የኮንሶ ህዝብ ጥያቄ ተገቢዉን ምላሽ ይሻል !

(ኮሎኔል አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሺፈራዉ)

በቅድሚያ በኮንሶ ህዝብ ላይ እየደረሰ ሲላለዉ በደል አንዳችም ትርፍ  ነገር ሳይጨምር ሳይቀንስና ሳይደባብቅ ሃቁን ለህዝብና ለሚመለከታቸዉ የመንግስት ባለስልጣና አካላት ሁሉ እንዲደርስ ባደረገዉ በአቶ ናሁሰናይ በላይ የተሰማኝን ኩራትና አድናቆት ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ናሁሰናይ አስታዋሽ ያጣዉና ትኩረት የተነፈገዉ  የኮንሶ ህዝብ  ብቻ  ሳይሆን  ጭቆናንና በደልን የሚጸየፉ የመላዉ የሀገራችን ህዝቦች ሁሉ እንደሚያሰግኑህ ቅንጣት ጥርጥር የለኝም፡፡ ሆርን አፌየርስም ለህዝብ እንዲደደርስ በማድረጉ ሊመሰገን ይገባል፡፡

በደቡብ ክልል ዉስጥ ሃላፊነት በማይሰማቸዉ አንዳንድ አመራሮች አማካኝነት በተለያዩ ጊዜያት በህዝብ ላይ እየደረሰ ያለዉ  የመብት ጥሰትና እንግልት ከፍተኛ ቢሆንም በየሚመለከታቸዉ ኃላፊዎች ሆኑ የሚዲያ ሰዎች  የመብት ጥሰቱን ለማዉገዝ፤ ለማስቆም ቢሎም  አጥፊዎችን ለመገሰጽ የተደረገ አንዳችም ጥረት ባለመደረጉ አጥፊዎች ይበልጥ በመበረታታት በድርጊታቸዉ እንዲገፉበት እድል አግኝተዋል፡፡

ከፍተኛ በደል እየተፈጸመበት ያለዉ የኮንሶ ህዘብ ምን ያህል ግፍ እንደተፈጸመበት ማሳያ የሚሆነዉ የመብት ጥያቄ በማንሳቱ ብቻ እየተፈጸመበት ካለዉ እስርና መኖሪያ ጎጆዉን ማቃጥልም በላይ ይህን ምስኪን ህዝብ በማያዉቀዉ ጉዳይ ከግንቦት ሰባትና ኦነግ ከመሳሰሉ ከለየላቸዉ የሽብር ሃይሎች ጋር ለማቆራኘት መሞከሩ ነዉ፡፡ ህዝቡን ለማሸማቀቅና በፍርሃት አንገቱን ሰብሮ ዝም እንዲል ለማድረግ ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለኮንሶ ህዝብ ባላቸዉ ንቀት የተነሳ በህጋዊ መንገድ የመብት ጥያቄ በማንሳቱ ብቻ  የብሄሩን አባላትና የብሄሩን ሽማግሌዎችና ባህላዊ መሪዉን በማሰርና ሌሎች አካላዊ ጉዳት በማድረስና መኖሪያ ጎጆአቸዉን  በማቃጠልም ጭምር ግፈኛ ደርጊት ሲፈጽሙ  አየታወቀ የሚመለከተዉ አካል ከማዉገዝ ይልቅ ዝምታን መምረጡ ነዉ፡፡

Map - Konso Cultural Landscape - Ethiopia
Map – Konso Cultural Landscape – Ethiopia

የኮንሶ ህዘብ እንደሌላዉ ህዝብ ለማንነቱ ዋስትና የሆነዉ ህገመንግስትና ፌዴራል ስርአቱ  እዉን ሆኖ  ቀርቶ ድሮም  አፋኝ በነበሩ ስርአቶች ዉስጥም ቢሆን በብሄራዊ ማንነቱ የሚኮራ ህዝብ ነዉ፡፡ የኮንሶ ህዝብ ባለፉት አፋኝ ስርአቶች  ለልማትና ለዲሞክራሲ መብት መረጋገጥ  አይታደል  እንጂ ባህሉን ፤አናናሩን ፤ቋንቋዉን አንድም ጊዜ ተደፍሮበት አያዉቅም፡፡ የኮንሶ ህዝብ  በአሁኑ የፈዴራላዊ ስርአት በተጎናጸፈዉ መብት እጅግ የሚኮራና ከስርአቱ ተጠቃሚ መሆኑን አንድም ጊዜ ተጠራጥሮ የማያዉቅ ህዝብ ነዉ፡፡ የኮንሶ ህዝብ ልዩ በሆነዉ የአስተራረስ ዘይቤዉ መልክምድራዊ አቀማመጡና  ሌሎች ባህላዊ እሴቶቹ ምክንያት ከሃገራችንም አልፎ በመላዉ ዓለም እዉቅና ያገኘ፤ በማንነቱ እጅግ የሚኮራ ህዝብ ነዉ፡፡

በንጉሱም ሆነ በደርግ ዘመን ኮንሶ በወረዳ ደረጃ ሆኖ ጋርዱላ አዉራጃ ይባል በነበረዉ ስር በወረዳነት የቆየ ነዉ፡፡ ወደ ልዩ ወረዳነት ደረጃ እንዲያድግ የተደረገዉ በዚህ በአሁኑ ስርአት በመሆኑ ለዚህ እድል ላበቃዉ ህገመንግስታዊ ስርአትና ለህገመንግስቱ ታላቅ አክብሮት ያለዉ ህዝብ ነዉ፡፤ እንደሚታወቀዉ የኮንሶ ህዝብ የሰፈረበት አካባቢ መልክአምድሩ እጅግ አስቸጋሪ ለግብርናም ሆነ ለኢንዱስትረና ለከተማ ማስፋፋትም ጭምር አመቺነት የለለዉ እጅግ አስቸጋሪ ሆኖ ሆኖ እያለም  ህዝቡ ግን ሁሉን ችግር በትእግስት ተቋቁሞ ከተፈጥሮ ጋር እየተጋለ ለዘመናት የኖረበት አካባቢ በመሆኑ ለሰፈረበት  አካባቢ ልዩ ፍቅር አለዉ፡፡

በዚህ ስርአትም የልማቱ ተቋዳሽ መሆን በመቻሉና በድሮዉ ስርአቶች ከነበረዉ በበለጠ አሁን ህዝቡ ሰፊ እዉቅና ማግኘቱ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም እዉቅና ያገኘ የቱርስት መዳረሻ መሆኑ በህዝቡ ላይ የፈጠረለት መነቃቃት እጅግ ከፍተኛ ነዉ፡፡ ስለዚህ ይህ ህዝብ ይብዛም ይነስም ለዚህ እድል ላበቃዉ ስርአት  ከፍተኛ አክብሮት ያለዉ ህዝብ ነዉ፡፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በዚህ ስርአት  ወደ ልዩ ወረዳነት የማደግ ዕድል በማግኘቱ እጅግ ደስተኛ የሆነ  ህዝብ ነዉ፡፤ ህዝቡ በስርአቱ ዉስጥ በተገኘዉ መልካም ዕድል ተጠቅሞ የበለጠ ማደግ እችላለሁ በሚል እምነት  ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ ” የዞን ደረጃ ይሰጠኝ” ቢሎ በመጠየቁ ተገቢዉን መልስ ከመስጠት ይልቅ ጭራሽ የባህላዊ አባቶቹን ጭምር በማሰር በማሰቃየት ጥያቄዉን ለማፈን ከተደረገዉ በደል ሌላ ሆን ተብሎ ከህዝብ ጋር እልህ ዉስጥ በመገባቱ እንኳን ዞን መሆን ይቅርና ጭራሽ  የነበረዉን  የልዩ ወረዳነት ደረጃም ተነጥቆ  በመቀጣጫነት ወደ ወረዳነት ዝቅ እንዲልና ያለፍላጎቱ በሌላ ዞን ዉስጥ እንዲካተት መደረጉ እጅግ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ድርጊትና በህዝብ ላይ ሆን ተብሎ የተሰራ ግፍ ነዉ፡፡

ህዝቡ መብቱ ታፍኖ ግፍ እየተፈጸመበት መሆኑን እየታወቀ  የፈዴራልም  ሆነ በክልል ደረጃ ጉዳዩ  ትኩርት ተነፍጎት ቆይቷል፡፡ ሌላዉ ቀርቶ በሃገሪቱ የመንግስት የዜና አዉታሮች ጭምር ተገቢዉን ሽፋን ተነፍጎት ጥያቄዉም ጠያቂዎቹም  እንዲታፈኑ ተደርጓል፡፡ ኮንሶ ህዝብ አስቸጋሪ ከሆነዉ ድንጋያማና ታራራማ መሬቱ ጋር እየተጋለ ከመኖር ዉጭ አንድም የጸጥታ ችግር ፈጥሮ የማያዉቅ ሌላዉ ቀርቶ አንድም የጥይት ድምጽ ተሰምቶበት የማይታወቅ እጅግ ሰላማዊ የነበረ አካባቢ ነበር፡፡

የኮንሶ ህዝብ ፋብሪካ ይቋቋምልኝ ፤ዩንቨርስቲ ይከፈትልኝ ፤ሪፌራል ሆስፒታል ይገንባልኝ ብሎ መንግስትን አስጨንቆ የሚያዉቅ ህዝብ አይደለም፡፤ የልማት ጥያቄ መጠየቅ መብት እንዳለዉ ቢገነዘብም የሰጡትን አመስግኖ ከመቀበል ዉጭ የሌለ አስቸጋሪ የሆነ የልማት ጥያቄ አቅርቦ መንግስትን አስቸግሮ  አያዉቅም፡፡ መብቱን በህጋዊና ህገመንግስታዊ አግባብ ስለጠየቀ ብቻ እንደ ወንጀለኛ እየታደነ የሚታሰርበት፤የሚጉላላበት ምክንያትን ማን ነዉ ሊያስረዳን የሚችለዉ? በህዝብ ስም በክልል የተቀመጡ ባለስልጣናት ህዝቡን ሆን ብለዉ እየበደሉ እንደዓይን ብሌኑ ከሚሳሳለት  ስርአትና ህገመንግሰት ላይ እንዲያኮርፍ፤ እንዲያምጽ የሚያደርጉ መሰሪዎች መቼ ይሁን ለፍርድ ቀርበዉ መቀጣታቸዉን የምንሰማዉ?

በሃገራችን ህዝብን መበደል እጅግ እየተለመደና እንደተራ ነገር እየታዬ የመጣ ይመስላል፡፡ በተለይ “ለህዝብ ቆመናል በህዝብ ተሹመናል” በሚሉ የወረዳ፤ የዞንና የክልል ሃላፊዎች በየአካባቢዉ በህዝብ ላይ እያደረሱት ያለዉ በደል ሀገሪቱን መንግስት የለለበት አገር እያስመሰላት ነዉ፡፡

ሀገሪቱ በኢህአዴግ አመራር ሰጭነት በዉጭ አለም እያገኘች የመጣችዉን ከበሬታና መልካም ስም ተጻራሪ በሆነ መልኩ በየስርቻዉ በሚፈጸሙ እኩይ ድርጊቶች ሰበብ በስንት ጥረት ያገኘችዉን መልካም ገጽታ እየተበላሸባት እንደሆነ ለመገንዘብ አያዳግተንም፡፡ በተለይም በሰብአዊ መብት አያያዝ ረገድ በተደጋጋሚ መወቀሳችንና ያንን ተከትሎም ለማእቀብ እየተዳረግን መሆናችንን ሳስብ በጣም አዝናለሁ፡፤ ብዙ የተለፋበትና የተደከመበተ ነገር ሁሉ እየተበላሸ ነዉ፡፡

ህዝብን የሚበድሉ ጥቂት ሰዎችን ለህግ አቅርቦ መቅጣት እየተቻለ በዝምታ ስለሚታለፉ በዚህ እየተበረታቱ በድርጊታቸዉ እንዲቀጥሉ ስለሚደረጉ መንግስትን የሚያስተችና ከበረታ የሚያሳጠዉ ሁኔታ እየተፈጠረ ነዉ፡፡ መንግስት ወዳጅ ከማበራከት ይልቅ ጠላት ማፍራትን የመረጠ ይመስል ወንጀለኞች እያሉ ወንጀል የተፈጸመባቸዉንና መብታቸዉን የጠየቁ ዜጎች ላይ ታጣቂ በመላክ ማገትና የማስፈራራት ዴባ እየተፈጸመ እያየ ዝም ብሏል፡፡ በዚህ ምክንያትም ስርአቱ የመጣላቸዉ ወገኖችንም በስርአቱ ላይ እንዲያኮርፉ እየተደረጉ ነዉ፡፤

ሌባዉ እያለ ንብረት የተሰረቀበትንና ሌባዉን የጠቆመዉ ላይ ነዉ ኃይላችን የሚበረታዉ፡፡ ብዙ ሚሊዮኖችን ከሚሰርቀዉ ሙሰኛ ይልቅ መንገድ ዳር ቁጭ ብሎ በሚቸረችረዉ ደሃ ላይ እንጎብዛለን፡፡ መብቱን ከሚጠይቀዉ መቶ ሺህ ህዝብ ይልቅ በህዝብ ላይ አፈና ለሚያደርጉ በጣት ለሚቆጠሩ ወንጀለኞች ጥብቅና እንቆማለን፡፤

ትላንት የቅማንት ህዝብን መብት ሲያፍኑ የነበሩ በየደረጃዉ ያሉ ሃላፊዎች ሲቀጡ ባለመስማታችን ስንገረም ቆይተናል፡፡ እንደገናም የወልቃይትን ህዝብ ጥያቄም ሆን ብለዉ በማወሳሰብ ሀገሪቱን ለብጥብጥ  የዳረጉ ባለስልጣናትና ግለሰቦችም ተገቢዉን ቅጣት ስለማግኘታቸዉ አልሰማንም፡፤ በሰሜኑ የሀገራችን አካባቢ በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ  እጅግ ዘሬኛ ድርጊት የፈጸሙ ግለሰቦችና ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ዉለዉ በህግ እንዲጠየቁ አስካሁን አለመደረጉን ስንሰማ በሀገራችን የሕግ የበላይነት ስለመኖሩ መጠራጠራችን አይቀርም፡፡

ከዚህ ቀደምም በደቡብ ክልል በጉራፈርዳ እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በአማራዉ ላይ ሆን ብለዉ በደል ያደረሱ ግፌኛ ባለስልጣናት ከሀገሪቱ ህግ በላይ ስለሆኑ ወይንም ከበደሉት ህዝብ የሚበልጥ መብት ሲላላቸዉ ነዉ አስካሁን ያልተቀጡት? ቢያንስ የፌዴራል መንግስት ደሃዉን ህዝብ የሚበድሉ ጥጋበኛ ባለስልጣናትና በድርጊቱ በቀጥታ እጃችዉ እንዳለበት የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን በህግ ለመጠየቅ ድፍረት ያጣዉ ለምንድነው? በህዝብ ላይ ወንጀል እንደሰሩ በግልጽ የሚታወቁ ባለስልጣናትን እንደመቅጣት ጭራሽ የተሻለ ሹመት እየተሰጣቸዉ በህዝብ ላይ እየተቀለደ ነዉ፡፤ እነዚህ ጥቂት ወንጀለኞች ለፍርድ የማይቀርቡት ከህግ በላይ ሲለሆኑ ነዉ?ወይንስ የእነሱ ክብርና መብት ከህዝብ መብት ስለሚበልጥ ነዉ?

የመንግሰት ትልቁ ኃላፊነቱ የዜጎቹን ደህንነት ማረጋገጥ ነዉ፡፡ይህን ማድረግ ያልቻለ መንግስት ስለዲሞክራሲና ስለልማት ቢያወራ የሚሰማዉ አይኖርም፡፡ ከአልሸባብ ፤ ከኦነግ ኦብነግ ባልተናነሰ በገዛ ህዝባቸዉ ላይ ስነልቡናዊ ሽብር የሚፈጥሩ ሽብርተኛ ባለስልጣናትን መንግስት በወረንጦ እየለቀመ በማዉጣት ለፍርድ ማቅረብ መጀመር አለበት፡፡ በመሰረቱ የኮንሶም ሆነ ሌላዉ ህዝብ የመብት ጥያቄ ሲላነሳ ብቻ ጥቃት ሊፈጸምበት ባልተገባ ነበር፡፡

በተለይ ኮንሶን በተመለከተ የሕዝቡን ጥያቄ በማፈን ብሄሩን አባላት ተወካዮችና የባህላዊ አባት በህገወጥ መንገድ በማሰርና ህዝቡን በማጉላላትና በማዋረድ የተሳተፉና እጃቸዉ ያለበት ሀላፊዎችና ግለሰቦች በአስቸኳይ ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባል፡፡ ሆን ብለዉ ስርአቱ የመጣለትን ህዝብ በራሱ ስርአት ላይ እንዲያኮርፍ ቢሎም እንዲያምጽ የሚያሴሩ ወንጀለኞች ከድርጊታቸዉ እንዲቆጠቡ ሊደረጉ ይገባል፡፤ መንግስት ወገንተኛነቱ ለጥቂት ወንጀለኛና ሙሴኛ ባለስልጣናት ሳይሆን ለህዝቡ መሆኑን በተግባር ማሳዬት አለበት፡፤ ያለአግባብ የታሰሩ የኮንሶ ብሔር አባላት በአስቸኳይ ተለቅቀዉ በምትካቸዉ አሳሪዎቻቸዉና ንብረታቸዉን ያወደሙ ህገወጥና ጉልበተኛ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር በማዋል መንግስት ወገንተኝነቱን ለህዝብ መሆኑን በተግባር እንዲያረጋግጥልን  እንፈልጋለን፡፤

የኢህአዴግ መንግስት ከህዝቡ ያተረፈዉን ከበሬታና ተቀባይነት ራሱ በሾማቸዉ ብልሹ ባለስልጣናት ምክንያት እየተሸረሸረበት መሆኑ ሊያሳስበዉ ይገባል፡፡በሺዎች የሚቆጠሩ ታጋዮችን ህይወት ገብሮ ደርግን በመጣል ስልጣን ለተቆናጠጠዉ ኢህአዴግ በጣት የሚቆጠሩ ጥቂት ግፌኛ ባለስልጣናቱ ላይ መድፈር ለምን እንደተሳነዉ ለመረዳት ተስኖናል፡፡

በመሰረቱ እየተከተልን ያለነዉ ፌዴራላዊ ስርአት ግጭትንና አለመግባባትን የሚፈለፊልና ቅራነን ሆን ብሎ የሚያረታታ ስለሆነ አይደለም፡፡ ስርአቱ የዚህ ዓይነት ባህሪይ የለዉም፡፡ በየቦታዉ የሚታዩ ችግሮች በስርአቱ ባህሪይ ምክንያት የተፈጠሩ አይደሉም፡፡ በርግጥ ልንክደዉ የማንችለዉ ነገር ቢኖር የሕዝብ ጥያቄዎችና ዉዝግቦች መብዛታቸዉ ነዉ፡፤ ይህ ግን በስርአቱ ብልሹነት ምከንያት የተፈጠረ ሳይሆን ሃላነታቸዉን በዘነጉ ግዴለሽ አመራሮች ምክንያት ነዉ፡፤

ዲሞክራሲያዊ- ፌዴራላዊ ስርአት በባህሪይዉ ለዘመናት ተደብቀዉና ታፍነዉ የቆዩ ቅራኔዎችንና የህዝብ ብሶቶችን ወደ አደባባይ ማዉጣቱ እሙን ነዉ፡፤ በዚህ ምክንያትም እዚህም እዚያም ችግሮች መታታቸዉን  እነደ ጤነኛ ሁኔታ ታይቶ ችግሩን ለዘለቀታዉ ለመቅረፍ ጥረት ከማድረግ ዉጭ የለለና የማይጠበቅ ተአምር እንደተፈጠረ ተደርጎ መቆጠር የሚገባዉ አይደለም፡፡አሁን እየታዩ ያሉ ችግሮች የስርአቱ ተፈጥሮአዊ ባህሪይ ያመጣቸዉ ችግሮች ሳይሆኑ ሰዉ ሰራሽ የሆኑ ደባዎች ናቸዉ፡፡

በቀላሉ መቋጫ ማግኘት ይችሉ የነበሩ የሕዝብ የመብት ጥያቄዎች ሆን ተብሎ እንዲድበሰበስና   እንዲወሳሰብ በመደረጉና መልኩን እየቀየረና እየሰፋ እንዲሄድ በመደረጉ ሁኔታዉን ለመፍትሄ ፍለጋ አስቸጋሪ እያደረገዉ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ በራሱ የቁርጠኝነት ማጣት ምክንያት ደጋፊዉን ህዝብ እየተነጠቀ ነዉ፡፡ ህዝቡም በኢህአዴግ ግደለሽነት ምክንያት ለጥፋት ኃይሎች ተጋላጭ እየሆነ ነዉ፡፤ ጸረ-ህዝብ ኃይሎች ህዝቡን በቀላሉ ከኢህአዴግ እጅ እየነጠቁት ነዉ፡፤ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ጥንካሬዉን ማሳየት መጀመር አለበት፡፡ ስለዚህ ነገሮች ይበልጥ ከመበላሸታቸዉ በፊት ፈጠን ፈጠን ብሎ ማስተካከያ እርምጃ መዉሰድ መጀመር ይጠበቅበታል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከኢህአዴግ መንግስት የሚጠብቀዉም ይሄንን ነዉ፡፡

ፈጣሪ ሃገራችንን ይጠብቃት!

*********

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories