ዳግመኛ ለኤርትራ ጥቃት እንዳንጋለጥ ለማይቀረዉ ጦርነት ካሁኑ መዘጋጀት (ኮ/ል አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ)

(ኮሎኔል አስጨናቂ ገ/ጻዲቅ ሺፈራዉ)

መግቢያ

ኤርትራ በግፍ ወረራ ፈጽማብን የተቀሰቀሰዉን ጦርነት በኛ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ እነሆ ሁለት አስርተ ዓመታት ሊሞላዉ ትንሽ ቢቀረዉ ነዉ፡፡እስካሁንም ችግሩ መቋጫ ስላልተበጀለት ሰላምም ጦርነትም በለለበት ሁኔታ የሁለቱ አገሮች ወታደሮች በድንበር አካባቢ ተፋጠዉ ይገኛሉ፡፡ስለ ኢትዮ- ኤርትራ ጉዳይ አልፎ አልፎ በአጋጣሚ ካልሆነ በስተቀር ብዙም የማይነገር ሆኖ ቆይቶ ጭራሽ የተረሳ በመሰለበት ወቅት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደገና የብዙ ሰዉ ትኩረት የሳበ ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል፡፡ ጦርነቱ ካበቃም በኋላ ላለፉት አስራ ሰድስት ዓመታት አንድም ቀን ሰላም ሰጥታን የማታዉቀዉ ኤርትራ ከሰሞኑ ደግሞ ለድጋሚ ጦርነት የተዘጋጀች በሚያስመስል ሁኔታ መተነኳኮስ እንደጀመረች እየተነረን ነዉ፡፡ ስለ ጉዳዩ የሰሙ ኢትዮጵያዉያን የኤርትራ ለድጋሚ ጦርነት ዳርዳር ማለትና አጉል ድፍረትእጅጉን አስቀጥቶአቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የጦርነት ወሬ የናፈቃቸዉ የሚዲያ ሰዎችና ፖለቲከኞች ስለ“ማይቀረዉ ኢትዮ- ኤርትራ” ጦርነት የበኩላቸዉን አስተያየት እየሰጡ ነዉ፡፡ አፍቃሪ ኢሳይያስ የሆኑ ኢትዮጵያዉያን ዲያስፖራዎችም በበኩላቸዉ በጦርነቱ መነሳት እርግጠኛ የሆኑ ይመስል የኢሳይያስን ስልጣን ማክተሚያ ሊሆን ይችላል በሚል ስጋት በተለያዩ መንገዶች በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ትችት እየሰነዘሩ ነዉ፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያዉም ስለኤርትራ ሰራዊት አይበገረነትና ኢትዮጵያ ወደ ጦርነት ከገባች ወዮላት እያሉ ሊያስፈራሩን ሞክረዋል፡፡ በኛ አካባቢም ስለቀጣዩ “አይቀረ ጦርነት “በስፋት የዉይይት አጀንዳ መሆኑ አልቀረም፡፡ ብዙ ወገኖችም በተለያዩ ሚዲያዎች የመሰላቸዉን አስተያየት እየሰጡ ነዉ፡፡ ኢትዮጵያዉያን ስለ አገራቸዉ በተለይም በሉአላዊነት ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት የዜግነት መብታቸዉም ግዴታቸዉም መሆኑን ተረድተዉ የመሰላቸዉን ሃሳብ መሰንዘራቸዉ ተገቢ ነዉ፡፡ በሀገር ቤት ያሉ ብቻ ሳይሆን በዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንም (አፍቃሪ ኢሳይያስ ከሆኑት አትዮጵያዉያን ዲያስፖራዎች ዉጭ) ነጋ ጠባ የሻዕቢያ የሽብር ጥቃት ሰለባ ከመሆን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚገላግላቸዉ እድል የተፈጠረ አድርገዉ በመቁጠራቸዉ በተዘዋዋሪ መንገድም ቢሆን ለኢትዮጵያ መንግስት በጦርነቱ እንዲገፋ አይዞህ እያሉት ነዉ፡፡ሌላዉ ቀርቶ ከአገዛዙ ጋር በአንድ ወቅት ሆድና ጀርባ ሆነዉ የነበሩ እንደ ጄነራል አበበ(ጆቤ) የመሳሰሉ እዉቅ ጡረተኛ ከፍተኛ የጦር ሹማምነት ሳይቀሩ ኤርትራን በሚመለከት መንግስት ምን ማድረግ እንዳለበት በሃላፊነት ስሜት የበኩላቸዉን ደጋፊ አስተያየት እየሰጡ ነዉ፡፡

መንግስት በድንበር አካባቢ ስለተከሰተዉ ግጭት በገለጸበት ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ የዘጠና ዓመተ ምህረቱን ጦርነት አስመልክቶ ተሰምቶት የነበረዉ ዓይነት የመደናገጥና የመገረም ስሜት አልታየበትም፡፡ምክንያቱም የባለፈዉጦርነትጠባሳ አስካሁን ሲላልሻረና ከኤርትራ ጋር በጠላትነትሁኔታ ዉስጥ ብዙ በመቆየታችን ምክንያት ከሁኔታዉ ጋር በመላመዱ በሌላ በኩል ደግሞ በማንኛዉም ጊዜ ወደጦርነትበድጋሚልንገባእንደምንችል ይገመት ስለነበር ስለሁኔታዉ ሲሰማ ብዙም አልተገረመም፡፡ የባለፈዉ ጦርነት ካበቃ በኋላ ዉጥረት በሰፈነበት ሁኔታ ዉስጥ ከአስርዓመታትበላይስለቆዬንና የጠላትነት ድባቡ(hostility) አሁንም እንዳለ በመሆኑ ከጊዜያዊ ግጭትም በላይ አጠቃላይ ጦርነት ቢነሳ እንኳን ህዝቡ ከእንግዲህ ብዙም የሚረበሽና የሚደናገጥ አይመስለኝም፡፡

በድንበር አካባቢ ግጭት መደረጉ ከተሰማ ወዲህ ብዙ ሰዎች ድጋሚ ጦርነት መነሳቱ እንደማይቀር ግምታቸዉን በሰፊዉ እየገለጹ ነዉ፡፡እንዲያዉም አንዳንዶቹ ጦርነቱ መነሳቱ እንደማይቀር እርግጠኛ ከመሆን አልፈዉ ኤርትራን እንዴት አድርገን ልክ ማስገባት እንዳለብን እየመከሩ ነዉ፡፡በኤርትራ ነገር እጅግ የተማረሩ አንዳንድ ኢትዮጵያዉያን አስፈላጊ ከሆነም እኛዉ ራሳችን ጦርነቱን መጀመር እንዳለብንና የሻዕቢያን አገዛዝ ወዲያ ጥለን መገላገሉ እንደሚሻል እየነገሩን ነዉ፡፡በተለይም የኤርትራን ባለስልጣናትን ባህሪይ ከድሮም ጠንቅቀዉ የሚያዉቁ ሰዎች ጊዜ ሳናባክን በኤርትራ ላይ አንድ እርምጃ መዉስድ ይገባናል በሚል እየጎተጎቱ ነዉ፡፡እነዚህ የእኛንም የእነሱንም አቅም የት ድረስ እንደሆነ ጠንቅቀዉ የሚያወቁ ሰዎች የሚሰጡትን ምክር ላለመቀበል ያዳግታል፡፡በዚህ ሁሉ መሃል ግን የመንግስት አዝማሚያ ዝንባሌና ዉጥን ምን እንደሆነ እስካሁን ስላልተነገረን በግምት ደረጃ ካልሆነ በስተቀር በእርግጠኝነት መናገር አንችልም፡፡መንግስት የግድ ካልሆነበት በስተቀር የጦርነት አጀንዳ እንደለለዉ ቀድሞዉኑ በሚገባ ስለሚታወቅ የተለየ የጦርነት ዝግጅት ከማድረግ ይልቅ የኤርትራን እንቅስቃሴ በቅርብ መከታተሉን የመረጠ ይመስላል፡፡የመንግስታችንን ትእግስተኝነት ባደንቅም እንደባለፈዉ ጦርነት ተዘናግቶ ቆይቶ”ሳላስበዉ በድንገት ተወረርኩ“ እንደይለን መስጋቴ አልቀረም፡፤

በዚህ ምክንያትም ለምናልባቱ ብለን ስለቀጣዩ ጦርነት አንዳንድ ጉዳዮችን እያነሳን መነጋገሩም ሆነ የሃሳብ ልዉዉጥ ማድረጉ አይከፋም፡፡ጦርነት የሁላችንም የጋራ አጀንዳ በመሆኑ በሚያሳስቡን ጉዳዮች ላይ ተነጋግረን የጋራ አረዳድ መያዝ ይገባናል ብየ አስባለሁ፡፡ያለበለዚያ ወደ ጦርነቱ መግባት ይገባን ወይም አይገባን እንደሆነ ፤ጦርነቱ የግድ ከሆነም የጦርነቱ ዓላማና ግብ ምን መሆን አለበት በሚለዉ ላይ ሳንግባባ ከነ ልዩነታችን ወደ ጦርነት መግባት ተገቢ አይሆንም፡፡መንግስት ከኛ የሚፈልገዉንና እኛም ከመንግስት የምንጠብቀዉን በግልጽ እየተነጋጋርን በአንድ ላይ ሰልፋችንን ማሳመር ይገባናል፡፡ እንደባለፈዉ ጦርነት ተዝረክርከን ለኢሳይያስ ጥቃት እንዳንጋለጥ መንግስትም ካሁኑ ተገቢዉን ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ከሁሉም በፊት ወደ ጦርነት የመግባትጉዳይ በአንድ ፖለቲካ ድርጅት ብቻ በር ተዘግቶ በምስጢር ዉሳኔ የሚሰጥበትጉዳይ ሳይሆን ህዝቡን በሚወክለዉ ምክር ቤት(ፓርላማ) ተወያይቶ በይፋ መወሰን የሚገባዉ ነዉ፡፡ከጦርነቱ ስንወጣም “የኢህአዴግ ማ/ኮሚቴ (ስራ አስፈጻሚ)-በወሰነዉ መስረት-ወዘተ” የሚባል ነገር ከአንግዲህ ለሀገር ጉዳይ ሲሆን አይሰራም፡፡ቢያንስ ከዚህ በኋላ የዚህ ዓይነት አሰራር መቅረት ያለበት ይመስለኛል፡፡ጦርነቱ የህዝብ እንጂ የኢህአዴግ (የፓርቲ)ጉዳይ አይደለም፡፡እንዲህ ስል የገዢ ፓርቲን የመሪነት ሚና ዘንግቼ ሳይሆን ሀገሪቱንና ህዝቡን ወደ ጦርነት ለማስገባት ብቸኛ ስልጣን ያለዉ የሀገሪቱ ፓርላማ በመሆኑ ያለ ፓርላማ እዉቅናና ፈቃድ (authorization) ወደ ጦርነት መግባት ስለማይገባን ነዉ፡፡ በጦርነቱ ዓላማና ግብና ለዚያ መዳረሻ የሚሆን ስትራቴጂ ላይ ጥሪት ያለ አቋም መያዝ ይገባናል፡፡ግማሹ “ሻዕቢያን እንደምስስና እንገላገል” ሲል ሌላዉ “እንዴት ተደርጎ” በሚል የሚቆጣ ከሆነ አንዱ “በእጅ ባለን መሳሪያ ጦርነቱን ማሸነፍ ስለምንችል አላስፈላጊ የዉጭ ምንዛሪ ማባከን የለብንም” ሲል ሌላዉ ደግሞ “ለጦርነቱ ያልሆነ ለመቼ ሊሆን ነዉ ? ” በሚል ሁሉንም ማግበስበስ የሚፈልግ ከሆነ አንዱ “አሰብን የማስመለስ ዓላማን የማያካትት ጦርነት ከምናደርግ እስከናካተዉ ቢቀርብን ይሻላል” ሲል ሌላዉ ደግሞ “ወደብ ምንም ጥቅም የለዉም” የሚል አቋም የሚይዝ ከሆነ እንዴት አድርገን ነዉ ጦርነቱን ማሸነፍ የምንችለዉ? ብዙ ነገር ሊያስተካክል ይችላል ብለን የምንጠብቀዉ ጦርነት እንደባለፈዉ ጊዜ እኛኑ መልሶ እንዳይከፋፍለንና እርስ በርስ እንዳያቧጭቀን ከአሁኑ ልናስብብት ይገባል፡፡

አገሪቱ የጋራችን ናት፤ለጦርነቱ የምናጠፋዉ ገንዘብና ጦር መሳሪያዉ ሁሉም ነገር የጋራችን ነዉ፡እንዲሞቱ ጦርነትየምንደግስላቸዉም የኛዉ ልጆች ናቸዉ፡፡በጠላት ወረራ ተጎጂ የምንሆነዉ ሁላችንም ነን፡፡ለምን ወደጦርነት መግባት እንዳለብን፤የጦርነቱ ትክክለኛ መነሾ ምን እንደሆነ መስማት ያለብን ከዉጭሚዲያ ሳይሆንከራሳችን ሊሆን ይገባል፡፡ጦርነቱሲያበቃምምንእንዳገኘን፤ምንእንደጎደለብን፡ ምን እንዳሳካን፤ምን እንደቀረን በግልጽ ሊነገረን ይገባል፡፡መደራደር ካለብንም ወይም ድርድር የሚደረግበት ሁኔታም ከተፈጠረ ያለ አንዳች መደባበቅ ህዝብ እንዲያዉቀዉ መደረግ ይኖርበታል፡፡ወደ ጦርነት ስለመግባትም ሆነ በሌሎች ብሄራዊ ጥቅምሞቻችን በሚመለከቱ አብይ ጉዳዮች ላይ ተወካዮቻችን በሃገሪቱ ፓርላማ ላይ በነጻነት ሲከራከሩና ሲሟገቱ ማየትና መስማት እንፈልጋልን፡፡

ህዝብ ስለጦርነቱ ማወቅ ያለበት ስናሸንፍና ድል ሲገኝ ብቻ ሳይሆን እድል ፍቷን አዙራብን ስንሸነፍም ጭምር መሆን አለበት፡፡ጦርነት በመሰረቱ መንግስት ሃላፊነቱን ከህዝብ ተቀብሎ በዉክልና የሚያካሂደዉ እንጂ ጦርነት ምንጊዜም የህዝብ ስራ ነዉ፡፡ወደ ጦርነት የመግባት ጉዳይ ላይ መወሰን ያለበትም ራሱ ህዝቡ ነዉ፡፡በጦርነቱ የሚወድቀዉም ህዝብ ነዉ፡፡ ልጆቹን መርቆ የሚሰጠዉ ህዝብ ነዉ፡፡ለጦርነቱ አስፈላጊዉን ድጋፍ የሚያደርገዉም ራሱ ህዝብ ነዉ፡፡ከጦርነቱ ምን እንደሚፈልግና ምን እንደጎደለዉ የሚወስነዉም ህዝብ ነዉ፡፡ማሸነፍና መሸነፍን የሚወስነዉም ህዝብ ነዉ፡፡ስለዚህ ወደ ጦርነት መግባታችን የግድ ከሆነ ከህዝብ ጋር መወያየት፤ የሕዝብን ፍላጎትና ሃሳብ ማዳመጥ ተገቢ ነዉ፡፡ሁላችንም በሀገራችን ዕጣፈንታ ላይ የመወሰን እኩል መብት ሊኖረን ይገባል፡፡ለሀገራችንና ለህዝባችን ይጠቅማል ብለን ያሰብነዉን አስተያየት ከመስጠት መቆጠብ የለብንም፡፡በሀገራችን ጉዳይ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፖለቲከኛ ወይም ባለስልጣን መሆን የግድ አይደለም፡፡ብዙ የተማረ ምሁርም ሆነ ምንም ያልተማረ አርሶ አደር በሃገራቸዉ ጉዳይ እኩል መብት ብቻ ሳይሆን እኩል ሊደመጡ ይገባል፡፡

እኔም ከዚህ መንፈስ በመነሳት ከኤርትራ ጋር ወደፊት ስለሚጠብቀን ጦርነት አንዳንድ አስተያየቶችን ለመስጠት መፈለጌ አልቀረም፡፡መጀመሪያ ላይ አነሳሴ “ አይቀረ” ነዉ ስለተባለዉ ቀጣዩ ጦርነት አስተያየት ከመስጠቴ በፊት በቅድሚያ ስለአለፈዉና ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ያሉት የዘጠና ዓመተ ምህረቱን ጦርነት ላይ የግለን አስተያየት ለመስጠት ነበር፡፡ሆኖም በጽሁፉ አለቅጥ መርዘም ምክንያት ስለ ባለፈዉ ጦርነት የሚያወሳዉን ክፍል ለጊዜዉ ቆርጨ ለማስቀረት ተገድጃለሁ፡፡ስለዚህ ተቆርጦ የቀረዉን በሌላ ጊዜ እንደማቀርብ ቃል በመግባት ለጊዜዉ በቀጣይ በሚጠብቀን ጦርነት ላይ በማተኮር አንዳንድ አስተያየቶችን ለመሰንዘር እሞክራለሁ፡፡

1. ድጋሚ ወደ ጦርነት እንገባ ይሆን?

ሁለቱ አገሮች በድንበር አካባቢ ግጭት ማድረጋቸዉ ከተሰማ በኋላ እርስ በርስ ጣት ከመጠነቋቆልና ከመካሰስ ባለፈ ተጨማሪ ሌላ ግጭት ወይም የተኩስ ልዉዉጥ ያደረጉ አይመስለኝም፡፡ ሁኔታዉ ለጊዜዉ የተረጋጋና ወደ ቀድሞዉ የተመለሰ ቢመስልም “ወደፊት ወደ ሙሉ ጦርነት ይገቡ ይሁን? “የሚል ስጋት ያዘለ ጥያቄ እዚህም እዚያም መነሳቱ አልቀረም፡፡ስለ ጦርነት ከነጭራሹ መስማት የማንፈልግ ወገኖች ድጋሚ ጦርነት እንዳይነሳ ብንመኝና አይነሳም ብለን ብንደመድም ስህተት አይሆንም፡፡ነገር ግን ጦርነት አይነሳም የምንልበት ምክንያት አሳማኝ ካልሆነ ከስጋት በመነጨ መንፈስ ራሳችንን ለማሳመንና ለማጽናናት ያደረግነዉ ማምለጫ ብልጠት ከመሆን የዘለለ አይሆንም፡፡በድንበር አካባቢ ሌላ የተኩስ ድምጽ አለመሰማቱ ከዚህ በኋላ ጦርነት አይነሳም ብለን ድምዳሜ ላይ እንድንደርስ አያደርግም፡፡መረጋጋቱና የተኩስ ድምጽ አለመሰማቱ ለቀናት ብቻ ሳይሆን ለሳምንታትና ለወራትም ሊቀጥል ይችላል፡፡ እንደዚያም ቢሆን ጦርነቱ ድጋሚ የመቀስቀስ እድሉን ዝግ አያደርገዉም፡፡ ጦርነት ይቀሰቀሳል ብሎ በርግጠኝነት መናገር ባይቻልም በቅርብ ጊዜም ይሁን ዘግይቶ ቢሆን ወደ ጦርነት መግባታችን የማይቀር ነዉ፡፡ለጦርነት መነሾ የሚሆኑ ምክንያቶችና ሰበቦች ከበቂ በላይ አሉ፡፡ ሁለቱም አገሮች ከየራሳቸዉ ምክንያት በመነሳት ጦርነት ቢቀሰቀስ የሚጠሉ አይመስለኝም፡፡ ከቅርብ ጊዜዉ መተነኳኮስ በኋላ አሁን ግልጽ እየሆነ የመጣዉ ነገር ቢኖር ከዚህ በኋላ የዚህ ዓይነት ግጭት ዳግመኛ ቢፈጠር በቀጥታ ወደ ሙሉ ጦርነት መግባታቸዉ የማይቀር መሆኑን ነዉ፡፡ አሁን አንዳቸዉም የግጭቱ ጀማሪ መባልን አልፈለጉም፡፡ምክንያቱም የጦርነት ጀማሪ መሆን የሚያስከትለዉን ጣጣ ወይም ተጠያቂነት ሁለቱም ጠንቅቀዉ ስለሚያዉቁ ነዉ፡፡ ያም ቢሆን አንዱ በሌላዉ ላይ ጣት ሲጠነቋቆሉና እርስበርስ ሲካሰሱ ከርመዉ አሁን ሁለቱም ምንም እንዳልሆነ ያህል ነገሩን ትተዉ ወደ መደበኛ ስራቸዉ የተመለሱ አስመስሎባቸዋል፡፡ ለእኔ ግን እንደዚያ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ በኋላ ሁለቱም ወገኖች ጦርነት አይቀረ መሆኑን ስለተረዱ አንዱ ከሌላዉ ላለመቀደም ራሳቸዉን ለጦርነት ወደ ማዘጋጀት የገቡ ነዉ የሚመስለኝ፡፡ ከዚህ በኋላ ትንሽ ሰበብ እንዳገኙ ሁለቱም አንዱ በሌላዉ ላለመቀደም ዘለዉ ወደ ጦርነት መግባታቸዉ አይቀርም፡፡

ሁለቱም አገሮች አንዱ ሌላዉን “በዉስጥ በተፈጠረበት ቀዉስ የህዝቡን ትኩረት ወደሌላ ለማስቀየስ …… ” በሚል እየተቸ ነዉ፡፡የማንኛቸዉ የዉስጥ ችግር ይብሳል የሚለዉን ሁለቱም ጥንቅቀዉ ያዉቃሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ በእኛ በኩል ለሀገራችን መንግስት አሳሳቢ የሆነ የዉስጥ ችግር የለም ባይባልም ነገር ግን መንግስት እነዚህን ችግሮች መፍታት አቅቶት የህዝቡን ትኩረት ለማስቀየር ብሎ ወደ ባሰ ቀዉስ -ወደ ጦርነት ይገባል ብዬ አላስብም፡፡በመጀመሪያ ነገር እነዚህ በአንዳንድ አካበቢዎች የተከሰቱ ችግሮች ከዚህ በፊት ከለመድነዉ ትንሽ ለዬት ባለ መልኩ አሳሳቢ መሆናቸዉ ባይካድም ነገር ግን ከመንግስት አቅም በላይ ሆኖ መንግስት ችግሮቹን መፍታት ይሳነዋል ብዬ አላስብም፡፡የኢህአዴግ መንግስት ችግሮቹን ከህዝቡ ጋር ተወያይቶ መፍታት ካልቻለም ስልጣኑን በገዛ ፈቃዱ መልቀቅን ይመርጣል እንጂ ስልጣኑን ከህዝብ ጥቅም አስበልጦና ለስልጣኑ ሳስቶ “የህዝብን ትኩረት ለማስቀየስ“ ሆን ብሎ አገሪቱንና መላዉን ህዝብ ወደ ጦርነት እንደማያስገባ እርግጠኛ ነኝ፡፡የኢህአዴግ መንግስት እኛ እንደምንመኘዉና በምንጠብቀዉ ደረጃ ዲሞክራት ላይሆን ይችላል፡፡በሰራቸዉ በርካታ ዘመን ተሸጋሪ ስራዎች የሚወደስበትን ያህል ባይሆንም ለትችት የሚጋብዙ ድክመቶች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ነገር ግን በምንም ምክንያት ቢሆን ለገዛ ህዝቡ ጦርነትን የመሰለ አደጋ ይጋብዛል ብዬ አላስብም፡፡ያን ያህልም ሃላፊነት የማይሰማዉና ከህዝብ ጥቅም ይልቅ ቅድሚያ ለስልጣኑ የሚያደርግ አይደለም፡፡ይህን ስል የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ ጋር ወደ አዲስ ጦርነት መግባትን ጨርሶ አይፈልግም ማለት ግን አይደለም፡፡መንግስት ጦርነቱን ሊፈልግ ይችላል፡፡ቢያንስ አይጠላም፡፡ነገር ግን ወደ ጦርነት የሚገባዉ አስቀድሜ እንደጠቀስኩት የህዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየርና ፋታ ለማግኘት ብሎ ሳይሆን ለሁላችንም ደህንነት ቋሚ ስጋት የሆነዉን አደጋ ከምንጩ ለማድረቅ በማሰብ ብቻ ነዉ ሊሆን የሚችለዉ፡፡ከኤርትራ ጋር የሚኖርን ጦርነት በዉስጣችን ካለዉ ችግር ጋር አንዳችም ቁርኝት አይኖረዉም፡፡የኤርትራ ችግር ግፋ ብል በጦር ሜዳ በጦርነት የሚለይለት ይሆናል፡፡የዉስጥ ችግራችን ግን አንድትም ጥይት መተኮስ ሳያስፈልገን ህዝቡና መንግስት እየተመካከሩ በሰላም የሚፈቱት ነዉ የሚሆነዉ፡፡

2. ቀጣዩ ጦርነት የህገ-መንግስታዊ ስርአቱንም ሆነ የአገዛዙን ጥንካሬና ድክመት በድጋሚ የምንፈትሽበት አንድ ሌላ አጋጣሚ ይሆናል፡፡

በብዙ አገሮች እንደታዬዉ መንግስታት (ዲሞክራት ሆኑም አልሆኑ) አገዛዛቻዉ ለአደጋ ተጋላጭ ከሚሆንበት ወይም ስልጣን የሚያሳጣ ሁኔታ ከሚፈጠርባቸዉ አጋጣሚዎች አንዱ ምናልባትም ዋነኛዉ ጦርነት ነዉ፡፡ መጀመሪያዉኑ በዉስጥ ችግሮች የተወጠረ መንግስት ጦርነት ሲጨመርበት ለከፋ አደጋ መጋለጥ መቻሉ ግልጽ ነዉ፡፤ጦርነት የመንግስትን ድክመት ለሚመኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ለመንግስት ታማኝ በሆኑ ፖለቲከኞችና ወታደሮችም ቢሆን ለጣልቃገብነት (intervention) አንድ ገፊ ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ጦርነት በአገዛዙ ላይ የስጋት ምንጭ የሚሆነዉ በሁለት ሁኔታዎች ነዉ፡፡

በአንድ በኩል ጦርነቱ እንደታሰበዉ ሳይሆን ቀርቶ ድል ካልተገኛና ሰራዊቱ ተሸናፊ ከሆነ በሰራዊቱ አባለት ዘንድ ከፍተኛ የሞራል ዉድቀትና ተስፋ መቁረጥ ስለሚያስከትል ለዚህ ሁሉ ጥፋት ተጠያቂ ነዉ ብለዉ በሚያስቡት በመንግስት ላይ አሜነታ ማጣትና ለመታዘዝ ፈቃደኛ አለመሆንና ሁኔታዉ ከከፋ ደግሞ ወታደሩ በራሱ ተነሳሽነት ወይም ስልጣን በአቋራጭ ለማግኘት በሚቋምጡ ሲቪል ፖለቲከኞችና ተቃዋሚ ፓርቲች አጉል ስብከት ተገፋፍቶ በመንግስት ላይ አመጽ ሊቀሰቅስ ይችላል፡፡ ከብዙ አገሮች ታሪክ መረዳት እንደሚቻለዉ በጦርነት ተሸናፊ የሆነ የመንግስት በስልጣን ላይ የመቆየት ዕድሉ በጣም አነስተኛ መሆኑን ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ ደግሞ ሰራዊቱ ድል አድርጎም እያለ ነገር ግን ጦርነቱ እጅግ አለቅጥ መራዘምና የተገኘዉም ድል ከተጠበቀዉ በታች መሆን ፤ድሉን ለማምጣት የተከፈለዉ መስዋእትነትና ወይም ኪሳራም እጅግ መብዛት፤ ጦርነቱ በህዝቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ላይ ትልቅ መመሰቃቀል ሲፈጥርና ሌሎች ያልተጠበቁ ቀዉሶች ተደማምረዉ ለአመጽ ቀስቃሽ ይሆናሉ፡፡ አንዳንዴ ወታደሩ በደሙ ተዋግቶ ያመጣዉን ድል በፖለቲከኞች ንዝህላልነትና ግደለሽነት ድሉን ከእጁ ልነጠቅ ይችላል፡፡

በጦርነት ሽንፈት ሲያጋጥም ደግሞ መዘዙ ብዙ ነዉ፡፡ መንግስት የህዝቡን አመኔታ ያጣል፡፡ሰራዊቱ ተሸናፊ ሰራዊት ስለሚሆን ሞራሉ ስለሚወድቅና ህዝቡም ለገዛ ሰራዊቱ ከፍተኛ ንቀት ስለሚያሳዬዉ በዚህ ምክንያትም ወታደሩ ሙያዉን ይጠላል፡፤ ሀገሩን በዉትድረና ለማገልገል አይሻም፡፡ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂዉ ነዉ ብሎ በሚያስበዉ በመንግስት ላይ አመጽ ሊያዉጠነጥን ይችላል፡፡ በተለይ እንደዚህ ዓይነት መመሰቃቀልን ለሚፈልጉ ተቀዋሚ ፓርቲዎች አመቺ ሁኔታ ስለሚፈጥርላቸዉ ወታደሩን ያለ ፍላጎቱ ገፋፍተዉ በመንግስት ላይ እንዲያምጽ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ተሸናፊ ሰራዊት በራሱ በተቋሙ ዉስጥም ሰላም ስለማይኖረዉ እርስበርሱ መወነጃጀል ይጀምራል፡፡ በተለይ አለቆቹን ለሽንፈቱ ግንባር ቀደም ተጠያቂ በማድረግ የከፋ እርምጃም እሰከመዉሰድ ሊደርስ ይችላል፡፡

በሀገራችንም ለዚህ ዓይነቱ አደጋ እንደማንጋለጥ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ምናልባት ዕድለኛ ሆነን ሌሎች ፓለቲካዊ ችግሮች ባይከሰቱ እንኳን በጦርነት በመሸነፋችን ወይም ጦርነቱ ከተጠበቀዉ በላይ መራዘም ምክንያት ለበርካታ ችግሮች ልንጋለጥ እንችላለን፡፡ የልማት ስራችንም በእጅጉ ይስተጓጎላል፡፡እንደ ህዳሴዉ ግድብ የመሳሰሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀዉስ ምክንያት ይስተጓጎላሉ፡፡መንግስትም አጠቃላይ መዳከም ስለሚያጋጥመዉ ግብጽን ለመሳሰሉ ስትራቴጂያዊ ጠላቶች ትልቅ የምስራች ይሆናል፡፡ በተለይ ግብጽ አሁን ከያዘችዉ የመለሳለስ አቋም በመዉጣት የተለየ አካሄድ ልትመርጥ ትችላለች፡፡ በዉጭገጽታችንምላይአሉታዊ ተጽኢኖ ሊፈጥር መቻሉ ግልጽ ነዉ፡፡ ከተሸናፊና ደካማ መንግስት ጎን የሚቆምና የሚተባበር አገር አይኖርም:: አስካሁን ስናገኝ የነበረዉን ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ሁሉ ሊቀንስ ወይንም እስከ ናካተዉ ሊቋረጥ ይችላል፡፡ ለእድገታችን በጣም አስፈላጊ የሆኑ ከዉጭ የሚናገኛቸዉ የኢኮኖሚ ተራዲኦ በእጅጉ ይቀንሳሉ፡፡ የዉጭ ኢንቬስትሜንትም ያለ ጥርጥር ይቀዛቀዛል፡፡ ጦርነቱ ቢቆምም እንኳን መልሰን ለማንሰራራት ረዥም ዓመታት ሊጠይቀን ይችላል፡፡ ባጠቃለይ የጦርነት ሽንፈት ሆነ በጦርነት መራዘም የሚፈጠሩ ሁኔታዎች በሀገሪቱ አለመረጋጋትን በመፍጠር ረገድ ቀላል የማይባል ጫና ያደርጋሉ፡፡

ስለዚህ ወደ ጦርነቱ የምንገባ ከሆነ ያለ ጥርጥር እንደምናሸንፍ ብቻ ሳይሆን ጦርነቱን እጅግ አጭር በሆነ ጊዜ በድል ለማጠናቀቅ እንደምንችል እርግጠኛ መሆን ይገባናል፡፡ ወደ ጦርነቱ ለመግባት የሚያስገድደን በጣም ጉልህ የሆነ ብሄራዊ ጥቅማችንን(vital interest) የሚነካ ስጋት ሲፈጠር ወይም ከጦርነት ዉጭ በሌላ መንገድ ማሳካት የማንችለዉ እጅግ ጠቃሚ የሆነ ዓላማ ይዘን ካልሆነ በስተቀር በረባ ባልረባዉና በስሜት ተገፋፍተን ወደ ጦርነት መግባት አይኖርብንም፡፡

3. አካባቢያዊ ሁኔታዎች በቀጣዩ ጦርነት ላይ ያላቸዉ አንድምታ

ከዚህ በኋላ የሚኖረዉ ጦርነት ባለፈዉ ጦርነት ወቅት ከነበርንበት በተለየ ሁኔታ ከአጠቃለይ ወታደራዊ ፤ ፖለቲካዊ ፡ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ሁኔታዎች አንጻር ሊታዩ የሚችሉ ከባባዊ (environment) ለዉጥ እንደሚኖር ግልጽ ነዉ፡፡የወቅቱ አለምአቀፍና አካባቢያዊ ሁኔታ ለሁለቱም አገሮች የማያዳሉና የጋራ መሆን መቻላቸዉ እንዳለ ሆኖ ሁለቱም አገሮች በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ሁኔታዎችን አንዱ ከሌላዉ በተሻለ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ መዘንጋት የለበትም፡፡

3.1 ለእኛ በበጎ ጎኑ የሚታይ ሁኔታ

ኤርትራ ከምንጊዜም በላይ ከአለም የተገለለች መሆንዋና በተደጋጋሚ በተጣለባት ማዕቀብ ምክንያትም እጅጉን በመጎዳቷ ለኛ እንደ መልካም ሁኔታ የሚቆጠር ነዉ፡፡ በአንጻሩ ኢትዮጵያ ከምንጊዜም በላይ በዉጭዉ ዓለም ተቀባይነትና ተደማጭነት ማትረፏ ይህም ከፍተኛ የዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጥቅም ሊያስገኝላት መቻሉ እሙን ነዉ፡፡ ኢትዮጵያ ከባለፈዉ ጦርነት በኋላ ምናልባት ከሁሉም ነገር በላይ በጣም ወሳኝ የሆነ ትልቅ አቅም ፈጥራለች ተብሎ ሊጠቀስላት የሚችል ሁኔታ ቢኖር በዉጭዉ ዓለም ያገኘችዉ ተቀባይነትና ተደማጭነት ነዉ፡፡ይህ በራሱ ብዙ ጠቃሚ ጎኖች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ አገራችን በብዙ ሁኔታዎች መለወጧ እሙን ነዉ፡: ሌላ ሌላዉን ትተን ሌሎች ስለኛ የነበራቸዉ አመለካከትና ግምት ምን ያህል እንደተቀየረ በተግባር እያየን ነዉ፡፡

ትላንት ስንቁን የነበሩ ዛሬ ግን የሚያከብሩን ብዙ ናቸዉ፡፡ ትላንት በራሳችን ጉዳይ ስንለማመጣቸዉ ደጅ የሚያስጠኑን፤ምክር ስንጠይቀቸዉ ፍታቸዉን የሚያዞሩብን ዛሬ የራሳቸዉን ችግር እንድንፈታላቸዉ ምክርና እገዛ ፍለጋ ወደኛ ይመጣሉ፡፡ ትላንት በርስ በርስ ጦርነት ስንጨራረስ እያዩ “ተዉአቸዉ ልማዳቸዉ ነዉ” እያሉ እንዳልተዘባበቱብን ዛሬ እነሱ አርስ በርስ ሲፋጁ እኛ እንድንገላግላቸዉና የሰላም አስከባሪ ሰራዊት እንድንልክላቸዉ ይማጠኑናል፡፡ ትላንት የሀገራችንን ጥቅም በአለም አቀፍ መድረክ ማስከበር የማንችልና አንድም አዳማጭና ደጋፊ ያልነበረን ዛሬ በሪጅኑ ለሚፈጠር ችግር ሁሉ የመንግስታቱ ድርጅት ሳይቀር የእኛን ትብብር የሚጠይቅበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ትላንት የራሳችን መብትና ጥቅም በዓለም መድረክ ተከራክርን ማስከበር ያልቻልን ዛሬ ጊዜዉ ተለዉጦ ለአፍሪካ ሀገሮች መብት ተከራካሪ ወኪል የሆንበት ሁኔታ ተፈጥሮአል፡፡ የዛሬ አርባ ዓመት ገደማ ኃያሏ አሜሪካ ራሳችንን ለመከላከል ብለን ለመሳሪያ መግዣ ገንዘብ ከፍለናት እያለ መሳሪያዉን በመከልከል ለዚያድ ባሬ ጥቃት እንዳላጋለጠችንና እንደገናም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅትም ለወራሪዋ ኤርትራ ዲፕሎማሲያዊ አድሎ ሲታደርግ እልዳልነበር ዛሬ በሪጅኑ ሽብተርተኝነትን ለመወጋት በከፈተችዉ ጦርነት ያለ ኢትዮጵያ እርዳታ አንዳችም ነገር ማድረግ እንደማትችል በመረዳቷ የእኛን እገዛ መሻቷና በሪጅኑ ዋነኛ ስትራቴጂያዊ አጋር ማድረጓ በራሱ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

የሀገራችን ክብሯ ከወደቀበት እየተነሳ መሆኑን አንዱ ማሳያ የሚሆነዉ የዓለም ብቸኛዋ ልዕለ ኃያልና አድራጊ ፈጣሪ የሆነችዉ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በስልጣን ላይ እያለ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸዉ ነዉ፡፡ይህ ታሪካዊ ክስተት በፊት በነበርንበት ሁኔታ ቢሆን ኖሮ ፈጽሞ የማይጠበቅና የማይገመት ነበር፡፡ የፕሬዝዳንት ባራክ አባማ አዲስ አበባ መምጣት ፖለቲካዊ ጠቀሜታዉ እጅግ ከፍተኛ ነዉ፡፡ሌላዉ ለሀገራችን ተደማጭነትና ተጽኢኖ ፈጣሪነት ትልቅ ማሳያ የሚሆነዉ ግብጽን የመሰለች ስትራቴጂያዊ ጠላታችንን ለእኛ ፈቃድ ማስገዛት መቻላችን ነዉ፡፡ ግብጽ በህዳሴ የኤሌክትክ ኃይል ማመነጫ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ደስተኛ ባትሆንም ነገር ግን ግንባታዉን ለአንድትም ቀን ማስቆም እንደማትችል ተረድታ ለኛ ፈቃድ ራሷን ማስገዛቷ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ይህ የግብጽ መላሳለስ ከዚህ በፊት ጨርሶ የማታሰብ ነበር፡፡ በተጨማሪ አሁን በቅርቡ አጅግ አስደንጋጭ የሆነ ድርቅ አጋጥሞን የከፋ ጉዳት ሳይደርስብን በራሳችን አቅም መቋቋም መቻላችን ለአንዳንዶቻችን ብዙም ትርጉም ባይሰጥም በዉጭዉ ማህበረሰብ ግን አስገራም ነበር፡፡

ብዙ ሁኔታዎችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በገንዘብ ሊተመን የማይችል እጅግ ትልቅ አቅም ነዉ የሆኑን፡፡ እዚህ ላይ መዘንጋት የለለብን ነገር ቢኖር ከበፊቱ ይልቅ አሁን ወደኛ የሚያደሉ በርካታ ሁኔታዎች እንደተፈጠሩ ተረድተን ይሄንን መልካም አጋጣሚ በደንብ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ የሁኔታዎችን መለወጥ ማወቃችን ብቻዉን የሚሰጠን ጥቅም አይኖርም፡፡ ከዚያ ይልቅ የወቅቱ ሁኔታዎች ለእኛ አመቺ መሆናቸዉን ተረድተን በአግባቡ ልንጠቀምባቸዉ ይገባል፡፡ይህን ዕድል ወደፊት በሆነ አጋጣሚ ሊናጣና በሪጅኑ ያለንን ተደማጭነታችን ልንነጠቅም እንደምንችል አስበን ካሁኑ ለሀገራችንን ተጨማሪ ጥቅም በሚያስገኝ መልኩ መጠቀም መቻል ይገባናል፡፡

3.2 ለኤርትራ ምቹ የሆነና ለእኛ ጫና ሊፈጥር የሚችል ሁኔታ

ዛሬ የምናደርገዉ ጦርነት ከዛሬ አስራ ስድስት ዓመታት በፊት ከነበረዉ ጦርነት ጋር በምንም መንገድ ሊመሳሰልና አንድ ሊሆን አይችልም፡፡ የትላንቱ ዓይነት ጦርነት ዛሬ ይደገማል ብለን መጠበቅም የለብንም፡፡ ብዙ ሁኔታዎች ተለዋዉጠዋል፡፡ የአካባቢያዊ ሁኔታዎች ተለዉጠዋል፡፡ ኤርትራም ሳትለወጥ እንደነበረች መቆየት አትችልም፡፡ በጥንካሬም ይሁን በድክመት፤ ወደ ላይም ይሁን ወደታች የሆነ መለወጥ ይኖራል፡፡የዛሬዋ ኤርትራም ከትላንቱ የምትለይበት ብዙ ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ ወቅቱ በፈጠረዉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ለሁለቱም አገሮች ትላንት መረጃ ለማግኘትም ሆነ መረጃ ለመለዋወጥ የነበረዉ ችግር ዛሬ እጅግ የቀለለ መሆኑ ግልጽ ነዉ፡፡ ለሁለቱም አገሮች የጦር መሳሪያን ከየትኛዉም ገበያ እንደልብ ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ፡፡ ኤርትራ ከመደበኛ ሰራዊቷ ጎን ቅጥረኛ ወታደሮችንና የሽብር ኃይሎችን ከመጠቀም ወደ ኋላ እንደማትልም መዘንጋትም አይገባም፡፡

በተለይም አለም አቀፍና የአካባቢዉ የሽብር ኃይሎች (አልሻባብ፡አይሲስ(isis)፤አልቃይዳ ፤አልታድ ወዘተ)ኤርትራን አጋር ማድረጋቸዉና ኢሳይያስን እንደባለዉለታ መቁጠራቸዉ በዚህም ምክንያትም ከኤርትራ ወታደሮች ጎን ባይሰለፉ እንኳን በመሃል አገር የተቀነባበረ ሽብር ድርጊት በመፈጸም ከጀርባችን ሊወጉን እንደሚችሉ ታሳቢ ማድረግ ብልህነት ነዉ፡፡ በተለይ በምስራቁ አገራችን ክፍልና እንዲሁም በሶማሊያ ሆን ብለዉ ትርምስ በመፍጠር የሰራዊታችን ኃይል ለመከፋፈልና መንግስትን ለማዳከም መጣራቸዉ ተጠባቂ ነዉ፡፡ ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት ከምንጊዜም በበለጠ አሁን የተጽአኖ አድማሱን ማስፋቱና በወታደራዊም ሆነ በገንዘብ አቅሙ ከድሮዉ በበለጠ በመጎልበቱ ባንድ ጊዜ በተለያዩ የአለም አካባቢዎችና አገሮች በተቀነባበረና በተቀናጀ ሁኔታ ሽብር መፍጠር የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡በየአካባቢዉ የሽብር ዓላማቸዉን የሚደግፉና በዉክልና የሚያስፈጽሙ አሻንጉልት መንግስታትን መልመለዉ እንደሚጠቀሙባቸዉ ከምንጊዜም በላይ አሁን ግልጽ እየሆነ መጥቷል፡፡ በዚህ ምክንያትም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለመፈጸም ላቀዱት የሽብር ዘመቻ የኤርትራን መንግስት በአጋሪነት ማጨታቸዉ እሙን ፡፡ የኤርትራ መንግስትም በሽብር ድርጊት አስፋጻሚነት ሃላፊነቱን ለመቀበል በጭራሽ ሳያቅማማ አካባቢዉን ማተረማመስ ቀጥሏል፡፡ኢትዮጵያን ሊጎዳ ይችላል ብላ ያሰበችዉን እርምጃ ሁሉ ከመዉሰድ ለማትቆጠበዉ ኤርትራ እንደ መንግስት ሽብር አስፈጻሚ መሆኗ (state- sponsored terrorism) ለቀጠናዉ አገሮች በተለይም ለሀገራችን ከፍተኛ ስጋት ሊፈጥር መቻሉ ግልጽ ነዉ፡፡

ሌላዉ ከዚሁ ጋር ተያያዥ የሆነዉ ያለንበት አካባቢ (የአፍረካ ቀንድ) ከአስራ ስድስት ዓመት በፊት ከነበረዉ በተለየ ሁኔታ አሁን ብዙ አገሮች በጥቅም የሚራኮቱበትና የማያባራ የጦርነት ቀጠና መሆኑ ነዉ፡፡ ለምሳሌ ሶማሊያ ፤ደቡብ ሱዳን፤የመን ኤርትራ ተጠቃሽ ናቸዉ፡፡ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከወትሮዉ በበለጠና ባልተለመደ ሁኔታ አረብ አገራትም ሆኑ ኃያላኑ መንግስታት ትኩረት አድርገዉ አካባቢዉን ዉጥረት እያነገሱበት መሆኑ ሌላዉ ተጠቃሽ ጉዳይ ነዉ፡፡በዚህ መሰረትም ኳታር፤የተባበሩት አረብ እምሬትስ፤ ሳዉዲ አረቢያ ፤ ግብጽ፤ ኢራን.፡ ኢስራኤል፤ አሜሪካ (ዩ.ኤ.ስኤ.)፣ፈረንሳይ፣ ቻይና.፣ ጃፓን የመሳሰሉ አገሮች በኤርትራ፤ በጂቡቲ፤ በሶማሊያና፤በሶማሌላንድ የጦር ሰፈሮችን በመገንባት አካባቢዉን በወታራዊ ኃይል ለመቆጣጠር እየተሸቀዳደሙ ነዉ፡፡ይህ አጋጣሚ ኤርትራ ካላት መልከአምድራዊ አቀማመጥ ምቹነት ምክንያት ከወትሮዉ በበለጠ ተፈላጊ እያደረጋት ነዉ፡፡ በኤርትራ ዉስጥ በአሰብ አካባቢ የገልፍ ማህበር አባል አገራት አዳዲስ የጦር ሰፈሮችን እያቋቋሙ ያሉትም ከዚሁ ጋር አብሮ የሚታይ ነዉ፡፡

የሶማሊያ የጸጥታ ሁኔታ በተለይ በኢትዮጵያ ብርታት ከፍተኛ መሻሻል የታየበትና የሽብር ቡድኑ የአልሸባብ ተጽኢኖ በእጅጉ እንዲቀንስ ማድረግ የተቻለ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ከአይሲስና አልቃይዳ ጋር በፈጠሩት የትብብር ስምምነት መሰረት አልሻባብ የአካበቢዉ ክንፍ በመሆን በቅንጅት መስራት ስለመጀመራቸዉ እየተናፈሰ ያለዉ መረጃ እዉነት ከሆነ አገራችን ከሶማሊያ ለቃ የምትወጣበትን ጊዜ መገመት እንኳን በሚያዳግት ደረጃ ሊያራዝመዉ ይችላል፡፡ አልሸባብም እንቅስቃሴዉን እንደከዚህ በፊቱ በሶማሊያ ብቻ ሳይገደብ ወደቀጠናዉ ሌሎች አገሮችም የማስፋፋት ዉጥን እንዳለዉ ከተሰማ ወዲህ ኢትዮጵያንም ጨምሮ የአካባቢዉን አገሮች ስጋት ዉስጥ መክተቱ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ሌላ በደቡብ ሱዳንም በርከት ያለ ሰራዊት ማሰማራቷ ተጨምሮበት በሰራዊት አቅሟ ላይ የኃይል መመናመን ማስከተል መቻሉና መንግስትም ሙሉ ትኩረቱን ኤርትራ ላይ ለማድረግ ሲለሚሳነዉ ይህም ሁኔታ ለኤርትራ እንደሚጠቅማት ግልጽ ነዉ፡፡ኤርትራ በሶማሊያና በኦጋዴን የምንቀሳቁትን የሽብር ቡድኖች በጽኑ የመደገፏ ዋና ምክንያትም ኢትዮጵያን በቀጥታ ከመዉጋት ይልቅ በዉክልና በሶስተኛ ወገን በኩል መተግበር እንደሚሻላት በማመኗ ነዉ፡፡

ኤርትራ የአሰብ ወደብንና አካባቢዉን እንዲጠቀሙበት ለተባበሩት አረብ እምሬትስ (UAE) በማከራየቷና ያን ተከትሎም ሳዉድ አረቢያ በአሰብ ላይ ጦር ሰፈር በመመስረቷ ለዚህ ዉሌታዋም ኤርትራ የተንኮታኮተዉን ኢኮኖሚዋን በመደጎም ረገድ ልታገኘዉ የምትችለዉ ጥቅም ከፍተኛ ነዉ፡፡ በቀጥታ በገንዘብ ልታገኝ ከምትችለዉ ገንዘብ ሌላ የሚያስፈልጋትን ያህል ነዳጅ እንደልብ እንድትጋኝ አስችሎአታል፡፡ ኤርትራ ኢኮኖሚዋን የሚደጉም ገንዘብ ስላገኘች ኢትዮጵያ የምትመቀኝበት ወይም የምትቃወምበት አንዳችም ምክንያት የለም፡፡ ችግሩ ግን ኤርትራ የኛን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶችን ለመፈጸም የበለጠ እንድትበረታታ በራስ መተማመን ሊፈጥርላት መቻሉ ነዉ፡፡ እስካሁን ያለዉ ባህሪዋም ይህን ከማድረግ እንደማትቆጠብ የሚያረጋግጥ ነዉ፡፡በዚህ ምክንያትም ጉዳዩን በዝምታ የምናየዉ አይሆንም፡፡በተለይ አንዳንድ አረብ አገሮች አፍንጫችን ስር ጦር ሰፈር መገንባት መጀመራቸዉና የኤርትራን የብስ፤ባህርና አየር ክልል እንደፈለጉ እንዲጠቀሙበት መደረጉ በደህንነታችን ላይ ሊያስከትል የሚችለዉ አደጋ ቀላል አይሆንም፡፡ለቀጠናዉ ሰላምም ጠንቅ ሊሆን ይችላል፡፡

ኤርትራ እሰካሁን በታዛቢነት በምትገኝበት የአረብ ሊግ ሙሉ አባል ለመሆን የማታደርገዉ ነገር የለም፡፡ እንደሚታወቀዉ የአረብ ሊግ በይፋ ከተቋቋመበት ዓላማ ቀስ በቀስ በመዉጣት ራሱን ወደ ወታደራዊ የቃል ኪዳን ድርጅት በመቀየር ወታደራዊ ተጽኢኖዉን ወደ የመንና ወደ አፍሪካ ቀንድ እያሰፋ ይገኛል፡፡ኤርትራም የመንግስታቱ ድርጅት የጣለባትን ማዕቀብ ችላ በማለት በድርጊቷ የቀጠለች ሲሆን ሳዉዲ አረቢያ በየመን እያካሄደች ላለዉ ጦርነት ኤርትራ ከአራት መቶ የሚበልጡ ወታደሮችን በመላክ አጋርነቷን ማሳየቷ ለኛ በበጎ የሚታይ አይደለም፡፡ሳዉዲ አረቢያ እጅግ አምባገነንና ጨቋኝ የሚባል አገዛዝ ያለባት፤አክራሪ የእስልምና ኃይማኖትን በግድ ለማስፋፋት የምትሞክርና ዓለም አቀፍ የሽብር ኃይሎችን፤በማደራጀት፤አክራሪ የእስልምና ሪይተዓለም በማስታጠቅ ፤ጦር መሳሪያና ገንዘብ በገፍ በመስጠት፤ በጥፋት ተልኢኮ በማሰማራት ወዘተ- ለበርካታ የሽብር ድርጊቶች ግምባር ቀደም ተዋናይና አቀነባባሪ እንደሆነች በሚገባ የሚታወቅ ነዉ፡፡ ሳዉዲ አረቢያ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሃ አገሮችን ይቅርና የአሜሪካ መንግስትንም ከመፈታተን አልተቆጠበችም፡፡በ2001 በአሜሪካ (ኒዉዮርክ) የደረሰዉ የ9/11 የሽብር ጥቃት ሙሉ በሙሉ የሳዉዲ አረቢያ እጅ እንዳለበት መረጃዎች ከሰሞኑ ይፋ እያደረጉ ነዉ፡፡ኤርትራም እስካሁን ያቅሟን ያህል በአካባቢዉ የሽብር ድርጊት ሲታቀነባብር መቆየቷ ሳያንስ አሁን ደግሞ ከዋነኛዋ፤ የሽብር ኃይሎች መፈልፈያ ከሆነችዉ ሳዉዲ አረቢያ ጋር የጀመረችዉ አዲስ ዱለታ ለሀገራችን ከፍተኛ ስጋት መሆኑ መቻሉ ጥርጥር የለዉም፡፡ ሳዉዲ አረቢያ የዋሃብዝምን እምነት(wahhabism)በመላዉ ዓለም በኃይል ለማስፋፋት ቆርጣ የተነሳች ሲሆን ሀገራችንም ዋነኛዋ የሳዉዲ ኢላማ እንደሆነች በደንብ የሚታወቅ ነዉ፡፡

የአረብ ሊግ አገሮችም በኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት ላይ ከበፊት ጀምሮ አደጋ ሲፈጥሩ እንደነበር በግልጽ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያን ለመጉዳት በወጭና ገቢ ንግድ አንቅስቃሴ በምንጠቀምባቸዉ ወደቦችም ላይም በተዘዋዋሪ መንገድ በኛ ላይ ተጽኢኖ ከመፍጠር ወደ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ በተለይ ኤርትራ ከ2003 ዓ/ም ጀምሮ የዐረብ ሊግ ታዛቢነት ደረጃ ያላትና ቋሚ አባል ለመሆን እንዲያስችላት የተጠየቀችዉን ሁሉ ከማድረግ የማትጥቆጠብ መሆኗ ሳያንስ የወደብ አገልግሎት የሚሰጡን አገሮችም ከኬንያ በስተቀር የቀሩት በሙሉ ማለትም ጂቡቲ፤ሶማሊያና ሱዳን ሶስቱም የዐረብ ሊግ አባል አገሮች በመሆናቸዉ በዋናዎቹ አረብ አገሮች ግፊት በኢትዮጵያ ላይ እንቅፋት ሊፈጥሩ መቻላቸዉ ሊያሳስበን ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ዋነኛዋ ባለንጣ የሆነችዉ ግብጽም ብትሆን የሊጉ መስራች አባልና የሊጉ መቀመጫም ካይሮ ዉስጥ የሚገኝ መሆኑ ሲታወስ ሁኔታዉ ምቾት የሚሰጥ አይደለም፡፡ እንደሚታወቀዉ ጂቡቲ በ1977፣ ሶማሊያ በ1974 እንዲሁም ሱዳን ከ1956 ጀምሮ የሊጉ አባልት ሲሆኑ ከቀይባህር ወዲያ በቅርብ ርቀት የምትገኘዉ የመንም ሊጉ በ1945ዓ ግብጽ ካይሮ ዉስጥ ሲመሰረት ጀምሮ ከግብጽ፤ ከኢራቅና ከዮርዳኖስ ጋር የሊጉ መስራች መሆን የቻለች አገር ናት፡፡ ሶማሊያ አረባዊት አገር ሳትሆን የሊጉ አባል እንድትሆን የተደረገዉም በግብጽ ግፊት ሲሆን ግብጽ ኢትዮጵያ ላይ ደባ ለመፈጸም ተባባሪ ያስፈልጋት ስለ ነበር ዚያድ ባሬን በማግባበት ያደረገችዉ ነዉ፡፡

ዛሬም ግብጽ ኢትዮዮጵያን በቀጥታ ማጥቃት ሲሳናት እንደ ለመደችዉ ሶማሊያንና ሶማሌላንድን በኢትዮጵያ ላይ ለማስነሳት ከመጣር አልቦዘነችም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነዉ ከሰሞኑ ሞሃመድ እድሪስ በሚባል የግብጽ ዲፕሎማት የሚመራና በብዛት የጦር ጄነራሎችንና አድምራሎችን ያካተተ ቡድን ሶማሊያ ከርሞ መመለሱ ነዉ፡፡ ልኡካን ቡድኑ ግብጽ ሶማሊያን በወታደራዊና ደህንነት ዘርፍ ለማገዝና ማሰልጠኛ ተቋማትንም ለመገንባት እንደምትተባበርና በሶማሊያ በኩል ግን በምላሹ የአየር ኃይል ጣቢያን እንዲሁም በበርበራና በክስማዩ ወደቦችም የባህር ኃይል መደብ ለማቋቋም እንዲፈቀድላቸዉ ያደረጉት አጉል ሙከራና ማግባባት በሶማሊያ ባለስልጣናት በኩል ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም፡፡የግብጽ ፍላጎት በኢትዮጵያ ጥቅምና ደህንነት ላይ ያነጣጠረ መሆኑን የተረዱት የሶማሊያዉ ፕሬዘዝዳንት ለግብጾች አጉል ማግባባት ሳይሸነፉ ሃሳባቸዉን ዉድቅ በማድረግ አሳፍረዉ መልሰዋቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ህዝብ ሰላም ለማስፈን ከማንም የበለጠ ጥረት እያደረገች ያለችና ብዙ መስዋእትነት እየከፈለች መሆኗን ለሚያዉቁት ሶማሊያዉያን ኢትዮጵያን በግብጽ እንደማይለዉጡ በተግባር አሳይተዋል፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ ሳዉዲ አረቢያ የአሰብ ወደብ ላይ ጦር ማስፈሯ ለኛ መልካም ዜና አይመስለኝም፡፡ እነዚህ አሰብን በሊዝ የተከራዩት ኃይሎች ድንገት ከኤርትራ ጋር ወደፊት በሆነ ጉዳይ ወደ ጦርነት ብናመራ ጥቅማቸዉ ላይ ያነጣጠረ አደጋ አድርገዉ በመቁጠር ሊይዙት የሚችሉትን አቋም ለመገመት አያዳግትም፡፡ ኤርትራም ይሄን አስቀድማ አስልታ በዉላቸዉ ላይ እንደቅድሜ ሁኔታ ያስቀመጠቸዉ ወይም ቃል ያስገባችዉ ነገር ሊኖር እንደሚችል መጠርጠር ይቻላል፡፡ የሳዉዲ አረቢያ መራሹ ወታደራዊ ጥምር ጦር በየመን እያደረገዉ ያለዉ ዘመቻን እንደሽፋን በመጠቀም በአካባቢዉ አገሮች ላይ ተጽኢኖን ለማሳረፍ አጋጣሚዉን ከመጠቀም ወደኋላ እንደማይሉ መገመት አይከብድም፡፡ በተለይ ግብጽ የዚህ ቡድን አባል መሆኗ ሳይዘነጋ ኤርትራም ያለ አቅሟ ከማን አንሼ በሚል ለቡድኑ አጋሪነቷን ለማሳዬት ደፋ ቀና እያለች ነዉ፡፡ ኤርትራ ገንዘብ ካገኘች ወታደሮቿን ለአይሲስ እና ለአልቃይዳ ጭምር ድጋፍ እንዲያደርጉ ከመላክ የምትመለስ አይደለችም፡፡ ኤርትራ አሰብ አካባቢ እየተደረገ ያለዉ ያልተለመደ እንቅስቃሴ በኢትዮጵ ደህንነት ላይ ያነጣጠረ እንዳይሆን መንግስታችን ተገቢዉን ክትትል እያደረገ መሆኑ ቢታወቅም ከዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ጎን ለጎን ወታደራዊ አቅምን የማሳደግ ጉዳይ ለአፍታም ችላ ሊባል የሚገባዉ አይደለም፡፡

ይሄ ሁሉ ትርምስ እየተደረገ ያለዉ ትላንት አናንቀን በተዉነዉ አሰብ ላይ መሆኑ ስናወቅ እጅግ መናደዳችን አይቀርም፡፡ ትላንት ያጣጣልነዉና ያናናቅነዉ የባህር በር ጉዳይ ይሄዉ አሁን ጊዜዉ ደርሶ እንደተፈራዉ ችግር ይዞብን እየመጣነዉ፡፡ እኔ በግሌ ስለ አሰብ ጉዳይ ማሰብ መወያየትም ሆነ ጭራሽ ማስታወስ ስለማይመቸኝ “የባህር በር አያስፈልገንም“በሚል ራሴን ለማሳመን ብዙ ብሞክርም ሊሳካልኝ የቻለ አይመስለኝም፡፡ በተለይ ኤርትራ አሰብንና አካባቢዉን ለአረቦች በገንዘብ አሳልፋ መስጠቷን ከሰማሁ ገዜ ጀምሮ በፊት ለመርሳት የሞከርኩት የአስብ ጉዳይ እንደገና ነፍስ እየዘራ ያስቸግረኝ ጀምሮአል፡፡ በርግጥ አሰብን በሚመለከት “የኤርትራን መንግስት አሰብን ለምን ለሌላ አገር አከራያችሁ?”ብለን መጠየቅም መመሪያ ለመስጠትም ስልጣን የለንም፡፡ በአሰብ ጉደይ ላይ ማዘዝ የምንችልበት አንዳችም እድል የለንም፡፡ አርትራ ከፈለገች አሰብን የግመል ዉሃ ማጠጫ ብታደርግ ከልካይ የላትም፡፡ ካሻት ደግሞ አሁን እንዳደረገችዉ በደህና ገንዘብ በሊዝ ማከራየትም አስከነካተዉ መሸጥም መብቷ ነዉ፡፡ ከዛሬ 147 ዓመት በፊት(በ1869) ሱልጣን ኢብራህም ሩባቲኖ ለሚባል የመርከብ ድርጅት እንደሸጠዉ ዛሬም ኤርትራ አሰብን ለሁለተኛ ጊዜ ለሽያጭ ልታቀርብ ትችላለች፡፡ በተለይ እኛን የጎዳች ከመሰላትና በአሰብ ላይ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጥያቄ እንዳናነሳ ለመዝጋት ካሰበች ይህን ከማድረግ እንደማትመለስ ግልጽ ነዉ፡፡ በዓለም አቀፍ ህግ አኳያ ኤርትራ ይህን ለማድረግ የሚከለክላት ህግ ይኑር አይኑር የማዉቀዉ ነገር የለም፡፡ አሰብንም ሆነ ሌላ የራሴ ነዉ የምትለዉን ግዛቷን እንዳዳሻት ለማድረግ የኛን ፈቃድ የመጠየቅ ግዴታ እንደለለባት ግን እረዳለሁ፡፡

አሁን የበለጠ እየተበላሸ ያለዉ ነገር ከዚህ በኋላ አሰብን ገንዘብ እየከፈልንም ቢሆን ለመጠቀም አለመቻላችን ነዉ፡፡ ከዚህ በኋላ ምናልባት ከኤርትራ ጋር በእርቅ ሰላም መፍጠር ብንችል እንኳን አሰብ ወደብን ለመጠቀም ድርድር ማድረግ የሚጠበቅብን ከኤርትራ ጋር ሳይሆን ከአረብ ኤምሬትስ ጋር መሆኑ ነዉ፡፡በደህና ጊዜ ከእጃችን ያመለጠን ነገር ላይ አሁን ብንጸጸት ምንም የምንጨምረዉ ነገር አይኖርም፡፡ ቆቅ ሰድዶ ማሳደድ ዓይነት ነዉ የሆነዉ ነገሩ፡፡ ከዚህ በኋላ በምን ተአምር የባህር በር መብታችንን ማስመለስ እንደምንችል አላዉቅም፡፡ በጦርነት ማድርግ እንደማንችል ግን እርግጠኛ ሆኘ መናገር እችላለሁ፡: ምናልባት በሰላማዊ መንገድ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ከተደረገ ሊሳካ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ግብጽን የመሰለ ስትራቴጂያዊ ጠላታችንን በዓባይ አጠቃቀም ጉዳይ ላይ ማሳመንና ማግባባት የቻለ የኢህአዴግ መንግስት የባህር በር መዉጫ ጉዳይን ለመጨረስ ዘዴ ያጣለታል ብዬ አላሰብም፡፡ በተለይም መንግስት በዉጭዉ ዓለም ያተረፈዉን ተቀባይነትና ከበረታ ለዚህ የተቀደሰ ተግባር ካልተጠቀመበት ትርጉም አይኖረዉም፡፡ እንግዲህ እኔም በወጣነት ዘመነ ለሰባት ተከታታይ ዓመታት በዉትድርና ያገለገልኩባትንና ትዝታዋ እስካሁን ከአይምሮዬ ልፋቅ ያልቻለዉ አሰብን እድሜ ከሰጠኝ በድጋሚ እንደምጎበኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡

4 ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን አድርገን በጋራ መቆም አለብን

ስለቀጣዩ ጦርነት ስናስብ ከሁሉም ነገር ቅድሚያ ሰጥተን መስራት የሚገባን የመንግስትና የህዝብን አንድነት ማረጋገጡ ላይ ነዉ፡፡ ህዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዲያጣ የሚደርጉ ሁኔታዎች ተከታትለን ማስወገድ ይገባናል፡፡በመካከላችንም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አንድ ዓይነት አቋም ላይኖረን ብችልም እንደችግር የሚታይ አይደለም፡፡ለሉአላዊነትና በብሄራዊ ጥቅማችን ጥያቄ ላይ ሲሆን ግን አንድ ዓይነት አቋም መያዝ ሲገባን ተለያይተን ከተገኘን ለጠላት ጥቃት ምቹ እንሆናለን፡፡እስካሁን ያለፍንበት ሁኔታ ሲቃኝ በብሄራዊ ጥቅምና በሉአላዊነት ጉዳይ ላይ መስማማት አቅቶን እርስበርስ እየተቧጭቅን ለጠላት ጥቃት መጋለጣችን የተለመደና አንዱ አሳፋሪ ታሪካችን ነዉ፡፡አገሪቱ በጠላት ወራሪ ሰራዊት ስር ወድቃ እያለም መንግስትን ስለምንጠላዉ ብቻ ከጠላት ጎን እንሰለፋለን፡፡ሰራዊታችንም ተዋግቶ አገሩንና ህዝቡን ነጻ እንዳያወጣ እንቅፋት እንሆናለን፡፡በጣሊያንም ሆነ በሶማሊያ ወረራዎች ወቅት የታዬ መጥፎ ታሪካችን ነዉ፡፡በኤርትራ ወረራ ወቅትም ቢሆን እንደ ሶማሊያዉ ባይሆንም ለሻዕቢያ የሞራል ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ነበሩ፡፡እንዲያዉም አንድን ብሄር ስም በመጥቀስ “ጦርነቱ ስለማይመለከትህ እንዳትዋጋ “እያሉ ዘረኛ ቅስቀሳ ሲደርጉ እንደነበር እናስታዉሳለን፡፡

ዛሬም የሃገራችንን ዉድቀት እዉን ለማድረግ ሃያ አራት ሰዓት እንቀልፍ አጥቶ ከሚሰራዉ ሻዕቢያ ጎን የተሰለፉ የኛዉ ሰዎች አልጠፉም፡፡

በአሁኑ ሰዓት ሁለቱም አገሮች ማለትም ኢትዮጵያና ኤርትራ በጠላትነት ሁኔታ ዉስጥ እንዳሉ እኛ ብቻ ሳንሆን መላዉ ዓለም የሚያዉቀዉ ነዉ፡፡ይህን ሁኔታ የሚቀይር የሰላም ስምምነት ተደርጎ መንግስት በይፋ አስካላስታወቀ ድረስ ማንም በግሉም ሆነ እንደ ድርጀት ከጠላት አገር ከኤርትራ ጋር የሚያደርገዉ የትኛዉም ዓይነት ግኑኝነት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ጦርነት እንዳወጀ ተደርጎ መቆጠር ያለበት ነዉ፡፡ዓላማቸዉ ምንም ይሁን ምን ኢትዮጵያዊ ስም ያላቸዉና በኢትዮጵያ ስም የሚንቀሳቀሱ የትኞቹም ድርጅቶችና ግለሰቦች ጠላታችን ከሆነችዉ ኤርትራ ጋር ግኑኝነት አስካደረጉና ለኤርትራ ጥብቅና በይፋ አስከቆሙ ድረስ ከኤርትራ ለይተን ለማዬት አንገደድም፡፡ ትንሽ ጥቅም ለማግኘት ተብሎ አገርንና ህዝብን ያክል ነገር ከድቶ ለጠላት ድጋፍ ማድረግና በአገር አንድነትና በህዝብ ደህንነት ላይ አደጋ እያደረሰ ካለ ጠላት ጋር መተባበር መወገዝ ያለበት እኩይ ድርጊት ነዉ፡፡ የዛሬ አርባ አመት ግድም የዚያድ ባሬ ሰራዊት ወረራ ፈጽሞብን በጠራራ ፀሃይ ወገኖቻችንን ሲጨፈጭፍና ሰፊ ግዛት ተቆጣጥሮ በነበረበት ወቅት አንዳንዶቻችን ለርካሽ ፖለቲካችንና ለመናኛ ዓላማችን ብለን ሰራዊታችን ጠንክሮ እንዳይዋጋ የተለያዩ ደባዎችን በመፈጸም የወራሪዉን የዚያድባሬን ሰራዊት ስናበረታታ እንደነበር ታሪክ የሚዘነጋዉ አይደለም፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ሰራዊት ጠላቱን አምርሮ እንዳይዋጋ አፍራሽ ቅስቀሳ ከማድረግ ጀምሮ በዉስጡ እየተሸሎኮለኩ ምርጥ ምርጥ አዛዦችንና ተዋጊዎችን እየመረጡ ከጀርባ ተኩሰዉ ይገድሉ እንደነበር እናስታዉሳለን፡፡የገዛ አገርንና ህዘብን መክዳትና ለጠላት መሰለፍ በጣም አስነዋሪና ልናስወግደዉ ያልቻልነዉ መጥፎ ባህሪያችን ሆኖ ቆይቷል፡፡

አሁንም ካለፈዉ ባለመማር ከቀንደኛ ጠላታችን ከኤርትራ መንግስት ጎን የሚቆሙ ኢትዮጵያዉያን ዲያስፖራዎች ጉዳይ እጅጉን ግራ የሚያጋባ ነዉ፡፡ የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላት ከሆነ አገር ጋር እያበሩ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም እየተገልን ነን ማለት ከቶ እንዴት ይቻላል?ኢህአዴግን መቃወማቸዉ ላይ ቅሬታ የለኝም፡፡መብታቸዉ ስለሆነ፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግን ሲለጠሉና በስልጣን ላይ ያለዉ መንግስት ስላልተመቻቸዉ ብቻ የኢትዮጵያ ህዝብ ቀንደኛ ጠላት ከሆነዉ ሻዕቢያ ጋር ማበር ምን የሚሉት ፖለቲካ ነዉ? አንዳንዴ ስለ ኤርትራዉያን ብሄርተኝነትና የሀገር ፍቅር ስሜት ሳስብ እንዳደንቃቸዉ የሚያደረገኝም ከእኛዎቹ ተቃዋሚዎች ሁኔታ ጋር ሳነጻጽር ነዉ፡፡ኤርትራዉያን ስደተኞች እኮ ኢትዮጵያዉያኑ እያደረጉት እንዳለዉ ሳይሆን በሃገራቸዉ ህዝብ ጥቅም ላይ በጭራሽ አይደራደሩም፡፤በዉጭ አገር የሚኖሩ ኤርትራዉያን ስደተኞች የመሰደዳቸዉ ዋናዉ ምክንያት ለስርአቱንና ለአገዛዙን ባላቸዉ ጥላቻ ቢሆንም በአገራቸዉ በኤርትራና በህዝባቸዉ ጥቅም ጉዳይ ሲሆን እንዴት በጋራ እንደሚጮሁ አይተናል፡፡ ሌላዉ ቀርቶ እዚሁ ኢትዮጵያ ዉስጥ እንዲኖሩና እንዲማሩ እድሉን ያገኙ ኤርትራዉያን ስደተኞች ኢትዮጵያ የማይረሳ ዉለታ እንደዋለችላቸዉ ለአፍታም ባይዘነጉም ነገር ግን በሃገራቸዉ ጉዳይ ላይ ግን በጭራሽ አይደራደሩም፡፡ አገራቸዉ የመጨረሻዉ መናጢ ደሃና የኑሮ ዋስትና የለለባት የችግርና የበሽታ ጎተራና አገዛዙም የለየለት ጨቋኝ መሆኗን ቢያዉቁም አገራቸዉን በጭራሽ በጭራሽ አይጠሉም፡፡ በሃገራቸዉ ላይ አያምጹም፡፡ ኢሳይያን ጠልተዉ አገር ለቀዉ ቢሄዱም ኢሳይያስን ለመጉዳት ብለዉ በአገራቸዉ በኤርትራ ላይ ደባ አይሰሩም፡፡በምንም ምክንያት ኢትዮጵያን ከኤርትራ አስበልጠዉ አገራቸዉን እያወግዙም፡፡ከሀገራቸዉ ይልቅ ለኢትዮጵያ ጥቅም ተጨንቀዉ ሰላማዊ ሰልፍ አያደርጉም ወይም ፊርማ የማሰባስብ ስራ ዉስጥ አይገቡም፡፡ የእኛዎቹ ዲያስፖራዎች ሁኔታ ግን ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነዉ፡፡ አገራቸዉን ለማፈራረስ ሌት ተቀን የሚጥረዉንና በሽብር ደርጊቱ ዓለም በሙሉ ያወገዘዉን የሻዕቢያን መንግስት በመደገፍ በአደባባይ ሰልፍ መዉጣትና ፍርማ ማሰባሰብ የጤና አይመስለኝም፡፡

“ዓባይ ላይ ግድብ ለምን ይሰራል?” ብለዉ ከግብጾች የበለጠ የሚጮሁት የኛዉ የራሳችችን ልጆች መሆናችዉን ማሰብ በራሱ በጣም ያሳምማል፡፡ ቀደም ሲልም “ግልገል ግቤ ሶስት” ፕሮጀክት ላይም ሲደረግ የነበረዉን አፍራሽ ቅስቀሳ እናስታዉሳለን፡፡ የሚገርመዉ ዛሬ ኤርትራን መጠጊያ አድርገዉ በኢትዮጵያ ላይ ጦር ለማዝመት ደፋ ቀና የሚሉ ድርጅት አመራሮች ዉስጥ የተወሰኑት ከዛሬ አርባ አመት በፊት የዚድባሬን ወረራ ደግፈዉ ለኢትዮጵያ ዉድቀት ሲሰሩ የነበሩ የአክራሪ ፓርቲዎች አባላት የነበሩ መሆናቸዉ ነዉ፡፡ ዛሬም ያ አመል አልለቅ ብሏቸዉ ከኢሳይያስ ጉያ ተሸጉጠዉ የገዛ ህዝባቸዉን ሰላም ለማናጋት እየተፍጨረጨሩ ነዉ፡፡

ኢሳይያስና የሻእቢያ አመራሮች ለኢትዮጵያ ህዝብ ምን ያህል የከረረ ጥላቻ እንዳላቸዉ እየታወቀ ኢሳይያስን የለለዉን ባህሪይ በማላበስና እንደ ቅዱስ በመቁጠር “ለኢትዮጵያ አንድነት የሚጨነቅ ሰዉ” አድርገዉ በአደባባይ የሚሰብኩ ኢትዮጵዉያን ፖለቲከኞች ሁኔታን ሳስብ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ትልቅ ክህደት እንደፈጸሙ አድርጌ ነዉ የምቆጥረዉ፡፡ ሌላዉ ቢቀር በ83ዓ/ም በፊት በተለያዩ አጋጣሚዎች በዉጊያ ላይ የተማረኩና በኋላም በሰላም እጃቸዉን የሰጡ በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵዉያን ወታደሮች ላይ በሻዕቢያ የተደረገዉን አረመናዊ ጭፍጨፋ እንዴት እንዘነጋለን፡፡ ይህ የሻዕቢያ ድርጊት የናዚ ባለስልጣነት በአሽወትዝ ካደረጉት ዘግናኝ ድርጊት በምንድነዉ የሚለየዉ? እንደገናም በ1990 ዓ/ም ጦርነት ወቅት በመቄለ ምንም በማያዉቁ የአይደር ት/ቤት ህጻናት ላይ በኢሳይያስ ትዕዛዝ የተደረገዉን ጭፍጨፋ እንዴት ተዘንግቶ ነዉ ከኢሳይስ ጋር ወዳጅነት የሚመሰረተዉ፡?ኢሳይያስ እኮ ህጻናቱን አስጨፍጭፎ ሲያበቃ ስለጉዳዩ ሲጠየቅ ለይምሰል እንኳን ይቅርታ መጠየቅ ቀርቶ “ጦርነት ፎርሙላ የለዉም፡፡ ምን ያስደንቃል” በሚል አረመነነቱንና መሃይምነቱን በአደባባይ ያጋለጠ ወንጀለኛን ደግፈዉ ሲሟገቱለት የሰሙ የዉጭ ሰዎችስ እይታዘቡንም እንዴ? የኢትዮጵያ ህዘብንስ ምን ያህል ቢጠሉና ቢንቁ ነዉ ከጠላቱ ጋር ወዳጅነት የሚፈጥሩት?

ይህ የከሃድነት ሁኔታ አንድ በደንብ የማዉቀዉን ሰዉ አስታወሰኝ፡፡ በአንድ ወቅት በሽግግሩ ዘመን አንድ የአማርኛ መጽሄት አዘጋጅ የነበረ፡ከሃዲና መክዳት ልማዱ የሆነ በሚያዘጋጀዉ “ኮከብ”በተሰኘ መጽሄት ርእሰ አንቀጽ ላይ “ለሶማሊያ መፈራረስ ተጠያቂዋ ኢትዮጵያ ነች”ብሎ ያለአንዳች ሃፍረት የገዛ አገሩን በድፍረት ሲወነጅል ነበር፡፡ ይህ ሰዉ እኔ እስከማዉቀዉ ድረስ ከአንድም ሁለት ጊዜ አገሩን የከዳ ሲሆን አሁን ለሶስተኛ ጊዜ ከድቶ አሜሪካን አገር ይገኛል፡፡ አገርን መክዳት እንደ ወንጀል በማይቆጠርበት ዘመን ላይ ያለን ይመስል ይሄዉ ሰዉ ያለምንም ሃፍረት ከአሜሪካ በየዓመቱ እየመጣ “ሀገርን መክዳት የማያስጠይቅና የማያሳፍር እንዲያዉም የሚያኮራ ተግባር“ መሆኑን በተግባር እያስተማረ ይመለሳል፡፡ ሀገሪቱ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ላይ በነበረች ወቅት አገሩን የከዳዊ ይህ የመከላከያ አባልና ከፍተኛ መኮንን ለዚህ ወንጀሉ አስካሁን ማንም የጠየቀዉ የለም፡፡ ለወደፊቱም ሊጠየቅበት ይችላል ብዬ አልገምትም፡፡ በዬትኛዉም አገር በጦርነት ጊዜ ሀገርን መክዳት ከወንጀሎች ሁሉ የከፋና አስከ ሞት የሚያደርስ ቅጣት የሚያስከትል ሆኖ እያለ በኛ አገር ገን ነገሩን ቀለል አደርገን ያየን ይመስለኛል:: የዚህ ዓይነት አሳፋሪ ድርጊቶች የሚፈጽሙትን መጸየፍና ማዉገዝ ሲገባ ለርካሽ ፖለቲካ ትርፍ ተብሎ ከሃዲዎችን ጭራሽ እንደ ጀግና መቁጠር ተጀምሮአል::

አንዳንደ ደግሞ ድክመታችንን ለመሸፋፈን ብለን ሁኔታዎችን ለመደባበቅ እንሞክራለን:: አንዳች ጦርነት በለለበት በሰላም ዉስጥ ሆነን ተራ ወታደርና የበታች መኮንን ብቻ ብቻ ሳይሆን ጄነራልም ሳይቀር ቀንደኛ ጠላታችን ለሆነ አገር አንዳችም ዉጊያ በለለበት ሁነታ እጁን ሲሰጥ እየሰማን ምንም እንዳልተፈጠረ ሆነን ዝም እንላለን፡፡ ይህች ደሃ አገር በሌላት ገንዘብ በሚሊዮኖች በሚቆጠር ዉጭ ምንዛሪ አዉጥታ የገዛችዉን አይሮፕላን ሰርቀዉ ለኢሳይያስ በገጸ በረከትነት ያቀረቡም አሉ:: በአሁኑ ሰዓት በሃገራችን እንደ ደርግ ስርአት በሰራዊቱ ዉስጥ በግድ እንዲያገለግል የሚያስገድድ አሰራር ስለለለ በዉትድርና መቀጠል የማይፈልግ አባል አመልክቶ አሰራሩ በሚፈቅደዉ መሰረት ሲፈቀድለት በሰላም ወደ ቤቱ መሄድ ይችላል፡፡ ይህ እየታወቀ አንዳንዴ እየሆነ ያለዉ ነገር ከዚህ ዉጭ ነዉ፡፡ ከዚህ በፊት በጦር ሜዳ ለሀገራቸዉ ሉአላዊነት ሲዋጉ ድል እምቢ ሲላቸዉ በጠላት እጅ ተማርከዉ ለወገን ማፈሪያ ላለመሆን በገዛ እጃቸዉ ራሳቸዉን የጨርሱ በርካታ ጄነራሎችን ኮሎነሎችን ወታደሮችን ታሪክ አንብበናል፡፡ አሁን ግን የሀገር ፍቅር ስሜት ደብዝዞ፤ ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ሲባል ራስን በመስዋእትነት አሳልፎ መስጠት እንደሞኝነት ተቀጥሮ፤ በምትኩ ለርካሽ ፖለቲካና ጠባብ አጀንዳ ተብሎ አገርንና ህዝብን መክዳት እንደ ቀላል ነገር የተቆጠረ ይመስላል፡፡ ክቡር የሆነዉን ሙያቸዉንና ምትክ የለለላት ሀገራቸዉን በሰበብ አስባቡና በማይረባ ምክንያት ጣጥለዉ ይሄዳሉ፡፤ እንደዚህ ዓይነት አስነዋሪ አጋጣሚዎች የሚከሰቱት አልፎ አልፎ ቢሆንም ስንሰማ ግራ መጋባታችን ሆነ ማዘናችን አይቀርም፡፡ለመሆኑ የሰራዊታችንን የሀገር ፍቅር ስሜት እንዴት ነዉ እየገነባን ያለነዉ?በዚህ ላይ ብዙ ማለት ቢቻልም ቦታዉ ስላልሆነ የሚመለከተዉ አካል ራሱን እንዲፈትሽ በማሳሰብ ብቻ ወደ ሌላ ጉዳይ ለማለፍ እወዳለሁ፡፡

5.ኤርትራ ዳግመኛ የስጋት ምንጭ እንዳትሆን ማድረግና አገዛዙን በኃይል የመቀየር ተገቢነት ጥያቄ

ከኤርትራ ጋር ከዚህ በኋላ በድጋሚ ወደ ጦርነት የምንገባ ከሆነ ኤርትራ ዳግመኛ እንዳይለምዳት ማድረግ አለብን የሚሉ አስተያየቶች በስፋት እየተደመጡ ነዉ፡፡የመንግስት ባለስልጣናት፤ሲቪል ፖለቲከኞች ፤ምሁራን ፤ወጣቶች ፤ሌላዉ ቀርቶ በጡሬታ ላይ የሚገኙ ከፍተኛ የጦር አዛዦች ሁሉ ሳይቀሩ ተመሳሳይ አስተያዬት አንብበናል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በኤርትራ ድርጊት ምን ያህል እንደተማረሩና ከድርጊቷ እንድትቆጠብ ለማድረግ በጋራ ለመሰለፍ ቆርጠዉ መነሳታቸዉን እያየን ነዉ፡፡ ኤርትራን ከድርጊቷ እንድትቆጠብ ማድረጉ ላይ ልዩነት ባይኖርም እንዴት ነዉ ይሄንን እዉን ማድረግ የሚቻለዉ የሚለዉ ላይ ግን በደንብ መነጋጋር የሚያሻ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይም በህትመት ዉጤቶች ብቻ ሳይሆን በኢንተርነት በሚሰራጩ ማህበራዊ የዉይይት ገጾች ሁሉ በስፋት ስንሸራሸር የነበረዉናእንደ መፍትሄ ከተሰጡ አስተያየቶች ዉስጥ ጎልቶ የታዬዉና አወዛጋቢም የሆነዉ የኤርትራን አገዛዝ እሰከ ማዉረድ የሚደርስ እርምጃ መዉሰድ አለብን የሚለዉ ነዉ፡፡ ኤርትራ ጦርነት ከቆሰቆሰች ብቻ ሳይሆን በራሳችን ተነሳሽነትም ቢሆን ወደ ጦርነት ገብተን የኤርትራን ሰራዊት በመደምሰስ አገዛዙን ማስወገድ አለብን የሚሉ ብዙ ናቸዉ፡፡ የዚህ ዓይነት አስተያት እየሰጡ ያሉት የኤርትራ ትንኮሳ ስላስመረራቸዉ አገዛዙን አስወግደን መገላገል አለብን የሚል መነሻ ያለዉ መሆኑ ግልጽ ነዉ፡፡

አስተያዬት ሰጪዎቹ የኤርትራን አገዛዝ በኃይል ለማዉረድ የኤርትራን ሕዝብፈቃድ ወይም ይሁንታ (consent) እንዲሁም የመንግስታቱ ድርጅትን(UN)ስምምነት በቅድሚያ ማግኘት እንደሚገባን ሳይረዱት ቀርተዉም አይመስለኝም፡፡ ምናልባት የኤርትራ ህዝብ ከሻዕቢያ አገዛዝ ብንገላግለዉ ስለማይጠላ ድጋፉን እንደማይነፍገን በማሰብ እንደዚሁም የመንግስታቱ ድርጅትም ሃሳባችንን ሊደግፍ እንደሚችል እርግጠኛ ሆነዉ ከሆነ ሀሳቡ አይከፋም፡፡እንደ እኔ አስተሳሰብ ግን የኤርትራ ህዝብ “ኢሳይያስን አስገወዱልኝ” ብሎ በይፋ ጥያቄ ቢያቀርብልን እንኳን ይህን ማድረግ አይደለም፤ ማሰብ እንኳን የሚገባን አይመስለኝም፡፡ የሌላን አገር መንግስት ስለጠላነዉና አምባገነን ስለሆነ ብቻ ጦር አዝምተን በኃይል ከስልጣን የማዉረድ መብት ያለን አይመስለኝም፡፡ አምባገነን ናቸዉ ተብለዉ የተፈረጁ አገዛዞች በዉጭ ኃይሎች ጣልቃገብነት ከስልጣን እንዲወርዱ በተደረገባቸዉ እጅግ በርካታ አገሮች አምባገነን ነዉ የተባለዉ አገዛዝ ከተወገደ በኋላ የተፈጠረዉን ምስቅልቅል ሁኔታ ካልዘነጋን በስተቀር ወደዚህ ዓይነት ዉስብስብ ሁኔታ ዉስጥ መግባት የሚገባን አይመስለኝም፡፡ ዛሬ የኤርትራ ህዝብ ኢሳይያስን ብናስወግድለት ለጊዜዉ ሊያመሰግነን ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን የኢሳይያስን መዉርድ ተከትሎ ሊፈጠር የሚችለዉን ስለማናዉቅ ድንገት ችግር ቢፈጠር ህዝቡ እኛን እንደ ጠላት ነዉ የሚቆጥረን፡፡ የኤርትራ ህዝብ የፈለገዉን ያህል አገዛዙን ቢጠላም በዉጭ ጦር ጣልቃገብነት ኢሳይያስ ከስልጣን እንዲወርድ የሚፈቅድ አይመስለኝም፡፡

ከዚህም ሌላ ይህንን ስራ መስራት የሚገባቸዉ ከዚያዉ ከህዝቡ መካከል የወጡ ኤርትራዉያን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸዉ፡፡ እነሱ ሊሰሩት ያልሞከሩትን ስራ እኛ እነሱን ተክተን ለመስራት ማሰብ የለብንም፡፡ ዋናዉ ጥያቄ ሻዕቢያን በመደምሰስ አገዛዙን ከስልጣን ማዉረድ በተግባር “ይቻላል! ?አይቻልም!? “የሚል አይደለም፡፡ እያልኩ ያለሁት ይህን ማድረግ የሚቻልና የማይሳነን ቢሆን እንኳን ማድረግ የለብንም ነዉ፡፡ የኤርትራን ህዝብ ለመብቱ መታገል የማይችል አድርገን መቁጠርም የለብንም፡፡ህዝቡ ታግሎ የሚያታግለዉ ፤አመራር የሚሰጠዉና የሚያስተባብረዉ የተደራጀ ኃይል ወይም ድርጅት ነዉ ያጣዉ፡፡ምናልባት በተዘዋዋሪ መንገድ ከኛ የሚፈለግ እገዛ ካለ ማሰቡ አይከፋም፡፡ከዚያ ዉጭ ግን ሰራዊት ልኬን አጋዛዙን አዉርደን ስልጣን እንካችሁ ብንላቸዉ እንኳን የኤርትራ ህዝብ ሆነ ብለን እንዳዋረድነዉ ነዉ ሊቆጥር የሚችለዉ፡፡እንዲያዉም ስለዚህ ጉዳይ ማሰብ ራሱ ተገቢ አይመስለኝም፡፡መንግስታችን የዚህ አይነት ምክር ከሚሰጡ አጉል መካሪዎች መጠንቀቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡ምናልባት የኤርትራ ጉዳይ እጅግ አድርጎ ስለአማረረን ከሆነ በስሜት ተገፋፍተን ከማንወጣዉ ችግር ዉስጥ ከመግባት ሌሎች አማራጮችን መፈለግ የተሻለ ይመስለኛል፡

የአስመራን አገዛዝ በኃይል ከስልጣን ማዉረድ ይገባል የሚሉ ሰዎች አንዳንዴ ከወታደራዊ ኩዴታ ጋር ያደበላልቁታል፡፡ኢትዮጵያ በምን ዓይነት ተአምር ነዉ አስመራ ዉስጥ ኩዴታ አድርጋ ኢሳይስን ከስልጣን ማዉረድ አለባት ተብሎ የሚታሰበዉ?ይሄ አስተያዬት ኦዛን ባሮል (Ozan O. Varol) የተባለዉ የሕግ ምሁር ስለ ዲሞክራሲያዊ ኩዴታ ካቀረበዉ ትንታኔ በመነሳት የተሰጠ አስተያየት ይመስላል፡፡ በኛ ሁኔታ ይሄ ንድፈ ሃሳብ የሚሰራ አይመስለኝም፡፡ምክንያቱም ቫሮል ስለዲሞክራሲያዊ ኩዴታ(democratic coup d’état )ያወሳዉ እዚያዉ በስርአቱና በሀገሬዉ መንግስት መዋቅር ዉስጥ ባለ የመንግስት ወታደር ስለሚደረግ ኩዴታ እንጂ ከዉጭ በሚመጣ ኃይል አይደለም፡፡ ዲሞክራሲያዊ ኩዴታ በስልጣን የባለገ አገዛዝን የህዘብን ብሶት ምላሽ ለመስጠት ተብሎ የመንግስት ወታደሮች አገዛዙን በኃይል ከስልጣን በማዉረድ አስፈላጊዉን የሽግግር ሂዴት (በአብዛኛዉ ለሁለት ዓመት)በኋላ ስልጣን በህዝብ ለተመረጠ አካል አስረክበዉ ወደ ጦር ካምፓቸዉ የሚመለሱበት ክስተት ነዉ፡፡ ይህ ሁኔታ በተለያዩ ጊዜያት በግብጽ፤ በቱርክ፤ በፖርቱጋል ተከስቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ዋናዉ ጉዳይ ለኤርትራ ችግር ፍቱን መድሃኒቱ ኩዴታ ነዉ ከተባለም አገዛዙን በኩዴታ ለማዉረድ የሚችሉት የኤርትራ ወታደሮችና ሲቪሎች እንጂ የኢትዮጰያ መንግስት አይደለም፡፡

ሌላዉ ከዚህ ለየት ባለ ሁኔታ ሊጠቀስ የሚችለዉ የአሜሪካ መንግስት የስለላ ድርጅት(CIA ) በተደጋጋሚ ሲያደርግ እንደነበረዉ አሜሪካ ያልጣማትን ወይም ወዳጅ ያልሆነ መንግስታት (non friendly state)መሪዎችን መወገድ አለበት በሚል የበርካታ አገራት መሪዎችን ከስልጣን ያስወገደችበት አግባብ ነዉ፡፡ለአሜሪካ መንግሰት ምቾት የማይሰጥ በመሆኑ ብቻ እንደጠላት ተቆጥሮ እንዲወገድ የተፈረደበትን መንግስት የሀገሪቱ ህዝብ ይደግፈዋል ወይንም አይደግፈዉም የሚባል ነገር የአሜሪካ ችግር አይደለም፡፡ ከስልጣን ለማዉረድ ለአሜሪካ ጥቅም የማይመች ሰዉ መሆኑ ብቻ በቂ ነዉ፡፡አሜሪካ አገዛዙን ከስልጣን በሃይል ለማስወገድ ስታስብ በቅድሚያ ቦታዉን የሚረከብ የነሱ ደጋፊ የሆነ አንድ አሻንጉልት ሰዉ በማዘጋጀትና አስፈለላጊ ሁኔታዎችን በቅድሚያ በማመቻቸት ነዉ፡፤ ይህን ለማድረግ የተቀናጁ ስራዎችን መስራትና ለዚሁ ተብሎ በርካታ ገንዘብ መመደብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በእኛ በኩል ግን የዚህ ዓይነት ዉስብስ ሴራ ለማዉጠንጠን አቅሙም ልምዱም የለንም፡፡እኛ እኮ የራሳችንን አንድ አምባገነን መሪ መንግስቱ ኃይለማሪምን ለማስወገድ ተብሎ በሀገሪቱ የነበሩ ጄነራሎች ሁሉ የተሳተፉበትና የደህንነት መስሪያ ቤቱ ኃላፊ ሳይቀር ድጋፍ ባደረገበት ሁኔታ አንድ መንግስቱን ማዉረድ ተስኖአቸዉ ከሰላሳ በላይ ምርጥ ጄነራሎች ለሞት የተዳረጉባት አገር ናች፡፡ እንዴት አድርገንስ ነዉ በሰዉ አገር ዉስጥ መዋቅሩን ሰብረን ገብተን ወታደሩን አሳምነን ኢሳይያን ከስልጣን የምናወርደዉ?የዚህ ዓይነት ድርጊት መሞከራችን በራሱ ለሃገራችን የባሰ መዘዝ ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ የኩዴታ ሴራ ዉስጥ መግባት ቀርቶ ማሰብ ራሱ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ምናልባት የኤርትራ ህዝብ ስምምነት ወይም ፈቃደኝነት (consent)ቢኖር እንኳን ራሳቸዉ የኤርትራ ፖለቲከኞች ሃላፊነት ወስደዉ እንዲሰሩ ከጀርባ ሆኖ የተወሰነ ድጋፍ መስጠት ይቻል ይሆናል፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ኢሳይያስን ከስልጣን ለማዉረድ ብለን አስመራ ቤተመንግስትን መቆጣጠር ወይም ወታደራዊ ኩዴታ ማዉጠንጠን አይኖርብንም፡፡ አሜሪካ በፓናማ ያካሄደችዉን ዓይነት ዘመቻ እኛም እንድናደርግ ማሰብ የለብንም፡፡ አሜሪካ በ1989 ዓ/ም ሉአላዊቷን አገር ፓናማን ሃያ ምስት ሺህ በሚበልጥ ወታደር በመዉረር የሀገሪቱን መሪ ማኑኤል ኖርዬጋን በሰንሰለት አስራ አሜሪካ ድረስ በመዉሰድ ለፍርድ አቅርባ 40ዓመት እንዳስፈረደችበት እናስታዉሳለን፡፡

እኛም ከዚህ ታሪክ ጋር በሚመሳሰል መልኩ ኢሳይስን ከስልጣን አዉርደን ከዚያም ያለ አንዳች ሥራ ለዓመታት እዚህ ሲያዉደለድሉ ለከረሙ የኤርትራ ተቃዋሚ ነን ባይ ፖለቲከኞች የአስመራዉን ቤተመንግስቱ አስረክበን….. የምንወጣበት ሁኔታ ቀልድ ነዉ የሚመስለኝ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ቀልደኛ አስተያቶች በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በብዛት እየወጡ ነዉ፡፡ የኤርትራን መንግስት በኃይል የመገልበጡ ጉዳይ ለቀልድ የተነገረ ሳይሆን የምር መሆኑን የተረዳሁት ግን ሃላፊነት ከሚሰማቸዉ አንዳንድ ሰዎች ተመሳሳይ አስተያየት ሲሰጡ በማንበቤ ነዉ፡፡በተለይም “ኢሳይያስን በኃይል ከስልጣን ማዉረድ ይቻላል ማለት ነዉ?” ብዬ እንዳዲስ ራሴን እንድጠይቅም ያደረገኝ እጅግ አድርጌ የማከብራቸዉን የድሮ አለቃዬ የነበሩትን የጄ/ል አበበን (ጆቤ) አስተያዬት ካነበብኩ በኋላ ነዉ፡፡አሳቸዉ ቀልደኛ እንዳልነበሩ በሀገር ጉዳይ ላይ ለመቀለድ ጊዜ እንዳልተረፋቸዉ ስለማዉቅ እንደ ሌሎች አስተያዬቶች የሳቸዉን አሰተያዬት ችላ ብዬ ማለፍ አልፈለኩም፡፡

ሜ/ጄል አበበ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ስለዚሁ ጉዳይ ተጠይቀዉ በሰጡት ምላሽ የሻቢያን አመራር አስከ መቀዬር ሊደርስ የሚችል እርምጃ መዉሰድ እንደሚገባ አቋማቸዉን ገልጸዋል፡፡ ጆቤ ይሄንን ያሉበት ምክንያት የኤርትራ ተደጋጋሚ ትንኮሳና ለሽብር ኃይሎችን መጠጊያ በመስጠት፤ በማሰልጠንና በእኛ ላይ በማዝመት ለደህንነታችን ቋሚ የሥጋት ምንጭ በመሆኗ ይሄ የሻዕቢያ ድርጊት ስላበሳጫቸዉ የገለጹት ይመስለኛል፡፡ ኤርትራን አገዛዝ በኃይል የማዉረድ ጉዳይ የጆቤ ብቻ ሳይሆን ብዙዎቹ ኢትዮጵያዉያንም የሚጋሩት ነዉ፡፡ ኢትዮጵያዉያን ያልሆኑ ፖለቲከኞችም ከዚህ ሃሳብ ጋር የሚስማማ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ ጆቤ እንዳሉትም እኔም ቢሆን የሻዕቢያ ስርአት ተቀይሮ ለማዬት ጽኑ ፍላጎት ብኖረኝም ነገር ግን በኃይል መንገድ(በጦርነት) ለዚያዉም ኢትዮጵያ እጇን አስገብታ መሆን አለበት ብዬ ግን አላስብም፡፡ ለኤርትራ ህዝብም ሆነ ለኛ ሰላም ሊመጣ የምችለዉ የኢሳይያስ አገዛዝ ሲወገድ መሆኑ ላይ ቅንጣት ጥርጣሬ ባይኖረኝም ነገር ግን በጦርነት ፡በወረራ ወይም በማንኛዉም ሌላ የኃይል መንገድ እኛ በቀጥታ እጃችንን አስገብተን አገዛዙን ማዉረድ አለብን ብዬ አላስብም፡፡ ይህንን ስራ በተሻለ ሊሰሩት የሚችሉት ኤርትራዉያን ናቸዉ፡፡ ኤርትራዉያን ራሳቸዉ ኃላፊነቱን ወስደዉ መስራት የሚገባቸዉ ሲሆን በእኛ በኩል ከጀርባ ሆነን በምክር ከማገዝና በርቀት ሆነን ከማቀነባበር ያለፈ ሚና ይኖረናል ብዬ አላብም፡፡ እኛ አሜሪካኖች አይደለንም፡፤ እነሱ አንደሚያደርጉት ወዳጅ ያልሆኑ መንግስታትን (non-friendly states/non-cooperating states)ከስልጣን ለመዉረድ የሚያበቃን አቅም የለንም፡፡

ስለመጭዉ የኢትዮጵያ ኤርትራ ጦርነትነና ተያያዥ ጉዳዮች ኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የዉጭ ሰዎችም በስፋት አስተያየት መስጠታቸዉ አልቀረም፡፡አብዛኛዎቹ በዉጭ ሰዎች እየተሰጡ ያሉት አስተያቶች እዚህ በኛዉ ሰዎች እየተሰጠ ካለዉ አስተያየት ጋር መመሳሰሉ ለእኔ አስገራሚ ነዉ፡፡የዉጭዎቹ አስተያየት ሰጪዎች ቀጣይ ጦርነት የማይቀር መሆኑን ከመግለጽ አልፈዉ ዳግመኛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ አትዮጵያ በአጭር ጊዜ ዉስጥ አስመራን በመቆጣጠር አገዛዙን ከስልጣን ከማዉረድ አትመለስም እያሉ ነዉ፡፡አንዳንዶቹማ ጭራሽ ከአራት አስከ ስድስት ሳምንታት ባልበለጠ አጭር ጊዜ ዉስጥ ኢትዮጵያ የኤርትራን ዋና ከተማ አስመራን መቆጣጠር እንደምትችል አርግጠኝነት በተላበሰ መንፈስ ትንተና እያቀረቡ ነዉ፡፡እኛ የፈለግነዉን አስተያየት ብንሰጥ የራሳችን ጉዳይ ስለሆነ ነዉ፡፡እነዚህ የዉጭ ሰዎች ስለ ኢሳይያስ ከስልጣን መወገድ ደጋግመዉ ደጋግመዉ የሚጽፉት ለምንድነዉ? ምናልባት ይሄንን ነገር እንድናደርግ በዜደ እየገፋፉን ይሁን? ምናልባትም ደግሞ እንዲሆን የሚመኙትን እዉን ሆኖ ለማዬት ስለፈለጉ ይሁን? የኢሳይያስ ጉዳይ ከኛ በላይ አሰጨንቋቸዉ ከሆነ ኢሳይያን ከስልጣን ለማዉረድ እኛን በዜደ ከሚገፋፉን እነሱ ራሳቸዉ ለምን እንደማያደርጉት ሊገባኝ አልቻለም፡፡ምናልባት ይሄን ነገር ቢታደርጉት የአለም ማህበረሰብ አይቃወማችሁም፡፡እንዲያዉም ድጋፍ ይሰጣችኋል እያሉን ይሁን ?ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ኤርትራዉያንና አፍቃሪ-ኤርትራ የሆኑ አትዮጵዉያን “ኢትዮጵያ ኤርትራን ለመዉረር እየተዘጋጀች ነዉ“ በሚል መጮህ ያበዙት ፡፡

የኢሳይያስን አገዛዝ በኃይል ማዉረድ ይቻላል /አይቻልም የሚለዉን ሙግት ለጊዜዉ ትተን አገዛዙን በሆነ መንገድ ተሳክቶልን ከስልጣን ማስወገድ ብንችል እንኳን የኢሳይያስን መወገድን ተከትሎ በሚፈጠረዉ የስልጣን ክፍተት ኢትዮጵያ ለጊዜዉ የተወሰነ እፎይታ እንድታገኝ ያስችላት ይሆናል፡፡ነገር ግን በሚፈጠረዉ የአመራር ክፍተት አጠቃላይ መመሰቃቀል ሊፈጠር ስለሚችል ከኤርትራም አልፎ ለራሷ ለኢትዮጵያም ሆነ በአካባቢዉ (ቀጠናዉ)ላይ አለመረጋጋትና የደህንነት ስጋት ሊፈጥር ይችላል፡፡የኢትዮጵያ መንግስትም ይህን ተጠባቂ ሁኔታ ከግምት በማስገባት በኢትዮጵያ “መሽጎ” የሚገኘዉን የኤርትራ ተቃዋሚ አንጃ ስብስብ የሆነዉ ድርጅት(Eritrean Democratic Alliance) አባል የሆኑ ድርጅቶች የዉስጥ አለመግባባታቸዉን ወደ ጎን አድርገዉ አንድነት በመፍጠር ይህን ከፍተት እንዲሞሉ ማድረግ ይገባል፡፡የእነዚህ ድርጅቶች ሁኔታ ግን በቅርበት ሲጤን እርስበርስ ስምምነት የጎደለቻዉና ከሀገራቸዉ ህዘብ ጋርም አንዳችም የትግል ቁርኝት የለላቸዉ ፤በኤርትራ ባለዉ ወቅታዊ ሁኔታ ላይም ባይተዋር የሆኑ ስለሆነ ብዙም እምነት የሚጣልባቸዉ አይደለም፡፡ እነሱ ታግለዉ ማምጣት የሚገባቸዉን ስራ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲሰራላቸዉ ይፈልጋሉ፡፡ስልጣን ለመረከብ ያለስራ ለዓመታት ተጎልተዉ የተቀመጡትን እነዚህን ደርጅቶች ኢትዮጵያ መንግስት ካሁኑ ማጠናከር ይጠበቅበታል፡፡በሌላ በኩል እነዚህ ኢትዮጵያን መጠጊያ አድርገዉ የተቀመጡ ኃይሎች በኤርትራ ህዝብ ዘንድ ምን ያህል ተአማንነትና ተቀባይነት አላቸዉ የሚለዉ ጥያቄም መልስ የሚሻ ነዉ፡፡እነዚህ ተቃዋሚዎች ስልጣን ለመያዝ እድል ቢያገኙ ለኤርትራ ህዝብ የተሻለ ለዉጥ ሊያመጡ ይችላሉ ብሎ ለመገመትም አዳጋች ነዉ፡፡በተጨማሪም ድርጅቶቹ ዛሬ በስልጣን ላይ ካለዉ የሻእቢያ አገዛዝ ባልተለየ ሁኔታ ለኢትዮጵያ መልካም ያስባሉ ብሎ መጠበቅ አይቻልም፡፡ በኤርትራ ኢሳይያስን መወገድ ተከትሎ ሊመጣ የሚችል ሰላምና መረጋጋት ምን ያህል እንደሆነ አሁን ላይ ሆኖ መገመት ያዳግታል፡፡ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ በሶማሊያ ጊዜያዊ ሽግግር መንግስት ያለፈና የአሁን ሁኔታ ትልቅ ትምህርት ያገኘች ይመስለኛል፡፡ የሶማሊያ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ያ ሁሉ በርካታ አለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ድጋፍ እየጎረፈለት እስካሁንም ራሱን ችሎ መቆም አለመቻሉ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነዉ፡፤ስለዚህ በኤርትራም ከኢሳይያስ ዉድቀት በኋላ የተረጋጋ ሁኔታ ይፈጠራል ብሎ ለማሰብ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ የኤርትራን አገዛዝ ከስልጣን ለማዉረድ ፍላጎቱ ካላት በቅድሚያ ለዚህ እርምጃዋ ጠንካራ አለምአቀፍ ድጋፍ መኖሩ ላይ እርግጠኛ መሆን ይገባታል፡፡ አለምአቀፉ ማህበረሰብ ኤርትራ ላይ ማእቀብ መጣሉና ኤርትራም በብዙ ነገር እንዲትገለል መደረጓ እንዲሁም አሜሪካ ኤርትራን በክፌ ዓይን ማየቷ፣ ይህ ሁሉ ሁኔታ ግን ኢትዮጵያ ኤርትራን እንድትወር ፈቃድ እንደመስጠት ተደርጎ የሚቆጠር አይደለም፡፡ኢትዮጵያ ይህንን ማድረግ ካለባትም በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ግፍትና ለአሜሪካ ፍላጎት ተብሎ መሆን የለበትም፡፡ኢትዮጵያ ኤርትራን በሚመለከት የምትወስደዉ አቋም ለራሷ ብላ ማድረግ ያለባት እንጂ የአሜሪካና መሰሎቿን ፍላጎት ለማስፈጸም ተብሎ መሆን የለበትም፡፡በመጀመሪያ ነገር እኛ የማንንም ሌላ አገር ጥቅም ለማስጠበቅ ብለን ችግር ዉስጥ መግባት ያለብን አይመስለኝም፡፡ሁለተኛ በአሜሪካ ግፊትና አይዞባይነት አንዳችም ቀዉስ ዉስጥ መግባት የለብንም፡፡ አሜሪካ ኢትዮጵያን በሚመለከት ስትከተለዉ የነበረዉ የዉጭ ግኑኝነት ፖሊሲ ሁልጊዜም ቋሚ ያልሆነና በማንኛዉም ጊዜ መልኩን ሊቀየር እንደሚችል የሁለቱ አገሮች ግኑኝነት የኋላ ታሪክ በሚገባ ያስታዉሰናል፡፡አሜሪካ በማንኛዉም ሰዓት ፊቷን ወደ ኤርትር ልታዞር እንደምትችል መጠርጠር ይገባናል፡፡ ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽኑን ዉሳኔ በሚመለከት የያዘችዉ አቋምና አሜሪካ ሁኔታዉን በዝምታ ያለፈችበት ምክንያት፤ነገና ተነገ ወዲያ ግኑኝነታችን በሆነ መንገድ ቢሻክር አሜሪካ በኛ ላይ ምን አቋም ልትወስድ እንደምትችል እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም፡፡

ቢያንስ ካለፉ ተሞክሮ በመነሳት የአሜሪካ ወዳጅነት በማንኛዉም ጊዜ ሊለወጥ እንደሚችል መጠርጠሩ ተገቢ ነዉ፡፡ አለምአቀፍ ሽብርተኝነትን በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በመዋጋት ረገድ አሜሪካ ኢትዮጵያን ቁልፍ ስትራቴጂያዊ አጋሯ(key strategic partner) ማድረጓ እየታወቀ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት በሽብርተኝነት የፈረጃቸዉን እነ ኦነግ አብነግና አርበኞች/ ግንቦት ሰባትን ወዘተ አሜሪካ አስካሁን በሽብርተኝነት ጎራ ለመመደብ አለመፈለጓ ብቻ ሳይሆን በሀገሯ ህጋዊ ቢሮ እንዲከፍቱና የገንዘብና ማሰባሰብና የጦርነት ቅስቄሳ ስራ በይፋ እንዲሰሩና የሬዲዮና ቴሌቭዝን ጣቢያ ሁሉ እንዲከፍቱ መፍቀዷ ሲታይ የአሜሪካ ወዳጅነት አስተማማኝ እንዳልሆነ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም፡፡ስለዚህ በወታደራዊ ኃይል በኤርትራ ያለዉን ስርአት እንድንቀይር መንግስትን የሚገፋፋ ወገኖች አሜሪካንን ድጋፍ ከግምት በማስገባት ወይም አሜሪካንን በመተማመን ከሆነ ሃሳባቸዉን እንደገና ቢያጤኑት ይገባል፡፡የኤርትራ አገዛዝ ጠንቅነቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንዲያዉም ከሁሉም በላይ ለአካባቢዉ(ሪጅን) ጭምር በመሆኑ የአስመራን አገዛዝ ለመጣል ኢትዮጵያ በብቸኝነት ሃላፊነት የምትወስድበት ምክንያት አይኖርም፡፡ምናልባት ኤርትራ በቀጥታ ወረራ በማድረግም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድና በእጅ አዙር በእኛ ላይ የምታደርገዉን ትንኮሳ ለመከላከል ለአፍታም ችላ ማለት እንደለለብን ግልጽ ነዉ፡፡ለዚህም የማንንም አርዳታ ሳያሻን እኛዉ ብቻችንን የምንወጣዉ ይሆናል፡፡ከዚያ ባለፈ ግን አገዛዛን/ ስርአቱን የመቀየር ጉዳይ ከተነሳ የኢትዮጵያ ብቻ ሃላፊነት ሳይሆን ሌሎች የሚመለከታቸዉ አገሮች ሁሉ በአፍሪካ ህብረትም ሆነ በመንግስታቱ ድርጅት ማንዴት ጣልቃ በመግባትና መተግበር ያለባቸዉ ነዉ፡፡ቢያንስ አሜሪካ በተለያዩ ዘመናት ከስልጣን በኃይል ካወረደቻቸዉ አምባገነን መሪዎች ይልቅ የኤርትራዉ አገዛዛ እጅግ የከፋ እንደሆነ ስለምትረዳ ሃላፊነቱን ወስዳ እርምጃ መዉሰድ ይኖርባታል ብየ አስባለሁ፡፡

ለነገሩ የኤርትራ አገዛዝ የኛ አንዳችም ተሳትፎና ጣልቃገብነት ሳያስፈልግ በራሱ ጊዜ እየወደቀ እንደሆነ እያየን ነዉ፡፡የኤርትራ መንግስት በብዙ ችግሮች ተቀፍድዶ ያለ በመሆኑ ኢትዮጵያ አንድም ጥይት ሳትተኩስ፤ አንድም ኃይል መጠቀም ሳያፈልጋትና ኤርትራ ላይ ወረራ ሳታደርግ ትንሽ ብቻ መታገስ ከተቻለ የኢሳይያስ አገዛዝ በራሱ ጊዜ በቅርብ ጊዜ ሊወድቅ እንደሚችል ይታመናል፡፡ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት በወታደራዊ ኃይል ኤርትራን አገዛዝ ለመጣል ፈጽሞ ማሰብ አይኖርበትም፡፡እንዲያዉም ኢሳይስ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን ከኛ በላይ የሚፈልጉትና ሁልጊዜም የሚመኙት ጉዳይ ነዉ የሚመስለኝ፡፡ምክንያቱም የመላዉ ኤርትራዉያንን ልብ ለመግዛትና ከጎናቸዉ ለማሰልፍ የሚያስችላቸዉ ትልቅ አጋጣሚ አድርገዉ ስለሚቆጥሩ ነዉ፡፡ኤርትራዉያን በኢሳይያስ አገዛዝ የቱንም ያህል ቢሰላቹም ቀንደኛ ጠላታቸዉ የሆነችዉ ኢትዮጵያ በጦር ኃይል ኤርትራን ተቆጣጥራና መሪያዉንና አገዛዙን ከስልጣን ለማዉረድ ስትሞክር ዝም ብለዉ ያያሉ ብሎ ማሰብ ሞኝነትነዉ፡፡

የኤርትራ መንግስት ህዝቡን ከአገዛዙ ጎን በአንድነት ለማቆም ሁለት መግፋኢ ሁነቶችን (motivation) በቀላሉ እየተጠቀመ ነዉ፡፡አንደኛዉ”በህግ የተፈረደልንን መሬታችንን በኢትዮጵያ እምቢተኝነት ምክንያት ተከልክለናል፡፡“ የሚለዉ አንዱ ነዉ፡፡ በዚህም ኢሳይያስን የማይደግፉ ወገኖችም ጭምር በቁጭትና በእልህ ከአገዛዙ ጎን መሰለፍ መቻላቸዉ ሳይታለም የተፈታ ሃቅ ነዉ፡፡ሁለተኛዉ ደግሞ ለሰላሳ ዓመታት ታግለን አመጣን የሚሉትን ” ነጻነት” ስሜት ከመጠን በላይ በማጮህ ነዉ፡፡ስለዚህ ኤርትራ በዚህ ረገድ ከባላንጣዋ ከኢትዮጵያ በተሻለ ሁኔታ ህዝቡን ለማነሳሳት የተሻለ ዕድል (qualitative advantage) እንዳላት መገመት አያዳግትም፡፡ የኤርትራ ህዝብ ለኢትዮጵያ ያለዉን አመለካከት በትክክል ለመረዳት ይከብዳል፡፡ከሪፌሬንደሙ በኋላ የኢትዮጵያ አካል ሆነዉ የኖሩበትን የሰላሳ ዓመታት ዘመን ቀደም ብሎ ከነበረዉ የአምሳ ዓመታት የጣሊያን የቅኝ አገዛዛ ዘመን የቀጠለና በባህሪዉ ያልተለየ አድርገዉ መቁጠራቸዉ ለኢትዮጵያ ያላቸዉ ስሜት በእጅጉ የቀዘቀዘ እንዲሆን አድርጓቸዋል፡፡

ሻዕቢያ ስልጣን ከያዘ በኋላም ቢሆን ለህዝቡ ስለ ኢትዮጵያ መልካም ነገር ሳይሆን በጥላቻ ላይ ያተኮረ ቅስቀሳ ነበር ሲያደርግ የቆየዉ፡፡ ደርግ ከወደቀ በኋላ የተወለዱ ኤርትራዉያን ስለኢትዮጵያ መልካም ስሜት ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነዉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት (እነሱ የወያኔ መንግስት ነዉ እያሉ የሚጠሩት) አንድ ቀን ነጻነታችንን ነጥቆ ወደ ቅኝ አገዛዝና ባርነት ሊመልሰን ይችላል የሚል የስጋት አመለካከት በኤርትራ ህዝብ ልብ እንዲሰርጽ ተደርጓል፡፡ ስለዚህ “ለነጻነትና ለሉአላዊነት “ስም የሚደረግን ማንኛዉም ጦርነት ከኢትዮጵያ ጋርም ቢሆን ህዝቡን ቀስቅሶ ለማነሳሳት ለሻእቢያ በጣም ይቀለዋል፡፡የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን ለኤርትራ ነጻነትና ሉአላዊነት ቋሚ የስጋት ምንጭ አድርጎ በማቅረቡ ህዝቡ የሻዕቢያን አገዛዝ እየጠላም ቢሆን ለሉአላዊነቱ ስል ለመንግስት ድጋፍ ማድረጉ የማይቀር ነዉ፡፡ በኤርትራ ሰፍኖ የሚገኘዉ ወታደራዊ ድባብ (ሚሊታሪዝም) ማሳያ የሚሆነዉ ኤርትራ ከየትኛዉም ወገን በተጨባጭ የሚታሰብ የዉጭ ስጋት ሳይኖርባት ራሷን ለአደጋ እንደተጋለጠች አድርጋ በመቁጠር እየወሰደች ያለችዉን እርምጃ ስንታዘብ ነዉ፡፡

ኤርትራ ለዉትድርና ብቁ ከሆነዉ ህዝቧ ከሩብ በላይ የሚገመተዉ የሚገኘዉ በወታደራዊ ተቋሙ ዉስጥ ነዉ፡፡ኤርትራ ያላት የወታደር ብዛት ከህዝቧ ብዛት አንጽር በመቶኛ ሲሰላ ስድስት ከመቶ (6%)የሚበልጥ በመሆኑ በዓለም በአንደኛ ደረጃ ያስቀምጣታል፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያ እንደ ኤርትራ ከህዝብ ብዛቷ 6% ወታደር ብትመለምል ኖሮ የኢትዮጵያ ወታደር ብዛት ወደ ስድስት ሚሊዮን አካባቢ ስለሚሆን ከኤርትራ ህዝብ ብዛት ጋር እኩል ሊሆን ይችል ነበር ማለት ነዉ፡፡በኤርትራ የሰፈነዉን ስርአት በተለይም የግዴታ ወታደራዊ አገልግሎትን ሸሽቶ በዉጭ አገር የሚኖረዉ ኤርትራዊ ብዛት ከአጠቃላዩ ህዝብ ቁጥር እሩብ ያህል ይሆናል፡፡ይህ ኃይል በዉጭ አገር ሰርቶ ከሚያገኘዉ ገቢዉ ለኤርትራ መንግስት በግብር መልክ መክፈል ግዴታ ሲላለበት ለሻዕቢያ ዋነኛዉ የዉጭ ምንዛሪ ምንጭ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ዛሬ ግን በዉጭ ያለዉም ኤርትራዊ በሻዕቢያ ድርጊት እጅግ በመማረሩ ምክንያት አብዛኛዉ ክፍያዉን በማቋረጡ ሻዕቢያ ከፍተኛ ችግር ዉስጥ ወድቋል፡፡የኤርትራ ወታደራዊ ባጀቷ በጂ›ዲ.ፒ በመቶኛ ሲሰላ በየትም አለም የለለ እጅግ ከፍተኛ ነዉ፡፡ያም ቢሆን ግን ኤርትራን ከዉድቀት ሊታደጋት የሚችል አስተማማኝ የሆነ መከላከያ አቅም መገንባት አላስቻላትም፡፡ምክንያቱም ወጣቱ ስርአቱን ጠልቶ በገፍ ወደ ዉጭ እየሸሸ በመሄዱ የህዝቡም ቁጥር እጅግ በመናመኑ ለዉትድርና ብቁ የሆነ ሰዉ ኃይል ማሟላት ስለተሳናት ነዉ፡፡

አንድ ምንጩን በዉል በማላስታዉሰዉ ጥናት ዉጤት የሆነ ሰነድ ” በዓላም ላይ በህዝቡ ዘንድ የዉትድርና ሙያ እጅግ የተጠላና የማይፈለግ ዉዳቂ ሙያ ተደርጎ ከሚቆጠርባቸዉ አገሮች በግንባር ቀደምነት ኤርትራ ትጠቀሳለች፡“ብሎ ነበር፡፤

በዚህ አጋጣሚ ለንጽጽር እንዲረዳን የኢትዮጵያን ሁኔታ ለአፍታ መቃኘቱ መልካም ነዉ፡፡ኢትዮጵያ በወታደራዊ አቅሟ በአፍሪካ ካሉት አምስት አገሮች አንዷ እንደሆነች ይታወቃል፡፡እነዚህም አገሮች ግብጽ፤ አልጄሪያ፤ደቡብ አፍሪካ፤ናይጄሪያና ኢትዮጵያ ናቸዉ፡፡ብዙዎቹ የጉዳዩ አጥኚዎች እጅግ እንዲደነቁ ያደረጋቸዉ ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ ጠንካራ መከላከያ ኃይል እያላት ለመከላከያ የመደበችዉ ባጄት ግን እነዚህ አገሮች ጋር ሲነጻጸጸር እጅግ አነስተኛ መሆኑ ነዉ፡፡መረጃዎቹ እንደሚጠቁሙት አገራችን ከሌሎች አፍሪካ አገሮች በወታደራዊ ባጄቷ አስራ አራተኛ ተርታ ላይ ነዉ የምትገኘዉ፡፡ወታደራዊ ባጀቷ አንስተኛ ሆኖ ጠንካራ መከላከያ መገንባት መቻሏ አድናቆት ያሰጣት አንድ ነገር ሆኖ በተጨማሪ ካላት ትልቅ የሕዝብ ብዛት አንጻር በመቶኛ ሲሰላ የወታደሩ ብዛት በጣም አነስተኛ መሆኑ ነዉ፡፡ኢትዮጵያ በመጠኑ አነስ ያለ ግን ደግሞ በዉጊያ ብቃቱና አጠቃላይ ወታደራዊ አቅሙ እጅግ ጠንካራ የሆነ መከላከያ ኃይል መገንባት በመቻሏ በአንድ ጊዜ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ተልዕኮዎች ላይ ለማሰማራት አልተሳናትም፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሶማሊያ ዉስጥ ከሽብር ኃይሎች ጋር እየተፋለመ እንደሆነ ይታወቃል፡፡በተመሳሳይ ሰዓት በደቡብ ሱዳን ዉስጥ በርካታ ሰራዊት አሰማርታለች፡፡ከዚህም ሌላ አገሪቷ በቋሚነት ለሽብር ተጋላጭ በመሆኗ በተለይ እጅግ ሰፊ በሆነዉ በምስራቁ የሀገራችን አካባቢ ያልተቋረጠ ወታደራዊ ጥበቃ ማድረግ የግድ ነዉ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ከኤርትራ ጋር ገና ባልተቋጨዉ ፍጥጫ ምክንያት በኤርትራ አዋሳኝ ድንበር ላይ ጠንከር ያለ ጥበቃ እያደረገች እንደሆነም ይታወቃል፡፡ እንግዲህ ይህች አገር ባላት በቁጥር አነስተኛ የወታደር ኃይልና በጣም የተመጠነ ወታደራዊ ባጄት አንጻር ሲታይ እንዴት አድርጋ ነዉ ይሄን ሁሉ ተልእኮ በአንድ ጊዜ መወጣት ያለችዉ በሚል የዉጭ ታዛቢዎች መገረማቸዉ አልቀረም፡፡

ኢትዮጵያ ከህዝብ ብዛቷ፡ በሀገሪቱ የቆዳ ስፋት ግዝፈት፤ሰራዊቷ እየተወጣ ካለዉ ዘርፈብዙ ወታደራዊ ተልዕኮዎች፤በፍጥነት እያደገ ከመጣዉ ኢኮኖሚያዊ አቅሟ አንጻር ሲታይ ወታደራዊ ባጄቷ መጠን ዉስንነት ደረጃ በሚገባ መረዳት የሚቻለዉ በወታደራዊ አቅም ተቀራራቢ ደረጃ አላት ከተባለችዉ ከናይጄሪያ ጋር ሲነጻጸር ነዉ፡፡ኢትዮጵያና ናይጀሪያ ተመጣጣኝ ወታደራዊ አቅም ቢኖራቸዉም ከባጄት አንጻር ሲታይ የኢትዮጵያ መከላከያ ባጄት የናይጄሪያን አንድ ስምንተኛ ብቻ ነዉ፡፡ ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚያዋ በፍጥነት ማደግ አንዱ አስተዋጽኦ ያደረገዉ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች በተለየ ሁኔታ እጅግ የተመጠነ ወታደራዊ ባጄት መመደቧ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፤የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኢኮኖሚዉን የሚጎዳ ነቀርሳ ሳይሆን እንዲያዉም የመንግስትን የልማት ጥሬት በሰፊዉ እያገዘ ያለ የልማት አጋዥ ኃይል ነዉ፡፡ኢትዮጵያ ፈጣን አድገት በማስመዝገብ ከዓለም ተጠቃሽ ከሆኑ ሶስት አገሮች አንዷ ለመሆን መቻሏና በአጭር ጊዜ ዉስጥም ከአፍሪካ ጠንካራ ኢኮኖሚ አላቸዉ ከሚባሉ አገሮች ዉስጥ አምስተኛ ድረጃ ላይ መገኘት ለመቻሏ በርካታ ምክንቶችን መዘርዘር ብቻልም የሀገሪቱ መከላከያ አስተዋጽኦም እንዳለበትም መካድ አይቻልም፡፤ ስለዚህ ጉዳይ አንድ ጋዜጣ ላይ ያገኘሁትን ቀጥዬ ላካፍላችሁ:-

“when looking from a demographic and financial point of view, the Ethiopian military is a sleeping giant. Like its military ranking, it is also the fifth-largest economy in Africa, but only uses a fraction of its available manpower and spends one-eighth of the annual defense budget of its closest equivalent Nigeria. In fact, Ethiopia has actually decreased its military budget, reversing Africa’s trend of increasing budgets. And this is despite the country’s impressive double-digit growth. Once known for its widespread famines, the “African Lion” is currently the third-fastest growing economy in the world”.

6.ምን ማድረግ ይገባናል?

ወደ ጦርነት መግባታችን ካልቀረ በቅድሚያ መሰራት ያለብንን የቤት ስራ ካሁኑ መስራት ይገባናል፡፡ በርግጥ የመከላከያችን አቅም የማጠናከርና ዝግጁነታችንን የማሳደግ ነገር ለኤርትራ ተብሎ የሚሰራ ሳይሆን ወደፊት ሊገጥመን ለሚችል ግዙፍ ጠላትን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት የሚያከራክር አይደለም፡፡እንደዚያም ቢሆን አሁን ከፍት ለፍታችን ለተደቀነዉ ስጋት የተለየ ትኩረት አድርገን ማስራትና ማስተካከል የሚገቡን ስራዎች ይኖራሉ፡፡ የሚከተሉትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

· ስለጦርነቱ ስናስብ በቅድሚያ እርስበርሱ ያልተከፋፈለ፤ በጦርነቱ ዓላማና ስትራቴጂ ላይ ልዩነት የለለዉ፤ ጠንካራ የፖለቲካአመራር ሊኖር ይገባል፡፡እንደባለፈዉ ጦርነት በረባ ባልረባዉ እርስ በርሱ የሚወዛገብና የተከፋፈለ የፖለቲካ አመራር ከሆነ በሃገሪቱ ላይ ዉድቀት እንዳያስከትል አመራሩ በቅድሚያ ራሱን ማስተካከል አለበት፡፡

* መንግስት ከሁሉ አስቀድሞ በጦርነቱ ላይ የሕዝብን አመለካከትና ዝንባሌ ወይም ፍላጎት ለማወቅ ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ህዝብ በጦርነቱ ተገቢነት ያምናል?አምኖም ከመንግስት ጎን ይሰለፋል? በጦርነቱ ላይ አጠቃለይ የሕዝብ የጋራ መግባበትና አንድነት መነፍስ መፍጠር ይቻላል?መከላከያ ሰራዊታችን የሕዝብ ፍቅርና ድጋፍ አሁንም አለዉ ?ህዝቡ እንደቀድሞዉ ለጦርነቱና ለሰራዊቱ በፈቃደኝነት አስፈላጊዉን ድጋፍ ሁሉ ለመስጠት ዝግጁ ነዉ?መንግስትስ እንደበፊቱ ጠንካራ የሕዝብድጋፍአለዉ?ህዝቡን ለጦርነቱ ለማነሳሳት አቅም አለዉ?ጥቂት ቢሆኑም ጦርነቱን የማይደግፉና ከዚያም በላይ ከጠላት ጎን ሊሰለፉ የሚችሉ አሉ? እነዚህ ምን ያህል ተደማጭነትና ተጽኢኖ መፍጠር ይችላሉ?እነዚህን ኃሎች አገሪቱ በአደጋ (ጦርነት)ላይ እያለች ለጊዜዉም ቢሆን ከመንግስት ጎን የማይቆሙበት ምክንያት ተለይቶ ይታወቃል?እነዚህንና የመሳሰሉ ጥያቄዎች መንግስት ሊያስብባቸዉ የሚገቡ ናቸዉ፡፡

* ጦርነቱን መደገፍ/መሸከም የሚችል ኢኮኖሚ ሊኖረን ይገባል፡፡ምናልባት የግድ ሆኖ ከዉጭ መግዛት የሚገባን ትጥቅ ካለ ያን ለመሟላት የሚችል በቂ የዉጭ ምንዛሪ ተቀማጭ ሊኖረን የግድ ነዉ፡፡ጦርነቱ እንዳሰብነዉ ሳይሆን ቀርቶ ከታሰበዉ ጊዜ በላይ ቢራዘም በዚያ ሁኔታ ለምን ያህል ጊዜ በጦርነቱ ዉስጥስ መቆዬት እንደምንችል ግምታዊም ቢሆን አስቀድሞ ማሰቡ ተገቢ ነዉ፡፡ባለፈዉ ጦርነት ከኤርትራ የተሻለ ኢኮኖሚ መገንባት ችለን ስለነበር በጦርነቱ ላይ ምን ያህል እንዳገዘን ማስታወስ ይገባናል፡፡

* ወደ ጦርነት የምንገባዉ ወይም ወታደራዊ ኃይል ለመጠቀም የምንገደደዉ የሃገራችን ብሄራዊ ጥቅም ላይ የተጋረጠ አደጋ ሲኖር ብቻ መሆን አለበት፡፡ያለበለዚያ በረባ ባልረባዉ ወደጦርነት መግባት የለብንም፡፡ “Forces should only be committed when vital national interest is at risk.”የሚለዉን መሪህ ማስታወስ ተገቢ ነዉ፡፡ያለእኛ ፍላጎት በኢሳይያስ ተንኮል ተገፋፍተን በስሜት ወደ ጦርነት መግባት አይገባንም፡፡

* ከጦርነቱ የምንጠብቀዉን ዉጤት ወይም ማሳካት የምንፈልገዉ ምን እንደሆነ ግልጽና ጥርት ያለ ስትራቴጂያዊና ፖለቲካዊ ግብ (clear objective) ማስቀመጥና በዚያ ላይ የጋራ አረዳድ መያዝ ይገባናል፡፡ በተጨማሪ ምን ምን ሁኔታዎች ሲሟሉ ከጦርነቱ እንደምንወጣ (pre condition for war termination)በቅድሚያ ማሰብና ለዚያ መዘጋጀት ይገባናል፡፡ቢያንስ በወታደራዊና በፖለቲካ አመራሩ ደረጃ መግባባት ላይ ሊደረስበት ይገባል፡፡እንደ ባለፈዉ ጦርነት ድንገት “ዉጊያዉን ኡቁሙና ወደኋላ ተመለሱ“ ዓይነት ያልተጠበቀና አስደንጋጭ ነገር እንዳይኖር በቅድሚያ መግባባት ላይ ቢደረስ ይበጃል፡፡በተጨማሪ ግልጽ የሆነ ከጦርነት መዉጫ ስትራቴጂ( exit strategy) በቅድሚያ ማስቀመጥና ቢቻል የጊዜ ገደብ እንዲኖረዉ (sharp withdrawal deadline) ማድረግ ተገቢ ነዉ፡፡

* ወደ ጦርነት ለመግባት ስናስብ በሙሉ ልብ ለመዋጋትና እንደምናሸንፍም እርግጠኛ ስንሆን መሆን አለበት፡፡(“The war had to be fought whole heartledly with clear intention of winning.”)

* በወታደራዊ መስክ ብቃታችንና ዝግጁነታችን ላይ እርግጠኛ መሆን አለብን፡፡የጎደለና ያልተስተካከለ ነገር ካለ በጊዜ ፈትሼን ማረም ይገባናል፡፡ተዝረክርከን እያለ ወደ ጦርነት መግባት የለብንም፡፡በተጨማሪ የራሳችንን ሆነ የሌሎች አገሮችንም የጦርነት ተሞክሮዎች በጥንቃቄ ማጥናት ብልህነት ነዉ፡፡ግልጽ ወታደራዊ ዶክትርንና የዉጊያ መስመር መያዝና ፡በጦርነት ንድፈሃሳብ ላይ የጠራ አረዳድ መፍጠር፤ሰፋፊ ወታደራዊ ልምመዶችንና ማኑቨር ማድረግ፤በጥምርና በቅንጅት ስራዎች ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረግና በስትራቴጂክና በኦፕሬሽናል ደረጃ የአመራር አቅም ማሳደግ ይገባናል፡፡የሞብላይዜሽን አቅማችንን ማሳደግም ችላ የማይባል ጉዳይ ነዉ፡፡በተለይ አየር ኃይላችን ለወትሮዉ በድጋፍ ሰጪነት ላይ ብቻ የተገደበ ልማዳዊ ሚና ይልቅ በጦርነቱ ድርሻዉ የጎላ እንዲሆን ለማድረግ ሁለንተናዊ አቅሙን ካሁኑ ማሳደግ ይገባል፡፡የአየር ኃይሉን ድርሻ ካሳደግን አጠቃላይ ጦርነቱን በጊዜም (dutration)ሆነ በኪሳራ (casualty)ደረጃ በግማሽ መቀነስ እንችላለን፡፡አየር ኃይሉን ማጠናከር ማለት በተዘዋዋሪ መንገድ ምድር ኃይሉን ማጠናከር ማለት እንደሆነ መዘንጋት የለበትም፡

* ለጦርነቱ ከምናደርገዉ ወታደራዊ ዝግጅት ጎን ለጎን ድጋፍ ሊያሰጠን የሚችል ጠንካራ የዲፕሎማሲ /የዉጭ ግኑኝነት ስራ በስፋት መስራት ይገባናል፡፡አለምአቀፍ ማህበረሰብና እንደ አሜሪካ ያሉ አገሮችን ፤አፍሪካ ህብረትና አዉሮፓ ኮሚሽን ኢትዮጵያ ራሷን ለመከላከል እየወሰደች ያለዉን እርምጃ ተገቢነት እንዲረዱ ማድረግ ይገባል፡፡

* ጦርነቱን በአጭር ጊዜና ባልተንዛዛ ሁኔታ ማጠናቀቅ፤በሁሉም አቅሞቻችን የኃይል ብልጫ ይዞ መገኘት(overwhelming force)ይገባናል፡፡የምናመጣዉ ድልም ጊዜያዊ እፎይታ ለማግኘት ተብሎ ሳይሆን ዘለቀታዊ ሰላም ማምጣት የሚያስችለን የማያዳግም (decisive victory) ድል መሆን አለበት፡፡ቀጣዩ ጦርነት ኤርትራን ነካክቶ ለመተዉ ያለመ ሳይሆን ኤርትራን ድጋሚ እንዳይለምዳት የመቅጣት ዓላማ(punishing objective) ያለዉ መሆን አለበት፡፡

* ጦርነቱንና ልማቱን ጎን ለጎን የማስከድ መሪህ መከተል አለብን፡፡ በጦርነቱ ሂደትም ቢሆን ልማት እንዳይደነቃቀፍ የጦርነቱ ድባብ በዚያዉ በጦር ግንባር አካባቢ ብቻ የተወሰነ እንዲሆን በማድረግ ከጦርነቱ ቀጠና ዉጭ ባሉ የሀገሪቱ አካባቢዎች የልማት ስራን በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል፡፤ሁሉም ዜጋ ለጦርነቱ መንግስት የሚጠይቀዉን ድጋፍ እያደረገ ነገር ግን መደበኛ ስራዉን ከወትሮዉ በበለጠ እንዲሰራ ማድረግ ይገባል፡፡በጦርነት ዉስጥ ያለች አገር ዉስጥ የሚታይ ዓይነት ነጋ ጠባ ስለጦርነት ወሬ የመሰለቅ ልማድ በጣም ስለሚጎዳን ሁሉም በልማቱ ላይ አትኩሮ እንዲሰራ ማድረግ አለብን፡፡ባለፈዉ የደርግ ዘመን አንደነበረዉ “ሁሉም ነገር ወደጦር ግምባር “የሚባል መፈክርና አሰራር መኖር የለበትም፡፡በተለይ የህዳሴዉ ግድብ “የኢትዮጵያ ህዳሴና እድገት ተምሳሌት(symbol)” የሆነ ፕሮጄክት በመሆኑ ስራዉ በግርግር እንዳይደነቃቀፍ ብሎም እንዳይቋረጥ በልዩ ሁኔታ መከታተል ይገባል ፡፡ የዉጭ እንቬስትሜንት እንዳይሸሽ ጥረት ማድረግ፤ከጦርነቱ ዉጭ ባለዉ በሌላዉ አገሪቱ አካባቢ ሰላም እንዳይስተተጓጎል ማድረግና የቱርስት ፍሰት እንዳይቀንስ የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ የግድ ነዉ፡፡

* ህዝቡ ለጦርነቱ በፈቃደኝነት ሊያደርግ የሚችለዉን አስተዋጽኦ ከማስተባበር ዉጭ የማስገደድና ጫና የማድረግ ነገር እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡

* ጦርነት በባህሪዉ ለሙስናና ለዝርፊያ መልካም አጋጣሚ በመሆኑ የህዝብ ገንዘብና የሀገር ሃብት ያለ አግባብ እንዳይባክን ጥረት ማድረግና ተገቢዉ ጥንቃቄ መወሰድ ይገባል፡፡ያለፈዉ ጦርነት በፈጠረላቸዉ አጋጣሚ ተጠቅመዉ ራሳቸዉን ወደ ሚሊዬነርነት የቀየሩ ሰዎች የሉም ብሎ የሚከራከር ሰዉ ካለ እሱ በጣም የዋህ መሆን አለበት፡፡ሰራዊታችን በጦር ሜዳ ከጠላቱ ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቆ በሚፋለምበት ሰዓት ሌላዉ ለግል ጥቅም መሯሯጥ እጅግ አስነዋሪ ተግባር በመሆኑ ተገቢዉ ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል፡፡

* በጦርነቱ ዙሪያ የአመለካከት ልዩነት እንዳይፈጠር ተቃዋሚና ደጋፊ የሚባል ከፋፋይ ነገር በለለበት ሁኔታ ለጦርነቱ ድል ማድረግ ሁሉም በዜግነቱ የሚችለዉን ድጋፍ የሚያደርግበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡መንግስት ጦርነቱ የመላዉ ኢትዮጵዉያን የጋራ ጉዳይ መሆኑን ዘንግቶ አንዱን አቅፎ ሌላዉን ገለል የሚያረግበት ሁኔታ መኖር የለበትም፡፡ተቃዋሚ ፓርቲ አባላትም ቢሆኑ ህዝብ የደገፈዉን ጦርነት የሚቃወሙበት ምክንያት ስለማይኖር መንግስት ከሚያገላቸዉ የኃላፊነት ስሜት እንዲሰማቸዉ ማድረግ ይገባዋል፡፡

* ከአንዳንድ ወገኖች ወደ ጦርነት መግባታችን ካልቀረ በኤርትራ ያለዉን አገዛዝና ስርአት መለወጥ አለብን የሚል ግፊት ስለበዛ መንግስት ቢቻል ለዚህ ዓይነቱ ምክር ጆሮዉን ባያዉስ ይመረጣል፡፡የግድ ማድረግ አለብኝ ካለም ሊገጥሙት የሚችሉ ተግዳሮቶችን ካሁኑ አዉቆ እንዴት ሊወጣቸዉ እንደሚችል ዝርዘር እቅድ ነድፎ ራሱን ለዚያ ማዘጋጀት ይኖርበታል፡፡

* ከባለፈዉ የኤርትራ ጦርነትም ሆነ ከዚያ በኋላ በነበሩት የተለያዩ ወታደራዊ ግዳጆች ወቅት የነበረዉን የመከላከያችንን ተልእኮ አፈጻጸም በሚገባ ገምግሞ ድክመቶች እንዳይደገሙ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ጎናችን ይበልጥ አጠናክረን መገኘት ይገባናል፡፡ለዚህም ሲባል መከላከያም ሆነ ብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ጠንከር ያለ ግምገማ ማድረግ ይገባዋል፡፡አቅምና ችሎታችንን፤ጥንካሬና እጥረቶቻችን በሚገባ ሳንፈትሽ ተቻኩልንና በጠላት ተገፋፍተን ዘለን ወደ ጦርነቱ ከመግባት መቆጠብ ይገባል፡፡ኢህአዴግ ደርግን የሚያህል ኃይል ማሸነፍ የቻለዉ ከእያንዳንዱ ዉጊያ በኋላ በመገምገም ነዉ ብሎ እንዳላስተማረን አሁን መንግስት ሲሆን በአስርሽዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቻችን የወደቁበትን የኤርትራን ጦርነትና እጅግ ፈታኝና ባህሪዉ ዉስብስብ የሆነዉን የሶማሊያን ጸረ-ሽብር ተልእኮ አፈጻጸም በሚመለከት ለመገምገም ፍላጎቱም ይሁን ድፍረት ማጣቱ የሚያስደስት አይደለም፡፡

ማጠቃለያ

ከኤርትራ ጋር ባልተዘጋጀንበትና ባልጠበቅነዉ ወቅት ወደ ጦርነት ብንገባም ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍለንም ቢሆን የተደፈረዉን ሉአላዊነታችንን ማስከበር ችለናል፡፡ይሁን እንጂ በጦርሜዳ በደማችን ያገኘነዉን ድል ሃላፊነት በማይሰማቸዉ ደካማ ተደራዳሪዎች ምክንያት በፍርድ ሸንጎ እንዲንነጠቅ ተደርጓል፡፡ ያም ሆኖ እስካሁን ጉዳዩን መቋጨት ባለመቻሉ ከነገ ዛሬ ድጋሚ ጦርነት ይነሳ ይሁን እያልን በስጋት ዉስጥ ሆነን አስራ ስድሰት ዓመታት ያህል ከቆየን በኋላ ጦርነት ሊቀሰቅስ ወደሚችል ግጭት ዉስጥ ገብተናል፡፡ ጦርነት ድጋሚ ሊቀሰቀስ መቻሉ ላይ ጠንከር ያሉ አስተያየቶች እየተሰጡ ቢሆንም ማንኛችንም ብንሆን በርግጠኝነት መናገር አንችልም፡፡ ለማንኛዉም ተብሎ በቂ ዝግጅት ማድረግ ግን ይገባናል፡፡

ከዚህ በኋላ እንደባለፈዉ ጊዜ “ድንገተኛና ያልተጠበቀ”የሚባል ነገር መኖር የለበትም፡፡ ለማይቀረዉ ጦርነት ስንዘጋጅ ከሁሉም በላይ ትልቅ ትኩረት ማድረግ ያለብን የህዝብንና የመንግስትን አንድነት ማረጋገጡ ላይ ነዉ፡፡ ይህን እንድናደረግ የወቅቱ ሁኔታም ያስገድደናል፡፡በሆነ ባልሆነዉ እርስበርሱ የተኮራረፈ ህዝብ ይዘን ወደ ጦርነት መግባት ትርፉ በጦርነቱ አዋራጅ ሽንፈት መቀበል ነዉ፡፡ ህዝቡ በጦርነቱ ማመን ብቻ ሳይሆን እንደከዚህ በፊቱ ከመንግስት ጎን እንደሚቆም እርግጠኛ መሆን የግድ ነዉ፡፡ ዉስጣችን ባልተረጋጋበትና መደማመጥ ባቆምንበት ወቅት ላይ ካልተገደድን በስተቀር ወደ ጦርነት መግባት የለብንም፡፡ አሁን ያለንበት ወቅት አንድነታችንን የሚፈታተኑ በርካታ ችግሮች የተከሰቱበት ወቅት ነዉ ፡፡ አንድነታችንን ወትሮዉኑ የማይፈልጉ ኃይሎች አሁን ያለንበት ጊዜ ለመሰሪ የጥፋት ዓላማቸዉ እጅግ የተመቻቸ ወቅት አድረገዉ በመቁጠራቸዉ ሊያጠፉን ከምንጊዜም በላይ ቆርጠዉ ተነስተዋል፡፡ ለእናት ሀገሩ በየቦታዉ እየተዋደቀ ያለዉን መከላከያ ሰራዊታችንን ወኔዉን ለማላሸቅና ከዓላማዉ ሊያናጥቡት አጉል መፍጨርጨር ማድረጋቸዉንም አላቋረጡም፡፡

በዚህ ስርአት ዉስጥ የትኛዉም ዓይነት ዉስብስብ ችግር ቢፈጠር ህዝብና መንግስት በጋራ ሆነዉ ሊፈቱት የማይችሉት ችግር ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ መንግስት የዉስጥ ጉዳዩን እያስታመመ ዳርዳሩን እየዞረ ሊፈታ አይችልም፡፡ ከዚያ ይልቅ ቆራጥ እርምጃ መዉሰድ መጀመር አለበት፡፡ለዚህ ሁሉ ምስቀልቅል ሁኔታ ሰበብ የሆኑና ሆነ ብለዉ ቀዉሱን የሚያባብሱ የፌዴራልም ሆነ የክልል ለስልጣናት ተለይተዉ ጥብቅ እርምጃ ሊወሰድባቸዉ ወይም የሆነ ማስተካከያ ሊደረግ ይገባል፡፡ የኢፌዴሪ መንግስት ከኢትዮጵና ህዝብና ከፓርቲ/መንግስት ባለስልጣናት ለየትኛዉ የበለጠ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ቸግሮት ከሆነ ይንገረን፡፡ ኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠዉን የወቅቱን አደጋ ለማስወገድ ለህዝብ ጥቅም ሲባል መንግስትና ገዢዉ ፓርቲ ራሳቸዉን መስዋእት አስከማድረግ ድረስ መሄድ ሊኖርባቸዉ ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ የሚወሰነዉም አሁን የታየዉን ቀዉስ በምን ያህል ደረጃና ፍጥነት እንፈታዋለን በሚለዉ ላይ ነዉ፡፡ ለማንኛዉም አሁን እየታየ ባለዉ ሁኔታ መንግስት ሳይደናገጥ በተጠና መንግድ ለመፍታት መሞከር አለበት፡፡ሙሉ ትኩረታችን በዉስጥ ጉዳይ አድርገን የሻዕቢያ ጉዳይ ተዘንግቶ ለተጨማሪ አደጋ እንዳንጋለጥም መስራት የሚገባንን ስራ ከአሁኑ በጥንቃቄ መስራት ይገባናል እላለሁ፡፡

************

* ለፀሐፊዉ /ል አስጨናቂ /ጻዲቅ ሺፈራዉ አስተያየት መስጠት ለሚፈልጉ በኢሜል አድራሻ ([email protected]) መጠቀም ይችላሉ፡፡

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ 1970/ ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ 2002 / ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

more recommended stories