የመምህራን ዝምታ አስፈሪ ጩኸት ነው

ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህብረሰብ እየተሰጠ ያለው ስልጠና በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የወሊሶ ካምፓስ እንደቀጠለ ነው። ዛሬ ጠዋት ሊካሄድ የታቀደው የውይይት ፕሮግራም ነበር። ነገር ግን፣ መምህራኑ ሃሳብና አስተያየት እንዲሰጡ ሲጠይቁ ምላሻቸው ዝምታ ነበር። በአሰልጣኝነት የተመደቡት የመንግስት ኃላፊዎች “ኧረ እባካችሁ ተናገሩ?” እያለ ቢለምኑም ለመናገር ፍቃደኛ የሆነ መምህር አልነበረም። አንዱ አሰልጣኝ በሁኔታው ግራ በመጋባት “ባለፈው አመት ከእናንተ ጋር ተመሳሳይ ውይይት አድርጌያለሁ። ከመምህራን ጋራ የተደረጉ ውይይቶችን ስመራ ይሄ ሦስተኛዬ ነው። እንዲህ ያለ ነገር ግን አጋጥሞኝ አያውቅም” አለ። ነገር ግን፣ ለሁለት ሰዓታት ያህል የመምህራኑ ምላሽ ዝምም…ማለት ነበር። በመጨረሻም የሻይ-ሰዓት ሲደርስ ሁሉም በአንድ ድምፅ “የሻይ ዕረፍት!” ብለው ከስብሰባው ወጡ። 

ዶ/ር መረራ ጉዳና “ኢህአዴግ ማውራት እንጂ ማዳመጥ አይችልም” አሉ ይባላል። በእርግጥ መቼና የት እንዳሉት’ አላውቅም፡፡ የሃሳቡን ትክክለኝነት ማረጋገጥ ግን በጣም ቀላል ነው። ለዚህ ደግሞ ዛሬ የታዘብኩትን ነገር መጥቀስ በቂ ነው። መምህራኑ ለሁለት ሰዓታት ያህል በዝምታ ተቀምጠው እንደ ተማሪ የዕረፍት ሰዓታቸውን ሲናፍቁ ማየት በራሱ ይገርማል። እንደ አጠቃላይ ሲታይ ግን፣ መምህራን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብና አስተያየት እንዲሰጡ እየተለመኑ ዝም ማለታቸው ሰሚ ጠፍቶ እንጂ በራሱ ጩኸት ነው። 

በእርግጥ ማዳመጥ አለመቻል አንድ ችግር ነው። ማዳመጥ ለማይችል አካል መናገር ግን ከመጀመሪያው የባሰ ድንቁርና ነው። ኢህአዴግ ብዙ ግዜ ተነግሮት አንድም ግዜ በትክክል ማዳመጥ የተሳነው ድርጅት ነው። ስለዚህ፣ መምህራኑ ‘ማዳመጥ ለተሳነው ድርጅት መናገር ፋይዳ-ቢስ ነው’ በማለት ነው ዝምታን የመረጡት። በቦታው የነበሩ የመንግስት ኃላፊዎችም የሚሰጡት አስተያየት ይህን የሚያጠናክር ነው። ለምሳሌ በአሰልጣኝነት የተመደበው የመንግስት ኃላፊ “ከመምህራን ጋራ ተመሳሳይ ውይይቶችን ስመራ ይሄ ሦስተኛዬ ነው” ሲል፣ እኔ ደግሞ “ሁለቴ ነግረንህ ካልሰማህ ለምን ለሦስተኛ ግዜ እንነግርሃለን?” እያልኩ በውስጤ ስጮህ ነበር። 

በመምህርነት መስራት የጀመርኩት ከ1998 ዓ.ም ነው። ታዲያ በዚያኑ ዓመት ከ1997ቱ ምርጫ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ችግር ዙሪያ ለመወያየት በአከባቢው የሚገኙ መምህራንና የኦህዴድ/ኢህአዴግ ባለስልጣናት ስብሰባ ተቀምጠው ነበር። በወቅቱ ብዙም ልምድ ስላልነበረኝ እንደ አሁኑ ሃሳብና አስተያየት አልሰጥም ነበር። የረጅም አመት ልምድና ተሞክሮ የነበራቸው አንጋፋ መምህራን ግን “ኢህአዴግ ማውራት እንጂ መስራት የማይችል ድርጅት ነው” እያሉ ሲተቹት አስታውሳለሁ። 

ከ1998 – 2007 ዓ.ም ባሉት አስር አመታት በአመት ወይም በሁለት አመት የፓርቲ ይሁን የመንግስት የተምታታበት ስብሰባ መደረጉ አይቀርም። በእነዚህ ስብሰባዎች መምህራንም በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ጠቃሚ የሚሏቸውን ሃሳቦችና አስተያየቶች ከመስጠት አይቆጠቡም። ምክንያቱም፣ የአንድ ሀገር ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ የመጨረሻ ግቡ የዜጎችን ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። የዜጎችን መብትና ነፃነት የሚጋፉ ሥራዎችና አሰራሮች እንዲሻሻሉ በመጠቆም ረገድ ደግሞ ምሁራን የማይተካ ድርሻ አላቸው። በዚህ ረገድ በ2007 የትምህርት ዘመን መጀመሪያ ላይ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተሰጠው ተመሳሳይ ስልጠና በአብነት የሚጠቀስ ነው። 

መስከረም 2007 ዓ.ም ላይ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መምህራንና ሰራተኞች ጋር በተደረገው ውይይት ላይ የኢህአዴግ መንግስት ያሉበት ችግሮች እና የመፍትሄ እርምጃዎች በግልፅ የተጠቆሙበት መድረክ ነበር። በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ መምህራን በውይይቱ ተሳታፊ ነበሩ። በተለይ እኔ የነበርኩበት የውይይት ቡድን በአረዓያነት ሊጠቀስ የሚችል ነበር። የሕግ፣ የፖለቲካ ሳይንስ፣ የማህብረሰብ ሳይንስ፣ የፍልስፍና፣ የቋንቋ፣ የሕክምና፣ የሥራ አመራር፣…ወዘተ መምህራን ለአስር ቀናት ሲያደርጉ የነበረው ውይይትና ክርክር እጅግ በጣም ማራኪና አስተማሪ ነበረ። 

ኢህአዴግ፡ ከለውጥ እና ከሞት አንዱን ምረጥ በሚለው ፅሁፍ ውስጥ እንደተጠቀሰው በ2007ቱ ስልጠና ኢህአዴግ ለልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ስርዓት ግንባታ መሰረታዊ ችግሮች ይላቸው የነበሩት፡- “የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ትምክህት፣ ጠባብነትና አክራሪነት” ነበሩ። ታዲያ በውይይት መድረኩ ላይ፤ ኢህአዴግ በሚያስተዳድረው ሀገር ላይ “የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩ”፣ የፓርቲው አመራሮችና አባላቱ በሙስና ተዘፍቀው “የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ችግር አለ” ማለቱ፤ የአንድ ብሔር ወይም ሕዝብ መብትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የሚጠይቁትን – “በጠባብነት”፣ ስለ ብሔራዊ አንድነት የሚያነሱትን – “በትምክህተኝነት”፣ ‘መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ-አይግባ’ ያሉትን – “በአክራሪነት” በመፈረጅ ኢህአዴግ ራሱ በራሱ የፈጠራቸው ችግሮች እንደሆኑ አስረግጠን ነገርነው።     

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህራን በኢህአዴግ ከተጠቀሱት ችግሮች ይልቅ ሕዝቡ በተጨባጭ እያነሳቸው ያሉትን ችግሮች በመዘርዘር በአስቸኳይ የመፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠየቁ። ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፤ በወቅቱ በአምቦ ከተማ ለብዙ ሰዎች ሕይወትና ንብረት መጥፋት ምክንያት የሆነው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን የክልሉን ሕዝብና መንግስት አሳታፊ በሆነ መልኩ እስካልተዘጋጀ ድረስ ተግባራዊ እንዳይደረግ፣ በኦሮሚያ እና በአዲስ አበባ መካከል ከአገልግሎት አቅርቦትና የሃብት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በኢፊዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 49(5) መሰረት ዝርዝር የሕግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ፣ በመሰረተ-ልማት ግንባታ ሰበብ የአርሶ-አደሮች ከመሬት ይዞታቸው ማፈናቀል እንዲቆም፣ መንግስት ራሱ ለሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱ ተገዢ በመሆን ለህግ የበላይነት ተገዢ እንዲሆን፣ የሕገ መንግስቱን መርሆች የሚፃረሩና የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚገድቡ የህግ አንቀፆች፣ መመሪያዎች እና አሰራሮች መስተካከል እንዳለባቸው፣ የመንግስት ሥራና የአሰራር ሂደት ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው … ወዘተ ናቸው። 

ነገር ግን ኢህአዴግ ከመምህራኑ የቀረቡትን የመፍትሄ ሃሳቦች አንዱንም አንኳን ተግባራዊ አላደረገም። ኢህአዴግ በመምህራኑ ከተሰጡት የመፍትሄ ሃሳቦች በተቃራኒ አቅጣጫ መሄዱን ቀጠለበት። የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ መሻሻል አለበት ሲባል የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅን አፀደቀ። ሀገራዊ ምርጫን ከ99.6% ወደ 100% አሳደገ። ዴሞክራሲን ስንጠይቅ አምባገነንነትን አሰፈነብን። ነፃነትን ለጠየቀ ሕዝብ ፍርሃትን ለቀቀበት። በመጨረሻም መብቱንና ነፃነቱን ለማስከበር ባዶ እጁን አደባባይ የወጣን ሕዝብ እንደ ጠላት በጥይት ይገድለው፣ ያለ ርህራሄ ይደበድበው፣ ያለ ፍርድ ያስረው ጀመር። 

በዚህ ምክንያት በሀገሪቱ ግጭትና አለመረጋጋት ነገሰ። አንደተለመደው ኢህአዴግ በሀገሪቱ በተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት ዙሪያ ከመምህራን ጋር ለመወያየት እንኳን አይደለም “ስልጠና” ልስጥ ብሎ መጣ። በ2009 ዓ.ም ለልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ስርዓት ግንባታ ችግሮች ናቸው በማለት ምን ይዞ መጣ? በ2007 ዓ.ም ኢህአዴግ ራሱ በራሱ የፈጠራቸውን፡-“የመልካም አስተዳደር፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ትምክህት፣ ጠባብነትና አክራሪነት” የፈጣሪ ያለህ!!! ታዲያ ከዚህ ጋር ማን ይነጋገራል??? 

አዎ…ኢህአዴግ ይናገራል እንጂ አያዳምጥም። የመምህራን ዝምታ ግን ጩኸት ነው። ከውጪ ሳይሆን ከውስጥ የሚሰማ ድምፅ ነው፣ ከሌላ ሳይሆን ከራስ ጋር የሚያወሩት። በጆሮ የሚሰሙት ሳይሆን በህሊና የሚያስቡት፣ መልስ ሳይሆን ጥያቄ ነው። ዝምታ “ለምን ዝም አሉኝ?” ብሎ መጠየቅ ነው። ይህን ጥያቄ ስታብሰለስል ጩኸቱ ይሰማሃል፣ የመምህራኑ ጭንቀት ይገባሃል። ባለፉት አመታት የሰራኸው ስህተት በግልፅ ይታይሃል። አዎ…በደንብ ላስተዋለው የመምህራኑ ዝምታ አስፈሪ ጩኸት ነው!!

******** 

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories