ኢትዮጲያ የማን ናት:- የወጣቶች ወይስ የባለስልጣናት?

ባሳለፍነው ሳምንት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተቃውሞ ሰልፍ በወጡ ዜጎች ላይ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች የተወሰደው እርምጃ ከማሳሰብ አልፎ በጣም አስጨንቆኝ ነበር። እንደ ሀገርና ሕዝብ ሕልውናችን አደጋ ላይ እየወደቀ እንደሆነ ተሰምቶኛል። በአካል ሆነ በስልክ ያገኘኋቸውን ሰዎች ስጠይቅ የነበረው፤ “ሰላማዊ ሰልፍ ስለወጣን ለምን ይገድሉናል?” እና “ለምንድነው የመንግስት ባለስልጣናት የህዝቡን ጥያቄ የማይሰሙት?” የሚሉትን ነበር። ጥያቄዎቹ እንዳስጨነቁኝ አልቀሩም፣ መልስ አገኘሁላቸው። የመጀመሪያው፣ የራሱን ዝርያ በጭካኔ የሚገድለው ብቸኛ እንስሳ “ሰው” ስለሆነ ነው። ሁለተኛው፣ በሀገራችን እየታየ ያለው የህዝብ ተቃውሞ ሳይሆን የትውልድ ግጭት ስለሆነ ነው። በቅድሚያ ግን በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ስለነበረው ሁኔታ የተወሰነ ዳሰሳ በማድረግ ወደ ዝርዝሩ ልግባ።

ሐምሌ 30/2008 ዓ.ም እስኪደርስ በጣም ጓጉቼ ነበር። በዕለቱ ሊደረግ ስለታቀደው ሰላማዊ ሰልፍ የመሣተፍ ጉጉት ኖሮኝ አይደለም። የእና ዋና ትኩረት ሁኔታውን በንቃት በመከታተል፤ ያየሁትን፣ የሰማሁትንና የታዘብኩትን እውነት ለብዙሃን ማካፈል ነው። እናም እንዳይደርስ የለምና ቀኑ ደረሰ። ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ከቤት ወጥቼ ሁኔታዎችን መታዘብ ጀመርኩ። የዝናቡ ካፊያ እና የሚነፍሰው ቀዝቃዛ ንፋስ እንኳን ሰላማዊ ሰልፍ ከቤት መውጣት አያስመኝም። እስከ ጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ድረስ የአየሩ ሁኔታ አልተቀየረም ነበር። የነዋሪዎቹ እንቅስቃሴ ግን ቀስ-በቀስ እየተቀየረ እንደመጣ መገንዘብ ይቻላል።

Photo - Oromo protest in Woliso, August 6, 2016 [Credit: Social media]
Photo – Oromo protest in Woliso, August 6, 2016 [Credit: Social media]

በሰላማዊ ሰልፉ ለመሳተፍ ወጣቶች ሁለትና ሶስት እየሆኑ ከየአቅጣጫው ወደ መሃል ከተማ መምጣት ጀመሩ። ከከተማዋ ዳርቻ ሰፈሮች የሚመጡት በአብዛኛው ወጣቶች ናቸው። መሃል ከተማ ደግሞ ግማሹ ህፃናት ናቸው። ከሞላ-ጎደል ሁሉም ተሳታፊዎች ከ35 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶችና ህፃናት ናቸው። አብዛኞቹ ከ35 ዓመት በላይ የሆናቸው ጎለማሶች፣ አዛውንቶችና ሽማግሌዎች ዳር ቆመው ከመመልከት ባለፈ በሰላማዊ ሰልፉ አይሳተፉም። ምክንየቱም፣ ልክ አንደ አብዛኞቹ የሀገሪቱ አከባቢዎች፣ በወሊሶም እየታየ ያለው የሕዝብ ተቃውሞ ሳይሆን የትውልድ ግጭት ነው። ላለፉት ስምንት ወራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ተገድለዋል፣ በብዙ ሺህዎች ደግሞ ታስረዋል፥ ተደብድበዋል። ባሳለፍነው ሳምንት ከወሊሶ በተጨማሪ፣ በነቀምት፣ ሻሸመኔ፣ ሳጉሬ፣ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ አዲስ አበባ፣ …ወዘተ የሆነው ይሄው ነው። ይሄ ደግሞ ልክ እንደ ትላንቱ ነገም ይቀጥላል። 

አዎ… ያለ ምንም ጥርጥር የ1960ዎቹ እና የ1990ዎቹ ትውልዶች ተጋጭተዋል። ስለዚህ፣ እዚህ ጋር ቆም ብለን በሰከነ አዕምሮ ማሰብና መጠየቅ ያስፈልጋል። በወላጆች እና በልጆች መካከል ልዩነት ተፈጥሯል፥ ተለያይተዋል። በልዩነት ፀብ ተፈጥሯል። ልጆች አምፀዋል፣ ወላጆች ተቆጥተዋል። የዘመኑ ልጆች ሲቆጧቸው አይፈሩም፣ ሲገርፏቸው አይተውም፣ ቢያስሯቸውም አይቆሙም። ይሄው በሁለቱ ትውልዶች መካከል ፀብ ከተጀመረ አመት ሊሞላው ነው። ልጆቹም ተቃውሟቸውን አላቆሙም፣ ወላጆችም ከአቋማቸው ትንሽ ፈቀቅ አላሉም። Edmund Leach የተባለው የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር “A Runaway World”[PDF] በሚል ርዕስ በሁለት ትውልዶች መካከል ስለሚፈጠር ግጭትና ችግሩ ዙሪያ ዝርዝር ትንታኔ ሰጥቷል። ይህን ትንታኔ መሰረት በማድረግ በመግቢያዬ ላይ ለጠቀስኳቸው ጥያቄዎች ዝርዝር ትንታኔ ለመስጠት እሞክራለሁ። 

ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ሰዎች ሲደበደቡ፣ ሲታሰሩና ሲገደሉ “ሰው በሰው ላይ እንዴት እንዲህ ይጨክናል?” የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ለዚህ “Edmund Leach” የሚከተለውን ትንታኔ ይሰጣል፡- 

“…we [humans] kill one another. How does this come about? …My own guess is that our propensity to murder is a back-handed consequence of our dependence on verbal communication: we use words in such a way that we come to think that men who behave in different ways are members of different species. …Because of the way our language is organised and because of the way we are educated, each of us is constantly- finding himself in a position of contest. I identify myself with a collective we which is then contrasted with some other. What we are, or what the other is, will depend upon context. If we are Englishmen, then the others are Frenchmen, or Americans, or Germans…

If we are ordinary simpleminded citizens, the other is a mysterious they, the government bureaucracy …But lying in between the remote Heavenly other and the close predictable other there is a third category which arouses quite a different kind of emotion. This is the other which is close at hand but unreliable. If anything in my immediate vicinity is out of my control, that thing becomes a source of fear. This is true of persons as well as objects. If Mr X is someone with whom I cannot communicate, then he is out of my control, and I begin to treat him as a wild animal rather than a fellow human being. He becomes a brute. His presence then generates anxiety, but his Jack of humanity releases me from all moral restraint: the triggered responses which might deter me from violence against my own kind no longer apply.” REITH LECTURES 1967: A Runaway World – Lecture 3: Ourselves and Others 

በፅሁፌ መግቢያ ላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት፣ አሁን በኢትዮጲያ እየታየ ባለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ያሉት በአብዛኛው ከ35 ዓመት በታች እድሜ ያላቸው ወጣቶች ናቸው። እነዚህ ወጣቶች ራሳቸውን “እኛ” ሲሉ፣ በአብዛኛው እድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ የሆናቸውን የመንግስት ባለስልጣናትን ደግሞ “እነሱ” ያሏቸዋል። የተገላቢጦሽ የመንግስት ባለስልጣናቱ ራሳቸው “እኛ” ሲሉ፣ በተለያየ የሀገሪቱ ክፍል መንግስትን እየተቃወሙ ያሉትን ወጣቶችን ደግሞ “እነሱ” ይሏቸዋል። ወጣቶቹ “እኛ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ወጣን” ሲሉ፣ መንግስት “አመፅና ብጥብጥ ለማስነሳት ወጡ” ይላቸዋል። “ሰላማዊ ነን” እያሉ “ፀረ-ሰላም” እንደሆኑ ይነገራቸዋል። ራሳቸውን “ብዙሃኑ የኢትዮጲያ ህዝብ” ሲሉ “ጥቂት የኤርትራ መንግስት ተላላኪዎች ናችሁ” ይባላሉ። ሁለቱም ወገኖች “ህዝብ” እና “ሕገ-መንግስት” ይላሉ። ነገር ግን፣ ስለአንድ ነገር እያወሩ በሃሳብ ግን ፍፁም አልተግባቡም። በዚህ መሃል፣ የሕዝንም ሰላምና ደህንነት እና ሕገ-መንግስቱን የማስከበር ግዴታ ያለባቸው ፖሊሶችና ወታደሮች፤ “የሕዝብን ሰለምና ደህንነት ለማደፍረስ እና ሕገ-መንግስቱን በኃይል ለመናድ የወጡ ናቸው” ተብለው ይላክና፣ “ሕገ-መንግስቱ ይከበር” እያለ የሚጮኸውን ሕዝብ በዱላ ይደበድባሉ፥ በጅምላ ያስራሉ፥ በጥይት ይገድላሉ።   

በእርግጥ ሁላችንም ኢትዮጲያኖች ነን። ችግሩ በኢትዮጲያና በግብፅ ወይም በኤርትራ መካከል የተፈጠረ ቢሆን፣ እኛ “ኢትዮጲያኖች” እነሱ ደግሞ “ግብፃዊያን” ወይም “ኤርትራዊያን” ይሆኑ ነበር። ባለፉት ስምንት ወራት በተፈጠረው ችግር በዳይና ተበዳይ ኢትዮጲያኖች ነን። ነገር ግን፣ ሁለቱም አካላት ራሳቸውን “እኛ” እያሉ ሌሎችን “እነሱ” ይላሉ። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ “በሦስተኛ ክፍል” (third category) ውስጥ የተጠቀሱትን፣ በቅርብ ያሉትና የማያስተማምኑት “ሌሎች፥ እነሱን” መለየት አይቻልም። አሁን ካለው የኢትዮጲያ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር፣ እነዚህ የቅርብ ሩቅ የሆኑ፣ አቋምና ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው በቀላሉ የማይታወቅና የማይገመት፣ በዙሪያቸው ላሉት የስጋትና ፍርሃት ምንጭ የሆኑት “እነሱ” እነማን ናቸው? ከዚህ በተቃራኒ፣ አመፅና ብጥብጥ በማስነሳት የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ ይጥላሉ፣ በስርዓቱ የተገኘውን ሰላምና ልማት ይቀለብሳሉ፣…ወዘተ በሚል እሳቤ እንቅስቃሴያቸውን በከፍተኛ ጥርጣሬና ስጋት እየተከታተሉ እርምጃ የሚወስዱትስ እነማን ናቸው? በእርግጠኝነት አንደኛው ወገን የመንግስት ባለስልጣናት ሲሆኑ ሌላኛው ደግሞ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት ወጣቶች ናቸው። 

በፅሁፌ መግቢያ ላይ እንደገለፅኩት፣ አሁን በኢትዮጲያ እየታየ ያለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ በመሰረቱ የሁለት ትውልዶች ግጭት ውጤት ነው። ይህ በሁለት ትውልዶች መካከል አንድን ስርዓት ለማስቀጠል ወይም ለመቀልበስ የሚደረግ ትግል እንደ እንግሊዝ ባሉ ሀገራት በ1960ዎች አከባቢ ያጋጠመ ችግር ነው።

“A Runaway World” በሚል ርዕስ Edmund Leach የሰጠው ትንታኔም በዋናነት በወቅቱ በአንግሊዝ ስለነበረው የትውልድ ግጭት ሲሆን፣ ቀጥሎ ባለው ጥቅስ ውስጥ፣ ከላይ በባለስልጣናት እና በወጣቶች መካከል “ማ…ማን ነው?” በሚል ላነሳነው ጥያቄ ግልፅ የሆነ ምላሽ ይሰጠናል።  

“Tension between the generations is normal for any society; every son is a potential usurper of his father‘s throne; every parent feels under threat; but the present anxiety of British parents seems altogether out of proportion. Young people are being treated as an alien category: ‘wild beasts with whom we cannot communicate’. They are not just rebels but outright revolutionaries intent on the destruction of everything which the senior generation holds to be sacred. …

Let us be clear about this. What is odd is not the behaviour of the young but the reaction of the old. …It is because the old allow themselves to feel separated from the young that the young create anxiety. They [youths} are the involuntary heirs to a generation of incompetents. Their seniors, who still keep all the power in their own hands, have made a total mess of things. …

The whole set-up is rigged to fit the belief that, when the young grow up and come to power, they too will carry on running the show just as before. But this assumption makes co-operation impossible. If the old expect the young to participate in planning the future, then they might at least take the trouble to find out what sort of future the young would actually like to have.” [Reith Lectures 1967: A Runaway World – Lecture 3: Ourselves and Others]

አሁን ማ…ማን እንደሆነ በግልፅ መለየት ይቻላል። በሦስተኛው ክፍል ስር ያሉት አመፀኞቹ ወጣቶች የለውጥ ኃይሎች ሲሆኑ፣ የለውጥ ማነቆ ሆነው ያሉት ደግሞ የመንግስት ባለስልጣናትና ደጋፊዎቻቸው ናቸው። በግልፅ አነጋገር ይሄ በልጆች እና ወላጆች መካከል የተፈጠረ ልዩነት ነው። ባለፉት ስምንት ወራት ልዩነቱ እየሰፋ ሄዶ የትውልድ ግጭት ለመሆን በቅቷል። ከዚህ በኋላ የ1960ዎቹ እና የ1990ዎቹ ትውልዶች እርስ-በእርስ ተነጋግረው መግባባት አይችሉም። ይህ የሆነው፣ የዚህ ዘመን ትውልድ ወጣቶች የሚናገሩትን ሳያውቁ ወይም ባለስልጣናቱ የሚናገሩት ነገር ሳይገባቸው ቀርቶ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ”Edmund Leach” እንዳለው፣ የ1960ዎቹ ትውልድ አባላት የሆኑት አብዛኞቹ ባለስልጣናት ወጣቶቹ የሚናገሩት ነገር ለመረዳት ብቃትና ፍላጎት ስለሌላቸው ነው። 

አሁን በኢትዮጲያ እየታየ ያለው ችግር  መንስዔ የወጣቶቹ አመፀኝነት፤ የተገነባውን የማፍረስ፥ ስርዓቱን የመቀልበስ፣ ሰላምና መረጋጋትን የማደፍረስ አባዜ ስለተጠናወታቸው ሳይሆን፣ የሚገባቸውን በመጠየቅና የማይገባውን ነገር በማስቀረት በወደፊት እድላቸው ላይ ለመወሰን ብቃትና መብት ስላላቸው የተፈጠረ ግጭት ነው። በተለይ ከቅርብ ግዜ ወዲህ መንግስት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ትችትና ተቃውሞ እያጋጠማቸው ያለው ለዘመኑ ወጣቶች ሃሳብና አስተያየት ትኩረት ሳትሰጡ በወደፊት እድላቸው ላይ የራሳችሁን ፍላጎትና ምርጫ እየጫናችሁ ስለሆነ ነው።

በአጠቃላይ፣ ከዚህ በኋላ ሀገሪቷንና ህዝቧን በበቂ ሁኔታ ለማስተዳደር የሚያስፈልገው ብቃት እና አመለካከት የላችሁም። ምክንቱም፣ እናንተ በስልጣን ላይ ያላችሁ አብዛኞቹ የቀድሞ ትውልድ አባላት፤ ብዙ ነገር አታውቁም፣ አለማወቃችሁንም አታውቁም፣ ያላወቃችሁትን ነገርም ማወቅም አትፈልጉም። ለምሳሌ ዴሞክራሲን በንድፈ-ሃሳብ ደረጃ እንጂ በተግባር አታውቁትም። በንድፈ-ሃሳብ ላይ የተመሰረተው እውቀትና ግንዛቤ ሕገ-መንግስትን ከማፅደቅ ያለፈ አልሄደም። በዚህ ምክንያት፣ አዲሱ ትውልድ ስርዓቱን በኃይል መናድ ይቅርና እናንተ ያወጣችሁትን ሕገ-መንግስት ለማክበርና ለማስከበር እንኳን እድል አልሰጣችሁትም። “ሕገ-መንግስቱ ይከበር” ብሎ የወጣ ወጣትን “ፀረ-ሰላም እና ፀረ-ልማት” እያላችሁ ለሞትና እስር እየዳረጋችሁ የሀገሪቷንና የትውልዱን ተስፋ አያጨለማችሁ ነው። እስካሁን ላበረከታችሁት አስተዋፅዖ እናመሰግናለን። በዚህ አያያዛችሁ ከ25 ዓመት በፊት የተረከባችኋትን ሀገር እንደነበረች መልሳችሁ እንደምታስረክቡን ምንም ጥርጥር የለውም። ስለዚህ፣ ኢትዮጲያ የወጣቱ ናትና እባካችሁ ልቀቋት!

*********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories