን ሲመርጥ በኤግዚት (ለምሳሌ በመሰደድ ወይም እንደ ቡድን በመገንጠል) ሊያገኘው ይችል የነበረውን ጥቅም ትቶና በድምጽ ማሰማቱ የሚከፍለውን ዋጋ ተቋቁሞ ነው ማለት ነው! ይህንን የሚያደርገው ደግሞ አንድም ሃገሬ የመሻሻል ተስፋ አላት ከሚል እምነት ሲሆን ሁለትም ለሃገሩ ያለው ፍቅርና ታማኝነት የመሰደድን (የኤግዚትን) ሳቢነት ቀንሶ ዋጋውን ደግሞ ከፍ ስለሚያደርግ ነው!

ስለዚህም የኔ ትውልድ ከኤግዚት ይልቅ ድምፅን፣ ከመሰደድ ይልቅ መቀመጥን፣ ከመገንጠል ይልቅ ፌደሬሽኑን የሚመርጠው፣ ተቃውሞውን እንደ ኤርትራውያን በእግሩ ሳይሆን በእጁ የሚያሳየው፣ ሃገሩን ስለሚወድና ለሃገሩ ታማኝ ስለሆነ ነው ! የኔ ትውልድ እንደ ኤርትራውያን አይሰደድም ! የኔ ትውልድ ይህ ፌዴሬሽን እንዲጎለብትና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ድምጹን ያሰማል እንጂ አይሸሽም! የኔ ትውልድ ከባዱን እንጂ ቀላሉን አማራጭ አይከተልም! ትክክለኛ ለውጥ ደግሞ በከባዱ ትግል እንጂ በቀላሉ አማራጭ አይመጣም ! የኔ ትውልድ ሃገሩን ይወዳልና ሃገሩን ጥሎ የትም አይሄድም! የኔ ትውልድ ከኢትዮጽያ ሌላ ሁለተኛ ሃገር የለውምና የትም አይሄድም! ለውጥ ደግሞ የትም መሄጃ በሌላቸው ሰዎች ነው የሚመጣው!

********

0 Comments

ስለጽሑፉ ምን ይላሉ? አስተያየቶን ያካፍሉን፡፡