ህገ መንግስቱን የሚጻረረው የሠራዊት ግንባታ ሰነድ ከሥራ ይታገድ (ሜ/ጄነራል አበበ ተ/ሃይማኖት)

(አበበ ተክለሃይማኖት – ሜጀር ጄነራል)

ግልፅ ደብዳቤ – ለክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ

ጉዳዩ – “የሰራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ” የሚለው መጽሐፍ ስለማገድ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር

በተለያዩ ግዜያት ለመጠቆም እንደሞከርኩት፤ አንዳንድ ግዜ እንደተቋም ሌላ ግዜ በከፍተኛ መኮንኖች ፀረ ህገ-መንግስት የሆኑ ድርጊቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ የአገራችን መከላከያ ተቋም ሕገ-መንግስቱ እና ሕገ-መንግስቱን ብቻ መሰረት አድርጐ መንቀሳቀስ ሲገባው በግላጭ ሕገ-መንግስቱን የመጣስ ክስተቶች እየታዩ ነው፡፡ አንድ ፀረ-ሕገመንግስት ተግባር ሲጠቆም በማረም ፈንታ በማን አለብኝነት እና በሕብረት በባሰ ሁኔታ እየተደገመ ነው፡፡ለምን? የሰራዊቱ አመራሮች ሕገ-መንግስቱን ጠንቅቀው አያውቁም ብሎ ለማመን አስቸጋሪ ነው፡፡

አሁን ስራ ላይ ካሉ ከፍተኛ መኮንኖች፣ በጡረታ ከተሰናበቱ፣ እንዲሁም ‹‹እንከን በሌለው መተካካት›› ከተገለሉ ከፍተኛ መኮንኖች ጋር በተለያዩ ግዜያት የመወየያት እድል ገጥሞኛል፡፡ከወርቃማው የ1997 አጠቃላይ ምርጫ በኋላ ህዝቦችን ለመቆጣጠር የተወሰዱት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ፖለሲዎች፣ መመሪያዎች፣ አሰራሮችና ተግባሮች ወደ መከላከያ ተቋም ገብተዋል እንዴ የሚል ጥያቄ ሲያጭርብኝ ቆይቷል፡፡ ሕገመንግስቱን መፃረር የሰራዊታችንን ሕዝባዊነት ጀግንነት እና ብቃት የሚሸረሽር በመሆኑ እና ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግሉን የሚያበላሽ በመሆኑ ለማንኛውም ኢትዮጲያዊ የሚያሳስብ ነው፡፡

‹‹የሰራዊቱ ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ›› የሚለውን መፅሐፍ ሳነብ ግን መሰረታዊ ችግሩ በከፊልም ቢሆን የት ላይ እንደሆነ ሊገለጥልኝ ቻለ፡፡ ሰራዊቱ የገዢው ፓርቲ ርዕዮተ አለም አራማጅ የኢህአዴግ ‹‹የመጨሻው ምሽግ›› እንዲሆን ወይም ‹‹ቀባሪው እንዳይሆን›› መገንባት ከተጀመረ አገሪቱን ወደ  ከፍተኛ ችግር ማስገባቱ የግድ ይሆናል:: የፓርቲው ውስጣዊ ፖለተካዊ እና ዴሞክራሲያዊ ህይወት በተዳከመበት ሁኔታ ደግሞ ሰራዊቱ የተወሰኑ አመራሮች “የመጨረሻ ምሸግ” ይሆናል ማለት ነው፡፡

በመከላከያ ሚኒስቴር ስር በሚገኘው “ብራና ማተሚያ ድርጅት“ የታተመው መፅሐፍ 209 ገፆች ያሉት ሲሆን ሕገ-መንግስቱን እና “አብዮታዊ ዴሞክራሲ“ የሚለውን ርዕዮተ ዓለም በማደባለቅና በማምታት ስለሰራዊት ግንባታ ይዘባርቃል::

ክቡር የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ

የመፅሐፉ ርዕስ ‹‹የሰራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ነው የሚለው፡፡ ሰነዱ ከርዕሱ ጀምሮ ምን ማለት መሆኑ ቢታወቅም የበለጠ ግልፅ ለማድረግ የተለያዩ ጥቅሶችን ማስቀመጥ ይበጃል በሚል ጥቂት ጥቅሶችን እንዳቀርብ እንዲፈቀድልኝ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡

የመከላከያ ኃይል ግንባታ አላማችን በሚል ንዑስ-ርዕስ ሥር፡-

‹‹እኛ የያዝነው አላማ እና ተግባራዊ እያደረግነው ያለ መደብ በሃገራችን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጦች እንዲካሄድ ይህ ስርአት ስር እንዲሰድ ማድረግ ነው፡፡›› (ገፅ 20)

 ‹‹እኛ የምንገነባው የመከላከያ ኃይል የአብዮታዊ ዲሞክሪሲያዊ ስርአታችን ዘብ ነው ብለን በግልፅ እና በጥሬው ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው›› ይላል ምን አይነት እብሪት ነው? (ገፅ 22)

‹‹ለአንድ ፓርቲ ዘብ በመሆን መልክ ሊገልፅ ይችላል፡፡ ከፓርቲው ውጭ ሆነም ስርአቱን እንደስርአት ሕግመንግስት  እና ሕገመንግስታዊ ስርአቱን በመጠበቅ አንፃር ሊገለፅ ይችላል፡፡›› (ገፅ 23)

‹‹በእኛ ተጨባጭ ሁኔታ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአታችን ደህንነት መከላከል ማለትና የሃገር ደህንነት መከላከያ ማለት በመሰረቱ አንድ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከሌለ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህብራዊ ልማት፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነት .. አይኖርም፡፡ ይህ ከሌለ ደግሞ ሀገሪቱ መጨረሻ ወደ ሌለው ቀውስና ግጭት ገብታ መበታተን ነው፡፡ ስለሆነም ሀገሪቱ  እንደሀገር መቀጠል የምትችለው በአብዬታዊ ዴሞክራሲ ነው ማለት ይቻለል፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ሀገራችንን መከላከልና አብዬታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን መከላከል አንድና የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡›› (ገፅ 25-26)

‹‹ስለሆነም ለእኛ የሃገራችንንናአብዮታዊ ዴሞክራስያዊ ስርአታችንን ደህንነት መከላከል (መጠበቅ) የተለያዩ ነገሮች አይደሉም፡፡አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአታችን ከሌለ የኛ የምንላት ሃገር አትኖርም›› (ገፅ 27)

‹‹የምንገነባቸው በመከላከያ ኃይል አላማው የስርአታችንን ደህንነት መጠበቅ ነው ሲባል የሚገነባውና የሚመራው የስርአቱ መሪ የሆነው አካል ብቻ መሆን አለበት ነው›› (ገፅ 28)

‹‹የመከላከያ ኃይላችን ግንባታ ስራ አላማው ምን እንደሆነና ከዚህ የሚመነጩ የመከላከያ ኃይላችን ባህሪያት ምን እንደሚሆኑ በግልፅ ለያይቶ ማስቀመጥ በዚያች ቁርጥ ቀን ማለት የስርዓታችን ህልውና በመከላከያ ኃይላችን ብቃትና ምንነት ላይ በምትንጠላጠልበት ጊዜና ወቅት አስተማማኝ መከላከያ ምሽግ መሆኑን በማረጋገጥ በኩል ወሳኝ ሚና ያለው ጉዳይ ነው፡፡›› (ገጽ 31)

‹‹ጉዳዩ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ስርዓቱ በመጨረሻ መከላከያ ምሽግ የሌለው ስርዓት ሆኖ እንዳይቀር በማድረግ ወይም በመከላከል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ጠባቂዬና አለኝታዬ ብሎ የሚለው ሰራዊት ተመልሶ ቀባሪው ሆኖ እንዳይገኝ የማድረግ ጭምር ነው፡፡›› (ገጽ 81)

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር

የኢትዮጵያ መከላከያ ተቋም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ብሎም የኢህዴግ ‹‹ጠባቂ›› እንዲሆን – በሌላ አነጋገር የጥቂት ሰዎች ‹‹ጠባቂ›› እንዲሆን – በተለያየ መንገድ በጭንቀት፣ በልመና የተደጋገመው ጸሎት አይሉት ምህላ በጣም እንደሚሰለች ይገባኛል፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝ፡፡ እኔም ስልችት እያለኝ ደጋግሜ ያነበብኩት የመከላከያ ተቋሙ በምን መልኩ ከህገ-መንግስታችን ተጻራሪ ሆኖ እየሰራ  መሆኑን እንዲያሳይ ነው እንጂ፡፡

መጽሐፉ ሕገ-መንግስታችንን በውል መጥቀስ የጀመረው በገጽ 87 ነው፡፡ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ “የቁርጥ ቀን” መከላከያ መሆኑን በተደጋጋሚ ካስረገጠ በኋላ በ2.1 ሕገመንግስታችን እንደ ሰራዊታችን ግንባታ መነሻ በማለት ማብራራት ይጀምራል፡፡ መዘባረቁን በማያሻማ ሁኔታ እየቀጠለ ፀረ ዲሞክራቲክ አስተሳሰብ ደግሞ ከደርግነት ባላነሰ መንገድ ሲገልጸው እንደገና “ኢህአዴግ ከሌለ ይህች ሀገር የለችም” በሚለው  አባባል ሲያመላልሰው ይታያል፡፡

እባክዎ  እንደገና ከመጽሐፉ በስፋት እንድጠቅስ ይፍቀዱልኝ፡-

ህገመንግስታችን  ለሰራዊት የፖለቲካ ግንባታ ስራችን ወሳኝ መነሻ ነው የምንለው ህገመንግስታችን ሰራዊቱ የህገመንግስቱ ታማኝ ጠባቂ መሆን አለበት በማለት በግልጽ ስለሚያስቀምጥ ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች ዲሞክራሲያዊ ስርዓቶች እንዲህ ዓይነት አካሄድ ስለተከተሉም አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህ አባባል በሕገመንግስታችን በግልፅ እንዲቀመጥ የተደረገበት ዋነኛ ምክንያት ህገመንግስቱ የአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ጠባቂ የሆነ ሰራዊት ለመገንባት ለሚካሄደው የፖለቲካ ግንባታ ስራ በቂና ብቁ መነሻ እንዲሆን ስለታመነበት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ቀደም ብሎ እንደተመለከትነው በሁሉም አገሮች በመከላከያ አቅም በሚገነባው አንድን ስርዓት ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ለመከላከል ተብሎ ነው፡፡ በእኛ ሁኔታም የተለየ ዓላማ ሊኖረው አይችልም፡፡ እኛ የምንገነባው ሰራዊት አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓታችንን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ለመከላከል ተብሎ በሚገነባ ሰራዊት ብቻ ነው መሆን የሚችለው፡፡ በአሁኑ ወቅት አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓታችን እና ኢህዴግ ተለያይተው ሊታዩ የሚችሉ አይደሉም፡፡ የሊበራል ዲሞክራሲ አስተሳሰብ የበላይነት በነገሰበት ወቅት ሁሉም ፓርቲዎች ማለት ይቻላል መሰረታዊ የሊበራል ዲሞክራሲ አስተሳሰቦችን ተቀብለው በዚህ ዙሪያ ብቻ ነው የሚለያዩት በየጊዜው እየተቀየሩ ወደ ስልጣን ቢመጡም በስርዓቱ ላይ የሚመጣ መሰረታዊ ለውጥ የለም፡፡ ስለሆነም ስርዓቱ ከእያንዳንዱ ፓርቲ ተለይቶ የሚታይና ሊታይ የሚገባው ይሆናል፡፡ (ገጽ 88 – 89)

ክቡር የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ

የ1997 ምርጫ ህዝቦቻችን ዕድል ሲያገኙ ምን ማድረግ እንደሚችሉ ያሳየ ነው፡፡ በቀጣዩ ምርጫ ለምሳሌ መድረክ ቢያሸንፍ የመከላከያ ሰራዊታችን የኢህአዴግ የቁርጥ ቀን በመሆን መድረክን ስልጣን እንዳይቆጣጠር ይከላከላሉ? ጠበንጃቸውን በህዝቦች የተመረጠ እና በህዝቦች ላይ ያዞራሉ ማለት ነው? መድረክ በሊበራል አስተሳሰቦች ዙረያ የተደራጀ በመሆኑ በምርጫ ከአሸነፈ አሁን ያለውን መከላከያ ተቋም እንዳለ አፍርሶ ሌላ የራሱ ሊገነባ ማለት ነው? የሆነ ፓርቲ በሰላማዊ  መንገድ ባሸነፈ ቁጥር በሚፈርስና በሚገነባ የመከላከያ ተቋም ታይቶም ተሰምቶም አያውቅም ፡፡ ለተወሰኑ ሰዎች ለኢህዴግ ሃላፊዎች ሲባል አገራችንን ለማፍረስ መዘጋጀት ማለት እኮ ነው፡፡

ይህ አስተሳሰብ አብዮታዊም ዲሞክራሲያዊም አይደለም፡፡ በእኔ አረዳድ አብዮታዊ ዲሞክራሲ “ሊበራል ዲሞክራሲ መራመድ እስከሚችለው ጫፍ መውሰድ ነው”፡፡ በሌላ አነጋገር አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከሊበራል ዲሞክራሲ በላይ ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ የህዝቦቻችን የመወሰን ስልጣን በተሻለ የሚያምን ነው፡፡ እኛ ካልተመረጥን አገሪቱ ገደል ትግባ የሚል የጽንፈኞች አስተሳሰብ መሆን አልነበረበትም፡፡

ክቡር የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ

በዚህ መፅሐፍ ውስጥ በእውነትና በቅንነት የታመነበት ቢሆን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ምን ማለት እንደሆነ ትርጓሜ ይሰጠው ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ምንነት በአንዳንድ ከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ ሳይቀር የማይታወቅ መሆኑን በየቀኑ በቴሌቪዥንም በአካል እየተስተዋለ ነው፡፡

አንድ ቀን ያጋጠመኝን ላካፍልዎ፡- ሶስት ሆነን ስለ ኢትዮጵያ ሁኔታና ስለአንድ መሪ ስናወራ የልማት መሪም አርበኛም (Champion) ናቸው በሚል ተስማማን፡፡ አንዱ ተነስቶ የልማት አርበኛ ብቻ ሳይሆኑ የዴሞክራሲያዊ ሻምፒዮን ናቸው አለ፡፡ ሶስተኛው ተነስቶ ‹‹እስኪ አብራራው›› አለው፡፡ በጥርናፈ (Centralism) ያምናል አለን:: አፈርን! ተሳቀቅን! ግን ስለዴሞክራሲ ያለው አመለካከት እስከዚያ ድረስ የወረደ መሆኑን በየቀኑ የምናየው ክስተት በመሆኑ አዝነን፤ ይህች አገር ወዴት እየሄደች ነው አልን፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር

አሁንም በተለያዩ መንገድ የአገር መከላከያ ተቋም እና የኢህዴግ አባላት የስራቸውና የአኗኗራቸው ሁኔታ የተለያየ በመሆኑ መጠነኛ የአቀራረብ ልዩነት ይኖር ይሆን እንጂ አንድ ናቸው በማለት በገጽ 100 – 101 እንዲህ ይላል፡፡

‹‹በሰራዊታችን የምናካሂደው የፖለቲካ ስራ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ግንባታ ሰራ ነው፡፡ ስለሆነምመሰረታዊ የአፈጻጸም አግባብ በድርጅታችን ውስጥ ከምናካሂደው የግንባታ ሰራ የተለየ አይሆንም፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖሰራዊቱ እና የኢህዴግ አባላት የስራቸውና የአኗኗራቸው ሁኔታ የተለያየ መሆኑ አይቀርም፡፡ ከዚህ የተነሳ በሁለቱም የግንባታው ሰራ አፈጻጸም አንዳንድ ልዩነቶች ሊኖሩት የግድ ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፖለቲካ ግንባታ ሰፊ መሰረታዊ አፈጻጸሞችን እንዳለ ነው የምንወስደው፡፡ የሚዲያው ሰራ በገዛ ራሱ ለህብረተሰቡ በሚዘረጋውና ሰራዊቱም እንደማንኛውም ሰው በሚሰማው ወይም ገዝቶ በሚያነበው በመንግስትና በድርጅት ሚዲያ አማካይነት ሊፈጸም ይችላል፡፡” (ገጽ 116) 

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር

በመጽሐፉ ውስጥ የተለያዩ ጥያቄዎችን ለማንሳት የሚያስችሉ የተዘበራረቁ ጉዳዮች አሉ፡፡

“እኛ” ብለው ስለሰራዊታችን ግንባታ የሚጽፉት አመራሮች “የቁርጥ ቀን” ደራሽ እንዲሆንላቸው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሽፋን በማላወስ እኛን አገልግሉ ከማለት ውጭ ያስቀመጡት የተለየ የግንባታ ዓላማዎች እና አቅጣጫዎች የሉም፡፡ ከሞላ ጎደል “በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ እና የብሔራዊ ደህንነት ፖሊሲ” ሰነድ ላይም የተቀመጡ ናቸው፡፡ በአደባባይ ለህዝብ በዚያ ሰነድ ላይ ግን “የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ኢህዴግ የመጨረሻ መከላከያ ምሽግ አይልም” ለምን?

ሕገ-መንግስቱ በሰላም እስኪታገሉ ድረስ ህገ-መንግስቱ ራሱን በማሻሻል መብት የሚያስቀምጥ ነው፡፡ ከበላይ ህጋችን አኳያ ሁሉም በሰላም የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች እና የህብረተሰብ ክፍሎች እኩል ናቸው፡፡ በሰራዊቱ ልዩ ጥበቃ የሚያስፈልገው ፓርቲ ወይም የሚገለል ወይም የሚመታ ፓርቲ የለም፡፡ የሚገርመው ነገር ግን በአሁን ጊዜ አብዛኛዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የህብረተሰብ ክፍሎች ‹‹ህገ-መንግስቱ ይከበር›› ሲሉ የህገ-መንግስቱ አቀንቃኝ የነበረው ኢህዴግ በግላጭ ሲሸረሸር እና “አብዮታዊ ዴሞክራሲ”ን እንደ አድሃሪያን መሸሸግያ ሲጠቀምበት በጣም ያሳዝናል፡፡ ገዥ ፓርቲ በመሆኑ ደግሞ ያስፈራል፡፡

አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚል “ምትሓተኛ” አስተሳሰብ እንዳለና እጅግ እንደላቀ ልዩ ነገር “Mystify” ተደርጎ የማይተነተን፣ የማይታወቅ፣ ሰው በጭፍን እንዲያምነው የሚደረግ ሙከራ አሳሳቢ ነው፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ይሁን ሊበራል ዲሞክራሲ ሁሉም ካፒታሊሰታዊ ስርዓት ለመገንባት ዓላማ አድርገው ነው የሚንቀሳቀሱት ያውም እስከ “ነጭ ካፒታሊዝም” ተብሎም ነበር፡፡ በካፒታሊስት ስርዓት ከማንም በላይ ተጠቃሚዎች ካፒታሊስቶች ናቸው፡፡

እስከሚገባኝ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሚገባ ከተተገበረ የገበሬዎች፣ የላብአደሮች ፣ሌሎች ዝቅተኛ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጥቅም በሚረጋገጥበት መንገድ ስርዓቱን ሊመራ ይችላል፡፡ ሃብት በመፍጠር ሂደት ክፍፍሉ በተቻለ ደረጃ ፍትሃዊ ማድረግ ነው፡፡ እንደዛውም ሆኖ አሁንም ዋናው ተጠቃሚ ካፒታሊስቱ ነው፡፡ አሁን እየተመዘገበ ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ብቻ እንኳን ብናይ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚዎች ቢሆኑም በሀብታም እና ድሃ ያለው ልዩነት በጣም እየሰፋ ከመሄድ አላገደውም፡፡ ባልሆነ ተስፋ በማይመስል አስተሳሰብ አገር እንዳይጎዳ መጠንቀቅ ጥሩ ነው፡፡

በገጽ 126 ያለውን እስኪ እንየው፡-

ሁሉም በተራ ውትድርና እንዲያልፍ የሚደረግ አሰራር ከሰራዊታችን ባህሪ ጋር የሚሄድ ብቻ ሳይሆን ለሰራዊታችን የተለያዩ ጥቅሞችም የሚያስገኝ ይሆናል፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ይህ አሰራር ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ በከፍተኛ ደረጃ የማይጠቀሙ ወገኖች ወደ ሰራዊቱ ለመግባት ፍላጎት እንዳይኖራቸው የሚያደርግና በአንጻሩ በስርዓቱ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ የሆኑ ወገኖች ብቻ ሰራዊቱን እንዲቀላቀሉ የሚያደርግ አካሄድ ነው፡፡››

ይህ ደግሞ ሌላ hypocrisy ይመስለኛል፡፡ ከስርዓቱ በከፍተኛ ደረጃ የማይጠቀሙ ወገኖች ሲባሉ እነማናቸው? መሳፍንት? አሁን የሉም የመሳፍንት ልጆች፡፡ እረ ተዉ! ኢሰፓ የነበሩ? እነሱም ወሳኝ ሚና የላቸውም፡፡ የሚቀሩት ገበሬ፣ ላብአደር፣ ምሁርና ካፒታሊስት ወዘተ ናቸው፡፡  ገበሬው መቼም አይታሰብም፤ ላብአደር ተጠቃሚ ተብሏል፤ ካፒታሊስቱ የለም – እሱማ ዋናው ተጠቃሚ ነው፤ ምሁሩ? አረ እንጃ እንዳይፈነግላቸው እየፈሩ ካልሆነ እሱም በጣም ተጠቃሚ ነው፡፡

ታዲያ በከፍተኛ ደረጃ የማይጠቀሙ ወገኖች እነማ ናቸው? ፖለቲካዊ ስርአቱ የራሱን ችግር ላለማየት (externalize) ለማድረግ የሚደረድራቸው ጠላቶች እንዳይሆኑ? ትምክህትና ጠባብነት በህብረተሰቡ በሚታዩ ኋላቀር አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ የተወሰኑ ልሂቃን ይህን በህብረተሰቡ ያለውን ኋላቀር አስተሳሰብ መሰረት አድርገው ለራሳቸው ጥቅሞች ሲሉ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ስርአቱን እንዲናጋ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህንም ቢሆን በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ለነሱ መሰረት የሚሆነው የዴሞክራሲ አሰተዳደር እጥረት ነው፡፡ እነዚህን ለማግለል ሲል ደግሞ የሰራዊቱን ሙሁራዊ አቅም እየገደለ እንዳይሆን መፈተሹ ተገቢ ነው፡፡

ወደ ሰራዊታችን በመጀመሪያ የሚሰለፈው ከ 18 – 23 አመት አካባቢ ያለ ወጣት ነው፡፡ የወላጆቹን የመደብ ጀርባ እያዩ ላለማስገባት ሲባል ከ10ኛ ክፍል በመመልመል በሚደረግ የሰራዊት ግንባታ ሂደት ከፍተኛ አመራር ለመፍጠር የሚደረግ አካሄድ አደገኛ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የተማረ ሰው የመጥላት አዝማሚያ እንዳይሆን፡፡

“እኛ” በቀዳማዊ ኃይለስላሴ አነጋገር አንድ ሰው ነው:: ምናልባትም ንጉሳዊ ቤተስብ ይሆናል፡፡ “እኛ” ማለት ከአንድ ሰው በላይ ቢሆን ማነው? 36ቱ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ? የኢህዴግ ምክር ቤት አባላት? 7 ሚሊዮን የሚሆኑት አባላት ቢሆኑስ? የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ልእልና እንዳልነገሰ መፅሃፉ በተደጋጋሚ ይገልፅልናል፡፡ ይህ ማለት ቢያንስ ከ85 ሚሊዮን በላይ ህዝባችን፤ ሰራዊታችን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የመጨረሻ ምሽግ እንዲሆን አልወሰነም፡፡ ‹‹የሰራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ላይ ያለው እኛ” አድሃሪ ነው፣ፀረ-ዴሞክራቲክ ነው፣ ፀረ-ህገመንግስት ነው፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር  እና የጦርሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ

በእኔ አመለካከት ሰራዊታችን የህዝቦቻችን እና የአገራችን አለኝታ የሚሆነው ህገመንግስቱንና ህገመንግስቱን መሰረት ተደርጎ የሚወጣ ፖሊሲ፣ መመሪያ፣ አሰራር እና ግንባታ ሲኖር ነው፡፡ ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የመጨረሻ ምሽግ ነው›› ሲባል ግን የሰራዊቱ ምልመላ፣ የስልጠና፣ የዝውውር፣ የእድገት፣ የጡረታ ማራዝም፣ በመተካካት የሚገለሉበት ሂደት እንዲሁም አጠቃላይ የሰራዊት ግንባታው “በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ” መዝሙር በሚዘምሩ፣ “የአብዮታዊ ዴሞከራሲ” ወሬ በሚያቀብሉ እና ህገመንግስቱን በግላጭ የሚጥስ አባላት ያለበት ሰራዊት እንዳይሆን ስጋት አለኝ፡፡ በአጠቃላይ ከህዝቦቻችን በተለይም ደግሞ ከፖለቲካ ድርጅቶች የሚኖረውን ግንኙነት በጣም አሳሳቢ ያደረገዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝቦች ለመብታቻው ባደረገት ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ለደረሰው ጉዳት እርሶዎ ይቅርታ ሲጠየቁ በኢትዮጵያ ውስጥ ባልተለመደ መንገድ ህዝብን የሚያከብር በመሆኑ ለህዝብ ይቅርታ ማለት ፈር ቀዳጅ በመሆንዎ ብዙዎቻችን ኮርተናል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የተወሰደው እርምጃ “ተመጣጣኝ” ነው ሲል እንደገና አፈርን፣ ፓርላማው ሲያፀድቀው የባሰ ተሸማቀቅን፡፡ ዴሞክራሲ አስተዳደርን በማበላሸት ዋናው ተጠያቂ የኢህአዲግ መንግስት ሆኖ እያለ በዜጎች ላይ የደረሰው ጉዳት ተመጣጣኝ ሲባል ያሳዝናል፡፡ እነዛ የሞቱት የቆሰሉት የታሰሩት በሙሉ አሸባሪዎች ናቸው ማለት ነው?

በአጠቃላይ የስርአቱ ጉዳይ ግን  እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤታችን ስለመከላከያ በየግዜው የሚገመግመው “እንደ መከላከያ የለም” የሚያሰኝ ነው፡፡ እንደ ‹‹የሰራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ያለ መሰረታዊ የግንባታ ዶክመንት እና ህገመንግስቱን በሚፃረር መንገድ የሰራዊቶቻችን ግንባታ ሲካሄድ “ዓይኑ እንዳላየ” “ጆሮው እንዳልሰማ” ማወደስ የማይሰለቸው ተቋም በመሆኑና በእርስዎ የሚመራው የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤትም ከዚህ አኳያ ቢፈተሽ መልካም ይመስለኛል፡፡

ይህ የሰራዊት ግንባታ መጽሐፍ፡- ሰራዊታችን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የመጨረሻ ምሽግ ነው የሚለው አስተሳሰብ፤ ኢህአዴግ ከሌለ የኢትዮጵያ ህዝቦች የሉምየዚህች አገር ችግሮች በኢህአዴግ ብቻ እና ብቻ ይፈታልአብዮታዊ ዴሞክራሲ ከሌለ አገር የምንለው የለም፣ የሚሉ ሀሳቦች፤ በተለይም የህገ መንግስት ምሰሶ ከሆኑት አንዱ ተቋም የሆነው መከላከያችን ከየትኛውም ዓይነት የፖለቲካ ድርጅት ወገንተኝነት ነፃ ይሆናል የሚለውን እና የሕገ -መንግስቱ አንኳር የሆነውን የመድብለ ስርአት ግንባታ የሚጻረር በመሆኑ ይወገድ፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ የህገ መንግስት ጠማማ አተረጓጎም ለአገር ጥፋት እንዴት እንደሚውል የሚያሳይ በመሆኑ እኛም ልጆቻችንን እንድንማርበት በሙዝየም ውስጥ ይቀመጥ፡፡ በአስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ፣ አጠቃላይ የመከላከያ እንደ ተቋሙ እንዲፈተሽ እና Re-indoctrination እንዲደረግ እንደማንኛው ዜጋ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡

********

* ሌሎች የሜ/ጄ አበበ ተክለሃይማኖት ጽሑፎች

Guest Author

more recommended stories