የሀብታሙ አያሌው ጉዳይ፡- “ፈጣን ውሳኔ ባለመሰጠቱ የመዳን ተስፋው እየጨለመ ይገኛል”

(ማይክ መላከ)

የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል አቶ ሀብታሙ አያሌው ከሃኪም ቤት ከወጣ እነሆ ዛሬ 12ኛ ቀኑ ነው።

በካዲስኮ ሆስፒታል አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ቢያገኘም ህመሙን ከማስታገስ በስተቀር ማዳን አልተቻለም። ብዙዎቻችን ኪንታሮት የተለመደና በቀላሉ የሚድን በሽታ መሆኑን እናውቃለን። ነገር ግን፣ የኪንታሮት ብሽታ አራት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን፣ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ያሉት በቀላሉ ግን በሀገር ውስጥ ህክምና የሚድኑ ናቸው። በሽታው ሶስተኛና አራተኛ ደረጃ ከደረሰ  የግድ የቀዶ-ጥገና ሕክምና ያስፈልጋል። የካዲስኮ አጠቃላይ ሆስፒታል የሕክምና ቦርድ እንዳረጋገጠው፣ ሀብታሙ አያሌውን የያዘው የኪንታሮት በሽታ አራተኛ ደረጃ ደርሷል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ሀብታሙ የኩላሊት ጠጠርና የጨጓራ በሽታ ታማሚ ነው።

የኪንታሮት በሽታን ለመታከም የተለያዩ ዓይነት የቀዶ-ጥገና ዘዴዎች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው በባህላዊ መንገድ የሚሰጠው ህክምና ሲሆን በሀገራችን በስፋት የተለመደ ነው። ነገር ግን፣ ባህላዊው ዘዴ ከፍተኛ የሕመም ስቃይ ያለው ከመሆኑም በላይ ኪንታሮቱ ዳግም ተመልሶ ሊወጣ ይችላል። ሁለተኛው አማራጭ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገራችን የሕክምና ተቋማት ውስጥ የሚሰጠው የ“traditional hemorrhoidectomy’ የሕክምና ዘዴ ነው። በዚህ መንገድ የሚሰጠው ሕክምና ረጅም የማገገምያ ጊዜ የሚጠይቅ ነው።

የካዲስኮ አጠቃላይ ሆስፒታል የሕክምና ቦርድ በሰጠው ማረጋገጫ መሰረት፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው በሀገር ውስጥ ሕክምና ለማግኘት አራት ጊዜ የቀዶ-ጥገና ማድረግ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ቀዶ-ጥገና የስድስት ወር የማገገሚያ ግዜ ይጠይቃል። በዚህ መሰረት፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው ከበሽታው ለመዳን ድፍን ሁለት (2) አመታት በሕክምና እና በሕመም ማስታገሻ መኖር ይጠበቅበታል። ሦስተኛው የሕክምና አማራጭ “stapled hemorrhoidopexy” የሚባለው ዘመናዊ የቀዶ-ጥገና ዘዴ ሲሆን በአንድ ጊዜና በአጭር የማገገምያ ጊዜ ከበሽታው የሚፈውስ ነው።

ይህ የሕክምና ዘዴ የተጀመረው ከስድስት አመታት በፊት በኦስትሪያ ሀገር ሲሆን፣ በአሁን ወቅት በህክምና ቱሪዝም በሚታወቁት እንደ ህንድ፣ ታይላንድና ፊሊፒንስም ባሉ ሀገራት የሕክምና አገልግሎቱ እየተሰጠ ይገኛል። ላለፉት ሁለት አስርት አመታት የሀገራችን ህክምና አገልግሎት ጥራትና ሽፋን በፍጥነት እያደገ ቢሆንም ከላይ የተጠቀሰው የሕክምና ዘዴና መሳሪያዎች ወደ ሀገር ውስጥ ገና አልገቡም። ስለዚህ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው ከላይ ወደ ተጠቀሱት ሀገራት ሄዶ የቀዶ-ጥገና ሕክምና ማግኘት አለበት።

Photo - Habtamu Ayalew
Photo – Habtamu Ayalew

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ በከፍተኛ የኪንታሮት ሕመም ምክንያት በማደንዘዣ የሚገኘው አቶ ሀብታሙ አያሌው ሕመሙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ በሀገር ውስጥ የሕክምና ተቋማት መታከም የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በዚህ መሰረት፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው ወደ ውጭ አገር ሄዶ መታከም እንዳለበት ክትትል ሲያደርግበት የነበረው የካዲስኮ አጠቃላይ ሆስፒታል ቦርድ በመወሰኑ ይታወቃል።

በፍርድ ቤት በተጠየቁት መሰረት፣ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተርን ጨምሮ የሦስት ሐኪሞች ፊርማ ያረፈበትን የሕክምና ሪፖርት፣ ማክሰኞ ሐምሌ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡

በዕለቱ ለጊዜው ዳኞች ባለመሟላታቸው እስከ ሐምሌ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንደሚሰጥና በጽሕፈት ቤት ወይም በመዝገብ ቤት እንዲከታተሉ፣ በቅርቡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትህግ ሆነው የተሾሙት አቶ ዳኜ መላኩ ተናግረው ነበር፡፡

ሆኖም ግን፣ ሐምሌ15 ቀን 2008 ዓ.ም.  ፍርድ ቤቱ የሰጠው ምላሽ ግን  ፍፁም ያልተጠበቀ ነበር። ይህም፣ አቃቢ  በጉዳዩ ላይ የቃል ክርክር እንዲያደርግ ለሐምሌ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲስ ቀጠሮ ሰጠ።

በተመሣሣይ፣ በዛሬው ዕለት፣ ሐምሌ 19 ቀን 2008 ዓ.ም አቃቤ ሕግ የቃል የመከራከሪያ ያቀርባል ተብሎ ሲጠበቅ፣ ችሎቱ የመከራከሪያ ሃሳቡን በፅሁፍ እንዲቀርብለት ለሐምሌ 22/2008 ዓ.ም ሌላ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ አቶ ሀብታሙ ሕክምናውን በአስቸኳይ ካላገኘ ሕመሙ ወደ ካንሰር ሊቀየር እንደሚችል፣ ከዚያ በኋላ የመዳን እድሉ በጣም ጠባብ እንደሆነ ሐኪሞቹ አስጠንቅቀዋል። ነገር ግን፣ ችሎቱ የጉዳዩን አስቸኳይነት ተረድቶ ፈጣን ውሳኔ ባለመስጠቱ ምክንያት በሽታው ከዕለት-ወደ-ዕለት እየተባባሰ፣ የግለሰቡም የመዳን ተሳፋ እየጨለመ ይገኛል።

ሀብታሙ አያሌውን በተደጋጋሚ በአካል ሄጄ ጠይቄዋለሁ። የሕመሙን ስቃይ እየተቋቋመ ያለው በማስታገሻ መድሃኒት ብርታት ነው። በእርግጥ የማስታገሻ መድሃኒት ደግሞ የስቃይ ማስታገሻ እንጂ ፈውስ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ፣ መፍትሄው አቶ ሀብታሙ አያሌው በአስቸኳይ ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ መታከም አለበት።

በአጠቃላይ፣ ስለ ሀብታሙ አያሌው ጤንነትና የሕክምና ጉዳይ በተለያዩ መድረኮች የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ሃሳቦች ይሰጣሉ።

እርግጥ ነው፣ የሚሰጡት ሃሳቦች እና የሚሰጡበት መድረኮች ይለያያሉ። ሆኖም ግን፣ ሃሳብና አስተያየት የምንሰጠው በሙሉ ሰዎች ነን። እንደ ሰው፣ ሁላችንም በአምላክ አምሳል የተፈጠርን ሰብዓዊ ፍጡራን ነን። ሀብታሙ አያሌው እንደ እኔና እናንተ የመኖር ተስፋና ጉጉት ያለው፣ እንደ ማንኛውም ሰው ሕክምና የማግኘትና በጤንነት የመኖር መብት ያለው ሰብዓዊ ፍጡር ነው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ እንደ ሁላችንም የእሱን በሕይወት መኖር ከማናችንም በላይ አጥብቀው የሚሹ ልጅና ሚስት፣ ወላጆችና ቤተሰቦች አሉት። እንደ ሰው እናስብ። እንደ ሰው ስናስብ፤ የሀብታሙን የሕመም ስቃይ፣ የሴት ልጁን ሰቀቀን፣ የባለቤቱን መከራ፣ የቤተሰቦቹን ጭንቀት እንረዳለን። እንደ ሰው ስናስብ ለራሳችን ሕይወት የምንሰጠውን ዋጋ ያህል ለሌሎችም ሕይወት ዋጋ እንሰጣለን። ለራሳችን ሕይወት ዋጋ የምንሰጥ ሁሉ ለሀብታሙ ሕይወትና ጤንነት ዋጋ እንሰጣለን።

በመሆኑም፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው ወደ ውጪ ሀገር ሄዶ አስፈላጊውን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ይፈቀድለት ዘንድ እንጠይቃለን።

************

Guest Author

more recommended stories