Aug 12 2016

የጎንደሩ ዓመፅ ለምን ኣሁን ሆነ? ዋና ዋና መነሻ ምክንያቶች

በ”ጥያቄ ኣለኝ ጓዶች”(የብዕር ስም)

በቅርብ ግዝያቶች በተለያዩ አከባቢዎች መልካቸዉና ይዘታቸው የተለያየ ዓመፆች እየታዩ ነው፤ ለግዜው ግን ትኩረቴ የጎንደሩ ላይ ነው። በጎንደርና ኣካባቢው የተነሳው ላይ ያተኮርኩበት ምክንያት ጎንደር የዚህ ሁሉ ማእከል ስለነበረችና ሌሎቹ በዋናነት የዚህ ተቀጥያ ስለነበር ምንጩን መረዳት ሌላዉን መረዳት ያስችላል ከሚል እሳቤ ተነስቼ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከሌሎች ለየት ባለ መልኩ ዘር ተኮር ጥቃቶች በስፋት የተፈፀሙበትና በርካቶችን ያሳዘነና ያሳፈረ ስለነበር ነው።

ኣንድ ግልፅ መሆን ያለበት ነገር በጎንደር ወይም በሌላ የመልካም አስተዳደር ችግር ኣለ፤ እንዲሁም በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች። ስለምንድነው ታድያ ጎንደር የዓመፅ መነሻ እና ሞዴል የሆነችው? ምን የተለየ ነገር ቢኖር ነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እና ጠቅለል ያለ የመፍትሔ ኣቅጣጫ ለመጠቆም ነው። ሶስት ደቂቃ የማትፈጅ ግን ደግሞ የጎንደሩን ዓመፅ እዉነተኛ ማንነት ቁልጭ አድርጋ የምታሳይ ፅሁፍ ስለሆነች ሁሉም እንዲያነበው እጋብዛለሁ።

1/ በታሪክ አንሶ የመታየት ስጋት

ቅማንትን እዉቅና መስጠት ማለት አፄ ቴድሮስን ከጎንደር መዉሰድ ማለት ነው። ይህም ጎንደሬው ለክፈለ ዘመን ያህል የኩራት ምንጩ ኣድርጎ ሲተርከው እና ሲኮራበት የነበረው፣ መገለጫየ ነው ብሎ የሚመካበትን ምልክቱ ነው ያጣው። አፄ ቴድሮስ ባባቱ ትግሬ በናቱ ቅማንቴ መሆኑ ኣንርሳ::በቅርቡም የቅማንት ህዝብ የኣፄ ቴድሮስ ሙዝየም እና መታሰብያ ሃወልት ሊገነቡ እንደሆነ መሰማቱ ለጉዳዩ ግለት ሰጥቶታል። ይህንን ቁጭት በቀጥታ መግለፅ ለጉዳዩ እዉቅና መስጠት ስለሚሆን ይህንን ሁኔታ እንዲፈጠር ቅማንቶችን ኣሞኝቶ ታሪካችን ላይ ኣሲሮብናል ብለው የሚያስቡትን ህወሓት መምታት የቅማንቱ በቀል ኣንዱ መገለጫ ተድርጎ ታይቷል። ይህ የማንነት ጥያቄ እኛው ኣዙረን ወደ ወልቃይት ከወሰድነው ከዚህ በፊት በህጋዊ መንገድ የቀረቡትን ትግራዋይ ነን የሚሉ የ ዓብዲራፊዕ፣ ኣብርሃጅራና ሌሎች የኣማራ ክልል ቦታዎች ወደ ትግራይ እንዳይካለሉ ማድረግ እንችላለን የሚል ስሌትም እንደሚኖረው ግልፅ ነው።

73 ያህል ሰው ቢገደልም በጎንደሩም በባህርዳሩም ሰልፎች በቅማንት ወንድሞቻችን የሚደረገውን ግድያ ይቁም የሚል አንድም መልእክት ኣልተላለፈም፤ እንዲተላለፍም ልንጠብቅ ኣንችልም። ምክንያቱም ሲጀመር ሰልፉን በስሜት ከገፉ ምክንያቶች ዋነኛው “ቅማንቶች ቴድሮስን ይዘዉብን ሄዱ” የሚል ቁጭት እንጂ የስብኣዊ ፍጡር ክብር እና መብት መብት ጥየቃ ዋናው ኣጀንዳው ኣልነበረም። ይህ ቢሆን ብኣዴንን የቅማንት ወንድሞቻችን ገድሎብናል የሚል ድምፅ በተሰማ። የክልል ድንበር ተሻግሮ ለኦሮሞ ተቆርቛሪ ነኝ ያለው የቁጭት ሃይል ቅማንትን እዉቅና ሊሰጠዉም ኣልፈለገም፤ ዋና ችግሩ ምን ሆነና።

2/ ሰዓቱ ኣሁን ነው ምክንያቱም:

2.1/ ኦሮሞው ከተነሳና ኣንዳንድ ዉጤቶች ካመጣ እኛስ ከማን እናንሳለን! (Imitation and competition)

ኢህአዴግ በነሱ ኣጠራር ከህወሓት ዉጪ ትንፋሽ ስለሌለው በኢህኣዴግ ላይ የኦሮሞ ህዝብ ስለተነሳና መንግስትም ግራ ስለገባው በዉጥረት ላይ ዉጥረት ፈጥረን ሱሪዉን በቁሙ ማስፈታት እምንችልበት ምርጥ ኣጋጣሚ ኣሁን ነው የሚል እሳቤ ነው። ይህ እሳቤ ኦሮሞና ኣማራ ሁለቱ ህወሓትን መጣል ኣላማቸው ስለሆነ በቀላሉ ይተባበራሉ የሚል ስሌት ነው። ለዚህም በኢህአዴግ የበላይ ለመሆን የሚፈልጉ የብኣዴንና የኦህዴድ ሰዎች ይተባበሩናል፣ በተጨማሪም በሙስና የተጨማለቀው ኣመራር በፀረ ሙስና ንቅናቄው ላለመመታት ከሚኖረው ተፍጥሯዊ ፍላጎት በፀረ ኢህአዴግ ትግል መሳተፉ ኣይቀርም።

እነ ጃዋር የአማራው ሊሂቅ ላይ ‹‹ለዓመታት ፎክራቹህ ምንም ሳታመጡ በጥቂት ግዜ ኢህኣዴግን ኣንቀጠቀጥነው›› ብለው እንዳይሳለቁና የኢትዮጵያ ፖለቲካም በዋናነት መምራት ያለብን እኛ ስለሆንን ያለ የሌለ ሃይላችን እምናንቀሳቅስበት ግዜው አሁን ነው፤ እነ ጃዋርንም በተግባር መብለጥ የሚል የፉክክር ስሜት በኢሳትና በማህበራዊ ሚድያዊ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሲታይ ነበር። መንግስትን አስፈራርቶ አንዳንድ ነገሮችን እንዲቀየሩ ማድረግ እንደሚቻል የኦሮሞ ሰልፈኞች ስላስተማሩን እኛም አነስ ባለ ጥያቄ ጀምረን መንግስትን ማንበርከክ የማንችልበት ምክንያት የለም። አንፃራዊ ኣቅማችንን እያጤንን እስከ ማስወገድ እንገፋለን ነው ነገሩ።

ስለዚ ይህ ሁኔታ እኛም ‘ቁስላችንን’ የምንገልፅበት እና ምሬታችንን የምናካክስበት ምቹ ሁኔታ ከዚህ ግዜ በላይ ኣይመጣም። ስለዚህም የኦሮሞን ጉዳይ የራሳችን ጉዳይ ኣድርገን በማቀፍ በተቻለ መጠን ጥምር ፀረ ህወሓት ትግል ማካሄድ። እዉነቱ ግን ሌላ ነው። ለምሳሌ ነቀምቴ ላይ ከነበሩት መፈክሮች ኣንዱ ኣዲስ ኣበባ ላይ ያለው የኣፄ ሚኒሊክ ሃወልት ይፍረስ ነበር፤ ለዛዉም የመገንጠል ኣላማ የሚያንፀባርቀዉን የኦነግ ኣርማ አንግበው፤ ጎንደር ላይ ደግሞ የጠርናፊት ኢትዮጵያን ኣፋኝ ኣርማ የሆነዉን መላጣ ባንዴራ ይዘው የፌዴራል ስርዓቱ እንደማይቀበሉ የሚያመላክቱ ግልፅ ምልክቶች እና መፈክሮች እያሳዮ። ስለዚህ መነሳት ያለብን አሁን ነው::

2.2/ በብአዴንና በህወሓት መሃከል ያለው ፉክክር

በብአዴንና በህወሓት መሃከል ፉክክር ስላለ ከዚህ ግዜ ዉጪ ምርጥ ሰዓት አናገኝም እናም የእርምጃ ግዜው ኣሁን ነው፤ ካልሆነ ወርቃማው እድል ያመልጠናል። ብኣዴንን ወረነዋል፣ ከኣመራሩም ወሳኝ ድጋፍም ኣለን ስለዚ ግዜው አሁን ነው። በተጨማሪም መንግስት በራሱ ኣፍ ችግር ኣለብኝ እያለ ስለሆነ እኛም ኣዎ ችግር ኣለብህ መፍታት ደግሞ ኣትችልም ብለን ህዝቡን ማነሳሳት ያለብን አሁን ነው።

2.3/ መንግስት ራሱ ችግር ኣለብኝ ስላለና ከዚህ ካንሰራራ ስለሚበቀለን

መንግስት ለሚነሱት ጥፋቶች ራሴ ሃላፊነት ስላለ ካልቻልክ መዉረድ ኣለብህ ብለን የምናስገድ ድበት ግዜም ኣሁን ነው፤ ራሱ መንግስት ምቱኝ ብሎ ዱላ ሲያቀብለን ዝም ብንል ወርቃማው እድል ማክሸፍ ስለሚሆን የዓመፅ ግዜው አሁን ነው። ህዝቡ በመልካም አስተዳደር ስለተማረረ፣ ለየትኛዉም ፀረ መንግስት ኣጀንዳ ለማሰለፍ ምቹ ሁኔታ ስለተፈጠረ፤ ኢህኣዴግም ለህዝቡ በተጨባጭ መፍት ሄ መስጥት ስለዘገየ ዓመፅ የመፍጠር ግዜው ኣሁን ነው።በተጨማሪም ኢህኣዴግ ከዚህ ነዉጥ ራሱን ካተረፈ መንግስቱንና ፓርቲዉን ካረጋጋ በኃላ የበቀል እርምጃ ስለሚወስዱ ያለን ኣማራጭ እስከ ፍፃሜው መግፋትና መግፋት ብቻ ነው የሚል ግልፅ ኣቛም በመያዙ (የዞን ዘጠኞቹ እነ በፍቃዱ ዘ ሃይሉ በቲዊተር እንዳሉት)::

2.4/ ዘር ተኮር የዓመታት ቅስቀሳው ፍሬ ስላፈራ

ለዓመታት በጋዜጣ፣ በመፅሄት፣ በቪኦኤ፣ በኢሳት በተለያዩ መፃሃፎች ሲተረክ የነበረው የትግራይ የበላይነት ፍሬው የሚያፈራበት ግዜው ስለደረሰ ይህን ኣራግቦ ትግራዮችን ለመምታት የሚያስችል መደላድል ስለተፈጠረ ይህንን መጠቀም። በስራ ኣጥነት፣ በድርቅ፣ በብድር እና ማዳበርያ ያኮረፈው ሃይል በዚህ ማዕቀፍ ከተን ፀረ ህወሓት (ትግራይ) ለማነሳሳት ግዜው ኣሁን ነው የሚል ግልፅ እሳቤም ኣይተናል። ትግራይ እየለማች ነው፣ በየጎዳናው እምታዪት ለማኝ እኛን ለማታለል የተመደቡ አክተሮች ናቸው፣ ቁራሌው እና መጥረግያ ሻጩ እንዲሁም ባለ ሚጥጥየ ሱቅ ባለቤቶች ሰላዮች ናቸው፣ ሁሉም ኣንድ ናቸው፤ ችግራችን እነሱ ስለሆኑ መፍትሄዉም እነሱን ማስወገድ ነው የሚል ፈሊጥ ባብዛኛው ህሊና እንዲሰፅ ስለሆነ ጥቃት እምንፈፅመው ኣሁን ነው ወደሚል ድምዳሜ መርቷቸዋል። ኦሮሞ እና ኣማራ ስላበረ ህወሓትን ኣንበርክከን እንጥለዋለን፣ ህወሓት ኣቅም እንደሌለው ለማሳየትም የትግራይን ሰዎች ብናጠቃም ማንም ተጠያቂ አያደርገንም።

2.5/ ሁከትን ለራሳችን ጥቅም ማዋል

ሁከት የሚፈጥረው ተጨማሪ ሁከት እና የሚጭረው ተስፋ በምንፈልገው መንገድ የምንመራበት ሰዓት ላይ ደርሰናል። ስልፍ ባልተለመደበት ሃገር ከሰልፍ በኃላ መንግስት የሚገለበጥ የሚመስለው ብዙ ስለሆነ ከዚህ ዓይነት ስነ ልቦና እንዳይወጣ ኣድርጎ ወደፊት እንጂ ወደኃላ እንዳይመለስ ማስቻያ ግዜው ኣሁን ነው፣ ህዝብም ወደ ጠነከረ ሃይል ማዘንበሉ ስለማይቀር የሃይል ሚዛኑንን ከመንግስት ለመንጠቅ ከዚህ ግዜ በላይ ምቹ ሁኔታ የለም ተብሎ የተገባበት ስራ ነው።

2.6/ ግብፅና ሳዑዲ እንዲሁም ኤርትራ ለራሳቸው ሲሉ ይደግፉናል

የዉጭ ሃይሎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለሚታሰበው የመንግስት ግልበጣ ተስፋ ሰጪ መስሎ ስለታየና፣ የግብፅና ሳዑዲ መንግስታት በኤርትራ በኩል ኣባይ እንዳይገደብ የሚያደርጉት ሩጫ የመጨረሻ ሙከራ ሊያደርጉ የሚችሉበት የመጨረሻ ሰዓት ስለሆነ አስፈላጊው የገንዘብ፣ የመረጃና የስልጠና ድጋፍ እየሰጡ በመሆኑ ይህን ወርቃማ እድል እንዳያመልጠን።

3/ የፌዴራል ስርዓቱ አይቀሬነት የወለድው ስጋት

በኢህአዴግ ደካማነት የፌዴራል ስርዓቱ በሚፈለገው መንገድ እየተተገበረ ኣይደለም፤ ሆኖም የኢትዮጵያ ህዝቦች ግን ከዚህ ስርዓት ዉጪ አብሮነታቸውና መብቶቻቸው የሚያረጋግጥላቸው ስርዓት እንደሌለ በቀጥታም በተዘዋዋሪም መልኩ እየገለፁ ነው። በኦሮምያ የሚታየው ሰልፍ የዚህ ስሜት ከፍተኛ መገለጫው ነው። ይህ ደግሞ በባህሪው የትምክህት ሃይሉን ኣጀንዳ ወሃ እንደሚበላው ግልፅ መልእክት አስተላልፏል። ከዚህ ተስፋ መቁረጥ የሚነሳ ስጋት የትምክህት ሃይሉን በእልህ እና በቁጭት ተሞልቶ ወደ በቀል እንዲሄድ እያደረገው ነው። በጎንደር የተያዘው ልሙጡ ኮከብ ኣልባ ባንዲራ፣ “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር” እሚለው መፈክር፣ የፌዴራሊዝሙ ጠንሳሽ ነው ያሉትን ህወሓትና መስራች አመራሮቹ ላይ የተንፀባረቀው ጥላቻ የትምክህት ግብኣተ መሬት የሚያመላክቱ ማሳያዎች ናቸው።

የፌዴራሊዝሙ አይቀሬነት ወይም የተፈፃሚነቱ ኣስፈላጊነት በብዙ ብሄር እና ብሄረሰቦች ዘንዳ ቅቡልነት ማግኘቱ ለትምክህት ሃይሉ ፈተና መሆኑ ግልፅ እየሆነ መጥቷል፤ የኣፋሩ ሰልፍና የሶማሌ ፕሬዝዳንት መግለጫ ለዚህ በቂ ማስረጃ ነው። የትምክህት ሃይሉ ኣንዱ የመወራጨት ምክንያትም የጥቅለላ ፖለቲካው ግብኣተ መሬት መግባት ነው። ልክ ፈረስ ሊሞት ሲል የሚያደርገው የጣር እንቅስቃሴ ዓይነት ነው በጎንደር የታየው ፀረ ብዙህነት መፈክርና መደናበር። የተያዙት መፈክሮች እርስ በርስ መጣረስም ከዚህ ግራ የገባው ተስፋ መቁረጥ የሚመነጩ ስለሆኑ የፀረ ትምክህት ጎራው ይህንን ነገር እንደ የኣደጋ ምልክት ያለው ፖለቲካዊ ድል መቁጠር ኣለበት።

ድምዳሜ

የጎንደሩና ተያያዥ ዓመፆች ከመልካም ኣስተዳደር ይሁን ዴሞክራስያዊ ስርዓት መቀጨጭ የሚመነጭ ሳይሆን፤ በነዚህ ክፍተቶች የተለየ ዓላማ ይዞ የመጣ የቁጭትና የተዋርደናል ንቅናቄ ነው። ከመፈክሮቹ፣ ዓመፀኛው ኢላማ ካደረገው ኣካል ማንነት፣ ከታዩት የዉጭና የዉስጥ ቅንጅታዊ ስራዎች ተነስተን ጉዳዩን ካየነው ዓመፁ ለዴሞክራስያዊ ስርዓት ግንባታ ሳይሆን ለቀጣይ መጠራጠር እና ዘረኛ ሁከት ነው በር የከፈተው። ከዚህ ሂደት ተምሮ ሰከን ብሎ ለሚያጤን ደግሞ ትልቅ ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ ዓመፅ ነበር። ዘር ተኮር ጥቃት እየፈፀምክ የዴሞክራሲ ሃይል ነኝ ማለት ቀልድ ነው።

መፍትሔዉም አሁን ያለዉን ፌዴራላዊ ስርዓት በማጠናከር “በታሪክ ኣንሰናልና… ግዜው ኣሁን” ነው ባዩ የቁጭት ሃይሎች ዘረኛ ኣጀንዳ ትግራይ እና ትግራዋዮች ላይ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ላይ የተቃጣ የስርዓት ኣደጋ እንደሆነ በተግባር ማሳየትና በዓፀፋዉም ሰላም እና ኣብሮነት ፈላጊ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር የጥፋት ሃይሉ ወደ መጠኑ እንዲመጣ ማድረግና በጥፋት መንገድ ልግጠም ካለም በብዙ ግንባር ከመዓት ሃይሎች በብዙ ግንባሮች እንደሚፋለም ኣሳይቶ ዓላማው ሊሳካ እንደማይችል ካሁኑ ማሳየት ለነገ የማይባል ተግባር ነው ።

*********

Source: HornAffairs.com
ይህን ጽሑፍ ወስደው ሊያትሙ ቢሹ፤ የሆርን አፌይርስን እና የፀሐፊውን ስም በግልጽ መጥቀስ እና የዚህን ፖስት Link ማስቀመጥ ይገባል፡፡

7 Comments
  1. Yismaw Gashaye

    First, the passage is not a three minute reading. The passage is narrow thinking. Kimant and Gonder are the same sisters and brothers and they were together at Gondar anti government protest. I think your comment shows no reality but leads to wrong judgement. The Gonder protest is historical for Amhara and cooprative nationalities movement.
    Thank you!!!