Nov 17 2016

አገራችን ኢትዮጵያ ያጠላባት አደጋና ስለ መውጫዋ አቅጣጫዎች

(በላይ ደርሸም)

አጠቃላይ

አገራችን ኢትዮጵያ ግዙፍ ፈተና ተደቅኖባታል፤ ዜጎችዋ ግዙፍ ፈተና ተደቅኖብናል፡፡ ከዚህ ፈተና ልንወጣ የምንችለው በራሳችን ጥረትና ብልህነት ብቻ ነው፡፡ እንባችንን ልናደርቅ የምንችለው እርስ በርሳችን ተመካክረን በምንደርስበት አግባቢ መንገድ ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁሉም በየራሱ ጉዳይ ተጠምዷል ወይም ቅድምያ የሚሰጣቸው ብሄራዊ ጥቅሞች አሉት፡፡ አጋር የሚባሉት ከጎናችን ይቆማሉ ወይም መፍትሄ እንዲመጣ ያደርጋሉ በሚል ተስፋና ስሌት ከመመራት ተቆጥበን በራሳችን የችግር መፍቻ እሴቶች ላይ ተመርኩዘን በጋራ መምከርና መፍትሔ መሻት አለብን፡፡ ነገሩ አሞሌ ለራስህ ብለህ … እንደተባለው ነው፤ እኛው ራሳችን ለራሳችን ብለን ነገሮች ከቁጥጥራችን ውጪ እንዲሄዱ መፍቀድ የለብንም፡፡

ይልቁንስ በእኛ መበጣበጥና እርስ በርስ መገዳደል ብሄራዊ ጥቅማችንን እናስጠብቃለን ብለው ለሚገምቱ ወገኖች በር እንዳንከፍትላቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚጠበቅብን እንገንዘብ፡፡ የምንገኝበት አካባቢ ውስጣዊ ሁኔታችንን ሊያወሳስቡ የሚችሉ ሃይሎችና ቀውሶች የተበራከቱበት አካባቢ ነው፡፡ የአገራችንን እና የሕዝባችንን ጥቅምና ህልውና አስቀድመን ነገሮችን አለዝበንና ልዩነቶቻችንን አመቻምቸን ችግራችንን በራሳችን ለመፍታት ካልተነሳን፤ አካባቢያችን ችግራችንን ይበልጥ ሊያቀጣጥል ካልሆነ በስተቀር ሊያበርድልን እንደማይችል መዘንጋት የለበትም፡፡

አገራችን የገባችበት ቀውስ በሃይል የሚፈታ አይደለም፡፡ የሃይልና የጉልበት መንገድ አሸናፊና ተሸናፊ አይኖረውም፤ ሁላችንንም ተሸናፊ የሚያደርግ እንጂ፡፡ የሃይልን መንገድ መግታት ላይ ለግመን እርስ በርሳችን እንገዳደል ካልን ደግሞ፤ ጠበንጃና ፈንጂ ቤታችን ደጃፍ ድረስ የሚያመጡልን አናጣም፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ የጥፋት አካሄድ አንዴ ተዳፋቱን ከያዘ በኋላ በሽምግልና የተገታ በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል አንዳችም የቀውስ ታሪክ በዚህ አካባቢ እንደሌለ ልብ ይሏል፡፡ የቁልቁለት መንገዱን ወደን ከገባንበት፤ ችግራችን ማቆምያ የሌለው በርካታ መንግስታትና ቡድኖች የሚምቦጫረቁበት፤ ለሽምግልና የማይመች ከፍተኛ ቀውስ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ በቅርቡ ያገኘሁት በሶርያ ለተባበሩት መንግሰታት ድርጅት በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ሲሰራ የቆየ ሰው እንዳጫወተኝ፤ በአሁኑ ወቅት በሶርያ ቀውስ ውስጥ ከዘጠና ያላነሱ መንግስታት እጃቸውን አስገብተዋል፡፡ የወቅቱ የአገራችን ጉዳይ ምን ያህል ሊያሳስበን እንደሚገባ የሚጠቁም ምሳሌ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ለአንድ ወይም ለሌላ ፓርቲ ወይም ብሄር እንዳሻው ያድርግ ወይም ይወጣው ተብሎ ዳር ቆሞ የሚመለከቱት ጉዳይ አይደለም፡፡ የአገራችንን ዕጣ ፈንታ የሚገዳደር ከባድ ጉዳይ ነው፡፡

ችግራችን በድንገት ከምንም የተነሳ አይደለም፤ እየተደመረና እያደገ የመጣ የፖለቲካ ችግር ነው፡፡ ጥያቄዎች የሚይዙት መልክ ከቦታ ቦታ ይለያይ እንጂ የሁሉም ማጠንጠኛ ግን የፖለቲካ ስልጣን ጥያቄ ነው፡፡ የችግሮች ማጠንጠኛው ነጥሮ ካልወጣና መፍትሔው በዚሁ ላይ ካላነጣጠረ ውሎው አጉል መዳከር ይሆናል፤ ጊዜም ይባክናል፡፡ ከእንግዲህ የሙከራ ጊዜ የለንም፡፡ አማራጮቻችንም ያንኑ ያህል እያነሱና እየጠበቡ ስለመሆናቸው መገንዘብ አለብን፡፡

አገራችን ያለችበት ሁኔታ አስቸጋሪና እጅግ አሳሳቢ መሆኑ የሁላችንንም ግንዛቤ የሚሻ ጉዳይ ቢሆንም፤ ይህ ግን በራሳችንና በአገራችን ዕጣ ፈንታ ላይ ተስፋ ሊያስቆርጠን አይገባም፡፡ ጉዳዩ የእያንዳንዳችን ጉዳይ እንደሆነ ተገንዝበን፤ እጅጉን ተጨንቀን ተጣበን ከመከርንበት መፍትሔ ሊገኝለት የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንደ ሩዋንዳ እርስ በርስ ወደ መተራረድ እንሄዳለን ይላሉ፡፡ አገራችን ትበታተናለችም ይላሉ፡፡ ነገሩን ወደ ዘር ጥላቻ የሚጠመዝዙና እርስ በርስ መበዳደልን የሚቀሰቅሱም አሉ፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ ጨለምተኝነትና ምፅአት ትንበያ ልንመራ አይገባም፡፡ ሽንፈትና የሞራል መላሸቅ ይሁን አይበገሬነትና አሸናፊነት እንደወረረሽኝ በቀላሉ ይተላለፋሉ፡፡ በተለይም ከመሪዎችና ከሊሂቃን ሲወጡ፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ከዚህ የደረሰችው በረጅም ችግርና ፈተና አልፋ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም፡፡ በእርስ በርስ ጦርነቶችን አልፈናል፡፡ በበርካታ የውጭ ወረራዎች ተፈትነናል፡፡ አስቃቂ በሆኑ የድርቅና ረሃብ ወቅቶችም አልፈናል፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ እንደ አገርና እንደ ሕዝብ አለን፡፡ እነዚህን አልፈን እዚህ ድረስ ለመዝለቅ ያስቻሉን እሴቶች አሁንም ሁሌም ከውስጣችን እንዳሉ አምነን፤ እንደዚህ ባለው ፈታኝ ወቅት እነሱን ማፈላለግና አጥብቆ መያዝ ይገባናል፡፡ ለመኖርና ለመበልፀግ የተፈጠርን አገርና ሕዝብ ነን፡፡ ፈጣሪያችን ይህን ያደረገው መልሶ ሊያጠፋንና ሊያጋድለን እንዳልሆነ አምነን፤ ከፈጣሪያችን ጋራ በልበ ሙሉነት እርስ በርስ በመተሳሰብ ችግራችንን እንፍታ ብለን መነሳት አለብን፡፡

መፍትሔው ከእያንዳንዳችን ዘንድ ነው ያለው፡፡ መንግስት የመፍትሔው አካል እንዲሆን እንጠይቅ እናበረታታ፡፡ መንግሰት የመፍትሔው አካል ቢሆን መውጫው የቀለለ ይሆናል፡፡ ይህ ሲባል ግን መንግስት ካልመጣ ብለን እኛ ግዴታችን መወጣቱን እንዘነጋለን ማለት አይደለም፡፡ ከወራት በፊት ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳኤ “የሃገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታና የመፍትሔ ሃሳቦች” የሚል ፅሑፍ አስነብቦናል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ፤ ለዚሁ ሁኔታ አስተዋፅኦ አድርገዋል ብሎ ያመነባቸውን ምክንያቶች፤ በሰፊው ከመተንተን ባሻገር አሁን ያለውን ሁኔታ ተከትሎ ሊከሰቱ ይችላሉ ያላቸውን ቢሆኖችም አስቀምጧል፡፡ በመጨረሻም አገራችን ከዚህ ችግር ትወጣ ዘንድ መደረግ አለበት ብሎ ያመነበትን አስቀምጦልናል፡፡ ጀኔራል ፃድቃን እኔ የሚታየኝን ወርውሬአለሁ፤ ሌሎቻችሁም የሚታያችሁን ወርውሩና ተወያይትን የምንደርስበት የሚያስማማ ሃሳብ ዙርያ ተባብረን አገራችንን ከችግር እናውጣ ብሎናል፡፡

ጥቂት ሳምንታት ቆየት ብሎም ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “የወያኔ አገዛዝና የኢትዮጵያ ወደፊት“ በሚል የፃፉትን ፅሑፍ አግኝቼ አንብቤ ነበር፡፡ እንዲህ ብለው ነበር ነገሩን የጀመሩት፤ “ከዚህ በፊት ከክንፈ.. ጋር ብቻ ተነጋግሬበት ነበር፤ ዛሬ እንደ ክንፈ የሚያምነኝና የማምነው ወያኔ የለም፤ ችግሩም እየተባባሰ በመሄዱ ጊዜ የሚሰጥ አልመሰለኝም፡፡ ስለዚህ አደባባይ ላውጣውና የሌሎች ሰዎች ሀሳብ ተጨምሮበት በጊዜ መፍትሔ ብንፈልግ ተገቢ ይመስለኛል፡፡” ፕሮፌሰር መስፍን ክንፈ ገብረመድህን ጋር ማለታቸው ነው፡፡ እርሳቸውም አገራችን ላይ ያጠላው አደጋ አሳስቦአቸው ምን እናድርግ ብለው አስበው እና ተጨንቀው ይህን ፅሑፍ እንዳካፈሉን መገንዘብ ይቻላል፡፡

ፕሮፌሰሩ ዘርን መሰረት ያደረገ የጥላቻ ፖለቲካ ሊያስከትል የሚችለውን መዘዝ እና አሁን ስልጣን ላይ ያለው ቡድን ስልጣን ላለመልቀቅ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ያሉዋቸውን ስጋቶች ከማመልከት ባሻገር አገራችንን ከችግር ያወጣልናል ያሉትን የእርቀ-ሰላም አቅጣጫ ጠቁመዋል፡፡ በርካታ የትግራይ ተወላጆች፤ ህወሓት እና ወያነ የተለያዩ እንደሆኑ፤ መወየን ማለት እምቢ ኣሻፈረኝ ብሎ ግፈኛ አገዛዝን መቃወም ማለት እንደመሆኑ፤ ወያነ መሆን ህወሓት መሆን አይደለም እንላለን፡፡ ፕሮፌሰሩ ወያነ ሲሉ ግን ህወሓትን ማለታቸው እንደሆነ እንገንዘብና፤ ያለኝን ወርውሬአለሁ ሌሎቻችሁም ጨምሩበትና መፍትሔ እናፈላልግ ብለው ለእያንዳንዳችን ያቀረቡትን ጥሪ አዳምጠን ሃሳቡን በጋራ እናዳብረው፡፡ ጀነራሉና ፕሮፌሰሩ አንዱ ሌላኛው ባነሳቸው ትንታኔዎች ላይ ይስማማሉ ማለት አይደለም፤ ሁለቱንም ያሚያስማማቸው የጋራ ጭብጥ ግን አለ፤ “ጎበዝ አገራችን ፈተና ላይ ናትና ለአጣዳፊ ተግዳሮት መፍትሄ ፍለጋ በጋራ እንምከር እንነሳ” የሚል፡፡ አቃቂርና ነገር መጠምዘዝ ይብቃ እንበልና፤ ሌሎቻችንም በቅንነትና በአገር ወዳድነት የሚታየንን እንወርውር፡፡

በዚህ መንፈስ ያለኝን ለመወርወር ብቅ ብያለሁ፡፡ ይህን የማደርገው የዜግነት ግዴታዬ ስለሆነ እንጂ ሌላ አላማና አጀንዳ ኖሮኝ አይደለም፡፡ ሕወሓትንና ኢህአዴግን አሳምሬ አውቃቸዋለሁ፡፡ እዚህ የማስቀምጠው ሃሳብ የእኔና የእኔን እምነትና አቋም እንጂ ማንንም ድርጅት ወይም ፓርቲ በመወከል፣ በመደገፍ ወይም በመቃወም አይደለም፡፡

ማጠንጠኛው ፖለቲካ ስልጣን ነው

ለአስርት አመታት ሰሚ ያጣው የዜጎች ተቃውሞና ብሶት ለድፍን አንድ ዓመት ወደ ዘለቀ የኢትዮጵያውያን እምቢታ ተሸጋግሮ በምርጫ ተረጋገጠ የተባለውን የምልአተ ሕዝብ ይሁንታ እርቃኑን አውጥቶታል፡፡ ብሶትና ችግሬ መንግስት ይፈታልኛል የሚለው የዜጎች ተስፋ ተሟጦ ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነት የመንግስትን የበታች አስተዳደራዊ መዋቅርን ማፍረስና በመሰለው መልኩ ተተኪውን ወደ ማስቀመጥ ተሸጋግሯል፡፡ የማጓጓዣ መስመሮች ተዘግተው የተለመደው የአገሬው የእለት ተእለት እንቅስቃሴ በመስተጓጎሉ መንግስት የተለመደው መንግስታዊ ተግባሮችን ማከናወን እንደተሳነው ለማንም ገልፅ ሆኗል፡፡

ይህንን ለማቆምና ለመቀልበስ መንግስት ባሰማራቸው የፀጥታ ሃይሎችና በሕዝቡ መካከል በተፈጠረ ግብግብ ፀጥታ ደፍርሷል፣ በሰው ሕይወትና አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ በመንግስትና በግል የልማትና የአገልግሎት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ መንግስት ይህንን ሁኔታ በለመደው ስርዓቱን የማስከበር ዘዴዎቹ ለማቆም እንዳልተቻለው አምኖ በሃያ አምስት ዓመት እድሜው ለመጀመርያ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡ በዚህ አስታኮም በፓርላማው ውስጥ ያለው የአንድን ወገን አቋም ብቻ የሚያስተጋባውን ውክልና አስተካክላለሁ ብሏል፡፡

እነዚህ እርምጃዎች መንግስት ያልተለመደ መፍትሄ ፍለጋ ውስጥ ለመግባቱ አመልካች ስለመሆናቸው የሚያከራክር አይሆንም፡፡ የፓርላማ ውክልና እንዲስተካከል ይደረጋል፤ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በሚደረግ ምክክር የምርጫ ህጉ እንዲሻሻል ይደረጋል፤ መባሉ ችግሩ የፖለቲካ ስልጣን ጥያቄ ለመሆኑ ግንዛቤ ያገኘ ይመስላል፡፡

ሰሞኑን በአገራችን የታየው የወገኖቻችን ክቡር ህይወት መጥፋት እና የአገር ቁሳዊ እሴቶት ቃጠሎና ጉዳት ሌላ ትልቅ መልእክትም አስተላልፏል፡፡ የዜጎች ነፃነትና የሃገር ኢኮኖምያዊ እድገት የማይነጣጠሉ መሆናቸውን፤ ቢነጣጠሉ የሚከተለው መዘዝ ግዙፍ መሆኑን፡፡

የአፈፃፀም ነው፣ የመልካም አስተዳደር ነው፣ እተባለ የችግሩን ክብደት በዝያውም የመፍትሔውን ጥልቀት ለማቃለል ሲካሄድ በቆየው ዳርዳርታ ወርቃማ ጊዜ ባክኗል፡፡ ቀደም ያለውን ትተን አምና ሕዳር ችግሩ ወደ ደም መፋሰስ መሸጋገሩ ሲታይ፤ ይህ አሁን ብቅ ያለው ግንዛቤ እንደግንዛቤ ቢያዝ ኖሮ ብዙ ህይወት፣ የስነልቦና ስብራት፣ የሕዝቦች ግንኙነት መሻከር እና የሃገር ቁሳዊ እሴቶች ጉዳትን ማስቀረት ወይም መቀነስ በተቻለ ነበር፡፡ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ችግሩ እስከዚህ ድረስ መወሳሰቡ ችግሮቻችንን ለመፍታት ያለን ጊዜ እጅጉን እየተጣበበ ለመምጣቱ አመልካች ነው፡፡

የፖለቲካዊ ስልጣን ጥያቄ ስለመሆኑ በመንግስት ባለስልጣናት መካከል በቂ ምክክርና መግባባትን ተንተርሶ የመጣ እና ጥልቀት ያለው ግንዛቤ ስለመሆኑ ብዙ ጥርጣሬ ማጫሩ አይቀሬ ነው፡፡ ይህንን ጥርጣሬ መቀነስ ከተቻለም መቅረፍ የሚቻለው የተሰጠው መግለጫ ተመጣጣኝ በሆኑ ድርጊቶች ሲታጀብ ነው፤ ለዚያውም በአፋጣኝ፡፡ ይህ ካልሆነ ችግሮቻችንን ለመፍታት ያለን ጊዜ ብቻ ሳይሆን እንደመፍትሔ ታሳቢ ሊሆኑ የሚችሉትም አማራጮቻችን እጅጉን እያነሱና እየጠበቡ መሄዳቸው ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡

ችግሩ የፖለቲካዊ ስልጣን ነው ማለት የችግሩን ግንድ መለየት ማለት ነው፡፡ ግንዱን ከያዙ መፍትሔውም ከግንዱ ዙርያ እንጂ ከቅርንጫፎቹ ዘንድ እንደማይሆን መገንዘብና ለዚህ የሚመጥን መፍትሔ መሻት ይጠይቃል፡፡ የፖለቲካ ስርዓቱ በአንድ ፓርቲ ወይም ቡድን ተጠቅልሏል፡፡ ለሃያ አምስት ዓመት ስልጣኑን ጠቅልሎ የያዘው ቡድን በሂደት ኢኮኖሚውንም ጠቅልሎ በመያዝ ፖለቲካዊ ስልጣንና ሃብት ማካበት የማይነጣጠሉበት ሁኔታ በመፍጠሩ የሕዝቡ የፖለቲካና የልማት ተቋዳሽነት ጥያቄዎች የተሳሰሩ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ከዚህም ባሻገር የፖለቲካና የልማት ተቋዳሽነት ጥያቄዎች ስልጣን ላይ ያለውን ቡድን ጥቅሞች የሚነኩና ገዢዎችን የሚያስፈሩ በመሆናቸው ወደ ሃይል አፀፋና የደም መፋሰስ ሰንሰለት የሚወስዱ እየሆኑ ነው፡፡ አንዱ ጥፋት ሌላውን እየወለደ አሁን ያለንበት ፖለቲካ ስልጣን፤ ዝርፍያ እና ቅጥ ያጣ አፈናና ጭካኔ እጅግ የተቆላለፉበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ ችግር በመንግስትና በሕዝብ መካከል የተፈጠረ ችግር ከመሆን አልፎ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን እየነካ ነው፡፡ ከዚህ የሚገኝ ትርፍ ያለ ይመስል የተወሰኑ ሊሂቃንም ይህንን ጉዳይ እያራገቡት ነው፡፡

ችግሩ ፖለቲካዊ ነው መፍትሔውም በዚህ ዙርያ ያተኩር ሲባል፤ የሌብነትን ችግር ለማቃለል አይደለም፡፡ ሌብነት የነገሰው ስልጣን በመጠቅለሉ ስለሆነ ሌብነትም ሆነ እሱን ተከትለው የሚመጡት ችግሮች መፍትሔ የሚበጅላቸው የፖለቲካ ስልጣን ጥያቄን በተገቢው መደላደል ላይ ስናስቀምጠው ነው፡፡ ይህም ማለት:-

* ምልአተ ሕዝቡ የመረጠው ፓርቲ ወይም ስብስብ ስልጣን ይይዝ ዘንድ ተኣማኒነት ላለው ምርጫ አገራችንን ለማዘጋጀት መወሰን ማለት ነው፡፡

* ለዚህ የሚያበቃን ፍኖተ ካርታ እንዲዘጋጅ ማድረግ ነው፡፡ ካለንበት ሁኔታ በመነሳት በነፃ ምርጫ ስልጣን የሚያዝበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች እንደመኖራቸው ከመነሻችን ወደ መድረሻችን የሚያሸጋግረን ሃገራዊ ፍኖተ ካርታ ያስፈልገናል፡፡ ይህን የሚቀርፅልን ገለልተኛ አካል ይቋቋም ዘንድ የመንግስት ሙሉ ፈቃደኝነት መኖር ማለት ነው፡፡

* ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሉንም፡፡ በአገራችን በሳልና ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አለመኖር ኢትዮጵያን አንድ ትልቅ ብሄራዊ እሴትና ተቋም እንዳሳጣት ሊታመንበት ይገባል፡፡ ጠናካራና በሳል ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዳይኖሩን በማድረጉ ረገድ መንግስት ትልቅ ድርሻ እንዳለው የሚካድ አይደለም፡፡ መንግስት ይህንን ስትራተጂውን በመቀልበስ አገራችን በሳልና ጠንካራ ፓርቲዎች እንዲኖሯት የሚያስችል ማእቀፍ መፍጠር ይኖርበታል፡፡

* በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና አባላት፤ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ‘አሸባሪ’ የሚል ታርጋ ተለጥፎባቸው ለእስር ተዳርገዋል፤ አገራቸውን ለቀው በስደት የሚኖሩም አሉ፡፡ የታሰሩትን በመፍታት ሕጎቹን በመፋቅና በማሻሻል የሕዝቡን ልቦና የማረጋጋት እርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ ከዚህ ባሻገር እነዚህ የመፍትሄው አካል ይሆኑ ዘንድ ሁኔታውን ሊያመቻች ይገባል፡፡

* ሰላማዊ ለሆነ የስልጣን ሽግግር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ከአሁኑ ማድረግ፡፡

ምርጫ 97 ሁላችንም ልንማርበት የምንችል ቁም ነገር ትቶ አልፎአል፡፡ ገዢው ፓርቲ ለነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ዝግጁ ነኝ አለ፤ ብሸነፍስ ለሚለው ቢሆን ግን አልተዘጋጀም ነበር፡፡ ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ከተካሄደ እናሸንፋለን አሉ፤ ቢያሽንፉ ሰላማዊ ሽግግር ይኖር ዘንድ ተሸናፊውን እንዴት እንያዘውና እንሸኘው የሚል መልስ አልነበራቸውም፡፡ አሁንም ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ይኑር ስለተባለ ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ ነፃ ምርጫ ከተካሄደ ኢህአዴግ ሊያሸንፍ ሳይሆን ሊሸነፍም እንደሚችል ማሰብ አለበት፡፡ ከተሸነፈ ሽግግሩ እንዴት ይከወናል የሚለው ጥልቅ ምክክርና ዝግጅት የሚጠይቅ ከባድ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ታሕሳስ 2001 ኢምፔርያል ሆቴል በተካሄደውና በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት የምክክር መድረክ (መድረክ) በተጠራ የፓርቲዎች የምክክር ስብሰባ ላይ በውቅቱ በመድረክ አመራር ውስጥ የነበሩት ግለሰቦች በርከት ያሉ ጥናታዊ ፅሑፎችን አቅርበው ነበር፡፡ በዚህ የመድረክ አመራሮች ባቀረቧቸው ፅሑፎች ውስጥ ሰላማዊ የትግል አማራጭ፤ የሰላማዊ ፖለቲካዊ ሽግግር ጥያቄ እና ሰላማዊ የትግል መልኮችና ተግባራዊነታቸው በኢትዮጵያ የሚል በአቶ ስየ አብርሃ በቀረበ ፅሑፍ ላይ በሰላማዊ ሽግግር ጥያቄ ላይ ዘርዘር ያለ ሃሳብ ቀርቦ ነበር፡፡ እንዲዚህ የሚል ይገኝበታል

ከእርስ በርስ መገዳደልና መውጫ የለሽ የድህነት አዙሪት ለመውጣት እስካስቻለ ድረስ፤ ኢህአዴግ ሽንፈቱን ተቀብሎ ለአሸናፊው ወገን ስልጣን ለማስተላለፍ ፈቃደኛ እስከሆነ ድረስ፤ኢህአዴግን በዘንባባ ዝንጣፊ መሸኘቱ ከባድ ዳገት ሊሆን አይገባም፡፡ ከብቀላ በፀዳ መንፈስ ኢህአዴግና መሪዎቹ ነፃነታቸው ተጠብቆ በሃገሪቱ ፖለቲካ ተዋናይ ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያስችል ዋስትና መስጠት ይገባል፡፡”

የአገራችን ሁኔታ ያኔ ከነበረበት ሁኔታ ይባሰውኑ መወሳሰቡ የዚህ ጉዳይ አስፈላጊነት አጅጉን ወቅታዊ ያደርገዋል፡፡ ከፍ ብየ በጠቀስኩት ፅሑፋቸው ፕሮፌሰር መስፍንም እንዲህ ብለዋል

ወያኔ በአለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ ብዙ ጥፋቶችን መፈፀሙ አይካድም፤ ምናልባት ፈረንጆች እንደሚሉት (The road to hell is paved with good intentions) በሌላ አነጋገር ሰዎች ወደገሀነመ እሳት የሚገቡት ጥሩ እንሠራለን እያሉ በፈፀሙት ጥፋት ነው ማለት ነው፤ ወይም ደግሞ ወያኔ በጎረምሳነት ስሜት የአክሱም ፅዮንን ኪዳን በአጉል ማርክሳዊ ፍልስፍና በመለወጣቸው ለወያኔም፣ ለትግራይ ሕዝብም፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብም በአጠቃላይ የሚጠቅም መስሏቸው የፈፀሙት የጉርምስና ጥፋት ነው፤በዚህ ሁሉ ምክንያት የወያኔን ጥፋት መከርከም ይቻል ይሆናል፤ ይህ የሚሆነው በሥልጣን ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ነገር ግን በወያኔ በኩል ሆነን ስናየው ከሥልጣንም ሌላ በጣም አስቸጋሪ ምርጫ ይገጥመዋል፤ ብዙዎቹ ባለሚልዮን ወይም ባለቢልዮን ዶላር ሀብታሞች ሆነዋል ይባላል፤ ይህንን ከኢትዮጵያ የተዘረፈ ሀብት መመለስ ሥልጣንን ለሕዝብ የማስረከቡን ያህል ቀላል አይመስለኝም፤ ቢሆንም በሁለት በኩል በጎ ፈቃድ ከአለ መፍትሔ የማይገኝለት ችግር አይኖርም፤ የደቡብ አፍሪካ ግፈኞችመፍትሔ አግኝተውለታል፤ በጎ ፈቃዱ ከአለን እኛም አያቅተንም፡፡ ፍትሐዊ የሆነ መፍትሔ ላይ ለመድረስ ለወያኔ መንፈሳዊ ወኔ ያስፈልገዋል፤ያለደ ክላርክ የመንፈሳዊ ወኔ የደቡብ አፍሪካ ችግር አይፈታም ነበር፤የወያኔ መሪዎችለእርቀ ሰላም የሚያዘጋጃቸውን መንገድ ቢመርጡ ለራሳቸውም፣ ለትግራይ ሕዝብም፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብም፣ ለአፍሪካ ቀንድ ሕዝብም ትልቅ የሰላምና የልማት በርን ይከፍታሉ፤ በጉልበተኛነት ያላገኙትን ክብር በሰላም ያገኙታል፤ ኢትዮጵያ በፖሊቲካም ሆነ በመንፈሳዊ ታሪክዋ የነበራትን የሽምግልና የበላይነት የአፍሪካ ቀንድን ሕዝቦች ለመምራት ትችላለች፡፡

በዚህ ፀሃፊ እምነት የፕሮፌሰሩ ዋነኛ ሃሳብ ያለው – የእርቀ ሰላም መንገድ ቢመርጡ ለራሳቸው ሳይቀር በጉልበት ያላገኙትን ክብር ያገኛሉ፤ ኢትዮጵያም በፖለቲካም ሆነ በመንፈሳዊ ታሪኳ የነበራትን ስፍራ ትቀዳጃለች ብለዋል፡፡ ይህ ለሁላችንም የተሰጠ የቤት ስራ አድርገን ልንወስደው ይገባል፤ በስልጣን ላይ ላሉት ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ ይህ እውን ይሆን ዘንድ እያንዳንዳችን ምን ማድረግ እንችላለን ብለን ራሳችንን መጠየቅ፤ እርስ በርሳችንም መመካከር ይጠበቅብናል፡፡ የአገራችንና የጋራችን ችግር ሆኖአልና፡፡

ይህንን በዚህ ልቋጨው፡፡ ነገሮችን ለማርገብ ይቻል ዘንድ ከቃላት ያለፈ ሊያረጋጋ የሚችል የፖለቲካ ተግባር መጀመር አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔአቸውን እንደአዲስ እንዳዋቀሩ ይፋ ሆኗል፤ በፕረዚዳንቱ ንግግር የተገባው ቃልና በሕዝቡ እየተጠበቀ ያለው ከዚህ የተለየም የገዘፈም ነው፡፡ ያለን ጊዜ አጭር ነው፤ ምናልባትም ችገሮቻችንን ፈተን ከአደጋ ለማምለጥ ይህ ወቅት የመጨረሻው ዕድላችን ሊሆን ይችላል፡፡ መንግስት በተገኘው ዕድል መቆመር የለበትም፡፡

የግጭትና የጉልበት መንገድ ማንኛውንም ወገን አሸናፊ አያደርግም

ዜጎች ፍርሃታቸውን ያሸነፉበት ደረጃ ላይ የደረስን ይመስላል፤ ሁኔታቸውን በራሳቸው መንገድ ለመለወጥ በወሰዱት ቀጥታዊ እርምጃ ቤተሰብ ድረስ የዘለቀው የቀበሌና የወረዳ የአፈና መዋቅር በበርካታ አካባቢዎች መፍረሱ ተመልክቷል፡፡ ይህን እርምጃ የክልል ፖሊስም ሆነ ፌዴራል ፖሊስ ሊያቆሙት ስላልተቻላቸው በብዙ አካባቢዎች መከላከያ ሰራዊት ወደ ማሰማራት ከተገባ ሰነባብቷል፡፡

ዜጎች ፍርሃትን ያሸነፉበት ምዕራፍ ላይ መድረሳቸው ጥልቅ ግንዛቤ ሊያገኝ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ወድያ መንግስትም ሆነ መንግስትን የሚገዳደሩት ወገኖች የሚኖሯቸው አማራጮች ምን ሊሆኑ ይገባል የሚለውን በጥሞና ለመመርመር ይገደዳሉ፡፡ ተገዳዳሪዎች አማራጭ የሚሉትን ሞዴል ከነመዳረሻው ማቅረብና ሕዝብ እንዲቀበለው ስለማድረግ ማሰብ ይኖርባቸዋል፤ መንግስትም ራሱንና አገርን ከቀውስ ለማውጣት አለኝ የሚለውን መፍትሔ ማቅረብና በተግባር ማሳየት ይኖርበታል፡፡ የሃይል እርምጃው ከዚህ ወድያ እንግፋበት ከተባለ ለመንግስትም ሆነ ለተገዳዳሪ ወገኖች የሚያዋጣ መንገድ አይደለም፡፡ ይህንን ዘርዘር አድርገን እንመልከተው፡፡

ብዙ ኩታ ገጠም ቀበሌዎችንና ወረዳዎችን ያዳረሰ፤ የአገሪቱን ሰፊ ጂኦገራፊያዊ አካባቢን ያጠቃለለ እና ብዙ ሚልዮን ዜጎች የተሳተፉበት የሕዝብ ተቃውሞ ነው፡፡ ወደ ሃይል እርምጃ ተሸጋግሮ የሰው ህይወትና የሃገር ቁሳዊ እሴቶች ቢወድሙም ችግሩ ፖለቲካዊ ሲቪላዊ ተቃውሞ መሆኑን አይቀይረውም፡፡ የዚህ ዓይነት ሲቪላዊ እምቢታ መከላከያ ሰራዊትን በማሰማራት እንደማይፈታ መንግስት ሊገነዘብ ይገባል፡፡ ሰራዊት በገባባቸው አካባቢዎች ለአጭር ጊዜም ቢሆን ነገሮች ፀጥ ረጭ ሊሉ ይችላሉ፤ ይህን አይቶ ነገሮች ወደ ነበሩበት ሁኔታ ተመልሰዋል፤ መረጋጋት ተፈጥሯል ማለት ግን ራስን ማታለል ነው፡፡ ከምድር በታች ያሉት ቀውሱን የፈጠሩት መስረታዊ ምክንያቶች ተገቢውን ምላሽ እስካላገኙ ድረስ ከመሬት በላይ የሚታየውን ዝምታ በመመልከት ስለመረጋጋት ማውራት እንደገና በድንገት መያዝን ያስከትላል፡፡ ከላይ ላዩ የሚታየው ዝምታ ውስጥ ለውስጥ የሚካሄደውን መብላላትን ይሸፍን እንደሆነ እንጂ መብላላትና መንተክተኩን አያስቀረውም፡፡

ሰራዊት የአገር ዳር ድንበርንና ሉኣላዊነትን ለማስጠበቅ ሲባል ጦርን በጦር ገጥሞ ለማሸነፍ የተቋቋመ እንጂ፤ እንደዚህ ያለን ሲቪላዊ እምቢታ ለስማቆም የተቋቋመ አይደለም፡፡ ብዙ ሰው መግደል ይቻላል፤ እየገደሉ የሚደረገው ግስጋሴ ግን ወደ ድል አይወስድም፡፡ በፍጹም፡፡

ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄያቸው ፖለቲካዊ ነው፡፡ ፖለቲከኞችም የሚመረጡበትና የስልጣን እርካብ ላይ የሚወጡበት ዋነኛ ምክንያት ይህንን አገልግሎት ለመስጠት ነው፡፡ ኃላፊነታቸውን መወጣት ስለተሳናቸው ወይም ለመወጣት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ለተፈጠረው ችግር ሰራዊትን በማርገብያነት መጠቀማቸውም ሆነ ወታደራዊ አዛዦች ይህንን መቀበላቸው ትልቅ ስህተት ነው፡፡ በዚህም ሰራዊቱ የአገርና የሕዝብ መሆኑ ቀርቶ የፖለቲከኞች መሳርያ ይሆናል፡፡

በኢትዮጵያ የታየው ሲቪላዊ እምቢታ ኢትዮጵያውያን የአገራችውን ፖለቲካዊ ገፀ-ምድር ለመቀየር ምን ያህል እንደቆረጡ የሚያመለክት ታላቅ አክብሮትና ሚዛን የሚሰጠው የፖለቲካ እድገት ነው፡፡ ብዙ ዓመታት ሊወስድ ይችል የነበረው ፍርሃትን የማሸነፍ ጉዞ እንዲህ በአጭር ጊዜ መሳካቱ በአገራችን ኢትዮጵያ በጎ ለውጥ ሊመጣ ለሚመኙ ዜጎች በሙሉ ትልቅ ድል ነው፡፡ የሚቀጥለውና ከባዱ ተግዳሮታቸው ይህንን ወደ ተሳካ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሽግግር እንዲያድግ ማድረግ ነው፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ሲቪላዊ እምቢታ በራሱ መሰረታዊ ድክመቶች እንዳሉት መገንዘብ ይገባል፡፡ የመከላከያ ሃይል ድጋፍ ወይም ገለልተኝነት ካልታከለበት ሲቪላዊ እምቢታና ዓመፅ ብቻውን መንግስትን ለመለወጥ የሚያስችል ጉልበት ላይኖረው ይችላል፡፡ በካይሮው ታሕሪር አደባባይና ሌሎች ታላላቅ የግብፅ ከተሞች የተከሰተው የሕዝብ እምቢታ ሊሳካ የቻለው የመከላከያ ሃይሉ ገለልተኛ አቋም ስለያዘ ነው፡፡ በቱኒዝያ የተቀሰቀሰው የሕዝብ እምቢታና ዓመፅ ሊሳካ የቻለውም የመከላከያ አዛዦች ሰራዊት አናዘምተም ብለው ስለወሰኑ ነው፡፡ በአገራችን የተከሰተው የሕዝብ እምቢታ ግዙፍ ቢሆንም ርእሰ ከተማዋንና በርካታ የአገሪቱ አካባቢዎችንና ከተሞችን አላደረሰም፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ገለልተኝነት ሊያረጋግጥ አልቻለም፡፡ ሁኔታዎች በዚህ ደረጃ ባሉበት ሲቪላዊ አመፅን ተማምኖ ሰራዊትን በሃይል መከጅል ሊታሰብ አይገባም፤ ውጤቱ እልቂት ነውና፡፡ በዚህ ላይ “ወያኔን” ከመጥላትና ከማስወገድ ባሻገር እሱን የሚተካው ምን እንደሚሆን ስምምነት የተደረሰበት አማራጭ የለም፡፡ እንዴት ነው እዚያ የሚደረሰው የሚለውን የሚመልስ የጋራ ስትራተጂ የለም፤ ይህን የሚመራና የሚያስተባብር አመራርና መዋቅርም የለም፡፡ እነዚህ በሌሉበት ሁኔታ በሶሻል ሚድያ ወይም በሪሞት ኮንትሮል ኢትዮጵያ ላይ ያለውን አገዛዝ እናስወግዳለን ማለት አላዋቂ ፖለቲከኝነት ነው፡፡

ለአፈና እምቢ ማለትና መወየን ተፈጥሮአዊ መብት ነው፡፡ የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ በዚህ እምቢታ ያለፈ እንደመሆኑ ለወጣቶቹ እምቢተኝነትና አይበገሬነት ታላቅ አክብሮት አለው፤ ትግላቹህን አቁሙ የሚል ምክር እየሰጠ አይደለም፡፡ የስትራተጂዎችና ስልቶች ጉልበትና ውሱንነት አስመልክቶ ካለው ግንዛቤ በመነሳት ይህ አይበገሬነትና አምቢተኝነት ባልሆነ አቅጣጫ እንዲነጉድ መደረግ የለበትም፡፡ ይህን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለው እልቂት ትግሉን ሊያንሰራራ አስቸጋሪ ወደ ሆነ ቅርቃር ሊያስገባው ይችላል ነው እያለ ያለው፡፡ የመንገዱ መታጠፍያ ላይ ተደርሰዋልና አስተውሎ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ መጠምዘዝ የሚያስፈልግበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ነው እየተባለ ያለው፡፡

ይህ መንገድ አዋጪ የማይሆነው ግን ከሲቪላዊ አመፁ በስተጀርባ ላሉት ወገኖች ብቻ አይደለም፤ ለመንግስትም ጭምር መሆኑ ሊጤን ይገባል፡፡ አስቸኳይ አዋጁ ከታወጀ በኋላ የሚታየው መረጋጋት በሲቪል ባለስልጣናትና በከፍተኛ የመከላከያና የደህንነት ባለስልጣናት ዙርያ ሊፈጠር የሚችለው መዝናናትና ነገሮችን አቅልሎ የማየት ሁኔታ ሊከስት እንደሚችል ታሳቢ ሲደረግ፤ መንግስት ሊያደርግ የሚችለው ስህተት ይበልጡኑ የሚያሳስብ ነው፡፡

በርካታ ዜጎች በተገደሉና በታሰሩ ቁጥር ምሬቱና ጥላቻው ይካረራል፤ በዚህ ሂደት ዜጎች ከራሳቸው ልምድ በመነሳት ሲቪላዊ አመፁ ሊሄድ የሚችለው ርቀት የተወሰነ መሆኑን እየተገነዘቡ ይሄዳሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት ወደ ሽምቅ ውግያ ይሽጋገራሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ከተከሰተ ደግሞ በመንግስትና በዜጎች መካከል የአይጥና የድመት ግንኙነት ይፈጠርና ለከተማና ለተቋም ጥበቃ፣ ለመንገድ ውጠራና ፍተሻ እየተባለ ሰራዊቱ በየቦታው ይበተንና ጎርፍ እያሳሳቀ ይወስዳል እንዲሉ ቀስ በቀስ አገሪቷ ወደ ጦር ሰፈር ትቀየራለች፡፡ ከዚህ በኋላ ልማትና እድገት የሚባል ነገር አይኖርም፡፡

ግድያና ጭካኔ ተበዳዮቹን ብቻ አይደለም የሚጎዳው፤ የአድራጊዎችን ሞራልና ስብእናም ነው ገደል የሚያስገባው፡፡ ወገኖቹን በመግደልና በማንገላታት ላይ የተሰማራ ሰራዊት የራሱንም ሞራል ያንኮታኩታል፤ ወታደራዊ ዲሲፕሊኑ የላላ በቀላሉ የሚፈታ ሰራዊት ያደርገዋል፡፡ በተለይ ወደ እኛ አገር ሲመጣ፤ እምቢ ባለ ህዝብ ላይ ሰራዊትን ማዝመት መዘዙ ግዙፍ ነው፡፡

በሽምቅ ውግያ መደበኛ ሰራዊትን አሸንፎ የመንግስት ለውጥ ማምጣት ይቻላል ወይ ለሚለው፤ የዚህ ፀሃፊ እምነት በሽምቅ ውግያ መንግስትን ማዳከም ይቻላል መንግስትን ለመጣል ግን አያስችልም የሚል ነው፡፡ ሰዎች ሽምቅ ውግያን በቁንጫና በቁንጫ በተወረረ ውሻ መካከል በሚኖረው ትግል ይመስሉታል፡፡ ቁንጫ የውሻውን ደም ይመጣል፤ ውሻውን እረፍትና እንቅልፍ ያሳጣዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ውሻው ይዳከማል፡፡ በዚህ ሰበብ ብቻ ውሻው ይሞታል ለማለት ግን አይቻልም፡፡ በሽምቅ ውግያ አልፎ መደበኛ ሰራዊትን ለማሸነፍ እሚቻልበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የሽምቅ ውግያው ወደ መደበኛ ፍልምያ ለመሸጋገር መቻል አለበት፡፡ ይህ ጉዞ እጅግ አስቸጋሪ ከመሆኑ ባሻገር እዚያ ላይ መድረስ የሚቻለው ከተራዘመ ጦርነት በኋላ ነውና በጣም ለሚቻኮሉት ወገኖች አይደርስላቸውም፡፡ ይህንን አሳክቶ የመንግስት ለውጥ ቢመጣ እንኳን በለውጡ የሚመጣው መንግስት ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሊሆን እንደማይችል የህወሐትና ኢህአዴግ መጨረሻ በራሱ ትልቅ ምሳሌ ነው፡፡

ይህም ሆኖ ሽምቅ ውግያ ጉዳት አያደርስም ማለት አይደለም፡፡ የኢኮኖሚ መዳከምን ያፋጥናል፤ አገሪቱን ወደ ጦር ሰፈር የመቀየር ሂደቱን እና የሰራዊት ሞራል መላሽቅን ያቀላጥፋል፡፡ ይህ ክስተት ከአካባብያዊ ብሄራዊ ስጋቶቻችን ጋር እንዲጠላለፍ፤ እድሉ ከተሰጠው ደግሞ ጉዳቱ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ ይህንን ወረድ ብየ እመለስበታለሁ፤ ከዛ በፊት አንድ ነገር ልበል፡፡

በአገሪቱ የሰፈነው አለመረጋጋት መታየት ከጀመረ ወዲህ ያለውን ንግግርና ድርጊት ለተከታተለ ሰው እውነትም መንግስት ነገሮችን ቀድሞ ማየትና መገመት ላይ እጅጉን የተቸገረ መሆኑን ያመለክታል፡፡ አስቀድሞ መገመት ካለ አስቀድሞ መዘጋጀት፤ ነገር ሳይበላሽና ከቁጥጥር ውጪ ሳይሆን በፊት ማርገብ ይመጣል፡፡ ይህ በሌለበት ሁኔታ በድንገት መያዝና ግብታዊ የሆኑ ያልታሰበባቸው እርምጃዎችን መውሰድ ይመጣል፡፡ እነዚህ የሚያስከፍሉት ዋጋ ደግሞ ትልቅ ይሆናል፡፡ የእስካሁኑ መንግስት ነገሮችን የያዘበት አካሄድ ይህንን በድንገት የመያዝና ግብታዊ የሆኑ መልሶችን የመስጠት ሁኔታን በእጅጉ ያንፀባርቃል፡፡

አስቸኳይ አዋጅ ከመታወጁ ጋር መንግስት የገባው ቃል አለ፡፡ አሁንም ግን የአመኔታ ችግር አለና መንግስት ሰራዊት አሰማርቶ ሁኔታውን ፀጥ ከአደረገ በኋላ ወደ ተለመደ ስራው ይመለሳል የሚል ስጋት አለ፤ ወይም ይስተካከላል የተባለው የፖለቲካ ስልጣን ጥያቄ ጥልቀት የሌለው የመቀባባት ስራ ከመሆን ያለፈ አይሆንም የሚሉ አሉ፡፡ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ከተሳሳተ መዘዙ ትልቅ እንደሚሆን ጀነራል ፃድቃን በሁለተኛው ይሆናሉ በሚገባ ገልፆታል፡፡ ጀነራል ፃድቃን ያለው እንደ መንደርደርያ ይሁንልኝና እሱን አስቀመጬ ወደ ሚቀጥለው ልለፍ፡፡

“ሁለተኛ ቢሆን ረዘም ላለ ግዜ አሁን ባለው ቀውስ ውስጥ መቆየት ነው። ይህ ከሁሉም አማራጮች የመሆን እድሉ የላቀ ነው። አሁን በስልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ … መጠነኛ ለውጦችን በውስጡ በማድረግ፣ በግልፅ ያመነበትን የመልካም አስተዳደር እጦትና ሙስና ቴክኒካዊና አስተዳደራዊ ትርጉም በመስጠት፣ በዚህ ዓይነት ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን ለመፍታት በመሞከር የተወሰነ ግዜ የጣላቸው የስራ ሃላፊዎችን በማስወገድ ከቀውሱ ለመውጣት ግዜ ለመግዛት በመፈለግ የሚፈጠር ሁኔታ ሊመጣ ይችላል። አሁን በስልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ በተፈጥሮ ሊያደላበት የሚችል የመጀመርያ ምርጫው የሚሆን በመሆኑ የመከሰት ዕድሉ የሰፋ አማራጭ ነው። ይህም አማራጭ ችግሩን ለተወሰነ ግዜ ሊያዘገየው እንደሆነ እንጂ አይፈታውም። ለተወሰነ ግዜ በማዘግየት ችግሩ ይበልጥ ስር እየሰደደ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውም እድል እየጠበበ እንዲሄድ ያደርጋል። … በመጨረሻም በጣም አውዳሚ በሆነ መንገድ ችግሩን ለመፍታት ለሚፈልጉ ሃይሎች የተመቻቸ ሁኔታ ይፍጥርላቸዋል። … እስከ አሁን ድረስ የተመዘገቡትን ድሎች ጠራርጎ ያጠፋል፡፡ አገሪቱን ወደኋላ ይመልሳል ብቻ ሳይሆን ቀጥሎ የሚመጣውም ምን ዓይነት ስርዓት እንደሆነ መተንበይና መገመት አይቻልም፡፡”

የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ጉዳይ

አገራችን አስቸጋሪ በሆነ አካባቢ እንደመገኘቷ ሁሉ አያያዙን ካበላሸነው የውስጥ ችግራችን ይበልጡኑ ሊወሳሰብ እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ስንራብና ስንታረዝ ዞር ብለው ለማየት እንኳን የሚጠየፉን የአካባቢያችን ሃይሎች እርስ በርሳችን እንገዳደልና የገዛ እሴቶቻችንን እናቃጥል ዘንድ ክርቢትና ላምባ፣ ጠመንጃና ጥይት ቤታችን ድረስ ሊያቀርቡልን እንደሚሽቀዳደሙ የአካባቢያችን ታሪክ አስተምሮናል፡፡

ችግራችንን ሊያወሳስቡ ከሚችሉት አያያዞች አንዱ አግባብነት ያላቸውን የፖለቲካ ስልጣንና የእድገት ተቋዳሽነት ጥያቄዎችን ከእኛ ጋር የጥቅም ግጭት ካላቸው አገሮችና ጥቂት ግብረ አበሮቻቸው ጋር አንድ ላይ ገምዶ መመልከቱ ነው፡፡

የኤርትራ መንግስት ብሄራዊ ስጋታችን እንደሆነ ይታወቃል፤ ከግብፅ ጋርም ከውሃ ጋር በተያያዘ ለዘመናት የጥቅም ግጭት እንዳለን ይታወቃል፡፡ ይህ የቆየ እውነታ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በመካከለኛው ምስራቅ ከምናየው እጅግ አስቸጋሪና ደም አፋሳሽ ግጭት ጋራ ተጠላልፎአል፡፡ የቀይ ባህር ውሃ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ከነበረው ባላነሰ ሁኔታ የጂኦፖለቲካ ውጥረት አካባቢ ሆኖአል፡፡ የኤርትራ መንግስት ከዚህ ሁኔታ ሊገኝ የሚችልን ዶላር ማግኘት ይችል ዘንድ የገዛ አገሩን የወደፊት ዕጣ ፈንታ አደጋ ላይ ሊጥል በሚችል የቁማር ጨዋታ ውስጥ ገብቷል፡፡

ኢትዮጵያውያን/ት ወጣቶች ያነሱትን የነፃነትና የእድገት ተቋዳሽነት ጥያቄ ከኦነግ፤ ከግንቦት 7፤ ከኤርትራ መንግስት ወይም ከግብፅ ጋር ማስተሳሰር አቅጣጫ የማስቀየር ጉጉት እንዳለ ያመለክት እንደሆነ እንጂ ችግሩን መገንዘብን አያመለክትም፡፡ ኦነግ ወጥ አቋምና አደረጃጀት ያለው ድርጅት እንዳልሆነ፤ በአንድ ወቅት የኦነግ አባላት የነበሩ እና ድርጅቱን ሲመሩ የነበሩ ሰዎች አስመራ ካለው ኦነግ የተለየ አቋምና አደረጃጀት ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ኦሮሞነታቸው ካልሆነ በስተቀር ከኦነግ ጋር ምንም ዳራ የሌላቸው አገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች እንዳሉም ይታወቃል፡፡ የአሁኑ የወጣቶቹ እንቅስቃሴ በዋናነት በራሱ ፈንቅሎ የወጣ እምቢታ ነው፡፡ የተለያዩ የኦሮሞ ድርጅቶች እንቅስቃሴውን ደግፈው ሊሆን ይችላል፡፡ “እኛ ነን የመራነው” እያሉ ከወጣቶቹ መስዋእትነት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሞክረውም ይሆናል፡፡ ይህንን ግዙፍ እንቅስቃሴ የፈጠረው ኦነግ ነው ማለት ግን እውነቱን ከማዛባቱ ባሻገር አስመራ ላይ ላለው ኦነግ የማይገባውን ስምና ጉልበት እንደመስጠት ይቆጠራል፡፡

ኤርትራም ሆነ ግብፅ በእኛው ውስጥ በዋናነት ደግሞ በመንግስት ድክመት ምክንያት የተፈጠሩትን ተቃውሞዎች ለራሳቸው አጀንዳ ማራመጃ ሊጠቀሙባቸው ሊሞክሩ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ አስመራና ካይሮ የአንዳንዶቹ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች መጠለያ እንደሆኑ ይታወቃል፤ አንዳንዶቹ ከውጭ የሚሰራጩት የሬድዮና የተሌቪዥን ስርጭቶች የአስመራና የካይሮ ድጋፍ እንደሚያገኙም ይገመታል፡፡ ይህም ሆኖ የችግሩ ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው መንግስት ጉድለት ነው፡፡ ግብፅና ኤርትራ ላይ ያሉት መንግስታት ብሄራዊ ጥቅማችንን ያራምድልናል ያሉትን ተግባር ነው እያከናወኑ ያሉት፡፡ የኢትዮጵያው መንግስት ይህንን እድል በመንሳትና በማጥበብ ፈንታ ሁኔታውን ነው እያመቻቸላቸው ያለው፡፡ እውነታው ይህ መሆኑ እየታወቀ ነገሩን ወደ ግብፅና ሻዕብያ ማዞር ከተግዳሮቱ ለማምለጥ የሚደረግ ሙከራ ያስመስለዋል፡፡ ይልቅ ነገሩ ሌላ ጥያቄ ያስነሳል፤ እውነት መተሳሰሩ መንግስት የሚገለፀው ደረጃ ላይ ከደረሰ፤ የደህንነት ተቋማችን ምን ሲሰራ ነው ይህ ነገር እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው የሚል ጥያቄ፡፡

ኢትዮጵያውያን ለነፃነታቸውና ሉአላዊነታቸው ቀናኢ መሆናቸው ታሪክ የመሰከረው ሃቅ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የኛ የሚሉትና የሚያምኑት መንግስት እንዲኖራቸው እየጠየቁ ነው፡፡ መጀመርያ ይህ ጥያቄአቸው ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት የመፍትሄ ፍኖተ ካርታው ይቅረብላቸው፡፡ ለአገር ነፃነትና ሉአላዊነት መቆምን በሚመለከት ምን እንደሚያደርጉ ሌላው ቀርቶ ሻዕብያና ግብፅም አሳምረው ያውቁታል፡፡

አገራችን ውስጥ ለተነሳው ጥያቄ ቅድምያ ሰጥቶ ያለማመንታትና በማያዳግም መልኩ መፍትሔ መስጠት በሁለቱም መካከል የመተሳሰር አደጋውን ያስቀራል፤ ችግራችንን ያለ ብዙ ጉዳት ለመፍታትና ወደ ፊት ለመገስገስ ያስችለናል፡፡ ጊዜ ተሰጥቷቸው ሁለቱም ቢጠላለፉ ግን የመንግስትን ስንፍና ያመለክት እንደሆነ እንጂ ለብሄራዊ ደህንነታችንና ጥቅሞቻችን ያለውን ትጋት ፈፅሞ አያመለክትም፡፡ የውስጥ ችግሮቻችንን መፍታትን ቅድምያ በመስጠት ፈንታ መንግስት በሃይል መፍታት ላይ ካተኮረ፤ ሃይል ወደ መጠቀም ዳር ዳር እያለ ያለውን የወጣቶች ቁጣ ወደ ሽምቅ ውግያ ሊሸጋገረው ይችላል፤ ወታደራዊ ስልጠና የሚሰጥም ሆነ ካላሽንኮቭ የሚያቀርብላቸው አያጡምና፡፡ ይህ ቀስ በቀስ አገሪቱን ወደ ጦር ሰፈርነት ሊቀይራት ይችላል፡፡ ይህ ከተከሰተ በኋላ እድገት የሚባል ነገር አይኖርም፤ ያለውን ማውደም እንጂ፡፡ ኢትዮጵያውያን ስለዚህ ጉዳይ አሳምረን እናወቃለን፡፡

ለሕዝብ ጥያቄዎች ተገቢና አጥጋቢ መልስ መስጠት ላይ በመለገሙ ምክንያት ነገሮች ከተበላሹ ግን፤ የኢትዮጵያ መንግስት በራሱ ፈቃድ ነገሮችን ለሻዕብያና አሳዳሪዎቹ እንዳመቻቸላቸው ይቆጠራል፡፡ ሰራዊታችን በአገር ውስጥ በበርካታ አካባቢዎች መሰማራቱንና መጠመዱን ሻዕብያ ካስተዋለ፤ አመቺ ሁኔታ አገኘሁ ብሎ ሊቆምር እንደሚችል መገመት አለብን፡፡ ይህንን ያደርግ ዘንድ አሳዳሪዎቹ የሚፈልገውን ገንዘብና መሳርያ ሊያቀርቡለት እንደሚችሉ፤ ከዚያም ባሻገር ቀጥታዊ ወታደራዊ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚችሉ መገመት ይገባል፡፡ ታድያ ሻዕብያ ይህን የሚያደርገው ባድመን ለማስመለስ ብሎ አይሆንም፤ አሳዳሪዎቹ ከባድመ የገዘፈ አጀንዳ በኢትዮጵያ ላይ አላቸውና፡፡

ስለ የውስጥ ጣልቃ ገብነት ስናስብ በግብፅና በኤርትራ ላይ ልዩ ትኩረት ማድረጋችን ተገቢ ቢሆንም የጣልቃ ገብነት አደጋውም ሆነ አድማሱ ከዚህ የሰፋ ነው፡፡

የአንድ መቶ ሚልዮን ሕዝብ አገር ነን፡፡ ድሃ አገር ብንሆንም ለራስ ሉኣላዊነትና ነፃነት ቀናኢና እምቢ ማለትን የምናውቅ አገር ነን፡፡ በጋራ ፈተናዎችን ማለፍና መዝለቅ የለመድንና አሁንም ድህነትን ሰብረን ለመውጣት በመፍጨርጨር ላይ ያለን አገር መሆናችንን ዓለም ያውቀዋል፡፡ አሁን በምንገኝበት ሁኔታ ውስጥ ሆነንም በአፍሪካ ቀንድ ፀጥታና መረጋጋት ላይ እየፈጠርን ያለነው ተፅእኖ ከፍተኛ መሆኑን እያየን ነው፡፡ ኢኮኖሚያችንና አንድነታችን እያደገ በሄደ ቁጥር ደግሞ እንደ ሃገር ተፅእኖ የመፍጠር አቅማችን ይበልጥ እየጨመረ ይሄዳል፡፡

የባሕር በር ባይኖረንም በቀይ ባሕር አካባቢ የምንገኝ የአካባቢው ትልቅ አገር እንደመሆናችን በቀይ ባሕር ጂኦፖለቲካ ላይ ተፅእኖ ፈጣሪ መሆናችንን አያስቀርም፡፡ በዚህ ላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማእከል እንደመሆንዋ ለየት ባለ መልኩ እንደገና እያንሰራራ ያለው ቀዝቃዛ ጦርነትና ይህን ተከትሎ በቀይ ባሕር አካባቢ እየታየ ያለው የውጭ ሃይሎች የጦር ሰፈሮች ክምችትን መመልከቱና ማጤኑ ተገቢ ይሆናል፡፡

እነዚህ እውነታዎች መልካም አጋጣሚዎችም ተግዳሮቶችም ናቸው፡፡ እንደአያያዛችን ወይ ሰብረን እንወጣና ጠንካራና ለሁላችንም እኩል ዕድሎች የፈጠረች አገር ትኖረናለች፡፡ የልጆቻችንን ተስፋም እናለመልመዋለን፡፡ ወይም የዜሮ ድምር የእልህ ፖለቲካ ውስጥ እየዳከርን ጊዜው ይመሽና ሁሉንም እናጣለን፡፡

“ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅና ጠላት የለም” አለ ይባላል የእንግሊዙ የአስራዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር ፓልመርስተን፡፡ መንግስታትም ሆኑ በእነሱ የሚደገፉት መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ወደ እኛ የሚጠጉት ብሄራዊ ጥቅማቸውንና ጂኦፖለቲካዊ ስሌቶቻቸውን መሰረት በማድረግ ነው፡፡

እኛው እንገዳደል ካልን ሌላው አለም ደርሶ ከችግር ያወጣናል ብለን ተስፋ አናደርግም፡፡ ወይ ዳር ሆኖ ይመለከታል ወይ ሶርያና የመን ላይ እንደሚታየው ማቀጣጠያ ይጨምራል፡፡ ለእኛው ችግር ፈውሱ እኛው ራሳችን ነን፡፡ በራሳችን እሴቶች ተማምነን ችግራችንን በምክክርና ሃሳቦችን በማመቻመች ከመፍታት ውጪ ሌላ መውጫ መንገድ የለንም፡፡ አገራችን ስትወረር ቀደምትም ሆኑ የዘመኑ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በጋራ ቆመው ፈተናውን ተወጥተውታል፤ አሁን የገጠመን ተግዳሮት ከዚህ ይብስ እንደሆነ እንጂ አያንስም፡፡ እንደበፊቱ አሁንም በጋራ ቆመን መፍትሔ እንፈልግ፡፡ በአገራችን ተስፋ መቁረጥ አይገባንም፡፡ ይልቁንስ ‘ብቸኛው መንገድ የእኔ መንገድ ነው’ ‘ብቸኛው መፍትሔ የኔ መፍትሔ ነው’ ማለቱን ትተን፤ ከአንተስ ዘንድ ካንቺስ ዘንድ ምን አለ ብለን እንደማመጥና አማካይ ስፍራ እንፈልግ፡፡ በዚህ አስቸጋሪ አካባቢና ወቅት ላይ መገኘታችንን ተገንዝበን የሌሎች የጂኦ-ፖለቲካል ገበጣ መጨወቻ ጠጠር እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን፡፡

*********

2 Comments
  1. Caalaa

    This is an interesting and useful observation. The greatest danger now is loss of common concern and factionalism across the politically vocal groups. I don’t there is “we” anymore in our conversation, and this is going to be even worse if the pattern we have observed so far continues. That class cleavage will shadow ethnic cleavage is a mirage. The leaders are stuck with old structuralism (naively for that matter) even if ethnicity is reigning in the western class-segmented society. Democracy is tough in multicultural society, let alone playing with authoritarianism. Leaders should take the long view of this situation. Or else, as you mentioned, the alternative is bad for everyone.

    Reply
  2. Ezana Minas

    Thank you for your constructive article. A breath of fresh air in the face of many demagogues and quite different from the finger pointing, Hate mongering, over critically negative or government apologetic articles. We are in a cross road. We either learn lessons and stop going the slippery slope or start the New Zemene Mesafint era in the 21st centaury. The old guards see the day light before it is too late for you and your children. Stop self preserving apologetic shortsightedness and accept reality. You will not win through military might except delaying it and making it very destructive. Do not try to hold the countries stability a hostage by threatening fragmentation. You have been given wise advise by many like this writer.

    Reply

ስለጽሑፉ ምን ይላሉ? አስተያየቶን ያካፍሉን፡፡