“አወቅሽ አወቅሽ ሲሏት…” (ለሜ/ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት ጽሑፍ የተሰጠ ምላሽ)

(መሓሪ ይፍጠር [email protected])

 (ክፍል አንድ)

የቀድሞው የአየር ኃይል አዛዥ የነበሩትና የዛሬ 15 ዓመት ገደማ ህወሓት (ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ) ውስጥ በአንድ በኩል በልማታዊ ዴሞክራሲ ኃይሎች፤ በሌላ በኩል ደግሞ በትምክህት፣ በጥበትና በኪራይ ሰብሳቢነት ጎራ መካከል በተካሄደው የሃሳብ ፍትጊያ ኪራይ ሰብሳቢነትን ከሚያቀነቅነው “አንጃ” ጋር ተሰልፈውና እንደ ሰራዊት አባል ለህገ-መንግስቱ ታማኝ ባለመሆናቸው ምክንያት ከስራቸው የተሰናበቱትን ግለሰብ አንድ ፅሑፍ እንደ ዋዛ አነበብኩ—በቅፅል ስማቸው “ጆቤ” እየተባሉ የሚጠሩት የጡረተኛው ሜ/ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖትን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፃፈ ደብዳቤ። 

በህወሓት ክፍፍል ወቅት ህገ መንግስቱን ተፃርረው በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ጭልጥ ብለው ገብተው የነበሩት የእኚሁ ግለሰብ ደብዳቤ ይዘት፤ “ህገ መንግስቱን የሚፃረረው የሠራዊት ግንባታ ሰነድ ከሥራ ይወገድ” የሚል ነው። ምንም እንኳን የ“ጆቤ” ደብዳቤ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፃፈ ቢሆንም፤ በደብዳቤያቸው ላይ “ከስራ ይወገድ” በማለት የጠቀሱት ሰነድ ላይ የሰነዘሯቸው ሃሳቦች አሁንም ሰውዬው ከቀደምት አስተሳሰባቸው ያልተላቀቁና የጠቀሱትን መፅሐፍ አዋቂ በመምሰል በውሸት አስተሳሰብ ለማጠብ በመሞከራቸው እንደ ዜጋ ይህን ምላሽ ለመስጠት ብዕሬን ከወረቀት ጋር አዋድጃለሁ።

እርሳቸው እንዳሉትና እኔም መፅሐፉን ፈልጌ እንዳነበብኩት “የሰራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ” የተሰኘው ሰነድ ባለ 209 ገፅና በብራና ማተሚያ ድርጅት የታተመ ነው። እርሳቸው ከጠቀሷቸው እውነቶች ውስጥ አንዱ ይኸው ጉዳይና ግለሰቡ ባያምኑበትም “ሰራዊቱ በህገ-መንግስቱና በህገ-መንግስቱ ብቻ መመራት አለበት” የሚለው አፋዊ ትረካቸው ይመስለኛል። የተቀሩት እሳቤዎች ግን በሃሳብ መንትዮቻቸው “አወቅክ…አወቅክ” ሲባሉ መፅሐፉን በኒዮ-ሊበራል አስተሳሰብ የማጠብ ጥረት ብቻ ሆኖ ነው ያገኘሁት። ከዚህ እልፍ ሲልም የመከላከያ ሰራዊቱን ከፍተኛ መኮንኖች በውሸት ኢ-ህገ መንግስታዊ አድርጎ የመሳል አባዜንም ያካተተ ነው። እንዲያውም በተሃድሶው መስመር ተጉዘው ውጤታማ በመሆን ላይ ያሉትን ስርዓቱንና ሰራዊቱን በሚያስገርም ሁኔታ በደርግነት እስከ መፈረጅ ይደርሳል። ይህም ግለሰቡ ዛሬም ቢሆን የተሃድሶው መስመር እንቅፋት ለመሆን መከጀላቸውን የሚያመላክት ይመስለኛል።

ጡረተኛው ሜ/ጄኔራል “የአገራችን መከላከያ ተቋም ሕገ-መንግስቱ እና ሕገ-መንግስቱን ብቻ መሰረት አድርጐ መንቀሳቀስ ሲገባው በግላጭ ሕገ-መንግስቱን የመጣስ ክስተቶች እየታዩ ነው” በማለት ተቋሙን ይከሳሉ። ለክሳቸው ያቀረቡት ማስረጃ ግን የለም። ምናልባት እርሳቸው በደፈናው ‘ውንጀላዬ ካለፈው ደርግ መጣ የኢትዮጵያ ህዝቦች ጠንቀቅ በሉ’ ከሚለው ፅሑፌ የቀጠለ ነው’ የሚሉን ከሆነ፤ ይህን ፅሑፋቸውን “ክፍል ሁለት” ብለው ሊያቀርቡልን በተገባ ነበር። ይህን ግን አላደረጉትም። ያም ሆኖ ግን እርሳቸው “ደርግ መጣ የኢትዮጵያ ህዝቦች ጠንቀቅ በሉ” ለሚለው ፅሑፋቸው መነሻ የሆናቸው የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ መቐለ ላይ ከወጣቶች ጋር ያደረጉት ተሞክሮ የማስተላለፍ ውይይትን ተከትሎ ነው።

ታዲያ በወቅቱ እኔም የ“ጆቤ”ን ሃሳብ ተንተርሼ በኢንተርኔት ላይ የተጫነ ነገር እንዳለ ፈትሼ ነበር። በትግርኛ የተካሄደውን ውይይቱንም አገኘሁት። ትግርኛ ሁለተኛ ቋንቋዬ በመሆኑም የውይይቱን መንፈስ በሚገባ ተረድቼዋለሁ። የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስን በአካል አላውቃቸውም። አልፎ…አልፎ በቴሌቪዥን መስኮት ካልሆነ በስተቀር እርሳቸውን የማግኘት ዕድሉም አላጋጠመኝም። ጡረተኛውን ሜ/ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖትንም በፅሑፋቸው እንጂ በአካል አግኝቻቸው አላውቅም። ሁለቱንም ባገኛቸውና ሃሳባቸው ምን እንደሆነ ብረዳ ጥሩ ነበር። ሆኖም የሚያገናኘን ነገር ባለመኖሩ “ጆቤ”ንም በፅሑፋቸው ጄኔራል ሳሞራንም በወቅቱ ካስተላለፉት የተሞክሮ ውይይት አንፃር መልዕክቶቻቸውን ለመመልከት ሞክሬያለሁ።

ሆኖም ተሞክሮን ከሚያስተላልፈው ከጄኔራል ሳሞራ ውይይት ጡረተኛው ሜ/ጄኔራል “ደርግ መጣ” ሊያስብላቸው ያስቻላቸውን ነገር ማግኘት አልቻልኩም። እናም “ጆቤን” ልታዘባቸው የግድ ብሎኛል። ምክንያቱም እርሳቸው እንዳሉት በኤታማዦር ሹሙ ንግግር ምክንያት የተጣሰ ህገ-መንግስትም አላገኘሁም—በህገ መንግስቱ ላይ ‘ወጣቶች ሀገራዊ ፍቅር እንዲያድርባቸው አንድ ጄኔራል መኮንን ተሞክሮውን ማካፈል አይችልም፤ ስለሚመራው መስሪያ ቤትም የመናገር መብት የለውም’ የሚል ድንጋጌ ተፅፎ ባለማየቴ ነው። እንዲሁም “ጆቤ” ውይይቱን ተከትለው ‘የጄኔራሉ ንግግር ህገ መንግስቱን የሚፃረር ነው’ ለማለት የፈለጉበት መንገድ ከራሳቸው የጥላቻ ምናብ ተነስተው መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደብኝም። እናም በዚያ አስተያየታቸው እኔ በእርሳቸው ቦታ ሆኜ ማፈሬን ልደብቃቸው አልሻም። 

ለነገሩ ስለ ውትድርና ምንም ዓይነት ዕውቀት ባይኖረኝም እንዲሁ ሳስበው ግን አንድ ጄኔራል መኮንን እንደ ዜጋ የሚያቀርባቸው ሃሳቦች እንደምን ህገ መንግስቱን ጥሷል ሊያስብል እንደሚችል ግልፅ ሊሆንልኝ አልቻለም። እንዲሁ ዝም ብዬ ስገምት ግን ጄኔራል ሳሞራ ከተራ ታጋይነት እስከ የአንድ ሀገር ሰራዊት ኤታማዦር ሹምነት ድረስ የደረሱ፣ ለዚያውም በሀገራችን ታሪክ ለህዝቦች ባበረከቱት አስተዋፅኦ የሙሉ ጄኔራልነት ማዕረግ ማግኘት የቻሉ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ይመስሉኛል። ታዲያ በዚህ የህይወት ጉዟቸው ውስጥ በርካታ ድሎችንና ውጣ ውረዶችን ያሳለፉ፣ ራሳቸውን በየጊዜው በልምድና በትምህርት ያበቁና ዛሬ ላሉበት የኃላፊነት ደረጃ የደረሱ በመሆናቸው የካበተ ተሞክሮ ያላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ለመገመት የሚከብድ አይመስለኝም። እርግጥም ጄኔራል መኮንኑ በኤታማዦር ሹምነት እየመሩ ያሉትና በዓለም አቀፍ ደረጃ “አንቱታን” የተቸረው እንዲሁም በተሰማራባቸው በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ግዳጆች በህዝባዊነቱ ከበሬታን ያተረፈ ሰራዊትን በህገ መንግስቱና በህዝባዊ ወገንተኝነት እምነቱ ፅናትንና ጀግንነትን እንዲላበስ በማድረግ ብሎም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ሰራዊቱን በማዘመን ረገድ እርሳቸውና የስራ ባልደረቦቻቸው የላቀ ሚና የተጫወቱ ይመስለኛል።

እናም በእኔ እምነት ወጣቶች ከእኚህ እጅግ የካበተ ልምድና ተሞክሮ ካላቸው ጄኔራል መኮንን ተሞክሮ ያገኙ ዘንድ መጋበዛቸውና እርሳቸውም በውይይቱ ላይ መገኘታቸው ሃጢያቱ ምን እንደሆነ ለማንም የሚገባ አይመስልም። በእኔ እምነት በዚህ ዓይነት ውይይት ላይ እንኳንስ ኤታማዦር ሹሙ ቀርቶ፣ ጡረተኛው ሜ/ጄኔራል አበበም ቢሆኑ ከክፍፍሉ በፊት የነበራቸውን ጤነኛ አመለካከት ለወጣቶች ቢያስረዱ ክፋት ያለው አይመስለኝም። እርግጥ የ“ጆቤ” ፍላጎት ቀደም ሲል የጠቀስኩትንና አመቺ ነው ተብሎ በታሰበ ወቅት የተሃድሶውን መስመር ማደናቀፍ በመሆኑ በተለያዩ ጉዳዩች ላይ ውሸትን እየቀመሩ መፃፋቸው ብዙም የሚደንቅ አይመስለኝም።

ጡረተኛው ሜ/ጄኔራል “የሰራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ” የሚለውን መፅሐፍ ሲያነቡ እርሳቸው በምናባቸው ውስጥ የፈጠሩት የሰራዊቱ ኢ-ህገ መንግስታዊነት በከፊልም ቢሆን መሰረታዊ ችግሩ የት ላይ እንደሆነ እንደተገለጠላቸው ሊነግሩን ሞክረዋል። በእርሳቸው እምነት የችግሩ ምንጭ በሰነዱ ላይ ሰራዊቱ የገዥው ፓርቲ “የመጨረሻው ምሽግ” እንዲሆን ወይም “ቀባሪው እንዳይሆን” ሆኖ መገንባቱ ነው። ይሁንና እንዲህ ዓይነቱ የሰራዊት አገነባብ መንገድ ለእርሳቸው እንዴት አዲስ እንደሆነባቸው ግልፅ አይደለም—በየትኛውም ሀገር ውስጥ ቢሆን የሚሰራበት አካሄድ ነውና።

አንድ ሀገር የሚከተለው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ስርዓት ፊውዳላዊም ይሁን አብዮታዊ ዴሞክራሲ አሊያም ሊበራል ዴሞክራሲ ወይም ሃይማኖታዊ ወይም ሌላ ሰራዊቱን የሚቀርፀው የስርዓቱ ነፀብራቅ እንዲሆን አድርጎ ነው። ሊበራል ዴሞክራሲን በሚከተሉ ሀገራት ውስጥ ሰራዊቱ የሚገነባው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዩተ-ዓለም እንደማይሆነው ሁሉ፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲን በሚከተል ስርዓት ውስጥም ሊበራል ዴሞክራሲን የሚያቀነቅን ሰራዊት ሊገነባ አይችልም። ሃይማኖታዊ በሆኑ ስርዓቶች ውስጥም “መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው” የሚል ሴኩላሪዝምን የሚያቀነቅን ሰራዊት ሊገነባ አይችልም። ከዚህ አኳያ ሀገራችን ውስጥም ሰራዊቱን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ- ዓለም መገንባት የቆመለትን ህገ-መንግስታዊ ስርዓት በፅናት እንዲጠብቅ የሚያደርገው እንጂ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚያጋጨው አይደለም። እናም ጡረተኛው ሜ/ጄኔራል አበበ በፅሑፋቸው ላይ ከሰነዱ ጠቅሰው “እኛ የምንገነባው የመከላከያ ኃይል የአብዮታዊ ዴሞክሪሲያዊ ስርአታችን ዘብ ነው ብለን በግልፅ እና በጥሬው ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው” የሚለውን አባባል “ምን አይነት እብሪት ነው?” በማለት የገለፁበትን ጨዋነት የጎደለውን አባባላቸውን ያስተካክሉታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ሌሎች ከመፅሐፉ የጠቀሷቸውንና “ለምን ሰራዊቱ በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ርዕዩተ-ዓለም ይመራል?” ብለው ለመሞገት ሲሉ ያነሷቸውን ጉዳዩችንም ከዚሁ አኳያ እንደሚያዩዋቸው በመተማመን።

ያም ሆነ ይህ ግን ዕውነታውን ለመረዳት በቅድሚያ ‘ህገ-መንግስቱ ስለ ሰራዊቱ ምን ይላል?’ ብሎ መጠየቅ የሚገባ ይመስለኛል። በህገ መንግስቱ አንቀፅ 87 ላይ “የመከላከያ መርሆዎች” በሚል ርዕስ ስር አምስት ድንጋጌዎች ተቀምጠዋል። እነርሱም፦ የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ሚዛናዊ ተዋፅኦ ያካተተ ይሆናል፣ የመከላከያ ሚኒስትር ሆኖ የሚሾመው ሲቪል ይሆናል፣ የመከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ በተጨማሪ በዚህ ህገ መንግስት መሰረት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚሰጡትን ተግባሮች ያከናውናል እና የመከላከያ ሰራዊቱ ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነፃ በሆነ አኳኋን ያከናውናል የሚሉ ናቸው። ህገ-መንግስት ጥቅል ሃሳቦችን የያዘ እንደመሆኑ መጠን፤ በዝርዝር አዋጆችና ደንቦች መደገፉ የግድ ነው። እናም መንግስት የሰራዊቱን ህገ መንግስታዊ ሚና ይበልጥ ለማጠናከር በአዋጅ ቁጥር 27/1988 የመከላከያ ሰራዊቱን አቋቁሟል።

ታዲያ እዚህ ላይ ሳልጠቀስ የማላልፈው ነገር ቢኖር የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በሀገር ውስጥ ፀጥታ የማስጠበቅ ተግባር የሚሰማራው የችግሩ ሁኔታ ከፖሊስ አቅም በላይ ከሆነ አሊያም ሊሆን ይችላል ተብሎ በመንግስት በኩል ሲታመንበት ነው። በተለይም ከክልሎች አቅም በላይ የሆነ የፀጥታ መደፍረስ ችግር ሲያጋጥምና ክልሉ የፌዴራል መንግስቱን ድጋፍ ሲጠይቅ ሰራዊቱ ጣልቃ ሊገባ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ጡረተኛው ሜ/ጄኔራል ከፖለቲካ ገለልተኛ መሆን ሲገባቸው ይህን ባለመፈፀማቸው ሳቢያ ከሰራዊቱ በጡረታ በመገለላቸው አላውቀውም ካላሉ በስተቀር፣ የሰራዊቱን ህገ-መንግስታዊ ሚና አስመልክቶ በአዋጅ ቁጥር 395/1995 ድንጋጌ ወጥቷል።

ይህ ድንጋጌ ሰራዊቱ ምን ያህል ህገ-መንግሰቱን ብቻ ተመስርቶ ተግባሩን እንደሚያከናውን የሚያሳይ ነው። ይኸውም አዋጁ ሰራዊቱ ለህገ-መንግስቱና ለህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ መከበር ዘብ እንደሚቆም፣ የሀገር ሉዓላዊነትን እንደሚያስከብር፣ በህገ-መንግስቱ የተረጋገጡትን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የማክበር፣ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች መከታተልና በመንግስት ሲታዘዝ አደጋውን ለማምከን መስራት እንዲሁም የተጣለበትን ኃላፊነት በህግና በህግ ብቻ የመወጣት ግዴታ ጥሎበታል።

ጡረተኛው ሜ/ጄኔራል ሰራዊቱን ኢ-ህገመንግስታዊ አድርገው ለማሳል ቢሞክሩም፤ መሬት ላይ ያለው ዕውነታ ግን ይህ አይደለም። ሰራዊቱ ለህገ መንግስቱና ለህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ያለው ታማኝነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሰላማዊ ሰልፍ እንደማያደርግና ሌሎች በሚጠሩት ሰልፎችም ላይ እንደማይገኝ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን እንደማይችል፣ በስውርም ይሁን በግልፅ የፖለቲካ ቅስቀሳ ማድረግ እንደማይችል፣ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በመቃወምም ይሁን በመደገፍ ቅስቀሳ እንደማያደርግ፣ የመምረጥ መብት ቢኖረውም በግሉም ይሁን የፖለቲካ ፓርቲን ወክሎ ስልጣን እንደማይዝ እንዲሁም ለፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ ድጋፍ እንዳማያደርግ በሰራዊቱ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ገደብ ተጥሎበታል። እንግዲህ እነዚህ ኃላፊነቶች፣ ግዴታዎችና ገደቦች በህገ መንግሰቱና ህገ መንግሰቱን ተመርኩዘው የሰራዊቱን ተልዕኮዎች በተዘረዘረ መልኩ ለመግለፅ የወጡት አዋጆች፤ ሰራዊቱ ህገ-መንግስታዊ አደራና ግዴታ ያሉበት እንጂ፣ ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን በደፈናው ሰራዊቱን ለመክሰስ ሲሉ ለማለት እንደከጀሉት ሰራዊቱ የሚመራባቸው ሰነዶች ኢ-ህገ መንግስታዊ መሆናቸውን የሚያሳዩ አይደሉም።

እናም እነዚህን ህገ መንግስታዊና ከህገ መንግስቱ መንጭተው የወጡ አዋጆችንና ደንቦችን በሰራዊቱ ውስጥ ለማስረፅ (Indoctrinate) የማድረግ ስራን ለማከናወን በመንግስት ደረጃ አንድ ሰነድ ተዘጋጅቶ መመሪያ መሆን እንዳለበት ግልፅ ነው። ለዚህም ይመስለኛል “የሰራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ” የሚለው ሰነድ የሰራዊቱ የግንባታ መመሪያ ሆኖ የተዘጋጀው። ታዲያ የሰነዱን አስፈላጊነት በዚህ ደረጃ ከተማመን ዘንዳ፤ አሁን ደግሞ ጡረተኛው ሜ/ጄኔራል አበበ ይህን ሰነድ “ኢ-ህገመንግስታዊ ነው” በማለት ወዳነሷቸው ጉዳዩች ላምራ። 

ማንኛውም የጡረተኛውን ጄኔራል መኮንን ፅሑፍ ያነበበ ሰው፤ “የሰራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የተሰኘው ሰነድ ህገ-መንግስቱን እና አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚለውን ርዕዮተ ዓለም በማደባለቅና በማምታት ስለ ሰራዊት ግንባታ ይዘባርቃል” ከሚለው ኢ-ተዓማኒና አስገራሚ ሃሳብ ጋር መፋጠጡ አይቀርም። እኔም የተሰማኝ እንዲህ ዓይነት ስሜት ነው። ይሁንና በእኔ እምነት የተሃድሶውን መስመር ለማደናቀፍ ሁለት የማይነጣጠሉ ሰነዶችን (ህገ መንግስቱንና የሰራዊት ግንባታ ሰነዱን ማለቴ ነው) በግድ ለማለያየትና ሆድና ጀርባ አድርገው ለማቅረብ እያምታቱና እያዘባረቁ ያሉት “ጆቤ” ይመስሉኛል። ምክንያቱም የሰራዊት ግንባታው ሰነድ በህገ መንግስቱ መሰረት ህገ-መንግስቱን ለመጠበቅና ለመከላከል ሲባል የወጣ የአንድ ተቋም የግንባታ መመሪያ እንጂ ህገ መንግስቱን የሚፃረር ሆኖ ስላላገኘሁት ነው።

እርሳቸው ሰራዊቱ ለህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ያለውን ውግንና በተመለከተ በመፅሐፉ ገፅ 23 ላይ “ለአንድ ፓርቲ ዘብ በመሆን መልክ ሊገልፅ ይችላል። ከፓርቲው ውጭ ሆኖም ስርአቱን እንደ ስርአት ሕገ-መንግስቱን እና ሕገ-መንግስታዊ ስርአቱን ከመጠበቅ አንፃር ሊገለፅ ይችላል” የሚለውን አባባል በመውሰድ ሰነዱ ከህገ መንግስቱ የሚለይ ለማስመሰል ሞክረዋል። ይሁንና ሆን ብለው ከዚህ ዓረፍተ ነገር በላይ ያለውን ሊጠቅሱት አልፈለጉም። እርሳቸው ከጠቀሷቸው ዓረፍተ ነገሮች ከፍ ብሎ የተመለከተው ጉዳይ የሚያስረዳው፤ የአንድ ሀገር መከላከያ ኃይል አቅምና ጥንካሬ ስርዓቱን እንዴት እንደሚከላከል የሚያትት ሲሆን፤ ስርዓቱ አብዮታዊም ይሁን አድሃሪ እንዴት አድርጎ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን መጠበቅ እንደሚችልም የሚያመላክት ነው። ይህ የሰራዊቱ አቅምና ጥንካሬ የህገ መንግስቱን ደህንነት መጠበቅና መከላከል በሚል ሊገለፅ እንደሚችልም ያብራራል። ታዲያ ጡረተኛው ጄኔራል ምን እያሉን ይሆን? እንዲህ ዓይነቱ ቅጥፈትስ ምን ይፈይዳል? ያም ሆነ ይህ እኔ በበኩሌ ሰውዬው የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ መሆናቸውን በተለያዩ ወቅቶች ደጋግመው ስለነገሩን፣ የሚማሩት ነገር “የሴራ ንድፈ – ሃሳብ”ንም (Conspiracy Theory) ያካትታል እንዴ? ብዬ እንዳስብ አድርገውኛል።

“ጆቤ” በመፅሐፉ ገፅ 25 ላይ “በእኛ ተጨባጭ ሁኔታ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችንን ደህንነት መከላከል ማለትና የሀገር ደህንነትን መከላከል ማለት በመሰረቱ አንድ ነው ማለት ይቻላል” መባሉንም ህገ መንግስቱን የሚቃረን አስመስለው አቅርበዋል። በእኔ እምነት ይህ አስተሳሰባቸው ትክክል አይደለም። ለዚህም ሁለት ምክንያቶችን ማንሳት እችላለሁ። አንደኛው ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት በየትኛውም ሀገር እንደሚደረገው የሰራዊት ግንባታንና አንድን ስርዓት ለያይቶ ማየት አለመቻሉ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ጡረተኛው ሜ/ጄኔራል ከመፅሐፉ ላይ ቀንጭበው ከመውሰድ ውጭ እርሳቸው ስላነሱት ፅንሰ-ሃሳብ በመፅሐፉ ላይ ምን እንደተባለ ሆን ብለው ስለዘለሉት ነው። ሁለቱንም ምክንያቶቼን ዘርዘር አድርገን እንያቸውና ሰውዬው ምን እያሉ እንደሆነ እንመልከት።

በቅድሚያ በማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሀገርን የሚመራው በህዝብ የተመረጠ ገዥ ፓርቲና እርሱ የሚከተለው ርዕዩተ-ዓለም መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል። እናም በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሀገሪቱን እየመራ ያለው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዩተ ዓለም እንጂ፣ የኒዮ-ሊበራል ስርዓት ቀኖና አይደለም። ስርዓቱ የሚመራበት ርዕዩተ ዓለምና የሰራዊት ግንባታ አንድ በመሆናቸውም፤ የሀገር ደህንነት የሚጠበቀው ይህንኑ ርዕዩተ-ዓለም በሚያራምደው አካል መሆኑ ግልፅ ይመስለኛል። ይህም ሀገርን መጠበቅ ማለትና ስርዓቱን መጠበቅ ማለት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። ይህ ማለት ግን “ጆቤ” እንደሚሉት ሰራዊቱ በስርዓቱ ርዕዩተ-ዓለም ስለተገነባ ከህገ መንግስቱ ጋር ይጣረሳል ማለት አይደለም። ሌላ በህገ መንግስቱ መሰረት ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ ተወዳድሮና አሸንፎ የሚመጣ አካል ካለም፤ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ተፃርሮ እስካልቆመ ድረስ እርሱኑ መጠበቁ የሚቀር አይመስለኝም። እናም ጉዳዩን አጣሞ ለማቅረብ ካልተፈለገ በስተቀር ሃቁ ይኸው ነው።…ውድ አንባቢያን ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን ሰነዱን አስመልክተው ያነሷቸውን ሌሎች ጉዳዩችን በቀጣዩ ክፍል ፅሑፌ እመለስበታለሁ።

*******

Guest Author

more recommended stories